ከደራሲያን ዓምባ

Friday, December 22, 2023

እያዩ ፈንገስ

እያዩ ፈንገስ ‹‹ከፌስታሌን›› እስከ ‹‹ቧለቲካ›› 

      ደራሲ፣ ገጣሚና ጋዜጠኛ በረከት በላይነህ

      ተዋናይ ግሩም ዘነበ

 

“እያዩ ፈንገስ” የተባለው ገፀ ባህሪ “ፌስታሌን” ሆኖ የሙሉ ሰዓት ተውኔት እስኪሆን ድረስ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በየወሩ በሚቀርበው ግጥምን በጃዝ ላይ ለሁለት ዓመት በ25 ክፍል ለተመልካች እይታ ቀርቧል።

የዚህ ገፀ ባህሪ ፈጣሪ ደራሲ፣ ገጣሚና ጋዜጠኛ በረከት በላይነህ ነው። በአንቲገን፣ ንጉስ አርማህ፣ፍቅርን የተራበና በበርካታ የመድረክ ትያትሩ የትወና ብቃቱ የሚታወቀው አርቲስት ግሩም ዘነበ ደግሞ ብቻውን መድረክ የሚቆጣጠርበት ሥራው ነው።


እያዩ ፈንገስ በኢትዩጵያ የአንድ ሰው ቴዓትር ታሪክ ውስጥ ዝነኛውና ግምባር ቀደም ገጸ ባህሪ እንደሆነ ይነገርለታል። ይኼ ገጸ ባህሪ ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት በደራሲ በረከት በላይነህና በተዋናይ ግሩም ዘነበ አማካይነት ለተመልካቾች እንዲታይ ሆነ።

ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ በራስ ሆቴል በየወሩ የጃዝ ግጥም ምሽት ይዘጋጃል፡፡ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ለማቅረብ የሄደው በረከት፣ በዚያው መድረክ ላይ ግሩም ዘነበ የአውግቸው ተረፈን እያስመዘገብኩ ነው የሚለውን አጭር የመፅሀፉ ታሪክ ሲጫወት ያየዋል።

 ‹‹ገጸ ባህሪው አንድ ጭቃ አቡኪ ሲሆን በማኅበራዊ ሕይወታቸው የተበደሉና የሚያዝኑ ዓይነት ገጸ ባህሪ ነበሩ፣ ግሩምም በጥሩ ሁኔታ ስለሠራቸው የተመልካች አድናቆት ልዩ ነበር፤›› ሲል በረከት ያስታውሳል።

ይህንን ገጸ ባህሪ በየወሩ የማስቀጠል ፍላጎት ያደረበት በረከት፣ ግሩምን በማናገር ገጸ ባህሪው በሚቀጥልበት ሁኔታ ተነጋግረው ተስማሙ። ነገር ግን ገጸ ባህሪው በረከት መናገር የሚፈልገውን ሐሳብ ለማንፀባረቅና ለመሸከም ስለማይችል እያዩ ፈንገስ የሚለውን ገጸ ባህሪ ለመፍጠር ተገደደ።

ፈንገስ የሚለው ቃል አፍራሽ ነገርን ይወከላል ያለው የገጸ ባህሪው ደራሲ በረከት በላይነህ፣ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እንዲሁም በመንግሥት ውስጥ ያለውን ንቅዘት የሚነካካና የሚገልጽ ዓይነት ገፀ ባህሪ ለመጻፍ መብቃቱን ይናገራል።

ገጸ ባህሪው መጀመርያ ላይ ሲጻፍ ስሙ ክንፉ የሚባል  እንዲሆን የተደረገ ቢሆንም፣ ተዋናይ ግሩም ዘነበ ስሙን እያዩ ወደሚል መጠሪያ ቀየረው።

በሚቀጥለው የራስ ሆቴል የግጥም ምሽት ፕሮግራም አንድ የአዕምሮ ሕመም ያለበት ዓይነት ሰው፣ በቁም ነገርና በቀልድ እያደረገ የሚናገር ገጸ ባህሪ ለሃያ ደቂቃ ያህል የአንድ ሰው አጭር ፕሌይ ለመጀመርያ ጊዜ መጋቢት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ለዕይታ ቀረበ፡፡

በሰው ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘቱም  ለተከታታይ ሃያ ወራት በግጥም ምሽቱ ፕሮግራም ለታዳሚው ቀረበ።


በእዚ መሀል የሰውን በጎ ምለሽ የተመለከቱት ግሩምና በረከት ይኼን መልካም አጋጣሚና ተወዳጅነቱን በመጠቀም በ2011 ዓ.ም. ከሃያ ደቂቃ ፕሌይ ሰፊ ወደሆነ የሁለት ሰዓት ተኩል ርዝማኔና የራሱ ታሪክ እንዲሁም መነሻና መድረሻ ያለው (ፌስታሌን) የሚል ቴዓትር፣ በሳምንት ለአራት ቀናት በአዶትና በዓለም ሲኒማ በማሳየት ተወዳጅነትን አተረፉ። አዳራሽ ሙሉ ታዳሚ የነበረው ይኸው ፕሌይ ለአሥር ወራት ያህል ተካሂዷል፡፡

ፌስታሌን የሚለው ቴዓትር በአጭሩ ሲተነተን አንድ ፌስታሉ የጠፋበት ሰው እሱን በመፈለግ ላይ ሆኖ፣ ነገር ግን እሱን በማስታከክ የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ፓለቲካዊ፣ መንግሥታዊ ጉዳዮችን በኮሜዲ፣ በትራጄዲና በፍልስፍና እያጣቀሰ የሚተውን ገጸ ባህሪ ነው።

‹‹በአሜሪካ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች አገር ውስጥ ያገኘነውን ዝና ሰምተው ቲዓትሩን እንድንጫወትላቸው ግብዣ አቀረቡልን›› ይላል በረከት፡፡ በዚህም መሠረት ለአሥራ አንድ ወራት በሃያ ሰባት የአሜሪካ ግዛቶች ፌስታሌን የሚለውን የአንድ ሰው ቴዓትር ማቅረባቸውን ያስረዳል።

ከአሜሪካ ከተመለሱም በኋላ ጊዜ ሳያጠፉ የፌስታሌን ቀጣይ ክፍል የሆነው አጀንዳዬን የተሰኘውን ቴዓትር ለተመልካች ቢያቀርቡም፣ ብዙም ሳይቆይ የኮሮና ወረርሽኝ እንዲሁም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገጉና የሰዎች መንቀሳቀስ መብት በመገደቡ ቲዓትሩ እንዲቋረጥ ተገደደ።

ገጣሚ፣ ጋዜጠኛና ደራሲ በረከት በላይነህ
                                       ገጣሚ፣ ጋዜጠኛና ደራሲ በረከት በላይነህ

ግሩምና በረከት ይኼ ቴዓትር እንዲባክን ስላልፈለጉ ለሰው መድረስ አለበት ብለው ስላመኑ ይህንን በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች እንዲለቀቅ አደረጉት።

አጀንዳዬን የፌስታሌን ቀጣይ ክፍል ሲሆን፣ ፌስታሌን ካቆመበት የሚቀጥል ነው፡፡ በውስጡም ከፌስታሌን ጋር  ተመሳሳይ ይዘት ያለው ቴዓትር ይዟል፡፡ የታሪክ መነሻና መድረሻም አለው።

አዲሱና ሦስተኛው ቧለቲካ የተሰኘው ቴዓትር ከጥቅምት 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በሳምንት ሁለት ጊዜ በዓለም ሲኒማ እየቀረበ ይገኛል። ቦለቲካ ከፌስታሌንና አጀንዳዬን ቀጥሎ እንደ አንድ ሰው ቴዓትር ሆኖ በበረከት በላይነህ ደራሲነት እንዲሁም በግሩም ዘነበ ተዋናይነት የቀጠለ ቢሆንም፣ የቲዓትሩ ይዘቶች የተለዩ ናቸው፡፡

 እንደ ቀድሞዎቹ ሁለት ቴዓትሮች መነሻና መድረሻ እንዲሁም አንድ ወጥ ታሪክን ተከትሎ የሚሄድ ታሪክ ባይኖረውም፣ እንደ ሁለቱ ቴዓትሮች ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ መንግሥታዊ ጉዳዮችን ይዳስሳል።

ቧለቲካ ለዘጠነኛ ጊዜ በዓለም ሲኒማ ታይቷል፡፡ የተመልካች ቁጥርም ከሌሎች ቴዓትሮች በተለየ ከፍተኛ መሆኑን ከዓለም ሲኒማ ሠራተኞች ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።   

‹‹የእኔ አገራዊ ዕይታ የሚመነጨው ከፖለቲካ ሥርዓቱ ነው፤›› ይላል በረከት። ለዚህም እንደ ምክንያትነት ሲያነሳ፣ ‹‹አንድ አገር ውስጥ ለሚከናወነው በጎም ነገር በማኅበራዊ ቀውስ የሚታየው መጥፎ ነገር ዋናው መሠረቱ የፖለቲካ ሥርዓቱ ነፀብራቅ ነው፤›› ብሎ ያምናል፡፡ ‹‹የአንድ አገር የፖለቲካ ፍልስፍናና የሚከተለው የፖለቲካ ሥርዓት በአገር ላይ የሚታዩ ነገሮችን የሚወልድ በመሆኑ፣ ፖለቲካን በተለያየ ዓይን ብናየው ጥሩ ነው፤›› ያለው በረከት፣ በዚህም ምክንያት ድርሰት በሚጽፍበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ፖለቲካ ነክ እንደሆነ ያስረዳል።

 


‹‹የፖለቲካ ይዘት ያለው ድርሰት እንደመጻፌ መጠን፣ እስካሁን  ምንም ዓይነት እስርም አካላዊ ጉዳትም አልደረሰብኝም” ያለው በረከት፣ ነገር ግን ራስ ሆቴል በሚሠሩበት ወቅት ፕሮግራሙ ላይ በሚነሱ ጉዳዮች የተናደደ አንድ የመንግሥት ካድሬ ሊያስፈራራቸው እንደሞከረ ያስታውሳል።

‹‹ማስተላለፍ የምንፈልገው እውነት ነው ወይስ ውሸት፣ ከዚያ ውጪ የምንዋሸው ነገር እስከ ሌለ ድረስ የምንፈራበት እንዲሁም የሚያሰጋን ነገር የለም››ሲል በረከት ያስረዳል።

ስለሦስቱ ቴዓትሮች ተፅዕኖ ሲያስረዳ፣ ‹‹በተለምዶ አካሄድ አንድ ቴዓትር በኪነ ጥበብ ሥራ ውስጥ ምንድነው ተፅዕኖው የሚለውን ለማየት በብዙ ነገር እንለካዋለን፡፡ በእዚህ ሰዓት የፊልምም የቴዓትርም ተመልካች ቀንሷል፡፡ ጠቅላላ ኢንዱስትሪውም ደክሟል፡፡ ሆኖም ሰው ተሠልፎ ቴዓትራችንን ያየዋል፣ በየዘርፉ ትልልቅ የሚባሉ ሰዎችም እየመጡ ያዩታል ለእኛም የገንዘብ ምንጭ በመሆን በግል ሕይወታችን ላይ ብዙ ጥሩ ነገር ይዞልን መጥቷል፤›› ይላል።

 በቀጣይም ለሦስት ወር ያክል በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ አውስትራሊያና በደቡብ አሜሪካ ሄደው ቦለቲካን እንደሚያሳዩ ያስረዳል።

ተዋናይ ግሩም ዘነበ ስለሚተውነው ገጸ ባህሪ እያዩ ፈንገስ ሲናገር፣ ‹‹እኔና እያዩ የግል ታሪካችን ካልሆነ በስተቀር ለምሳሌ እሱ ሚስቱ የሞተችበት ነው፣ መምህር ነው፣ እሱ ካልሆነ በስተቀር ለሕዝብ ይድረስልኝ የሚላቸው መልዕክቶች ሙሉ በሙሉ የእኔ ሐሳብ ነው፡፡ ገጸ ባህሪው ሊናገር የሚፈልጋቸውን ነገሮች ተቃውሜ አላውቅም፤›› ይላል።

ገጸ ባህሪውን ስለሚወደው ለማጥናትና ወደራሱ ለመቀላቀል ያን ያህል እንዳላስቸገረው፣ ለአገሩ አንደበት ለመሆን ሚገርም ዘመን ላይ ያገኘው ገጸ ባህሪ በመሆኑም አክብዶ እንደሚሠራ፣ ግሩም ይናገራል።

‹‹እያዩ ፈንገስ የመጀመሪያው የአንድ ሰው ቴዓትር እንደመሆኑ መጠን ተጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ፤›› በማለት ተዋናይ ግሩም ያስረዳል፡፡


 

የእያዩ ፈንገስ ገጸ ባህሪ የተዋቀረባቸው ማለትም ኮሜዲ፣ ትራጄዲና ፍልስፍና ወይም ወሳኝ ጉዳዮችን የሚያይበት ነገር በጣም ትልቅ አድርጎታል፡፡ ገጸ ባህሪውን የሚጽፈው ሰው ጎበዝ ባለተሰጥኦ በመሆኑ፣ ተወዳጅነቱን እንደያዘ አሥር ዓመታት አስጉዞታል፡፡ በመሆኑም ለባልደረባው ለደራሲ በረከት ያለውን አድናቆት ይገልጻል።

ስለቧለቲካ ቴዓትር ሐሳቡን ሲገልጽም፣ ‹‹የእኛ ፍላጎት ቶሎ ቶሎ ለሰዎች ማድረስ ነው፣ ነገር ግን የመድረክ ሥራ በመሆኑ ያንን ለማድረግ ዕድል ስለማይሰጥ የተወሰኑ ወራት ለዕይታ ይቀርባል፤›› ብሏል፡፡

 

 

የእያዩ ፈንገስ ‹‹ፌስታሌን››

የቴአትሩ አዘጋጅና ተዋናይ :- ግሩም ዘነበ 

 ደራሲው:- በረከት በላይነህ 

‹‹…በነገራችን ላይ ጋሽ ቆፍጣናው ማለት የሠፈራችን ደረጃ አንድ ታጥቦ የተቀሸረ ሙጢ ማለት ነው፡፡ ፊት ለፊት ተናጋሪ እና ሐቀኛ፡፡ ለማንም የማይመለሱ ቆፍጣና፡፡ የነገር ጠጠር ውርወራና ምክራቸው፡፡ በሰከንድ በአሽሙር ቋጥኝ ይፈረካክሱኋል፡፡ ቆፍጣናው እንዲህ ናቸው፡፡ አንድ የፈረደበት ተከራይ ጋዜጠኛ አላቸው፡፡ እንዲሁ ፍዳውን የሚያሳዩት፡፡ አንድ ቀን የሆነ ባለሥልጣኖችና ባለሀብቶች ኳስ ጨዋታ አድርገው ነበር መሰለኝ፡፡ ይኼንን ዘገባ ሠርቷል ጋዜጠኛው ተከራይ ሲመጣ ምን ቢሉት ጥሩ ነው በምን ለየሃቸው ግን?…››

ንግግሩ የተቀነጨበው ‹‹ፌስታሌን›› ከተሰኘው ዋን ማን ሾው (አንድ ተዋናይ ብቻውን የሚተውንበት ቴአትር) ነው፡፡ ቴአትሩ የታየበት መድረክ ከተጨናነቁ የመዲናችን መንደሮች አንዱ ይመስላል፡፡

የደሳሳው ጭቃ ቤት ልስን ፈራርሶ የቤቱ ማገር ይታያል፡፡ ከቤቱ አጠገብ ያሉ ሌሎች መኖሪያዎች ግርግዳዎችም እንዲሁ ያረጁ ናቸው፡፡ የጭቃ ቤቱ መጠነኛ መስኮትና በር ላይ ‹‹ታሽጓል›› የሚል ጽሑፍ ተለጥፏል፡፡ እዛው አካባቢ የሚታዩ ማስታወቂያዎች የአብዛኛውን የአዲስ አበባ መንገዶች ገጽታ ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ሠርግዎን በዲጄ››፣ ‹‹ዋ ትሸናና፤ ከሸናህ ትሸነሸናለህ››፣ ‹‹አርቲስት መሆን ይፈልጋሉ?›› እና ‹‹እፀነፍስ የባህል መድሐኒት ቤት›› የሚሉ የኮምፒዩተር ጽሑፎች ይጠቀሳሉ፡፡

ካረጁ ቆርቆሮዎች እንደነገሩ የተሠራው መጠለያ ባደፉ ጨርቆች ተሸፋፍኗል፡፡ መጠለያው ውስጥ ጋደም ብሎ የነበረው እያዩ ፈንገስ ወደ መንገድ ዳር ይወጣል፡፡ ፊቱን በንዴት ቅጭም አድርጓል፤ በቁጭትም ይንዘፈዘፋል፡፡ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ፌስታሉን ሌቦች ሰርቀውታል፡፡ ይገኝበታል ብሎ በገመተው ሥፍራ ሁሉ ተዘዋውሮም ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በፍለጋ ላይ ሳለ ይባስ ብሎ ዘለፋ ይደርስበታል፡፡ እንዲህ ሲልም እያዩ ምሬቱን ይገልጻል፡፡

‹‹… የእትዬ ምልጃን ምክር ሰምቼ እኮነው ጉድ የሆንኩት፡፡ የሰፈሩን ቆሻሻ የሚያነሱት እነሱ ስለሆኑ ጠይቃቸው ያገኙልሃል ብለውኝ ሄጄ እኮ ነው በጠዋት ያገኙኝ፡፡ የቆሻሻ ገንዳቸውን እየገፉ ቁልቁል ሲወርዱ አየዋኋቸውና ሮጥ ሮጥ ብዬ ደረስኩባቸው፡፡ ያለ የሌለ ትህትናዬን አጠራቅሜ እባካችሁ ወንድሞቼ ትናንትና አሮጌ ልብሶች የያዘ ፌስታል ጠፍቶብኝ ነበረ፤ ምናልባት ካገኛችሁት ብዬ ነው አልኩኝ፡፡ አንደኛው እስኪ ምልክቱን ተናገር አለኝ፡፡ ሁሉም ፌስታሉ ውስጥ ያለውን ልናገር አልኩ፡፡ ታዲያስ ምልክት አይደለም እንዴ ሁሉንም ነው እንጂ መናገር አለኝ፡፡

ድምፄን ከፍ አድርጌ አራት የሽንት ጨርቆች ከነመዓዛቸው፣ አንድ እግር ጫፍ አይጥ የበላው የሕፃን ልጅ የዳንቴል ካልሲ፣ ጡጦ ክዳኑ የተሰነጠቀ፣ ሁለት የሴት ፓንቶች፣ ድርያ ከድሬዳዋ ፊልድ ስመለስ የተገዛና እንዲሁም ተረከዛቸው የሳሱ ነጠላ ጫማዎችና ቀዩ አጀንዳዬ፡፡ የእኔና የብዙ ሰዎች ሐሳብ የሰፈረበት ቀዩ አጀንዳዬ፡፡ ይኼ ሁሉ ውድ ንብረት ፌስታሌ ውስጥ ነበር አልኳቸው፡፡ ዘውድዬ ትሙት እርስ በርስ ሲተያዩ ልቤ ቀጥ ነበር ያለው፡፡ አግኝተውታል ብዬ ጠርጥሬ እኮ ነው፡፡ ከዛ በአንክሮ ካዩኝ በኋላ አንደኛው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? 904 ደውለህ አዘጋው፡፡ እየሳቁ ሄዱ፤››

እያዩ ፈንገስ የተባለው ገፀ ባህሪ የአዕምሮ ሕመምተኛ ነው፡፡ በገጠመው መሪር ሐዘን ሕይወቱ እንዳይሆን ሆኗል፡፡ ቴአትርሩም እያዩ የጠፋበትን ፌስታል መነሻ ያደረገ ነው፡፡

ብዙዎች የእያዩ ፈንገስን ገፀ ባህሪ የሚያውቁት በጦቢያ ግጥምን በጃዝ መርሐ ግብር ላይ ነው፡፡ በየወሩ በሚካሄደው ዝግጅት ላይ በዋነኛነት ግጥሞች የሚደመጡ ሲሆን፣ ወግ፣ መነባንብ፣ ዲስኩርና ሌሎችም ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች ይስተናገዳሉ፡፡ ታዳሚዎች የየወሩን የመጀመሪያ ረቡዕ በጉጉት እንዲጠባበቁ ከሚያደርጉ አንዱ ደግሞ የእያዩ ፈንገስ ትዕይንት ነው፡፡

ለአንድ ዓመት ያህል ወደ 13 የሚደርሱ ክፍሎች ታይተዋል፡፡ የእያዩ ፈንገስ አንደኛ ዓመት የመድረክ ቆይታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ተከብሮ ነበር፡፡ በየክፍሎቹ የተወሰኑ ደቂቃዎች ይወስድ የነበረው ትዕይንቱ አሁን የሙሉ ጊዜ ቴአትር ሆኗል፡፡ ሰኞ ሐምሌ 27፣ 2007 ዓ.ም. በአዶት ሲኒማና ቴአትር ተመርቋል፡፡

አስቂኝ በሆነ ዘዬ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትችቶችን በመሠንዘር የሚታወቀው እያዩ፣ በ‹‹ፌስታሌን›› ላይም በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ያነሳል፡፡ የኅብረተሰቡን አኗኗርና የወቅቱን ሥርዓት ያጠይቃል፡፡ መጨካከን፣ መታበይ፣ ሸፍጥና ሌሎችም ሕፀፆችን ይተቻል፡፡ የመሠረተ ልማት አለመስፋፋት፣ ኢኮኖሚያዊ ችግርና መሰል ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡

 

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች እየሳቁ፣ በጭብጨባ ድጋፋቸውን እየገለጹም ተውኔቱን ይከታተሉ ነበር፡፡ ሲገባደድም ከመቀመጫቸው ተነስተው ለደቂቃዎች በማጨብጨብ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ እያዩ ፈንገስን ሆኖ የሚተውነው እንዲሁም የቴአትሩ አዘጋጅ ግሩም ዘነበ ሲሆን፣ ደራሲው በረከት በላይነህ ነው፡፡

እያዩ የሚነቅሳቸውን ችግሮች ‹‹ፈንገሱ ነው›› በማለት ይገልጻል፡፡ በተለያየ ዘርፍ አግባብ ያልሆኑ አካሄዶች ሥር መስደዳቸውንና በፍጥነት መስፋፋታቸውን ያመላክታል፡፡ ‹‹ፈንገስ›› የሚለው ቃል በማኅበረሰቡ ውስጥ የተንሰራፉ ችግሮችን እንደሚያሳይ በረከት ይናገራል፡፡ እያዩ አንድም የባዬሎጂ መምህር ስለነበር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፈንገስ በፍጥነት የመራባት ባህሪ ስላለው ለገፀ ባህሪው መጠሪያ እንዲሆን መመረጡን ይገልጻል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ ገፀ ባህሪው የተጠነሰሰው ግሩም ከአውግቸው ተረፈ ‹‹ያስመዘገብኩት›› ላይ በጥቂቱ ቀንጭቦ በጦቢያ ግጥምን በጃዝ መድረክ ላይ ባቀረበበት ወቅት ነበር፡፡ ግሩም መኩሪያ የሚባል ገፀ ባህሪን ተላብሶ ነበር የሚጫወተው፡፡ ከተመልካቾች ያገኘውን በጎ ምላሽ በመመልከትም ቴአትሩ ተጀምሯል፡፡

እያዩ በነጻነት እንዲናገር ሲባል የአዕምሮ በሽተኛ ገፀ ባህሪ እንደተሰጠው በረከት ይናገራል፡፡ ‹‹ብዙ ነገሮችን መናገር የምችለው በእያዩ ነው፤›› ይላል፡፡ በአንድ ጉዳይ ዙሪያ ሐሳብ ይሰጣሉ ተብለው ከሚጠበቁ ግለሰቦች ውጪ ያልተገመቱ ሰዎች ሲናገሩ የበለጠ ተሰሚነት እንደሚኖራቸውም ያምናል፡፡

የአዕምሮ ሕመምተኛው እያዩ የተቀዳደደ ልብስ ለብሶ በደሳሳ መጠለያ ይኖራል፡፡ ፌስታሉን ፍለጋ ከቆሻሻ መጣያ ገንዳ ውስጥም ሳይቀር ይገባል፡፡ ‹‹ይህን ዓይነት ሰው ተመልካች የማይገምተውን ነገር ሲናገር ተደማጭነት ይኖረዋል፤›› ይላል በረከት፡፡

እንደ ደራሲው ገለጻ፣ የአዕምሮ ሕመምተኞች ወይም በልዩ ልዩ ምክንያት ማኅበረሰቡ የገፋቸው ሰዎች በምሬት የተሞሉና ቁጡ የሚሆኑበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ ተውኔቱም ይህን እውነታ ተመርኩዞ ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፡፡ ‹‹ቴአትሩ በዋነኛነት ማኅበራዊ ትችት አዘል ነው፤ ፖለቲካዊ ሽሙጥ (ፖለቲካል ሳታየር)ና ፍልስፍናዎችም አሉት፤›› በማለት ይዘቱን ያብራራል፡፡

እያዩ በገጠመው መሪር ሐዘንና የሕይወት ውጣ ውረድ አዕምሮውን ቢስትም ንግግሮቹ ፍልስፍናውን እንደሚያንፀባርቁ ይናገራል፡፡ የታዳሚዎችን ቀልብ ለመግዛትና መሰላቸት እንዳይኖርም አስቂኝ ሁነቶች ይካተታሉ፡፡

በደራሲው እምነት፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የግለሰቦች መብት በሚገባ አልተተነተነም፡፡ የየራሳቸው ስሜትና ምልከታ ያላቸው ግለሰቦች ማንነት በተናጠል መፈተሽ ሲገባው በቡድን መፈረጅ እንደሚያመዝን ይገልጻል፡፡ እያዩን ሰዎች እንደገፉት በመጥቀስ፣ ‹‹እያዩ ጨርቁን ስለጣለ አገር ጨርቁን አይጥልም፤ ሰው በሕይወቱ አሳዛኝ ነገር ይገጥመዋል፤ ዋናው ጥያቄ ሌሎች ሰዎች እንዴት ይቀበሉታል የሚለው ነው፤›› ሲል ይናገራል፡፡

ቴአትሩ መገፋፋትና ጭቆና ተቀርፎ አጠገባችን ያለውን ሰው ትኩረት እንስጠው የሚል መልዕክት ያስተላልፋል ይላል፡፡ የአንድ ማኅበረሰብ ጥንካሬና ትስስር የሚታየው ለግለሰቦች በሚሰው ቦታ መሆኑን በአጽንኦት ይናገራል፡፡

በየወሩ ይቀርብ የነበረው የእያዩ ትዕይንት በየመድረኩ የተለያዩ ጉዳዮች አንስቷል፡፡ በአንፃሩ ‹‹ፌስታሌን›› ወጥና የቴአትር ግብዓቶችን ያሟላ ነው፡፡ ባለቤቱ ዘውድዬን የመሰሉና ከእያዩ ጋር የሚታወቁ ገፀ ባህሪያት በአዲሱ ተውኔትም ይገኛሉ፡፡ ቴአትሩ የራሱ ማጀቢያ ሙዚቃ አለው፡፡ ተውኔቱ የሚያጠነጥንባቸውን ጉዳዮች የሚያጎሉት ሙዚቃዎች ከአንድ ትዕይንት ወደ ሌላው እንደመሸጋገሪያ የሚለቀቁ ሲሆኑ፣ የሚያዜሙት በዛወርቅ አስፋውና ግዛቸው ተሾመ ናቸው፡፡

ቴአትሩ የፌስታሉን ፍለጋ ተከትሎ በሚያስቁ በሚያሳዝኑም ሁነቶች የተሞላ ነው፡፡ በረከት እንደሚናገረው፣ ተመልካች ትዝብትና ስላቁን እንዲሁም አዝናኝነቱን ፈልጎ ይሄዳል፡፡ አንዳንዴ በትዕይንቱ መሳቅ ብቻ ሊያመዝን ቢችልም እያንዳንዱ ሰው የሚወስደው መልዕክት እንዳለ ያምናል፡፡



‹‹የእያዩ ሥራ ሌላ አይን የመትከል ያህል ነው፤ ታዳሚው ወደየቤቱ ሲገባ ራሱን እንዲመለከት እንፈልጋለን፤›› ይላል፡፡ የተመልካቾችን ቀልብ ለመሳብ ሲባል የሚያስቁ ሁነቶች ቢኖሩም ጠቃሚ መልዕክቶችም ተሳስረው እንደሚቀርቡ ያክላል፡፡ እያዩ እያዝናና መልዕክቱን ማስተላለፉ እንደ ገፀባህሪ እውቅና እንዲያገኝ እንዳደረገውም ያምናል፡፡

ደራሲው ከመድረክ ቆይታቸው የማይዘነጉ ከሚላቸው የእያዩ ፈንገስ መድረኮች አንደኛ ዓመት ክብረ በዓሉ ላይ የቀረበውን ይጠቅሳል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ግሩም የ40 ደቂቃ ትዕይንት አቅርቦ ነበር፡፡ ትዕይንቱ ‹‹ፌስታሌን›› ወደሚለው የሙሉ ጊዜ ቴአትር ለመሸጋገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይናገራል፡፡ ሰዎች ለረዥም ደቂቃ ያለ ምንም ቴአትራዊ ግብዓት መመልከታቸው፣ ግብዓቶች ተካተውና ተራዝሞ ቢቀርብ ተመልካች እንደሚያገኝ እንዳመለከታቸው ይገልጻል፡፡

የዋን ማን ሾው አለመለመድ ቴአትሩ ተመልካች ያገኝ ይሆን የሚል ጥያቄ እንዳጫረባቸው ይናገራል፡፡ በአንድ ተዋናይ የሰውን ስሜት መንካትና ቀልብ ገዝቶ ለረዥም ጊዜ መመልከት እንዲቻል ለማድረግ ፈታኝ እንደነበረም ይገልጻል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ አንዳንዶች እያዩን የሚረዱበት መንገድም ሌላው ችግር ነው፡፡ ‹‹እያዩን የፖለቲካ መሣሪያ አድርገው የሚወስዱ አሉ፡፡ እውነታው ግን እንደዛ አይደለም፡፡ ስለ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሲያነሳ ፖለቲካውን ይዳስሳል፡፡ ይህ ደግሞ የተቃውሞ ጽምፅ አይደለም፤›› ይላል፡፡

እያዩ በጦቢያ ግጥምን በጃዝ መድረክ ሲቀርብ ካገኛቸው ምላሾች መካከል ጥቂቱን ይጠቅሳል፡፡ እያዩ ላይ ያተኮረ ጥናት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሠራቱን፣ ከአዲስ አበባ ውጪ ጎንደርና ሻሸመኔ በሄደበት ወቅት የተገኘውን ምላሽና በእያዩ ስም በማኅበረሰብ ድረ ገጽ የተከፈተውን ገጽ ማንሳት ይቻላል፡፡ ቴአትሩ ስኬታማ መሆኑ ሌሎች ባለሙያዎችንም ወደ ዘርፉ የሚስብ እንደሆነ ተስፋ ያደርጋል፡፡

 

ቴአትሩን ፕሮዲውስ ያደረገው አበባው መላኩ ሲሆን፣ ማጀቢያ ሙዚቃው ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች አበጋዝ ክብረወርቅ ሺኦታ፣ ግሩም መዝሙር፣ ጆርጋ መስፍንና አለማየሁ ደመቀ ናቸው፡፡ ተውኔቱን ከአዲስ አበባና ከኢትዮጵያ ውጪ የማሳየት እቅድ እንዳለ በረከት ይናገራል፡፡ ቴአትሩ አንድ ተዋናይ ያለው መሆኑ ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር እንደሚያመች ያክላል፡፡

 ‹‹ፌስታሌን›› ለጥቂት ጊዜ ከታየ በኋላ ‹‹አጀንዳዬን›› የሚል ቀጣይ ክፍል ይኖራል፡፡ ቴአትሩን በቪሲዲ የማሳተም እቅድም አለ፡፡ የእያዩ ትዕይንት በጦቢያ ግጥምን በጃዝ መድረክም ይቀጥላል፡፡ በያዝነው ሳምንት ምርቃቱን ምክንያት በማድረግ አርብና ቅዳሜ በ12 ሰዓት በአዶት ሲኒማና ቴአትር ይታያል፡፡

 ምን

https://www.ethiopianreporter.com/124596/ 

https://www.ethiopianreporter.com/53041/ 

https://amharic.voanews.com/a/ethiopia-poltical-satire-festalen/3585071.html
 
 

 

Wednesday, December 13, 2023

የኢትዮጵያን የሥነ-ጽሑፍ ሐብት ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ እንዴት ማምጣት ይቻል ይሆን?

 የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ሽልማትና የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ሐብት

 

አፍሪቃዉያን በተለያየ ግዜያት የሥነ-ጽሑፍ ኖቤልን አሸንፈዋል። ይህ የአፍሪቃን ብዙ ዓመታት የሥነ-ጽሑፍ ታሪክን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እንዲገባና ሌሎች የአፍሪቃ እንቅስቃሴዎችም በዓለም ትኩረት እንዲያገኙ ይረዳል። 

የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ሃብት ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ እንዴት ማስገባት ይቻል ይሆን?

«አፍሪቃዉያን በተለያየ ግዜያት የሥነ-ጽሑፍ ኖቤልን አሸንፈዋል። ዘንድሮም አንድ አፍሪቃዊ ተሸላሚ ተገኝቶአል። ይህ የብዙ ዓመታት የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ያላትን አህጉር አፍሪቃን የሥነ ጽሑፍ ሃብቷ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እንዲገባ እና  አፍሪቃ ከስነ-ጥበቡ ዘርፍ በተጨማሪ በሌሎችም እንቅስቃሴዎችም በዓለም ያላትን ትኩረት እንዲጎላ ያደርጋል።»  

በአዲስ አበባ የሆሄ የሥነ-ጽሑፍ ሽልማት አዘጋጅ አቶ ኤፍሬም ብርኃኑ፤  ታንዛንያዊው የ72 ዓመቱ ደራሲ፤ አብዱልረዛቅ ጉርናህ የዘንድሮዉን የዓለም የሥነ-ጽሑፍ የኖቤል ሽልማት ማሸነፋቸዉን ተከትሎ የሰጡን አስተያየት ነበር። በየዓመቱ እንደሚደረገዉ ሁሉ፤ ባለፈዉ ሳምንት ሃሙስ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ቀትር ላይ፤ በስቶክሆልም የሚገኘዉ የስዊድኑ ንጉሣዊ የሳይንስ አካዳሚ ሕንጻ ዉስጥ የሚገኘዉ ከባድ የሚመስል ትልቅ በር፤  ስዊድናዊዉ ታዋቂ ደራሲ ማትስ ማለም ከፍተዉ የሚያነቡትን ጽሑፍ ይዘዉ፤ የድምፅ ማጉያ እና መቅረጫ ወዳለበት ቆም ብለዉ፤ ተከታዩን ለዓለም አወጁ።

«የ 2021  » የሥነ-ጽሑፍ የኖቤል ሽልማት ደራሲ አብዱልራዛቅ ጉርናህ አሸንፈዋል። በዛንዚባር የወተወለዱት እና በአሁኑ ወቅት ኑሮአቸዉን እንጊሊዝ ያደረጉት ደራሲ ለሽልማት የበቁት የቅኝ ግዛት በባህልና፤ በአህጉር መካከል በስደተኛዉ እጣ ፈንታ ላይ ያሳደረዉን ጉልህ ተጽዕኖ የሚጋፈጡ ሥነ-ጽሑፎችን በማበርከታቸዉ ነዉ።»

ታንዛንያዊዉ ደራሲ አብዱልራዛቅ ጉርናህ ምናልባት የሆነ ሰዉ ቀልድ ቀልዶ የሚያታልላቸዉ ስለመሰላቸዉ፤ ነገሩ ቀልድ ነዉ ብለዉ አልተታለልኩም ቢጤ ለማለት ለመልስ ተዘጋጅተዉ እየተጠባበቁ ነበር። በቴሌቭዥን ላይ ቀርበዉ ከስዊድኑ የንጉሳዊ ሳይንስ አካዳሚ የአብዱልራዛቅ ጉርናህን አሸናፊነት ለዓለም ያወጁት ስዊድናዊዉ፤ ደራሲ አብዱልራዛቅ ጉርናህ  ጋር ስልክ ደዉለዉ እንኳን ደስ ያሎ የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ሽልማትን አሸንፈዋል ብለዉ፤ ሲልዋቸዉ ነዉ ጥቂት እንደማመን ቢጤ የዳዳቸዉ። ከዝያም በተለያዩ የዜና ምንጮች በዜና መልክ መቅረቡን ሲሰሙ፤ እዉነት ለመናገር ይህ ጉዳይ በተለያዩ ጣብያዎች በይፋ መነገሩን እስክሰማ ድረስ ማመን ተስኖች ነበር ብለዋል።

 በሞዕራብ አፍሪቃዊትዋ ቤኒን ታዋቂ የሆነዉ ደራሲ ፍሎሪን ኩዋዞቲ ዜናዉ የአፍሪቃን የኪነ-ጥበብ ዓለም የሚያነቃቃ ነዉ። «ይህ ለመላው አፍሪቃ ኪነ-ጥበባዊ ዓለም ታላቅ ዜና ነው። ሌሎች የአፍሪቃ ሥነ-ጽሑፍ ባሞያዎች የእሱን ፈለግ እንደሚከተሉ ተስፋ አደርጋለሁ። ከዚህ ቀደም የናይጀርያዉ ደራሲ፤ ቮለ ሲይንካ ይህን የስነጽሑፍ ኖኔል ሽልማት ሲሸለም ሰማን ዓመት እስኪሞላዉ በጠበቁ ይቆጨናል። የታንዛንያዊዉ ደራሲ ገና የ 20 እና 30 ዓመት እድሜ ክልል ሳለ ጀምሮ በስደት ዓለም ነዉ የሚኖረዉ። ታንዛንያዊ እንደሆነም ነዉ የሚናገረዉ።  በርካታ ጽሑፍንም አቅርቦአል። ሽልማቱን እስኪያገኝ ግን ብዙ ጊዜን ወስዶአል። የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ሽልማት ከሰሃራ በታች ካሉ አፍሪቃ ሃገራት መካከል ለሦስተኛ ደራሲ ብዙ ዓመታት ሳንጠብቅ ያገኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።» 

የቶጎዉ ተወላጅ እና በቶጎ በፈረንሳይኛ ሥነ-ጽሑፋቸዉ የሚታወቁት ኮሲ ኢፎይ የዛንዚባሩ ተወላጅ የዘንድዎዉን ሥነ-ጽሑፍ ማሸነፋቸዉ፤ ለአፍሪቃ ሥነ-ጽሑፍ እዉነተኛ ማበረታቻ ነዉ ብለዋል። «ይህ ለአፍሪቃ አንባቢዎች መልካም ዜና ነው። ምክንያቱም አፍሪቃውያን አንባቢዎች የአፍሪቃ ሥነ-ጽሑፎች ለምን በኢንጊሊዘኛ አይተረጎሙም ብለው እራሳቸውን ስለሚጠይቁ ነዉ። እንዳየነዉ ብዙ ጊዜ አይተረጎምም።  ይህ ጉዳይ በእንግሊዝኛ የሌሉ ፈረንሣይ ተናጋሪ ደራሲያን ስራዎችን ይመለከታል። ግን ደግሞ ከሁሉ በላይ በአፍሪቃ ቋንቋዎች የሚጽፉ ብዙ የአፍሪቃዉያን ድርሰቶች አልተተረጎሙም። ይህንን ሽልማት አንድ አፍሪቃዊ ደራሲ ማግኘቱ ለአፍሪቃ ሥነ-ጽሑፍ እውነተኛ ማበረታቻ ነዉ ብዬ አምናለሁ» 

በጎርጎረሳዉያኑ  በ1948 ዓ.ም በታንዛንያዋ ዛንዚባር የተወለዱት ደራሲ አብዱልራዛቅ ጉርናህ፤ በ1960ዎቹ ዓመታት በስደት ወደ ብሪታንያ ከሄዱ በኋላ የከፍተኛ ትምህርታቸዉን እዝያዉ በብሪታንያ አጠናቀዉ ፤ እስከአሁኑ ጊዜ ድረስ  በኬንት ዩንቨርስቲ የእንጊሊዘኛ እና የድሕረ-ቅኝ ግዛት ዘመን ታሪክ አስተማሪ ሆነዉ በማገልገል ላይ ናቸዉ። ወጣቱ አብዱልራዛቅ ጉርናህ፤ ወደ ብሪታንያ የተሰደዱት ከዛንዚባር አመጽ እና አብዮት ብሎም ነጻነት በኋላ፤ 21 ዓመት ሲሞላቸዉ ነበር። አብዱልራዛቅ ጉርናህ ቅን ግዛትን ጠቅሰዉ ሥነ-ጽሑፍን የጀመሩት በጣም በወጣትነት እድምያቸዉ እንደሆነ ይነገራሉ።

በሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ተሸላሚዉ አብዱልራዛቅ ጉርናህ፤ የቀድሞውን የትውልድ አገራቸዉን ታንዛንያን ደጋግመዉ የሚጠቅሱበት እና የጀርመን እና የእንግሊዝን የቅኝ ግዛት አገዛዝ የሚያወሳ፤ አሥር ልብ ወለዶችን እና በርካታ አጫጭር ታሪኮችን አሳትመዋል። ደራሲ አብዱልራዛቅ የአፍ መፍቻ ቋንቋዋቸዉ የስዋሂሊ ቋንቋ ቢሆንም ፣ ያሳተምዋቸዉ መጽሐፍቶች ሁሉ ግን በእንግሊዝኛ ናቸዉ።

በአፍሪቃ የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ሽልማትን ያገኙ አፍሪቃዉያን ከዘንድሮዉ ተሸላሚ ጋር በቁጥር ስድስት ናቸዉ።  

በ 1986 ዓ.ም ናይጀርያዊዉ ደራሲ ዎሌ ሶይንካ በጎርጎረሳዉያኑ ሽልማቱን ወስዶአል።


ዎሌ ሶይንካ _Wole Soyinka

በ 1988 ዓመት፤ ግብጻዊዉ ነጂብ ማህፉዝ ተሸላሚ ነበር።

 ነጂብ ማህፉዝ_Najib Mahfuz

በ 1991 ነጭዋ ደቡብ አፍሪቃዊት ፀሐፊ በመባል የምትታወቀዉ ናዲን ጎርድሜር የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ሽልማትን ተቀብላለች።

ናዲን ጎርድሜር _Nadine Gordimer

2003  ዓመት ደቡብ አፍሪቃ የተወለደዉ ነጩ አፍሪቃዊ ጆን ማክስዌል ኮቲዝ የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ተሸላሜ ነበር።

ጆን ማክስዌል ኮቲዝ_John Maxwell Coetzee

በ 2008 ደግሚሞ የሞሪታንያ እና የፈረንሳይ ዜንግነት ያለዉ ደራሴ ጂያን ማሬ ጉስታቭ ለክለዚዮ በሥነ-ጽሑፎቹ ኖቤልን አግኝቶአል።

ጂያን ማሬ ጉስታቭ ለክለዚዮ_Jean-Marie Gustave Le Clézio

2021 በዛንዚባር የተወለዱት አብዱልራዛቅ ጉርናህ ተሸላሚ ናቸዉ።

አብዱልራዛቅ ጉርናህ_Abdulrazak Gurnah  

 

በአዲስ አበባ የሆሄ የሥነ-ጽሑፍ ሽልማት አዘጋጅ፤ አቶ ኤፍሬም ብርኃኑ፤ ሽልማቱ ዳግም ወደ አፍሪቃ መምጣቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለዉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በጣም ግዙፍ የሆነ የሥነ-ጽሑፍ ሐብት ያላት ሃገር ናት። እና ይህን የሥነ-ጽሑፍ ሐብት ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ ለማምጣት ምን አይነት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም በአዲስ አበባ የሆሄ የሥነ-ጽሑፍ ሽልማት አዘጋጅ አቶ ኤፍሬም ብርኃኑ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ መጽሐፍን የማንበብ ባህል እየተበረታታ እና እየተጠናከረ መሆኑን በአዲስ አበባ የሆሄ የሥነ- ፅሑፍ ሽልማት አዘጋጅ አቶ ኤፍሬም ብርኃኑ ተናግረዋል። ነገር ግን መጽሐፍን ለማሳተም የህትመት ዋጋ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ የዘርፉን እንቅስቃሴ እንዳይጎዳዉ የሚል አስተያየትም አለ። በዚህም በህትመት አኳያ መንግሥት እርዳታ እንዲያደርግ ጥያቄ ቀርቦአል።     

በስዊድናዊዉ የኬምስትሪ ልሂቅና አዲስ ነገር ፈጣሪ በአልፍሪድ ኖቤል ስም የተሰየመዉና፤ በሞተበት በጥቅምት ወር የስዊድኑ የንጉሳዊ ሳይንስ አካዳሚ ሽልማት መስጠት የጀመረዉ ከጎርጎረሳዉያኑ 1901 ዓመት ጀምሮ እንደሆነ ጽሑፎች ያሳያሉ። በብሪታንያ ነዋሪ የሆኑት የሥነ-ጽሑፍ  ኖቤል አሸናፊ ደራሲ አብዱልራዛቅ ጉርናህ፤ በያዝነዉ የጎርጎረሳዉያን ዓመት 2021 ዓመት መጨረሻ ላይ ከንጉሳዊዉ የሳይንስ አካዳሚ፤ 10 ሚሊዮን የስዊድን ክሮን ወይም ወደ አንድ ሚሊዮን ዶላር ይቀበላሉ።

ከዛንዚባር የመጡት አብዱልራዛቅ ጉርናህ የዘንድሮዉን የሥነ-ጽሑፍ ሽልማት ማግኘታቸዉን የሰሙት በካሜሩን ታዋቂዉ ደራሲ ኤጉኔ አቦዴ ለሽልማቱ አፍሪቃዉያን ልንደሰት ልንኮራ ይገባል ብለዋል። “ለዚህ ድንቅ ሽልማት እና ክብር በመብቃታቸዉ አብዱልረዛቅ ጉርናንን እንኳን ደስ አሎት እላለሁ! አፍሪቃ ስትሸለም ማየት ሁሌም ትልቅ ክብር ነው። በአፍሪቃ ከሰሜን እስከ ደቡብ ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያለን ሁሉ ዜጎች ሁሉ በሽልማቱ ደስተኞች መሆን አለብን!” 

የኢትዮጵያን የሥነ-ጽሑፍ ኃብት በዓለሙ መድረክ እንዲነበብ ምን እናድርግ? 

 

የኢትዮጵያን የሥነ-ጽሑፍ ሐብት ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ እንዴት ማምጣት ይቻል ይሆን? – DW – 4 ጥቅምት 2014

የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ሽልማትና የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ሐብት (ethiopanorama.com)



  • * Wole Soyinka (Nigeria, 1986): ...
  • * Naguib Mahfouz (Egypt, 1988): ...
  • * Nadine Gordimer (South Africa, 1991): ...
  • * John Coetzee (South Africa, 2003) ...
  • *  Abdulrazak Gurnah (Tanzania 2021)

Thursday, November 16, 2023

የምስኪኖቹን መንደር በስካቫተር ያፈረሰው ሚሊየነር

የምስኪኖቹን መንደር በስካቫተር ያፈረሰው ሚሊየነር

Chinese Millionaire Bulldozes This Village’s Run Down Huts And Builds Free Houses For Residents

በደቡባዊ ቻይና ግዛት የምትገኘው የደሳሳዋ ዦንኪንግ መንደር ነዋሪዎች ፡ ሸቀጣሸቀጥ ጭነው ከሚመጡ አሮጌ ከባድ መኪኖች ውጭ አንድም መኪና ወደመንደራቸው ዘልቆ አይተው አያውቁም ። ዛሬ ግን እጅግ ዘመናዊ ፡ መርሰዲስ መኪና መጥታ ቆማለች ።

እናም ነዋሪዎች ፡ በመኪናዋ እዚህ መገኘት በመገረም ዙሪያውን ከበው በማየት ላይ እያሉ ፡ አንድ በጠባቂዎች የታጀበ እድሜው በሀምሳዎቹ የሚገመት ሰው ከመኪናው ወጣ ። ማንም ደፍሮ ሰላም ሊለው ወይም ሊያናግረው የመጣ ሰው ግን አልነበረም ። እናም ሰውየው መንደሩን ለደቂቃዎች ከተመለከተ በኋላ ተመልሶ ወደመኪናው ገብቶ ሄደ ።


ይህ በሆነ በማግስቱ ወደዛች ደሳሳ መንደር ሌላ መኪና መጣ ። ከመጡት ሰወች ውስጥ የትናንቱ ሰውዬ አልነበረም ። በቁጥር በዛ የሚሉ መሀንዲሶች ነበሩ የመጡት ። በዚህ ጊዜ ነዋሪዎቹ ነገሩ ገባቸው ፡ የትናንቱ ሰው ባለሀብት መሆኑን በሁኔታው አውቀዋል ፡ እናም ይህን መንደር ሊያፈርስ መሀንዲሶች ልኳል ።


እነዚህ ነዋሪዎች ፡ ይህም ኑሮ ሆኖ ፡ ደሳሳ ጎጇቸውን የሚያፈርስ ሰው ይመጣል ብለው መቼም አስበው አያውቁም ነበር ። እና ሽማግሌዎች ቀርበው መሀንዲሶቹን አናገሯቸው ። ፍርሀታቸው ልክ ነበር ፡ ትናንት የመጣው ባለሀብት እዚህ መንደር ላይ ሪል ስቴት መገንባት ፈልጓል ፡፡ ለዚህም ከመንግስት ፍቃድ እንዳገኘ ፡ ከሰባ በላይ ለሚሆኑት ለመንደሩ ነዋሪዎችም ካሳ እና መኖሪያ ቤት የሚገነቡበት ገንዘብ እንደሚሰጣቸው እስከዛ ግን በመጠለያ መቆየት እንደሚችሉ ፡ እስከነገ ድረስም እቃቸውን አውጥተው በተዘጋጀላቸው ማረፊያ እንዲያስቀምጡ ነግረዋቸው ሄዱ ።

ከቀናት በኋላም ፡ ብዛት ያላቸው ግሪደሮች እና የህንጻ ሰራተኞች ትንሿን መንደር አጥለቀለቋት ።

ያለቻቸውን አሮጌ እቃ አውጥተው ከቤታቸው አቅራቢያ በተዘጋጀላቸው መጠለያ ውስጥ የገቡት የዦንኪንግ መንደር ነዋሪዎች ፡ ቆመው እያዩ ለዘመናት የኖሩባቸው ደሳሳ ጎጆዎች በስካቫተር ፈረሰ ።


ቃል የተገባላቸው ቤት መስሪያ ቦታም ሆነ ካሳ ሳይሰጣቸው ለወራት በመጠለያ እየተረዱ ቆዩ ። ከአመታት በፊት ከነሱ ብዙም በማይርቅ ቦታ የሚገኙ መንደሮች ልክ እንደነሱ በጨካኝ ባለሀብት ተፈናቅለው ፡ መሰደዳቸውን እያሰቡ ፡ እጣ ፈንታቸውን መጠባበቅ ጀመሩ ።

ይህ በሆነ በጥቂት ወራት ውስጥም የባለሀብቱ ዘመናዊ ቪላዎች ተገንብተው ተጠናቀቁና ፡ ነዋሪዎቹ በስነስርአቱ ላይ እንዲገኙ ፡ በፕሮግራሙም ላይ ለነሱም ቃል የተገባላቸው ካሳ እንደሚሰጥ ተነገራቸው ። ብዙዎች ነዋሪዎች ግብዣውን ተቃወሙ ።


ትንሿ የዦንኪንግ መንደር ዛሬ በልዩ ሁኔታ ደምቃለች ። ከሰባ በላይ ዘመናዊ መኖሪያዎችን ለመመረቅ የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል ። ያቺ የድሆች መንደር ፡ አይታ በማታውቀው ሁኔታ በዘመናዊ መኪኖችና በሀብታሞች ተጥለቅልቃለች ።

የምረቃው ፕሮግራም ተጀመረ ።

 

ያ ፡ በመጀመሪያ ቀን መርሰዲስ መኪና ይዞ ወደዚህ መንደር የመጣው ባለሀብት ፡ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረኩ ወጣ ።
ክቡራንና ክቡራት የዦንኪንግ መንደር ነዋሪዎችና ፡ ክቡራን እንግዶች ዛሬ ልዩ የሆነውን ይህን የዘመናዊ መኖሪያ ቤት ፕሮጀክት ለመመረቅ ስለተገኛችሁ አመሰግናለሁ ።

እኔ የማየው ዛሬ ሚሊየነር መሆኔን አይደለም ። የኔ ስብእና የኔ የሀብት ምንጭ ይሄ መንደር ነው ።. ... እኔ ..... ትንሽ ልጅ ሆኜ የምታውቁኝ Xiong Shuihua ነኝ ። 


በርግጥ ከዚህ መንደር ከወጣሁ ብዙ አመታት ተቆጥረዋልና ፡ አላወቃችሁኝም ። እኔ ግን ሁላችሁንም አስታውሳለሁ ።

ለኔና እጅግ ድሆች ለነበርነው ቤተሰቦቼ በየወሩ ቀለብ ይቆርጥልን የነበረው ሚስተር ዣይን ፡ ከልጆቻቸው እኩል ልብስ ይገዙልኝ የነበሩት የሚስ ታዮኒ ቤተሰቦች ፡ ሲርበን የሚያበሉን የዚህ መንደር ነዋሪዎች ሁላችሁንም አስታውሳለሁ ።

የኔ የአሁን ህይወት ላይ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጣችሁ እናንተ ናችሁ ። ለዚህም ነው መንደሩን ለመለወጥ በተሻለ ህይወት እንድትኖሩ ለማሰብ የተገኘሁት ።


 

እናም እነዚህ ቤቶች የተሰሩት ለናንተ ነው ። ያለምንም ክፍያ በነዚህ ቤቶች ትኖራላችሁ ። ቤቶቹ ንብረቶቻችሁ ናችሁ ። በነጻ የተሰጧችሁ አይደሉም ፡ ከአመታት በፊት ለኔና ለቤተሰቦቼ መልካም ነገር በማድረግ ኢንቨስት አድርጋችሁበታል ።

እያለ እንባ እየተናነቀው ሲናገር የመንደሩ ሰወች በሙሉ በታላቅ ድንጋጤ ውስጥ ሆነው ይሰሙት ነበር ።
ባለሀብቱ ንግግሩን ቀጥሏል ።


 

እናም ከሀምሳ ሚሊየን ዶላር በላይ ወጭ ተደርጎባቸው የተሰሩት ፡ እነዚህ ቤቶች በፈረሱት ቤቶቻችሁ ቁጥር ልክ የተሰሩ ናቸው ፡ ነገ አዳዲስ የቤት እቃ የጫኑ መኪኖች ይደርሳሉ ። መብራትና ውሀም አትከፍሉም ። መስራት ለምትችሉ የስራ እድል ይዘጋጃል ፡ ለአቅመ ደካሞችና ማብሰል ለማይችሉ ደግሞ ዘመናቸውን ሙሉ የሚፈልጉትን መርጠው የሚመገቡበት መመገቢያ አዳራሽም ተገንብቷል ። 

 

የናንተ ውለታ ከዚም በላይ ነው አላቸውና ፡ ከመድረኩ ወረደ ።

 

 


 

ከመጻሕፍት ዓለም - Book shelf 📗📚📖
© Wasihune Tesfaye

https://www.atchuup.com/xiong-shuihua-acts-of-kindness/

https://www.dailymail.co.uk/news/article-2850436/Millionaire-Chinese-businessman-bulldozes-run-huts-village-grew-builds-luxury-flats-residents-instead-free.html




Wednesday, August 30, 2023

ጆሴፍ ፑልቲዘር

 

የፕሬስ ነጻነት ጠበቃ - ጆሴፍ ፑልቲዘር 

ጋዜጠኛ፣ መርማሪ  ሪፖርተር፣ አሳታሚ፣ የፕሬስ ነጻነት ጠበቃ፣ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያውን የጋዜጠኝነት ት/ቤት ከፍቷል - በተጨማሪም ለጋዜጠኝነትና ሥነጽሁፍ ዘርፎች፣ ዝነኛውን የፑልቲዘር ሽልማትም ፈጥሯል፡፡

ጆሴፍ ፑልቲዘር፤ የተሻለ የዕይታ ብቃት ይዞ ቢወለድ ወይም ቼዝ መጫወት ባይችል ኖሮ፣ ጋዜጦቻችን ዛሬ ከምናውቃቸው የተለዩ ይሆኑ ነበር፡፡ ጆሴፍ በ1860ዎቹ በሃንጋሪ በታዳጊነት ዕድሜው ሳለ፣ ወታደር የመሆን ብርቱ ፍላጎት ነበረው፡፡ ነገር ግን ዓይኑ (ዕይታው) ደካማ በመሆኑ የተነሳ የትኛውም ሠራዊት ሊቀበለው አልቻለም፡፡ በመጨረሻ ግን የአሜሪካ ቀጣሪዎች፣ በአሜሪካው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንዲዋጋ መለመሉት፡፡  
በወታደርነት ለአንድ ዓመት ያገለገለው ጆሴፍ፤ ከእርስ በርስ ጦርነት ህይወቱ ተርፎ እዚያ አሜሪካ ተቀመጠ - ያገኘውን  ሥራ እየሰራና እንግሊዝኛ ቋንቋ እየተማረ፡፡ ከዚያም በአጋጣሚ የተከሰተ ድንገተኛ ትውውቅ፣ የራሱንም ህይወት ሆነ የዓለም ጋዜጠኝነትን ታሪክ ለዝንተ-ዓለም ለወጠው፡፡
እንዲህ ነው የሆነው፡፡
ጆሴፍ በቅዱስ ሉዊስ ቤተመጻህፍት ውስጥ እያጠና ሳለ፣ ሁለት ወንዶች ቼዝ ሲጫወቱ ይመለከታል፡፡ ጠጋ ብሎም የአንደኛውን የቼዝ አጨዋወት በማድነቅ ተናገረ፡፡ ከዚያም ሦስቱ ሰዎች መጨዋወት ይጀምራሉ፡፡ ሁለቱ ሰዎች የጋዜጣ አሳታሚዎች ነበሩ፡፡ እናም የሥራ ዕድል ሰጡት - ለጆሴፍ፡፡  

ጆሴፍ ፑልቲዘር ብሩህና ትጉህ ሪፖርተር መሆኑን አስመሰከረ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላም የጋዜጣ አሳታሚ ሆነ፡፡ ከዚያም  አዋጭ  ድርድሮችን ተራ በተራ  ሲያካሂድ ቆይቶ፣ የከተማው ትልቁን ጋዜጣ በእጁ አስገባ - ”St. Louis Post- Dispach” የተሰኘውን ጋዜጣ ገዛው፡፡


ይሄኔ ነው የፑልቲዘር እውነተኛ የላቀ አዕምሮ  የታየው፡፡ ጋዜጣውን የሰፊው ህዝብ ድምጽ አደረገው፡፡ ህገወጥ የቁማር ተግባራትን፣ የፖለቲካ ሙስናንና ዳጎስ ያሉ የግብር ስወራዎችን መመርመርና  ሃቁን አደባባይ ላይ ማስጣት ያዘ፡፡ ሰዎች ይህን አዲስ የምርመራ ጋዜጠኝነት ስታይል ወደዱለት፤የጋዜጣው ሥርጭትም በእጅጉ አሻቀበ፡፡
ጆሴፍ ፑልቲዘር ከታመመም በኋላ እንኳን ተግቶ መሥራቱን አላቋረጠም፤ እናም የዓይኑን ብርሃን ሊያጣም ደርሶ ነበር፡፡ ፑልቲዘር፤ጋዜጦች የማህበረሰቡን ዓላማ ማገዛቸው እንዲሁም ህዝቡን ከሸፍጥና ሙስና መታደጋቸው አስፈላጊ ነው ብሎ ያምን ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሌላ ጋዜጣ መግዛት ቻለ፡፡ የኒውዮርክን ጋዜጣ፡፡ የህዝበኝነት አቀራረቡንም ለብዙ ተደራሲያን ተገበረ፡፡



እ.ኤ.አ በ1909 ዓ.ም የኒውዮርክ ጋዜጣው፣ በአሜሪካ ታሪክ ታላቁ የፖለቲካ ቅሌት የተባለውን ታሪክ ሰበር ዜና አድርጎ አወጣው - የፓናማ ካናል ስምምነት፣ 40 ሚሊዮን ዶላር ህገወጥ ክፍያን  አጋለጠ፡፡ ይሄን ጊዜ የአሜሪካ መንግሥት ፍ/ቤት ሊያቆመው ሞክሮ ነበር፤ ነገር ግን ፑልቲዘር ”ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ” አለ፡፡ በጽናት በመቆም፣ ለፕሬስ ነጻነት ትልቅ  ድል አስመዘገበ፡፡


ጆሴፍ ፑልቲዘር፤በዓለም የመጀመሪያው  የጋዜጠኝነት ት/ቤት፣ በኒውዮርክ፣ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ እንዲቋቋም ከሃብቱ ከፊሉን መድቧል፡፡ ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ለጋዜጠኞችና ጸሃፍት ዓ መታዊ የሽልማት መርሃግብር የሚሆን ገንዘብም ለግሷል፤ ዛሬ ከዝነኞቹ የፑልቲዘር ሽልማቶች አንዱን ማሸነፍ፣ በጸሃፍት ዘንድ እንደ ልዕለ ኮከብ የሚያስቆጥር መሆኑ ይታወቃል፡፡   

ጆሴፍ ፑልቲዘር፤ ምንም እንኳ ወደ  ጋዜጠኝነት  የገባው በአጋጣሚ ቢሆንም ቅሉ፣ ጋዜጦች ዛሬም ድረስ ሊያሳኩት የሚተጉበትን ስታንዳርድ አስቀምጦ ነው ያለፈው፡፡

 ************************

ምን

 https://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=31574:%E1%8B%A8%E1%8D%95%E1%88%AC%E1%88%B5-%E1%8A%90%E1%8C%BB%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8C%A0%E1%89%A0%E1%89%83-%E1%8C%86%E1%88%B4%E1%8D%8D-%E1%8D%91%E1%88%8D%E1%89%B2%E1%8B%98%E1%88%AD&Itemid=209

Thursday, August 24, 2023

የኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ተሳትፎ

 


የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እ.ኤ.አ. በ1983 በፊንላንድ ሔልሲንኪ ከተማ የተጀመረው በቀድሞ አጠራሩ የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር አማካይነት ነው።

ከመጀመሪያው ውድድር በኋላ ሻምፒዮናው እስከ 1991 ድረስ፣ በየአራት ዓመቱ ይደረግ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ውድድሩ በሁለት ዓመት እንዲከናወን ተወሰነ።

በመጀመርያ ሻምፒዮና ከ153 አገሮች የተውጣጡ 1,333 አትሌቶች ተሳትፎ ማድረግ ችለዋል።

እ.ኤ.አ. በ1987 የሴቶች 10,000 ሜትር እና 10 ኪሎ ሜትር ዕርምጃ ተጨምሯል። በ1995 የሴቶች 3000 ሜትር በ5000 ሜትር ሲተካ። በ2005 የሴቶች 3000 ሜትር መሰናከል ተጨምሯል። ዓምና በአሜሪካ ኦሪገን በተከናወነው (2022) የዓለም ሻምፒዮና የ50 ኪሎ ሜትር የወንዶችና የሴቶች፣ የ35 ኪሎ ሜትር ዕርምጃ ተካቷል።

 


ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና ተሳትፎ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን በመጀመርያው ሻምፒዮና 10 አትሌቶች በአምስት የውድድር ዓይነቶች ተሳትፏል። ኢትዮጵያ በወዳጆ ቡልቲ፣ ሥዩም ንጋቱ፣ መሐመድ ከድር፣ በቀለ ደበሌ፣ ግርማ ብርሃኑ፣ እሼቱ ቱራ፣ ግርማ ወልደሃና፣ ከበደ ባልቻና ደረጀ ነዲ ነበር የተወከለችው። አትሌቶቹ በ3000 ሜትር መሰናከል፣ 5000 ሜትር፣ 10 ሺሕ ሜትር፣ ማራቶንና 20 ኪሎ ሜትር የዕርምጃ ውድድሮች ተሳትፈዋል። ከእነዚህ አትሌቶች መካከል ከበደ ባልቻ በወንዶች ማራቶን ለኢትዮጵያ የመጀመርያውን የብር ሜዳልያ አስገኝቷል፡፡

በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ 15ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ኢትዮጵያ የዓለም ሻምፒዮና ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በ18ቱም ሻምፒዮናዎች መካፈል ችላለች። እ.ኤ.አ. በ1993 በስቱትጋርት በተደረገው ውድድር ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በ10 ሺሕና በ5 ሺሕ ሜትር ወርቅና ብር አግኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ ስኬታማ ውጤት

እ.ኤ.አ. በ2009 በጀርመን በርሊን በተከናወነው የዓለም ሻምፒዮና በተለያዩ ርቀቶች የሚሳተፉ 38 አትሌቶችን ይዛ ቀርባለች። ቡድኑ በመካከለኛ ርቀት ጭምር የሚሳተፉ አትሌቶችን ያቀፈ ነበር። በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በተለያዩ ርቀቶች የሚወዳደሩ ተጨማሪ አትሌቶች ይዛ እንድትገባ የተፈቀደላት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በእነዚህ ውድድሮች ተጠባባቂ አትሌቶችን መርጦ ይዞ ቀርቦ ነበር።

በሻምፒዮናው በወንዶች 5000 ሜትርና 10 ሺሕ ሜትር ቀነኒሳ በቀለ ሁለት ወርቅ በማምጣት አዲስ ታሪክ ያጻፈበት ክስተት ነበር። ቀነኒሳ በ10 ሺሕ ሜትር 26:46.31 በማጠናቀቅ የቦታውን ክብረ ወሰን ጭምር ማሻሻል ችሏል። በ1500 ሜትር ወንዶች ደረሰ መኮንን የብር ሜዳልያን ሲያሳካ፣ ፀጋዬ ከበደ በማራቶን ሁለተኛውን የብር ሜዳልያ ያስገኝ አትሌት ሆኗል።

በሴቶች መሠረት ደፋር በ5000 ሜትር የነሐስ ሜዳልያ፣ መሰለች መልካሙ በ10 ሺሕ ሜትር ብር፣ ውዴ አያሌው ነሐስ፣ እንዲሁም አሠለፈች መርጋ በማራቶን የነሐስ ሜዳልያ አስገኝተዋል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ስምንት ሜዳልያ በመሰብሰብ ከዓለም ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ የቻለችበት ሻምፒዮና ነበር።

ከሁለት ዓመት በኋላ በ2011 በደቡብ ኮሪያ ዴጉ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተካፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 34 አትሌቶችን ይዞ መሳተፍ ችሎ ነበር። ሆኖም በ10 ሺሕ ሜትር ወንዶች በኢብራሂም ጄላን ወርቅ ሲገኝ፣ ደጀን ገብረ መስቀል በ5000 ሜትር፣ ኢማና መርጋ 10 ሺሕ፣ ፈይሳ ሌሊሳ በማራቶን እንዲሁም በ5000 ሜትር ሴቶች በመሠረት ደፋር አራት የነሐስ ሜዳልያ በአጠቃላይ አምስት ሜዳልያዎች ማጠናቀቅ ትችሏል። ይህም ውጤት ኢትዮጵያ በበርሊን ዓለም ሻምፒዮን ከነበረው ውጤት ዝቅተኛው ነበር።

በ2013 በሩሲያ በተሰናዳው የሞስኮ የዓለም ሻምፒዮን ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት ያመጣችበት ነበር። በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በመሠረት ደፋር በ5000 ሜትር ወርቅ፣ በጥሩነሽ ዲባባ 10 ሺሕ ሜትር ወርቅ፣ እንዲሁም በ800 ወንዶች በመሐመድ አማን ወርቅ ማምጣት ተችሎ ነበር። በተለይ ባልተለመደ መልኩ በ800 ሜትር ርቀት በመሐመድ ወርቅ መምጣቱ ሻምፒዮናው ለኢትዮጵያውያን ልዩ አድርጎታል። በሌሎች ርቀቶች ሦስት የብርና ሦስት የነሐስ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም ስድስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ትችሏል።

ሌላው ኢትዮጵያ የደመቀችበት የ2015 ዓለም ሻምፒዮና ይጠቀሳል። የአትሌቲክስ ቡድኑ በሻምፒዮናዎች በረዥም ርቀቶች ብቻ ውጤት ከማምጣት በዘለለ፣ በመካከለኛ ርቀትም የተሻለ ውጤት ማምጣት የቻለበት አጋጣሚም እየተፈጠረ የሄደበት ሁኔታ ነበር። በዚህም መሠረት በቤጂንግ ዓለም ሻምፒዮን ገንዘቤ ዲባባ በ1500 ሜትር ወርቅ ማምጣት ችላ ነበር። ይህም ኢትዮጵያ በመካከለኛ ርቀት በዓለም ሻምፒዮና ተስፋ የሰነቀችበት ነበር።

ኢትዮጵያ በቤጂንጉ የዓለም ሻምፒዮን አልማዝ አያና በ5000 ሜትር ወርቅ፣ ማሬ ዲባባ በማራቶን ወርቅ ሲያሳኩ፣ በሦስት የብርና በሁለት የነሐስ ሜዳልያዎችን  በመሰብሰብ ከዓለም አምስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በ2017 የለንደን ዓለም ሻምፒዮን ሁለት ወርቅና ሦስት የብር ሜዳልያ፣ በ2019 በኳታር ሁለት ወርቅ፣ አምስት ብርና አንድ የነሐስ ሜዳልያ ማምጣት ተችሏል። በኳታር ዓለም ሻምፒዮን ለሜቻ ግርማ በ3000 መሰናክል የብር ሜዳልያ ማሳካት፣ ሌላው ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ተስፋ የተሰነቀበት ድል ያደርገዋል።

ዓለም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ዝግ ሆና መቆየቷን ተከትሎ በተለይ አትሌቶች አስቸጋሪ ጊዜ ያሳለፉበት ወቅት ነበር። ይህም ለሁለት ዓመታት ማንኛውም ውድድሮች ሳይከናወኑ መቆየታቸው ይታወሳል። በአንፃሩ ወረርሽኙ አገግሞ የ2022 የኦሪገን ዓለም ሻምፒዮን ለአትሌቶች ተስፋ ያጫረ ሆነ። በልምምድ የዛለው የአብዛኛው አትሌት ጉልበት መፈተሻ መድረክ አገኘ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንም ስኬታማውን የዓለም ሻምፒዮን ያስባለውን ውጤት አስመዘገበ። ኢትዮጵያ 21 ወንድና 19 ሴት አትሌቶችን በተለያዩ ርቀቶች ማሳተፍ ቻለች። ይህም ቁጥር ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና ካሳተፈቻቸው አትሌቶች ቁጥር ላቅ ያለ ነበር። የቁጥር መጨመር ምክንያትም በየሻምፒዮናው የሚመዘገቡ ውጤቶች አማካይነት ነው። በኦሪገን ዓለም ሻምፒዮን በማራቶን በሁለቱም ፆታ (በታምራት ቶላና ጎተይቶም ገብረ ሥላሴ)  እንዲሁም በ10 ሺሕ ሜትር ሴት ለተሰንበት ግደይና በ5000 ሜትር ሴቶች ጉዳፍ ፀጋይ አራት ወርቅ ማሳካት ተችሏል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማራቶን በሁለቱም ፆታ የቦታውን ክብረ ወሰን ማሻሻል የቻሉበት ሲሆን፣ በ10 ሺሕ ሜትር ለተሰንበት የዓመቱን ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ መቻላቸው ልዩ ያደርገዋል። ኢትዮጵያ በኦሪገኑ ዓለም ሻምፒዮን ከአራቱ ወርቅ በተጨማሪ አራት የብር፣ ሁለት የነሐስ ሜዳልያ በድምሩ 10 ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ የቻለችበት ስኬታማው የዓለም ሻምፒዮን ያደርገዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት በዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት ውስጥ ሆና የተመዘገበ ውጤት መሆኑ የተለየ ቦታ እንዲሰጠው አስችሎታል።

ከኦሊምፒክ ጨዋታና ከእግር ኳሱ የዓለም ዋንጭ ቀጥሎ፣ ምርጡ ውድድር እንደሆነ የሚገለጽለት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን፣ ዘንድሮ በቡዳፔስት ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዓምና በአራት ወርቅ የተመለሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድኑ ዘንድሮስ ምን ሊያሳካ ይችላል? የሚለው በአብዛኛው ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።

https://www.proworksmedia.com/121159/ ዳዊት ቶሎሳ


Wednesday, August 23, 2023

‹‹የሩጫዎች ሙሽሪት›› አትሌት መሰለች መልካሙ ኃይለእየሱስ

 

Written by  ግሩም ሠይፉ(አዲስ አድማስ)

ሰሞኑን ለየት ያለ መልዕክት ደረሰኝ፡፡ በፅሁፍ የተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ወይንም በመግለጫ ላይ እንድገኝ የሚጋብዝ ጥሪ አልነበረም፡፡ የሙያ ባልደረባዬ በመጀመርያ መልዕክቱን ያደረሰኝ በስልክ ነው፡፡ አትሌት መሰለች መልካሙ ሰርግ ጠርታሃለች በማለት ጥሪው እንዳስደሰተኝ በመግለፅ እዚያው እንገናኝ ብለን ተለያየን፡፡
አዎ የሠርግ ካርዱ ደርሶኛል፡፡ 

“ይድረስ ለወዳጃችን ይላል… እንደምን ሰንብተዋል፡፡ እኛም ባለንበት በእግዚአብሄር ቸርነት በጣም ደህና ነን፡፡ ይኸው እንደ ወግ ልማዳችን ልጃችን አትሌት መሰለች መልካሙ እና አቶ አብርሃም በቀለ የፍቅር አጋር ሊሆኑ ተጫጭተዋል፡፡ እኛም ይሁን ብለን የሰርጉን ቀን ቆርጠናል፡፡…. ሚያዚያ 7 በምናደርገው የእራት ግብዣ ላይ ብቅ ብለው ያዘጋጀነውን ድግስ አብረን ተቋድሰን እንመርቃቸው፡፡ ወዲያውም ስንጫወት እናመሻለን፡፡ ታዲያ እንዳይቀሩ የቀሩ እንደሆነ ግን ማርያምን እንቀየምዎታለን……
አክባሪዎ ወይዘሮ የአለምወርቅ አዘነ
እና አቶ ይታያል መልካሙ
 


በዚህ አጋጣሚ አትሌት መሰለች መልካሙንና ቤተሰቧን በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በስፖርት ጋዜጠኝነት እኔም የናንተ ቤተሰብ አክባሪ ነኝ፡፡ በዚህ የስፖርት አድማስ አምድ የታሪክ ማስተወሻ ላይ ስለ አትሌት መሰለች መልካሙ የሩጫ ዘመን ለመፃፍ አጋጣሚውን ስፈልግ ነበር፡፡ በነገው እለት ከአቶ አብርሃም በቀለ ጋር በሠርግ መሞሸሯን ምክንያት በማድረግ የሩጫ ገድሏ እንዲህ አቅርቤላችኋለሁ፡፡

 ሙሉ ስሟ መሰለች መልካሙ ኃይለእየሱስ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ 360 ኪሎሜትሮች ርቃ በምትገኘው ደብረማርቆስ ተወልዳለች። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ከ18 ዓመታት በላይ በመስራት ከፍተኛ እውቅና እና ክብር አግኝታለች፡፡ ምንም እንኳን የሩጫ ዘመኗን በአገር አቋራጭ ውድድር ብትጀምርም በትራክ ላይ በ5ሺ ሜትር እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች ላይ በመሮጥም ከ8 የውድድር ዘመናት በላይ ልምድ አላት፡፡ በቤት ውስጥ አትሌቲክስ፤ በጎዳና ላይ ሩጫ፤ በተራራ ላይ ሩጫዎች በግማሽ ማራቶንና ማራቶኖችም ተወዳዳሪ በመሆን ተሳክቶላታል፡፡
ከ10 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ስታድዬም በተካሄደው 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከታዩ አስደናቂ ውድድሮች የማይረሳው የሴቶች አምስት ሺ ሜትር ውድድር ነበር። በ5ሺ ሜትር የምንግዜም ምርጥ ሯጭ የሆነችውን መሰረት ደፋር በማሸነፍ የአፍሪካ ሻምፒዮን ሆና የወርቅ ሜዳልያውን አትሌት መሰለች ስትጎናፀፍ ሙሉ ስታድዬም ቆሞ ነበር ያጨበጨበላት። በሴቶች 10ሺ ሜትር ደግሞ በ2009 እኤአ ላይ  ያስመዘገበችው 29:53.80 የሆነ ጊዜ ከቻይናዋ የዓለም ሪከርድ ባለቤት ዋንግ ዡንክስያ ቀጥሎ ለ7 ተከታታይ የውድድር ዘመናት በ2ኛ ደረጃ ለመቀመጥ የበቃ የምንግዜም ፈጣን ሰዓት ነበር፡፡ በሪዮ ኦሎምፒክ ይህን ደረጃዋን በኦሎምፒክ ሻምፒዮናዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት አልማዝ አያና 29:53.80 በሆነ ጊዜ የተረከበችውና የኢትዮጰያ ሪከርድ ሆኖ የሚገኝ ነው፡፡ በሴቶች የ10ሺ ሜትር ሩጫ ታሪክ ከ30 ደቂቃ በታች ከገቡ 10 አትሌቶች አንዷ ስትሆን ይህን የሰዓት ገደብ ካስመዘገቡ አምስት የኢትዮጵያ ሴት ሯጮችም አንዷ ናት፡፡ 

ሩጫን ከ18 ዓመታት በፊት የጀመረችው የአባቷን ተቃውሞ በመቋቋም ሲሆን በደብረማርቆስ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ልምምድ በመስራት ነበር፡፡ በደብረማርቆስ ከተማ በተካሄዱ የተለያዩ ውድድሮች በተለይ በአገር አቋራጭ ሩጫዎች ስኬታማ ከሆነች በኋላ ክልሏን በመወከል በኢትዮጵያ የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና የምትሳተፍበት እድል ተፈጠረላት፡፡ በወጣቶች ውድድር ጃንሜዳ ላይ ተሳትፎ አድርጋ በ11ኛ ደረጃ ነበር የጨረሰችው፡፡ ከዚህ ውድድር በኋላ ክልሏን በመወከል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ በቃች በትራክ የ1500 ሜትር ውድድር ተሳታፎ በመሆን ባሳየችው ልዩ ብቃት በመብራት ሃይል የአትሌቲክስ ክለብ የምትቀጠርበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ በዚህ መሰረት ከምትኖርበት የደብረማርቆስ ከተማ የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን በማቋረጥ ወደ አዲስ አበባ መጥታ በመብራት ኃይል ክለብ አትሌትነት ሙሉ ለሙሉ ወደሩጫ ስፖርት ገብታለች፡፡ አባቷም ሩጫን ሙያዋ አድርጋ እንደምትዘልቅ በመረዳታቸው ድጋፋቸውን በዚህ ወቅት መስጠት ጀምረዋል፡፡ በማንኛውም ውድድር ለሁሉም ተፎካካሪ ግምት ሰጥታ ለማሸነፍ እንድትወዳደር ነበር የአባቷ ምክር፡፡  በመጀመርያው ዓመት በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመካተት ህልም የነበራት ቢሆንም አልተሳካላትም፡፡ ከ2003 እኤአ ጀምሮ ወደ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ በወጣቶች ደረጃ መሳተፍ ጀምራለች የመጀመርያ ውድድሯ የነበረው በሉዛን የተደረገው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሲሆን፤ ጥሩነሽ ዲባባ ባሸነፈችበት የወጣቶችውድድር 4ኛ ደረጃ አግኝታ ነበር፡፡ ከዚያም በ2004 እኤአ ላይ በኢትዮጵያ የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና በወጣቶችውድድር አሸንፋ በአዋቂዎች የ4ኪሜትር ውድድር ደግሞ 4ኛ ደረጃ በማስመዝገብ ለዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመመረጥ እድሏን አሰፋች፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ መጥቃ የወጣችበት የውድድር ዘመን በ2004 እኤአ ሲሆን በወጣቶች ምድብ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናንና የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች በድርብ ድል የተቀዳጀችበት ነበር፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን በዋናው የአዋቂ ሴቶች አጭር ርቀት 4 ኪሎሜትር ውድድር አራተኛ እንዲሁም በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ በ5ሺ ሜትር 4ኛ ደረጃ ነበራት፡፡ይህ ልምዷን በማጠናከር በ2004 እና በ2005 እኤአ የውድድር ዘመናት በአገር አቋራጭ ውድድሮች ብቻ ሳይሆን፤ በትራክ እና የጎዳና ላይ ሩጫዎች ከ1500 ሜትር እስከ 10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ከ16 በላይ ውድድሮች አድርጋለች፡፡
ከወጣቶች ምድብ ወደ አዋቂ ደረጃ ከተሸጋገረች በኋላ ከፍተኛ የሜዳልያ ውጤት ለማስመዝገብ የበቃችው በ2006 እኤአ ላይ ነው፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአጭር ርቀት 4 ኪሜትር እና በረጅም ርቀት 8 ኪሜትር ውድድሮች ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎች እና በቡድን ደግሞ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን በመውሰድ ነበር። ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በግሬት አየርላንድ ራን የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ላይ በስፍራው ሪከርድ 31:41  በማሸነፍ ተሳክቶላታል፡፡
ከጎዳና ላይ ሩጫው በኋላ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በመመለስ በ2007 እኤአ ላይ በድጋሚ የነሐስ ሜዳልያ ከመውሰዷም በላይ በቡድን ተጨማሪ የወርቅ ሜዳልያ አስገኝታለች፡፡ በተመሳሳይ የውድድር ዘመን ላይ ደግሞ ወደ ትራክ በመግባት በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ አትሌት መሰረት ደፋርን ተከትላ በመግባት በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ አግኝታለች። በዚያው የውድድር ዘመን ማብቂያ ላይ  በ5ሺ ሜትር በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ 6ኛ ደረጃ ነበራት፡፡
በ2007 እኤአ ላይ በአንድ የውድድር ዘመን ከጎዳና ላይ ሩጫ ተነስታ በአገር አቋራጭ ከዚያም በትራክ በመወዳደር የተለየ አቅም ነበር ያሳየችው፡፡ በ2008 እኤአ ደግሞ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ3ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ አገኘች። የወርቅ ሜዳልያው የአትሌት መሰረት ደፋር ነበር፡፡ በዚያው የውድድር ዘመን ከፍተኛ ልምድ ባካበተችበት የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በዘጠነኛ ደረጃ ብትጨርስም ይህን የሚያካክስ ውጤት ደግሞ አሳክታለች፡፡ በ2008 እኤአ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተስተናገደው 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አትሌት መሰረት ደፋርን ቀድማ በመግባት የወርቅ ሜዳልያ በ5ሺ ሜትር የተጎናፀፈችበት ነበር፡፡ ይህ ውጤቷም በቻይናዋ ቤጂንግ ከተማ ለተካሄደው 29ኛው ኦሎምፒያድ ተሳትፎ አብቅቷታል፡፡ በ5ሺ ሜትር በሆነ ጊዜ በስምንተኛ ደረጃ ነበር የጨረሰችው፡፡ ከዓመታት በኋላ በዚሁ ኦሎምፒክ በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ የወሰደችው የቱርኳ ኤልቫን አብይ ለገሰ በዶፒንግ ውጤቷ በመሻሩ፤ አትሌት መሰለች መልካሙ በተሳተፈችበት የመጀመርያ ኦሎምፒኳ በ5ሺ ሜትር የ7ኛ ደረጃ እንዲመዘገብላት ሆኗል፡፡


በ2009 እኤአ ላይ ወደ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ስትመለስ የሜዳልያ ውጤት ነበራት፡፡ በረጅም ርቀት የ8 ኪሎሜትር ውድድር የነሐስ ሜዳልያ ወሰደች፡፡  በጥቂት ወራት ውስጥ ደግሞ በሆላንዷ ኡትርቼት በተካሄደ የ10ሺ ሜትር ሩጫ አዲስ የአፍሪካና የኢትዮጵያ ሪከርድ 29:53.80 በሆነ ጊዜ አስመዘገበች፡፡ አስቀድሞ በጥሩነሽ ዲባባ የተያዘውን የአፍሪካና የኢትዮጵያ ሪከርድ 29:54.66 የሆነ ጊዜ በማሻሻል ነበር፡፡ ያን የውድድር ዘመን የመጀመርያውን የዓለም ሻምፒዮና ከፍተኛ ውጤት በ10ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ በመጎናፀፍ አጠናቀቀች፡፡
በ2010 እኤአ ላይ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በመሳተፍ  የለመደችውን የነሓስ ሜዳልያ በረጅም ርቀት ለመውሰድ የበቃች ሲሆን፡፡ በዚያው የውድድር ዘመን በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ በ10ሺ ሜትር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን ተከትላ በመግባት የብር ሜዳልያ ተጎናፅፋለች፡፡ የውድድር ዘመኑን ያገባደደችው በናይጄርያ ኦቡዱ ግዛት በተካሄደ የአፍሪካ ረየተራራ ላይ ሩጫ ጫምፒዮንሺፕ Obudu Ranch International Mountain Race አስደናቂ ድል በማስመዝገብ ነበር፡፡ በ2011 እኤአ ላይ ትልቁ ውጤታ በጃንሜዳ አገር አቋራጭ ለ4ኛ ጊዜ ማሸነፏ ነበር፡፡
ከ2012 እኤአ ወዲህ ያለፉትን አምስት የውድድር ዘመናት ደግሞ ዋና ትኩረቷ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ግማሽ ማራቶንና ማራቶኖች ሆነዋል፡፡ በ2012 እኤአ በጀርመን ፍራንክፈርት ማራቶኑን ስታሸንፍ 2:21:01 በሆነ ጊዜ የግሏን ፈጣን ሰዓት እና የስፍራውን ሪከርድ አስመዝግባለች፡፡ ይህ የመሰለች መልካሙ የማራቶን ሰዓት ከኢትዮጵያ ሴት ማራቶኒስቶች ፈጣን ሰዓቶች አንዱ ነው፡፡ በ2013 እኤአ ላይ በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ የራስ አልካሂማህ ግማሽ ማራቶን ስትወዳደር በ7ኛ ደረጃ ብትጨርስም በርቀቱ የግሏን ፈጣን ሰዓት 1:08:05  አስመዝግባለች፡፡
ባለፉት 4 የውድድር ዘመናት  በተሳተፈችባቸው የማራቶን ውድድሮች የተሳካላት ናት፡፡ በ2013 እ.ኤ.አ ላይ ሞስኮ ባስተናገደችው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን ብትሳተፍም ውድድሩን ለመጨረስ አልቻለችም፡፡ የመጀመሪያ ማራቶን የሮጠችው በ2012 እኤአ በፍራንክፈርት ማራቶን ሲሆን፣ ውድድሩን ስታሸንፍ 2:21:01 በሆነ ጊዜ ሲሆን  ብርቀቱ የተመዘገበላት ምርጥ ሰዓቷ ነው፡፡ በዱባይ ማራቶን  ሁለት ጊዜ ስትሳተፍ በ2016 እኤአ ላይ በ2፡22፡29 በሆነ ጊዜ ሦስተኛ ደረጃ ማግኘቷ ይታወሳል፡፡  በ2017 እኤአ ደግሞ አልተሳካለትም ከዱባይ ማራቶን ባሻገር በጀርመንና በሆላንድ ከተሞች ሁለት ትልልቅ ማራቶኖችን አሸንፋለች፡፡ በተለይ  በጀርመን ሀምቡርግ ካስመዘገበችው ድል ቀጥሎ ሁለተኛውን የትልቅ ከተማ ማራቶን አሸናፊነት ክብር በአምስተርዳም ለመቀዳጀት መብቃቷ ይጠቀሳል፡፡
በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ማህበረሰብ፤ በዓመለሸጋነቷ፤ በልምምድ ትጋቷ እና በውድድር ላይ ለቡድን ውጤት በምታበረክተው አስተዋፅኦ የምትከበረው አትሌት መሰለች መልካሙ በአገር አቀፍ እንቅስቃሴዎችም ንቁ ተሳታፊ ናት፡፡ ከ4 ዓመታት በፊት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ማሰባሰቢያ የሚውል 20 ኤል.ሲ.ዲ ቴሌቪዥን በስጦታ ያበረከተች ሲሆን ባለ 32 ኢንች ኤል.ሲ.ዲ ሳምሰንግ ቴሌቪዥኖች  ከ153 ሺህ ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸዋል፡፡ በ2017 ላይ ግን አንድ አሳዛኝ ገጠመኝ ነበር፡፡ አትሌት መሰለች መልካሙን ጨምሮ አምስት አትሌቶች ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ደረቅ ቼክ በመጻፍ ማናጀር አታሏቸው መነጋገርያ ሆነው ነበር፡፡ በማታለል ወንጀል የተከሰሰው የአትሌቶች ማናጀር ወላይ አማረ የሚባል ሲሆን በወቅቱ የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንዳመለከተው ተከሳሽ ወንጀሉን በአትሌቶቹ ላይ የፈፀመው ከ2008 እስከ 2009 ዓ.ም ባለው ጊዜ ነው።
ማናጀሩ  ከአምስቱ አትሌቶች በተለያዩ ጊዜና ሀገራት ባደረጉት ውድድር የተሳትፎ የኮንትራት ውል ክፍያን ገንዘብ ሳይኖረው በአዋሽና በሌሎች ባንኮች ሂሳቡ ውስጥ ገንዘብ እንደሌለው እያወቀ ደረቅ ቼክ በመጻፍ ማታለሉ በክሱ ተጠቅሷል። በዚህም መልኩ ለአትሌት አፀደ ፀጋዬ ከ1 ሚሊየን 15 ሸህ ብር በላይ፣ ለአትሌት መሰለች መልካሙ ከ2 ሚሊየን 368 ሺህ ብር በላይ እንዲሁም ለአትሌት በላቸው አለማየሁ 230 ሺህ ብር እና ለሌሎችም አትሌቶች ተመሳሳይ የገንዘብ መጠን ደረቅ ቼክ በመጻፍ የማታለል ተግባር መፈጸሙ በክሱ ተዘርዝሯል፡፡
 የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሽ ወላይ አማረ በ10 ዓመት ከ11 ወራት ፅኑ እስራትና በ2 ሺህ 500 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።
በአሁኑ ወቅት አትሌት መሰለች መልካሙ ለኢትዮጵያ አትሌቶች ዋና ተምሳሌት ሆና የምትጠቀስ ናት፡፡  የሩጫ መደቦቿ 1500ሜ፤ 3000ሜ፤ 5000ሜ ፤ 10,000ሜ፤ የቤት ውስጥ አትሌቲክስ፤ አገር አቋራጭ፤ የጎዳና ላይ ሩጫዎች፤ ግማሽ ማራቶንና ማራቶን ናቸው፡፡


በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ለረጅም ጊዜ ያገለገለችበት ክለብ  መብራት ኃይል ሲሆን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከአሰልጣኝ ዶክተር መስቀል ኮስትሬ እንዲሁም ከዶክተር ይልማ በርታ ጋ ሰርታለች። ለረጅም ጊዜ ማናጀሯ ሆነው ያገለገሏት የግሎባል አትሌቲክስ ኮሚኒኬሽኑ ሆላንዳዊው  ጆስ ሄርማንስ ናቸው፡፡
በዓለም የጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታስቲክስ ድረገፅ ኤአርአርኤስ (Arrs) የመረጃ መዝገብ መሰረት አትሌት መሰለች መልካሙ በሩጫ ዘመኗ 41 ውድድሮችን ያሸነፈች ሲሆን በይፋ የሚታወቅ የገንዘብ ሽልማቷ ከ701ሺ 150 ዶላር በላይ ነው፡፡
ፈጣን ሰዓቶቿ
- በ1500 ሜትር – 4:07.52 (2007)
- በማይል ሩጫ– 4:33.94 (2003)
- 2000 ሜትር ቤት ውስጥ - 5:39.2 (2007) 12ኛው የምንግዜም ፈጣን ሰዓት
• በ3000 ሜትር ትራክ- 8:34.73 (2005)
• 3000 ሜትር ቤት ውስጥ - 8:23.74 (2007) 4ኛው የምንግዜም ፈጣን ሰዓት
• 5000 ሜትር ትራክ– 14:31.91 (2010)
• 10,000 ሜትር ትራክ – 29:53.80 (2009) 6ኛው የምንግዜም ፈጣን ሰዓት
• 10 ኪ ሜትር ጎዳና – 31:17 (2013)
• 15 ኪ ሜትር ጎዳና  - 47:54 (2013)
• 20 ኪ ሜትር ጎዳና  - 1:04:32 (2013)
• ግማሽ ማራቶን - 1:08:05 (2013)
• 30 ኪ ሜትር ጎዳና - 1:39.21 (2014)
• ማራቶን – 2:21:01 (2012)
ዋና ዋና ውጤቶቿ
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና፤ በወጣቶች, በ2003 4ኛ እንዲሁም በ2004 1ኛ፤
በ2004   በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና, 5000ሜ የወርቅ ሜዳልያ
ከ2005 እኤአ ጀምሮ  በ6 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች በመሳተፍ፤  በአጭር 4ኪ.ሜ 6ኛ እንዲሁም በረጅም ርቀት 3 የነሃስ ሜዳልያዎች፤ ሁለት 4ኛ ደረጃዎች እና 9ኛ ደረጃ አስመዝግባለች፡፡
ከ2006 እስከ 2010 እኤአ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5000ሜ 1 የወርቅ ሜዳልያ እና 6ኛ ደረጃ እንዲሁም በ10ሺ 1 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች አግኝታለች፡፡
በ2007 መላው አፍሪካ ጨዋታዎች በ5000m የብር ሜዳልያ እንዲሁም በ2008 በዓለም አትሌቲክስ ፍፃሜ 5000m የነሐስ እና በየዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና 3000ሜ የብር ሜዳልያ
ከ2005  ጀምሮ እስከ 2011   በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 5000ሜ 4ኛ፤6ኛ እና 5ኛ ደረጃ በ10ሺ ሜትር ደግሞ የብር ሜዳልያ እና 5ኛ ደረጃ



https://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=21677:%E2%80%B9%E2%80%B9%E1%8B%A8%E1%88%A9%E1%8C%AB%E1%8B%8E%E1%89%BD-%E1%88%99%E1%88%BD%E1%88%AA%E1%89%B5%E2%80%BA%E2%80%BA-%E1%8A%A0%E1%89%B5%E1%88%8C%E1%89%B5-%E1%88%98%E1%88%B0%E1%88%88%E1%89%BD-%E1%88%98%E1%88%8D%E1%8A%AB%E1%88%99&Itemid=276

የአትሌት መሰለች መልካሙ የሰርግ ቪዲዮ

https://www.youtube.com/watch?app=desktop&v=A9dkNo-Zzww