ገጣሚ፣ ደራሲና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን ወንድም (1946 - 2016)
ገጣሚ፣ ደራሲና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፣ ከአባቱ ከአቶ መኮንን ወንድም እና ከእናቱ ከወይዘሮ በለጤ በድሉ፣ በነሐሴ ወር 1946 ዓ.ም፣ በቀድሞዋ ናዝሬት፣ በአሁኑ አዳማ ከተማ ተወለደ፡፡
ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመግባቱ አስቀድሞ፣ መምህር ተከስተ ጋር የቄስ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን፤ እዚያም ሳለ ዳዊትን በቃሉ በመሸምደድ የማስታወስ ችሎታውን አዳበረ፡፡የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው ናዝሬት በአጼ ገላውዲዮስ ት/ቤት የተከታተለው ነቢይ መኮንን፤ በትምህርት አቀባበሉም ከጎበዞቹ ተርታ የሚሰለፍ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ለትምህርት ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ባልደረባ የነበሩት አባቱ፤ ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡ ልጃቸው ሁልጊዜም በትምህርቱ ብርቱ ሆኖ ምክራቸውን ይለግሱት ነበር፡፡ ነቢይም፣ ከክፍሉ አንደኛ በመውጣት አባቱን ከማስደሰት ቸል ብሎ አያውቅም፡፡ ነቢይ አባቱን አቶ መኮንን ወንድምን በሞት ያጣው የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነበር፡፡
ነቢይ መኮንን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ፣ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ልኡል በእደ ማርያም ተማሪ ቤት ከገቡ ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ ነበር፡፡ በመቀጠልም በ1966 ዓ.ም፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲን የተቀላቀለው ነቢይ፤ ኬሚስትሪን በዋናነት (ሜጀር)፣ ሂሳብን ደግሞ ማይነር በማድረግ አጥንቷል፡፡
እንደ ዘመነኞቹ በወቅቱ የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ተሳትፎ የነበረው ነቢይ መኮንን፤ ከደርግ ወጥመድ አላመለጠም፡፡ በኢህአፓ አባልነቱ ታስሮ ለ10 ዓመታት መከራውን በልቷል፡፡ ነገር ግን ደርግንም ሆነ አገሪቱን ወይም ሌላ ወገን ሲያማርር፣ ሲወቅስ ወይም ሲረግም ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ እንደ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታግዬለታለሁ፣ ሞቼለታለሁ ወዘተ እያለም መመጻደቅ አያውቅበትም፡፡ በሚመጻደቁትም ይስቃል፡፡ እሱና ዘመነኞቹ በአብዮቱ ወቅት ያሳለፉትን በጎም ሆነ ክፉ፣ ያሁኑ ትውልድ እንዲማርበት ከመጻፍና ከመናገር ግን ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ጽንፈኝነትና አክራሪነት እንደማያዋጣ ሲመክር ኖሯል፤ በጽሁፎቹ፡፡
ነቢይ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኬሚስትሪ ያጠና ቢሆንም፣ በገጣሚነት፣ በደራሲነት፣ በተርጓሚነትና በጋዜጠኝነት በርካታ ሥራዎችን ለአንባቢያን ያበረከተ ታላቅ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ነበር።
በ1992 ዓ.ም ህትመት የጀመረችውን አዲስ አድማስ ጋዜጣን ከመሰረቱት አንዱ የነበረው አንጋፋው የጥበብ ባለሙያ ነቢይ መኮንን፤ ለሁለት አስርት ዓመታት ጋዜጣዋን በዋና አዘጋጅነት በመምራት፣ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ስኬታማ አድርጓታል፡፡ የአዲስ አድማስ ዋና አዘጋጅ የነበረው ነቢይ፣ በጋዜጣው ላይ በየሳምንቱ በተረትና ምሳሌ እያዋዛ በሚጽፋቸው ርዕሰ አንቀጾች ታዋቂነትን ያተረፈ ሲሆን፤ ለጋዜጣዋም ተነባቢነትን አቀዳጅቷታል፡፡
ሁለገቡ ከያኒ ነቢይ መኮንን፣ ከአሰርት ዓመታት በፊት “ባለጉዳይ” የተሰኘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ ለዕይታ ከማብቃቱም በላይ በትወናም ተሳትፎበታል፡፡ የእዚህ ተከታታይ ድራማ ጭብጥ ከመሬት ጋር የተያያዘ የሙስና ጉዳይ ሲሆን፣ ታዋቂዎቹ ተዋናዮች አበበ ባልቻ፣ ፈቃዱ ተክለማሪያምና ፍቅርተ ጌታሁንን ጨምሮ ሌሎችም ተሳትፈውበት ነበር፡፡
ነቢይ፣ “ናትናኤል ጠቢቡ” እና “ጁሊየስ ቄሳር” የተሰኙ ተውኔቶችንም ተርጉሞ ለመድረክ አቅርቧል። ”ባለካባ እና ባለዳባ” በተሰኘ ተውኔት ላይ ደግሞ በትወና ተሳትፏል።
“ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነኝ” የሚለው ነቢይ መኮንን፤ “ጥቁር፣ ነጭ፣ ግራጫ ግጥሞች” እና “ስውር ስፌት- (ሁለት ቅጾች)” የግጥም መድበሎችን ለንባብ አብቅቷል፡፡
ነቢይ፤ “የኛ ሰው በአሜሪካ” - የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻው፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ሲወጣ ቆይቶ፣ በመጨረሻ በመጽሐፍ ተዘጋጅቶ ለህትመት የበቃ ሌላኛው ሥራው ነው። ለንባብ የበቃው ሌላው የነቢይ መጽሐፍ ደግሞ “የመጨረሻው ንግግር” የተሰኘ ሲሆን፤ “ዘ ላስት ሌክቸር” ከሚለው መጽሐፍ የተተረጎመ ነው።
ነቢይ፤ ዳን ብራውን የጻፈውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ የነበረውን "The Davinci Code" የተሰኘ መጽሐፍ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ አስነብቧል፡፡
ከነቢይ ጥበባዊ ሥራዎች ሌላው የሚጠቀሰው "ማለባበስ ይቅር" ነው፡፡ ኤች አይቪ-ኤይድስ የሀገር አደጋ በሆነበት ዘመን፣ ነቢይ መኮንን "ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩትን ማግለል በሽታውን ያባብሳል፤ ስለዚህ ፍቅር እንስጣቸው፤ አናግልላቸው" የሚል መልእክት ያዘለ ግጥም ገጥሞ ታዋቂ ወጣት ዘፋኞች አቀንቅነውታል፡፡ "ማለባበስ ይቅር" የተሰኘው የሙዚቃ ሥራ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ ይታይ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ከ32 ዓመት በፊት ሜጋ ኪነጥበባት ማእከልን ከመሰረቱት አንዱ የነበረው ነቢይ መኮንን፤ በጊዜው በሜጋ ኪነጥበባት ማእከል አሳታሚነት ትወጣ የነበረችውን ‹‹ፈርጥ›› የኪነ-ጥበብ መጽሄትንም በዋና አዘጋጅነት በመምራት ይታወቃል፡፡
ነቢይ፣ ከጋዜጠኝነቱና ከጥበብ ሥራው ጋር በተገናኘ የተለያዩ የዓለም አገራትን የመጎብኘት ዕድል የገጠመው ሲሆን፤ ከጎበኛቸው ሀገራት መካከልም ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ኢራን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣ ኬንያና ሱዳን ይገኙበታል፡፡
ነቢይ ለሀገሩ ኪነጥበብ ማደግ ከወጣትነቱ ጀምሮ ብዘ የለፋ ታላቅ የሀገር ባለውለታ እንደመሆኑ መጠን፣ ይህንኑ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የቅርብ ወዳጆቹ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ፣ ነቢይ በሀገሩ ይከበራል የሚል የምስጋና መሰናዶ አዘጋጅተውለት ነበር፡፡
.ከሁሉ ወዳጅና ተግባቢ የነበረው ነቢይ መኮንን፣ ባለትዳርና የሦስት ሴት ልጆች አባት ነበር፡፡ አንጋፋው ገጣሚ፣ ደራሲና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፣ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ፣ ረቡዕ ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም በተወለደ በ69 አመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን እንመኛለን፡፡
- ኢዮብ ካሳ -
ለራስ የተጻፈ ወቀሳ
እንጠራራ እንጂ
እንፋለግ እንጂ
ከያለንበቱ
ሰው የለም አንበል፣ አለ በየቤቱ
ምን ቢበዛ ጫናው፣ አንገት ቢያቀረቅር
ምን አፉ ቢታፈን፣ዝም ቢልም አገር
ምን መሄጃ እስኪያጣ፣ መንገዱ ቢታጠር
ጎበዝ እንደ ጭስ ነው፤ መተንፈሻ አያጣም
ቀን መርጦ ሰው መርጦ መነሳቱ አይቀርም፡፡
(ነቢይ መኮንን፤ አዲስ አድማስ ግንቦት 9፣1995 ዓ.ም)
**
በዚህች አጭር ማስታወሻ በቅርበት ስለማውቀው ገጣሚ፣ ተርጓሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን በጥቂቱ አወጋችኋለሁ - በወፍ በረር እንደሚሉት፡፡ ነቢይ የትያትርና ድራማ ጸሃፊም ነው፡፡ ከዓመታት በፊት ባለጉዳይ የተሰኘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ ለዕይታ አብቅቷል፤ አንጋፋው አርቲስት አበበ ባልቻ፣ ራሱ ነቢይ መኮንንና ሌሎችም አርቲስቶች የተወኑበት፡፡ ጭብጡ ዛሬም ድረስ ተባብሶ የቀጠለው ከመሬት ጋር የተያያዘ የሙስና ጉዳይ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ድራማው ከ10 ዓመታት በኋላ በድጋሚ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቦ፣ እንደ አዲስ በከፍተኛ አድናቆት መታየቱ ነው፡፡ ናትናኤል ጠቢቡ የተሰኘ ተውኔትም ተርጉሞ ለመድረክ አቅርቧል፡፡ ጁሊየስ ቄሳር ሌላው ተርጉሞ ለዕይታ ያበቃው ተውኔት ነው፡፡
ነቢይን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅሁት የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ነው - በተወዳጇ ሳምንታዊ ጋዜጣ አዲስ አድማስ በኩል፡፡ ዕድሜ ለአዲስ አድማስ፤ ይኸው እስከ ዛሬ ድረስ በሥራ ባልደረባነትና በቅርብ ወዳጅነት አብረን ዘልቀናል፡፡ የጋዜጣዋ መሥራችና ባለቤት የነበረውን (ነፍሱን ይማረውና) አሰፋ ጎሳዬንና ነቢይን እኩል ነው የማውቃቸው፡፡ አለቃዬ ቢሆኑም አንድም ቀን እንዲያ ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ ወይም እንዲሰማኝ አላደረጉም፡፡ የጓደኝነትና የታላቅ ወንድምነት እንጂ የአለቃና ሎሌነት ስሜት ኖሮን አያውቅም፡፡
ሥራ ስጀምር በዕድሜና በህይወት ተመክሮ ከነቢይ በእጅጉ ባንስም፣ አጠገቡ ሆኜ አንድ ቢሮ እየሰራን፣ ሁሉንም ነገር እንድማር ዕድል ሰጥቶኛል፡፡ ይሄ እምብዛም በአበሻ ዘንድ የማይገኝ ደግነቱና ቅንነቱ ሁሌም ይደንቀኛል፡፡ ይታያችሁ --- ያኔም ቢሆን ነቢይ የታወቀ የሥነጽሁፍ ባለሙያ ነው፡፡ ዝነኛ ገጣሚ ነው፡፡ ዝነኛ ተርጓሚ ነው፡፡ ዝነኛ ጸሃፌ ተውኔት ነው፡፡ ዝነኛ የጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነው፡፡ ነገር ግን በችሎታውም ሆነ በታዋቂነቱ አይታበይም፤ አይኮፈስም፡፡
በደርግ ዘመን በኢህአፓ አባልነቱ ታስሮ ለ10 ዓመታት መከራውን በልቷል፡፡ ነገር ግን ደርግንም ሆነ አገሪቱን ወይም ሌላ ወገን ሲያማርር፣ ሲወቅስ ወይም ሲረግም ሰምቼው አላውቅም፡፡ እንደ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታግዬለታለሁ፣ ሞቼለታለሁ ወዘተ እያለ አይመጻድቅም፡፡ በሚመጻደቁትም ይስቃል፡፡ እሱና ዘመነኞቹ በአብዮቱ ወቅት ያሳለፉትን በጎም ሆነ ክፉ ያሁኑ ትውልድ እንዲማርበት ከመጻፍና ከመናገር ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ጽንፈኝነትና አክራሪነት እንደማያዋጣ ሲመክር ኖሯል፤ በጽሁፎቹ፡፡ ቁምነገርን በቀልድ እያዋዛ ማቅረብ ይወዳል - በጽሁፉም በንግግሩም፡፡ መድረክ ላይ ከወጣ ታዳሚን በሳቅ ያፈርሳል - አፍ ያስከፍታል፡፡ አንደበቱም ብዕሩም የተባ ነው፡፡
ነቢይ ባህልና ጥበብ አገርን እንደሚለውጥ ጽኑ እምነት አለው፡፡ በዚህ እምነቱ ነው አዲስ አድማስ በተለይ ጥበብና ባህል ላይ አተኩራ እንድትሰራ ያደረገው፡፡ የየሳምንቱን ርዕሰ አንቀጽ በተረትና ምሳሌ መጻፍ የጀመረው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ሃሳብ አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኝ ድልድይ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ለዚህም ነው የተለያዩ ሃሳቦችና አስተያየቶች በአዲስ አድማስ ላይ ያገደብ በነጻነት ሲስተናገዱ የኖሩት፡፡ እሱም እንደ ጋዜጣው መሥራችና ባለቤት አሰፋ ጎሳዬ ሁሉ ሃሳብን አይፈራም፡፡ ለህዝብና ለአገር የሚጠቅም አንዳች ሃሳብ ያላቸው ወገኖች ሁሉ፣ እንዲጽፉ ሲያበረታታና ሲደግፍ ነው የኖረው፡፡
ወጣት ገጣምያንና ጸሃፍት በአዲስ አድማስ ላይ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ሰፊ መድረክ ፈጥሮላቸዋል፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ዛሬ መጽሐፍት ያሳተሙ ታዋቂ ደራስያንና ገጣምያን ለመሆን በቅተዋል፡፡ በአጭሩ ተተኪ ጸሃፍት፣ ደራሲያን፣ ገጣሚያን፣ ወዘተ-- ፈጥሯል - በዋና አዘጋጅነት በሚሰራባት አዲስ አድማስ በኩል፡፡
እኔም የዚያ ውጤት ነኝ፡፡ በአዲስ አድማስ ላይ ከ30 የማያንሱ አጭር ልብወለዶችን ተርጉሜ አቅርቤአለሁ፡፡ ወደ አምስት ገደማ መጻህፍት አሳትሜአለሁ፡፡ ጋዜጣዋን ከ15 ዓመታት በላይ በምክትል ዋና አዘጋጅነት መርቼአለሁ፡፡ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ የነቢይ መኮንን በጎ ተጽዕኖ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ገና ከፍተኛ ሪፖርተር ሳለሁ፣ የተለያዩ ጽሁፎችን በጋራ እየተረጎምን በስማችን ጋዜጣው ላይ እንዲወጣ ያደርግ ነበር - በእኔ ጥያቄ ወይም ግፊት ሳይሆን በሱ ደግነትና ቅንነት፡፡ ፕሮፌሰሩ እና የዩክሬን ትራክተሮች የተሰኙ መጻህፍትን ለሁለት እየተረጎምን በተከታታይ አስነብበናል፡፡ የኔ ስም ከታዋቂው ገጣሚና የሥነጽሁፍ ሰው ነቢይ መኮንን ስም ጎን አብሮ ሲወጣ የሚፈጥርብኝን አዎንታዊ ስሜትና ብርታት አስቡት፡፡ በዚህ ሂደትም በነቢይ አስገራሚ የሥነጽሁፍ ብቃትና መክሊት እየተደመምኩ ብዙ ተምሬአለሁ፡፡ ነቢይ እኔን ገጣሚ ባያደርገኝም፣ከግጥም ጋር በፍቅር እንድወድቅ ማድረግ ችሏል፡፡ ደግነቱና ቅንነቱ ተጋብቶኝ ይሁን አይሁን ግን በእርግጠኝነት መናገር ያዳግተኛል፡፡
በነገራችን ላይ ዛሬ ስለ ነቢይ መኮንን እንዳወጋ ያነሳሳኝ፣ በነገው ዕለት ሦስት መጻሕፍት የሚያስመርቅ መሆኑ የፈጠረብኝ የደስታ ስሜት ነው፡፡ እናም ይህች አጭር ማስታወሻ ገጣሚውንና ሁለገብ የሥነጽሁፍ ሰው የሆነውን - ነቢይ መኮንን -እንኳን ደስ ያለህ- ለማለት ያህል፣ የከተብኳት ተደርጋ ትቆጠርልኝ፡፡ እንደሱ ገጣሚ ብሆን ኖሮ፣ ይሄን ሁሉ ሃሳብ በአጭር ግጥም ጽፌው እገላገል ነበር፡፡ እኔ ግን የግጥም አፍቃሪና አድናቂ እንጂ ገጣሚ አይደለሁም፡፡ ምናልባት ወደፊት --- ማን ያውቃል?
በነገው ዕለት በፍሬንድሺፕ ሆቴል ከሚመረቁት የነቢይ ሦስት መጻህፍት አንዱ፣ በ1970ዎቹ መጨረሻ ለህትመት የበቃውና በደርግ ዘመን በእስር ቤት ሳለ የተረጎመው ነገም ሌላ ቀን ነው የተሰኘው ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ነው፡፡ ነቢይ መኮንን Gone With The Wind የተሰኘውን የአሜሪካ ክላሲክ መጽሐፍ የተረጎመበትና ያሳተመበት ሂደት፣ በራሱ አስደናቂ መጽሐፍ ይወጣዋል፡፡ ጎበዝ የፊልም ባለሙያ ይፈልጋል እንጂ አስገራሚ ፊልምም የሚወጣው ነው፡፡
በደርግ ዘመን እንደ እኩዮቹ ሁሉ፣ በጸረ-አብዮተኝነት ተጠርጥሮ ወህኒ የተወረወረው ነቢይ መኮንን፤ ከዛሬ ነገ ይሙት ይትረፍ እርግጠኛ ባልሆነበት ሁኔታ፣ Gone With The Wind የተሰኘውን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ በሲጋራ ወረቀት ላይ እየተረጎመ፣ በድብቅ በማስወጣት ነው፣ በመጨረሻ ሲፈታ ያሳተመው፡፡
በነገራችን ላይ ይህን አስገራሚ ታሪክ ሰምታ የተደመመች አንዲት አሜሪካዊት ጋዜጠኛ፣ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ባህር ተሻግራ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ከነቢይ ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እኔ ደግሞ ወደ ሃገሯ ልትመለስ አንዲት ቀን ሲቀራት የማግኘት ዕድል አግኝቼ፣ ኢንተርቪው በማድረግ፣ ለአዲስ አድማስ አንባቢያን ታሪኩን አጋርቼዋለሁ፡፡
ነገም ሌላ ቀን ነው የተሰኘው መጽሐፍ የመጀመሪያ ዕትም በሳንሱር ምክንያት መግቢያውና አንዳንድ ሃሳቦቹ ተቆራርጠው መውጣታቸውን የሚያስታውሰው ነቢይ መኮንን፤ አሁን - ያልታተመው መግቢያ- ታክሎበት በአዲስ መልክ መታተሙን ተናግሯል፡፡
በነገው ዕለት የሚመረቀው ሌላው መጽሐፍ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ለዓመት ያህል በተከታታይ ሲወጣ የነበረውና ከፍተኛ ተነባቢነትን የተቀዳጀው የኛ ሰው በአሜሪካ - የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻ ነው፡፡ በአሜሪካ በሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ህይወት ላይ ያጠነጥናል፡፡ ሦስተኛው መጽሐፍ የመጨረሻው ንግግር የተሰኘ ሲሆን The Last Lecture ከሚለው መጽሐፍ የተተረጎመ ነው፡፡
እኒህ የነቢይ ሥራዎች ታትመው ለምርቃት መብቃታቸው በእጅጉ አስደስቶኛል፡፡ ከዚህ በላይ ግን የህይወት ታሪኩን ጽፎ እንደጨረሰና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህትመት እንደሚበቃ መስማቴ አስፈንድቆኛል፡፡ ነፍሴ በደስታ ጮቤ ረግጣለች፡፡ የመጽሐፍቶቹን ምረቃ በተመለከተ ባለፈው ሐሙስ በብሔራዊ ቤተመዘክርና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የኤጀንሲው ሃላፊ፣ ነቢይ መኮንን ራሱ ቤተመጻህፍት መሆኑን ጠቅሰው፤ የዚህን ሁለገብ የሥነጽሁፍ ሰው የህይወት ታሪክ መጽሐፍ ለህትመት ለማብቃት መጠነኛ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል - በተቋማቸው ስም፡፡ ይሄም ዜና ተስፋ ሰጪና አበረታች ነው፡፡ ለነቢይ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ደራሲያንና ሥነጽሁፍም ጭምር፡፡
በዚህ አጋጣሚ የነቢይ ሥራዎች ተሰባስበውና ተደራጅተው በመጽሐፍ መልክ ለትውልድ ይተላለፉ ዘንድ ከጎኑ ሆነው በትጋት እየሰሩ ያሉትን ወገኖች ሁሉ ማመስገን ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በድጋሚ ለነቢይ መኮንን -እንኳን ደስ ያለህ- ለማለት እወዳለሁ፡፡
ረዥም ዕድሜ፣ የተትረፈረፈ ፍቅርና የተሟላ ጤና ተመኘሁልህ!