ከደራሲያን ዓምባ

Monday, March 1, 2021

የአድዋ ድል _ በእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)

 

እጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ)_አድዋ
♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪ 

የሰው ልጅ ክቡር
ሰው መሆን ክቡር
ሰው ሞቷል

ሰው ሊያድን

ሰውን ሲያከብር
በደግነት፣  

በፍቅር፣  

በክብር ተጠርቶ፣
በክብር ይሄዳል፥ ሰው ሊኖርሰው ሞቶ፤

♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪
የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ካጥንት፣
ስንት ወገን ወደቀ በነፃነት ምድር
ትናገር አድዋ፣ ትናገር ትመስክር፣
ትናገር አድዋ፣ ትናገር አገሬ፤
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ፤

 
♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪
በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር፣
በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን
ደሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን።

♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪
አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትናንት፣
መቼ ተነሱና የወዳደቁት፣
ምስጋና ለእነሱ ለአድዋ ጀግኖች፣
ለዛሬ ነፃነት ላበቁኝ ወገኖች፣

♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪
የጥቁር ድል አምባ፣ አድዋ
አፍሪካ፣ እምዬ ኢትዮጵያ
ተናገሪ
የድል ታሪክሽን አውሪ።
♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪

 አድዋ- ጂጂ

♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪

 


 

የእጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) ሰርክ ገዝፎ የሚንጥ፣ እሩቅ ግን ቅርብ ውብ ስሜት…. አድዋ!!

| ተስፋዬ እሸቱ (/ ፕሮፌሠር)

*******************



ከያኒ የአንጻር ጌታ ነው፡፡ የነበረውን፣የሰማውን፣ ያነበበውን የኖረውን ሁነትና እውነት ለመገልበጥ አይታትርም፡፡ ሰው አይቶት፣ ተገንዝቦ የኖረበትን ወይንም እየኖረበት ያለን እውነት አይደግምም፤ ከያኒ፡፡

ለዚህም ነው የከያኒ እውነት ሁሌም አንጻር (point of view) አለው የሚባለው፡፡ በጋራ ያየነውን ሀቅ፣ አምነን እየኖረበት ያለን እውነት፤ እሱ በወደደው፣ በፈለገው መንገድ ሌላ የሚተኮር፣ የሚወደድ፣ ግብ ይሰጠዋል፡፡ የግቡ ትልም ደግሞ አንጻር ነው፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ የከያኒ እውነት ትናንትን አጣቅሶ፣ ዛሬ እንድንኖርበት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ነገንም እንድንናፍቅ ያስገድደናል፡፡

ከያኒ ሲልቅ፣ ታሪክ ላይ ሌላ እውነት ፈልፍሎ፤ አውዱ ላይ ሌላ ሀቅ አብጅቶ በጉዳዩ እንድናተኩር፣ አተኩረንም ህይወትን እንድናጣጥም አድርጎ እያዋዛ፤ ረግቶ ከጠነዛ መንፈስ ይፈታናል፡፡

˝አይለወጥም፣ አይነካም ቅዱስ ታሪክ ነው˝ ብለን ከታሰርንበት፣ ሀቅ ብለን ካመለክነው አምልኮ አላቆ ሌላ መንገድ፣ ሌላ ስርየት ያጎናጽፈናል፡፡ የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) አድዋም ነገረ-መሰረቱ፣ ማጠንጠኛ ሀቁ ይሄው ነው፡፡ ሌላ ደግሞ፤ሌላ እውነት! ሌላ አድማስ! ገዝፎ የሚንጥ፤ እሩቅ ግን ደግሞ ቅርብ ውብ ስሜት፤ የጂጂ አድዋ!

የእጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) አድዋ፣ ስር እና መንፈሱ ድሮ ጥንት ተጉዞ፤ የሰው ልጅ ˝˝ ብሎ ሲፈጠር ከተሰጠው ጸጋና ክብር ይጀምራል፡፡ ˝የሰው ልጅ ክቡር፤ ሰው መሆን ክቡር…˝ እያለ እየተጎነጎነ፣ እየተስረቀረቀም፡፡ ሰውን በአምላኩ አምሳያ ፈጠረው የተባለውንም አገናዝባ፤ ˝ሰብዕ የዐቢ እምኩሉ ፍጥረት˝ ያለውን አስታውሳም ነው፡፡ ጂጂ አድዋን፣ ˝የሰው ልጅ ክቡር፣ ሰው መሆን ክቡር˝ ብላ አህዱ ያለችበት መንገድ ታሪከ-አድዋን ያየችበት፣ ሀቁን የተገነዘበችበት እና እንዲተኮር የፈለገችው ትርጓሜ ነው፡፡

የሰው ልጅ ትልቁ ጻጋ፣ ሰው ሆኖ የመፈጠር፣ ተፈጥሮም በክብር የመኖር ጸጋ ሲገፈፍ ሰው መሆን ˝አዲዎስነው ትላላች ጂጂ በአድዋ ውስጥ ስታስብ፤ ደግሞም ከሩቅ ስባ በምክንያት ስታመጣም፤ ስትመዝም፡፡ ታዲያ እጅጋየሁ ሽባባው ይህንን የመሰለ የእይታ አድማስ ይዛ ስትመጣ ንቡር ነቃሽም ነበረች ማለት ይቻላል፡፡

የሰው ልጅ ከተሰጠው ክብር አንሶ ሲወርድ፣ ረክሶ ግን ለዘለአለም እንዳይኖር፣ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መድህን ይሆን ዘንድ፣ አምላክ ሰው ሆኖ ሞቶ፣ ለሌሎች ምሳሌነትን የገለጸበት፤ "አንዱ፡ስለ፡ዅሉ፡ሞተ" እሷ በአድዋ ˝ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን…˝ ብላ አዛምዳዋለች፡፡ እናም የጅግጋየሁ ሽባባው አድዋ ጥንት፣ ድሮ የትየለሌን ከትልቁ መጽሀፍ፣ መጽሀፍ ቅዱስ አጣቅሷል ስል መነሻዬ ይሄው ነው፡፡

ይህንን ለሰው ልጅ ቤዛ የመሆንን አስተምህሮት፤ ለሰው መሞት፣ ለሰው ክብር መሰዋት፤ ከምንም በላይ ሰው ክብር መሆኑን መገንዘብ ነው የአድዋ አባቶቻችን በአፍ ሳይሆን በተግባር ሳያጎድሉ ከወኑት የምትለን ጂጂ፤ በአድዋ፡፡ የጂጂ ንቡር ጠቃሽነትም ወደር የማይገኝለትና ምክንያታዊ ሆኖ የቀረበው፣ በሙዚቃው ወስጥ ጀግኖች አባቶቻቻን ሰው ልጅ ክብር፣ ሰው መሆን ክቡር መሆኑን ተገንዝበውና አስገንዝበው እንዳለፉ አጽንዖት ሰጥታው ታልፋለች፡፡

ይህንን ከላይ የተወሰደ እና ለሰው ክብር ሲባል መሞት ትልቁ የፍቅር መገለጫ በዚህችው አገር፣ በአድዋ ተራራ ሲከወን ˝ በክብር ይሄዳል፣ ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ…˝ እያለች በድጋሚ፤ ግን ደግሞ በተለየ ገለጻ በደማቁ ከትባው ታልፋለች፤ በሙዚቃ- አድዋዋ፡፡

ቀጠል አድርጋም አባቶቻችን የህይወት፣ የመዳን፣ የፈውስ፣ የቤዛ ምልክቶች ናቸው ልትለን እና አድዋን ግዘፍ ልትሰጠው ስትፈልግ ˝ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት…˝ ስትለንም ተምሳሌትነቱ ክርስቶሳዊ፤ ሰማያዊ እንጂ ምድራዊስ አይደለም ብላ አጽንዖት ልትሰጥ የፈለገች ይመስላል፡፡ ይህ የአምላክን ድንቅ ፍቅር፣ አምላክን አባት፣ ሰውን ልጅ ያደረገ ኪዳን፣ አባቶቻቸን ˝ የሰው ልጅ ክቡር፤ ሰው መሆን ክቡር…˝ ብለው ስለከወኑት፤ ደግሞም ውድ ህይወታቸውን ሳይሰስቱ፣ በደግነት፣ በፍቅር፣ ሰጥተው ስላለፉ፤ ለዛሬ ሳይጓደል ለተገኘ ነጻነት ህያው ምስክር እንደሆኑ ምስክር ስትጠቅስም ˝ትናገር አድዋ፣ ትናገር ትመስክር፤ ትናገር አድዋ፣ ትናገር አገሬ…˝ እያለች ቋሚ እማኝ፤ ቋሚ የታሪክ ምሥክር ትጠራለች - ህያው አብነትነቱ በእኛ በልጆቻቸው ልቦና ውስጥ ህይወት ዘርቶ፤ ግዘፍ ነስቶ በዘላቂነት እንዲኖር!

 

የእጅጋየሁ ሽባባው አድዋ ትዕምርታዊ ተምሳሌቱ ክርስቶሳዊ እንደሆነ፤ ተመርጠው በተደጋጋሚ፤ ግን ደግሞ በተለያያ መንገድ ተሰድረው በመካነ ድምጿ የሚንቆረቆሩት ስንኞች ጉልህ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ስትጀመር ˝ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን…˝ ትለናለች፡፡ ˝ሰው ሊኖር ሰው ሞተ…˝ እያለች ትቀጥልናም ˝ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት…˝ ብላ ትሠልሳሰች፡፡ በእጅጋየሁ ሽባባው አድዋ ሰው በክብር ለሰው መድህን እንዲሆን የሞተው፤ ወራሪን ለመመከት፣ አገር ለመስራት፣ ቅኝ ግዛትን ለማውገዝ ወዘተ ለሚባል ታካችና ሰርክ ለምንሰማው ጉዳይም አይደለም፡፡

ጂጂም ˝ የሰው ልጅ ክቡር፤ ሰው መሆን ክቡር…˝ ብላ ጀምራ፣ አባቶቻችን የወደቁት ወራሪን ገጥሞ ለመጣል ነው ብትል የተነሳችበትን የዳጎሰና ፍጹም የሆነ የሀሳብ ልቀት የታየበትን አድማስ ያኮስስባት ነበር፡፡ እሷስ ምኗ ሞኝ፤ ወራሪ ምናምን የሚል ነገር አልወጣትም፡፡ ይልቅ የተነሳችበት ሀሳብ ይበልጥ ይጎለብት ዘንድ፤ የሰው ልጅ ሰውን በመውደድ፣ ሰው መሆን ክቡር መሆኑን በተግባር ሲገልጥ ሌላ የደረጀ ሀሳብ ባለቤት ይሆናል፡፡ እሱም ደረጃ ነጻነትን ይጎናጸፋል ትለናለች፤ቃሉን ˝ነጻነት˝ እየደጋጋመች፣ እኛ ዘንድ እንዲታተም፡፡

ነጻነትም ሰው ሆኖ ከመፈጠር ጋር የሚሰጥ እንጅ የማንም ችሮታን እንደማይጠይቅ፣ ጥንት አባቶቻቻን እንደተረዱት በጂጂ ሙዚቃ ውስጥ በጉልህ ተመልክቷል፡፡ በሙዚቃው፣ የጻነት ትርጓሜ ደግሞ ምንጩ የሰው ልጅ ክቡር እንደሆነ መረዳትና ለዚህም እንደክርስቶስ እራስን አሳልፎ መስጠት እንደሚያስፈልግ አስገንዝባ አልፋለች፤ እጅጋየሁ ሽባባው፡፡

እንደካባ የተጎናጸፈችውን ነጻነት፣ ˝በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር፤ በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን…˝ እያለች ታሽሞነሙናለች ፡፡ የእውነት ግን ማን እንደእሷ፣ ማን እንደህዝቧ ˝ሰው ልጅ ክቡር፤ ሰው መሆን ክቡር˝ በአግባቡ ተረድቶ፣ ድልን፣ ነጻነትን በቀን በቀን ይተነፍሳል? ኣባቶቾ፣ አባቶቻችን የፈጸሙት ገድል ክርስቶሳዊ ካልሆነ በስተቀር!

ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ የእጅጋየሁ ሽባባው አድዋ የትላንት በፊትን፣ ከትላንት ጋር ብቻ አስተሳስሮ ለማለፍ አልተጋም፡፡ ይልቅስ አድዋ ትላንትን ከዛሬ ጋር ሲያዛምድ፣ ሲሰፋ ይታያል፡፡ ˝አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትናንት….˝ እያለ፤ ከትናንት ሽቅብ ወደ ዛሬ እንድንደረድር እየፈለገ፡፡ በሁለት መንገድ፤ አንድም በኩራት፡፡….. ሁለትም በቁጭት፡፡

ከቁጭቱ ልጀምር፡፡ ከላይ ከክርስቶስ፣ እራስን ለሰው ልጅ አሳልፎ መስጠትን በወጉ ተምረውም ተግብረውም፣ አድዋ ላይ ህይወታቸውን ለሰው ልጅ ክብር የሰጡ፣ ˝ሰው መሆን ክቡር˝ ያሉ የጀግኖች አባቶቻችን ርዕይ ሜዳ ላይ ብቻ፣ በወሬ ብቻ ወድቆ መቅረቱ ጂጂን ያንገበገባት ይመስላል፡፡

በጂጂ አድዋ ጀግኖች አባቶቻቻን በክብር አላረፉም፡፡ የሚያሳርፉ ልጆች አላገኙም እና ቁጭቷን እንዲህ ትገልጸዋለች፡፡ ˝አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትላንት፤ መቸ ተነሱና የወዳደቁት…˝!

የወዳደቁት አልተነሱም፡፡ ጂጂ እውነት ያላት ይመስላል፤ ደግሞም እውነቷን ነው - እንደእኔ፡፡ በጂጂ ˝አድዋ˝ የተሰዉት ጀግኖች አባቶቻቻን በሰላም አላረፉም፡፡ በየጥሻው እንደወዳደቁ ናቸው፡፡ ይሄ ለጂጂ ጸጸት ነው፤ ውስጥ ድረስ ሰርስሮ የሚበላ ቁጭት! ትላንት ስለሰው ልጆች ክብር ˝ሰው መሆን ክቡር˝ ብለው የወደቁ አባቶች በነበሩባት አገር፣ ዛሬ ሰው እንደ ተራ ቁስ የሚቆጠርበት አገር ሲሆን፣ የአድዋ ኣባቶቻችን መንፈስ ወድቆ እንደቀረ ነው፤ እንደተሰበረ፡፡

ትላንት ˝በነጻ ምድር˝ ስለሰው ልጅ ክብር ሲባል ደምና አጥንቱን ከፍሎ አገሩን፣ ጦቢያን የአፍሪካ እና የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ቀንዲል እንድትሆን ያደረገ ጀግና በተፈጠረበት አገር፣ ዛሬ አገረ ኢትዮጵያ አገር-ተከታይ፤ ድህ፣ ጭቁን፣ ርሀብተኛ፣ ውዳቂ የምትባል አገር ስትሆን የወደቁት ኣባቶቻችን አጥንት ገና አልተሰበሰበም፤ በክብር፡፡ ህያው አገር፣ ነጻ አገር ለመፍጠር የወደቁ አባቶች በነበሩበት አገር፣ ዛሬ ˝ብሄር˝ በሚባል ጥብቆ ታንቀው፤ጎሳን ከአገር፣ ያውም ኢትዮጵያን ከምታክል ታላቅ አገር የሚያስበልጡ ህዝቦች አገር ሆንና አረፍነው፡፡

እናስ?... ጂጂ ˝መቸ ተነሱና የወዳደቁት˝ ብትል ሀቅ አላት፡፡ ትላንት ሰው የሚባል አርማ አንስተው፣ ሰው በሚባል የወል ስም ለሰው የሞቱ አባቶች በነገሱበት አገር፣ ዛሬ ˝አድዋ ላይ የተታኮሰው ቀኝ አዝማች እከሌ፣ የወደቀው ደጃዝማች እከሌ እኮ ብሄሩ እንትን ነው…..የኛ ጀግና ሳይሆን የኔ ዘር ብቻ ጀግና ነው….˝ በሚባልበት አገር፣ የሞቱትን አላሰረፈምና፤ ተከታይም አላፈሩምና ጂጂ ˝አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትላንት፤ መቼ ተነሱና የወዳደቁት…˝ ብትል፤ አብዝታም ብትቆጭ የሚጨበጥ አመክንዮ አላት፡፡

በሚስረቀረቅ፤ ግን ደግሞ በሚንገበገብ ድምጿም ˝ተናገሪ˝ ትላላች፤ አድዋ አፍ ያለት ይመስል፡፡ ˝ተናገሪ˝ ጦቢያ ትላላች፣ አገር ያልታዘበች ይመስል፡፡ ትናገር ትላለች ትውልድ ዠሮ ያለው ይመስል፡፡ ምንታድርግ፤ ጂጂ ብትበሽቅ ነውና ደግ አደረግሽ እላላሁ፤ እኔ ደግሞ፡፡
ከያኒ ሲበቃ እንደ ጂጂ ነው፤ ከትላንት ወዲያን ከትላንት ማዛመድ ብቻ ሳይሆን ትላንት ላይ ቆሞ ተንብዮ፣ መሲህ ሆኖ የአገር ጌጥ ይሆናል፤ ሲመጥቅ፡፡

ሌላው ጂጂ፣ ˝አድዋ ዛሬ ናት፣ አድዋ ትላንት˝ ስትል ያዛመደችው እውነተኛ ከሆኑት የዛሬ የአድዋ ልጆ ጋር ነው፡፡ ሰውን በሰውነቱ ለሚወዱ፣ አገራቸው ነጻ አገር እንደሆነች ለሚያሰቡ፣ ˝እኔ ኢትዮጵያ ነኝ˝ ለሚሉ፤ የሰው ህመም ህመማቸው፣ ስቃዩ ስቃያቸው ለሆነባቸው፤ አገራቸው የምንግዜም ጌጣቸው የሆነችላቸው የዛሬ የአድዋ እውነተኛ ልጆችን እጅጋየሁ ሽባባው በተቃራኒው እንዲህ ትላቸዋለች - እሷኑ ራሷኑም ጨምራ፡በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር፤ በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን!…˝፡ ከነዚህኞቹ ወገን ያድረገኝ - እኔን፡፡

በመጨረሻም፤ ራስን ለሰው ልጆች አሰልፎ የመስጠትን ክርስቶሳዊ አስተምህሮ ከአድዋ ጀግኖች፤ የአድዋ ጀግኖችን ደግሞ ከዛሬዎቹ አውነተኞቹ የአድዋ ልጆችና ጋዜጣ-ውልድ ጎሳዊያን ጋር የሰፋችበት መንገድ እጅን በአፍ አስጭኖ ˝አጀብየሚያሰኝ ነውና ጂጂን፡እድሜና ጤና ይስጥሽ፤ ˝አድዋ˝ የተጠበበው አእምሮሽ ብርሀኑን አይጣ፡፡˝ ልላት እወዳለሁ፡፡ እኔው ራሴውም ደግሞ ስለእሷው ˝አሜን˝ብልላት ምን ይለኛል?…አሜን!!


 

************************* 

አድዋ – የሰው ልጅ ክቡር! _ዮሐንስ ሞላ

************************* 

በአድዋ- የደመቁ ጥበበኞች

************************

የጂጂ ቃለ መጠይቅ - Ejigayehu Shibabaw (GiGi) Interview 


እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ከመዓዛ ብሩ ቆየት ያለ ጨዋታ Sheger Fm Yechewata Engida - Ejigayehu Shibabaw (Gigi) Interview With Meaza Birru


ናፋቂዋ ተናፋቂ፤ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)_ፋና ቴሌቪዥን