ከደራሲያን ዓምባ

Wednesday, November 25, 2020

ለሰው ልጆች ሰላም

ለሰው ልጆች ሰላም  

ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ

 *************************


 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
ለሰው ልጆች ፍቅር ለሰው ልጆች ሰላም
ለሰው ልጆች ፍቅር ለሰው ልጆች ሰላም
ለሰው ልጆች በዓለም ዙሪያ ሁሉ
ሰላም ይሁን ምድሩ ሁሉ

ሰላም
ሰላም
ሰላም
በዓለም ዙሪያ ሁሉ
ለሰው ዘር በሙሉ
ሰላም
ሰላም
ሰላም
በዓለም ዙሪያ ሁሉ
ለሰው ዘር በሙሉ

ከባሕር ከየብሱ ከሰፊው ውቅያኖስ
በሚመጣው አየር በሚነፍሰው ንፋስ
ያለን መልካም ምኞት ያለን ቀና መንፈስ
የሰላም ጥሪያችን መልዕክታችን ይድረስ
የተበከለ አየር ጠፍቶ ከላያቸው
የዱር አራዊቶች አእዋፍ በጎጇቸው
ሁሉም በያሉበት በየበኩላቸው
የሰላሙ ፋና ይድመቅ ይብራላቸው

በዓለም በዓለም
ይስፈንልን ሰላም
በዓለም በዓለም
ይስፈንልን ሰላም
ሰላም
ሰላም
ሰላም
በዓለም ዙሪያ ሁሉ
ለሰው ዘር በሙሉ
ሰላም
ሰላም
ሰላም
በዓለም ዙሪያ ሁሉ
ለሰው ዘር በሙሉ


 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
ህጻናት እንዲያድጉ በንጹህ አይምሮ
ነጻ ህሊናቸው ጎልብቶና ዳብሮ
ወጣት ሽማግሌ የሰው ዘሮች ሁሉ
ሰላም ለዓለማችን ይላሉ በሙሉ
ዘንባባ ዘንጥፈን እርግቦችን ለቀን
ዘር ቀለም ሳንለይ ጥላቻን አርቀን
ለሰው ልጆች ደስታ ለሰው ልጆች ፍቅር
ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ለሰላም እንዘምር

በዓለም በዓለም
ይስፈንልን ሰላም
በዓለም በዓለም
ይስፈንልን ሰላም

ሰላም
ሰላም
ሰላም
በዓለም ዙሪያ ሁሉ
ለሰው ዘር በሙሉ
ሰላም
ሰላም
ሰላም
በዓለም ዙሪያ ሁሉ
ለሰው ዘር በሙሉ
ሰላም
ሰላም
ሰላም
በዓለም ዙሪያ ሁሉ
ለሰው ዘር በሙሉ
 

‹‹ለሰው ልጆች ሰላም. . .››  22 November 2020

 ***********

ከ1980ዎቹ መባቻ ጀምሮ በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን ይሰማ፣ ይደመጥ የነበረ አሁንም ደግሞ ሞገድ አሳብሮ የሚሰማ የሚደመጥ አንድ ዜማ/ዘፈን አለ፡፡

‹‹ለሰው ልጆች ፍቅር ለሰው ልጆች ሰላም፣

ለሰው ልጆች በዓለም ዙሪያ ሁሉ

 ሰላም ይሁን ምድሩ ሁሉ፡፡››

ታዋቂውና አንጋፋው ድምፃዊ መሐመድ አህመድ ያቀነቀነው ሌሎች ድምፃውያንም በኅብረ ዝማሬ ዓምና ያቀረቡት የሰላም ጥሪ፣ የሰላም ደወል ነው፡፡


 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

በየዐረፍተ ዘመኑ ስለኢትዮጵያ ሰላም ያልተዘመረበት ያልተገጠመበት፣ ያልተተወነበት ጊዜ የለም፡፡ ሁሉም በየቤተ እምነቱ፣ በየደጀ ሰላሙ ስለሰላም ጸልየዋል፣ ስለሰላም ዘምረዋል፣ ስለ ሰላም አልቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ በየዐረፍተ ዘመኑ የሰላም ድምፅ እየራቀ፣ ሁከት እየሰፈነና፣ ጦር ንቅነቃ፣ ዘገር ውዝወዛ መንሰራፋቱ ሰውን ለጥፋት፣ ለስደት፣ ለጉዳት መዳረጉ አልቀረም፡፡

ሰላምና ጽንሰ ሐሳቡ

በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በተዘጋጀው ‹‹መዝገበ ቃላት ሐዲስ›› የሰላምን ፍች ከሌሎች የምሥራቅ ሴማዊ ቋንቋ ቤተሰብ ስያሜ ጋር አያይዘው አቅርበውታል፡፡ ሰላም በሱርስት (የሶርያ ቋንቋ) ሽላም፣ በዕብራይስጥ (የእስራኤል ቋንቋ) ሻሎም፣ በዓረብ ሰላም እንደሚባል ትርጉሙም ፍፁም ጤናን፣ ዕረፍትን፣ ዕርቅን፣ ፍቅርን አንድነትን፣ ደኅንነትን፣ ተድላ ደስታን፣ ሰላምታን ያቀፈ ጽንሰ ሐሳብ ነው ይሉታል፡፡ ሰላም ሰው ሲገናኝ፣ ሲለያይ የሚለው፣ የሚናገረው ወይም የሚጥፈው የቡራኬ የምርቃት ቃል ነው ሲሉም ያክሉበታል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ‹‹የሰላም ግንባታ ማሠልጠኛ›› በተሰኘው ጥናታዊ መድበሉ ስለ ሰላም ምንነት እንደሚከተለው አብራርቷል፡፡

‹‹ሰላም›› የሚለው የአማርኛ ቃል የተሸከመው ጽንሰ ሐሳብ ከጦርነትና ከአመፅ ነፃ መሆን ከሚለው የአንዳንድ መዛግብት ቃላት ውሱን ድንጋጌ የሰፋ ትርጉም ይዟል፡፡ ‹‹ሰላም›› ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታና ከመለኮታዊ ዕድቅ ጋር የሚጣጣም ሰብዓዊ ዕቅድ ከመሆኑ በፊት በዋናነት የእግዚአብሔር የራሱ ዓይነተኛ ባህሪ  ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ‹‹እግዚአብሔር ሰላም ነው›› (መጽሐፈ መሳፍንት 6፡24) በማለት ማረጋገጫውን ሰጥቷል፡፡

‹‹በቅዱሳት መጻሕፍት ሰላም የሚለው መሠረታዊ ቃል የሚያመለክተው በሰዎች ሕይወት ውስጥ ተሟልቶ መገኘት የሚገባውን ደኅንነት፣ ምሉዕነት፣ ፍፁምነትና ዋስትናን በመሆኑ ቃሉ የያዘው ፍቺ ላቅ ያለ ሐሳብን ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ሰላም ማለት ሰዎች በግል ኑሯቸውም ሆነ በማኅበራዊ ግንኙነታቸው ወቅት ሊኖራቸው የሚገባ ሁለንተናዊና ምሉዕ የሆነ የሕይወት መገለጫ ነው ማለት ይቻላል፡፡

‹‹ሰላም›› (Sala’am) የሚለው የዓረብኛው ቃልም እንዲሁ ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ጽንሰ ሐሳቦች ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ከመያዙ በተጨማሪ በምድራዊም ሆነ በመንፈሳዊ ዓለም ከአደጋ ነፃ የሆነ የጤናማ ሕይወት ማረጋገጫ የሚል ከፍ ያለ ትርጉም ተሸክሟል፡፡

በግዕዝ ቋንቋም ሰላም ቀደም ሲል የተጠቀሱት ትርጉሞች እንደ ተጠበቁ ሆነው ማክበርን፣ ደስታን፣ ዋጋን የሚመለከት ትርጉም እንዳለው የሚያብራራው መድበሉ፣ ይህንን መሰል ሰላም ማግኘት የሚቻለው ራስን ከፈጣሪ ሐሳብ ጋር በማስማማት፣ ከተፈጥሮ ጋር በመታረቅና ከማኅበረሰብ አንፃርም ፍትሕና ማኅበራዊ መረጋጋት ባሰፈነ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ መኖር ሲቻል መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

ሰላም ሰዎች ከራሳቸው ጋርና እርስ በርስ፣ ከፈጣሪና ከተፈጥሮ ሥርዓት ጋርም እንዲሁ ጤናማ ግንኙነት በመፍጠር በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ ሥርዓት፣ በማኅበራዊና በመንፈሳዊ ዘርፎች ውስጥ ዋስትና የሚሰጥና የሰከነ ሕይወት የሚመሩበት እንደሆነም ያሰምርበታል፡፡ ሰላም ለሰዎች ሁለንተናዊ ሕይወት ዋስትና በመስጠት ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥር የጽንሰ ሐሳቡ ትርጉም ሲተነተን ሰፋ ተደርጎ እንጂ በቁንፅል ሊሆን እንደማይገባም እንዲሁ፡፡

ሰላም የባህል አንዱ ክፍል መሆኑን፣ ባህልም የአንድ ሕዝብ ሁለንተናዊ መገለጫ፣ ማለትም ኅብረተሰቡ የተፈጠረበትን ማኅበረሰብ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሕይወት በተገቢ ሁኔታ የማንፀባረቅ አቅሙ ከፍ ያለ እንደሆነም ያብራራል፡፡

የማኅበረሰቡ ሐዘን፣ ደስታ ችግሩና ብልፅግናው የሚገልጸው በባህሉ ሲሆን፣ የዜጎች ሁለንተናዊ የግልና የማኅበራዊ ሕይወት አመራር ሥልት የሚወሰነውም በባህል አማካይነት ነው፡፡ አንድን ማኅበረሰብ ከሌላው ልዩ የሚያደርገው መታወቂያ በዋነኛነት ባህሉ ነው የሚባለውም ስለዚሁ ምክንያት መሆኑን ጥናቱ ገልጾ በማሳያነት እንግዳ ተቀባይነትን፣ ተካፍሎ በጋራ መብላትን፣ ተከባብሮና ተፈቃቅሮ መኖሩ፣ ዕድር ዕቁቡ፣ ሠርግ ሐዘኑ፣ አለባበስ አመጋገቡ ወዘተ. ስለባህል ብዙ የሚነገረውን ያህል፣ ስለሰላም ባህል እጅግም ሲነገር አይደመጥም ሲል አሳሳቢ ገጽታውን ይጠቁማል፡፡


የሰላም ባህል፣ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራ በሚኖሩባት ኢትዮጵያ በሰላም ተከባብረው ለዘመናት እንዲኖሩ ያስቻላቸው የአኗኗር ዘይቤ መሆኑን፣ የሰላምን ቀጣይነት ከሚያረጋግጡትና ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው የሰላማዊነት መገለጫ ባህላዊ እሴቶች መካከል ቤተሰብ ተኮር የሰላም ባህል አንዱና ቀዳሚው መሆኑንም ይገልጻል፡፡

በኢትዮጵያ ለረዥም ዘመናት ጠንካራ የሰላም ባህል እንዲኖር ቤተሰብ ተኮርነት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡

‹‹የሰላም ባህላችንን ውበት ለመግለጽ የማኅበረሰባችን መሠረት የሆነውን የቤተሰብ አስተዋጽኦ ማውሳት እጅግ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙውን ጊዜ በፍቅርና በመከባበር በጋራ ሠርተን የምንኖረው፣ አደጋን የምንከላከለው፣ ሰላማዊ ሕይወት ለመምራት የምንለማመደውና መተባበርን የምንለማመደው በቤተሰብ መካከል በመኖር ነው፡፡ የአመለካከት ልዩነቶችን የምንፈታውና ለቤተሰቡ የጋራ ደኅንነትና ዕድገት ጠቃሚ መንገዶችን የመቀየስ ልምድ የምንማርበት ትልቁ ትምህርት ቤታችን ቤተሰብ ነው ቢባል ከእውነት አያርቀንም፡፡››

እንደ ጥናታዊው መድበል አገላለጽ፣ በየዘመናቱ ለሕዝቡ ሰላምና የጋራ ዕድገት ቅድሚያ እየሰጡ ያታገሉና የታገሉ ጀግኖችም አገራቸውን እንደ ቤተሰብ በመቁጠር ታላላቅ የሚሰኙ አገራዊ ቅርሶች ሊያቆዩ የቻሉት ቤተሰብ ተኮር መሠረት ላይ ታንፀው በማደጋቸው ነው፡፡

በአንፃሩም በጋራ ሠርቶ በጋራ ማደግ፣ ከራስ ጥቅም ይልቅ አገርንና ሕዝብን ማስቀደም የሚሳናቸው ግለሰቦች እየተነሱ መነጋገሪያ ለመሆን የቻሉበት ሲመረመር ምክንያቱ ምናልባትም በቤተሰብ ተኮር እሴት ላይ የማደጉን አጋጣሚ ስላልተመቻቸላቸው ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አይከብድም፡፡

የብዙ ኢትዮጵያውያን ዕድገት፣ ኑሮ፣ ደስታ፣ ሐዘን፣ ወዘተ. ከቤተሰባዊ አብሮነት ጋር በእጅጉ የተሳሰረ በመሆኑ፣ በቤተሰቡ መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲቀጥል እያንዳንዱ ዜጋ ብርቱ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሥር ሰዶ የሚገኘው የቆየው የሰላም ወዳድነት ምንጭም ዜጎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ከቤተሰቦቻቸው ከተማሯቸው ሰው አክባሪነትና በጋራ ሠርቶ የማደግ መሠረት ላይ የታነፀ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም የሚለው ጥናቱ፣ በመሆኑም ዘላቂ ሰላም በማስፈን ቁሳዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሥነ ልቦናዊም ሆነ ማኅበራዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ቤተሰባዊ ውርስ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ያሰምርበታል፡፡

 **************************************************

ምንጭ:- https://www.ethiopianreporter.com/article/20539


 

 

 

 

Monday, November 16, 2020

ባለ አጉረምራሚ ድምጹ "ጎልደን ቮይስ" ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ

 

ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ

ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴን ብዙዎች እንደሚያውቁት አስባለሁ። በተለይ በጉልምስና ዕድሜና ከዛም ከፍ ባለ የዕድሜ ክልል የሚገኘው ኢትዮጵያዊ አለምነህ ዋሴን ያውቀዋል። በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ ሬድዮ ውስጥ ሲሰራ ለየት በሚለው ጆሮ ገብ ድምጹና ልዩ በሆነው የዜና አቀራረቡ ተወዳጅ እንደነበር ራሴን አንድ ብዬ በማስረጃ ምስክርነት እጠራለሁ።

ዜና-ፋይል! የሚለው የዜና አቀራረብ ፎርማት ሲታወስ አለምነህ ዋሴ፤ ዳሪዎስ ሞዲ፤ ነጋሽ መሐመድ፤ ንግስት ሰልፉን ... የማያስታውስ ካለ እሱ በዛ ወቅት ያለጥርጥር ከኢትዮጵያ ውጭ ነበር። የዛሬውን አያድርገውና በኢትዮጵያ ሬድዮ ብሄራዊ አገልግሎት ብቸኛዋ የዜናና የመረጃ  ምንጫችን ስለነበረች እነ አለምነህን አለማወቅ አይቻልም።

በተለይ አለምነህ ዋሴ ደግሞ በአሜሪካና ኢራቅ ጦርነት ወቅት የሚያቀርበው ዘገባ እንዴት በጉጉት ይጠበቅ እንደነበር ሳስታውስ፤ ዜና ድሮ ቀረ! ለማለት ይዳዳኛል።

አለምነህ ዋሴን ከምናስታውስባቸው ስራዎቹ ዋናው የአሜሪካና ኢራቅ ጦርነት ዘገባው ነው።

በዛ ወቅት በማለዳው የኢትዮጵያ ሬድዮ ብሄራዊ አገልግሎት ዜና አለምነህ፤ 

 

”ባግዳድ ጸጥ ረጭ ብላ አድራለች፤ ምድሯን የተቆለመመ ብረት፤
የግንብ ፍርስራሽ፤ አቧራ ... ሞልቶታል” 

 

እያለ በዓይነ ልቦናችን ወደ ባግዳድ ተጉዘን አዳሯን እንድንመለከት የሚያደርግበትን አቀራረቡን ዛሬም ድረስ በከፊልም ቢሆን አስታውሰዋለሁ። ስእላዊ ዜናውን ያቀርብልን የነበረው ምናልባት በምስል ያገኘውን የባግዳድን የማለዳ ገጽታ ወደ ቃላት ተርጉሞ፤ አልያም ገጽታውን የዘገበ ዜና ወደ አማርኛ መልሶ ይመስለኛል። ያም ሆነ ይህ አለምነህ በአሜሪካና ኢራቅ ጦርነት የማይረሳ አሻራውን በማሳረፉ ሁላችንም የምንስማማ ይመለኛል።

 

 “እጅ መስጠት የለም አሉ ሳዳም ሁሴን” 

 

የሚለው ድምጹ ዛሬም ድረስ ይሰማኛል።

እንዳሁኑ መረጃ ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደ ሌላው የዓለም ጫፍ በብርሃን ፍጥነት በማይደርስበት በዛን ወቅት አለምነህ ዋሴ የአሜሪካና የኢራቅን ጦርነት እግር በግር ተከታትሎ የሚዘግብልን ከዓለም አቀፍ የዜና ዲስፓች ላይና ከእንግሊዘኛ መጽሔቶች ላይ እንደነበር ሲናገር የሰማሁ ይመስለኛል። በግዜው እሱም ከኢ.ዜ.አ. የዜና ዲስፓች ሌላ አማራጭ አልነበረውም። እኛም እሱን ከመስማት በስተቀር ሌላ አማራጭ አልነበረንም።

 

ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ 

 
 
 
https://www.youtube.com/watch?v=3dVNaqsLl4A

https://Interview with Journalist Alemneh Wasse on Yezinegnochu Chewata program Zami Radio.youtube.com/watch?v=VHSvzaAEL_k 


 


ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ


 
 

 

 

Monday, September 28, 2020

አደይ አበባ በመስከረም

 

አደይ አበባ

                                                                       *🌻🌻🌻*

የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ በአል ሁሌም በየአመቱ መስከረም አንድ ቀን ይከበራል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያንም ዘመን በሚለውጡበት መስከረም ወር ተፈጥሮ የምትለግሳቸውን አደይ አበባ በናፍቆት ይጠብቃሉ፡፡ ዙሪያው ገባውን በቢጫው አበባ ተውቦ ሲመለከቱ ያኔ አዲስ አመት ባተ ይላሉ፡፡ ወለል ግድግዳቸውን በአበባው ያስጌጣሉ፡፡ ልጃገረዶች “አባባዮሆሽ” ሲጨፍሩ አደይ አበባን ይዘው መዞራቸውም የተለመደ ውብ የበዓል ትእይንት ነው፡፡
 
የአደይ አበባ ከዘመን መለወጫ ጋር የመተሳሰሩ ሚስጥርም ከኖህ ታሪክ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ነገሩ እነዲህ ነው ምድር በጥፋት ውሃ በተጥለቀለቀች ጊዜ ኖህ እና ቤተሰቦቹ በመርከብ ውስጥ ገብተው ተርፈዋል፡፡ ታዲያ ከጊዜ በሁዋላ ኖህ የውሃውን መጉደል ለማረጋገጥ እርግብን ይልካታል፤እርግብም ለምለም ቅጠል፣አደይ አበባ እና ሳር ይዛ በመመለስ የውሃውን መጉደል አበሰረች፡፡ በዚህም በተለይ አደይ አበባ የአዲስ አመት ማብሰሪያ እና የተስፋ ምልክት ሆኖ በኢትዮጵያ ይታወቃል፤ይዘከራል፡፡
 
የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ የሆነው አደይ አበባ ከምን ዓይነት የዕጽዋት ዝርያ ይመደባል? ምን አይነት ጥቅም እንዳለው? ምን ያህል ዝርያዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ? ከኢትዮቤስት ዶት ኮም እና ከዲደብሊው ያገኘነውን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበንላችሀል!መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆንላችሁም ተመኝተናል!
 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-እፅዋት መምህር ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው ከኢትዮቤስት ዶት ኮም ባደረጉት ቃለምልልስ እንደተናገሩት አደይ አበባ የሚባሉት አንድ አይነት ብቻ ዝርያ ያላቸው ሳይሆኑ ሁለትና ሶስት የሚሆኑ በቤተሰብ ተመሳሳይነት ያላቸው ዝርያዎች ናቸው::በቤተሰብ የሳይንሳዊ መጠሪያቸው ባይደንስ በሚል ይታወቃሉ::
የዘርፉ አጥኝዎች በአለም እስከ 300 የሚደርሱ የባይደንስ ዝርያዎች እንዳሉ ጠቁመዋል:: በአሃያ ዩኒቨርሲቲ የእጽዋት እና ብዝሃ ህይወት መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን ታደሰ ከመረጃ ምንጫችን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደጠቆሙትም አፍሪካው ውስጥ ወደ 64 የባራደንስ ዝርያዎች ሲኖሩ ከነዚህ ውስጥ 21 ያህሉ ዝርያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ:: ከ21 ውስጥ ወደ 12 ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ናቸው::እነዚህ ደግሞ ባይደንስ ማይክሮ ካርፖ የሚባለው በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያዎች አካል ናቸው::
ባይደንስ ማክሮ ካርፖ የተባሉት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙት የአደይ አበባ ዝርያዎች ከሌሎች መሰሎቻቸው(የባይደንስ ቤተሰቦች) የሚለዩባቸው ባህርያት አሏቸው:: ፅዋቶቹ አንዳቸውን ከሌላቸው ከሚለያቸው መገለጫዎቻቸው መካከል የቅጠሎቻቸው ቁጥር መብዛት እና ማነስ አንዱ ነው:: ሌላው ደግሞ የቅጠሎቻቸው አዘረጋግ ነው:: የአበባዎቻቸው እና የፍሬያቸው ሁኔታም ልዩነቶች ከሚገለፁባቹው መስፈርቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው::
 

 
አንዳነዶቹ የባይደንስ ቤተሰብ የአደይ አበባ ዝርያወች ቅጠሎቻቸው ከሁለት እስከ ሶስት ስንጥቅ ሲኖራቸው አንዳንዶቹ ደግሞ አምስትና ስድስት ስንጥቆች አሏቸው::
ሌላው ከአባባው ጋር የተያያዘው ልዩነት የቀለም ነው:: የአንዳንድ የአደይ አበባዎች ቀለም ፈዘዝ ያለ ቢጫ ሲሆን የሌሎቹ ቀለም ደመቅ ያለ እና የተለየ ነው:: ከፍሬውም አንፃርም በእኛ አገር የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያ ከሌሎች ዝርያዎች አንፃር ፍሬው ትልቅ መሆኑም ሌላዉ የሚለየው ባህሪ ነው::
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያ የዕድገት ጊዜውን ሲጨርስ የሚሞት ሲሆን ፍሬው ብቻ መሬት ውስጥ ተቀብሮ የሚቀር ነው:: የሌሎች ግን ግንዳቸው ወይም ስራቸው ተርፎ የሚቀር ነው::
የዚህ የአደይ አበባ ዝርያ ፍሬ አፍርቶ አትክልቱ ከሞተ በኋላ ፍሬው መሬት ተቀብሮ ከስድስት ወር እስከ ሁለት አመት ሊቆይ ይችላል:: ይህ ወቅትም የሽልብታ /የዶርማንሲ ፔሬድ/ ጊዜ ይባላል:: በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ፍሬው እንደገና ዕፅዋቱ እንዲበቅል ያደርጋል ማለት ነው::
አበባው አንዴ ካበበ በኋላ እንደፈካ ምድርን አስውቦ የሚቆየው ለረጅም ጊዜ አይደለም:: ቢበዛ ለሶስት ወራት ብቻ ጋራና ሸንተረሩን፤ ሜዳና ተራራውን በተስፋ ሰጪው ቢጫማ ቀለም አስውቦ ይቆይና ይጠፋል:: ይህም ሌላው የአደይ አበቦች መለያ ባህሪ ነው::
የኦሀዮ ዩኒቨርሲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን አደይ አበባ ጋራና ሸንተረሩን፤ ሜዳና ተራራውን ከማስጌጥ ያለፈ ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል:: አበባው በተለይ በአሩሲና በከፋ አካባቢ ጥቅም ላይ ይውላል፤በነዚህ አካባቢዎች የአደይ አበባ በስፋት ለደም ማቆሚያት እንደሚውል ተናግረዋል::
ፕሮፌሰሩ ከ30 አመት በፊት በኢትዮተያ ባደረጉት ጥናት የአደይ አበባ በተለይ ሴቶች ወልደው ደም እየፈሰሰ አልቆም ካላቸው ጨቅጭቀው ጭማቂውን እንዲጠጡ በሚደረግበት ጊዜ የሚፈሰውን ደም እንደ ሚያስቆምላቸው መስማታቸውን ተናግረዋል::ከዚህ በተጨማሪ ፀረ ተዋህስ /Anti- infction/ በመሆን እንደሚያገለግለም ጠቁመዋል::
ሌሎች አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም የአደይ አበባ ለስኳር በሽታና ለጭንቅላት ካንሰር ህክምና እንደሚውል ፍንጭ ሰጥተዋል:: ዩኮፒያ የተባለ አንድ በኢትዮጵያ የሚገኝ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከአደይ አበባ ክሬም አምርቶ ለገበያ ማቅረቡም ታውቋል::
ክሬሙ ወንዶች ፂማቸው ከተላጩ በኋላ ለማለስለሻነት የሚቀቡት ነው:: ሌላው ከዚህ በአበባ ለሴቶች የተሰራው ክሬም ደግሞ ለማዲያት መከካለያ(ማጥፊያነት) የሚውል መሆኑም ታውቋል::
ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙ የተለያዩ የአደይ አበባ ዝርያዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚውሉም መረጃዎች ይጠቁማሉ::የአበባው ዝርያ ዋና መገና እንደሆነች በሚነገርባት ሜክሲኮ ሴቶች ጨቅጭቀው ፊታቸውን በመቀባት ለውበት መጠበቂያነት ይገለገሉበታል:: ከዚህ በተጨማሪም ከአበባው ተጨምቆ የሚገኘውን ፈሳሽ ለልብስ ማቅለሚያነት ይጠቀሙበታል::
አደይ አበባዎች ከፍተኛ የሆነ ማር ለማምረት የሚውል ንጥረ ነገር በውስጣቸው አላቸው::በዚህም ምክንያት በማር ምንጭነቱ ይታወቃል::ታዲያ ንቦች ይህን ንጥረ ነገር በመቅሰም የሚሰሩት ማር ለምግብነት ለመድሃኒትነት እና ለሌሎችም በርካታ አገልግሎቶች ይውላል፡
 

 ********************************************************************************
መልካም አዲስ ዓመት
(አዲሱ አያሌው)
በኩር ጳጉሜ 4 ቀን 2011 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዘወትር ሰኞ የምትታተም  ጋዜጣ
https://www.dw.com/am/%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%8B%B0%E1%8B%AD-%E1%8A%A0%E1%89%A0%E1%89%A3-%E1%89%A3%E1%88%85%E1%88%AD%E1%8B%AB%E1%89%B5-%E1%8A%A5%E1%8A%93-%E1%8C%A5%E1%89%85%E1%88%9E%E1%89%B9/a-40495412
 

 

Thursday, March 19, 2020

ካርል ሄንዝ በም_"ሰዎች ለሰዎች"

🌻    ካርል ሄንዝ በም    🌻(1928-2006)

ካርል ሄንዝ በም (Karlheinz Böhm)

" ሰብአዊነት ዘር ቀለም ዝና ማንነት ቦታ እንደማይገድበው ማሳያ የሆኑ የሰዎች ለሰዎች የእርዳታ ድርጅት መስራች"
ካርል ሄንዝ በም ጀርመናዊ ሲሆኑ የተወለዱት መጋቢት 16 ቀን 1928 ዓ.ም ነው፡፡ታዋቂ ተዋናይ እና የመድረክ ሰው የነበሩት "የሰዎች ለሰዎች" ግብረሰናይ ድርጅት መስራች እና ሊቀመንበር ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ በረሃብና በድርቅ በተመታችበት ጊዜ ብዙ ድጋፍ ያደረጉ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡
ሰብአዊነት ዘር ቀለም ድንበር አይገድበውም

 ካርል ወደ እርዳታ ፊታቸውን ከማዞራቸው በፊት ከ45 በላይ የመድረክና የፊልም ስራዎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ካርል ሀይንስ ሲተውኑ ‘ሲሲ’(Sissi)

ካርል ሀይንስ ‘ሲሲ’(Sissi: Fateful Years of an Empress_1957, Sissi: The Young Empress_1956)፣ ‘ፎክስ ኤንድ ሂዝ ፍሬንድስ’(Fox and His Friends (Faustrecht der Freiheit_1975)
፣ ‘ላ ፓሎማ’(La Paloma_1959)፣ ‘ዘስቶው አዌይ’ እና ‘ካም ፍላይ ዊዝ ሚ’(Come Fly with Me_1963) ን ጨምሮ፤ በአሜሪካ፣በጀርመን፣ በኦስትሪያና በሌሎች አገሮች በተሰሩ 45 ያህል ፊልሞች ላይ በመተወን ችሎታቸውን ያስመሰከሩ ተዋናይ ነበሩ፡፡

ካርል ሄንዝ በም እና ባለቤታቸው አልማዝ በም 


በ1981 ዓም ይህንን ታዋቂነታቸውን ተጠቅመው ለበጎ አድራጎት ስራቸው በወቅቱ በጀርመን ቴሌቪዥን ቀርበው 1.2 ሚሊዮን የጀርመን ማርክ አሰባስበው "ሰዎች ለሰዎች" ግብረሰናይ ድርጅትን መሠረቱ፡፡ በ1982 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በሀረርጌ ክፍለ ሀገር በየረር ሸለቆ ባቢሌ ላይ በጦርነትና በርሃብ የተፈናቀሉትን በማቋቋም ስራቸውን ጀመሩ፡፡ ከዛም በብዙ ክፍለ ሀገራት በመዘዋወር በትምህርት፣ በውሃ ማስፋፋት፣ በጤና ተቋማት ግንባታ፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት የተቀናጀ ልማት በማስፋፋት በብዙ ሚሊዮን የማሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ታድገዋል፡፡

 በዚህም ዘርፈ ብዙ ተግባራቸው የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተገኙበት መርሀቤቴ ላይ በተካሄደው ዝግጅት የኢትዮጵያ ዜግነት አግኝተዋል (Mr. Böhm was made an honorary Ethiopian citizen in 2001.)፡፡
የኢትዮጵያ የክብር ዜግነት ሲሰጣቸው


በሀረር፣ በአዲስ አበባ፣ በመርሃቤቴና በደራ ጉንዶመስቀል እንዲሁም በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የመታሰቢያ ሀውልት ቆሞላቸዋል፡፡
                                     በአዲስ አበባ ከተማ የቆመላቸው የመታሰቢያ ሀውልት                                                                                 Menschen für Menschen Employees Commemorated Dr. Karheinz Böhm at Karl Square, 
Addis Ababa


"የጅማ ዩኒቨርስቲም በ1993 የክብር ዶክትሬት አበርክቶላቸዋል" AWARDING 21ST CENTURY HEROES OF HUMANITARIAN
ካርል ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ከአልማዝ ተሾመ ጋር ትዳር መስርተው ልጆች ያፈሩ ሲሆን ጡረታ በወጡም ጊዜ የድርጅታቸውን አመራር ያስተላለፉት ለባለቤታቸው ለአልማዝ በም ነበር፡፡

እኚህ ታላቅ ሰው በተለያዩ የኢትዮጵያ ገጠራማ ክልሎች የሠሯቸው ልማቶች እጅግ ሰፊ ናቸው።

Project areas


በኢትዮጵያ በርካታ ሰብዓዊ ስራዎችን በመስራት ውለታን ከውለታም በላይ መሆን እንደሚችል ያሳዩት የሰው ለሰው ድርጅት መሥራቹ ካርል ሄንዝ በም ለረዥም ጊዜ በህመም ሲሰቃዩ ቆይተው ግንቦት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በጀርመን ሳልበርግ ህይወታቸው ያለፈው፡፡ ታዋቂው ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ Karlheinz Böhm, Actor-Turned-Humanitarian, Dies at 86   ነበር ያላቸው።

ታላቁን ባለውለታችንን ካርል ሄንዝ በም ለሠሩት ሥራ እጅግ በጣም እናመሰግናለን ልንላቸው ይገባል ፡፡

===============================***==================================
ምንጭ:- Sheger FM 102.1 Radio ካርል ሄንዝ በም - Karlheinz Böhm -  ትዝታ ዘ አራዳ
             ካርል ሄንዝ በም - Karlheinz Böhm - ትዝታ ዘ አራዳ - ሸገር ሬድዮ
             https://www.sewasew.com/karlheinz-bo-hm
            https://www.ju.edu.et/?q=karlheinz-b%C3%B6hm