ከደራሲያን ዓምባ

Monday, May 3, 2021

ሚሻ ሚሾ (ሙሾ)

 


 ከበዓለ ስቅለት ባህላዊ መገለጫዎች አንዱ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚዘወተረው ‹‹ሚሻ ሙሾ›› ነው፡፡

ስለዚህ ባህላዊና ትውፊታዊ ሥርዓት ቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ መታፈሪያ ‹‹መዝገበ በረከት ዘሰሙን ቅድስት›› በተሰኘውና መሰንበቻውን ለንባብ በበቃው መጽሐፋቸው ዘርዘር አድርገው ማስረጃዎች እያጣቀሱ አቅርበውታል፡፡

በደራሲው አገላለጽ፣ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ወንዶች ሕፃናት ደግሞ ‹‹ሚሻ ሙሾ›› እያሉ እየዘመሩ በየቤቱ እየዞሩ ዱቄት ይለምናሉ፡፡ በዓሉ በቂጣ ስለሚከበር የአይሁድ የቂጣ በዓልን ይመስላል፡፡ አለቃ ታየ ገብረ ማርያም በ1902 ዓ.ም. በታተመው የትብብር ሥራቸው ‹‹ሚሻ ሚሾ›› የሚለው ስያሜ የት መጣ ‹‹ውሾ ውሾ›› ከሚል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህ ‹‹ማኅበራዊ ኑሮ በኢትዮጵያ›› ብለው በሰየሙት መጽሐፋቸው፣ ይህም አይሁድን ለመስደብ የተሰነዘረ እንደሚመስል ይገልጻሉ፡፡ በሌላ መልኩ መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ደግሞ ‹‹ሚሻ ሚሾ›› ወዲያ ወዲህ፣ ከዚያ ከዚህ ማለት ነው፡፡ ይህም ከየቤቱ ዱቄቱ የሚሰበሰብ መሆኑን ለማመልከት ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም የትውፊቱ ትክክለኛ መጠሪያ ‹‹ሙሾ ሙሾ›› የክርስቶስን ሕማም ለመግለጽ የተሰጠ መሆኑን፣ በጊዜ ሒደት ተለውጦ ‹‹ሚሻ ምሾ›› መባሉንም ይገልጻሉ፡፡

አለቃ ደስታ ተክለ ወልድም የቃሉን ፍች ‹‹ሙሾ (ምሾ) የለቅሶ ዜማ፣ የለቅሶ ቅንቀና፣ ግጥም፣ ዜማ፣ ቁዘማ፣ እንጉርጎሮ፣ ረገዳ፣ ጭብጨባ ያለበት›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ ይኼኛው ሐተታ ከክዋኔው ጋር ቀጥታ ቁርኝት አለው፡፡ ሕፃናቱ በየቤቱ መሄዳቸው አይሁድ ሐሙስ ሌሊት ከሐና ወደ ቀያፋ፣ ከቀያፋ ወደ ሊቀ ካህናቱ ቤት መዞራቸውን ለመዘከር ነው፡፡ ሕፃናት ይህን ዕለት እንዲያስታውሱት በየዓመቱ እንዲዘክሩ በማድረግ ይቻል ዘንድ ሊቃውንት ይህንን ሥርዓት እንደሠሩ ይናገራሉ፡፡

‹‹ሕፃናት ከምሴተ ሐሙስ ጀምረው እስከ በዓለ ስቅለት ምሽት የሚሻ ሙሾን ዝማሬ እያሰሙ በየቤቱ በመዞር ዱቄት የሚያሰባስቡት ትውፊታዊ ክዋኔ አለው፡፡ ሕፃናቱ በየቤቱ ዱቄት ለመሰብሰብ ሲዞሩ በቀለማት ወይም በእሳት ተለብልቦ የተዥጎረጎረ ቀጭን ዘንግ ይይዛሉ፡፡ መሬቱን በዘንግ በመምታት ዱቄት እስኪሰጣቸው ድረስ በተለያዩ ግጥሞች የታጀበ ዝማሬ ያሰማሉ፡፡ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዘንግ መመታቱን ለማዘከር ነው፡፡

 


 

በዝማሬያቸው

‹‹ሙሻ ሙሾ ስለ ስቅለቱ

አይንፈጉኝ ከዱቄቱ፡፡

ሚሻ ምሾ፣ ሆ ሚሻ ሙሾ

ሳይጋገር መሸ፣

እሜቴ ይውጡ ይውጡ

ይበላዋል አይጡ፣

እሜቴ ይነሱ

ይንበሳበሱ፣

ከቆምንበት

ቁንጫው ፈላበት፣

ስለ አቦ

ያደረ ዳቦ፣

ስለ ስቅለቱ

ዛቅ አድርገው ከዱቄቱ፤››

በማለት ይዘምራሉ፡፡

ሕፃናት ሚሻ ሙሾ ብለው አንድ ቤት ሲጨፍሩ ከቤቱ ዱቄት፣ አዋዜ፣ ቅባኑግ ወይም ጨው ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ ይኼንን ሲያገኙ 

‹‹ዕድሜ የማቱሳላን፣

 ጽድቅ የላሊበላን ይስጥልን፤›› ብለው መርቀው ይሄዳሉ፡፡ 

በተጨማሪም ሕፃናት በዚህ ክዋኔ ታላቅ ምርቃት ይሰጣቸዋል፡፡ ሕፃናቱ ለምነው ምንም ነገር ሳይሰጣቸው ከቀረ

‹‹እንደ ሰፌድ ይዘርጋሽ፣ 

እንደ ማጭድ ይቆልምሽ፣ 

ቁመት ያውራ ዶሮ፣ 

መልክ የዝንጀሮ፣ 

ግማት የፋሮ ይስጥሽ፤›› ብለው ተራግመው እንደሚሄዱ አለቃ ታየ ትውፊቱን አስቀምጠዋል፡፡

ሕፃናቱ በልመና ባገኙት ዱቄት ቂጣ ጋግረው ቅዳሜ ምሽት በጋራ ይመገቡታል፡፡ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህ ግን ዳቦውን በትንሣኤ ሳምንት አስጋግረው ጎረቤቶችንና ሽማግሎችን ጋብዘው እንደሚበላ ተናግረዋል፡፡

 ******+++******


 

አርብ ፦ሚሻሚሾ

ሆሆ ሚሻ ሚሾ ሚሻ ሚሾ
አንድ አውራ ዶሮ እግሩን ተሰብሮ
እሜቴ ይነሱ ጉሽጉሻውን ይዳስሱ
ስለ ስቅለቱ ዛቅ አድርገው ከዶቄቱ


እያሉ ህፃናት ተሰብስበው በየቤቱ እየዞሩ የቤቱን ደጃፍ በያዙት ዱላ እየደበደቡ ከላይ ያለውን ግጥም በዜማ ይላሉ። አስቀድመው ግን ዱላ ያዘጋጃሉ ዱላ ሲያዘጋጁም ይልጡትና በልጡ ግማሹን ይሸፍኑትና በእሳት ይለበልቡታል ከዛ ሲወጣ ዝንጉርጉር ይሆናል ነጭና ጥቁር ።በጲላጦስ አደባባይ ጌታችን አጥንቱ እስኪታይ መገረፉን ለማመልከት መሆኑንም ታላላቆቻችን ይናገራሉ.... ሚሻ ሚሾ አንዳንዶች ውሾ ውሾ እያሉ ጌታችንን ማህበራነ አይሁድ መስደባቸውን ለመግለፅ ነው ይላሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ዕለቱ የሐዘን ነው አልቅሱ እዘኑ ለማለት ነውም ይላሉ ምሻሚሾ (ሙሾ-ሐዘን ፣ለቅሶ እንዲል ዱቄቱን ከሰበሰቡ በኃላ ደግሞ ድንጋይ እና ድንጋይ በማጋጨት ጫጫ መሰልቀጫ ሚስቴ ወልዳብኝ ጨውና ዘይት ብላብኝ እያሉ ይዞራሉ ለምን ድንጋይ እንደሚይዙ ግን እስካሁን አልገባኝም በኃላም ከተመረጠ ቤት ይሰበሰቡ እና የሰበሰቡት ዱቄት ተቦክቶ ቂጣ ይጋገራል ከዛ ደግሞ የሰበሰቡት ጨው እና ዘይት ይለወስና ቂጣው ይቀባል ከዛ የሚበላው ተቆርሶ ይሰጠዋል ለሚፆመው ደግሞ ይቀመጥለት እና ከቤተ ክርስቲያን መልስ ትልቁም ትንሹም ከተመረጠው ቤት ቡና ተፈልቶ የሚበላው በልተው ጠጥተው የሚያከፍለውም በጨዋታው መሀል ተገኝቶ ተመራርቀው ይለያያሉ

የአርብ ስቅለት በጎንደር እና አከባቢው እንደዚህ ይከበራል እንደሰማሁት በትግራይ አከባቢ ደሞ ልጃገረዶች ሙሉ ቀኑን በባዶ ሆዳቸው ሆዳቸውን በመቀነት አጥብቀው በማሰር ዥዋዥዌ እያሉ ይውላሉ መንገላታቱን ለማሰብ፤ በዋግም እንደዚሁ፤በጎጃም አገዎችም አጎላ ጎሊ ይባላል።


 በጎጃም አገዎችም አጎላ ጎሊ ይባላል:-


 
 
#EBC ሚሻ ሚሾ/አጎላ ጎሌ በአ እንዴት እንደሚጨፈር እና ምን አይነት ሂደቶችና ስርዓቶች እንዳሉት ያስቃኘናል
 


እጅጋየሁ (ጂጂ) ሽባባው አጎላ ጎሌ


***********************************************

ምንጭ:- https://www.ethiopianreporter.com/article/21944

           :- የጥበብ ወሬዎች 

 

 

No comments:

Post a Comment