ከደራሲያን ዓምባ

Wednesday, December 24, 2025

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት

 ከ 1914 ዓ.ም. - 2016 ዓ.ም.


     ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የተመሰረተው           

መስከረም 3 ቀን 1914 ዓ.ም


ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ታኅሣሥ ፳፫ ቀን ፲፱፻፲፯ ዓ.ም. በአንዲት “ብርሃንና ሰላም” በተሰኘች አነስተኛ ጋዜጣ ሕትመት ሥራውን ጀመረ። በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መጻሕፍት ፣ ጋዜጦች ፣ መጽሔቶችና የምስጢራዊ ሕትመት ሥራዎች በተለያዩ ቋንቋዎች እያተመ ይገኛል። ማተሚያ ቤቱ በርካታ የመንግሥት እና የግል ጋዜጦችን የሚያትም ሲሆን ፥ በተጨማሪም በየዓመቱ በርካታ የፈተና ሥራዎችን በማተም ይታወቃል። 


 

ምሥረታ

ጥንታዊ ኢትዮጰያውያን ሊቃውንት የሚጽፏቸው መጻሕፍት ለሕዝብ የሚቀርቡት ብራና ተፍቆ ፣ ቀለም ተቀምሞ በእጅ ተፅፎ ነበር። በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት የተጀመረው የዘመናዊ ሕትመት ሥራ በሀገሪቱ ቁጥራቸውና መጠናቸው በርከት ያሉ ጋዜጦች፣ መፅሔቶች፣ መጻሕፍት፣ እንዲሁም ሌሎች የሕትመት ውጤቶች መታተም በመጀመራቸው የትምህርትና የሥልጣኔ መሰፋፋት ላይ የበኩሉን ሚና መጫወት ጀመረ።


የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትም ምሥረታ ዋና ዓላማ የአገሪቱን መንፈሳዊ መጻሕፍት በብዛት እና በዘመናዊ መልክ ከእጅ ጽሑፍ ወደ ሕትመት ለማሸጋገር ሲሆን፤ ምሑሩ ተክለጻድቅ መኩሪያ (፲፱፻፷፩ ዓ.ም)፣ ማተሚያ ቤቱ መስከረም ፫ ቀን ፲፱፻፲፬ ዓ.ም መቋቋሙን እና ብዙ ሥጋዊና የመንፈሳዊ መጻሕፍት እንዲሁም ምክርና ተግሣጽ፣ የለት ወሬ፣ የሹም-ሽር አዋጆችን ያትም እንደነበር ዘግበዋል።  በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ረዳት መምህር መኩሪያ መካሻ፤ “የፕሬስ ታሪክ” በተሰኘ ጽሑፋቸው ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ፣ ራስ ተፈሪ መኮንን በ፲፱፻፲፫ ዓ.ም የማተሚያ መሣሪያ አስመጥተው “ትንሹ ግቢ” (በኋላ ገነተ ልዑል — አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) ይባል በነበረው መኖሪያቸው ውስጥ አስተክለው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የተባለውን እንደመሠረቱ ዘግበዋል። 


ከሁለት ዓመት በኋላ በ፲፱፻፲፭ ዓ.ም አራት ተጨማሪ ማተሚያዎች ተገዝተው ከተተከሉ ከአንድ ዓመት በኋላ ሣምንታዊው ‘ብርሃንና ሰላም’ የተሰኘው ጋዜጣ እየታተመ፣ አስቀድሞ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ከተጀመረችው ‘አዕምሮ’ ጋዜጣ ጋር እስከ ጠላት ወረራ ዘመን ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ ይሠራጩ ነበር።

የወቅቱ ማተሚያ መሣሪያዎች በእግር እየተረገጡ የሚንቀሳቀሱ መሣሪያዎች ሲሆኑ የሠራተኞቹ ቁጥር ከሰባት እስከ አሥራ-ሁለት እንደነበር ተዘግቧል። ራስ ተፈሪም አልፎ-አልፎ በብርሃን እና ሰላም ጋዜጣ ላይ በአዘጋጅነት ይረዱ እንደነበረና ጽሑፎቻቸውንም ለሕትመት ያበቁ እንደነበር ተምዝግቧል። 


ከጠላት ወረራ ወዲህ

በ፲፱፻፴፫ የፋሺስት ኢጣልያ ኃይል ተሸንፎ የኢትዮጵያ መንግሥት ዳግም ሲቋቋም “ባንዲራችን” የተባለ ጋዜጣ እና ቅዳሜ ፣ ግንቦት ፴ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም በይፋ ሥራ ጀመሮ የመጀመሪያ እትሙን በ፲ ሺ ቅጅ ለአንባብያን ያበቃው አዲስ ዘመን (ጋዜጣ) የሚታተሙት በዚሁ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ነበር።


የዘውድ ሥርዓት አብቅቶ የ፲፱፻፷፮ቱ ዓብዮት ከታወጀ በኋላ የግል ማተሚያ ቤቶችን በሙሉ በመንጠቅ የብሔራዊ ንብረት ከማድረጉም ባሻገር፤ የግል ጋዜጣዎችንና መጽሔቶችን በሙሉ ከለከለ። በዚህ ፖለቲካዊ መንስዔ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከቀድሞው የበለጠ፤ በመንግሥት ሥር የሚተዳደርና ለሕትመት የተፈቀዱትን ጋዜጣዎች፤ መጽሔቶች፤ መጻሕፍት እና ሌላም የሕትመት እሴቶችን ከሞላ ጎደል አጠቃሎ ያዘ።


የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ በአሁኑ ጊዜ ከ፰መቶ በላይ የሚቆጠሩ ሠራተኞችና በዘመናዊ መሣሪያዎች የቅድመ-ሕትመት ፣ የሕትመትና የድህረ-ሕትመት አገልግሎት ላይ የተሠማራ ድርጅት ሲሆን ንብረትነቱም፤ አስተዳደሩም ሆነ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂነቱ የመንግሥት ነው። ስለሆነም የመንግሥትን ፖለቲካዊ አቋም፣ በተለይም መንግሥት የማይፈልጋቸውን የግል ፕሬስ ድርጅቶችን እና ሌሎች ለሕትመት የሚቀርቡ ዝግጅቶችን ያሰቃያል፤ የነጻ ፕሬስን መንፈስ ያቀጭጫል፤ ተቀናቃኝ የግል ማተሚያ ቤቶች ስለሌሉበትም እንዳሻው ፈላጭ ቆራጭነትን ያካሂዳል የሚሉ ነቀፋዎች በብዛት ይሰነዘሩበታል። 

 

ምንጮች:-

 ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ድረ-ገጽ https://ethbspe.org/
 
 

 

 

“ስሜ ለምን? ነው” ፤ የለምን ሲሳይ ግለ ታሪክ

 


ስሜ ለምን? ነው” – My Name Is Why በሚል ርዕስ ስመጥሩ ኢትዮ- ኢንግሊዛዊው ገጣሚ በራሱ ሕይወት ዙሪያ የጻፈውን፣ ለገበያ በዋለ በኹለተኛ ሳምንት ብዙ ቅጂዎች የተሸጡለት መጽሐፍ ሆኖ በኢንግሊዝ በሚታተመው ሰንዴይ ታይምስ ላይ የተመዘገበ መጽሐፍ ነው

የመጽሐፉ ርዕስ ፡ “ስሜ ለምን? ነው” – My Name Is Why
ደራሲ ፡ ለምን ሲሳይ
የገጽ ብዛት – 208
አሳታሚ – ካኖንጌት መጽሐፍት
የህትመት ዓመት ፤ ነሐሴ 2019 እኤአ
ለንደን፤ ዩናይትድ ኪንግደም
ዋጋ – 16፡99 ፓውንድ

“በዜማ የተሞላ፣ የሚያም ግን ደግሞ በተስፋ የተሞላ ታሪክ ….. የሚሰባብር፣ ብርሃንን የሚሻ” ኦብዘርበር ጋዜጣ
“አስደናቂ ታሪክ” ሰንዴይ ታይምስ
“ከዚህ መጽሐፍ የሚያስገርመው ነገር ፈጠራ ታሪክ አለመሆኑ፣ በእርግጥ ሆኗል። የሚገርም ታሪክ ነው” ቤንጃሚን ዘፋንያህ

ሰሞኑን በሃገራችን ካለው ውዥንብርና ሥጋት፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ምን ማለት እንዳለብኝም ባለማወቅ፣ ለዛሬ ከብዙ አታካች ጉዳዮች አረፍ እንድንል፣ መታከቱ ያልፋል በሚል እንደማሳለፊያም የመጽሐፍት ቅኝት ይዤ መጥቻለሁ። መጽሐፉን በቅርብ ላታገኙት እንደምትችሉ ቢገባኝም ራሱ ደራሲው ወገናችን ለምን ሲሳይ በመጽሐፉ መግቢያ “መጽሐፉ ለኢትዮጵያውያንም ነው” ስላለ ለእኛ የተባለውን ትንሽ ቅኝት ላደርግበት ስለወደድኩ ነው።

የኢትዮ- ኢንግሊዛዊው ስመጥር ገጣሚ ባለብዙ ስምና ክብር ለምን ሲሳይ በመንግሥት በማደጎ ልጅነት በእጓለ ማውታን ድርጅቶች፣ ማንነቱ ተደብቆት እንደልጅ መዳበስ ናፍቆት በመንግሥት እጅ ሲያድግ የደረሰበትን አሳዛኝ ግን ድንቅ ታሪክ የተረከበት መጽሐፍ ነው፤ ስሜ ለምን ነው ሲል የሰየመው መጽሐፍ።
ለምን ከስሙ ጀምሮ አስገራሚ ታሪክ ያለው ልጅ ነበር። ለአማርኛም ቢሆን ለምን ለልጅ የወጣ ስም ሰምተን የምናውቅ አይመስለንም። ኢንግሊዝኛ ሲሆን ደግሞ የበለጠ አስገራሚ ይሆናል፤ ስሙን በኢንግሊዝኛ በቀጥታ ተርጉሞ የመጽሐፉን ርዕስ My Name Is Why ያለውም ለዚህ ይመስለኛል።

በዛ ላይ ባልተንዛዛው ግለ ታሪኩ የሕይወቱን ብዙ ክንውኖችና ሲያድግ ሆድ ሆዱን የሚበሉትን በኋላ ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ የደረሰባቸውን እውነቶች የጠየቀበትም ነው። ለምን?
ለምን ከእናቱ ጋር ተለያየ፣ አሳዳጊ ወላጆቹ ለምን ጠሉት፣ መንግሥት እናቱ ስትፈልገው እንደነበር ለምን ደበቀው? ስሙን ለውጦ ከወገን ከዘሩ ለይቶ በእጓለ ማውታን እንዲድግ ለምን ፈረደበት? ለምን? ለምን?

የለምን መጽሐፍ በኢንግሊዝ በሚታተመው ሰንዴይ ታይምስ በጣም ብዙ ቅጂዎች የተሸጡለት መጽሐፍ ሆኖ ለመመዝገብ የበቃው ነሐሴ 29 ሽያጭ ላይ ውሎ ኹለተኛውን ሳምንት ሳይጨርስ ነበር። የመጽሐፉ ማስተዋወቂያ ላይ በግልጽ እንደሚለው “መንግሥት ህፃን ልጅ ሰርቆ እንዴት ያስራል? ይህንንስ ምስጢር አድርጎ መቆየት እንዴት ይቻለዋል? ይህ መጽሐፍ ይህንን ያብራራል”


ለምን 17 ዓመት ሆኖት፣ ሲወለድ የተሰጠውን የልደት ሰርቲፊኬት እስኪያገኝ እናቱ ያወጣችለትን ትክክለኛ ስሙን እንኳን አያውቅም ነበር። ይጠራ የነበረው በማደጎ ሂደት ሲያልፍ ጉዳዩን ይከታተል የነበረው ሰው ባወጣለት ስም ኖርማን (የራሱን ስም ነበር ሰውየው የሰጠው) እና ከፋም ለማም ቤተሰብ ብሎ በሚያውቃቸው ሰዎች የቤተሰብ መጠሪያ ኖርማን ግሪንውድ ተብሎ ይጠራ ነበር። በ17 ዓመቱ እናቱ ለምን ብላ እንደሰየመችው፣ በዘርና በምንጭም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ተረዳ።

መጽሐፉ ‹‹ስሜ ለምን ነው›› ይህንን ማንነቱንና ፍቅር፣ የኔ የሚለውን ወገን ፍለጋ ለዓመታት የተራበ የተጠማ በብዙ መልስ ያልነበራቸው ጥያቄዎች ራሱን ሲያስጨንቅ ያደገ ልጅ ታሪክ ነው። ካለፈበትና ከሆነው በተቃራኒ በ21 ዓመቱ የግጥም መጽሐፍ ለማሳተም የበቃ፣ ግጥሞቹ በለንደንና ሌሎች የኢንግሊዝ ከተሞች አደባባዮች የቆሙለት ድንቅ ገጣሚና ጸሐፊ ለመሆን የበቃ ነው። ታሪኩ በአብዛኛው ስለተጨማለቀው አሳፋሪ ስለሚለው የኢንግሊዝ የእጓለማውታን ሲስተምና አሠራር ሲሆን የዚህ ዘመን ስኬቱ ዓለምም ሚዲያም በሚያውቀው መልኩ በመጽሐፉ አልተካተተም።

መጽሐፉ የተፃፈበት ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ምዕራፍ መግቢያ ጣል የሚያደረገው ግጥም በቋንቋና በአገላለጽ ላይ ያለውን ጌትነትና ምጥቀት የሚያሳይ ነው።
ምሳሌ ብናይ – በግርድፉ ለመተርጎም ከሞከርኩት ጋር ኢንግሊዝኛውም እነሆ
(Chapter 2)
I will build an Embassy
In your heart over time
There is a plot of land inside me
Build one in mine
ኤምባሲዬን እገነባለሁ
በልብሽ – በጊዜ ሒደት
በልቤ ባዶ መሬት አለ
አንቺም የራስሽን ገንቢበት።
የለምን ልጅነት ያልተረጋጋ የማይጨበጥ ትዝታ የነበረው ነበር። ከህፃንነቱ ወራት እስከ 12 ዓመቱ በቆየበትና እስከ 17 ዓመቱ መጠሪያው ከነበረው ግሪንውድ ቤተሰብ የነበረውን የልጅነቱን ትዝታ፣ ያደገበትን ግቢ ውብ ዛፍና አበቦች፣ በልጅነቱ የነበረውን የተጫዋችነትና በሁሉም የሚወደድ ባህሪ ድምቀት በልጅነት ዓይን ይተርካል። በዚያው መጠን በሌላ ጽንፍ በትምህርት ቤቱ በቆዳው ቀለም ከሌሎች የተለየ ስለነበር የሚደርስበትን ትንኮሳና መገለል ይዘረዝራል።


ከዚያም በ12 ዓመቱ በልጅነት ዓለሙ የሚያውቃቸው ቤተሰቤ ያላቸው አንፈልግህም ሲሉት ዓለሙ ሲጨልም፣ ለመቆየት ሲጣጣር አቅም አጥቶ ህፃናት ማሳደጊያ ሲገባ፣ በዚህ ሁሉ በልጅ አዕምሮ ያጠፋው ጥፋት እንዳለ ሲጠይቅ፣ የሃዘን የደስታና የጥንካሬ ታሪኩ መጽሐፉን እንዳናስቀምጠው ያደርገናል።
የልጅነቱን ብቸኝነት፣ የሁኔታውን አሳዛኝነት የገለጠበትን አንድ ግጥም ብናይ
He lost touch at night
Their fingertips withdrew
Nobody touched him, light,
Except you
በማታ ማንነቱን ረሳ
ጣቶቻቸው ተሰበሰቡ
ማንም አልነካውም፤ ብርሃን
ካንቺ በቀር
ለምን ታሪኩ በመጨረሻ ተገጣጥሞ በመጽሐፍ እንደቀረበው ቅርፅ እንዲይዝ ያስቻለው ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር ለ34 ዓመታት ታግሎ በመጨረሻ ሙሉ ፋይሉን መንግሥት ለዓመታት በሱ ላይ የሰነደውን ሰነድ ማግኘት ሲችል ነበር። ከዚሁ ዶኩመንት ያገኛቸውን ደብዳቤዎች (የእናቱን የልጄን መልሱልኝ ተማጽኖ ጨምሮ) ኦፊሻል ውሳኔዎች፣ አስተያየቶች፣ ግምቶች፣ ትንተናዎች አለፍ አለፍ እያለ ዋና ዋናዎቹን በመጽሐፉ ገጾች አትሟቸዋል። በነገራችን ላይ መንግሥት ልጅነቱን ስለነጠቀው፣ እንዳይጠገን አድርጎ ስለሰበረው፣ መልሶ የማያገኘውን ከእናቱና ከወገኖቹ ጋር የማደግ ዕድል ስለወሰደበት መንግሥትን ፍርድ ቤት ገትሮ ከፍርድ ቤት ውጪ በተደረገ ድርድር መጠኑ ያልተገለፀ ካሳ እንዲከፈለው ተደርጓል።

ለምን በሥራዎቹ፣ በዓለም እየዞረ በሚያቀርባቸው አነቃቂ ንግግሮች በሚያገኘው ገቢ እሱ ባደገበት የእጓለማውታን ሥር ለሚያድጉ ልጆች ድጋፍ የሚያደርግ ተቋም አቋቁሞ ይሠራል። በተቋማት የሚገኙ ልጆች በተለይ በገና ወቅት ታዋቂ ሰዎችና ሌሎችም አብረዋቸው እንዲያሳልፉ የገና እራት የሚባል ፕሮግራም በየዓመቱ በመላው ኢንግሊዝ እንዲካሔድ ያስተባብራል፤ ይመራል።


ለምን የተወለደው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1967 ዊጋን በተሰኘች የሰሜን ምዕራብ ኢንግላንድ ከተማ ሲሆን ኢትዮጵያዊት እናቱ ለትምህርት ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝታ በመጣችበት ከጋብቻ ውጪ ፀንሳ ነበር። በወቅቱ ኢንግሊዝ ይደረግ እንደነበረው መውለጃዋ ሲደርስ በተቋም ገብታ ወልዳ ወደ ትምህርት ስትመለስ ‹‹ስጨርስ ልጂን ትመልሱልኛላችሁ›› ብላ እሺ ሲሏት እውነት መስሏት አምና የሰጠች ናት። ከዛ ምን ሆነ የሚለውን ከመጽሐፉ እንድትረዱ ስጋብዝ፤ በብዙ መከራ ውስጥ አልፎና ወላጅ አልባ ሆኖ አድጎ ለከፍተኛ ስኬትና ለዓለም አቀፍ እውቅና መብቃት ይቻላል የሚለውን በማስመር በራሱ በለምን ሲሳይ ግጥም ልሰናበት።

Look what was sown by the stars
At night across the fields
I am not defined by my scars
But by the incredible ability to heal
እዩ በኮከቦች የተዘራውን
ሌሊቱን በመስኩ ሁሉ ላይ
በጠባሳዬ አልገመትም
ለመዳን ባለኝ ድንቅ ችሎታ እንጂ
(ምዕራፍ ዘጠኝ መጀመሪያ)

“ስሜ ለምን? ነው” ፤ የለምን ሲሳይ ግለ ታሪክ | Addis Maleda

"The battle of Adewa" | ገጣሚ ለምን ሲሳይ | ጦቢያ ግጥምን በጃዝ @Arts Tv World


Saturday, October 25, 2025

የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች

 


የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች
(ከጥቅምት 14 ቀን 1900 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ.ም. __118 ዓመት)

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሚኒስትሮች የተሾሙት

ጥቅምት 14 ቀን 1900 ዓ.ም ነው ።

በዳግማዊ አጤ ምኒልክ የተሾሙት የመጀመሪያዎቹ ሰባት ሚኒስትሮች የሚከተሉት ናቸው፦

1. ኣፈንጉሥ ነሲቡ መስቀሉ...የዳኝነት ሚኒስትር
2. ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ...የጦር ሚኒስትር
3. ፀሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ወልደ አረጋይ...የጽሕፈት ሚኒስትር
4. በጅሮንድ ሙሉጌታ.....የገንዘብና የጓዳ ሚኒስትር
5. ሊቀ መኳስ ከተማ.......ያገር ግዛት ሚኒስትር
6. ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ....የንግድና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
7. ከንቲባ ወልደ ጻዲቅ ጐሹ......የርሻና የመሥሪያ ሚኒስትር



ምኒልክ እነኚህን ሚኒስትሮች እንደሾሙ በአዲስ አበባ ያሉ የውጭ አገር መንግሥታት ተወካዮች ሹመቱን እንዲያውቁት የሚከተለውን ደብዳቤ ጻፉ ።

.....የሮፓን ፡ ሥርዓት ፡ በአገራችን ፡ በኢትዮጵያ ፡ ካሰብን ፡ ብዙ ፡ ጊዜ ፡ ነው ። እናንተም ፡ የሮፓ ፡ ሥርዓት ፡ በኢትዮጵያ ፡ ቢለመድ ፡ መልካም ፡ ነው ፡ እያላችሁ ፡ ስታመለክቱኝ ፡ ነበር ። አሁንም ፡ የእግዚአብሔር ፡ ፈቃዱ ፡ ሆኖ ፡ ለመፈፀም ፡ ቢያበቃኝ ፡ ምኒስትሮች ፡ ለመሾም ፡ ዠምሬ ። አፈንጉሥ ፡ ነሲቡን ። ፊታውራሪ ፡ አብተ ፡ ጊዮርጊስን ። ጸሐፌ ፡ ትእዛዝ ፡ገብረ ፡ ሥላሴን ። በጅሮንድ ፡ ሙሉጌታን ። ሊቀመኳስ ፡ ከተማን ። ነጋድራስ ፡ ኃይለጊዮርጊስን ። ከንቲባ ፡ ወልደጻዲቅን ፡ አድርጌአለሁና ፡ ይህንን ፡ እንድታውቁት ፡ ብዬ ፡ ነው ።

ጥቅምት ፲፬ ቀን ፲፱፻ ዓመተ ምህረት አዲስ አበባ ተጻፈ


ሚኒስትሮቹ ከተሾሙ ከ15 ቀናት በኋላ ደግሞ ለሚኒስትሮቹ መመሪያ የሚሆን ደንብ አወጡ። የወጣውንም ደንብ በሚቀጥለው ደብዳቤ ሸኚነት ለእያንዳንዱ ሚኒስትር ላኩላቸው ።


የመንግሥት ሥርዓት ባገራችን በኢትዮጵያ የሮጳ ሰው ነገሥታቱም ቆንሲል ሁሉ ገቡ። እነዚህም በኢትዮጵያ መንግሥት ሥራት ያልተለመደ ነው። ሥራት የሌለው አገር ምን መንግሥት ይባላል እያሉ አገራችን መወረፉን ታውቃላችሁ። ለመውሰድም በኛ ላይ እንደተነሱም ታውቃላችሁ።
አሁንም ምንም የቀድሞው የኢትዮጵያ ሥራት ቢኖር ከጥቂት ቀን በኋላ ቀርቷልና አገራችንን እንደ አሮጳ ሥራት ለማድረግ አስቤ ይሄንን ባንደኛ ወረቀት የተፃፈውን ደንብ ጽፌላችኋለሁና በዚሁ ባስያዝኳችሁ ሥራ ሳትጣሉ ፡ ሳትመቀኛኙ በእውነት እርስ በርሳችሁ ተስማምታችሁ ጠንክራችሁ መንግሥታችንን መርዳት ነው።
እንዲህ ሁነን በሚገባ ሥራት ሕዝባችንን ጠብቀን ከያዝነው ለመንግሥታችንና ለሀገራችን ጥቅም ይሆናል። አገራችንን ሌላ አይመኘውም። እኔም እስካሁን ብደክም ብደክም ሚኒስቴር ፡ መማክርት ፡ ቆንሲል የለበት ፡ ባንድ ሰው አሳብ ብቻ እያሉ አሙን እንጂ አላመሰገኑንም።
አሁንም እንቅልፍ ሳትወዱ ፡ መጠጥ ሳታበዙ ፡ ገንዘብን ጠልታችሁ ፡ ሰውን ወዳችሁ ፡ ተግታችሁ ይሄንን ሥራ እንድትፈፅሙልኝ ተስፋ አለኝ። ለዚህ ሥራ እኔ እናንተን አምኜ ስላደረግሁ እናንተም የምታምኑትን ፡ ገንዘብ የማይወደውን ፡ ድሃ የማይበድለውን ፡ እናንተን የሚረዳችሁን ሰው እየፈለጋችሁ እያመለከታችሁኝ ከሥራው ማግባት ያስፈልጋችኋል።
ገንዘብም ቢሆን እኔ ደሞዝ እሰጣለሁ እንጂ ከድሃ ፡ እንኳን ትልቅ ገንዘብ አንድ መሀለቅም እንኳ ቢሆን ከዚያው ከተወሰነለት ከግብሩ በቀር ሌላ እንዳይነካ ማድረግ ነው። ከዚህ ከተጻፈው ደንብ አልፋችሁ ድሃ አላግባብ የተበደለ እንደሆነ እኔም እጠላችኋለሁ። እናንተም ትዋረዳላችሁ። በነፍሳችሁም በወንጌል ፡ በመስቀል አምላችኋለሁ አስገዝታችኋለሁ።


የመጀመሪያዎቹ ሰባት ሚኒስትሮች ተሹመው ሥራ ከጀመሩ በኋላ ሥራ የሚበዛበትና አስፈላጊ የሆኑ ሚኒስቴሮች እየተከፈቱ በተጨማሪ አዛዥ መታፈሪያ የግቢ ሚኒስትር ፡ ቀኛዝማች መኰንን ተወንድ በላይ የሥራ ሚኒስትር ተብለው ተሾሙ ። የፖስታና የቴሌፎን ሥራ በዚያን ጊዜ እጅግም ያልተስፋፋ ስለነበረ በግቢ ሚኒስቴር ሥር ሆኖ የበላይ አለቃ ልጅ በየነ ይመር የፖስታ ቴሌግራፍና ቴሌፎን ሹም ተብለው ተሾሙ ።

ዳግማዊ አጤ ምኒልክ የመጀመሪያዎቹን ሚኒስትሮች ከሾሙ ከአምስት ወር በኋላ ደግሞ ለጠቅላላ ተሿሚዎቹ የሚከተለውን ደብ ዳቤ ፃፉላቸው ።

እኔ እናንተን ምንስቴርም ፥ ወንበርም መሾሜ ለመንግሥታችንና ለሕዝባችን ጥቅም እንዲሆን ነው ።አሁንም በዚህ ባስያዝኳችሁ ሥራ ሳትጣሉ ፥ ሳትመቀኛኙ እንቅልፍ ሳትወዱ መጠጥ ሳታበዙ ገንዘብ ጠልታችሁ ፡ ሰውን ወዳችሁ እርስ በርሳችሁ ተስማምታችሁ ፥ ጠንክራችሁ ፡ በውነት መንግሥ ታችንን እንድትረዱ ይሁን። በዚህም በያዛችሁት ሥራ ከእውነተኛው ነገር በቀር እገሌን አንወደውም በዚህ ነገር እንጉዳው እንዳትሉ ። ገንዘብም መተያያ ብትቀበሉ ገንዘብ ሰጥቶናል ብላችሁ ሳታደሉ ፥ በእውነት ሕዝባችንን ልትጠብቁ አምኛችኋለሁና እናንተም በዚሁ ቃል ታመኑልኝ።
ሚያዝያ ፩ ቀን ፲፱፻ ዓመተ ምህረት አዲስ አበባ ከተማ ተፃፈ "


============================

ምንጭ:- ጳውሎስ ኞኞ አጤ ሚኒሊክ

sewasew.com

Thursday, August 14, 2025

የተራራው ምርኮኞች

 የተራራው ምርኮኞች_አሳፍ ሃይሉ
 Alive : The Story of the Andes

 Survivors




"ሁላችንም ጥቂት ጥቂት የተራራ ምርኮኞች ነን!"

ይሄን መፅሐፍ የኢትዮጵያ አንባብያን "የተራራው ምርኮኞች" በሚል በሀዲስ እንግዳ አይቼህ ግሩም ተደርጎ ተተርጉሞልን አንብበነዋል። ሁልጊዜ ከሃሳቤ የማይጠፋ መፅሐፍ ነው።

በዕለተ አርብ፣ በፈረንጆቹ አቆጣጠር Friday 13 October 1972 ዓመተ ምህረት፣ የፓራጓይን የራግቢ ኳስ ተጫዋቾች ቡድን የያዘ የአየር ኃይል አውሮፕላን፣ በላቲን አሜሪካ እጅግ ግዙፉ በሆነው የአንዲዝ በበረዶ የተሸፈነ ተራራ ላይ ይከሰከሳል።

ይህ መፅሐፍ፣ ከአደጋው በህይወት የተረፉት እነዚያ ተሳፋሪዎች፣ በዚያ ከዜሮ በታች በሆነ በረዷማ ተራራ ላይ ለቀናት፣ ለሣምንታት፣ ... ብሎም ከሁለት ወራት በላይ ከበረዶ፣ ከረሃብ፣ ከጥማት፣ ከአሰቃቂ ህመምና ከሞት ጋር እየታገሉ ለመቆየት የተገደዱበትን እጅግ አስከፊ የህልውና ግብግብ የተረከ መፅሐፍ ነው።

ከታሪኩ የማይረሳኝ እነዚያ የተራራ ምርኮኞች የሚፈልጋቸውና የሚያድናቸው አካል ጠፍቶ፣ እነሱን ፍለጋ ይደረግ የነበረውም የቅኝት በረራ በተስፋ መቁረጥና በአስቸጋሪ አየር ንብረት ተቋርጦ፣ በቅርቡ እንደሰማናቸው የማሌይዢያ አየር መንገድ ተሣፋሪዎች ደብዛቸው ስለመጥፋቱ የመርዶ ዜናዎችን ዓለምና ቤተሰቦቻቸው እየተቀባበሉ እያለ፣ የሚላስ የሚቀመስ በሌለበት፣ በመጨረሻ በህይወት ለመሠንበት አንድ ነገር መወሰን ነበረባቸው።

ከመካከላቸው የበረዶውን ቅዝቃዜና ስቃይ መቋቋም ያልቻሉ ጓደኞቻቸው ሞተው፣ አስከሬናቸው በበረዶው እንደቀዘቀዘ አለ። ሁላችንም በረሃብ ከምንሞት ቀድመው የሞቱትን አስከሬን እንብላና የቻልነውን ያህል እንሰንብት፣ እስከዚያ እርዳታ ይደርስልን ይሆናል የሚል ሃሳብ ያመጣሉ።

ሃሳቡ አሰቃቂ ነው። ግን ካሉበት ነቅነቅ ለማለትም የሚበላ መቅመስ አለባቸው። መኖር፣ መትረፍ አለባቸው። ብዙዎቹ በመጨረሻ እየዘገነናቸውም ቢሆን በሃሳቡ ይስማማሉ። አልበላም የሰው ሥጋ ልሙት ብሎ ከነአቋሙ በጠኔ የሞተም አለ።

ሌሎቹ ግን የቀዘቀዙ የጓደኞቻቸውን አካል ቀስ በቀስ እየቆነጠሩ በሉ። ቀድሜ ከሞትኩ ብሉኝ የሚሉም ነበሩ ከመሐላቸው። ከፊት ሆኖ እያበረታ ይመራቸው የነበረ ጓደኛቸው በመጨረሻ አቅሙም ቅስሙም ዝሎ ወደ ወዲያኛው ሲያሸልብ፣ ቀድሞ የመነሳሳት መንፈስ ያልነበረው ሰው፣ አስገራሚ ቆራጥነትን ተላብሶ የተረፉትን አደፋፍሮ ሲመራቸው ይታያል።


በዚያ የፍጡራን ዘር ዝር በማይልበት የበረዶ ተራራ፣ 72 ቀናት ዙሪያቸውን ከከበባቸው ነጭ ሞት ጋር ታላቅ የሰርቫይቫል ግብግብ ገጥመው፣ በቃላት ሊነገር የማይችል ስቃይን ተቋቁመው፣ አሳሽ ሄሊኮፕተሮች ሊያዩአቸው ወደሚችሉበት ቦታ እያነከሱም፣ እየተሳቡም በበረዶ መሐል ተጉዘው፣ በመጨረሻ 16 ሰዎች በህይወት ተገኙ።

ዜናው ሲሰማ ዓለም ተንጫጫ። ግማሹ በአድናቆት። ግማሹ በውግዘት። በሰው ልጅ የቅርብ ዘመን ታሪክ በአንዲዝ ተራራ 72 ቀን አይደለም፣ ለአስር ቀን ብቻውን ተጥሎ ሊተርፍ የሚችህ ሰው አይታሰብምና ለብዙዎች የመትረፋቸው ዜና ተዓምር ሆነ።

አስከሬናቸው በጓደኞቻቸው የተበሉትን ተጓዦች ቤተሰቦች ሆነህ አስበኸዋል? ምን ዓይነት ሰቆቃ እንደሚሆንብህ?

ተጫዋቾቹ የጓደኞቻቸውን ሥጋ በልተው እንደተረፉ መጀመሪያ ደብቀው ነበር፣ በኋላ ያገራቸውን ጋዜጠኞች ለብቻ ጠርተው፣ በቃ እውነቱን እንንገራችሁ፣ የሆነው ይህ ነበር አሉ።

ከፈለጋችሁ ፍረዱብን፣ ማንም ህሊና ያለው ሰው በኛ ቦታ ቢሆን ማድረግ የነበረበትን ውሳኔ ወስደን አድርገነዋል። ለመትረፍ ያላየነው ስቃይ የለም። በህይወት ያለን ጓደኛችንን ለመብላት ስንል አልገደልንም። ...

ያለፍንበትን ገሃነማዊ ቆይታ ተረዱን፣ ይህ የፅናት ታሪካችን ነው። ከሰቆቃ የተረፍን ንፁህ ሰዎች ነን። ይህ በማንም ላይ እንዲደርስ አንፈልግም። ተገደን ያደረግነውን አድርገናል አሉ። የሰማ ሁሉ በድንጋጤ ተያዘ። እውነቱን ተናግረው ሀዘንና ፍቅር ግን ዘነበላቸው።

ይሄ እንግሊዛዊ ጋዜጠኛና ደራሲ፣ ተራፊዎቹን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ የአሳሽ ግብረሃይል አባላትንና የህክምና ቡድኖችን ሁሉ ጠይቆ፣ ተዓምራዊው ዜና በተሰማ በሁለት ዓመቱ በመፅሐፍ መልክ አተመው። የራሳችንን ጨምሮ፣ 20 በላይ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ታሪካቸው ለዓለም ተዳረሰ። ፊልሞችም ተሠርተውበታል።

የሰው ልጅ ከማይቻል መከራ ጋር ሲጋፈጥ፣ ችሎ የሚወጣ ፅኑ ፍጥረት መሆኑን የእነዚህ ኡራጓውያን እውነተኛ ታሪክ ህያው ምስክር ሆኖ፣ ተደጋግሞ ይወሳል።

ስሱ የሚመስለው ሰው፣ የቁርጡ ቀን ሲመጣ፣ መኖሩንም የማያውቀው ተፈጥሮ በውስጡ ያኖረችው የመኖር instinct ይወጣል። ያላሰበውን ቆራጥነት ይላበሳል። ተፈጥሮ ከሰው ልጅ አቅበላይ የሆነ ችግርን አልደቀነችም። ሰው ብርቱ ነው። ፅኑ መንፈስ የሰው ልጅን በመከራዎች መሐል ያኖረው ትልቁ ፀጋው ነው።

ዛሬ በመከራ የተከበብን ሰዎች፣ በተስፋ አስቆራጭ ችግር የተያዝን ሰዎች፣ እንደ አንዴዝ ተራራ፣ ከአቅማችን በላይ የመሠለን ስቃይ ዙሪያችንን ያጠረብን ምስኪኖች፣ ችግራችን እንደ ተራራ ተከምሮ ገዝፎ የታየን፣ አትተርፉም አበቃላችሁ የተባለልን፣ ከንፈር የተመጠጠልን ሰዎች... ከእነዚህ ባለታሪኮች ምን እንማር ይሆን?

በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንገኝ ተስፋ አለመቁረጥን። ፅናትን። ዕምነትን። የማንቋቋመው የመከራ ተራራ እንደሌለ። ሰው በመሆናችን ብቻ አይበገሬነት በውስጣችን እንዳለ።...

ዕምነት ካለን ተራራውን ከፊታችን ነቅለን ማንሳትና መሻገር እንደምንችል። ከመከራ ፊት ቀድሞ ከመሸነፍ፣ እየታገሉ መሸነፍ ታላቅ ክብር እንደሆነ።...

እና ደሞ በሰው ቶሎ አለመፍረድን...! በሰው ቦታ ብሆን እኔስ ምን አደርግ ነበር? ብሎ ቆም ብሎ ማሰብን። ...

እና ምናልባት... የፈጣሪንም ተዓምር አለመርሳትንም የሚያስተምር ይመስለኛል ይሄ የተራራው ምርኮኞች ታሪክ።

ሁላችንምኮ የዚህን ያክል extreme የወጣ ባይሆንም፣ የየራሳችን ተራራ ያለን ነን። ሁላችንም የየራሳችንን የኑሮ ዐለት በተራራው ላይ የምንገፋ የየራሳችን ሲሲፈሶች ነን። ሁላችንም ትንሽ ትንሽ የተራራው ምርኮኞች ነን።...

ይህን አለመርሳት፣ ህይወትን እንዳመጣጧ ማስተናገድ፣ ትዕግሥት፣ ፅናት፣ ተስፋ፣ ፍቅር..! የሰው ልጅ የመከራ ቀን ማለፊያዎች፣ የደስታ ቀን ጌጦች ናቸው። Nothing is impossible! Even the sky is not the limit!😊

Live and Let Live!

ሸጋ ቀን ተመኘሁ።

*****************

Assaf Hailu Facebook page

https://web.facebook.com/photo/?fbid=24143585448603261&set=a.222487634473044