ጋዜጠኛው ኤን. ማንዴላ (N. Mandela)-በኢትዮጵያ!
(99 ቀናት በአዲስ አበባ)
(በሰሎሞን
ተሰማ ጂ.)
በታኅሣሥ አጋማሽ 1954 ዓ.ም በግርማዊ ንጉሠ ነገሥቱ ጥሪ ተደረገለትና
በጥር መጀመሪያ ላይ አዲስ አበባ ገባ፡፡ ይህ ሰው በሦስት ወራት ከአንድ ሳምንት (በ98 ቀናት) ቆይታው ወቅት እጅግ የተጣበበ
መርሐ ግብር እንደነበረበት ያስታውቃል፡፡ በጥር 8/1954 ዓ.ም በንጉሠ ነገሥቱ በተከፈተውና ለአሥር ቀናት ያህል በቆየው፣ “የአፍሪካ
ኤኮኖሚና ሶሻል ዕድገት ጉባኤ” ላይ ተካፍሏል፡፡ ከተካፋይነትም አልፎ፣ ስሜታዊ የሆነ ንግግር አድርጓል፡፡ ብዙዎቹ የጉባኤው ተሳታፊዎች፣
ስለሀገሩና ስለሕዝቡ ሰቆቃ ባለማወቃቸውም አዝኗል፡፡ (አዲስ ዘመን፣ ጥር 9 ቀን 1954፣ ገጽ 1) ከዚያም በመቀጠል ከጥር 6
እስከ ጥር 14 ቀን 1954 ዓ.ም የተደረጉትን የአፍሪካ ዋንጫ ግጥሚያዎች በዛሬው የአዲስ አበባ ስታዲዮም ተገኝቶ ተከታትሏል፡፡
ሀገሩ፣ ለምን በዚህ የአፍሪካ ዋንጫም እንዳልተካፈለች የኢትዮጵያን
እግር ኳስ ባለስልጣኖች ጠይቆ ተረድቷል፡፡ እንዲህ አሉት፤ “በወርኃ የካቲት 1950ዓ.ም ጨዋታው ሊጀመር ሦስት ቀናት ሲቀረው፣ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን
አባላት የደቡብ አፍሪካ ቡድን አስመልክቶ የውሳኔ ሃሳብ/ሞሽን/ አቀረቡ፡፡ “የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን መንግሥት በጥቁር አፍሪካውያን
ላይ የሚያራምደውን የዘር መድሎ አገዛዝ ካላቆመ በስተቀር፣ የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ አይገባውም”
የሚል አቋም ያዙ፡፡ እርግጡን ለመናገር፣ ወደካርቱም መጥቶ የነበረው የደቡብ አፍሪካ ቡድን አንድም የአፍሪካነር/ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ/
አላሣተፈም ነበር፡፡ በመስራች አገሮቹ የጋራ ስብሰባ ላይ፣ ሐሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ደቡብ አፍሪካ ከዋንጫው በእግድ ተሠናበተች፡፡”
ሲሉ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ነገሩት፡፡ ውሳኔውም
ትክክለኛ ነው ሲል ድጋፉን ሰጠ፡፡
በጥር 10 ቀን 1954 ዓ.ም በዋለው
የከተራ በዓልም ላይ ተገኝቶ “ግርማዊ ንጉሠ ነገሥቱ” በጃን ሜዳ ተገኝተው በዓሉን ከሕዝቡ ጋር ሲያከብሩት ባይኑ አይቷል፡፡ የአልጋ
ወራሹንና የአቡኑንም ንግግሮች በቱርጁማን አዳምጣቸዋል፡፡ ሁሉም ነገር ገርሞታል፡፡
በሕዝቡና በከሕናቱ፣ በሕዝቡና በመኳንንቱና በመሳፍንቱ መካከል ያለው ልዩነት የፕሮቶኮል ብቻ እንደሆነ ተሰማው፡፡ በጥር 13 ቀን
1954 ዓ.ም (በዕለተ እሑድ ሃምሳ ሺህ ሕዝብ በተሰበሰበበት የቀ.ኃ.ሥ ስታዲየም ተገኝቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግብፅ አቻውን
4 ለ 2 ሲያሸንፍ አይቶ፣ ልቡ በድሉ ሰበብ ደስፈቅ ብሏል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም
ለብሔራዊ ቡድኑ አባላት ዋንጫ ሲሰጡ የነበረውን ሥነ ስርዓት ተመልክቷል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ከሕዝቡ ጋር ናቸው፤ ገረመው፡፡ ደነቀው፡፡
በሕዝቡና በንጉሠ ነገሥቱ እንዲሁም በሹማምንቱ መካከል ያለው ልዩነት የኃላፊነትና የተዋረድ እንደሆነ ገመተ፡፡ እራሱንም፣ የዚህ
ሕዝብ አካል አድርጎ ለመቁጠር ከጀለ፡፡ ማን ያውቃል? ዜግነቱን የሚገልጽ የመታወቂያ ወረቀት (I.D Card/Passport) ያገኝ
ይሆናል፡፡ ያኔ ታዲያ፣ ዜግነቱ ተረጋገጠለት ማለት አይደለ? ሆኖም፣ በዘር መድሎና በጭቆና ሥር ያለውን የራሱን ሕዝብ ለራሱ ምቾትና
ድሎት ሲል ሊሰደድ ፈለገ፡፡ “በአፓርታይድ እስር ቤት ከመታጎር መሰደድ ይሻላል፤” ሲል አወጣ አወረደ፡፡ በታኅሣሥ የኢትዮጵያ ንጉሠ
ነገሥት መንግሥት ጥሪ አድርጎለት ወደ አዲስ አበባ ከመመጣቱ ሁለት ወራት በፊት፣ የፓርታይድ መንግሥት የእስር ማዘዣ አውጥቶበት
ነበር፡፡ ለጥቂት ነው፣ አምልጦ የወጣው፡፡ “ከስደት መታሰር!” ወይስ “ከመታሰር መሰደድ!” ይሻል ይሆን? እያለ ማመንታቱ አልቀረም፡፡
ከብዙ ማመንታትና ማውጠንጠን በኋላ፣
“እንዴት አድርጎ ሕዝቡን ነፃ ሊያወጣ እንደሚችል ጭላንጭል ስለታየው፣ ቀሪ መርኀ-ግብሩን መተግበሩን ቀጠለ፡፡ በጣም የተጣበበው
የሰውዬው መርሐ ግብር እንደቀጠለ ሲሆን፣ ወቅታዊ ዘገባዎችንና ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባወችን መከታተሉን አላስታጎለም፡፡ በጥር
20/1954 ዓ.ም፣ ወዳጁ-የታንዛኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚ/ር ጁሊዬስ ኔሬሬ ሥራውን/ሥልጣኑን በገዛ ፈቃዱ ሲለቅም አዲስ አበባ
ሆኖ ዜናውን ተከታትሎታል፡፡ (በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን የለቀቀ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ጠቅላይ ሚ/ር ጁሊዬስ ኔሬሬ ነው፡፡) በጥር
25/1954 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ላይ በአፍሪካ አዳራሽ በንጉሠ ነገሥቱ የመክፈቻ ንግግር በይፋ በተከፈተው፣ “የማዕከላዊና የምሥራቅ
አፍሪካ የነጻነት ንቅናቄ ድርጅት ጉባኤም” ላይ፣ የፓርቲው የANC (African National Congress)ን በመወከል፣ የልዑካን ቡድኑ አባል ሆኖ በጉባኤው ላይ ተካፍሏል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የመጡት
ሁለት የደቡብ አፍሪካ ፓርቲዎች (የፖለቲካ ፓርቲዎች) ሲሆኑ፣ የANC ተወካዮች ሆነው የመጡት ሦስት ነበሩ፤ ሚ/ር ታንያሳን ማኪዋኒ
(የANC ሊቀ መ/ር)፣ ሚ/ር ኤን. ማንጄላ (“ማንዴላ” ለማለት ነው፤) የANC ም/ል ሊቀ መ/ር፣ እና ሚ/ር ኦሊበር ታንቦ
(የANC የውጭ ጉዳይ ኃላፊ) ናቸው፡፡ የPAC (Peoples of Africa Congress)ን በመወከል የመጡት የልዑካን ቡድኑ አባላት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ሚ/ር
ሞሎትሲ፣ ሚስስ ዲጀ. ማቱትሀ፣ እና ሚ/ር ቪ.ኤል. ማኪ ትበሩ እንደነበሩ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በጥር 26/1954 ዓ.ም ዕትሙ
(ገጽ-1) ላይ አስፍሮታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ የሰሜን ሮዴሺያ
(ያሁኗን “ዛምቢያ” ማለቱ ነው) በመወከል፣ ሚ/ር
ኬኔት ካውንዳ፣ ሚ/ር አር.ሲ ካማንጋ፣ ሚ/ር ጄ.ኬ. ሙሉንጋ፣ ሚ/ር ኤም. ሲፖሎ ተገኝተዋል፡፡ የኬንያውን ካኑ ፓርቲም በመወከል፣
ሚ/ር ማዋያ ኪባኪ (ያሁኑ የኬንያ ፕ/ት) እና ሚ/ር ማሉ ነበሩ የመጡት፡፡ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድንም በአቶ ከተማ ይፍሩ የሚመራ
ሲሆን እነአቶ ጌታቸው መካሻንና እነአቶብርሃኔ ባሕታን ያካተተ ነበር፡፡
አምባሳደር ዮዲት እምሩም የውጭ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳዮች ዴስክን በመወከል ተናጋሪ ነበሩ፡፡
የANC ም/ል ሊቀ-መንበር፣ በጉባኤው
ላይ ከመካፈሉም በላይ፣ (ኧረ ምን መካፈል
ብቻ!) ስለአፓርታይድ ዘረኛና ነውረኛ አገዛዝም ሰፊ ዲስኩር አቅርቧል፡፡ (አዲስ ዘመን ጥር 26/1954 ዓ.ም ገጽ 1)፡፡ የEthiopia
Herald (February, 4/1962) በጥር 27/1954 ዓ.ም እንደዘገበው ከሆነ፣ ሰውዬው ለጉባኤተኞቹ ያቀረበውን ንግግር
ሙሉ-ቃል በገጽ-1፣3 እና 4 ላይ አውጥቶታል፡፡ ጉባኤው በዋናነት የሚነጋገርባቸው አራት ዓላማዎችን ያነገበ ነበር፡፡ የጉባዔው
አጀንዳዎች፣ “1ኛ) አውሮፓውያኖች ባሪያ ለመሸጥና የአቅኝነት ተግባራቸውን ለመፈጸም ሲሉ የአፍሪካ አህጉርን ምንም ባህል የሌላቸው
ሰዎች የሚኖሩበት (የአውሬ ሕዝብ) አህጉር አድርገውታል፡፡ ይህን ከእውነት የራቀ ግምትና ሥዕል ማስወገድ አለብን፡፡ 2ኛ) አፍሪካዊ
ያልሆኑትን ሕዝቦች ስለአፍሪካ ታሪክና ባህል፤ እንዲሁም ስለሕዝቡ የጋለ ምኞትና የማደግ ተስፋ እንዲረዱት ማድረግ፤ 3ኛ) የአፍሪካን
አንድነት ማጠንከርና የያዝነው ጠንካራ አቅምም በዓለም ፊት እንዲገለጥ ማድረግ፤ 4ኛ) ቅኝ አገራቸውን አንለቅም ሲሉ የሚንገታገቱትን
ቅኝ ገዢዎች በዓለም ፊት እንዲዋረዱ፣ መውቀስና ማስወቀስ አለብን፤” የሚሉ ነበሩ፡፡ አፍሪካዊ የጋራ መከላከያ (ማኅበር) ስለማቆም
ጉዳይ ለመወያየት የተጠራ ጉባኤ ነበር፡፡ (አዲስ ዘመን፣ ጥር 26 ቀን 1954 ዓ.ም ገጽ 2)፡፡ ለዚህ ጉባኤ መነሻ (እርሾ የነበረው)፣
ከጥር 17-19/1954 ዓ.ም በሌጎስ፣ ናይጄሪያ ተደርጎ የነበረው የ19ኙ የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት መሪዎች ጉባኤ ውሳኔ ሃሳብን
ገቢራዊ በማድረግ ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ የሌጎሱን የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት ጉባኤ ተካፍለው በጥር 20 ቀን 1954 ዓ.ም አዲስ
አበባ ከገቡ በኋላ በአስቸኳይ የተከናወነ ጉባኤ ነበር፡፡
ጃንሆይ ጉባኤውን ሲከፍቱ እንዲህ አሉ፤ “ፊሎዞፊውን በዘር
ልዩነት ላይ የመሠረተው የደቡብ አፍሪካ ነጮች መንግሥት፣ በሕዝብ ቁጥር እጅግ የሚበልጡትን አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ላይ የሚፈጽመውን
የዘር ልዩነትና የጭቆና አገዛዝ እንደቀጠለ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው ምንግሥት የሚከተለውን የግፍ አገዛዝ እንዲያሻሽለው ለማስገደድ
ልዩ ልዩ እርምጃዎችን እየወሰድን ቢሆንም፣ እስካሁን በደቡብ አፍሪካ ነጮች መንግሥት በኩል አንዳችም የመለወጥ ነገር ባለመኖሩ፣
አፍሪካውያን ወንድሞቻችን አሁን ከሚገኙበት የጭቆና አገዛዝ ሥር ነፃ ለማጣት የአፍሪካውያን ደጋፊዎች ሁሉ፣ ካሁን ቀደም ከታሰበው
እርምጃ ሌላ እንዲወስዱ አሳስባለሁ፡፡ መንግሥታችንና የኢትዮጵያ እኅት የሆነችው የላይቤሪያ መንግሥት የጀመሩት ሕጋዊ ትግል መልካም
ፍሬ ያሳያል ብለን እናምናለን፡፡” ካሉ በኋላ፣ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉም እንዲህ ብለው ነበር፤ “የተሰበሰባችሁበትን ከፍተኛ ሥራ
ለማከናወን ሁሉን የሚችል አምላክ ረድኤቱን ይስጣችሁ፡፡” ጃንሆይ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁ፣ ሰውዬውና ሌሎችም ተሰብሳቢዎች በሙሉ
ከመቀመጫቸው ተነስተው እጃቸው እስኪቀላ ድረስ አጨበጨቡ፤ የአፍሪካ አዳራሽም በጭብጨባው ተናወጠ (የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ጥር
26/1954 ዓ.ም፣ ገጽ-1)፡፡
ያወሳነው ሰውዬ፣ የANC ምክትል ሊቀመንበር ሆኖ በዚሁ
“የአፍሪካ የነፃነት ትግል ጉባኤ” ላይ ከመገኘቱም በላይ፤ እንዲህ ብሎ ነበር፤ “አንዳንድ የአፓርይድ መንግሥት ጠፍጥፎ የሠራቸው
ተቋሚ ነን ባይ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፣ የፈለጉትን ያህን ቢፍጨረጨረና ትግላችንን ለማኮላሸት ከአፓርታይድ መሪዎች ጋር ቢሠሩም እንኳን፣
ለሕዝባችን በጽናት ታግለንና አታግለን ነፃ እናወጣዋለን፤ እናንተም ከዚህ ዓላማችን ጎን እንደምትሰለፉ ጥርጥር የለኝም፤” አለ፡፡
የአርባ ሦስት አመቱ ሠውዬ፣ ቁርጠኝነቱም እየጨመረ ሄዴ፡፡ ጉባኤው በየካቲት 2/1954 ዓ.ም የመግባቢያ ሰነድ አጽድቆ ተበተነ፡፡
በየካቲት 1/1954 ዓ.ም በገነት የቀ.ኃ.ሥ የጦር ትምህርት
ቤትም ተገኝቶ የ21ኛውን የመምሪያ መኮንኖችና የዕጩ መኮንኖች ኮርስ ጨርሰው ለወጡት ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማና የምስክር ወረቀት ንጉሠ
ነገሥቱ ሲሰጡ የክብር እንግዳ ሆኖ ተገኝቶ ነበር፡፡ በየካቲት 2/1954 ዓ.ም የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳረጋገጠው ከሆነ፣
“በዚሁ የ21ኛው ኮርስ የምረቃ በዓል ላይ፣ ጥሪ የተደረገላቸው የሚሊታሪ አታሼዎችና ሰሞኑን በአፍሪካ አዳራሽ ውስጥ ስለአፍሪካ
የነፃነት ንቅናቄ ስብሰባቸውን የጀመሩት መልዕክተኞች በሙሉ በሥነ በዓሉ ላይ እንዲገኙ በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት ተገኝተው ስለነበሩ፤
ግርማዊ ጃንሆይ እንግዶቹን እየተቀበሉ የእጅ ሰላምታ ሰጥተዋቸዋል፤” ይላል፡፡ ስለሆነም፣ ሰውዬው በገነት ጦር ትምርት ቤት ተገኝቶ
ይጉሡን እጅ ጨብጧል፡፡ ለዚህም ነው፤ ሁኔታውን አስታውሶ ከሠላሳ ሦስት ዓመታት በኋላ ባሳተመው “Long Walk To Freedom” በተባለው መጽሐፉ በ47ኛው ምዕራፍ ላይ ዕለቱን እንዲህ ሲል ዘክሮታል “…Meeting the Emperor himself
would be like shaking hands with history…” (ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር መገናኘትና መጨባበጥ በራሱ፣ ከታሪኬና
ከአፍሪካዊነት ታሪክ ጋር አንደመጨባበጥ ያለ ነው!” ያለው፡፡
እንደአዲስ ዘመን ዘገባ ከሆነ፣ ከጧቱ 3፡00 ሰዓት ላይ
ንጉሠ ነገሥቱ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ሲደርሱ የመከላከያ ሚኒስትሩ ክቡር ሌትናንት ጄኔራል መርድ መንገሻ፣ ክቡር የጦር ኃይሎች
ጠ/ኤታማዦሩ ሌትናንት ጄኔራል ከበደ ገብሬ፣ የምድር ጦር ዋና አዛዡ፣ ክቡር ሜ/ር ጄኔራል ኢሳያስ ገ/ሥላሴ፣ እና የትምህርት ቤቱ
ዋና አዛዥ ኮሎኔል ኃይሌ ባይከዳኝ ሲቀበሏቸው ሲያይ የተፈጠረበትን ስሜት እንዲህ ሲል መዝግቦታል፤ “Here, for he first time
in my life, I was witnessing black soldiers commanded by black generals
applauded by black leaders who were all guests of black head of state. It was a
heady moment. I only hoped it was a vision of what lay in future for my own
country…” በዚሁ ታሪካዊ ዕለት ማግስት፣
ንጉሠ ነገሥቱ በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ባደረጉት የእራት ግብዣ ላይ ተገኝቶ ንጉሠ ነገሥቱን አነጋግሯል፡፡ (አዲስ ዘመን፣ የካቲት
3 ቀን 1954 ዓ.ም፣ ገጽ 1) በእራት ግብዣውም ላይ ንጉሠ ነገሥቱ የጉባኤውን ተሳታፊዎች በየተራ ሲያነጋግሩ፤ የሰውዬው ተራ
ደረሰና ማነጋገር ጀመረ፤ “የጦር ስልጠናም መሠልጠን” እንደሚፈልግ ነገራቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም የኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ማሰልጠኛን
ዋና አዛዥ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩን ጠሩና ሰውዬውን ለሁለት ወራት ያህል በፈጥኖ ደራሽ ማሰልጠኛ ውስጥ እንዲያሰለጥኑት አዘዙ፡፡
ሰውዬው፣ በዕለተ ሰኞ የካቲት 5/1954 ዓ.ም፣ በኮልፌ የፈጥኖ ደራሽ ማሰልጠኛ ገብቶ መሠልጠን ጀመረ፡፡ እስከ ሚያዚያ
4/1954 ዓ.ም ድረስም በኮልፌ ማሰልጠኛ ጣቢያ እየተመላለሰ ይሰለጥን ነበር፡፡
ሰውዬው ስልጠና ከጀመረ ከሁለት ቀናት በኋላ፣ በየካቲት
7/1954 ዓ.ም አርፈው በየካቲት 8/1954 ዓ.ም ሥርዓተ ቀብራቸው በተፈጸመው እቴጌ መነን አስፋው ቀብርም ላይ ከብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩ ጋር ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሄዶ፣ ለቀበር የወጣውን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚገመት የአዲስ አበባ
ነዋሪ ሕዝብ ለቅሶና ዋይታ አይቷል፡፡ በዚህ ጊዜ የጠበቃ ነፍሱ ምን እንዳሰበች የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው፡፡ በየካቲት 10 ቀን
1954 ዓ.ም የነበረውን የእቴጌይቱ የሳልስት ቀን አከባበርም አይቶ ተገረመ፡፡ ከዚያም ከየካቲት 12 ቀን 26 ቀን 1954 ዓ.ም
ድረስ በተደረገው የአፍሪካ ኤኮኖሚ ኮሚሽን ጉባኤ ላይ ተገኝቶ ስለደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መንግሥትና እየተፈጸመ ሥላለው የዘር
ልዩነትና ጭቆና ሠፊ ማብራሪያ ሰጠ፡፡ በጉባኤው ማጠቃለያም ላይ 25 ያህል ውሳኔዎችን ሲያስተላልፍ፣ የደቡብ አፍሪካን ጉዳይ በተመለከተ
ጠንካራ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ አምስተኛው አንቀጽ እንዲህ ይላል፤ “ስለዘር ልዩነት፤ ደቡብ አፍሪካ አሁን የሚመራውን የዘር ልዩነት ፖሊሲ
እስኪለውጥ ድረስ ከጉባኤው አባልነት እንዲፋቅ የአፍሪካ ኤኮኖሚክ ኮሚሲዮን ለተባበሩት መንግሥታት የኤኮኖሚና የሶሻል ምክር ቤት
ሐሳብ አቅርቧል፡፡” (አዲስ ዘመን፣ የካቲት 27 ቀን 1954 ዓ.ም፣ ገፅ-3)፡፡
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የአፍሪካ ክፍል (በአምባሳደር ዮዲት እምሩ የሚመራ ነበር፤) በመጋቢት 8 ቀን 1954 ዓ.ም ስለደቡብ አፍሪካ ጉዳይ መግለጫ አወጣ፡፡
“የአፓርታይድ መንግሥት” ይላል መግለጫው “የአፍሪካውያኖችን የተመረጡና ለም የእርሻ መሬቶችና የማዕድን መሬቶች 88% ከጥቁሮች
ላይ ነጥቆ ለአውሮፓውያን ጥቅም እንዲውሉ ሰጥቷል፡፡ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን፣ 12% በሚሆነው ደረቅና በረሃማ ሥፍራ “ለጥቁሮች ብቻ” ተብሎ በተለየውና በታጠረው ሥፍራ እንዲሰፍሩ ተደርገዋል፡፡
በእነዚህ ድህነትና ችግር ባጠቃቸውም ስፍራዎች አፍሪካውያኖች እንዲሰደዱ ተገደዱ፡፡” እያለ ይቀጥላል (መጋቢት 10 ቀን 1954፤
ገጽ 3 እና 4)፡፡ ሰውዬው የውጭ ጉዳይ ባለስልጣናቱን ቀልብ ከመሳቡም በላይ፣ ወደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆዶ፣ የኢትዮጵያ
እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወሰደውን አቋም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑም እንዲደግመው ጠየቀ፡፡ ዘረኛው የደቡብ አፍሪካ የነጮች ልዑክ የኦሎምፒክ
ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፍ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ የጃፓኑን ኦሎምፒክ አልሳተፍም እንድትል ጠየቀ፡፡ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ዋና ፕ/ት አቶ
ይድነቃቸውም “ጉዳዬ ፓለቲካዊ ስለሆነ፣ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ገና ተነጋግሬበት ነው፤” ስላሉት ተበሳጭቶ ንጉሡን እንደዘለፈ ፓልራምፓን
Bare Foot Runner ባለው የአበበ ቢቂላ ዘካሪ መጽሐፍ ላይ አስፍሮታል፡፡ (ገጽ 165-6)፡፡ የሰውዬው ጥያቄ፣ በኢትዮጵያ
ባለሥልጣነት ዘንድ ተገቢውን ክብር አግኝቶ ኖሮ፣ ከስድስት ዓመታት በኋላ በሜሰኮው ኦሎምፒክ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካን ተሳትፎ በማውገዟና ሌሎች
የአፍሪካ አገሮችንም በማስተባበሯ፣ ዘረኛው የደቡብ አፍሪካ የኦሎምፒክ ቡድን እንዳይሳተፍ ማዕቀብ ተጣለበት፡፡
ለሦስት ወራት ያህል ያለማሰለስ ስለ ANC
/African National Congress) እና ስለ ደቡብ አፍሪካ የነጮች ዘረኛ መንግሥት ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲያዊ ሥራ ሲሰራ
ከቆየ በኋላ፣ በሚያዝያ 5/1954 ዓ.ም የፈጥኖ ደራሽ ዋና አዛዡ ብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩ መረቁት፡፡ አንድ ቡልጋሪያ ሠራሽ
የሆነ ሽጉጥ ከ200 ጥይቶች ጋር ሰጡት፤ ከዚያም ወደሀገሩ ለመመለስ ተዘጋጀ፡፡ እንደሄደ
እንደሚታሰር የጠረጠሩት የኢትዮጵያ ባለስልጣናትም ለሰውዬው የኢትዮጵያዊ ፓስፖርት ሰጡት፡፡ ስሙም “ዱዋል ሰዋዬ” የሚል ሆነ፡፡
ትውልዱ በችዋን ላንድ ሲሆን፣ የትውልድ ዘመኑም 1910 ዓ.ም (እ.አ.አ 18/7/1918) ነው፡፡ ሥራውም ጋዜጠኛ የሚል ሆነ፡፡
የሚስቱ ፎቶ አልተለጠፈበትም፡፡ Long Walk to Freedom ባለው መጽሐፍ በ47ኛ ምዕራፍ ላይ እንደሰፈረው ከሆነ፣
ያረፈውም ራስ ሆቴል ነበር፡፡ ረፍት የለሽና ተናግሮ የመደመጥ ፀጋ ያለው ይህ ሰውዬ፣ በሚያዝያ አጋማሽ ላይ ወደሀገሩ እንደተመለሰ ሰሞን ሊሌስሊፍ በተባለ ቦታ ሽጉጡንና 200ዎቹን
ጥይቶች ራቅ አድርጎ ቀበራቸው፡፡ እነዚህ የኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ማሰልጠኛ ተቋም ሥጦታዎች እስከዛሬም ድረስ ደብዛቸው አልተገኘም፡፡
(በቅርቡ “Mandela’s Gun” በሚል ርእስ አንድ ጆን ኢርቪን የተባለ እንግሊዛዊ የፊልም ዳይሬክት ለፊልሙ ጥናት አዲስ አበባ
መጥቶ ነበር፡፡)
ማጠቃለያ፤
ከ28 ዓመት ከ2 ወራት ገደማ በኋላ፣ በሐምሌ 3/1982
ዓ.ም፣ የ27 ዓመታት እስሩን ጨርሶ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመገኘት ወደአዲስ አበባ መጣ፡፡ አዲስ አበባ
የተለየች ሆነችበት፤ ለወራት አይደለም ለቀናትም እንደማይቆይባት ሳይታወቀው አልቀረም፡፡ ቦሌ አለማቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ ድረስ
ሄደው፣ ፕ/ቱ ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ
ጓድ ብርሃኑ ባይህ ነበሩ፡፡ በ26ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤም ላይ ተገኝቶ ንግግር አደረገ፡፡ “አፓርታይድ ከምድረ-ደቡብ አፍሪካ
ብቻ ሳይሆን፣ ከመላው ዓለም እስኪወገድ ድረስ፣ ማዕቀቡ ተጠናክሮ እዲቀጥል አሳሰበ፤” (አዲስ ዘመን፣ ሐምሌ 3/1982፣ ገጽ-7)፡፡
ሰውዬው፣ በ1982 ዓ.ም በመጣ ጊዜ አዲስ አበባ የቆየው ለ24 ሰዓታት ብቻ ነበር፡፡ ለምን ከዚያ በላይ ለቆየት እንዳልፈቀደ መጠርጠር
ካልሆነ በስተቀር፣ ትክክለኛውን ምክንያት ማወቅ ያስቸግራል፡፡ በ43 ዓመቱ ለ98 ቀናት ያህል የተንፈላሰሰባት አዲስ አበባ፣ ከ28
ዓመታት በኋላ በ24ኛው ሰዓት ጥሏት ነጎደ፡፡ ከዚያን በኋላም አልመጣም፡፡ በሐምሌ 19/1995 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
የክብር ዶክትሬት ሊሠጠው ቢጋብዘው ዝር ሳይል ቀረ፡፡ እግረመንገዱንም እነፕ/ር አንድሪያስ ያሰሩትን መስታወታማ ሕንፃ ይመርቃል
ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡
በወቅቱ አንዳንድ የግል ፕሬስ ውጤቶች፣ “ማንዴላ አልመጣም ያለው፣ ከዘረኞች
እጅ ምንም አይነት ሽልማትም ሆነ ዲግሪ አልቀበልም በሎ ነው” ማለታቸውን አስታውሳለሁ (ጦቢያ፣ ልሳነ ሕዝብና አስኳል የሚጠቀሱ
ናቸው፡፡) ያም ሆነ ይህ፣ ማንዴላና ኢትዮጵያ ልብ ለልብ እንደተነፋፈቁ ይቀጥላሉ፡፡ ዛሬ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ማንዴላ የርቀት ት/ት
ኮሌጅ ተከፍቷል፡፡ ከላይ እንዳወሳሁት፣ የማንዴላ ሕንፃ በአዲስ አበባ ዩቢቨርሲቲ ዋናው ግቢ ውስጥ ተሰይሟል፡፡ አርባ ምንጭ ከተማም
ውስጥ “ማንዴላ” የሚባል ት/ት ቤት ተክቷል፡፡ አይ ማንዴላ! አይ “ሚ/ር ማንጄላ!” ኢትዮጵያ ውስጥ የቆየባቸውን ቀናት መቶ ሳየደፍን
ሊሞት ይሆን እንዴ? ማን ያውቃል?! (ቸር ወሬ ያሰማን!)
*********************************************************************************
*********************************************************************************
ምንጭ:--http://semnaworeq.blogspot.com/
No comments:
Post a Comment