ከደራሲያን ዓምባ

Thursday, March 14, 2019

የአክሱም ጫፍ አቁማዳ

ገጣሚ ደበበ ሰይፉ
*****************



















ትግራይ ላከ ወሎ ጋ አበድረኝ ብሎ አንድ ቁና ጤፍ
ወሎም አፈረና የለኝም ማለቱን ባህሉን መዝለፍ ቆሌውን መንቀፍ
ላከ ወደ ሸዋ ምናልባት ቢሰጠው ለሰው እሚተርፍ፡፡
ሸዋም አፈረና የለኝም ማለቱን ወደ ሐረር ዞረ
ሐረርም መልሶ ባሌን አተኮረ
ባሌም ወደአርሲ ፤ አርሲ ሲዳሞን
ሲዳሞም ተክዞ ፤ ግን የለኝም ብልስ ማን ያምነኛል ብሎ
ወደጋሞ ላከ አቁማዳ ጠቅሎ፡፡

ጋሞን ብርድ መታው ሐዘን ገባውና
የራሱን ምንዳቤ የግል ስቅየቱን ችሎት በጥሞና
በጋቢ ደቡኖ የልቡን ጠባሳ ሲኖር እንደደህና
ዛሬ የወንድሙን የእርዳኝ አቤቱታ መስማት አልቻለና፡፡
አውጥቶና አውርዶ ላከ ወደ ከፋ እጅግ አስተዛዝኖ
ከሀፍረት ያድነኛል ፤ከረሃብ ያወጣኛል ሲል ባያሌው አምኖ፡፡
ከፋ እንደደረሰው በድንገት አቁማዳው በነብሱ ዋይታ
ሐራራው ተሰማው የሥጋው ድንፋታ
በብልሃት አዛጋ ቆይቶ ቆይቶ የተስፋ ጠል ቀዳ
ሲልክ ከኢሉባቦር አበድረኝ ብሎ እህል በአቁማዳ፡፡
ጭምቱ ኢሉባቦር ይኖር የነበረ የቤቱን ጉድ ጓዳ
በሞኝሞኝ ገላው ቆዳው ውስጥ ወሽቆ
ጠየቀ ወለጋን ሐፍረቱን ደብቆ ኩራቱን ዘቅዝቆ፡፡
ኬት አመጣ ብሎ ወደኔ ላከብኝ እያለ ወለጋ
እጅጉን ተደሞ
ሄደ ወደጎጃም ዛሬን ሁነኝ ብሎ ሲማፀነው ቁሞ፡፡
ጎጃምም ተሰምቶት ፤ሰቀቀን ሐዘን
ደረት እየመታ ፤ ቅኔ እያወረደ ፤እንባ እያፈሰሰ
ወግና ኩራቱን በየቦዳው መሐል እየነሰነሰ
ዐባይን ተሻግሮ ከጎንደር ደረሰ፡፡
ፋሲል ላይ ተነጥፎ፤ ጎንደርም ሐዘን ላይ ነበረ ተቀምጦ
ተድላ ልጁ ሙቶ ፣ ገናን ክንዱ ታጥፎ በዘመን ተድጦ
ጎጃም መጣ ሲሉት የእዝን የተመኘን ልቡን በታዘበ
የኩራት ካባውን ሊጥል ባንጓበበ
የወንድሙ መምጣት እቅጩ መንስዔ ፤መሆኑን ሲረዳ ረሀብ አበሳ
ጥንትም አልሆነኝም ከእንግዲህ ይበቃኛል ለይሉኝታ አልሳሳ
ብሎ ከኤርትራ እህል ለመበደር በርትቶ ተነሳ፡፡

የዘመዱ እጦት ነበረና እጦቱ በዝቶ ሰቀቀኑ
ኤርትራ ታመመ ደም ጎረፈ ከዓይኑ
ወደትግራይ ላከ መላ ባገኝ ብሎ ከአደራ ደብዳቤ
"እባክህ ላክልኝ አንድ አቁማዳ እህል ልሞት ነው ተርቤ፡፡"
ትግራይ አስተውሎ አቁማዳው የራሱ መሆኑን ለይቶ
ረሃብ ዕጣቸው የሁሉ ወንድሞቹ መሆኑን አካቶ
ሐዘኑ አነቀው ፣ትንፋሹ መረረው ትካዝ ሆዱ ገብቶ፡፡
"እኔና ወንድሞቼ" አለ በለዘብታ
ለራሱ እንዲያወራ የራሱን ስሞታ፣

"እኔና ወንድሞቼ ሁላችን...ሁላችን
ከባዶ አቁማዳ ነው እሚዛቅ ፍቅራችን
ይህ ነው አንድነታችን
ይህ ነው ባህላችን
ዘመን ማ
ጋቱ በያንደበታችን፡፡
ለኋላ ትውልዶች ተረት እንዳይመስል ይህ ብካይ እሮሮ
ይህ ጠፍ ሰብእና ይህ ስቁይ አእምሮ
እንዳኖረው ያሻኛል ይህንን አቁማዳ ከፍ ካለ ስፍራ መጥቆ እንደባንዲራ
ምንም ባዶ ቢሆን በውስጡ አይጠፋና የታሪክ አዝመራ"

ይህንን ተናግሮ ከአክሱም ሐውልት ዘንድ ትግራይ ተጠግቶ
አንዴ እየፀለየ አንዴ እያወዘመረ ያለመጠን ተግቶ
ጫፉ ላይ ሰቀለው ያን አቁማዳ አውጥቶ፡፡
*************************************
ደበበ ሰይፉ
1967 ዓ.ም.

                   ይህው በድምፅ:-
                                          https://www.youtube.com/watch?v=7rSJw8ipadQ


Tuesday, October 23, 2018

ፀሐፊ ተውኔት ኃይሉ ፀጋዬ _በሸገር መዝናኛ

ሰብአዊ ስሜት ….የህሊና ‘ረፍት!_ኬቨን ካርተር


በፈረንጆቹ አቆጣጠር ማርች 1993 ‹‹ኬቨን ካርተር›› የተባለ ደቡብ አፍሪቃዊ የፎቶ ግራፍ ባለሙያ ሱዳን ውስጥ ተከስቶ በነበረው ችጋር የተነሳ ከተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ልኡክ ጋር ለደግነት በደቡብ ሱዳን ከተመ፡፡ በአንዱ መከረኛ እለትም ይህቺን ከታች የምትመለከቷትን ምስል በካሜራው አስቀረ፡፡
‹‹ርሀብ አድቅቆት የገዛ ራሱን መሸከም ያቃተው ህፃን ልጅ ‹‹……….እና ……..››ይህን ገላ ለመግመጥ የቋመጠ ጥንብ አንሳ››
የረሀብን ክፉ ገፅታ ….የድርቅን አሰቃቂ ሁነት….የምስኪኖችን እልቂት ….ቃላት ሊገልፁ ከሚችሉበት አቅም በላይ በሆነ መንገድ በድንቅ ካሜራው ለአለም አስቃኘ፡፡
‹‹ቀጫጫ እጆች…..እንኳን ለመሮጥ፣ለመቦረቅ ይቅርና የገዛ አካሉን ለመሸከም ያዳገተው እግር፣ መቆም የከበደው ገላ‹‹….. እና …….››ፈርጣማ አሞራ!!››


 ይህ ፎቶ እንደ እ.ኤ.አ በማረች 26 1993 ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ተሸጦ ታተመ፡፡ ምስሉ በመላው አለም ታየ፣ ክብር እና ዝናን አተረፈ፡፡ የባለሙያው ስም….ከፍ ከፍፍፍፍፍፍፍ…. አለ፡፡ተሸለመ፣ተሞገሰ፣ተከበረ፡፡
ከዚህ ሽልማት በውሀላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከአንድ ጥግ የተወረወረች ያልተጠበቀች ጥያቄ ግን የህይወቱን አቅጣጫ እስከወዲያኛው ቀየረችው፡፡አመሳቀለችው፡፡
‹‹ህፃኗ ልጅ እንዴት ሆነች….ታደግካት?????????>>
አይኖቹ ፈጠጡ….ላብ አጠመቀው………ቃላት ከአንደበቱ ጠፋ!!………..በሀሳብ ጥቂት ወደ ደቡብ ሱዳንዋ መንደር ተሰደደ፡፡ጠያቂው ግን ድጋሚ በጩኸት ጠየቀ
‹‹ህፃንዋን ልጅ ታደግካት ወይ????››
ካርተር ጋዜጣዊ መግለጫውን አቋርጦ ወጣ፡፡ ከወዳጅ ከዘመድ ሁሉ ተሰወረ፡፡ በብቸኝነት ገዳም ውስጥ….በፀፀት ተከተተ፡፡



በገዳይዋ ፊት ጥሏት የሄደው ጎስቋላ ህፃን ነፍስ ለወራት እንቅልፍ ነሳው፡፡የፎቶግራፍ ሽልማቱን ባሸነፈ በሶስት ወሩ በልጅነቱ ሲቦርቅ ባደገባት ‹‹ፓርክሞር›› በተባለች ለምለም ቀዬ በ33 አመቱ እራሱን ገድሎ ተገኘ፡፡
በሞቱ ዋዜማ ላይ ሆኖ ለወዳጅ ዘመዶቹ ባስቀረው ማስታወሻ የሚከተለውን ፀፀት አሰፈረ
.
“I’m really, really sorry. The pain of life overrides the joy to the point that joy does not exist… depressed … without phone … money for rent … money for child support … money for debts … money!!! … I am haunted by the vivid memories of killings and corpses and anger and pain … of starving or wounded children, of trigger-happy madmen, often police, of killer executioners … I have gone to join Ken if I am that lucky.”
ስንደመድም፡-
ከምንም ከምንም ነገር በፊት ሰብአዊ ስሜት!!! ክብር ፣ሽልማት፣ አዱኛ………ከሰውነት ወዲያ ይደርሳል!!!! /////////////////////////////////////////////////////********************///////////////////////////////////////////////////
ምንጭ:- http://getutemesgen24.com/
              http://100photos.time.com/photos/kevin-carter-starving-child-vulture

Monday, November 20, 2017

ሕዳር ሲታጠንና ዓለምን ያጠቃው የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ

ሀብታሙ ግርማ
***************
የ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ሁለት አስርት ዓመታት ለመላው የዓለም ህዝብ የሰቆቃ ዓመታት ነበሩ፤ ምክንያቱ ደግሞ የወቅቱ ሃያላን መንግስታት በሁለት ጎራ ሆነው ጦርነት ውስጥ ገብተው ስለነበር ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ1914 ዓ.ም እስከ 1918 ድረስ የዘለቀውና የ15 ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ይህ ጦርነት፣ በታሪክ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡  የጦርነቱ ማብቃት ሊታወጅ ጥቂት ሲቀረውና ዕልቂቱ ቆመ ሲባል ግን የዓለም ህዝብ ሌላ ፍዳ ማስተናገድ ግድ ሆነበት፤ በሰው ሰራሽ ችግሮች (በዋነኝነት በጦርነት) ተወጥሮ የቆየው መላው የአለም ህዝብ አሁን ደግሞ በእንፍሉዌንዛ በሽታ ከዳር እስከ ዳር  ተጠቃ፡፡

በተለምዶ የስፓኒሽ ፍሉ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ፣ መነሻው ከወደ አሜሪካ እንደሆነ ይታመናል፡፡ እ.ኤ.አ በጥር ወር 1918 ዓ.ም በአንደኛው የአለም ጦርነት ማብቂያ ዋዜማ፣ በጦርነቱ ለመካፈል የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት ከተከሰተው ወረርሽኝ ጋር ይያያዛል፡፡ በካንሳስ በሚገኘው ፉንስተን የወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የተቀሰቀሰው ወረርሽኙ፣ በሶስት ቀናት ብቻ 45 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አጠቃ፤ወታደሮቹ አትላንቲክን አቋርጠው አውሮፓን እንደረገጡ በሽታውም አውሮፓ ደረሰ፡፡ የእንፍሉዌንዛ በሽታው በአውሮፓ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በፈረንሳይ ቢሆንም በጦርነቱ ምክንያት ለፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ይሆናል በሚል ወረርሽኙ ለህዝብ ሳይገለጽ ተደብቆ ቆይቷል፡፡ በሽታው ይፋ የሆነው  እ.ኤ.አ በህዳር ወር 1918 ዓ.ም  በስፔን  ለመጀመሪያ ጊዜ በሽታው መታየቱን ተከትሎ ነበር፡፡ 


ስፔን በጦርነቱ ተካፋይ አልነበረችምና በአገሪቱ የጦርነት ጊዜ ሳንሱር አልነበረም፤ በመሆኑም የበሽታው መስፋፋት ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን በማግኘቱ ወረርኙ እስፓኒሽ እንፍሉዌንዛ (ስፓኒሽ ፍሉ) የሚለውን ስያሜ አገኘ፡፡
የበሽታው ምልክቶች ሳል፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ነስር፣ የጆሮና የአንጀት መድማት፣ ተቅማጥ፣ የአይን ማስለቀስና ውጋት ሲሆኑ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስም የአእምሮ ህመም ያስከትላል፡፡
  በሽታው ከኮሌራ ወይም ከፈንጣጣ በሽታዎች ጋር ተቀራራቢ ምልክቶችን ስለሚያሳይ ብዙ ያምታታ ነበር፡፡ የበሽታው አስገራሚ ባህሪ፣ አንድ ሰው በበሽታው በተጠቃ በአምስት ቀን ውስጥ ወይ ይሞታል አልያም ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ ይፈወሳል፡፡ ይህም እንደ ግለሰቡ የበሽታ መከላከል አቅም ይወሰናል፤ ቫይረሱ የተፈጥሮ የበሽታ የመከላከል አቅምን የሚያዳክም ሲሆን ጠንካራ የመከላከል አቅም ያለው ሰው ከአምስት ቀናት በላይ  መቋቋም ስለሚያስችለው  በስድስተኛው ቀን ፈውስ ያገኛል፡፡
የበሽታው አማጪ ቫይረስ ባለመታወቁ መድሃኒትም ሆነ ማስታገሻ አልተገኘለትም፡፡ (እ.ኤ.አ በ1933 ዓ.ም በእንግሊዛዊያን ሳይንቲስቶች እንደተረጋገጠው የበሽታው አማጪ ቫይረስ በሳይንሳዊው አጠራር H1N1 ተብሎ ይታወቃል፡፡) በዚህም የተነሳ የበሽታውን ስርጭት ለማቆም አልተቻለም፡፡ በጥቂት ጊዜም ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከኤሽያ እስከ አፍሪካ፣ከአርክቲክ እስከ ፓስፊክ ደሴቶች ድረስ በከፍተኛ ፍጥነት ተዛመተ፡፡ በሽታው እንዲዛመት የአለም የወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ ይህም ወታደሮች ከአንዱ የአለም ክፍል ወደ ሌላው ለዘመቻ መንቀሳቀሳቸው ነበር፡፡ አንድ ሶስተኛው የአለም ህዝብ በዚህ በሽታ እንደተያዘም ይነገራል፤ በበሽታው ከተያዙት ውስጥ ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ሲኖ ባይሎጂካ የተሰኘ የህክምና ጥናት ማዕከል ባደረገው ጥናት መሰረት፤ በአሜሪካ እስከ 28 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በበሽታው ተጠቅቶ ነበር፤ 675 ሺህ ገደማ የሚሆነው ህዝብ ደግሞ በበሽታው ሞቷል፡፡ ወረርሽኙ  በህንድ የከፋ ነበር፡፡ 


መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ 17 ሚሊዮን ህንዳዊያን በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በጃፓን 23 ሚሊዮን ህዝቦችን ያጠቃ ሲሆን 400 ሺህ ገደማ የሚሆኑትንም ገድሏል፡፡ እንግሊዝ  ሩብ ሚሊዮን፣ ፈረንሳይ ደግሞ 400 ሺህ ዜጎቻቸውን በበሽታው አጥተዋል፡፡ እ.ኤ.አ ከጥር ወር 1918 ዓ.ም እስከ ታህሰስ 1920 ዓ.ም በመላው ዓለም ተንሰራፍቶ የቆየው የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ፣አንድ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ፈጅቷል፤ የሟቾቹ ቁጥር እስከ 200 ሚሊዮን ይደርሳል የሚሉ መረጃዎችም አሉ፡፡ የወረርሽኙን ጉዳት የከፋ ያደረገው አምራች ዜጎችን በከፍተኛ ሁኔታ በማጥቃቱ ነበር፡፡ በበሽታው ከሞቱት መካከል ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 34 ዓመት የሆኑ ወጣቶች አብዛኛውን ድርሻ ይወስዳሉ፤ በመሆኑም በሽታው ካደረሰው ሰብዓዊ ውድመት ባለፈ ጥሎት ያለፈው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠባሳ የከፋ ነበር፡፡
ወረርሽኙ በአፍሪካ በሁለት ዙር ነበር የተከሰተው፤ የመጀመሪያው  በፈረንጆቹ በ1918 ዓ.ም የጸደይና የበጋ ወራት ሲሆን ሁለተኛውና የከፋ ጉዳት ያደረሰው ደግሞ  በበልግ ወራት የታየው ነበር፡፡ በሽታው ለመጀመረያ ጊዜ በአፍሪካ የታየው በወቅቱ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበረችው በሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታዎን ሲሆን በአጭር ጊዜ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ተስፋፋ፡፡ ሚስተር መሪ (Murray) የተባሉ አጥኚ Global Pandemic በተሰኘ ጥናታቸው እንዳሰፈሩት፤ የበሽታው ስርጭት ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት ላይ ሰፊ ነበር፤ በክፍለ አህጉሩ የተከሰተው የሞት መጠን በመላው ዓለም በበሽታው ከተከሰተው ሞት ውስጥ የ29 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ በተለይም በምዕራብና ደቡባዊ አፍሪካ ጥፋቱ የከፋ ነበር፤ በጋና እስከ መቶ ሺህ ዜጎች እንዳለቁ ይገመታል፤ በምስራቅ አፍሪካም ቀላል የማባል ቁጥር ያላቸው ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በእንግሊዝ ሶማሊ ሰባት በመቶ የሚሆኑ ህዝቦች በበሽታው ሲሞቱ፣ በኢትዮጵያም ከአርባ ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ከሰብዓዊ ውድመቱ ባለፈ ወረርሽኙ በአፍሪካ ከባድ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ በጊዜው አጠራር ደቡብ ሮዴሺያ (የዛሬዋ ዚምባብዌ) አምራች የሰው ሀይል በበሽታው በመያዙ የወርቅ ማውጫ ስፍራዎች እንዲዘጉ ሆኖ ነበር፤ በዚህም በማዕድን ዘርፍ ላይ የተንጠለጠለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ክፉኛ ተጎዳ፡፡  ወረርሽኙ በማላዊና በዛምቢያም ያደረሰው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ከፍ ያለ ነበር፡፡ በናይጀሪያም፣በተለይ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በሽታው የከፋ ጥፋት በማድረሱና ምርት በማሽቆልቆሉ፣ ቀድሞ ለምግብነት የማይውለው ካሳቫ ለምግብነት መዋል ጀመረ፡፡ በአነስተኛ ጉልበትና ያለ ብዙ ልፋት የሚመረተው ካሳቫ ተመራጭ ምግብ ሆነ፡፡ 


የ1918ቱ የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ በአፍሪካ ያስከተለው ማህበራዊ ቀውስ ቀላል አልነበረም፡፡ በሽታው ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት፣ የኢኮኖሚ ደረጃን ሳይለይ ሁሉንም ሰው የሚያጠቃ ቢሆንም ቅኝ ገዢዎች በሽታው ከጥቁር ህዝቦች የመጣ እንደሆነ በማናፈስ የዘር መድልዖ ለማድረግ ተጠቅመውበታል፡፡ ይህ ችግር በተለይም በደቡብ አፍሪካ የጎላ ነበር፤ በዚህም ነጮችና ጥቁሮች ማንኛውንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በአንድ ላይ እንዳያደርጉ የሚደነግግ አዋጅ እንዲጸድቅ ተደረገ፡፡ በቦትስዋናም በሽታው በርካታ ህጻናትን ወላጅ አልባ አድርጓል፡፡ በጋና የሆነው ደግሞ ትንሽ ለየት ያለ ነበር፤ በሽታው ተንሰራፍቶ በርካታ ሴቶች በመጠቃታቸው፣ ከነባራዊው የጋናዊያን ባህልና ወግ ባፈነገጠ መልኩ ባሎች የሴቶች ድርሻ ተደርጎ ይወሰድ የነበረውን የቤት ውስጥ ስራዎች መስራት ግድ ሆነባቸው፡፡  ወንዶች ማዕድ ቤት ገብተው በቆሎ መፍጨት፣ ምግብ ማብሰል የመሳሰሉትን ስራዎች ይከውኑ ጀመር፡፡
በኢትዮጵያ በሽታው የታየው የመጀመሪያው የበሽታው ምልክት በዓለም ላይ ከታየ ከአስር ወራት በኋላ በህዳር ወር 1911 ዓ.ም ነው፡፡ ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ በሽታው መግባቱ አይቀርም በሚል የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች መስራት እምብዛም የተለመደ አልነበረም፡፡ በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚችለው በኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቆንሰላ ያደረገው ነገር ነበር፡፡ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሪቻረድ ፓንክረስት እ.ኤ.አ በ1990 ዓ.ም ባሳተሙት An Introduction to the Medical History of Ethiopia በሚለው የምርምር ስራቸው ላይ እንደጻፉት፤ በሽታው በውል ያልታወቀ ነበርና ምናልባትም የፈንጣጣ በሽታ ይሆናል በሚል በወቅቱ በኢጣሊያ ቆንስላ ትብብር በሀምሌ ወር 1910 ዓ.ም አስር ሺህ ዶዝ የፈንጣጣ ክትባት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ተደርጎ ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ከዘመናዊ ህክምና ጋር ለማይተዋወቀው የኢትዮጵያ ህዝብም ወረርሽኙ ታላቅ መቅሰፍት ነበር፡፡ በሽታው ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ በመላው አገሪቱ ከባድ ዕልቂት ማስከተል ጀመረ፡፡ በተለይም ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን  በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ መረበሽን ፈጥሯል፡፡  


በበሽታው ከተጠቁ ታላላቅ የዘመኑ ሹመኞችና የቤተ መንግስት ሰዎች መካከል ራስ ተፈሪ መኮንን (ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ) እና ባለቤታቸው ወ/ሮ አቴጌ መነን አስፋው ይገኙበታል፡፡ እንዲያውም የራስ ተፈሪና ቤተሰቦቻቸው  ሀኪም የሆኑት ሊባኖሳዊው ዶክተር አሳድ ቼይባን ራሳቸው የበሽታው ተጠቂ ነበሩና የራስ ተፈሪን ቤተሰብ የሚያክም ጠፍቶ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ከህዳር 7 እስከ ህዳር 20 ቀን 1911 ዓ.ም  ለአስራ አራት ቀናት ገደማ የቆየው በሽታው በህዳር ወር የተከሰተ በመሆኑም ህዝቡ የህዳር በሽታ እያለ ይጠራው ጀመር፡፡ ብላቴን ጌታ መርስዔ ሀዘን ወልደቂርቆስ የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በተሰኘው መጽሀፋቸው እንዳሰፈሩት፤ ወረርሽኙ እስከ አርባ ሺህ ኢትዮጵያዊንን ለሞት ዳርጓል፤ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ዘጠኝ ሺህ ዜጎች በበሽታው ሞተዋል፡፡ በተለይም ህዳር 12 ቀን 1911 ዓ.ም በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሞቱበት በመሆኑ በቀኑ የጽዳት ዘመቻ እንዲደረግ በአዋጅ ተነግሮ ስለነበር፣ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ይህ ነገር እንደባህል ተወስዶ በየዓመቱ ህዳር 12 ቀን  የጽዳት ዘመቻ ይደረግ ጀመር፤ ይህም በተለምዶ ህዳር ሲታጠን የምንለው ነው፡፡ዶ/ር እናውጋው መሃሪ፣ዶ/ር ክንፈ ገበየሁ እና ዶ/ር ዘርጋባቸው አስፋው የተባሉ የህክምና ባለሙያዎች በጋራ ያሰናዱትና በ2013 እ.ኤ.አ የታተመው The Manual of Ethiopian Medical History ላይ እንደሰፈረው፤ የ1918ቱ የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ክትባት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በአሜሪካን የቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ (Vanderbilt University) ምሁራን ሲሆን ወቅቱም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናት በየጊዜው የተሻሻሉ ክትባቶች በምርምር ተገኝተዋል፡፡ በ1918 ዓ.ም እንደተከሰተው እንፍሉዌንዛ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ባያውቅም ዛሬም ድረስ ግን የሰው ልጆች የጤና ፈተና መሆኑን አላቆመም፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም ብቻ በመላው ዓለም አምስት መቶ ሺህ ሰዎች በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ የእንፍሉዌንዛ ክትባቶች የዋጋ ውድነት መፍትሄ ካላገኘ፣ ህዝቡ ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ ካላገኘ፣ መንግስታት በሽታውን ለመከላከል ከፍ ያለ ትኩረት ካልሰጡ ---- በእንፍሉዌንዛ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት መቀነስ አዳጋች ነው፡፡  


*******************************************************************************
 http://www.addisadmassnews.com/    Saturday, 21 November 2015

Monday, March 27, 2017

ዋ …ያቺ አድዋ_ፀጋዬ ገብረመድኅን



ዋ …
አድዋ ሩቅዋ
የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ችጋግ ዳስዋ
አድዋ . . .
ባንቺ ብቻ ህልውና
በትዝታሽ ብጽዕና
በመስዋእት ክንድሽ  ዜና
አበው ታደሙ እንደገና፡፡
ዋ …
ዓድዋ የዘር ዐፅመ ርስትዋ
የደም ትቢያ መቀነትዋ
በሞት ከባርነት ስርየት
በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰውብሽ ለት
ዓድዋ
የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ
የኢትዮጵያዊነት ምስክርዋ
ዓድዋ
የኩሩ ደም ባንቺ ጽዋ
ታድማ በመዘንበልዋ
ዐፅምሽ ቤንሳኤ ነፋስ
ደምሽ በነፃነት ህዋስ
ሲቀሰቀስ ትንሳኤዋ
ተግ ሲል ሲንር ትቢያዋ
ብር ትር ሲል ጥሪዋ
ድው እልም ሲል ጋሻዋ
ሲያስተጋባ ከበሮዋ
ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ
ያባ መቻል ያባ ዳኘው
ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው
ያባ በለው በለው ሲለው
በለው በለው በለው በለው!

ዋ …ዓድዋ …
ያንቺን ጽዋ ያንቺን አይጣል
ማስቻል ያለው አባ መቻል
በዳኘው ልብ በአባ መላው
በገበየሁ በአባ ጎራው
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው
በለው ብሎ፡ በለው በለው!
ዋ . . .ዓድዋ . . .
ዓድዋ የትላንትናዋ
ይኸው ባንቺ ህልውና
በትዝታሽ ብፅዕና
በመስዋዕት ክንድሽ ዝና
በነፃነት ቅርስሽ ዜና
አበው ተነሱ እንደገና፡፡
ዋ!  . .  ያቺ ዓድዋ . . .
አድዋ ሩቅዋ
የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ችጋግ ዳስዋ
አድዋ . . .


Thursday, March 9, 2017

ስለ ቋንቋ መበላሸት ትንሽ እናውራ!



አንዳንድ ሰዎች በተሳሳተ አነጋገር ላይ እርማት ሲደረግ “ቋንቋ መግባቢያ ስለሆነ ሰው እንደ ፈለገ ቢናገረው ምናለበት” ሲሉ ይሰማሉ። አዎ ቋንቋ መግባቢያ ነው። ነገር ግን መግባቢያነቱ የሚሰምረው በትክክል ሲነገር ወይም ሲጻፍ ብቻ ነው። ስህተት ሆኖ ሲነገር ግን ሌላ ቢቀር ማደናገሩ አይቀርም። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ ወሎ ውስጥ በገጠር አካባቢዎች በሁለተኛና በሦስተኛ ሰው (በርስዎና በሳቸው) መካከል የተሳሳተ አነጋገር ይሰማል። እሳቸው መጥተው ነበር ለማለት እሰዎ (እርስዎ) መጥተው ነበር እያሉ ሲያወሩ ይሰማል። ልክ በጎጃም አባባል አልበላሁም ለማለት “አልበልቸም” እንደሚለው አነጋገር መሆኑ ነው። ጎጃምኛው አለመለመዱ ነው እንጅ ስህተት አይመስለኝም። ታዲያ አንድ መንደርኛውን አነጋገር የረሳ ወሎየ ዘመዶቹ ዘንድ (ጋ) ሄዶ ሲጫወት የገጠሬው ዘመዱ “ያንዬ እስዎ ሞተው ሃዘን ላይ ሆነን” ሲለው “እረ ተው ምቸ ሞትኩ እኔ” ሲል ደነገጠ ይባላል። ያ ገጠሬው ሰው ሊል የፈለገው “ያንየ እሳቸው ሞተው ሀዘን ላይ ሆነን” ለማለት ነው። ስለዚህ ቋንቋ በትክክል ካልተነገረ ወይም ካልተጻፈ መግባባት ሳይሆን ማደናገርን ነው የሚፈጥረው-ከላይኛው ምሳሌ እንዳየነው።
ዛሬ የቋንቋ ብልሽት በብዙ መልክ ይታያል። የፈረንጅኛ ቃላት፣ ያውም የተሳሳቱ አባባሎችን ካልጨመሩ ሃሣባቸውን መግለጽ የማይችሉ የሚመስላቸው ሰዎች ብዙ ናቸው። ፋዘር፣ ማዘር፣ ፍሬንድ የሚሉት ቃላት በሰፊው ሲነገሩ ይሰማል። ሽማግሌዎችና አሮጊቶችም ፋዘር፣ ማዘር ሲሉ መሰማት ጀምሯል። ለምን ቢባል “ዘመናዊ” ለመሆን ነዋ! “አባት፣ እናት፣ ጓደኛ ካለ አንድ ሰው ስልጡን እንዳልሆነ ነው የሚታሰበው” አለኝ አንድ ወያላ ሲያብራራልኝ። ለመሆኑ ፋዘር፣ ማዘር የሚባሉት የሰንት ዓመት ሰዎች ናቸው ብዬ ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ የሚገርም ነው። “ወንዱን ፋዘር የምንለው ትንሽ ሽበት ካወጣ ወይም ጸጉሩ ከተመለጠ ነው። ሴትዋም ሻሽ ካሠረች ያው ማዘር ነች” አለ እየሳቀ። ወያላዎች ግራንድ ፋዘር (ግራንድፓ) ወይም ግራንድ ማዘር (ግራንድማ) የሚሉትን የእንግሊዝኛ ቃላት ስለማያውቋቸው ያርባ አመትም ሆነ የሰማንያ ዓመት ሰው ያው ፋዘር ነው የሚባለው። ሴትዋም ያው ማዘር ነች። እነኝህ ፋዘር፣ ማዘር፣ ፍሬንድ የሚሉት ቃላት ትርጉሞች በሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እንደሚገኙ የሚታወቅ ነው። ቁልምጫዊ ዘይቢያቸው ሳይቀር አለ። ለምሳሌ በአማርኛ አባቴ፣ አባብዬ፣ እማማ፣ እማምዬ፣ ጓደኛዬ፣ ጓዴ ወዘተ የሚሉ ቃላት አሉ። የቅርብ ዘመድንና የቤተሰብ አባላትን በቁልምጫ ለመጥራትም ብዙ ቃላት አሉ። ታላቅ ወንድምን፣ ወይንም አጐትንም ሆነ የቅርብ ወንድ ዘመድን፣ ጋሽየ፣ ወንድምዓለም፣ ወንድምጋሼ፣ ጥላዬ ማለት እንደሚቻለው ሁሉ፣ ለሴት እህትም ወይም አክስት፣ እታለም፣ እትአበባ፣ አክስቴ ማለት ይቻላል።
ሌላው በብዛት ስህተት ሲስተናገድበት የሚታየው/የሚሰማው በግዕዝና በአማርኛ እርባታ ላይ ነው። ብዙ ሰዎች በግዕዝ በተረባው ቃል ላይ ቶች፣ ዎች ወይም ኖች በመጨመር የብዙ ብዙ አነጋገር ስህተቶችን ሲፈጽሙ ይሰማሉ። የሚከተሉትን እንመልከት!
የአማርኛ ዕርባታ (ነጠላ-ብዙ) የግዕዝ ዕርባታ (ብዙ)   ጸያፍ ዕርባታ (የብዙ ብዙ)
ሊቅ         ሊቆች             ሊቃውንት             ሊቃውንቶች
አስተማሪ    አስተማሪዎች       መምሕራን             መምሕራኖች
ሕፃን        ሕፃኖች            ሕፃናት                ሕፃናቶች
ቄስ          ቄሶች             ቀሳውስት              ቀሳውስቶች
መነኩሴ      መነኩሴዎች        መነኮሳት              መነኮሳቶች
ካህን         ካህኖች            ካህናት                ካህናቶች
ዲያቆን       ዲያቆኖች          ዲያቆናት              ዲያቆናቶች
ንጉሥ        ንጉሦች           ነገሥታት              ነገሥታቶች
እንስሳ        እንስሶች           እንስሳት               እንስሳቶች
ገዳም         ገዳሞች           ገዳማት                ገዳማቶች
ጳጳስ          ጳጳሶች           ጳጳሳት                 ጳጳሳቶች
ባህታዊ        ባህታዊዎች       ባህታውያን             ባህታውያኖች

ባሁኑ ጊዜ በጣም ገንኖ የሚታየው ሌላው ስህተት በ ጋ እና ጋር መካከል ያለው ያጠቃቀም ውዥንብር ነው። በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው “አማርኛ መዝገበ ቃላት” እንደሚገልጸው ጋ የሚለው ፊደል “አንድ ነገር የት እንደሚገኝ የሚያመለክት ቃል” ነው። መጽሐፉ ጠረጴዛው፣ እዚያ ነው። ጋር የሚለው ቃል ደግሞ “አብሮ” የሚለውን ሃሣብ የሚገልፅ ነው። ስለዚህ ጋ ዘንድ ሲሆን ጋር ደግሞ አብሮ ማለት ነው። ምሳሌ፣ እኔ ዛሬ ወንድሜ ጋ እሄድና ከሱ ጋር ሄደን ምሳ እንበላለን። ስለዚህ ጋ የሚለው ዘንድ ማለት ሲሆን ጋር የሚለው ቃል ግን አብሮ ማለት ነው። ለምሳሌ ስልክ ተደውሎ የት ነው ያለኸው ሲባል ወንድሜ ጋ ነኝ (ወንድሜ ዘንድ ነኝ) መሆን ነው ያለበት መልሱ። ዛሬ ግን ጋ ለማለት ጋር በማለት ውዥንብር እየተፈጠረ ነው። መጽሐፉ የት ነው ያለው? ብለህ ስትጠይቅ ከበደ ዘንድ ነው ለማለት ከበደ ጋር ነው ይልሃል። ትክክል ያልሆነ አነጋገር ነው። የቃና ቴሌቪዥን ተዋንያን ሳይቀሩ የተሳሳተውን የቋንቋ አገባብ ይዘው ጋ የሚለውን ጋር እያሉ ነው የሚያወሩት። ከአንድ ሰዓት በኋላ ወንድሜ ጋ (ቤት) እሄዳለሁ ለማለት፣ ከአንድ ሰዓት በኋላ ወንድሜ ጋር እሄዳለሁ እየተባለ ነው። ስህተት ነው።
ሌሎች በባዕድ ቋንቋዎች የምንሠራቸው አስቂኝ ስህተቶች አሉ። አንድ ልጅ አባቱ ያልሆነውን ሰው ፋዘር ወይም ዳዲ ብሎ ሊጠራው አይችልም። አንድ ጊዜ አራት ኪሎ አንድ ፈረንጅ ታክሲ ውስጥ ሆኖ ወጣቶች ከበው ገንዘብ ስጠን ለማለት ፋዘር፣ ዳዲ እያሉ ሲያስቸግሩት ደርሼ ገላግየዋለሁ። “ፋዘር ዳዲ ሞኒ ሞኒ” እያሉ በግራና በቀኝ ሲጮሁበት ፈረንጁ ተናዶ I swear I did not father any of these kids (ከነኝህ ልጆች አንዱንም እንዳላስወለድኩ እምላለሁ ነበር ያለው።) ሌላው አስቂኝ ቃል ክላስ የሚለው ነው። ሆቴል ስትገቡ እንግዳ ተቀባዩ ክፍል ይፈልጋሉ ለማለት ድፍረት በተሞላ አነጋገር ክላስ ነው የሚፈልጉት ነው የሚላችሁ። ክላስ ወይም ክላስሩም የመማሪያ ክፍል ነው እንጅ የመኝታ ክፍል አይደለም። የኛም የውጭውም ቋንቋ እንደዚህ ተዘበራርቋል።
በየቀኑ በስህተት የሚነገሩ የውጭ አገር ቋንቋዎችና ቃላት ብዙ ናቸው። አመሰግናለሁ ለማለት ቴንክዩ ወይም ታንክዩ የሚሉ ብዙ አሉ። የቋንቋው ባለቤቶች እንግሊዞች ግን ትክክለኛውን ቃል ለማውጣት ምላስን በላይኛውና በታችኛው ጥርሶቻችን መካከል ብቅ አድርጎ መልሶ ወደ ውስጥ በመሰብሰብ የሚፈጠር ድምፅ ነው ይላሉ። ያን ድምፅ በአማርኛ መጻፍ ባይቻልም ሳንክዩ ለሚለው ቃል ነው የሚቀርበው።
ባሁኑ ጊዜ ቋንቋን ከሚያበላሹ ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የመገናኛ ብዙሐን ሰራተኞች በተለይ የቴሌቪዥንና የሬድዮ ጋዜጠኞች ናቸው። እጅግ በጣም ጥሩ፣ በጣም ቆንጆ የሚሉትን የአማርኛ ገላጭ ቃላት አሪፍ በሚል የአረብኛ ቃል ለውጠዋቸዋል። አገሩ ሁሉ አሪፍ፣ አሪፍ እያለ ነው። “አሁን ደግሞ “አሪፍ” ሙዚቃ እንጋብዛችኋለን” ማለት የተለመደ የሬድዮ ጣቢያ አነጋገር እየሆነ መጥቷል። ከፈረንጅ ጥገኝነት ወደ አረብ ጥገኝነት በቀላሉ እየተሽጋገርን ይመስላል። ምንም እንኳን ቋንቋ ይወራረሳል፣ ያድጋል ቢባልም የሚወራረሰውም የሚያድገውም የራስ ቋንቋ የማይገልጸውን የሚገልጹ የባዕድ ቃላት ሲገኙና በግልጽ በሥራ ላይ መዋል ሲያስፈልጋቸው ነው። ዛሬ ቀኑ፣ ዓየሩ፣ ጥሩ ነው፣ ቆንጆ ነው፣ ተወዳጅ ነው ወዘተ ለማለት ሁሉም የሚሸፈነው “አሪፍ” በሚለው ቃል ሆኗል። ቃሉ በጣም ከመወደዱ የተነሳ በረጅም ቅላጼ ነው የሚነገረው። ይህ ደግሞ የራሳችንን ቋንቋ ማሳደግ ሳይሆን ለባዕድ ቋንቋ ጥገኛ መሆንና የራስን ቋንቋ ማዳከም ነው። እንድንግባባ እኔም ቃሉን ልዋሰውና አሪፍ የጥገኝነት ባህሪ ነው ልበላችኋ!
ሰርተፊኬት የሚለው ቃል በሰፊው ተለምዶ በሬድዮና በቴሌቪዥን ሲነገር በጽሁፍም ሲቀርብ ይታያል። የቋንቋው ባለቤቶች ሰርቲፊኬት ነው የሚሉት። ስለዚህ እኛ ቃሉን በትክክል ለመጠቀም ወይ ባለቤቶቹ እንደሚሉት ሰርቴፊኬት ማለት አለብን አለዚያም በራሳችን ትርጉም የምስክር ወረቀት ማለቱ ይመረጣል። ሌላው ተመሣሣይ ችግር ያለው ፕረስ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ነው። ቃሉ ከሕትመት ሥራ ጋር ማለት ከመጫን፣ ከማተም ጋር የተያያዘ ስለሆነ በእንግሊዝኛ ፕረስ የሚለው አነባበብ ይስማማዋል። እኛ ግን ለራሳችን የሚስማማን ፕሬስ ነው በማለት ቃሉን ከትክክለኛው አነጋገር ከፕረስ ወደ ፕሬስ ወስደነዋል። ይህ ድርጊት ምንም ምክንያታዊ አይደለም። አሁንም ሌላው ከትክክለኛ አነጋገር ወደ ተሳሳተ አባባል በልማድ የተወሰደና በስህተት እየተነገረ የምሰማው ኦሎምፒክ የሚለው ቃል ነው። ቃሉ በእንግሊዝኛ OLYMPIC (ኦሊይምፒክ) ነው። የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለማለት OLYMPIC GAMES ነው የሚባለው። ባንድ ወቅት አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ኦሊይምፒክ የሚለውን ቃል ኦሎምፒክ ብሎ በስህተት አነበበው። ከዚያ ወዲህ እኛ አገር ትክክለኛው አነባበብ ተሽሮ ኦሎምፒክ ሆኖ ቀረ።
ወደ ጣልያንኛ ቋንቋ ደግሞ እንሂድ። በመኪና ላይ ከሁዋላ የሚመጡትን ተሽከርካሪዎች ለመቆጣጠር በግራና ቀኝ ያሉት መስትዋቶች በጣልያንኛ ስፔኪዮ ነው የሚባሉት። ከተጠራጠሩ የጣሊያንኛ ቋንቋን በደምብ የሚያውቅ ሰው ይጠይቁ ወይም የኢጣልያንኛ መዝገበቃላትን ይመልከቱ። በኛ አገር ግን ሕዝቡ በሙሉ ስፖኪዮ ሲል ነው የሚሰማው። ስፖኪዮ አይደለም ስፔክዮ ነው ብለህ ብታርመው ሰው ሁሉ ይስቅብሃል። ብዙዎቻችን ይበልጥ ከሚያውቁ ሰዎች ጠይቀን ከመማር ስህተታችንን ይዘን መኖር የምንመርጥ ይመስላል።
SERIES ተመሣሣይ፣ ተዛማጅ ወይም ተከታታይ ማለት ነው። Series of books ማለት ተከታታይ መጸሕፍት ማለት ነው። በቴሌቪዥን የምንሰማው ማስታወቂያ ግን SERIOUS (ሲሪየስ) of books እየተባለ ነው የሚነበበው። SERIOUS የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ደግሞ ኮስታራ፣ ቁም ነገረኛ፣ ምራቁን የዋጠ ማለት ነው። ሁለቱ የእንግሊዝኛ ቃላት አነባበባቸውም፣ ትርጉማቸውም የተለያየ ነው። አንድ ሰው አነባበቡን በትክክል የማያውቀው የባዕድ ቃል ሲገጥመው በግምት ከማንበብና መሣቂየ ከመሆን ይልቅ ያንን ቋንቋ የሚያውቀውን ሰው ጠይቆ መረዳት ወይም የዚያን ቋንቋ መዝገበ ቃላትን ማየት ያስፈልጋል።
የዘመኑን ቋንቋ በተመለከተ ሌላው አነጋጋሪ ቃል ማለት የሚለው ነው። ማለት ግልጽ ያልሆነን ሃሣብ ለማብራራት፣ ለመግለጽ የምንጠቀምበት ቃል እንደሆነ ለሆሉም ግልጽ ይመስለኛል። አንድን ቃል ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ለመተርጎም ይህ ቃል ምን ማለት ነው፣ ይህ ጽንሠ ሃሣብ ምን ማለት ነው ወዘተ እያልን በቃሉ ስንጠቀም ኖረናል። ያሁኑ አዲሱ አጠቃቀም ግን “ማለት ነው” የሚሉትን ሁለት ቃላት ትርጉም የሌላቸው ያደርጋቸዋል። አሁንም በዚህ በተሳሳተ መንገድ በቃሉ እየተኩራሩ የሚጠቀሙት ሕዝብን ማስተማር የማገባቸው የመገናኛ ብዙሐን ሰዎች ናቸው። ያሳዝናል! ጥቂት ምሳሌዎችን ልጥቀስ።
ከዜናው በኋላ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የተዘጋጀውን የትንተና ጽሑፍ እናቀርባለን ማለት ነው። ለዚህ አረፍተ ነገር መጨረሻ ሆነው የገቡት “ማለት ነው” የሚሉት ሁለት ቃላት ለአረፍተ ነገሩ ምንድን ነው የጨመሩለት? “ከዜናው በኋላ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የተዘጋጀውን የትንተና ጽሁፍ እናቀርባለን የሚለው በቂ አይደለም? ለምንድን ነው “ማለት ነው” የተባሉት ሁለት ቃላት የተጨመሩት? ሌላ ምሳሌ፣ ዘንድሮ ትምሕርቴን በደንብ ተከታትዬ የመጀመሪያ ዲግሪየን ከያዝኩ ሥራ ሳልፈልግ በቀጥታ ለሁለተኛ ዲግሪ ማለት ለማስተርስ እመዘገባለሁ ማለት ነው። አሁንም በዚህ አረፍተ ነገር የመጀመሪያው ማለት ትክክል ሲሆን መጨረሻ ላይ የገቡት “ማለት ነው” የሚሉት ሁለት ቃላት ግን ፈጽሞ አስፈላጊ አይደሉም።
 የጠቃሽ አመልካች ሥራዋን እንዳታከናውን ተጽዕኖ እየደረሰባት ነው። ስለሆነም አባቴን ለማየት ወደ አገር ቤት እሄዳለሁ በማለት ትክክለኛው አነጋገር ፈንታ አባቴ ለማየት ወደ አገር ቤት እሄዳለሁ ሆኗል የዘመኑ አነጋገር። አባቴን፣ እናቴን፣ አገሬን እወዳለሁ የሚለው ትክክለኛ አነጋገር ቀርቶ አባቴ፣ እናቴ፣ አገሬ እወዳለሁ ሆኗል አሪፉ የዘመኑ አነጋገር። በዉ ካዕብና በው ሳድስ መካከል ያለው ልዩነት እየጠፋ በመሄድ ላይ ነው። በላሁ በማለት ፈንታ በላው እየተባለ ይጻፋል። ለመሆኑ ወዴት እየሄድን ነው? አደግን፣ ሠለጠንን ተባለና ፊደሎቻችንን መለየት ከማንችለበት ደረጃ ደረስን ማለት ነው?
የባዕድ ቋንቋዎችን በትክክል ለማወቅ መሞከርና በትክክል በጥቅም ላይ ማዋል ተገቢ ነው። ከራስ ቋንቋ በላይ (ለዚያውም በተሳሳተ መልኩ) ለባዕድ ቋንቋና ቃላት ጥገኛና ተገዥ መሆን ግን ጤነኛ አስተሳሰብ አይመስለኝም። አመሰግናለሁ።
*****************************************
* አቶ ማዕረጉ በዛብህ አንጋፋ ጋዜጠኛ ሲሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ክፍል ማኔጂንግ ኤዲተር ናቸው።
****************************************
http://www.sendeknewspaper.com/milkta/item/5545_Wednesday, 08 March 2017



  


Sunday, July 24, 2016

አባተ መኩሪያ ‹‹ተንቀሳቃሹ ቴአትር ቤት›› (1932 - 2008)


‹‹ጥበበኛ በጥበብ እግር ይመላለሳል›› (ጠቢብ የሐውር በእግር ጥበብ) እንዲሉ፣ አባተ መኩሪያ ከግማሽ ምታመት በዘለለ በኢትዮጵያ ቴአትር ሕዋ ውስጥ በጥበብ ለጥበብ ኖሯል፡፡ ለቴአትር እስትንፋሱ ነበርም ይሉታል፡፡ በርሱ ጥበብ ያለፉት ሁሉ፡፡
በጥበብ የባተው አዘጋጅ፣ የውዝዋዜ አሠልጣኝ (ኬሪዮግራፈር)፣ ጸሐፌ ተውኔት፣ የፊልም አዘጋጅ የነበረው አባተ መኩሪያ በአገሪቱ የቴአትር ታሪክ ውስጥ ስማቸው በግዘፍ ከሚነሱትና አሻራቸውን ካሳረፉ በኩሮች አንዱ ነበር፡፡ በተለይ በተውኔት አዘጋጅነት ስመ ጥር ለመሆኑ ዘመን ተሻጋሪ ተውኔቶችን ወጥ እና ትርጉሞች በማዘጋጀቱ ይጠቀሳል፡፡
ከታዋቂ ሥራዎቹ መካከል ሀሁ በስድስት ወር (1966) አቡጊዳ ቀይሶ (1971)፣ መልእክተ ወዛደር (1971)፣ የመንታ እናት (1971)፣ መቅድም (1972)፣ ጋሞ (1973)፣ አሉላ አባነጋ (1979) ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ በ19ኛው ምታመት አሐዳዊት ኢትዮጵያን እውን ባደረጉት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ላይ የተመሠረተው የጸሐፌ ተውኔት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹ቴዎድሮስ›› ነውን ከነበር ጋር ያስተሳሰረበት አዘገጃጀቱ፣ የንጉሠ ነገሥቱን ቴዎድሮስ ልዕልና ያንፀባረቀበት ነበር፡፡
ብዙዎቹ አባተ ያዘጋጃቸው ተውኔቶች በሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን የተደረሱ ሲሆኑ ረዣዥም ቃለ ተውኔት፣ ታሪክ ጠቃሽ ዘይቤዎችን ያዘሉ ናቸው፡፡ የአባተ ክሂል የተንፀባረቀውም እነዚያን ረዣዥም ቃለ ተውኔቶች (መነባነቦች) ተደራሲን በሚይዝ መልኩ እንዲመደረኩ በማድረጉ ነበር፡፡ እንደ አዘጋጅነቱም የድራማን ሥነ ጽሑፍ በምሁራዊ ዓይን አይቶ ማዳበሩን ተክኖታል፡፡
በዎርልድ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ ኮንቴምፖራሪ ቴአትር እንደተገለጸው፣ አባተ ተውኔት ተመልካቹን በግሩም ሁኔታ መቆጣጠር የሚያስችል ክሂል ነበረው፡፡ በጸጋዬ የተተረጐሙት የዊልያም ሼክስፒር ማክቤዝ፣ ኦቴሎና ሐምሌት በታዳሚው ትውስታ ውስጥ የቃለ ተውኔቱ (ግጥም) ውበት ብቻ ሳይሆን፣ ተውኔታዊ ክዋኔዎች እንዲታወሱ የሆነው በአባተ መኩሪያ አዘገጃጅ ስምረት መሆኑን ኢንሳይክሎፒዲያው አስነብቧል፡፡
ከመንግሥቱ ለማ ታዋቂ ሥራዎች አንዱ የሆነው ‹‹ያላቻ ጋብቻ›› የአባተ አዘጋጅነት እጅ አርፎበታል፡፡ አባተ ከሚታወቅባቸው የመድረክ ተውኔቶች ባሻገር በአደባባይ ላይ ባዘጋጃቸው (ከአዳራሽ ውጭ) ተውኔቶቹም ይወሳል፡፡ ‹‹ኤዲፐስ ንጉሥ›› ተውኔትን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኰንን አዳራሽ ፊት ለፊት በሚገኘውና በዘልማድ ‹‹ኪሲንግ ፑል›› በሚባለው ወለል ላይ ያሳየው ይጠቀሳል፡፡ ሐቻምና በኢትዮጵያ የተውኔት ታሪክ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፈው የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ‹‹አፋጀሽኝ›› ዳግም የመድረክ ብርሃን ያየው በአባተ መኩሪያ ነበር፡፡
አባተ ከአዘጋጅነቱ ሌላ በጸሐፌ ተውኔትነቱም ይታወቃል፡፡ ራሱ ደርሶ ራሱ ያዘጋጀው ‹‹የሊስትሮ ኦፔራ›› (1982) በወቅታዊ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የተመሠረተ በሙዚቃ የታጀበ ሥራው ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ ሽልማትም አግኝቶበታል፡፡
በዩኔስኮ አፍሪካዊ ተውኔትን በደብሊን አቤይ ቴአትር እንዲያዘጋጅ የተመረጠው አባተ፣ የጸጋዬ ገብረ መድኅንን “Oda Oak Oracle” (የዋርካው ሥር ንግርት) አዘጋጅቷል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከእንግሊዛዊው ዕውቅ የቴአትር አዘጋጅ ሰር ፒተር ሆል ጋር በኮንቬንት ጋርደን ኦቴሎን ለማዘጋጀት ዕድል አግኝቷል፡፡
መቀመጫውን በታንዛኒያ ያደረገውን የምሥራቅ አፍሪካ ቴአትር ኢንስቲትዩት በመሥራች አባልነትና በኃላፊነት ከመምራቱም ባሻገር፣ በአዲስ አበባ የመኩሪያ ቴአትር ስቱዲዮና መዝናኛ የተሰኘ ተቋምን መሥርቶ ‹‹ቴአትር ለልማት›› የሚባለውን የተውኔት አቀራረብ ፈለግ መሠረት በማድረግ ብዙ ትምህርት ሰጪ ተውኔቶችን በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተመሥርተው በማዘጋጀት ለመድረክ አብቅቷል፡፡ በታሪካዊ መዝገበ ሰብ እንደተመለከተው፣ ለመድረክ ካበቃቸው ተውኔቶች መካከል ሕሊና፣ ጠለፋ፣ ጆሮ ዳባ፣ በሐምሌ ጨረቃ ጉዞ፣ ድንቅ ሴት ሲጠቀሱ ከዘጋቢ ፊልሞችም የፍትሕ ፍለጋ እና የመስከረም ጥቃት ይገኙበታል፡፡
መኩሪያ ስቱዲዮ በየክልሉና በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ አማተር ከያንያን የቴአትር፣ የሰርከስና የሙዚቃ ሥልጠና መስጠቱን፣ ከኢትዮጵያ ውጪም ወደ ተለያዩ አገሮች እየተጓዘ ትርኢት ማቅረቡም ይታወቃል፡፡
በየዓመቱ ከሚከበረው የዓድዋ ድል ጋር ተያይዞ አባተ መኩሪያ ከነጥበብ ጓዙ የሚነሳበት አጋጣሚ ከ30 ዓመት በፊት ተፈጥሯል፡፡ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. በዳግማዊ ምኒልክ ጠቅላይ አዝማችነት፣ በወራሪው የኢጣሊያ ሠራዊት ላይ ኢትዮጵያ የተቀዳጀችው ድል በየዓመቱ ሲዘከር በቴሌቪዥን መስኮት የሚታይ የቅድመ ጦርነት ዝግጅት የቪዲዮ ምሥል የአባተ መኩሪያ ትሩፋት ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ የተመሠረተችበት 100ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓል ሲከበር ለበዓሉ ድምቀት ከተዘጋጁት አንዱ ንጉሠ ነገሥቱ ‹‹ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት›› ብለው ለዘመቻ ሲነቃነቁ ባለፉበት በባልደራስ አካባቢ በሚገኘው የቀበና ወንዝ ነባር ድልድይ አጠገብ አዲስ የተሠራው ‹‹የዓድዋ ዘመቻ መታሰቢያ ድልድይ›› የተመረቀው የዚያን ዘመን የክተት ስሪት በሚያሳይ መልኩ አምሳያ የተፈጠረላቸው ንጉሠ ነገሥቱን፣ እቴጌይቱን፣ መኳንንቱን፣ የጦር አዝማቾችን፣ ዘማቾቹን፣ ሴቶች አገልግል ተሸክመው ሁሉም እየፎከሩ እየሸለሉ የሚያሳየውን ‹‹የራስ አባተ ጦር እለፍ ተብለሃል…›› ወዘተ እየተባለ በ400 ተሳታፊዎች የቀረበው ክዋኔ ለዘመን ተሻጋሪነት የበቃው በአባተ መኩሪያ ነበር፡፡ አባተ ዓድዋንና ድሉን የሚዘክር ላቅ ያለ ይዘት ያለውን የዓድዋ ፊልም ፕሮጀክትን ከአራት ዓመት በፊት ቢቀርጽም፣ በወቅቱም በ35 ሚሊዮን ብር በጀት ሊሠራ መታቀዱንና ፕሮጀክቱን ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በበላይ ጠባቂነት እንደያዙት ቢነገርም እስካሁን ድምፁ አልተሰማም፡፡
ትምህርትና ኃላፊነት
አባተ በትምህርት ዝግጅቱ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በእንግሊዝኛና በንኡስ ትምህርት (ማይነር) ድራማን በማጥናት አግኝቷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በጀርመን ብሮድካስቲንግ ኢንስቲትዩት በፊልምና ሚዲያ ሲሠለጥን ከለንደን ኦፔራ ሴንተር የኦፔራ ትምህርት፣ በአየርላንድ አቤይ ቴአትርና በአሜሪካ ቴአትርና ሙዚቃ በምሥራቅ አውሮፓና በአፍሪካ አዘገጃጀትን አጥንቷል፡፡ የተለያዩ አገሮች ትምህርታዊ ጉዞም አድርጓል፡፡
በሥራ አገልግሎትም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት (የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር) የቴአትር ዳይሬክተር፣ እንዲሁም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኪነ ጥበባት ወቴአትር (ባህል ማዕከል) ዳይሬክተር ሆኖ ሠርቷል፡፡
በ1950ዎቹ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹መዝናኛ በክዋኔ ጥበባት›› (Entertainment in Performing Arts) በሚል ርዕስ በየሳምንቱ ዓርብ ለአንድ ዓመት የዘለቀ ፕሮግራም ማዘጋጀቱን፣ ፕሮግራሙም የአዝማሪ ጨዋታ በኢትዮጵያ ሕዝብና በክዋኔ ጥበባት ውስጥ የነበራቸውን ሚና ይዳስስበት ነበር፡፡ የተለያዩ ብሔረሰቦች ባህልን፣ እምነትን፣ ደስታን፣ ሐዘን፣ ወዘተ በጥበብ አንፃር ይታይበት እንደነበር፣ ቤተ ክህነት ለጥበቡ ዕድገት ያደረገችውን አስተዋጽኦ ከታዋቂ የጥበብ ሰዎች ካበረከቱት ሥራ ጋር የሚቀርብበት እንደነበር ገጸ ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ለምሳሌ ጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹የከርሞ ሰው›› የሚለውን የጻፈውና ሙላቱ አስታጥቄ ለከርሞ ሰው ሙዚቃውን የሠራው በዚሁ የአባተ ፕሮግራም ነበር፡፡
አባተ ከብሔራዊ ቴአትር ሌላ በሀገር ፍቅር ቴአትር፣ በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ በአዘጋጅነት፣ በጸሐፌ ተውኔትና መራሔ ተውኔትነት እንዲሁም በኃላፊነት ጭምር አገልግሏል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ ነበር፡፡ ባለፈው ታኅሣሥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከል ‹‹ዝክረ አባተ መኩሪያ›› ብሎ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ዲን አቶ ነቢዩ ባዬ እንደተናገረው፣ ‹‹አባተ የዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት በትክክለኛው መሠረት ላይ እንዲገኝ የላቀ ሚና ተጫውቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የኪነ ጥበብ የፈጠራ ማዕከል እንዲቋቋም አሻራውን አኑሯል፡፡ የተለያዩ የቴአትር ንድፈ ሐሳቦችን በማቅረብ ግንባር ቀደም አርቲስት ነው፡፡››

ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያን የቴአትር ዕድገትና የተመልካቹን ሁኔታ በተመለከተ አባተ መኩሪያ በአንድ መድረክ የተናገረውን የፋንታሁን እንግዳ ‹‹ታሪካዊ መዝገበ ሰብ›› እንዲህ ገልጾታል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ባህል አትኩሮ የሚያጣጥምና የሚወድ ነው፡፡ ቴአትር ቤቱ ይሞላል፡፡ ግን ከቴአትር አንፃር (ከድርሰቱ) ያየነው እንደሆነ ብዙ የሚተቹ ነገሮች አሉ፡፡ እንደ ቴአትር አዋቂ ተመልካች ቴአትሮቹን ብናያቸው ብዙ ግድፈቶች እናገኛለን፡፡ ተመልካቹ ለዚያ ሁሉ ደንታ የለውም፡፡ የራሱን ሕይወት ማየት ይወዳልና ይመጣል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥበቡ ሳይሆን ተመልካቹ ነው የሚፈታተነን፡፡ ደግሞ የኛን አገር ቴአትር እንዳያድግ የገደለው ቴአትር ቤቶች በመንግሥት እጅ መሆናቸው ነው፡፡ ቴአትር ቤቶች አንድ ዓይነት ሥራ ነው የሚሠሩት፡፡››
የአባተ የጥበብ ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ውጣ ውረዶችን አይቷል፡፡ ቀዳሚው ፈተና በዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ጐን ለጐን በኪነ ጥበብ ወቴአትር (ክሬቲቭ አርት ሴንተር) በሚሠራበት አጋጣሚ በነበረው የግጥም ጉባኤ ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ ያቀረበው ‹‹ላም እሳት ወለደች በሬ ቀንድ አወጣ፣ በሥልጣን ሊቅ መሆን ይህም አለ ለካ›› ግጥም በዩኒቨርሲቲው ኃይለኛ ቁጣ በመቀስቀሱ ማዕከሉ ይዘጋል፡፡ አባተን ጨምሮ ሁሉም ባልደረቦች እንዲባረሩ መደረጉ አንዱ ነው፡፡
በየዐረፍተ ዘመኑ በሦስቱ ሥርዓተ መንግሥታት ፈተና አልተለየውም፡፡ ቴአትር ቤቶች መድረክም ነፍገውት ነበር፡፡ የሎሬት ጸጋዬ የተውኔቶች መድበል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በተመረቀበትና ቅንጫቢ ትዕይንቶች በቀረቡበት ጊዜ መድረክ እንደሚሰጠው ቢነገርም የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡
ለዚህም ይመስላል በታኅሣሡ የብሔራዊ ባህል ማዕከል የአክብሮት መድረኩ ላይ አባተ ለተሰጠው ሽልማትና ለደረቡለት ካባ ምስጋናውን ያቀረበው፣ ‹‹እባካችሁ መድረክ ስጡኝ ልሥራበት፡፡ እኔ ሠርቼ አልጠገብኩም፤ ገና ብዙ መሥራት እፈልጋለሁ፤ ስለዚህ እባካችሁ መድረኩን ስጡኝ፤›› ብሎ በመማፀን ነበር፡፡ ሳይሆንለት አዲሱ ትውልድም ነባሩን ብሉዩን (ክላሲክ) የነጸጋዬ ገብረመድኅን ሥራዎችን በአባተ መኩሪያ አጋፋሪነት ሳያይ አመለጠ፡፡
ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 1932 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አዋሬ ሠፈር ከአባቱ ከአቶ ስለሺ ማንደፍሮና ከእናቱ ከወ/ሮ ውብነሽ መኩሪያ የተወለደው አባተ መኩሪያ፣ የእናቱ አባት ስምን እንደ አባት የወሰደው አያቱ ‹‹እኔ ነኝ የማሳድገው›› ብለው በስድስት ወሩ ወስደው ስላሳደጉት ነው፡፡ በተወለደ በ76 ዓመቱ ሐምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ያረፈው አባተ በማግሥቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡ ከ42 ዓመት በፊት ከወ/ሮ ምሕረት አረጋ ጋር ጎጆ የቀለሰው አባተ ቴዎድሮስና ውቢት የተባሉ ሁለት ልጆቹን ሲያፈራ የልጅ ልጆችም አይቷል፡፡
በዐውደ ምሕረቱ ላይ የሕይወት ታሪኩን ያነበበው ከዕለታት ባንዱ ዕለት ‹‹ራሴን ፈልጌ እንዳገኝ የገራኝ፣ መንገዱን ያሳየኝ፣ የገሰፀኝ፣ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ያበቃኝና ያሳደገኝ የጥበብ አባቴ ነው፤›› ያለው ታዋቂው ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም ነበር፡፡
እንዲህም አነበበ፤ ሕፃኑ አባተም በአያቱ አባትነት ያድጋል፡፡ አያቱ አባትም ሆነውታልም፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስማቸው መጠሪያው ሆነ፡፡ እነሆም በተግባር የናኘው የዛሬው ገናን ስም ‹‹አባተ መኩሪያ!›› እንዳባተ እንዳኮራ ዘመናትን ሊሸጋገር በቃ! የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት (ኮከበ ጽባሕ) ሲከታተል፣ አቶ መኩሪያ ልጃቸው ነገረ ፈጅ እንዲሆንላቸው ቢፈልጉም አባተ ግን ‹‹በፊደል ነው የተለከፍኩት!›› እንዲል እሱ ያገዘፈው የ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››ሩ ገጸ ባሕሪ፣ እሱውም ‹‹በጥበብ ነው የተለከፍኩት!›› ብሎ ጥበብን የሙጥኝ አለ፡፡ ተለክፎም ቀረ! መለከፉም ለመልካም ሆነ፡፡ ተከታታይ የጥበብ ትውልድ ፈጠረ፤ እሱውም በትውልዶች ውስጥ ኖረ፡፡ …ከዚያስ በሰባ ስድስት ዓመቱ… ተንቀሳቃሹ ቴአትር ቤት አረፈ!
**********************************************
ምንጭ:--- http://www.ethiopianreporter.com/ _ እሁድ  ሐምሌ 17  ቀን 2008 ዓ. ም.