ከደራሲያን ዓምባ

Tuesday, August 25, 2015

ታላቁ ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን ከ1925-1979

ከ1925-1979 ዓ. ም.
==============
ኢትዮጵያ ውስጥ በ1925 ዓ.ም አንድ ታላቅ ሰው ተወለደ። ይህ ሰው እያደገ ሲመጣ የብዙ ሚሊዮን ህዝቦችን ታሪክ፣ ባህል፣ እምነትና አስተሳሰብ የሚገልፅ ደራሲ ለመሆንም በቃ። ብዕሩ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ላይ በሰፊው ያተኩራል። የዚህችን ሀገር ታላላቅ ጀግኖች ታሪክ እያነበበ እና እየመረመረ ለትውልድና ለእናት ምድራቸው ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ውበትና ለዛ ባላቸው የገለፃ ጥበቦቹ እየፃፈ የሚሊዮኖችን መንፈስ ሲያረካ ኖሯል። ኢትዮጵያም ታላላቅ ደራሲዎቿን ማነሳሳት ስትጀምር ስሙ እና ተግባሩ ከፊት ከሚሰለፉት የብዕር አርበኞች መካከል ያደርገዋል። አንዳንድ ሃያሲያን ደግሞ የተዋጣለት የድርሰት ገበሬ ነው ይሉታል። በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ ለዘላለም እንደ ከዋክብት ሲያበሩ ከሚኖሩት ደራሲያን እና ፀሐፊ- ተውኔቶች ውስጥ ታላቁን የሊትሬቸር ሰው ብርሃኑ ዘሪሁንን በጥቂቱ አነሳሳላችኋለሁ።
ብርሃኑ ዘሪሁን የተወለደው ድሮ የበጌምድር ጠቅላይ ግዛት ርዕሰ ከተማ በሆነችው እና በተለይም የ17ኛው እና የ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የስልጣኔ ማዕከል እንደነበረች በሚገለፅበት በሰሜናዊቷ ክፍለ -ግዛት በጎንደር ከተማ ነው። ዘመኑም 1925 ዓ.ም ነበር። አባቱ መሪ ጌታ ዘሪሁን መርሻ የሚባሉ ሲሆን እናቱ ደግሞ ወ/ሮ አልጣሽ አድገህ ይባላሉ። አባቱ መሪ ጌታ ዘሪሁን የቤተ-ክህነት ሰው ስለነበሩ እና በዘመናቸውም የተማሩ ስለሆኑ ለልጃቸው ትምህርት የሚጨነቁ ነበሩ። እናም አራት ዓመት ሲሆነው እቤት ውስጥ ከርሳቸው ዘንድ የሚማረው ትምህርት ተጨምሮ የቤተ-ክህነትን ትምህርት ተማረ።
ብርሃኑ ዘሪሁን ጎንደር ውስጥ የሚሰጠውን የቤተ-ክህነት ትምህርት ከተከታተለ በኋላ ወደ ዘመናዊ ት/ቤት ገባ። ይህ ዘመናዊ ት/ቤት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ት/ቤት በመባል ይጠራ ነበር። ብርሃኑ ዘሪሁን የሀገሩ ኢትዮጵያን ባህላዊ፣ ታሪካዊና ኃይማኖታዊ ትምህርቶችን በቤተ-ክህነት ውስጥ ከተከታተለ በኋላ ወደ ዘመናዊ ት/ቤት ሲገባ ልዩ ተሰጥኦው ብቅ አለ። ይህም አንባቢነት ነው። ፈረንጆቹ “Book Worm” እንደሚሉት መፅሐፍን የሚያነብ ብቻ ሳይሆን እንደ ምግብም የሚጠቀምባቸው አይነት ሰው እንደነበር የህይወት ታሪኩ ያወሳል።
ብርሃኑ ዘሪሁንን ቀልቡን ከሚከቡት ታሪኮች መካከል ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው። ኢትዮጵያን በመፃህፍቶቿ አማካይነት እያነበባት አወቃት። እርሱ ያልነበረበትን ዘመን በሰፊ ንባቡ እና ጠያቂነቱ የማንነቱን ክፍተት ሞላው። እናም ሙሉ ኢትዮጵያዊ እየሆነ መምጣት ጀመረ።
የብርሃኑ ዘሪሁንን ቀልብ ከሳቡት ታላላቅ መፃህፍት ውስጥ ደብተራ ዘነብ የፃፏቸው ታሪኮች ናቸው። አንደኛው የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክን የሚያወጣው መፅሀፍ ነው። ደብተራ ዘነብ በቴዎድሮስ ቤተ-መንግስት ውስጥ የነበሩ እና ከቴዎድሮስ ጎን የማይጠፉ የዚያን ዘመን ሊቅ ብሎም ፈላስፋ ናቸው። ታዲያ እርሳቸው የፃፉትን የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ብርሃኑ ዘሪሁን ይወደው ነበር። ከዚህ መፅሀፍ በተጨማሪም ደብተራ ዘነብ “መፅሀፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሳዊ” የተሰኘች መፅሐፍ አለቻቸው። ይህች መፅሃፍ ሃይማኖት ላይ መሰረት አድርጋ የተዘጋጀት ከኢትዮጵያ የፍልስፍና ጽሁፎች መካከል አንዷ ናት። ብርሃኑ ዘሪሁን ይህችን መፅሀፍ የመፅሀፎች ሁሉ ቁንጮ አድርጓት በየጊዜው ያነባት ነበር። በነገራችን ላይ ይህች መፅሃፍ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሳዊ በውስጧ ምን ቢኖር እንዲህ የተወደደችው ለሚል ሰው ሁለቱን ነጥቦች ብቻ ጠቅሼ ልለፍ።
መፅሃፏ በዋናነት አላማዋ ሃይማኖትን ማስተማር ቢሆንም፣ የተጻፈችበት ቴክኒክ ግን ፍፁም በተለየ አቀራረብ ነው። ለምሳሌ ፈጣሪን የምትወቅስ እየመሰለች የፈጣሪን ታላቅነት የምታስተምር ናት። እንዲህ የሚል ሃሳብ አለባት “እየሱስ ስራብ አላበላችሁኝም፣ ስጠማ አላጠጣችሁኝም፣ ስታረዝ አላለባሰችሁኝም ይለናል። ለመሆኑ ከርሱ የበለጠ ሃብታም አለ ወይ? ለምን ይጨቀጭቀናል. . .” እያሉ ደብተራ ዘነብ ጽፈዋል። የደብተራ ዘነብ አፃፃፍ በዚህ ብቻም አያቆምም። እንዲህም የሚል ሃሳብ ያንፀባርቃል። “እንደ አይሁድ ጅል አላየሁም” የአለሙን ጌታ በ30 ዲናር ሸጠው። ወየሁ እኔ ባገኘሁት” እያለ ከተለመደው የስብከት መንገድ ወጥቶ ሌላ የአፃፃፍ እና የአተያይ መንገድ የከፈተ መጽሐፍ ነው። ብርሃኑ ዘሪሁን ደብተራ ዘነበን አእምሮው የተሳለ ፈላስፋ ይላቸው ነበር። እናም ደብተራ ዘነብ የብርሃኑ ዘሪሁንን አእምሮ ገና በልጅነቱ ስለውለታል ማለት ይቻላል።
በነገራችን ላይ ደብተራ ዘነብ የአፄ ቴዎድሮስን ልጅ ልዑል አለማየሁን በቤት ውስጥ የሚያስተምሩ መምህርም ነበሩ።
ብርሃኑ ዘሪሁን በንባብ ልምዱ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ከሚላቸው መካከል ነጋድራስ /ፕሮፌሰር/ አፈወርቅ ገ/እየሱስን ነው። እርሳቸውም በኢትዮጵያ የታሪክ እና የልቦለስ ጽሁፍ ውስጥ ከከፍተኛ ተዕዕኖ ፈጣሪ በመሆናቸው የብርሃኑ ዘሪሁንን የልጅነት እውቀት በመፃፍቶቻቸው አስፍተውለታል። የነ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ስላሴ እና የክብር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል መፃህፍት ኢትዮጵያዊ እውቀቱን በከፍተኛ ደረጃ እንዳጎለመሱለት ይነገራል።
ብርሃኑ ዘሪሁን በ1945 ዓ.ም ላይ ብዙ እውቀቶችን ከገበየበት ጎንደር ከተማ ተነስቶ አዲስ አበባ መጣ። በአዲስ አበባም ቆይታው ተግባረ ዕድ ት/ቤት ገብቶ የሬዲዮ ቴክኒሻንነት በመማር በ1948 ዓ.ም ላይ በዲፕሎማ ተመረቀ። ታዲያ በዚያ በምረቃ ወቅት ከተማሪዎቹ ሁሉ አንደኛ ወጥቶ ተሸላሚ የነበረው ብርሃኑ ዘሪሁን ነው።
ብርሃኑ ዘሪሁን ተግባረ ዕድ ት/ቤት ሲማር የታላላቅ የአለማችንን ደራሲያን ስራዎችን ለማንበብ ዕድሉን አገኘ፡ የነ ዊሊያም ሼክስፒርን፣ የአሌክሳንደር ዱማስ ፔሬን፣ የቻርልስ ዲክነስን፣ የነ አሌክሳንደር ፑሽኪንን እና የሌሎችንም መፃህፍት አነበበ። እውቀቱንም እያስፋፋ መጣ። በንባብ የተከማቸው እውቀቱም በፅሁፍ መውጣት ጀመረ። እዚያው ተግባር-ዕድ ት/ቤ ሲማር የት/ቤቱ ልሳን የነበረችውን “ቴክኒ-ኤኮ” የምትሰኘውን መፅሄት አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል። ከዚህ በተጨማሪም እዚያው ተማሪ ሳለ በ1947 ዓ.ም ተውኔት ጽፎም አሳይቷል። እናም እንግዲህ በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ሊወስድ ብርሃኑ ዘሪሁን የሚባል ብዕረኛ ወደ አደባባይ ብቅ ማለት ጀመረ።
ብርሃኑ ዘሪሁን ተግባረ ዕድ ውስጥ ውጤቱ ከፍተኛ ስለነበር እዚያው ት/ቤት ውስጥ ተቀጠረ። ከት/ቤቱ ውስጥም ሆኖ ለተለያዩ ጋዜጦች ይፅፍ ነበር። ከተግባረ ዕድ ት/ቤት በመልቀቅ በወቅቱ አጠራር የጦር ሚኒስቴር በአሁኑ መከላከያ ሚኒስቴር በሚባለው መስሪያ ቤት በአስተርጓሚነት ተቀጥሮ መስራት ጀመረ። እዚያም ብዙ ሳይሰራ 1952 ዓ.ም ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተዘዋወረ።
ብርሃኑ ዘሪሁን ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ወዲያው “የኢትዮጵያ ድምጽ” ተብሎ በሚታወቀው ጋዜጣ ላይ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሰራ። ታዲያ በዚህ ወቅት ጋዜጣዋን ታዋቂ ከማድረጉም በላይ በብዙዎች ዘንድ የሚነበቡ መጣጥፎችን እና ታሪኮችን በመፃፍ ዝነኛ እየሆነ መጣ። ቀጥሎም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ተዘዋወረ። ብርሃኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያዊያን አንባቢያን ልብውስጥ ሰተት ብሎ ገባ። በአንድ ጊዜ ስሙ እና ዝናው እየናኘ መጣ።
ብርሃኑ ዘሪሁን በድርሰት ዓለም ውስጥ በተለይ በ1958 ዓ.ም አዲስ የታሪክ አብዮት ማቀጣጠል ጀመረ። “የቴዎድሮስ ዕንባ” የሚሰኝ መፅሐፍ አሳተመ። መፅሀፉ የአፄ ቴዎድሮስን አነሳስ እና ለኢትዮጵያ ያላቸውን ርዕይ ብሎም የመጨረሻውን የህይወት ፍፃሜ የሚያሳይ ነበር። በወቅቱ ማለትም ብርሃኑ ይህን መፅሀፍ ከማዘጋጀቱ በፊት የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ በጭካኔያቸው ላይ ተመስርቶ ብቻ የሚዘጋጅ በመሆኑ የቴዎድሮስን ውስጣዊ ስብዕና ያን ያህል ጎልቶ አይነገርም ነበር። እናም ብርሃኑ ዘሪሁን አፄ ቴዎድሮስ ብሔራዊ ጀግና መሆናቸውን የሚገልፅ ድርሰት ፅፎ በማቅረቡ በዘመኑ በጣም ታዋቂ ሆነ። ይህን “የቴዎድሮስ ዕንባ” የተሰኘውን ታሪክ መስፍን አለማየሁ ወደ መድረክ ቀይሮት በኢትዮጵያ የቴአትር አለም ውስጥም ከታላላቅ ቴአትሮቹ ተርታ የሚሰለፍ አድርጎታል።
በቴአትሩ ውስጥ የእንግሊዙ ቆንሲል አፄ ቴዎድሮስን እንዲህ ይላቸዋል “ጃንሆይ እኔ ተልኬ የመጣሁት ከታላቋ የብሪታኒያ የጦር ጀነራል ከናፒር ዘንድ ነው” ይላቸዋል።
ቴዎድሮስም “እና ምን ይዘህ መጣህ” አሉት።
መልዕክተኞች “ጃንሆይ ጦርነቱ እየከፋ ስለመጣ በሰላም እጅዎን ለታላቋ የብሪታኒያ መንግስት እንዲሰጡ ነው። እጅዎን በሰላም ከሰጡ የእንግሊዝ መንግስት በእንክብካቤ ይይዝዎታል” ይላቸዋል።
ቴዎድሮስም “ኧ ኧ ኧ ኧ ብለው የምፀት ሳቅ ከሳቁ በኋላ “ስማ! እኔ እንደ ፈረንጅ ጅል አላየሁም! መንጋ መሳፍንት እና መኳንንት ያንቀጠቀጠ ነበልባል እጄን ልያዘው አለ? የሚፋጅ የእሳት አሎሎ ነው በለው! ደግሞ . . . እጅህን ብትሰጥ በክብር ትያዛለህ ይለኛል። በየት አገር ነው እስረኛ በክብር የሚያዘው? ወይስ በሌላ የአፍሪካ ሀገር እንደለመዱት እኔን እስረኛ አድርገው ሀገሬ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ሊይዙ? እኔ እንደሁ ህይወቴ እያለች ሀገሬ ኢትዮጵያን ከጥቁር ዘራፊ አውጥቼ ለነጭ ዘራፊ አልሰጥም ብሎሃል በለው! ሂድ ንገረው! ውጣ!” እያሉ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር የሚገልፁበት ታሪካዊ ተውኔት ነው።
አፄ ቴዎድሮስ ወታደሮቻቸውን ሁሉ ከነ መሳሪያቸው ካሰናበቱ በኋላ ራሳቸውን ሊያጠፉ በሚወስኑበት ወቅት ባለቤታቸው እቴጌ ጥሩወርቅ እንዲህ አሏቸው።
“ኧረ በአማየሁ፣ በአለማየሁ ይሄን ሃሳብዎን ይተው!” ይሏቸዋል።
ቴዎድሮስም፡- “ለአለማየሁ ምንም የማወርሰው ነገር የለኝም። ብቻ ሲያድግ አባትህ አንዲት ኢትዮጵያ በአይኑ እንደዞረች ሞተ ብለሽ ንገሪው”
በእንዲህ አይነት ሀገራዊ ፍቅር የታጀቡት የብርሃኑ ዘሪሁን የአፃፃፍ ቴክኒኮች ዘመን ሰበር ታሪኮች ሆነው ዛሬም እናወጋቸዋለን።
ብርሃኑ ዘሪሁን በድርሰት ዓለም ውስጥ ሲያዥጎደጉዳቸው ከነበሩት መፃሐፍት መካከል በ1961 ዓ.ም “የእንባ ደብዳቤዎች” በሚል ርዕስ ያሳተመው በሰፊው የተነበበለት ሲሆን ከዚያም በመለጠቅ “ድል ከሞት በኋላ ነው” የሚለውም መፅሐፉ እንዲሁ በወቅቱ ይቀነቀን የነበረውን ተራማጅ እንቅስቃሴ የሚያቀጣጥል ነበር። “የበደል ፍፃሜ” እንዲሁም “ጨረቃ ስትወጣ” የተሰኙትም መፅሐፍቶቹ በኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍ ውስጥ የብርሃኑ ዘሪሁንን ስም እናማንነት እየገነቡ የመጡ ስራዎቹ ናቸው። ብርአምባር ሰበረልዎ የተሰኘው መፅሐፉም ታትማ ስትወጣ አምራች ደራሲነቱን /Productive Author/ የሚል ቅፅል አሰጥታዋለች።
በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሶስት ተከታታይ የሆኑ መፃሐፍትን በማሳተም ረገድ ብርሃኑ ዘሪሁን በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ አለም ውስጥ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ይጠቀሳል። በ1970ዎቹ ውስጥ ብርሃኑ ዘሪሁንን በሥነ-ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ስሙ እንዲነሳለት ያደረጉት እነዚህ ሶስት መፅህፍቶቹ “ማዕበል የአብዮቱ ዋዜማ”፣ “ማዕበል የአብዮቱ መባቻ” እና “ማዕበል የአብዮቱ ማግስት” ይሰኛሉ። መፅሐፎቹ በአንድ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ወሎ ውስጥ ተከስቶ በነበረው የረሃብና የድርቅ አደጋ ላይ ተመስርቶ የፃፋቸው ውብ መፅሀፎቹ ናቸው። እንዲህ አይነት ሶስት መፃህፍትን ፈረንጆቹ /Trilogy/ ይሏቸዋል። እናም በኛ ሀገር ደግሞ “ስልስ ድጉስ” ብለው የተረጎሙት ሰዎች አሉ። ብርሃኑ ዘሪሁን የስልስ ድጉስ መፃሐፍትም ደራሲ ነው።
ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በኢትዮጵያዊያን የመፃህፍት አንባቢያን ዘንድ በእጅጉ የተወደደውን እና በተደጋጋሚ የታተመውን መጽሐፍ በ1978 ዓ.ም አሳተመ። መፅሀፉ “የታንጉት ምስጢር” ይሰኛል። በአፄ ቴዎድሮ ዘመድ በታንጉት እና በቴዎድሮስ የጦር አበጋዝ በሆነው በፊታውራሪ ገብርዬ ጎሹ መካከል ያለውን ፍቅር እና የዘመኑን ታሪክ የፃፈበት ውብ ድርሰት ነው። ሶስቱን ማዕበሎች እና የታንጉት ምስጢርን በኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ ድንቅየው ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ በመተረኩ ከህዝብ አእምሮ እና ልቦና ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።
ብርሃኑ ዘሪሁን ከደራሲነቱ ባሻገር ፀሐፊ-ተውኔት ነው። የቴአትር ፅሁፎችን በማዘጋጀት እና በኢትዮጵያ መድረክ ላይ ግዙፍ ሰብዕና የሰጡትን ስራዎች አቅርቧል። ከቴዎድሮስ እንባ በኋላ በ1972 ዓ.ም “ሞረሽ” የተሰኘ ተውኔት በብሔራዊ ቴአትር ቤት አቅርቧል። በ1975 ዓ.ም ደግሞ “ጣጠኛው ተዋናይ” የተሰኘ ተውኔት በሐገር ፍቅር ቴአትር ቤት አቅርቧል። በ1976 ደግሞ “የለውጥ አርበኞች” የተሰኘ ተውኔት ጽፏል። በኢትዮጵያ የታሪክ ተውኔቶች አለም ውስጥ በዘመን አይሽሬነታቸው ከሚጠቀሱት ቴአትሮች መካከል “ባልቻ አባነፍሶ” የተሰኘው ቴአትር ነው። ይህን ቴአትር በ1977 ዓ.ም የፃፈው ይኸው ጎምቱ ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን ነው።
ብርሃኑ ዘሪሁን ከደራሲነቱ እና ከፀሐፊ ቴውኔትነቱ ባሻገር ሃያሲም ነበር። የተለያዩ ደራሲያንን ስራዎችን ፅሁፎችን እየተከታተለ ሂሳዊ መጣጥፎችን ያቀርብ ነበር። ከዚህ በላይ ደግሞ የተዋጣለት ጋዜጠኛ ሆኖ በዘመኑ በብዕሩ የናኘ ስብዕና የተጎናፀፈ ሰው ነበር።
     ይህ የድርስት ገበሬ ስራዎቹ በበርካታ የስነ-ጽሁፍ እና የታሪክ ተመራማሪ በሆኑ ምሁራን ጥናት ተደርጎባቸዋል። የዩኒቨርስቲ የመመረቂያ ጽሁፎችም ሆነው በርካቶችን አስመርቀዋል። ሞልሸር የተባለው የኖርዌይ ዜጋ እና የኢትዮጵያን ደራሲዎች ታሪክ Black lions በሚል ርዕስ የፃፍው ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁንን ከኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን ተርታ ያስቀምጠዋል። ብርሃኑ ዘሪሁን ተግቶ በማንበቡ እና በመመራመሩ በኢትዮጵያ ሥነ -ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ለትውልድ ውለታ ውለው ካለፉ ጥበበኞች መካከል አንዱ ሆኖ ይጠራል። ሀገርን እና ትውልድን በብዕሩ ቀለማት ሲዘክር የኖረው ይህ ሰው ሚያዚያ 16 ቀን 1979 ዓ.ም በ54 ዓመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ። ቀብሩም በባለወልድ ቤተ-ክርስቲያን ተፈፀመ። ዛሬ በአፀደ ስጋ ከኛ ጋር ባይኖርም ስራዎቹ ግን ዘመንን እየተሻገሩ ገና ወደፊትም ስሙን ያስጠሩታል።

ምንጭ:--በጥበቡ በለጠ ___http://www.sendeknewspaper.com/arts-sendek/item/559
****************************************************************************************************



ብርሃኑ ዘሪሁን እና “ድል ከሞት በኋላ”

**** ******************** ****

ባዩልኝ አያሌው 

  የአንዳንድ ፀሐፍቶቻችንን ብርታትና ትጋት፣ በዚህም ያበረከቱልንን ረብ ያላቸው ፍሬዎቻቸውን ሳስብ በመደነቅ ውስጤ ይሞላል፡፡ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ እነዚህ ጠቢባንና ስራዎቻቸው እውቅና እና ትኩረት ማጣታቸውን ሳስብ ልቤ በቁጭት ይጨመቃል፡፡ እናም “እድል እና ቲፎዞ አቦ ላትመለሱ እንጦሮንጦስ ውረዱ!” ብዬ እራገማለሁ። የፀሐፊ ክፍያው መነበብ በመሆኑ አለመነበብ መከፋትን ቢጭርም ቅሉ የምር ፀሐፊ ይህንንም ቸል ብሎ መጻፉን ይቀጥላልና ስሜቱ የወል አይሆን ይሆናል፡፡ የምር እውቅና መስጠትስ መረዳትን የግድ ይል የለ። እንደዛ!
ብዙ ተግተው ብዙ ቢሰጡንም፣ ብዙም “ካልዘመርንላቸው” ብርቱ ደራሲዎቻችን አንዱ ብርሃኑ ዘሪሁን ይመስለኛል፡፡ ስለደራሲውና ስራዎቹ በጋዜጣ አምድ ላይ ለማውሳት መሞከር “ሆድ ላይሞሉ አጉል ማላስ” ቢሆንም፣ ካለማለት ጥቂት ማለት ያተርፋልና በዚህ ጽሑፌ ስለደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁንና አስተዋጽኦዎቹ፣ እንዲሁም “ድል ከሞት በኋላ” ስለተባለው ድርሰቱ ጥቂት አወሳለሁ፡፡
በኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ስራዎችን ካበረከቱ ደራሲያን አንዱ ብርሃኑ ዘሪሁን ነው፡፡ የአጭርና የረዥም ልቦለድ ደራሲ፣ ጸሐፌ ተውኔት እና ጋዜጠኛ የነበረው ብርሃኑ ከ1952 ጀምሮ ከዚህ ዓለም በሞት እስካለፈበት 1979 ዓ.ም ድረስ 11 ልቦለድ ድርሰቶችንና 3 የሙሉ ጊዜ ተውኔቶችን ለተደራሲያኑ እንካችሁ ያለ ብርቱ ብዕረኛ ነው፡፡
በ1952 ዓ.ም “የእንባ ደብዳቤዎች” የተባለ ድርሰቱን እንካችሁ በማለት ጉዞውን አንድ ያለው ብርሃኑ፤ በኋላም “ድል ከሞት በኋላ”፣ “አማኑኤል ደርሶ መልስ”፣ “የበደል ፍጻሜ”፣ “ጨረቃ ስትወጣ” እና “ብር አምባር ሰበረልዎ” የተባሉትን ድርሰቶቹን አበርክቶአል፡፡ እንዲሁም “የቴዎድሮስ እንባ” እና “የታንጉት ምስጢር” የተባሉ ሁለት ታሪካዊ ልቦለዶችንና በወሎ ክፍለ ሀገር ተከስቶ የነበረውን ድርቅና የመንግስቱን ቢሮክራሲ ህያው አድርጎ የከተበባቸውን “ማዕበል የአብዮት ዋዜማ”፣ “ማዕበል የአብዮት መባቻ” እና “ማዕበል የአብዮት ማግስት” የተባሉ 3 ልቦለዶችን አስነብቦአል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ “ጣጠኛው ተዋናይ”ን እና “አባ ነፍሶ”ን የመሰሉ ተውኔቶችንም ጽፎ ለመድረክ አብቅቶአል፡፡
የብርሃኑን ድርሰቶች በጥሞና ለመረመረ አንባቢ አንድ ነገር አይሸሸገውም፡፡ ይኸውም ደራሲው ከጊዜ ጊዜ እያደገና እየበሰለ መሄዱ ነው፡፡ ደራሲው በገፀ ባህርያት አሳሳል፣ በግጭት አፈጣጠር እና በአተራረክ ጥበብ እንዲሁም በአጻጻፍ ብልሀቱ እየሰላ ሲሄድ በድርሰቶቹ በጉልህ ይስተዋላል፡፡ ምንም እንኳን ሲመሰከር ባይሰማም ብርሃኑ አጭር፣ ቀጥተኛና ግልጽ አረፍተ ነገሮችን በድርሰቶች ውስጥ በመጠቀም፣ እንዲሁም ቀድሞ የነበረውን ተረታዊ የታሪክ መንገሪያ ስልት በመቀየር ፈር ቀዳጅ ከሆኑ የሀገራችን ደራሲያን አንዱ ነው፡፡ ድርሰቶቹን የሚጽፈው እጅግ ቀላል እና ግልጽ በሆነ ስልት ነው፡፡ ከይዘት አንጻር አብዛኞቹ ድርሰቶቹም የሚያተኩሩት ማህበራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡
የብርሃኑ ድርሰቶች ከቅርጽም ሆነ ከይዘት አንጻር ብዙ ሊባልላቸው የሚችሉ ናቸው፡፡ ሁሉም ድርሰቶቹ ማለት ይቻላል እጅጉን ለመነበብ የማይጎረብጡ ናቸው፡፡ ታሪክ ሲተርክም ሆነ መዋቅር ሲያበጅ ያውቅበታል፡፡ በየድርሰቶቹ የምናገኛቸው ገጸ ባህሪያቱ የቅርብ ሰዋችን ያህል የሚሰሙን ናቸው፡፡ የዚህም ምክንያቱ ምናልባት ማንነታቸው ከእኛ እንደ አንዱ ስለሆነ ታሪካቸውም እኛው የምንኖረው ያልራቀን፣ ያልረቀቀን አይነት ስለሆነ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ስሜታቸውን ሁሉ እንድንጋራ እንሆናለን፡፡ የብዙዎቹ ድርሰቶቹ ጭብጦችም እንዲሁ ኑሮአችንና የየእለት ጉዳያችን ናቸው፡፡
ብርሃኑንና ድርሰቶቹን ሳስብ ሁሌም የሚደንቀኝ አንድ እውነት አለ፡፡ ያለኝ መረጃ እርግጥ ከሆነ ብርሃኑ ለብዙ ዓመታት ጋዜጠኛ፣ በኋላም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበር፡፡ የጋዜጣ ስራ ደግሞ ምን ያህል ጊዜን እንደሚወስድ ብቻ ሳይሆን አድካሚና የአፍታ ረፍት የለሽ መታተር እንደሆነ እናውቃለን። ዛሬ ለነገ ሰርቶ ዛሬውኑ ለቀጣዩ ቀን ማሰብን፣ መሮጥን ያለ ረፍት መድከምን… ይጠይቃል፡፡ ጋዜጣው እለታዊ ሲሆን ደግሞ አስቡት፡፡ የጋዜጣው አዘጋጅ ሲኮንስ? ሌላ ሌላውን ትተን ዋና አዘጋጁ ቢያንስ በየእለቱ ርዕሰ አንቀጽ መጻፍ ይጠበቅበታል። እንግዲህ በዚህ ሁሉ ውጥረት ውስጥ ሆኖ ነው ብርሃኑ በቁጥር የበዙ በጥራትም የላቁ ድርሰቶችን የጻፈው፡፡ ይህ ሁሌም ያስገርማኛል፡፡
“ድል ከሞት በኋላ” ብርሃኑ ዘሪሁን “የእንባ ደብዳቤዎች”ን ካቀረበ ከ3 ዓመታት በኋላ በ1955 ዓ.ም ያሳተመው ሁለተኛው ልቦለዱ ነው፡፡ ብርሃኑ ልቦለዱን የጻፈው በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ ይካሄድ በነበረው የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ የድርሰቱ ጭብጥ የነጻነት ትግል፣ ትኩረቶቹም በወቅቱ ነጻ ያልወጣችው ደቡብ አፍሪካ እና በነጮች ስር ሆነው በመሰቃየት ላይ የሚገኙት ህዝቦቿ ናቸው፡፡ የታሪኩ ስፍራ ደቡብ አፍሪካ፣ የልቦለዱ ገጸ ባህሪያትም ለነጻነት የሚታገሉት ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን እና ገዢዋቻቸው የሆኑት ነጮች ናቸው፡፡
ልቦለዱ የሚተርከው የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ህዝቦች በነጮች ስለሚደርስባቸው ጭቆና እና ይህንን ጭቆና ለማስወገድ ጥቁሮቹ ስለሚያደርጉት ትግል ነው፡፡ በዘመኑ በደቡብ አፍሪካ የነበረው ጨቋኝ የነጮች አገዛዝ፣ የጥቁሮቹ በገዛ ሀገራቸው በባርነት መገዛት በዚህም ይደርስባቸው የነበረው ግፍና መከራ ሁሉ በልቦለዱ ግሩም በሆነ መልኩ ቀርቦአል፡፡
የልቦለዱ ዋና ገጸ ባህሪ የዙሉ ጎሳ አባል የሆነው ድኩማ ነው፡፡ የድኩማ አባት ኪሙይ በሚሰራበት የነጮች ንብረት በሆነው የዱቄት ፋብሪካ ውስጥ ከሌሎች የስራ ባልደረቦቹ ጋር ባነሱት የህክምና አበል ጥያቄ ምክንያት በነጮች ላይ ትልቅ ሤራ ጠንስሰዋል በሚል በሀሰት ተወንጅሎ ይታሰራል። አባቱ በመታሰሩ ምክንያት የቤተሰቡ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ በድኩማ ትከሻ ላይ ይወድቃል፡፡ ዘሩ ነጭ ቢሆንም የነጮቹን የግፍ አገዛዝ የሚቃወመውና ለጥቁሮቹ የሚቆረቆረው ዶክተር እስቴዋርድ ድኩማን የቆዳ ፋብሪካ ውስጥ በጉልበት ሰራተኛነት ያስቀጥረዋል፡፡
 ድኩማ በፋብሪካው እየሰራ ቤተሰቡን ለማስተዳደር ጥረት ቢያደርግም አባቱ በወንጀለኛነት ስለተፈረደበት ብቻ የወንጀለኛ ልጅ ነህ በሚል ምክንያት ከቆዳ ፋብሪካው ይባረራል፡፡ በድኩማ ቤተሰብ ላይም ከፍተኛ ችግር ይወድቃል። በዚህም ድኩማ የመከራው ጥልቀት እያንገሸገሸው ይመጣል።
ቆይቶም ሲያግዘው የቆየው እስቴዋርድ ዱርባን በምትባልና ጥቁሮች በሚኖሩባት ከተማ ለሚኖር አባ አሊንጎ ለተባለ ወዳጁ ድኩማን ላይ የደረሰበትን ችግር ሁሉ ገልጾ ደብዳቤ በመጻፍ እንዲረዳው ድኩማን ይልከዋል፡፡ ሆኖም አሊንጎ ስራ ሊያገኝለት ባለመቻሉ ድኩማ አሊንጎ ቤት መኖር ይጀምራል፡፡ በአሊንጎ መኖሪያ ቤት ማታ ማታ በየአካባቢው የሚኖሩ የጥቁሮች ተወካዮች ስለተጫነባቸው የመከራ ሕይወትና እንዴት ነጻ መውጣት እንደሚችሉ ያደርጉት የነበረው ውይይት ድኩማን እየሳበው ይመጣል፡፡ በሂደትም የውይይቱ አካል ይሆናል፡፡
ምክክሩና እቅዱ ቀጥሎ እነ አሊንጎ አመጹን ለማንሳት ምቹ ጊዜን እየጠበቁ ባሉበት ወቅት ድኩማ በፖሊስ ተይዞ ይታሰራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለጥቁሮች ወደ ተከለከለው ኮከብ አደባባይ ገብቶ መገኘቱ ነበር። የድኩማ መታሰርም አመጹ ተጠንቶ እና ምቹ ሁኔታ ሲገኝ ያለ ደም መፋሰስ ነው መደረግ ያለበት የሚል አቋም የነበረውን አሊንጎን ተስፋ ያስቆርጠዋል። ስለዚህም አመጹ መካሄድ እንዳለበት ይወስናል፡፡ በመሆኑም ድኩማ ፍርድ ቤት በሚቀርብበት ሰዓት 50 ሺ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን በሰልፍ ሆነው የተቃውሞ መዝሙር በመዘመር ወደ ፍርድ ቤቱ ያመራሉ። ሆኖም የነጭ ፖሊሶች ጥይት በመተኮስ የአመጹን መሪዎች ጨምሮ ብዙ ጥቁሮችን ይገድላሉ፡፡  ከፍርድ ቤቱ በመውጣት አመጹን የተቀላቀለው ድኩማ እና የትግሉ መሪ የነበረው አሊንጎም ከፖሊሶቹ በተተኮሰ ጥይት ይገደላሉ፡፡ የጀመሩት ትግል እንደሚቀጥል ተስፋ አድርገው፣ ሞታቸውን በጸጋ እንደተቀበሉት ተገልጾ ታሪኩ ይቋጫል፡፡
ታሪኩ እጅግ አጓጊና የማይሰለች፣ አተራረኩም ውብ ነው፡፡ እነ ድኩማና አባቱ ኪሙይ፣ አሊንጎ፣ ዶክተር እስቴዋርድ የመሳሰሉት የታሪኩ ባለቤቶች በውብ መንገድ የተቀረጹና ቅርባችን ያሉ ያክል የሚሰሙን አይረሴ ገጸ ባህሪያት ናቸው፡፡
ብርሃኑ ዘሪሁን ብዙዎቹን ታሪካዊ ልቦለዶቹን የጻፈው ታሪኩ የተፈጸመበት ቦታ በአካል ተገኝቶ መረጃዎችን በመሰብሰብና የሁነቱን መንፈስ ለመላበስ በመሞከር ነው፡፡ “የቴዎድሮስ እንባ”ን ሲጽፍ ጎንደርና መቅደላ፣ 3ቱን “ማዕበሎች” ሲጽፍ ደግሞ ከወሎ የገጠር ቀበሌዎች ደሴ እስከነበረው የስደተኞች ካምፕ ድረስ ተዘዋውሮ በድርቅ የተጠቁትን ሰዎች በማየትና በማነጋገር መረጃዎችን ሰብስቦአል፡፡ “ድል ከሞት በኋላ”ን ለመጻፍ ግን ደቡብ አፍሪካ አልሄደም፡፡ ያም ሆኖ ባለመሄዱ ከመቼትም ሆነ ከታሪክ አንጻር ምንም እንዳላጎደለና  የወቅቱን የደቡብ አፍሪካን ጥቁሮች የመከራ ህይወትና የነጻነት ትግል በጥሩ አቀራረብ ለአንባቢያን ማሳየቱን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
ልቦለዱን ከራሱ ከደራሲው ስራዎችም ሆነ ከሌሎች በዘመኑና ከእሱም ቀድመው ከታተሙ ልቦለድ ድርሰቶች የሚለየው አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም የሌሎች ሕዝቦችን ታሪክ መተረኩ ነው፡፡
ቀደም ሲል ለድርሰቶቻቸው በእውኑ ዓለም የሌሉ መቼቶችን እየፈጠሩና ሰው ያልሆኑ ገጸ ባህሪያትን እየቀረጹ ጭምር የጻፉ ደራሲያን ቢኖሩም የሌላ ሀገርን ታሪክና መቼት በሙሉ ጊዜ በድርሰቱ ውስጥ በመገልገል፣ በአጠቃላይ የሌሎች ሕዝቦችን ጉዳይ የድርሰቱ አቢይ ትኩረት አድርጎ የጻፈ ደራሲ አላጋጠመኝም፡፡ ይህንን ለማንሳት የወደድኩት ደራሲው ይህንን ልቦለድ መጻፍን ለምን ፈለገ? ወደሚለው ጥያቄ ስለሚመራኝ ነው፡፡
ደራሲው ስለመጽሐፉ የመጻፍ ምክንያት በከተበበት መግቢያ ላይ “መጽሐፉን የጻፍኩት ስለ ነጻነትና ስለመብት ለተሰዉ ሰዎች እና ወደፊትም በመታገል ላይ ለሚገኙት ሕዝቦች ሁሉ መታሰቢያ የምትሆን አንዲት ድርሰት ማበርከት እዳዬ ሆኖ ስለተሰማኝ ነው” ይላል፡፡ ሆኖም መጽሐፉ የታተመበትን ጊዜ (1955 ዓ.ም) እና በልቦለዱ የተነሱ ጉዳዮችን ይዘን ስናስብ አማራጭ የለንም ብለን እጅ ካልሰጠን በቀር ብርሃኑ ድርሰቱን ለመጻፍ ምክንያቴ ነው ያለንን ለማመን እንቸገራለን፡፡ ወቅቱ ምንም እንኳን የብዙ የአፍሪካ ሀገሮች የነበሩበትን መንፈስ ያህል ባይሆንም በኢትዮጵያም የለውጥ ነፋስ መንፈስ የጀመረበት ጊዜ ነው፡፡ እርግጡን መናገር ቢቸግርም ደራሲው ልቦለዱን ሲጽፍ ሌላ ዓላማ ያለው ይመስላል፡፡ ምናልባትም የደቡብ አፍሪካውን የነጻነት ትግል መንፈስ በዚህች ሀገር ወጣቶች ላይ ማጋባት፣ እኛም የተጫነን ቀንበር አለና ከተቀመጥንበት እንነቃነቅ የማለት… የመሳሰሉት አይነት ዓላማዎች፡፡
አስገራሚው ጉዳይ ታዲያ ይህንን የመሰለ የነጻነት ትግልን ጭብጡ ያደረገ ይህንንም በበርካታ  ሁነቶች ማሳየት የቻለ ልቦለድ፣ የለውጥ ነፋስ እየመጣባት ባለች ሀገርና ነፋሱን እየጠሩት ባሉት የዘመኑ ወጣቶች ሳይቀር ብዙም አለመነበቡ ነው፡፡ በወቅቱ ልቦለዱ 2,000 ኮፒ እንደታተመና ብዙም እንዳልተሸጠ፣ ለዚህም ምክንያቱ የዘመኑ አንባቢያን ለደቡብ አፍሪካ ታሪክ ብዙም ፍላጎት ያልነበራቸው በመሆኑ እንደሆነ ደራሲው (ብርሃኑ) ገልጾልኛል፤ በማለት የብርሃኑን የህይወት ታሪክ እና ስራዎቹን ያጠናው ሪዱልፍ ኬ. ሞልቬር Black Lions- The Creative Lives of Moderen Ethiopia’s Literary Giants and Pioneers (1997) በተባለው መጽሐፉ አስፍሮአል፡፡ መተላለፍ ይሉታል ይሄ ነው።

ምንጭ:--http://www.addisadmassnews.com/
*************************************************************************** 

Friday, November 21, 2014

የባንዲራ ታሪክ_በኑረዲን ዒሣ

የግጥም ጣዕም 

የባንዲራ ታሪክ_ኑረዲን ዒሣ

 

በሃበሻ ምድር
እንዲህ እንደዛሬው ዋጋው መሣ ሳይሆን
እኩል ከእራፊ ጨርቅ
ለሃገር ክብር ሲባል
ከባንዲራ በፊት – ሰው ነበር የሚወድቅ።
መሣፍንቱ በጎጥ ሸንሽኖ ከፋፍሎ
የማሽላ ዳቦ ያረጋትን ሃገር
ገብርዬ ሲለካት – እንቅጯን ሁለት ክንድ
በሆነች ባንዲራ ገጣጥሞ በማሰር
አንድን ሕዝብ አንድ አርጎ
ማኖር እንደሚችል ከተዋበች በቀር
ሕዝቡም፣ ሹማምንቱም፣ እራሱ ቴዎድሮስም – ከቶ አያውቅም ነበር።
የዛን ቀን ለሊት ግን
እንደ ነገ ጠዋት፣ ደረስጌ ማርያም ላይ
ንግሥና ሊቀባ፣ ክፉኛ ሃሳብ ይዞት
እንቅልፍም እንደሰው ሙልጭ አርጎ ክዶት
እልፍኙ ውስጥ ሆኖ….
ስለአንዲት ሃገሩ፣ ስለአንዲት ወዳጁ
እቋፍ ላይ ስላለች
ላሳቡ ማሰሪያ አጥቶ – እግር ተወርች
እንዲህ ሲንጎራደድ
ሌላኛ ወዳጁ
የሴት ባለመላ – ተዋበች አሊ ግን ልታነቃው አለች።
«ካሣ መከታዬ»
ሃሳብ ለምን ገባህ አልልም የኔ አባት
ቅድምም አየውህ – ማዱን ስትገፋው
አልዋጥ ብሎ፣ ባፍህ ሲንከራተት የጎረስከው እራት።
አውቃለሁ ጌታዬ
የእንቅልፍህ፣ የእረፍትህ፣ ያንዠትህም ጠላት
ይቺው ሃገርህ ናት።
ደሞ ምናባቱ…እንቅልፍስ ይቅርብህ – ወዴት ታውቀውና
እጣህን የመንቃት አድርጎት ሲያበቃ…
ምኑን ታርፈዋለህ
ይኼው ጎበጥክ አይደል – ሃገር ስታቀና።
እንቅልፍስ ይቅርብህ ወዴት ታውቀውና።
ቁስሉን ነካችበት
ብሶቱ ልፋቱን – መከራውን አልፋ ሕልሙን አየችበት።
ካሣ አንገቱን ደፋ
እሷ ፊቷን ዞረች።
እንዲህ የሆነ ዕለት – ከሱና እሷ በቀር – ባዕድ የማያውቃት
ያይኑን ገደብ አልፋ – የምትፈስ እንባ አለች
ያቺ ዕንባ ጠብ አለች።
እንግዲህ አለ መይሳው
እንግዲህ…
በእኔ ልፋትና በኔ ድካም ሳይሆን
በእግዜር ይሁን ማለት
ለዚህ ማዕረግ መርጦ – ሰጥቶኛል ይኽን ሹመት
እኔ ስሰነዝር እሱ ከኔ ቀድሞ ባላንጦቼን እየጣለ
ወሰኔን እያሰፋ – የታጠቅ ጉልበት እንደቻለ
ሞገሴን እያገዘፈ….
እንደልቤ መሻት—እርከኔን እያከለ።
እግዛቤር ይመስገን
ይኼው … ለዚህ በቅቻለሁ
ተመስገን ከማለት ውጪ
ለስለት እከፍለውስ—ምን የከበረ አስገባለሁ።
ግን አለ መይሳው!
ግን ነገ ማለዳ…ቅባቱን ተቀብዬ – ዘውዱን ስደፋ
ሕዝቡ!
ይጠብቃልና…እገባለት ኪዳን – ፈቅደህ ስጠኝ ስለው ይቺን ትልቅ ሃገር
ምን ይዤ ልማልለት – ምን ጨብጬ ልቁረብለት
ምንስ ብዬ ልናገር
እስኪ መላ ካለሽ – ተዋቡ – ካንቺ እንኳን ልበደር።
በማተቤ እንዳልምል
የባለሌጣ አንገቱም የእስላሙም ናት ይቺ ሃገር
በጊዮን እንዳልምል
ኦሞ፣ ጉደር፣ አዋሽ፣ ቦርከና፣ ባሮ፣ ተከዜ፣ ጉማራ በይው ሎኒያ
ሁሉም ገንዘቧ ነው
የቱ ከየትኛው በልጦብኝ – በየትኛው ልማልላት ለኢትዮጵያ!
ሽናሻ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ አገው፣ ወላይታ
ትግሬ በይው አማራ፣
በምድሯ የተቀነበበ ሁሉ በስሟ ነው የሚጠራ።
እህም…አለች ተዋቡ
እህም…አሁን እስላም ስትል – ሸማኔው ትዝ አለኝ
እጀ ወርቅ የሚሉት – አህመዴ ቦጋለ
በል ቶሎ በል ካሣ – አሽከር አስጠራልኝ – ገብርዬ የታለ
ገብርዬን አስጠራው
እሱ ነው የልቤ – ሲጋልብ የሚነፍስ
ከጎህ ቅዳጅ በፊት – መልዕክቴን ይዞልኝ – ከደጁ የሚደርስ።
ካሣን ግራ ገባው፣ ግን አይጠይቃትም፣
አምስት ስድስት ጊዜም እንደዚህ አዋክባው
እሷው ነድፋ፣ እሷው አባዝታ
እሷው አድርታ፣ እሷው ፈትላ
ባመጣችው ሃሳብ፣ ባሳየችው መላ
ብትንትን ሃሳቡን ገጣጥማ ስትሰፋው – አይቷልና ባይኑ
ለምን ማለት ትቶ፣ እንዴት ማለት ትቶ
«ገብርዬ ይጠራ» አለ ወዲያውኑ።
ገብርዬ
ከታንጉት ሙቅ እቅፍ
በውድቅት ተላቆ – ከነ ጋሻ ጃግሬው ገና እንደደረሰ
«እሰይ የኔ አንበሳ» ስትለው ተዋበች
ገና እንኳን በወጉ የወጉን እጅ መንሳት ሰጥቶም አልጨረሰ።
«እሰይ የኔ አንበሳ…
እንትፍ ይቺ ምራቅ ምድር መጥጧት ሳትከር
ስትገሰግስ ሄደህ…ደገኞቹ መንደር
አህመዴ ለሚባል
እጀ ወርቅ ሸማኔ … ቃሌን ቃል ሳትጨምር፣ እንዲህ ብለህ ንገር።
ባገር ሠማይ ስትፈልቅ
የቅርቡም የሩቁም እኩል እንደሚያያት የማሪያም መቀነት፣
በዚህ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ጥለት
አንተ ስትለካት – ሁለት ክንድ የሆነች – ጥብቅ ምት ባንዲራ፣
ሁነኛ አርጎ ሰርቶ
ነገ ማሪያም ድረስ – ይዟት እንዲመጣ – አጥብቀህ … አርቀህ ንገረው አደራ።
በማለት ተዋበች…
ግብጦች ለእጅ መንሻ – ከላኩላት መሐል -
የሃር የሆነውን ጥለት ጥድፍ ብላ
ለገብርዬ ሰጥታው – እሱም ጥድፍ ብሎ
ከነጀሌዎቹ ከወጣ በኋላ
ካሣ ፈገግ አለ፣
የጥድፈቷ ሚስጥር ቋጠሮው ተፈትቶ፣ ብትንትን ሃሳቡን
ባንድ ስላዋለ
ካሣ ፈገግ አለ።
ሺህ ስምንት መቶ አርባ አምስት – ዓመተ ምህረት
የተራራው አናት – ገና ሳይላቀቅ
ካድማስ ጥቁር እግር
ባህመዴ አማርኛ – ሠማዩ ሳይቀላ ባግባቡ ሳይፈጅር
አህመዴ ቦጋለ
የንጋት ስግደቱን – አስላምቶ አብቅቶ
ልክ! ፊቱን እያበሰ
ፊታውራሪ ገብርዬ
ከነጀሌዎቹ ደጁ ላይ ደረሰ።
የፈረሶች ኮቴ – ደጁን ሲረመርም የሰማው አህመዴ
ልቡ ድንግጥ አለ፣
«እንዲህ በማለዳ – የሚደርስ ከደጄ
መርዶ ነጋሪ ነው
ደሞ ማን ተለየኝ – የትኛው ዘመዴ?
ከቶ የኔ ሐዘን ዳርም የለው እንዴ
«እንዴት አደራችሁ…ቤቶች»
ይበልጥ ተረበሸ ይኼን ድምፅ ያውቀዋል፣
ምላሽም አልሰጠ፣ በርም አልከፈተ
ድርቅ ብሎ ቁሞ – ወይ ወንድሜን አለ
ክተት ሲባል ከቶ ከመይሣው ጋራ አብሮ የዘመተ
አንድ ወንድም ነበረው… ያ ወንድሙ ሞተ?
«ቤቶች…ቤቶች
ገብርዬ ጥሪውን እንዲህ ሲደጋግም
ገፋ አድርጎ ወጥቶ የጎጆውን ግርግም
ድሮ አውቄዋአለሁ
ለደግም አልነበር አደባባይ ቆሜ
ሸማ ሳውለበልብ ያየሁት በህልሜ
ወይ ወንድሜን ወንድሜ!
«የለ እንደሱም አይደል» ገብርዬ አቋረጠው
«ተዋበች ልካን ነው»
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ጥለቱን ሰጠው።
አስከትሎ ደግሞ
ቃሌን ቃል ሳትጨምር – ያለችውን መልዕክት
ቃሏን ቃል ሳይጨምር – ረግጦ ሲነግረው
የመናቡ ተፍሲር – ብስራት ሆኖለት
እጀ ወርቅ ደስ አለው።
አለም፦
እንዴት ያንድ እናት ሆድ፣ አንድ ላይ ያበቅላል፣ አንድ ደህና አንድ ጠፍ
ብረገም ነው እንጂ
ክተት ሲል ከትቼ – እንደዚያ ወንድሜ – ከመይሣው ጋራ ጎኑ ማልሰለፍ፣
ብዬ እቆጭ ነበር፣… ይኼው ዛሬ ግና
አላህ ያለ ለታ፣ ላገር ሥራ ሲለኝ ረብ ያለው ሥራ
ያውም የመይሳውን ያውም የኢትዮጵያን … ያውም ያገሬን ባንዲራ
ያውም በኔ ጥበብ…
ያውም በሰው እጆች … ከሰውም በኔ እጆች … በሸማ እንድሰራ
ታሪክ እድል ሰጠኝ፣ ብሞትም አይቆጨኝ ከዚህስ በኋላ!
አህመዴ ሸለለ፣
አህመዴ ፎከረ … በደስታ ሰከረ፣ በደስታ አለቀሰ
ሩጦ ቤቱ ገባ፣ ሦስቱንም ልጆቹን – ሚስቱን ቀሰቀሰ።
ነገራት ለሚስቱ፣
ከምርጥ ዘሃ መሀል – ምርጡን ዘሃ መርጣ
እንድታቀርብለት – ቶሎ ብላ አዝግታ።
አዘዘ ልጆቹን
ቱባ ተከፋፍለው – ከየአንዳንዱ ጥለት
አሥር አሥር ቀለም – እንዲያዳውሩለት።
ሦስት ሰዓትም አልፈጀ
መቀነት ሸማቃው ከኖረበት ወርዶ
ዝግ ዘሃው ተቋጥሮ
ጥለቱ ተጥሎ.. ድምድሙ ተመትቶ – ባንዲራው ሲቆረጥ
በቅሎው ከጋጥ ወጥቶ
በጌጥ ተሸልሞ አህመድ ተነሚስቱ እጋማው ላይ ወጥቶ
እሱ – ሲኮለኩል – በቅሎው ንሮ ሲሮጥ … ሲሮጥ … ሲሮጥ
ደረስጌ ማሪያም ላይ ደርሰው ሆታው ሲቀልጥ
በዚያ መሀል አልፈው አህመድ ለመይሣው ባንዲራውን ሲሰጥ
ሰዓትም አልፈጀ
መይሣው ደስ አለው
የወርዱ ምጣኔ፣ የጠርዙ ጥብቅነት፣
የጥለቱ አጣጣል፣ ጥበቡ ደነቀው፣
ቁርጥማት አይንካህ
በሆዱ መረቀው
ካሣ ዞሮ ሄደ።
አህመዴ ተጣራ
መይሳው ዞር አለ
ባንዲራው ሲሰራ
ተርፎ ስለነበር ብዙ የሃር ጥለት ካቁማዳው አውጥቶ … እጁን ዘረጋለት።
ካሣ….!!
የዚህን ደሃ ሰው – ፍፁም ታማኝነት፣ ገራገር ልቦና ባስተዋለ ጊዜ፣
የጎንደር አዝማሪ ያቀነቀናትን በልቡ እያዜማት
በልቡ ያላትን … ያቺኑ ምርቃት…
ተባረክ እጅህን አይንካው ቁርጥማት
በአፉም ደገማት።
የጎንደር አዝማሪ በእነ አህመዴ ዘመን፣
«እስላም አልኩሽ እንጂ – እጁ የሚታመን
ሸማኔማ ሞልቷል ደሞ ለመሸመን»
ይል ነበር።                        

https://www.youtube.com/watch?v=rekboLUx2wI

Wednesday, November 19, 2014

የሚጸልዩ እጆች_እና_አልብሬሽት ዱረር

(እውነተኛ ታሪክ)
*************


ከስድስት ምእት ዓመታት በፊት በጀርመን ኑረምበርግ ከተማ በአንድ ትንሽ መንደር ውስጥ አሥራ ስምንት ልጆች ያሉበት አንድ ቤተሰብ ይኖር ነበር፡፡ አሥራ ስምንት! ለዚህ ሁሉ ማቲ ምግብ ለማቅረብ በሙያው አንጥረኛ የሆነው አባ ወራ በቀን አሥራ ስምንት ሰዓት በሙያውና ከሙያው ውጪ መሥራት ነበረበት፡፡

የቤተሰቡ የኑሮ ሁኔታ የከፋ ቢሆንም ከልጆቹ ውስጥ ሁለቱ ታላላቆች ልዩ ሕልም ነበራቸው ሥነ ጥበብን ማጥናትና ዝነኛ ሠዓሊ መሆን፡፡ አባታቸው ማንኛቸውንም ኑረምበርግ ወደ ሚገኘው የሥነ ጥበብ አካዳሚ ልኮ ሊያስተምራቸው የሚያስችል የገንዘብ አቅም እንደሌለው ግን ሁለቱም ያውቁ ነበር፡፡

አንድ ምሽት በተጨናነቀው አልጋቸው ላይ ሆነው በሕልማቸው ዙሪያ ለረጅም ሰዓት ተወያዩና ወደ አንድ ስምምነት ደረሱ፤ ዕጣ ሊጣጣሉም ወሰኑ፡፡ በዕጣው የተሸነፈው በአቅራቢያቸው ወደ ሚገኝ አንድ የማዕድን ማውጫ ሄዶ እንዲሠራ፣ በሚያገኘውም ገቢ ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚሄደውን ወንድሙን እየረዳ እንዲያስተምር፡፡ ዕጣ የወጣለት ወንድም ደግሞ በኑረምበርግ ከተማ በሚገኘው የሥነ ጥበብ አካዳሚ የአራት ዓመታት ትምህርቱን እንዲማርና ትምህርቱንም ሲጨርስ፣ በሚመረቅበት የሥነ ጥበብ ሙያ ከሚሠራቸው ሥዕሎች ሽያጭ በሚያገኘው ገቢ ወይም አስፈላጊ ከሆነ እርሱም በማዕድን ቁፋሮ ሥራ ተቀጥሮ በተራው ያስተማረውን ወንድሙን ሊያስተምር ወደ ውሳኔ ደረሱ፡፡

አንድ እሑድ ጠዋት ዕጣው ተጣለ፣ ታላቁ አልብሬሽት ዱረር የተባለው ወንድም ዕጣው ወጣለት፡፡ ኑረምበርግ ከተማ ወደ ሚገኘውም የሥዕል አካዳሚ ገባ፡፡

ዕጣ ያልወጣለት ወንድም ወደ አደገኛው የማዕድን ቁፋሮ ሥራ አመራ፣ ለተከታዮቹ አራት ዓመታትም ወንድሙን በገንዘብ እየረዳ አስተማረ፡፡ አልብሬሽት የአካዳሚው የሥዕል ትምህርት ተዋጣለት፡፡ በልዩ ልዩ የሥዕል ሥራዎች የተካነ ሆነ፡፡ የሚሠራቸው የቅብ ሥዕሎች ከመምሕራኖቹ ሥራዎች ይልቅ እየላቁና እይተወደዱ መጡ፡፡ በኮሚሸን ለሚሠራቸውም ሥዕሎች ዳጐስ ያለ ገንዝብ ይከፈለው ጀመር፡፡

ወጣቱ ሠዓሊ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ መንደሩ ሲመለስ ቤተሰቡ በድል መመለሱን ምክንያት በማድረገ ድግስ ደግሶ ጠበቀው፡፡ በሙዚቃና በሳቅ በደመቀው ግብዣ መጨረሻ ላይ ሠዓሊው አልብሬሽት ከክብር ወንበሩ ተነሳና ለተወዳጅ ወንድሙ፣ ላመታት ስለከፈለው መስዋዕትነት፣ ሕልሙንም እንዲያሳካ ስለ ረዳው ጽዋ አነሳ፡፡ በመዝጊያ ንግግሩም፣ ‹‹የተባረክህ ወንድሜ አልበርት ሆይ፣ አሁን እንግዲህ ተራው ያንተ ነው፣ ወደ ኑረምበርግ ትሄዳለህ አንተም ሕልምህን ታሳካለህ፣ እኔም በተራዬ እንከባክብሃለሁ›› አለ፡፡

በገበታው የታደሙት ሁሉ አንገታቸውን ከገበታው አንድ ጥግ ላይ ወደ ተቀመጠው የማዕድን ሠራተኛ አልበርት አዞሩ፡፡ በገረጣው ፊቱ ላይ እንባው እየተንከባለለ በጉንጮቹ ላይ እይፈሰሰ ነው፣ ራሱንም ከግራ ወደ ቀኝ እያወዛወዘ፣ ሳግም እየተናነቀው ደጋግሞ፣ ‹‹አይሆንም….. አይሆንም ወንድሜ ሆይ፣….. አይሆንም!›› አለ፡፡

በመጨረሻ ብድግ ብሎ እንባውን ከጉንጮቹ ላይ በማበስ፣ አሻግሮም በገበታው ላይ የታደሙትን የሚወዳቸውን ፊቶች በፍቅር እየተመለከ፣ ሁለት እጆቹን አጣምሮ ወደ ቀኝ አገጩ በማስጠጋት ለስለስ ባለ ድምጽ ‹‹የለም ወንድሜ ሆይ፣ ወደ ኑረምበርግ ልሄድ አልችም፣ ለእኔ ዘግይቷል፣ የአራት ዓመታት የማዕድን ቁፋሮ ሥራ እጆቼን ምን እንዳደረጋቸው ተመልከትማ በጣቶቼ ላይ ያሉ አጥንቶች ሁሉ በቀን ቢያንስ አንድ ጊዜ ይጐዱ ነበር፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በከባድ የቁርጥማት በሸታ እየተሰቃየሁ ነው፣ በእርሳስና በብሩሽ በሸራ ላይ ሥዕሎችን መቀባት ይቅርና፣ አላስተዋልከኝም እንጂ፣ ጽዋችንን እናንሳ ስትል ጽዋውን ለመያዝ እንኳ የቀኝ እጄ አልቻለም፡፡ አሁን ለእኔ ዘግይቷል›› አለ፡፡

ይህ ታሪክ ከተፈጸመ ከ450 ዓመት በላይ አልፈዋል፡፡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የአልብሬሽት ዱረር እጹብ ድንቅ ሥራዎች፣ የራስ ምስሎች፣ የእርሳሰና የውኃ ቀለም ቅቦች፣ የቻርኮል ሥራዎች፣ የእንጨት ቅርጻ ቅርጾችና፣ የመዳብ ውቅሮች በመላው ዓለም ባሉ ሙዚየሞች ተሰቅለው ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ከሌሎች ሥራዋቹ ይልቅ ‹‹እጆቹ›› የሚለው ሥራውን ቅጅ በየቤቶቻቸውና ቢሮዎቻቸው ግድግዳዎች ላይ አንጠልጥለውታል፡፡

አንድ ቀን ወንድሙ ለከፈለለት መስዋዕትነት አክብሮት ለመስጠት፣ አልብሬሽት ዱረር በከፍተኛ ጥንቃቄ የወንድሙን የተጎዱ እጆች፣ መዳፎቹ ተጋጥመው፣ ቀጫጭን ጣቶቹ ወደ ሰማይ ተዘርግተው የሚታዩበትን ሥዕል ሳለ፡፡ ይህን ድንቅና ኃያል ሥራውንም ‹‹እጆቹ›› የሚል ስያሜ ሰጠው፡፡ ብዙም ሳይቆይ በዓለም ዙሪያ ሥዕሉን የተመለከቱ ሁሉ፣ ለዚህ ታላቅ እጹብ ድንቅ ሥራ ልባቸውን ከፈቱለት፡፡ ይህን ከፍቅር የተነሳ የተሳለ ሥዕልም ‹‹የሚጸልዩ እጆች›› ብለው ሰየሙት፡፡



አልብሬሽት ዱረር (Albrecht Dürer) ማን ነው?
 
Albrecht Dürer (German: 21 May 1471 – 6 April 1528)


ንደ አውሮፓው አቆጣጠር ግንቦት ፳፩ ቀን ፲፬፻፸፬ ኑረምበርግ ጀርመን ተወልዶ በ፶፮ ዓመቱ (ሚያዚያ ፮ ቀን ፲፭፻፳፰) እዛው ኑረምበርግ ከተማ የሞተው አልብሬሽት ዱረር (ከዚህ በኋላ ዱረር ብለን እንጠራዋለን) (German: [ˈalbʁɛçt ˈdyːʁɐ]) የተሳካለት የወርቅ ኣንጥረኛና ከሃንጋሪ ወደ ኑረምበርግ የፈለሰው አባቱና እናቱ ሦስተኛ ልጅ (ሁለተኛው ወንድ) ሲሆን፤ ወላጆቹ ከ፲፬ እስከ ፲፰ ልጆች እንደነበራቸው ይገመታል።
      ዱረር ለጥቂት ዓመታት ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ የወርቅ አንጥረኝነትና የስዕል ሙያ መሰረቶችን ከአባቱ ተማረ። ምንም እንኳን አባቱ በአንጥረኝነቱ እንዲቀጥልበት ቢፈልግም፤ በጣም ላቅ ያለ የስዕል ችሎታ በማሳየቱ ምክኒያት ገና በ፲፬ ዓመቱ በኑረምበርግ ታዋቂ አርቲስትና የኪነ ጥበብ ማዕከል (የአርት ወርክ ሾ) ባለቤት ለነበረው ሚካኤል ዎልጌሙት (Michael Wolgemut) ረዳት ሆነ።
 
 ‹‹የሚፀልዩ እጆች›› /Betende Hände/ በእንግሊዘኛ Praying hands (በጀርመንኛም Studie zu den Händen eines Apostels in German, ወይም "Study of the Hands of an Apostle": የሐዋሪያው እጅ ጥናት) በመባል የሚታወቀው በብዕርና ቀለም በጀርመናዊው የኪነ ጥበብ ሰው አልብሽሬት ዱረር በ፲፭፻፰ የተሰራ ሲሆን፤ ይህ ሥራ ቪየና/ኦስትሪያ (Vienna, Austria) በሚገኘው አልበርቲና (Albertina) ሙዚየም ይገኛል።በብዕርና (እራሱ በሰራው) ሰማያዊ ወረቀት ላይ ዱረር ነጩ ሄይተኒንግ በመባል የሚታወቀውን ቴክኒክ ለዚህ ስራው ተጠቅሟል። ሥዕሉ እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ የሚፀልዩ ሁለት የወንድ እጆች ሲሆን፤ የቀኙ እጅ ሙሉ ክፍል ካለመታየቱ ባሻገር፣ የፀላዩን እጅ የሸፈነው ልብስ (ክሳድ) ጫፍ በጥቂቱ ወደላይ ተቀልብሶ ይታያል። ይህ ሥዕል በ፲፯፳፱ በእሳት የነደደው ባለ ሶስት ክፍሉ የሄለን መስዋዕት ማቅረቢያ (the Heller altar,) በመባል ይታወቅ ለነበረው የዱረር ሥራ መካከለኛው ክፍል ላይ ለተሳለው ሐዋሪያ እጅ (an apostles' hand) እንዲሆን ታስቦ የተነደፈ ነው። ይህ የእጅ ንድፍ ሊደረግ በታሰበበት ሥዕል በመካከለኛው ክፍል በቀኝ በኩል በተመሳሳይ ግን በትንሽ መጠን ተስሎ ይገኛል። በወረቀቱ የሐዋሪያው ራስ ንድፍ የተሰራበት ቢሆንም፤ ሁለቱ የተቀመጡት ተለያይተው ነው። ዱረር ለዚህ (የሄለን መስዋዕት ማቅረቢያ) ስራው በጠቅላላ ፲፰ ንድፎችን ሰርቷል። ቪየና ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ዕይታ በ፲፰፻፸፩ ቀረበ። ሥራው ምናልባት የሰሪው እጅ እንደሆነ ይገመታል።
 
*******************************************************************************

ምንጭ፥ http://www.ethiopianreporter.com/issues/Reporter-Issue-1419.pdf __ኃይል   ከበደ «ምስካይ» (2004)
         :- http://enaseb.blogspot.com/2013/12/blog-post_2986.html 
         :-  የ ኛ ጉ ዳ ይ - Yegna Guday Blog

Thursday, September 25, 2014

የመስቀል በዓል


ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት መጣ? የመስቀል በዓል እንጨት ተደምሮ እሳት ተቀጣጥሎ ለምን ይከበራል? ለመስቀሉ መገኘት የሮሙ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ እና የንግስት ዕሌኔ ሚና ምን ነበር?

***********************************************************************************

ፎቶ -በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓል  በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ

ዕሌኒና ተርቢኖስ


ዕሌኒና ተርቢኖስ የሚባሉ ሁለት ደጋግ ክርስቲያኖች ተጋብተው ይኖሩ ነበር፡፡ተርቢኖስና ዕሌኒ ኑሮአቸው ፍቅርና ሰላም የሰፈነበት በመሆኑ ለብዙ ሰዎች እንደ ምሳሌ ሆነውይኖሩ ነበር፡፡ ተርቢኖስ ነጋዴ ነበር፡፡ከዕለታትአንድቀን ራቅ ወዳለ ሀገር በመርከብለንግድ ሄደ፡፡ ዕሌኒም ባለቤቷ ተርቢኖስ ለንግድ ወጥቶ እስኪመለስ ስለባሏ ከመጸለይና ከማሰብ በቀር ከግቢዋ አትወጣም ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ተርቢኖስ ለንግድ ሄዶ ብዙ ዓመታትን ቆይቶ ከጓደኞቹ ጋር ወደሀገሩ ሲመለስ ከነጋዴዎች አንዱ በእግዚአብሔር ፈቃድ ከሽፍታና ከማዕበል ከልዩ ልዩ አደጋ ተርፈን በሰላም ተመልሰን ግን ሚስቶቻችን ሌላ ሳይወዱ ሳይለምዱ እናገኛቸው ይሆን? ብሎጠየቀ፡፡ ተርቢኖስ ግን "እንኳን በሰላም አደረሰን እንጂ ሚስቴን በዚህ አልጠረጥራትም" ብሎ ሲመልስ ሌላው ጓደኛው "ያንተሚስት ከማን ትበልጣለችና ነው አሁን ሄጄ ከሚስትህ ጋር ለምዳኝ ወዳኝ ወድጃት ብመጣስ ምን ይቅጣህ?" አለው፡፡


ተርቢኖስም በሚስቱ እሌኒ ተማምኖና ይህንን ብታደርግ ይህን ያህል ዓመት የለፋሁበት ሀብት ከነትርፉ ውሰድ አንተም ብታደርግ እንዲሁ ሀብትህ ከነትርፉ ለእኔ ይሁን ተባብለው ተወራረዱ፡፡ከዚያም መርከቡ ወደብ ከመድረሱ በፊት ነጋዴው ወደ ዕሌኒ ቤት ደረሰና በሩን አንኳኩቶሠራተኛይቱን ዕሌኒን ማነጋገር እፈልጋለሁና ንገሪልኝ ብሎ ጠየቃት፡፡ እሷም እያፈረችየተላከችውን ለዕሌኒ ነገረቻት ዕሌኒም ተቆጥታ ከመች ወዲህ ነው እንግዳ የማነጋግረው ብላ አሳፈረቻት፡፡

ሠራተኛይቱም ለነጋዴው መልሱን ስትነግረው ነጋዴው እንደማይሆንለት ከተረዳበኋላ ሌላ ተንኮል አቀደና ለሠራተኛይቱ ባልና ሚስቱ ብቻ የሚያውቁትን አንድ ነገር ብቻብትሰጪኝ ብዙ ገንዘብ ወርቅ እሰጥሻለሁ ብሎ ወርቅ ሰጣት፡፡ ሠራተኛይቱም ሁለቱ ብቻ የሚያውቁትን የእመቤቴ ሀብል አለ ያንን እመጣልሀለሁ መጀመርያ አንተ በከተማው ውስጥ እየዞርህነጋዴዎችን መጡ የብስ ረገጡ እያልክ አስወራ ከዚያም ተመልሰህ እንድትመጣ ብላ ሰደደችው፡፡ነጋዴውም እንደተመከረው የነጋዴዎቹን መምጣት በከተማይቱ እንዳወራ የነጋዴዎቹ ቤተሰቦችነጋዴዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ፡፡ የዕሌኒም ሰራተኛ እመቤቴ ነጋዴዎች መጡተብሎ ይወራልና፡፡ ባለቤትዎ በሰላም ስለመጡ ይዘገጃጁ ገላዎን ይታጠቡ ብላ መከረቻት፡፡ዕሌኒም ገላዋን ስትታጠብ ያንገቷን ሐብል ቁጭ ካደረገችበት ቦታ ሠራተኛይቱ አንስታ ለነጋዴውበተቃጠሩበት ዕለት ሰጣች፡፡ ነጋዴውም ለሠራተኛይቱ የውለታዋን ብዙ ገንዘብ ሰጥቶአት ደስእያለው ወደ ጓደኞቹ ሄደ፡፡ ለተርቢኖስ ሚስትህን ለምጃት ወድጃት መጣሁ አለው ተርቢኖስምውሸት ነው ለዚህ ምን ምልክት አለህ ብሎ ጠየቀው፡፡ ተንኮለኛውም ነጋዴ ያንን ሐብል አውጥቶይህ ሐብል የሚስትህ አይደለምን ብሎ ሰጠው ተርቢኖስም ደነገጠ የሚናገረውን አጣ፡፡በውርርዱምመሰረት ሀብቱን ሁሉ አስረከበና ባዶ እጁን ወደቤቱ እያዘነ እየተቆጨ ሔደ፡፡


ባለቤቷንበናፍቆትና በታማኝነት ስትጠብቅ የከረመችው ዕሌኒ በተርቢኖስ ያልተለመደ ሀዘንና ብስጭት ግራተጋብታ ወንድሜ ምን ሆነሀል? ለወትሮው እንኳን ይህን ያህል ዘመን ተለያይተን ቀርቶ ለጥቂትቀናት ተለያይተን እንኳ ለጥቂት ቀናት ተለያይተን ስንገናኝ እንነፋፈቃለን፡፡ አሁን ግን ከመጣህበትጊዜ ጀምሮ አዝነህ አይሀለሁ ብላ ጠየቀችው፡፡ ተርቢኖስም ብዙ የደከምኩበትና የለፋሁበት ሀብትንብረቴ እንዳለ ማዕበል አጠፋብኝ እኔ ያላዘንኩ ማን ይዘን አላት፡፡ እሌኒም የተማረች ናትናእግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሣ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን እንዳለ ኢዮብን አስበውአንተ እንኳን በሰላም መጣህ እንጂ ሀብቱ ውሎ አድሮ ይመጣል፡፡ እያለች አጽናናችው፡፡ተርቢኖስም እንግዲህ በተከበርኩበት ሀገር ተዋርጄ፣ በሰጠሁበት ሀገር ለምኜ ለመኖር አልችልምናወደሌላ ወደማያውቁኝ ሀገር እሔዳለሁ አንቺ ግን ሁሉ ይወድሻል ያከብርሻል ከወደድሸው ጋር ኑሪአላት፡፡ ዕሌኒም በደስታ ጊዜ አብሬህ እንደሆንኩ በችግርም ጊዜ ልለይህም የኔንና ያንተን አንድነትችግር አይፈታውም ከአንተ ተለይቼ ወዴት እቀራለሁ ወደምትሄድበት አብሬህ እሄዳለሁ ብላተነሳች፡፡

ሁለቱም ቤታቸውን ጥለው ሲሄዱ በመንገድ ላይ ተርቢኖስ በልቡናው ይዞት የነበረውን ምሥጢርአወጣው "ዕሌኒ ስወድሽ የጠላሽኝ ሳምንሽ የከዳሽኝ ምን አድርጌሽ ነው?" ብሎ ጠየቃት፡፡ ዕሌኒምእኔ አንተን አልጠላሁም አልከዳሁምም ይህንን ሐሳብ እንዴት አሰብህ ብትለው ከኪሱ አውጥቶሐብሉን አሳያትና የሆነውን ሁሉ ነገራት፡፡ ዕሌኒም ያልጠበቀችው ነገር ስለተፈጸመ አዝና የሆነውንእውነተኛ ታሪክ በሙሉ ነገረችው፡፡

ተርቢኖስ ግን አላመናትም፡፡ ከባህር ዳር በደረሱ ጊዜ በቁመቷልክ ሳጥን አሠርቶ ዕሌኒን በውስጡ አስገባትና ብታደርጊውም ባታደርጊውም እንደሥራሽ ሥራሽያውጣሽ ብሎ ወደ ባህሩ ወረወራት፡፡ ዕሌኒ ያለችበት ሳጥን በፈቃደ እግዚአብሔር እየተንሳፈፈከወደብ ደረሰ በዚያ ወደብ አካባቢ ምዕራብ ሮምን ያስተዳደር የነበረው ኮስታንዲዮስ /ቁንስጣ/የተባለው ንጉሥ ነበርና ሳጥኑን አይቶ አውጥቶ እንዲከፍቱት ወታደሮችን አዘዘ፡፡ ሳጥኑንአውጥተውም ሲከፍቱት እጅግ የተዋበች ሴት ሆና አገኟት ንጉሡም ዕሌኒን ወስዶ ሚስቱአደረጋት፡፡ ኮስታንዲዮስ /ቁንስጣ/ የመክስምያኖስ ቄሳር ሆኖ ምዕራብ ሮምን ያስተዳደር ነበር፡፡ንግስት ዕሌኒም በ272.ም ታላቁ ቆስጠንጢኖስን ወለደችለት ቆስጠንጢኖስም ገና በወጣትነቱየአባቱ እንደራሴ ሆኖ እንደሠራ አባቱ ሞተ፡፡ የአባቱ ባለሟሎችና ህዝቡ ተስማምተው የ18ዓመቱን ቆስጠንጢኖስን በአባቱ ቦታ ሐምሌ 25 ቀን 316 .ም በሮም ምዕራብ ክፍል በገላትያአነገሡት፡፡ በጦር ሜዳዎች ብዙ የጀግንነት ሥራዎች ስለሰራ በሠራዊቱ ዘንድ ይወደድ ነበር፡፡

ንግሥት ዕሌኒ ልጅዋን ቆስጠንጢኖስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለክርስትና ሃይማኖትና ስለክርስቲያኖችመከራ ታስተምረው ስለነበር በክርስቲያኖች ላይ የነበረው አመለካከት በሮም ከነገሡት ቄሣሮች ሁሉየተሻለ ነበር፡፡ በተለይም በ312.ም ከጠላቱ ከመክስምያኖስ ጋር ለመዋጋት ምታ ነጋሪት ክተትሠራዊት ብሎ ለዘመቻ እንደተሰለፈ በራዕይ በሰማይ ላይ "በዚህ መስቀል /ምልክት/ ጠላትህን ድልታደርጋለህ" የሚል መስቀልና ጽሑፍ ስላየ ለሠራዊቱ የመስቀል ምልክት በመሳሪያቸው እናበሰንደቅ ዓላማው ላይ እንዲያደርጉ አዘዘ፡፡ ወደያው ጦርነት ቢገጥም በቲቤር ወንዝ ድልድይ ላይጠላቱን ድል ነስቶ በጠቅላላው የሮም መንግስት ግዛቶች ሁሉ ገዥሆነ፡፡

ታላቁ ቆስጠንጢኖስ የሮም ንጉሠ ነገሥት

ታላቁ ቆስጠንጢኖስ የሮም ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ በ300 ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜለክርስቲያኖች የነጻነት ዐዋጅ ዐወጀ፡፡ ክርስትናም ብሔራዊ ሃይማኖት ተባለች፡፡ ንግሥት እሌኒምበተፈጠረላት አመች ሁኔታ በመጠቀም የጌታችን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ327.ም ወደኢየሩሳሌም ሔደች፡፡ ዕሌኒ ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳመስቀሉን ለመፈለግ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትንለማሳነጽ ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡ ከዚህ በኋላ ቆስጠንጢኖስ አምኖ በ337.ም ተጠመቀ፡፡ቅድስት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች ከእርሷም ጋር ብዙ ሠራዊት ነበር፡፡ እንደደረሰችም ስለከብረ መስቀል መረመረች ጠየቀች፡፡ ቦታውን የሚያስረዳት አላገኘችም፡፡ የአይሁድ ወገን እንቢቢሉም በኋላ ግን ባደረገችው ጥረት አረጋዊው ኪራኮስ የጎልጎታን ኮረብታ አመለከታት አስቆፍሪውብሎ ነገራት ኪራኮስም ዘመኑ ከመርዘሙ ጋር ተያይዞ እውነተኛው ተራራ ይህ ነው ብሎ ማሳየትባለመቻሉ ከሦስቱ ተራሮች አንዱ ነው ስላላት አይሁድ ተራሮቹን ይቆፍሩ ዘንድ አዘዘቻቸው፡፡የጌታችን ቅዱስ መስቀል ከጌታ ሞት እያመነ በተቸገሩ ግዜ ማንም እንዳያገኘው የኢየሩሳሌም ነዋሪሁሉ የእቤቱን ቆሻሻ የከበረ መስቀል ባለበት ቦታ እንዲጥል አይሁድ አዝዘው ስለነበር ከሁለት መቶዓመት በላይ ጥራጊ ስለጣሉበት ታላቅ ተራራ ሆነ፡፡

ንግስት ዕሌኒ እና የመጀመርያው ደመራ

ዕሌኒ ተራሮቹን ለማስቆፈር ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ ለመለየት ደመራ አስደምራ ብዙእጣንም በመጨመርና በማቃጠል ከአኢየሩሳሌም ወጣብለውያሉትንኮረብቶች አሳያት፡፡ የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፍናበመስገድ መስቀሉ ያለበትን ትክክለኛ ስፍራ አመለከታት፡፡ ቅዱስ ያሬድም "ሰገደ ጢስ" ጢሱሰገደ ብሎታል፡፡ ከዚያም መስከረም 16 ቀን ቁፋሮው እንዲጀመር አዘዘች፡፡ ሰባት ወር ያህልከተቆፈረ በኋላ መጋቢት 10 ቀን ሦስት መስቀሎች በአንድነት ተገኙ፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችንየተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ተቸገሩ፡፡ የሞተ ሰው አምጥተው በሁለቱ መስቀሎች ላይበተራ ቢያስቀምጡት አልተነሣም፡፡ በመጨረሻ በአንዱ መስቀል ላይ ቢያስቀምጡት ያን ጊዜየሞተው ሰው ተነሣ፡፡ በዚህም የጌታን መስቀል ለዩት፡፡ ዕሌኒም የጌታ መስቀል እንደሆነ አወቃሰገደችለት፡፡ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰገዱለት፡፡ በየሀገሩ ያሉ ክርስትያኖች ሁሉ የመስቀሉን መገኘትበሰሙ ግዜ መብራት አብርተው ደስታቸውን በመግለጥ ለዓለም እንዲታወቅ አደረጉ፡፡ በዚህምምክንያት ይህ ታላቅ የድኅነት ምልክት የሆነው መስቀል የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ደመራበመደመር በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ታከብረዋለች፡፡


 
ንግሥትዕሌኒ መስከረም 16 ቀን 320.ምበዕጣን ጢስ ምልክት ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት 10ቀን አግኝታ በማውጣት ታላቅ ቤተመቅደስ ጎልጎታ ላይ ሠርታ በክብር አስቀመጠችው ይህመስቀልም ከዚያ ዕለት ጀምሮ እንደ ፀሐይ እያበራ ድውይ እየፈወሰ አጋንንት እያባረረ ልዩ ልዩተአምራት እየሰራ ሙት እያነሳ ዕውር እያበራ ተአምራቱን ቀጠለ፡፡ ይህንንም ከኃያላን ነገሥታትመካከል የፋርስ ንጉሥ መስቀሉን ማርኮ ፋርስ ወስዶ አስቀመጠው፡፡ በዚህ ጊዜ የአየሩሳሌምምዕመናን የድሉን ዜና ሰምተው ስለነበር የአንድ ቀን መንገድ ያህል ሄደው በመቀበል ካህናቱበዝማሬና በቸብቸቦ ወንዱ በሆታ ሴቱ በእልልታ ሆ! እያሉና ችቦ አብርተው ተቀብለዋቸዋል፡፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ለመስቀል ችቦ እያበሩ በዓሉን በሆታ በእልልታበስብሐተ እግዚአብሔር የምታከብረው ይህንን ታሪካዊ ትውፊት በመከተል ነው፡፡ ብዙየቤተክርስቲያን አባቶች እንደሚሉት ንጉሡ ሕርቃል ይህንን ታላቅ ድል ለማግኘትና የጌታን ቅዱስመስቀል ከአሕዛብ /ከፋርሶች/ እጅ ለማስመለስ የቻለው በዚያን ጊዜ አብያተ ክርስቲያንናት ሁሉለአንድ ሳምንት /አንድ ሱባዔ/ ባደረጉት ጾም ጸሎት ነው፡፡ ይህንንም ለማስታወስና ጌታንለማመስገን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያንበየዓመቱ የዐቢይ ጾም /የጌታ ጾም/ ከመጀመሩ አስቀድሞ "ጾመ ሕርቃል" ብለው አንድ ሳምንትይጾማሉ፡፡

የጌታ መስቀል ለብዙ ግዜያት ኢየሩሳሌም ከቆየ በኋላ ነገሥታት ይህን መስቀል እኔ ልውሰድ እኔልውሰድ በማለት ጠብ ፈጠሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርማንያ፣ የግሪክ፣የእስክንድርያ፣ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን አበረዱት ከዚያም አያይዘው በኢየሩሳሌምየሚገኘውን የክርስቶስን መስቀል ከ4ት ከፍለው በዕጣ አድርገው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎችታሪካዊ ንዋያተ ቅዱሳት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት የቀኝ ክንፉ የደረሰውለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋየ ቅዱሳት ጋር በግብጽ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡


ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት መጣ?


ግማደ መስቀሉ ለብዙ ዘመን በእስክንድርያ ሲኖሩ በግብጽ ያሉ እስላሞች እየበዙ ኃይላቸውእየጠነከረ ሲሔድ በእስክንድርያ የሚኖሩ ክርስትያኖች ላይ ሥቃይ ያጸኑባቸው ጀመር፡፡ክርስቲያኖቹም አንድ ሆነው መክረው ለኢትዮጵያዊው ዓጼ ዳዊት እንዲህ የሚል መልእክት ላኩ"ንጉሥ ሆይ! በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናልና ኃይልህን አንሥተህአስታግስልን ብለው ጠየቁት ዳግማዊ ዓጼ ዳዊትም ለመንፈሳዊ ኃይማኖት ቀንተው የክርስቶስ ፍቅርአስገድዷቸው 20,000 ሠራዊት አስከትለው ወደ ግብጽ ዘመቱ በዚህ ጊዜ በግብጽ ያሉ ኃያላን ፈሩተሸበሩ ንጉሡ ዳግማዊ ዳዊትም እንዲህ የሚል መልዕክት ለእስላሞቹ ላከ በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁከሆኑት ክርስቲያኖች ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋለሁ" የሚል ማስጠንቀቂያ ላከ፡፡የንጉሡ መልዕክትም ለእስላሞቹ እንደደረሳቸው ፈርተው እንደ ጥንቱ በየሃይማታቸው ጸንተውበሰላም እንዲኖሩ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ታረቁ፡፡ መታረቃቸውን ዓጼ ዳዊት ሰሙበዚህም ጉዳይ ንጉሡ ደስ አላቸው፡፡

እግዚአብሔርንም አመሰገኑ በግብጽ የሚኖሩ ክርስቲያኖችምከ12,000 ወቄት ወርቅ ጋር ደስታቸውን ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ለዳግማዊ ዳዊት በደብዳቤአድርገው ላኩላቸው፡፡ ንጉሡም የደስታውን ደብዳቤ ተመልክተው ደስ አላቸው ወርቁን ግንመልሰው በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ፡፡ በግብጽ የምትኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ የላካችሁልኝ 12,000 ወቄት ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ፡፡ የእኔ ዓላማ ወርቅፍለጋ አይደለም የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ አሁንምየምለምናችሁ በሀገሬ ኢትዮጵያ ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስየተሰቀለበት ቅዱስ መስቀልና የቅዱሳን አጽም ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ ነውየሚል ነበር፡፡

በእስክንድርያም ያሉ ምዕመናን ይህ መልዕክት እንደደረሳቸው ከሊቃነ ጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳቱጋር ውይይት በማድረግ ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ ልቡን ደስ እንዲለውየፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል ከቅዱሳን አጽምና ንዋየ ቅዱሳት ጋር አሁን በመለሰው ወቄትወርቅ የብርና የነሐስ የመዳብና የወርቅ ሣጥን አዘጋጅተን እንላክለት ብለው ተስማምተው በክብርበሥነ ሥርዓት በሠረገላና በግመል አስጭነው ስናር ድረስ አምጥተው ባስረከቧቸው ጊዜ በእጃቸውእያጨበጨቡ በእግራቸው እያሸበሸቡ በግንባራቸው እየሰገዱ በክብር በደስታ ተቀበሏቸው፡፡

ግሸን ደብረ ከርቤ ግማደ መስቀሉ የሚገኝበት
 
ግማደ መስቀሉ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ሳይደርስ በድንገት ዓጼ ዳዊት ስናር በሚባልበረሀ ላይአረፉ፡፡ ግማደ መስቀሉም የግድ በዚያው በስናር መቆየት አስፈለገው፡፡ ከዚህ በኋላ የሟቹየዳግማዊ ዳዊት ልጅ ዓጼ ዘርዓ ያዕቆብ እንደነገሠ ወደ ስናር ሔደው ግማደ መስቀሉን ከሌሎቹንዋያተ ቅዱሳት ጋር አምጥተው በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን ላይ ቤተመቅደስ ሠርተውለማስቀመጥ ሲደክሙ በሕልማችው ‘’ አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል‘’ ወዳጄ ዘርዐ ያዕቆብሆይ መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ የሚል ሕልም አዩ፡፡

ከእስክንድርያሀገር ከመስቀሉ ጋር በልዩ ልዩ ሣጥን ተቆልፈው የመጡትም ዝርዝር ስማቸው ጌታ በዕለተ ዓርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ፣ ከሮም የመጣው ከለሜዳው፣ ሐሙት የጠጣበት ሰፍነግ /ጽዋ/፣ ዮሐንስ የሳለው ኩርዓተ ርዕሱ ስዕል እንዲሁም የተለያዩ የቅዱሳን አጽም፣ ከግብጽ ታላላቅ ገዳማት የተቆነጠረአፈር፣የዮርዳኖስውሃይገኛል፡፡ ንጉሡም መስቀለኛ ቦታ እየፈለጉ በኢትዮጵያ አውራጃዎች ሁሉበመፈለግ ከብዙ ቦታ አስቀምጠውት ነበር፡፡ ለምሳሌ በሸዋ በደብርቅዱስደብረጽጌ ማርያምገዳም፣ በማናገሻ ማርያም፣ በወጨጫ መስቀሉን አሳርፈውት ነበር፡፡ ነገር ግን የመጨረሻውን ቦታባለማግኘታቸው በራዕይ እየደጋገመአንብርመስቅልየበዲበመስቅል መስቀሌን በመስቀለኛ ሥፍራአስቀምጥ እያለ ይነግራቸው ነበር፡፡ ዓጼ ዘርዓ ያዕቆብም ለሰባት ቀን ሱባዔ ገቡ፡፡

በዚያምየተገለጸላቸው መስቀለኛውን ቦታ የሚመራህ ዓምደብርሃን ይመጣል አላቸው፡፡ እርሳቸውም ከዚያእንደወጡ መስቀለኛውን ቦታ የሚመራ የብርሃን ዓምድ ከፊታቸው መጥቶ ቆመ፡፡ በዚያ መሪነትወደ ወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል አውራጃ ውስጥ ግሸን ከምትባል አምባ መርቶመስከረም21ቀን1440ዓም አደረሳቸው፡፡ በእውነትም ይህች ግሸን የተባለችው አምባ ጥበበኛ ሰው እንደቀረጻትየተዋበች መስቀለኛ ቦታ ሆና ስላገኟት የልባቸው ስለደረሰ ደስ አላቸው፡፡ በዚያም አምባ ታላቅቤተመቅደስ ሰርተው መስቀሉንና ሌሎች ንዋየ ቅዱሳቱን በየመዓረጋቸው የክብር ቦታ መድበውአስቀመጡዋቸው፡፡ ዘመኑም በ14ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡


የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ


በሀገራችን በኢትዮዽያ የመስቀል በዓል የሚከበረው አበቦች በሚፈኩበት የጥቢ ወራት መግቢያ በመኾኑ ጸሎቱም (መስቀል ኣብርሃ በከዋክብት አሠርገወ ሰማየ እምኵሉሰ ፀሐየ አርኣየ) ሲሆን ሕዝባዊ ዜማውም (ኢዮሀ አበባዬ ÷ መስከረም ጠባዬ)በማለት የመስቀልን ክብር ሳይለቅ ነው፡፡

በተያያዘም በወሎ ክፍለ ሀገር በአንባሰል አውራጃ ውስጥ ግሸን ማርያም የምትባል ደብር ትገኛለች፡፡ግሸን አምባ ከአዲስ አበባ 480 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ቅድስት ሥፍራ ናት። ይህች ደብር በሐይቅና በመቅደላ በደላንታ በየጁ መካከልና በበሽሎ ወንዝ አዋሳኝ በርዋ አንድ ዙርያውን በገድል የተከበበች አምባ ናት፡፡ በበርዋ ከተገባ በኋላ ግቢዋ፣ ከላይ ሜዳና መስቀለኛ ቦታ ነው፡፡ ወደዚህች ደብር ለመሔድ በረሃን አቋርጦ ተለያየን ወንዝና በሽሎን በመሻገር የተጠማዘዘ አስፈሪ ገደሉን ማለፍ ግድ ይላል፡፡ ግሸን የመጀመርያ ስሟ ደብረ እግዚአብሔር በመባል ይጠራ ነበር፡፡

ይህ ደብረ እግዚአብሔር የሚለው ስያሜም በጻድቁ ንጉሥ ላሊበላ እጅ ከቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍሎ
 
የተሠራ ቤተመቅደስ በእግዚአብሔር አብ ስም ስለነበረ ደብረ እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ከዚያም በዓጼ ድግናዥን ዘመነ መንግሥት የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሲመሰረት ሐይቅ ደብረ ነጐድጓድ ተብሎ ሲሰየም ግሸን የሐይቅ ግዛት ስለሆነች ደብረ እግዚአብሔር ተብላለች፡፡ ከዚያም በ14ኛው መቶ ከፍለ ዘመን ላይ በዓጼ ዘርአያዕቆብ ዘመነ መንግስት ግማደ መስቀሉ ግሸን ገብቶ ሲቀመጥ ደብረ ነጐድጓድ የሚለው ደብረ ከርቤ በማለትተቀይሮአል፡፡ በጊሸንደብረከርቤ አምባ በሁሉም ማዕዘንአብያተ ክርስቲያናት የታነፁ ሲሆን ከመስቀሉ ራስጌ የእመቤታችን፣ ከመስቀሉ ግርጌ የቅዱስሚካኤል ከቀኝ ክንፉ ላይ ቅዱስ ገብርኤል ከግራ ክንፉ ደግሞ ቅዱስ ዑራኤል ሲሆኑ መካከሉ ላይመስቀሉ የተቀበረበት የእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ይገኛል፡፡
***************************************************************************ምንጭ:--ጉዳያችን(http://gudayachn.blogspot.no/2013/09/blog-post_22.html)

Wednesday, July 16, 2014

የግጥም ጥግ

አገር ያለፍቅር -ፍቅርም ያለአገር

(የገጣሚና ጋዜጠኛ ነብዩ መኮነን ግጥም)
*************************************
መቼም ጮኸው ካልዘመሩት ; ነጻነት ቃሉ አይሰማ
ባንዲራው የሰማይ ችካል ; የፀሐይ እግር ኅብር -አርማ
ከቶም አገር ያለፍቅር ; ፍቅርም ያለውድ ሀገር
ነብስ የለሽ ስጋ ነውና ; እርሻ ያለ -ፍሬ መከር
ጀግና በልቡ እንደሚዳኝ ; በመንፈሱ ጽናት ካስማ
አገር ያለ ፍቅር ጠበል ; ፍቅር ያለ አገር ሙቅ ማማ
ከቶ አንዱም ያለ አንዱ አይለማ !
የልብ ወኔ ንዝረትኮ ; የአበው በገና ነው ምቱ
ወትሮም የሸንጎ ተውኔቱ ; ጥበብ ፋኖ ነው ቅኝቱ !
ማተብ እንደክራር ሲከር ; ቃኝው አርበኛ ነው ጎምቱ !
ያ ነው የነፃነት ዕፁ ; የሀገር ፍቅር ዕውነቱ ::
ለዚህ ነው ጥበብ መቆሟ ; ለሰው ልጂ ለሚሟገቱ !
ዱሮም ከሰቆቃ አንጀት ነው ; ኃያል ዜማ
________________________ የሚወለድ
በአርበኝነት ጥበብ ላንቃ ; ያገር ፍቅር እሳት ሲነድ !

ከዛሬ ስልሳ ዓመት በፊት ...
አገር ተወረረችና ; በነጭ አረመኔ መዓት
ሞትና ስደት አጠጠ ; አንዱ ዘመን ጣር በዛበት ::
መቼም ሰው ጠላቱን አይመርጥ ; የባላንጣም ቦቃ
___________________________ __የለው
በተለይ ባገር የመጣ ; የአገር ክንድ ነው 'ሚቀምሰው ::
የሀቅ ዐይኗ ተደንቁሎ ; የሰላም ብሌን ተጓጉጦ
የአውሮፖ ግፍ እንደጎሽ ግት ; አመፃው እንደጉድ
________________________________ፈጦ
አበሻ ሰቆቃው መጥቆ ;መከራ ሌት ከቀን ባርቆ
ሳቅ እንደዘላለም ርቆ
ጣሊያን ባመጣው ፍዳ አሣር ;በበላዔ -ሰብ ትናጋ
ጦቢያ ባንድ ልብ ደምቶ ; ከጠላት ግንባር ሊላጋ
ከፋሺስት ጥርስ ሊወጣ ; ከግፉ መንጋ መንጋጋ
አንድም ቅኔ ; አንድም ወኔ : ነፃነት ፋና ፍለጋ
አንድም ምሬት ; አንድም እሬት ; በህይወት
________________________ተውኔት አለንጋ
አንድም ፊድል ; አንድም ገድል : የግፍ ምዕራፍ
____________________________እስኪዘጋ
ጥበብን ማተብ አረጋት ; የአርበኛ ልቡን ሲያተጋ

መቼም መከራ ዳር አያውቅ
አንዱ ጠላት ከዚያ ዘልቆ ; አንዱ ጠላት ከዚህ ፈልቆ
ፋሺስትና ባንዳ ፈልቶ ; የወራሪ ግፉ ልቆ
ዕምነት እንደቅሌት አዋይ ; እንደ እራፊ ተበጫጭቆ
ስንቱ በደል እንደባህር ;ስንቱ ዕንባ ከኅዋ መጥቆ ...
አንድነት እንደሩቅ ዋይታ ; በሚስጥር ጎራ ለጎራ ;
በሙሾው ዋልታ ለዋልታ
በመቀነት በዝናር ድግ ; በዱር ትንፋሽ -በሹክሹክታ
ነበር ; እስኪነጋ ጀንበር ::
ፋኖ የልቡን አታሞ ; በአጥንቱ ቋር እየመታ
ነብሱን ከቸነከረበት ; የነፃነት ጎለጎታ
በደሙ ስርየት ሊያመጣ ; በእልሁ ድሆ አፍታ ካፍታ
ሰንደቅ አላማ እንደግማድ ;ተሸክሞ ነው የረታ ::
ጠላት ባንድ ፊት ሲባረር ;ባንዳ ባንድ ፊት ሲወገር
አገር በኪን አፍ ሲመሰክር
ፍቅር በጥበብ ሲዘከር
ኪነት እንደኩራት እርሾ
ቴያትር እንደጎበዝ ማሾ
መራር ያገር ፍቅር ዜማ
ከመድረኩ ዱር ሲያሰማ
ሽቅብ ሲል እስከነፃነት
ቁልቁል ሲል እስከአማን መሬት
ቃሉን በቃናው ልጎ ; ዳንሱን ሶምሶማ አድርጎ
ጦር ውስጥ በደሙ ሠርጎ
ትውልድን ለዛሬ አበቃ ; ስንቱ በጥበቡ ኮርቶ
አይሰው ተሰውቶ ; እስከ ንጋት ጎሁ ሞቶ !
ያ ነው ያገር ፍቅር ማለት ; የጥቁርም አህጉር ፀጋ
ማንም የማይሽረው ምትሀት ; ደም ያጠራው ታሪክ ዋጋ
መከራ አሳር ሲቀበል ; አርበኛ ገድሉን ሲሰራ
ጣልያንን "" ጣል -ያን !"" እያለ ;ጥልያንን ""ጥል -ያኔ !""
_____________________________________እያለ
አንዱ ጎራው ጥበብ ነበር ; የአገር የሽመናው ስራ
እየታየው የንጋት ጎህ ; በደም የተቀባው ሸራ
ያው ታሪኩን ቀልሞበታል ; የውሎ ገድሉን ደመራ ::
ፈርሶ የመገንባቱ ....ወድቆ የመነሳቱ
ይኸው ነው የታሪኩ ጽንስ ;የሀገር ፍቅር እትብቱ !!
እናም አገር ያለፍቅር ; ፍቅርም ያለውድ አገር
ደሞም ያለጥበብ አጋር
ለአፍታም ለዝንተ -ዓለምም
አንዱ ያላንዱ አይኖርም ::
አገር ቢሉ ፍቅር ነው
ፍቅርም ቢሉ አገር ነው
አገር -ፍቅርም ይኼው ነው !

****************************
ሐምሌ 1993 ዓ .ም
(ለሀገር ፍቅር ዳግም ልደት )

ከስውር ስፌት ገጽ 50-52.

Thursday, June 12, 2014

ካሳየን አጣሁት – አቦነሽ አድነው


 

ለጎንደሩ ጀግና ለጠፋው መቅደላ፣
አብሮ አልቅሱለት ቋራና ኦሜድላ፣
ፍቅሩም ሳይወስነው በትግሬ በወሎ፣
እራሱን የጣለው ጦቢያን አድን ብሎ።
ምንጊዜም ይወራል ዝናው፣
በታሪክ አይሞትም ጀግናው፣
ይጠራል ስሙ በዚህች ምድር፣
ላገሩ ስለዋለው ብድር።

በሰንበት ባውዳመት ተጎድቼ በባል፣
እንግዲህ ምንጠቅሞኝ ተዋበችስ ብባል፣
ከፍቅሬም ካካሌም ባንዴ እየተለየሁ፣
ቀረሁኝ በተስፋ እያልኩ ዓለማየሁ።



 እናቴ ሞሽራ ልትድረኝ ለጀግና፣
ተነስቶ ባገሩ አንድነት ያፀና፣
ሚስት ናት ገረድ ናት ሲለኝ እንዳልኖረ፣
ነፍሱን ላገር ሰጥቶ የኔ ካሳ ቀረ።
ከንግስ ከግርማዊነት ያኮራል ያለው ጀግንነት፣
ወገኔ ጥለህ ተሰደድ እያየው የሱ ጀግንነት።
ዓለማየሁ ብሎ ሀዘንን መቀበል፣
ዕጣው በኔ ሲደርስ እንግዲህ ምን ልበል፣
ጎንደርን ማሳለፍ ምንስ ጎደለብኝ፣
መቅደላ ነው እንጂ ካሳው የቀረብኝ።
 
ሙሉ ቤቴን ሳጣው አላልኩም እየዬ፣
የኑሮ መከታ ባላገር ነው ብዬ፣
ተዋቡ ለሚለኝ ለፍቅሬም ሳይሳሳ፣
ከኔ ለበለጠው ለአገር ሆኗል ካሳ።

ማተብ በጥሶ ቃል ከማጠፍ፣
ይሻላል ቆርጦ ነፍስን መቅጠፍ፣
ሆነልት እንጂ ታሪክ ርስቱ፣
አላጓጓውም ቤተመንግስቱ።
ይሄ ነው ቆራጥ ይሄ ነው ጀግና፣
በታላቅ ስራው ፍቅሩን የሚያፀና።


ስሙ አባታጠቅ የሱ ፈረስ፣
ያውቃል ካሰበው ፈጥኖ መድረስ፣
ቼ እያለ ገስጋሽ ብርቱ ጋላቢ፣
ሜዳነው ሲሉት የሚገኝ ግቢ።
ዘውዱ ነበርኩኝ በሚስትነቴ፣
ንጉሴን አጥታ ጠፋች እናቴ፣
በጎዶሎ ቀን በዕድለ አንካሳ፣
አልኖርም አለች ነፍሴ ያለካሳ።



 


ማተብ በጥሶ ቃል ከማጠፍ፣
ይሻላል ቆርጦ ነፍስን መቅጠፍ፣
ሆነልት እንጂ ታሪክ ርስቱ፣
አላጓጓውም ቤተመንግስቱ።
ይሄ ነው ቆራጥ ይሄ ነው ጀግና፣
በታላቅ ስራው ፍቅሩን የሚያፀና።






https://www.youtube.com/watch?v=ZVKUwPtV5ec 

Tuesday, June 3, 2014

የሙዚቃ ሊቁ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ

የሙዚቃ ሊቁ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ
(ከ 1930 - 1990 ዓ.ም)
በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ እውቀት ላይ የተመሠረተ ትምህርት በመማር የላይኛው
ጥግ ላይ የደረሰ ነው። በሀገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሙዚቃ ት/ቤት እንዲከፈት አስተዋፅኦ
ካደረጉ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። በዚሁ የሙዚቃ ት/ቤት ማለትም በቅዱስ ያሬድ ሙዚቃ
ት/ቤት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዳይሬክተር ሆኖ አገልግሏል። ከዚህምአልፎ በዓለም
አቀፍ ደረጃ የሙዚቃን ጥበብ እና መንፈስ ሲያስተምር የኖረ ነው። ዛሬ የሕይወት ታሪኩን
በጥቂቱ የምናነሳሳለት ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ሊቅ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ነው። አሸናፊ
ከበደ የተወለደው እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በ 1930 ዓ.ም ነበር። አሸናፊ ከበደ ገና
በህፃንነቱ ድክ ድክ ሲል ነው ከሙዚቃ ጋር የተዋወቀው። የተዋወቀበትም አጋጣሚ በእናቱ
በኩል ነው። ወላጅ እናቱ ሁሌም ትዘምራለች። መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ሀረጋት
ከመዝሙረ ዳዊት ውስጥ እያወጣች ትዘምራለች።
ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ዜማዎችን ታንጐራጉራለች። ታዲያ ይህ መዝሙር እና እንጉርጉሮ በሕፃኑ
አሸናፊ ልብ ውስጥ፣ ጭንቅላት ውስጥ እና በአጠቃላይ እዝነ ልቡናው ውስጥ እየተዋሀደው
መጣ። የሙዚቃ ረቂቅ ስሜት እና ፀጋ በእናቱ በኩል ወደ እርሱ ተሸጋግራ አሸናፊ ውስጥ
ጓዟን ጠቅልላ ገባች። የሥነ-ጽሑፍ መምህሩ እና ታዋቂ ገጣሚ የሆኑት ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በ
1980 ዎቹ አጋማሽ ላይ Ethiopian Review በተባለ መፅሔት ላይ እንደፃፉት ከሆነ
የሙዚቃ ለዛ እና ጣዕም ኮተቷን ሰብስባ ወደ አሸናፊ ከበደ ሰብዕና ውስጥ የገባችው በእናቱ
በኩል ነው። እናቱ አሸናፊ ከበደ የሚባል የሙዚቃ ሊቅ ፈጥራለች እያሉ ፅፈው እንደነበር
አንብቤያለሁ። ታዲያ ምን ያደርጋል ይህች እናት ተልዕኮዋን ፈፀመች መሰል፣አሸናፊ ከበደ
ገና የዘጠኝ ዓመት ጮርቃ ሳለ ሕይወቷ አለፈች።
ግን የዘራቻት ዘር ዘላለማዊ ፀጋ ተጐናፅፋለችና ከአሸናፊ ከበደ ጋር አብራ አደገች፤ በኋላም
በአሸናፊ በኩል ተወለደች። ከዚያም እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ
እንዳስደሰተች ትኖራለች። እ.ኤ.አ በ 1999 ዓ.ም ኪምበርሊን ቺንታ የተባሉ ፀሐፊ ስለ
አሸናፊ ከበደ የሕይወት ታሪክ ፅፈው ነበር። ርዕሱም The Scholarship and Art of
Ashenafi Kebede (1938-1998) የሚል ነበር። በአማርኛ “ምሁሩ እና ጥበበኛው
አሸናፊ ከበደ ከ 1930-1990 ዓ.ም” ብለን ልንተረጉመው እንችላለን። ታዲያ በዚህ ጽሁፍ
ውስጥ ፀሐፊው ከሚገልጿቸው ሃሳቦች መካከልየአሸናፊ ከበደን የእውቀት ርቀት እና ጥልቀት
ነው።
እንደ ፀሐፊው አባባል ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ኢትዮጵያ ካሏት (ካፈራቻቸው)
የባህልናየማንነት ቅርሶች መካከል በሙዚቃው ዓለም ትልቁን ስፍራ የሚይዝ ነው። አሸናፊ
የኢትዮጵያ የባህል ቅርስ ነው። የሙዚቃ አቀናባሪ ነው። መራሔ-ሙዚቃ /Conductor/
ነው። የሙዚቃ ታሪክ ተመራማሪ ነው። የሙዚቃ መምህር ነው። የልቦለድ ድርሰት ፀሐፊ
ነው። ባለቅኔ ነው። ወደር የማይገኝለት ጥበበኛ እያለ ኪምበርሊን ቺንታ ፅፏል።
Professor Ashenafi Kebede, one of Ethiopia’s greatest
cultural treasurescomposer, conductor, ethnomusicologist,historical musicologist, music educator, novelist and poet.
እየተባለ ለፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ተፅፏል።



አሸናፊ ከበደ አብሮት ያደገውን የሙዚቃ ፍቅር ቅርፅ ሊያሲይዘው በ 1950 ዓ.ም ወደ
ዩናይት ስቴትስ አሜሪካ ተላከ። እዚያም Eastman School of Music ከተባለ
ዩኒቨርሲቲ በሙዚቃ ጥናት በ B.A ድግሪ ተመረቀ። ከዚያም ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ መጥቶ
የቅዱስ ያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት እንዲከፈት ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት መካከል አንዱ ስለሆነ
በተጨማሪም ደግሞ ሙዚቃን እንደ ጥበብ ተምሮ የመጣ ወጣት በመሆኑ የመጀመሪያው
የት/ቤቱ ዳይሬክተር ሆኖ ተሾመ። በዚህ በቅዱስ ያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት ለአምስት ዓመታት
ካገለገለ በኋላ እንደገና የሁለተኛ ድግሪውን ሊያጠና ወደ አሜሪካ ተጓዘ። Wesleyan
University ገብቶ በ 1960 ዓ.ም የማስትሬት ድግሪውን ተቀበለ። የሙዚቃ ሊቁ አሸናፊ
ከበደ በዚህ ብቻም አላቆመም። የሙዚቃን ጥግ ማወቅ ስላለበት የዶክትሬት ድግሪውንም
ሊያጠና አመለከተ። ከዚያም የመግቢያ ፈተና ተሰጠው። ፈተናውንም በከፍተኛ ውጤት
አልፎ የዶክትሬት ድግሪውን መማር ጀመረ። በአስገራሚ ብቃት እና ችሎታ የአራት ዓመቱን
ትምህርት በሦስት ዓመት ውስጥ አጠናቆ በ 1963 ዓ.ም የዶክትሬት ድግሪውን እንዳገኘ
የሕይወት ታሪኩ ያወሳል።
አሸናፊ ከበደ በሙዚቃው ዓለም የተማረውና የዶክትሬት ድግሪውን ያገኘው ሙዚቃን
ከባሕል፣ ከታሪክ፣ ከማንነት፣ ከቋንቋ፣ ከሰው አንፃር በሚያጠናው የትምህርት ክፍል ማለትም
ethno-musicology የትምህርት ዘርፍ ነው። በዚሁ የትምህርት ዘርፍ የዶክትሬት
ድግሪውን ያገኘው በከፍተኛ ማዕረግ ነው። የሚገርመው ማዕረጉ አይደለም። በዚህ
የትምህርት ዘርፍ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ የመጀመሪያው ተመራቂ እንደሆነም ተፅፎለታል።
ስለዚህ አሸናፊ የባሕል፣ የታሪክ፣ የማንነት፣ የቋንቋ እና የሰው ልጅን ስነ-ልቦና በሙዚቃ
ዓለም ውስጥ የሚያጠና እና ሙዚቃንም የሚቀምር ባለሙያ ነበር። አሸናፊ ከበደ፣ የሕይወት
አጋጣሚ ጠለፈችውና አሜሪካ የምትባል ሀገር አለቅህም ብላ ያዘችው። በተፈጥሮ እና
በትምህርት የተሰጠውን ፀጋ በአሜሪካ ልዩ ልዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ማስተማር ቀጠለ።
በመጀመሪያ ያስተምር የነበረው Queens College ውስጥ ነበር። እዚያ የተወሰኑ
ዓመታትን ካገለገለ በኋላ የማስትሬት ድግሪ ተመራቂ ተማሪዎች ወደሚማሩበት The City
University of New York ተብሎ ወደሚጠራው ተቋም ተዘዋውሮ ማስተማሩን
ቀጠለ። ከዚያም Brandeis University በሚባለው የሙዚቃ ት/ቤት ውስጥ አስተማረ።
ከነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ሌላም በተለያዩ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተጋባዥ ፕሮፌሰር
እየሆነ ሙዚቃን ለአሜሪካ ያስተምር ነበር።
አሸናፊ ከበደ ከማስተማሩ ጐን n ለጐን በስፋት የሚታወቅበት ችሎታው የጥናትና የምርምር
ሰው መሆኑ ነው። በተለይ በአፍሪካ ባሕሎችና ታሪኮች ላይ የተለያዩ የምርምር ወረቀቶችን
አቅርቧል። ከአፍሪካም ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ እያተኮረ የዚህችን ሀገር ጥንታዊ ስልጣኔና
ማንነት እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የዋለችውን የታሪክና የባህል ብሎም
የስልጣኔ ውለታ በጥናቱ ያካትት ነበር። ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፣ 
ዓለም ገናከእንቅልፉ ሳይነቃ በዝማሬና በዜማ በኩል ያበረከተውን አስተዋፅኦ አሸናፊ ለዓለም
ሲያስተዋውቅ ኖሯል።
አሸናፊ ከበደ በተለያዩ አፍሪካዊ ጥናቶቹ እና ምርምሮቹ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ በሙዚቃው
ዓለም ተቀብሏል። ወደ ፍሎሪዳ ስቴትስ ዩኒቨርሲቲም በመሄድ የጥቁሮች የባሕል ማዕከል
/Center for Black Culture/ ተብሎ በሚጠራው ተቋም ውስጥ ዋና ዳይሬክተር ሆኖ
ተሾመ። ይህ ተቋም በኋላ “የአፍሪካ አሜሪካውያን የባህል ማዕከል” በሚል መጠራት
ጀምሯል። እስከ አሁንም ድረስ መጠሪያው Center for African American Culture
እየተባለ ነው። ዳይሬክተሩ ደግሞ ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ሊቅ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ
ነበር።በዚህ ታላቅ ተቋም ውስጥ ዳይሬክተር ከሆነ በኋላም፤ ጥቁሮች እና ነጮች እንደ ሰው
የሚያገናኛቸውን ባሕላዊ፣ ሙዚቃዊ እና ታሪካዊ ጉዳዮችን እያነሳሳ ያወያያል። ያቀራርባል።
የተለያዩ ታላላቅ የዓለማችንን የሙዚቃ ሊቆች እየጋበዘ ኮንሰርቶችን እና አውደጥናቶችን
ሲያዘጋጅ ኖሯል። ፕሮፌሰር አሸናፊ ደራሲም ነው። በተለይ የጥቁር ህዝቦችንየሙዚቃ
ታሪክና ባህል ብሎም ማንነትን በሚያሳየው Roots ofBlack Music በተሰኘው
መፅሐፍውስጥ አያሌ መጣጥፎችን በዋናነት የሚፅፈው ይኸው ኢትዮጵያዊው ሊቅአሸናፊ
ነበር። በ 1959 ዓ.ም ደግሞ ሀንጋሪ ውስጥ The Black Kodaly በተሰኘ ዝግጅት ላይ
ባለ ዋሽንቱ እረኛ /The Shepherd Flutist/ በሚል ርዕስ አጅግ ድንቅዬውን ሙዚቃ
አቀረበ። ይህ ባለ ዋሽንቱ እረኛ የተሰኘው ሙዚቃ በዘመኗም ሆነ እስከ አሁን ድረስ የረቂቅ
ሙዚቃዎች ሁሉ የቁጥር አንድ ቦታዋን እንደያዘች ትገኛለች። ፕሮፌሰር አሸናፊ
ሌሎችአያሌ ሙዚቃዎችንም ተጫውቷል። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ሰፊ ምርምርና ጥናት
ያደረገው ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ፣ ዛሬም ድረስ ፅሁፎቹ በአሜሪካን ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች
መማሪያዎች ናቸው። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሙዚቃ እና ባህል ላይ ተመርኩዞ ባህሉንና
እድገቱንየፃፈበት የዶክትሬት መመረቂያ ፅሁፉ በቅርቡ በአንድ ጆርናል ላይ ዳሰሳ
ተሰርቶበታል። የዶክትሬት መመረቂያ ፅሁፍ ርዕሱም The Music of Ethiopia: Its
Development and Cultural setting የሚል ነበር። ኢትዮጵያ ሐገሩን እናህዝቦቿን
በተለይም ደግሞ መላውን አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲያስጠራ የኖረው ፕሮፌሰር አሸናፊ
ከበደ ግንቦት አንድ ቀን 1990 ዓ.ም በ 60 ዓመቱ ፍሎሪዳ ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት
ተለየ። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ሊቅ አረፈ እያሉ በርካታ ሚዲያዎች በጊዜው ዘግበውለታል።
አሸናፊ ከበደ የሦስት ሴቶችና የአንድ ወንድ ልጅ አባትም ነበር። የመጀመሪያ ልጁ ኒና አሸናፊ
ዳኛ ናት። ሰናይት አሸናፊ ደግሞ ተዋናይት ሆናለች። ሦስተኛዋ ሴት ልጁ ሳምራዊት አሸናፊ
ስትባል ወንድየው ደግሞ ያሬድ አሸናፊ ይባላል። በአጠቃላይ ሲታይ የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ
የጥናትና የምርምር ፅሁፎች በአብዛኛው አሜሪካ ውስጥ ስለሚገኙ የያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት
ሰብስቧቸው ለትውልድ መማሪያ እንዲሆኑ ማድረግ አለበት እላለሁ። በተረፈ እንዲህ አይነት
የሙዚቃ ሊቅ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲፈጠር ሁሉንም ነገር ያመቻቹለትንም ግርማዊ
ቀዳማዊ ኃይለስላሴም ምስጋና ይገባቸዋል።
***********************************************************
ምንጭ :--ሰንደቅ 9 ኛ ዓመት ቁጥር 447 ረቡዕ መጋቢት 24 2006 ዓ.ም.