ከደራሲያን ዓምባ

Thursday, September 29, 2022

"የማሽላው አባት!"__ ተመራማሪ እና የዓለም ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጀታ

 

ዓለም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሰሩት ሥራ በአለም መድረክ ስማቸውንና የሀገራቸውን ስም ያስጠሩ ፀኃፊ፣ አርታኢ፣ መምህር፣ አማካሪ እና ተመራማሪ የአለም ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታን ከረጅሙ የሂወት ጉዞአቸው በጥቂቱ ይዘንላቹ ቀርበናል፡፡

ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ ከአዲስ አበባ ስልሳ ሁለት ኪሎሜትር በስተ ምእራብ እርቀት ላይ በምትገኘው ኦሎንኮሜ በ1950 እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር ተወለዱ፡፡ የቄስ ትምህርታቸውን በአካባቢያቸው ሲከታተሉ ቆይተው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በአካባቢያቸው ስላልነበረ 20 ኪሎሜትር በግራቸው ተጉዘው ተከታትለዋል፡፡



የአለም ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጅታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጅማ የግብርና ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ የተከታተሉ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በእፅዋት ሳይንስ ከአለማያ ኮሌጅ በ1973 ዓ.ም ወስደዋል፡፡ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ1976 በእፅዋት ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በ1978 በእጽዋት ማዳቀል እና ዘረመል ኢንጂነሪንግ አሜሪካ ከሚገኘው ፔድሩ ዩኚቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጅታ ከሁለት መቶ በላይ የጥናት ጽሁፎችን ለህትመት ያበቁ ሲሆን አራት መፅሐፎችን የአርትዎት ስራ ሰርተዋል፡፡

ላለፉት 28 አመታት በአሜሪካ በሚገኘው ፔድሩ ዩኚቨርስቲ ያገለገሉት የአለም ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ ዩኒቨርስቲው አሉኝ ከሚላቸው ተመራማሪዎችም አንዱ ናቸው፡፡ ዶክትሬታቸውን ከተመረቁ በሆላ ወደ ሱዳን በመሄድ ማሽላ ላይ ምርምራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በምርምራቸውም ድርቅን መቋቋም የሚችል የማሽላ ዘርያ ለአለም ማህበረሰብ ማበርከት ችለዋል፡፡ በ150 እጥፍ ምርታማነትን የሚጨምር የማሽላ ዝርያን ለአለም አበርክተዋል፡፡ ድርቅን መቋቋም የሚችል የማሽላ ዝርያ ላይ ባስገኙት ውጤት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አፍሪካዊያን የምግብ ዋስትንን ማረጋገጥ ችለዋል፡፡



ጥናታቸው በዚህ ሳያበቃ በአፍሪካ ምርታማነትን በ40 በመቶ የሚቀንሰው እስትራጋ የሚባለውን አረም መቋቋም የሚችል የተሸሻለ የማሽላ ዝርያን ኢትዮጲን ጨምሮ ለ12 አፍሪካ ሃገሮች ማቅረብ ችለዋል፡፡
ለእነዚህ እና መሰል የምርምር ስራዎቻቸው ከ17 በላይ አለም አቀፍዊ ፣ ሀጉራዊ እና ሀገራዊ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2009 ወርልድ ፉድ ኖብል ፕራይዚ የተሸለሙ ሁለተኛው አፍሪካዊ ለመሆን በቅተዋል፡፡ በአፍሪካ ናሽናሊቲ ሳይንስ ሂሮ ሽልማት ከተሸለሙ አፍሪካዊ ሰባት ተመራማሪዎችም አንዱ መሆን ችለዋል፡፡

ከሰባ በላይ አለም አቀፍ እና ሀገራዊ ተቋሞች በተለያዩ የሀላፊነት ደረጃዎች ላይ የሰሩት የአለም ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ የአለም ህዝብ ቁጥር በጨመረ ቁጥር የምግብ ፍላጎት እየጨመረ ይመጣል ይህን ለመቋቋም ሳይንስ ፣ ቴክኖሎጂ እና የምርምር ፈጠራ ውጤቶች በመጨመር ይሄንን መቋቋም የግድ የሚል ነው ይላሉ፡፡ ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2011 በፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ የአለም አቀፍ የምግብ እና ግብርና ልማት ቦርድ ውስጥ እንዲሁም ከ2014 ጀምሮ በዩናይትድ ኔሽን ሴክሬተሪ ጄነራል ባኒኪሞን የዩዔን የሳይንስ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡


SOURCE:- Technology and Innovation Institute, Ethiopia

Tuesday, September 13, 2022

መስከረም ፩ ቀን ለምን የዘመን መለወጫ ሆነ?

~ የአመቱ ወራት ~

ጨለማው ሲጠፋ ዝናቡ ሲያቆም ፥
ያ የለውጥ ወራት መጣ መስከረም
ሰዎች ይነሣሉ ሊሰሠሩ ታጥቀው ፥
መስከረም ነውና ብርሃን ሰጭው ።
ብዙ እህል እሸት ጥቅምት ሲገባ ፥
ሜዳውና ጋራው አጊጦ ባበባ ፥
ህዳር ወር ደርቆ እረገፈ አበባ ፥
የኑግ ፥ የጎመን ዘር የሰሊጥ የተልባ ።
ታኅሣሥ እኩል ነው አዋቂና ልጁ ፥
ሊሠራ ይነሣል ሁሉም በየደጁ ።
ጥር ነው ወራቱ ያጨዳው ክምሩ ፥
ምርትን ለመሰብሰብ ያለው ግርግሩ ።
የካቲት መውቂያ ነው ክምሩ ፈረሰ ፥
ገለባው ተለየ ንፋሱ ነፈሰ ።
መጋቢት መጣልን ዓመት ተጋመሰ ፥
መጋቢት ወራት ሄደ እየቀነሰ ።
ሚያዝያ ተተክቶ መጋቢት አለፈ ፥
በልጉ ዝናብ ጣለ እያርከፈከፈ ።
ግንቦት ደረቅ ወር ነው ፀሐይዋ ከረረች ፥
አቧራው ቦነነ መሬት ተራቆተች ።
ሰኔ ደግሞ መጣ ክረምት አስከትሎ ፥
ገበሬው ተነሣ ማረሻውን ስሎ ።
ሐምሌም ተከተለ ገባ ዝናም ጭኖ ፥
ቀንና ሌሊቱን በዝናብ ጨፍኖ ።
ነሐሴ ተተካ ኅይለኛው ክረምት ፥
ያወርደው ጀመረ የዝናብ መዓት ።
አምስት አምስት ቀን ሦስቱን አመታት ፥
ባራተኛው አንዴ ስድስት ቀን ያላት ፥
መሸጋገሪያዋ የጳጉሜ ወር ናት ።
===============
ምንጭ 📖 ገፅ ፴፬ የ ፫ኛ ክፍል የአማርኛ መፅሃፍ


መስከረም 1 ቀን ለምን የዘመን መለወጫ ሆነ?
መስከረምና የዓመቱ ወራት ትርጉማቸውስ?
ዘመን መለወጫ ለምን መስከረም ወር ላይ እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሲያትቱም ብርሃናት/ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜን ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱም ከቀኑ ጋር ይተካከላል፡፡ ዓመቱንም ጠንቀቀው ቢቆጥሩት 364 ቀናት ይሆናል፡፡ ለዘመን መታወቂያ ይሆን ዘንድ ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትን ፈጠረ ይላልና /ሔኖክ.21.49/፡፡ በሌላ በኩልም በዘመነ ኖኅ ዓለምን ውኃ አጥለቅልቋት ከቆየ በኋላ ዳግመኛ ከነበረው ውኃ የተገለጠችበት ወር «በመጀመሪያም ወር በምድር ታየች የንፍር ውኃው ከምድር ደረቀ» የሚለውን መሠረት አድረገው የአቡሻኽር ሊቃውንት የዘመን መለወጫን ታሪካዊ አመጣጥ ያስረዳሉ፡፡/ኩፋ.7.1/
በመሠረቱ ዘመን ተለወጠ ሲባል የሚለወጡት ወራቱ ብቻ አይደሉም፡፡ በወቅቱ የሚከሰቱት/የተከሰቱት/ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር /ገጠመኝ/ ሲሆን ወራቶቹ ግን ያው በየዓመቱ እየተፈራረቁ ይመጣሉ፡፡ ዘመን መለወጫ ላይ የሰው ልጆች ሕይወት ሊለወጥ ይገባል፡፡ ተማሪው ተምሮ ወደቀጣዩ ክፍል /ደረጃ/ የሚለወጥበት፣ ገበሬው የክረምቱን ወራት በሚገባ ተጠቅሞ የሚቀጥለውን የበጋ ወራት የሚቀበልበት፣ ሠራተኛው የክረምቱን ዝናብ ታግሶ የፀሐይን ወራት የሚቀበልበት ሌላውም እንደዚያ ሆነው ወራቶቹ በዚያ ዘመን ያለው የተፈጥሮ ክስተቶች የሚለወጥበት ዘመን ተለወጠ እየተባለ ይነገራል፡፡
የቀመር መጀመሪያ የሆነው ዕለት ማክሰኞ ሚያዝያ 1 ቀን ነው። ነገር ግን የሚያዝያን እንዳንጠቀም መዓልቱና ሌሊቱ እኩል አይደለም፡፡
ይህን ተከትሎ በሚዞር ነገር መስማማት እንጂ ሁሉም መነሻ ሆኖ ማገልገል ይችላሉ፡፡ ለመስማማት ደግሞ በቂ ምክንያት ያስፈልጋል፡፡ሊቃውንት ደግሞ ብዙ ምክንያት ያለው መስከረም ስለሆነ መነሻቸው በመስከረም እንዲሆን አድርገዋል፡፡ የመጻሕፍት መምህራን ሌላ ምክንያት ይጨምራሉ፡፡ እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡበት የሰባተኛው ወር መባቻ እንደሆነ እግዚአብሔር አዝዟል፡፡ ይኸውም መስከረም ነው ይላሉ፡፡ ክረምት በጨለማ በብሉይ ይመሰላል ፀሐይ የሚወጣበት መስከረም ደግሞ በብርሃን በሐዲስ ኪዳን ይመሰላል፤ ስለዚህ ለዓውደ ዓመት መነሻ ወር መስከረም ነው፡፡

የኢትዮጵያውያን የዘመን መለወጫ መስከረም ነው፡፡ መስከረም 1 ቀን ርእሰ ዓውደ ዓመት ተብሎ ይጠራል፡፡ ትርጉሙም ርዕስ የአንድ ጽሑፍ /ንግግር በር እንደሆነ ሁሉ በዓመት ውስጥ ያሉ ዓውደ ዓመቶች /በዓሎች/ እና አጽዋማት ማወቂያ /ማመላከቻው/ መስከረም 1 ቀን የሚውልበት ነውና፡፡ እንዲሁም የዓመቱ በዓላትና አጽዋማት የሚታወጀው መስከረም 1 ቀን ነው፡፡ በዚሁም ዕለት መዓልቱን /በፀሐይ/ ሌሊቱን /በጨረቃ/ በመቁጠር ምሥጋና ለእግዚአብሔር ይቀርባል፡፡
መስከረም ማለት ምን ማለት ነው ? የመስከረም ወር ትርጓሜስ?
መስከረም ማለት ከግእዝ የመጣ ቃል ሲሆን (ከሪም- ወይም ከሪሞት)
(መዝከረ-ውይም -ከረም) ከሚሉ የግእዝ ቋንቋዋች የተገኘ የውህድ አረፍተ ነገሮች ውጤት ነው ።
1️⃣ ከሪም ወይም ከሪሞት ማለት ምን ማለት ነው ?
ከሪም ወይም ከሪሞት ማለት-በግእዝ የከረመ፣ የቆየ የሰነበተ ማለት ሲሆን ይህም የክረምት ቆይታ የሚገልፅ እና የክረምት መገባደጃ እንደሆነ የሚያመለክት ነው በሌላ ፍቺ የከረመው ክረምት ማለቂያ የመፀው መባቻ መጀመሪያ ማለት ነው ።
2️⃣ ሌላው ደሞ መዝከረ - ከረም ከግእዝ ቃል የተገኝ ቃል የተገኝ ውህድ ሲሆን ትርጓሜውም መዝከር ማለት በግእዝ መዘከር፣ ማስታወስ፣ ማሰብ ማለት ነው።
ከረም ማለት ደሞ የቆየ፣ የከረመ፣ የሰነበተ ማለት ሲሆን በአጠቃላይ
መዝከረ ከረም ማለት የከረመን የቆየን መዘከር ማስታወስ ማለት ነው
ለዚህም ሲባል የቆየውን አመት የምንዘክርበት አዲሱን ዓመት የምንቀበልበት ወር ለማለት መዝከ ከረም(መስከረም) እንለዋለን። በዚህም ምክንያት አውደ ዓመት አዲስ ዓመት ሆነ የከረመውን የቆየውን አሮጌውን ዓመት ተሸኝ የምንቀበልበት ሰናይ ወር መስከረም ሆነ አሮጌው የቆየው ክረምት ተሸኜ ማለት ነው።
መዝከ ከረም ወደ አማርኛ ሲመለስ አንዱን ከግእዝ በመተው
መስከረም ወደሚል አማርኛ ተቀይሮ ይጠራል። የወራቶች መጀመሪያ የአዲስ ዓመት መባቻ የክረምት መገባደጃ ለማለት መስከረም ተባለ።

13ቱ የኢትዮጵያ ወራት አሰያየም
1️⃣. መስከረም
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - መስ እና ከረም ሲሆን
ትርጉሙም መስ፣ አለፈ፤
ከረም፣ ክረምት ማለት ሲሆን፤ መስከረም ማለት ክረምት አለፈ ማለት ነው።
2️⃣. ጥቅምት
የግእዝ ሥርወ ቃሉ ጠቀመ።
ትርጉም ሠራ፣ ጠቃሚ ጊዜ ማለት ነው።
3️⃣. ኅዳር
የግእዝ ሥርወ ቃሉ - ኀደረ።
ትርጉም አደረ፣ ሰው በወርሃ አዝመራ ማሳ ውስጥ ለጥበቃ ማደሩን ይገልፃል።
4️⃣. ታኅሣሥ
የግእዝ ሥርወ ቃሉ ኀሠሠ።
ትርጉም መረመረ፣ ፈለገ፣ በመኽር ወቅት የሰብል ምርመራ ያመለክታል።
5️⃣. ጥር
የግእዝ ሥርወ ቃሉ ነጠረ።
ትርጉም ጠረረ፣ ብልጭ አለ፣ ነጻ በራ የፀሀይን ግለት ወቅት ያሳያል።
6️⃣. የካቲት
የግእዝ ሥርወ ቃሉ ከቲት።
ትርጉም (የእህልን) መክተቻ ማለት ነው።
7️⃣. መጋቢት
የግእዝ ሥርወ ቃሉ መገበ።
ትርጉም በቁሙ የሚመግብ (በጎተራ የተከተተው የሚበላበት) ማለት ነው።
8️⃣. ሚያዚያ
የግእዝ ሥርወ ቃሉ መሐዘ።
ትርጉም ጎረመሰ ጎበዘ ሚስት ፈለገ(ወርኀ ሰርግ መሆኑን ሲያጠይቅ)
9️⃣. ግንቦት
የግእዝ ሥርወ ቃሉ ገነበ።
ትርጉም ገነባ፣ ሰራ፣ ቆፈረ፣ ሰረሰረ (ለእርሻ የመሬቱን መዘጋጀት ያሳያል።
1️⃣0️⃣. ሰኔ
የግእዝ ሥርወ ቃሉ ሰነየ።
ትርጉም፣ አማረ ማለት ነው።
1️⃣1️⃣. ሐምሌ
የግእዝ ሥርወ ቃሉ ሐመለ።
ትርጉም ለቀመ(ለጎመን)
1️⃣2️⃣. ነሀሴ
የግእዝ ሥርወ ቃሉ አናህስየ።
ትርጉም አቀለለ፣ ተወ የክረምቱን እያደረ መቅለሉን ያመለክታል።
1️⃣3️⃣. ጳጉሜን
ሥርወ ቃሉ ግሪክ ሲሆን ኤጳጉሚናስ።
ትርጉም ተጨማሪ ወር ማለት ነው ።
መልካም አዲስ ዓመት ‼

https://www.facebook.com/petros.kebede




ለምን መስከረም? – ለምን ዕንቁጣጣሽ?


“መስከረም በአበባው ሠርግ በጭብጨባው ይታወቃል” ነው የሚባለው

  • ለንጉሥ ቢኾን ኑሮ “ዕንቁ ፃዕፃኹ” ይባል ነበር እንጂ ዕንቁጣጣሽ አይባልም ነበር  

ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ፣ የመሸጋገሪያው ዕለት “ቅዱስ ዮሐንስ” እየተባለ ሲጠራ፣ በባህላዊና ትውፊታዊ መዘክሩ ደግሞ “ዕንቁጣጣሽ” በመባል ይታወቃል፡፡ ሁለቱም ማለትም ቅዱስ ዮሐንስ እና ዕንቁጣጣሽ መስከረም ፩ ቀን ተደርገው ሲዘከሩም፣ ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ትርጓሜያቸውን ይዘው እንደኾነ መዘንጋት የለበትም፡፡

ሃይማኖት ስንልም ብራና ፍቃ፣ ቀለም አውጥታ፣ ብርዕ ቀርጻ፣ ታሪክን፣ ፍልስፍናን፣ ቁጥርን፣ የሀገር ፍቅርን፣ ነፃነትን፣ ጀግንነትን – መምህርቷ የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ማለታችን እንደኾነ ይታወስልን፡፡ እንግዲህ መስከረም ፩ ቀን ለእኛ ኢትዮጵያውያን የዘመን መለወጫ ወይም ወደ አዲስ ዓመት ተሸጋገርንበት ስንል፣ አዲስነቱ እንዲታወቅ እንደ መጽሐፉ ሥራት፣ እንደ ሊቃውንቱ ትምህርት የገበየነውን ለማካፈል ነው፡፡ ከነይትበሃሉም “መስከረም በአበባው ሠርግ በጭብጨባው ይታወቃል” ነው የሚባለው፡፡

ለምን መስከረም? መስከረም የጨለማው (ክረምት ለማለት) ጊዜ አልፎ ብርሃን የሚታይበት፣ ዕፅዋት፣ አዝርዕት፣ አታከልት፣ የሚያብቡበት፣ የሚያፈሩበት፣ እንስሳት የጠራ ውሃ እየጠጡ፣ ለምለም ሣር እየነጩ የሚቦርቁበት፣ በአጠቃላይ መሬት በልምላሜ አጊጣ፣ ተውባ የምትታይበት በዚሁ በወርኀ መስከረም ነው፡፡ አንዳንድ መምህራንም መስከረምን “የወራት ፊታውራሪ” ይሏታል፡፡

የአቡሻኸር ሊቃውንት እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረው መስከረም ፩ ቀን ነው ሲሉ ያትታሉ፡፡ ሌሎቹም መስከረም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን፣ ከዘመነ ሥጋዌ በፊት በዓለም ኹሉ የወርና የዓመት መጀመሪያ እንደነበር ይገልጹና የክረምት ጫፍ መጨረሻ፣ የመፀው መባቻ ከመኾኑም በላይ መዓልቱና ሌሊቱ ትክክል የሚኾንበት ወር ነው ይሉታል፡፡ በነገራችን ላይ መስከረም፡- ከረመ ከሚለው ግስ የተገኘ፣ ትርጓሜውም ቀዳማይ፣ ለዓለም ኹሉ መጀመሪያ፣ ርዕሰ ከራማት፣ መቅድመ አውራኅ ማለት እንደኾነ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

መስከረም ሌላም አብነት አለው፡፡ “ርዕሰ-ዓውደ ዓመት”፣ “ዕንቁጣጣሽ” የተባሉትን ምሥጢራት ተሸክሟል፡፡ የምሥጢር አባቶቻችንም ይህንን በአፍም በመጽሐፍም ሲነግሩን ዘመናትን አስቆጥረዋል፣ ነገም እንዲሁ ነው፡፡ እና ለምን መስከረም? ለምን ዕንቁጣጣሽ? በሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ የሊቃውንቱን የቃልና የጽሑፍ አስረጅ እንደሚከተለው እናየዋለን፡፡ የመጀመሪያው አፈሊቅ አክሊሉ ገብረኪሮስ ናቸው፡፡

ሊቁ የኢትዮጵያ ጋዜጦችና መጽሔቶች አቋማቸውን የሚገልጹበትን ቦታ “ርዕስ አንቀፅ” በሚል ስያሜ እንዲጠራ ያደረጉ ዜና ቤተክርስቲያን እና በኋላም የአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ የነበሩ ናቸው፡፡ ያልጻፉት ታሪክ፣ የማያውቁት ትውፊት እና ያልተቀኙት የቅኔ ዓይነት የለም ማለት ይቻላል፡፡ ምሉዕ በኩለሄ፡፡

እኚሁ ሊቅ ታዲያ ከዛሬ 56 ዓመት በፊት፣ ማለትም በ1955 ዓ.ም በዚያው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስለዘመን መለወጫና ዕንቁጣጣሽ ሲተርኩ፣ “ስለዕንቁጣጣሽ በቃል የተነገረ እንጂ በጽሑፍ የሠፈረ አልተገኘም” ነው ያሉት፡፡ ኾኖም አሉ፤ “…ኾኖም በቃል ሲወርድ ሲወራረድ እንደመጣ ‹ዕንቁ› ብሎ ‹አዕናቁ› ከግእዝ የተወረሰ ቃል ነው፡፡ ዕንቁ ለአንድ፣ አዕናቁ ለብዙ ይነገራል፡፡ ጣጣሽ፡- “ፃዕፃዕ” ከሚለው የግእዙ ቃል የተወረሰ ነው፡፡ በአማርኛ ጣጣ፣ መባዕ፣ ግብር፣ መፍቀደ፣ በረከተ-ገጽ ማለት ይኾናል፡፡ መጽሐፍተ ብሉያት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርበውን መባዕ፣ የሚገባውን ግብር “ፃዕፃዕ” ይሉታል፡፡ በየዓመቱ ዕንቁጣጣሽ ማለታችን “የዕንቁጣጣሽ ግብር፣ የዕንቁጣጣሽ በረከተ-ገጽ ነው ብለን የምሥራች ማሰማታችን ነው፡፡

በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ዕንቁጣጣሽ የተበረከተው፣ ለቀዳማዊ ሚኒሊክ እናት ለንግሥት ማክዳ ነው፡፡ ንግሥት ማክዳ ቀዳማዊ ሚኒሊክን በወለደች ጊዜ ሕዝቡ “ንጉሥ ተወለደ” ብሎ ዕልል ዕያለ፣ የአበባ ዕንቁጣጣሽ ለንግሥት ማክዳ አበረከተ፡፡ ዕንቁጣጣሽ መባሉም መጀመሪያ ለንግሥቲቱ ስለተገበረ ነው፡፡ ለንጉሥ ቢኾን ኑሮ “ዕንቁ ፃዕፃኹ” ይባል ነበር እንጂ ዕንቁጣጣሽ አይባልም ነበር፡፡ በሸዋም ሕዝቡ ግብር አለብኝ ሲል “ጣጣ አለብኝ” ይላል፡፡ ከዚህም በቀር ንጉሥ ሰሎሞን፣ ከደስታው ብዛት የተነሣ ለንግሥቲቱ፣ አስቀድሞ ለጣትሽ መታሰቢያ ይኹንሽ ብሎ የዕንቁ ቀለበት ሰጥቷት ነበር እያሉ ሊቃውንቱ ነግረውናል …” ብለዋል፡፡

ሌሎችም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት፣ ስለዕንቁጣጣሽ፣ ስለመስከረም እና ዘመን መለወጫ ምሥጢር፣ ከሃይማኖታዊ ትርጓሜው ባሻገር ከሥነ-ቃል ወይም አፍኣዊ ኪነተ ቃል አኳያ አያሌ መጣጥፎችን አኑረውልን አልፈዋል፡፡ በዚህ ረገድ አለቃ አያሌው ታምሩ /ነፍስ ሔር/ ምንጊዜም ሲታወሱ፣ እንደ መምህር ሀብተ ማርያም ተድላ፣ እንደ አለቃ ነቢየ ልዑል ዮሐንስ /ነፍስ ሔር/ እና ቀሲስ ልሳኑ በዛብህ /ነፍስ ሔር/ የምንጠራቸው መምህራነ ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡

አለቃ ነቢየ ልዑል ደግሞ ስለዕንቁጣጣሽ ሲተርኩ፣ “ዕንቁጣጣሽ ግጫ ማለት ነው” ይላሉ፡፡ “ግጫ ደግሞ የሣር ዓይነት ነው፡፡ የአበባ እርጥብ ስጦታ መስጠት የተጀመረው በኖኅ ዘመን ነው፡፡ ኖኅ የጥፋት ውሃ በጎደለ ጊዜ፣ መጉደሉን ለማረጋገጥ ርግብን ልኳት የወይራ ቅጠል አምጥታለች፡፡ እርሱም የመርከቡን ጣራ አንስቶ ከወጣ በኋላ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት በማቅረብ፣ ልዩ ልዩ ጸዐዳ ሽታ ያላቸውንም አበቦች አቅርቧል፡፡ ንግሥት ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ዘንድ ስትኼድ አምስት መቶ ደናግል ተከትለዋት ነበር፡፡ የእልፍኝ አሽከሮቿም እነሱ ሲኾኑ አበባውም የዕንቁጣጣሹም አሰጣጥ በእነሱ ተፈጽሟል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ልጃገረዶች አበባ ቀጥፈው፣ እንግጫ ነቅለው፣ ሸልመው የሚያቀርቡበት ነው፡፡ ይህም በአበው ዘንድ ሲያስመርቃቸው፣ በጎረምሳው ዘንድ ደግሞ የመታጨት ዕድል ያስገኝላቸዋል …” ነው ያሉት፡፡

በነገራችን ላይ ከላይ የጠቀስኳቸው ሊቃውንት፣ ከአለቃ አያሌው በስተቀር ቤተክርስቲያኗ በምታሳትማቸው መጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ ሲጽፉ የነበሩ ዓምደኞች እንደነበሩ ላስታውሳችሁ፡፡ እናም ከዛሬ አርባና ሃምሣ ዓመታት በፊት፣ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሰፈሯቸው መጣጥፎች፣ በመስኩ ጥናትና ምርምር ማድረግ ለሚፈልጉ የጥንታዊ መዛግብትና ኪነቃል ተማሪዎች ግሩም የኾነ ምንጭ እንደሚኾኗቸው እጠቁማለሁ፡፡

እኔም ታዲያ፣ አለቃ አያሌው ታምሩን /ነፍስ ሔር/ መላልሼ ከጠየቅኋቸው ልዩ ልዩ ጉዳዮች መካከል፣ ለዘመን መለወጫ እና ዕንቁጣጣሽ ከ20 ዓመት በፊት “ጦማር” ጋዜጣ ላይ የጠየቅኋቸው ነው፡፡ እርሳቸውም ስለታሪኩ፣ “የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕገጋት” የተሰኘ መጽሐፋቸውን ጠቅሰው ያስረዱኝ የሚከተለው ነው፡፡ “የዘመን መለወጫ የታወቀው በሦስት ዓይነት ነው፡፡

አንደኛ እስራኤል በብሉይ ኪዳን ያከብሩት የነበረው ሚያዚያ ፩ ቀን፣ ሁለተኛ የዓለም ክርስቲያን የክርስቶስን ልደት ተቀዳሚ በማድረግ የሚያከብሩት ጥር ፩ ቀን፣ ሦስተኛ ኢትዮጵያ ጥንተ መሠረትነቱን አውቃ የምታከብረው መስከረም ፩ ቀን ነው፡፡ እስራኤል የዘመን መለወጫ በዓልን በሚያዚያ ማድረጋቸው፣ በዚህ ወር ከግብፅ ባርነት ነፃ ስለወጡና እግዚአብሔር ይህንን የነፃነት በዓል በየዓመቱ እንዲያከብሩት ስለአዘዛቸው ነው፡፡ የዓለም ክርስቲያን ጥር ፩ ቀን ማክበራቸው የክርስቶስን ልደት ምክንያት በማድረግ መኾኑ የታወቀ ነው፡፡

ኢትዮጵያ መስከረም ፩ ቀን የምታከብረው ዘመን መለወጫ የተቀበለችው ከካም ነው፡፡ የተጀመረበትም ካምና ልጁ ኩሳ ወደ ኢትዮጵያ የገቡበት፣ አኵሱም በኩሳ ስም የተመሠረተችበት ጊዜ ነው፡፡ ዘመኑም በኢትዮጵያ ላይ ከ4 ሺህ 900 በላይ ሲኾን፣ ከጥፋት ውሃ በኋላ በኖኅ ዕድሜ 601 ጀምሮ 552 ዓመት አሳልፎ እነሆ ደርሰንበታል፡፡

ኖኅም ሲያከብረው፣ ጥንቱን ዓለም የተፈጠረበት ወር እንደመሆኑ መጠን ከአዳም ጀምሮ ወረደ፣ በአበው እየተላለፈ እስከ እርሱ የደረሰ መኾኑና ኋላም የቀላይ አፎች የተከፈቱበት፣ የጥፋት ውሃ መጉደል የተጀመረበት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጥፋት ውሃ ወዲህ ክረምትና በጋ መፈራረቅ የጀመሩበት፣ ምድር የፍሬ ጽንስ፣ አበባ መልክ ያሳየችበት ስለኾነ ነው፡፡ ፊተኛው ሲጨመር 7 ሺህ 452 ዘመናትን ማሳለፉ ነው፡፡ ስሙም በግእዝ “ርዕሰ-ዐውደ ዓመት”፣ በአማርኛ “ዘመን መለወጫ” “ዕንቁጣጣሽ”፣ “ቅዱስ ዮሐንስ” እየተባለ ይጠራል፡፡

ርዕሰ-ዐውደ ዓመት ማለት፣ የዘመን መለወጫ መጀመሪያ፣ ዕንቁጣጣሽ ማለት “ዕንቁ ዕጽ አወጣሽ ብሎ የአበባውን መፈንዳት ወይም “ዕንቁ ዕጣ ወጣሽ” ብሎ፣ መልካሚቱ ምድር ኢትዮጵያ በዕጣ ለካም መድረሷን የሚያመለክት፣ ቅዱስ ዮሐንስ ማለት፣ በዓሉ ከመጥምቁ ዮሐንስ ዕረፍት ጋር የተደጋገፈ መኾኑን ስለሚገልጥ ነው፡፡

… መስከረም ማለትም፣ እግዚአብሔር ከዚህ እስከ ብሩህ ሰማይ ድረስ ሞልቶ የነበረውን ውሃ ከሦስት ከፍሎ በጠፈር፣ በሐኖስ፣ በውቅያኖስ ከወሰነ በኋላ ደረቁ ይገለጥ ባለ ጊዜ ምድር ገብሬ አርሶ፣ አለስልሶ እንዳከተማት ሁሉ፣ ለዘር የተመቸች ኹና ተገኝታ ነበርና፣ መሀሰ ቆፈረ ከረመ- ከረመ የሚሉትን ሁለቱን ግሶች በማቀነባበርና በማስተባበር መስከረም አጥብቆ፣ ታርሶ፣ ከረመ እንደ ማለት፣ ስሙን ከግብሩ ነስቶ የሚጠራበት ነው፡፡

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም አታሚን – አታኒም የተባለውን ቃል ሲተረጉሙ፣ አታን ወይም ኤታን ማለት ጥንተ ፍጥረት እንደኾነ ዕብራይሰጢውን በማዋሐድ ገልጠው፣ ይኸውም በዕብራውያን ሰባተኛ ወር ጥቅምት፣ በኢትዮጵያውያን በፀሐይ አቆጣጠርና በአቡሻኸር ጠንቃቃ ቁጥር ግን መስከረም መኾኑን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአኵሱም መዲናነት የተቀበለችውና ስታከብረው የምትኖረው መስከረም ፩ ቀን የሚውለው፣ ርዕሰ-ዓውደ ዓመቷ የኩሽ ኩሳ መዲናና መቃብር በመኾኗ፣ አኵሱም ርዕሰ አኅጉር ኩሺ /ኩሳ/ አሞን ለአኅጉረ ኩሺ /ኩላ/ ተብላ የምትጠራውን አኵሱምን /አኩሺምን/ ያህል ጥንታዊነቷን ሲመሰክር የሚኖር ነው፡፡ በዓመተ ዓለም፣ በዓመተ ኩነኔ፣ በዓመተ ምሕረት ደመራ፣ ዘርዝራ፣ ዐጥፋ፣ ነጥላ፣ ጠቅልላ፣ ከፍላ የምትሰጠው የዘመን ቁጥርም የጥንትነቷ ፍሬ ነው” ብለዋል አለቃ አያሌው፡፡

እንግዲህ ተደጋግሞ እንደሚገለጸውና እንደሚታወቀውም፣ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው መኾኑ ነው፡፡ ካስማዋም ከአዳም እስከ ልደተ ክርስቶስ አምስት ሺህ አምስት መቶ የሚለው ኾኖ፣ በ550፣ ክርስቶስ ተወለደ ብላ እነሆ አሁን ፳፻፲፪ /ሁለት ሺህ አሥራ ሁለተኛው/ ዘመን ላይ መኾኗን ልብ ይሏል፡፡

https://ethio-online.com/archives/4924



Thursday, September 1, 2022

መምህር፣ጋዜጠኛ እና ወግ አዋቂው ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል

 


የወዲያነሽ - ረዥም ልቦለድ 1978ዓ.ም.
ጉንጉን - ረዥም ልቦለድ 1982ዓ.ም.
እንካሰላምታ - 2005ዓ.ም.
ኦቴሎ - (ትግርኛ) 2007ዓ.ም.

መምህር እና ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል በሰሜን ሸዋ ማጀቴ ከተማ ተወልዶ፣ ኮምቦልቻና አስመራ አድጓል። አስመራ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ከጨረሰ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የቀን ሥራ ሠርቷል፤ በመምህርነትም አገልግሏል። የግል ትምህርት ቤቶች መምህራንና ሠራተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን ለመብታቸው ተሟግቷል። በደርግ ሥርዓት በኢህአፓ ውስጥ በኅቡእ ተደራጅቶ ሲታገል በደርግ መንግሥት ተይዞ ሁለት ዓመት ከአስር ወር ከታሰረ በኋላ ተፈቷል። ከተፈታ በኋላ ደርግ በድጋሚ ሊያስረኝ ይችላል ብሎ ስለሰጋ ወደ ትውልድ አካባቢው ሰሜን ሸዋ ማጀቴ ገጠር ሄዶ ከፊል ገበሬ ሆኖ እየሠራ በኋላ “የወዲያነሽ” በሚል ርዕስ ያሳተመው ተወዳጅ መጽሐፉን ይጽፍ ነበር።

በ1976 ዓ.ም. በሚኖርበት አካባቢው ድርቅ በመከሰቱ ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት መጀመሪያ ጋራዥ ውስጥ ሰርቷል ፤ ቀጥሎም በመምህርነት አገልግሏል። በመምህርነት ለ33 ዓመታት ያገለገለ ሲሆን “የወዲያነሽ” እና “ጉንጉን” የሚባሉ የልቦለድ መጽሐፍ እንዲሁም “እንካስላንቲያ” በሚል ርዕስ ሥነቃላዊ መጽሐፍ በአማርኛ ቋንቋ ጽፎ ለንባብ አብቅቷል። የአቶ ገብረክርስቶስ ገብረእግዚአብሔር የሕይወት ታሪክንም ጽፎ አሳትሟል።

በትግሪኛ ቋንቋ ደግሞ “ኦቴሎ” ቲያትርን ተርጉሞ በ2005 ዓ.ም. ከማሳተሙ በተጨማሪ ሌሎች ቲያትሮችም ጽፎ ለሕትመት ዝግጁ አድርጎል። የማክሲም ጎርኪን “እናት” የተባለውን ድርሰት ወደ ቲያትር በመቀየር በአማርኛ ቋንቋ ተርጉሟል። በጋዜጠኝነት ከመሥራቱ በተጨማሪ “እረኛዬ” በተሰኘ ተከታታይ ድራማ ላይ ተውኗል። የብዙ ወጣቶችን ድርሰት የአርትኦት ሥራ በመሥራት አስተምሯል፤ አግዟል። በተለያዩ ፕሮግራዎች ላይ አስተማሪና አዝናኝ ንግግሮች በማድረግ ወግ አዋቂነቱንም አስመስክሯል። የዚህ መምህር፣ ደራሲ፣ ጋዜጠኛ እና ወግ አዋቂ ሕይወት ብዙዎችን ያስተምራል ብለን በማመን እንግዳችን አድርገነዋል። መልካም ንባብ!

ውልደትና ዕድገት

መምህርና ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል፣የጣልያኖችን የግፍ አገዛዝ በመሸሽ በ1926 ዓ.ም. ከአስመራ ወደ መሃል አገር ከመጡት አቶ መዋዕል መሐሪ እና ማጀቴ ተወልደው ካደጉት ከወይዘሮ ሙላቷ ሀብተሚካኤል በሰሜን ሸዋ ይፋትና ጥሙጋ አውራጃ ገምዛ ወረዳ ሰኔ 16 ቀን 1943 ዓ.ም. ማጀቴ ከተማ ደይ-ምድር መንደር ተወለደ። ኃይለመለኮት ለእናቱ የመጀመሪያ ልጅ፣ ለአባቱ ደግሞ ሰባተኛ እና የመጨረሻ ልጅ ነው። የአራት ዓመት ሕጻን ሳለ ወላጆቹ በመለያየታቸውና አባቱ ለሥራ ኮምቦልቻ ተቀይረው ስለሄዱ አጎቱ ቤት ጌሾ፣ጥጃ እና ማሽላ እየጠበቀ አደገ። ከአጎቱ ቤት በመቀጠል አያቶቹ ዘንድ አድጓል። አያቶቹ ከፍተኛ ፍቅር ቢያሳዩትም ከአባትና እናት ጋር በመሆን የሚገኝን ልዩ የወላጅ ፍቅርን ሳያገኝ እንዳደገ ይናገራል።

አያቶቹ ዘንድ እያደገ ሳለ አባቱ የቴሌኮሚኒክሽን ሥራ ከሚሠሩበት ከኮምቦልቻ በመምጣት ወደ ሥራ ቦታቸው ይዘውት ሄዱ። ያን ጊዜ የኮምቦልቻ ከተማ ሃያ እና ሰላሳ ቤቶች ብቻ የነበሩባት በመሆኗ በሆያ ሆዬ የሚዳረሱ ነበሩ በማለት ይገልጸዋል። ኮምቦልቻ ከሄደ በኋላ የመጀመሪያዋ እንጀራ እናቱ ክፉ ስለነበሩ ከእሳቸው ጋር አብሮ መኖሩ አሰልቺ ሆነበት። ከእንጀራ እናቱ ጋር ሲኖር በድሮው ፋሽኮ ጠርሙስ ውሃ ለመቅዳት ይዞ ወጥቶ ሳለ አዳልጦት ወድቆ ጠርሙሱ ስለተሰበረ ወደ ቤት መሄድ ፈርቶ ዛፍ ላይ ያደረበትን ቀን አሁን ድረስ በኀዘን ያስታውሳል። እኚህ እንጀራ እናቱ ከአባቱ ጋር ተጣልተው ከሄዱ በኋላ ወደ አራት እንጀራ እናት አይቷል። ኮምቦልቻ የቄስ ትምህርት መማር እንደጀመረ ዘመናዊ ትምህርት በስፍራው ስለተከፈተ አንደኛ ክፍል ገብቶ በእጥፍ (ደብል እየመታ) እያለፈ እስከ አራተኛ ክፍል ተምሯል።

አባቱ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ኤርትራ ሲሄዱ ከኮምቦልቻ ወደ አስመራ በትሬንታ ኳትሮ የጭነት መኪና ከአባቱ ጋር ተሳፍሮ ሄደ። በመቀጠልም ከአስመራ ስምንት ኪሎ ሜትር ያህል ወደምተርቀው ወክድባ መንደር በመሄድ መኖር ጀመረ። በዚያን ወቅት እዚያ መንደር አማርኛ መናገር የሚችሉት እሱና አባቱ ብቻ ስለነበሩ ትምህርት ለመቀጠል ተቸገረ። ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ውጭ ትምህርት የሚሰጠው በትግርኛ ስለሆነ አንድ ዓመት ቆይቶ እንዲመጣ በአስተማሪዎች ስለተነገረው በመንደሩ ውስጥ ያለትምህርት ትግርኛ ቋንቋ እየለመደ ቤተሰቡን ሲያገለግል ቆየ።

በመቀጠል አስመራ ከተማ ሐዲሽ ዓዲ ሰፈር አክስቱ ጋር ሆኖ በመማር አክሪያ ትምህርት ቤት ከ5- 8 ክፍል፣ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ከ9- 12 ክፍል ተምሮ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ። አስመራ እየተማረ ሳለ ዕዳጋ ዓርቢ በሚባል የገበያ ቦታ ሽሮ፣ በርበሬ፣ ተልባ እና ቆሎ ከአክስቱ ጋር ይዞ በመሄድ ሸጧል። አክስቱ ዶሮ ያረቡ ስለነበረ የዶሮዎቹ ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አገልግሏል፤ በከተማው ውስጥ በመዘዋወርም እንቁላልና ዶሮ ይሸጥ ነበር። ክረምት- ክረምት ደግሞ ክብሪትና ጆንያ ፋብሪካ በቀን አርባ ሳንቲምና ከዚያ በታች እየተከፈለው የጉልበት ሠራተኛ በመሆን ሠርቷል።

አሥራ ሁለተኛ ከፍል ከጨረሰ በኋላ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ውጤት ባለማምጣቱ ወክድባ በመሄድ ቤተሰቡን አገልግሏል። ከዚያም አዲስ አባባ በ1962 ዓ.ም. በመምጣት መጀመሪያ በግንባታ ሥራ ውስጥ በጉልበት ሠራተኝነት በቀን ሰባ አምስት ሳንቲም እየተከፈለው ሠርቷል። በመቀጠልም በ19 ዓመቱ ዓለም ማያ በሚባል በግል ትምህርት ቤት በወር ሠላሳ ስምንት ብር እየተከፈለው በመምህርነት ተቀጠረ። በጊዜ ሂደት ደግሞ ክረምት- ክረምት (1967- 68ዓ.ም) በመማር በመምህርነት መጠነኛ ስልጠና አገኘ። ኮልፌ መሠረተ ዕድገት ትምህርት ቤት በኋላም እድገት ጎልማሶች አዳሪ ትምህርት ቤት አስተምሯል። በመሃል በተለያዩ ምክንያቶች እያቋረጠ እንደገና እየጀመረ በአጠቃላይ በመምህርነት 33 ዓመታት አገልግሏል።

የንባብና ድርሰት ጅማሮ

የድርሰት ሥራ ጅማሮው አስመራ ከተማ ሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ የቤት ሥራውን ስለግመል ጽፎ የመጣው ነበር። በወቅቱ እስኪርቢቶ አምስት ሳንቲም በሚሸጥበት ጊዜ የአምስት ብር ፓርከር በጻፈው ድርሰት ምክንያት ከአማርኛ አስተማሪው ከመምህር ጌታቸው ተሸልሟል። መምህር ጌታቸው የንባብ ዓለምን ያስተዋወቁት የንባብ አባቱ ናቸው(መምህር ጌታቸው በኋላ አዲስ አበባ የኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል)። ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበበው መጽሐፍ “ገልጠን ብናየው” የሚል በቤካ ነሞ የተጻፈውን ነበር። ከዚያ በኋላ በአማርኛም በእንግሊዝኛም የተጻፉ መጻሕፍትን አስመራ በሚገኙ ቤተመጻሕፍት በመግባት አንብቧል።

ዘጠነኛ ክፍል እያለ አንድ ጊዜ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ሲሄድ ለሚያያት ልጅ አንዴ ስለእግሯ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስለፀጉሯ፣ ወዘተ. በትግሪኛ ግጥም በመጻፍ ለመስጠት ፈልጎ ሲተወው፤ በነጋታው ሌላ ሲጽፍ ለመስጠት ሲፈራ፤ ሌላ ጊዜ ተጨማሪ በመጻፍ ለመስጠት ሲፈራ፤ በመጨረሻ አንዱንም ሳይሰጣት ተወው። ለጓደኛው የተሻለ የሚለውን ግጥም ሲያሳየው አምጣ ብሎ ለራሱ የሴት ጓደኛ ሰጣት። የሴት ጓደኛው ደግሞ ለጋሽ ኃይለመለኮት ጎረቤቱ ስለነበረች ምላሽ ጻፍልኝ በማለቷ የሁለቱን የጽሑፍ ምልልስ በመፃፍ የመጻፍ ችሎታውን አሻሽሏል። ችሎታውንም ለማሳየት አንዳንድ ጽሑፎቹን የቤተክህነት ትምህርት ዕውቀት ላላቸውና አንባቢ ለሆኑት አባቱ በማንበብ ያቀርብ ነበር። ከእሳቸውም አድናቆት ተችሮታል።

የእኔ ዩኒቨርሲቲ ቤተመጽሐፍ ወመዘክር ነው የሚለው እንግዳችን ወመዘክር ቤቱ የሆነ ያክል የተጠቀመበት ሥፍራ ነው። ጠዋት ለንባብ ገብቶ ምሳውን እዚያው አካባቢ ከበላ በኋላ ተመልሶ ለንባብ ገብቶ ማታ የሚወጣባቸው ጊዜያት ብዙ ናቸው። አክስቱ ጋር በነበረባቸው ጊዜያት ለአራት ዓመት ከስድስት ወር በተከታታይ የተወሰኑ ቀናትን ሥራ ለመሥራት ከቀረባቸው ጊዜያት ውጭ ወመዘክር ገብቶ አንብቧል። አንድ ጊዜ ወመዘክር ያነበበው ሄንሪ ዴቪድ ቶሮ የተባለ ደራሲ የጻፈውን መጽሐፍ አሮጌ መጽሐፍ መሸጫ ሥፍራ ያይና ገዝቶ የራሱ ለማድረግ ስንት እንደሆነ ይጠይቃል። ሻጩ ሦስት ብር እንደሆነ ሲነግረው ሦስት ብር ስላልነበረው በጣም ያዝናል። ትንሽ ቆይቶ ግን አንድ ሐሳብ መጣለት፤ ሦስት ብር ባይኖረውም ሦስት ሱሪ ስላለው አንዱን ሸጦ መጽሐፉን መግዛት። አላወላወለም፤ ሌላ ሰው ቀድሞት መጥቶ መጽሐፉን እንዳይወስድበት በፍጥነት ወደ ቤቱ ሄዶ ሱሪውን ገበያ ውስጥ ሸጦ መጽሐፉን እጁ አስገባ። አሁን ድረስ መጽሐፉ እሱ ዘንድ ይገኛል። መጽሐፉን የሸጠለት ደግሞ ያን ጊዜ መጽሐፍ ሻጭ የነበረው ደራሲ አውግቸው ተረፈ (ህሩይ ሚናስ) ነበር።

ወመዘክር የሕይወቴ አቅጣጫ መለወጫ እና ዕውቀት የገነባሁበት ቦታ ነው የሚለው እንግዳችን ወመዘክር ካነበባቸው መጻሕፍት ውስጥ “ጫት እንደበላ ሰው ያመረቀነኝ” የሚለው የፀጋዬ ገብረመድሕን “ኦቴሎ” የሚለው መጽሐፍ ነበር። የሼክስፒርን እንግሊዘኛ መጽሐፍና የፀጋዬን አማርኛ መጽሐፍ በመያዝ በ1963 ዓ.ም. “ኦቴሎ”ን ወደ ትግርኛ ቋንቋ ተርጉሟል። “ፀላም መቀነት” (ጥቁር መቀነት)፣ “ጋሕሲ ስቃይ” (የስቃይ መቃብር) የሚል ርዕስ ያላቸው ቲያትሮች በትግርኛ ቋንቋ ጽፏል። የቲያትር ጽሑፎቹን ለደራሲ ፀጋዬ ገብረመድህን ተርኮለት ታሪኩ ጥሩ ነው፤ ቲያትር በመድረክ ላይ በተግባር የሚታይ፣ የሰውን ኅሊና መመሰጥ የሚችል ስለሆነ በዚህ ጽሑፍ ያሰፈርከውን ታሪክ በሙሉ የሚያጤንልህ ስለሌለ በዚህ መልኩ ጻፈው ብሎ ምሳሌ በመስጠት አስተያየት ሰጥቶታል። በተጨማሪም በቲያትር መድረክ ላይ ብቻ አይደለም መቅረት ያለብህ በሰፊው መሄድ የምትችለው ልቦለድ (ኖቭል) በመጻፍ ነው በማለት መክሮታል። አስተያየቱን ተቀብሎ አስተካክሏል፤ ልቦለድ በመጻፍም የተሰጠውን ምክር ተግባራዊ አድርጓል።

ኃይለመለኮት የጽሕፈት ሥራውን በመቀጠል የውጭ ጸሐፍት ሥራዎችን መገሻ ዓሻ (የቂል ጉዞ)፣ ሩፋኤል ጸበል፣ የደንከል ዱቄት፣ በሚል በትግርኛ እና በአማርኛ ቋንቋ ተርጉሞ በመጨረስ የድርሰት ችሎታውን ይበልጥ በማሻሻል “የወዲያነሽ” የሚለውን ልቦለድ በአማርኛ መጻፍ ጀምሯል።



የትግል ሕይወት

በ1965 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ወመዘክር ቤተመጽሐፍ ያገኘው አንድ መምህር፣ ቡና እና ሻይ ሕንጻ አጠገብ ኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር ውይይት ስላለ እንድትገኝ ብሎ ሁለት- ሦስት ጊዜ ዓለም ማያ ትምህርት ቤት ድረስ መጥቶ ጋበዘው፤ ኃይለመለኮት ጊዜውን በማንበብ ለማሳለፍ ስለፈለገ አልሄደም። መምህሩ ባለመሰልቸት መጋበዙን በመቀጠሉ በመጨረሻ በውይይቱ ላይ ተገኘ። የሄደበት ስፍራ ስለመበዝበዝ፣ ስለመጨቆን እና ስለመደራጀት አለመቻል በሁለት የማኅበሩ መሪዎች ትምህርት ከመሰጠቱ በላይ፣ ውይይት ተደርጎ ስለነበረ ለሕልሙ ፈውስ ያገኘ መሰለው። ከዚያ በኋላ የትምህርቱና ውይይቱ ዋና ተከታታይሆነ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሁለቱ የማኅበሩ መሪዎች ሌላ ሥራ አግኝተው መሪነቱን ስለለቀቁ ማኅበሩን በፈቃደኝነት የሚመራ ሰው አልተገኘም። ኃይለመለኮት ማኅበሩ መፍረስ የለበትም በሚል ቁጭት ተመራጭ አመራር እስኪሰየም ድረስ በፈቃደኝነት እንደሚመራ መድረክ ላይ ወጥቶ ተናገረ። ሌላም ሰው ሊያግዘው ፈቃደኛ ሆኖ በመገኘቱ ማኅበሩም ከመፍረስ ዳነ።

ሁለት ወር ያህል በመሪነት እንደሠራ ምርጫ ሲካሄድ የግል ትምህርት ቤት መምህራንና ሠራተኞች አንድነት ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ። ከ1965 ዓ.ም. እስከ 1969 ዓ.ም. የማኅበሩ መሪ በመሆን ከመቶ በላይ ለሆኑ በደል ለደረሰባቸው መምህራንና ሠራተኞች ከሌሎች የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ጋር በመተባበር ፍርድ ቤት በመቅረብ ስለደረሰባቸው በደል ተከራክሯል። በዚህ ጊዜ ባደረገው እንቅስቃሴ በየካቲት 1966 ዓ.ም. በንጉሡ ጊዜ ለአምስት ቀን ታስሮ ክስ ተመስርቶበት፣ በደርግ ጊዜ በ1967 ዓ.ም. ሃምሳ ብር ቅጣት እንዲከፍል ተበይኖበት ከፍሏል።

የማኅበሩ መሪ ሆኖ ሳለ የወዲያነሽን ከአጠገቡ ገሸሽ አደረገ፤ ልቦለድ ድርሰት መጻፉንም አቋረጠ። በቤተመጽሐፍ ስለሙያ ማኅበራት የሚተርኩ መጻሕፍትን አብዝቶ አነበበ፤ የሶሻሊዝም ርዕዮት ተከታይም ሆነ። ጋዜጣ ላይ በብዕር ስም ሲጽፍ የነበረውን ሥነጽሑፋዊ ሥራዎች በመተው ስለሠራተኛው መደብ መጨቆን እና ስለመደራጀት መጻፍ ጀመረ። በዚህ ሂደት በኢሕአፓ ውስጥ በኅቡእ ተደራጅቶ እየታገለ ሳለ በደርግ መንግሥት ተይዞ በቅድሚያ ሶስት ወር በታላቁ ቤተመንግሥት (በወቅቱ ደርግ ጽ/ቤት በነበረው) ታስሯል። ከሦስት ወር በኋላ ደግሞ በዝውውር ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሯል። በአጠቃላይ ሁለት ዓመት ከአስር ወር ከታሰረ በኋላ በ1972 ዓ.ም. ተፈታ።

ስለእስር ቤት ሕይወቱ ሲናገር ‹‹እስር ቤቱ እጅግ በጣም የስቃይ ቦታ ነው። አንድ ሰው ጠቦ፣ ጠቦ፣ ጠቦ ሲጨንቀው ራሱ ውስጥ የሚቀርበት ሥፍራ ነው። በሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የመጀመሪያው 10 ካሬ ሜትር ሁለተኛው 12 ካሬ ሜትር በሆነ መስኮት በሌላቸው ቤት ውስጥ 46 እስረኞች ታስረን ነበር። በመኝታ ጊዜ አስቸጋሪ ስለሆነ እግራችን በግራና በቀኝ ተላልፎ ቁልፍልፎሽ ነው የምንተኛው። በጣም የሚገርመኝ ጉዳይ በዚያን ጊዜ የነበረው የስቃይ ሁኔታ እስከ አሁን ድረስ ሳይቀረፍ ዘልቆ መቀጠሉ ነው። ሲገረፍ የነበረው ሰው ገራፊ ይሆናል ብዬ አላስብም ነበር፤ በተግባር ያየሁት ግን ብሶበት መገኘቱን ነው›› ይላል።

ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እስር ቤት ውስጥ የማክሲም ጎርኪን “እናት” የተባለውን ድርሰት አብሮት የታሰረው ዮሐንስ ክፍሌ ከእንግሊዝኛው መጽሐፍ ወደ አማርኛ ሲተረጉም፣ ኃይለመለኮት የአርትኦት ሥራውን እየተከታተለ ከአሳሪዎቹ ተደብቆ አከናውኖ ጨርሷል። አርትኦቱን ከጨረሰ በኋላ ደግሞ አሳሪዎቹ እንዳያውቁበት ሌሊት ከስድስት ሰዓት በኋላ እየጻፈ ደግሞ “እናት” መጽሐፍን ብቻውን ወደ ቲያትር በመለወጥ በአማርኛ ጽፏል። ጽሑፉን ሲጽፍ የደብተር ሉክን አንዷን መስመር ለሁለት በመክፈል ነበር። የጻፈበትን አንድ መቶ ሰባት ገጽ ደብተር ከእስር ቤት እንዲወጣ ያደረገው ደግሞ በፔርሙስ ቂጥ ሥር አስገብቶ በመደበቅ አምስት ስድስት ሉክ በማስቀመጥ ለወንድሙ በመላክ ነበር። በዚያ ደብተር የተጻፈው ጽሑፍ አሁን የአርትኦት ሥራው ተጠናቆ ለሕትመት ዝግጁ ሆኖ አልቋል። አሳታሚ ቢያገኝ ለማሳተም ፈቃደኛ ነው።

ወደ ስነጽሑፍ ሥራ መመለስ

እንግዳችን ሁለት ዓመት ከአስር ወር ታስሮ ከተፈታ በኋላ ሳጥን ውስጥ አስቀምጦት የነበረውን የወዲያነሽን ድርሰት አውጥቶ መጻፍ ቀጠለ። ትንሽ ቆይቶ ደርግ በድጋሚ ሊያስረኝ ይችላል ብሎ ስለሰጋ ወደ ትውልድ አካባቢው ሰሜን ሸዋ ማጀቴ ገጠር በ1973 ዓ.ም. ሄዶ ከፊል ገበሬ ሆኖ እየሠራ የወዲያነሽ ድርሰትን ካቆመበት መጻፉን ተያያዘው። በ1976 ዓ.ም. ደግሞ በአካባቢው ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት ከማጀቴ ወደ አዲስ አበባ መጣ። አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ አንድ ዓመት ያህል ጋራዥ ሠራ። ጋራዡ አካባቢ ለሚሠራ ጓደኛው ለሆነ አቶ ዘለቀ ብሩ ለሚባል ሰው የወዲያነሽን ረቂቅ እንዲያነበው ሲሰጠው፣ ለሦስት ቀን ያህል ካነበበ በኋላ ድርሰቱን አድንቆ ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት እንዲያትምለት መስጠት እንደሚችል ይነግረዋል።

ከአቶ ዘለቀ ጋር አብረው በመሄድ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ረቂቁን ይሰጣሉ። ከአስር ወር በኋላ የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ቦርድ እንዲታተም መፍቀዱ ተነገረው። መስፍን ሀብተማርያም ደግሞ የአርትኦት ሥራ እንዲሠራለት ተመደበ። መስፍን መጽሐፉን በአድናቆት እየካበ ከነገረው በኋላ ማስተካከል የሚገባውን አንድ ነገር ነገረው። ባሻ ያየህይራድ ጨቋኝ ስለሆኑ፣ በደል ስለፈጸሙ፣ ጊዜው ሶሻሊዝም ስለሆነ መሞት ስላለባቸው ግደላቸው ተብሏል አለው። እሱም ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ገደላቸው። “የወዲያነሽ” በ1978 ዓ.ም. ታተመ። የመጀመሪያ መጽሐፉ ሲታተም ኮልፌ መሠረተ ዕድገት የሚባል ትምህርት ቤት ያስተምር ነበር። እጅግ በጣም ደስተኛ ከሆነባቸው ቀኖች አንዱ እንዲታተምልህ ተፈቅዷል ተብሎ የተነገረው ቀን እንደሆነ ይናገራል።

“የወዲያነሽ” ታትሞ በወጣ በሃያ ቀኑ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ መጽሐፉን በመተቸት ወቀሳ አዘል አስተያየት ሰጡ። ኃይለመለኮት ምላሽ እንዲሰጥ ሲጠየቅ ‹‹እኔ እሳቸው በጻፉት መጽሐፍ ተምሬ ያደኩኝ ስለሆነ ምላሽ መስጠት አልችልም›› አለ። መምህር፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ደምሴ ጽጌ ግን ‹‹“የወዲያነሽ” እንደዚህ አይደለችም›› ብሎ ለጽሑፉ ምላሽ ሰጠ። ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ‹‹ባለአደራ ይጣራል ከጋራ›› በሚል በድጋሚ ጻፉ። እንኳን ባለአደራነት ደረጃ ሊዳረሱ ኃይለመለኮትና ደምሴ በወቅቱ በአካል የሚተዋወቁ ሰዎች አልነበሩም። በመጨረሻ አሸናፊ ዘደቡብ አዲስ አበባ የሚባሉ እውቅ ጸሐፊ ማሞ ውድነህን ነቅፈው ኃይለመለኮትን ደግፈው ጻፉ። በዚህ ሂደት “የወዲያነሽ” ታዋቂና ተነባቢ መጽሐፍ ሆነ። በኢትዮጵያ ሬድዮ “የመጽሐፍ ዓለም” በሚል ፕሮግራም ላይ በ1979 ዓ.ም. በተፈሪ ዓለሙ ለመተረክም በቃ። ከኢትዮጵያ ሬድዮ በተጨማሪ በአሜሪካና በጀርመን አገር በማኅበረሰብ ሬዲዮ ተተርኳል።

በሠዓሊ ጥበበ ተርፋ እና በአውግቸው ተረፈ መኖሪያ ቤት ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ አልአዛር ሳሙኤል፣ ሥዩም ተፈራ፣ መስፍን ዓለማየሁ፣ ባሴ ሀብቴ፣ ደምሴ ጽጌ ፣ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ ቅድስት ክፍለዮሐንስ እና የቤቱ ባለቤቶች ቅዳሜ – ቅዳሜ እየተገናኙ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ሥነጽሑፋዊ ሥራዎችን እያቀረቡ እርስ በእርስ በነፃነት አስተያየት ይሰጣጡ ነበር። ተሳታፊዎቹ የሚሰጡት አስተያየት ጸሐፊውን የሚገነባ፣ የተሻለ እንዲሆን ጥረት ያደርጉ ነበር። ከተጠቀሱት ዋነኛ ተሳታፊዎች በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት በጊዜያዊነት ሌሎች ባለሙያዎችም እየመጡ ተሳትፈዋል። ደራሲና ጋዜጠኛ ኃይለመለኮት በዋነኛነት የሚሳተፉትን አባላት ሲገልጻቸው‹‹በየግሉ አንብቦ የመጣ፤ ሰው ማክበር ራስን ማክበር እንደሆነ የተረዳ፣ ለሥነጽሑፍ (ጥበብ) ከፍተኛ ፍቅር ያለው፣ አንብቦና አድምጦ የማይጠግብ፤ አንዱ የሌላውን ነፃነት የሚጠብቅ ስብስብ ነበር›› ይላል።

በዚህ የስነጽሑፍ ስብስብ ውስጥ የ“ጉንጉን” መጽሐፍ በማጀቴ አነጋገር ዘይቤ መጻፍ ተጀምሮ ተጠናቋል። መጀመሪያ ኃይለመለኮት ህዳር ወር 1980 ዓ.ም. አስራ ስምንት ገጽ ጽፎ አነበበ፤ ጋሽ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ካዳመጠ በኋላ ‹‹ለእኔ ክላሲክ ሥራ ነው›› አለ። በቡድኑ አስተያየት እየተሰጠበት በየጊዜው ጋሽ ኃይለመለኮት ሲጽፍ፣ ሲያነበብ እንዲሁም አስተያየት ሲሰጥበት ቆይቶ ነሐሴ ወር 1980 ዓ.ም. ተጽፎ ተጠናቀቀ። በ1981 ዓ.ም. ደግሞ የአካባቢውን ስያሜዎች ትክክለኛነት ለማጣራት ማጀቴ ድረስ በመሄድ በየመንደሩ በመዘዋወር አረጋግጧል። በመጨረሻ በ1982 ዓ.ም. ኩራዝ አሳታሚ ድርጅትን ሳይጠይቅ ድርጅቱ ራሱ ኃይለመለኮት በግሉ በማሳተም ላይ እንዳለ አውቆ ጥያቄ አቅርቦ “ጉንጉን” ታተመ። ከታተመ በኋላ በሸገር ሬዲዮ ለሁለት ጊዜ ተተርኳል። ከሸገር ሬድዮ በተጨማሪ በጀርመን አገር በማህበረሰብ ሬዲዮ ለመተረክ በቅቷል።

ከ“የወዲያነሽ”ና ከ“ጉንጉን” በተጨማሪ በ2005 ዓ.ም. “እንካስላንቲያ” በሚል ርዕስ ሥነቃላዊ መጽሐፍ አሳትሟል፤ እንዲሁም በ2013 ዓ.ም. የዶክተር ተወልደ እና ጋሽ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ታላቅ ወንድምን የአቶ ገብረክርስቶስ ገብረእግዚአብሔር የሕይወት ታሪክ ጽፎ ለንባብ አብቅቷል። በትግርኛ ቋንቋ ደግሞ “ኦቴሎ”ን በ2005 ዓ.ም. አሳትሟል። “ኦቴሎ” በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ተማሪዎች ለከተማዋ ነዋሪዎች በመድረክ ቀርቦ ታይቷል። ከጎቴ የባህል ማዕከል ጋር በመተባበርም ወደ ስምንት የሚሆኑ የሕጻናት መጽሐፍ ተርጉሞ ታትመዋል።

ዶክተር እንዳለጌታ ስለ አንጋፋው የስነ ጽሁፍ ሰው ሲናገር ‹‹ድንቅ መምህርና ደራሲ ብቻ ሳይሆን ድንቅ ወግ አዋቂ ነው›› በማለት ይገልጸዋል። በተለያዩ ጋዜጦች ላይ ጽሑፎች በማቅረብ እየተሳተፈ ታትሞለታል። በጋዜጠኝነት “እፎይታ” መጽሔት ላይ ምክትል አዘጋጅ በመሆን ከመሥራቱ በተጨማሪ “ፈርጥ” መጽሔት ላይ የአርትኦት ሥራ ሠርቷል። በ“እረኛዬ” ተከታታይ ድራማ ላይ ተዋናይ በመሆንም ሠርቷል። ጋሽ ኃይለመለኮት በድራማው ላይ የተሳተፈው በአጋጣሚ መሆኑን ይናገራል። የፊልሙ ደራሲ ከሆኑት ውስጥ አንዷ የሆነችው አዜብ ወርቁ በአጋጣሚ ታገኘውና ከአንተ ሕይወት ጋር የሚሄድ አንድ ድራማ ስላለ ትተውናለህ በማለት ትጠይቀዋለች። እሱ መጀመሪያ አይሆንልኝም ብሎ ቢያንገራግርም በመጨረሻ እንደሚችል ታግባባውና ለፊልሙ ታሪክ መነሻ የሚሆን ሥራ በማቅረብ አብዬ በቃሉን ወክሎ ሲተውን ታይቷል።

ሌሎች የሕይወት ገጾች

መምህርና ደራሲ ኃይለመለኮት ላበረከተው አስተዋጽኦ የተለያዩ እውቅናዎችን አግኝቷል። በኮልፌ መሠረተ እድገት ትምህርት ቤት በ1976 ዓ.ም. እና በ1977 ዓ.ም. በትምህርት ቤት ደረጃ ምስጉን መምህር በሚል ተሸላሚ ሆኗል። በ1979 ዓ.ም. ደግሞ ከአዲስ አበባ ብቸኛ ተመራጭ በመሆን በኢትዮጵያ ደረጃ ምስጉን የትምህርት ባለሙያ ተብሎ የነሐስ ሜዳልያ ተሸልሟል። በወቅቱ በአገር ደረጃ የተሸለሙት መምህራን ሃያ አንድ ነበሩ። ኮልፌ መሠረተ እድገት ትምህርት ቤት ያስተማራቸው ተማሪዎቹ ደግሞ በመምህርነት ላደረክልን ሁሉ እናመሰግንሀለን በማለት በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ውስጥ በአካባቢው ሕዝብ ፊት ዕውቅና በመስጠት ልዩ ተሸላሚ በማድረግ ካባ አልብሰውታል፤ ገንዘብም ሰጥተውታል።በሽልማቱ ሥነሥርዓት ላይ ግን ሌላ ጊዜ ለመናገር የማይቸገረው አንደበቱ በደስታ ብዛት ተሳስሮበት እንደነበረ ያስታውሳል። በደራሲነቱ ባበረከተው አስተዋጽኦ ደግሞ “ኢትዮጵያ ታመሰግናለች” ተብሎ ከሌሎች የሥነጥበባት ሰዎች ጋር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ ሜዳልያ ተበርክቶለታል።

በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ከወረዳ 24 የምርጫ ጣቢያ በ1987 ዓ.ም. አንደኛ በመሆን ተመርጦ በሥራ አስፈጻሚነት በማኅበራዊ ዘርፍ ቢሮ ተሰጥቶት ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሠርቷል። በዚህ ወቅት የቢሮክራሲው አስተዳደር ልምድ ስላልነበረው መንፈሱ የተጨነቀበትና በመምህርነት ሲያገኝ የነበረው ነጻነቱን ያጣበት ጊዜ መሆኑን ይናገራል። ስለሆነም ነፃነቱን ወደሚያገኝበት መምህርነት ሥራ ተመልሷል።

በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ስድስት ዓመት ሙሉ አባትህ ኤርትራዊ ነው በሚል ሰበብ ያለቀበሌ መታወቂያ ቆይቷል። በወቅቱ እናታቸው ወይም አባታቸው ኤርትራዊ ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለሥልጣን ሆነው እያስተዳደሩ ባሉበት አገር፣ እሱ ኢትዮጵያዊነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ መታወቂያ መከልከሉ እጅጉን አበሳጭቶታል፤ አሳዝኖታል። ባንክ ቤት የራሱን ገንዘብ ለማውጣት ሄዶ “የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ ከሌለህ አትስተናገድም” የተባለበትን ቀን አሁን ድረስ በሀዘን ያስታውሰዋል። በዚሁ ሰበብ ከሚያስተምርበት ት/ቤት እንዲባረር ሲመከርበት እንደነበረና በመጨረሻ እንዳልተባረረ ይናገራል።

የይፍራታ ተወላጅ የሆኑት ባለቤቱ ወይዘሮ ጽዱ ጌታቸው የቤት እመቤት ሲሆኑ የድርሰት ሥራውን ሲሠራ ቋንቋውን ከማስተካከል በተጨማሪ የማጀቴ አካባቢ ቃላት ሲጠፋው በማስታወስ አስተዋጽኦ አድርገዋል። የአንድ ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት እንዲሆንም አድርገውታል። ባለቤቱ የቤተሰብ ጉዳይን ጠቅልለው ስለሚሠሩ እሱ ጊዜ ኖሮት መሥራት የሚፈልገውን እንዲሠራ ጊዜ አግኝቷል።

መምህርና ደራሲ ኃይለመለኮት ለፍትሕ የሚቆምን ሰው ያደንቃል። ሰው አደርገዋለሁ ባለው ጉዳይ አሸናፊ መሆኑ አይቀርም፤ዋናው ተስፋ አለመቁረጥና አለመንበርከክ ነው። ተስፋ ላለመቁረጥና ላለመንበርከክ የሚያግዘው ደግሞ ማንበብና የተግባር ሰው መሆን ነው የሚል ፍልስፍና የሚከተል መሆኑን የሚናገረው እንግዳችን የአርትኦት ሥራ አስተማሪዎቼ አረፍአይኔ ሃጎስ እና ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ናቸው ይላል። የሰማንያ ሰዎችን መጽሐፍ በነጻም በክፍያም የአርትኦት ሥራ ሠርቷል። በአርትኦት ሥራ የሰጠውን አገልግሎት በጣም እንደሚደሰትበትና ብዙ ወጣቶችን እንዳስተማረበትና እንደረዳበት በኩራት ይናገራል። በዚህም ምክንያት የራሱን የድርሰት ሥራ አጠናቆ ለማውጣት እንዳዘገየበት ይጠቅሳል። ለጸሐፊዎች ምክር ሲሰጥ፤ ሀሳባችሁን ለማውረድ ፍጠኑ፣ ያለማቋረጥ ጻፉ፣ ደጋግማችሁ አንብቡና አስተካክሉ፣ የጽሞና ጊዜ እየሰጣችሁ አርሙ፣ ሥራችሁ እንዲያድግና እንዲስፋፋ ችሎታችሁን በንባብ አበልጽጉ፣ ያነበበ ሰው ብዙ የእውቀት ምንጮች ይኖሩታልና አንብቡ- አንብቡ፣ ከሰዎች ጋር በቅንነት ስለሥራችሁ ተወያዩ፣ በአጭር ጊዜ ጥሩ ደራሲ መሆን አይቻልምና አትቸኩሉ ይላል።

ስሜነህ ደስታ

ዘመን መጽሔት ሐምሌ 2014 ዓ. ም

ስለ ኃይለመለኮት መዋዕል ተስፋዬ ገብረአብ በአንድ መጻሕፉ እንዳሰፈረው፣ "... [ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል] ግማሽ መንዜ - ግማሽ ኤርትራዊ ነው። ከሁለቱም ወገን አክስቶቹ እሱ ቤት ሲገናኙ እሱ አስተርጓሚ ሆኖ ያዋያቸዋል። ማርያም ሰላም ታመጣ ዘንድ የሚለምኑ ደጋግ አክስቶች ነበሩት። የኢትዮ - ኤርትራ ጦርነት እየተካሄደ እነሱ ቡና እየጠጡ አምላክን ይለማመኑ ነበር።"__ዳኛቸው ወርቁ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሌሎች ጋር ያልተቀላቀለ ንፁህ ብሔር የለም ይላል፡፡ የአባቱ የአቶ ወርቁ በዛብህ እናት የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ እንደሆኑም ራሱ ዳኛቸው ለዶክተር ሬይዱልፍ ሞልቬር ተናግሯል፡፡ ስለ ራሱ ብሔር በዶክተር ሞልቬር ተጠይቆ የሰጠው መልስም፤ “no tribal feelings”፡፡

ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ፣ ባለበቱ ወ ሮ ፅዱ ጌታቸው ፣ ልጆቹ ዶ/ር ማህደረ ኃይለመለኮት እና  ዮናታን ኃይለመለኮት

‹‹አእምሮን በተገደበ ነፃነት ውስጥ ማንቀሳቀስ ትርፉ ባርነት ነው››

‹‹ንጉን›› እንዲሁም ‹‹የወዲያነሽ›› በተሰኙ መጻሕፍቱ ይታወቃል፤ ኃይለመለኮት መዋዕል። እርሱ ዋናው ሥራዬ መምህርነት ነው፤ ደስታና ክብር የሚሰማኝ በመምህርነቴ ስጠራ ነው ቢልም፤ እነዚህ መጻሕፈቱ ዘመን ተሸጋሪ ደራሲ አሰኝተውታል። ሰሜን ሸዋ ማጀቴ ከተማ 1943 ነው ትውልዱ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ወሎ ኮምቦልቻ የተማረ ሲሆን፣ ከ5ኛ ክፍል እስከ 8ኛ አስመራ አክሪያ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ኹለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ተምሯል።

1962 ጀምሮ በመምህርነት ማገልገል የጀመረው ኃይለመለኮት፣ ከ1969 ጀምሮ እስከ 1972 በእስር ቆይቷል። ‹‹በእኔ እምነት ዋናው ሥራዬ መምህርነት ነው።›› የሚለው ኃይለመለኮት፣ ከ43 ዓመታት በላይ በመምህርነት ሠርቷል። አሁንም ላይ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሆን በተለያዩ ክልል ከተሞችና ትምህርት ቤቶች እየተንቀሳቀሰ የንባብን ባህል በተመለከተ እይታውን፣ ልምዱንና እውቀቱ ያካፍላል።

የንባብን ነገር በሚመለከት እንዲሁም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ስምምነትን ተከትሎ ከ50 ዓመት በኋላ ኤርትራ የሔደበትን ምክንያትና ሌሎችም ጉዳዮችን በማንሳት ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል? ከሆነስ ምን ዓይነት ሙላት ነው?

ይህ አባባል መቼ እንደመጣ ዓመቱን በትክክል ባላስታውስም 10 ዓመት ገደማ ይሆነዋል። በትክክል እነማን ጀመሩት የሚለውንም ለይቼ ባላውቅም፣ ወደ ሕዝብ ያመጡት እነ በፍቃዱ አባይ (ጋዜጠኛ- ብራና የራድዮን ፕሮግራም አዘጋጅ) እና ባልደረቦቹ ይመስሉኛል። እነሱ የንባብ ፕሮግራም፣ የመጻሕፍት ግምገማ ያዘጋጃሉ፣ መጽሐፍት እንዲነበቡና ደራስያን እንዲበረታቱም ጥረት ያደርጋሉ። ጥረታቸውን የሚያግዙ ልዩ ልዩ ድርጅቶች በዚህ ተሳታፊ ናቸው።

አባባሉ ግን ከእኛው አገር የበቀለ አይደለም። ሆኖም ይህ አባባል በቀጥታ መተርጎም የለበትም። ይዘቱ ነው መተንተን ያለበት። ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል ስንል የአሠራር ባህርያትን፣ የአገላለጽ መንገድን ነው የሚመለከተው። ሙሉ ሰው ሲባል ምንም ያልጎደለው፣ እንከን የሌለው ወይም ስህተት የማይገኝበት ማለት አይደለም። ሰው እያነበበና እየተመራመረ በሔደ ቁጥር እየተሻሻለ ይሔዳል። ከትላንት ዛሬ ይሻላል የሚለውን ማመላከቻ ነው።

በዚህ ዓለም ላይ ሙሉና ፍጹም ሰው የለም/ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም የምንኖረው አንዳችን በሌላችን እውቀት እየተጋገዝን እየተሞላላን ነው። ግንበኛው፣ አናጢው፣ ጸሐፊው፣ የፖለቲካ መሪ፣ ገበሬው፣ በሙሉ የተለያየ እውቀትና ችሎታ ይዘው ይመጣሉ። ሌሎችም ሙያዎች አንድ ላይ ተጠራቅመው አንድ ኅብረተሰብ የሚፈልገውን ሊያሟሉ ይችላሉ ነው።

አንድ ሰው በእድሜ ዘመኑ ኹለት ወይም ሦስት ሺሕ መጽሐፍ ቢያነብ በሁሉ ነገር የተሟላ ይሆናል ማለት አይደለም። እውቀቶች ግን ይኖሩታል። በእያንዳንዱ ጉዳይ የተወሰነ እውቀት ይይዛል። እናም አባባሉን አስፋፍተንና አብራርተን ስንመለከተው የተሻለ ሰው ለመሆን የምንታገዝበት መንገድ ለማለት ነው።

እውቀት የሚገነባ ሕንጻ ነው። ሕንጻው እያደገ ይሔዳል። የእውቀት መጨረሻ ገደብ የለም፤ ቢኖር ኖሮ የሰው ልጅ ሥልጣኔ አንድ ቦታ ላይ ይቆም ነበር። እየጨመረበት ስለሚሔድ ነው ያልቆመው፤ ሙሉ ስላልሆነ።

ማንበብ የተለያዩ ሰዎችን ሐሳብ በራስ ላይ መጫን ነው፤ በራስ ማሰብን ይገታል የሚሉ ሰዎች አሉ። ትስማማለህ?

እኔ በዚህ አላምንም። እንደውም የራስን አስተሳሰብና አስተያየት፣ ግንዛቤ እያሰፋ የሚሔድው ከሌሎች ሲጨመር ነው። እኔ የራሴን ሻማ ልለኩስ እችላለሁ። ያቺን ሻማ ይዤ ብቀመጥ በቂ ብርሃን አትሰጠኝም። በአንድ አካባቢ የተሰበሰብን ሰዎች አንድ ላይ ሆነን ብዙ ሻማ ስናበራ የበለጠ ብርሃን እናገኛለን። የራስ ሐሳብ የሚያጠብ ሳይሆን እንደውም ሐሳብን እንዲያሰፋ ያደርጋል፤ ማንበብ።

ሐሳብ ከፍ እያለ የሚሔደው በተጨማሪ ጉልበት ነው። እንዲህ የሚል ሰው ሐሳቡ ሊያድግና ሊሰፋ የሚችለው የሌሎችን ሐሳብ ወደ ውስጡ ባስገባ ቁጥር ነው። ይሔኔ ይተቻቸዋል፣ ይነቅፋቸዋል፣ የተሳሳቱት ካለ ሐሳባቸውን ያርማቸዋል። ይህን የሚያደርገው ስላነበበ ነው። አልፎም እነሱ ካዩበት ርቀት አልፎ ሊመጥቅ ይችላል።

ማንበብ ውስጥሽ የነበረውን ስህተት ለማረም ይጠቅማል። የመጥፎ ሐሳብ አረም የሚነቀለው ከሌሎች በሚወሰድ ልምድ፣ በሚመጣ እውቀትና ተሞክሮ ነው። ትምህርት ቤት የምንገባውምኮ ያለን እውቀት አነስተኛ ስለሆነ የሌሎችን ለመጨመር ነው። እንቢ ካለማ አንደኛ ክፍል ይቀራል አይጨምርም ማለት ነው።

ማንበብ በራስ ሐሳብ መወሰን ሳይሆን ተጨማሪ ሐሳብ እንዲፈልቅ መንገድ መጥረግ ነው። እውቀት በአንድ ሰው አይገነባም። እውቀት የኅብረተሰብና የአገር ሐብት ነው። ያንን በማስፋፋት ነው ወደ ትልቅነት የሚመጣው። አለበለዚያ ትምህርት ቤትና ተጨማሪ እውቀት አያስፈልገንም፤ ሁሉም እንደጋሪ የየራሱን ብቻ እያየ የሚሔድ ነው የሚሆነው።

አእምሮአችንን በተገደበ ነጻነት ውስጥ ማንቀሳቀስ የለብንም። ያ ከሆነ ትርፉ ባርነትና ተገዢነት ነው። ከሌሎች እውቀት መሸመትና እየመረጡ ሥራ ላይ መዋልና ማሳደግ ያስፈልጋል። እንጂ የራስን ሐሳብ አይገድብም። ዓለም እዚህ የደረሰችው እንደዛ ባለ አስተሳሰብ ሳይሆን ሌሎች የጻፉትን በማንበብ የእኔ ያድጋል በማለት ነው። እናም ይህ የሚያሳድግ ሐሳብ አይደለም።

የንባብ ባህል ምን ማለት ነው? በአገራችንስ ይህ ባህል አለ?

ባህል ሰዎች በተደጋጋሚ የሚያደርጉት ጠቃሚ ድርጊት ነው። ከባህል የሚታረም አለ። ጥርት ብሎ የሚወጣ ነገር አይደለም። ያም ደረጃ በደረጃ ይስተካከላል፣ ይታረማል። ዘመኑን እያየ ደግሞ ኅብረተሰቡ የሚቀበለውና የሚቀጥል ባህል አለ፤ ከኅብረሰተቡ እድገትና የአእምሮ ስፋት ጋር የማይሔድ ባህል ሲኖር ደግሞ ኅብረተሰቡ ራሱ ቀስ እያለ ያገለዋል። አንዳንዴ ሕግ ያስፈልገዋል።

ባህል የመጨዋወት፣ የአበላል፣ የአጠጣጥ፣ የሽምግልና፤ ጸብን የማስወገድ፣ የመቻቻል ባህል ወዘተ ሊሆን ይችላል። በጥቅሉ ባህል ሰፊ ትርጉም አለው።

የንባብ ባህል ነበረን ወይ ለሚለው አልነበረንም፤ ወይም በጣም ውስን ነው። የንባብ ባህል የነበራቸው በሐይማኖት አካባቢ የነበሩት ናቸው። በእስልምናም ይሁን በክርስትና ወይም በሌላ የሚገኙ የሐይማኖት ሰዎች፣ ከሐይማኖት መጻሕፍት ጋር በተያያዘ በየእለቱ ስለሚጽፉ፣ ስለሚያነቡና ስለሚመዘግቡ፣ እነዛ የማንበብ ባህል አላቸው። ሰፊው ሕዝብ ወይም ገበሬው፣ አርሶ አደሩ፣ ላብ አደሩ፣ የቤት እመቤቱ ግን በእለታዊ ሥራ ተጠምዶ ስለሚውል፣ እለታዊ ሥራው ከኑሮው ጋር የተያያዘ ስለሆነ ያንን ለማሟላት ሲል ሲራወጥ ይውላል።

ተማር ብሎ ትምህርት ቤቶች የሚከፍትለት አልነበረም። ይህን ኅብረተሰብ ለመለወጥ ትምህርት ያስፈልጋል። ትምህርት የአንድ ሕዝብ ትልቁ የባህል መገለጫ፣ የእድገቱ ደረጃ ነው። የሚማር ኅብረተሰብ ለማንኛውም የእውቀት ዘርፍ መንገዱ የተከፈተ ነው። ለራስና ለሌሎች ነጻነት ለመቆም የንባብ ባህል አስፈላጊ ነው።

ባለፉት ዘመናት የማንበብ እድላችን እጅግ አነስተኛ እና ጠባብ ነበር። አነበቡ የሚባሉ ደግሞ የማንበብ እድሉ የተሰጣቸው ናቸው። ሠራተኛውና ‹ተራው› ሕዝብ ሳይሆን በድሮ አገላለጽ ሐብት ያላቸውና ንብረት የተረፋቸው ወይም ሐይማኖቱ አካባቢ ያሉ ሰዎች ነበሩ እድሉ የነበራቸው። 

ስለዚህ ባህሉ አለን ወይ ለማለት ትምህርት ነበር ወይ የሚለውን ማንሳት ያስፈልጋል። ትምህርት ተስፋፍቶ አልነበረም። ስለዚህ የንባብ ባህላችን እጅግ በጣም ደካማ ነው። በእርግጠኝነት ማለት የምችለውም የማንበብ ባህል አልነበረንም። በቅርብ ቀን አንድ ደራሲ እንደገለጸው፤ ከአፍሪካ በአንደኛ ደረጃ የሚያነቡት ግብጻውያን ናቸው። መጨረሻ ተርታ ካሉት አገራት ነው እኛ ያለነው።

በዓመት 20/30 ልብወለድ የሚነበብበት አገር አለ፤ በግለሰብ። ከዛ እየቀነሰ ወደ አፍሪካ አንድና ኹለት፣ ሦስትና አራት መጽሐፍ ይሆናል። እኛ አገር ግን በዓመት አንድ አንቀጽ ወይም አንድ አረፍተ ነገር ነው የሚደርሰን። ይህ የመጨረሻ አሳፋሪ ነው። በንባብ ደረጃ የዘቀጥን መሆኑን ያሳያል። ለዚህ ማስረጃው አሁን በአገራችን መጻሕፍት ይታተማሉ። ብዙ ታተመ ሲባል ሦስት ወይም አምስት ሺሕ ነው። የአዲስ አበባ ነዋሪ 6 ሚሊዮን ደርሷል ይባላል፤ በግምት። ሦስት ሺሕ መጻሕፍት እኮ በአንድ ቀን ማለቅ ያለበት ነው።

ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ ከግማሽ በላዩ አያነብም ብንል፤ ከቀረው ግማሽ ገሚሱ ማንበብ ባይፈልግ እንኳ ቢያንስ ኹለት ሚሊዮን ተኩሉ ወይም 1 ሚሊዮን አንባቢ እንዴት እናጣለን? ስለዚህ የማንበብ ባህላችን የመጨረሻው የወረደ ቦታ ላይ የደረሰ እንደሆነ በዚህ መረዳት ይቻላል። ሦስት ሺሕ መጻሕፍት አሳትሞ አንድ ዓመትና ስድስት ወር የሚቆይበት ጊዜም አለ። 

አምስት ሺሕ በአሁኑ ጊዜ በጣም ትልቅ ቁጥር ነው። በደርግ ዘመን እነ ሰመመን፣ ዶሰኛው፣ የወዲያነሽ ሲታተሙ ህትመት ብዛቱ 15 እና 20 ሺሕ ነበር። ስድስት ወር ቆይቶም ኩራዝ በድጋሚ ያሳትማል። በጣም የታወቀ ደራሲና ጥሩ መጽሐፍ ከተባለና መጽሐፉ ተፈላጊ ከሆነ እስከ 80/90 ሺሕ ተሸጧል። አንባቢ ኅብረተሰብ እየፈጠርን ነበር።

አሁን በዛ ደረጃ አይደለም፤ ተሻሚ መጥቷል። ሕዝቡ ባለው የኑሮ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታዎች መለዋወጥ የተነሳ ከመጻሕፍት ንባብ ይልቅ ወደ ጋዜጣ ንባብ ሔዷል። ከዛ ቀጥሎ ደግሞ በእጁ ላይ ያሉ ሞባይሎች ከዓለም ጋር የሚያገናኙ መገናኛ ብዙኀን ሆነዋል። ስለዚህ በኢንተርኔት ጠቃሚም ይሁን አይሁን ወይም ሐሰተኛ ዜና ያያል። ቀጥታ ከመረጃው ጋር ይገናኛል። ቀጥታ የሚያነበውም ክፉውን ነው፤ ከሕይወቱ ጋር ያያይዝና ከመከራ ሚዛን ውስጥ ይገባል።

ይህን ትውልድ ግን ለምን አላነበበም ብለን ለመውቀስ የሚያስችለን የተረጋጋ ሁኔታ የለም። ለማንበብ ሰላምና እርጋታ ያስፈልጋል፤ ለማንበብ የኢኮኖሚ ወጪ መሸፈኛም ያስፈልጋል። አንድ ምግብ በሰባ ሰማንያ ብር የሚበላ ወጣት፣ በዛ ብር መጽሐፍ ግዛ ቢባል የነገ ምሳውስ? ንባብ በአንድ በኩል ከኢኮኖሚና ከሕይወት ጋር ይያያዛል። በብዙ ነገር ተጨንቆና ነገን በደቀቀና ቆሞ በማይሔድ ተስፋ እየተመለከቱ ለንባብ የሚጋብዝ ነገር የለም።

አንድ ጋዜጠኛ ከደሞዙ ግማሹን ለኪራይ ሰጥቶ የቀረውን ለምግብና ትራንስፖርት እንዲሁም ማኅበራዊ ግንኙነት ዙሪያ ካወጣ በኋላ እጁን አጣምሮ ይቀመጣል። ስለኑሮው እንጂ ምርጥ መጽሐፍ ወጣ ቢባል የንባብ ሱስ ከሌለበት በቀር ገዝቶ ለማንበብ እድሉ ጠባብ ነው።

ግን ብዙዎቹ ወጣቶች ያነባሉ። ለዛ ነው ምርጥ መጽሐፍ እየወጣ እያየን ያለነው። በተለያየ ሙያ ውስጥ ያሉ ሰዎችም ጽፈው አስነብበውናል። ለአእምሮ የሚያስደንቁ ልጆችን በየመድረኩ እያየን ነው። ግን የማንበብ ባህላችን ሊሠራበት ይገባል። መንግሥት ለተለያዩ ጉዳዮች ዓመታዊ በጀቶች እንደሚመድበው ሁሉ፣ ለአብያተ መጻሕፍት የሚያገለግል ዓመታዊ በጀት ያስፈልጋል።

አሁን ላይ ለማረሚያ ቤቶች መጽሐፍት እየተሰጠ ነው፤ ይሄ ድንቅ ነገር ነው። ትልቁ ስጦታም ነው። መንግሥትም በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ወመዘክር በኩል ለተለያዩ ማረሚያ ቤቶች መጻሕፍት እየሰጠ ነው። መንገድና ሌላው መሠረተ ልማት ላይ እንደሚሠራው፣ አብያተ መጻሕፍት ተከፈቱ ማለት የኅብረተሰቡ እድገተ ማስፋፋት ስለሆነ ሊበረታታ የሚገባው ነገር ነው።

በመጽሐፍት ሥራዎቻችን የቋንቋ ብዝኀነት በበቂ ሁኔታ ታይቷል?

በቂ አይደለም። አማርኛ ባለፉት በርካታ ዓመታት የመንግሥት መጠቀሚያ ቋንቋ ከመሆኑ የተነሳ በማኅበራዊ ኑሮም እየሰፋ መጥቷል። ይህ በመሆኑ አማርኛ በኢትዮጵያ የትኛውም ቦታ መነጋገሪያ መሆን ችሏል። ኹለትና ሦስት ብናደርገውም የበለጠ ጥሩ ነው። ቋንቋን ማስፋፋት ግንኙነትን ማዳበር ነው። የአገራችን ሁሉም ቋንቋዎች እንዲያድጉ፣ እንዲበለጽጉና እንዲስፋፋ ማድረግ በእኔና በሌሎች ሰዎች መካከል የሚገኝን ግንኙነት የበለጠ ማሻሻል፣ እድገትን፣ ልማትን ፍቅርን መጨመር ነው።

ከመንግሥት ብቻ ሳይጠበቅ ኅብረተሰቡም ቋንቋውን ለማሳደግ መጣር አለበት። ግንኙነታችን የሚጠነክው አንዳችን የሌላችንን ቋንቋ ስናውቅ ነው፤ ለማወቅ ደግሞ ሁላችንም ልባችን ክፍት መሆን አለበት። የማወቂያ መንገዱም ሊከፈት ይገባል። እኔ አማርኛ እንዲሁም ትግረኛ አሳምሬ እናገራለሁ። ነገ የኦሮምኛ ቋንቋ ማስተማርያ ቢከፈት ብማር ደስ ይለኛል። ብዙ ጓደኞች አሉኝ፣ እነርሱ ቤት ገጠር ስሔድ በኦሮምኛ ቋንቋ ብግባባ ደስ ይለኛል።

በተቻለ መጠን ሁላችንም በምንግባባበት ቋንቋ መነጋገር አለብን። ይሄ ነው ሊያዋህደን የሚችለው፤ ቂቤና ሽሮ ሲገናኙ ይጥማሉ። እንዲሁ ሆነን ነው አንድነታችን እና ኅብረታችን ሊያድግ የሚችለው። እንጂ የአንተን ቋንቋ አልሰማም፣ አልማርም ብሎ አይደለም። በቋንቋ ምክንያት መጋጨት የለብንም። ሁሉም የእኛ ናቸው።

መጻሕፍት ግን የሉም ማለት ይቻላል፤ በጣም አነስተኛ ነው። ይህ ትልቅ ሥራ ይጠይቃል። በየብሔረሰቡ የሚገኙ የተማሩ ሰዎች የተለያዩ መጻሕፍትን በየሙያ ዘርፋቸው ሊጽፉ ይገባል። ሲጻፍበት ነው ቋንቋ የሚያድገው እንጂ በግድ አይደለም። ቋንቋዎቻችን ሊያድጉ የሚችሉት በተለያ የትምህርት ዘርፍ የተማሩ የብሔሩ ሰዎች ሲጽፉባቸው ነው። ቴአትርን፣ ሙዚቃውን የግብርና እና የጤናውን የመሳሰለውን ከተራ ጉዳይ አንስቶ መጻፍ ያስፈልጋል።

መጀመሪያ እንዳልኩት ትምህርት መሠረት ነው። ሰው ከተማረ ነው ወደ ማንበብ የሚመጣው። በትምህርቱ ደረጃ በደረጃ መጽሐፍ ማቅረብ ያስፈልጋል። እኛም ጋር ከአነስተኛው ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ድረስ እየጨመረ በሚሔድ ደረጃ ሊዘጋጅ ይገባል። ይህን መሥራት የሚችሉት የተማሩ ቋንቋውን የሚያውቁት ናቸው። የመንግሥትንም ከፍተኛ ድርሻ ይጠይቃል። የወረቀት ዋጋን ዝቅ በማድረግ፣ ቀረጥን በማሳነስ። እንጂ አንድ ጸሐፊ ወይም ደራሲ ሠርቶ ማሳተሚያ ካጣ የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ ይቀራል።

ሁሉም ቋንቋዎች እንዲያድጉ የተማሩ ሰዎች ሊጽፉ ይገባል፤ የተጻፉት እንዲደርሱ ደግሞ የህትመት ዋጋው ሊታሰብበት ያስፈልጋል።

በሥም የሚታወቁ ደራሲያን ሥራዎች ምንም ሆነ ምን በብዛት ይነበባሉ። አዳዲስ ጸሐፍያንየሚታዩበት አጋጣሚ ግን ጠባብ ነው። ይህን እንዴት ታየዋለህ?

ነባርና የታወቁ ደራስያን መጻሕፍት ይሸጣል። ይህ በመላው ዓለም ያለ ነው። በየትኛውም ዓለም 5 እና 6 መጻሕፍት ወይም 1 እና 2 ጽፎ ዝነኛ ከሆነ፣ የዛን ሰው ለመግዛት እሽቅድድም አለ። ግሩም ሆቴል አዲስ አበባ የከፈተ ሰው ከአዲስ አበባ ውጪ የሆነ ከተማ ሌላ ሆቴል ቢከፍት፣ በቀጥታ ‹የአዲስ አበባው ሰውዬ› ብሎ ሰው ይሔድለታል። መጀመሪያ ጥሩ አሠራር ስላሳየ ነው።

አንድ መልካም ደራሲም ጥሩ ሥራ ካበረከተ፣ በቋንቋ፣ በታሪክ አወቃቀርና አቀራረብ፣ በድርሰቱ ተዓማኒነት ይወዱታል፤ ቅድሚያም ይሰጡታል። ይሄ ግን አያዋጣም። ምክንያቱም ከሱ በኋላ ያንን ሰው የሚበልጡ ሥራዎች ይወጣሉ። ስለዚህ ኅብረተሰቡ በነባር ሥራዎች ብቻ የተመሠረተ እውቀትና ፍቅር ሊኖረው አይገባም። ከአዳዲሶችም መምጣት አለበት።

የተሻሉና የበለጸጉ የብዕር ሰዎች እንዳሉ ማወቅ አለብን። ይሄ ማበረታታት ብቻ ሳይሆን ተመራምሮና መርጦ ማንበብ ያስፈልጋል ነው። አዲሱ ትውልድ ካለፈው ተምሮ የተሻለ እንደሚፈጥር መገንዘብ ያስፈልጋል። አንዴ ታውቀዋል ብለን በነዛ ሰዎች ላይ አምልኮተ ብዕር ሊኖር አይገባም። የ‹ፍቅር እስከ መቃብሩ› ሐዲስ ዓለማየሁ ሳያሳትሙት የቀረ አንድ መጽሐፍ ተገኘ ቢባል፣ በሥማቸው በወረፋ ነው የሚሸጠው። ወይ የበዓሉ ግርማ ያልታተመ ያስቀመጠው አንድ መጽሐፍ ተገኘ ቢባል ሰዉ በሰልፍ ነው የሚገዛው።

በዘመናችን ያለ ደራሲ ድርሰት ሲያወጣ ራድዮ እና ጋዜጣ፤ ያነበቡ ሰዎችም ሊያስተዋውቁለት ይገባል። በዚህ መልክ ነው መሆን ያለበት። በሥም ብቻ ለዘለዓለም መኖር አይቻልም። ሥም እየታደሰ መሔድ አለበት። አዳዲስ ምርጥ ተነበው የተመሰከረላቸው የመጻሕፍት ሥራዎችንም ማየት ያስፈልጋል።

ስለዚህ የድሮዎቹን ብቻ እያደነቁ አዲሶቹን ገለል ማድረግ አዳዲስ ብርሃን እንዳይፈነጥቅ ማድረግ ነው። አዲስ ብርሃን ሲመጣ እድል መስጠት ያስፈልጋል። ይህም የሚሰጠው በሥራው ነወ። እስከዛሬ ድረስ በተለያዩ የዓለም አገራት በሥራቸው የተደነቁና ምንጊዜም ቢሆን ሥራዎቻቸው ቸል የማይባል ሥራ የሠሩ ደራስያን አሉ። መምረጥ መብት ነው። ስንመርጥ ግን አዳዲሶቹንም ማየት አለብን።

በአሁን ሰዓት ብዙ ደራስያን አሉ፤ በተቻለን መጠን ያተሙትን መጽሐፍ መግዛት፣ አይተንም ማበረታታት አለብን። ሒስ ደግሞ እንዲበረቱ አስፈላጊ ነው። አጥፊ ሳይሆን ገንቢ ሒስ መስጠት፣ ትክክለኛውን እርማት መስጠት። አንድ አትክልት አየተኮተኮተ ሲሔድ እያደገ ይሔዳል። ደራሲም በትክክል በእውቀት ከታረመ እያደገ እየበለጸገ ይሔዳል።

ኃይለመለኮት ከ‹ወዲያነሽ› እና ከ‹ጉንጉን› በኋላ በስፋት ለሕዝብ የደረሰ ሥራ አላቀረበምና የት ጠፋእየተባለ ነው። ጋሽ ኃይለመለኮት የት ጠፋ?

ባለፉት ዓመታት በብዛት ስሠራ የነበረው በንባብ ባገኘሁት፣ ባለኝ አቅምና እውቀት ወጣቶችን ማገዝ ነው። በተለያዩ በተለይም በአጫጭር ታሪኮችና ልብወለዶች አንዳንድ ጥያቄ ሲያቀርቡ ማማከርና ማገዝ ላይ ነበርኩ። የአርትዖተ ሥራ ስሠራም ነበር። ባልመዘግባቸውም በጥቂቱ ከማስታውሰው ወደ 64 መጻሕፍት አርትዖት ሠርቻለሁ። የራሴንም በፊት ተሠርተው የነበሩ ሥራዎች አርትዖት እየሠራሁ ነው፤ በወጣትነት እድሜ የጻፍኳቸውንም። አሁንም እየጻፍኩ እየሠራሁ ነው። በሕይወት ትግል ያለውን ውጣ ውረድ አልፎ አሁን እየደረሰ ነው። እና አለሁ፣ እየሠራሁ ነው።

ከበርካታ ዓመታት በኋላ ኤርትራ ሔደሃል። ቆይታህ እንዴትና ስለምን ነበር?

በሕይወቴ ብዙ የደስታ ጊዜ አሳልፌአለሁ። የመከራ ጊዜም እንደዛው። መከራው ብዙም የሚያስመርር አይደለም። አብዛኛው የሕይወቴ ክፍል በደስታ የተሞላ ነው። በሥራዬ፣ በትዳሬ፣ በልጆቼ፣ ከሰዎች ባለኝ ግንኙነት በጣም ደስተኛ ነኝ። አንዴ የታሰርኩበት ጊዜ ነው የከፋው። እሱም በዘመኑ በማንኛውም ኢትዮጵያዊ ላይ የደረሰ እንጂ ለብቻዬ የመጣ መከራ አይደለም።

በወቅቱ በመንግሥት በኩል የነበሩትም መከራ ነበረባቸው፣ በእኛም ተቃዋሚ በነበርነው መከራ ነበረብን። እና የሁላችን እንጂ በእኔ ለይቶ የመጣ አልነበረም። ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ የኑሮ ውጣ ውረድና መሰናክል እንጂ የሚያስመርር ችግር ገጥሞኝ አያውቅም። በኑሮ ትግል ተሸንፌ አላውቅም፤ እፍጨረጨራለሁ ድል አደርጋለሁ።

በሕይወቴ ደስ ከተሰኘሁበት ቀናት መካከል ግን አንዱ ልክ የዛሬ ዓመት ነው፤ ኤርትራ አስመራ ነበርኩ። በ1962 ከኤርትራ አንዴ ከወጣሁና እዚህ [ኢትዮጵያ] ከገባሁ ወዲህ አልተመለስኩም። በመጀመሪያዎቹ ዓመታት አባቴ ጋር ምን ይዤ እሔዳለሁ ስል ቆየሁ፤ ከዛ አብዩቱ መጣ። ያኔ ደግሞ ለመሔድ ለመምጣት የሚቻልበት ጊዜ አልነበረም። በደርግ 17 ዓመታት መሔድ ይቻል ነበር፤ ነገር ግን ዛሬ ነገ ስል በዛ አለፈ። ከ1983 በኋላም በተመሳሳይ ነገ ከነገ ወዲያ ስል ቆየሁና ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲነሳ ጨርሶ ተቋረጠ። ከሃምሳ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ አንዴ ከመጣሁ ወደ ኤርትራ አልተመለክስኩም።

አባቴን ሳላገኘው እዚህ እያለሁ ነው የሞተው፤ በመሃል አንድ ጊዜ መጥቶ ተያይተናል እንጂ። የምወዳቸው ሦስት እህቶቼ ሞተው ነው የቆዩኝ፣ በጣም የምወደው ወንድሜ ‹ጉንጉን› መጽሐፍ ላይ መታሰቢያ ያደረኩለት አፈወርቅ የሚባለውና ብዙዎቹን በአባቴ ወገን ያሉትን በሕይወት አላገኘኋቸውም። ያው ትውልድ ይቀጥላል፤ ‹‹ሲፈጭ ሲቢካ ሲሞት ሲተካ›› እንዲሉ የአጎቶቼን ልጆች እና የእህት ወንድሞቼን ልጆች አግኝቻለሀ። ከእህት ወንድሞቼ ታላቆቼን ኹለት አግኝቻለሁ።

ኅዳር 20 አስመራ ኤርፖርት ስደርስ የተቀበሉኝ የእህት የወንድም፣ የአጎት የአክስት ልጆች አበባ ይዘው ነው፤ ሠላሳ ይጠጋሉ። እኔ ወደዛ ከመሔዴ በፊት ድንበሩ እንደተከፈተ ታላቅ ወንድሜ ከባለቤቱ ጋር መጥቶ ነበር። እሱ በመጣ በኹለተኛ ሳምንት ነው የሔድኩት። እና በቴሌቭዥን ያዩኝ ስለነበር ገና ስመጣ ‹‹አያይ መጣ!›› አሉ፤ ጋሼ ማለት ነው። በደስታ አለቀስኩ። ልቆጣጠረው አልቻልኩም። ተቃቅፈን ተላቅስን፤ የደስታ እንባ ነው። 

ያን ጊዜ ለመግለጽ ያስቸግራል። ለቅሶ የጀመርኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስመራ ሔዱ መባሉን ልጄ ነግሮኝ በቴሌቭዥን ተከፍቶ ስመለከት ነው። ልጄ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አንድ ላይ ተሰቅሎ አሳየኝ። ‹‹ዐቢይ አስመራ ሔዷል›› አለኝ። በእለቱ የነበረውን ስርዓት ስመለከት አንድ ጊዜ ብቻ ነው ከወንበሬ የተነሳሁት፤ እዛው ቲቪ ላይ ተተክዬ እየተደጋገመ ሲታይ እኔም ሳይ ነበር። ይህ ሲሆን ግን አለቅስ ነበር። ይህ ቀን በሕይወቴ ይመጣል ብዬ አልጠበኩም።

በሔድኩኝ በማግስቱ አስመራ ማርያም ጽዮን ነበር። አስመራን እንደ እጄ መዳፍ ነው የማውቀው። ተሠርቶ ያለቀ ከተማ ስለነበር፤ ታክሲ ተሳፍሬ መሃል ከተማ ኩምቡሽታቶ ውሰደኝ አልኩት። ሔድኩኝ፤ ቅድስት ማርያምን ተሳለምኩም፤ ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ የተማርኩበት ‹አክሪያ› የተባለ ትምህርት ቤት ሔድኩ። ክፍሎቹ እንዳሉ አሉ።

ግን አይቼ አልጠገብኩም። ጎዳናውን፣ ሰዉንም፣ በአካባቢው የነበረውን ትዕይንት በሙሉ አልጠገብኩም። ቀጥሎ የአባቴ አገር ከአስመራ 8 እና 9 ኪሎሜትር በምዕራብ ነው። እዛ ሔጄ ታላቅ እህቴንና ዘመዶቼን አገኘሁ። እስከ እኩለ ሌሊት የልጅነት ዘመናችንን ከቤተሰብ ጋር ስንጫወት፣ ሳናወራ ሰነበትኩ። 26 ቀን ገደማ ቆይቼ ነው የተመለስኩት።

በልጅነት ከነበሩ ጓደኞቼ መካከል ግን ኹለቱን ብቻ ነው ያገኘሁት። የተቀሩት በሙሉ በጦርነት፣ ግማሾቹ ታጋይ ሆነው በዛው ሞተዋል፤ አንዳንዶቹ የት እንዳሉ አድርሻቸውን ማወቅ አልቻልኩም። አስመራን ከዳር እስከ ዳር አዳረስኩት። በጉብኝቴ ረክቻለሁ፤ ሆኖም ገና ማየት እፈልግ ነበር። በጣም ደስ ካለኝና ካየሁት ነገር አንዱ፣ እንጨትና በለስ የምንለቅምበት ነበር። ከአስመራ ወደ ምጽዋ መንገድ አካባቢ ከጓደኞቼ ጋር ነበር የምንሔደው። አሁን በምሔድበት ጊዜ ግን አንድም ጓደኛ በዛ ደረጃ ባለማግኘቴ ዐስሩን ኪሎሜትር በትዝታ እያለቀስኩ ነው የሔድኩት።

በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው ሰላም ለእኔ ከምንም ነገር በላይ ትልቁ ደስታዬ ነው። የእነዚህ ሕዝቦች አንድነትና ፍቅር ለዘለዓለም ጸንቶ እንዲኖር ምኞቴ ነው። ከዛም ባለፈ ሁኔታ ቢፈጸም። እናም የኹለቱ ሕዝቦች አንድነት በመመለሱ፣ የጦርነት ስጋት በመቀነሱ፣ አሁን ደግሞ እያደር በፖለቲካና በዲፕሎማሲ መንገድ ለጊዜው የተዘጋው ድንበር ሕግን ስርዓት ተበጅቶለት፤ የኤርትራ ሕዝብ እንደልቡ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ኤርትራ እንደ ልቡ እንዲሔድ፤ አልፎ ተርፎ እዛም እዚም እንዲሠራ የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሮ አይቼ ብሞት እላለሁ፤ እንደሚፈጠር ደግሞ ተስፋ ነኝ።

ያ ሕዝብ እና ይሄ ሕዝብ ከኩሬ አይደለም ከአንድ ትልቅ የታሪክ ባህር የተቀዳ አንድ ሕዝብ ነው። ወንድማማች ሕዝብ ነው። አንዱ በሌለው የሚቆም ነው። አንዱ በሌላው ላይ ፍጹም ጠመንጃ መምዛዝ የለበትም። ከዚህ በፊት የተደረገውም የስህተት፣ የአስተሳሰብ ድህነት ጦርነት ነው። ከእንግዲህ ስለ ሰላም እና በጋራ ስለመበልጸግ ነው ማሰብ ያለብን።

የጦር ሜዳ ዛሬ የእህልና የልማት አውድማ ማድረግ አለብን። በአንድ ላይ ስንሆን አብረን እንበለጽጋለን፤ ለሕዝቦች ጥቅምና መብት በጋራ እንታገላለን። ስለዚህ የኹለቱ ሕዝቦች ፍቅርና አንድነት ዘለዓለም ይኑር እላለሁ።

የማንን መጽሐፍ ደጋግመህ አንብበሃል?

አነባለሁ፤ ጊዜ ባለኝ ቁጥር ሁሉ ማንበብ ሥራዬ ነው። የወጣቶቹን በብዛት አነባለሁ፤ መምረጥ ያስቸግራል። መጀመሪያ ያነበብኩትን መጽሐፍ መጥቀስ ደስ ይለኛል። ‹‹ገልጠን ብናየው›› የምትባል፣ ቤካን የተባሉ ደራሲ ናቸው የደረሷት። እርሳቸውን ምንጊዜም አልረሳቸውም፤ ወደ ንባብ ያመጣኝ የእርሳቸው መጽሐፍ ነው።

ከዛ በኋላ የድሮዎቹን ደራስያን በሙሉ ከነቋንቋቸው፣ በዘመኑ ከነበረው ታሪክ፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ ትስስር ላይ ተመሥርተው የጻፉትን እወደዋለሁ። ብርሃኑ ዘሪሁንን በጣም እወደዋለሁ፤ በጣም። የ‹አደፍርስ›ን ደራሲ ዳኛቸው ወርቁን በጣም እወደዋለሁ። እና ወዘተ…ብዙ ናቸው። ብዙ ስለሆኑ እገሌ እገሌ የለውም። ለእኔ ሁሉም ደራሲ በየአቅሙ በሚጽፈው መጠን አደንቃለሁ። ምክንያቱም ሁላችን በአቅማችን ነው የምንዘለው። በየአቅሙ የሚጽፍን ወጣትም ሆነ የድሮ ደራሲም ቢሆን፣ አደንቃለሁ።

በ2012 የጻፈ ደራሲ ከዓመታት በኋላ ቢጽፍ ሌላ ሰው ሆኖ ነው የሚገኘው። እነ እንዳለጌታ ከበደ እና እነ ዓለማየሁ ገላጋይ የጀመሩበትን መጽሐፍ እና አሁን ያሉበትን መጽፍ ስታነጻጽሪ፤ ሲጀምሩ እና አሁን አንድ አይደሉም። በእውቀቱ ስዩም ድሮ ሲጽፍበት የነበረውን የግጥም ደረጃ ዛሬ ላይ ሲታይ አንድ አይደለም። ይህን እድገታቸውንና ጥረታቸውን አደንቃለሁ። እነዚህን ለምሳሌ ነው ቅርብ ስለሆኑ የማነሳው። ስለዚህ ሁሉም ደራሲ አቅሙ እየጨመረ እንደሚሔድ ስለማምን፣ ባነበበ ቁጥር የተሻለ እንደሚሆን ስለማውቅ፣ አንባቢዎችም ስለሆኑ አድናቆቴ ለሁሉም ደራስያን፣ ገጣምያን፣ ሰዓልያን እና ሙዚቀኞች ነው። ሙዚቃ ደግሞ እጅግ ነው የምወደው።

ከአዲስ ማለዳ የተወሰደ | እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 01 ቀን 2020 

https://bfaethiopia.wordpress.com/2020/02/24/%E1%8A%A0%E1%8A%A5%E1%88%9D%E1%88%AE%E1%8A%95-%E1%89%A0%E1%89%B0%E1%8C%88%E1%8B%B0%E1%89%A0-%E1%8A%90%E1%8D%83%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8B%8D%E1%88%B5%E1%8C%A5-%E1%88%9B%E1%8A%95/

በአዝናኝና አሳዛኝ ገጠመኞች የተሞላው የደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ጨዋታዎች ከደራሲ ዶ/ር እንዳለገታ ከበደ ጋር ክፍል 1 


 የደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ጨዋታዎች ከደራሲ ዶ/ር እንዳለገታ ከበደ ጋር ክፍል 2