1927 ዓ.ም - 2015 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ በዋናነት የሚነሱት ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ የተወለዱት በ1927 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ነው።
አባታቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ የነበሩ ሲሆን፣ የክለቡን ተጫዋቾች ከትምህርት ቤት ወደ ስታዲየም ይዞ በመሄድ ይታወሳሉ፡፡
በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ከአባታቸው ጋር የመሆን ዕድል የነበራቸው አቶ ፍቅሩ በኋላ የስፖርት አስተማሪ ሆነዋል።
በኢትዮጵያ ሬዲዮና የተለያዩ የአገር ውስጥ የሕትመት ውጤቶች ስለ አገር ውስጥ ስፖርት መዘገብ የጀመሩት አቶ ፍቅሩ በ1943 ዓ.ም በሱዳን እና ኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን ጨዋታ በቀጥታ በሬዲዮ ማስተላለፍ የቻሉ የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኛ ናቸው።
አቶ ፍቅሩ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በ1961 ዓ.ም ሲመሰረት የመጀመሪያው ፕሬዝደንት የነበሩ ሲሆን በብስክሌት ፌዴሬሽን፣ቴኒስ ፌዴሬሽን እና በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በዋና ፀሐፊነት፣ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል፡፡
በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥም በአመራርነት ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የቀድሞ ፕሬዝደንት የነበሩት የኢሳ ሃያቱ አማካሪ ጭምር የነበሩ ፡፡
ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ ኑሯቸውን በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ያደረጉት አቶ ፍቅሩ በአገሪቷ ለሚገኘው ዕለታዊ የስፖርት ጋዜጣ ለኪፕ እና ሳምንታዊ የእግር ኳስ መጽሔት ፉትቦል ፍራንስ፣ ዶቼቬሌ (የጀርመን ድምፅ) እና ሌሎች የአለም አቀፍ ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን መስራት ከመቻላቸው በተጨማሪ “የፒያሳ ልጅ” እና “የስፖርት ጨዋነት ምንጮች” የተሰኙ መጻሕፍት መጻፍ ችለዋል፡፡
ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ አንድ ልጅ ያላቸው ሲሆን ሁለት የልጅ ልጆችንም አይተዋል።
አንጋፋው የስፖርት ሰው ፍቅሩ ኪዳኔ ሲታወሱ
በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፖርቶች ውስጥ አሻራቸውን ካሳረፉ ሰዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ።
በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያውን የእግር ኳስ ግጥሚያ በሬዲዮ ከማስተላለፍ አንስቶ፣ በሬዲዮና በጋዜጣ ላይ ስፖርትን የሚመለከቱ ዘገባዎች ቦታ እንዲያገኙ አድርገዋል።
በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት ውስጥ ጉልህ ሚና ካላቸው ጥቂት ኢትዮጵያውያን መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። በ87 ዓመታቸው ያረፉት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ እንዴት ይታወሳሉ?
በኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኝነት ሙያ የመጀመሪያው የእግር ኳስ ግጥሚያ በሬዲዮ ከማሰራጨት እስከ ፀሐፊ እና የስፖርት ሕትመቶች ዋና አርታዒነት ደርሰዋል።
በስፖርት እውቀታቸው ዓለም አቀፍ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ሴክሬታሪያት ፀሐፊ ሆነው አገልግለዋል። በዘረፉ ለስመዘገቡት አስተዋጽኦ በዓለም አቀፉ የስፖርት ፕሬስ ማኅበር የሕይወት ዘመን ስኬት ሽልማትን ተቀብለዋል።
ጥቅምት 01/2015 ዓ.ም. ፈረንሳይ ውስጥ በ87 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን አንጋፋውን የስፖርት ሰው ፍቅሩ ኪዳኔን ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛው ገነነ መኩሪያ “የሕይወት ዘመናቸውን በሙሉ ለኢትዮጵያ ስፖርት ያዋሉ” ሲል ይገልጻቸዋል።
ፍቅሩ ኪዳኔከኔልሰን ማንዴላ ጋር
የመጀመሪያው የእግር ኳስ ግጥሚያ በሬዲዮ
አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ እአአ 2016 ላይ ለሲቢሴስ አማርኛ ሲናገሩ፤ በኢትዮጵያ የሕትመት ውጤቶች እና የሬዲዮ ስርጭት ውስጥ የስፖርት ፕሮግራሞች እንዲከፈቱ ጥረት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
አቶ ፍቅሩ እርሳቸው በጀመሩት የመጀመሪያው የሬዲዮ ፕሮግራም የኢትዮጵያ እና የሱዳን ብሔራዊ ቡድኖችን የእግር ኳስ ግጥሚያ ለመጀመሪያ ጊዜ ማሰተላለፋቸውን ይገልጻሉ።
አቶ ፍቅሩ ይህን ጨዋታ እንዴት በሬዲዮ እንዲያስተላለፉ የተደረገው በድንገትና ሳያስቡት ነበር። ይህም ጨዋታውን ለሕዝብ ጆሮ እንደሚያደርሱ ሳይነገራቸው እና ምንም አይነት ዝግጅት ሳያደርጉ ነበር የመጀመሪያውን የቀጥታ ሥርጭት ያስተላለፉት።
አቶ ፍቅሩ ይህን ጨዋታ እንዴት በሬዲዮ እንዲያስተላለፉ የተደረገው በድንገትና ሳያስቡት ነበር። ይህም ጨዋታውን ለሕዝብ ጆሮ እንደሚያደርሱ ሳይነገራቸው እና ምንም አይነት ዝግጅት ሳያደርጉ ነበር የመጀመሪያውን የቀጥታ ስርጭት ያስተላለፉት።
ሱዳኖች የእግር ኳስ ጨዋታውን ከአዲስ አበባ በቀጥታ በሬዲዮ እንደሚያስተላልፉ የተረዱት አቶ ይደነቃቸው ተስማ፣ እኛስ ለምን አናስተላልፍም? በማለት ሐሳቡን በድንገት እንዳመጡት ጋዜጠኛ ገነነ ይናገራል።
ከዚያም ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር የቀጥታ ሥርጭቱ በመፈቀዱ ጨዋታው ከመጀመሩ ከደቂቃዎች በፊት አቶ ፍቅሩ እንደሚፈለጉ በድምጽ ማጉያ ተጠርተው ነበር በድንገት ተጠርተው የቀጥታ ሥርጭት ማይክሮፎን የቸበጡት ይላል ገነነ።
አቶ ፍቅሩም “ጨዋታው ሊጀመር 10 ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩት ትፈለጋለህ ተብዬ ተጠርቼ ስሄድ፣ አቶ ይድነቃቸው አንተ እኮ ነው የምትፈለገው ብሎ የተጫዋቾችን አሰላለፍ ሰጥቶ ጨዋታውን እንዳስተላልፍ ነገረኝ” ሲሉ አስታውሰዋል።
“ጨዋታው ሊጀመር 10 ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩት ትፈለጋለህ ተብዬ ተጠርቼ ስሄድ፣ አቶ ይድነቃቸው አንተ እኮ ነው የምትፈለገው ብሎ የተጫዋቾችን አሰላለፍ ሰጥቶ ጨዋታውን እንዳስተላልፍ ነገረኝ።”
ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ የስፖርት ውድድር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ስታዲዮም (በ1948 ዓ.ም.) የእግር ኳስ ጨዋታ በሬዲያ በቀጥታ በሬዲዮ በማስተላከፍ አቶ ፍቅሩ ቀዳሚው ሆኑ።
በሕትመት ውጤቶች ላይም ቢሆን ስፖርታዊ ጉዳዮችን መዘገብ የተጀመሩት በአቶ ፍቅሩ ጥረት ነበር። ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ለቢቢሲ ሲናገር፤ “በጋዜጦች ላይም ስፖርት የሚባል አይታወቅም ነበር። ከ1950 በኋላ ፍቅሩ ነበር መጻፍ የጀመረው።”
ጫማ ለአበበ ቢቂላ
ገነነ እንደሚለው በባዶ እግሩ የኢሊምፒክ ማራቶንን በማሸነፍ የሚታወቀው የዓለማችን ታላቁ የማራቶን ሯጭ አበበ ቢቂላ በጫማ እንዲሮጥ ያደረጉት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ናቸው።
“ፍቅሩ ከአንድ ጫማ አምራች ድርጅት ጋር ተነጋግሮ ለአበበ በነጻ የመሮጫ ጫማ እንዲሰራለት አስደርጓል። ጫማ አምራቹም በአበበ ስም ታዋቂነትን ለማግኘት ችሏል።”
በኒውዮርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ሲሰሩ የቆዩት አቶ ፍቅሩ፣ ወታደራዊው መንግሥት ወደ ሥልጣን በመጣበት ጊዜ እንደወጡ ቀርተው ለበርካታ ዘመናት በተለያዩ አገራት ውስጥ ኖረዋል።
ነገር ግን ባሉበት ሆነው በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፖርቶች እንዲጎለብቱ የሚችሉትን አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ቆይተው፤ አብዛኛውን እድሜያቸውን በቆዩባቸው የውጭ አገራት ውስጥ ሆነው እንኳን ለኢትዮጵያ ስፖርት ሲሰሩ እንቆዩ ገነነ ገልጿል።
አቶ ፍቅሩ በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፖርቶች ውስጥ ፍቅሩ ያልገቡበት ዘርፍ የለም የሚለው ገነነ፣ አሁን ትኩረትን እየሳበ ያለው የሴቶች እግር ኳስ እንዲጎለበት የአቶ ፍቅሩ ሚና ጉል እንደነበር ይጠቅሳል።
ፍቅሩ ከእግር ኳስ ባሻገር በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ውስጥ ኢትዮጵያ ውክልና እንዲኖራት በግሉ የቻለውን ሁሉ ሲያደርግ እንደቆየ የሚናገረው ጋዜጠኛ ገነነ፤ ብዙም አቅም የሌላቸው የስፖርት ፌዴሬሽኖችን በመወከል በእራሱ ወጪ በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ይሳተፍ ነበር።
እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የዘር መድልዎ (አፓርታይድ) ሥርዓት በመቃወም አገሪቱ ከዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች እንድትታገድ ከአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ጋር ከፍተኛ ጥረት ከማድረግ ባሻገር፤ በዓለም አቀፍ ሕትመቶች ላይ ፀረ አፓርታይ የቅስቀሳ ጽሁፎችንም ያቀርብ እንደነበር ገነነ አስታወሷል።
የዓለም ዋንጫን በፕሮጀክተር
አቶ ፍቅሩ ስፖርት በመገናኛ ብዙኃን ላይ ቦታ እንዲያገኝ ከመጣራቸው ባሻገር፣ ቴሌቪዥን ባልተስፋፋበት በዚያ ዘመን ከአዲስ አበባ ውጪ ያለው ስፖርት አፍቃሪ ታላላቅ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን እንዲመለከትም አስችለዋል።
ለዚህም እአአ 1958 በስዊዲን አገር ተካሂዶ የፔሌ ትውልድን የያዘው የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ዋንጫ የወሰደችበትን ግጥሚያ አቶ ፍቅሩ በክፍለ አገር ከተሞች እየተጓዙ በፕሮጀክተር ጨዋታውን ያሳዩ እንደነበረ ጋዜጠኛ ገነነ ይናገራል።
“እኛ ፔሌ፣ ጋሪንቻ የሚባሉትን በስም እንኳ አናውቃቸውም ነበር። እሱ በየክፍለ አገሩ ዞሮ ካሳየ በኋላ ነው ተጫዋቾቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የታወቁት።”
አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ በስፖርት ጋዜጠኝነት ሙያ ከማገልገላቸው በተጨማሪ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ፣ የማስታወቂያ ባለሙያ ሆነውም ሠርተዋል።
በተጨማሪም በመንግሥታቱ ድርጅት በኩል ኢትዮጵያ ወደ ኮንጎ ጦሯን ባሰማራችበት ወቅት ጦሩን የሚመሩት የኢትዮጵያ ጄኔራሎች ፈረንሳይኛ የሚናገር ወጣት በመፈለጋቸው፣ ፍቅሩ የመቶ አለቃ ማዕረግ ይዘው ወደ ኮንጎ መዝመተውም ነበር።
ይህ አጋጣሚ ነበር አቶ ፍቅሩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሥራ ዕድል በር ከፍቶላቸው የማስታወቂያ ባለሙያ ሆኖ የመስራት ዕድልን እንደከፈተላቸው ጠቅሰው ነበር።
ኦሊምፒክ እና አቶ ፍቅሩ
አቶ ፍቅሩ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ስለኦሊምፒክ ጨዋታዎች ያለው እውቀት እምብዛም ባልነበረበት ወቅት ውድድሩን ለአገሬው ለማስተዋወቅ መጽሐፍ እስከ ማሳተም ደርሰው ነበር።
“የኦሊምፒክ ጨዋታ የሚል መጽሐፍ በ1960 አሳተምኩ። ይህን መጽሐፍ ያዘጋጀሁት ሕዝቡ ስለ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች እውቀት እንዲኖረው ነው።”
ይህን መጸሐፍም ለትምህርት ሚኒስቴር በመስጠት በአገሪቱ ባሉ ትምህርት ቤቶች እንዲታደሉ በማድረግ ወደ ወጣቶች እንዲደርስ አድርገዋል።
አቶ ፍቅሩ ከስፖርት ጋር በተቆራኘው ሕይወታቸው በበርካታ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል። በኢትዮጵያ የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ተቀጥተው የኢትዮጵያ የብስክሌት ፌዴሬሽን፣ የቴኒስ ፌዴሬሽን፣ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።
አቶ ፍቅሩ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበርን አቋቁመው የማኅበሩ ፕሬዝዳንት በመሆንም ሠርተዋል።
ከኢትዮጵያም ውጪ አቶ ፍቅሩ ከኦሊምፒክ ውድድር ጋር ባላቸው ቁርኝት ትልቅ የሥልጣን ደረጃ ላይ መድረስም ችለው ነበር።
ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ አቶ ፍቅሩ የመጀመሪያው ጥቁር የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና የፕሬዝዳንቱ ልዩ አማካሪ ሆነው ተሹመው እንደነበረ ይገራሉ።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የፕሬዝዳንቱ ልዩ አማካሪ፣ የአፍሪካ የሰፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር ዋና ፀሐፊ በመሆን አገልግለዋል።
የፊፋ የፕሬስ ኮሚቴ አባል የነበሩ ሲሆን እንደ ቢቢሲ፣ የአሜሪካ ድምጽ፣ ሬዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል ላሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን ይሰሩም ነበር።
ጥር 17፡2008 ዓ.ም ከጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ጋር የተደረገ ቆይታ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር
ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ SBS Amharic
Life and Legacy: Fikrou Kidane – Pt 1 - SBS Amharic
Life and Legacy: Fikrou Kidane – Pt 2 - SBS Amharic
Life and Legacy: Fikrou Kidane – Pt 3 - SBS Amharic
http://www.danielkibret.com/2010/11/blog-post_21.html
http://www.tadias.com/index.php?s=60th
https://www.aipsmedia.com/aips/pages/articles/2018/23368.html
https://www.aipsmedia.com/aips/pages/articles/2022/32933.html
https://ethiopiazare.com/amharic/images/doc/pdf/books/2011/1105ye-piassa-lij-by-mesfin-mammo.pdf
********************************
ምንጭ:-- https://www.bbc.com/amharic/articles/cx76v13n28eo