የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች
(ከጥቅምት 14 ቀን 1900 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ.ም. __118 ዓመት)
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሚኒስትሮች የተሾሙት
ጥቅምት 14 ቀን 1900 ዓ.ም ነው ።
በዳግማዊ አጤ ምኒልክ የተሾሙት የመጀመሪያዎቹ ሰባት ሚኒስትሮች የሚከተሉት ናቸው፦
1. ኣፈንጉሥ ነሲቡ መስቀሉ...የዳኝነት ሚኒስትር
2. ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ...የጦር ሚኒስትር
3. ፀሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ወልደ አረጋይ...የጽሕፈት ሚኒስትር
4. በጅሮንድ ሙሉጌታ.....የገንዘብና የጓዳ ሚኒስትር
5. ሊቀ መኳስ ከተማ.......ያገር ግዛት ሚኒስትር
6. ነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ....የንግድና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
7. ከንቲባ ወልደ ጻዲቅ ጐሹ......የርሻና የመሥሪያ ሚኒስትር
.....የሮፓን ፡ ሥርዓት ፡ በአገራችን ፡ በኢትዮጵያ ፡ ካሰብን ፡ ብዙ ፡ ጊዜ ፡ ነው ። እናንተም ፡ የሮፓ ፡ ሥርዓት ፡ በኢትዮጵያ ፡ ቢለመድ ፡ መልካም ፡ ነው ፡ እያላችሁ ፡ ስታመለክቱኝ ፡ ነበር ። አሁንም ፡ የእግዚአብሔር ፡ ፈቃዱ ፡ ሆኖ ፡ ለመፈፀም ፡ ቢያበቃኝ ፡ ምኒስትሮች ፡ ለመሾም ፡ ዠምሬ ። አፈንጉሥ ፡ ነሲቡን ። ፊታውራሪ ፡ አብተ ፡ ጊዮርጊስን ። ጸሐፌ ፡ ትእዛዝ ፡ገብረ ፡ ሥላሴን ። በጅሮንድ ፡ ሙሉጌታን ። ሊቀመኳስ ፡ ከተማን ። ነጋድራስ ፡ ኃይለጊዮርጊስን ። ከንቲባ ፡ ወልደጻዲቅን ፡ አድርጌአለሁና ፡ ይህንን ፡ እንድታውቁት ፡ ብዬ ፡ ነው ።
ጥቅምት ፲፬ ቀን ፲፱፻ ዓመተ ምህረት አዲስ አበባ ተጻፈ
ሚኒስትሮቹ ከተሾሙ ከ15 ቀናት በኋላ ደግሞ ለሚኒስትሮቹ መመሪያ የሚሆን ደንብ አወጡ። የወጣውንም ደንብ በሚቀጥለው ደብዳቤ ሸኚነት ለእያንዳንዱ ሚኒስትር ላኩላቸው ።
የመንግሥት ሥርዓት ባገራችን በኢትዮጵያ የሮጳ ሰው ነገሥታቱም ቆንሲል ሁሉ ገቡ። እነዚህም በኢትዮጵያ መንግሥት ሥራት ያልተለመደ ነው። ሥራት የሌለው አገር ምን መንግሥት ይባላል እያሉ አገራችን መወረፉን ታውቃላችሁ። ለመውሰድም በኛ ላይ እንደተነሱም ታውቃላችሁ።
አሁንም ምንም የቀድሞው የኢትዮጵያ ሥራት ቢኖር ከጥቂት ቀን በኋላ ቀርቷልና አገራችንን እንደ አሮጳ ሥራት ለማድረግ አስቤ ይሄንን ባንደኛ ወረቀት የተፃፈውን ደንብ ጽፌላችኋለሁና በዚሁ ባስያዝኳችሁ ሥራ ሳትጣሉ ፡ ሳትመቀኛኙ በእውነት እርስ በርሳችሁ ተስማምታችሁ ጠንክራችሁ መንግሥታችንን መርዳት ነው።
እንዲህ ሁነን በሚገባ ሥራት ሕዝባችንን ጠብቀን ከያዝነው ለመንግሥታችንና ለሀገራችን ጥቅም ይሆናል። አገራችንን ሌላ አይመኘውም። እኔም እስካሁን ብደክም ብደክም ሚኒስቴር ፡ መማክርት ፡ ቆንሲል የለበት ፡ ባንድ ሰው አሳብ ብቻ እያሉ አሙን እንጂ አላመሰገኑንም።
አሁንም እንቅልፍ ሳትወዱ ፡ መጠጥ ሳታበዙ ፡ ገንዘብን ጠልታችሁ ፡ ሰውን ወዳችሁ ፡ ተግታችሁ ይሄንን ሥራ እንድትፈፅሙልኝ ተስፋ አለኝ። ለዚህ ሥራ እኔ እናንተን አምኜ ስላደረግሁ እናንተም የምታምኑትን ፡ ገንዘብ የማይወደውን ፡ ድሃ የማይበድለውን ፡ እናንተን የሚረዳችሁን ሰው እየፈለጋችሁ እያመለከታችሁኝ ከሥራው ማግባት ያስፈልጋችኋል።
ገንዘብም ቢሆን እኔ ደሞዝ እሰጣለሁ እንጂ ከድሃ ፡ እንኳን ትልቅ ገንዘብ አንድ መሀለቅም እንኳ ቢሆን ከዚያው ከተወሰነለት ከግብሩ በቀር ሌላ እንዳይነካ ማድረግ ነው። ከዚህ ከተጻፈው ደንብ አልፋችሁ ድሃ አላግባብ የተበደለ እንደሆነ እኔም እጠላችኋለሁ። እናንተም ትዋረዳላችሁ። በነፍሳችሁም በወንጌል ፡ በመስቀል አምላችኋለሁ አስገዝታችኋለሁ።
የመጀመሪያዎቹ ሰባት ሚኒስትሮች ተሹመው ሥራ ከጀመሩ በኋላ ሥራ የሚበዛበትና አስፈላጊ የሆኑ ሚኒስቴሮች እየተከፈቱ በተጨማሪ አዛዥ መታፈሪያ የግቢ ሚኒስትር ፡ ቀኛዝማች መኰንን ተወንድ በላይ የሥራ ሚኒስትር ተብለው ተሾሙ ። የፖስታና የቴሌፎን ሥራ በዚያን ጊዜ እጅግም ያልተስፋፋ ስለነበረ በግቢ ሚኒስቴር ሥር ሆኖ የበላይ አለቃ ልጅ በየነ ይመር የፖስታ ቴሌግራፍና ቴሌፎን ሹም ተብለው ተሾሙ ።
ዳግማዊ አጤ ምኒልክ የመጀመሪያዎቹን ሚኒስትሮች ከሾሙ ከአምስት ወር በኋላ ደግሞ ለጠቅላላ ተሿሚዎቹ የሚከተለውን ደብ ዳቤ ፃፉላቸው ።
እኔ እናንተን ምንስቴርም ፥ ወንበርም መሾሜ ለመንግሥታችንና ለሕዝባችን ጥቅም እንዲሆን ነው ።አሁንም በዚህ ባስያዝኳችሁ ሥራ ሳትጣሉ ፥ ሳትመቀኛኙ እንቅልፍ ሳትወዱ መጠጥ ሳታበዙ ገንዘብ ጠልታችሁ ፡ ሰውን ወዳችሁ እርስ በርሳችሁ ተስማምታችሁ ፥ ጠንክራችሁ ፡ በውነት መንግሥ ታችንን እንድትረዱ ይሁን። በዚህም በያዛችሁት ሥራ ከእውነተኛው ነገር በቀር እገሌን አንወደውም በዚህ ነገር እንጉዳው እንዳትሉ ። ገንዘብም መተያያ ብትቀበሉ ገንዘብ ሰጥቶናል ብላችሁ ሳታደሉ ፥ በእውነት ሕዝባችንን ልትጠብቁ አምኛችኋለሁና እናንተም በዚሁ ቃል ታመኑልኝ።ሚያዝያ ፩ ቀን ፲፱፻ ዓመተ ምህረት አዲስ አበባ ከተማ ተፃፈ "
============================
ምንጭ:- ጳውሎስ ኞኞ አጤ ሚኒሊክ


