የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አ.አ.ድ)
The Organization of African Unity(OAU)
ግንቦት
17 ቀን 1955 ዓ.ም) የ32 ነፃ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት
(OAU) ያሁኑ የአፍሪካ ህብረት (AU) ምስረታ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሤና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተማ
ይፍሩ ያላሠለሠ ጥረት በአዲስ አበባ ከተማ እውን ሆነ ።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ በመሰብሰቢያው አዳራሽ የሚገኘው በአሰፋና ሠረቀ የማነብርሃን የተሣለ የ፴፪ቱ መሥራች መሪዎች ምስል።
ለብዙ ሺ ዓመታት ኢትዮጵያ ብቻዋን በአኅጉሩ ውስጥ ከአውሮፓ ውያኖች የቅኝ ግዛት ቀንበር ውጪ ቆይታ የሙሶሊኒ ፋሺስት ኢጣልያ በ፲፱፻፳፰ ዓ/ም ወርራት በነበረ ጊዜ አርበኞች ልጆቿ ውድ አገራቸውንና ነጻነታቸውን አሳልፈው ላለመስጠት አምስት ዓመታት ሙሉ ተዋጉ። ንጉሠ ነገሥታቸውም የእዚህን የግፍ ወረራ ለማጋፈጥ በዓለም መንግሥታት ማኅበር መድረክ ላይ ሲቀርቡ፣ ከአፍሪቃ አኅጉር ብቸኛዋ አባል ኢትዮጵያ ማንም አጋዥ አገር አልነበራትም።
ለአኅጉሩ ነጻነት በቅኝ ግዛት ሥርም የነበሩት ሕዝቦች፤ በነጻነትም ላይ የነበሩት አገራት የአውሮፓውያንን መዥገራዊ ልጥፍነት ለማላቀቅ ብዙ ከታገሉ በኋላ በሰሐራዊ አፍሪቃ የካቲት ፳፯ ቀን ፲፱፻፵፱ ዓ/ም ጋና ነጻ ሆነች። ከዚያ አስከትሎ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት እስከተመሠረተ ድረስ በ፲፱፻፶፩ ዓ/ም ጊኒ ነጻ ስትሆን በ ፲፱፻፶፪ ዓ/ም አሥራ አምስት አገራት፤ በ፲፱፻፶፫ ዓ/ም ሦሥት አገራት፤ በ፲፱፻፶፬ ዓ/ም ደግሞ አራት አገራት ነጻነታቸውን ተቀዳጁ።
የአኅጉሩ መሪዎች በዓለም መድረክ ላይ ለበለጠ ተሰሚነት የትብብርን ግንባር ማሳየት እንደነበረባቸው
በመገንዘብና ገና ነጻ ላልወጡትም ወንድም አገሮች ሉዐላዊነት መታገል ስለነበረባቸው ዓላማቸውን ግብ ለማድረስ በሁለት
ቡድን ተከፍለው ፣ ባንድ በኩል እራሱን “የዘመናዊ ተራማጅ” ብሎ የሚጠራው፣ በጋና ው ፕሬዚደንት ክዋሜ ንክሩማ የሚመራው የ “ካዛብላንካ ቡድን” በ ፲፱፻፶፬ ዓ/ም ተመሠረተ። ይሄ ቡድን የአኅጉሩን መንግሥታት በኅብረት ለማዋሃድ ዓላማ የያዘ ሲሆን አባላቱ ጋና ፣ አልጄሪያ ፣ ጊኒ ፣ ሞሮኮ ፣ ግብጽ ፣ ማሊ እና ሊቢያ ነበሩ።
ሁለተኛው ቡድን የ”ሞንሮቪያ ቡድን” ሲሆን የተመራው በ ሴኔጋል ፕሬዚደንት ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንግሆር ነበር። አባላቱ ሴኔጋል ፣ ናይጄሪያ ፣ ላይቤሪያ እና ኢትዮጵያ ሲሆኑ የነሱ የኅብረት አስተያየት ደግሞ የዱኛ ኅብረት ሳይሆን ፍላጎታቸው ረጋ ባለ ሁኔታ የዱኛኪን ኅብረት አንድነትን ያስከትላል የሚል ነበር።
መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ከተማ ይፍሩ ታላቅ ጥረትና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ ሁለቱም ወገኖች አዲስ አበባ ላይ እንዲገናኙ በተደረገው ጥሪ መሠረት ተሰባስበው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን የስምምነት ውል ፴፪ ነጻ ሀገሮች ሲፈርሙ ድርጅቱ ተመሠረተ።
************************************
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘኢትዮጵያ የአፍሪካ አባት Haile Selassie I of Ethiopia: Father of the O.A.U.’’ (የናይጄሪያው ሳንዴይ ኦብዘርቨር፤ ጁላይ 23፣ 1972)
ኢትዮጵያዊ ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ ስለ አፍሪካ ነፃነት
በጀግንነት የተዋጋ፣ ነፃነትም ቋሚ እንዲሆን፣ ሕዝቦቻችን ያለ ምንም የውጭ መንግሥታት ተቆጣጣሪነትና ጣልቃ ገብነት
በተገቢ ሥልጣናቸው እየተመሩ የገዛ ራሳቸውን ዕድል እንዲመሩ ያላቸው ሥልጣን እንዲጠበቅላቸው የደከመ አፍሪካዊ ሕዝብ
ነው፡፡ ይህ በንጉሡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ አስተባባሪነትና መሪነት፣ የአፍሪካውያኖች ጉባኤ የተደረገው በኢትዮጵያ
መናገሻ ከተማ ስለሆነ፣ አዲስ አበባና ኢትዮጵያ አሁንም የበለጠ ከአፍሪካ ታሪክ ጋር የተሳሰሩ እንዲሆኑ
አድርጓቸዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት በአንድ አኅጉር ሕዝቦች ፈቃድ ተነሳስቶ በሚመራው የዕድገት ፍላጎትና ሥራ ሁሉ
ሳይቋረጥ ስማቸው ተያይዞ የሚኖር ይሆናል…፡፡’’ (የጊኒው ፕ/ት የነበሩት ሴኮቱሬ)
የትናንቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የዛሬው የአፍሪካ
ህብረት የተመሰረተው ከ59 ዓመታት ግንቦት 16 ቀን 1955 ዓ.ም ነበር፡፡ ወቅቱ የአፍሪካ አገራት በሁለት
የተከፈሉበት ነበር፡፡ በአንድ ወገን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ሀገራቱ በፍጥነት ተዋሕደው አፍሪካ አንድ ልትሆን
ይገባል የሚለው የካዛብላንካ ቡድን፤ እንዲሁም አንድ ከመሆን በፊት ሌሎች ትብብሮች ሊቀድሙ ይገባል የሚለው
የሞኖሮቪያ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያም በወቅቱ የሞኖሮቪያን ቡድን ተቀላቅላ ነበር፡፡ በኋላ ኢትዮጵያ ባደረገችው
ከፍተኛ ጥረት ሁለቱ ቡድኖች የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት ባስቻለው ስብሰባ ላይ ለመታደም አዲስ አበባ
ከተሙ፡፡
ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በጉባኤው ላይ ለተገኙት የአፍሪካ መሪዎች ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንዲህ አሉ፡-
“በዚህ በዛሬው ቀን በዚህች በዋና ከተማችን በአዲስ
አበባ የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ተካፋይ ለመሆን የመጣችሁትን የነፃ አፍሪካ አገር መሪዎች፣ ወንድሞቻችን በራሳችንና
በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ስንቀበል በጣም ደስ ይለናል፡፡ ይህ ዛሬ እኛ የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት መሪዎች
የምናደርገው ጉባኤ በዓለም ላይ እስካሁን ድረስ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ የዚህን ታላቅ ጉባኤ መደረግና የመላው አፍሪካ
አገሮች መሪዎች ተካፋይ በመሆን ለዚህች ክፍለ ዓለማችን በውስጧም ለሚገኙት ሕዝቦቻችን ላለን ጥልቅ አሳቢነት
ዓይነተኛ ምስክር ነው፡፡ ባጭሩ ይህ ቀን ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን በመላ ታሪካዊና ታላቅ ቀን ነው…፡፡’’
ዕለታዊው የአዲስ ዘመን የወርኻ ግንቦት 15 ቀን 1955
ዓ.ም. ዕትሙ በፊት ለፊት ገጽ ላይ፣ ‘‘ሠላሳ የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት ጉባኤ በአፍሪካ አዳራሽ ተከፈተ፤
ግርማዊ ጃንሆይም የጉባኤው የክብር ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተመረጡ፡፡’’ በሚል ዐቢይ ርዕስ ስር እንዲህ ይላል፡-
“ቁጥራቸው ከ250 ሚሊየን በላይ በሆኑ አፍሪካውያን እጅግ
በጋለ ስሜት ይጠበቅ የነበረውና መላው ዓለም ሁኔታውን በቅርብ ይከታተለው የነበረው የ30ዎቹ የአፍሪካ ነጻ
መንግሥታት መሪዎች ጉባዔ ግንቦት 14 ቀን ትናንት ከእኩለ ቀን በኋላ በአፍሪካ አዳራሽ ተከፍቷል፡፡ ጉባኤውን
የከፈቱት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጉባኤው ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የአንድ ደቂቃ የኅሊና ጸሎት
እንዲደረግ አሳስበው ጸሎት ተደረገ፡፡’’
ቀጥሎም የሊቀመንበር ምርጫ እንዲደረግ አሳስበው የጊኒው
ፕሬዚደንት ሴኩቱሬ የመጀመሪያውን ምርጫ እንዲያደርጉ ተጠየቁ፡፡ እርሳቸውም የኢትዮጵው ንጉሥ ኃ/ሥላሴ የጉባኤው
ሊቀመንበር እንዲኾኑ ጠቆሙ፤ የፕሬዚደንት ሴኩቱሬ ሐሳብ በጉባኤው አባሎች በሙሉ በመደገፉ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ
የአፍሪካ አንድነት ደርጅት የመጀመሪያው ፕሬዚደንት ኾነው ተመረጡ፡፡ ከዚህ በኋላ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ለዚህ
ታሪካዊ ጉባኤ ሥራ ታላቅ መመሪያ የሚሰጥ የሚከተለውን ንግግር አደረጉ፡፡
“ዛሬ የገጠመን ዕድል በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ መቼም
ያልተገኘ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ በፊታችን የተደቀኑት ችግሮች ያንኑ ያህል ከፍ ያሉና ከባድ ናቸው፡፡ ታሪክና ጊዜ
የጣሉብን ከፍተኛ ኃላፊነት ሁላችንም ረጋ ብለን እንድናስብና እንድናመዛዝን ያስገድደናል፡፡ የተነሳንበትን ከፍተኛ
ተግባር በመልካም አከናውነን ብንገኝ ስማችንና ተግባራችን በታሪክ መልካም ስም ይኖረዋል፡፡ ተግባራችንን ሳንፈጽም
ብንቀር ግን ይታዘንብናል፡፡ ስለዚህ እምነታቸውን የጣሉብንን ሕዝቦቻችን በሚመጡት ጊዜያቶች ውስጥ ከእኛ የሚጠብቁትን
ሁሉ ለመፈጸም እንዲያበቃን ሁሉን የሚችለውን ፈጣሪያችን ጥበብንና አስተዋይነትን እንዲሰጠን እናምነዋለን፣
እንለምንዋለንም፡፡’’
በወቅቱ በአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ የተገኙት የናይጄሪያው
ጠቅላይ ሚኒስትር ታፌዋ ባሌዋ ለአፍሪካ አንድነት እውን መሆን ኢትዮጵያና ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ያደረጉትን ታላቅ
አስተዋጽዖ ሲገልጹ ተከታዩን ብለው ነበር፤
“መላው የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎችና የመንግሥታት ባለ
ሥልጣኖች በአዲስ አበባ ላይ ሊገኙ ለመቻላቸው በግርማዊነትዎ ጥረት ስለሆነ በተለይ ለግርማዊነትዎ እጅግ ከፍ ያለ
ክብር የሚያሰጥ ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ አንድነት እንዲገኝ የምናደርገው ጥረት ወደፊት የኢትዮጵያን መናገሻ ከተማ
የአዲስ አበባ ስም ደጋግሞ የሚያወሳ ስለሆነ የአዲሲቱ አፍሪካ ታሪክ የግርማዊነትዎን ስም በተቀዳሚው ገጹ ላይ
አሳምሮ የሚያኖረው ለመሆኑ ጥርጥር የለበትም፡፡’’
የጊኒ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሴኮቱሬም በአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ለአፍሪካ አንድነት ምስረታ ኢትዮጵያ ያደረገችውን ታላቅ አስተዋጽዖ እንዲህ ገልጸውታል፡-
“… ኢትዮጵያዊ ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ ስለ አፍሪካ
ነፃነት በጀግንነት የተዋጋ፣ ነፃነትም ቋሚ እንዲሆን፣ ሕዝቦቻችን ያለ ምንም የውጭ መንግሥታት ተቆጣጣሪነትና ጣልቃ
ገብነት በተገቢ ሥልጣናቸው እየተመሩ የገዛ ራሳቸውን ዕድል እንዲመሩ ያላቸው ሥልጣን እንዲጠበቅላቸው የደከመ
አፍሪካዊ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ በንጉሡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ አስተባባሪነትና መሪነት፣ የአፍሪካውያኖች ጉባኤ የተደረገው
በኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ስለሆነ፣ አዲስ አበባና ኢትዮጵያ አሁንም የበለጠ ከአፍሪካ ታሪክ ጋር የተሳሰሩ እንዲሆኑ
አድርጓቸዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት በአንድ አኅጉር ሕዝቦች ፈቃድ ተነሳስቶ በሚመራው የዕድገት ፍላጎትና ሥራ ሁሉ
ሳይቋረጥ ስማቸው ተያይዞ የሚኖር ይሆናል…፡፡’’
ድርጅቱን በመመስረት ረገድ አፄ ኃይለ ሥላሴ የነበራቸውን
ሚና አስመልከቶ፣ ኢንሳክሎፒዲያ ብሪታኒካ ስለ አፄ ኃ/ሥላሴ ባቀረበው አጠር ያለ ጽሑፍ ‘‘Haile Selassie
played a very important role in the establishment of the Organization of
African Unity in 1963’’ ብሏል፡፡
‘‘ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ቀኃሥ) የአአድ መሥራች እና አባቱም የሆኑለት ከድርጅቱ ዋናዎቹ አንቀሳቃሾች አንዱ እንደነበሩ የጋናው ዘጋኔያን ታይምስ በጁላይ 24፣ 1972 ዕትሙ የፊት ገጽ ላይ ጽፎአል፡፡
የናይጄሪያው ሳንዴይ ኦብዘርቨር ቀኃሥ 80ኛ ዓመታቸውን
ባከበሩበት ሐምሌ 16 ቀን 1964 ዓ.ም. (ጁላይ 23፣ 1972) ባወጣው ዕትሙ ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት
አባት ኢትዮጵያዊው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› (Haile Selassie I of Ethiopia: Father of the
O.A.U.) በሚል ርዕስ ስለግርማዊነታቸው ሰፊ ሐተታ አውጥቶ ነበር፡፡
እንደ ሰንዴይ ኦብዘርቨር አገላለጽ፣ ቀኃሥ ስለ አፍሪካ
ያላቸው ውጥን እጅግ በጣም የተዋጣና የተቃና መሆኑን ጠቅሶ፣ አዲስ አበባ ‹‹የፓን አፍሪካን መዲና›› (የአፍሪካ
አንድነት ከተማ) ለመባል የበቃችበትን ምክንያት አስታውሶ ነበር፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ኢትዮጵያ ስለአፍሪካ ሕዝብ
የፖለቲካ ደኅንነት ላላት ተቆርቋሪነት ጉልህ ምልክት ነው፡፡ ድርጅቱ የተቋቋመውም በድንገት ከተፈጠረ ስሜት
አልነበረም፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በእርጋታና አንዳንድ ጊዜም በግላቸው የአፍሪካ አገሮች ገና ነፃነታቸውን ሳይጎናጸፉ
የወደፊት መሪዎች ለሚሆኑት ሰዎች የትምህርትን ዕድል በመስጠት ረድተዋል፡፡ ግርማዊነታቸው በአፍሪካ አህጉር ያላቸው
ተሰሚነት አገራቸው ከድንበሮቿ ውጭ ካላት ተሰሚነት የተገኘ ሳይሆን ንጉሠ ነገሥቱ ካተረፉት የመከበር ዕድል ነው፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም የአፍሪካ ኃይሎች ራሳቸውን
ለመከላከል ይተባበሩ ዘንድ ግርማዊ ጃንሆይ ባላቸው እምነት መሠረት ፈቃዳቸውን ከግቡ ማድረሳቸው የሚያስደንቅ ነው፡፡
በዚህም መሠረት፣ በየትኛም የአህጉሩ ክፍል አምባጓሮ ቢነሳ ተገቢው ስምምነት እንዲፈጸም ግርማዊነታቸው ዓይነተኛ
መድኅን ሆነዋል፡፡ በዚህም መሠረት የናይጄሪያ ችግር በተፈጠረበት ጊዜ የአስታራቂነት ዕርምጃ የወሰዱ ሲሆን ይህም
ፍጻሜ እንዳገኘ በችግሩ ምክንያት አለመግባባት የተፈጠረባቸውን አፍሪካውያን መሪዎችን ፈጥነው ለማስማማት ችለዋል፡፡
ጃንሆይ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ድርጅት ጋር በመተባበር የወጠኑት 16 ዓመታት የፈጀውን የሱዳንን ችግር
በማስወገድ ታሪካዊ ስምምነት እንዲፈጸም አስችሏል፡፡
ግርማዊነታቸው ሴኔጋልና ጊኒ አለመግባባታቸውን ለማስወገድ
በተስማሙበት ይኸውም በላይቤሪያ ዋና ከተማ በሞንሮቪያ ውስጥ በተደረገው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ ሊቀ
መንበር ሆነው መርተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቀደም ሲል ጀምሮ የታሪክ
ሥፍራቸውን መያዛቸው ጉልህ ነው፡፡
በውጩም ዓለም ቢሆን አፍሪካ ግንባራቸው ሳይታጠፍ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከእስያ መሪዎች ጋር ለመቋቋም የሚችሉ ከፍተኛ መሪዎች ያላት መሆኑን ግርማዊ ጃንሆይ በሚገባ አስመስክረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ጋዜጦች በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ፣
ፈረንሣይኛና ጣሊያንኛ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ልዩ ካቢኔ ፕሬስ ክፍል ከ1957 እስከ 1966 ዓ.ም. ይታተም
የነበረው መጽሔት የቀኃሥን ተግባሮች መዘከሩ ይታወቃል፡፡ አንዱ የጠቀሰው ለንደን ታይምስ (The Times
London) በጁላይ 22፣ 1972 (ሐምሌ 15 ቀን 1965 ዓ.ም.) ዕትሙ፣ ‹‹የንጉሠ ነገሥቱ ጽኑ ሥልጣን
በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ታፋሪነትን አትርፎላቸዋል›› (Emperor’s firm authority earns respect
among the Leaders of Africa) በሚል ርዕስ ሐተታውን አስፍሮ ነበር፡፡
በመጭረሻም፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ዋነኛ
አላማው በቅኝ አገዛዝ ስር የነበሩ አገሮችን ነጻ ማውጣት ነበር፡፡ ድርጅቱ ሲመሰረት 32 ነጻ ሀገራት ብቻ
የነበሩት፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በወቅቱ በቅኝ አገዛዝ ለሚማቅቁ አገሮች ተገቢውን ወታደራዊ ድጋፍና ስልጠና
ሰጥቷል፡፡ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ /ANC/ አፓርታይድን እንዲዋጋና ZANU እና ZAPU የተባሉ የፖለተካ
ድርጅቶች ዚምባብዌን ነጻ እንዲያወጡ ድርጅቱ መሳሪያና ወታደራዊ ስልጠና አበርክቷል፡፡
አፓርታይድን ለማውገዝ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ
በአህጉሪቱ እንዳይበር ማዕቀብ መጣሉና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በማሳመን የተመድ አካል የሆነው የዓለም የጤና
ድርጅት ከደቡብ አፍሪካ እንዲወጣ ማድረጉ ታሪክ ከመዘገባቸው የድርጅቱ ስኬቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በተመሰረተ በ39 ዓመቱ በ1994 ዓ.ም. ስሙን ለውጦ፣ ዛሬ 55ቱም የአፍሪካ አገራት አባል በሆኑበት የአፍሪካ ኅብረት ተተክቷል፡፡
https://ethioreference.com/archives/31356
***************************************
አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ኢትዮጵያና የአፍሪካ አንድነት/ኅብረት – በፍቅር ለይኩን
en-haile-selassie‹‹ኢንሳክሎፒዲያ ብሪታኒካ›› ስለ አፄ ኃ/ሥላሴ ባቀረበው አጠር ያለ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹Haile Selassie played a very important role in the establishment of the Organization of African Unity in 1963.›› ዕለታዊው የአዲስ ዘመን የወርኻ ግንቦት 15 ቀን 1955 ዓ.ም ዕትሙ በፊት ለፊት ገጽ ላይ፣ ‹‹ሠላሳ የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት ጉባኤ በአፍሪካ አዳራሽ ተከፈተ፡፡ ግርማዊ ጃንሆይም የጉባኤው የክብር ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተመረጡ፡፡›› በሚል ዐቢይ ርዕስ ዜናና ሰፊ ሐተታን ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡
የሰኞ ማለዳው የግንቦት 19 ቀን 1955 ዓ.ም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ደግሞ በርእሰ አንቀጹ፣
‹‹የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ የሌሎችንም ብሎኮችና ቻርተሮች ሠርዞ የአፍሪካ አንድነትን የሚመሠርተው ‹የአፍሪካና የማላጋሲ አገሮች ድርጅት ቻርተር› ግንቦት 17 ቀን ለግንቦት 18 ቀን አጥቢያ 1955 ዓ.ም. ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ላይ በአፍሪካ አዳራሽ ውስጥ ተፈርሟል፡፡ በአራቱ ቀን ጉባኤ ፍጻሜ አዲስ የአፍሪካ ታሪክ፣ አዲስ የዓለም ታሪክ ተጽፏል፣ ተመዝግቧል፡፡›› ሲል የምስራቹን ዜና አስነብቧል፡፡ የትላንትናው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት የ50ኛ ዓመቱን የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን በተለያዩ አገር አቀፍና አኅጉር አቀፍ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅቱን ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በተለይም ደግሞ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት ግንባር ቀደም ሚና ባላትና ታላቅ አስተዋጽኦ ባደረገችው፣ የኅብረቱም ዋና መቀመጫ በሆነችው በአገራችን ኢትዮጵያ የበዓሉን ዝግጅት የደመቀና ልዩ ለማድረግ ሽር ጉድ እየተባለ ነው፡፡
ይህን በዓልም ባማረና በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ራሱን የቻለ የበዓል ዝግጅት ሴክረታሪያት ቢሮ ተቋቁሞ፣ የአፍሪካ ኅብረት የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት በዓሉን ዓመቱን ሙሉ ለማክበር፣ የተለያዩ ዝግጅቶችን ቀርጾ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ አይተናል፣ ሰምተናል፣ አውቀናልም፡፡
ከወራት በፊትም በመዲናችን በአዲስ አበባ ዋና ዋና ቦታዎችና አደባባዮች ላይ ‹‹I am African. I am the African Union›› የሚሉ የአፍሪካ ሕዝቦችን ማንነት፣ ታሪክ፣ ቅርስና ባህል የሚያንጸባርቁ፣ የአፍሪካዊነትን ስሜት፣ ኩራትና ወኔ የሚቀሰቅሱ ፖስተሮችን አይተናል፡፡ ከዑራኤል ወደ እስጢፋኖስ በሚወስደውም መንገድ ላይም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ያቋቋሙ የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ የሆኑ አባቶች ምስልም በትልቁ ተሰቅሎ አይቻለሁ፡፡ ይህ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መልካም ሊባል የሚችል ነው፡፡ ለወደፊቱም በዓሉ በተለያዩ መጠን ሰፊ በሆኑ ዝግጅቶች እንደሚከበርና በበዓሉም ላይም የአፍሪካ አገራት ርዕሳነ ብሔራት፣ ተወካዮችና ባለ ሥልጣናት፣ ዓለም አቀፍ መሪዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለ ሙያዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ደራሲያን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች … ወዘተ በሚሳተፉበት በደመቀ ሁኔታ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የበዓሉ ዝግጅት ኮሚቴ በተደጋጋሚ አሳውቋል፡፡
በዚህ ጽሑፌ ከሰሞኑ መላው አፍሪካና አፍሪካውያን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና እንዲሁም በአጠቃላይ የአፍሪካ ወዳጆች፣ የመንግሥታቱ ድርጅት፣ የተለያዩ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ታዋቂ ሰዎች አብርውን በደስታ ሊያከብሩት እየተዘጋጁ ስላለው የአፍሪካ ኅብረት የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ስናወራ ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ትልቅ ቁም ነገር አለ፡፡
ይኸውም በዚህ በዓል ላይ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለአፍሪካ ኅብረት እውን መሆን ትልቅ መሥዋዕትነት የከፈሉትንና ስማቸውን በወርቅ ቀለም በታሪክ ማሕደር የጻፉትን አፍሪካውያን አባቶቻችንን ማስታወስ የሚገባን ይመስለኛል፡፡ ይህ ጽሑፍም ለትላንትናው አፍሪካ አንድነት ድርጅት ለዛሬው የአፍሪካ ኅብረት እውን መሆን የታገሉትን የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ አባቶቻችንን ታሪክ በተከታታይ በአጭሩ ለማቅረብ ይሞክራል፡፡
ይህ ጹሑፍ የአፍሪካ ኅብረትን የ50ኛ ዓመት ወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ በቅድሚያ የአፍሪካ አባት፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማትና የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ዓርማ፣ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቋቋምና በሂደትም ለኅብረቱ እውን መሆን ትልቁን የመሠረት ድንጋይ ስላስቀመጡት ስለ አፄ ኃ/ሥላሴ ታሪክ፣ ፖለቲካዊ ሰብእና፣ በአፍሪካውያንም ሆነ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ስለነበራቸው መወደድ፣ ተቀባይነትና ታላቅ ክብር በአጭሩ በማዘከር የታሪክ ማስታወሻውን አሐዱ ብሎ ይጀምራል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ስለ አፄ ኃ/ሥላሴ መንግሥት ታሪክ በእሳቸው ዘመን ከነበሩ ከተራው የኅብረተስብ ክፍል ጀምሮ እስከ ታላላቅ ባለ ሥልጣናትና የሃይማኖት አባቶች፣ ዲፕሎማቶች፣ የውጭ አገር መሪዎች፣ ታላላቅ ሰዎችና ፖለቲከኞች በቃል ከተናገሩት፣ በጽሑፍ ካስቀመጡት፣ በግል ማስታወሻዎቻቸው ከተዉልን፣ እንዲሁም የአጼ ኃ/ሥላሴንና የኢትዮጵያን ታሪክ በተመለከተ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጸሐፍት በመጻሕፍቶቻቸው ካሰፈሯቸው መረጃዎች በመነሣት ነው ይህን አጠር ያለ የታሪክ ማስታወሻ ጽሑፍ ያዘጋጀሁት፡፡
በአጭር ቃል የዚህ ተከታታይ ታሪክ አቅራቢ የአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመን ጣእሙንም ሽታውንም አልደረስበትም፡፡ በእሳርቸው ዘመንም አልታሰበም፣ አልተፈጠረምም፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ታሪክ ተማሪነቴና ባለሙያነቴ የኢትዮጵያን ታሪክ በሰፊውና በሚገባ ማጥናት ከጀመርኩበት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አንስቶ አሁን እስካለሁበት የትምህርት ሕይወቴና የሥራ ልምዴ እንዳስተዋልኩት፣ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ አፄ ኃ/ሥላሴ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የሚገለጹበት ታሪክ፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ዘንድም አንቱታን ያተረፉበትን ዝናና ክብር እንዲጎናጸፉ ያደረጋቸው በሳል የሆነ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሰብእና እንዳላቸው ነው የተረዳሁትና ያስተዋልኩት፡፡ በስድስት ዓመታት ውስጥ ለሁለት ጊዜ ‹‹Man of the Year›› የዓመቱ ምርጥ ሰው በማለት የለንዶኑ ታይምስ መጽሔት የመረጣቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ ከፍ ያለ ሰብእና የነበራቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ታላቅ መሪና አባት የሚታዩ የተዋጣላቸው ዲፕሎማቲክ፣ እንዲሁም በዓለማችን ከሚገኙ ታላላቅ መሪዎችና ፖለቲከኞች ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የነበራቸው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናትና ብዙዎች ሰዎች ይመሰክራሉ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ኃ/ሥላሴ ከሀያ በየሚበልጡ የክብር ዶክትሬት ድግሪዎችን ከተለያዩ አገራት መሪዎችና ዩኒቨርስቲዎች ተቀብለዋል፡፡ ምናልባትም አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምትታወቀበት ድርቅ፣ ራብና የእርስ በርስ ጦርነት ባሻገር በአንጻራዊ መልኩም ቢሆን በአዎንታዊነት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአገራችንን ስም በመልካም እንዲነሣ ምክንያት ከሆኑ የኢትዮጵያ መሪዎች መካከል አፄ ኃ/ሥላሴ አንዱ፣ ብቸኛውና ዋንኛው ናቸው ብል፣ ብዙም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ ይህን ኢትዮጵያን አዎንታዊ በሆነ መልኩ እንድትነሳ በማድረግ ረገድና ዓለም አቀፉ የፖለቲካ መድረክ የነበራቸውን ተቀባይነት፣ ክብርና ዝና እንዲሁም ለባለ ቃል ኪዳን አገሮችና በኋላም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሥረት፣ ለ50ኛ ዓመቱ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉ ዋዜማ ላይ ለሚገኘው ለአፍሪካ ኅብረት እውን መሆን፣ ንጉሡ አፄ ኃ/ሥላሴ የነበራቸውን ትልቅ ሚና የሚያስታውስ አንድ ያጋጠመኘኝን ታሪክ እዚህ ጋር ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
እውቁ የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላና በርካታ አፍሪካውያን የነጻነት ታጋዮች ለ27 ዓመታት በተጋዙበትና በመንግሥታቱ ድርጅት፣ ዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ቅርስ አድርጎ በመዘገበው በሮቢን ደሴት ሙዚየምና በደቡብ አፍሪካ የአርትና ካልቸር ደፓርትመንት የሚሰጠውን የስኮላር ሺፕ አሸንፌ፣ በተማርኩበት በኬፕታውኑ የዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርስቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ቆይታዬ ከኢትዮጵያዊነት የነጻነት መንፈስና ከአፄ ኃ/ሥላሴ ጋር በተገናኘ አንድ በእጅጉ ያስደነቀኝ ነገር ገጥሞኝ ነበር፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በዋነኝነት በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርስቲና በኬፕ ታውን ዩኒቨርስቲ በሚገኙ ደቡብ አፍሪካውያንና የሌሎች አፍሪካ አገሮች የተቋቋመ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ (የራስ ተፈሪያን) የተማሪዎች እንቅስቃሴ ኅብረት በሚል መጠሪያ የሚታወቅ በዩኒቨርስቲው ግቢ ቢሮ ተሰጥቶት የሚንቀሰቀስ ማኅበር ነበር፡፡ በነገራችን ላይ በደቡብ አፍሪካ አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች እንደታዘብኩት በፖለቲካና በሃይማኖት፣ እንዲሁም ኪነ ጥበብን፣ ባህልንና ታሪክን መሠረት አድርጎ የተቋቋሙና በነጻነት በዩኒቨርስቲው ግቢ ቢሮ ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ በተማሪዎች የተቋቋሙ የተለያዩ ድርጅቶችና ፓርቲዎች ይገኛሉ፡፡
ታዲያ እኔ በተማርኩበት በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርስቲ በሚገኘው የግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የተማሪዎች ኅብረት እንቅስቃሴ ቢሮ ውስጥ የእንቅስቃሴው ደጋፊዎችና አባላት የሆኑት ተማሪዎች ለኢትዮጵውያን የስኮላር ሺፕ ተማሪዎች ባቀረቡላቸው ጥያቄ መሠረት የአማርኛ ቋንቋን የሚያስተምሯቸው ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ከእኔ ቀደምው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለምርምር ሥራ፣ ለልምድ ልውውጥና ለተጨማሪ ጥናት ወደ አውሮፓ በሄዱበት አጋጣሚ ለእነዚህ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ከአንተ በተሻለ ስለ ኢትዮጵያችን የሺህ ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ የነጻነት ተጋድሎና ቋንቋችንን ሊያስተምራቸው የሚችል የለም በማለት ከራስ ተፈራውያኑ የዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ ጋር አስተዋወቁኝ፡፡
ከዚሁ ማኅበር አባላት ተማሪዎቹ ጋር በተዋወኩበት በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚገባ ለመግባባት ቻልን፡፡ ለጥቂት ወራት እነዚህ ወጣት ተማሪዎች የአማርኛ ቋንቋ ማስተማር ቆይታዬ እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ሃይማኖት … ወዘተ ባደርግናቸው ውይይቶች በርካታ ቁም ነገሮችን አንስተን እንነጋገር ነበር፡፡ በአብዛኛው የውይይታችን ማእክል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ፣ ለአፍሪካ የፀረ-ባርነትና የፀረ-ቅኝ ግዛት የነፃነት ትግል፣ በደቡብ አፍሪካ ፀረ-አፓርታይድ ትግል ውስጥ ስለነበራቸው ጉልህ ሚናን በተመለከተ ነበር፡፡ በዚህ ውይይታችን ውስጥ ደግሞ ደጋግመው ከሚነሱት መካከል አፄ ኃ/ሥላሴ አንዱና ዋናው መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
እኔ እንደ ኢትዮጵያዊነቴና የታሪክ ባለሙያነቴ ስለ አገሬ ኢትዮጵያ ታሪክና ስለ መሪዎቻችን ካለኝ ግንዛቤና እውቀት ይልቅ እነዚህ አፍሪካውያን ተማሪዎች ስለ አኅጉራችን አፍሪካና ስለ አገሬ ታሪክ ያካፈሉኝ እውቀታቸውና ያላቸው መረዳት በጊዜው በእጅጉ ግርምትን አጭሮብኝ ነበር፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህልና የነጻነት ተጋድሎ ውስጥ ያላቸውን ማእከላዊ ስፍራን በተመለከተ የሚያስረዱ በቢሮአቸው ያሰባሰቧቸው መጻሕፍቶችና መዛግብቶቻቸው፣ የምስልና የድምፅ መረጃ ክምችቶቻቸው በእጅጉ ነበር ያሰደነቀኝ፡፡
ከዚህም በላይ ደግሞ ሌላው በእጅጉ ያስደመመኝ ነገር ቢኖር በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ በሚገኘው የራስ ተፈሪያኑ ተከታዮች ማኅበር ቢሮ ግድግዳ አንድ ጎን በሁለት የታሪክ መስመር ተከፍሎ በተለያዩ ሰዎች ምስሎችና መረጃዎች አሸብርቆ ያየሁት Wall of Fame እና Wall of Shame የሚለው የቢሮው ግድግዳ ክፍል ነው፡፡ በዚሁ Wall of Fame እና Wall of Shame ወይም ‹‹የታሪክ ዕንቁዎችና የታሪክ አተላዎች›› ተብሎ በተከፈለው ግድግዳ ላይ ‹‹በዎል ኦፍ ፌም›› ምስላቸውና ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከተለጠፉት መካከል የአፄ ኃ/ሥላሴና የባለቤታቸው የእቴጌ መነን በመጀመሪያው ረድፍ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በዓድዋው ዘመቻ የኢጣሊያንን ወራሪ ኃይል አሸንፈው አዲስ የጥቁር ሕዝቦችን አዲስ ታሪክ የጻፉት የአፄ ምኒልክ፣ እንዲሁም ከእንግሊዞች ጋር ተዋግተው ራሳቸውን የሠዉት የአፄ ቴዎድሮስ ምስሎችና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በዚህ ‹‹የታሪክ ዕንቁዎች›› የክብር ግድግዳ ላይ አፄ ኃ/ሥላሴ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በገፍ በወረረች ጊዜ በሊግ ኦፍ ኔሽን፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያቀረቡት አቤቱታና ንግግራቸው በልዩ ንድፍና በአገራችን ሰንደቀ ዐላማ አሸብርቆ በግድግዳው ላይ ይታያል፡፡ ‹‹የዎል ኦፍ ፌምን›› ግድግዳ ካስዋቡ የታሪክ ሰዎች ፎቶግራፎች በአብዛኛው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሸቱት በዓይነትም በብዛትም እጅግ ልቀው ይገኛሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ ‹‹በዎል ኦፈ ፌም›› የታሪክ መስመር ውስጥ ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት ትልቅ ተጋድሎ ያደረጉ እንደ እነ ማርከስ ጋርቬይ፣ አፍሪካ አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር፣ የፓን አፍሪካ አባቶች የጋናው ንኩርማ፣ የኬንያው ጆሞ ኬንያታ፣ ሴኔጋላዊው ሴዳር ሴንጎርና ሌሎችም የአፍሪካ የነጻነት ታጋዮችና መሪዎች በኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማና በኃ/ሥላሴ ግንባር ቀደም አዝማችነት የክብር ግርግዳውን ተጋርተውታል፡፡
ሌላው አስገራሚው ነገር የንጉሡን የአፄ ኃ/ሥላሴን ልደትና የነገሡበትን ዕለት የራስ ተፈራውያኑ ማኅበር ተከታይ ተማሪዎች እንግዶችን ከውጭ ሁሉ ሣይቀር በመጋበዝ ጭምር የዩኒቨርስቲውን የተማሪዎች ማእክልንና የግቢውን ሜዳ በኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማ፣ በኃ/ሥላሴና በባለቤታቸው እቴጌ መነን ፎቶ ግራፍ አሸብርቀውና በአፍሪካ የሬጌ ሙዚቃ ስልት አጅበው በታላቅ በሆነ የኢትዮጵያዊነት የነጻነት መንፈስ ቀናቱን ያከበሩ እንደነበረ ትዝ ይለኛል፡፡
የማስታውሰው በዩኒቨርስቲው የምንገኘው በጣት የምንቆጠር ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በአፍሪካም ሆነ በተቀረው ዓለም በድርቅ፣ በራብና በእርስ በርስ ጦርነት ስማችን እየተነሳ የምንሳቀቅበትን ምስላችንን፣ እነዚህ የዩኒቨርስቲው የራስ ተፈራውያን ተከታይ ተማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት በግቢው ውስጥ የአገራችንን አረንዴ፣ ብጫና ቀይ ሰንደቀ ዓላማ ሰቅለው ሲያከብሩ ስናይ በአገር ፍቅር ናፍቆትና ትዝታ፣ በኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜትና ኩራት ውስጣችን የተናጠበትን አጋጣሚ አልረሳውም፡፡ በእርግጥ የእነዚህ ተማሪዎች እንቅስቃሴና አካሄድ በአብዛኛው ሃይማኖታዊ መልክ ያለውና ኃ/ሥላሴን መለኮታዊ ሰብእና እንዳላቸው አድርጎ የሚያቀርብ ቢሆንም የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ከሃይማኖታዊ መልኩ ይልቅ አፍሪካዊነቱና ፖለቲካዊ አንድምታው በእጅጉ የጎላ ነው፡፡ እነዚህ ደቡብ አፍሪካውያንም ሆነ የሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተማሪዎች ልብም ሆነ በአብዛኛው ጥቁር ሕዝቦች ልብ ውስጥ ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ሃይማኖት፣ ነጻነት ትልቅ ተምሳሌትና ማእክል ተደርጋ የምትወሰድ አገር ናት፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ባላት የሺህ ዘመናት የረጅም ዘመን ሥልጣኔ፣ ታሪክና ቅርስ የተነሣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ የሆነ የታሪክ እሴት ያላት አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ በተለይም ደግሞ መላው አፍሪካንና የጥቁር ዘርን ሁሉ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያነቃነቀው ኢትጵያውያን በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገቡት አንጸባራቂ ድል ኢትዮጵያን ከጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ማማ ላይ እንድትወጣ አስችሏታል፡፡
ለአፍሪካ፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያንና በጃማይካና በካረቢያ ላሉ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል መለኮስ ይኸው የአድዋው ድል ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ የእነ ማርከስ ጋርቬይና የትግል አጋሮቹ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነትና የመብት ጥያቄ ውሉ የሚመዘዘው ከኢትዮጵያዊነት የነጻነት መንፈስ፣ የአባቶቻችን የአይበገሬነትና ቆራጥ የተጋድሎ ታሪክ ውስጥ ነው፡፡ የአፍሪካውያኑ የፓን አፍሪካ አቀንቃኞችና የፀረ ቅኝ ግዛት ታጋዮች የእነ ንኩርማ፣ የእነ ጆሞ ኬንያታ የአፍሪካዊነት ስሜትና ቆራጥ መንፈስ መፍለቂያ ምንጩም ይኸው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከተሸከሙት ክቡር የነጻነት ተጋድሎ አኩሪ ታሪክና ቅርስ የሚመዘዝ ነው፡፡
ከአፄ ምኒልክ የዓድዋው ድል በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኃያላኑ አገሮች እኩል የተሠለፈችው ብቸኛው የጥቁር ሕዝብ አገር ኢትዮጵያ ይህ ገናና የነጻነት ተጋድሎ ታሪኳ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ ኤዥያ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጃማይካና ካረቢያን ምድር ድረስ ዘልቆ ተሰምቶ ነበር፡፡ ይህ የኢትጵያዊነት የነጻነት መንፈስ ውሉ ሳይቋረጥ በአፍሪካውያንና በጥቁር ሕዝቦች ደም ውስጥ በሚገባ ተዋህዶ፣ በተባበረ ክንድ የጸናችና አንድ የሆነች አፍሪካ በዓለም መድረክ ከፍ ብላ እንድትታይ ደግሞ ትልቁን ሚና በመጫወት ረገድ አፄ ኃ/ሥላሴ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡
ይህን ለአፍሪካ አንድነት እውን መሆን ኢትዮጵያና አፄ ኃ/ሥላሴ ያደረጉትን ታላቅ አስተዋጽኦና ተደናቂ ሥራ በተመለከተ በወቅቱ በአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ የተገኙት የናይጄሪያው ጠቅላይ ሚኒስቴር የሆኑት፣ ክቡር ሰር አል ሃጂ አቡበከር ታፌዋ ባሌዋ እንደሚከተለው ነበር ያሉት፡- መላው የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎችና የመንግሥታት ባለ ሥልጣኖች በአዲስ አበባ ላይ ሊገኙ ለመቻላቸው በግርማዊነትዎ ጥረት ስለሆነ በተለይ ለግርማዊነትዎ እጅግ ከፍ ያለ ክብር የሚያሰጥ ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ አንድነት እንዲገኝ የምናደርገው ጥረት ወደፊት የኢትዮጵያን መናገሻ ከተማ የአዲስ አበባ ስም ደጋግሞ የሚያወሳ ስለሆነ የአዲሲቱ አፍሪካ ታሪክ የግርማዊነትዎን ስም በተቀዳሚው ገጹ ላይ አሳምሮ የሚያኖረው ለመሆኑ ጥርጥር የለበትም፡፡ አፄ ኃ/ሥላሴ በ1930ዎቹም ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል እንድትሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ኢትዮጵያንም ብቸኛዋ አፍሪካዊትና የጥቁር አገር ሊግ ኦፍ ኔሽን አባል በማድረግ ጥረታቸውን በሚገባ አሳክተዋል፡፡
በኋላም በተባበሩት መንግሥታት ምሥረታ ስብሰባ ወቅትም ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዜቬልት፣ ከብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችልና ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ስታሊን ጋር በያልታ ጥቁር ባሕር ልዩ ስብሳባ ላይ ተሣትፈዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጋራ ስምምነት መሠረትም በኮሪያ ልሣነ ምድር የኢትዮጵያን የሰላም አስከባሪ ኃይል በማሰማራት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በዚህም አፄ ኃ/ሥላሴ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ መድረክ እንዲታወቁ ትልቁን ሚና ተጫውተው አልፈዋል፡፡
ፍቅር፣ ወንድማማችነት፣ ሰላም፣ አንድነትና ኅብረት ለአፍሪካና ለአፍሪካውያንን ወሳኝና ተቀዳሚ ነገር መሆኑ የተረዱት አፄ ኃ/ሥላሴ አፍሪካውያን አባቶችን፣ ፖለቲከኞችንና መሪዎችን በማስተባበር የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲቋቋም የላቀ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
በወቅቱ ድርጅቱ ሲቋቋም የነበሩ ሰዎች እንደመሠከሩት አፄ ኃ/ሥላሴ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የአፍሪካ መሪዎችን ጉባኤ ስብሰባ በመምራት፣ ይህ የአፍሪካውያን የወንድማማችነት፣ የአንድነትና የፍቅር ሰነድ ሳይፈረም ማንኛችንም ብንሆን ከዚህ ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በጭራሽ አንወጣም በማለት የተኮራረፉና የተለያዩ ፖለቲካዊ ቁርሾ ውስጥ የገቡትን የአፍሪካ አገራት መሪዎችን በማግባባትና በማሸማገል ንጉሡ ኅብረቱ እውን እንዲሆን ታላቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡
የትላንትናው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት በሁለት እግሩ እንዲቆም በማስቻል የኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔና ቅርስ፣ የቀደሙ አባቶቻችን ጽኑና አይበገሬ የሆነው የኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ኩራትና መንፈስ እንዲሁም ጥቁር ሕዝቦችን ሁሉ ያኮራውና አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲራመድ ያስቻለው የኢትዮጵያውያኑ የነፃነት ተጋድሎ፣ በባርነትና በቅኝ ግዛት ስር ይማቅቁ ለነበሩ ለአፍሪካ አገሮች ነፃነትና አንድነት እውን መሆን ትልቁን መሠረት ጥሏል፡፡
ይህን የኢትዮጵያንና የኢትጵያውያንን ታላቅ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ብሔራዊ ኩራትና የአባቶቻችንን አኩሪ የነፃነት ገድል ለዘመናዊው ዓለም በማስተዋወቅና ረገድ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ኃ/ሥላሴ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ክቡር ስምና ዝናና የፈተረላቸውን በርካታ አኩሪ ስራዎችን ሠርተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዛሬ የ50ኛ ዓመቱን የወርቅ ኢዮቤልዩ ልደቱን ለማክበር ዋዜማ ላይ ያለውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት/ኅብረት እንዲቋቋም ከሐሳብ ወይም ከጽንሱ አንስቶ እስከ ተግባራዊነቱ ድረስ የላቀ ተሣትፎ ነበራቸው ንጉሡ አፄ ኃ/ሥላሴ፡፡
ንጉሡ ቀዳማቂ አፄ ኃ/ሥላሴ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንዲህ ነበር ያሉት፡- በዚህ በዛሬው ቀን በዚህች በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ተካፋይ ለመሆን የመጣችሁትን የነፃ አፍሪካ አገር መሪዎች፣ ወንድሞቻችን በራሳችንና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ስንቀበል በጣም ደስ ይለናል፡፡ ይህ ዛሬ እኛ የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት መሪዎች የምናደርገው ጉባኤ በዓለም ላይ እስካሁን ድረስ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ የዚህን ታላቅ ጉባኤ መደረግና የመላው አፍሪካ አገሮች መሪዎች ተካፋይ በመሆን ለዚህች ክፍለ ዓለማችን በውስጧም ለሚገኙት ሕዝቦቻችን ላለን ጥልቅ አሳቢነት ዓይነተኛ ምስክር ነው፡፡ ባጭሩ ይህ ቀን ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን በመላ ታሪካዊና ታላቅ ቀን ነው … ፡፡ የጊኒ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሴኮ ቱሬም በአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ለአፍሪካ አንድነት ምስረታ ኢትዮጵያና ንጉሡ አፄ ኃ/ሥላሴ ያደረጉትን ታላቅ አስተዋጽኦና ሥራ በተመለከተ ሲናገሩ እንዲህ ነበር ያሉት፡-
… ኢትዮጵያዊ ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ ስለ አፍሪካ ነፃነት በጀግንነት የተዋጋ፣ ነፃነትም ቋሚ እንዲሆን፣ ሕዝቦቻችን ያለ ምንም የውጭ መንግሥታት ተቆጣጣሪነትና ጣልቃ ገብነት በተገቢ ሥልጣናቸው እየተመሩ የገዛ ራሳቸውን ዕድል እንዲመሩ ያላቸው ሥልጣን እንዲጠበቅላቸው የደከመ አፍሪካዊ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ በንጉሠ በአፄ ኃ/ሥላሴ አስተባባሪነትና መሪነት፣ የአፍሪካውያኖችም ጉባኤ የተደረገው በኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ስለሆነ፣ አዲስ አበባና ኢትዮጵያ አሁንም የበለጠ ከአፍሪካ ታሪክ ጋር የተሳሰሩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት በአንድ አኅጉር ሕዝቦች ፈቃድ ተነሳስቶ በሚመራው የዕድገት ፍላጎትና ሥራ ሁሉ ሳይቋረጥ ስማቸው ተያይዞ የሚኖር ይሆናል … ፡፡ ለአፍሪካ አንድነት እውን መሆን ከአገራችን ኢትዮጵያና ከአፄ ኃ/ሥላሴ ጋር አብሮ ስማቸው የሚነሡ ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ድርጅቱንም በጸሐፊነት ያገለገሉ ባለ ታሪክ የሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ እነርሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ አቶ ከተማ ይፍሩና የድርጅቱ የመጀመሪያ ዋና ጸሐፊ ሆነው የተመረጡት አቶ ክፍሌ ወዳጆ ናቸው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አቶ ከተማ ይፍሩ በመላው አፍሪካ አገራት በመዞርና መሪዎቹን ወደ ጉባኤው እንዲመጡ በመጋበዝና በማግባባት ታላቅ የሆነ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አንዳንድ ጸሐፊዎችና ታሪክ አዋቂዎች እንደሚሉትም አቶ ከተማ ይፍሩ ከመሪዎቹ ማረጋገጫ እስከሚያገኙ ድረስ ወደ አገራቸው መሄድ እንደማይችሉ በመግለጽ አፍሪካውያን መሪዎች በስብሰባው ላይ እንዲገኙ በማድረግ ትልቅ ጥረት ማድረጋቸውን ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡
የዛሬውን መጣጥፌን ከማጠናቀቄ በፊት በቀጣይ ጽሑፌ ስለ ፓን አፍሪካ አመሠራረትና፣ በፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ውስጥ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውን ድርሻ ምን እንደነበር ከታሪክ ማሕደር በማጣቀስ ለመጻፍ እሞክራለሁ፡፡ በጽሑፌም ቀንደኛ ፓን አፍሪካኒስት ስለነበረው የጋናው ዶ/ር ንኩርማ በጥቂቱ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ የዛሬውን አጭር መጣጥፌን ኢትዮጵያ፣ ጀግና ልጆቿና ንጉሠ ነገሥቷ የነበሩት አፄ ኃ/ሥላሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅትና መመሥረትና በኋላም ለኅብረቱ እውን መሆን ያበረከቱትን ትልቅ አስተዋጽኦ ያዘከርኩበትን አጭር የታሪክ ማስታወሻ፣ አፄ ኃ/ሥላሴ በአዲስ አበባ ላይ በተደረገው የግንቦት 15ቀን 1955 ዓ.ም. የአፍሪካ መሪዎች መክፈቻ ጉባኤ ላይ ባሰሙት ታሪካዊ ንግግራቸው ጽሑፌን ልቋጭ፡፡
ዛሬ የገጠመን ዕድል በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ መቼም ያልተገኘ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ በፊታችን የተደቀኑት ችግሮች ያንኑ ያህል ከፍ ያሉና ከባድ ናቸው፡፡ ታሪክና ጊዜ የጣሉብን ከፍተኛ ኃላፊነት ሁላችንም ረጋ ብለን እንድናስብና እንድናመዛዝን ያስገድደናል፡፡ የተነሳንበትን ከፍተኛ ተግባር በመልካም አከናውነን ብንገኝ ስማችንና ተግባራችን በታሪክ መልካም ስም ይኖረዋል፡፡ ተግባራችንን ሳንፈጽም ብንቀር ግን ይታዘንብናል፡፡ ስለዚህ እምነታቸውን የጣሉብንን ሕዝቦቻችን በሚመጡት ጊዜያቶች ውስጥ ከእኛ የሚጠብቁትን ሁሉ ለመፈጸም እንዲያበቃን ሁሉን የሚችለውን ፈጣሪያችን ጥበብንና አስተዋይነትን እንዲሰጠን እናምነዋለን፣ እንለምንዋለን፡፡
ክብር ለአፍሪካ አንድነት ለደከሙ አፍሪካውያን አባቶቻችንና ጀግኖቻችን ሁሉ! ሰላም! ሻሎም!
***********************************
የዛሬው አፍሪካ ሕብረት የትላንቱ የአፍሪካ አንድነት ምስረታየትናንቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የዛሬው የአፍሪካ ህብረት የተመሰረተው ከ57 አመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 16 ቀን 1955 ዓ.ም ነበር::
ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በጉባኤው ላይ ለተገኙት የአፍሪካ መሪዎች ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንዲህ አሉ፡-
"በዚህ
በዛሬው ቀን በዚህች በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ተካፋይ ለመሆን የመጣችሁትን የነፃ አፍሪካ አገር መሪዎች፣ ወንድሞቻችን በራሳችንና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ስንቀበል በጣም ደስ ይለናል:: ይህ ዛሬ እኛ የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት መሪዎች የምናደርገው ጉባኤ በዓለም ላይ እስካሁን ድረስ ተወዳዳሪ የለውም:: የዚህን ታላቅ ጉባኤ መደረግና የመላው አፍሪካ አገሮች መሪዎች ተካፋይ በመሆን ለዚህች ክፍለ ዓለማችን በውስጧም ለሚገኙት ሕዝቦቻችን ላለን ጥልቅ አሳቢነት ዓይነተኛ ምስክር ነው:: ባጭሩ ይህ ቀን ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን በመላ ታሪካዊና ታላቅ ቀን ነው … ::"
ዕለታዊው የአዲስ ዘመን የወርሀ ግንቦት 15 ቀን 1955 ዓ.ም ዕትሙ በፊት ለፊት ገጽ ላይ፣ ‹‹ሠላሳ የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት ጉባኤ በአፍሪካ አዳራሽ ተከፈተ:: ግርማዊ ጃንሆይም የጉባኤው የክብር ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተመረጡ::›› በሚል ዐቢይ ርዕስ ስር እንዲህ ይላል፡-
"ቁጥራቸው ከ250 ሚሊየን በላይ በሆኑ አፍሪካውያን እጅግ በጋለ ስሜት ይጠበቅ የነበረውና መላው ዓላም ህዝብ ሁኔታውን በቅርብ ይከታተለው የነበረው የ30ዎቹ የአፍሪካ ነጻ መንግስታት መሪዎች ጉባዔ ግንቦት 14 ቀን ትናንት ከእኩለ ቀን በኋላ በአፍሪካ አዳራሽ ተከፍቷል:: … ጉባኤውን የከፈቱት ግርማዊ ንጉሠ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጉባኤው ስራውን ከመጀመሩ በፊት የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት እንዲደረግ አሳስበው ጸሎት ተደረገ:: ቀጥሎም የሊቀ መንበር ምርጫ እንዲደረግ አሳስበው የጊኒው ፕሬዚደንት ሴኩቱሬ የመጀመሪያውን ምርጫ እንዲያደርጉ ጠየቁ:: ክቡር ፕሬዚደንት ሴኩቱሬ ቀደም ብሎ ተደርጎ የነበረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባዔ ጠቅላላ ውሳኔ ያልሰጠ መሆኑን በመግለጽ ከተናገሩ በኋላ፣ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት የጉባዔው ፕሬዚደንት የላይቤሪያው ፕሬዚደንት ተብማን፤ የተባበረው የአረብ አንድነት ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት ናስርና የጋናው ፕሬዚደንት ንኩሩማህ፤ የአይቮሪኮስቱ ፕሬዚደንት ቧኜ፤ የናይጄሪያው ታፌዋ ባሌዋ የሴኔጋሉ ሊዎፖልድ ሴንጎር፤ የኮንጎ ብራዛቪሉ ኦቦ ፋልቤር ዩሉና የታንጋኒካው ጁሊየስ ኔሬሬ የጉባኤው ተከታታይ ፕሬዚደንቶች እንዲሆኑ ሐሳብ አቀረቡ::
ይህ ሐሳብ በጉባኤው አባሎች በሙሉ በመደገፉ በፕሬዚደንት ሴኮቱሬ የቀረበው ምርጫ ጸደቀ:: ከዚህ በኋላ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ለዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ሥራ ታላቅ መመሪያ የሚሰጥ ንግግር አደረጉ::"
አፄ ኃይለ ሥላሴ በወቅቱ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግራቸው እንዲህ ብለው ነበር::
"ዛሬ የገጠመን ዕድል በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ መቼም ያልተገኘ ትልቅ ዕድል ነው:: በፊታችን የተደቀኑት ችግሮች ያንኑ ያህል ከፍ ያሉና ከባድ ናቸው:: ታሪክና ጊዜ የጣሉብን ከፍተኛ ኃላፊነት ሁላችንም ረጋ ብለን እንድናስብና እንድናመዛዝን ያስገድደናል:: የተነሳንበትን ከፍተኛ ተግባር በመልካም አከናውነን ብንገኝ ስማችንና ተግባራችን በታሪክ መልካም ስም ይኖረዋል:: ተግባራችንን ሳንፈጽም ብንቀር ግን ይታዘንብናል:: ስለዚህ እምነታቸውን የጣሉብንን ሕዝቦቻችን በሚመጡት ጊዜያቶች ውስጥ ከእኛ የሚጠብቁትን ሁሉ ለመፈጸም እንዲያበቃን ሁሉን የሚችለውን ፈጣሪያችን ጥበብንና አስተዋይነትን እንዲሰጠን እናምነዋለን፣ እንለምንዋለን::"
ግንቦት 17 ቀን ማታ ከምሽቱ ሁለት ሰኣት ጀምሮ በታላቁ ቤተመንግስት ስለአፍሪካ መሪዎች እንግድነት ክብር ታላቅ የእራት ግብዣ አድርገው ነበር::
ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 1955 ዓ.ም የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ "ካዛብላንካና ሞኖሮቪያ ተሰርዞ አንድ ቻርተር ተፈረመ" በሚል ርዕስ ባወጣው ዜና ‹‹የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ የሌሎችንም ብሎኮችና ቻርተሮች ሠርዞ የአፍሪካ አንድነትን የሚመሠርተው ‹የአፍሪካና የማላጋሲ አገሮች ድርጅት ቻርተር› ግንቦት 17 ቀን ለግንቦት 18 ቀን አጥቢያ 1955 ዓ.ም ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ላይ በአፍሪካ አዳራሽ ውስጥ ተፈርሟል::"
ተደናቂ ሥራ በወቅቱ በአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ የተገኙት የናይጄሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ታፌዋ ባሌዋ ለአፍሪካ አንድነት እውን መሆን ኢትዮጵያና አፄ ኃይለ ሥላሴ ያደረጉትን ታላቅ አስተዋጽኦ ሲገልጹ ተከታዩን ብለው ነበር::
"መላው የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎችና የመንግሥታት ባለ ሥልጣኖች በአዲስ አበባ ላይ ሊገኙ ለመቻላቸው በግርማዊነትዎ ጥረት ስለሆነ በተለይ ለግርማዊነትዎ እጅግ ከፍ ያለ ክብር የሚያሰጥ ነው:: በዚህ ጉባኤ ላይ አንድነት እንዲገኝ የምናደርገው ጥረት ወደፊት የኢትዮጵያን መናገሻ ከተማ የአዲስ አበባ ስም ደጋግሞ የሚያወሳ ስለሆነ የአዲሲቱ አፍሪካ ታሪክ የግርማዊነትዎን ስም በተቀዳሚው ገጹ ላይ አሳምሮ የሚያኖረው ለመሆኑ ጥርጥር የለበትም::"
የጊኒ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሴኮቱሬም በአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ለአፍሪካ አንድነት ምስረታ ኢትዮጵያ ያደረገችውን ታላቅ አስተዋጽዎ እንዲህ ገልጸውታል፡-
"… ኢትዮጵያዊ ታላቅ ሕዝብ ነው:: ስለ አፍሪካ ነፃነት በጀግንነት የተዋጋ፣ ነፃነትም ቋሚ እንዲሆን፣ ሕዝቦቻችን ያለ ምንም የውጭ መንግሥታት ተቆጣጣሪነትና ጣልቃ ገብነት በተገቢ ሥልጣናቸው እየተመሩ የገዛ ራሳቸውን ዕድል እንዲመሩ ያላቸው ሥልጣን እንዲጠበቅላቸው የደከመ አፍሪካዊ ሕዝብ ነው:: ይህ በንጉሡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ አስተባባሪነትና መሪነት፣ የአፍሪካውያኖች ጉባኤ የተደረገው በኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ስለሆነ፣ አዲስ አበባና ኢትዮጵያ አሁንም የበለጠ ከአፍሪካ ታሪክ ጋር የተሳሰሩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል:: ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት በአንድ አኅጉር ሕዝቦች ፈቃድ ተነሳስቶ በሚመራው የዕድገት ፍላጎትና ሥራ ሁሉ ሳይቋረጥ ስማቸው ተያይዞ የሚኖር ይሆናል …::"
በፍቅር ለይኩን የተባሉ የታሪክ ባለሙያ የአፍሪካ ኅብረት የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓልን አስመልክተው ባሰናዱት ጽሑፍ ድርጅቱን በመመስረት ረገድ አፄ ኃይለ ሥላሴ የነበራቸውን ሚና እንደገለጹት ፣ "‹ኢንሳክሎፒዲያ ብሪታኒካ› ስለ አፄ ኃ/ሥላሴ ባቀረበው አጠር ያለ ጽሑፍ ‹Haile Selassie played a very important role in the establishment of the Organization of African Unity in 1963›› ብሏል:: …
ፍቅር፣ ወንድማማችነት፣ ሰላም፣ አንድነትና ኅብረት ለአፍሪካና ለአፍሪካውያንን ወሳኝና ተቀዳሚ ነገር መሆኑ የተረዱት አፄ ኃይለ ሥላሴ አፍሪካውያን አባቶችን፣ ፖለቲከኞችንና መሪዎችን በማስተባበር የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲቋቋም የላቀ አስተዋጽኦ አድርገዋል::
በወቅቱ ድርጅቱ ሲቋቋም የነበሩ ሰዎች እንደመሠከሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የአፍሪካ መሪዎችን ጉባኤ ስብሰባ በመምራት፣ ይህ የአፍሪካውያን የወንድማማችነት፣ የአንድነትና የፍቅር ሰነድ ሳይፈረም ማንኛችንም ብንሆን ከዚህ ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በጭራሽ አንወጣም በማለት የተኮራረፉና የተለያዩ ፖለቲካዊ ቁርሾ ውስጥ የገቡትን የአፍሪካ አገራት መሪዎችን በማግባባትና በማሸማገል ኅብረቱ እውን እንዲሆን ታላቅ ሚና ተጫውተዋል::
***********************************
ግንቦት 17 ቀን ከተፈፀሙ የታሪክ ክስተቶች መካከል
•1955 ዓ/ም - የ22 ነጻ የአፍሪቃ አገራት መሪዎች አዲስ አበባ ላይ ተሰብስበው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን መሠረቱ።
•1963 ዓ/ም - በአዲስ አበባ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ፤ በከተማው ወጥቶ-እብሶች እና ንብረት ላይ ጉዳት አደረሱ። በዚህም ምክንያት አሥር ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤቶች ተዘጉ።
•1977 ዓ/ም - በባንግላዴሽ ታላቅ አውሎ ነፋስ ተነስቶ ያስከተለው የዝናብ ጎርፍ ፲ ሺ የሚጠጉ ሰዎችን ገደለ።
•1989 ዓ/ም - በሲዬራ ሌዎን፣ በሻምበል ጆኒ ፖል ኮሮማ የተመራ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ፕሬዚደንት አህመድ ቴጃን ካባህን ከሥልጣን አወረደ።
.......................................................
#የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) ምስረታ - 57ኛ ዓመት
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ "የአፍሪካ ኅብረት - AU") የተመሰረተው ከዛሬ 57 ዓመታት በፊት (ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም) ነበር፡፡
እ.አ.አ በ1884/85 ከተካሄደው የበርሊን ጉባዔ (Berlin Conference) በኋላ ኃያላኑ የአውሮፓ አገራት የአፍሪካ አገራትን በመቀራመት የቅኝ ግዛት አደረጓቸው፡፡ አውሮፓውያኑ አገራትም በቀጥተኛ አስተዳደር እንዲሁም በከፋፍሎ መግዛት መርሆች በመታገዝ አፍሪካውያኑን ለባርነት ዳረጓቸው፡፡ የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ለኢንዱስትሪዎቻቸው ግብዓት ወደ አገራቸው አጋዙት፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም አውሮፓዊው ወራሪ የኢጣሊያ ጦር በታላቁ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በተመራው የኢትዮጵያ ጦር ሲሸነፍ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ያሉ አፍሪካውያን ስለነፃነት በርትተው ማለም ጀመሩ፡፡ ታላቁ የዓድዋ ድል የማንቂያ ደወል ሆነላቸው፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ አፍሪካውያን በአንድም ይን በሌላ መንገድ ለነፃነታቸው መዋጋት ጀመሩ፡፡ ጋና የጀመረችው የነፃነት ችቦ በሌሎቹም አገራት አበራ፡፡
የአኅጉሩ መሪዎች በዓለም መድረክ ላይ ለበለጠ ተሰሚነትና የትብብርን ግንባር ማሳየት እንደነበረባቸው በመገንዘብና ገና ነጻ ላልወጡትም ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሉዐላዊነት መታገል ስለነበረባቸው ዓላማቸውን ግብ ለማድረስ የሚያስችል ኅብረት/ማኅበር ለመመስረት አሰቡ፡፡ ማኅበሩን በመመስረት ሂደት ላይም ኢትዮጵያና ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡት አገራት በሁለት የተለያዩ ጎራዎች ተከፈሉ፡፡
አንደኛው ቡድን ራሱን ‹‹የዘመናዊ ተራማጅ›› ብሎ የሚጠራው ‹‹የካዛብላንካ ቡድን›› ሲሆን የቡድኑ አባላት በፖለቲካና በኢኮኖሚ የተዋሃደች የአፍሪካ ፌደሬሽንን የመመስረት ዓላማና የግራ ዘመም ፖለቲካ አቀንቃኝ በሆኑ መሪዎች የተዋቀረ ነበር፡፡ በዚህ ጎራ የተሰለፉት አገራት ጋና፣ አልጄሪያ️፣ ጊኒ
️፣ ሞሮኮ
️፣ ግብጽ
️፣ ማሊ
️ እና ሊቢያ
️ሲሆኑ የቡድኑ መሪም የወቅቱ የጋናው ፕሬዝደንት ክዋሜ ንክሩማህ ነበሩ፡፡
ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ‹‹የሞንሮቪያ ቡድን›› ሲሆን የአፍሪካ አገራት ያለፖለቲካዊ ውህደት በኢኮኖሚያዊና በሕዝብ ለሕዝብ ትስስሮች ተባብረው መዝለቅ እንዳለባቸው ያምናል፡፡ በዚህ ጎራ የነበሩት አገራት ሴኔጋል
️፣ ናይጄሪያ
️፣ ላይቤሪያ
️ እና ኢትዮጵያ
ነበሩ።
በመጨረሻም በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ታላቅ ጥረትና በንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ ሁለቱም ወገኖች አዲስ አበባ ላይ እንዲገናኙ በተደረገው ጥሪ መሠረት ግንቦት 14 ቀን 1955 ዓ.ም የ32 ነጻ አገራት ተወካዮች አዲስ አበባ ላይ ለስብሰባ ተቀመጡ፡፡ ከሦስት ቀናት ውይይት በኋላም፣ ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም አገራቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የስምምነት ውል (OAU Charter) ሲፈርሙ የድርጅቱ ምስረታ እውን ሆነ።
በወቅቱም የአገራቱ መሪዎች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ፣ ጸሐፌትዕዛዝ ክቡር አቶ አክሊሉ ሀብተወልድና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ላቅ ያለ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ ወገኖች ለቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ‹‹የአፍሪካ አባት›› የሚል ስም ሰጥተዋቸዋል፡፡
ምንጭ:- ልዑል ዓምደጽዮን ሠርፀድንግል እና ልዩ ልዩ
**********************************
የአፍሪካ ኅብረት (አንድነት ድርጅት) ምሥረታ የዓይን እማኝ የነበሩት ፊታውራሪ ምን ይላሉ?
መንግሥቱ አበበ__ Saturday, 01 June 2013 *************************************
እንግዶች በመሳፍንትና በመኳንንት ቤቶች አርፈዋል ሁፌት ቧኜ አውሮፕላን ስለማይወዱ በመርከብና በባቡር ነበር የመጡት
የኋላ ማርሽ አስገብተን ወደ ዛሬ 51 ዓመት እንጓዝ፡፡ ብዙዎቹ
የአፍሪካ አገራት ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡበት ጊዜ ነበር፡፡ ነፃ ያልወጡም አገራት ነበሩ፡፡ አፍሪካ ተባብራ
ችግሮቿን እንድትፈታ፣ ነፃነቷንም እንድታስከብርና ነፃ ያልወጡ አገራትን እንድትደግፍ፣ በአንድነት የምንትቀሳቀስበት
ኅብረት ያስፈልጋታል በማለት የፓን አፍሪካኒዝም የሚቀነቀንበት ወቅት ነበር፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ ሐሳቡ ተቀባይነት
አገኘና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሠረት ነፃ የአፍሪካ መንግሥታት ተስማሙ፡፡
ነገር ግን ማን አስተባባሮ ድርጅቱ ይመሥረት? ቻርተሩንስ ማን ያዘጋጀው? የድርጅቱ መቀመጫስ የት ይሁን? … የሚሉት ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች ነበሩ።
በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ እኔ ኃላፊነቱን እወጣለሁ አለች፡፡ ይኼኔ
ከየአካባቢው ተቃውሞ ተነሳ፡፡ “ኢትዮጵያ መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ሆቴል፤ መንገድ፤ ንፅህና፣ … የላትም፡፡ ካይሮ፣
ሌጐስ፣ ናይሮቢ፣ … እያሉ እንዴት አዲስ አበባ መቀመጫ ትሆናለች? በማለት የተቃወሙ ፖለቲከኞች ብዙ ናቸው፡፡ ነገር
ግን ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በነበራቸው ብልህ ፖለቲካዊ ብስለት፣ ከፍተኛ ጥረትና የማሳመን ችሎታ፣ አዲስ አበባ
ከ51 ዓመት በፊት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የአፍሪካን አንድነት ድርጅት ምሥረታ ጉባኤ እንድታዘጋጅ ተወሰነ፡፡
ከውሳኔው በኋላ ጃንሆይ የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውን ሰብስበው፣ ጉዳዩን ካስረዱ በኋላ “ጊዜ የለንም፤ ያሉን 12 ወራት
ብቻ ናቸው። የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ፣ መሪዎች ሲመጡ የሚያርፉበትና የሚሰበሰቡበት አዳራሽ የለም። ጎበዝ! እንዴት
ይህን ኃላፊነት እንወጣ? በማለት ጠየቁ፡፡ ለዝግጅት የተሰጠው ጊዜ በጣም አጭር ነው፡፡
ለምን ስብሰባው ለሌላ ጊዜ አይተላለፍም? በማለት ሐሳብ ያቀረቡ
ሚኒስትሮች ነበሩ፡፡ ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም (በወቅቱ ደጃዝማች) “ዕድሉ ሊያመልጠን አይገባም፡፡ ገንዘቡ
ከተፈቀደልኝ በተባለው ጊዜ ውስጥ (እንዲያውም ከዚያ ቀደም ብዬ በዘጠኝና በአስር ወር) ሥራውን አጠናቅቄ
አስረክባለሁ” በማለት ቃል ገቡ፡፡ ንጉሡም፣ ልዑል ራስ መንገሻ የተግባር ሰው መሆናቸውን ስለሚያውቁ “መንገሻ
አደርገዋለሁ ካለ ያደርገዋል” በማለት በሐሳባቸው ተስማሙ፡፡ “ሥራው ወዲያውኑ ተጀምሮ ሌት ተቀን እየተሠራ የቦሌ
ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ፣ የአፍሪካ አዳራሽና የግዮን ሆቴል ተሠርተው ስላለቁ፣ ጉድ ተባለ፡፡ ልዑል ራስ
መንገሻም “ልጄ ተባረክ” በመባል በንጉሡ ተመሰገኑ ያሉት በወቅቱ የፓርላማ አባል የነበሩት ፊታውራሪ አበበ ሥዩም
ደስታ ናቸው፡፡
ፊታውራሪ አበበ ሥዩም የዛሬ 50 ዓመት የአፍሪካ አንድነት
ድርጅት ሲመሠረት በፓርላማ ሕግ መምሪያ ም/ቤት የተንቤን ሕዝብ እንደራሴና የበጀት ኮሚቴ ሊቀመንበር ነበሩ፡፡ ስለ
አፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ፣ ስለ እንግዶቹ አቀባበልና ዝግጅት፣ … የሚናገሩት አላቸው። ዛሬ ፊታውራሪ አበበ
የ83 ዓመት አዛውንት ናቸው። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በዝርዝር ሲናገሩ የማስታወስ ችሎታቸው ይደንቃል፡፡ ከ50
ዓመት በፊት የነበረውን ነገር ከዓመትና ከሁለት ዓመት በፊት እንደተፈፀመ ታሪክ ነው የሚያንበለብሉት፡፡ የሕይወት
ታሪካቸውንም ጽፈው “ዝክረ ሕይወት” በሚል ርዕስ አሳትመዋል፡፡
ፊታውራሪ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሠረተው እንዴት
እንደነበር ያጫውቱናል፤ እንከታተላቸው፡፡ በዚያን ጊዜ አፄ ኃይለ ሥላሴ አፍሪካን አንድ የማድረግ ሕልም ነበራቸውና
ሕልማቸው ተሳካ። በንጉሡ ዙሪያ የተሰባሰቡት ሚኒስትሮች በሳል ዲፕሎማቶች ነበሩ፡፡ ካቢኔው የሚመራው በጸሐፌ ትዕዛዝ
አክሊሉ ሀ/ወልድ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ክቡር ከተማ ይፍሩ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ ክቡር ዶ/ር ተስፋዬ ገ/እግዚ
የማስታወቂያ ሚ/ር፣ ክቡር ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ፤ ክቡር አቶ ሰይፉ ማኅተመ ሥላሴ፣ እንዲሁም አፈ-ንጉሥ ተሾመ …
የሚባሉ ሚኒስትሮች ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገሮች እየሄዱ ሲያስተባብሩና ሲያግባቡ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ብዙ
ተደማጭነት የነበራቸው የግብፁ መሪ ጋማል አብዱልናስር ነበሩ፡፡ እሳቸውን ለማግባባት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡
ይኼው የማግባባት ጥረት ተሳክቶ ስብሰባው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ሲወሰን እንግዶቹ መጥተው የሚሰበሰቡበት አዳራሽ፣
የሚያርፉበት ሆቴል፣ የለም፡፡ የተሰጠን ጊዜ ደግሞ አንድ ዓመት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ካላዘጋጀን ዕድሉ ለሌላ
ይተላለፋልና ምን ይደረግ? ተባለ።
የሲዳሞ ጠቅላይ ገዥ የነበሩት ክቡር ደጃዝማች መንገሻ ሥዩም
የሥራና መገናኛ ሚኒስትር ሆነው ስለተሾሙ፣ “ገንዘብ ከተሰጠኝ በአንድ ዓመት ውስጥ አይደለም፤ በዘጠኝ ወር ግፋ ቢል
በአስር ወር ጨርሼ አስረክባለሁ” በማለት ለጃንሆይ ቃል ገቡ፡፡ “መንገሻ አያደርግም አይባልም፤ ይሠራል” ተባለ፡፡
የገንዘብ ሚ/ር የነበሩት እነ ክቡር አቶ ይልማ ዴሬሳና አንዳንድ ሚኒስትሮች “ይኼ እንዴት ይሆናል?” በማለት
ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ ሥራው ተጀምሮ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፍያና የአፍሪካ አዳራሽ የተሠራው ያኔ
ነው፡፡ 24 ሰዓት ሌት ተቀን በሦስት ፈረቃ ሲሠራ 11 ሰዎች ሞተውበታል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጽ/ቤት
የድሮው ረዥሙ ሕንፃ ለአባዲና ፖሊስ ኮሌጅ የተሰጠ ሕንፃ ነበር፡፡ ጽ/ቤቱ የት ይሁን ተብሎ ሲፈለግ የድሮው ዓለም
በቃኝ (ወህኒ ቤት) የነበረበት አጠገብ ያለው ሕንፃ ተመረጠ፡፡ ሌሎች ዙሪያውን ያሉት ከዚያ በኋላ የተሠሩ ናቸው፡፡
በዚያን ጊዜ የነበሩት ግዮን፣ ኢትዮጵያ፣ ራስ፣ ጣይቱ፣ ሒልተንና
ገነት ሆቴሎች ብቻ ነበሩ፡፡ መሪዎቹ ሲመጡ የት ይረፉ ሲባል፣ በግዮን ሆቴል 32 መሪዎች የሚይዝ ቅጥያ ሁለት ፎቅ
የተሠራው ያኔ ነው፡፡ ስብሰባው የተካሄደው አሁን ብሔራዊ ቤተመንግስት (ያኔ ኢዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት) ተብሎ
በሚጠራው ነበር፡፡ አዲስ አበባ አሸብርቃለች፡፡ በተለይ ከፒያሳ ማዘጋጃ ቤት እስከ ለገሃር ባቡር ጣቢያ ያለው
ቸርችል ጐዳና፣ ከመስቀል አደባባይ እስከ ስድስት ኪሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (ያኔ ገነተ - ልዑል ቤተመንግሥት)
ድረስ በኢትዮጵያና በተለያዩ አገራት ባንዲራና መብራት አጊጦ ነበር፡፡ ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ በኋላ መሪዎቹ የሚመጡበት
ቀን ተቆረጠና ግንቦት 1955 ዓ.ም እንዲሆን ተወሰነ፡፡ የዝግጅቱ ዋና ተዋናይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ
ከተማ ይፍሩ ነበሩ።
በወቅቱ ኃይለኛ ዝናብ ስለነበር ጃንሆይ ቦሌ ዓለም አቀፍ
አውሮፕላን ጣቢያ እየተገኙ ሁሉንም መሪዎች የተቀበሉት በዣንጥላ ነው - ዝናብ እየዘነበባቸው፡፡ ቀይ ምንጣፍ
ተነጥፎና ፖሊስ ባንድ ማርሽ እያሰማ፣ ለእያንዳንዱ መሪ 21 ጊዜ መድፍ እየተተኮሰ ነበር የተቀበሏቸው፡፡ በዚያን
ጊዜ ትዝ የሚለኝ፣ የኮትዲቫር (ያኔ አይቮሪኮስት) መሪ የነበሩት ሁፌት ቧኜ በፍፁም በአውሮፕላን መጓዝ አይወዱም፡፡
ስለዚህ በመርከብ እስከ ጅቡቲ መጥተው ከዚያ ደግሞ በልዩ ባቡር ግንቦት 16 ቀን አዲስ አበባ ሲገቡ ደማቅ
አቀባበል ተደርጐላቸዋል፡፡ በተወካይ የተሳተፉ አገሮች ቢኖሩም ኢትዮጵያን ጨምሮ 32 አገራት በመሪዎቻቸው አማካኝነት
በስብሰባው ላይ ተሳትፈዋል፡፡ መሪዎቹና የልዑካን ቡድኑ አባላት አዲስ አበባ መግባት የጀመሩት ከግንቦት 13 ቀን
ጀምሮ ሲሆን ተጠቃለው የገቡት ግንቦት 15 ቀን ነበር፡፡ ግንቦት 16 ቀን ምሽት ጃንሆይ በታላቁ ቤተመንግሥት በአፄ
ምኒልክ አዳራሽ ለመሪዎቹ ክብር፤ ለልዑካን ቡድን አባላት፣ ለዲፕሎማቶች፣ ለጋዜጠኞች፣ በሀገር ውስጥ ላሉ
መሳፍንት፣ ጳጳሳት፣ ሚኒስትሮች፣ መኮንኖች፣ ለታዋቂ ነጋዴዎችና ግለሰቦች በአጠቃላይ ከሦስት ሺም አምስት መቶ በላይ
ለሚሆኑ እንግዶች ታላቅ የራት ግብዣ አደረጉ፡፡
ተጋባዦቹ ወደ አዳራሹ ከመግባታቸው በፊት በቤተመንግሥቱ ፊት
ለፊት ባለው ሜዳ ላይ የተለያዩ ቀለማት ያላቸው ሪችት ተተኩሷል። አዳራሹ በአገር ባህል ቁሳቁሶች፣ የኢትዮጵያን
ጥንታዊ ሥልጣኔ በሚያሳዩና በታዋቂ አርቲስቶች በተሣሉ ሥዕሎችና በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓለማ አሸብርቋል፡፡ የክብር
ዘበኛ፣ የጦር ሠራዊትና የፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃ ቦንቦችም ልዩ ልዩ ጥዑመ ዜማዎችን በማቅረብ እንግዶቹን ሲያስደስቱ
አምሽተዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካዊቷ ማሪያ ማኬባ “የጥንቱ ትዝ አለኝ” የሚለውን የዶ/ር ጥላሁን ገሠሠን ዜማ
ስታንቆረቁር ጭብጨባው ቀለጠ፡፡ ወደ አዳራሹ የተገባው ሁለት ለሁለት እጅ ተያይዞ ነበር፡፡ በመጀመሪያ የገቡት
የኢትዮጵያ ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የግብፁ ፕሬዚዳንት ጋማል አብዱልናስር ነበሩ፡፡ ጃንሆይ አጭር እንደ
መሆናቸው መጠን፣ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲገቡ ጭብጨባው ቀለጠ፡፡ በጣም ረዥም ከሚባሉት ጋማል አብድልናስር ሌሎችም
በፊደል ተራቸው መሠረት ሁሉም መሪዎች እንዲገቡ ተደረገ፡፡
እራት ከተበላና ከተጠጣ በኋላ ክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ
ሀብተወልድ ከፈረንሳዊት ሚስታቸው ጋር ወደ መድረክ በመውጣት ዳንስ አስጀምረዋል። በማግሥቱ ግንቦት 17 ቀን 1955
ዓ.ም 32ቱ መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካን አንድነት ድርጅት ቻርተር በፊርማቸው አፀደቁ፡፡ ቻርተሩ ለም/ቤቱ
ቀርቦ በሙሉ ድምፅ አፀደቅነው። ቻርተሩ ለፓርላማ የቀረበው፣ ዓለም አቀፍ ውሎችንና ስምምነቶችን ም/ቤቱ ማወቅ
ስላለበትና በቻርተሩ አንቀጽ 23 መሠረት አባል አገሮች ለድርጅቱ በየዓመቱ የሚከፍሉትን መዋጮ በበጀት ተይዞ መፅጸቅ
ስላለበት ነው፡፡ ክቡር ፊታውራሪ አበበ ሥዩም ግን ጥቂት ቅሬታ አላቸው፡፡
“ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እንግሊዝኛ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ በመጋል
የተከፋፈሉትን የአፍሪካ መንግሥታት አስተባብረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር እንዲፈረም ያደረጉ ታላቅ መሪ
ነበሩ፡፡ አሁን በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ፊትለፊት የጋናው መሪ የክዋሜ ንኩሩማ ሐውልት ብቻ እንዲቆም በመደረጉ
ቅሬታ አለኝ፡፡ ወደፊትም ቢሆን ለጃንሆይና ለመሥራች መሪዎች መታሰሲያ ሐውልት ይቆምላቸዋል የሚል እምነት አለኝ”
ብለዋል፡፡ ሌላው ቅሬታቸው ደግሞ የአፍሪካ አንድነት ሲመሠረት የነበሩ ጥቂት የዓይን እማኞች ስላሉ እነሱ በአፍሪካ
ኅብረት ምሥረታ 50ኛ ኢዮቤልዩ በዓል ላይ እንዲገኙ ያለመጋበዛቸው አሳዝኖአቸዋል፡፡