ከደራሲያን ዓምባ

Saturday, January 4, 2014

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በዓሉ በሰላም አደረሳችሁ


ገና

***********************
"ታኅሣሥ ገሠገሠ ከተፍ አለ ገና፣
እጠብቅሃለሁ አንተ ልጅ ቶሎ ና፡፡
የታኅሣሥ ትውውቅ በገና ፍቅር፣
ይላል ቅር ቅር፡፡"
ዓመት ጠብቀው፤ ዐውደ ዓመትን ዙረው ከሚመጡት በዓላት አንዱ የገና (ልደት) በዓል ነው፡፡ በያመቱ ታኅሣሥ 29 ቀን ይከበራል፡፡ ሃይማኖታዊ ይዘቱ የክርስቶስ ኢየሱስ 2006ኛ የልደት በዓሉ የሚዘከርበት ነው፡፡
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 ቀን 2006 ዓ.ም. የገና በዓል በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ግብፅ እና በመካከለኛው ምሥራቅና በምሥራቅ አውሮፓ ያሉት ሀገሮች ይከበራል ፡፡

የጁሊያን ቀመር የሚከተሉት ምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን ገናን ሲያከብሩ ዕለቱን ..ዲሴምበር 25.. ብለው ሲሆን፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ታኅሣሥ 29፣ ግብፅ (ኮፕቲክ) ደግሞ ኮያክ 29 ብለው ያከብሩታል፡፡

በ16ኛው ምእት ዓመት ከጁሊያንን ቀመር ተከልሶ የተዘጋጀውን የጎርጎሪያን ቀመር የተከተሉት ምዕራባውያን ደግሞ በነርሱ "ዲሴምበር 25" ባሉት ታኅሣሥ 16 ቀን አክብረውታል፡፡ በዓሉ አንድ ሆኖ የቀኑ ልዩነት የተፈጠረው መሬት ፀሐይን ለመዞር የሚፈጅባት ጊዜ በምሥራቆች 365 ቀን ከ6 ሰዓት ነው በማለታቸው ምዕራቦች ደግሞ 365 ቀን ከ5 ሰዓት 48 ደቂቃ 46 ሰኮንድ ነው በሚል ልዩነት በመፈጠሩ ነው፡፡

"ዮም ተወልደ ቤዛ ኵሉ ዓለም" (ዛሬ የዓለም ቤዛ ተወለደ) እያሉ ኢትዮጵያውያኑ በደማቅ ሥነ ሥርዓት በዓሉን እያከበሩ ነው፡፡ የዛሬውን በዓለ ልደት ለማክበር በመንፈቀ ኅዳር የጀመሩትን ጾም ለ43 ቀኖች አሳልፈዋል፡፡
"ያለም ሁሉ መድኃኒት
ተወለደ በበረት፣
እያሞቁት እንስሳት
ብርሃን ሆነ በዚያች ሌት
ሲዋዥቡ መላእክት
ደስ አሰኙ ለኖሩት" የሚለው ኅብረ ዝማሬ የበዓሉ መገለጫ ሲሆን፤ ቀደም ባለው ዘመንም ተማሪዎች በገና በዓል ፍቅረ ሀገርንም የሚገልጹበት አጋጣሚ ነበር፡፡
"እናታችን ኢትዮጵያ፣
መልካም ቆንጆ ባለሙያ
አቁማለች የውቀት ገበያ፣
ለመንግሥቷ መከላከያ
ሕያው ትሁን ኢትዮጵያ"

በሀገር ውስጥና በውጭ (ድዮስጶራ) በሚገኙ በሁሉም የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት፣ ሌሊቱ ማሕሌት ተቁሞ ቅዳሴ እንዳበቃ፣ የበዓል ፍጻሜ ቢሆንም በተለይ በላሊበላ ግን በተጨማሪ በዕለቱ ጧት ላይ "ቤዛ ኵሉ" የተሰኘው ክብረ በዓል ከአለት ከተፈለፈሉት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በአንዱ በቤተ ማርያም ካህናቱ ጋራና መሬት ላይ ሆነው ያከብሩታል፡፡

የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችና ምዕመናን (ነጋድያን-ፒልግሪምስ) ትኩረት የሚስብ ዐቢይ ትርዒት ነው፡፡ የላሊበላው "ቤዛ ኵሉ" አከባበር ትእምርታዊ ነው፡፡ ማሜ ጋር ላይ ያሉት የመላእክት ምሳሌ፣ መሬት ላይ ያሉት ደግሞ የእረኞች ምሳሌ ሆነው ዝማሬውን በሆታና በዕልልታ ያጅቡታል፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስን መወለድ መጀመሪያ ያወቁ እረኞች በመሆናቸው በአገር ቤት ትውፊቱ እየተነገራቸው የሚያድጉት እረኞች በተለየ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡

የበዓለ ልደቱ ማሕሌቱ በካህናት በሚቀጥልበት ሌሊት ሊቃውንቱ ልደቱን አስመልክተው በየአጥቢያው በቅኔ ማሕሌት ዙርያ ቅኔውን ይዘርፉታል፡፡ አንዱ፣ ከሰባት አሠርት ዓመት በፊት ታላቁ ሊቅ አለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ እንዲህ ተቀኝተው ነበር፡፡

"ፍጡራን ላዕለ ፈጣሪ
ኅሊናሆሙ ይግድፉ በሕገ ልቡና ተጽሕፈ
ይእዜሰ እምግብረ ልማዱ ፈጣሪ አዕረፈ
እስመ እንዘ በጎል ይሬኢ ንዴተ ወልዱ ትሩፈ
መንበረ መንግሥት ኢይኅሥሥ ወዘወርቅ አጽፈ
ኅሊናሁ በድንግል ገደፈ፡፡"
(
ፍጡራን ሁሉ፣ ሐሳባቸውን በፈጣሪያቸው
ይጥሉ ዘንድ በሕገ ልቡና ተነግሯል፡፡
ዛሬ ከልማዱ ሥራ ፈጣሪ አረፈ፡፡
የተረፈ የልጁን ድህነት መዋረድ በጎል ሲያይ
የመንግሥት ዙፋን እንዳይሻ የወርቅ ልብስ እንዳይሻ
አሳቡን ከድንግል (ማርያም) ላይ ጣለ፡፡)
ልደት በኢትዮጵያ ዐውድ ከገና ጨዋታ ጋር ተያይዞ በባህላዊ ጨዋታዎች ይከበራል፡፡ የተለያዩ መንፈሳዊና ባህላዊ አከባበር ከሚከበርባቸው ስፍራዎች አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ጃንሜዳ ተብሎ የሚታወቀው ገናን ነው፡፡
በዓሉ በሁለት ቡድኖች መካከል ሚና ለይተው በሚጫወቱበት ጊዜ ተጫዋቾቹም ሆኑ ታዳጊዎች በሆታና በዕልልታ ከሚያዜሟቸው መካከል በዚህ ጽሑፍ መግቢያው ላይ የተጻፈው አንጓ ይጠቀሳል፡፡

የጃንሜዳ ባህላዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎች ዙሪያ ጥናት ያደረጉት አቶ አባይነህ ደስታ፣ ጃንሜዳ በከፍተኛ ደረጃ ሕዝብ ተሰብስቦ ከሚያከብራቸው የክርስቲያኖች በዓል ገና እና ጥምቀት ዋነኛ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
የገናን ሀገር ባህላዊ ጨዋታን ስንመለከት አስቀድሞ የቡድን አባላት የሚሆኑ ሁለት ሰዎች ይመረጣሉ፡፡ ሁለት ሁለት ተጫዋቾች ወደ አባቶች ይቀርቡና በምርጫው ወደ ቡድን ውስጥ ይገባሉ፡፡ የሚያስፈልገው የተጫዋች ቁጥር ሲሞላ ወገን ወገናቸውን ይዘው በዱላ ቀልጣፋ የሆኑ ተጫዋቾች ጥንጓን ወደፊት እንድትቀጥል ይመቷታል ወይም ይመልሷታል፡፡ ተጫዋቾች ብዙ ጊዜ በጨዋታው ስለሚሰጡ ጥንጓን ከእግር መካከል በገባች ጊዜ ከሰው እግር ጋር ደርበው ስለሚመቱ የእግር መሰበር በዚህም ሳቢያ ወገን ለይተው እስከመፈናከት ይደርሳሉ፡፡ የመኳንንቱም አሽከሮች፣ የንጉሡና የንግሥቲቷ አሽከሮች የጌቶቻቸውን ስም በጉብዝና የሚያስጠሩት በባህላዊው የገና ጨዋታ ነው፡፡  
ጨዋታው በመንደር ልዩነት ከሆነ የታች አምባ ቡድን ሀምሳ ተጫዋቾች ቢሆኑ የላይ አምባ ቡድን ሰባ ሆነው ቢጫወቱ የሚከለክል ደንብ አልነበረም፡፡ ጨዋታው በመጨረሻ ፀብ ስለሚያነሳ ብዙ ጊዜ ጉዳት ያጋጥማል፡፡ ጥንጓም ኃይለኛ ለጊ በመታት ጊዜ ዐይን እስከ ማጥፋት ትደርሳለች፡፡ ተጫዋቾች "በሚና" ብለው በሚጫወቱበት በቆልማማ ዱላ ቢደባደቡም የሚገላግል ዳኛ አልነበረም፤ ጨዋታውን በሚመለከቱ አባቶችም በድብድብ ከመሳቅ በስተቀር ሽምግልናቸው ለገና ጨዋታ አልተለመደም፡፡ "እግር ይብሳል፣ ያንከላውሳል፡፡" እያለ ማስፈራራት፣ ራስን መቀወር ወይም እንቆራቆስ ብሎ እጅና እግርን በዱላው መምታት በገና ጨዋታ የተለመደ ነበር፡፡

የገና ጨዋታ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮች የታወቀውና በኦሊምፒክ የስፖርት በዓል ከሚደረጉ ውድድሮች አንዱ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህም ጨዋታ ሆኪ በሚል ስም ይጠራል፡፡ ፈረንጆች የፊት አደጋን መከላከያ ዘዴ ይጠቀማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያገር ባህል ገና ጨዋታ በሚደርስ አደጋ ማንም ተጫዋች አይጠይቅም፡፡
በገና ጨዋታ አሸናፊ ለሆኑት ቡድኖች ፊሪዳና ጠጅ ተሰጥቷቸው እየበሉና እየጠጡ፣ እየዘፈኑ ሲሸልሉና ሲያቅራሩ ሜዳውን የጦርነት ድል ያገኙበት ያስመስሉት ነበር፡፡ ከሚዘፍኑትና ግጥሞች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

"
ማታ ነው ድሌ፣
ይሄ ነው አመሌ፡፡
አሲና በል አሲና ገናዬ፡፡
ኦ! ጉ! አሲና በል አሲና ገናዬ፡፡
ግፋው ግፋው አለኝ እኔ እንደምን ልግፋው፣
የአንድ በሬ ጨጓራ እንደ ቅል የነፋው፡፡
የብብቱ ሽታ፣ የመንፈቅ በሽታ፡፡
የጀርባው መርሬ፣ ያውላል ጥድ በሬ፡፡
ካስር ጋን አተላ፣
አይተርፈው በአንኮላ፡፡
እግርህ የሸረሪት ሆድህ የእንቁራሪት፣
ቀን እንደጠላሁ ና እንዳትመጣ ሌሊት፡፡"
ስድብ ለተራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በመኳንንቱና በነገሥታቱም ላይ ሊሰነዘር ይችላል፡፡ በሚደርስባቸው ስድብ ግን ምንም ዓይነት ቁጣና ቅጣት አያደርጉም፡፡

"
በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ
በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፡፡" የሚለው የዘፈን ግጥም ይህን ባህል ይገልፃል፡፡
የገና ጨዋታ ከክርስትና ሃይማኖት በፊት ይዘወተር እንደነበርና በኢትዮጵያ ከታኅሣሥ የመኸር ወቅት ጋር የተያያዘ ባህል እንደሆነ አቶ አባይነህ ያመለክታሉ፡፡ ከበዓሉ ጋር የተያያዘ ብዙ የስነቃል ግጥሞችን ይገኛሉ፡፡

"ታኅሣሥ ገሠገሠ ከተፍ አለ ገና፣
እጠብቅሀለሁ አንተ ልጅ ቶሎ ና፡፡
ይወዘውዘኛል አልጠላኝም ገና፣
ፍቅር ሞገደኛው እየነሳኝ ጤና፡፡
ምግብ አያስበላ አያስለብስ ልብስ፣
ሞገደኛው ፍቅሩ ይዞኝ በታኅሣሥ፡፡
በማለዳ ጀንበር በገና ጨረቃ፣
እኔን እኔን ብላ መጣች ተደብቃ፡፡" ሠናይ በዓል፡፡
**********************************
በሔኖክ ያሬድ
ምንጭ:-http://modersmal.skolverket.se/amhariska/

1 comment:

  1. ሚስተር ቤንጃሚን የኢሜል ዝርዝሮችን እነሆ ፣ Lfdsloans@outlook.com ፡፡ / ወይም ደግሞ ንግዴን ለመጀመር በ 90,000.00 ዩሮ ብድር የረዳኝ WhatsApp + 1-989-394-3740 እና እኔ በጣም አመስጋኝ ነኝ ፣ እዚህ አንድ ነጠላ እናት ነገሮች እንዳላደረጉ መንገድ ለመፍጠር እየሞከርኩ ነው ፡፡ ከእኔ ጋር ቀላል ይሁኑ ግን ንግዴ እየጠነከረ ሲመጣ እና እያሰፋ ሲሄድ እያየሁ በሚስተር ሚስተር እርዳታ ፊቴ ላይ ፈገግታ አሳየኝ ፡፡ የገንዘብ ድጋፍን መፈለግ ወይም በዚያ ንግድ ውስጥ መከራን ማለፍ ወይም የመነሻ የንግድ ሥራ ፕሮጀክት መጀመር መፈለግ ይህንን ማየት እና ከችግራቸው ለመውጣት ተስፋ ሊኖረው ይችላል ... እናመሰግናለን ፡፡

    ReplyDelete