በዓለ ጥምቀት በሀገረ ኢትዮጵያ ፤ የወፍ በረር ቅኝት
ደመቀ ከበደ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ድምቀት በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት ውስጥ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት አንዱና ዋናው ነው፡፡ ይህ ታላቅ በዓል በመላዋ ኢትዮጵያ በገጠርም ሆነ በከተማ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ከዋዜማው ጀምሮ ታቦታቱ በምስጋና ታጅበው ወደ ባሕረ ጥምቀት ወርደው በማደርና በመመለስ ከበዓላት ሁሉ በተለየ ድምቀት ይከበራል፡፡
ጥምቀት ቤተ ክርስቲያኒቱ ለምዕመናን ከምትፈጽማቸው ምሥጢራት አንዱና ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ልጅነት በማግኘት የሚከብሩበት፣ ለሁሉም አማኞች የሚዳረስና የማይደገም ሲሆን መሥራቹም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን የዕለት ከዕለት ክንውንና ዋና አገልግሎት ሆኖ መቀጠሉን ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠቅሰው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስረዳሉ፡፡
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ጥምቀትን ውኃ ውስጥ ገብቶ መነከር፣ መዘፈቅ፣ መጠመቅ ማለት ነው ሲሉ ይተረጉሙታል፡፡
የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በማየ ዮርዳኖስ መጠመቁን ለመዘከር የሚከበር በዓል ነዉ፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተገለጸው ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በባህረ ዮርዳኖስ ነው፤ ይህም ተምሳሌትነት ስላለው ነው ይላል መላኩ በጥናት መፅሐፉ፡፡ "የሰው ሁሉ መገኛው አንድ አዳም እንደሆነ፥ ባህረ ዮርዳኖስም ከላይ ነቁ/መገኛው አንድ ነው፡፡ ነገር ግን ዝቅ ብሎ በደሴት ይከፈላል፤ ሕዝበ እስራኤልና አሕዛብም በግዝረትና በቁልፈት ተለያይተዋል፡፡ ባህሩ ወደታች ወረድ ብሎ እንደገና በወደብ ይገናኛል፤ ይህም ሕዝብና አሕዛብም በክርስቶስ ጥምቀት አንድ የመሆናቸው ተምሳሌት ነው፡፡"
ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጠመቁ አንድ ቀን አስቀድሞ በዋዜማው ከገሊላ መንደር መጥምቁ ዮሐንስ እያጠመቀ በወደነበረት ወደማዕከላዊው የዮርዳኖስ ባሕር ክፍል ወርዷል፡፡ ሊቃውንቱ ኢየሱስ ወደ ዮሐንስ መሄዱ በተዋሐደው ሥጋ ትኅትናን ገንዘብ በማድረግ ለሰው ልጅ አርአያና ምሳሌ ለመሆን ነው ይላሉ፤ እንደ ጌትነቱ ዮሐንስን ‘መጥተህ አጥምቀኝ’ ቢለው ኖሮ፥ የየዘመኑ ጌቶች ካህናቱን ‘መጥታችሁ አጥምቁን’ ባሉ ነበርና 'ሄዳችሁ ተጠመቁ' ለማለት ለአብነት ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ መጠመቁም፥ ውኃ በዙፋን ካለ ንጉስ በአደባባይ እስካለ ጽንስ ለሁሉም በቀላሉ የሚገኝ ስለሆነ ነው፤ ጥምቀትም መሠራቱ ለሁሉ ነውና፡፡ ውኃ ያነፃል፥ ጥምቀትም ያነፃል፣ ውኃ የወሰደው ፍለጋ የለውም(አይገኝም)፥ በጥምቀት የተሰረየ ኃጢአትም በፍዳ አይመረመርም፣ ሸክላ ሠሪ ቢነቃባት ከስክሳ አፍርሳ መልሳ በውኃ አርሳ ትሰራዋለች፥ ጥምቀትም ተሃድሶ ነፍስ ያስገኛልና ለዚህ ነው ይላሉ ሊቃውንቱ።
በመሆኑም በዓለ ጥምቀት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ለተጠመቁ ክርስቲያኖች ሁሉ በጥምቀት በሚገኝ ዳግም ልደት የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸው የተረጋገጠበት ስለሆነ የዳግማዊ ልደታቸው ክብረ በዓል አድርገው በደመቀና በላቀ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡
እግዚአብሔር ለእስራኤል ልጆች አወርሳችኋለሁ ብሎ ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድረ ርስት ሲጓዙ፥ በፊታቸው ያለውን የዮርዳኖስ ወንዝ በደህና ይሻገሩ ዘንድ ታቦተ ጽዮንን አስቀድመው ወንዙን እንዲያቋርጡ ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ካህናቱ ታቦቱን ይዘው ወደ ወንዙ ሲገቡ ውኃው ለሁለት ተከፍሎ በራሱ ኃይል ተከትሮ ቆሞላቸው ሕዝቡ በቀይ ባህር እንደሆነው በደረቁ መሬት ተሻግረዋል፡፡
የጥምቀት በዓል አከባበር ሥርዓት መነሻም ይሄው ነው፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም በበዓለ ጥምቀቱ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ያሉ ታቦታት በጣዕመ ዝማሬና በሆታ ታጅበው በባህረ ዮርዳኖስ አምሳል ወደሚዘጋጁት አብህርተ ምጥማቃት በተለምዶ ባህረ ጥምቀት ወርደው በማደርና በማግስቱ በመመለስ የሚከብሩበት በዓል ነው፡፡
የልጅነት ጥምቀት በኢትዮጵያውያን የተጀመረው በንግሥቷ ህንደኬ ጃንደረባ በ34 ዓ.ም እንደሆነ በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገበ ታሪክ ነው፡፡ የንግሥቲቱ ጃንደረባ ኢየሩሳሌምን ተሳልሞ ሲመለስ መጽሐፍ ሲያነብ ያገኘው ሐዋርያው ፊሊጶስ ስለ እግዚአብሔር ልጅነት አስተምሮት በጋዛ አጥምቆታል፡፡
እስከ 326 ዓ.ም ድረስ ሕዝቡ በዚሁ መንገድ ሲጠመቅ የቆየ ሲሆን በ326 ዓ.ም አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን/ፍሬምናጦስ/ ከእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ አትናትዮስ ጵጵስና ተቀብለው በመምጣት ሕዝበ ክርስቲያኑን ማጥመቅ እንደጀመሩ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይተርካሉ፡፡
በመላኩ የጥናት መፅሐፍ እንደተገለፀው የበዓለ ጥምቀት አከባበር በኢትዮጵያ የተጀመረው የክርስትና እምነት እንደተሰበከ መሆኑ ይታመናል፤ ታቦትን ወደ ጥምቀተ ባህር ማውረድ የተጀመረው ግን በ328 ዓ.ም በጣና ቂርቆስ እንደሆነ ይነገራል፡፡
አቡነ ፍሬምናጦስ ጣና ሐይቅ ላይ ሕዝቡን ሲያጠምቁ ውጭ ላይ ሆነው የቀደሱበት የድንጋይ መንበር፣ ሴቶችና ወንዶች የቆሙበት ምልክት ወደ ደንባዛ ቁስቋም መሄጃ መንገድ ላይ እንደሚገኝ የአራቱ ጉባኤያት ሊቅ የሆኑት ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ ያስረዳሉ፡፡ እስከ 6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ግን የጥምቀት በዓል አሁን በምናከብርበት ሁኔታ የሚከበር አልነበረም።
በዓለ ጥምቀትን በሜዳና በውኃ አካላት ዳር ማክበር የተጀመረው በዓፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግስት(ከ530-544 ዓ.ም) እንደሆነ ይነገራል። ለዚህም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ(ከ505-572 ዓ.ም) የደረሳቸው ዜማዎች መስፋፋት አስተዋጽኦ የነበረው ሲሆን ታቦታቱ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን ጠዋት ወደ ወንዝ ወርደው ማታ ወደ መንበረ ክብራቸው እንዲመለሱ ይደረግ ነበር።
ጻድቁና ጠቢቡ ንጉሥ ላሊበላም(ከ1140–1180 ዓ.ም) በዘመኑ ሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለየብቻቸው በሚቀርባቸው ቦታ በተናጠል ሲፈጽሙት የነበረውን አከባበር አስቀርቶ በአንድ አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት ተሰባስበው በአንድ ጥምቀተ ባሕር እንዲያከብሩ ትእዛዝ አስተላልፏል።
ይህም ተግባራዊ በመሆኑ የበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት ቅንጅትና ድምቀት እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በዘመኑ በምድረ ኢትዮጵያ በብሕትውናና በስብከተ ወንጌል ተግተው ያገለገሉት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም በትግራይና በጎጃም መርጡለማርያም አካባቢ እየተዘዋወሩ ባሕረ ጥምቀቱን ይባርኩ ነበር፡፡
ዐፄ ይኩኖ አምላክም(ከ1260-1275 ዓ.ም) በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አሳሳቢነት የተጀመረው የበዓል አከባበር ሥነ-ሥርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ታቦታቱም በሕዝብ ጥበቃና አጀብ ተደርጎላቸው በየጥምቀተ ባሕሩ እንዲያድሩ በዐዋጅ ወስነዋል።
የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ አድማሱን እያሰፋና ብሔራዊነትን እየያዘ መጣ። በመንፈሳዊነታቸውና በደራሲነታቸው የሚታወቁትና ብዙ መጻሕፍትን ጽፈው፣ ሥርዓትን ሠርተው ለቤተ ክርስቲያን ያበረከቱት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ(ከ1426-1460 ዓ.ም) ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ፣ በጥምቀት ዋዜማ ጥር 10 ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባህረ ጥምቀቱ ወርደው እንዲያድሩና ሀገሩን በኪደተ እግር ይባርኩም ዘንድ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ በዐዋጅ ወሰኑ።
ይህንኑ ፈለግ የተከተሉት ዐፄ ናዖድም (ከ1486-1500 ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ታቦተ ሕጉ ወደ ባህረ ጥምቀቱ በሚወርድበትና ከባህረ ጥምቀቱ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ አውርዶ፥ አጅቦ መመለስ እንዳለበት በዐዋጅ አስነግረው ነበር።
ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን በሆታና በእልልታ ከቤተ መቅደስ አጅቦ በማውጣት በባሕረ ጥምቀት ከትሞ አብሮ ማደርና ሊቃውንቱም እንዲሁ ለበዓሉ የሚስማማውን ቃለ እግዚአብሔር እያደረሱ ያድሩ ጀመር። በየጊዜው የነበሩ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እና በየዘመኑ የነገሡ ነገሥታትም አሁን ላለው ድምቀት የየራሳቸውን አሻራ ትተው አልፈዋል፡፡
ከቀደምት አበው የተላለፈውን እምነትና ሥርዓት ሳትለቅ የምትጓዘው ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህን የጥምቀት በዓል አከባበር ትውፊት ጠብቃ በመያዝና በማዳበር በየዓመቱ ጥር 11 ቀን እያደር እየጎላና እየደመቀ በሚመጣ የአከባበር ሥርዓት በበዓሉ ዕለት የተፈጸመውን ድርጊት በኅሊና በማሰብ ብቻ ሳይወሰን የበዓሉን ጥንተ ታሪክ በሚከስት ይዘትና ሁኔታ የረቀቀውን አጉልቶ በሚያሳይ ክንውንም ጭምር ማክበሯን ቀጥላለች።
ይህም የዓለምን ሕዝብ ዓይንና ጆሮ ወደ ሀገራችን እየሳበ የመጪው ዘመን የቱሪዝም መዳረሻነትን እየጋበዘ መጥቷል፡፡
በጥምቀት ዋዜማ - ከተራ በመላዋ ኢትዮጵያ በከተማና በገጠር ባሉ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ታቦታት ከመንበራቸው ተነሥተው ወደ ተዘጋጀው ባሕረ ጥምቀት በመውረድ በድንኳን ውስጥ ያድራሉ፡፡ በሚያድሩበት ባህረ ጥምቀት በሚዘጋጀው ድንኳን ውስጥ ማኅሌቱ ከደረሰ በኋላ በማለዳው ሥርዓተ ቅዳሴ ተከናውኖ ባሕረ ጥምቀቱ ይባረክና ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ በመጠመቅ የበዓሉን በረከት ይሳተፋል፡፡
በዓሉ ታቦታቱ ወደ የአብያተ ክርስቲያናቱ ተመልሰው በመንበራቸው ላይ እስኪያርፉ ድረስም ከሁለት ቀን በላይ በየባሕረ ጥምቀቱና በየመንገዱ ሁሉ በድምቀት የሚከበር ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን አበው በብሉይ ዘመን ኪዳነ ኦሪቱን በዚያው ሥርዓት ሲያከብሩ የቆዩ በመሆኑ፥ በዘመነ ሐዲስም በጥምቀት ሥርዓት ተክተው የአዲስ ኪዳኑን ታቦት በተንቆጠቆጠ መጎናጸፊያ ተሸክመው በዝግታ እየተራመዱ፣ ካህናቱ የተዋበ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ መስቀልና ጽንሐ ማዕጠንተ ወርቅ ይዘው፤ መብራት፣ ዣንጥላና ድባብ በያዙ ልዑካን ተከበው፤ በማኅሌታውያኑ ደብተራዎች ሀሌታ፣ በወጣት መዘምራን ምስጋና፣ በወንዶች ሆታና በሴቶች እልልታ ታጅበው ያከብሩታል፡፡
በመላኩ ጌታቸው ሀተታ መሰረት ሊቀ ነብያት ሙሴ የኪዳኑን ጽላት ከእግዚአብሔር ሲቀበል በሲና ተራራ ደመና ጋርዶት ነበርና ዛሬም ለታቦተ ሕጉ በደመናው ተምሳሌት ድባብ(ትልቅ ጃንጥላ) ይዘረጋል፡፡ ሕዝበ እስራኤልም ከግብጽ ወጥተው በበረሃው ወደ ምድረ ርስት ሲጓዙ የጸሐዩ ሐሩር እንዳይጎዳቸው ደመና ይጋረድላቸው ስለነበር በዚህ አብነት ሊቀውንተ ቤተ ክርስቲያን አባቶችም ክብር ስለሚገባቸው ድባብ ይዘረጋላቸዋል፡፡
ጥምቀትን የሚያጅበው ዘፈንና ጭፈራም ንጉስ ዳዊት ታቦተ ጽዮን ተረስታና ተጥላ ከነበረችበት አምጥቶ በኢየሩሳሌም ባዘጋጀላት ማረፊያ ድንኳን ሲያስገባት ልብሱን እስከመጣል ያደረሰውን ደስታውን የሚያስታውስ ነው፡፡
በጥምቀት ዘፈኑና ጨዋታውም ቢሆን ምስጋና ነው፤ በጌታ መገለጥ ለተገኘው ድኅነት ደስታን ለመግለጥ ነው፡፡ በውዳሴው የሚነሳሱትም ቤተ ክርስቲያን፣ ቅዱሳን፣ ሀገርና ጀግኖች ናቸው፡፡
የጥምቀት በዓል በመላው ኢትዮጵያና በውጭ ሀገራት ባሉ በሁሉም አህጉረ ስብከቶች እጅግ በደመቀ ሁኔታ የሚከበርና አከባበሩም አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ይዘት ያለው ቢሆንም እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ግን ታሪካዊና ባህላዊ መነሻ ኖሮት በተለየ የአከባበር ገጽታ በተለየ ቀለምና መልክ የሚከበርባቸው ባህረ ጥምቀቶች አሉ፡፡
ከእነዚህ ባህረ ጥምቀቶች በተለየ የሚጠቀሱት በጎንደር የዐፄ ፋሲል መዋኛ፣ የአዲስ አበባው ጃንሜዳ/የጃንሆይ ሜዳ፣ በሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ፍርድ መስጫ አደባባይና አርባ አራት ታቦታት የሚያድሩበት የምንጃሩ ሸንኮራ ወንዝ ኢራንቡቲ፣ የቅዱስ ላሊበላ እንዲሁም በአክሱም የንግሥተ ሳባ መዋኛ የነበረው ‘ማይ ሹም’ ዋና ዋናዎቹ የነበሩ ሲሆን የባህር ዳሩ የጣና ዳርቻ፣ የዝዋይ ደሴቶች፣ የጋምቤላው የባሮ ወንዝ ዳርቻ እና ሌሎቹም ጥምቀተ ባሕሮች ቀጣይ መስሕቦችና መዳረሻዎች መደመሆኑ እየተሰናዘሩ መምጣታቸው ጥምቀት ከነበረው በላቀ ሀገራዊ ድምቀት እየተከበረ ለመምጣቱ ማሳያዎች ናቸው።
ለማሳያነትም፡-
የጥምቀት በዓል በጎንደር
በጎንደር ታቦታትን ወደ ባሕር ማውረድ የተጀመረው በቀዳሚ አድባራት ቀሃ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቀሃ ኢየሱስ ዐፄ ፋሲለደስ ጎንደርን ከመመስረታቸው በፊት በባላባቶች በቀሃ ወንዝ ዳርቻ እንደተተከለ ይነገራል፡፡ በዚሁ የቀሃ ወንዝ ዳርቻም ድንኳን እየተተከለ የጥምቀት በዓል ይከበር ነበር፡፡
በኋላም ዐፄ ፋሲል ጎንደርን መስርተው መንግሥታቸውን ካደላደሉ በኋላ 7 አብያተ ክርስቲያናትን ተክለው በቀሃ ወንዝ ዳርቻ ማክበሩን የቀጠሉበት ሲሆን ታሪኩን ለመጠበቅም በቦታው የጥምቀቱን ግንብና ታቦት ማደሪያ አስገንብተው አጽንተውታል፤ ወደ መጠመቂያው የሚገባውም ውኃ ከዚሁ ከቀሃ ወንዝ የተሳበ ነው፡፡
የጎንደር ጥምቀት ከዐፄ ፋሲለደስ ዘመን ጀምሮ በደማቁ የሚከበር በዓል ለመሆን የበቃው ዐፄ ፋሲል በበዓሉ ላይ የሚገኙትን ሊቃውንትና ምዕመናን በቤተ መንግሥታቸው ከፍተኛ ግብር ጥለው ይጋብዙ ነበርና ሕዝቡ ከሩቅና ከቅርብ እየመጣ ማክበር በመልመዱ ሲሆን በ7ቱ ምዕራፋት የሚቀርበው ቃለ እግዚአብሔር ድምቀትም ሌላው ምክንያት ነው፡፡
ሊቃውንቱ በነዚህ ምዕራፋት አገልግሎት ለመሳተፍ ከሩቅና ከቅርብ ይሰባሰባሉ፡፡ በርካታ የመንፈሳዊ ትምህርት ማስመስከሪያ ትምህርት ቤቶች በጎንደር መኖራቸውና በእነዚህም ብዙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ መሆኑም ለበዓሉ ድምቀት የራሱ የሆነ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲኖረው አድርጓል፡፡
በተለምዶ “አርባ አራቱ ታቦት” የጎንደር መገለጫ ቢሆንም በጥምቀት በዓል ወደ ፋሲለደስ መጠመቂያ ግንብ የሚወርዱት መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም፣ አጣጣሚ ሚካኤል፣ እልፍኝ ጊዮርጊስና አባጃሌ ተክለ ሃይማኖት፣ ቀሃ ኢየሱስ፣ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ፣ ፊት ሚካኤልና ቅዱስ ፋሲለደስ ብቻ ናቸው፡፡
ይህም የሆነው የቦታ ጥበት እንዳይኖር በማሰብ ዐፄ ፋሲለደስና ሊቃውንቱ ተመካክረው በዓለ ጥምቀቱን ተምሳሌታዊ በሆነ መልኩ እንዲገልጽ በማድረግ ቀሃ ኢየሱስና መንበረ መንግስት መድኃኔዓለም ተጠማቂውን ኢየሱስ ክርስቶስን በማስመልከት፣ እልፍኝ ጊዮርጊስ ከሰማዕታት ወገን፣ አጣጣሚ ሚካኤልና ፊት ሚካኤል ከመላዕክት ወገን፣ አባጃሌ ተክለ ሃይማኖትና ቅዱስ ፋሲለደስ ከጻድቃን ቅዱሳን ወገን እንዲሁም አጥማቂው ደብረ ጽጌ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ በምዕመናን ታጅበው ወደ ባህረ ጥምቀቱ ይወርዳሉ፡፡
አባጃሌ ተክለ ሃይማኖትና አጣጣሚ ሚካኤል ከዐፄ ፋሲል በኋላ በነገሡ ነገሥታት የተተከሉ ሲሆን በዘመኑ ሊቃውንት ወደ ሥርዓቱ እንደተካተቱ ይነገራል፡፡
የጥምቀት በዓል በጃንሜዳ
በአዲስ አበባ በዓለ ጥምቀት በጃን ሜዳ መከበር የጀመረው በ1887 ዓ.ም ነው፤ “ጃን ሜዳ” ጃንሆይ ሜዳ ወይም ጃኖ ከሚለው ቃል ጋር ተናቦ የሚነገር ነው፡፡ የቀድሞ ነገሥታት ለመሾምም ሆነ ለመሻር፣ ዳኝነት ለማየት፣ ለሊቃውንቱ ማዕረግ ለመስጠት እንዲሁም አዋጅ ሲያስነግሩ በቤተ መንግሥቱ አቅራቢያ የሚገኝ ሰፊ ሜዳን ይጠቀማሉ፡፡
ይህ ሜዳ ለመንግሥታዊ አገልግሎት በመዋሉ ምክንያት ጃንሆይ ሜዳ በመባል ይጠራል፡፡ ነገሥታቱ በሜዳው ማዕከላዊ ቦታ ጃኖ(ቀይ) ድንኳን አስተክለው በመቀመጥ መኳንንቱ ከበው የተፈለገውን ሥርዓት ያከናውናሉ፡፡ በዚህም ከጃኖው ድንኳን ጋር በተያያዘም ጃን ሜዳ ይባላል፡፡
በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ጃንሜዳ ከመንግሥታዊ ሥራ ይልቅ አድመኛና መሀል ሰፋሪ እየተሰበሰበ የሚዶልትበትና ነገር የሚሠራበት መሆኑ ያስቆጫቸው እቴጌ ጣይቱ ቦታው የክፉ ምክር መምከሪያ ሆኖ ከሚቀር ታቦት ማደሪያ ቢሆን ብለው ለዐፄ ምኒልክ ሃሳብ በማቅረባቸው የጥምቀት ማክበሪያ እንዲሆን በአዋጅ አጽንተውታል፡፡
ባህረ ጥምቀቱ ደግሞ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በ1936 ዓ.ም ተሰርቷል፡፡
የጥምቀት በዓል በምንጃር ሸንኮራ
በሰሜን ሸዋ ምንጃር የሸንኮራ ወንዝ ዳርቻ ኢራንቡቲ 44 ታቦታት በአንድነት የሚያድሩበት ልዩ ጥምቀተ ባህር ነው፡፡ ይህ ቦታ መስቀሉን ከግብጾች የተቀበሉት ደገኛው ንጉሥ ዐፄ ዳዊት ያሠሩት ታሪካዊው በሳ ሚካኤል፣ ጥንታዊውን የባልጪ አማኑኤልና ታዋቂውን ሸንኮራ ዮሐንስን ጨምሮ የሌሎች ዕድሜ ጠገብ አድባራትን ታቦታት በአንድነት የሚያስተናግድና ዘመናትን ካስቆጠሩ ቀደምት ጥምቀተ ባሕሮች አንዱ ሲሆን ከዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ አባት ዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት መጨረሻ ጀምሮ ዘንድሮ 623ኛ ዓመቱን የጥምቀት በዓል የሚያከብር ጥንታዊ ጥምቀተ ባህር ነው፡፡
የአካባቢው ሕዝብም ታቦታቱን በሆታና በእልልታ አጅቦ ከማክበር ጋር ያለፈ ያገደመውን በመጋበዝና በማስተናገድ ድንቅ ክርስቲያናዊና ትውፊታዊ ባህሉን የሚያሳይበት የአደባባይ በዓሉ ነው፡፡
ቀደምት አበው ይህን የሸንኮራ ወንዝ ዳርቻ ለባህረ ጥምቀትነት የመረጡበትን ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ማምራቱን በማሰብ ተፈጥሮአዊ ወንዝ ፍለጋ እንደሆነ የአካባቢው የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ይናገራሉ፡፡
የሸንኮራ ወንዝ ዳርቻው ጥምቀተ ባህር፥ ወንዙ እንደ ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ አንድ ሆኖ መሀል ላይ ለሁለት ተከፍሎ ዝቅ ብሎ የሚገናኝ፣ ውኃውም ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ የሚፈስ መሆኑና ከመነሻው ጀምሮ የ44ቱም ታቦታት ጸበል መኖሩ ለጥምቀቱ ያለውን ተምሳሌትነት ከፍ ያደርገዋል ይላሉ፡፡
ቦታው በዐፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት በሀገራችን ኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል በደመቀ ሁኔታ ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱና ዋነኛው እንደነበረም ያወሳሉ፡፡
የጥምቀት በዓል በላሊበላ
ቅዱስ ላሊበላ ከውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ ጋር ባህረ ጥምቀቱንም አብሮ አንጾ ዮርዳኖስ ብሎ ሰይሞት እስካሁንም በዚህ ስም ይጠራል፡፡ የአካባቢው አባቶች እንደሚገልጹት በቀደመው ጊዜ ጥምቀተ ባሕሩ መንታ ውኃዎች ማለትም ‘ዮር’ እና ‘ዳኖስ’ የሚባሉ ወንዞች በሚገናኙበት ዮርዳኖስ በሚባል ቦታ ነበር የሚከበረው፤ ከጊዜ በኋላ ግን ቦታው በመራቁ በዕድሜ የገፉ ሰዎችም ለመሄድ እየተቸገሩ ስለመጡ ቀረብ ካለ ሜዳ ላይ ውኃ እየተከተረ ሥርዓተ ጥምቀቱ ይከናወናል፡፡
ወደ ቁራቁርና ሽንብርማ በሚወስደው መስቀለኛ መንገድ ገጠርጌ ላይ ታቦታቱ ከየመጡበት ተገናኝተው ወደ ጥምቀተ ባሕሩ ይገባሉ፡፡ ታቦታቱ ወደ ማደሪያቸው ከገቡ በኋላ የአስራ አንዱም አብያተ ክርስቲያናት ቄሰ ገበዞች ድንኳን ጥለው ባዘጋጁት ድግስ የመጣውን ሁሉ ያስተናግዳሉ፡፡
የበዓሉ ዕለት እንደሌላው አካባቢ ስብሐተ እግዚአብሔር በሰባት ምዕራፋት እየደረሰ ታቦታቱ በከፍተኛ አጀብና ድምቀት ወደመንበረ ክብራቸው ይገባሉ፡፡
የጥምቀት በዓል በአክሱም
በአክሱም ማይ ሹም/የሹም ውኃ እየተባለ የሚጠራው ግድብ ከንግሥተ ሳባ ጊዜ ጀምሮ ለመጠጥ ውኃ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን አክሱማውያኑም የጥምቀቱን ሥርዓት በዚሁ የውኃ ግድብ በመሰባሰብ ማክበር እንደጀመሩ ይነገራል፡፡
የጥምቀት በዓል በዝዋይ ሐይቅ ደሴት
ዓመታዊው የጥምቀት በዓል ከተከበረባቸው ቦታዎች መካከል በዝዋይ ሐይቅ ውስጥ የሚገኙት ገዳማት ይጠቀሳሉ፡፡ ከአዲስ አበባ 161 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ዝዋይ (ባቱ) ከተማ ዳርቻ፣ ባለው ሐይቅ የሚገኙት አቡነ ተክለሃይማኖት፣ ቅዱስ ሚካኤል፣ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም፣ አርባዕቱ እንስሳትና ፀዴቻ አቡነ አብርሃም ገዳማት ጥር 10 እና 11፣ 2009 ዓ.ም. በዓሉን አክብረዋል፡፡ ከአምስቱ ገዳማት አቡነ ተክለሃይማኖትና ደብረ ጽዮን ከደሴታቸው በመውጣት ሦስት ኪሎ ሜትር የሚሆነውን የሐይቁን ክፍል አቋርጠው ምድር ላይ በማክበር ብቸኛ ያደርጋቸዋል፡፡ የተቀሩት ሦስቱ ደግሞ ከሐይቁ ዳር በጣም የራቁ በመሆናቸው ከቤተ መቅደሳቸው በመውጣት በግቢያቸው የሐይቁ ጠርዝ ላይ ድንኳን በመጣል እዚያው ያከብራሉ፡፡
መልካም በዓል ለሚያከብሩ ሁሉ!
++++++++++++++++++
++++++++++++++++++
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]
No comments:
Post a Comment