ኦሎምፒክና የኢትዮጵያ ወርቃማ ኦሎምፒያኖች_ግሩም ሠይፉ( አዲስ አድማስ )
በ1896
እኤአ ላይ የግሪኳ አቴንስ ከተማ ካስተናገደችው የመጀመርያው ኦሎምፒድ አንስቶ ባለፉት 125 ዓመታት ውስጥ በተካሄዱት 31 ኦሎምፒያዶች ኢትዮጵያ በ13 ተሳትፋለች፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ ሁሉንም ሜዳልያዎችን የሰበሰበችው በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ ሲሆን በከፍተኛ የውጤት ታሪካቸው ከሚጠቀሱ 8 አገራት አንዷ ናት። አፍሪካን በመወከል ደግሞ ከኬንያ ቀጥሎ ከፍተኛውን ስኬት አስመዝግባለች፡፡
የጃፓኗ ቶኪዮ ከምታስተናግደው የ2020ው 32ኛው ኦሎምፒያድ በፊት ኢትዮጵያ በተካፈለችባቸው 12 ኦሎምፒያዶች 227
ኦሎምፒያኖች (168 ወንድ እና 59 ሴት) ተሳትፈዋል፡፡ ከእነሱም መካከል 32 ኦሎምፒያኖች ከ1 እስከ 3 ባሉ ደረጃዎች ስኬታማ በመሆን 54 ሜዳልያዎችን (22 የወርቅ፤ 11 የብርና 21 የነሐስ) ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል፡፡
ከሜዳልያዎቹ ስብስብ 22 የወርቅ ሜዳልያዎችን ለኢትዮጵያ ያጎናፀፉት 13 ኦሎምፒያኖች ናቸው፡፡ በተረፈ 11 የብር ሜዳልያዎች በ10 እንዲሁም 21 የነሐስ ሜዳልያዎች በ18 የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ተገኝተዋል፡፡
የወርቅ ሜዳልያ ክብርና ዋጋ
ኦሎምፒክ የዓለም አገራትና ህዝቦቻቸውን በአንድ መንፈስ የሚያስተባብር መድረክ ነው፡፡ በስፖርት መድረኩ በድህነት የተጎሳቆሉ፤ በበቂ የስፖርት መሰረተ ልማት ዝግጅታቸውን ያላከናወኑ፤ በየአገራቸው ባሉ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የተረበሹ፤ በጦርነት እና በኢኮኖሚ ቀውስ የሚገኙ አገሮቻቸውን የወከሉ ኦሎምፒያኖች ሲሳተፉ ሁሉም አንድ ዓላማ ይኖራቸዋል፡፡ ይህ ዓላማ በሜዳልያ ክብር አገራቸውን ማኩራትና ሰንደቅ አለማቸውን ማውለብለብ ነው፡፡ የኦሎምፒክ የሜዳልያ ክብር መጎናፀፍ ደግሞ የየትኛውም የዓለም ስፖርተኛ ህልም እንደሆነ ይታወቃል።
በኦሎምፒክ ታሪክ ሙሉ ለሙሉ ከወርቅ የተሰሩ ሜዳልያዎች ለአሸናፊዎች ለመጨረሻ ግዜ የተሰጠው በ1912 እኤአ ላይ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች ገፅታ በአዘጋጅ አገራት የዲዛይን ፍላጎት እንዲሆን ቢፈቀድም ሜዳልያዎኙ የሚሰሩበት ማእድን በኦሎምፒክ ቻርተር መሰረት የሚዘጋጅ ይሆናል፡፡ በኦሎምፒክ ለ1ኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የሚሸለሙት የወርቅና የብር ሜዳልያዎች 92.5 በመቶ የሚሰሩት ከብር እንዲሁም 6 በመቶ ከመዳብ ነው፡፡
ለ3ኛ ደረጃ ተሸላሚዎች የሚሰጡት የነሐስ ሜዳልያዎ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ከነሐስ የተሰሩ ናቸው፡፡ የወርቅ ሜዳሊያዎች በ6 ግራም ወርቅ መለበጣቸው ግድ ነው፡፡ ሁሉም ሜዳልያዎች ውፍረታቸው 3ሚሜ ዲያሜትራቸው 60 ሚሜ መሆን አለበት፡፡ አንድ የወርቅ ሜዳልያን አቅልጦ ይሸጥ ቢባል ከ706 ዶላር ጀምሮ ዋጋ ይኖረዋል፡፡
በ30ኛው ኦሎምፒያድ 4700 ሜዳልያዎች ለተሸላሚዎች የተዘጋጁ ሲሆን በሜዳልያዎቹ ስራ 802
ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡ ለኦሎምፒክ ሻምፒዮኖች የቀረቡ 302 የወርቅ ሜዳልያዎች 400 ግራም ይመዝናሉ፡፡
አበበ ቢቂላ
ትውልዱ ደብረብርሃን አቅራቢያ ጃቶ በተባለች ቦታ ነበር፡፡ በ1960 እኤአ ከ83 አገራት የተውጣጡ ከ5ሺ በላይ አትሌቶች በተካፈሉበት የሮም ኦሎምፒክ ላይ ለአፍሪካ እና ለኢትዮጰያ በኦሎምፒክ ታሪክ የመጀመርያውን ሜዳሊያ በማስገኘት ፈርቀዳጅ ታሪክ ሰርቷል፡፡ በባዶ እግሩ ሮጦ ታላቁን የኦሎምፒክ ማራቶን በአንደኝነት ከማሸነፉም በተጨማሪ፤ 2፡16፡2 በሆነ ሰአት አዲስ የአለም ሪከርድ አስመዝግቦም ነበር፡፡
ከ4 ዓመታት በኋላ በ1964 እኤአ የኦሎምፒክ አዘጋጅ የጃፓኗ ከተማ ቶኪዮ ነበረች፡፡ የቶኪዮ ኦሎምፒክ 6 ሳምንታት ሲቀሩት፤ አበበ ቢቂላ የቀዶ ህክምና ተደርገለት። በፍጥነት እንደሚያገግም ተስፋ በማድረግ፤ የኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ መካተቱ አልቀረም፡፡
ከቀዶ ጥገናው ሙሉ ለሙሉ ሳያገግም ማራቶኑን በመሮጥ በድጋሚ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ሆኖ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ አስመዘገበ፡፡ ድሉ ለኢትዮጵያ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ብቻ አልነበረም በድጋሚ የዓለም ማራቶንን ሪከርድ አሻሽሏል - 2፡12፡11 በሆነ ሰአት በመግባት፡፡ በሁለት ኦሎምፒኮች በማራቶን አከታትሎ በማሸነፍ፤ በሁለቱም ሪከርድ በማስመዝገብ እና ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች በማግኘት፤ አበበ ብቸኛው ኦሎምፒያን ነው፡፡
ማሞ ወልዴ
ማሞ ወልዴ የተወለደው ከአዲስ አበባ 60 ኪ.ሜ. ርቀት ድሪጂሌ በተባለች የገጠር ከተማ ተወልዷል፡፡ ከአበበ ቢቂላ በኋላ የኢትዮጵያ ብቸኛ ተስፋ አንተ ብቻ ነህ ተብሎ በ1968 እኤአ ላይ የሜክሲኮን ኦሎምፒክ የተሳተፈ ነበር፡፡
በሜክሲኮ ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር ውድድር ኢትዮጲያን ወክሎ እንዲሮጥ የተመረጠው አትሌት ማሞ፤ ከከባድ ተቀናቃኞች ጋር ተፎካክሮ በአጨራረስ ብልሃት ስላልነበረው ውድድሩን በሁለተኛነት ጨርሶ፤ በኦሎምፒክ ተሳትፎው ለራሱ የመጀመሪያውን የብር ሜዳሊያ ተጎናፅፏል፡፡
ማሞ ወልዴ ከ10ሺ ሜትር የብር ሜዳልያው ድል በኋላ ግን ከዚህ አድካሚ ውድድር እፎይ የሚልበት ጊዜ አልነበረውም፤ በማራቶን እንዲወዳደርና የአበበን የድል ታሪክ መድገም እንደሚኖርበት የኢትዮጲያን ክብር የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት በወቅቱ አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ተነገረው፡፡ በ10ሺ ሜትር ተወዳድሮ የብር ሜዳልያ ባገኘ በማግስቱ ነበር ማራቶኑ፡፡ ለመፎካከር ከተሰለፉት የ44 አገራት አትሌቶች ውስጥ፤ ከኢትዮጲያ አበበ ቢቂላ፤ ማሞ ወልዴና ደሞሴ ነበሩበት፡፡ 15 ኪሎ ሜትር ያህል ሲመራ የቆየው የማራቶን ጀግና አበበ ቢቂላ በህመም ውድድሩን አቋርጦ ለመውጣት ተገደደ፡፡ የስፖርት አፍቃሪዎች ልብ በሃዘን ተሰበረ፡፡ ጀግና ጀግናን እንደሚተካ የተዘነጋ ይመስላል፡፡
በአበበ ቢቂላ በተከታታይ ሁለት ኦሎምፒክ ድል የተገኘበትን የማራቶን ውድድር ማሞ ወልዴ በድጋሚ አሸንፎ ታሪክ በመስራት የኢትዮጵያን ክብር አስጠበቀ፡፡ በ35 አመቱ በአንድ ኦሎምፒክ ሁለት ሜዳሊያ ያጠለቀው ማሞ፤ ጀግንነቱ ለኢትዮጵያውን ኩራትንና ደስታን አጎናፀፈ፡፡ ከዚህ ስኬቱ በኃላ አትሌት ማሞ ወልዴ በ1965 በጀርመን ሙኒክ በተካሄደው ኦሎምፒክ በ10 ሺ ሜትር ሶስተኛ በመውጣት የነሃስ ሜዳሊያ አግኝቷል፡፡
ምሩፅ ይፍጠር
ምሩፅ ይፍጠር በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ በአዲግራት ተወለደ፡፡ በወጣትነቱ ከጋሪ ነጂ ጀምሮ፤ በተለያዩ ፋብሪካዎች ተቀጥሮ ሰርቷል፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ በኦሎምፒክ የተሳተፈው የጀርመኗ ከተማ ሙኒክ ባስተናገደችው ኦሎምፒክ ሲሆን በአስር ሺ ሜትር ሶስተኛ ወጥቶ የነሃስ ሜዳሊያ አግኝቷል፡፡በ1980 እኤአ የራሽያ ዋና ከተማ ያስተናገደችው የሞስኮ ኦሎምፒክ የምሩፅ ነበር፤ አለምን ጉድ ያሰኘበት፡፡ በሞስኮ ኦሎምፒክ በ10ሺና በ5ሺ ሜትር ኢትዮጵያን በመወከል የተወዳደረው ምሩፅ፤ በፍፁም ብቃት በሁለቱም በማሸነፍ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ያገኘ ሲሆን በሁለቱም ርቀቶች በኦሎምፒክ ያሸነፈ የመጀመርያው አትሌት ነበር፡፡
ደራርቱ ቱሉ
ደራርቱ ቱሉ ትውልዷ በአርሲዋ ትንሽ ከተማ በቆጂ ነው፡፡ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ለኢትዮጲያዊያን ብቻ ሳይሆነ ለአፍሪካዊያን እንስት አትሌቶች ፈርቀዳጅ የሆኑ ድሎችን በአለም አቀፍ ደረጃ ታሪክ ሠርታለች፡፡
በተለይ ደግሞ የሚጠቀሰው በ1992 እ.ኤ.አ በስፔን ባርሴሎና በተከናወነው ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ መጎናፀፏ ነው፡፡ ይህ ድል በአፍሪካ የኦሎምፒክ ታሪክ በረጅም ርቀት በሴቶች የመጀመርያው ድል ነበር። በ2000 እኤአ በአውስትራያ በተካሄደው የሲድኒ ኦሎምፒክም ደራርቱ በ10ሺ ሜትር ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ለመጎናፀፍ በቅታለች፡፡ በተጨማሪም በ2004 እኤአ በአቴንስ ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ አግኝታለች፡፡
ፋጡማ ሮባ
አትሌት ፋጡማ ሮባ የተወለደችው በአርሲዋ በቆጂ ከተማ ነው፡፡ በ1996 እ.ኤ.አ ላይ የአሜሪካዋ አትላንታ ባስተናገደችው ኦሎምፒክ በሴቶች ማራቶን በታሪክ የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮ‹ያ ለመጎናፀፍ በቅታለች፡፡
ኃይሌ ገብረስላሴ
ትውልዱ በአርሲዋ ትንሽ ከተማ በቆጂ ነው። ኃይሌ ገ/ሥላሴ ለመጀመርያ ጊዜ በ1996 እ.ኤ.አ ላይ በአትላንታ ኦሎምፒክ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በመሳተፍ በ10ሺ ሜትር ውድድር ተካፍሎ በአስደናቂ የአጨራረስ ብቃት በማሸነፍ የመጀመሪያውን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ አግኝቷል፡፡
በ2000 እ.ኤ.አ ላይ የ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጨረሻ ኦሎምፒክ በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ ሲካሄድ ኃይሌ በ10ሺ ሜትር በተካሄደው ውድድር ከቅርብ ተቀናቃኙ የኬንያው አትሌት ፖልቴርጋት ጋር ያደረገው እልህ አጨራረስ ትንቅንቅ በ0.09 ሰኮንድ ልዩነት በመቅደም 2ኛውን የወርቅ ሜዳልያ ለመጎናፀፍ በቅቷል፡፡
ሚሊዩን ወልዴ
አትሌት ሚሊዩን ወልዴ ትውልዱ በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ በ2000 ኤ.ኤ.አ በአውሰትራሊያ ሲዲኒ በተከናውነው 27ኛው ኦሎምፒያድ አዲስ እና ፈርቀዳጅ ታሪክ ለኢትዮጰያ አትሌቲክስ በማስመዝገብ ተሳክቶለታል፡፡
በወቅቱ የ22 ዓመት ወጣት የነበረው አትሌት ሚልዩን በተካፈለበት የ5ሺ ሜትር ውድድር አሸንፎ በርቀቱ የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳልያ ሲያስመዘግብ በመጨረሻዎቹ 200 ሜትሮች ድንቅ የአጨራረስ ብቃት በማሳየት ነበር፡፡
ገዛሐኝ አበራ
የአትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው አርሲ የተወለደው ገዛሐኝ በኢትዮጲያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ማሞ ወልዴ ካስመዘገበው የወርቅ ሜዳልያ በኋላ በማራቶን ሊያሽንፍ የበቃ አትሌት ነው፡፡
በ2000 እኤአ በሲዲኒ ኦሎምፒክ ላይ ገዛሐኝ በማራቶን የወርቅ ሜዳልያውን ሊጎናፀፍ የበቃ ሲሆን በ22 ዓመቱ በኦሎምፒክ ታሪክ የመጀመሪያው ወጣት የማራቶን ባለድል ለመሆን ፈርቀዳጅ ታሪክ ለመስራት የቻለበት ነበር፡፡
ቀነኒሳ በቀለ
ትውልዱ በአርሲ በቆጂ የሆነው ቀነኒሳ በ10ሺ ሜትር ሶስት ጊዜ ፤ በ5ሺ ሜትር አንድ ጊዜ በአጠቃላይ 4 የኦሎምፒክ የወርቅ እንዲሁም በሺ ሜትር 1 የብር ሜዳልያዎችን በተጨማሪ በማስመዝገብ በወንድ አትሌቶች በኦሎምፒክ መድረክ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበ ነው፡፡
ቀነኒሳ በኦሎምፒክ መድረክ የመጀመርያ ተሳትፎው በ28ኛው ኦሎምፒያድ በግሪክ አቴንስ ላይ የነበረ ሲሆን፤ አዲስ የኦሎምፒክ ክብረወሰን በማስመዘገብ ለራሱ የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳልያ ለማጥለቅ በቃ፡፡ በወንዶች 5ኺ ሜትር ደግሞ የብር ሜዳልያ ነበረው፡፡
ከ4 ዓመታት በኋላ የቻይናዋ ዋና ከተማ ባስተናገደችው 29ኛው ኦሎፒያድ በድጋሚ አዲስ የኦሎምፒክ ክብረወሰን በማስመዝገብ በ10ሺ ሜትር የሻምፒዮናነት ክብሩን አስጠብቆ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ሊያገኝ የበቃ ሲሆን በ5ሺ ሜትርም ድል በማድረግ ሌላ የወርቅ ሜዳልያውንም ተጎናፅፏል፡፡ በ1980 እኤአ ላይ በሞስኮ ኦሎምፒክ አትሌት ምሩፅ ይፍጠር በ5ሺና በ10ሺ ድርብ ድል በማግኘት ያስመዘገበውን ታሪክ በመድገምም አስደናቂ ታሪክ ሊሰራ በቅቷል፡፡ በ2012 እኤአ ለየእንግሊዟ ከተማ ለንደን ባስተናገደችው 30ኛው ኦሎምፒያድ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ10ሺ ሜትር ለሶስትኛ ጊዜ የወርቅ ሜዳልያ በመጎናፀፍ በታሪክ የመጀመርያው አትሌት ሆኖ አዲስ ታሪክም ሊያስመዘግብ በቅቷል፡፡
ጥሩነሸ ዲባባ
ትውልዷ አርሲ ውስጥ በቆጂ አጠገብ በምትገኝ ጨፌ በተባለች ስፍራ ነው፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ በኢትዮጲያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በሁለቱም ፆታዎች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛው የውጤት ክብረወሰን በማስመዝገብ በግንባርቀደምነት ትጠቀሳለች፡፡
ጥሩነሽ ዲባባ በተሳተፈችባቸው 3 የኦሎምፒክ መድረኮች በ2004 እኤአ በአቴንስ፤ በ2008 እኤአ በቤጂንግ እንዲሁም በ2012 እኤአ በለንደን 5 (3 የወርቅና ሁለት የነሐስ) ሜዳልያዎችን በማግኘት ከረጅም ርቀት አትሌቶች በአንደኛ ደረጃ የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን ይዛለች፡፡
እነዚህ ሜዳልያዎች ላይ በ5ሺ ሜትር ነሐስ በ2004 አቴንስ ላይ፤ በ10ሺ እና በ5ሺ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች በ2008 ቤጂንግ ላይ፤ እንዲሁም በ10ሺ ወርቅ እና በ5ሺ ነሐስ ሜዳልያዎች በ2012 ለንደን ላይ ያገኘቻቸው ናቸው።
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ 5 የወርቅ እና ሜዳልያዎች በመሰብሰብ በረጅም ርቀት ብቸኛውን የውጤት ክብረወሰን እንደያዘች ነው፡፡
መሰረት ደፋር
አትሌት መሰረት ደፋር ትውልዷ በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ በኦሎምፒክ የተሳትፎ ታሪክ በ5ሺ ሜትር ሴቶች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ያስመዘገበች ምርጥ አትሌት ናት፡፡
የመጀመርያ የወርቅ ሜዳልያዋን ያስመዘገበችው በ2004 እኤአ በአቴንስ ኦሎምፒክ ሲሆን በተመሳሳይ በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ በ2008 ቤጂንግ ላይ አስመዝግባ ፤ በ2012 ለንደን ደግሞ በኦሎምፒክ የተሳትፎ ታሪኳ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ በ5ሺ ሜትር አስመዝግባለች፡፡
ቲኪ ገላና
በ30ኛው የለንደን ኦሎምፒያድ በ2012 አትሌት ፋጡማ ሮባ ከ16 ዓመታት በፊት በአትላንታ ኦሎምፒክ ያስመዘገበችውን ታሪክ በመድገም ለሁለተኛ ጊዜ በሴቶች ሁለተኛውን የማራቶን የወርቅ ሜዳልያ የተጎናኘፈች ናት፡፡
በለንደን ኦሎምፒክ ቲኪ ገላና በማራቶን አሸንፋ የወርቅ ሜዳልያ የተጎናፀፈችው አዲስ የኦሎምፒክ ክብረወሰን በማስመዝገብ ጭምር ነው፡፡
አልማዝ አያና
ትውልዷ በቤንሻንጉል ጉምዝ ነው፡፡በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሮ በተካሄደው 31ኛው ኦሎምፒያድ በ10ሺ ሜትር ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ወስዳለች፡፡ ያስመዘገበችው ሰዓት 29፡17.45 አዲስ የዓለም ሪከርድ ነው፡፡
ለ23 ዓመታት በቻይናዊ አትሌት ተይዞ የነበረውን ሰዓት በ14 ሰከንዶች ያሻሻለ ነው፡፡ በዚያው 31ኛው ኦሎምፒያድ ላይ በተጨማሪ በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ አግኝታለች፡፡
በ55 ሜዳልያዎች ከዓለም 41
በወንዶች
12 የወርቅ፣ 6 የብርና 12 የነሀስ ሜዳሊያዎች፣ 4ኛ ደረጃዎች 9፣ 5ኛ ደረጃዎች 3፤ እና 8ኛ ደረጃዎች 30
ከ1-5 ደረጃ ውጤች 30 ነጥብ - ከዓለም 17ኛ
በሴቶች
10 የወርቅ፣ 5 የብርና 9 የነሐስ ሜዳሊያዎች፣ 4ኛ ደረጃዎች 8፤ 5ኘ ደረጃዎች 5፣ 6ኛ ደረጃዎች 1፣ 7ኛ ደረጃዎች 3 እና 8ኛ ደረጃዎች 2
ከ1-3 ደረጃ ውጤቶች 24 ነጥብ - ከዓለም 11ኛ 55 የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች 31 ኦሎምፒያዶች ተካሂደዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ13 ተሳትፋለች 12 የወርቅ፣ 11 የብር እና 21 የነሐስ ሜዳሊያዎች፤ 4ኛ ደረጃዎች 17፤ 5ኛ ደረጃዎች 8፣ 6ኛ ደረጃዎች 11፣ 7ኛ ደረጃዎች 6 እና 8 ደረጃዎች
የኦሎምፒክ ሪከርዶች
በኦሎምፒክ መድረክ በወንዶች በ5ሺ ሜትር እና በ10ሺ ሜትር ሁለት ክብረወሰኖችን የያዘው ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ ሁለቱንም የኦሎምፒክ ክብረወሰኖች እኤአ በ2008 በቤጂንግ በተካሄደው 29ኛው ኦሎምፒያድ ሲያስመዘገባቸው በ5 ሺ ሜትር 12 ደቂቃ ከ57.82 ሰኮንዶች እንዲሁም በ10ሺ ሜትር 27 ደቂቃ ከ04.7 ሰኮንዶች የሰፈሩ ናቸው፡፡
ኬንያውያን በ800፤ በ1500፤ በ3ሺ መሰናክልና በማራቶን የተያዙ የኦሎምፒክ ሪከርዶችን በመቆናጠጥ የተሻለ ውክልና አላቸው፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ በሴቶች ምድብ በተመዘገቡ ሪከርዶች ኢትዮጵያ በሁለት አትሌቶች ስትጠቀስ ኬንያ ግን አንድም አላስመዘገበችም፡፡
በኢትዮጵያውያን የተያዙት ሁለት የረጅም ርቀት የኦሎምፒክ ሪከርዶች በ2016 እእአ ላይ በሪዩዲጄኔሮ ኦሎምፒክ አትሌት አልማዝ አያና በ10ሺ ሜትር 29 ደቂቃ ከ17.45 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበችውና በ2012 እኤአ ላይ በለንደን በተካሄደው 30ኛው ኦሎምፒያድ ቲኪ ገላና በማራቶን ስታሸንፍ ርቀቱን የሸፈነችበት 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ07 ሰኮንዶች፡፡
ምንጭ :-- ኦሎምፒክና የኢትዮጵያ ወርቃማ ኦሎምፒያኖች - Addis Admass Newspaper | Amharic news | Ethiopian news
No comments:
Post a Comment