ከደራሲያን ዓምባ

Friday, October 2, 2015

የሙዚቃ ጣዕም

በሰባ ደረጃ
ቴዲ አፍሮ /ቴዎድሮስ ካሳሁን

******************
ግጥምና ዜማ፡- ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)
ሙዚቃ ቅንብር፣ ሚክሲንግ፣ ኪቦርድ እና ቤዝ ጊታር፡-  ዳግማዊ ዓሊ
ናሙና ዝግጅት፡-  አብርሃም ዘዉዴ
ክራር፡-  ታመነ መኮንን
ድምጵ ቀረጳ፡-  ክብረት /ኪዮስ
ፕሮዲዩስድ፡-  በቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)
******************************
Teddy Afro's Be Seba Dereja Wins Leza Radio Show Best Single of the Year Award
http://www.diretube.com/teddy-afros-be-seba-dereja-wins-leza-radio-show-best-single-of-the-year-award_16d01931c.html
********************

አርቲስት: ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)
ርእስ: በሰባ ደረጃ [2006]
************************************
ከመኮንን ድልድይ: ከንጨት ፎቁ በላይ
ሲመሽ እንገናኝ
መጣሁ አንችን ብዬ: ሳይከብደኝ እርምጃው
በሰባ ደረጃው
በሳሪያን ኮት ላይ: ያንን ቀጭን ኩታ
ጣል አድርጌ
በመኮንን ድልድይ: ልምጣ በደረጃው
በፒያሳ አርጌ
በፍቅር ማነቂያው: ዶሮ እንዳይል በከንቱ
እሪ አንችን ወዶ
ክራሩን ስትሰሚ: ብቅ በይ ቆሚያለሁ
ከበርሽ ማዶ
ሲመሽ ወደማታ: ማታ ማታ
አቤት ያንቺ ፍቅር ሲበረታ
ሲመሽ ወደማታ: ማታ ማታ
ብቅ በይ ሲገረፍ: ክራር ሲመታ
ማታ ማታ: ማታ ማታ
ማታ ማታ: ማታ ማታ
ማታ ማታ: ማታ ማታ
ማታ ማታ: ማታ ማታ
ማታ ማታ
አምጧት ከጎኔ: ትቀመጥ
እንጀራ አይቀርብም: ካለወጥ
አቅፎ ገላዋን: አልጠግብ ያለው
ማነው ካላችሁ: ማነው ማነው
ልቤ ልቤ ነው: ልቤ እረሃብተኛው
እሷን ወዶ: ሌት እማይተኛው
ይውጣ ይውጣ: እግሬ ይዛል በርምጃው
ከሷ አይብስም: ሰባ ደረጃው
ዎይ… ዘበናይ: ነይ ዘበናይ
ዘበናይ ዘበናይ
ሲመሽ ወደማታ
ሁሉ ዘግቶ በሩን
ታም ታራም ሳረገው
ብቅ በይ ክራሩን
ታም-ታራራም ታራራም ታራራም
ሳረገው ክራሩን
ታም-ታራራም ታራራም ታራራም
ፀጉሯን ተተኩሳው: እንዳርምዴ ሜሪ
ዘበናይ ናት ፍቅሯን: በክራር ነጋሪ
ታም-ታራራም ታራራም ታራራም
በክራር ነጋሪ
ታም-ታራራም ታራራም ታራራም
ሄዶ ከኮሪያ: ዘማች ሲመለስ
ዘማች ሲመለስ
ያወሳል ናፍቆቱን: ብክራሩ ድምፅ
ብክራሩ ድምፅ
ፍቅርሽ አስጨንቆ: መላዎስ አቃተኝ
መላዎስ አቃተኝ
ተደናበርኩልሽ: ጥይት እንደሳተኝ
ጥይት እንደሳተኝ
ሳተና ነበርኩኝ: ተኳሽ በመውዘሬ
ተኳሽ በመውዘሬ
ለዘበናይ ብቻ: እጄን ሰጠሁ ዛሬ
እጄን ሰጠሁ ዛሬ
ዎይ…ዘበናይ: ነይ ዘበናይ
ዘበናይ ዘበናይ
በሳሪያን ኮት ላይ: ያንን ቀጭን ኩታ
ጣል አድርጌ
በመኮንን ድልድይ: ልምጣ በደረጃው
በፒያሳ አርጌ
እንዳውራ ዶሮ ክንፍ: ኮቴን እየሳብኩት
መሬት ለመሬት
በዞርኩት ገላሽን: ሳትወጣብኝ ፀሐይ
ሳይነጋብኝ ሌት
ሲመሽ ወደማታ: ማታ ማታ
አቤት ያንቺ ፍቅር ሲበረታ
ሲመሽ ወደማታ: ማታ ማታ
ብቅ በይ ሲገረፍ: ክራር ሲመታ
ማታ ማታ: ማታ ማታ
ማታ ማታ: ማታ ማታ
ማታ ማታ: ማታ ማታ
ማታ ማታ: ማታ ማታ
ማታ ማታ
ሞልቶ ባራዳ: ያርመን ዳቦ
ሳሳ አከላቴ: ሰው ተርቦ
አቅፎ ገላዋን: አልጠግብ ያለው
ማነው ካላችሁ: ማነው ማነው
ልቤ ልቤ ነው: ልቤ እረሃብተኛው
እሷን ወዶ: ሌት እማይተኛው
ይውጣ ይውጣ: እግሬ ይዛል በርምጃው
ከሷ አይብስም: ሰባ ደረጃው
ዎይ… ዘበናይ: ነይ ዘበናይ
ዘበናይ ዘበናይ
አይወጣም ደረጃ: ቢፈጥር ሴሸኝቶ
እንደኔ ካልሄደ: በፍቅር ተገፍቶ
ታም-ታራራም ታራራም ታራራም
በፍቅር ተገፍቶ
ታም-ታራራም ታራራም ታራራም
መድፈሪያሽ ወርቅ ነው
ብርም አይገዛሽ
ልብ የሌለው ሀብል: ግድም አይሰጥሽ
ኬረዳሽ
ታም-ታራራም ታራራም ታራራም
ግድም አይሰጥሽ
ታም-ታራራም ታራራም ታራራም
ካንገትሽ ላይ አርጊኝ
እንደማር ተሬዛ
እንደማር ተሬዛ
ወዲህ ወዲያ እንዳልል
አደብ እንድገዛ
አደብ እንድገዛ
ተከለከለ አሉ: የንጉሥ አዳራሽ
የንጉሥ አዳራሽ
የክት ያለበሰ: አይገባም በጭራሽ
አይገባም በጭራሽ
መጣሁ ከኮሪያ: ይዤልሽ ሰዓት
ይዤልሽ ሰዓት
በፓሪ ሞድሽ ላይ: አምረሽ ታይበት
አምረሽ ታይበት
ዎይ… ዘበናይ: ነይ ዘበናይ
ዘበናይ ዘበናይ
ዘናይ እናናዬ: ተይ አሁን ነይ
አሁን ነይ
ዘናይ እናናዬ: ተይ አሁን ነይ
አሁን ነይ አሁን ነይ
ዘናይ እናናዬ: ተይ አሁን ነይ
አሁን ነይ አሁን ነይ
ዘናይ እናናዬ: ተይ አሁን ነይ
አሁን ነይ አሁን ነይ
************************
ግጥምና ዜማ፡ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)
ሙዚቃ ቅንብር፣ ሚክሲንግ፣ ኪቦርድ እና ቤዝ ጊታር፡ ዳግማዊ ዓሊ
ናሙና ዝግጅት፡ አብርሃም ዘዉዴ
ክራር፡ ታመነ መኮንን
ድምጵ ቀረጳ፡ ክብረት ዘ/ኪዮስ
ፕሮዲዩስድ፡ በቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)
*****************************

‹‹ከመኮነን ድልድይ …ከንጨት ፎቁ በላይ … ሲመሽ እገናኝ ››
(አሌክስ አብርሃም)
****************************************
አንድ ቁመቱ መለል ያለ ወጣት በሳርያን ኮት ላይ ባለቀጭን ጥለት ኩታውን ጣል አድርጎ በሰባ ደረጃ ዱብ ዱብ እያለ ሽቅብ … ቆንጅትን ፍለጋ … ስንጠረጥር በግራ እጁ ክራር ይዟል ….ሰባዋን ደረጃ እንደጨረሰ ተረረም ሊያደርጋት ….እናም የክራሩን ተረረም ቅኔ እንደመጥሪያ ደውል በተጠንቀቅ የምትጠብቅ አንዲት ቆንጁ…ዘበናይ የቤት ልጅ አለች …እዛው አካባቢ …እንግዲህ አስቡት ሲመሽ ወደማታ ሁሉም ዘግቶ በሩን …አንድ ሰው ውጭ ላይ ክራሩን ተረረም ሲያደርገው …አንድ ተረረም ለአድማጮቹ የተለያየ ትርጉም ይሰጣል ….የተኙትና የክራሩ ተረረም ያልገባቸው ‹‹የማነው አዝማሪ በዚህ ምሽት ክራር …›› ይላሉ ….በፍቅር ለምትጠብቀው ኮረዳ ግን (ያውም እንደሜሪ አርሚዴ ፀጉሯን ተተኩሳ) በዚች ምድር ላይ ካሉ ድምፆች ሁሉ ምርጥ የፍቅር ጥሪ ደውል ነው …. አንድን ጉዳይ በተፈጥሮዋዊ እውነቱ ለመስማት ከስጋዊ ጆሮ በላይ ከፍ ያለ የፍቅር ጆሮ ያሻል !
እና ሲመሽ ወደማታ ክራሩ ተረረም ሲል አንዳንዶች ‹‹አዝማሪ ›› እያሉ ሲያሽጓጥጡ አንዳንዶቹም እንቅልፋቸውን ሲለጥጡ …እኛ ግን የፍቅር ቅኔዋ ስለምትገባን ጉዳይ አለንና ሰባውን የፍቅር ደረጃ ወጥተን … ያው ባለቅኔው እንዳለው
አይወጣም ደረጃ ቢፈጥን ሴሸንቶ 
እንደኔ ካልሄደ በፍቅር ተገፍቶ ….
የመኮነን ድልይን የፍቅር ድልድይ እድርገን ‹‹በፍቅር ተገፍተን›› ወደፍቅር ከተሻገርን በኋላ ….ከእንጨት ፎቁ በላይ ተም ተረረም ! በነገራችን ላይ ይሄ ዘፈኑ ውስጥ የምትሰሙት አፍቃሪ ገፀ ባህሪ ተራ ሰው እንዳይመስላችሁ …ሰባ ደረጃን ከመውጣቱ በፊት …ተረረም ከማድረጉም በፊት …ልጅቱ ክራሩን ሰምታ ከመውጣቷ በፊት ሳሪያን ኮቱን ለብሶ ለቆንጅትም የእጅ ሰዓት ስጦታ ይዞ ከመከሰቱ በፊት …ኮሪያ ነበር!! ምን ሊሰራ ኮሪያ ሄደ ማለት ተገቢ ነው …የቴዲ አፍሮ ዘፈኖች ውስጥ የሚከሰቱ የፍቅር ገፀ ባህሪያት ተራ አፍቃሪዎች አይደሉም ….ወደፊት እመለስበታለሁ ወንዱም ሴቱም በቴዲ ዘፈኖች ውስጥ ያሉ ገፀ ባህሪያት የአገርና የወገን አደራን ጥንቅቅ አድርገው የሚወጡ አገር ወዳድ መሆናቸውን ታያላችሁ …..
እና ይሄንኛውም አፍቃሪ ኮሪያ ከፍ ባለ የአገር ሃላፊነት ላይ ከርሞ አረፍ እንኳን ሳይል መሳሪያውን አስቀምጦ ክራሩን ያነሳ ትንታግ ወጣት ነው …. ቆይማ ይሄ ምርጥ አፍቃሪ፣ ይሄ የሳሪያን ኮት ለባሽ ለምን ኮሪያ እንደሄደ ላስታውሳችሁ ….ከዛ በፊት ግን ጥያቄ... ከእናተ መካከል የሳሪያን ኮት የማያውቅ ካለ እጁን ያውጣ …እሽ ሳሪያን ኮት ማለት ከታች ፎቶውን የለጠፍኩላችሁ ነው …ከዛ በዚህ ኮት ላይ ባለቀጭን ጥለት ኩታ ጣል አድርጎበት ማለት ነው ….ኩታ ምንድነው የሚል የለም መቸም (አሁንስ አበዛችሁት ) እሽ ኩታ የማያውቅ ሰው ካለ ቢፈልግ ከቤቱ ወጥቶ እናቶችን ይመልከት ዘመናዊ እናቶች ያሉበት ሰፈር ያለ ሰው ሽሮ ሜዳ ይሂድና ኩታ አይቶ ይመለስ !!
እንግዲህ ከ1945 ዓ/ም ማለትም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ ቀደም ብሎ .... አሁን የምናውቃቸው ዓለም ላይ አንዴ ኒውክሌር አንዴ ምናምን እያሉ ‹‹የሚያነጅቡት›› ሁለቱ ኮሪያዎች (ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ) …በጃፓን ቅኝ ግዛት ስር ነበሩ…ጃባን እንአብረት ቀጥቅጣ ገዝታቸዋለች ! ታዲያ ይህ ቅኝ ግዛት ይበቃል ያሉ ወገኖች አገራቱን ከጃፓን ቅኝ ግዛት ነፃ ለማድረግ ጦር አዘመቱ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት እና ቻይና ከሰሜን ኮሪያ ጎን ፤ አሜሪካ እንግሊዝና ፈረንሣይ ደግሞ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ተሰልፈው ቅኝ ገዢዋን ጃፓን ከኮሪያ ምድር ለማባረር ዘመቱ …ዘመቻው ሰምሮላቸው በሰሜኑ በኩል የተሰለፈው ኃይል ቅኝ ገዥዋን ጃፓንን ወደ ደቡብ ….በደቡብ በኩል የተሰለፈው ኃይል ደግሞ ወደ ሰሜን አቅጣጫ እያባረረ ሄደው ሁለቱን ኮሪያዎች በሚያለያየው 38ኛው በሚባለው መስመር ላይ ደረሱ ….አሁን ጃፓን የለችም …ነፃ እናውጣ ብለው የዘመቱት አገራት ተፋጠጡ ይታያችሁ በሰው አገር !
ይህ ከሆነ በኋላ በደቡብና በሰሜን የተሰለፉት አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡና ሁለቱ ኮሪያዎች በሚፈልጉት መልክ ይተዳደሩ የሚል ስምምነት ላይ ተደረሰ …የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ነበር ውሳኔውን ያሳለፈው … በደቡብ የተሰለፈው የውጭ ኃይል ማለትም እንግሊዝ ፈረንሳይና አሜሪካ በስምምነቱ መሠረት ለቀው ወጡ ….በሰሜን የተሰለፉት ቻይናና ሶቬት ግን ሲቆዩ ደንበሩ የራሳቸው መሰላቸው መሰል ለቀን አንወጣም ብለው ሙጭጭ !! እንደውም ጭራሽ መስመሩን አልፈው ደቡቦቹ የለቀቅትን አንዳንድ ቦታዎች በጉልበት ያዙ 
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተበሳጨ ‹‹እንዴ የሰው አገር ልቀቁ እንን ‹ሸም› ነው …አላቸው …እናጅሬ በስሚያችን ጥጥ ነው !! የሰሜኑ ኃይል ወርሮ ከያዘው የደቡብ ክልል ወጥቶ ቀድሞ ወደነበረበት ቦታ እንዲመለስ ውሳኔ አስተላለፈ ….ይሁንና እነዛንኞቹ ብንሞት ወደነበርንበት አንመለስም ማነው ወንዱ የሚያስለቅቀን አሉ!! ስለዚህ የሰሜኑ ሃይል ደቡቡን የያዙትን በሃይል እንዲያስለቅቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወሰነ!
ታዲያ እነዚህን የሰው መሬት ይዘው አንለቅም ያሉ ጥጋበኞች ለማስተንፈስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን አላማ የሚደግፉ አገራት ወታደር እንዲልኩ ሲጠየቁ በወቅቱ ከአፍሪካ ብቸኛ የሆነው እና ጀግናው የቃኘው ሻለቃ ሠራዊትን ከ1943 ዓ.ም. እስከ 1945 ዓ.ም. ድረስ በተባበሩት መንግስታት እዝ ስር ሁኖ ወደኮሪያ ዘመተ ...መዝመት ብቻ አይደለም ኢትዮጲያው ቃኘው ሻለቃ ጦር ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሌሎች አገራት ዘማቾች ጋር በመሆን እነዛን ጥጋበኞች ጠራርጎ እያንከሳከሰ ከምድረ ኮሪያ አስወጣቸው !!

ያኔ ኢትዮጲያችን ያዘመተችው ጦር 6037 (ስድስት ሽ ሰላሳ ሰባት) ወታደሮች እንደነበር ነው አንዳንድ የታሪክ መዛግብት የሚነግሩን …ከእነዚህ ውስጥ 120 ወታደሮቻችን ሲሰው 530 ወታደሮች ቆስለዋል …ታዲያ ያኔ አለምን ያስደመመው የኢትዮጲያዊያን ጀግንነት ምን መሰላችሁ ኢትዮጲያዊ ወታደሮች ቢሞቱ እጃቸውን አይሰጡም ….እንኳን በህይዎት ቀርቶ የቆሰሉና የተሰው ጓደኞቻቸውንም አሳልፈው አይሰጡም ነበር ኢትዮጲያዊያኑ ወታደሮች ! ጦርነቱ ተጠናቆ የእስረኛ ልውውጥ ሲደረግም የታየው ይሄ ነው ኢትዮጲያ የተማረከ አንደም ወታደር አልነበራትም !!አንድም !! ልውውጡ እንዴት መሰላችሁ ….በዚህ በኩል የየአገራቱ ባንዲራ ይተከልና የተማረከው ወታደር ሲለቀቅ ባንዲራው አጠገብ ይቆማል …ታዲያ ሁሉም ባንዲራወች ስር በመቶና በሽ የሚቆጠር እስረኛ እንደንብ ሲሰፈር የኢትዮጲያ ባንዲራ ብቻዋን በክብር ስትውለበለብ ነበር ..!! በቃ ኢትዮጲያዊ እጁን አይሰጥማ !!

እንግዲህ የዛሬዋ ደቡብ ኮሪያ እንዲህ ወታደሮቻችን ከቀን ጅቦቹ ወራሪዎች ታደጓት አገር ናት …በደም የተሳሰርን ህዝቦችም ሁነናል !! ወደቴዲ አፍሮ ስንመለስ እንግዲህ ይሄ ሰባ ደረጃ ላይ ክራሩን ተረረም ሲያደርግ ያየነው ወታደር ከእዛ አለም አቀፍ እሳት እጁን ጠላት ሳይነካው ሃሎቹን አፈር ከድቤ አስበልቱ የተመለሰ ትንታግ ከአገሩ አልፎ የሰው አገር ድንበር አስጠብቆ የተመለሰ ጀግና ነው …ስንቱን አገር አዳርሰው የመጡ ወላፈን እግሮች ሰባ ደረጃን ያውም በፍቅር መውጣት ምናቸው ነው ….ይሄ ሰው ድል ካደረገም በኋላ ጀብዱውን እያወራ መሳሪያ ተሸክሞ የሚጃጃል በጠብመንጃው የሚመካ ሰው አልነበረም ….በቦታው ጠላትን አገላብጦ ሲመለስ መውዚሩን አስቀምጦ ስለፍቅር ክራሩን ይዞ ተረረም ! ይታያችሁ የኢትዮጲያ ወታደር ለጠላቱ ቢሞት እጅ አይሰጥም ብያችኋለሁ …ለፍቅር ግን ….እንዲህ አለ ቴዲ …
ሳተና ነበርኩኝ ተኳሽ በመውዚሬ 
ለዘበናይ ብቻ እጀን ሰጠሁ ዛሬ !!
ስለፍቅር እጅ መስጠት ለፍቅር ሰዎች ብቻ የተሰጠ ፀጋ ነው !በፍቅር ጦርነት የፍቅር ባንዲራችን ስር ተማርኮ መቆምም ውርደት አይደለምና …ገጭ ያውም ከወታደራዊ ሰላምታ ጋር፡) ጃ ….ወደፊት ብያለሁ !! የመውዚርም ፎቶ ያውላችሁ ከታች ….የኮሪያም ዘማቾች ለፍቅረኞቻቸው ያመጡላቸው ከነበሩት ሰዓቶች የአንዷ ፎቶ ይቻትላችሁ !
መጣሁ ከኮሪያ ይዠልሽ ሰዓት 
በፓሪሞድሽ ላይ አምረሽ ታይበት …..አይደል ያለው …ሃሃ እንግዲህ የቴዲን ‹‹ ሰባ ደረጃ ›› ባለፍ ገደም እንዲህ አየሁት !
*****************************************************************************

ቴዲ አፍሮ በሰባ ደረጃ ነጠላ ዜማ ማህበራዊ ድረገጾችን ተቆጣጠረ
*****************************************
ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “በሰባ ደረጃ” በሚል ስም ሰሞኑን የለቀቀው ነጠላ ዜማ በተለይ እንደፌስ ቡክ ባሉ ማህበራዊ ድረገጾች ላይ ከፍተኛ አድናቆትን በማግኘት ላይ እንደሚገኝ የሚሰጡ አስተያየቶች አመለከቱ።
     ቴዲ ነጠላ ዜማውን በዩቲዮብ ለተለቀቀ በኋላ የተለያዩ የኢትዮጵያዊን ድረገጾች የተቀባበሉት ሲሆን በፌስቡክ ላይ በሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵዊን ዘፈኑን መውደዳቸውን ለመግለጽ “like” በማድረግ አድናቆታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
     ደራሲና ገጣሚ በዕውቀቱ ሥዩም በፌስቡክ ድረገጽ በሰጠው አስተያየት “ሣልሳዊ ቴዎድሮስ ወይም “ቴዲ አፍሮ” በሰባ ደረጃ የተባለ(ች) ነጠላ ዘፈን ለቆልናል። “በሰባ ደረጃ”ን እኔ ስሰማው እልም ያለ የፍቅር ዘፈን ነው። ፍቅርን ልዩ በሆነ ቦታና ልዩ በሆነ ሥፍራ የሚያሳይ ዘፈን። በአማርኛ ዘፈን ባህል ውስጥ ቦታን ማስጎብኘት የተለመደ ነው። “የሐረር ልጅ ነች ወጣቷ/ጀጎል ነው ቤቷ” አይነት ዘፈን ሞልቶናል። አብዛኛው ያገራችን ዘፋኝ፣ ያስጎብኝነት ሚናም ደርቦ ሲጫወት ኖሯል። በዚህ ምክንያት ተፈቃሪዋ ሴት ሁሌም ከታሪካዊ ቦታ አጠገብ ለመወለድ ትገደዳለች። ቴዲ በዚህ ዜማው ባልተሄደበት መንገድ ሄዷል። ሲጀምር፣ እዚህ ግባ የማይባል፣ ለዓይን የማይሞላ ቦታ መረጠ። ብዙ ጊዜ፣ ታሪካዊ ቦታ ሲባል፣ አክሱም ላሊበላ፣ ፋሲል ሶፍኡመር ጀጎል እንላለን። ካሜራው በኒህ ቅርሶች ላይ አፍጥጦ ኖሯል። ታሪክ አክሱም ላይ ጀምሮ ጀጎል ላይ የተጠናቀቀ ይመስል። ብዙዎቻችን በሸገር ላይ አድልኦ ስንፈጽም ኖረናል። አዲስ አበባ ለአቅመ ቅርስ የምትበቃ ከተማ አትመስለንም። ሸገር ታሪክ ሲሠራባትና ሲሠራላት እንደኖረች አናውቅም። ወይም ለማወቅ አንፈልግም። ቴዲ ይህንን እይታ ቀየረው” ብሏል። 
     አያይዞም “ሁለተኛ፣ ከላይ የጠቀስኳቸው ቅርሶች የጌቶች መታሰቢያ ናቸው። የምድራዊና ሰማያዊ መሪዎችን የሚወክሉ ናቸው። የስም የለሹን፣ የተርታውን ሰው ኑሮ የሚያሳዩ ቅርሶች ግን ደምቀው አልወጡም። አይተን እንዳላየን፣ ቸል ብለናቸው ቆይተናል። ቴዲ ግን ማንም ሲወጣበትና ሲወርደበት ለኖረው አንድ መንገድ ዘፈነለት። መዝፈን ቢሉህ ዝም ብሎ መዝፈን ብቻ አይደለም፤ አንድ ውብ የሆነ የፍቅር ታሪክ ተረከበት። ነጠላ ዜማው ከተለቀቀበት ጊዜ አንስቶ ሰባ ደረጃን በድሮ ዓይናችን አናየውም። አሪፍ ጥበብ ዓይን ገላጭ ነው የሚባለው ለዚህ ነው።
     ሦስተኛው ነጥብ፣ ዘፋኞች ልዩ ቦታን ሲያሳዩ ኖረዋል። ቴዲ ደግሞ አንድን ልዩ ዘመን ለማሳየት ሞክሯል። የቴዲን ዘፈን ስሰማ፣ በካሳሁን ግርማሞ ዘመን የኖረ አንድ ሮሚዎ ይታየኛል። ሸዋ ዳቦ ሳይቋቋም፣ ከአርመን ሱቅ ፉርኖ በሚሸመትበት ዘመን፣ ምኒባስ ሳይገባ፣ ሰዎች ሴቼንቶ የሚሳፈሩበት ዘመን፣ ከጄኔራሎች በላይ ሴቼንቶ ነጂዎች ስመጥር የነበሩበት ዘመን፣ ሴቶች የጥላቸውን ቁመት አይተው ሰአት ከመገመት ወጥተው፣ ክንዳቸው ላይ ሰአት ማሰር የጀመሩበት ዘመን -
     በዚያ ዘመን የኖረ አፍቃሪ ይታየኛል። አንድን ልዩ ዘመን በሲኒማና በልቦለድ ማሳየት የተለመድ ነው። በጣም አጭር ቆይታ ባለው ዘፈን ውስጥ ዘመንን ለማሳየት በመሞከር ግን ቴዲ ፋና -ወጊ ይመስለኛል።
     ዜመኛ ስላልሆንሁ ስለቴዲ ዜማ ምንም ማለት አልችልም። ያም ሆኖ ፣ግጥሙ የተዋጣለት እንደሆነ መመስከር እችላለሁ። አንድ ቦታ ላይ ‹‹አንደ አርሚዴ ሜሪ›› የሚል ሐረግ ሰምቻለሁ። ዜመኛው፣ ሜሪ አርምዴን፣ አርምዴ መሪ ብሎ መጥራት የገጣሚነት ነጻነቱ ይፈቅድለታል። ገጣሚ እንደ ህጻን ልጅ፣ እንደ እብድና እንደ ቅዱሳን ከቋንቋ ሕግ በላይ ነው። እንደ ጋዜጠኛ፣ በሰዋስው ህግ አይታሠርም። እንዲያውም ሳይራቀቁ መግጠም፣ ፈሳሽ ውስጥ ሳይገቡ መስጠም አይታሰብም። በነገራችን ላይ በድሮ ዘመን በኢትዮጵያ የአባት ስም ከልጅ ስም ቀድሞ ይጻፍ ነበር።ቴዲን ትውፊትም ያግዘዋል ለማለት ፈልጌ ነው” ሲል አድናቆቱን ጽፎአል። 
     ትብለጥ በሚል ስም የምትታወቅ አድናቂ “ለእኔ ሁሌም ቴዲ አዲስ ነው። እግዚአብሄር ይባርከው” በማለት አድናቆቷን ሰጥታለች።
     አንዳንድ የማህበራዊ ገጽ ታዳሚዎች ቴዲ በተለይ ግጥም በራሱ ብቻ እየሠራ የመምጣቱ ጉዳይ ጥበቡን ሊጎዳው ይችላል በሚል ሥጋታቸውን ጽፈዋል።
**************************************************************************
ምንጭ:----https://www.facebook.com/alex.abreham.31/posts/1640063316276878
         ----http://ethiozeima.com/tag/teddy-afro-lyrics/
        ----http://www.addislive.com/teddy-afro-beseba-dereja/
       ----http://www.sendeknewspaper.com/news-sendek/item/

No comments:

Post a Comment