በየዓመቱ በፈረንጆች ሚያዚያ 1 ቀን የሚውል የአውሮፖውያን የቀልድ ልማድ ቀን ነው በዚህ ዕለት አውሮፖውያን ወዳጅ ዘመድ ጓደኛን በማሞኘት ነው የሚያሳልፉት፡፡ ለመሆኑ የዚህን ዕለት ታሪካዊ አመጣጥ ያሉቃሉ ?
እ.ኤ.አ በ16ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ የኖርዌይ ተወላጅ የሆነው ሉፍ ሊርፖ(Loof Lirpa)የተባለ ሳይንቲስት የበራሪ ምስጢርን ለማወቅ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ አንድ ቀን ሙከራው ስለተሳከለት በወቅቱ የሀገሪቱ ንጉስ ለነበረው ለንጉስ ሄነሪ 8ኛ ደብዳቤ ያፅፍለታል፡፡ የደብዳቤው ፍሬ ሃሳብ የበራሪ ምስጢርን ተመራምሮ ማግኘቱንና አውሮኘላን ሠርቶ መጨረሡን የሚገልፅ ነበር፡፡ የሙከራው ድነቅ ውጤት ለህዝብ በትርኢት መልክ ለማሳየት ስለፈለገም በዚሁ ዕለት ንጉሱ የክብር እንግዳ በመሆን የልፋቱን ውጤት እንዲመለከትለት ይጋብዘዋል፡፡ ትርኢቱም የሚቀርብበት ዕለት እ.ኤ.አ ሚያዚያ 1 ቀን 1545 ነበር፡፡
ንጉሱ የሊርፖን ደብዳቤ ካነበበ በኃላ በሳይንቲስቱ የምርምር ችሎታ በመደሰት ታላላቅ ሹማምንቱን አስከትሎ ወደ ትርኢቱ ሥፍራ ይሄዳል፡፡ ለክብር በተዘጋጀው ሰገነት ላይ በአካባቢው ከተሠበሰበው ህዝብ ጋር ሆኖ ሳይንቲስቱን መጠባበቅ ጀመረ፡፡ ይሁን እንጅ ሊርፖ በወቅቱ ሳይመጣ ቀረ የንጉሱ ባለሟሎች ተጨነቁ ተጠበቡ፡፡ በመጨረሻም ንጉሱም ተናዶ ወደ ቤተ መንግስቱ ተመለሠ፡፡ ለጊዜው የሊርፖ ጉዳይ ምስጢር ሆኖ ቆየ፡፡
ድርጊቱ ሊርፖ ንጉሱን ለማሞኘት ሆነ ብሎ ያደረገው አልነበረም፡፡ ሙከራው ሳይሳካለት ቀርቶም አይደለም፡፡ ከጊዜ በኃላ እንደተረጋገጠው ሉፍ ሊርፖ የበራሪውን ትርኢት ሳያሳይ የቀረዉ እጅግ በማያሳዝን ሁኔታ ነበር፡፡
ሊርፖ የክቡር እንግዳውና ህዝቡ ወደ ተሠበሰበበት ቦታ አውሮኘላኑ እያበረረ ለመድረስ ገና ጉዞ እንደጀመረ ከአንድ ትልቅ ዛፍ ጋር ተላትሞ ህይወቱ ያልፋል፡፡ በዚህም የተነሳም ከሚያዚያ 1 ቀን 1545 እ.ኤ.አ ጀምሮ የደረሠውን አጋጣሚ መሠረት በማድረግ ልክ እንደ አንድ ልማድ በመውሠድ ዘመድ ወዳጅና ጓደኞቻቸውን በማሞኘት በተሞኙት ላይም በመሳቅ ቀኑን ማክበር ጀመሩ፡፡ ባሉርፖ ስምም ከአሳ ከሙዝ ከማርማላታና ከቼኮሌት ልዩ ልዩ ኬኮችን በመስራት በመመካብ ያከብሩታል፡፡ አብዛኛዎቹ ግን ቁራን የሚያከብሩት ሰዎችን በሚያስቅና በሚያዝናና ሁኔታ በማሞኘት ነው፡፡
ይህ ልማድ ከግለሠቦች የእርስ በርስ ማሞኘት ሌላ በዜና ማሠራጫዎችም አልፎ አልፎ ይደረጋል፡፡ ግን በማይጐዳ መልኩ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የቢቢሲ ቴሌቨዥን ጣቢያ በዚያን ዕለት ያቀረበው ዜና ከማሞኘትም አልፎ የሚያጃጅል ነው፡፡ ጣቢያው እንዳለው ከሜዲትራኒያን የባህር ዳርቻ የነፈሠው ነፋስ በዛፍ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱና የፖስታ ምርት ስለቀነሰ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እንዳስከተለ የሚገልፅ ዜና አስተላለፈ፡፡
ይህንን አስከፊ ዜና የሠማው ህዝቡም ከየመደብሮች የቀሩትን ፖስታ ለመግዛት ሰልፍ ያዘ፡፡ ህዝቡ በወቅቱ ፖስታ ከዱቄት እንጅ ከዛፍ እንደማይመረት ለማገናዘብ አልቻለም ነበር፡፡ ከጥቂት ሠዓታት በኃላ ጣቢያው ዕለቱ ኤንሪትል ዘፈል መሆኑን ሲገልፅ ህዝቡ በራሱ ላይ ስቋል፡፡
******************************************************************
ምንጭ:--በታከለ ኩዳን/ቁምነገር መፅሄት ቅፅ 2 ቁጥር 14 መጋቢት 1995 ዓ.ም/
No comments:
Post a Comment