ከደራሲያን ዓምባ

Tuesday, September 10, 2019

አዲስ ዓመት

  • ቅዱስ ዮሐንስ
  • ርእሰ ዐውደ ዓመት 
  • የዘመን መለወጫ
  •  እንቁጣጣሽ
እነሆ ይህ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ጦማራችን ከተጀመረ

፯ ዓመታትን

አስቆጠረ ልክ በመስከረም  2005 ዓ.ም. ተጀመረ2005 - 2011
አዲስ ዓመት ዞሮ በመጣ ቁጥር ሁሌም አዲስ ነውና ካነበብነው እነሆ፡፡
ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የመሸጋገሪያው ዕለት በየዓመቱ ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራል፡፡ የዘመን መለወጫ፣ እንቁጣጣሽ፣ ሌላም መጠሪያ ስሞቹ ናቸው፡፡ በግእዝ ርእሰ ዐውደ ዓመትም ይባላል፡፡ ይህ በዓል የዓመት መጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን በየዓመቱ ወሮች በመጀመሪያ ቀን ይከበራል፡፡


አዲስ ዓመት መቼ ይከበራል?

አዲስ ዓመት መስከረም አንድ ቀን ለምን ይከበራል? በኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በመስከረም ወር የሆነበትን ምክንያት ሊቃውንቱ ሲያትቱ ብርሃናት ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ክዋክብት የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱ ከቀኑ ጋር እኩል 12 ሰዓት ይሆናል፡፡ ዓመቱን ጠንቅቀው ሲቆጥሩ 364 ቀናት ይሆናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመን መታወቂያው ይሆን ዘንድ ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትንም ፈጠረ ይላልና /ሔኖክ. 2149/፡፡ በሌላ በኩልም በዘመነ ኖኅ በፍል ውኃ አጥለቅልቆ በኃጢአት ሕይወት ይኖሩ የነበሩት የኖኅ ዘመን ሰዎች ቀጥቶ ካጠፋ በኋላ ከንፍር ውኃ ምድር የተገለጠችበት ወር ነው /ኩፋሌ. 71/፡፡ በመጀመሪያው ወር ምድር ታየች የንፍር ውኃም ከምድር ደረቀየሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መሠረት አድርገው የአቡሻኸር ሊቃውንት የዘመን መለወጫን ታሪካዊ አመጣጥ ያስቀምጣሉ፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖናዊ ሥርዐት ያጠኑ ሊቃውንት ደግሞ አዲስ ዓመት መስከረም አንድ ቀን መሆኑን አስመልክተው በክታባቸው እንዳስቀመጡት በአራቱ ወንጌላውያን ዘመኑን ይከፍሉታል፡፡ ምክንያቱም በዘመነ ዮሐንስ ተፀንሶ በዘመነ ማቴዎስ ተወልዶአል፡፡ በዘመነ ማርቆስ ተጠምቋል፡፡ በዘመነ ሉቃስ ተሰቅሎ ዓለምን ከፍዳና ከመርገም ነጻ አውጥቷል፤ እያሉ ታሪካዊ ሐረጋቸውን ጠብቆ አራቱ ወንጌላውያን ተከትለው ያለ እንቅፋት እንደሚጓዙ ያስረዳሉ፡፡
ወንጌላዊውን ወይም ዘመኑን ለማወቅ ዓመተ ኩነኔ 5500 እና ዓመተ ምሕረት /አሁን ያለንበትን ዓመት/ በመደመር ውጤቱ ለአራቱ ወንጌላውያን /ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ/ በማካፈል የምናገኘው ነው፡፡ ይህም የአንዱ ወንጌላዊ ድርሻ ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቀሪው አንድ ከሆነ ዘመኑ ማቴዎስ፣ ሁለት ከሆነ ዘመነ ማርቆስ፣ ሦስት ከሆነ ዘመነ ሉቃስ ምንም ቀሪ ባይኖር ደግሞ ዘመነ ዮሐንስ ነው፡፡
እንቁጣጣሽ



ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ የጠቢቡ ሰሎሞንን ዝና ሰምታ ኢየሩሳሌም ተጉዛ ስትመለስእንቁ ለጣትሽ /ለጣትሽ እንቁ/ በማለት ከእንቁ የተሠራ የጣት ቀለበት ንጉሥ ሰሎሞን እጅ መንሻ እንዲሆናት አበርክቶላት ነበርና ይህን ታሪክ መነሻ አድርገው እንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜ ከዚያ እንደመጣ የታሪክ ድርሳናት ያስረዱናል፡፡ በኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ዕለት ምድሪቱ በክረምቱ ዝናብ ረስርሳ ድርቀቷ ተወግዶ በአርንጓዴ እጸዋት ተውባ ሜዳው፣ ሸለቆውና ተራራው በአደይ አበባ ተንቆጥቁጠው የሚታዩበት ወቅት በመሆኑ ዕለቱእንቁጣጣሽየሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
በዚህ ወቅት ሕፃናትና ልጃገረዶች ነጭ ባሕላዊ ልብስ በመልበስ ለምለም ቄጤማና አደይ አበባ በመያዝ በአካባቢያቸው በመዞር አዲስ ዘመን መበሠሩንእንኳን አደረሳችሁበማለት በቸርነቱ ዓመታትን የሚያፈራርቀውን እግዚአብሔርን በዝማሬ ያመሰግናሉ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ለምን ተባለ?

ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን ሲጽፍየእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ እነሆ መንገድህን የሚጠርግ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፡፡ የጌታን መንገድ አዘጋጁ፡፡ ጥርጊያውን አቅኑእያለበምድረ በዳ የሚጮኸ ሰው ድምፅተብሎ በኢሳይያስ እንደተነገረ የነቢዩ ዘካርያስ ልጅ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ላይ ተነስቶ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!” እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እየመሰከረ በምድረ በዳ የንስሐን ጥምቀት እያጠመቀ መጣ ብሎ ለዘመነ ወንጌል የመጀመሪያ ምዕራፍ ትምህርትና ተግሳጽ እንዳደረገው ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ ይነግረናል፡፡ /ማር. 114 ኢሳ. 403-4/፡፡
የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱን በመረዳት የቤተ ክርስቲያን አበው የበዓላትን ድንጋጌ በወሰኑበት አንቀጽ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በሚከበርበት መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ እንደወሰኑ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ /ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 1-3/፡፡




የዘመን አቆጣጠራችን ከሌሎች ለምን ተለየ?

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ባሕረ ሐሳብ በሚል መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከምዕራባውያን የተለየበትን ምክንያት ሲገልጹሮማውያን የሮም ከተማ የተቆረቆረችበትን ዘመን መነሻ ያደርገው ይተቀማሉ፤ ታላቁ እስክንድርም የገነነበት ዘመን መቁጠሪያቸው ሆኖ ነበርየእኛ ካህናትም ዘመነ እስክንድር በሚል ይጠቀሙበት እንደነበር መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ሶርያውያን የዘመን አቆጣጠራቸውን የሚለኩት በፀሐይ ቆጥረው ለዓመቱ 365 ቀን 6 አካፍለው ዕለትን መስጠትን ከሮማውያን በተዋሱት ጊዜ የዓመቱን መጀመሪያ አዲስ ዓመት ይሉታል፡፡ በኋላ የሰማዕታት መታሰቢያ እንዲሆን 460 ዓመተ እግዚእ ወደ መስከረም 1 ቀን ለወጡት፡፡ የሀገራችን ሊቃውንትም አዲስ ዓመታችን መስከረም አንድ ቀን እንዲሆን የወሰኑት ይኸንን በመከተል ነው፡፡ የዓመቱን መጀመሪያ በመስከረም ማድረግን ከሶርያውያንም ሆነ ከግብጾች ብናገኘውም ጀማሪው 46 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ይገዛ የነበረው ዩልዮስ ቄሣር ስለነበር በዩልዮስ ባሕረ ሐሳብ ይባላል፡፡
ዩልዮስ ቄሣ 46 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ባወጣው የዘመን አቆጣጠር ሥርዐት መሠረት ዓመቱን 365 ዕለት 6 ሰዓት አድርጎ ለአራቱ ወራት 3030 ዕለት ለእንዱ 28 ቀን 4 ዓመት አንዴ 29 ቀናት ለቀሩት ሰባት ወራት 3131 ቀናት መድቦላቸው 12 ቦታ ከፍሎታል፡፡ አውሮፓውያኑ የሚጠቀሙበትን ይህን አቆጣጠር መነሻ አድርገው ነው፡፡ የእኛ ዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን እንዴት እንደተለየ አሥራት ገብረ ማርያም የዘመን አቆጣጠር በሚለው መጽሐፋቸው ሲገልጹዲዮናስዮስ የተባለው የሮም መነኩሴ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተወለደበት ዘመን በስሌት ለመድረስ የተከተለው መንገድ የታሪክ ክስተትን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት ዘመን ለመሰወን የታሪክ ክስተትን አልተከተለችም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የተከተለችው ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን 5500 ዘመንን ነውበማለት የልዩነቱን ምክንያት ይገልጻሉ፡፡
የዘመን አቆጣጠር ልዩነት መነሻው የዚህ ክስተት መሆኑን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲያረጋግጡኢትዮጵያ ዘመነ ብሉይን እንዲህ አስከትላ 5500 ብላ ስትቆጥር ዘመነ ሐዲስ ልዩ ሆኖ ከማንም ቁጥር አይገጥምም፡፡ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ከምስራቆቹም ከምዕራቦቹም ሁል ጊዜ በሰባት ዓመት ታጎድላለች፡፡ ምክንያቱም ባለ ታሪኮችን ትታ ወንጌል ተርጓሚዎችን መነሻዋ ስላደረገች ነውብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያና የአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ልዩነት ሊኖረው ቻለ፡፡

አዲሱን ዓመት እንዴት እናክብረው?

እግዚአብሔር አምላካችን እድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ የሚሰጠን መልካም ነገር እንድንሠራበት ነው፡፡ አዲስ ዓመት በየዓመቱ የሚሰጠን የትናንት ስህተታችንን እንድናርምበት ነው፡፡ የተጣላን እንድንታረቅ፣ የበደልን እንድንክስ፣ የታረዘን እንድናለብስ፣ የተጠማን እንድናጠጣ፣ የራበውን እንድናበላ እንጂ፤ በኃጢአት ሕይወት እንድንመላለስ አይደለም፡፡ የዘመኑ መቀየር ከቁጥር በዘለለ የእኛውም አስተሳሰብ እንዲቀየር ነው፡፡ ለሥጋዊ ኑሮአችን መሳካት በእቅድ እንደምንመራው ሁሉ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን እናስብ፤ ቃለ እግዚአብሔር ለመማር፣ ንስሐ ለመግባት፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል መንፈሳዊ እቅድ እናውጣ! ተግባራዊ ለማድረግም ጥረት እናድርግ፡፡ ከዘመን ወደ ዘመን የምንሸጋገረው ቅዱሳን መላእክት በሚለምኑልን የብደር እድሜ እንደሆነ እንረዳ፡፡ አምላካችን ከእኛ ሕይወት ፍሬ ለማግኘት በልጅነታችን፣ በወጣትነትና በሽምግልና እድሜያችን ሦስት ጊዜ መጣ ፍሬ ሃይማኖትና ምግባር አጣብን አትክልተኞቹን ቅዱሳን መላእክትንስለምን ደግሞ መሬቱን ታጎሳቁላለች?” ቢላቸውጌታ ሆይ ዙርያዋን እስክኮተኩትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋትእያሉ በለመኑት የብድር እድሜ ነው አዲስ ዓመቱን ለማየት የቻልነው /ሉቃ. 136-9/፡፡
በተሰጠን የብድር እድሜ መልካም ነገር ለመሥራት እንነሣ በስንፍና ያሳለፍነው ጊዜ ይብቃን! ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ እንዲህ ይለናልየአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት ጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና /1 ጴጥ. 43/፡፡ እንደማያይ ዝም ሲለን ነገ ሊፈርድ ዛሬን ስለታገሰን እግዚአብሔር አምላካችን በኃጢአታችን የተስማማ አድርገን የምንቆጥር ካለን ተሳስተናል፡፡ አዲሱን ዓመት በጭፈራና በዳንኪራ ለማሳለፍ ያቀድን ከዚህ መጥፎ ሕይወት እንውጣና ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ ለኃጢአት ሥራ የምናወጣውን ገንዘብ ለድሆች በመስጠት አብረናቸው እናክብር፤ ያን ጊዜ እኛ በሕይወት ተቀይረን አዲሱ ዓመት መቀበላችን እውነት ይሆናልና፡፡
  


ምንጭ:--


Wednesday, August 21, 2019

አስገራሚ የታክሲ ላይ ጥቅሶች


• ምክረው ምክረው እንቢ ካለ በሴት አስመክረው::
• አንድ ማፍቀር ግድ ነው፤ ሁለት ማፍቀር ንግድ ነው፤ ሦስት ማፍቀር ኮንትሮባንድ ነው፡፡
• ምን ጊዜው ቢረዝምም ቋንጣና ባለሥልጣን መውረዱ አይቀርም፡፡
• ሹፌሩን በፍቅር ማሳቅ እንጂ በነገር ማሳቀቅ ክልክል ነው፡፡
• ድብርትንና ጥይትን ተኝቶ ማሳለፍ ነው፡፡
• በፍርፍር ያዘነ በጥብስ ይደሰታል፡፡ በፍቅር ያዘነ…?
• የዓለም ሙቀት መጨመር መንስኤ ጭቅጭቅ ነው፡፡
• ባለጌና ዋንጫ ወደ አፉ ሰፊ ነው፡፡
• ባጃጅን አወቅሽ አወቅሽ ሲሏት ታፔላ አወጡላት::
• ይሄ አናት ለቴስታ እንጂ ለትምህርት አይሆንም፡፡
• ሲጠሉህ ሳይሆን ሲወዱህም ለምን በል፡፡
• ማንም ሰው የጣለውን ሲያነሱበት አይወድም፡፡

• የኪስ ሌቦች ቆዩ! ሂሳቡን ሳንቀበል ሥራ እንዳትጀምሩ፡፡
• ሂሳብ ሳይከፍሉ ሀሳብ አይጀምሩ፡፡
• ኑሮና ታክሲ ካልታገሱት አይሞላም፡፡
• እስክናውቅ እንጂ እስክናብድ አንማርም፡፡
• ሱሪህን ሳይሆን ራስህን ዝቅ አድርገህ ኑር፡፡
• ያለውን የሰጠ ባዶውን ይቀራል፡፡
• ምክርና ቦክስ ለሰጪው ቀላል ነው፡፡
• ቅን ሁን እንጂ ቅንቅን አትሁን፡፡
• ለማይጨቃጨቅ የፀባይ ዋንጫ እንሸልማለን፡፡
• ለከፈሉት መጠነኛ ታሪፍ ዘና ይበሉ እንጂ አይኮፈሱ፡፡
• 3 ቀን ለመኖር 4 ቀን አትጨነቅ፡፡
• ሻወርና ትችት ከራስ ሲጀምር ጥሩ ነው፡፡
===================================
ምንጭ፡- https://www.addisadmassnews.com/
 

Thursday, March 14, 2019

የአክሱም ጫፍ አቁማዳ

ገጣሚ ደበበ ሰይፉ
*****************



















ትግራይ ላከ ወሎ ጋ አበድረኝ ብሎ አንድ ቁና ጤፍ
ወሎም አፈረና የለኝም ማለቱን ባህሉን መዝለፍ ቆሌውን መንቀፍ
ላከ ወደ ሸዋ ምናልባት ቢሰጠው ለሰው እሚተርፍ፡፡
ሸዋም አፈረና የለኝም ማለቱን ወደ ሐረር ዞረ
ሐረርም መልሶ ባሌን አተኮረ
ባሌም ወደአርሲ ፤ አርሲ ሲዳሞን
ሲዳሞም ተክዞ ፤ ግን የለኝም ብልስ ማን ያምነኛል ብሎ
ወደጋሞ ላከ አቁማዳ ጠቅሎ፡፡

ጋሞን ብርድ መታው ሐዘን ገባውና
የራሱን ምንዳቤ የግል ስቅየቱን ችሎት በጥሞና
በጋቢ ደቡኖ የልቡን ጠባሳ ሲኖር እንደደህና
ዛሬ የወንድሙን የእርዳኝ አቤቱታ መስማት አልቻለና፡፡
አውጥቶና አውርዶ ላከ ወደ ከፋ እጅግ አስተዛዝኖ
ከሀፍረት ያድነኛል ፤ከረሃብ ያወጣኛል ሲል ባያሌው አምኖ፡፡
ከፋ እንደደረሰው በድንገት አቁማዳው በነብሱ ዋይታ
ሐራራው ተሰማው የሥጋው ድንፋታ
በብልሃት አዛጋ ቆይቶ ቆይቶ የተስፋ ጠል ቀዳ
ሲልክ ከኢሉባቦር አበድረኝ ብሎ እህል በአቁማዳ፡፡
ጭምቱ ኢሉባቦር ይኖር የነበረ የቤቱን ጉድ ጓዳ
በሞኝሞኝ ገላው ቆዳው ውስጥ ወሽቆ
ጠየቀ ወለጋን ሐፍረቱን ደብቆ ኩራቱን ዘቅዝቆ፡፡
ኬት አመጣ ብሎ ወደኔ ላከብኝ እያለ ወለጋ
እጅጉን ተደሞ
ሄደ ወደጎጃም ዛሬን ሁነኝ ብሎ ሲማፀነው ቁሞ፡፡
ጎጃምም ተሰምቶት ፤ሰቀቀን ሐዘን
ደረት እየመታ ፤ ቅኔ እያወረደ ፤እንባ እያፈሰሰ
ወግና ኩራቱን በየቦዳው መሐል እየነሰነሰ
ዐባይን ተሻግሮ ከጎንደር ደረሰ፡፡
ፋሲል ላይ ተነጥፎ፤ ጎንደርም ሐዘን ላይ ነበረ ተቀምጦ
ተድላ ልጁ ሙቶ ፣ ገናን ክንዱ ታጥፎ በዘመን ተድጦ
ጎጃም መጣ ሲሉት የእዝን የተመኘን ልቡን በታዘበ
የኩራት ካባውን ሊጥል ባንጓበበ
የወንድሙ መምጣት እቅጩ መንስዔ ፤መሆኑን ሲረዳ ረሀብ አበሳ
ጥንትም አልሆነኝም ከእንግዲህ ይበቃኛል ለይሉኝታ አልሳሳ
ብሎ ከኤርትራ እህል ለመበደር በርትቶ ተነሳ፡፡

የዘመዱ እጦት ነበረና እጦቱ በዝቶ ሰቀቀኑ
ኤርትራ ታመመ ደም ጎረፈ ከዓይኑ
ወደትግራይ ላከ መላ ባገኝ ብሎ ከአደራ ደብዳቤ
"እባክህ ላክልኝ አንድ አቁማዳ እህል ልሞት ነው ተርቤ፡፡"
ትግራይ አስተውሎ አቁማዳው የራሱ መሆኑን ለይቶ
ረሃብ ዕጣቸው የሁሉ ወንድሞቹ መሆኑን አካቶ
ሐዘኑ አነቀው ፣ትንፋሹ መረረው ትካዝ ሆዱ ገብቶ፡፡
"እኔና ወንድሞቼ" አለ በለዘብታ
ለራሱ እንዲያወራ የራሱን ስሞታ፣

"እኔና ወንድሞቼ ሁላችን...ሁላችን
ከባዶ አቁማዳ ነው እሚዛቅ ፍቅራችን
ይህ ነው አንድነታችን
ይህ ነው ባህላችን
ዘመን ማ
ጋቱ በያንደበታችን፡፡
ለኋላ ትውልዶች ተረት እንዳይመስል ይህ ብካይ እሮሮ
ይህ ጠፍ ሰብእና ይህ ስቁይ አእምሮ
እንዳኖረው ያሻኛል ይህንን አቁማዳ ከፍ ካለ ስፍራ መጥቆ እንደባንዲራ
ምንም ባዶ ቢሆን በውስጡ አይጠፋና የታሪክ አዝመራ"

ይህንን ተናግሮ ከአክሱም ሐውልት ዘንድ ትግራይ ተጠግቶ
አንዴ እየፀለየ አንዴ እያወዘመረ ያለመጠን ተግቶ
ጫፉ ላይ ሰቀለው ያን አቁማዳ አውጥቶ፡፡
*************************************
ደበበ ሰይፉ
1967 ዓ.ም.

                   ይህው በድምፅ:-
                                          https://www.youtube.com/watch?v=7rSJw8ipadQ


Tuesday, October 23, 2018

ፀሐፊ ተውኔት ኃይሉ ፀጋዬ _በሸገር መዝናኛ

ሰብአዊ ስሜት ….የህሊና ‘ረፍት!_ኬቨን ካርተር


በፈረንጆቹ አቆጣጠር ማርች 1993 ‹‹ኬቨን ካርተር›› የተባለ ደቡብ አፍሪቃዊ የፎቶ ግራፍ ባለሙያ ሱዳን ውስጥ ተከስቶ በነበረው ችጋር የተነሳ ከተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ልኡክ ጋር ለደግነት በደቡብ ሱዳን ከተመ፡፡ በአንዱ መከረኛ እለትም ይህቺን ከታች የምትመለከቷትን ምስል በካሜራው አስቀረ፡፡
‹‹ርሀብ አድቅቆት የገዛ ራሱን መሸከም ያቃተው ህፃን ልጅ ‹‹……….እና ……..››ይህን ገላ ለመግመጥ የቋመጠ ጥንብ አንሳ››
የረሀብን ክፉ ገፅታ ….የድርቅን አሰቃቂ ሁነት….የምስኪኖችን እልቂት ….ቃላት ሊገልፁ ከሚችሉበት አቅም በላይ በሆነ መንገድ በድንቅ ካሜራው ለአለም አስቃኘ፡፡
‹‹ቀጫጫ እጆች…..እንኳን ለመሮጥ፣ለመቦረቅ ይቅርና የገዛ አካሉን ለመሸከም ያዳገተው እግር፣ መቆም የከበደው ገላ‹‹….. እና …….››ፈርጣማ አሞራ!!››


 ይህ ፎቶ እንደ እ.ኤ.አ በማረች 26 1993 ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ተሸጦ ታተመ፡፡ ምስሉ በመላው አለም ታየ፣ ክብር እና ዝናን አተረፈ፡፡ የባለሙያው ስም….ከፍ ከፍፍፍፍፍፍፍ…. አለ፡፡ተሸለመ፣ተሞገሰ፣ተከበረ፡፡
ከዚህ ሽልማት በውሀላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከአንድ ጥግ የተወረወረች ያልተጠበቀች ጥያቄ ግን የህይወቱን አቅጣጫ እስከወዲያኛው ቀየረችው፡፡አመሳቀለችው፡፡
‹‹ህፃኗ ልጅ እንዴት ሆነች….ታደግካት?????????>>
አይኖቹ ፈጠጡ….ላብ አጠመቀው………ቃላት ከአንደበቱ ጠፋ!!………..በሀሳብ ጥቂት ወደ ደቡብ ሱዳንዋ መንደር ተሰደደ፡፡ጠያቂው ግን ድጋሚ በጩኸት ጠየቀ
‹‹ህፃንዋን ልጅ ታደግካት ወይ????››
ካርተር ጋዜጣዊ መግለጫውን አቋርጦ ወጣ፡፡ ከወዳጅ ከዘመድ ሁሉ ተሰወረ፡፡ በብቸኝነት ገዳም ውስጥ….በፀፀት ተከተተ፡፡



በገዳይዋ ፊት ጥሏት የሄደው ጎስቋላ ህፃን ነፍስ ለወራት እንቅልፍ ነሳው፡፡የፎቶግራፍ ሽልማቱን ባሸነፈ በሶስት ወሩ በልጅነቱ ሲቦርቅ ባደገባት ‹‹ፓርክሞር›› በተባለች ለምለም ቀዬ በ33 አመቱ እራሱን ገድሎ ተገኘ፡፡
በሞቱ ዋዜማ ላይ ሆኖ ለወዳጅ ዘመዶቹ ባስቀረው ማስታወሻ የሚከተለውን ፀፀት አሰፈረ
.
“I’m really, really sorry. The pain of life overrides the joy to the point that joy does not exist… depressed … without phone … money for rent … money for child support … money for debts … money!!! … I am haunted by the vivid memories of killings and corpses and anger and pain … of starving or wounded children, of trigger-happy madmen, often police, of killer executioners … I have gone to join Ken if I am that lucky.”
ስንደመድም፡-
ከምንም ከምንም ነገር በፊት ሰብአዊ ስሜት!!! ክብር ፣ሽልማት፣ አዱኛ………ከሰውነት ወዲያ ይደርሳል!!!! /////////////////////////////////////////////////////********************///////////////////////////////////////////////////
ምንጭ:- http://getutemesgen24.com/
              http://100photos.time.com/photos/kevin-carter-starving-child-vulture

Monday, November 20, 2017

ሕዳር ሲታጠንና ዓለምን ያጠቃው የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ

ሀብታሙ ግርማ
***************
የ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ሁለት አስርት ዓመታት ለመላው የዓለም ህዝብ የሰቆቃ ዓመታት ነበሩ፤ ምክንያቱ ደግሞ የወቅቱ ሃያላን መንግስታት በሁለት ጎራ ሆነው ጦርነት ውስጥ ገብተው ስለነበር ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ1914 ዓ.ም እስከ 1918 ድረስ የዘለቀውና የ15 ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ይህ ጦርነት፣ በታሪክ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡  የጦርነቱ ማብቃት ሊታወጅ ጥቂት ሲቀረውና ዕልቂቱ ቆመ ሲባል ግን የዓለም ህዝብ ሌላ ፍዳ ማስተናገድ ግድ ሆነበት፤ በሰው ሰራሽ ችግሮች (በዋነኝነት በጦርነት) ተወጥሮ የቆየው መላው የአለም ህዝብ አሁን ደግሞ በእንፍሉዌንዛ በሽታ ከዳር እስከ ዳር  ተጠቃ፡፡

በተለምዶ የስፓኒሽ ፍሉ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ፣ መነሻው ከወደ አሜሪካ እንደሆነ ይታመናል፡፡ እ.ኤ.አ በጥር ወር 1918 ዓ.ም በአንደኛው የአለም ጦርነት ማብቂያ ዋዜማ፣ በጦርነቱ ለመካፈል የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት ከተከሰተው ወረርሽኝ ጋር ይያያዛል፡፡ በካንሳስ በሚገኘው ፉንስተን የወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የተቀሰቀሰው ወረርሽኙ፣ በሶስት ቀናት ብቻ 45 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አጠቃ፤ወታደሮቹ አትላንቲክን አቋርጠው አውሮፓን እንደረገጡ በሽታውም አውሮፓ ደረሰ፡፡ የእንፍሉዌንዛ በሽታው በአውሮፓ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በፈረንሳይ ቢሆንም በጦርነቱ ምክንያት ለፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ይሆናል በሚል ወረርሽኙ ለህዝብ ሳይገለጽ ተደብቆ ቆይቷል፡፡ በሽታው ይፋ የሆነው  እ.ኤ.አ በህዳር ወር 1918 ዓ.ም  በስፔን  ለመጀመሪያ ጊዜ በሽታው መታየቱን ተከትሎ ነበር፡፡ 


ስፔን በጦርነቱ ተካፋይ አልነበረችምና በአገሪቱ የጦርነት ጊዜ ሳንሱር አልነበረም፤ በመሆኑም የበሽታው መስፋፋት ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን በማግኘቱ ወረርኙ እስፓኒሽ እንፍሉዌንዛ (ስፓኒሽ ፍሉ) የሚለውን ስያሜ አገኘ፡፡
የበሽታው ምልክቶች ሳል፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ነስር፣ የጆሮና የአንጀት መድማት፣ ተቅማጥ፣ የአይን ማስለቀስና ውጋት ሲሆኑ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስም የአእምሮ ህመም ያስከትላል፡፡
  በሽታው ከኮሌራ ወይም ከፈንጣጣ በሽታዎች ጋር ተቀራራቢ ምልክቶችን ስለሚያሳይ ብዙ ያምታታ ነበር፡፡ የበሽታው አስገራሚ ባህሪ፣ አንድ ሰው በበሽታው በተጠቃ በአምስት ቀን ውስጥ ወይ ይሞታል አልያም ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ ይፈወሳል፡፡ ይህም እንደ ግለሰቡ የበሽታ መከላከል አቅም ይወሰናል፤ ቫይረሱ የተፈጥሮ የበሽታ የመከላከል አቅምን የሚያዳክም ሲሆን ጠንካራ የመከላከል አቅም ያለው ሰው ከአምስት ቀናት በላይ  መቋቋም ስለሚያስችለው  በስድስተኛው ቀን ፈውስ ያገኛል፡፡
የበሽታው አማጪ ቫይረስ ባለመታወቁ መድሃኒትም ሆነ ማስታገሻ አልተገኘለትም፡፡ (እ.ኤ.አ በ1933 ዓ.ም በእንግሊዛዊያን ሳይንቲስቶች እንደተረጋገጠው የበሽታው አማጪ ቫይረስ በሳይንሳዊው አጠራር H1N1 ተብሎ ይታወቃል፡፡) በዚህም የተነሳ የበሽታውን ስርጭት ለማቆም አልተቻለም፡፡ በጥቂት ጊዜም ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከኤሽያ እስከ አፍሪካ፣ከአርክቲክ እስከ ፓስፊክ ደሴቶች ድረስ በከፍተኛ ፍጥነት ተዛመተ፡፡ በሽታው እንዲዛመት የአለም የወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ ይህም ወታደሮች ከአንዱ የአለም ክፍል ወደ ሌላው ለዘመቻ መንቀሳቀሳቸው ነበር፡፡ አንድ ሶስተኛው የአለም ህዝብ በዚህ በሽታ እንደተያዘም ይነገራል፤ በበሽታው ከተያዙት ውስጥ ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ሲኖ ባይሎጂካ የተሰኘ የህክምና ጥናት ማዕከል ባደረገው ጥናት መሰረት፤ በአሜሪካ እስከ 28 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በበሽታው ተጠቅቶ ነበር፤ 675 ሺህ ገደማ የሚሆነው ህዝብ ደግሞ በበሽታው ሞቷል፡፡ ወረርሽኙ  በህንድ የከፋ ነበር፡፡ 


መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ 17 ሚሊዮን ህንዳዊያን በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በጃፓን 23 ሚሊዮን ህዝቦችን ያጠቃ ሲሆን 400 ሺህ ገደማ የሚሆኑትንም ገድሏል፡፡ እንግሊዝ  ሩብ ሚሊዮን፣ ፈረንሳይ ደግሞ 400 ሺህ ዜጎቻቸውን በበሽታው አጥተዋል፡፡ እ.ኤ.አ ከጥር ወር 1918 ዓ.ም እስከ ታህሰስ 1920 ዓ.ም በመላው ዓለም ተንሰራፍቶ የቆየው የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ፣አንድ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ፈጅቷል፤ የሟቾቹ ቁጥር እስከ 200 ሚሊዮን ይደርሳል የሚሉ መረጃዎችም አሉ፡፡ የወረርሽኙን ጉዳት የከፋ ያደረገው አምራች ዜጎችን በከፍተኛ ሁኔታ በማጥቃቱ ነበር፡፡ በበሽታው ከሞቱት መካከል ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 34 ዓመት የሆኑ ወጣቶች አብዛኛውን ድርሻ ይወስዳሉ፤ በመሆኑም በሽታው ካደረሰው ሰብዓዊ ውድመት ባለፈ ጥሎት ያለፈው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠባሳ የከፋ ነበር፡፡
ወረርሽኙ በአፍሪካ በሁለት ዙር ነበር የተከሰተው፤ የመጀመሪያው  በፈረንጆቹ በ1918 ዓ.ም የጸደይና የበጋ ወራት ሲሆን ሁለተኛውና የከፋ ጉዳት ያደረሰው ደግሞ  በበልግ ወራት የታየው ነበር፡፡ በሽታው ለመጀመረያ ጊዜ በአፍሪካ የታየው በወቅቱ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበረችው በሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታዎን ሲሆን በአጭር ጊዜ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ተስፋፋ፡፡ ሚስተር መሪ (Murray) የተባሉ አጥኚ Global Pandemic በተሰኘ ጥናታቸው እንዳሰፈሩት፤ የበሽታው ስርጭት ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት ላይ ሰፊ ነበር፤ በክፍለ አህጉሩ የተከሰተው የሞት መጠን በመላው ዓለም በበሽታው ከተከሰተው ሞት ውስጥ የ29 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ በተለይም በምዕራብና ደቡባዊ አፍሪካ ጥፋቱ የከፋ ነበር፤ በጋና እስከ መቶ ሺህ ዜጎች እንዳለቁ ይገመታል፤ በምስራቅ አፍሪካም ቀላል የማባል ቁጥር ያላቸው ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በእንግሊዝ ሶማሊ ሰባት በመቶ የሚሆኑ ህዝቦች በበሽታው ሲሞቱ፣ በኢትዮጵያም ከአርባ ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ከሰብዓዊ ውድመቱ ባለፈ ወረርሽኙ በአፍሪካ ከባድ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ በጊዜው አጠራር ደቡብ ሮዴሺያ (የዛሬዋ ዚምባብዌ) አምራች የሰው ሀይል በበሽታው በመያዙ የወርቅ ማውጫ ስፍራዎች እንዲዘጉ ሆኖ ነበር፤ በዚህም በማዕድን ዘርፍ ላይ የተንጠለጠለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ክፉኛ ተጎዳ፡፡  ወረርሽኙ በማላዊና በዛምቢያም ያደረሰው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ከፍ ያለ ነበር፡፡ በናይጀሪያም፣በተለይ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በሽታው የከፋ ጥፋት በማድረሱና ምርት በማሽቆልቆሉ፣ ቀድሞ ለምግብነት የማይውለው ካሳቫ ለምግብነት መዋል ጀመረ፡፡ በአነስተኛ ጉልበትና ያለ ብዙ ልፋት የሚመረተው ካሳቫ ተመራጭ ምግብ ሆነ፡፡ 


የ1918ቱ የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ በአፍሪካ ያስከተለው ማህበራዊ ቀውስ ቀላል አልነበረም፡፡ በሽታው ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት፣ የኢኮኖሚ ደረጃን ሳይለይ ሁሉንም ሰው የሚያጠቃ ቢሆንም ቅኝ ገዢዎች በሽታው ከጥቁር ህዝቦች የመጣ እንደሆነ በማናፈስ የዘር መድልዖ ለማድረግ ተጠቅመውበታል፡፡ ይህ ችግር በተለይም በደቡብ አፍሪካ የጎላ ነበር፤ በዚህም ነጮችና ጥቁሮች ማንኛውንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በአንድ ላይ እንዳያደርጉ የሚደነግግ አዋጅ እንዲጸድቅ ተደረገ፡፡ በቦትስዋናም በሽታው በርካታ ህጻናትን ወላጅ አልባ አድርጓል፡፡ በጋና የሆነው ደግሞ ትንሽ ለየት ያለ ነበር፤ በሽታው ተንሰራፍቶ በርካታ ሴቶች በመጠቃታቸው፣ ከነባራዊው የጋናዊያን ባህልና ወግ ባፈነገጠ መልኩ ባሎች የሴቶች ድርሻ ተደርጎ ይወሰድ የነበረውን የቤት ውስጥ ስራዎች መስራት ግድ ሆነባቸው፡፡  ወንዶች ማዕድ ቤት ገብተው በቆሎ መፍጨት፣ ምግብ ማብሰል የመሳሰሉትን ስራዎች ይከውኑ ጀመር፡፡
በኢትዮጵያ በሽታው የታየው የመጀመሪያው የበሽታው ምልክት በዓለም ላይ ከታየ ከአስር ወራት በኋላ በህዳር ወር 1911 ዓ.ም ነው፡፡ ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ በሽታው መግባቱ አይቀርም በሚል የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች መስራት እምብዛም የተለመደ አልነበረም፡፡ በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚችለው በኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቆንሰላ ያደረገው ነገር ነበር፡፡ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሪቻረድ ፓንክረስት እ.ኤ.አ በ1990 ዓ.ም ባሳተሙት An Introduction to the Medical History of Ethiopia በሚለው የምርምር ስራቸው ላይ እንደጻፉት፤ በሽታው በውል ያልታወቀ ነበርና ምናልባትም የፈንጣጣ በሽታ ይሆናል በሚል በወቅቱ በኢጣሊያ ቆንስላ ትብብር በሀምሌ ወር 1910 ዓ.ም አስር ሺህ ዶዝ የፈንጣጣ ክትባት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ተደርጎ ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ከዘመናዊ ህክምና ጋር ለማይተዋወቀው የኢትዮጵያ ህዝብም ወረርሽኙ ታላቅ መቅሰፍት ነበር፡፡ በሽታው ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ በመላው አገሪቱ ከባድ ዕልቂት ማስከተል ጀመረ፡፡ በተለይም ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን  በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ መረበሽን ፈጥሯል፡፡  


በበሽታው ከተጠቁ ታላላቅ የዘመኑ ሹመኞችና የቤተ መንግስት ሰዎች መካከል ራስ ተፈሪ መኮንን (ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ) እና ባለቤታቸው ወ/ሮ አቴጌ መነን አስፋው ይገኙበታል፡፡ እንዲያውም የራስ ተፈሪና ቤተሰቦቻቸው  ሀኪም የሆኑት ሊባኖሳዊው ዶክተር አሳድ ቼይባን ራሳቸው የበሽታው ተጠቂ ነበሩና የራስ ተፈሪን ቤተሰብ የሚያክም ጠፍቶ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ከህዳር 7 እስከ ህዳር 20 ቀን 1911 ዓ.ም  ለአስራ አራት ቀናት ገደማ የቆየው በሽታው በህዳር ወር የተከሰተ በመሆኑም ህዝቡ የህዳር በሽታ እያለ ይጠራው ጀመር፡፡ ብላቴን ጌታ መርስዔ ሀዘን ወልደቂርቆስ የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በተሰኘው መጽሀፋቸው እንዳሰፈሩት፤ ወረርሽኙ እስከ አርባ ሺህ ኢትዮጵያዊንን ለሞት ዳርጓል፤ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ዘጠኝ ሺህ ዜጎች በበሽታው ሞተዋል፡፡ በተለይም ህዳር 12 ቀን 1911 ዓ.ም በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሞቱበት በመሆኑ በቀኑ የጽዳት ዘመቻ እንዲደረግ በአዋጅ ተነግሮ ስለነበር፣ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ይህ ነገር እንደባህል ተወስዶ በየዓመቱ ህዳር 12 ቀን  የጽዳት ዘመቻ ይደረግ ጀመር፤ ይህም በተለምዶ ህዳር ሲታጠን የምንለው ነው፡፡ዶ/ር እናውጋው መሃሪ፣ዶ/ር ክንፈ ገበየሁ እና ዶ/ር ዘርጋባቸው አስፋው የተባሉ የህክምና ባለሙያዎች በጋራ ያሰናዱትና በ2013 እ.ኤ.አ የታተመው The Manual of Ethiopian Medical History ላይ እንደሰፈረው፤ የ1918ቱ የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ክትባት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በአሜሪካን የቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ (Vanderbilt University) ምሁራን ሲሆን ወቅቱም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናት በየጊዜው የተሻሻሉ ክትባቶች በምርምር ተገኝተዋል፡፡ በ1918 ዓ.ም እንደተከሰተው እንፍሉዌንዛ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ባያውቅም ዛሬም ድረስ ግን የሰው ልጆች የጤና ፈተና መሆኑን አላቆመም፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም ብቻ በመላው ዓለም አምስት መቶ ሺህ ሰዎች በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ የእንፍሉዌንዛ ክትባቶች የዋጋ ውድነት መፍትሄ ካላገኘ፣ ህዝቡ ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ ካላገኘ፣ መንግስታት በሽታውን ለመከላከል ከፍ ያለ ትኩረት ካልሰጡ ---- በእንፍሉዌንዛ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት መቀነስ አዳጋች ነው፡፡  


*******************************************************************************
 http://www.addisadmassnews.com/    Saturday, 21 November 2015

Monday, March 27, 2017

ዋ …ያቺ አድዋ_ፀጋዬ ገብረመድኅን



ዋ …
አድዋ ሩቅዋ
የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ችጋግ ዳስዋ
አድዋ . . .
ባንቺ ብቻ ህልውና
በትዝታሽ ብጽዕና
በመስዋእት ክንድሽ  ዜና
አበው ታደሙ እንደገና፡፡
ዋ …
ዓድዋ የዘር ዐፅመ ርስትዋ
የደም ትቢያ መቀነትዋ
በሞት ከባርነት ስርየት
በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰውብሽ ለት
ዓድዋ
የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ
የኢትዮጵያዊነት ምስክርዋ
ዓድዋ
የኩሩ ደም ባንቺ ጽዋ
ታድማ በመዘንበልዋ
ዐፅምሽ ቤንሳኤ ነፋስ
ደምሽ በነፃነት ህዋስ
ሲቀሰቀስ ትንሳኤዋ
ተግ ሲል ሲንር ትቢያዋ
ብር ትር ሲል ጥሪዋ
ድው እልም ሲል ጋሻዋ
ሲያስተጋባ ከበሮዋ
ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ
ያባ መቻል ያባ ዳኘው
ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው
ያባ በለው በለው ሲለው
በለው በለው በለው በለው!

ዋ …ዓድዋ …
ያንቺን ጽዋ ያንቺን አይጣል
ማስቻል ያለው አባ መቻል
በዳኘው ልብ በአባ መላው
በገበየሁ በአባ ጎራው
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው
በለው ብሎ፡ በለው በለው!
ዋ . . .ዓድዋ . . .
ዓድዋ የትላንትናዋ
ይኸው ባንቺ ህልውና
በትዝታሽ ብፅዕና
በመስዋዕት ክንድሽ ዝና
በነፃነት ቅርስሽ ዜና
አበው ተነሱ እንደገና፡፡
ዋ!  . .  ያቺ ዓድዋ . . .
አድዋ ሩቅዋ
የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ችጋግ ዳስዋ
አድዋ . . .