የምስኪኖቹን መንደር በስካቫተር ያፈረሰው ሚሊየነር
በደቡባዊ ቻይና
ግዛት የምትገኘው የደሳሳዋ ዦንኪንግ መንደር
ነዋሪዎች ፡ ሸቀጣሸቀጥ ጭነው ከሚመጡ አሮጌ
ከባድ መኪኖች ውጭ አንድም መኪና ወደመንደራቸው
ዘልቆ አይተው አያውቁም ። ዛሬ ግን እጅግ
ዘመናዊ ፡ መርሰዲስ መኪና መጥታ ቆማለች ።
እናም
ነዋሪዎች ፡ በመኪናዋ እዚህ መገኘት በመገረም
ዙሪያውን ከበው በማየት ላይ እያሉ ፡ አንድ
በጠባቂዎች የታጀበ እድሜው በሀምሳዎቹ የሚገመት
ሰው ከመኪናው ወጣ ። ማንም ደፍሮ ሰላም ሊለው
ወይም ሊያናግረው የመጣ ሰው ግን አልነበረም
። እናም ሰውየው መንደሩን ለደቂቃዎች ከተመለከተ
በኋላ ተመልሶ ወደመኪናው ገብቶ ሄደ ።
ይህ በሆነ
በማግስቱ ወደዛች ደሳሳ መንደር ሌላ መኪና
መጣ ። ከመጡት ሰወች ውስጥ የትናንቱ ሰውዬ
አልነበረም ። በቁጥር በዛ የሚሉ መሀንዲሶች
ነበሩ የመጡት ። በዚህ ጊዜ ነዋሪዎቹ ነገሩ
ገባቸው ፡ የትናንቱ ሰው ባለሀብት መሆኑን
በሁኔታው አውቀዋል ፡ እናም ይህን መንደር
ሊያፈርስ መሀንዲሶች ልኳል ።
እነዚህ
ነዋሪዎች ፡ ይህም ኑሮ ሆኖ ፡ ደሳሳ ጎጇቸውን
የሚያፈርስ ሰው ይመጣል ብለው መቼም አስበው
አያውቁም ነበር ። እና ሽማግሌዎች ቀርበው
መሀንዲሶቹን አናገሯቸው ። ፍርሀታቸው ልክ
ነበር ፡ ትናንት የመጣው ባለሀብት እዚህ
መንደር ላይ ሪል ስቴት መገንባት ፈልጓል ፡፡
ለዚህም ከመንግስት ፍቃድ እንዳገኘ ፡ ከሰባ
በላይ ለሚሆኑት ለመንደሩ ነዋሪዎችም ካሳ
እና መኖሪያ ቤት የሚገነቡበት ገንዘብ
እንደሚሰጣቸው እስከዛ ግን በመጠለያ መቆየት
እንደሚችሉ ፡ እስከነገ ድረስም እቃቸውን
አውጥተው በተዘጋጀላቸው ማረፊያ እንዲያስቀምጡ
ነግረዋቸው ሄዱ ።
ከቀናት
በኋላም ፡ ብዛት ያላቸው ግሪደሮች እና የህንጻ
ሰራተኞች ትንሿን መንደር አጥለቀለቋት ።
ያለቻቸውን
አሮጌ እቃ አውጥተው ከቤታቸው አቅራቢያ
በተዘጋጀላቸው መጠለያ ውስጥ የገቡት የዦንኪንግ
መንደር ነዋሪዎች ፡ ቆመው እያዩ ለዘመናት
የኖሩባቸው ደሳሳ ጎጆዎች በስካቫተር ፈረሰ
።
ቃል
የተገባላቸው ቤት መስሪያ ቦታም ሆነ ካሳ
ሳይሰጣቸው ለወራት በመጠለያ እየተረዱ ቆዩ
። ከአመታት በፊት ከነሱ ብዙም በማይርቅ ቦታ
የሚገኙ መንደሮች ልክ እንደነሱ በጨካኝ
ባለሀብት ተፈናቅለው ፡ መሰደዳቸውን እያሰቡ
፡ እጣ ፈንታቸውን መጠባበቅ ጀመሩ ።
ይህ
በሆነ በጥቂት ወራት ውስጥም የባለሀብቱ ዘመናዊ
ቪላዎች ተገንብተው ተጠናቀቁና ፡ ነዋሪዎቹ
በስነስርአቱ ላይ እንዲገኙ ፡ በፕሮግራሙም
ላይ ለነሱም ቃል የተገባላቸው ካሳ እንደሚሰጥ
ተነገራቸው ። ብዙዎች ነዋሪዎች ግብዣውን
ተቃወሙ ።
ትንሿ የዦንኪንግ
መንደር ዛሬ በልዩ ሁኔታ ደምቃለች ። ከሰባ
በላይ ዘመናዊ መኖሪያዎችን ለመመረቅ የተለያዩ
እንግዶች ተገኝተዋል ። ያቺ የድሆች መንደር
፡ አይታ በማታውቀው ሁኔታ በዘመናዊ መኪኖችና
በሀብታሞች ተጥለቅልቃለች ።
የምረቃው
ፕሮግራም ተጀመረ ።
ያ ፡ በመጀመሪያ
ቀን መርሰዲስ መኪና ይዞ ወደዚህ መንደር
የመጣው ባለሀብት ፡ ንግግር ለማድረግ ወደ
መድረኩ ወጣ ።
ክቡራንና
ክቡራት የዦንኪንግ መንደር ነዋሪዎችና ፡
ክቡራን እንግዶች ዛሬ ልዩ የሆነውን ይህን
የዘመናዊ መኖሪያ ቤት ፕሮጀክት ለመመረቅ
ስለተገኛችሁ አመሰግናለሁ ።
እኔ
የማየው ዛሬ ሚሊየነር መሆኔን አይደለም ።
የኔ ስብእና የኔ የሀብት ምንጭ ይሄ መንደር
ነው ።. ... እኔ
..... ትንሽ
ልጅ ሆኜ የምታውቁኝ Xiong Shuihua ነኝ
።
በርግጥ ከዚህ መንደር ከወጣሁ ብዙ አመታት ተቆጥረዋልና ፡ አላወቃችሁኝም ። እኔ ግን ሁላችሁንም አስታውሳለሁ ።
ለኔና እጅግ
ድሆች ለነበርነው ቤተሰቦቼ በየወሩ ቀለብ
ይቆርጥልን የነበረው ሚስተር ዣይን ፡ ከልጆቻቸው
እኩል ልብስ ይገዙልኝ የነበሩት የሚስ ታዮኒ
ቤተሰቦች ፡ ሲርበን የሚያበሉን የዚህ መንደር
ነዋሪዎች ሁላችሁንም አስታውሳለሁ ።
የኔ
የአሁን ህይወት ላይ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጣችሁ
እናንተ ናችሁ ። ለዚህም ነው መንደሩን ለመለወጥ
በተሻለ ህይወት እንድትኖሩ ለማሰብ የተገኘሁት
።
እናም እነዚህ ቤቶች የተሰሩት ለናንተ ነው ። ያለምንም ክፍያ በነዚህ ቤቶች ትኖራላችሁ ። ቤቶቹ ንብረቶቻችሁ ናችሁ ። በነጻ የተሰጧችሁ አይደሉም ፡ ከአመታት በፊት ለኔና ለቤተሰቦቼ መልካም ነገር በማድረግ ኢንቨስት አድርጋችሁበታል ።
እያለ እንባ እየተናነቀው ሲናገር የመንደሩ ሰወች በሙሉ በታላቅ ድንጋጤ ውስጥ ሆነው ይሰሙት ነበር ።
ባለሀብቱ ንግግሩን ቀጥሏል ።
እናም ከሀምሳ ሚሊየን ዶላር በላይ ወጭ ተደርጎባቸው የተሰሩት ፡ እነዚህ ቤቶች በፈረሱት ቤቶቻችሁ ቁጥር ልክ የተሰሩ ናቸው ፡ ነገ አዳዲስ የቤት እቃ የጫኑ መኪኖች ይደርሳሉ ። መብራትና ውሀም አትከፍሉም ። መስራት ለምትችሉ የስራ እድል ይዘጋጃል ፡ ለአቅመ ደካሞችና ማብሰል ለማይችሉ ደግሞ ዘመናቸውን ሙሉ የሚፈልጉትን መርጠው የሚመገቡበት መመገቢያ አዳራሽም ተገንብቷል ።
የናንተ ውለታ ከዚም በላይ ነው አላቸውና ፡ ከመድረኩ ወረደ ።
© Wasihune Tesfaye
https://www.atchuup.com/xiong-shuihua-acts-of-kindness/
https://www.dailymail.co.uk/news/article-2850436/Millionaire-Chinese-businessman-bulldozes-run-huts-village-grew-builds-luxury-flats-residents-instead-free.html
No comments:
Post a Comment