ከደራሲያን ዓምባ

Tuesday, August 25, 2015

ፋኖስና ብርጭቆ

 
 
 
 
አንድ የፋኖስ መብራት በግብሩ የኮራ፤
እንዲህ ሲል ተጣላ ከብርጭቆ ጋራ፡፡
‹‹እኔ ነኝ መብራቱ ብርሃን የምሰጥ፤
ጨለማን አጥፍቼ የምገላልጥ፡፡
አንተ ግን ከፊቴ እንዲህ ተደንቅረህ፤
ዙሪያዬን ከበኸኝ እንዲያው ተገትረህ፡፡
አልገባኝም ከቶ የምትሰራው ስራ፤
ብርሃኔ ሩቅ ደርሶ ደምቆ እንዳያበራ፤
አንተን ፈጠረብኝ መንገድ የምትዘጋ፡፡
እንቅፋት እየሆንክ ስራዬን አታጥፋ
ገለል በል ከፊቴ ብርሃኔ ይስፋፋ፡፡››
‹‹አገልግሎቴማ ከሆነብኝ ጥፋት፤
እውነት ላንተ ከሆንኩህ እንቅፋት፡፡
ልሂድልህ›› ብሎ ሲለቅለት ቦታ፤
ከጎን የነፈሰ የንፋስ ሽውታ፣
መጣና መብራቱን አጠፋው ባንዳፍታ፡፡
አጭር እየሆነ ተመልካችነቱ፣
መለየት አቅቶት ጥቅሙን ከጉዳቱ፣
እወቁኝ እወቁኝ እያለ ሲነሳ
ሰውም እንደዚሁ ያመጣል አበሳ፡፡

(/ ከበደ ሚካኤል)

ታላቁ ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን ከ1925-1979

ከ1925-1979 ዓ. ም.
==============
ኢትዮጵያ ውስጥ በ1925 ዓ.ም አንድ ታላቅ ሰው ተወለደ። ይህ ሰው እያደገ ሲመጣ የብዙ ሚሊዮን ህዝቦችን ታሪክ፣ ባህል፣ እምነትና አስተሳሰብ የሚገልፅ ደራሲ ለመሆንም በቃ። ብዕሩ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ላይ በሰፊው ያተኩራል። የዚህችን ሀገር ታላላቅ ጀግኖች ታሪክ እያነበበ እና እየመረመረ ለትውልድና ለእናት ምድራቸው ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ውበትና ለዛ ባላቸው የገለፃ ጥበቦቹ እየፃፈ የሚሊዮኖችን መንፈስ ሲያረካ ኖሯል። ኢትዮጵያም ታላላቅ ደራሲዎቿን ማነሳሳት ስትጀምር ስሙ እና ተግባሩ ከፊት ከሚሰለፉት የብዕር አርበኞች መካከል ያደርገዋል። አንዳንድ ሃያሲያን ደግሞ የተዋጣለት የድርሰት ገበሬ ነው ይሉታል። በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ ለዘላለም እንደ ከዋክብት ሲያበሩ ከሚኖሩት ደራሲያን እና ፀሐፊ- ተውኔቶች ውስጥ ታላቁን የሊትሬቸር ሰው ብርሃኑ ዘሪሁንን በጥቂቱ አነሳሳላችኋለሁ።
ብርሃኑ ዘሪሁን የተወለደው ድሮ የበጌምድር ጠቅላይ ግዛት ርዕሰ ከተማ በሆነችው እና በተለይም የ17ኛው እና የ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የስልጣኔ ማዕከል እንደነበረች በሚገለፅበት በሰሜናዊቷ ክፍለ -ግዛት በጎንደር ከተማ ነው። ዘመኑም 1925 ዓ.ም ነበር። አባቱ መሪ ጌታ ዘሪሁን መርሻ የሚባሉ ሲሆን እናቱ ደግሞ ወ/ሮ አልጣሽ አድገህ ይባላሉ። አባቱ መሪ ጌታ ዘሪሁን የቤተ-ክህነት ሰው ስለነበሩ እና በዘመናቸውም የተማሩ ስለሆኑ ለልጃቸው ትምህርት የሚጨነቁ ነበሩ። እናም አራት ዓመት ሲሆነው እቤት ውስጥ ከርሳቸው ዘንድ የሚማረው ትምህርት ተጨምሮ የቤተ-ክህነትን ትምህርት ተማረ።
ብርሃኑ ዘሪሁን ጎንደር ውስጥ የሚሰጠውን የቤተ-ክህነት ትምህርት ከተከታተለ በኋላ ወደ ዘመናዊ ት/ቤት ገባ። ይህ ዘመናዊ ት/ቤት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ት/ቤት በመባል ይጠራ ነበር። ብርሃኑ ዘሪሁን የሀገሩ ኢትዮጵያን ባህላዊ፣ ታሪካዊና ኃይማኖታዊ ትምህርቶችን በቤተ-ክህነት ውስጥ ከተከታተለ በኋላ ወደ ዘመናዊ ት/ቤት ሲገባ ልዩ ተሰጥኦው ብቅ አለ። ይህም አንባቢነት ነው። ፈረንጆቹ “Book Worm” እንደሚሉት መፅሐፍን የሚያነብ ብቻ ሳይሆን እንደ ምግብም የሚጠቀምባቸው አይነት ሰው እንደነበር የህይወት ታሪኩ ያወሳል።
ብርሃኑ ዘሪሁንን ቀልቡን ከሚከቡት ታሪኮች መካከል ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው። ኢትዮጵያን በመፃህፍቶቿ አማካይነት እያነበባት አወቃት። እርሱ ያልነበረበትን ዘመን በሰፊ ንባቡ እና ጠያቂነቱ የማንነቱን ክፍተት ሞላው። እናም ሙሉ ኢትዮጵያዊ እየሆነ መምጣት ጀመረ።
የብርሃኑ ዘሪሁንን ቀልብ ከሳቡት ታላላቅ መፃህፍት ውስጥ ደብተራ ዘነብ የፃፏቸው ታሪኮች ናቸው። አንደኛው የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክን የሚያወጣው መፅሀፍ ነው። ደብተራ ዘነብ በቴዎድሮስ ቤተ-መንግስት ውስጥ የነበሩ እና ከቴዎድሮስ ጎን የማይጠፉ የዚያን ዘመን ሊቅ ብሎም ፈላስፋ ናቸው። ታዲያ እርሳቸው የፃፉትን የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ብርሃኑ ዘሪሁን ይወደው ነበር። ከዚህ መፅሀፍ በተጨማሪም ደብተራ ዘነብ “መፅሀፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሳዊ” የተሰኘች መፅሐፍ አለቻቸው። ይህች መፅሃፍ ሃይማኖት ላይ መሰረት አድርጋ የተዘጋጀት ከኢትዮጵያ የፍልስፍና ጽሁፎች መካከል አንዷ ናት። ብርሃኑ ዘሪሁን ይህችን መፅሀፍ የመፅሀፎች ሁሉ ቁንጮ አድርጓት በየጊዜው ያነባት ነበር። በነገራችን ላይ ይህች መፅሃፍ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሳዊ በውስጧ ምን ቢኖር እንዲህ የተወደደችው ለሚል ሰው ሁለቱን ነጥቦች ብቻ ጠቅሼ ልለፍ።
መፅሃፏ በዋናነት አላማዋ ሃይማኖትን ማስተማር ቢሆንም፣ የተጻፈችበት ቴክኒክ ግን ፍፁም በተለየ አቀራረብ ነው። ለምሳሌ ፈጣሪን የምትወቅስ እየመሰለች የፈጣሪን ታላቅነት የምታስተምር ናት። እንዲህ የሚል ሃሳብ አለባት “እየሱስ ስራብ አላበላችሁኝም፣ ስጠማ አላጠጣችሁኝም፣ ስታረዝ አላለባሰችሁኝም ይለናል። ለመሆኑ ከርሱ የበለጠ ሃብታም አለ ወይ? ለምን ይጨቀጭቀናል. . .” እያሉ ደብተራ ዘነብ ጽፈዋል። የደብተራ ዘነብ አፃፃፍ በዚህ ብቻም አያቆምም። እንዲህም የሚል ሃሳብ ያንፀባርቃል። “እንደ አይሁድ ጅል አላየሁም” የአለሙን ጌታ በ30 ዲናር ሸጠው። ወየሁ እኔ ባገኘሁት” እያለ ከተለመደው የስብከት መንገድ ወጥቶ ሌላ የአፃፃፍ እና የአተያይ መንገድ የከፈተ መጽሐፍ ነው። ብርሃኑ ዘሪሁን ደብተራ ዘነበን አእምሮው የተሳለ ፈላስፋ ይላቸው ነበር። እናም ደብተራ ዘነብ የብርሃኑ ዘሪሁንን አእምሮ ገና በልጅነቱ ስለውለታል ማለት ይቻላል።
በነገራችን ላይ ደብተራ ዘነብ የአፄ ቴዎድሮስን ልጅ ልዑል አለማየሁን በቤት ውስጥ የሚያስተምሩ መምህርም ነበሩ።
ብርሃኑ ዘሪሁን በንባብ ልምዱ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ከሚላቸው መካከል ነጋድራስ /ፕሮፌሰር/ አፈወርቅ ገ/እየሱስን ነው። እርሳቸውም በኢትዮጵያ የታሪክ እና የልቦለስ ጽሁፍ ውስጥ ከከፍተኛ ተዕዕኖ ፈጣሪ በመሆናቸው የብርሃኑ ዘሪሁንን የልጅነት እውቀት በመፃፍቶቻቸው አስፍተውለታል። የነ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ስላሴ እና የክብር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል መፃህፍት ኢትዮጵያዊ እውቀቱን በከፍተኛ ደረጃ እንዳጎለመሱለት ይነገራል።
ብርሃኑ ዘሪሁን በ1945 ዓ.ም ላይ ብዙ እውቀቶችን ከገበየበት ጎንደር ከተማ ተነስቶ አዲስ አበባ መጣ። በአዲስ አበባም ቆይታው ተግባረ ዕድ ት/ቤት ገብቶ የሬዲዮ ቴክኒሻንነት በመማር በ1948 ዓ.ም ላይ በዲፕሎማ ተመረቀ። ታዲያ በዚያ በምረቃ ወቅት ከተማሪዎቹ ሁሉ አንደኛ ወጥቶ ተሸላሚ የነበረው ብርሃኑ ዘሪሁን ነው።
ብርሃኑ ዘሪሁን ተግባረ ዕድ ት/ቤት ሲማር የታላላቅ የአለማችንን ደራሲያን ስራዎችን ለማንበብ ዕድሉን አገኘ፡ የነ ዊሊያም ሼክስፒርን፣ የአሌክሳንደር ዱማስ ፔሬን፣ የቻርልስ ዲክነስን፣ የነ አሌክሳንደር ፑሽኪንን እና የሌሎችንም መፃህፍት አነበበ። እውቀቱንም እያስፋፋ መጣ። በንባብ የተከማቸው እውቀቱም በፅሁፍ መውጣት ጀመረ። እዚያው ተግባር-ዕድ ት/ቤ ሲማር የት/ቤቱ ልሳን የነበረችውን “ቴክኒ-ኤኮ” የምትሰኘውን መፅሄት አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል። ከዚህ በተጨማሪም እዚያው ተማሪ ሳለ በ1947 ዓ.ም ተውኔት ጽፎም አሳይቷል። እናም እንግዲህ በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ሊወስድ ብርሃኑ ዘሪሁን የሚባል ብዕረኛ ወደ አደባባይ ብቅ ማለት ጀመረ።
ብርሃኑ ዘሪሁን ተግባረ ዕድ ውስጥ ውጤቱ ከፍተኛ ስለነበር እዚያው ት/ቤት ውስጥ ተቀጠረ። ከት/ቤቱ ውስጥም ሆኖ ለተለያዩ ጋዜጦች ይፅፍ ነበር። ከተግባረ ዕድ ት/ቤት በመልቀቅ በወቅቱ አጠራር የጦር ሚኒስቴር በአሁኑ መከላከያ ሚኒስቴር በሚባለው መስሪያ ቤት በአስተርጓሚነት ተቀጥሮ መስራት ጀመረ። እዚያም ብዙ ሳይሰራ 1952 ዓ.ም ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተዘዋወረ።
ብርሃኑ ዘሪሁን ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ወዲያው “የኢትዮጵያ ድምጽ” ተብሎ በሚታወቀው ጋዜጣ ላይ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሰራ። ታዲያ በዚህ ወቅት ጋዜጣዋን ታዋቂ ከማድረጉም በላይ በብዙዎች ዘንድ የሚነበቡ መጣጥፎችን እና ታሪኮችን በመፃፍ ዝነኛ እየሆነ መጣ። ቀጥሎም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ተዘዋወረ። ብርሃኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያዊያን አንባቢያን ልብውስጥ ሰተት ብሎ ገባ። በአንድ ጊዜ ስሙ እና ዝናው እየናኘ መጣ።
ብርሃኑ ዘሪሁን በድርሰት ዓለም ውስጥ በተለይ በ1958 ዓ.ም አዲስ የታሪክ አብዮት ማቀጣጠል ጀመረ። “የቴዎድሮስ ዕንባ” የሚሰኝ መፅሐፍ አሳተመ። መፅሀፉ የአፄ ቴዎድሮስን አነሳስ እና ለኢትዮጵያ ያላቸውን ርዕይ ብሎም የመጨረሻውን የህይወት ፍፃሜ የሚያሳይ ነበር። በወቅቱ ማለትም ብርሃኑ ይህን መፅሀፍ ከማዘጋጀቱ በፊት የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ በጭካኔያቸው ላይ ተመስርቶ ብቻ የሚዘጋጅ በመሆኑ የቴዎድሮስን ውስጣዊ ስብዕና ያን ያህል ጎልቶ አይነገርም ነበር። እናም ብርሃኑ ዘሪሁን አፄ ቴዎድሮስ ብሔራዊ ጀግና መሆናቸውን የሚገልፅ ድርሰት ፅፎ በማቅረቡ በዘመኑ በጣም ታዋቂ ሆነ። ይህን “የቴዎድሮስ ዕንባ” የተሰኘውን ታሪክ መስፍን አለማየሁ ወደ መድረክ ቀይሮት በኢትዮጵያ የቴአትር አለም ውስጥም ከታላላቅ ቴአትሮቹ ተርታ የሚሰለፍ አድርጎታል።
በቴአትሩ ውስጥ የእንግሊዙ ቆንሲል አፄ ቴዎድሮስን እንዲህ ይላቸዋል “ጃንሆይ እኔ ተልኬ የመጣሁት ከታላቋ የብሪታኒያ የጦር ጀነራል ከናፒር ዘንድ ነው” ይላቸዋል።
ቴዎድሮስም “እና ምን ይዘህ መጣህ” አሉት።
መልዕክተኞች “ጃንሆይ ጦርነቱ እየከፋ ስለመጣ በሰላም እጅዎን ለታላቋ የብሪታኒያ መንግስት እንዲሰጡ ነው። እጅዎን በሰላም ከሰጡ የእንግሊዝ መንግስት በእንክብካቤ ይይዝዎታል” ይላቸዋል።
ቴዎድሮስም “ኧ ኧ ኧ ኧ ብለው የምፀት ሳቅ ከሳቁ በኋላ “ስማ! እኔ እንደ ፈረንጅ ጅል አላየሁም! መንጋ መሳፍንት እና መኳንንት ያንቀጠቀጠ ነበልባል እጄን ልያዘው አለ? የሚፋጅ የእሳት አሎሎ ነው በለው! ደግሞ . . . እጅህን ብትሰጥ በክብር ትያዛለህ ይለኛል። በየት አገር ነው እስረኛ በክብር የሚያዘው? ወይስ በሌላ የአፍሪካ ሀገር እንደለመዱት እኔን እስረኛ አድርገው ሀገሬ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ሊይዙ? እኔ እንደሁ ህይወቴ እያለች ሀገሬ ኢትዮጵያን ከጥቁር ዘራፊ አውጥቼ ለነጭ ዘራፊ አልሰጥም ብሎሃል በለው! ሂድ ንገረው! ውጣ!” እያሉ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር የሚገልፁበት ታሪካዊ ተውኔት ነው።
አፄ ቴዎድሮስ ወታደሮቻቸውን ሁሉ ከነ መሳሪያቸው ካሰናበቱ በኋላ ራሳቸውን ሊያጠፉ በሚወስኑበት ወቅት ባለቤታቸው እቴጌ ጥሩወርቅ እንዲህ አሏቸው።
“ኧረ በአማየሁ፣ በአለማየሁ ይሄን ሃሳብዎን ይተው!” ይሏቸዋል።
ቴዎድሮስም፡- “ለአለማየሁ ምንም የማወርሰው ነገር የለኝም። ብቻ ሲያድግ አባትህ አንዲት ኢትዮጵያ በአይኑ እንደዞረች ሞተ ብለሽ ንገሪው”
በእንዲህ አይነት ሀገራዊ ፍቅር የታጀቡት የብርሃኑ ዘሪሁን የአፃፃፍ ቴክኒኮች ዘመን ሰበር ታሪኮች ሆነው ዛሬም እናወጋቸዋለን።
ብርሃኑ ዘሪሁን በድርሰት ዓለም ውስጥ ሲያዥጎደጉዳቸው ከነበሩት መፃሐፍት መካከል በ1961 ዓ.ም “የእንባ ደብዳቤዎች” በሚል ርዕስ ያሳተመው በሰፊው የተነበበለት ሲሆን ከዚያም በመለጠቅ “ድል ከሞት በኋላ ነው” የሚለውም መፅሐፉ እንዲሁ በወቅቱ ይቀነቀን የነበረውን ተራማጅ እንቅስቃሴ የሚያቀጣጥል ነበር። “የበደል ፍፃሜ” እንዲሁም “ጨረቃ ስትወጣ” የተሰኙትም መፅሐፍቶቹ በኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍ ውስጥ የብርሃኑ ዘሪሁንን ስም እናማንነት እየገነቡ የመጡ ስራዎቹ ናቸው። ብርአምባር ሰበረልዎ የተሰኘው መፅሐፉም ታትማ ስትወጣ አምራች ደራሲነቱን /Productive Author/ የሚል ቅፅል አሰጥታዋለች።
በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሶስት ተከታታይ የሆኑ መፃሐፍትን በማሳተም ረገድ ብርሃኑ ዘሪሁን በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ አለም ውስጥ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ይጠቀሳል። በ1970ዎቹ ውስጥ ብርሃኑ ዘሪሁንን በሥነ-ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ስሙ እንዲነሳለት ያደረጉት እነዚህ ሶስት መፅህፍቶቹ “ማዕበል የአብዮቱ ዋዜማ”፣ “ማዕበል የአብዮቱ መባቻ” እና “ማዕበል የአብዮቱ ማግስት” ይሰኛሉ። መፅሐፎቹ በአንድ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ወሎ ውስጥ ተከስቶ በነበረው የረሃብና የድርቅ አደጋ ላይ ተመስርቶ የፃፋቸው ውብ መፅሀፎቹ ናቸው። እንዲህ አይነት ሶስት መፃህፍትን ፈረንጆቹ /Trilogy/ ይሏቸዋል። እናም በኛ ሀገር ደግሞ “ስልስ ድጉስ” ብለው የተረጎሙት ሰዎች አሉ። ብርሃኑ ዘሪሁን የስልስ ድጉስ መፃሐፍትም ደራሲ ነው።
ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በኢትዮጵያዊያን የመፃህፍት አንባቢያን ዘንድ በእጅጉ የተወደደውን እና በተደጋጋሚ የታተመውን መጽሐፍ በ1978 ዓ.ም አሳተመ። መፅሀፉ “የታንጉት ምስጢር” ይሰኛል። በአፄ ቴዎድሮ ዘመድ በታንጉት እና በቴዎድሮስ የጦር አበጋዝ በሆነው በፊታውራሪ ገብርዬ ጎሹ መካከል ያለውን ፍቅር እና የዘመኑን ታሪክ የፃፈበት ውብ ድርሰት ነው። ሶስቱን ማዕበሎች እና የታንጉት ምስጢርን በኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ ድንቅየው ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ በመተረኩ ከህዝብ አእምሮ እና ልቦና ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።
ብርሃኑ ዘሪሁን ከደራሲነቱ ባሻገር ፀሐፊ-ተውኔት ነው። የቴአትር ፅሁፎችን በማዘጋጀት እና በኢትዮጵያ መድረክ ላይ ግዙፍ ሰብዕና የሰጡትን ስራዎች አቅርቧል። ከቴዎድሮስ እንባ በኋላ በ1972 ዓ.ም “ሞረሽ” የተሰኘ ተውኔት በብሔራዊ ቴአትር ቤት አቅርቧል። በ1975 ዓ.ም ደግሞ “ጣጠኛው ተዋናይ” የተሰኘ ተውኔት በሐገር ፍቅር ቴአትር ቤት አቅርቧል። በ1976 ደግሞ “የለውጥ አርበኞች” የተሰኘ ተውኔት ጽፏል። በኢትዮጵያ የታሪክ ተውኔቶች አለም ውስጥ በዘመን አይሽሬነታቸው ከሚጠቀሱት ቴአትሮች መካከል “ባልቻ አባነፍሶ” የተሰኘው ቴአትር ነው። ይህን ቴአትር በ1977 ዓ.ም የፃፈው ይኸው ጎምቱ ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን ነው።
ብርሃኑ ዘሪሁን ከደራሲነቱ እና ከፀሐፊ ቴውኔትነቱ ባሻገር ሃያሲም ነበር። የተለያዩ ደራሲያንን ስራዎችን ፅሁፎችን እየተከታተለ ሂሳዊ መጣጥፎችን ያቀርብ ነበር። ከዚህ በላይ ደግሞ የተዋጣለት ጋዜጠኛ ሆኖ በዘመኑ በብዕሩ የናኘ ስብዕና የተጎናፀፈ ሰው ነበር።
     ይህ የድርስት ገበሬ ስራዎቹ በበርካታ የስነ-ጽሁፍ እና የታሪክ ተመራማሪ በሆኑ ምሁራን ጥናት ተደርጎባቸዋል። የዩኒቨርስቲ የመመረቂያ ጽሁፎችም ሆነው በርካቶችን አስመርቀዋል። ሞልሸር የተባለው የኖርዌይ ዜጋ እና የኢትዮጵያን ደራሲዎች ታሪክ Black lions በሚል ርዕስ የፃፍው ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁንን ከኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን ተርታ ያስቀምጠዋል። ብርሃኑ ዘሪሁን ተግቶ በማንበቡ እና በመመራመሩ በኢትዮጵያ ሥነ -ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ለትውልድ ውለታ ውለው ካለፉ ጥበበኞች መካከል አንዱ ሆኖ ይጠራል። ሀገርን እና ትውልድን በብዕሩ ቀለማት ሲዘክር የኖረው ይህ ሰው ሚያዚያ 16 ቀን 1979 ዓ.ም በ54 ዓመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ። ቀብሩም በባለወልድ ቤተ-ክርስቲያን ተፈፀመ። ዛሬ በአፀደ ስጋ ከኛ ጋር ባይኖርም ስራዎቹ ግን ዘመንን እየተሻገሩ ገና ወደፊትም ስሙን ያስጠሩታል።

ምንጭ:--በጥበቡ በለጠ ___http://www.sendeknewspaper.com/arts-sendek/item/559
****************************************************************************************************



ብርሃኑ ዘሪሁን እና “ድል ከሞት በኋላ”

**** ******************** ****

ባዩልኝ አያሌው 

  የአንዳንድ ፀሐፍቶቻችንን ብርታትና ትጋት፣ በዚህም ያበረከቱልንን ረብ ያላቸው ፍሬዎቻቸውን ሳስብ በመደነቅ ውስጤ ይሞላል፡፡ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ እነዚህ ጠቢባንና ስራዎቻቸው እውቅና እና ትኩረት ማጣታቸውን ሳስብ ልቤ በቁጭት ይጨመቃል፡፡ እናም “እድል እና ቲፎዞ አቦ ላትመለሱ እንጦሮንጦስ ውረዱ!” ብዬ እራገማለሁ። የፀሐፊ ክፍያው መነበብ በመሆኑ አለመነበብ መከፋትን ቢጭርም ቅሉ የምር ፀሐፊ ይህንንም ቸል ብሎ መጻፉን ይቀጥላልና ስሜቱ የወል አይሆን ይሆናል፡፡ የምር እውቅና መስጠትስ መረዳትን የግድ ይል የለ። እንደዛ!
ብዙ ተግተው ብዙ ቢሰጡንም፣ ብዙም “ካልዘመርንላቸው” ብርቱ ደራሲዎቻችን አንዱ ብርሃኑ ዘሪሁን ይመስለኛል፡፡ ስለደራሲውና ስራዎቹ በጋዜጣ አምድ ላይ ለማውሳት መሞከር “ሆድ ላይሞሉ አጉል ማላስ” ቢሆንም፣ ካለማለት ጥቂት ማለት ያተርፋልና በዚህ ጽሑፌ ስለደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁንና አስተዋጽኦዎቹ፣ እንዲሁም “ድል ከሞት በኋላ” ስለተባለው ድርሰቱ ጥቂት አወሳለሁ፡፡
በኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ስራዎችን ካበረከቱ ደራሲያን አንዱ ብርሃኑ ዘሪሁን ነው፡፡ የአጭርና የረዥም ልቦለድ ደራሲ፣ ጸሐፌ ተውኔት እና ጋዜጠኛ የነበረው ብርሃኑ ከ1952 ጀምሮ ከዚህ ዓለም በሞት እስካለፈበት 1979 ዓ.ም ድረስ 11 ልቦለድ ድርሰቶችንና 3 የሙሉ ጊዜ ተውኔቶችን ለተደራሲያኑ እንካችሁ ያለ ብርቱ ብዕረኛ ነው፡፡
በ1952 ዓ.ም “የእንባ ደብዳቤዎች” የተባለ ድርሰቱን እንካችሁ በማለት ጉዞውን አንድ ያለው ብርሃኑ፤ በኋላም “ድል ከሞት በኋላ”፣ “አማኑኤል ደርሶ መልስ”፣ “የበደል ፍጻሜ”፣ “ጨረቃ ስትወጣ” እና “ብር አምባር ሰበረልዎ” የተባሉትን ድርሰቶቹን አበርክቶአል፡፡ እንዲሁም “የቴዎድሮስ እንባ” እና “የታንጉት ምስጢር” የተባሉ ሁለት ታሪካዊ ልቦለዶችንና በወሎ ክፍለ ሀገር ተከስቶ የነበረውን ድርቅና የመንግስቱን ቢሮክራሲ ህያው አድርጎ የከተበባቸውን “ማዕበል የአብዮት ዋዜማ”፣ “ማዕበል የአብዮት መባቻ” እና “ማዕበል የአብዮት ማግስት” የተባሉ 3 ልቦለዶችን አስነብቦአል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ “ጣጠኛው ተዋናይ”ን እና “አባ ነፍሶ”ን የመሰሉ ተውኔቶችንም ጽፎ ለመድረክ አብቅቶአል፡፡
የብርሃኑን ድርሰቶች በጥሞና ለመረመረ አንባቢ አንድ ነገር አይሸሸገውም፡፡ ይኸውም ደራሲው ከጊዜ ጊዜ እያደገና እየበሰለ መሄዱ ነው፡፡ ደራሲው በገፀ ባህርያት አሳሳል፣ በግጭት አፈጣጠር እና በአተራረክ ጥበብ እንዲሁም በአጻጻፍ ብልሀቱ እየሰላ ሲሄድ በድርሰቶቹ በጉልህ ይስተዋላል፡፡ ምንም እንኳን ሲመሰከር ባይሰማም ብርሃኑ አጭር፣ ቀጥተኛና ግልጽ አረፍተ ነገሮችን በድርሰቶች ውስጥ በመጠቀም፣ እንዲሁም ቀድሞ የነበረውን ተረታዊ የታሪክ መንገሪያ ስልት በመቀየር ፈር ቀዳጅ ከሆኑ የሀገራችን ደራሲያን አንዱ ነው፡፡ ድርሰቶቹን የሚጽፈው እጅግ ቀላል እና ግልጽ በሆነ ስልት ነው፡፡ ከይዘት አንጻር አብዛኞቹ ድርሰቶቹም የሚያተኩሩት ማህበራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡
የብርሃኑ ድርሰቶች ከቅርጽም ሆነ ከይዘት አንጻር ብዙ ሊባልላቸው የሚችሉ ናቸው፡፡ ሁሉም ድርሰቶቹ ማለት ይቻላል እጅጉን ለመነበብ የማይጎረብጡ ናቸው፡፡ ታሪክ ሲተርክም ሆነ መዋቅር ሲያበጅ ያውቅበታል፡፡ በየድርሰቶቹ የምናገኛቸው ገጸ ባህሪያቱ የቅርብ ሰዋችን ያህል የሚሰሙን ናቸው፡፡ የዚህም ምክንያቱ ምናልባት ማንነታቸው ከእኛ እንደ አንዱ ስለሆነ ታሪካቸውም እኛው የምንኖረው ያልራቀን፣ ያልረቀቀን አይነት ስለሆነ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ስሜታቸውን ሁሉ እንድንጋራ እንሆናለን፡፡ የብዙዎቹ ድርሰቶቹ ጭብጦችም እንዲሁ ኑሮአችንና የየእለት ጉዳያችን ናቸው፡፡
ብርሃኑንና ድርሰቶቹን ሳስብ ሁሌም የሚደንቀኝ አንድ እውነት አለ፡፡ ያለኝ መረጃ እርግጥ ከሆነ ብርሃኑ ለብዙ ዓመታት ጋዜጠኛ፣ በኋላም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበር፡፡ የጋዜጣ ስራ ደግሞ ምን ያህል ጊዜን እንደሚወስድ ብቻ ሳይሆን አድካሚና የአፍታ ረፍት የለሽ መታተር እንደሆነ እናውቃለን። ዛሬ ለነገ ሰርቶ ዛሬውኑ ለቀጣዩ ቀን ማሰብን፣ መሮጥን ያለ ረፍት መድከምን… ይጠይቃል፡፡ ጋዜጣው እለታዊ ሲሆን ደግሞ አስቡት፡፡ የጋዜጣው አዘጋጅ ሲኮንስ? ሌላ ሌላውን ትተን ዋና አዘጋጁ ቢያንስ በየእለቱ ርዕሰ አንቀጽ መጻፍ ይጠበቅበታል። እንግዲህ በዚህ ሁሉ ውጥረት ውስጥ ሆኖ ነው ብርሃኑ በቁጥር የበዙ በጥራትም የላቁ ድርሰቶችን የጻፈው፡፡ ይህ ሁሌም ያስገርማኛል፡፡
“ድል ከሞት በኋላ” ብርሃኑ ዘሪሁን “የእንባ ደብዳቤዎች”ን ካቀረበ ከ3 ዓመታት በኋላ በ1955 ዓ.ም ያሳተመው ሁለተኛው ልቦለዱ ነው፡፡ ብርሃኑ ልቦለዱን የጻፈው በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ ይካሄድ በነበረው የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ የድርሰቱ ጭብጥ የነጻነት ትግል፣ ትኩረቶቹም በወቅቱ ነጻ ያልወጣችው ደቡብ አፍሪካ እና በነጮች ስር ሆነው በመሰቃየት ላይ የሚገኙት ህዝቦቿ ናቸው፡፡ የታሪኩ ስፍራ ደቡብ አፍሪካ፣ የልቦለዱ ገጸ ባህሪያትም ለነጻነት የሚታገሉት ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን እና ገዢዋቻቸው የሆኑት ነጮች ናቸው፡፡
ልቦለዱ የሚተርከው የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ህዝቦች በነጮች ስለሚደርስባቸው ጭቆና እና ይህንን ጭቆና ለማስወገድ ጥቁሮቹ ስለሚያደርጉት ትግል ነው፡፡ በዘመኑ በደቡብ አፍሪካ የነበረው ጨቋኝ የነጮች አገዛዝ፣ የጥቁሮቹ በገዛ ሀገራቸው በባርነት መገዛት በዚህም ይደርስባቸው የነበረው ግፍና መከራ ሁሉ በልቦለዱ ግሩም በሆነ መልኩ ቀርቦአል፡፡
የልቦለዱ ዋና ገጸ ባህሪ የዙሉ ጎሳ አባል የሆነው ድኩማ ነው፡፡ የድኩማ አባት ኪሙይ በሚሰራበት የነጮች ንብረት በሆነው የዱቄት ፋብሪካ ውስጥ ከሌሎች የስራ ባልደረቦቹ ጋር ባነሱት የህክምና አበል ጥያቄ ምክንያት በነጮች ላይ ትልቅ ሤራ ጠንስሰዋል በሚል በሀሰት ተወንጅሎ ይታሰራል። አባቱ በመታሰሩ ምክንያት የቤተሰቡ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ በድኩማ ትከሻ ላይ ይወድቃል፡፡ ዘሩ ነጭ ቢሆንም የነጮቹን የግፍ አገዛዝ የሚቃወመውና ለጥቁሮቹ የሚቆረቆረው ዶክተር እስቴዋርድ ድኩማን የቆዳ ፋብሪካ ውስጥ በጉልበት ሰራተኛነት ያስቀጥረዋል፡፡
 ድኩማ በፋብሪካው እየሰራ ቤተሰቡን ለማስተዳደር ጥረት ቢያደርግም አባቱ በወንጀለኛነት ስለተፈረደበት ብቻ የወንጀለኛ ልጅ ነህ በሚል ምክንያት ከቆዳ ፋብሪካው ይባረራል፡፡ በድኩማ ቤተሰብ ላይም ከፍተኛ ችግር ይወድቃል። በዚህም ድኩማ የመከራው ጥልቀት እያንገሸገሸው ይመጣል።
ቆይቶም ሲያግዘው የቆየው እስቴዋርድ ዱርባን በምትባልና ጥቁሮች በሚኖሩባት ከተማ ለሚኖር አባ አሊንጎ ለተባለ ወዳጁ ድኩማን ላይ የደረሰበትን ችግር ሁሉ ገልጾ ደብዳቤ በመጻፍ እንዲረዳው ድኩማን ይልከዋል፡፡ ሆኖም አሊንጎ ስራ ሊያገኝለት ባለመቻሉ ድኩማ አሊንጎ ቤት መኖር ይጀምራል፡፡ በአሊንጎ መኖሪያ ቤት ማታ ማታ በየአካባቢው የሚኖሩ የጥቁሮች ተወካዮች ስለተጫነባቸው የመከራ ሕይወትና እንዴት ነጻ መውጣት እንደሚችሉ ያደርጉት የነበረው ውይይት ድኩማን እየሳበው ይመጣል፡፡ በሂደትም የውይይቱ አካል ይሆናል፡፡
ምክክሩና እቅዱ ቀጥሎ እነ አሊንጎ አመጹን ለማንሳት ምቹ ጊዜን እየጠበቁ ባሉበት ወቅት ድኩማ በፖሊስ ተይዞ ይታሰራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለጥቁሮች ወደ ተከለከለው ኮከብ አደባባይ ገብቶ መገኘቱ ነበር። የድኩማ መታሰርም አመጹ ተጠንቶ እና ምቹ ሁኔታ ሲገኝ ያለ ደም መፋሰስ ነው መደረግ ያለበት የሚል አቋም የነበረውን አሊንጎን ተስፋ ያስቆርጠዋል። ስለዚህም አመጹ መካሄድ እንዳለበት ይወስናል፡፡ በመሆኑም ድኩማ ፍርድ ቤት በሚቀርብበት ሰዓት 50 ሺ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን በሰልፍ ሆነው የተቃውሞ መዝሙር በመዘመር ወደ ፍርድ ቤቱ ያመራሉ። ሆኖም የነጭ ፖሊሶች ጥይት በመተኮስ የአመጹን መሪዎች ጨምሮ ብዙ ጥቁሮችን ይገድላሉ፡፡  ከፍርድ ቤቱ በመውጣት አመጹን የተቀላቀለው ድኩማ እና የትግሉ መሪ የነበረው አሊንጎም ከፖሊሶቹ በተተኮሰ ጥይት ይገደላሉ፡፡ የጀመሩት ትግል እንደሚቀጥል ተስፋ አድርገው፣ ሞታቸውን በጸጋ እንደተቀበሉት ተገልጾ ታሪኩ ይቋጫል፡፡
ታሪኩ እጅግ አጓጊና የማይሰለች፣ አተራረኩም ውብ ነው፡፡ እነ ድኩማና አባቱ ኪሙይ፣ አሊንጎ፣ ዶክተር እስቴዋርድ የመሳሰሉት የታሪኩ ባለቤቶች በውብ መንገድ የተቀረጹና ቅርባችን ያሉ ያክል የሚሰሙን አይረሴ ገጸ ባህሪያት ናቸው፡፡
ብርሃኑ ዘሪሁን ብዙዎቹን ታሪካዊ ልቦለዶቹን የጻፈው ታሪኩ የተፈጸመበት ቦታ በአካል ተገኝቶ መረጃዎችን በመሰብሰብና የሁነቱን መንፈስ ለመላበስ በመሞከር ነው፡፡ “የቴዎድሮስ እንባ”ን ሲጽፍ ጎንደርና መቅደላ፣ 3ቱን “ማዕበሎች” ሲጽፍ ደግሞ ከወሎ የገጠር ቀበሌዎች ደሴ እስከነበረው የስደተኞች ካምፕ ድረስ ተዘዋውሮ በድርቅ የተጠቁትን ሰዎች በማየትና በማነጋገር መረጃዎችን ሰብስቦአል፡፡ “ድል ከሞት በኋላ”ን ለመጻፍ ግን ደቡብ አፍሪካ አልሄደም፡፡ ያም ሆኖ ባለመሄዱ ከመቼትም ሆነ ከታሪክ አንጻር ምንም እንዳላጎደለና  የወቅቱን የደቡብ አፍሪካን ጥቁሮች የመከራ ህይወትና የነጻነት ትግል በጥሩ አቀራረብ ለአንባቢያን ማሳየቱን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
ልቦለዱን ከራሱ ከደራሲው ስራዎችም ሆነ ከሌሎች በዘመኑና ከእሱም ቀድመው ከታተሙ ልቦለድ ድርሰቶች የሚለየው አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም የሌሎች ሕዝቦችን ታሪክ መተረኩ ነው፡፡
ቀደም ሲል ለድርሰቶቻቸው በእውኑ ዓለም የሌሉ መቼቶችን እየፈጠሩና ሰው ያልሆኑ ገጸ ባህሪያትን እየቀረጹ ጭምር የጻፉ ደራሲያን ቢኖሩም የሌላ ሀገርን ታሪክና መቼት በሙሉ ጊዜ በድርሰቱ ውስጥ በመገልገል፣ በአጠቃላይ የሌሎች ሕዝቦችን ጉዳይ የድርሰቱ አቢይ ትኩረት አድርጎ የጻፈ ደራሲ አላጋጠመኝም፡፡ ይህንን ለማንሳት የወደድኩት ደራሲው ይህንን ልቦለድ መጻፍን ለምን ፈለገ? ወደሚለው ጥያቄ ስለሚመራኝ ነው፡፡
ደራሲው ስለመጽሐፉ የመጻፍ ምክንያት በከተበበት መግቢያ ላይ “መጽሐፉን የጻፍኩት ስለ ነጻነትና ስለመብት ለተሰዉ ሰዎች እና ወደፊትም በመታገል ላይ ለሚገኙት ሕዝቦች ሁሉ መታሰቢያ የምትሆን አንዲት ድርሰት ማበርከት እዳዬ ሆኖ ስለተሰማኝ ነው” ይላል፡፡ ሆኖም መጽሐፉ የታተመበትን ጊዜ (1955 ዓ.ም) እና በልቦለዱ የተነሱ ጉዳዮችን ይዘን ስናስብ አማራጭ የለንም ብለን እጅ ካልሰጠን በቀር ብርሃኑ ድርሰቱን ለመጻፍ ምክንያቴ ነው ያለንን ለማመን እንቸገራለን፡፡ ወቅቱ ምንም እንኳን የብዙ የአፍሪካ ሀገሮች የነበሩበትን መንፈስ ያህል ባይሆንም በኢትዮጵያም የለውጥ ነፋስ መንፈስ የጀመረበት ጊዜ ነው፡፡ እርግጡን መናገር ቢቸግርም ደራሲው ልቦለዱን ሲጽፍ ሌላ ዓላማ ያለው ይመስላል፡፡ ምናልባትም የደቡብ አፍሪካውን የነጻነት ትግል መንፈስ በዚህች ሀገር ወጣቶች ላይ ማጋባት፣ እኛም የተጫነን ቀንበር አለና ከተቀመጥንበት እንነቃነቅ የማለት… የመሳሰሉት አይነት ዓላማዎች፡፡
አስገራሚው ጉዳይ ታዲያ ይህንን የመሰለ የነጻነት ትግልን ጭብጡ ያደረገ ይህንንም በበርካታ  ሁነቶች ማሳየት የቻለ ልቦለድ፣ የለውጥ ነፋስ እየመጣባት ባለች ሀገርና ነፋሱን እየጠሩት ባሉት የዘመኑ ወጣቶች ሳይቀር ብዙም አለመነበቡ ነው፡፡ በወቅቱ ልቦለዱ 2,000 ኮፒ እንደታተመና ብዙም እንዳልተሸጠ፣ ለዚህም ምክንያቱ የዘመኑ አንባቢያን ለደቡብ አፍሪካ ታሪክ ብዙም ፍላጎት ያልነበራቸው በመሆኑ እንደሆነ ደራሲው (ብርሃኑ) ገልጾልኛል፤ በማለት የብርሃኑን የህይወት ታሪክ እና ስራዎቹን ያጠናው ሪዱልፍ ኬ. ሞልቬር Black Lions- The Creative Lives of Moderen Ethiopia’s Literary Giants and Pioneers (1997) በተባለው መጽሐፉ አስፍሮአል፡፡ መተላለፍ ይሉታል ይሄ ነው።

ምንጭ:--http://www.addisadmassnews.com/
***************************************************************************