ከደራሲያን ዓምባ

Wednesday, November 16, 2022

አውራ አምባዎች - የሰላም ሠፈርተኞች

 አውራ አምባዎች - የሰላም ሠፈርተኞች_አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 25 ቀን 2014 ዓ.ም 

(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)


አንዲህም ይኖራል! 
“ላለፉት 50 ዓመታት ያህል አውራ አምባ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ የኖረ ማሕበረሰብ ነው። አንድም ጊዜ ተከሶም ሆነ ከሶ አያውቅም። ከግጭቶች ነፃ ምድር ነው። ይህ ሰላማዊ ማሕበረሰብ ለዓለምና ለሰው ልጆች ሁሉ የሚያስተምረው የሰላም ሕይወት ምሥጢር አለው። ዓለም በሰላም እጦት እንዲህ ስትናወጥ አውራ አምባ ማሕበረሰብ እንዴት 50 ዓመታት ሙሉ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ ኖረ? - [ይህ እውነታ] እንደ መስታወት ሆኖ ራሳችንን የት እንዳለን እንድንጠይቅ ይሞግተናል” (ዝክረ አውራ አምባ - ዙምራ፤ ሰኔ 2014 ገጽ 14። ) በሰላም እጦት ርሃብተኛ ለሆነው ለእኛ ለዛሬዎቹ የሀገሪቱ ወርተረኛ ትውልዶች፤ በእኛው ቀዬ በአውራ አምባ ማሕበረሰብ መካከል እየተመረተ ያለው ይህን መሰሉ “ለዓለምና ለሰው ልጆች ሁሉ የሚተርፍ” የተባለለት የሰላም አዝመራ ስለምን ብርቅና ሩቅ ሆኖብን ባይተዋር በመሆን የተለያዩ ግጭቶችና ጦርነቶች እያስተናገድን ለመኖር ምርጫችን ማድረጉን ማሰቡ በራሱ ግራ ያጋባል። ለሃምሳ ዓመታት ያህል እድሜያችንን አባክነን ዛሬ እንደ አዲስ ይህን ጥያቄ ጠይቀን መልስ መፈለጋችን እፍረት ቢሆንብንም “በሆድ ይፍጀው” ለሆሳስ ከማለፍ ይልቅ የአውራ አምባዎችን ድንቅ ሰላማዊ አኗኗር እየጠቃቀስን ደፈር ብለን ራሳችንን ብንወቅስ ይበጅ ይመስለናል።

 በሰላም እጦት ወጀብ እየተላጋች ያለችው ሀገር ይህንን የልጆቿን መልካም እሴት ተቀብላ ለማስፋፋት እውነት ስለምን ዐይኗ ተጨፈነ? የዘንባባ ዝንጣፊ በአፏ ይዛ በዚያ ማሕበረሰብ ውስጥ ሃምሳ ዓመት ሙሉ በዓየሩ ላይ ስትቀዝፍ የነበረችውን የሰላም ተምሳሌት ርግብ “ነይ ርግብ አሞራ!” እያልን ከማሕበረሰቡም ከፍ ብላ በራ ወደ ሌሎች ክልሎችም የምሥራች እንዳታበስር በእርግጡ ዐይነ ጥላውን ያሳረፈብን አዚም ምን ይሆን? ቢቸግረውና መልሱ ግራ ቢያጋባው ሳይሆን አይቀርም፣ አንጋፋው ነፍሰ ሄር ድምጻዊ “ጥያቄ አቅርቤያለሁ መልሱን ብትሰጡኝ…” በማለት ያንጎራጎረው። “ግዛዋ ሳለ ከደጅሽ፤ ለምን ሞተ ልጅሽ” አለች ይባላል ግራ የተጋባች አንዲት ስም የለሽ እናት ባለሀገር። አውራ አምባዎች ያስታወሱን የጥበብ ምሳሌ፤ ከአሁን ቀደም ጠቀስ አድርጌ ያለፍኩትን አንድ ጥበብ ነክ ታሪክ ለማዋዣነት እንዲረዳ ደግሜ ላስታውስ። በአንድ ሀገር ውስጥ ታላላቅ የዓለም ሠዓሊያንን ያሳተፈ የሥዕል ውድድር ተደርጎ ነበር ይባላል። ሁሉም ሠዓሊያን በሥዕላቸው እንዲወክሉ የተወሰነው “የሰላምን” ማሳያ ነበር። ውድድሩ ብዙ ፍልሚያ ተደርጎበት ለመጨረሻው የደረጃ ፍጻሜ የደረሱት ሦስቱ ተወዳዳሪ ሠዓሊያን ብቻ የጥበብ ሥራቸውን እንዲያስገመግሙ የተለያዩ የየግላቸው ስቱዲዮ ተሰጣቸው ይባላል። የመጀመሪያው ሠዓሊ ሰላምን የወከለው የተንዠረገገና አጓጊ ፍሬ በተሸከመ አንድ ትልቅ ዛፍ አማካይነት ነበር። ሦስቱ ዓለም አቀፍ ዳኞች ይህንን የፈጠራ ውጤት ለማየት የስቱዲዮውን በር ከፈት አድርገው ሲገቡ ከየት መጣች የማትባል ወፍ እየበረረች ሄዳ አብራቸው ዘው ብላ በመግባት ፍሬው የጎመራው ያ ዠርጋዳ ዛፍ እውነተኛ መስሏት በላዩ ላይ ለማረፍ ሥዕሉ ሸራ ላይ ታንቧችር ጀመር። ዳኞቹ በእጅጉ ተገርመው “እንኳን ሰብዓዊ ፍጡርን ቀርቶ ተፈጥሮን ሳይቀር ያማለለ የጥበብ ስራ” የሚል አስተያየት በማስታወሻቸው ላይ በማስፈር ወደ ሁለተኛው ሠዓሊ ስቱዲዮ አመሩ። ሁለተኛው ሠዓሊ ሰላምን የወከለው እጅግ በሚማርክና በተዋበ መጋረጃ ነበር። ዳኞቹ ልክ ወደ ስቱዲዮው እንደገቡ መጋረጃው ከፊት ለፊት ባለው ሸራ ላይ ዧ ብሎ ተዘርግቶ ሲያስተውሉ እውነተኛ መጋረጃ መስሏቸው ለመግለጥ እጃቸውን ዘረጉ። ሥዕል መሆኑን ሲያውቁ ግን በራሳቸው ድርጊት እንዳፈሩ አቀርቅረው በየግል ማስታወሻቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ሃሳባቸውን አሰፈሩ። “የመጀመሪያው ሠዓሊ ተፈጥሮን እንኳን የማሞኝት ከፍተኛ ክህሎት ያዳበረ የምር ጠቢብ ሲሆን ይህ ሁለተኛው ሠዓሊ ደግሞ እኛን ዳኞቹን ሳይቀር የማቄል ከፍተኛ ተሰጥዖ ያለው ታላቅ ባለሙያ ነው። ” በሁለቱ የጥበብ ሥራዎች እጅግ የተመሰጡት ዳኞች ወደ ሦስተኛው ሠዓሊ ስቱዲዮ ያመሩት እየተገረሙ ነበር። በዚህ በሦስተኛው ስቱዲዮ ውስጥ ሰላምን ወክሎ የቀረበው የሥዕል ስራ እጅግም የተወሳሰበና የሚያማልል አልነበረም። አንድ የተንጣለለ ታላቅ ውቂያኖስ ከዳር ዳር ተዘርግቷል። ውቂያኖሱ በከባድ አውሎ ነፋስ እንደሚላጋ በግሩም ሁኔታ በቀለማት ጥበብ ተከሽኗል። በውቂያኖሱ መሃል ለመሃል አንድ ቋጥኝ ከፍ ብሎ ተገሽሯል። በዚያ ቋጥኝ ላይ እንዲት ወፍ አንገቷን ወደ ላይ ቀና አድርጋ ትዘምራለች። ከሥዕሉ በላይ “ሰላም” የሚል ቃል ተጽፏል። የሥዕሉ አጠቃላይ ይዘት ይኼው ነበር። ዳኞቹ ሥራቸውን አጠናቀው ውጤት ለመስጠት ተሰበሰቡ። “ለሰላም ውክልና” የቀረበውን የመጀመሪያውን ሥዕል በተመለከተ ሦስቱም ዳኞች የተስማሙበት አስተያየት እንዲህ የሚል ነበር። “እርግጥ ነው የሠዓሊው የተንዠረገገ ዛፍ እንኳንስ እኛን ወፏን እንኳን እውነተኛ ዛፍ እስኪመስል ድረስ አሞኝቷል። ድንቅ ስራ ነው። ቢሆንም ሰላምን ለመወከል አቅም የለውም። ” ወደ ሁለተኛው የጥበብ ስራ ተሸጋገሩ፤ “የሁለተኛው ሠዓሊ የመጋረጃ ሥዕልም በጥበብነቱ እጅግ ሊደነቅ ይገባል። ቢሆንም ግን ሰላም የሚገኘው በውብ መጋረጃ ውስጥ ታልፎ በሚገኝ ደስታ ብቻ ከሆነ ስህተት ነው። ስለዚህም ሰላምን በሚገባ አይገልጥም። ” ሦስተኛው የሥዕል ስራ ለውሳኔ አሰጣጥ አላዳገታቸውም። በአውሎ ነፋስ ወጀብ በሚላጋው ውቂያኖስ መሃል በሚገኘው ቋጥኝ ላይ ያረፈችው ወፍ አንገቷን ቀና አድርጋ ተረጋግታ ትዘምራለች እንጂ በሚደነፋውና “ዱታ ነኝ” ብሎ በሚፎክረው ማዕበል ተረትታ ከዝማሬዋ አልተገታችም። እውነተኛ ሰላም የሚመዘነው በወጀብና በአውሎ ነፋስ መካከል አለመናወጥ ነው። ስለዚህ ሦስተኛው ሥዕል ማሸነፍ ሲያንሰው ነው። ” ዳኞቹ ውሳኔያቸውን አሳውቀው ለሠዓሊው ተጨበጨበለት፤ አድናቆትና ሽልማትም ተዥጎደጎደለት። 

ክብር ዶ/ር ዙምራ ኑሩ
                                                                የክብር ዶ/ር ዙምራ ኑሩ

 የአውራ አምባ ማሕበረሰብ በሦስተኛው አሸናፊ ሥዕል ቢመሰል ያንስበት ካልሆነ በስተቀር ይበዛበታል ተብሎ አያከራክርም። የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ዙሪያ ገባዋ በውስጥና በውጭ ጠላቶቿ አማካይነት በሰላም እጦት ወጀብና አውሎ ነፋስ እየተላጋች ባለችበት ወቅት “መድኃኒቱ በደጃፏ እያለ” ይህ የአውራ አምባ ማሕበረሰብ ሃምሳ ዓመት ሙሉ ወጀብ በበዛበት ሀገር በሰላም እየኖርኩ ነው ብሎ እኛን ባለሀገሮችን ብቻም ሳይሆን የዓለምን ማሕበረሰብ ጭምር ማስደመሙ ከማስገረም የሚዘል አድናቆት ሊቸረው ይገባል። ለመሆኑ ይህንን ማሕበረሰብ የሰላም ተምሳሌት ያሰኙት ምሥጢሮች ምንድን ናቸው? የአጀማመሩን ዳራ ጠቃቅሰን ከብዙ እሴቶቹ መካከል ጥቂቶን እሴቶቹን ብቻ ለማመላከት እንሞክራለን። የአውራ አምባ ማሕበረሰብ የተመሠረተው በ1964 ዓ.ም ሲሆን መገኛውም ከባሕር ዳር ከተማ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 67 ኪ.ሜ በሚርቀው በደቡብ ጎንደር አስተዳደር በፎገራ ወረዳ በወጅ አውራ አምባ ቀበሌ ውስጥ ነው። መስራቹ ደግሞ የክብር ዶ/ር ዙምራ የኑስ ናቸው። ማሕበረሰቡ “አንቱታ ያራርቃል” የሚል እምነት ስላለው “አንተ/አንቺ” መባባልን ስለሚያዘወትር ይህ ጸፊም ዕድሜው ወደ ሰማኒያው እየተንደረደረ ያለውን መሥራቹን ዙምራን አንተ እያለ የሚገልጸው ባህላዊ አክብሮቱ ሳይጓደል ነው። 
የአውራ አምባ ማሕበረሰብ ከተመሰረተ ሃምሳ ዓመታት ቢያስቆጥርም የጉዞው ውጣ ውረድ ግን በመከራና በፈተና የታጀበ እንደነበር ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ውስጥ ክብርት ከንቲባዋን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ሹመኞች በተገኙበት ፕሮግራም ላይ በቀረበው ዶኪዩመንተሪ ፊልምና በተመረቀው መጽሐፍ ውስጥ በዝርዝር ተተርኳል። ባለ ራእዩ ዙምራና የማሕበረሰቡ አባላት በቆራጥነት ተቋቁመው ያሳለፏቸው እንግልት፣ ስደትና መገለል ዓይነታቸውም ሆነ አበዛዛቸው ለቁጥር ያታክታል። ተርበዋል፣ ተጠምተዋል፣ በግፈኞች ተሳደዋል። ከትውልድ አካባቢያቸው ብቻም ሳይሆን ተሰደው ከሚያርፉባቸው አካባቢዎችም ጭምር ማረፊያ በሚያሳጡ አሳዳጆች ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ስለምን? ሰላምን ስለሚሰብኩ፣ በሰው ልጅ እኩልነት ስለሚያምኑ፣ የጾታ ልዩነትን ስለማይቀበሉ፣ ከሃይማኖቶች ቀኖና ይልቅ በአንድ ፈጣሪ ብቻ በማመናቸው ወዘተ. ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ነበሩ። ለሰላማዊ አኗኗራቸው እንደ ሕይወት ፍልስፍና የሚከተሏቸው እሴቶች የሚከተሉት ናቸው። እነዚህ እሴቶች የአብዛኛዎቹን የሀገራችን ማሕበረሰቦች ነባርና ቅቡል ልምምዶች ስለሚገዳደሩ አውራ አምባዎች እንደ ተለየ የማሕበረሰብ ክፍል እንዲታዩ፣ እንዲገፈተሩና እንዲገለሉ ምክንያት ሆነዋል። 
አንባቢው የራሱን ፍርድ እንዲሰጥ ዋና ዋናዎቹ ብቻ እንደሚከተለው ይታወሳሉ፡ ሀ. ሰው ሁሉ እኩል ነው። ማንኛውም ሰው አዳምና ሔዋን (አደምና ሐዋ) ከተባሉ ሁለት የዘር ምንጮች የተገኘ ነው። ስለዚህ ከአንድ አባትና እናት የተገኘ ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ በምንም መስፈርት ሊበላለጥና ከእከሌ እንቶኔ ይሻላል ተብሎ በምንም መስፈርት እየተመዘነ ሊፈረጅ አይገባውም። ለምን ቢሉ ሴት በሴትነቷ እናት ናት፤ ወንድ በወንድነቱ አባት ነው። እናት በሌለችበት አባት የለም፤ አባት በሌለበትም እናት የለችም። ስለዚህም፡- ለ. የጾታ ልዩነት ተፈጥሯዊ እንጂ አብሮ በመኖር ሕይወት ውስጥ መለያያና መከፋፈያ ሊሆን አይገባም። የጾታ ልዩነት እየተደረገም ለወንድና ለሴት በሚል የተግባር ክፍፍል ሊደረግ አይገባም። ወንዱም ሆነ ሴቷ እኩል የማጀቱንም ሆነ የውጭውን ስራ እየተጋገዙ መስራት ይገባል። ሊጥ አቡክቶ፣ አብሲት ጥሎ እንጀራ መጋገርም ሆነ እንዝርት እያሾሩ ፈትል መፍተል ለሴቶች ብቻ የተሰጠ ሳይሆን ወንዶችም ሊሰሩት ይገባል። እርሻም ቢሆን በሬ ጠምዶ ማረስ ለወንዶች ብቻ የተሰጠ ሳይሆን ሴቶችም ሊተገብሩት ይገባል። ሐ. ለራስ የሚደረገውን ለሌሎች ማድረግ፣ በራስ ላይ እንዲደረግ የማይፈለገውንም በሌላው ላይ አለመፈጸም። መ. አረጋውያን የትውልድ መሰረት፣ ጌጥና ውበት ስለሆኑ ተገቢው አክብሮትና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል። አቅመ ደካሞችም መደገፍና መጦር ይገባቸዋል። ሕጻናትም የነገው ትውልድ እርሾዎች ስለሆኑ በተገቢ እንክብካቤ፣ ትምህርትና ሥነ ምግባር ተኮትኩተው ሊያድጉ ይገባል። በቤተሰብና በማሕበረሰቡ አዋቂዎች ውይይት ወቅትም ልጆች ናችሁ ተብለው ሳይናቁ ተገቢው ወንበርም ሆነ የመወያየትና የማወያየት እድል ሊነፈጋቸው አይገባም። ሠ. የማሕበሩ አባላት ጥረው ግረው የሚያፈሩት ሀብት ሁሉም እኩል የሚከፋፈሉት እንጂ የተበላለጠ ድርሻ ሊኖር አይገባም። ረ. የእነዚህ ሁሉ መልካም እሴቶች ማሰሪያው ሰላም ነው። የሰላም ጉዳይ በማሕብረተሰቡ ውስጥ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። ጠብና ጭቅጭቅ፣ ንትርክና አተካራ በእነርሱ ዘንድ አይታወቅም ለምን ቢሉ ሁሉም ሰው በማሕበረሰቡ ውስጥ እኩል ነው፣ ሃሳቡ ይደመጣል፣ ውጤቱ ይመዘናል፣ ቅሬታው ሳይውል ሳያድር ይፈታል፤ ስለዚህም አምባጓሮ ጥዩፍ ነው። ምንጭም ስርም አይኖረውም። 
 በአጠቃላይ አውራ አምባዎች የሚገለጹት ከኢትዮጵያ ምድር የተገኙ የሀገር ውበትና የዓለም ሀብት እንደሆኑ ነው። መርህና እሴታቸው በመላው ሀገሪቱ ውስጥ ቢስፋፋና ቢሰርጽ የዛሬው መከራችን በአጭሩ በተቀጨ፣ እምባችንም በታበሰና የዓለም ሕዝብ “ወደ ሰላም ምድር” እንፍለስ ብሎ አዋጅ ባስለፈፈ ነበር። ይህ ጸሐፊ ይህንን ምስክርነት የሚሰጠው በቀዬአቸው ተገኝቶ ጎብኝቷቸው፣ የተመለከተውንም በመጽሐፍና በጋዜጦች አስተዋውቆ፣ የሃምሳኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን ሲያከብሩም ምስክርነቱን አጠንክሮ የሰጠ ስለሆነ መልእክቱ እውነተኛ፣ ራእያቸውም ለሀገራችን ሥር የሰደዱ ወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ ሊሆን ስለሚችል እሴቶቻቸው የጋራና የሕዝብ መርህ እንዲሆኑ እውቅና ሊያገኙ ስለሚገባ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ፈጥነው ምላሽ ይስጡ። በመጨረሻም ሃሳቡን የምናጠቃልለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ስለዚህ የሰላም ተምሳሌት ማሕበረሰብ ከቀናት በፊት በሰጡት ምስክርነት ይሆናል፤ “የአውራ አምባ ማሕበረሰብ እምነት፣ ብሔርና የፖለቲካ አመለካከት አንድ ሆነን ከመኖር እንደማያግዱን ሕያው ምስክር ነው። የጾታ እኩልነት፣ የሕጻናትና የአካል ጉዳተኞች ማሕበራዊ ፍትሕ በተግባር ተፈትኖ ያየንበትም ነው። ” ረጂም እድሜ ለባለራእዩ ለክብር ዶ/ር ዙምራ ኑሩ፣ የተባረከ ቀሪ ዘመን ለአውራ እምባ ማሕበረሰብ አባላት ይድረስልን። 
ሰላም ይሁን!


No comments:

Post a Comment