ከደራሲያን ዓምባ

Monday, December 16, 2013

የግጥም ጥግ

ልረሣሽ እየጣርኩ ነው
--------------------
ልረሣሽ እየጣርኩ ነው
በጣራው ላይ ሲረማመድ፣የዝናቡ ልዝብ ኮቴ
መጋረጃው ሲውለበለብ፣ሰንደቅ ሆኖ ለመስኮቴ
ዋርካው፣ በቅጠል ጥዋ
ውኃ ሲያቁር ፣ከህዋ
የምድርን ጉሮሮ ሊያርስ
መሬት ፣ፍጥረትን ስትጸንስ
በዚህ ሁሉ ጸጋ መሀል ፣ያንችን መሄድ ስተምነው
ምንም ነው፣ኢምንት ነው
ልረሣሽ እየጣርሁ ነው፡፡
መጣ፣ መጣ ፣መጣ፣ የዝናቡ ኮቴ አየለ
ክረምት የፍጥረት መሲሕ፣ በቀጠሮው ከተፍ አለ፡፡
ስስ የጉም አይነርግብ፣ውብ ገጽሽን ሸፋፈነው
የርጥብ አፈር፣ርጥብ ሽታ ፣ውብ ሽቶሽን አዳፈነው
ልረሣሽ እየጣርኩ ነው፡፡
የዝናቡ ኮቴ ይደምቃል
እንደ ብስል ሾላ ፍሬ፣አሮጌው ሰማይ ይወድቃል
አዲስ ሰማይ ይነቃል
አዲስ ጅረት ይፈልቃል
እንኳንስ የእግርሽ ኮቴ፣ ጎዳናሽም ታጥቦ ያልቃል፡፡
ልረሳሽ እየጣርኩ ነው፡፡
---------------------------

በእውቀቱ ሥዩም ፣ክረምት፣ 2005

No comments:

Post a Comment