ከደራሲያን ዓምባ

Monday, December 16, 2013

ከመጽሃፍት ዓለም



“ ፈረንጆች፣ በውቀት ይሁን በስ ህተት በየትኛው መሆኑን እግዜር ይወቀው የሚጽፉት ሆነ የሚያስተምሩት፣ ፈረንጅን እና የፈረንጅ የሆነውን ሁሉ የሚያስወድ ድ፣ የሚያስደንቅ፣ የሚያስመኝ፣ ሌሎችንና ሌሎች የሆነውን፣ እኛንና የኛ የሆነውን ጭምር አዋርዶ፣ አጎሳቅሎ የሚያሳይና የሚያስንቅ፣ የሚያስጠላ፣ የሚያስጸይፍ ነው።
ታዲያ እንግዲህ፣ ከህጻንነታቸው ጀምረው እንዲያ ያለውን ትምርት ብቻ በትምርት ቤት እየተማሩ የሚያድጉ ልጆች፣ እንዲያ ያለው ትምርት እውነት አለመሆኑን የሚያስረዳ ማረሚያ ማስተባበያ፣ ማስተሀቀሪያ በመስጠት ፈንታ፣ በሱ ለላቁ ሽልማት እየሰጠን  በሱ እንዲመሩ እያደፋፈርን የምናስድጋቸው ልጆች  በጠቅላላው የራሳቸው የሆነውን የሚንቁ የሚጠሉ፣  በጠቅላላው የፈረንጅ የሆነውን ሁሉ የሚወዱ፣ የሚያደንቁና የሚመኙ መሆናቸው የማይቀር ነው።”  ( ሀዲስ አለማየሁየልም ዣት)
“ የቆየ ልማድ የቆየ በመሆኑ ሁሉ አይወድቅም፤ ወይም ሁሉ አይያዝም። መልካሙና ጠቃሚው ይያዛል የሚሻሻለው ይሻሻላል ሊሻሻል የማይችለው ይወድቃል። ነገር ግን የሚወድቀው ክፉ ልማድ ከስራ ይወገዳል እንጂ ከታሪክ ጸሃፊዎች መጽሀፍና ከደራሲዎች ድርሰት ሊወገድ አይገባውም። ያለዚያ በየጊዜው የሚደረገው የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚክ ወይም የአስተዳደርና የማህበራዊ ኑሮ መሻሻል ከምን ተነስቶ እምን እንደደረሰ ሊታወቅ አይችልም።” (  ሀዲስ አለማየሁ፣ፍቅር እስከ መቃብር)
“ በኔ አስተያይት ዛሬ ኢትዮጵያ በጣም የሚያስፈልጋት ኢኮኖሚዋን አፋጥኖ አልምቶ በጠቅላላ የህዝብዋን የኑሮ ደረጃ ማሻሻልና ያስተዳድርዋንም ሆነ የፍርድ ስራትዋን ለዘመናዊ ኑሮ እንዲስማማና ልማቱን እንዲረዳ ማድረግ ነው እንጂ የምዕራብን ወይም የምስራቅን ያስተዳድር ስራት እንዲሁ እንዳለ ተውሶ መልበስ ምስራቅን፣ ወይም ምዕራብን ሊያደርጋት ይችልም። ስለዚህ ያቀረብነው አሳብ ከምዕራብና ከምስራቅ የመንግስት ስሪቶች ኢትዮጵያ ዘመናዊ አስተዳድርና ልማትዋን ለማፋጠን ይረዳሉ ተብሎ የሚታመንባቸው አሳቦች ተዋጥተው ያሉበት፣ በዚያ ላይ ኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ጋር የሚስማሙ አዳዲስ አሳቦች የተጨመሩበት፣ አይነተኛ አላማው ባሥር ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያን በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚክና በማኀበራዊ ኑሮ አሁን ካለችበት ዝቅተኛ ቦታ በኃይል ገፍቶ ወደፊት ሊያራምዳት ይችላል ብለን የምናምንበት ነው።” ( ሀዲስ አለማየሁ፣ኢትዮጵያ ምን አይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል)
***********************************************************
ምንጭ:-- ሀዲስ አዲስ

የግጥም ጥግ

ልረሣሽ እየጣርኩ ነው
--------------------
ልረሣሽ እየጣርኩ ነው
በጣራው ላይ ሲረማመድ፣የዝናቡ ልዝብ ኮቴ
መጋረጃው ሲውለበለብ፣ሰንደቅ ሆኖ ለመስኮቴ
ዋርካው፣ በቅጠል ጥዋ
ውኃ ሲያቁር ፣ከህዋ
የምድርን ጉሮሮ ሊያርስ
መሬት ፣ፍጥረትን ስትጸንስ
በዚህ ሁሉ ጸጋ መሀል ፣ያንችን መሄድ ስተምነው
ምንም ነው፣ኢምንት ነው
ልረሣሽ እየጣርሁ ነው፡፡
መጣ፣ መጣ ፣መጣ፣ የዝናቡ ኮቴ አየለ
ክረምት የፍጥረት መሲሕ፣ በቀጠሮው ከተፍ አለ፡፡
ስስ የጉም አይነርግብ፣ውብ ገጽሽን ሸፋፈነው
የርጥብ አፈር፣ርጥብ ሽታ ፣ውብ ሽቶሽን አዳፈነው
ልረሣሽ እየጣርኩ ነው፡፡
የዝናቡ ኮቴ ይደምቃል
እንደ ብስል ሾላ ፍሬ፣አሮጌው ሰማይ ይወድቃል
አዲስ ሰማይ ይነቃል
አዲስ ጅረት ይፈልቃል
እንኳንስ የእግርሽ ኮቴ፣ ጎዳናሽም ታጥቦ ያልቃል፡፡
ልረሳሽ እየጣርኩ ነው፡፡
---------------------------

በእውቀቱ ሥዩም ፣ክረምት፣ 2005

Tuesday, October 29, 2013

በውስጥዎ ስንት አስደናቂ ነገር አለ!


 
እያንዳንዱ ሰው በቀን 2 ሊትር ምራቅ ያመርታል
በየደቂቃው ከ30ሺ - 40ሺ የቆዳ ሴሎች ይሞታሉ
 ዓይኖቻችን በየዕለቱ 15ሺ ያህል ጊዜ ይርገበገባሉ
ከተፀነስንበት ሴኮንድ ጀምሮ፣ በሕይወትና በጤንነት የምንንቀሳቀሰው ቅንጣት ታህል ስህተት ሳይፈፅሙ ተግባራቸውን ስለሚፈፅሙ ነው፡፡

እስቲ ጥቂቱን እንይ፡፡ 20ሺህ ያህል ሀሳቦች በአንጎላችን ውስጥ ምን ያህል የነርቭ ሴሎች እንዳሉ ያውቃሉ? እጅግ በርካታ ናቸው-እስቲ ይገምቱ፡፡ በአንድ ሴኮንድ ውስጥ በአማካይ ከአምስት እስከ 50 ጊዜ እርስ በርስ መልእክት ይለዋወጣሉ፡፡ የነርቭ ሴሎች የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች በቀን ከ10ሺ ኪ.ሜ በላይ ይጓዛሉ፡፡ ከአዲስ አበባ አስመራ ድረስ አምስት ጊዜ እንደመመላለስ ነው፡፡ የነርቭ ሴሎቹ ቁጥር ከመቶ ቢሊዮን በላይ ነው፤ የፀጉር ያህል ውፍረት የላቸውም፡፡ በመሃላቸው ያለው ርቀትም እንደዚያው ኢምንት ነው፡፡ ነገር ግን ከብዛታቸውና በየሴኮንዱ ከሚለዋወጡት የመልእክት ብዛት የተነሳ ተዓምር ይፈጥራሉ፡፡ አንድ ነገር አይተው ወዲያውኑ “ይሄ ውሻ ነው፣ እንዳይነክሰኝ!” “ብርቱካን ነው፣ ይጣፍጣል” “ሰው ነው፤ ዝነኛው ሯጭነቱ ይደነቃል” “አንበሳ ነው፣ የጀግንነት ምሳሌ ተደርጎ ይቆጠራል” … ለማለት የሚችሉት በዚህ ፍጥነት ነው፡፡ በእነዚህ ነርቮች ነው እንግዲህ በቀን፣ 20ሺህ ያህል ጊዜ የምናስበው።
እንደ በረዶ እንዳንቀዘቅዝ፣ እንደ ውሃ እንዳንፈላ
የሰውነታችን “አውቶማቲክ” እንቅስቃሴዎችንና ሂደቶችን የሚቆጣጣረው hypothalamus የተባለው የአንጎል ክፍል ነው፡፡ የሰውነታችን የሙቀትና የቅዝቃዜ መጠን ከልክ እንዳያልፍም ይቆጣጠራል፡፡ በአንዳች ውጫዊ ወይም ውስጣዊ ምክንያት የግማሽ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ለውጥ ከተፈጠረ፤ ሰውነታችን ሕይወት አድን የሙቀት መጠን ማስተካከያ ያከናውናል፡፡
የሰውነታችን ሙቀት በጣም ከፍ ሲል፣ በቆዳችን ውስጥ ያሉ የደም ስሮች ይሰፉና ሙቀት ያስወጣሉ፡፡ ቅዝቃዜ ሲከሰት ደግሞ የደም ስሮች ጠበብ ይላሉ፤ ላብ አመንጪ ዕጢዎችም ይዘጋሉ፡፡ ቅዝቃዜው ሲበረታማ ሰውነታችን ሙቀት ለመፍጠር መንቀጥቀጥ ይጀምራል፡፡
የልብ ምት
የትም ሆነ የት ቢሆኑ፣ ሲራመዱም ሆነ ሲያንቀላፉ፣ ልብ በአንድ ደቂቃ ከ60 እስከ መቶ ጊዜ ይመታል፡፡ በአማካይ ልብዎ በቀን መቶ ሺህ ጊዜ ይመታል፡፡ በዚህ ስሌት ስድሳ ዓመት አማካይ ዕድሜ ላይ የደረሰ ሰው ከ2 ቢሊዮን ጊዜ በላይ የመታ ልብ ይኖረዋል፡፡
በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ የደም ስሮች ብዛትና ርዝመት ጉድ ያሰኛል፡፡ ከጫፍ ጫፍ የተቀጣጠሉ 160 ሺህ ኪ.ሜ ያህል ይረዝማሉ፡፡ የደም ማጣሪያ ባይኖር ኖሮ፣ ሰውነታችን ምን ያህል የደም መጠን እንደሚያስፈልገው ያውቃሉ? በቀን 5,720 ሊትር! በሌላ አነጋገር እንደ ሳንባ፣ ጉበትና ኩላሊት የመሳሰሉ የደም ማጣሪያ የሰውነት ክፍሎች በቀን ወደ 6ሺ ሊትር ገደማ ደም የማጣራት አቅም አላቸው ማለት ነው፡፡
ሳይፈልጉ በቀን 25ሺህ ጊዜ መተንፈስ
አልመውና አቅደው 25ሺህ ያህል ጊዜ ልተንፍስ ካሉ፣ ሌላ ነገር በፍፁም አይሰሩም፤ እንቅልፍም አይተኙም፡፡ ቀንና ሌት ስራዎ መተንፈስ ብቻ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አንጎላችን የመተንፈስ ልምድን አውቶማቲክ ስላደረግልን ምስጋና ይግባው፡፡ ለመሆኑ በየጊዜው አየር ወደ ውስጥ የምንስበውና የምናስወጣው (የምንተነፍሰው) ለምንድነው?
የሰው ልጅ ፍጡራን በእያንዳንዷ ደቂቃ ከ200 እስከ 300 ግራም ገደማ ኦክስጅን ያስፈልገናል፡፡ ይህንን የማያቋርጥ የአየር ፍሰት ለማስተናገድ ሳንባችን ውስጥ 300 ሚሊየን ያህል ለዓይን የማይታዩ alveali የተባሉ የአየር ከረጢቶች ተዘጋጅተው ይጠብቃሉ፡፡ የተቃጠለ አየር (ካርቦንዳይ ኦክሳይድ) ከደማችን ያስወግዳሉ፤ ኦክስጅንን ተቀብለው ለደማችን ያስረክባሉ፡፡
የዓይን ጡንቻዎች
አንድ ነገር ላይ እንድናተኩር የሚረዱን የዓይናችን ጡንቻዎች በቀን 100ሺህ ጊዜ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይህም ከ80ኪ.ሜ ጉዞ ጋር እኩል ይሆናል፡፡ ዓይኖቻችን በየእለቱ 15ሺህ ያህል ጊዜ ይርገበገባሉ፡፤ ለምን እንደሆነ ያውቃሉ? ዓይንን ከአደጋ ለመከላከል፣ ቆሻሻ ለማስወገድና ዓይንን ለማርጠብ ነው፡፡ ዓይናችንን ስንጨፍንና ስንከፍት ያመለጠንን መረጃ አንጐላችን ስለሚያሟላልን መጨፈናችን እንኳ በፍፁም ትዝ አይለንም፡፡
ሁለት ሊትር ምራቅ
ሰውነታችን በቀን የሚያመነጨው ምራቅ ከጥቂት ማንኪያ የማይበልጥ ሊመስለን ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ሰው በቀን ሁለት ሊትር ምራቅ ያመርታል፡፡ “አቤት! ምን ሊጠቅም?” ሊሉ ይችላሉ፡፡ ያለ ምራቅ አንድ ነገር መቅመስ፣ ምግብ መዋጥም ሆነ ቃላት መፍጠር አንችልም፡፡ በዚያ ላይ፣ ምራቅ ከፍተኛ የጀርም ጠላትና የምርቀዛ (የኢንፌክሽን) መከላከያ ነው፡፡ ስለዚህ፣ እንስሳት ቁስላቸውን ሲልሱ ማየት አያስደንቅም፡፡
በሴኮንድ 3 ሚሊዮን ቀይ የደም ሴል
በየደቂቃው፣ ከኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር በእጥፍ የሚበልጡ ቀይ የደም ሴሎች በሰውነታችን ውስጥ ይፈጠራሉ፡፡ የዚያኑ ያህልም ይሞታሉ፡፡ በቀን 260 ቢሊዮን ያህል ቀይ የደም ሴሎች እናመርታለን ማለት ነው፡፡ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ኦክስጂን ለሁሉም የሰውነታችን ሴሎች የሚዳረሰው በቀይ የደም ሴሎች ነው፡፡ አንድ ጠብታ ደም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቀይ የደም ሴሎች ሲኖሩት፣ ቀዩን ቀለም የሚያገኙት ሄሞግሎቢን ከተሰኘው ፕሮቲን ነው፡፡
መብላትና መጠጣት ጥበብ ነው
ምግብ መዋጥና ፈሳሽ መጠጣት ቀላል ጥበብ እንዳይመስላችሁ፡፡ ህፃናት ሲቸገሩ ካላየን በቀር በእግር ቆሞ መራመድ ቀላል ይመስለን የለ? ጥበብ ነው፡፡ ምግብ መዋጥና ፈሳሽ መጠጣትም እንደዚያው ነው፡፡
የአዋዋጥን ጥበብ ለማድነቅ ከፈለጉ፣ ሕፃን ልጅ በማንኪያ ስታጐርሱት ምን እንደሚያደርግ ተመልከቱ፡፡ በምላሱ ምግቡን ወደ ውጭ ገፍቶ ያስወጣዋል፡፡ ለምን መሰላችሁ? ወደ አየር መተላለፊያ እንዳይገባ የሚያደርግ የአዋዋጥ ስልት ገና በሚገባ ስላልተካነበት ነው፡፡
ምንጊዜም ምግብ ሲበሉም ሆነ ፈሳሽ ሲጠጡ፣ ከአፍ ጀርባ፣ ምግቡም ሆነ መጠጡ ወደ አየር ቧንቧ እንዳይሄድ ዘግተው የሚከላከሉ አስገራሚ ሕይወት አዳኝ የሰውነት ክፍሎች አሉ፡፡ የሚበሉትንና የሚጠጡትን ነገር ለመዋጥ ሲዘጋጁ፣ Soft Palate የተሰኘው አካል ይመጣና ወደ አፍንጫ የሚወስደውን መተላለፊያ ይዘጋል፡፡ ወደ ሳንባችን እንዳይገባ ደግሞ Epiglottis ይከላከላል፡፡
የሆድ ውስጣዊ ግድግዳ ራሱን ያድሳል
የሆድ ግድግዳ በየሳምንቱ እንደሚታደስ ያውቃሉ? ሆዳችን፣ ሃይድሮክሎሪክ አሲድ የተባለ ኃይለኛ አሲድ የሚውልበትና የሚያድርበት ቤት ነው፡፡ አሲዱ ምግብን ሰባብሮ ይበልጥ እንዲብላላ ይረዳል” አሲዱ ከባድ በመሆኑ፣ ብረት የማቅለጥ አቅም አለው፡፡ የጨጓራ ጡንቻ በአሲድ እንዳይጎዳም ነው፤ የሆዳችን ግድግዳ በአራት ወይም በአምስት ቀን ራሱን የሚያድሰው፡፡
አጥንት
እንደ ብረት ጠንካራ፤ እንደ አሉሚኒየም ቀላል የሆነው አጥንታችን፣ ሕይወት አልባ ምሰሶ ነገር ወይም ድጋፍ አይደለም፡፡ የራሱ የደም ስርና ነርቭ ያለው ሕያው አካል ነው፡፡ በየጊዜው ሳያቋርጥ ራሱን ያድሳል፡፡ የአዋቂ አጥንት በየዓመቱ 10 በመቶ ያህል ራሱን ይተካል፡፡
የምድር ወገብን በእግር መዞር
ጤነኛ ሰው በአማካይ በየቀኑ ከ8 እስከ 10ሺህ እርምጃዎች ይጓዛል፡፡ በ70 ዓመት የምድርን ወገብ አራት ጊዜ እንደዞረ ይቆጠራል፡፡
50 ሚሊዮን ያህል የቆዳ ሴሎች ይሞታሉ
በየደቂቃው ከ30 እስከ 40ሺህ የቆዳ ሴሎች ይሞታሉ፡፡ ቆዳዎ፣ በየቀኑ 50 ሚሊዮን ያህል የሞቱ ሴሎችን ያስወግዳል ማለት ነው፡፡
ከሰውነት ክፍሎች ሁሉ ትልቁ አካል ቆዳ ነው ሲባል ሰምተው ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በርካታ ጠቃሚ ነገሮች ስለሚሠራ ነው፡፡ 5 ሴንቲ ሜትር በ5 ሳንቲ ሜትር ስፋት ያለው ቆዳ፤ 650 የላብ ዕጢዎች፣ 9 ሜትር ያህል የደም ስሮች፣ 60ሺህ ቀለም አመንጪ ሴሎችና ከአንድ ሺህ በላይ የነርቭ ሴሎች ጫፍ አሉት፡፡
*************************************
ምንጭ :--http://www.addisadmassnews.com
Reader’s nigest - September 2013
By Dr. Traris Stork

Thursday, May 23, 2013

ከታሪክ ዓምባ

 ጋዜጠኛው ኤን. ማንላ (N. Mandela)-በኢትዮጵያ!

(99 ቀናት በአዲስ አበባ)

(በሰሎሞን ተሰማ ጂ.)

በታኅሣሥ አጋማሽ 1954 ዓ.ም በግርማዊ ንጉሠ ነገሥቱ ጥሪ ተደረገለትና በጥር መጀመሪያ ላይ አዲስ አበባ ገባ፡፡ ይህ ሰው በሦስት ወራት ከአንድ ሳምንት (በ98 ቀናት) ቆይታው ወቅት እጅግ የተጣበበ መርሐ ግብር እንደነበረበት ያስታውቃል፡፡ በጥር 8/1954 ዓ.ም በንጉሠ ነገሥቱ በተከፈተውና ለአሥር ቀናት ያህል በቆየው፣ “የአፍሪካ ኤኮኖሚና ሶሻል ዕድገት ጉባኤ” ላይ ተካፍሏል፡፡ ከተካፋይነትም አልፎ፣ ስሜታዊ የሆነ ንግግር አድርጓል፡፡ ብዙዎቹ የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ ስለሀገሩና ስለሕዝቡ ሰቆቃ ባለማወቃቸውም አዝኗል፡፡ (አዲስ ዘመን፣ ጥር 9 ቀን 1954፣ ገጽ 1) ከዚያም በመቀጠል ከጥር 6 እስከ ጥር 14 ቀን 1954 ዓ.ም የተደረጉትን የአፍሪካ ዋንጫ ግጥሚያዎች በዛሬው የአዲስ አበባ ስታዲዮም ተገኝቶ ተከታትሏል፡፡ ሀገሩ፣ ለምን  በዚህ የአፍሪካ ዋንጫም እንዳልተካፈለች የኢትዮጵያን እግር ኳስ ባለስልጣኖች ጠይቆ ተረድቷል፡፡ እንዲህ አሉት፤ “በወርኃ የካቲት 1950ዓ.ም ጨዋታው ሊጀመር ሦስት ቀናት ሲቀረው፣ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት የደቡብ አፍሪካ ቡድን አስመልክቶ የውሳኔ ሃሳብ/ሞሽን/ አቀረቡ፡፡ “የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን መንግሥት በጥቁር አፍሪካውያን ላይ የሚያራምደውን የዘር መድሎ አገዛዝ ካላቆመ በስተቀር፣ የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ላይ መሳተፍ አይገባውም” የሚል አቋም ያዙ፡፡ እርግጡን ለመናገር፣ ወደካርቱም መጥቶ የነበረው የደቡብ አፍሪካ ቡድን አንድም የአፍሪካነር/ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊ/ አላሣተፈም ነበር፡፡ በመስራች አገሮቹ የጋራ ስብሰባ ላይ፣ ሐሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ደቡብ አፍሪካ ከዋንጫው በእግድ ተሠናበተች፡፡” ሲሉ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ነገሩት፡፡ ውሳኔውም ትክክለኛ ነው ሲል ድጋፉን ሰጠ፡፡ 
በጥር 10 ቀን 1954 ዓ.ም በዋለው የከተራ በዓልም ላይ ተገኝቶ “ግርማዊ ንጉሠ ነገሥቱ” በጃን ሜዳ ተገኝተው በዓሉን ከሕዝቡ ጋር ሲያከብሩት ባይኑ አይቷል፡፡ የአልጋ ወራሹንና የአቡኑንም ንግግሮች በቱርጁማን አዳምጣቸዋል፡፡ ሁሉም ነገር ገርሞታል፡፡ በሕዝቡና በከሕናቱ፣ በሕዝቡና በመኳንንቱና በመሳፍንቱ መካከል ያለው ልዩነት የፕሮቶኮል ብቻ እንደሆነ ተሰማው፡፡ በጥር 13 ቀን 1954 ዓ.ም (በዕለተ እሑድ ሃምሳ ሺህ ሕዝብ በተሰበሰበበት የቀ.ኃ.ሥ ስታዲየም ተገኝቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግብፅ አቻውን 4 ለ 2 ሲያሸንፍ አይቶ፣ ልቡ በድሉ ሰበብ ደስፈቅ ብሏል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ለብሔራዊ ቡድኑ አባላት ዋንጫ ሲሰጡ የነበረውን ሥነ ስርዓት ተመልክቷል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ከሕዝቡ ጋር ናቸው፤ ገረመው፡፡ ደነቀው፡፡ በሕዝቡና በንጉሠ ነገሥቱ እንዲሁም በሹማምንቱ መካከል ያለው ልዩነት የኃላፊነትና የተዋረድ እንደሆነ ገመተ፡፡ እራሱንም፣ የዚህ ሕዝብ አካል አድርጎ ለመቁጠር ከጀለ፡፡ ማን ያውቃል? ዜግነቱን የሚገልጽ የመታወቂያ ወረቀት (I.D Card/Passport) ያገኝ ይሆናል፡፡ ያኔ ታዲያ፣ ዜግነቱ ተረጋገጠለት ማለት አይደለ? ሆኖም፣ በዘር መድሎና በጭቆና ሥር ያለውን የራሱን ሕዝብ ለራሱ ምቾትና ድሎት ሲል ሊሰደድ ፈለገ፡፡ “በአፓርታይድ እስር ቤት ከመታጎር መሰደድ ይሻላል፤” ሲል አወጣ አወረደ፡፡ በታኅሣሥ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ጥሪ አድርጎለት ወደ አዲስ አበባ ከመመጣቱ ሁለት ወራት በፊት፣ የፓርታይድ መንግሥት የእስር ማዘዣ አውጥቶበት ነበር፡፡ ለጥቂት ነው፣ አምልጦ የወጣው፡፡ “ከስደት መታሰር!” ወይስ “ከመታሰር መሰደድ!” ይሻል ይሆን? እያለ ማመንታቱ አልቀረም፡፡   
ከብዙ ማመንታትና ማውጠንጠን በኋላ፣ “እንዴት አድርጎ ሕዝቡን ነፃ ሊያወጣ እንደሚችል ጭላንጭል ስለታየው፣ ቀሪ መርኀ-ግብሩን መተግበሩን ቀጠለ፡፡ በጣም የተጣበበው የሰውዬው መርሐ ግብር እንደቀጠለ ሲሆን፣ ወቅታዊ ዘገባዎችንና ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባወችን መከታተሉን አላስታጎለም፡፡ በጥር 20/1954 ዓ.ም፣ ወዳጁ-የታንዛኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚ/ር ጁሊዬስ ኔሬሬ ሥራውን/ሥልጣኑን በገዛ ፈቃዱ ሲለቅም አዲስ አበባ ሆኖ ዜናውን ተከታትሎታል፡፡ (በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን የለቀቀ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ጠቅላይ ሚ/ር ጁሊዬስ ኔሬሬ ነው፡፡) በጥር 25/1954 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ላይ በአፍሪካ አዳራሽ በንጉሠ ነገሥቱ የመክፈቻ ንግግር በይፋ በተከፈተው፣ “የማዕከላዊና የምሥራቅ አፍሪካ የነጻነት ንቅናቄ ድርጅት ጉባኤም” ላይ፣ የፓርቲው የANC (African National Congress)ን  በመወከል፣ የልዑካን ቡድኑ አባል ሆኖ በጉባኤው ላይ ተካፍሏል፡፡ 
በዚህ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የመጡት ሁለት የደቡብ አፍሪካ ፓርቲዎች (የፖለቲካ ፓርቲዎች) ሲሆኑ፣ የANC ተወካዮች ሆነው የመጡት ሦስት ነበሩ፤ ሚ/ር ታንያሳን ማኪዋኒ (የANC ሊቀ መ/ር)፣ ሚ/ር ኤን. ማንጄላ (“ማንዴላ” ለማለት ነው፤) የANC ም/ል ሊቀ መ/ር፣ እና ሚ/ር ኦሊበር ታንቦ (የANC የውጭ ጉዳይ ኃላፊ) ናቸው፡፡ የPAC (Peoples of Africa Congress)ን  በመወከል የመጡት የልዑካን ቡድኑ አባላት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ሚ/ር ሞሎትሲ፣ ሚስስ ዲጀ. ማቱትሀ፣ እና ሚ/ር ቪ.ኤል. ማኪ ትበሩ እንደነበሩ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በጥር 26/1954 ዓ.ም ዕትሙ (ገጽ-1) ላይ  አስፍሮታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ የሰሜን ሮዴሺያ (ያሁኗን “ዛምቢያ” ማለቱ ነው) በመወከል፣ ሚ/ር ኬኔት ካውንዳ፣ ሚ/ር አር.ሲ ካማንጋ፣ ሚ/ር ጄ.ኬ. ሙሉንጋ፣ ሚ/ር ኤም. ሲፖሎ ተገኝተዋል፡፡ የኬንያውን ካኑ ፓርቲም በመወከል፣ ሚ/ር ማዋያ ኪባኪ (ያሁኑ የኬንያ ፕ/ት) እና ሚ/ር ማሉ ነበሩ የመጡት፡፡ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድንም በአቶ ከተማ ይፍሩ የሚመራ ሲሆን እነአቶ ጌታቸው መካሻንና   እነአቶብርሃኔ ባሕታን ያካተተ ነበር፡፡ አምባሳደር ዮዲት እምሩም የውጭ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳዮች ዴስክን በመወከል ተናጋሪ ነበሩ፡፡   
የANC ም/ል ሊቀ-መንበር፣ በጉባኤው ላይ ከመካፈሉም በላይ፣ (ኧረ ምን መካፈል ብቻ!) ስለአፓርታይድ ዘረኛና ነውረኛ አገዛዝም ሰፊ ዲስኩር አቅርቧል፡፡ (አዲስ ዘመን ጥር 26/1954 ዓ.ም ገጽ 1)፡፡ የEthiopia Herald (February, 4/1962) በጥር 27/1954 ዓ.ም እንደዘገበው ከሆነ፣ ሰውዬው ለጉባኤተኞቹ ያቀረበውን ንግግር ሙሉ-ቃል በገጽ-1፣3 እና 4 ላይ አውጥቶታል፡፡ ጉባኤው በዋናነት የሚነጋገርባቸው አራት ዓላማዎችን ያነገበ ነበር፡፡ የጉባዔው አጀንዳዎች፣ “1ኛ) አውሮፓውያኖች ባሪያ ለመሸጥና የአቅኝነት ተግባራቸውን ለመፈጸም ሲሉ የአፍሪካ አህጉርን ምንም ባህል የሌላቸው ሰዎች የሚኖሩበት (የአውሬ ሕዝብ) አህጉር አድርገውታል፡፡ ይህን ከእውነት የራቀ ግምትና ሥዕል ማስወገድ አለብን፡፡ 2ኛ) አፍሪካዊ ያልሆኑትን ሕዝቦች ስለአፍሪካ ታሪክና ባህል፤ እንዲሁም ስለሕዝቡ የጋለ ምኞትና የማደግ ተስፋ እንዲረዱት ማድረግ፤ 3ኛ) የአፍሪካን አንድነት ማጠንከርና የያዝነው ጠንካራ አቅምም በዓለም ፊት እንዲገለጥ ማድረግ፤ 4ኛ) ቅኝ አገራቸውን አንለቅም ሲሉ የሚንገታገቱትን ቅኝ ገዢዎች በዓለም ፊት እንዲዋረዱ፣ መውቀስና ማስወቀስ አለብን፤” የሚሉ ነበሩ፡፡ አፍሪካዊ የጋራ መከላከያ (ማኅበር) ስለማቆም ጉዳይ ለመወያየት የተጠራ ጉባኤ ነበር፡፡ (አዲስ ዘመን፣ ጥር 26 ቀን 1954 ዓ.ም ገጽ 2)፡፡ ለዚህ ጉባኤ መነሻ (እርሾ የነበረው)፣ ከጥር 17-19/1954 ዓ.ም በሌጎስ፣ ናይጄሪያ ተደርጎ የነበረው የ19ኙ የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት መሪዎች ጉባኤ ውሳኔ ሃሳብን ገቢራዊ በማድረግ ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ የሌጎሱን የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት ጉባኤ ተካፍለው በጥር 20 ቀን 1954 ዓ.ም አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ በአስቸኳይ የተከናወነ ጉባኤ ነበር፡፡ 
ጃንሆይ ጉባኤውን ሲከፍቱ እንዲህ አሉ፤ “ፊሎዞፊውን በዘር ልዩነት ላይ የመሠረተው የደቡብ አፍሪካ ነጮች መንግሥት፣ በሕዝብ ቁጥር እጅግ የሚበልጡትን አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ላይ የሚፈጽመውን የዘር ልዩነትና የጭቆና አገዛዝ እንደቀጠለ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው ምንግሥት የሚከተለውን የግፍ አገዛዝ እንዲያሻሽለው ለማስገደድ ልዩ ልዩ እርምጃዎችን እየወሰድን ቢሆንም፣ እስካሁን በደቡብ አፍሪካ ነጮች መንግሥት በኩል አንዳችም የመለወጥ ነገር ባለመኖሩ፣ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን አሁን ከሚገኙበት የጭቆና አገዛዝ ሥር ነፃ ለማጣት የአፍሪካውያን ደጋፊዎች ሁሉ፣ ካሁን ቀደም ከታሰበው እርምጃ ሌላ እንዲወስዱ አሳስባለሁ፡፡ መንግሥታችንና የኢትዮጵያ እኅት የሆነችው የላይቤሪያ መንግሥት የጀመሩት ሕጋዊ ትግል መልካም ፍሬ ያሳያል ብለን እናምናለን፡፡” ካሉ በኋላ፣ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉም እንዲህ ብለው ነበር፤ “የተሰበሰባችሁበትን ከፍተኛ ሥራ ለማከናወን ሁሉን የሚችል አምላክ ረድኤቱን ይስጣችሁ፡፡” ጃንሆይ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁ፣ ሰውዬውና ሌሎችም ተሰብሳቢዎች በሙሉ ከመቀመጫቸው ተነስተው እጃቸው እስኪቀላ ድረስ አጨበጨቡ፤ የአፍሪካ አዳራሽም በጭብጨባው ተናወጠ (የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ጥር 26/1954 ዓ.ም፣ ገጽ-1)፡፡   
ያወሳነው ሰውዬ፣ የANC ምክትል ሊቀመንበር ሆኖ በዚሁ “የአፍሪካ የነፃነት ትግል ጉባኤ” ላይ ከመገኘቱም በላይ፤ እንዲህ ብሎ ነበር፤ “አንዳንድ የአፓርይድ መንግሥት ጠፍጥፎ የሠራቸው ተቋሚ ነን ባይ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፣ የፈለጉትን ያህን ቢፍጨረጨረና ትግላችንን ለማኮላሸት ከአፓርታይድ መሪዎች ጋር ቢሠሩም እንኳን፣ ለሕዝባችን በጽናት ታግለንና አታግለን ነፃ እናወጣዋለን፤ እናንተም ከዚህ ዓላማችን ጎን እንደምትሰለፉ ጥርጥር የለኝም፤” አለ፡፡ የአርባ ሦስት አመቱ ሠውዬ፣ ቁርጠኝነቱም እየጨመረ ሄዴ፡፡ ጉባኤው በየካቲት 2/1954 ዓ.ም የመግባቢያ ሰነድ አጽድቆ ተበተነ፡፡
በየካቲት 1/1954 ዓ.ም በገነት የቀ.ኃ.ሥ የጦር ትምህርት ቤትም ተገኝቶ የ21ኛውን የመምሪያ መኮንኖችና የዕጩ መኮንኖች ኮርስ ጨርሰው ለወጡት ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማና የምስክር ወረቀት ንጉሠ ነገሥቱ ሲሰጡ የክብር እንግዳ ሆኖ ተገኝቶ ነበር፡፡ በየካቲት 2/1954 ዓ.ም የወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳረጋገጠው ከሆነ፣ “በዚሁ የ21ኛው ኮርስ የምረቃ በዓል ላይ፣ ጥሪ የተደረገላቸው የሚሊታሪ አታሼዎችና ሰሞኑን በአፍሪካ አዳራሽ ውስጥ ስለአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄ ስብሰባቸውን የጀመሩት መልዕክተኞች በሙሉ በሥነ በዓሉ ላይ እንዲገኙ በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት ተገኝተው ስለነበሩ፤ ግርማዊ ጃንሆይ እንግዶቹን እየተቀበሉ የእጅ ሰላምታ ሰጥተዋቸዋል፤” ይላል፡፡ ስለሆነም፣ ሰውዬው በገነት ጦር ትምርት ቤት ተገኝቶ ይጉሡን እጅ ጨብጧል፡፡ ለዚህም ነው፤ ሁኔታውን አስታውሶ ከሠላሳ ሦስት ዓመታት በኋላ ባሳተመው “Long Walk To Freedom” በተባለው መጽሐፉ በ47ኛው ምዕራፍ ላይ ዕለቱን እንዲህ ሲል ዘክሮታል “…Meeting the Emperor himself would be like shaking hands with history…” (ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር መገናኘትና መጨባበጥ በራሱ፣ ከታሪኬና ከአፍሪካዊነት ታሪክ ጋር አንደመጨባበጥ ያለ ነው!” ያለው፡፡ 
እንደአዲስ ዘመን ዘገባ ከሆነ፣ ከጧቱ 3፡00 ሰዓት ላይ ንጉሠ ነገሥቱ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ሲደርሱ የመከላከያ ሚኒስትሩ ክቡር ሌትናንት ጄኔራል መርድ መንገሻ፣ ክቡር የጦር ኃይሎች ጠ/ኤታማዦሩ ሌትናንት ጄኔራል ከበደ ገብሬ፣ የምድር ጦር ዋና አዛዡ፣ ክቡር ሜ/ር ጄኔራል ኢሳያስ ገ/ሥላሴ፣ እና የትምህርት ቤቱ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ኃይሌ ባይከዳኝ ሲቀበሏቸው ሲያይ የተፈጠረበትን ስሜት እንዲህ ሲል መዝግቦታል፤ “Here, for he first time in my life, I was witnessing black soldiers commanded by black generals applauded by black leaders who were all guests of black head of state. It was a heady moment. I only hoped it was a vision of what lay in future for my own country…” በዚሁ ታሪካዊ ዕለት ማግስት፣ ንጉሠ ነገሥቱ በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ባደረጉት የእራት ግብዣ ላይ ተገኝቶ ንጉሠ ነገሥቱን አነጋግሯል፡፡ (አዲስ ዘመን፣ የካቲት 3 ቀን 1954 ዓ.ም፣ ገጽ 1) በእራት ግብዣውም ላይ ንጉሠ ነገሥቱ የጉባኤውን ተሳታፊዎች በየተራ ሲያነጋግሩ፤ የሰውዬው ተራ ደረሰና ማነጋገር ጀመረ፤ “የጦር ስልጠናም መሠልጠን” እንደሚፈልግ ነገራቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም የኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ማሰልጠኛን ዋና አዛዥ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩን ጠሩና ሰውዬውን ለሁለት ወራት ያህል በፈጥኖ ደራሽ ማሰልጠኛ ውስጥ እንዲያሰለጥኑት አዘዙ፡፡ ሰውዬው፣ በዕለተ ሰኞ የካቲት 5/1954 ዓ.ም፣ በኮልፌ የፈጥኖ ደራሽ ማሰልጠኛ ገብቶ መሠልጠን ጀመረ፡፡ እስከ ሚያዚያ 4/1954 ዓ.ም ድረስም በኮልፌ ማሰልጠኛ ጣቢያ እየተመላለሰ ይሰለጥን ነበር፡፡ 
ሰውዬው ስልጠና ከጀመረ ከሁለት ቀናት በኋላ፣ በየካቲት 7/1954 ዓ.ም አርፈው በየካቲት 8/1954 ዓ.ም ሥርዓተ ቀብራቸው በተፈጸመው እቴጌ መነን አስፋው ቀብርም ላይ ከብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩ ጋር ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሄዶ፣ ለቀበር የወጣውን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚገመት የአዲስ አበባ ነዋሪ ሕዝብ ለቅሶና ዋይታ አይቷል፡፡ በዚህ ጊዜ የጠበቃ ነፍሱ ምን እንዳሰበች የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው፡፡ በየካቲት 10 ቀን 1954 ዓ.ም የነበረውን የእቴጌይቱ የሳልስት ቀን አከባበርም አይቶ ተገረመ፡፡ ከዚያም ከየካቲት 12 ቀን 26 ቀን 1954 ዓ.ም ድረስ በተደረገው የአፍሪካ ኤኮኖሚ ኮሚሽን ጉባኤ ላይ ተገኝቶ ስለደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መንግሥትና እየተፈጸመ ሥላለው የዘር ልዩነትና ጭቆና ሠፊ ማብራሪያ ሰጠ፡፡ በጉባኤው ማጠቃለያም ላይ 25 ያህል ውሳኔዎችን ሲያስተላልፍ፣ የደቡብ አፍሪካን ጉዳይ በተመለከተ ጠንካራ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ አምስተኛው አንቀጽ እንዲህ ይላል፤ “ስለዘር ልዩነት፤ ደቡብ አፍሪካ አሁን የሚመራውን የዘር ልዩነት ፖሊሲ እስኪለውጥ ድረስ ከጉባኤው አባልነት እንዲፋቅ የአፍሪካ ኤኮኖሚክ ኮሚሲዮን ለተባበሩት መንግሥታት የኤኮኖሚና የሶሻል ምክር ቤት ሐሳብ አቅርቧል፡፡” (አዲስ ዘመን፣ የካቲት 27 ቀን 1954 ዓ.ም፣ ገፅ-3)፡፡
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ክፍል (በአምባሳደር ዮዲት እምሩ የሚመራ ነበር፤) በመጋቢት 8 ቀን 1954 ዓ.ም ስለደቡብ አፍሪካ ጉዳይ መግለጫ አወጣ፡፡ “የአፓርታይድ መንግሥት” ይላል መግለጫው “የአፍሪካውያኖችን የተመረጡና ለም የእርሻ መሬቶችና የማዕድን መሬቶች 88% ከጥቁሮች ላይ ነጥቆ ለአውሮፓውያን ጥቅም እንዲውሉ ሰጥቷል፡፡ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን፣ 12% በሚሆነው ደረቅና በረሃማ ሥፍራ  “ለጥቁሮች ብቻ” ተብሎ በተለየውና በታጠረው ሥፍራ እንዲሰፍሩ ተደርገዋል፡፡ በእነዚህ ድህነትና ችግር ባጠቃቸውም ስፍራዎች አፍሪካውያኖች እንዲሰደዱ ተገደዱ፡፡” እያለ ይቀጥላል (መጋቢት 10 ቀን 1954፤ ገጽ 3 እና 4)፡፡ ሰውዬው የውጭ ጉዳይ ባለስልጣናቱን ቀልብ ከመሳቡም በላይ፣ ወደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆዶ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወሰደውን አቋም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑም እንዲደግመው ጠየቀ፡፡ ዘረኛው የደቡብ አፍሪካ የነጮች ልዑክ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፍ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ የጃፓኑን ኦሎምፒክ አልሳተፍም እንድትል ጠየቀ፡፡ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ዋና ፕ/ት አቶ ይድነቃቸውም “ጉዳዬ ፓለቲካዊ ስለሆነ፣ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ገና ተነጋግሬበት ነው፤” ስላሉት ተበሳጭቶ ንጉሡን እንደዘለፈ ፓልራምፓን Bare Foot Runner ባለው የአበበ ቢቂላ ዘካሪ መጽሐፍ ላይ አስፍሮታል፡፡ (ገጽ 165-6)፡፡ የሰውዬው ጥያቄ፣ በኢትዮጵያ ባለሥልጣነት ዘንድ ተገቢውን ክብር አግኝቶ ኖሮ፣ ከስድስት ዓመታት በኋላ በሜሰኮው ኦሎምፒክ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካን ተሳትፎ በማውገዟና ሌሎች የአፍሪካ አገሮችንም በማስተባበሯ፣ ዘረኛው የደቡብ አፍሪካ የኦሎምፒክ ቡድን እንዳይሳተፍ ማዕቀብ ተጣለበት፡፡ 
ለሦስት ወራት ያህል ያለማሰለስ ስለ ANC /African National Congress) እና ስለ ደቡብ አፍሪካ የነጮች ዘረኛ መንግሥት ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲያዊ ሥራ ሲሰራ ከቆየ በኋላ፣ በሚያዝያ 5/1954 ዓ.ም የፈጥኖ ደራሽ ዋና አዛዡ ብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩ መረቁት፡፡ አንድ ቡልጋሪያ ሠራሽ የሆነ ሽጉጥ ከ200 ጥይቶች ጋር ሰጡት፤ ከዚያም ወደሀገሩ ለመመለስ ተዘጋጀ፡፡ እንደሄደ እንደሚታሰር የጠረጠሩት የኢትዮጵያ ባለስልጣናትም ለሰውዬው የኢትዮጵያዊ ፓስፖርት ሰጡት፡፡ ስሙም “ዱዋል ሰዋዬ” የሚል ሆነ፡፡ ትውልዱ በችዋን ላንድ ሲሆን፣ የትውልድ ዘመኑም 1910 ዓ.ም (እ.አ.አ 18/7/1918) ነው፡፡ ሥራውም ጋዜጠኛ የሚል ሆነ፡፡ የሚስቱ ፎቶ አልተለጠፈበትም፡፡ Long Walk to Freedom ባለው መጽሐፍ በ47ኛ ምዕራፍ ላይ እንደሰፈረው ከሆነ፣ ያረፈውም ራስ ሆቴል ነበር፡፡ ረፍት የለሽና ተናግሮ የመደመጥ ፀጋ ያለው ይህ ሰውዬ፣ በሚያዝያ አጋማሽ ላ ወደሀገሩ እንደተመለሰ ሰሞን ሊሌስሊፍ በተባለ ቦታ ሽጉጡንና 200ዎቹን ጥይቶች ራቅ አድርጎ ቀበራቸው፡፡ እነዚህ የኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ማሰልጠኛ ተቋም ሥጦታዎች እስከዛሬም ድረስ ደብዛቸው አልተገኘም፡፡ (በቅርቡ “Mandela’s Gun” በሚል ርእስ አንድ ጆን ኢርቪን የተባለ እንግሊዛዊ የፊልም ዳይሬክት ለፊልሙ ጥናት አዲስ አበባ መጥቶ ነበር፡፡)
ማጠቃለያ፤   
ከ28 ዓመት ከ2 ወራት ገደማ በኋላ፣ በሐምሌ 3/1982 ዓ.ም፣ የ27 ዓመታት እስሩን ጨርሶ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመገኘት ወደአዲስ አበባ መጣ፡፡ አዲስ አበባ የተለየች ሆነችበት፤ ለወራት አይደለም ለቀናትም እንደማይቆይባት ሳይታወቀው አልቀረም፡፡ ቦሌ አለማቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ ድረስ ሄደው፣ ፕ/ቱ ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ጓድ ብርሃኑ ባይህ ነበሩ፡፡ በ26ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤም ላይ ተገኝቶ ንግግር አደረገ፡፡ “አፓርታይድ ከምድረ-ደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን፣ ከመላው ዓለም እስኪወገድ ድረስ፣ ማዕቀቡ ተጠናክሮ እዲቀጥል አሳሰበ፤” (አዲስ ዘመን፣ ሐምሌ 3/1982፣ ገጽ-7)፡፡ ሰውዬው፣ በ1982 ዓ.ም በመጣ ጊዜ አዲስ አበባ የቆየው ለ24 ሰዓታት ብቻ ነበር፡፡ ለምን ከዚያ በላይ ለቆየት እንዳልፈቀደ መጠርጠር ካልሆነ በስተቀር፣ ትክክለኛውን ምክንያት ማወቅ ያስቸግራል፡፡ በ43 ዓመቱ ለ98 ቀናት ያህል የተንፈላሰሰባት አዲስ አበባ፣ ከ28 ዓመታት በኋላ በ24ኛው ሰዓት ጥሏት ነጎደ፡፡ ከዚያን በኋላም አልመጣም፡፡ በሐምሌ 19/1995 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሊሠጠው ቢጋብዘው ዝር ሳይል ቀረ፡፡ እግረመንገዱንም እነፕ/ር አንድሪያስ ያሰሩትን መስታወታማ ሕንፃ ይመርቃል ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ 
በወቅቱ አንዳንድ የግል ፕሬስ ውጤቶች፣ “ማንዴላ አልመጣም ያለው፣ ከዘረኞች እጅ ምንም አይነት ሽልማትም ሆነ ዲግሪ አልቀበልም በሎ ነው” ማለታቸውን አስታውሳለሁ (ጦቢያ፣ ልሳነ ሕዝብና አስኳል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡) ያም ሆነ ይህ፣ ማንዴላና ኢትዮጵያ ልብ ለልብ እንደተነፋፈቁ ይቀጥላሉ፡፡ ዛሬ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ማንዴላ የርቀት ት/ት ኮሌጅ ተከፍቷል፡፡ ከላይ እንዳወሳሁት፣ የማንዴላ ሕንፃ በአዲስ አበባ ዩቢቨርሲቲ ዋናው ግቢ ውስጥ ተሰይሟል፡፡ አርባ ምንጭ ከተማም ውስጥ “ማንዴላ” የሚባል ት/ት ቤት ተክቷል፡፡ አይ ማንዴላ! አይ “ሚ/ር ማንጄላ!” ኢትዮጵያ ውስጥ የቆየባቸውን ቀናት መቶ ሳየደፍን ሊሞት ይሆን እንዴ? ማን ያውቃል?! (ቸር ወሬ ያሰማን!) 
*********************************************************************************
ምንጭ:--http://semnaworeq.blogspot.com/

Tuesday, May 21, 2013

ከባሕል አምባ

                                 ጥር፣ጥምቀት፣ ፍቅርና ትዳር

                                                    ****************************በአለማየሁ ታደለ 


የፍቅረኛዋ ድንገት ከሰፈሩ መጥፋት ሲከነክናት የሰነበተችው ኮረዳ ከእለታት አንድ ቀን ማለዳ ተነስታ ውሃ ለመቅዳት ከመሰሎቿ ጋር ወደጅረት ስትሄድ ያን ፍቅረኛዋን ለምሳ የሚሆነውን ስንቅና ወንጭፉን ይዞ ወደ ማሽላ ጥበቃው ሲገሰግስ ታገኘዋለች፡፡ በዚያን ጊዜ ሲያብከነክናት የነበረው ትዝታው ይቀሰቀስባትና ናፍቆቷም ጤና ይነሳታል፡፡ መናፈቋን እንዲያውቅላትም በዘፈን አስመስላ ጓደኞቿ እንዳያውቁባት እንዲህ ትለዋለች፡፡
እያለ የሌለው ሲሹት የማይገኝ
እኔስ የሱ ነገር እረ ምን ይበጀኝ
ምንድነው ነገሩ ምንድነው ምስጢሩ
ለእይታ የጠፋው እንዲህ ከመንደሩ
እናወዛለሁኝ በውሃ ወረፋ
የሚረዳኝ የለም ብቻዬን ስለፋ፡፡
ብላ ለፍቅረኛዋ ናፍቆቷን ብታስተላልፍለት እሱም ሚስጢሩ ስለገባውና ምንም ያህል ብትናፍቀው የመኸር ወቅት ስለሆነ ጥበቃውን ትቶ ወደየትም መሄድ እንደማይችል ለመግለጽ እንዲህ ይላታል፡፡
የሆድ ነገር ሆድ ነው ትቼ አልመጣ ወፉን
አፋፍ ቁጭ ብለሽ አድምጪው ወንጭፉን
በማለት ጭውውትም ሆነ ፍቅር ከስራ በኋላ መሆኑንና ያለስራ መደሰት የሌለ መሆኑን እሱም መልሶ በግጥም ነገራት፡፡
ውድ አንባቢያን እንደምን ከርማችኋል? እነሆ አዲስ ብለን ከተቀበልነው 2004 ዓ.ም አራቱን ወራት ሸኝተን አዝመራው ፍሬ በሚያፈራበት፣ ጎተራው በሚሞላበት፣ የመኸር ወቅት ላይ ደረስን፤ እንኳን አደረሰን፡፡ ለዛሬው የርዕሳችን መነሻ የወጋችን መጠንሰሻ የመኸር ወቅትን ተከትሎ የሚመጣው የጥር ወር ነው፡፡ ለወራት ሲባክን ለከረመው አርሶ አደር የእፎይታ ወቅት የሆነው የጥር ወር በባላገሩ ህብረተሰብ ዘንድ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ማህበራዊ ትስስሩ የሚጠነክርበትና ጥንዶችም በጋብቻ ተጫብጠው ጎጆ ለመውጣት በጉጉት የሚጠብቁት ተመራጭ ወር ነው፡፡ ጥርን የፍቅርና የትዳር ወር ከሚያስብሉት ነገሮች አንዱ የጥምቀት በዓል በዚህ ወር ላይ መከሰቱ ነው፡፡
ጥምቀት በሀገር ቤት የኮረዳና ኮበሌዎቹ መተያያና መተጫጫ ሁነኛ ጊዜ ሲሆን የጥር ወር ደግሞ ጥንዶቹ በጋብቻ ተጫብጠው ለሶስት ጉልቻ የሚበቁበት ተመራጭ ወር ነው፡፡
ጥር፣ ጥምቀት፣ ፍቅርና ትዳር ሰምና ፈትል ናቸው በሚለው ከተስማማን ዘንዳ ከላይ በመግቢያችን ያየናቸው አይነት ባተሌ ፍቅረኞች ከሰብል ጥበቃ፣ ከእንስራ ሸከማ፣ ከኩበት ለቀማ፣ ከአክርማ ቀጨታና ከልብስ አጠባ ከመሳሰሉ የእለት ተዕለት ክንውንና የኑሮ ዘይቤው ግድ ከሚለው ዘለለታዊ ህይወት ለጊዜውም ቢሆን ተላቀው ከከንፈር ወዳጆቻቸው ጋር በነፃነት ከሚገናኙበት አብይ በዓል ከሆነው ጥምቀት ወጋችንን እንጀምራለን፡፡
ጥምቀት ከሀይማኖታዊ አከባበሩ ባሻገር ባህላዊ ጎኑ ያመዝናል፡፡ ከክርስትና እምነት ተከታዮች አበይት በዓላት አንዱ የሆነው ይኸው በዓል በአብዛኛው የሀገሪቱ ክልሎችና በመዲናችን አዲስ አበባም እንደጃንሜዳ ባሉ ሰፋፊ የህዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎችና አደባባዮች በዝማሬ፣ በእልልታ፣ በጭፈራና በሆታ ይከበራል፡፡ በዚህ በዓል ኮረዶችና ኮበሌዎች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ አምረውና ደምቀው ይወጣሉ፡፡ ወጣቶቹ ለፈቀዱት ከንፈር ወዳጅ ሎሚ ብቻ ሳይሆን ለዛ ያላቸውን የፍቅር ስንኞችንም ይወረውራሉ፡፡
በቀደመው ጊዜ ነው አሉ አንዲት አፍቃሪ የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ጃንሜዳ አካባቢ በአይን ፍቅር ትብሰከሰክለት የነበረውን አንድ የአራዳ ጎልማሳ ድንገት ታገኘውና አጋጣሚውን በመጠቀም ፍቅሯ እንደፀናባትና ጓዟን ጠቅላ መግባት እንደከጀለች እንዲህ በማለት ገለፀች ይባላል፡፡
በፍቅርህ ስቃጠል ሆነህ ለልቤ እሳት
ታቦታቱን ሳስስ ሳስጨንቅ በስለት
ልመናዬን ሰማ ይመስገን አቤቱ
አምላኬ ላከልኝ በእለተ ጥምቀቱ
አራዳ ገበያ ይሸጣል ባርኔጣ
ትችለኝ
እንደሆን ከነጓዜ ልምጣ፡፡ ብትለው ወዲህ የሷ ልጅነት እና የሱ ጎልማሳነት እያሳሰበው፣ ወዲያ ደግሞ የልጅቷ ውበት እያነሆለለው
"አይ፣ አይ፣ ልጅም አይደለሽ
ለምንስ ቸኮልሽ?" ቢላት እሷ ደግሞ መለስ አድርጋ
ምነው ትለኛለህ ልጅ ገና ልጅ ገና፣
ዶሮም ትበላለች አጥንቷ ሳይጠና፡፡ 
ብላ ገላገለችው፡፡
እርሱም ምንተፍረቱን ወደማርጀት የተጠጋና ጠና ያለ ሰው መሆኑን ቢገልፅላት መች ልትሰማው፡፡ ጭራሽ የመጣው ይምጣ ብላ
አረጀህ አረጀህ የሚልብኝ ማነው
ዶሮም የሚወደድ ገብስማ ሲሆን ነው፡፡ 
ብላ ያሰበችውን አሳካች፡፡ እሱም በውበቷ እንደተማረከና በሷም ደስ እንደሚለው ለመግለፅ
እስቲ ወዲያ ሄደሽ ወዲህ ተመለሽ
እኔም ደስ ይበለኝ አራዳም ይይሽ፡፡ 
የሚለውን ዜማ እያንጎራጎረ ይዟት በረረ ይባላል፡፡
ዛሬ ዛሬ በጥምቀት ጃንሜዳ ላይ ይሰሙ የነበሩ እነዛ ለዛ ያላቸው ባህላዊ ግጥሞች ድሮ ቀሩ በሚባሉበት ደረጃ ላይ የደረሱ ይመስላል፡፡ በቀደመው ዘመን ጃንሜዳ የታደመ ማንኛውም ሰው ይሰማቸው የነበሩ አንዳንድ ባህላዊ ዘፈኖች መልካቸውን እየቀየሩ እንደመጡም ይገነዘባል፡፡ ድሮ ይዜሙ የነበሩ
ሎሚ ብወረውር ደረቱን መታሁት
አወይ ኩላሊቱን ልቡን ባገኘሁት፡፡ 
መሰል ልብ ስር ተጎዝጉዞ ፍቅርን ለመቋደስ ይቀርቡ የነበሩ የተለመዱ የፍቅር ተማፅኖ ዜማዎች ባለፈው አመት በታደምኩበት የጃንሜዳው ጥምቀት በዚህ መልኩ ተለውጠው ሲቀነቀኑ አድምጫለሁ፡፡
እባክህ አምላኬ አዲስ ዘመን አምጣ ፍቅር በቆርቆሮ ታሽጐ እንዲመጣ፡፡
ወርቃማ ባህላዊ ዘፈኖቻችን በመሰል ስንኞች ተተክተው ሲዜሙ ያደመጠ ሰው በርግጥም ወጣቱ ፍቅርን ባቋራጭ እየሻተ ከመምጣቱ ባሻገር ባህሉንም እየዘነጋ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
"የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው" እንዲሉ ፍቅር እንዴትም ሆኖ ቢመጣ ወደ ትዳር ከማምራት አስቀድሞ እርስ በእርስ መገማገም መጠናናትና ለቁም ነገር መብቃት ከፍቅር ሀሁ ጀምሮ ሊዘነጉ የማይገባቸው አበይት ተግባራት ናቸው፡፡ እንደቀደመው ዘመን
የአይኔ ማረፊያ የነፍሴ ትፍስህት
ካንቺ ጋራ አድሬ ሲነጋ ልሙት፡፡ አይነት እንጉርጉሮ በዚህ ዘመን እንደተመኙት የምር ይገድላልና ጠንቀቅ ማለቱ ይበጃል፡፡ እንዲህ በየቦታው ስለጥምቀትና መጠናናት ሲወጋ ትዝ የምትለኝ አንዲት አብሮ አደግ ጓደኛዬ አለች፡፡ ልጅቱ ውብናት፡፡ ውብ ብቻ አይደለችም ባለቅኔው እንዳለው
"የናት ያባቷን ቅርስ አጥብቃ የያዘች
ወንድ ሲስቅላት ግንባር የቋጠረች
በቁጣ ግልምጫ አፈር ያለበሰች፡፡ ሁለመናዋ የሚያባብል ኮረዳም ጭምር ናት፡፡ እናም ይቺ ልጅ የፍቅርን ሀሁ ያስጀመራትን የመጀመሪያ ፍቅሯን አትረሳውም፡፡ የከተራ እለት ታቦታቱን ወደ የማደርያዎቻቸው ለማስገባት ሲባል በተከሰተ ግርግር የወደቀችዋን ቆንጆ ከመረጋገጥ የታደጋት አንድ ወንዳወንድና መልከ መልካም ወጣት ቀልቧን ገዛው፡፡ ልጁ በልጅነቷ የም ትመኘውን አይነት ወንድ ነበረና የፍቅር ጥያቄ ሲያቀርብላት እንደሌሎቹ ወንዶች ምላሿን አልነፈገችውም፡፡ "ጉድና ጅራት ወደኋላ" እንዲሉ ያቺ ጠንቃቃ ልጅ በጨቅጫቃ መዳፍ ውስጥ እንደወደቀች ዘግይታ ተረዳች፡፡ አፍቃሪዋ በተደጋጋሚ እኩለ ሌሊት ላይ በተንቀሳቃሽ ስልኳ ይደውልላታል፡፡ ልጅቱ በድንጋጤ ከእንቅልፏ ባንና ስልኩን ታነሳና "ሄሎ" ትላለች፡፡ አፍቃሪው የረባ ሰላምታም ሳያቀርብ "የት ነሽ?" ይላታል፡፡ "ቤት ነኝ ተኝቻለሁ፡፡; እንግዲያውስ በቤት ስልክ እደውላለሁ፡፡" ይላታል፡፡ ድንገት የቤት ስልኳ ከተበላሸ ደግሞ "እስቲ የቴዲ አፍሮን ዘፈን ክፈቺልኝ::" ብሏት ላምባዲና አላምን አለና … ወዘተ ዘፈኖችን በስልኩ እየኮመኮመ ይነዘንዛታል፡፡ በቤት ውስጥ መብራት ከሌለና ቴፕ መክፈት ካልቻለች "ማንኪያና ስኒ አጋጭልኝ፡፡" ይላትና በሌሊት ሻማ ለኩሳ ማንኪያና ስኒ ለማጋጨት ረከቦት ፍለጋ ትማስናለች:: ይቺ ልጅ ታዲያ ፍቅራቸው ሶስተኛ ወሩን እንዳገባደደ ልጁን ትጠራውና አንተ "ቦዲጋርድ; እንጂ "ቦይፍሬንድ; መሆን ስለማትችል በቃኸኝ ብላ ስቃይዋን አበቃች፡፡
እንግዲህ ከጋብቻ በፊት መጠናናት ቢያንስ ብዙ ከመራመዳችን አስቀድሞ እንዲህ እንደልጅቱ የማያዳግም ውሳኔ ለማሳለፍ የሚረዳ ቢሆንም በእንጠናና እና በሁነኛ ሰው ፍለጋ ሰበብ በስተርጅናም ከቤተሰብ ጋር የምንኖር ላጤዎችም አንታጣምና ከወዲሁ ልናስብበት ይገባል፡፡ የእድሜ ጣርያ አርባ ቤት ውስጥ በሚጫወትባት ኢትዮጵያ ይህ እድሜ ጉድጓድ የመማሻ እንጂ ፍቅር መጠንሰሻ ስላይደለ ቢያንስ ለምንወልዳቸው ልጆች በማሰብ ፈጠን ማለቱ አይከፋም፡፡ በተገረዙበት ቤት መገነዙስ አይከብድም ትላላችሁ?
ይህን ጉዳይ ካነሳሁ አይቀር ከአባባሌ ጋር የሚዛመድ የአንድን ሰው ታሪክ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ ሰውየው ለወላጆቹ አንድያ ልጃቸው ነው፡፡ አሳድገውና ለቁም ነገር አብቅተውት በአንድ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ተቀጥሮ ወፍራም ደሞዝ ያገኛል፡፡ ወላጆቹ ከሀያዎቹ እድሜው አንስቶ እንዲያገባና ዘራቸውን እንዲቀጥል ቢወተውቱትም ሁነኛ ሚስት ፍለጋ በሚል ሰበብ ሰላሳዎቹን ያልፋል፡፡ ቤተሰቡ በወዳጅ ዘመድ ቢያስመክሩትም በድጋሚ "ትዳር ዝም ብሎ ማንም የሚደልቀው ከበሮ አይደለም ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡" እያለ የመጣውን ሁሉ በመመለስ አርባዎቹን ይሻገራል፡፡ ከእለታት አንድ ቀን አባት ወደ ልጃቸው ቤት በማምራት ለመጨረሻ ጊዜ የማያገባበትን ምክንያት እንዲያስረዳቸው ይጠይቁታል፡፡ ልጅ አሁንም ሁነኛ ሚስት ማግኘት እንዳልቻለ ያስረዳል፡፡ አባትየውም በእጅጉ ተገርመው "አንተ ልጅ በዚህ ሀገር ላይ እየፈለግክ ያለኸው ሚስት ነው ወይስ ነዳጅ; አሉት ይባላል፡፡
ምንም እንኳ እንደ ሰውየው ባናበዛውም የትዳር አጋር ፍለጋና መጠናናቱ በብልሀት መሆኑ ይደገፋል፡፡ መገማገሙ አብቅቶ ትዳር ሲታሰብም በተለይ በከተሞች ከጋብቻ ይልቅ በየዓመቱ የፍቺ ቁጥር እያደገ የመምጣቱን ጉዳይ ከቁም ነገር ልንጥፈው ይገባል፡፡ ግንኙነታችን የተመሰረተው በጥቅም ወይስ በፍቅር የሚለው ጉዳይም መጤን አለበት፡፡እንዲህ በጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ሲወሳ የሚነገር አንድ አፈታሪክ አለ፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡
ሰውየው በአንድ ምሽት ከተዋወቃት ከአንዲት ባለመሸታ ቤት ጋር በጊዜው እንደ መገበያያ የሚያገለግለውን ሁለት አሞሌ ጨው ከፍሎ አብሮ ለማደር ይስማማል፡፡ አዳር ላይ ሁለቱም ይስማሙና ለዘለቄታው አብሮ ለመኖር ይወስናሉ፡፡ እሷም ያላትን ገንዘብ ለሱ ሰጥታ ንግድ ይጀምራሉ፡፡ ኑሮ "ፏ"ይላል፡፡ ንብረት በንብረት ሀብት በሀብት ይሆናሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ 10 ዓመታት ከቆዩ በኋላ ሰውየው በዘመዶቹ ሴትኛ አዳሪ አግብቶ መኖሩ ተገቢ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ስለተነገረው እሱም አምኖበት ያባርራታል፡፡ ሴትየዋ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ብትከሰውም ሰማንያ የሌላት በመሆኑ ንብረቱን መካፈል እንደማትችል እየተነገራት ትመለሳለች፡፡ ተስፋ ያልቆረጠችው ሴት በጊዜው አባመላ ወደ ሚባሉ ሹም በማምራት ጉዳይዋን በድጋሚ እንዲያዩላት ደጅ ትጠናለች፡፡ ሹሙም ይስማሙና ባልና ሚስት ባሉበት ጉዳያቸው ይታያል:: ሁለቱም የመከራከርያ ሃሳባቸውን አሰምተው እንዳበቁ ሹሙ ፍርድ ሰጡ፡፡ በፍርዳቸውም ሚስት ሰማንያ ወረቀት የሌላት በመሆኑ ንብረት የመካፈል መብት እንደሌላት ይወስናሉ፡፡ ሆኖም በመጀመሪያ ቀን አብረው ሲያድሩ በተስማሙት መሰረት ከ10 ዓመታት በላይ አብራው ላደረችበት ለያንዳንዱ ቀን ሁለት አሞሌ ጨው አስቦ እንዲከፍላት ወስነው ችሎቱን ዘጉ ይባላል:: በቡዳ ቤት ሰላቢ ገባ ይላችኋል ይሄ ነው፡፡ በአጠቃላይ ብቸኝነት አንገፍግፎት ከወዳጁ ጋር ተጠቃሎ ሶስት ጉልቻ ለማበጀት የሚፈልግ እንዳለ ሁሉ ለጥቅም ሲል መዳበል የሚፈልግም ይኖራልና መጠርጠሩ አይከፋም፡፡
በተረፈ ሁሉንም ደረጃዎች አልፋችሁ በጥር ወር ለትዳር የምትበቁ ጥንዶች እንኳን ለዚህ ክብር አበቃችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡ በግምገማ ላይ ላላችሁ የከርሞ ሙሽራ ያድርጋችሁ በማለት ከወዲሁ እሰናበታለሁ፡፡

*****************************************************
ምንጭ--:WWW.addisababacity.gove,et