- ቅዱስ ዮሐንስ
- ርእሰ ዐውደ ዓመት
- የዘመን መለወጫ
- እንቁጣጣሽ
እነሆ ይህ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ጦማራችን ከተጀመረ
፯ ዓመታትን
አስቆጠረ ልክ በመስከረም 2005 ዓ.ም. ተጀመረ2005 - 2011
አዲስ ዓመት ዞሮ በመጣ ቁጥር ሁሌም አዲስ ነውና ካነበብነው እነሆ፡፡
አዲስ ዓመት መቼ ይከበራል?
አዲስ ዓመት
መስከረም አንድ ቀን ለምን ይከበራል? በኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በመስከረም ወር የሆነበትን ምክንያት ሊቃውንቱ ሲያትቱ ብርሃናት ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ክዋክብት የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱ ከቀኑ ጋር እኩል 12 ሰዓት ይሆናል፡፡ ዓመቱን ጠንቅቀው ሲቆጥሩ 364 ቀናት ይሆናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ለዘመን
መታወቂያው ይሆን ዘንድ ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትንም ፈጠረ”
ይላልና /ሔኖክ. 21፥49/፡፡ በሌላ በኩልም በዘመነ ኖኅ በፍል ውኃ አጥለቅልቆ በኃጢአት ሕይወት ይኖሩ የነበሩት የኖኅ ዘመን ሰዎች ቀጥቶ ካጠፋ በኋላ ከንፍር ውኃ ምድር የተገለጠችበት ወር ነው /ኩፋሌ. 7፥1/፡፡ “በመጀመሪያው
ወር ምድር ታየች የንፍር ውኃም ከምድር ደረቀ”
የሚለውን
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መሠረት አድርገው የአቡሻኸር ሊቃውንት የዘመን መለወጫን ታሪካዊ አመጣጥ ያስቀምጣሉ፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖናዊ ሥርዐት ያጠኑ ሊቃውንት ደግሞ አዲስ ዓመት መስከረም አንድ ቀን መሆኑን አስመልክተው በክታባቸው እንዳስቀመጡት በአራቱ ወንጌላውያን ዘመኑን ይከፍሉታል፡፡ ምክንያቱም በዘመነ ዮሐንስ ተፀንሶ በዘመነ ማቴዎስ ተወልዶአል፡፡ በዘመነ ማርቆስ ተጠምቋል፡፡ በዘመነ ሉቃስ ተሰቅሎ ዓለምን ከፍዳና ከመርገም ነጻ አውጥቷል፤ እያሉ ታሪካዊ ሐረጋቸውን ጠብቆ አራቱ ወንጌላውያን ተከትለው ያለ እንቅፋት እንደሚጓዙ ያስረዳሉ፡፡
ወንጌላዊውን ወይም ዘመኑን ለማወቅ ዓመተ ኩነኔ 5500 እና ዓመተ ምሕረት /አሁን ያለንበትን ዓመት/ በመደመር ውጤቱ ለአራቱ ወንጌላውያን /ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ/ በማካፈል የምናገኘው ነው፡፡ ይህም የአንዱ ወንጌላዊ ድርሻ ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቀሪው አንድ ከሆነ ዘመኑ ማቴዎስ፣ ሁለት ከሆነ ዘመነ ማርቆስ፣ ሦስት ከሆነ ዘመነ ሉቃስ ምንም ቀሪ ባይኖር ደግሞ ዘመነ ዮሐንስ ነው፡፡
ወንጌላዊውን ወይም ዘመኑን ለማወቅ ዓመተ ኩነኔ 5500 እና ዓመተ ምሕረት /አሁን ያለንበትን ዓመት/ በመደመር ውጤቱ ለአራቱ ወንጌላውያን /ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ/ በማካፈል የምናገኘው ነው፡፡ ይህም የአንዱ ወንጌላዊ ድርሻ ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቀሪው አንድ ከሆነ ዘመኑ ማቴዎስ፣ ሁለት ከሆነ ዘመነ ማርቆስ፣ ሦስት ከሆነ ዘመነ ሉቃስ ምንም ቀሪ ባይኖር ደግሞ ዘመነ ዮሐንስ ነው፡፡
እንቁጣጣሽ
ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት
ሳባ የጠቢቡ ሰሎሞንን ዝና ሰምታ ኢየሩሳሌም ተጉዛ ስትመለስ “እንቁ ለጣትሽ /ለጣትሽ እንቁ/ በማለት ከእንቁ የተሠራ የጣት ቀለበት ንጉሥ ሰሎሞን እጅ መንሻ እንዲሆናት አበርክቶላት ነበርና ይህን ታሪክ መነሻ አድርገው “እንቁጣጣሽ”
የሚለው ስያሜ ከዚያ እንደመጣ የታሪክ ድርሳናት ያስረዱናል፡፡ በኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ዕለት ምድሪቱ በክረምቱ ዝናብ ረስርሳ ድርቀቷ ተወግዶ በአርንጓዴ እጸዋት ተውባ ሜዳው፣ ሸለቆውና ተራራው በአደይ አበባ ተንቆጥቁጠው የሚታዩበት ወቅት በመሆኑ ዕለቱ “እንቁጣጣሽ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
በዚህ ወቅት
ሕፃናትና ልጃገረዶች ነጭ ባሕላዊ ልብስ በመልበስ ለምለም ቄጤማና አደይ አበባ በመያዝ በአካባቢያቸው በመዞር አዲስ ዘመን መበሠሩን “እንኳን አደረሳችሁ” በማለት በቸርነቱ ዓመታትን የሚያፈራርቀውን እግዚአብሔርን በዝማሬ ያመሰግናሉ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ
ለምን ተባለ?
የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱን በመረዳት የቤተ ክርስቲያን አበው የበዓላትን ድንጋጌ በወሰኑበት አንቀጽ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በሚከበርበት መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ እንደወሰኑ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ /ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 1-3/፡፡
የዘመን አቆጣጠራችን
ከሌሎች ለምን ተለየ?
ፕሮፌሰር ጌታቸው
ኃይሌ ባሕረ ሐሳብ በሚል መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከምዕራባውያን የተለየበትን ምክንያት ሲገልጹ “ሮማውያን የሮም ከተማ የተቆረቆረችበትን ዘመን መነሻ ያደርገው ይተቀማሉ፤ ታላቁ እስክንድርም የገነነበት ዘመን መቁጠሪያቸው ሆኖ ነበር” የእኛ ካህናትም ዘመነ እስክንድር በሚል ይጠቀሙበት እንደነበር መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ሶርያውያን የዘመን አቆጣጠራቸውን የሚለኩት በፀሐይ ቆጥረው ለዓመቱ 365 ቀን ከ6 አካፍለው ዕለትን መስጠትን ከሮማውያን በተዋሱት ጊዜ የዓመቱን መጀመሪያ አዲስ ዓመት ይሉታል፡፡ በኋላ የሰማዕታት መታሰቢያ እንዲሆን በ460 ዓመተ እግዚእ ወደ መስከረም 1 ቀን ለወጡት፡፡ የሀገራችን ሊቃውንትም አዲስ ዓመታችን መስከረም አንድ ቀን እንዲሆን የወሰኑት ይኸንን በመከተል ነው፡፡ የዓመቱን መጀመሪያ በመስከረም ማድረግን ከሶርያውያንም ሆነ ከግብጾች ብናገኘውም ጀማሪው በ46 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ይገዛ የነበረው ዩልዮስ ቄሣር ስለነበር በዩልዮስ ባሕረ ሐሳብ ይባላል፡፡
ዩልዮስ ቄሣ
በ46 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ባወጣው የዘመን አቆጣጠር ሥርዐት መሠረት ዓመቱን 365 ዕለት ከ6 ሰዓት አድርጎ ለአራቱ ወራት 30፣30 ዕለት ለእንዱ 28 ቀን በ4 ዓመት አንዴ 29 ቀናት ለቀሩት ሰባት ወራት 31፣31 ቀናት መድቦላቸው በ12 ቦታ ከፍሎታል፡፡ አውሮፓውያኑ የሚጠቀሙበትን ይህን አቆጣጠር መነሻ አድርገው ነው፡፡ የእኛ ዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን እንዴት እንደተለየ አሥራት ገብረ ማርያም የዘመን አቆጣጠር በሚለው መጽሐፋቸው ሲገልጹ “ዲዮናስዮስ የተባለው የሮም መነኩሴ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተወለደበት ዘመን በስሌት ለመድረስ የተከተለው መንገድ የታሪክ ክስተትን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት ዘመን ለመሰወን የታሪክ ክስተትን አልተከተለችም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የተከተለችው ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን 5500 ዘመንን ነው” በማለት የልዩነቱን ምክንያት ይገልጻሉ፡፡
የዘመን አቆጣጠር
ልዩነት መነሻው የዚህ ክስተት መሆኑን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲያረጋግጡ “ኢትዮጵያ ዘመነ ብሉይን እንዲህ አስከትላ 5500 ብላ ስትቆጥር ዘመነ ሐዲስ ልዩ ሆኖ ከማንም ቁጥር አይገጥምም፡፡ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ከምስራቆቹም ከምዕራቦቹም ሁል ጊዜ በሰባት ዓመት ታጎድላለች፡፡ ምክንያቱም ባለ ታሪኮችን ትታ ወንጌል ተርጓሚዎችን መነሻዋ ስላደረገች ነው” ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያና የአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ልዩነት ሊኖረው ቻለ፡፡
አዲሱን ዓመት እንዴት እናክብረው?
እግዚአብሔር አምላካችን
እድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ የሚሰጠን መልካም ነገር እንድንሠራበት ነው፡፡ አዲስ ዓመት በየዓመቱ የሚሰጠን የትናንት ስህተታችንን እንድናርምበት ነው፡፡ የተጣላን እንድንታረቅ፣ የበደልን እንድንክስ፣ የታረዘን እንድናለብስ፣ የተጠማን እንድናጠጣ፣ የራበውን እንድናበላ እንጂ፤ በኃጢአት ሕይወት እንድንመላለስ አይደለም፡፡ የዘመኑ መቀየር ከቁጥር በዘለለ የእኛውም አስተሳሰብ እንዲቀየር ነው፡፡ ለሥጋዊ ኑሮአችን መሳካት በእቅድ እንደምንመራው ሁሉ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን እናስብ፤ ቃለ እግዚአብሔር ለመማር፣ ንስሐ ለመግባት፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል መንፈሳዊ እቅድ እናውጣ! ተግባራዊ ለማድረግም ጥረት እናድርግ፡፡ ከዘመን ወደ ዘመን የምንሸጋገረው ቅዱሳን መላእክት በሚለምኑልን የብደር እድሜ እንደሆነ እንረዳ፡፡ አምላካችን ከእኛ ሕይወት ፍሬ ለማግኘት በልጅነታችን፣ በወጣትነትና በሽምግልና እድሜያችን ሦስት ጊዜ መጣ ፍሬ ሃይማኖትና ምግባር አጣብን አትክልተኞቹን ቅዱሳን መላእክትን “ስለምን ደግሞ መሬቱን ታጎሳቁላለች?”
ቢላቸው
“ጌታ ሆይ ዙርያዋን እስክኮተኩትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት” እያሉ በለመኑት የብድር እድሜ ነው አዲስ ዓመቱን ለማየት የቻልነው /ሉቃ. 13፥6-9/፡፡
በተሰጠን የብድር
እድሜ መልካም ነገር ለመሥራት እንነሣ በስንፍና ያሳለፍነው ጊዜ ይብቃን! ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ እንዲህ ይለናል “የአሕዛብን ፈቃድ
ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ
ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ
ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት ጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” /1ኛ ጴጥ. 4፥3/፡፡ እንደማያይ ዝም ሲለን ነገ ሊፈርድ ዛሬን ስለታገሰን እግዚአብሔር አምላካችን በኃጢአታችን የተስማማ አድርገን የምንቆጥር ካለን ተሳስተናል፡፡ አዲሱን ዓመት በጭፈራና በዳንኪራ ለማሳለፍ ያቀድን ከዚህ መጥፎ ሕይወት እንውጣና ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ ለኃጢአት ሥራ የምናወጣውን ገንዘብ ለድሆች በመስጠት አብረናቸው እናክብር፤ ያን ጊዜ እኛ በሕይወት ተቀይረን አዲሱ ዓመት መቀበላችን እውነት ይሆናልና፡፡
ምንጭ:--