ከደራሲያን ዓምባ

Thursday, September 27, 2012

ከኢትዮጵያ ተረቶች

ንግስት ፉራ 

 

ንግስት ፉራ ስመጥር የሲዳማ ንግስት የነበረች ሲሆን ሴቶችን ሁሉ መልካም ባህሪን ያስተማረችና እስካሁንም ድረስ ተቀባይነት ያላት ሴት ነች፡፡ ንግስቲቱ በጣም ብልህ ነበረች፡፡ በቅድሚያ ሴቶች ለወንዶች ሙሉ ለሙሉ ተገዢ እንዳይሆኑ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሴቶች ለወንዶች ሙሉ ለሙሉ ታዛዥ እንዳይሆኑ ትመክራቸው ነበር፡፡ ከዚያም በላይ ሴቶች አይን አፋር እንዲሆኑና ወንዶች እነርሱ ስለሚያስቡት ነገር ሁልጊዜም ግምታዊ እንጂ ግልፅ እንዳይሆን ታስተምራቸው ነበር፡፡ ሃፍረተ ገላቸውንም በአደባባይ እንዳያሳዩና ሰውነታቸውንም ከጉልበታቸው እስከ ወገባቸው ድረስ እንዲሸፍኑ ትነግራቸው ነበር፡፡ ወንዶች በውበት ስለሚማረኩ ሴቶች ራሳቸውን በደንብ እንዲጠብቁ ታስተምራቸው ነበር፡፡
ነገር ግን ንግስት ፉራ ለወንዶች በጣም መጥፎ ሴት ነበረች፡፡ የማይቻሉ ነገሮችን ሁሉ እንዲሰሩ ታዛቸው ነበር፡፡
“ወደ ወንዙ ሄደህ ውሃ በወንፊት አምጣ፡፡” እያለች ታዝ ነበር፡፡ ወይም በጣም ስስ ከሆነ ሳር ትልልቅ ገንዳዎችን እንዲሰሩ አለያም ከረጃጅም ፀጉሮቿ አንዱን ነቅላ ስድስት ቦታ እንዲሰነጥቁት በማዘዝ ወንዶችን ታሰቃያቸው ነበር፡፡
ከሁሉ በላይ ግን ራሰ በራና አጭር ወንዶችን አጥብቃ ትጠላ ነበር፡፡ ስለዚህ አጫጭር እንዲሁም ራሰ በራ ሰዎችን ሁሉ እንዲገደሉ ታዝ ነበር፡፡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አጫጭርና ራሰ በራ ሰዎች ሲገደሉ አንድ መላጣና አንድ ራሰ በራ ወንዶች ግን ከዚህ ችግር ተርፈው ነበር፡፡ አጭሩ ሰው ረጃጅም ተረከዝ ያሏቸው ጫማዎች በማድረግ ሲተርፍ (ረጅም ተረከዝን የፈጠረው እርሱ ነው) ራሰ በራው ሰው ደግሞ ሰው ሰራሽ ጸጉር (ዊግ) በማድረግ ከሞት ዳነ፡፡ (ዊግን የፈጠረው ሰው እርሱ ነው፡፡)
ታዲያ አጭሩና ራሰ በራው ሰዎች ንግስቲቱን ምን እንደሚያደርጓት ግራ ገብቷቸው ነበር፡፡ ሊገድሏትም አሰቡ፡፡ ነገር ግን ይህን ማድረግ ሁለት ግዙፍ ችግሮች ነበሩት፡፡ የመጀመሪያው በባህሉ መሰረት ሴትን መግደል በፍፁም ነውር ነው፡፡ ሁለኛው ደግሞ እርሷ ንግስት ስለነበረች ይህ የማይሆን በመሆኑ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተቸገሩ፡፡
ከዚያም ጥቂት ካሰቡ በኋላ አንድ ዘዴ ዘየዱ፡፡ አንድ ቀጭኔ ለመያዝ አስበው ቀጭኔዎቹን ሁሉ እያሳደዱ ወደ ረግረጋማው ስፍራ ከነዷቸው በኋላ አንዱ በጭቃው ተይዞ ሲቀር እርሱን ያዙት፡፡
ንግስቲቱንም ጠርተው “አንቺ ታላቅ ንግስት ነሽ፡፡ አንቺ መሳፈር ያለብሽ ተራውን እንስሳ ሳይሆን ረጅምና ሞገስ ያለውን እንስሳ ነው፡፡” አሏት፡፡
ከዚያም በሰአቱ ቀጭኔው እግሩ ጭቃው ውስጥ ዘልቆ ስለነበረ ንግስቲቱ ያለችግር ተሳፈረችው፡፡ ከዚያም ንግስቲቱን ቀጭኔው ላይ አስረዋት ቀጭኔውን ከጭቃው ካወጡ በኋላ ሲያባርሩት ቀጭኔው ሲሮጥ፣ ሲሮጥ፣ ሲሮጥ፣ ንግስቲቱ እየተቆራረጠች መውደቅ ጀመረች፡፡ ጭንቅላቷ ወደ አንድ ቦታ፣ እጆቿ ወደ ሌላ ቦታ፣ አንጀቷ ወደ አንድ አቅጣጫ፣ እግሮቿ ወደ ሌላ ስፍራ ተበጣጥሰው ወደቁ፡፡
በዚህ ምክንያት ነው እስከ ዛሬ ድረስ ሲዳማ ውስጥ ጭንቅላት፣ እግር፣ ሰውነት፣ አንጀት፣ እጅ የሚባሉ የከተማ ስሞች ያሉት፡፡
አኦውን፣ ጭንቅላት፤ ጎዱቦሬ፣ አንጀት፤ ሌላ፣ እግር፤ አንጋ፣ እጅ ማለት ነው፡፡
********************************************************
በአበበ ከበደ የተተረከ
ምንጭ:-- www.ethiopianfolktales.com

 

Monday, September 24, 2012

የመስቀል በዓል / በዓለ መስቀል

 እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሠላም አደረስዎ!
 
 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው ዐበይት እና ንዑሳን በዓላት መካከል አንዱ በዓለ መስቀል ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በወርኃ መስከረም ብቻ በዓለ መስቀልን አራት ጊዜ ታከብራለች፡፡
የመጀመሪያው ምክንያተ ክብረ በዓል፣ በኢትዮጵያ ነግሦ የነበረው ዓፄ ዳዊት ከግብፅ ንጉሥና ሊቃነጳጳሳት የተላከለትን በቅዱስ ሉቃስ እጅ የተሳለችውን ስዕለ ማርያምን፣ በወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ የተሳለውን ኩርዓተ ርእሱን ፣ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳትን እና የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ግማደ መስቀል የግብፅ እና ኢትዮጵያ ድንበር ከነበረችው አስዋን ከተባለችው ቦታ ተረክቧል፡፡
ንጉሡ የያዘውን በረከት ወደኢትዮጵያ ሳያደርስ ስናር በተባለው ቦታ ዐረፈ፡፡ ከጊዜ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ የተባለው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ  ተቀብሎ በደብረ ብርሃን፣ በየረር፣ በመናገሻ እና በልዩ ልዩ ተራራማ ቦታዎች ሲዘዋወር ቆይቶ “ መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አኑር ”  የሚል ራእይ ተገልጦለት ቅዱስ መስቀሉን በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ በግሸን ደብረ ከርቤ አስቀምጦታል ፡፡ መጋቢት ዐሥር ቀን ደብረ ብርሃን ሲገባ ብርሃን ስለወረደና ዐፄ ዳዊት ከግብፃውያን ጳጳሳት እና ንጉሥ እጅ መስቀሉን የተረከቡበትን ቀን በማዘከር የአድባራት እና የገዳማት ሊቃውንት ልብሰ ተክህኖአቸውን ለብሰው የብር መቋሚያ እና ጸናጽል  ይዘው ወደ ነገሥታቱ ሔደው ተቀጸል ጽጌ እያሉ  እያሸበሸቡ ጸሎተ ወንጌል  ያደርሱ ስለነበር መስከረም ዐሥር ቀን የዓፄ መስቀል በዓል ተብሎ ይከበራል፡፡
ሁለተኛው  መስቀሉን በቁፋሮ ያገኘችው ንግሥት እሌኒ ደመራ ያስደመረችበት እና የእጣኑ ጢስ መስቀሉ ወደተቀበረበት ድልብ አከል ተራራ ያመለከተበት ዕለት መስከረም ዐሥራ ስድስት ቀን በመሆኑ የመስቀል ደመራ በዓል በዚሁ ዕለት ይከበራል፡፡
መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ደግሞ ቁፋሮ ያስጀመረችበት ዕለት ሲሆን መጋቢት ዐሥር ቀን መስቀሉን አግኝታለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን አሠርታ፣ መስቀሉን አስገብታ ቅዳሴ ቤቱን ያከበረችበት ዕለት ግን መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ነው፡፡ የመስቀሉ መገኘት ጥንተ በዓሉ መጋቢት ዐሥር ቀን ቢሆንም አባቶቻችን በታወቀና በተረዳ ነገር ዋናው የመስቀል በዓል የሚከበርበት ዕለት መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም መስከረም ሃያ አንድ ቀን በዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በግሸን ደብረ ከርቤ መስቀሉ ያረፈበት ዕለት ስለሆነ
“ በልደቱ ፍስሐ ፤
በጥምቀቱ ንስሐ ፤
በመስቀሉ አብርሃ፤ ” እያልን  በማኅሌት፣ በዝማሬና  በቅዳሴ ለዘለዓለም ስናከብረው እንኖራለን ፡፡
 
 
 
በሰማኸኝ በለው - ደቦት እንስራ  
***********************



እንደምነሽ ዘፈን እንዴት ነሽ ድለቃ
ስክስክ እንክትክቱ የዋንጫ ልቅለቃ
ታሪክ ሆኖ እንዳይቀር እንደነበር እቃ
ያበሻነት ዘሩ እንዲህ ሳያበቃ
ደቦት እንስራ……..…………………...ሆ እያበላ ሆ
ውጣ ኮበሌ…………….………….…..ሆ እያበላ ሆ
ሽንሺንህ ይሸንሸን እያለች አሌ.………..ሆ እያበላ ሆ
ጉብሌ አትፍሪ………………………….ሆ እያበላ ሆ
መጣን ከደጂሽ…………………………ሆ እያበላ ሆ
ቤትና አዝመራውን ጎሮ ገባሽ……………ሆ እያበላ ሆ
ሆ እያበላ ሆሆ ሆ እያበላ ሆሆ
ሆ እያበላ ሆሆ ሆ እያበላ ሆሆ…………..ሆ በል ጃሌ
ቆንጆና ኮበሌ…………………………..ሆ በል ጃሌ
እየተጠራራ………………………….…ሆ በል ጃሌ
የሰበሰብንበት……………………….….ሆ በል ጃሌ
የፍቅር አዝመራ………………….……ሆ በል ጃሌ
ደሞ ሲቀራርብ…………….………….ሆ በል ጃሌ
እንዲጠጣ ጠላ………………………..ሆ በል ጃሌ
ደመራዉም ሲነድ………………….….ሆ በል ጃሌ
ሲበላ ………………………………..ሆ በል ጃሌ
ሆ በል ጃሌ ሆሆ ሆ በል ጃሌ ሆ
ሆ በል ጃሌ ሆሆ ሆ በል ጃሌ ሆ
እያ በል እያ………………………………….እያ
እያ በልያ……………………………………እያ
ጋሬጣና እሾክ…………………….…………እያ
ካልተክነህ………………………………….እያ
ያሳፍርሃል………………………………….እያ
ወንድነትህ.………………………………..እያ
አጎጠጎጤው………………………………..እያ
ጎፈሬው በዛ………………………………..እያ
ማነው ደፋሩ……………………………….እያ
አሁን የዋዛ…………………………….…..እያ
ማነው ሚነካሽ…………………………….እያ
ምን ያጎበረው……………………………..እያ
አሳይኝና………………………………….እያ
ልቡን ልበለው…………………………….እያ
እያ በል እያ……………………………….እያ
እያ በል እያ……………………………….እያ
እያ በል እያ………………………………እያ
እያ በል እያ……………………………….እያ
ደቦት እንስራ……………………………….ሆ እያበላ ሆ
ውጣ ኮበሌ………………………….…….ሆ እያበላ ሆ
ሽንሺንህ ይሸንሸን እያለች አሌ…………….ሆ እያበላ ሆ
ጉብሌ አትፍሪ………………………….…ሆ እያበላ ሆ
መጣን ከደጂሽ…………………………...ሆ እያበላ ሆ
ቤትና አዝመራውን ጎሮ ገባሽ………………ሆ እያበላ ሆ
ሆ እያበላ ሆሆ ሆ እያበላ ሆሆ
ሆ እያበላ ሆሆ ሆ እያበላ ሆሆ…………….....…ሆ በል ጃሌ
ገና ጉብሉን ልጅ……………………………….ሆ በል ጃሌ
ያደገ በቁምጣ……………………………..…..ሆ በል ጃሌ
ልቡን አስወጋችው……………………………..ሆ በል ጃሌ
ሳያስበው መጣ…………………………..…….ሆ በል ጃሌ
የመስቀል ወፍና…………………………………ሆ በል ጃሌ
አንቺ ልጅ ያው ናችሁ……………………...…..ሆ በል ጃሌ
ባመት አንዴ ብቻ…………………………….....ሆ በል ጃሌ
ብቅ ትላላችሁ…………………………………..ሆ በል ጃሌ
ሆ በል ጃሌ ሆሆ ሆ በል ጃሌ ሆ
ሆ በል ጃሌ ሆሆ ሆ በል ጃሌ ሆ
እያ በል እያ……………………………………..እያ
እያ በል እያ……………………………………..እያ
ጭሱን አባሪው……………………………….…እያ
ዓይኔን አሞኛል…………………………………..እያ
በየሰበቡ………………………………………….እያ
ማልቀስ መሮኛል………………………………...እያ
በጋው ዘለቀ………………………………………እያ
እሰየው ጓዴ………………………………………እያ
እጨድ እንግዲህ………………………………….እያ
ጤፍና ስንዴ……………………………………..እያ
ጎተራው ይሙላ…………………………………..እያ
አይጉደል ቤቱ……………………………………እያ
እንደውሃ ሙላት…………………………………እያ
ይፍሰስ ሙሂቱ……………………………………እያ
አብሮ ያዝልቀን………………………………….እያ
ይፍጠን አመቱ…………………………………..እያ
እያ በል እያ……………………………………..እያ
እያ በል እያ………………………………………እያ
እያ በል እያ……………………………………..እያ
እያ በል እያ………………………………………እያ
 
 
 

የግጥም ጥግ

እሳት ወይ አበባ 

ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን
እሳት ወይ አበባ

 ሌት ከዋክብቱ  እንደ ፀደይ
አጥለቅልቆን  በቀይ አደይ
ሰማዩ  ሥጋጃ  አጥልቆ
ተሽለምልሞ  አንጸባርቆ
ፈክቶ አሸብርቆ  ደምቆ
በአዝመራ  በአጥቢያ  ዐፀድ  ሰፍኖ
የዓደይ  አዝርዕት  ተከሽኖ
በዕንቁጣጣሽ  ሰብል  ታጥኖ
ኢዮሃ  አበባዬ  ሆኖ፥
ጨረቃዋ  ከቆባዋ፥  ከሽልምልሚት  እምቡጧ
ብላ ከሰንኮፈንዋ፥ ተንዠርግጎ የእንኮይ ቡጧ፥
ድንግል  ጽጌ-ረዳ  ፈልቃ
ፍልቅልቂት  ድምቡል ቦቃ
ተንሠራፍታ  የአበባ  ጮርቃ፥
ታድያን  ብሌኑ  የጠጠረ
ባሕረ-ሃሳቡ የከረረ
የውበት ዓይኑ የታወረ
ልበ-ሕሊናው  የሰለለ
አይ፥ አበባ አይደለም አለ፤
አይ፥ እሳት አይደለም አለ፤
ያልታደለ።
ሰማይ  ጨለማ  ነው እንጂ፥  እሳት አደል ብሎ ካደ
እቶን  ባይኑ  እየነደደ።
ከዋክብቱ  እንደ  ችቦ
በነበልባል  ወርቀ  ዘቦ
ከፅንፍ  ፅንፍ  አውለብልቦ
ደመራው  እየተመመ
እየፋመ  እየጋመ
ደመና  እንደንዳድ  ሲነድ
መንጸባርቅ  ሰደድ  ሲወርድ፥
በራሪ  ኮከብ  ተኩሶ
በአድማሳት  እሳት  ለኩሶ
ይኸ እንደኔና  እንዳንቺው፥  የውበት ዓይኑ  የሰለለ
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ፥  እሳት እኮ አይደለም አለ፥
ያልታደለ።

ይቅር ብቻ  አንናገርም፥
እኔና  አንቺ  አንወያይም፤
ለውይይት  አልታደልንም
እንዲያው ዝም፥ እንዲያው ዝምዝም።
አበባ አንሆን ወይ እሳት
ተጠምደን  በምኞት  ቅጣት
ሰመመን  ባጫረው  መዓት
ዕድሜ አችንን እንዳማጥናት፤

እሳት አንሆን ወይ አበባ
በሕቅ  እንቅ  ስንባባ
ባከነች  ልጅነታችን፥ እየቃተትን ስናነባ
ሳንፈጠር  በሞትንባት
ሳናብብ  በረገፍንባት
ሳንጠና ባረጀንባት
አበባ ወይንም እሳት፥  መሆኑን ብቻ አጣንባት።
*************************************************
1966 ዓ.ም.
ብርሀንና ሠላም ማተሚያ ቤት

 

 

ከመጽሃፍት ገፆች

ደራስያን በተለያዩ ዘመናትና ሁኔታዎች ውስጥ ያጋጠማቸውን የማኅበረሰቡን የሮሮም ሆነ የፍስሐ መንፈስ በመገምገምና አስመስለው በመቅረጽ ሥነ ቃልን ይጠቀማሉ፡፡ ለመልዕክቶቻቸው ማጉያ በማድረግ በሚፈጥሯቸው ገፀ ባሕርያት አማካይነት በልዩ ልዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸው ውስጥ ሲጠቅሷቸውም እናስተውላለን፡፡


"እግዚአብሔር ሲፈጥረኝ ጥንቱን በዚህ መሬት፣
ሳለቅስ ተወልጄ ሳለቅስ ኖሬበት፣
ሳለቅስ እንድሔድ ወደ ማልቀርበት፣
መከራን ጠግቤ ደስታን ምራብበት፣
ሌሎች የበሉትን እዳ ልከፍልበት፡፡ "


(ከ ፍቅር እስከ መቃብር)

Wednesday, September 19, 2012

የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር

በዘመነ ኢህአዲግ













የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ፀንቶ
ታየ ህዝባዊነት ዳር እስከዳር በርቶ
ለሰላም ለፍትህ ለህዝቦች ነፃነት
በእኩልነት በፍቅር ቆመናል ባንድነት
መሰረተ ፅኑ ሰብዕናን ያልሻርን
ህዝቦች ነን ለስራ በስራ የኖርን
ድንቅ የባህል መድረክ ያኩሪ ቅርስ ባለቤት
የተፈጥሮ ፀጋ የጀግና ህዝብ እናት
እንጠብቅሻለን አለብን አደራ
ኢትዮጵያችን ኑሪ እኛም ባንቺ እንኩራ።
*****************************
በ1984 ዓ.ም
ግጥም፦-ደረጀ መላኩ መንገሻ፤
ዜማ፦- ሰሎሞን ሉሉ ምትኩ

*********************
*********************

በዘመነ ደርግ



















ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ -ኢትዮጵያ ቅደሚ
በኅብረተሰባዊነት - አብቢ ለምልሚ!
ቃል ኪዳን ገብተዋል - ጀግኖች ልጆችሽ
ወንዞች ተራሮችሽ - ድንግል መሬትሽ
ለኢትዮጵያ አንድነት - ለነፃነትሽ
መስዋዕት ሊሆኑ - ለክብር ለዝናሽ!
ተራመጂ ወደፊት - በጥበብ ጎዳና
ታጠቂ ለሥራ - ላገር ብልጽግና!
የጀግኖች እናት ነሽ -  በልጆችሽ ኩሪ
ጠላቶችሽ ይጥፉ - ለዘላለም ኑሪ።
*************************
በ1968 ዓ.ም 
ግጥም፦-በአሰፋ ገብረማርያም
ዜማ፦-አቶ ዳንኤል ዮሐንስ

*********************
*********************

በንጉሱ ዘመን


ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ
በአምላክሽ ኃይል በንጉስሽ
ተባብረዋልና አርበኞችሽ
አይነካም ከቶ ነፃነትሽ
ብርቱ ናቸውና ተራሮችሽ
አትፈሪም ከጠላቶችሽ።
ድል አድራጊው ንጉሣችን
ይኑርልን ለክብራችን።
****************
በ1919 ዓ.ም
ግጥም፦-በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ
ዜማ፦-ኬቨርክ ናልባልድያን

********************

ኢትዮጵያ



ኢትዮጵያ ~ Ethiopia  /aityoP'ya/


ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ መሠረቱ ግሪክ ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት በውል ከታወቀችው ከግብፅ በስተደቡብ የሚገኘው የአፍሪቃ ክፍልና ደቡብ ምዕራብ እስያ የሚጠሩበት አጠቃላይ ስም ነበር፡፡ ይሁንና ከክርስቶስ ልደት በኋላ አገባቡ ጠበብ እያለ አሁን ኢትዮጵያ የምትገኝበት አካባቢ መጠሪያ ለመሆን በቃ፡፡ ስያሜውን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ በጠበበና እስካሁንም ቋሚ በሆነ መልኩ የምናገኘው
በ4ኛው ምእተ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የክርስትናን እምነት የተቀበለው የአክሱም ንጉሥ ዔዛና በድንጋይ ላይ ባስቀረፀው አንድ ጽሑፍ ላይ ራሱን የኢትዮጵያ ንጉሥ ብሎ ሲጠራ ነው፡፡ ከዚያም በተከታታዮቹ ምእተ ዓመታት በጊዜው በተጻፉ ጽሑፎች አክሱም የኢትዮጵያውያን ከተማ፣ አፄ ካሌብ ደግሞ የኢትዮጵያውያንንጉሥ ተብለው ሲጠቀሱ ስናይ ስያሜው ቋሚ መልኩን እየያዘ መምጣቱን እንረዳለን፡፡ በ14ኛው ምእት ዓመት መጀመሪያ ላይ የተጻፈው ክብረ ነገሥት የተሰኘው ንግሥተ ሳባ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ያደረገችውን ጉዞ የሚያትተው መጽሐፍም፣ ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ በአሁኒቱ ኢትዮጵያ ካለችበት ግዛት ጋር ያለውን መያያዝ ኦፊሲዬል አድርጎታል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ነገሥታት መደበኛ መጠሪያቸውም "ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ" ወይም "ንጉሠ ኢትዮጵያ" ሆኖ ቆይቷል፡፡
 
 

ስለ ኢትዮጵያ ዕይታ

ኢትዮጵያ በሰሜን ምስራቅ የአፍሪካ ቀንድ በመባል በሚታወቀው አካባቢ የምትገኝ ከአፍሪካ በቆዳ ስፋቷ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የምትገኘ አገር ናት፡፡ ዙሪያዋን አምስት አገሮች ያዋስኗታል፡፡ በምስራቅ በኩል ጅቡቲና ሶማሊያ፤ በሰሜንና በሰሜን ምስራቅ ኤርትራ፤ በደቡብ ኬንያ እና በምእራብ ሱዳን ናቸው፡፡ ጠቅላላ የቆዳ ሰፋት 1.1 ሚሊዬን ካሬ ሲሆን በውስጧ 7000 ኪ.ሜ የሚደርስ ርዝማኔ ያላቸው አስር ትላልቅ ወንዞችና ወደ 7000 ካሬ ጠቅላላ ስፋት ያላቸው ሀይቆች አሏት፡፡
መልክአ ምድር
ኢትዮጵያ በውስጧ የተለያዩ መልክአ ምድር ያላት አገር ከመሆኗ በተጨማሪ የአየር ንብረት አፈር የእንስሳትና የዕፅዋት ስብጥር የሚስተዋልባት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ከፍተኛ የሆኑ ተራሮች ከላያቸው ጠፍጣፋ የሆኑ አምባ የሚባሉ ኘላቶዎች ስምጥ የሆኑ ሸለቆዎች፤ ጥልቅ የወንዝ ሸለቆዎችና ሰፋፊ ሜዳዎች በውስጧ ይዛለች፡፡ ከባህር ጠለል በላይ 4620 ሜትር ከሚደርሰው ዳሽን ተራራ እስከ 148 ሜትር ከባህር ጠለል በታች እስከሆነው የዳሎል ዲኘረሽን ድረስ የሚሆን ልዩነት ያለው የከፍታና ዝቅታን የምታስተናግድ አገር ናት፡፡
ለም ከሆኑ መሬቶችና ተራሮች ምንም የማይታይባቸው ከሚመስሉ መሬቶች አንስቶ፣ ኢትዮጵያ በብዙ ገባሮችና ትላልቅ እንደ አባይ ተከዜ አዋሽ ኦሞ ዋቢ ሸበሌና ባሮ-አካቦ በመሳሰሉ ወንዞች የታደለች አገር ናት፡፡
ከሜዲትራንያን ምስራቃዊ መጨረሻ ተነስቶ፣ ደቡብ ምስራቅ አፍሪካ የምትገኘው ሞዛንቢክ ድረስ የሚደርሰው ታላቁ የስምጥ ሸለቆ ኢትዮጵያን ለሁለት ከፍሏት ያልፋል፡፡
የአየር ንብረት
ኢትዮጵያ እንደ መልክአ ምድራዊ አቀማመጧ የአየር ንብረቷም በተለያዩ ቦታዎች የተለያየ ሁኔታ ይታዩባታል፡፡ የመካከለኛው ኘላቶ አካባቢ ብዙም የማይፈራረቅ አይነት ወይናደጋማ አይነት የአየር ንብረት ይታይበታል፡፡ ዝቅተኛው የአየር ንብረት በአማካኝ 60c ሲሆን ነገር ግን ወደ ቀይባህር በረሀ አካባቢ 600c የሚደርስበት ጊዜዎች አሉ፡፡ በብዙ የአገሪቱ አካባቢ በክረምት ወራት ይኸውም ሰኔ ሀምሌና ነሀሴ ውስጥ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ይመዘገባል፡፡ 
የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር
የኢትዮጵያ (እንዲሁም በኤርትራ አብያተ ክርስትያናት) ዋና ካሌንደር ነው። አዲስ ዓመት በጁሊያን ካሌንደር አቆጣጠር በኦገስት 29 ወይም 30 የሚጀምር ሲሆን በግሪጎሪያን ካሌንደር ደግሞ 1901 ... እስከ 2099 ... ድረስ በሴፕቴምበር 11 ወይም 12 ይጀምራል። በየአራት ዓመቱ አንድ ቀን ይጨመራል። በአንድ ዓመት ውስጥ አስራ-ሁለት ባለሠላሣ ቀናት እና አንድ ባለ አምስት (ስድስት በአራት ዓመት አንዴ) ቀናት ያሉባቸው ወራት አሉ።
የአመተ ምህረት ዘመናት ከጎርጎርዮስ 'አኖ ዶሚኒ' 7 ወይም 8 አመታት የሚለይበት ምክንያት፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት 400 አመት ያህል በኋላ አኒያኖስ እስክንድራዊ ዘመኑን ሲቆጥረው ትስብዕቱ በመጋቢት 29 1 .. እንደ ሆነ ስለ ገመተ ይህ ትስብዕት ዘመን 1 አመት ሆኗል። ይህ አቆጣጠር በምሥራቅ ክርስቲያን አገራት ከተቀበለ በኋላም 443 .. ከሮማ ፓፓና ከምሥራቅ አቡናዎች መካከል ልዩነት ደርሶባቸው፤ 517 ሌላ መነኩሴ ዲዮኒሲዮስ ኤክሲጉዎስ ሌላ አቆጣጠር (አኖ ዶሚኒ) አቀረበ። በሱ ግምት ትስብዕቱ የተከሠተበት ቀን ከአኒያኖስ ግምት በፊት 8 አመታት አስቀደመው። አኖ ዶሚኒ አቆጣጠር በምዕራብ አውሮፓ ላይኛነት በማግኘቱ የትስብእት ዘመን 1 አመተ ምህረት አኖ ዶሚኒ 9 .. ሆነ።
የኢትዮጵያ ዘመን ኣቆጣጠር የጁልያን ዘመን ኣቆጣጠር ኣይደለም።
ወራት
የወራት አቆጣጠር የተወረሰ ቅብጢ ዘመን አቆጣጠር ይህም የወጣ ጥንታዊ ግብጽ ዘመን አቆጣጠር ነው። ሆኖም የወሮች ስሞች ግዕዝ ተለውጠዋል።

ቋንቋ
አራት መሰረታዊ የቋንቋ ቤተሰቦች ሲኖር እነርሱም ኩሺቲክ (Cushitic) ፣ ሴሜቲክ (Sematic) ፣ ኦሜቲክ (Omotic) ፣ ኒሎ ሻሮን (Nilo-Saharan) በመባል ይታወቃሉ።
በግምት 83 የተለያዩ ቋንቋዎችና ከ200 የሚበልጡ የአነጋገር ዘዬዎች በአገሪቱ ይነገራሉ።
አማርኛ የብሄራዊ ቋንቋ ሲሆን የንግድና የስራ መግባብያ ቋንቋዎች አማርኛ እና እንግሊዝኛ ናቸው።
መልክአ ምድር
ኢትዮጵያ በውስጧ የተለያዩ መልክአ ምድር ያላት አገር ከመሆኗ በተጨማሪ የአየር ንብረት አፈር የእንስሳትና የዕፅዋት ስብጥር የሚስተዋልባት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ከፍተኛ የሆኑ ተራሮች ከላያቸው ጠፍጣፋ የሆኑ አምባ የሚባሉ ኘላቶዎች ስምጥ የሆኑ ሸለቆዎች፤ ጥልቅ የወንዝ ሸለቆዎችና ሰፋፊ ሜዳዎች በውስጧ ይዛለች፡፡ ከባህር ጠለል በላይ 4620 ሜትር ከሚደርሰው ዳሽን ተራራ እስከ 148 ሜትር ከባህር ጠለል በታች እስከሆነው የዳሎል ዲኘረሽን ድረስ የሚሆን ልዩነት ያለው የከፍታና ዝቅታን የምታስተናግድ አገር ናት፡፡
ለም ከሆኑ መሬቶችና ተራሮች ምንም የማይታይባቸው ከሚመስሉ መሬቶች አንስቶ፣ ኢትዮጵያ በብዙ ገባሮችና ትላልቅ እንደ አባይ ተከዜ አዋሽ ኦሞ ዋቢ ሸበሌና ባሮ-አካቦ በመሳሰሉ ወንዞች የታደለች አገር ናት፡፡
ከሜዲትራንያን ምስራቃዊ መጨረሻ ተነስቶ፣ ደቡብ ምስራቅ አፍሪካ የምትገኘው ሞዛንቢክ ድረስ የሚደርሰው ታላቁ የስምጥ ሸለቆ ኢትዮጵያን ለሁለት ከፍሏት ያልፋል፡፡
የአየር ንብረት
ኢትዮጵያ እንደ መልክአ ምድራዊ አቀማመጧ የአየር ንብረቷም በተለያዩ ቦታዎች የተለያየ ሁኔታ ይታዩባታል፡፡ የመካከለኛው ኘላቶ አካባቢ ብዙም የማይፈራረቅ አይነት ወይናደጋማ አይነት የአየር ንብረት ይታይበታል፡፡ ዝቅተኛው የአየር ንብረት በአማካኝ 60c ሲሆን ነገር ግን ወደ ቀይባህር በረሀ አካባቢ 600c የሚደርስበት ጊዜዎች አሉ፡፡ በብዙ የአገሪቱ አካባቢ በክረምት ወራት ይኸውም ሰኔ ሀምሌና ነሀሴ ውስጥ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ይመዘገባል፡፡
በከፍታና በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ዐይነት የአየር-ንብረት ክልሎች ይገኛሉ። እነሱም:-
  • ደጋ - ከፍታቸው ከባሕር ጠለል 2400 ሜትር የሚጀምር እና የሙቀት መጠናቸው ከ 16 ዲግረ ሴ.ግ የማይበልጥ፤
  • ወይናደጋ - ከፍታቸው ከባሕር ጠለል ከ1500 እስከ 2400 ሜትር፣ ሙቀታቸውም ከ16 ዲግረ ሴ.ግ እስከ 30 ዲግረ ሴ.ግ የሚደርስና፣
  • ቆላ - ከባህር ጠለል በታች ጀምሮ እስከ 1500 ሜትር ከፍታ ያላቸው፣ የሙቀት መጠናቸውም ከ30 ዲግረ ሴ.ግ እስከ 50 ዲግረ ሴ.ግ የሚደርስ አከባቢዎች ናቸው።
ዋናው የዝናብ ወቅት ከሰኔ አጋማሽ እስከ መስከረም አጋማሽ ሲሆን፣ ከሱ ቀደም ብሎ አልፎ አልፎ የሚጥል የበልግ ዝናብ በየካቲት እና በመጋቢት ይከሰታል። የተቀሩት ወራት በአብዛኛው ደረቅ ናቸው።
*********************************************************************************
ምንጭ:--http://am.wikipedia.org/// http://www.ethiopia.gov.et