ከልብ
ከሆነ የጥርጣሬን በረዶ ያቀልጣል። ለዓመታት ሲከማች የኖረ ጭፍን ጥላቻን ያስወግዳል። በእምነት ማጣት ስነልቦናዊ
ፍራቻን አሳድሮ በጥርጣሬ ዓይን ያስተያይ የነበረን ልብ ያለሰልሳል። ብዙዎቹ እፎይታና ደስታ እንዲያገኙ ያደርጋል።
“ገብቶኛል፤ ችግር የለም” የሚል መልዕክት ያስተላልፋል። “ጓደኛ ልንሆን እንደምንችል ይሰማኛል” የሚል ግብዣ ያቀርባል። “ፈገግታ!’’
“ፈገግታ”
ምንድነው? መዝገበ ቃላት ‘መደሰትን ወይም መስማማትን ለመግለጽ ከንፈር ሲሸሽና በመጠኑ ጥርስ ሲገለጥ በፊት ላይ
የሚታይ ሁኔታ’ እንደሆነ አድርገው ይፈቱታል። ሞቅ ያለ ፈገግታ ለማሳየት ምሥጢሩ ይኸው ነው። ፈገግታ አንድ ሰው
ያለ አንደበት ስሜቱን የሚገልጽበት ወይም ከሌላው ሰው ጋር ልብ ለልብ የሚግባባበት መንገድ ነው። እርግጥ ነው
ፈገግታ ንቀትን ወይም ጥላቻን ወይም ንዴትን ሊገልጽ ይችላል።
በርግጥ
ፈገግታ ማሳየት ወይም አለማየት ይህንን ያህል ለውጥ ያመጣልን? አንድ ሰው ፈገግታ ሲያሳይ ደስ የተሰኛችሁለትን
ወይም ዘና ያላችሁበትን ጊዜ አስታወሱ፤ ወይም ደግሞ ሰዎች ፈገግታ ሲነፍጓችሁ የሚጨንቃችሁን ጊዜ ልብ በሉ። አዎ!
ፈገግታ ማሳየት ወይም አለማሳየት ልዩነት ያመጣል። በፈገግታ ሰጪውም በተቀባዩም ላይ ተፅዓኖ ያሳድራል።
ሞቅ
ያለ ፈገግታ ከውጥረት ተንፈስ ለማለት ሊረዳ ይችላል። ፈገግታ “በፕሬዠር ኩከር” ላይ ከምትገኝ ማስተንፈሻ ባልቦላ
ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ውጥረት ወይም ብስጭትን አንዲሁም አእምሮአችን የተጨነቀበትን ሁኔታ ለማቅለልና ችግሮቻችንን
ለመቋቋም ሊረዳን ይችላል።
ሳንድራ
የተባለችው ወጣት ብዙውን ጊዜ ሰዎች ዝም ብለው እንደሚመለከቷት አስተዋለች። እርሷ አትኩራ ስታያቸው ደግሞ ቶሎ
ብለው ዓይናቸውን ከእርሷ ላይ ስለሚነቅሉ የሚያሽሟጥጧት እየመሰላት ጠንካራው ስነልቦናዋ እየተሸረሸረ ሲሄድ ይታወቃት
ነበር። አንድ ቀን አንዲት ጓደኛዋ ሰዎች ሲያይዋት ፈገግ እንድትል ሐሳብ አቀረበችላት።
ሳንድራ ይህንን ሀሳብ ለሁለት ሳምንታት በተግባር አዋለችው። በአፀፋው ሌሎችም ፈገግ ሲሉላትና ምላሽ ሲሰጡዋት ተገረመች፤ ውጥረቱም ለቀቃት። “ሕይወት የበለጠ አስደሳች ሆነልኝ” በማለት ተናግራለች።
ፈገግታ በሌሎች ፊት ዘና እንድንልና ይበልጥ ተግባቢ እንድንሆን እንደሚረዳ የስነልቦና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ፈገግታ
በአንድ ሰው ስሜት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። አንድ ሰው ጥሩ ስሜት እንዲሰማውም ያደርጋል። ለአካላዊ ጤናም
ጥሩ መሆኑን ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ። ረጅም ጊዜ የቆየ ውጥረትና ጭንቀት የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም
እንደሚያዳክሙ ብዙ ጥናቶች ያመለክታሉ። ይሁን አንጂ ሳቅ በአንፃሩ የሰውነታትንን በሽታ የመከላከል አቅም ሊያጠናክር
እንደሚችል ተመራማሪዎቹ ያስረዳሉ።
አንድ
ምክር የሚሰጥ ሰው ምን ዓይነት ፊት ቢያሳየን እንመርጣለን። የንዴት፤ የቁጣ፤ ፊት የመንሳት ወይም ጥላቻን
የሚያስተላልፍ ፊት እያሳየን ቢሆን ምክሩን እንዴት ልንቀበለው እንደምንችል መገመት አያዳግትም።
በሌላ
በኩል ምክር የሚሰጠን ሰው ወዳጅነት የተላበሰ ፈገግታ ቢኖረው ይበልጥ ዘና እንድንልና ምክሩን በደስታ እንድንቀበል
ያደርግናል። ታዲያ ፈገግታ ውጥረትና ጭንቀት በነገሰበት ወቅት አለመግባባቶችን ሊቀንስ የሚያስችል ተጽዕኖ አለው።
ብዙዎቻችን እንደ ተዋንያን እነርሱ በፈለጉት ጊዜ ፈገግታ ማሳየት እንደሚችሉት ለመሆን ወይም ለመምሰል አንፈልግም። ፈገግታችን ተፈጥሮአዊና ልባዊ እንዲሆን እንፈልጋለን።
አንድ የስነ ልቦና ባለሙያ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥተዋል። “ዘና ብላችሁ ከልብ ፈገግ ማለታችሁ አስፈላጊ ነው። ይህ ካልሆነ የምታሳዩት ፈገግታ የጥርስ ፈገግታ ብቻ እንጂ ልባዊ አይደለም”።
ፈገግታ
የውስጥ ስሜችንን ያለ ንግግር የምናሳይበት መንገድ እንደሆነ ከአስተዋልን የምንናገረው “በልብ ሞልቶ የተረፈውን”
እንደሆነና መልካም ነገር የሚወጣው “ከመልካም መዝገብ” ውስጥ እንደሆነ ካወቅን ፈገግታችን ከውስጥ ስሜታችን ጋር
በቀጥታ የተያያዘ እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል።
በልባችን
ውስጥ ያለው ነገር ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ በንግግራችንና በድርጊታችን ብቻ ሳይሆን በፊታችንም ላይ መገለጡ የማይቀር
ነው። ስለሌሎች ሰዎች ያለን አስተሳሰብ በፊታችን ላይ በግልጽ ይነባበል። የቤተሰቦቻችንን አባላት፤ በአካባቢያችን
የሚኖሩ ሰዎችና የቅርብ ወዳጆቻችን ከልባችን በምናሳያቸው ፈገግታ ቀረቤታቸው የጠነከረ ይሆናል።
ለሰዎች የምናሳየው ፈገግታ ጥሩነት፤ ምህረትና ደግነት ከሞላው ልብ የሚወጣ ልባዊ ፈገግታ ይሆናል። ዓይናችን ብሩህ ይሆናል፤ ሌሎችም ፈገግታችን ከልብ እንደሆነ ይገነዘባሉ።
አንዳንድ
ሰዎች በአስተዳዳጋቸው ወይም ያደጉበት አካባቢ ባሳደረባቸው ተፅዕኖ ምክንያት እንደ ሌሎች ፈገግታ ማሳየት ቀላል
ላይሆንላቸው እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። ለሰዎች ጥሩ ስሜት ያላቸው ቢሆንም እንኳ ፈገግታ ማሳየት
ይቸግራቸዋል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ጃፖናውያን ወንዶች በሌሎች ፊት ረጋ ያሉና ዝምተኛ እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ የተነሳ ለማያውቋቸው ሰዎች ፈገግታ የማሳየት ልማድ የላቸውም።
አንዳንድ
ግለሰቦች በተፈጥሮአቸው ዓይን አፋር ሊሆኑና ለሌሎች ፈገግታ ማሳየት ሊከብዳቸው ይችላል። ስለዚህ ሰዎችን
በፈገግታቸው መጠን ወይም ብዛት መገመት አይኖርብንም። አንዱ ከሌላው እንደሚለይ ሁሉ ጠባያቸውም ሆነ ከሰዎች ጋር
የሚግባቡበት መንገድ ይለያያል።
የሆነ
ሆኖ ለሰዎች ፈገግታ የማሳየት ችግር ካለብን ለምን ለማሻሻል ጥረት አናደርግም? መልካምን ነገር ማድረግ
ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ ፈገግታ ማሳየት ሲሆን፤ ይህ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር አይደለም።
ፈገግታን በተመለከተ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚናገሩት “ከሰዎች ጋር ጤናማ የህይወት መስተጋብርን
ይፈጥርልናል። በጭንቀትና በውጥረት በተያዝንበት ወቅት እፎይታን ይሰጠናል። ምንም ይሁን ምን ግን በጐ አመለካከታችን
የሚያስከፍለን ዋጋ የለም፤ በጐ ከማሰብ በስተቀር” በማለት የሥነልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
*************************************