ከደራሲያን ዓምባ

Thursday, November 28, 2024

'ነገም ሌላ ቀን ነው' _ነብይ መኮንን

 

                                                       Margaret Mitchell _Gone with the Wind 

ነብይ መኮንንን በብዙ ነገሮች እናስታውሰዋለን። ከ20 አመታት በላይ የተወዳጁ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበር። ለጋዜጠኝነት ስልጠና ወደ ሰሜን አሜሪካ አቅንቶ ለጥቂት ወራት በከረመበት ወቅት በዚያ የሚኖሩ የኢትዮጵያውያንን ኑሮ ተነቦ በማይጠገብ ለዛ በመጀመሪያ በዚያው በአዲስ አድማስ ጋዜጣ አምድ፣ በኋላ ደግሞ ተሰብስቦ በአንድ መጽሐፍ የእኛ ሰው በአሜሪካ በሚል ርእስ አቅርቧል። በሁለት የስውር ስፌት ግጥም መድብሎችና በሌሎችም ጥልቅ መልእክት ያላቸው ውብ ግጥሞቹን አስነብቦናል። አበበ ባልቻ፣ ፈቃዱ ተክለማርያም፣ ፍቅርተ ጌታሁን እንዲሁም ራሱ አነስተኛ ሚና ይዞ የተወነበትን እጅግ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ "ባለጉዳይ"ን ጽፏል። ከመአዛ ብሩ ጋር በሸገር ጨዋታ ለ14 ሳምንታት የዘለቀ ተሰምቶ የማይሰለች ውብ ጨዋታ ተጫውተዋል።

እኔ ግን ነብይ መኮንን ሲባል መጀመሪያ ትዝ የሚለኝ የማርጋሬት ሚሸል Gone With the Wind 'ነገም ሌላ ቀን ነው' ነው—በብዙ ምክንያቶች። በመጀመሪያ ነብይ መኮንን የሚለውን ስም ለመጀመሪያ ግዜ የሰማሁት/ያነበብኩት ከዚህ መጽሐፍ ትርጉም ሽፋን ነው። First impressions are powerful ይባል የለ። መጽሀፉ የተተረጎመበት አጋጣሚ በራሱ epic/ድንቅ የሚባል ነው። በእርግጥ ነብይ እራሱ እንደነገረን መጽሀፉን ለመተርጎም የተነሳሳው በኢህአፓነት ማእከላዊ ለ10 አመት ታስሮ በነበረበት ወቅት ነበር። በግዜው ለማእከላዊ እስረኞች መጽሐፍ አይገባም፣ አይፈቀድም። ወረቀትና ብእር ጨምሮ። እስረኞቹ የፖለቲካ ስለሆኑ ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን እንዲያዳብሩ ወይም እንዲያስተላልፉ አይፈለግም። የታሰረው አካላቸው ብቻ አልነበረም። አእምሮና መንፈሳቸው ጭምር እንጂ።
ታዲያ ነብይ ይህንን ድንቅ መጽሀፍ እንዴት ለመተርጎም በቃ? ነገሩ አጋጣሚ ይመስላል ግን አጋጣሚ አልነበረም። በግዜው በእስርቤቱ ውስጥ ነብይ ሊያገኝ የቻለው መጽሐፍ የማርጋሬት ሚሸል Gone With the Wind ብቻ ነበር። ይህም የሆነው አንድ ሌላ እስረኛ ወደ እስር ቤት ሲወሰድ በአጋጣሚ በኪሱ ይህንን መጽሀፍ ይዞ ነበር። ነገር ግን በዚህ አለም አጋጣሚ ብሎ ነገር የለም። "There are no accidents" ይላሉ ብልሁ ኤሊ ማስተር ኡግዌይ። ይህ መጽሐፍ ማእከላዊ እስር ቤት በዚያ ወቅት በነብይ መዳፎች ስር የወደቀው በፍጹም በአጋጣሚ አይደለም። አጋጣሚ ይመስላል ግን አይደለም።
በመጀመሪያ መጽሐፉ ስለ አሜሪካ የእርስበእርስ ጦርነት ነው። ኢትዮጵያም በዚያ ወቅት ከአሜሪካው የእርስበርስ ጦርነት መቶ ምናምን አመት በኋላ በአሰቃቂ የእርስበእርስ ጦርነት እየማቀቀች ነበር። የማይመስል አጋጣሚ አንድ። ሁለተኛ መጽሐፉ በአሜሪካ የእርስበእርስ ጦርነት አሳብቦ ለሁሉም የሰው ልጆች ትርጉም ስለሚሰጠው ስለ አይበገሬው የሰው ልጆች ጠንካራ መንፈስ ነው። በተለይ ማእከላዊ ለ10 አመታት ታስሮ ለሚማቅቅ ሰው የበለጠ ትርጉም ይሰጣል። የመጽሐፉ አብይ ጉዳይ የአንድ ሃገር ጦርነት ቢሆንም የትም፣ መቼም ላለ ሰው ጥልቅ መልእክት አለው። ደግሞም የላቀ የአማርኛና የእንግሊዝኛ እውቀት ያለው ሰው በዚያ እስር ቤት መገኘቱ መጽሐፉ በዚህ ሁኔታ መተርጎሙ ከአጋጣሚ እጅግ ያርቀዋል።
እኛ ሰዎች ነን። እውቀታችን በግዜ፣ በቦታ፣ በሁኔታ የተወሰነ ነው። ከምናውቀው የማናውቀው ይበልጣል። እናም በዚህ ውስንነታችን የተነሳ የመጽሐፉ በነቢይ መተርጎም ተራ አጋጣሚ ይመስለናል። አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች አስደናቂ ነገሮችም አሉ በመጽሐፉ አተረጓጎም ዙሪያ። ለትርጉም ስራ የሚያስፈልጉት ወረቀትና እስክሪፕቶ ወደ እስር ቤቱ እንዲገቡ አይፈቀድም። ነብይ የነበረው ብቸኛ አማራጭ የሲጋራ ፓኬት ውስጥ የሚገኘውን የአልሙኒየም ወረቀት መጠቀም ነበረበት። ነብይ ይህንን መጽሐፍ ተርጉሞ ለመጨረስ 3000 የሲጋራ የአልሙኒየም ወረቀት ፈጅቷል። ይህ ብቻ አይደለም። መጽሀፉ የሚተረጎመው በድብቅ ነው። ከእስር ቤቱ ተበታትኖ የሚወጣውም በድብቅ ነው። ወረቀቱን ተከፋፍለው ይዘው የሚወጡት የመፈቻ ግዜያቸው የደረሰ እስረኞች ነበሩ። ታዲያ እስረኞቹ ተፈትተው አንዱ ወለጋ፣ አንዱ ጅማ፣ አንዱ ባሌ ይሆናል የሚሄዱት። ታዲያ ለነብይ ፈተና ከሆነበት ጉዳይ አንዱ የእስር ግዜውን ጨርሶ ሲወጣ የተበታተነውን ወረቀት ለማሰባሰብ ወደ ብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች መጓዝ ነበረበት። ወረቀቱን በስርአቱ አስቀምጠው የጠበቁት እንደነበሩ ሁሉ በእንዝህላልነት የጠፋባቸውም ነበሩ። ብዙ መከራ ያየ መጽሐፍ ነው—ለመተርጎም፣ ለመሰብሰብ፣ ለመታተም።
ብቻ ያ ሁሉ መከራ ታልፎ መጽሀፉ በ1982 ታተመ። በነገራችን ላይ መጽሐፉ ሁለት ቅጽ ነው ያለው። ሙሉ መጽሀፉ ከ1000 ገጽ በላይ ነው ያለው። ያኔ የታተመው ግን ግማሹ ወይም አንዱ ቅጽ ብቻ ነበር። ምክንያቱም ከሺ በላይ ገጾች ያሉትን መጽሐፍ ማሳተም ከህትመት ወጪ አንጻር አዋጭ ስላልነበር ነው። እኔም ለመጀመሪያ ግዜ ያነበብኩት ይህንኑ አንዱን ቅጽ ብቻ ነበር። በእርግጥ የመጽሐፉ የመጀመሪያው ቅጽ ከሁለተኛው ይልቅ ስነጽሁፋዊ ለዛው ይልቃል። የመጀመሪያው ቅጽ ስለ እርስበእርስ ጦርነቱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ቅጽ ከእርስበእርስ ጦርነቱ በኋላ ደቡባውያን ስለሚያሳልፉት ፍዳና ሃገራቸውን መልሰው ለመገንባት ስለሚያደርጉት ጥረት ነው። የህትመት ዋጋ አሁን የበለጠ ንሯል። ነገር ግን ነብይ ሙሉውን መጽሐፍ ስለተረጎመው ወራሾቹ ሁለተኛውን ቅጽም ለብቻው ቢያሳትሙት ጥሩ ነው።
ነብይ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሳለ የአንድ ዝነኛ የአሜሪካ ጋዜጣ — The Guardian ይመስለኛል — ጋዜጠኛ የነብይን ታሪክ ሰምታ ተደነቀች። ተደንቃ ብቻ አልቀረችም ነብይን ለማናገር አዲሳባ ድረስ መጣች። በእርግጥ አስደማሚ ታሪክ ነው። በመጀመሪያ Gone With the Wind አሜሪካኖች ትልቅ ቦታ የሚሰጡት የስነጽሁፍ ስራ ነው። ሃገራቸውን ለሁለት ሊከፍል የነበረ ወሳኝ የታሪክ አጋጣሚ ነው። አሜሪካውያን ምንግዜም ምርጥ ፕሬዚዳንታችን ነው የሚሉት አብርሃም ሊንከን የዚህ የታሪክ አጋጣሚ አብይ ምክንያትና ውጤት ነው። ደራሲ ማርጋሬት ሚሼል ደግሞ ታሪኩን በተባ ብእሯ ዘለአለማዊ አድርጋዋለች። አሜሪካንን አፍርሶ እንደ አዲስ አስበልጦ የሰራ ጦርነት ነው። ይቺ ደራሲ ጋዜጠኛ ነበረች። ባጋጠማት የጀርባ ህመም ከቤት ዋለች። ግን ስራ አልፈታችም። አስር አመት ፈጅታ ይህንን ውብ ልብወለድ አብስላ ጻፈች። እዚህ እኛ ሃገር ደግሞ ነብይ መኮንን የተባለ ጀግና ተርጓሚ እንደሷ 10 አመታት ፈጅቶ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተረጎመው። ይቺ የዘ ጋርዲያን ጋዜጠኛ አዲስአበባ ድረስ መጥታ ነብይን አናግራ ቆንጆ መጣጥፍ ጽፋላታለች።
¤¤¤
ሬት በትለር እስካርሌት ኦሃራን አፈቀረ። እስካርሌት አሽሌ ዊክስን ፈቀደች። አሽሌ ሜላኒ ሃሚልተንን አገባ። የአራት ሰዎች የፍቅር ህይወት ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሆነ።
ግዜው 1860 ነው። ሬት በትለር 35 አመት ሞልቶታል። የእርስ በእርስ ጦርነቱ ሊጀምር ነው። ሁለቱም ወገኖች የጦርነት ድቤ እየደለቁ ነው። ደቡባውያኑ ሰፋፊ የጥጥ እርሻ ያላቸው ሃብታሞች ናቸው። እርሻው የሚለማው በባሮች ጉልበት ነው። ሰሜናውያኑ በበኩላቸው ባርነትን አጥፍተው ህገወጥ አድርገውታል። በምትኩ ትላልቅ ኢንደስትሪዎችን ተክለዋል።
አብርሃም ሊንከን ለፕሬዚዳንት ሲወዳደር ከተመረጠ ባርነትን ከመላው አሜሪካ እንደሚያጠፋ ቃል ገባ። ምርጫውን ሲያሸንፍ የገባውን ቃልኪዳን ለመጠበቅ ስራውን ጀመረ። አንድ ሃገር በሁለት የተለያየ ስርአት መተዳደር እንደሌለባቸው አወጀ። ይኼኔ ሁለቱም ወገኖች ተቆጡ።
ደቡባውያኑ ያላቸው አንድ ነገር ሰፋፊ እርሻ ነው። ባርነት ከተወገደ እርሻቸውን ማን ያለማላቸዋል? በባሮች ትከሻ ቀለል ያለ ኑሮ የሚኖሩ ህዝቦች ነበሩ። የባርነት ስርአትን ማፍረስ ያንን የተንደላቀቀ ህይወት መሰናበት ነው።
ሬት በትለር ግን እንደ ሌሎቹ ደቡባዊውን አይደለም። የኮንፌዴሬሲው ባንዲራ ሲውለበለብ ሰውነቱን አይወረውም። ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር አይነሽጠውም። እንዲያውም ሬት እንዲህ ይላል፦
"ሃገር ስትበለጽግ አብሮ ሃብታም መሆን ይቻላል። በተቃራኒው አለም ወደ ውድቀት ስትንደረደር የበለጠ እጥፍ ሃብታም መሆን ይቻላል።"
በዚህ ፍልስፍና እየተመራ ሬት በሙሉ ሃይሉ ወደ ኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ ይገባል። ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የማይሸጠው ቁሳቁስ አልነበረም—ከሽቶ እስከ መሀረብ፣ ከመጠጥ እስከ ልብስ። ሬት በትለር መላው ሃገር ወደ አመድነት ቢቀየር ግድ የሚሰጠው ሰው አይደለም። ለሱ ዋጋ ያላቸው ነገሮች የንግድ ስራውና ትርፉ ብቻ ናቸው።
ጦርነቱ ሲገባደድ ሬት ሚሊየነር ሆኗል። ይህ ሃብት በብዙሃን ደም የተገኘ ነው። ሬት በተደጋጋሚ የሚጠቀማት አንድ ሃረግ አለች፦
"እንደ እውነቱ ከሆነ ውዴ ምንም ግድ አይሰጠኝም።"
አዎ ሬት ግድ አይሰጠውም። ሃገሪቷ በእሳት ብትነድ ግድ አይሰጠውም፤ ሚሊየኖች ቢሞቱ ግድ አይሰጠውም፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ቀውስ ቢሰፍን ግድ አይሰጠውም። ለሬት ግድ የሚሰጠው አንድ ነገር ብቻ ነው—ገንዘብ፣ እጅግ ብዙ ገንዘብ። ገንዘብ የሚያስገኝለት ከሆነ ለመስዋዕትነት የማያቀርበው ነገር የለም። አለማችን ወደ ሲኦል የምትንደረደረው በነዚህ አይነት ሰዎች ምክንያት ነው።
¤¤¤
ነገም ሌላ ቀን ነው ውስጥ በጣም የምወዳት ገጸባህሪይ ሜላኒ ሃሚልተን ነች። ልቧ ትልቅ ነው— ያለ ምንም ተቀጥላ ምክንያት ሁሉንም እኩል ትወዳለች። አምስት ደቂቃ አብሯት ያሳለፈ ሁሉ ይወዳታል። ነፍሷ ምትሃታዊ ባህሪ አለው። ሰዎች ለራሳቸው እንኳን የማይታያቸውን ጥሩነት በማየት ዘወትር ታስደንቀኛለች።
ሰዎች ላይ አትፈርድም። ሁሉንም እንዳሉ ትቀበላቸዋለች ጨካኝና መጥፎ እንኳን ቢሆኑ። ልቧ ግዙፍ ስለሆነ ለሁሉም የሚበቃ ቦታ አላት።
ደቃቃ ብትሆንም ደፋር ናት—ፍርሃት የሚባል ነገር አልፈጠረባትም። ትልቅ ነፍሷ ትንሹ ሰውነቷን ሸፍኖታል። በአስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ሆና እንኳን አትፈራም። እንደዚያ አምርራ የምትጠላት ስካርሌት እንኳን በሃቀኛነቷ ታከብራታለች። በአረብኛ እንዲህ የሚል አባባል አለ፦
"ለልበ ንጹህ፣ ሁሉም ንጹህ ነው"
.
እኔ ደግሞ በልብወለድም ይሁን በእውነታ ከሜላኒ የበለጠ ንጹህ አልገጠመኝም።
¤¤¤
እስካርሌት ከአሽሌይ ድብን ያለ ፍቅር ይዟታል። ከሱ ጋር ለመሆን የማትፈነቅለው ድንጋይ፣ የማታደርገው ነገር የለም። እሱ ግን እስካርሌትን ትቶ የምትመስለውን፣ የሚመስላትን ሜላኒን አገባ። ይኼኔ እስካርሌት አረረች ፤ ቆሽቷ ደበነ።
እስካርሌት ለሶስት ግዜ ያህል አግብታለች—ግን አንዱም ለፍቅር አልነበረም። ሌላ ድብቅ አላማ ነበራት—ቁሳዊም ሆነ ሌላ።
በመጨረሻ ሜላኒ በወሊድ ሞተች። አሁን ህይወቷን ሙሉ ስታሳድደው የኖረችው አሽሌይ ነጻ ሆነ። ነገር ግን ለሱ የነበራት ስሜት ሁሉ ተኖ ማለቁ ገረማት።
አሁን የሚወዳትን ሬት መውደድ ጀመረች። ነገር ግን ረፍዶ ነበር። እሷ ለአሽሌይ የነበራት ስሜት እንደሞተ ሁሉ፤ ሬት ለሷ የነበረው ስሜት ሞቷል። የምትወደውን አሽሌይን ስታሳድድ የሚወዳትን ሬትን አጣች። እስካርሌት ግራ የሚያጋባ የህይወት እንቆቅልሽ ሲገጥማት ዘወትር እንደዚህ ትላለች፦
"ይሄን ዛሬ አላስበውም። ነገም ሌላ ቀን ነው!"
¤¤¤
ስለ ጀራልድ እና ኤለን
ጉጉት የሚጭሩ ገፀ-ባህሪያት ናቸው፤ እና ልጃቸው ስካርሌት ከየት እንደመጣች እንድናይ ይረዱናል። ስካርሌት እንደ አባቷ ጨካኝ እና ግትርእና እንደ እናቷ የዋህ ነች። ለእስካርሌት በዚህ ዓለም ውስጥ ሁለት ሴቶች አሉ - እናቷ እና የተቀሩት ሴቶች። እናቷን እንደ አምላክ ትመለከታለች። በኤለን እና በእግዚአብሔር እናት— በማርያም— መካከል ያለውን ልዩነት አታውቅም።
ጄራልድ አጭር ቁመት አለው። ነገር ግን በአለም ላይ የሚፈልገውን ሁሉ ከማግኘት የሚያግደው ምንም ነገር የለም። ቆንጆዋን ኤለን እንኳን ቢሆን። የአይሪሽ አእምሮው አረቄን እንዴት እንደሚይዝ እና ቁማር መጫወትን ያውቃል። የመጀመሪያውን ባሪያውን እና ትልቁን ታራ በቁማር አሸንፏል። ከኤለን ፍላጎት ውጪ ሰክሮ በፈረስ ላይ የወጣበትን እና አጥሩን ለመዝለል የሚሞክርበትን ትዕይንት ሁልጊዜ አስታውሳለሁ። ስካርሌት በረንዳ ላይ ተቀምጣ ጄራልድ እየዘለለ ሲመለከት ለኤለን መልሳ አላቃጠረችበትም። የሁለቱ ምስጢር ነው።
ኤለን የአጎቷን ልጅ እና ወላጆቿ የከለከሉትን እውነተኛ ፍቅሯን ፊሊፕን ማግባት ፈለገች። ፊሊፕ ግን በቡና ቤት ጸብ ተጋድሎ ሞተ። ወላጆቿን ለማበሳጨት፣ ጄራልድ ኦሃራን አገባች፣ በኋላ ግን ተጸጸተች። ደራሲው ኤለን ለጄራርድ ምንም አይነት ፍቅር እንደሌለው ይነግሩናል. ልቧ ባዶ ቀፎ ነበር።
ከብዙ አመታት በኋላ ትልቋ ሴት ልጇ ስካርሌት የእናቷን ተመሳሳይ ስህተት ለመስራት ተነሳች። ስካርሌት አታውቀውም ነበር፣ ኤለን ግን አወቀች። እና ይህን እውነት ለመናገር ምንም አይነት ጨዋ መንገድ የለም። ኤለን እራሷን ብቻ አስቀምጣ ጋብቻውን ለመረዳት በማይቻል ሁኔታ ተቃወመች።
ኤለን እውነተኛ ፍቅሯን የተናገረችው፣ ስሙን የጠራችው በሞቷ አልጋ ላይ ብቻ ነው። የመጨረሻ እስትንፋሷን ከመውሰዷ በፊት የፊሊፕን ስም ጮኸች። ይህ የፊሊፕ ሰው ማን ነው፣ እና እሱ ለእስካርሌት እናት ምንድነው?! ከማሚ በስተቀር ማንም አያውቅም።
በሌላ በኩል ጄራልድ ኤለንን በእውነት ይወዳት ነበር። እሷ ለስላሳ እና ቆንጆ ነች። ሁሉም ያከብሯታል። ለዚህም ነው መሞቷ ሙሉ በሙሉ አለሙን ያጨለመው። አእምሮው ከኤለን ሞት ወዲህ ልክ አልነበረም። ደራሲው ማርጋሬት ሚቼል ግራ የተጋባውን የአዕምሮ ሁኔታውን በሚያምር ሁኔታ ገልጻዋለች።
¤¤¤
እነሆ በወንድማማቾሽ መካከል መራር ጦርነት ተደረገ። የደቡብ ኮንፌዴሬሲው ተደመሰሰ። የያንኪ ወታደሮች በደቡባዊ አሜሪካ ውስጥ ሴቶችን እየደፈሩ፣ ንብረት እየዘረፉ፣ ቤት እያቃጠሉ ብዙ ጉዳት አደረሱ። ደቡባውያን የተሰበረ ቅስማቸውን እያስታመሙ፣ ዳግም ከተሞቻቸውን መገንባት ጀመሩ። ባሮች ነፃ ወጡ። ዘረኛውን ኬኬኬ የሚቀላቀሉ ወጣቶች በዙ። ከጦርነቱ በኋላ ሌላ "ሰላማዊ" ጦርነት ተጀመረ።
የመፅሀፉ ርእስ "Gone the Wind" ነው። ለአማርኛ ትርጉሙ የተመረጠው ርእስ "ነገም ሌላ ቀን ነው" ነበር። ይህ መጽሐፍ የጦርነትን አውዳሚነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። በተለይ የእርስ በእርስ ጦርነት መዘዙ ብዙ ነው። ዳፋው ለትውልድ ይተርፋል። ቁስሉ ቶሎ አይጠግም።
ለኛ የእርስ በእርስ ጦርነት አዲሳችን አይደለም። ለዘመናት አቆርቁዞናል። ዛሬ ግን አይናችንን መግለጥ አለብን። ብልጥ ከሰው ይማራል ሞኝ ደግሞ ከራሱ። ከዚህ አለፍ ሲል ግን፣ ከራሱ የቀደመ ታሪክ የማይማር ግን ከሞኝነትም አልፎ ደደብ ነው።
¤¤¤
Gone With the Wind"/ "ነገም ሌላ ቀን ነው" የተሰኘውን ታላቅ መፅሀፍ በትንሹ አምስት ግዜ አንብቤዋለሁ― በእድሜዬ አስራዎቹ፣ ሀያዎቹ፣ ሰላሳዎቹ ውስጥ ሆኜ። ታድያ መፅሀፉን ደጋግሜ ሳነሳው ሁሌም አዲስ ነገር አገኝበታለሁ። በእርግጥ መፅሀፉ የድሮው ነው፤ ቃላቶቹ አልተለወጡም፤ ገፆቹ አልተለጠጡም። ታዲያ እንዴት ይህ አሮጌ መፅሀፍ በእኔ ውስጥ አዲስ ሐሳብና ስሜት ፈጠረ ብዬ ስጠይቅ መልሱ ብሩህ ሆኖ ታየኝ። ምንም እንኳን መፅሀፉ ባይለወጥም፣ እኔ አንባቢው ተለውጬያለሁና ነው። እኔ ስለወጥ አሮጌውን መፅሀፍ የማይበት መነፅር አዲስ ነው፤ ፍፁም ከተለየ አቅጣጫ /perspective ነው ታሪኩን ገፀ ባህሪያትን የማየው።
¤¤¤
በማያልቅ የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ለምንኖረው እኛ ይሄ መጽሐፍ ትልቅ መልእክት አለው። ከታሪክ የምንማረው ከታሪክ አለመማራችንን ነው ይባላል። እንኳን ከአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ ከራሳችንም ታሪክ አልተማርንም። በናፍቆት የሚጠበቅ የኦሎምፒክ ውድድር ይመሰል በየ10 አመቱ ጦርነት እንገጥማለን።
¤¤¤
Gone with the Wind
ይህን ልብወለድ በብዙ ምክንያቶች እወደዋለሁ። አሜሪካንን ለመረዳት ይሄንን የCivil War Era የእርስበርስ ጦርነት ዘመን ልብወለድ ማንበብ ተገቢ ነው። በሌላ አነጋገር ገን ዊዝ ዘ ዊንድ ጠቃሚ የታሪክ ሰነድ ነው። የሬት በትለርና የእስካርሌት ኦሃራ የፍቅር ታሪክ መንፈስን ሰቅዞ የመያዝ አቅም አለው። በአጠቃላይ ግሩም የስነጽሁፍ ስራ ነው።
ብዙውን ግዜ ታላቅ የስነጽሁፍ ስራ የሆነ መጽሐፍ ወደ ፊልም ሲላመድ ይኮስሳል፤ ግዙፍ ግርማ ሞገሱን ያጣል። Gone With the Wind መጽሐፉ በ1936 ተጽፎ ወደ ፊልም የተላመደው ቶሎ ከሶስት አመት ብቻ በኋላ በ1939 ነበር። በእርግጥ በብዙ ምክንያቶች ፊልሙን ለማየት ጓጉቼ ነበር—ሆሊውድ የክላሲካል ኢራው ማስተርፒስ ከሚላቸው ፊልሞች አንዱ ነው። ጋሽ ስብሐት ራሱ ፊልሙን አለመጠን ሲያዳንቅ "ፊልሙን ከተመለከትኩ በኋላ በጣም ስለረካሁ መጽሐፉን ለማንበብም አላሰኘኝ" እኔ ግን ጥርጣሬዎች ነበሩኝ። ከ1000 በላይ ገጾችና እጅግ ብዙ ዝርዝር ታሪክ ያለውን መጽሀፍ በሶስት ሰአት ፊልም ሳያጎድሉ ማሳየት ይቻላል?! በመጨረሻ የገባኝ አንድ ትልቅ እውነት አለ። መጽሐፍ እና ፊልም እጅግ የተለያዩ ሚዲየሞች ወይም ቅርጾች ናቸው። እርስበእርስ አይወዳደሩም። መመዘን ያለባቸውም እንደ አውዳቸው ነው። ለመዝናናት፣ ግዜ ለመቆጠብ ፊልም ጥሩ አማራጭ ነው። ለቁምነገር ከሆነ ግን መጽሀፉን ማንበብ ይመረጣል። በዚህ መመዘኛ ሁሌም መጽሀፍን እመርጣለሁ። ግን ፊልሙም ጥሩ መዝናኛ ነው።
በነገራችን ላይ መጽሀፉን ከማንበብና ፊልሙን ከመመልከት ባሻገር፣ ይህ መጽሀፍ በአሁን ወቅት በሬዲዮ ፋና እየተተረከ ነው። የመጽሀፍት ትረካ ለምትወዱ ጥሩ አማራጭ ነው። ዩትዩብ ላይም ስላለ አውርዳችሁ ልትመሰጡበት ትችላላችሁ። ተራኪው ዳንኤል ሙሉነህ ነው። መጽሀፉ በአንድ አረፍተ ነገር ሲጠቃለል፦
"Yesterday has Gone With The Wind. Tomorrow is another day"
"ትላንት ከንፋሱ ጋር አልፏል። ነገም ሌላ ቀን ነው"



Sunday, July 7, 2024

ገጣሚ፣ ደራሲና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን ወንድም

ገጣሚ፣ ደራሲና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን ወንድም (1946 - 2016)

ገጣሚ፣ ደራሲና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፣ ከአባቱ ከአቶ መኮንን ወንድም እና  ከእናቱ ከወይዘሮ በለጤ በድሉ፣ በነሐሴ ወር 1946 ዓ.ም፣ በቀድሞዋ ናዝሬት፣  በአሁኑ አዳማ ከተማ ተወለደ፡፡

 ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመግባቱ አስቀድሞ፣ መምህር ተከስተ ጋር የቄስ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን፤ እዚያም ሳለ ዳዊትን በቃሉ በመሸምደድ የማስታወስ ችሎታውን አዳበረ፡፡  
 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው ናዝሬት በአጼ ገላውዲዮስ ት/ቤት  የተከታተለው ነቢይ መኮንን፤ በትምህርት አቀባበሉም ከጎበዞቹ ተርታ የሚሰለፍ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ለትምህርት ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው  የገንዘብ ሚኒስቴር ባልደረባ የነበሩት አባቱ፤ ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡  ልጃቸው ሁልጊዜም  በትምህርቱ ብርቱ ሆኖ  ምክራቸውን  ይለግሱት  ነበር፡፡ ነቢይም፣ ከክፍሉ አንደኛ በመውጣት አባቱን ከማስደሰት ቸል ብሎ አያውቅም፡፡  ነቢይ አባቱን አቶ መኮንን ወንድምን በሞት ያጣው  የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነበር፡፡
ነቢይ መኮንን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን  እንዳጠናቀቀ፣ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ልኡል በእደ ማርያም ተማሪ ቤት ከገቡ ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ ነበር፡፡  በመቀጠልም በ1966 ዓ.ም፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲን የተቀላቀለው ነቢይ፤ ኬሚስትሪን በዋናነት (ሜጀር)፣ ሂሳብን ደግሞ  ማይነር በማድረግ አጥንቷል፡፡
  


እንደ ዘመነኞቹ  በወቅቱ  የተማሪዎች  ንቅናቄ ውስጥ ተሳትፎ የነበረው ነቢይ መኮንን፤ ከደርግ ወጥመድ አላመለጠም፡፡ በኢህአፓ አባልነቱ ታስሮ ለ10 ዓመታት መከራውን በልቷል፡፡ ነገር ግን ደርግንም ሆነ አገሪቱን ወይም ሌላ ወገን ሲያማርር፣ ሲወቅስ ወይም ሲረግም ተሰምቶ አይታወቅም፡፡  እንደ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታግዬለታለሁ፣ ሞቼለታለሁ ወዘተ እያለም መመጻደቅ አያውቅበትም፡፡  በሚመጻደቁትም ይስቃል፡፡ እሱና ዘመነኞቹ በአብዮቱ ወቅት ያሳለፉትን በጎም ሆነ ክፉ፣ ያሁኑ ትውልድ እንዲማርበት ከመጻፍና ከመናገር ግን  ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ጽንፈኝነትና አክራሪነት እንደማያዋጣ ሲመክር ኖሯል፤ በጽሁፎቹ፡፡    
 ነቢይ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኬሚስትሪ ያጠና  ቢሆንም፣ በገጣሚነት፣ በደራሲነት፣ በተርጓሚነትና በጋዜጠኝነት  በርካታ ሥራዎችን ለአንባቢያን  ያበረከተ ታላቅ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ነበር።



በ1992 ዓ.ም ህትመት የጀመረችውን አዲስ አድማስ ጋዜጣን ከመሰረቱት አንዱ የነበረው አንጋፋው የጥበብ ባለሙያ  ነቢይ መኮንን፤ ለሁለት አስርት ዓመታት ጋዜጣዋን በዋና አዘጋጅነት በመምራት፣ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ስኬታማ አድርጓታል፡፡ የአዲስ አድማስ ዋና አዘጋጅ የነበረው ነቢይ፣ በጋዜጣው ላይ በየሳምንቱ በተረትና ምሳሌ እያዋዛ በሚጽፋቸው ርዕሰ አንቀጾች ታዋቂነትን ያተረፈ ሲሆን፤ ለጋዜጣዋም ተነባቢነትን አቀዳጅቷታል፡፡  
ሁለገቡ ከያኒ ነቢይ መኮንን፣ ከአሰርት ዓመታት በፊት “ባለጉዳይ” የተሰኘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ ለዕይታ ከማብቃቱም በላይ በትወናም ተሳትፎበታል፡፡ የእዚህ ተከታታይ ድራማ ጭብጥ ከመሬት ጋር የተያያዘ የሙስና ጉዳይ ሲሆን፣ ታዋቂዎቹ ተዋናዮች  አበበ ባልቻ፣ ፈቃዱ ተክለማሪያምና ፍቅርተ ጌታሁንን ጨምሮ ሌሎችም ተሳትፈውበት ነበር፡፡
ነቢይ፣ “ናትናኤል ጠቢቡ” እና “ጁሊየስ ቄሳር” የተሰኙ ተውኔቶችንም ተርጉሞ ለመድረክ አቅርቧል። ”ባለካባ እና ባለዳባ” በተሰኘ ተውኔት ላይ ደግሞ በትወና ተሳትፏል።
“ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነኝ” የሚለው ነቢይ መኮንን፤ “ጥቁር፣ ነጭ፣ ግራጫ ግጥሞች” እና “ስውር ስፌት- (ሁለት ቅጾች)” የግጥም መድበሎችን ለንባብ  አብቅቷል፡፡  

ነቢይ፤ “የኛ ሰው በአሜሪካ” - የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻው፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ሲወጣ ቆይቶ፣ በመጨረሻ  በመጽሐፍ ተዘጋጅቶ ለህትመት የበቃ ሌላኛው ሥራው ነው። ለንባብ የበቃው ሌላው  የነቢይ መጽሐፍ ደግሞ “የመጨረሻው ንግግር” የተሰኘ ሲሆን፤ “ዘ ላስት ሌክቸር” ከሚለው መጽሐፍ የተተረጎመ  ነው።
ነቢይ፤ ዳን ብራውን የጻፈውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ የነበረውን "The Davinci Code" የተሰኘ መጽሐፍ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ አስነብቧል፡፡  
ከነቢይ ጥበባዊ ሥራዎች  ሌላው  የሚጠቀሰው  "ማለባበስ ይቅር" ነው፡፡ ኤች አይቪ-ኤይድስ  የሀገር አደጋ በሆነበት ዘመን፣ ነቢይ መኮንን "ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩትን ማግለል በሽታውን ያባብሳል፤ ስለዚህ ፍቅር እንስጣቸው፤ አናግልላቸው"  የሚል መልእክት ያዘለ  ግጥም ገጥሞ  ታዋቂ ወጣት ዘፋኞች አቀንቅነውታል፡፡  "ማለባበስ ይቅር" የተሰኘው የሙዚቃ ሥራ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ ይታይ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ከ32 ዓመት በፊት ሜጋ ኪነጥበባት ማእከልን ከመሰረቱት አንዱ የነበረው ነቢይ መኮንን፤ በጊዜው በሜጋ ኪነጥበባት ማእከል አሳታሚነት ትወጣ የነበረችውን  ‹‹ፈርጥ›› የኪነ-ጥበብ መጽሄትንም በዋና አዘጋጅነት በመምራት ይታወቃል፡፡
ነቢይ፣ ከጋዜጠኝነቱና ከጥበብ ሥራው ጋር በተገናኘ የተለያዩ የዓለም አገራትን የመጎብኘት ዕድል የገጠመው ሲሆን፤ ከጎበኛቸው ሀገራት  መካከልም ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ኢራን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣  ኬንያና   ሱዳን ይገኙበታል፡፡
ነቢይ ለሀገሩ ኪነጥበብ ማደግ ከወጣትነቱ ጀምሮ ብዘ የለፋ ታላቅ የሀገር ባለውለታ እንደመሆኑ መጠን፣ ይህንኑ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የቅርብ ወዳጆቹ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ፣ ነቢይ በሀገሩ ይከበራል የሚል  የምስጋና መሰናዶ አዘጋጅተውለት ነበር፡፡  
.ከሁሉ ወዳጅና  ተግባቢ የነበረው ነቢይ መኮንን፣ ባለትዳርና  የሦስት ሴት  ልጆች አባት ነበር፡፡ አንጋፋው ገጣሚ፣ ደራሲና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፣ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ፣ ረቡዕ ሰኔ 26 ቀን  2016 ዓ.ም  በተወለደ በ69 አመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ለአድናቂዎቹ  መጽናናትን እንመኛለን፡፡

********************************
ስለ ነቢይ መኮንን የማውቀውን ልንገራችሁ!

ኢዮብ ካሳ -

ለራስ የተጻፈ ወቀሳ

እንጠራራ እንጂ
እንፋለግ እንጂ
ከያለንበቱ
ሰው የለም አንበል፣ አለ በየቤቱ
ምን ቢበዛ ጫናው፣ አንገት ቢያቀረቅር
ምን አፉ ቢታፈን፣ዝም ቢልም አገር
ምን መሄጃ እስኪያጣ፣ መንገዱ ቢታጠር
ጎበዝ እንደ ጭስ ነው፤ መተንፈሻ አያጣም
ቀን መርጦ ሰው መርጦ መነሳቱ አይቀርም፡፡
(ነቢይ መኮንን፤ አዲስ አድማስ ግንቦት 9፣1995 ዓ.ም)

**

በዚህች አጭር ማስታወሻ በቅርበት ስለማውቀው ገጣሚ፣ ተርጓሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን በጥቂቱ አወጋችኋለሁ - በወፍ በረር እንደሚሉት፡፡ ነቢይ የትያትርና ድራማ ጸሃፊም ነው፡፡ ከዓመታት በፊት ባለጉዳይ የተሰኘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ ለዕይታ አብቅቷል፤ አንጋፋው አርቲስት አበበ ባልቻ፣ ራሱ ነቢይ መኮንንና ሌሎችም አርቲስቶች የተወኑበት፡፡ ጭብጡ ዛሬም ድረስ ተባብሶ የቀጠለው ከመሬት ጋር የተያያዘ የሙስና ጉዳይ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ድራማው ከ10 ዓመታት በኋላ በድጋሚ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቦ፣ እንደ አዲስ በከፍተኛ አድናቆት መታየቱ ነው፡፡ ናትናኤል ጠቢቡ የተሰኘ ተውኔትም ተርጉሞ ለመድረክ አቅርቧል፡፡ ጁሊየስ ቄሳር ሌላው ተርጉሞ ለዕይታ ያበቃው ተውኔት ነው፡፡

ነቢይን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅሁት የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ነው - በተወዳጇ ሳምንታዊ ጋዜጣ አዲስ አድማስ በኩል፡፡ ዕድሜ ለአዲስ አድማስ፤ ይኸው እስከ ዛሬ ድረስ በሥራ ባልደረባነትና በቅርብ ወዳጅነት አብረን ዘልቀናል፡፡ የጋዜጣዋ መሥራችና ባለቤት የነበረውን (ነፍሱን ይማረውና) አሰፋ ጎሳዬንና ነቢይን እኩል ነው የማውቃቸው፡፡ አለቃዬ ቢሆኑም አንድም ቀን እንዲያ ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ ወይም እንዲሰማኝ አላደረጉም፡፡ የጓደኝነትና የታላቅ ወንድምነት እንጂ የአለቃና ሎሌነት ስሜት ኖሮን አያውቅም፡፡

ሥራ ስጀምር በዕድሜና በህይወት ተመክሮ ከነቢይ በእጅጉ ባንስም፣ አጠገቡ ሆኜ አንድ ቢሮ እየሰራን፣ ሁሉንም ነገር እንድማር ዕድል ሰጥቶኛል፡፡ ይሄ እምብዛም በአበሻ ዘንድ የማይገኝ ደግነቱና ቅንነቱ ሁሌም ይደንቀኛል፡፡ ይታያችሁ --- ያኔም ቢሆን ነቢይ የታወቀ የሥነጽሁፍ ባለሙያ ነው፡፡ ዝነኛ ገጣሚ ነው፡፡ ዝነኛ ተርጓሚ ነው፡፡ ዝነኛ ጸሃፌ ተውኔት ነው፡፡ ዝነኛ የጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነው፡፡ ነገር ግን በችሎታውም ሆነ በታዋቂነቱ አይታበይም፤ አይኮፈስም፡፡

በደርግ ዘመን በኢህአፓ አባልነቱ ታስሮ ለ10 ዓመታት መከራውን በልቷል፡፡ ነገር ግን ደርግንም ሆነ አገሪቱን ወይም ሌላ ወገን ሲያማርር፣ ሲወቅስ ወይም ሲረግም ሰምቼው አላውቅም፡፡ እንደ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታግዬለታለሁ፣ ሞቼለታለሁ ወዘተ እያለ አይመጻድቅም፡፡ በሚመጻደቁትም ይስቃል፡፡ እሱና ዘመነኞቹ በአብዮቱ ወቅት ያሳለፉትን በጎም ሆነ ክፉ ያሁኑ ትውልድ እንዲማርበት ከመጻፍና ከመናገር ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ጽንፈኝነትና አክራሪነት እንደማያዋጣ ሲመክር ኖሯል፤ በጽሁፎቹ፡፡ ቁምነገርን በቀልድ እያዋዛ ማቅረብ ይወዳል - በጽሁፉም በንግግሩም፡፡ መድረክ ላይ ከወጣ ታዳሚን በሳቅ ያፈርሳል - አፍ ያስከፍታል፡፡ አንደበቱም ብዕሩም የተባ ነው፡፡

ነቢይ ባህልና ጥበብ አገርን እንደሚለውጥ ጽኑ እምነት አለው፡፡ በዚህ እምነቱ ነው አዲስ አድማስ በተለይ ጥበብና ባህል ላይ አተኩራ እንድትሰራ ያደረገው፡፡ የየሳምንቱን ርዕሰ አንቀጽ በተረትና ምሳሌ መጻፍ የጀመረው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ሃሳብ አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኝ ድልድይ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ለዚህም ነው የተለያዩ ሃሳቦችና አስተያየቶች በአዲስ አድማስ ላይ ያገደብ በነጻነት ሲስተናገዱ የኖሩት፡፡ እሱም እንደ ጋዜጣው መሥራችና ባለቤት አሰፋ ጎሳዬ ሁሉ ሃሳብን አይፈራም፡፡ ለህዝብና ለአገር የሚጠቅም አንዳች ሃሳብ ያላቸው ወገኖች ሁሉ፣ እንዲጽፉ ሲያበረታታና ሲደግፍ ነው የኖረው፡፡

ወጣት ገጣምያንና ጸሃፍት በአዲስ አድማስ ላይ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ሰፊ መድረክ ፈጥሮላቸዋል፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ዛሬ መጽሐፍት ያሳተሙ ታዋቂ ደራስያንና ገጣምያን ለመሆን በቅተዋል፡፡ በአጭሩ ተተኪ ጸሃፍት፣ ደራሲያን፣ ገጣሚያን፣ ወዘተ-- ፈጥሯል - በዋና አዘጋጅነት በሚሰራባት አዲስ አድማስ በኩል፡፡

እኔም የዚያ ውጤት ነኝ፡፡ በአዲስ አድማስ ላይ ከ30 የማያንሱ አጭር ልብወለዶችን ተርጉሜ አቅርቤአለሁ፡፡ ወደ አምስት ገደማ መጻህፍት አሳትሜአለሁ፡፡ ጋዜጣዋን ከ15 ዓመታት በላይ በምክትል ዋና አዘጋጅነት መርቼአለሁ፡፡ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ የነቢይ መኮንን በጎ ተጽዕኖ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ገና ከፍተኛ ሪፖርተር ሳለሁ፣ የተለያዩ ጽሁፎችን በጋራ እየተረጎምን በስማችን ጋዜጣው ላይ እንዲወጣ ያደርግ ነበር - በእኔ ጥያቄ ወይም ግፊት ሳይሆን በሱ ደግነትና ቅንነት፡፡ ፕሮፌሰሩ እና የዩክሬን ትራክተሮች የተሰኙ መጻህፍትን ለሁለት እየተረጎምን በተከታታይ አስነብበናል፡፡ የኔ ስም ከታዋቂው ገጣሚና የሥነጽሁፍ ሰው ነቢይ መኮንን ስም ጎን አብሮ ሲወጣ የሚፈጥርብኝን አዎንታዊ ስሜትና ብርታት አስቡት፡፡ በዚህ ሂደትም በነቢይ አስገራሚ የሥነጽሁፍ ብቃትና መክሊት እየተደመምኩ ብዙ ተምሬአለሁ፡፡ ነቢይ እኔን ገጣሚ ባያደርገኝም፣ከግጥም ጋር በፍቅር እንድወድቅ ማድረግ ችሏል፡፡ ደግነቱና ቅንነቱ ተጋብቶኝ ይሁን አይሁን ግን በእርግጠኝነት መናገር ያዳግተኛል፡፡

በነገራችን ላይ ዛሬ ስለ ነቢይ መኮንን እንዳወጋ ያነሳሳኝ፣ በነገው ዕለት ሦስት መጻሕፍት የሚያስመርቅ መሆኑ የፈጠረብኝ የደስታ ስሜት ነው፡፡ እናም ይህች አጭር ማስታወሻ ገጣሚውንና ሁለገብ የሥነጽሁፍ ሰው የሆነውን - ነቢይ መኮንን -እንኳን ደስ ያለህ- ለማለት ያህል፣ የከተብኳት ተደርጋ ትቆጠርልኝ፡፡ እንደሱ ገጣሚ ብሆን ኖሮ፣ ይሄን ሁሉ ሃሳብ በአጭር ግጥም ጽፌው እገላገል ነበር፡፡ እኔ ግን የግጥም አፍቃሪና አድናቂ እንጂ ገጣሚ አይደለሁም፡፡ ምናልባት ወደፊት --- ማን ያውቃል?

በነገው ዕለት በፍሬንድሺፕ ሆቴል ከሚመረቁት የነቢይ ሦስት መጻህፍት አንዱ፣ በ1970ዎቹ መጨረሻ ለህትመት የበቃውና በደርግ ዘመን በእስር ቤት ሳለ የተረጎመው ነገም ሌላ ቀን ነው የተሰኘው ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ነው፡፡ ነቢይ መኮንን Gone With The Wind የተሰኘውን የአሜሪካ ክላሲክ መጽሐፍ የተረጎመበትና ያሳተመበት ሂደት፣ በራሱ አስደናቂ መጽሐፍ ይወጣዋል፡፡ ጎበዝ የፊልም ባለሙያ ይፈልጋል እንጂ አስገራሚ ፊልምም የሚወጣው ነው፡፡

በደርግ ዘመን እንደ እኩዮቹ ሁሉ፣ በጸረ-አብዮተኝነት ተጠርጥሮ ወህኒ የተወረወረው ነቢይ መኮንን፤ ከዛሬ ነገ ይሙት ይትረፍ እርግጠኛ ባልሆነበት ሁኔታ፣ Gone With The Wind የተሰኘውን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ በሲጋራ ወረቀት ላይ እየተረጎመ፣ በድብቅ በማስወጣት ነው፣ በመጨረሻ ሲፈታ ያሳተመው፡፡

በነገራችን ላይ ይህን አስገራሚ ታሪክ ሰምታ የተደመመች አንዲት አሜሪካዊት ጋዜጠኛ፣ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ባህር ተሻግራ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ከነቢይ ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እኔ ደግሞ ወደ ሃገሯ ልትመለስ አንዲት ቀን ሲቀራት የማግኘት ዕድል አግኝቼ፣ ኢንተርቪው በማድረግ፣ ለአዲስ አድማስ አንባቢያን ታሪኩን አጋርቼዋለሁ፡፡

ነገም ሌላ ቀን ነው የተሰኘው መጽሐፍ የመጀመሪያ ዕትም በሳንሱር ምክንያት መግቢያውና አንዳንድ ሃሳቦቹ ተቆራርጠው መውጣታቸውን የሚያስታውሰው ነቢይ መኮንን፤ አሁን - ያልታተመው መግቢያ- ታክሎበት በአዲስ መልክ መታተሙን ተናግሯል፡፡
በነገው ዕለት የሚመረቀው ሌላው መጽሐፍ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ለዓመት ያህል በተከታታይ ሲወጣ የነበረውና ከፍተኛ ተነባቢነትን የተቀዳጀው የኛ ሰው በአሜሪካ - የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻ ነው፡፡ በአሜሪካ በሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ህይወት ላይ ያጠነጥናል፡፡ ሦስተኛው መጽሐፍ የመጨረሻው ንግግር የተሰኘ ሲሆን The Last Lecture ከሚለው መጽሐፍ የተተረጎመ ነው፡፡

እኒህ የነቢይ ሥራዎች ታትመው ለምርቃት መብቃታቸው በእጅጉ አስደስቶኛል፡፡ ከዚህ በላይ ግን የህይወት ታሪኩን ጽፎ እንደጨረሰና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህትመት እንደሚበቃ መስማቴ አስፈንድቆኛል፡፡ ነፍሴ በደስታ ጮቤ ረግጣለች፡፡ የመጽሐፍቶቹን ምረቃ በተመለከተ ባለፈው ሐሙስ በብሔራዊ ቤተመዘክርና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የኤጀንሲው ሃላፊ፣ ነቢይ መኮንን ራሱ ቤተመጻህፍት መሆኑን ጠቅሰው፤ የዚህን ሁለገብ የሥነጽሁፍ ሰው የህይወት ታሪክ መጽሐፍ ለህትመት ለማብቃት መጠነኛ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል - በተቋማቸው ስም፡፡ ይሄም ዜና ተስፋ ሰጪና አበረታች ነው፡፡ ለነቢይ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ደራሲያንና ሥነጽሁፍም ጭምር፡፡

በዚህ አጋጣሚ የነቢይ ሥራዎች ተሰባስበውና ተደራጅተው በመጽሐፍ መልክ ለትውልድ ይተላለፉ ዘንድ ከጎኑ ሆነው በትጋት እየሰሩ ያሉትን ወገኖች ሁሉ ማመስገን ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

በድጋሚ ለነቢይ መኮንን -እንኳን ደስ ያለህ- ለማለት እወዳለሁ፡፡
ረዥም ዕድሜ፣ የተትረፈረፈ ፍቅርና የተሟላ ጤና ተመኘሁልህ!



https://www.facebook.com/photo.php?fbid=8507341872617042&id=245686495449329&set=a.316574961693815

Thursday, June 27, 2024

የአለም የሴቶች ሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮና መንታ ንግስቶች


 

ቴሌቪዥኑ ተከፍቶ የስፖርት ዜና እየቀረበ ነው. ..
ከሚወራው ውስጥ ደግሞ በተለይ .....
" ሰሞኑን ሲካሄድ በሰነበተው የአለም አቀፍ የቴኒስ ሻምፒዮና አሸናፊ ለሆነችው ወጣት የ40 ሺህ ዶላር ሽልማት ተበረከተላት " . ..የሚለው ዜና የሪቻርድን ጆሮና አእምሮ በርግዶ ገባ.
.......
ይህ አሁን የሰማው ነገር ለሪቻርድ ከባድ እና ለማመን የሚያስቸግር ዜና ነበር. ..
ላሸነፈችው ልጅ የተሰጣት አርባ ሺህ ዶላር ማለት የሱ የአመት ደሞዙ ነው ።
እና ይህን እያሰበ አንድ ነገር ወደ አእምሮው መጣና አጠገቡ ሆነው ይጫወቱ ወደነበሩት ሁለት ሴት ልጆቹ ተመለከተ ።
.......
ሪቻርድ በእለቱ የሰማው ዜና ጉዳይ መላ ሀሳቡን ተቆጣጠረው ፡ ጊዜ አላባከነም ፡ እናም የዛኑ ቀን ልጆቹ የቴኒሱን አለም መቀላቀል እንዳለባቸው ወስኖ ባለብዙ ገፅ እቅድ መጻፍ ጀመረ ።
.........
አስቀድሞ በያዘው እቅድ መሰረት በቴኒስ ዙሪያ የተጻፉ መፅሄቶችን እና ቪዲዮዎችን ሰብስቦ የተዋጣለት አሰልጣኝ ለመሆን ራሱን በራሱ ማስተማር ያዘ ። በመቀጠልም ልጆቹ ቴኒስ እንዲለማመዱ የሚያስችለውን እቅድ በስራ ላይ ለማዋል አሰበ ። ችግሩ ግን ይህን ለማድረግ የሚያስችል የገንዘብ አቅም አልነበረውም ። ሌላው ቀርቶ የቴኒስ መጫወቻ ራኬትና ኳሶችን እንኳን መግዛት አይችልም ። ስለዚህ ይህን ለማሟላት በጎን ራሱን እያስተማረ ገንዘብ ማጠራቀም ጀመረ ። 

ከጥቂት ጊዜያት በኋላም ባጠራቀመው ገንዘብ የቴኒስ ራኬት መግዛት ቻለ ። የቴኒስ መጫወቻ ሜዳዎች አካባቢ ያሉ የቆሻሻ መጣያዎችን እየፈለገ የተጣሉ የሜዳ ቴኒስ ኳሶችን እየሰበሰበ ማጠራቀም ያዘ ።
...
ይህን ካደረገ በኋላ በአካባቢው ወደሚገኝ ሜዳ እየወሰደ ልጆቹን ማሰልጠን ጀመረ ።
....
ሆኖም አንድ ችገር ገጠመው ፡ ይኸውም ልጆቹን የሜዳ ቴኒስ በሚያለማምድበት ሜዳ አካባቢ የሚገኙ ምግባረ ብልሹ ወጣቶች ልጆቹን መተንኮስ ጀመሩ ፡ ሪቻርድ የሚበገር አባት አልነበረምና ልጆቹን ከጥቃት ለመከላከል ሲል ከነዚህ ሰወች ፀብ ውስጥ ገባ ።
.......
ትንኮሳው እየባሰ መጥቶም በዚህ ሜዳ መጠቀም እንደማይችል ተነገረው ፡ ይህን ሳይቀበል በመቅረቱም ፡ ጣቶቹ እስኪሰበሩና ጥርሶቹን እስኪያጣ ድረስ ከፍተኛ ድብደባ ደረሰበት
እንደዛም ሆኖ ሪቻርድ ፈርቶ ወደኋላ የሚልና ፡ ያሰበውን ሳያሳካ የሚተው ሰው አልሆነም ፡
ልጆቹን ዘወትር ይዞ እየሄደ ማሰልጠኑን ቀጠለበት ።
......
እንዲህ እንዲህ እያለ አመታት ተቆጠሩ ። ሁለቱ የሪቻርድ ልጆች ፡ በአካልም በእድሜም ፡ በቴኒስ ችሎታቸውም አደጉ ።
.........
የምርት መሰብሰቢያ ጊዜ !. .. የመኸሩ ወራት ደረሰ !!!

July 8/ 2000
በዚህ እለት የአለም የሴቶች ሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮና የፍጻሜ ውድድር የእንግሊዝ ልኡላን ቤተሰቦች እና ታዋቂ ሰወች እንዲሁም የአለም ህዝብ በቀጥታ የሚከተታለው ውድድር በዊምበልደን የሚካሄድበት እለት ነው ።
.....
አንዲት ለአለም አቀፉ የቴኒስ መድረክ አዲስ የሆነች ፡ ቬኒስ ዊሊያምስ የምትባል ወጣት ተአምር በሚመስል መልኩ ራኬቷን ስትጠቀምበት የሚያየው ተመልካች በአድናቆት እየጮኸ ነው ።
አሰልጣኟ ከርቀት ሆኖ አንዴ ተመላካቾቹን አንዴ ልጁን ያያል ።
እናም ከደቂቃዎች በኋላ ቬኒስ ዊሊያምስ ተጋጣሚዋን በሚገርም ብቃት አሸነፈች ።
.....
ያ ፡ ለልጆቹ ሲል ብዙ ስቃይ ያየው አሰልጣኝ ፡ የተደበደበው. ... ከቆሻሻ መጣያ ኳስ እየሰበሰበ ልጆቹን ያለማመደው አሰልጣኝ በአለም ዝነኛ በሆነው የሜዳ ቴኒስ ሜዳ. በዊምበልደን መድረክ ልጁን አቅፎ በደስታ አለቀሰ ።
.....
ከጥቂት ጊዜያት በኋላም ሌላኛዋ ሴት ልጁ በትልቅ መድረክ አሸንፋ ድል ተቀዳጀች ። ሪቻርድ በደስታ አለም ዞረበት ።
....
ሴሪና ዊሊያምስ እና ቬኒስ ዊሊያምስ በሜዳ ቴኒስ ስፖርቱ አለም ፡ ለአመታት ብቻቸውን ነገሱበት ።
 

....
ከአመታት በፊት በአርባ ሺህ ዶላር ሽልማት ለተደነቀው አባትና ፡ ለልጆቹ ሚሊዮን ዶላሮችን በየጊዜው ማፈስ ቀላል ነገር ሆነ ።
.....
እድለኛው አባት ለአመታት ጥረቱ ተሳክቶ ፡ ልጆቹን በቴኒሱ አለም የማይረሳ ስም እንዲኖራቸው አደረገ ።
.........



 
 
 

Friday, March 15, 2024

የዱባይ ከተማ ግዙፍ ፍሬም

 


አሮጌው ዱባይንና አዲሱን ዱባይ ለመለየት የተሰራው ግዙፍ ፍሬም ።

Wasihune Tesfaye

...
ይህ በአለም ተወዳዳሪ የሌለው ግዙፍ ፍሬም ፡ ከዋናው ( አዲሱ ) ዱባይ በ7 ኪ/ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አል ኪፋፍ በተባለው የከተማዋ ክፍል ይገኛል ።
....
ዱባዮች ይህንን የ150 ሜትር ቁመትና ፡ ወደጎን 90 ሜትር ስፋት ያለው ፡ በውስጡ ዘመናዊ ሊፍቶች የተገጠሙለትን የአለማችን ግዙፍ ፍሬም ሲሰሩ ያለምክንያት አልነበረም ።
....................
ብልህና አርቆ አሳቢዎቹ የዱባይ መሪዎች ፡ ገንዘብ እንደጉድ ሲጎርፍላቸው ያችን በበረሀ ላይ የነበረች ከተማቸውን መለወጥ ፈልገው ተነሱ ።
ይህን ሲያደርጉ ግን ያችን የድሮዋን ከተማ ቅርሶች እና ታሪካዊ ነገሮቿን ባጠቃላይ አፍርሰው ሳይሆን ፡ በትንሽ ኪሎ ሜትሮች ራቅ ብለው ነበር ።
 

.........
እና ያሰቡት ተሳክቶ ፡ ማመን በሚያስቸግር መልኩ ዱባይ በግዙፍ ህንጻዎች ተሞላች ።
ከዛስ. ...
ከተማዋን ለሚጎበኙ ቱሪስቶች የድሮዋን ዱባይን እና የአሁኗን ዱባይ መመልከት እንዲችሉ ይህንን ግዙፍ ፍሬም ገነቡ ።
አሁን እዚህ ፍሬም ላይ ወጥቶ መጎብኘት የቻለ ሰው ፡ ከወዲህ ፡ ያችን ጥንታዊ መደብሮች ፡ የቅመማ ቅመም ሱቆች ፡ ጥንታዊ ሙዚየሟን እና የጥንታዊቷ ዱባይ ገፅታን የሚያሳዩ አሮጌ ቤቶች ያሉባትን የድሮዋን ዱባይ እና ከወዲያ በኩል ደግሞ ቡርጅ ኻሊፋን እና መሰል ህንጻዎች ያሉባትን አዲሷን ዱባይ መመልከት ይችላል ።
 
 
......
ስለዱባይ ካነሳን አይቀር ፡ በቡርጅ ኻሊፋ ህንጻ ውስጥ ስለሚገኘው Burj Al Arab's Royal Suite ጥቂት ነገር እንበል ።
ይህ በህንጻው 25 ኛ ፎቅ ላይ የሚገኘው ፡ በአለም የቅንጦት ተብለው ከሚመደቡ ሆቴሎች መሀከል አንዱ የሆነው ሆቴል ፡ ከቅንጡነቱ የተነሳ ፡ የክፍሉ ኮርኒስ እና ግድግዳዎቹ ፡ በ24 ካራት ወርቅ የተለበጡ ናቸው ።
ይህ ብቻ አይደለም ፡ በነዚህ የቅንጦች ክፍሎች ውስጥ የሚገኘው ቴሌቪዥን ራሱ በ24 ካራት ወርቅ የተለበጠ ነው ።
 

.....
ወደ ፅሁፋችን መነሻ ስንመለስ ፡ አንድን ከተማ ፡ ዘመናዊ የሚያስብለው ፡ የነበረውን የድሮ ገፅታ እና የከተማዋ ታዋቂ ስፍራዎች፡ አፍርሶ በአዲስ በመተካት አይደለም ፡ ዱባዮች ከላይ ለንፅፅር ያመች ዘንድ እንዳየነው አይነት ግድግዳና ኮርኒሱ ወርቅ የሆነ ቤት መስራት ቢችሉም ያንን የትናንቱን ትውስታና ታሪክ ያለበትን አሮጌውን የከተማ ገፅታ ግን አልነኩትም ።
 
 

......
። የድሮው ለታሪክ ፡ ለትውስታ ፡ እና ለጎብኚዎች ተትቶ ከተማን አሮጌውና አዲሱ በማለት ከፍሎ እንዲህ እንደዱባዮች ማስቀመጥ ይቻል ነበር ።
.....
" በአንድ ወቅት ፒያሳ የሚባል ቦታ ነበር " ልንል በተቃረብንበት ጊዜ ላይ ሆነን በቁጭት የተጻፈ ❤️
photo - old dubai and new dubai

 

Tuesday, February 20, 2024

የካቲት12 ቀን 1929 የሰማዕታት ቀን

 

ወራሪዋ ጣልያን በአዲስ አበባ የፈጸመችው ጭፍጨፋ 

አርብ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም.

፨፨፨(የየካቲት 12) የሰማዕታት ሐውልት፨፨፨
መታሰቢያነቱ - ፋሽስት ጣሊያን በወገኖቻችን ላይ ላደረሰው መከራና በግፍ 
በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ለተጨፈጨፉ ኢትዮጵያውያን
የሐውልቱ ቀራጮች - አጉበቲን ሲች አንቶንና ከርሰኔች ፋራን 
የተባሉ የዩጎዝላቪያ ዜጎች ናቸው፡፡
ሐውልቱ የቆመበት ቦታ ዲያሜትር - 26 ሜትር
የሐውልቱ ቁመት - 28 ሜትር
መገኛ ሥፍራ - 6 ኪሎ

(ምንጭ ፡- ኅብረ ኢትዮጵያ ፣ ቴዎድሮስ በየነ)


 

“--አየህ! የዚያን ዕለት ብዙ ጣሊያኖች ብዙ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ወደ ማታ ገደማ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ስንገናኝ፣ ጓደኛዬ ቦምብ ስጥል የዋልሁበት እጄ ዝሏል ብሎ ነገረኝ። አንዱ ኢጣሊያዊ ሲያጫውተኝ፣ ባንዲት ትንሽ ጣሳ በያዝኳት ቤንዚን አስር ቤቶች አቃጠልኩበት አለኝ፤ በዋናው ጦርነት ጊዜ ጥይት ተኩሰው የማያውቁት ጣሊያኖች ሁሉ በዚያን ቀን ሲተኩሱ ዋሉ--”

           ይህ አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ኢጣሊያዊ፣ ለጓደኛው ለሲኞር ዲሰማን የነገረውና  የታሪክ ጸሐፊው አንጄሎ ዲል ቦኮ የመዘገበው ሲሆን ደራሲ ጳውሎስ ኞኞም  “ኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት; በተባለው መጽሐፉ ታሪኩን ለእኛ አድርሶታል። የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላይ፣ በጣሊያን ወታደሮች የተፈጸመው ጭፍጨፋ ታሪክ ቀርቧል፤ በመጽሐፉ፡፡ በዚህ ወቅት በመዲናዋ  ለሦስት ተከታታይ ቀናት በጣልያን ጨካኝ ወታደሮች በተካሄደው ጭፍጨፋ፣ 30 ሺህ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል፡፡ አንዳንዶች ይህ ቁጥር የሚታመን ነውን? የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ጥያቄውን ለመመለስ ከላይ የተጠቀሰውን ምስክርነት ይዘን፣ በወቅቱ በአዲስ አበባ የከተመውን የጣሊያን የጦር ሰራዊት ክምችት መመልከት ተገቢ ይሆናል።
ጳውሎስ ኞኞ፣  በወቅቱ የነበረውን የጣሊያን የወታደር ኃይል በመጽሐፉ ሲገልጽ፤ “35ሺ የጣሊያን ሜትሮ ፖሊታንት (የከተማው ወታደሮች)፣ 40ሺ ባለ ጥቁር ሸሚዝ ሚሊሺያ፣ 3ሺ የሊቢያ ተወላጅ ወታደሮች፣ 5ሺ የኤርትራ ወታደሮች ነበሩ፡፡; ብሏል፡፡ በተጨማሪም #የኤርትራ ተወላጅ ወታደሮች፤ “እኛ ወታደሮች ነን፤ መሳሪያ በሌለውና በሴት ላይ አንተኩስም” በማለታቸው ብዙዎቹ በሰፈራቸው ውስጥ ተገደሉ” ሲልም አክሎ ጽፏል፡፡ ከዚህ አንጻር 78ሺ የሚሆነውን የጣሊያን ሠራዊት፣ በጭፍጨፋው ላይ ከማሰማራት የሚያግደው ነገር አልነበረም፡፡
የኒፒልስ ልዕልት መውለዷን ምክንያት በማድረግ ጀኔራል ግራዚያኒ፣ ለድሆች ምፅዋት ለመስጠት በገነት ልዑል ቤተ መንግሥት፣ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ፣ ድሆች  እንዲሰበሰቡ ጥሪ አድርጎ ነበር።   እስከ እኩለ ቀን ባለው ጊዜም ሶስት ሺህ የሚሆኑ ድሆች ተሰበሰቡ፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ ሰላሳ የሚሆኑ የጣሊያን ከፍተኛ ሹማምንቶች ተገኝተዋል፡፡ ይህን አጋጣሚ ራሳቸውን እያዘጋጁ ይጠብቁ የነበሩት አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም፣ ከነሱ ጀርባ የተሰለፉት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴን ጨምሮ፣ ብዙዎች ጄኔራል ግራዚያኒን በመግደል፣ የጣሊያንን የወራሪነት ቅስም ለመስበር ቆርጠው ተነሱ፡፡ ጄኔራል  ግራዚያኒ፣ ለድሆችና በቦታው ለተገኙ ሰዎች ንግግር እያደረገ እያለ፣ እነ አብርሃም አከታትለው የእጅ ቦንብ ወረወሩ፡፡ ግራዚያኒ  ጀርባው ላይ ተመታ፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጣሊያናዊው ጎይዶ ክርስቴና ሌሎች ሰላሳ ሰዎችም ቆሰሉ፡፡ ከሚወረወረው ቦምብ ለማምለጥ መሬት ላይ ተኝተው የነበሩት ከርቤጌሮች ከተኙበት ተነስተው ተኩስ ከፈቱ፡፡ ያገኙትን አበሻ ሁሉ እንዲገድሉ ከንቲባ ጐይዶ ክርስቴ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ የጣሊያን ሹፌሮች ሳይቀሩ በአዲስ አበባ ከተማ እየተዟዟሩ ሕዝቡን ፈጁት፡፡ የቤተ መንግሥቱ ዙሪያ መንገዶች በሬሳ ተሞሉ። የመዲናዋ ቤቶች ከነዋሪዎቹ ጋር በእሳት ነደዱ፡፡ ነፍሳቸውን ለማትረፍ የሚሞክሩ ሰዎች እየተያዙ፣ ቤት እየተዘጋባቸው እንዲቃጠሉ ተደረገ፡፡ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው በዚህ ጭፍጨፋ፣ ሰላሳ ሺህ ሰዎች እንደተገደሉ ነው የተመዘገበው፡፡  
እኔ በዚህ ቁጥር አልስማማም፡፡ መግቢያው ላይ ያሰፈርኩትን ምስክርነት ይዞ ነገሩን የሚገመግም ሰውም ይስማማል ብዬ አልጠብቅም፡፡ ከጣሊያን ጦር ውስጥ ከ15ሺ እስከ 20ሺ  የሚሆነው ለሰፈር ጥበቃ እንዲቀር ቢደረግና  ቀሪው ሃምሳ ሺህ ወታደር እንኳን አንድ አንድ ሰው ቢገድል፣ ያለ ጥርጥር  የተጨፈጨፉት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ሃምሳ ሺህ ይደርሳል፡፡ 


አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአንድ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩ የዓይን ምስክርን አነጋግሮ፣ የሟቾቹ  ቁጥር ከሀምሳ ሺህ እስከ ሰማኒያ ሺህ ሊደርሱ እንደሚችሉ በመጠቆም መዘገቡን አስታውሳለሁ። እኒህ ሰው እንደተባለው ጭፍጨፋው በሦስት ቀናት ውስጥ አለመቆሙንና ለወር ያህል መዝለቁንም ተናግረዋል፡፡  ከዚህ አንጻር የየካቲት ሰማዕታት ቁጥር 30 ሺህ ነው ማለት ትክክል አይመስለኝም፡፡ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት እልቂትም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ የየካቲት 12 አንድ ገጽታ ነውና፡፡
ከሃምሳ ሺህ ሰዎች በላይ የተጨፈጨፉበት፣ ከአስር ሺህ በላይ ደግሞ ደናኔ ተወስደው በእስርና በበሽታ እንዲያለቁ የተደረገበት የየካቲት 12 ቀን መስዋዕትነት በከንቱ አልቀረም፡፡ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ለኢጣሊያ መንግሥት አልገዛም በማለታቸው፣ በአደባባይ በጥይት ተደብድበው በተገደሉት በአቡነ ጴጥሮስ ሞት ያኮረፈውን የአዲስ አበባን ነዋሪ፣ በየካቲት 12 ጭፍጨፋ፣ ጨርሶ ልቡ እንዲቆርጥና እንዲነሳሳ አድርጎታል። እጅግ የሚበዛውም ፊቱን ወደ አርበኝነት አዞረ፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሳይቀር ለነፃነት በሚደረገው ትግል፣ የውስጥ አርበኛው እየተናበበ ሔደ፡፡
እንደ ሚያዚያ 27 የድል ቀን ሁሉ፣ በየዓመቱ ብሔራዊ በዓል ሆኖ ሲከበር የነበረው የየካቲት 12 ሰማዕታት ቀን፣ እየታሰበ መዋል ከጀመረ አርባ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት አንድም የመንግሥት ባለሥልጣንም ሆነ መንግሥት ወደ ቀድሞ ክብሩ ሊመልሰው አልቻለም፡፡  
“ኢትዮጵያ የቆመችው በልጆቿ መስዋዕትነት ነው; እያልን እንዴት  ዓመታዊ  የሰማዕታት ቀን አይኖረንም?
ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ድረስ በዱር በገደሉ ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ነፃነታችን ተከብሮ እንዲቆይ ያደረጉ የአምስት ዓመቱ አርበኞች፣ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ሰማዕት ናቸው፡፡
ሁለት ጊዜ የተቃጣውን የሞቃዲሾ ወረራ የመከቱ፣ የተጣሰውን ድንበር ያስከበሩና የሀገር ታሪክ እንዳይደፈር የተሰዉ ወገኖቻችን ሰማዕቶቻችን ናቸው፡፡
የጦርነቱ ምክንያት በግልጽ ባይታወቅም፣ ከኤርትራ ጋር በተቀሰቀሰው ጦርነት፣ ከአካል እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ወገኖቻችን ለሀገራችን ሰማዕት ናቸው፡፡
 ሰማዕታት ትናንትም ዛሬም አሉን፤ነገም መስዋዕትነት የሚከፍሉና ሰማዕታት የሚሆኑ ወገኖቻችንን  የምንዘክርበት የሰማዕታት ቀን የሚኖረን መቼ ነው? ሺህ ጊዜ የሚነሳ ጥያቄ! 

                              ስድስት ኪሎ የሚገኘው የካቲት 12 የሰማዕታት ሃውልት ላይ

https://www.addisadmassnews.com/ 

Written by  አያሌው አስረስ Saturday, 20 February 2021

***********

የካቲት 12 እና የግራዚያኒ አዲስ አበባ

ህላዊ ሰውነት በሻህ (አርኪቴክት)
Helawi Sewnet Beshah (Architect) 
ጣሊያን ኢትዮጵያ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ወረራ አድርጎ ለአምስት አመት በተቆጣጠረበት ወቅት 1929 ዓ.ም. በየካቲት 12 እለተ አርብ ነበር። የአጼ ሀይለስላሴን ወደ እንግሊዝ መሰደድ ተከትሎ እና የሙሶሊኒን የቅኝ ግዛት ህልም እንዲያሳካ የኢትዮጵያ አስተዳዳሪ ሆኖ የተሾመው ግራዚያኒ፣ የኔፕልሱን ልዑል መወለድ አስመልክቶ ለችግርተኛ ቤተሰቦች ገንዘብ እሰጣለሁ ብሎ በገነተ ልዑል ቤተመንግስት (የዛሬው አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስድስት ኪሎ ግቢ) በርካታ እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች እንዲሰበሰቡ አዘዘ። ከተጋባዥ እንግዶቹም መካከል የጣልያን ሹማምንት የሜትሮፖሊታን ጳጳስ አቡነ ኪርል እና ሌሎች የኢትዮጵያ መኳንንቶች ተገኝተው ነበር።

ብራማ በነበረችው በዛች የወረሃ የካቲት አርብ የተገኙትም ኢትዮጵያውያን ከጠዋት ጀምረው አንድ በአንድ ቤተመንግስቱ ግቢ መሰብሰብ ጀመሩ። እስከረፋዱም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሶስት ሺህ ያህል ነዋሪዎች በተገኙበት የግራዚያኒ መረሃ ግብር ተጀመረ። የዕለቱ አጀማመር ሲታይ ሊመጣ ያለውን የሀዘን ድባብ የገመተ ሰው ይኖራል ብሎ ለማሰብ ያዳግታል። ጥቂት ቆይቶ እኩለ ቀን ገደማ ሊሆን አካባቢ በዋናው በር በኩል ቦንብ ፈነዳ፣ ሁለተኛም ፈነዳ። ገነተ ልዑል ቤተመንግስት ከየአቅጣጫው ጩኸት አስተጋባ። ሶስተኛ ቦብም ግራዚያኒ እና መኳንንቱ ከተቀመጡበት ጠረጴዛ አጠገብ ሲወረወር ግራዚያኒ ጠረጴዛ ስር ወደቀ። የተወሰኑ የጣልያኖቹን ሹማምንት መታ።

ቦምቡን የጣለው ከጣልያኖቹ ዘንድ በአስተርጉዋሚነት ይሰራ የነበረ አብርሃ ደቦጭ እና ጓደኛው ሞገስ አስገዶም የሚባሉ የኤርትራ ክፍለሀገር ተወላጅ ወጣቶች ነበሩ። በጥቅሉ ሰባት ቦምቦች ፈነዱ። ወዲያው ካርቴሲ ወደኢትዮጵያውያኑ መኩዋንንት ሽጉጡን አነጣጥሮ የመጀመሪያዋን አንድ ጥይት ተኮሰ። ካራ ቢኔሬዎችም (የጣሊያን የሲቪል ጠባቂዎች) ምሳሌውን ተከተሉ። በጥቂት ጊዜ ውስጥም ሶስት መቶ ሬሳዎች በዛ ግቢ ውስጥ ተከመሩ። ሀይለኛና ተገቢ ያልሆነ ጭፍጨፋ ነበር። ሽማግሌዎች፣ አይነስውራን፣ እግር የሌላቸው ለማኞች፣ ድሆች እናቶች እስከልጆቻቸው ነበሩበት። ሰላሳ ያህል ሰዎች ቆሰሉ። ለሶስት ሰአታት ያህል ያለቋረጥ በግቢው ውስጥ ተኩስ ተከፈተ። ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ባለጥቁር ሸሚዞች፣ የጣልያን ሾፌሮች የቅኝ ግዛቱ ወታደሮች በአዲስ አበባ ከተማ እየዞሩ ህዝቡን ይፈጁት ጀመር።

እዚህ ቀን ላይ እንዴት ተደረሰ የሚለውን ታሪካዊ ዳራ ወደኋላ መለስ ብለን እንመልከት። አውሮፓውያን በ1877 ዓ.ም. በጀርመን በርሊኑ ኮንፈረንስ ተገናኝተው አፍሪካን አንደቅርጫ ከተከፋፈሏት ከ11 ዓመታት በኋላ ጣልያን ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ስትመጣ አድዋ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ድል ትደረጋለች። አንድ ትውልድ አልፎ ከአርባ አመታት ቆይታ በኋላ በስልጣን ላይ የነበረው የጣልያኑ ፋሽስት ሙሶሎኒ የአድዋን ቁጭት ባለመርሳቱ ከበቀል ጋር ዘመናዊ የሆነ የአየርና የምድር ጦሩን ይዞ ኢትዮጵያ በድጋሚ መጣ። በዚህ ወቅት የጣሊያን ጦር ለኢትዮጵያ ሰራዊት ብርቱ ስለሆነበት አጼ ሃይለስላሴ በሚያዝያ (May 2, 1936) ጠዋት ከአገር ይሰደዳሉ። የጣሊያኑ ሙሶሊኒም ኢትዮጵያን በስተመጨረሻ በእጁ እንዳስገባ በሮማ ለተሰበሰበው ህዝቡ በደስታ አዋጁን አሰማ።

የኢትዮጵያን ጦር ማይጨው ላይ መሸነፍ እና እንዲሁም የንጉሱን ከአገር መውጣት ተከትሎ የጣሊያኑ አስተዳደር አዲስ አበባ እስኪገባ ድረስ በመሀል በተፈጠረው ክፍተት መዲናዋ ክፉኛ በተደራጁ ሌቦች ተዘረፈች፣ ጣሊያኖቹ እንዳይጠቀሙ በሚል ብዙ ህንጻዎችም በግለሰቦች ተቃጠሉ፣ ፈረሱ። ሙሶሊኒ ከጣሊያን በሰጠው ቀጥተኛ ትእዛዝ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የቅጣት እርምጃ አስወሰደ። ጉዳት የደረሰባት አዲስ አበባም ለወራሪዎቹ መልካም አቀባበል ያደረገች ምቹ ከተማ አልሆነችላቸውም። የጣሊያኑ ኮማንደር ባዶግሊዮ ወዲያውኑ ለሮም በላከው ቴሌግራም ላይ ሙሶሊኒ ወደኢትዮጵያ በስድስት ወራት ውስጥ ሊልካቸው ያሉትን የጣሊያናዊ ቤተሰቦች ዕቅድ ትንሽ እንዲቆጥበው መልዕክቱን አደረሰ። አዲስ አበባም የአዲሱ የፋሺስት ግዛት መዲና የመሆኗ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አነጋጋሪ ሆነ።

የጣሊያንን መንግስት ከሚያማክሩት ባለሙያዎች ውስጥ አብዛኞቹ አዲስ አበባን መዲና አድርጎ ማስቀጠል ስህተት እንደሚሆን አስጠነቀቁ። በሸለቆዎች የተሰነጣጠቀው ተራራና ኮረብታማ የመልከአ ምድሯ አቀማመጥና ከፍታማነት አድካሚ እና ለጉልበት ስራ አዳጋች እንደሚሆንባቸው እንዲሁም ዘርዘር ያለው የከተማዋ አሰፋፈር ለትራንስፖርት ፈተና እንደሚሆን ቅሬታዎች ቀረቡ። የአፈሩ ባህሪ ተንሸራታችነት ለመሰረት ግንባታ የሚኖረው ተግዳሮት እንዲሁም የነበረው በርካታ የባህር ዛፍ ደን ለኢትዮጵያ ሽፍቶችና ታጋዮች ምሽግ እንደሚሆን ጣሊያኖቹ ሰጉ። ከሁሉም በላይ ግን በአዲስ አበባ የነበረው ብዝሃ ጥቁር አፍሪካዊና ኢትዮጵያዊ ህዝብን አፈናቅሎ ወደሌላ ቦታ ለማስፈርና የቅኝ ገዢዎቹን የመከፋፈል ፖሊሲ ለማራመድ ፈተና እንደሚሆንና እንደፋሺስቱ አመለካከት ከአገሬው ተወላጅ አሻራ የጸዳ አዲስ ከተማ መቆርቆር እንደሚያስፈልግ አመላከቱ። ለአዲስ መዲናነት ደሴ፣ ሞጆ፣ ነቀምት እና ሐረር እንደ አማራጭነት ቀረቡ። ነገር ግን በሙሶሊኒ እይታ ከአዲስ አበባ ውጪ የሆነ የዋና ከተማ ሀይሉን እና ክብሩን ለማሳየት በፍጹም አማራጭ እንደማይሆን ከለንደኑ ዴይሊ ቴሌግራፍ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ይፋ ቢያደርግም ብዙ የቅኝ ግዛት ሹማምንቶቹ ሀሳቡን ይቀይራል የሚል ተስፋ ነበራቸው።

በመጀመሪያዎቹ ወራት የፋሽስቱ አስተዳደር የህዝብ የመንገድ ዳር ምልክቶች በጣልያንኛ ተተርጉመው እንዲጻፉ ተደረገ። የዋና ጎዳናዎች ስሞችም በሙሶሊኒ መንግስት ውስጥ በነበሩ አንዳንድ አመራሮች ስም ተሰየሙ። በየቦታውም ሆነ በየቤቱ የሙሶሊኒ ምስል እና በአንዳንድ ቦታዎች ለህዝቡ ፕሮፖጋንዳ የሚያስተላልፉ የድምጽ ማጉያዎች ተሰቀሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ፋሺስቶቹ ከኢትዮጵያ ነጻነት ጋር የተያያዙ ምስሎች እና ሀውልቶችን ማስወገድ ላይ ተጠመዱ። ከነዚህም ውስጥ አራዳ ጊዮርጊስ አደባባይ ላይ የሚገኘው የምንሊክ ፈረስ ጋላቢ ሀውልት፣ ታላቁ ቤተመንግስት አጠገብ ያለው የባእታ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው የምኒሊክ መቃብር፣ ለገሀር ባቡር ጣቢያ ፊት ለፊት የቆመው የይሁዳ አንበሳ ሀውልት፣ በወቅቱ አዲስ አበባ ላይ የነበረ የአክሱም ሀውልት አምሳያ፣ የስላሴ ኮኮብ ሀውልት፣ እና በርካታ በወቅቱና ቀደምት የነበሩ መሪዎች ምስሎችን ያካትታል። ሙሶሊኒም በቴሌግራፍ በላከው መልዕክት “የምኒሊክ ሀውልትን መፈንዳት ይኖርበታል” ሲል አቅጣጫውን አስቀመጠ።

በወቅቱ የአገሪቱ ተጠባባቂ ገዢ ሆኖ ወደአዲስ አበባ የመጣውና በቅጽል ስሙ “የሊቢያ ጅብ” በመባል ይታወቅ የነበረው የቀድሞ ወታደሩ ግራዚያኒ ከሀውልቶቹ ጋር ተያይዞ የተሰጠውን ትዕዛዝ ለመፈጸም በማቅማማት ለጣልያኑ የቅኝ ግዛቶች ሚንስትር እንዲህ የሚል ቴሌግራፍ መልዕክት ላከ። “አዲስ አበባ እንደመጣሁ የምኒሊክ እና የይሁዳ አንበሳ ሐውልት አልተነሱም ነበር፤ ማንም የክቡርነትዎን ትዕዛዝም አላስተላለፈልኝም ነበር። ነገር ግን አሁን እንዲህ አይነቱ እርምጃ ማስተዋል ያለበት አይመስለኝም፣ በተለይ ተከትሎኝ ከመጣው መጥፎ ስሜ አንጻር። እናም ስኬታማ የሆነ ፖለቲካዊ ውጤት የማመጣ ከሆነ የበረደ አካሄድ መከተል ይኖርብኛል፤ በተለይ የዚህ አይነቱ እርምጃ ከሚነጥለን ከቤተክህነት ጋር፣” በማለት ስጋቱን ገለጸ።

በእንደዚህ አይነት ምክንያት ያልተደነቀው ሙሶሊኒ፣ ውሳኔው በአፋጣኝ እንዲፈጸምለት በድጋሚ ስላዘዘ በሀያ አራት ሰዐት ውስጥ የምኒሊክን እና የይሁዳ አንበሳን ሐውልት እንድታነሳ የሚል ትዕዛዝ ለግራዚያኒ በቴሌግራፍ ደረሰው። ከእንደዚህ አይነት ዱብ እዳ ጋር የተጋፈጠው ግራዚያኒ ትዕዛዙን እንደሚፈጽም ነገር ግን ጊዜ እንደሚያስፈልገው ጠቅሶ ለቅኝ ግዛት ሚንስትር ድኤታው ጻፈ። “እለምንዎታለሁ ክቡርነትዎ፤ የሚንስትሩን ትዕዛዝ እንደምፈጽም ያረጋግጡልኝ። ነገር ግን ሁለቱም ሀውልቶች በርካታ ቶን የሚመዝኑ እንደመሆናቸው፣ ከቆሙበት የማንሳቱ ስራ ባለሙያዎችን እና በርካታ ቀናት ይፈልጋል፣” ሲል በድጋሚ ተማጸነ። ከበርካታ ወራት በኋላ ስራው በጥቅምት 6 ሌሊት ላይ ተጠናቀቀ።

ኢትዮጵያውያኑ ከእንቅልፋቸው ተነስተው የምኒሊክን ሀውልት መነሳት ሲያዩ እጅግ ተቆጡ። በአደባባይ ላይ በርካቶች በእንባ ተራጩ። “ምኒሊክን አበቃ። በሌሊት ሰረቁት” ሲሉ አለቀሱ። ህዝቡ ሲሰበሰብ የጣሊያን ወታደሮች በሳንጃ ያባርሯቸው ጀመር። ይህም የሀውልቶቹን መነሳት ተከትሎ የተፈጠረው የኢትዮጵያውያኑ ፀረ ፋሽስት ተአማኒ ስሜት ዜና የጣሊያን መንግስት ጋር ደርሶ ብስጭት ፈጠረ። ግራዚያኒም ከሳምንታት በኋላ በእርምጃ እንደተቆጣጠረው አሳወቀ። በወቅቱ የነበረ አንድ ስዊድናዊ ከአመት በኋላ እንደተናገረው፣ ኢትዮጵያውያኑ እርስ በእርሳቸው ስለጣሊያኖቹ “መንፈሱን እራሱ ይፈሩታል። አድዋን እኛ እንደምናስታውሰው ነው የሚያስታውሱት፤” እያሉ እንደሚንሾካሾኩ ምልከታውን ገልጿል። የኢትዮጵያውያኑም ተቃውሞ እና ትግል በየቦታው ቀጠለ።

እናም በዚህ ሁኔታ ከወራት በኋላ አብርሃና ሞገስ በዳግማዊ ምንሊክ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ለመከታተል የመጡት። አብርሃ በጽኑ የጣሊያኖቹን ዘረኛ ተግባራት ይቃወም ስለነበር ትግሉን ተቀላቅሎ ግራዚያኒን ከግብረአበሮቹ ጋር ለመግደል ሙከራ ያደረገው። በግራዚያኒም አጸፋ ሰላሳ ሺህ ያህል ንጹሀን ተገደሉ፤ ክስተቱም በኢትዮጵያ ታሪክ እጅግ አስከፊ የነበረ ጭፍጨፋ ሆነ።

ለማጠቃለል፣ አዲስ አበባ ከአድዋ ድል ማግስት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎችና ከውጭ ሀገራት በመምጣት ሀብትና ንብረት አፍርቶ እየኖረ የነበረው እንዲሁም በከተማዋ እየተበራከተ በመጣውና በተለያዩ የንግድ እና የማህበራዊ አገልግሎት ስራ መስኮች ላይ በተሰማራው የከተማዋ ነዋሪ ቅሬታ አማካኝነት አጼ ምኒሊክ ወደ አዲስ አለም ከተማ ሄዶ አዲስ መዲና የመቆርቆር እቅዳቸውን ሊቀለበስ ችሎ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታም፣ ከአርባ አመት በኋላ የጣሊያን መንግስት ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ፣ በርካታ የሙሶሊኒ መንግስት አማካሪዎች አዲስ አበባን ትተው አዲስ ከተማ እንዲቆረቆር ቢጎተጉቱትም ሙሶሊኒ አሻፈረኝ በማለቱ አዲስ አበባም አሁን ላለችበት ትሩፋትና ማንነት የካቲት 12 እና በወቅቱ የነበረው የግራዚያኒ አስተዳደር የራሱን አሻራ ጥሎ ሊሄድ ችሏል። ለዚህም ነው የከተማ ቅርስ ስላለፈው ታሪካችን፣ ባህላችን እና ስለማህበረሰባችን ዝግመተ ለውጥ ፍንጮች የሚሰጠን መስኮት ነው የምንለው። ቸር እንሰንብት!

https://ketemajournal.com/issue/

*******************************

ምላሹ የዘገየው የኢትዮጵያዊያን የካሳ እና ይቅርታ ጥያቄ ፣ወደ ቫቲካን ሰዎች

ከያኔው ገነተ-ልዑል ቤተመንግስት፣ከዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዝቅ ብሎ ኢትዮጵያ መቼም የማትዘነጋውን የእልቂት ቀን የሚዘክር ባለ 28 ሜትር ሃውልት አለ፡፡

በያመቱ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ስፍራ የካቲት 12 ቀን ይሰበሰባሉ፡፡አባት እና እናት አርበኞች "እመ-ሰቆቃ" ግራዚያኒን በቀረርቶ ያወግዛሉ፣አምስት አመት ጣልያን ታግለው ለሀገሪቱ ዳግም ነጻነትን ያመጡትን ጀግኖች እያነሳሱ በፉከራ ያሞግሳሉ፡፡አንዳንዶቹ ደግሞ የዚህ ሁሉ በደል ፈጻሚ ሀገር መቼ ይሆን ይፋዊ ይቅርታ የምትጠይቀው? እጃቸው ያለበት አካላትስ የካሳ ከረጢታቸው መቼ ይሆን የሚፈታው ? ሲሉ ከንፈራቸውን ይነክሳሉ ::

የካሳ እና ይቅርታ ዘመቻ ወደ ቫቲካን ሰዎች

የሙዚቃ መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀ የማርሽ ባንድ ሰራዊት፣ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የመጡ ብላቴናዎች ክያኔ፣ለዝክር የመጣው ሰው ስነ-ስርዓቱ ካለቀ በኋላ ቤቱ ገብቶ የሚያወራው አዲስ ነገር አሳጥተውት አያውቁም፡፡

የ2002 ዓመተ ምህረቱ የሰማዕታት ቀን ማግስት አዲስ ነገርን በተመለከተ በአያሌው ዕድለኛ ሳይሆን አልቀረም፡፡

አዲስ አበባ ጀግኖችን አሞግሳ ፤ለሰማዕታት የነፍስ ይማር ጸሎት አድርሳ በተመለሰች ማግስት፣ የካቲት 29-2002 ዓ.ም ፣ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ‹ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ› የተሰኘ ተቋም በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ትብብር የሚጠይቅ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ይፋ አደረገ።

የዘመቻውን ይዘት ከሚያብራራው ጥራዝ ላይ ትንሽ እንቆንጥር፣

"በ1935-41(እኤአ) ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወርራ ባደረሰችው አሰቃቂ የጦር ወንጀል፣ የቫቲካን መንግስት እጅ ከጓንት ሆና ተባባሪ ስለነበረች፤የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ ተጽዕኖ እንዲደረግባት ፣ለዓለማቀፋዊው ህብረተሰብ ፣በዓለም ላሉ መንግስታት ሁሉ ፣ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፤ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣….ለሌሎች ለሚመለከታቸው ድርጅቶችና ለእውነት ለቆሙ ህዝቦች ድጋፋቸውን እንዲያበረክቱ አቤቱታችንን በታላቅ ትህትና እናቀርባለን፡፡"

የዘመቻው ተጽዕኖ ውጤታማ ይሆን ዘንድ፣ 100ሺ ሰዎች ፊርማቸውን እንዲያኖሩ ተቋሙ በወቅቱ ጠይቋል።

ስምንት ዓመታት አለፉ፣ዘመቻውን የተቀላቀሉ ሰዎች ቁጥር 7ሺ አልሞላም፣ቫቲካንም ይቅርታ አልጠየቀችም።

የቫቲካን ዝምታ …የአረጋዊው ቁጭት

ዘመቻው ይፋ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በየአደባባዩ ብቅ እያሉ የዘመቻውን አስፈላጊነት ለማስረዳት ሲለፉ የሚታዩ አረጋዊ አሉ። እኝህ ሰው "ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ" የተሰኘው ተቋም ሀላፊ ኪዳኔ ዓለማየሁ ናቸው ፡፡

የታለመው የፈራሚ ብዛት ካለመስመሩ ጎን ለጎን፣ ቫቲካን ካለወትዋች እስከአሁን ኢትጵያዊያንን ይቅርታ አለመጠየቋ አይወጥላቸውም ፣"ናዚዎች በአይሁዶች ላይ እልቂት ሲፈጽሙ ቫቲካን ዝም በማለቷ ብቻ በክርስቲያናዊ ትህትና አይሁዶችን ይቅርታ ጠይቃለች ፣" ሲሉ የሚያነሱት አቶ ኪዳኔ ፣« እንደ ክርስቲያን ድርጅት ለፈፀሙት የወንጀል ተባባሪነት ይቅርታ መጠየቅ አይበዛባቸውም። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገር ስለሆነች ይሆን ወደኃላ የሚሉት?ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው፣›› ሲሉ ጥያቄ ይመዛሉ፡፡

የተቋማቸውን ስልክ የመታ ሰው ከሚነሳቸው ጥያቄዎች አንዱ ቫቲካን በኢትዮጵያዊያን እልቂት ውስጥ ያላት ተሳትፎ ምን ያህል ነው? የሚል ነው፡፡ ከሌላኛው ጫፍ ብዙ ጊዜ የማይጠፉት አቶ ኪዳኔ የቫቲካንን ተሳትፎ ፤ የይቅርታውን አስፈላጊነት ለማስረዳት አይታክቱም።

"ፋሽስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ብዙ ወንጀሎች ተፈፅመዋል። አንድ ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ተጨፍጭፈዋል፣ከዚያ ውስጥ በአዲስ አበባ በሶስት ቀናት ብቻ 30ሺ ሰዎች ተጨፍጭፈዋል፣ ከ2ሺ በላይ ቤተ-ክርስቲያኖችና 525ሺ ቤቶች ወድመዋል። ፋሽስት ጣልያኖች ብዙ ዝርፊያ፣ስደት እና እንግልት በኢትዮጵያዊያን ላይ አድርሰዋል።እንዲያ በሚሆንበት ጊዜ ቫቲካኖች ፋሽስት ጣልያኖችን ደግፈዋል፣ባርከዋል ቀድሰዋል፣" ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።

አቶ ኪዳኔ ዓለማየሁ ከታሪክ አዋቂዎች፣ ከንጉሳዊያን ቤተሰቦች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በመሆን ያቋቋሙት ተቋም፣ ቫቲካን ይቅርታ ትጠይቅ ዘንድ የሚለፋው -ይቅርታው ለኢትዮጵያዊያን ስነልቦናዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ካሳን ብሎም ዓለማቀፋዊ ዕውቅና እንደሚያመጣ በማመን እንደሆነ ያብራራሉ።

በተቀናጀ ዘመቻ አቤቱታቸውን ያሰሙ ህዝቦች ለተገቢ ካሳ መብቃታቸውንም ለአብነት ይዘረዝራሉ፣"ጣልያኖች 30ሺ ሊቢያዊያንን በመጨፍጨፋቸው ፣ለዚህ አድራጎታቸው 5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ካሳ (በልማት ስራ መልኩ) ለመክፈል ተስማምተዋል፣" በማለት ካለመናገር ደጅ አዝማችነታችን እንዴት እንደተነፈገ ያሰምራሉ፡፡

ይሄ ዘመቻ እንደ ኢትዮጵያ መንግስት እና የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ያሉትን ተቋማት ድጋፍ ቢያገኝ ኖሮ ውጤቱ ይፈጥን እንደነበረ የሚያነሳሱት አቶ ኪዳኔ ፣ዘመቻው ከታለመው የፈራሚዎች ቁጥር እስከ አሁን ድረስ አንድ አስረኛውን አለማግኘቱ የፈጠረባቸውን ቅሬታ አይሸሸጉም፡፡

"ዲፕሎማሲን " የሚመክረው የአርበኞች ማህበር

"በደም እና አጥንት ግብር " ሀገራቸውን ያቆዩ እናትና አባት አርበኞች ያቋቋሙት "የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር" በስምንት ዓመታት ውስጥ የተለያዩ ለውጦችን አስተናግዷል፡፡

ጥቂት የማይባሉት አባላቱን በሞት ተለይተዋል፣ የአስተዳደር ሽግሽግም ተፈጽሟል፡፡ የዛሬ ስምንት ዓመት ማህበሩን ይመሩ የነበሩት ሊቀ-ትጉሃን አስታጥቄ አባተ -በልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ተተክተዋል፡፡እንደነበር ከቀጠሉት አንዱ ወኔ ይመስላል፣በማህበሩ መሪ ድምጸት ውስጥ እንደሚሰማው ያለ፣

"የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የኢትዮጵያ ንብረት የሆነ ሚስማር ጭምር ያለአግባብ ሄዶ እንደሆነ 'ወደ ሀገሩ መመለስ አለበት' የሚል ፅኑ የሆነ፣ የማያወላውል አቋም አለው ፣" ይላሉ ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የቫቲካን እና የይቅርታው ጉዳይ ሲነሳ፣ የጋለ ድምጸታቸው መልሶ ይሰክንና በተጀመረው አይነት መንገድ ካሳ እና ይቅርታን የመጠየቅ ሂደት ውስጥ ማህበራቸው ሊሳተፍ እንደማይችል ይናገራሉ። ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ማህበሩ የተመሰረተበት ህግና ደንብ ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት ዘመቻ ለመከወን የማያስችል መሆኑ ነው።

ከሁሉም ከሁሉም ግን የማህበሩ ፕሬዚደንት በግለሰቦች አስተባባሪነት እዚህ የደረሰው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ውጤታማ ስለመሆኑ ጥርጣሬ አላቸው።በጋርዮሽ ተፅዕኖ የመፍጠር ሙከራ ይልቅ በመንግስታት መካከል የሚደረግ ንግግር ፍቱን መፍትሄ እንደሚያመጣ ለማሳየት ባቀደ መልኩ፣ "የአክሱምን ሀውልት የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ሄዶ አላመጣውም … ዲፕሎማሲ እንጂ" ይላሉ፡፡

ቫቲካን 'አላት'የሚባለውን የግፍ ተሳትፎንም ልጅ ዳንኤል ጆቴ ይጠራጠሩታል፣ "እኛ እንደምንረዳው( የጣልያንን ጦር) ባርኮ የላከው ሚላኖ ላይ የነበረ ቄስ ነው። የአቶ ዘውዴ ረታን መፅሃፍ ላይ ራሱን የቻለ ታሪካዊ መግለጫ አለው(አቶ ዘውዴ ረታ አምባሳደር በነበሩበት ወቅት ተመራምረው እና ጥናት አድርገው የፃፉት መፅሃፍ ነው)። አንዳንድ ታሪኮችን በስሜታዊነት ተነስቶ ከማየት ርቀን፣ አንስተን እና አውርደን በደንብ ተዘጋጅተን የቀረብን ጊዜ ጣልያኖችም ሆነ እንግሊዞች ነገሮችን የማይመልሱበት ፣የተጠየቁትን የማያደርጉበት ምንም ምክንያት የለም፣"ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር በዘመቻው ላይ ያለውን የፍሬ ነገር ጥርጣሬ ያጋራሉ፡፡ 

"የኢትዮጵያ አምላክ፣ይረዳናል!"

በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው ‹ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ› ሃላፊ ኪዳኔ ዓለማየሁ ድምጽ ውስጥ ሀዘን ተጠልሏል፡፡በልጅ ዳንኤል ጆቴ በኩል የተሰጠው ምላሽ እንዳልተዋጠላቸው ያሳብቃል፡፡

"ለፍትህ ጉዳይ ሁላችንም ሃላፊነት አለብን።እንኳን እኛ ኢትዮጵያዊያኑ ይቅርና ጣልያኖች ሳይቀሩ እየደገፉት ያለ ጉዳይ ነው።በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ኋላ ማለት ለአገር የሚያኮራ ጉዳይ አይደለም፣" ሲሉ ይመክታሉ፡፡ የቫቲካን ተሳትፎ ላይ ጥያቄ መነሳቱም ቢሆን ለእሳቸው እንቆቅልሽ ነው፣ "ብዙሃኑ ጳጳሳት ወርቃቸውን ሳይቀር እያወጡ ለጦርነቱ አስተዋፅኦ ያደረጉ መሆኑን፣ አንደኛው ‹ካርዲናል› ይሄ ጦርነት ቅዱስ ጦርነት ነው ሲሉ የተናገሩት መረጃ አለን፣ የጣልያን ጦር አዲስ አበባ ሲገባ የደስታ መግለጫ ካወጡት መካከል የመጀመሪያው (የቫቲካኑ) ፖፕ ሃያስ ነበሩ፡፡ ይሄንና ሌላ ማስረጃዎችን ያየ ..እንዲህ ያለ የማይሆን ነገር ለመናገር አይችልም፣" ሲሉ ይሟገታሉ፡፡

አቶ ኪዳኔና አጋሮቻቸው ከእኒህ ሁሉ ዓመታት በኃላ "ይሄ ነገር አይሰምርም" ብለው መዝገባቸውን ለማጠፍ ዝግጁ አይደሉም፡፡ ከዚህ ቀደም በቫቲካን ተባባሪነት ለደረሰ በደል፣ የነዋይ ካሳን እና ይፋዊ ይቅርታን ማግኘት እንዲሁም በወቅቱ የተዘረፉ ቁሳቁሶች እና ቅርሶች ወደሀገራቸው ተመላሽ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረታቸው እንደሚቀጥል ይናገራሉ።

በእነ አቶ ኪዳኔ አለማየሁ መንደር የተስፋ ጀምበር አልጠለቀችም ፡፡በዚህ ዓመት ህዳር ወር ላይ ከ81 ዓመት በፊት የካቲት 12 ለተፈጠረው እልቂት ሰበብ የሆነው ሩዶልፎ ግራዚያኒ መታሰቢያ ሃውልት 'አፊል' ከተሰኘችው የሮማ ጎረቤት ከተማ እንዲነሳ ተወስኗል፡፡

ሃውልቱ እንዲሰራ የገንዘብ ፈሰሱን ያጸደቁት የከተማዋ ከንቲባ እና ሁለት የአስተዳደር አባላት ‹‹ፋሽስት ይቅርተኝነት›› Apologia del Fascismo የሚሰኘው ህግ ተጠቅሶ በስምንት እና ስድስት ወራት እስር እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡

ሃውልቱ መወገድ እንዳለበት ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ሲጎተጉቱ ከነበሩ ተቋማት አንዱ ለሆነው 'ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ'፣ውሳኔው የሌሎች ዘመቻዎች ተስፋም ፈጽሞ እንዳልከሰመ የሚያሳይ ምልክት ይመስላል፡፡

ሃላፊው የ ቫቲካን ይቅርታ መዘግየት የሚያብከነክናቸውን ያክል አንድ ቀን ይቅርታው እንደሚሰማ ያላቸውን ዕምነትም ከፍተኛ ነው፡፡ ይሄን የሚደግፈው የሚደጋግሙት ሀረግ ነው ''የፍትህ አምላክ፣የኢትዮጵያ አምላክ፣ይረዳናል!'' የሚለው፡፡

https://www.bbc.com/amharic/news-44198353

**********************************************

https://www.gudayachn.com/2014/02/12.html

 

 https://www.facebook.com/1845896815651636/photos/%E1%8B%A8%E1%8A%AB%E1%89%B2%E1%89%B5-121929-%E1%8B%93%E1%88%9D-%E1%8A%A0%E1%8B%B2%E1%88%B5-%E1%8A%A0%E1%89%A0%E1%89%A3-%E1%8A%A8-%E1%88%B0%E1%88%8B%E1%88%B3-%E1%88%BA%E1%88%85-%E1%89%A0%E1%88%8B%E1%8B%AD-%E1%8A%90%E1%8B%8B%E1%88%AA%E1%8B%8E%E1%89%BD%E1%8B%8B-%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%8B%B2%E1%89%B5-%E1%8C%80%E1%8A%95%E1%89%A0%E1%88%AD-%E1%88%B0%E1%88%9B%E1%8A%A0%E1%89%B5%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%89%80%E1%89%A0%E1%88%89%E1%89%A3%E1%89%B5-%E1%89%80%E1%8A%95-%E1%8A%90%E1%89%A0%E1%88%A8%E1%89%BD-%E1%8B%A8%E1%8B%9B%E1%88%AC/1846383585602959/?paipv=0&eav=AfZREjMYFPEAQaC2VRnSiLcsQAmnYg9Hb5p8A9BfqGm_g6GUJluev1DD_RYna2cmipU&_rdr