ከደራሲያን ዓምባ

Monday, June 27, 2022

ጎዳናው ይገርማል?! ___በረከት በላይነህ



ጎዳናው ይገርማል?!

በረከት በላይነህ _ጋዜጠኛ፣ ገጣሚና ደራሲ
************************
ይገርማል መንገዱ
እግረኛው ይገርማል

ሸራ ጫማ ባ'ይነት
በነጫጭ ካልሲ
በሲኪኒ ሱሪ
ከመምህሩ ጋራ
አይስክሬም ሚልስ
የሀይስኩል ተማሪ
.
ፀባይኛ ወጣት
ጃንቦ ተከልሎ
በምርቃና ሆኖ
ሀሳብ የሚፈትል
አንዲት ሙ......ደኛ እናት
በ'ድሜ ከልጆቼ አንሳለው የምትል
ፒዛውን የሚገምጥ
ጭማቂ የሚመጥ
አራዳ አባወራ
በሚስቱ ትከሻ
በልጆቹ ምላስ
ቅምጥ የሚጣራ
.
አንድ ፍሬ ሴቶች
በተገዛ ቅንድብ
በተገዛ ፀጉር በተገዛ ጥፍር
በውሰት ወዘና የተብለጨለጩ
ማኪያቶ ከበው
ለውስኪ ሚንጫጩ
ጅናም ጅንሳም ወንዶች በሴቶች ጫጫታ የሚቁለጨለጩ
.
ይገርማል ጎዳናው ይገርማል መንገዱ....
.
ድንቡሽቡሽ ህፃናት
በቶም ኤንድ ጄሪ ሱስ
ቀልባቸው የከሳ
በአይፎኑ አጮልቆ
ያንጀሊናን ከንፈር የሚስም ጎረምሳ
.
ቀውጢ ዳያስፖራ
.
የሎቲው የቁምጣው የቲሸርቱ ጥለት የተንዘረፈፈው
አማርኛ ሲሸሽ "what's happen" የጠለፈው
.
ነቄ ብላቴና
.
ከዮፍታዬ ቀዬ
ካ'ዲስ አለማየሁ
ከመዝገቡ መንደር
የአዲስ አ'ባ ጥሪ
በቁምጣ ያበረረው
ከቅኔ ተጣልቶ
ከግዕዝ ተኳርፎ ሎተሪ ሚያዞረው
.
ፀዴ ብላቴና
.
ከባላገር ዘመን
ከጨለማ ዘመን
ወደ ብርሃን ጥግ ተሸጋገርኩ ብሎ
በሸንኮራ ምርኩዝ ከተማ ሚያካልል መቋሚያውን ጥሎ
ነብሱ እየሰለለች
በከተሜነት ወግ ባ'ራዳነት ልምሻ
ሲያዘግም የሚውል
ሊስትሮውን ጭኖ በታቦት ትከሻ
.
ፎቆቹ
.
በመስታወት ቁመት በቆርቆሮ ገፆች
ባ'ልሙኒየም ጥራዝ የተብረቀረቁ
የጌቶቻቸውን እድሜ ሚያሳብቁ
ሁሉም........ ሁሉም......ሁሉም ጥግ ናቸው
ለወደቀ ወገን ይራራል ልባቸው
.
ሁሉም
...... ሁሉም
.
ከዘለለት ጥድፊያ
ከሰርክ ውጣ ውረድ በተረፈች አንጀት
ለወደቀ ወገን ምርኩዝ ማበጃጀት
ሁሉም...... ሁሉም ይችላሉ
ስለ'ግዚአር ላለ ይመፀውታሉ
.
እኔ ግን........ እኔ ግን .........ቆጥራለው
የ'ድሜ ክቡር ጀንበር
በጎዳና ፅልመት ሲዋጥ አስተውላለው
ጡረታ መንገድ ዳር ሲከፈን አያለው
.
ቆጥራለው.....ቆጥራለው
.
ቆጥራለው አዛውንት
በየአቀበቱ በየቁልቁለቱ
ማረፊያ ፍለጋ የሚንከራተቱ
ቆጥራለው አዛውንት ከልጆቻቸው ፊት
የልመና መዝገብ የገለጡ አሮጊት
ቆጥራለው በየመንገዱ ዳር
እርጅና ሙሽራው ለምፅዋት ሲዳር
ቆጥራለው በየሸንተረሩ በየተፋሰሱ
አቀርቅሮ ሲያዘግም እርጅና ሞገሱ
ቆጥራለው በ'ያደባባዩ
የሽማግሌ አይኖች የልጅ ፊት እያዩ
ቆጥራለው በየሰርጣሰርጡ
በልመና ጉልበት ከሞት ሲፋጠጡ
የ'ርጅና መዳፎች እሾህ ሲጨብጡ
.
ቆጥሬ..... ቆጥሬ.......ቆጥሬ
በለማኝ አዛውንት ብዛት ተሳክሬ
የማሰንበቻ ስንቅ ከኪሴ ቆንጥሬ
ያፅድቆቴን ዋጋ በሳንቲም መንዝሬ
ባ'ዛውንት ምርቃት ከሀገር ከቀዬው ትርፌን ሳመሳስል
በጎዳናው ቀለም ፃድቅ መልኬን ስስል
ጎልቶ ሚታየኝ ግን የሚያሳፍር ምስል
በቀላል ጥያቄ የነተበ ምስል
.
ጥያቄ
.
የዲጄ ኳኳታ የደናሽ ጋጋታ
የድራፍት እርካታ ያ'ረቄ ድንፋታ
ባጣበበው መንገድ
እንደምን ይቻላል
ላ'ያት ሳንቲም ሰጥቶ በ'ርካታ መራመድ?
.
ለወጣት ሹክሹክታ ለገደል ዝምታ
ላስመሳይ ጫጫታ ላድርባይ እሪታ
በተሰራ መንገድ
እውነት ቀላል ነው ወይ
ላ'ያት ሳንቲም ሰቶ በ'ርካታ መራመድ?
.
ለቡቲክ ሰልፈኛ ለካፌ 'ድምተኛ
ለውስኪ ጭሰኛ ለበርገር ምርኮኛ
በተሰራ መንገድ
እንደምን ይቻላል
ላ'ያት ሳንቲም ሰቶ በ'ርካታ መራመድ?
.
አያት....አያት...አያትነት ማለት
በደማቅ አሻራ የሸመኑት ጥለት
ለተራኪ እድሜ የተሰጠ አንደበት
ባ'ባት በ'ናት ፅናት የማይደክም ጉልበት
በልጅ ልጅ መነፅር የማያረጅ ውበት
በልጅ ልጆች ጥበብ የሚታደስ እውቀት
.....................................የሚታደስ እውነት
አያት ሆኑ ማለት
ድርብ አባትነት
ድርብ እናትነት
.
በተለይ እዚህማ.......
በዚህች አይነት ሀገር
ጎጆዋን ላቆመች
በተጋድሎ ካስማ
ባርበኝነት ማገር
በዚህች አይነት ሀገር
ጥያቄና መልሷን
ባ'ዛን በቅዳሴ በምትሰራ መንደር
በዱአ በፀሎት
በምናኔ ምርኩዝ በከረመች ሰፈር
የአያትነት ዋጋው በልኩ ቢሰፈር
ለሳንቲም ምርቃት ባልተሻማን ነበር!
.
ታሪክ በመዳፉ ስላደላደለው
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንጉስ አያት አለው
የልጅ ልጆች ስባት ባያመነምነው
ያያቶቻችን መልክ ሁሌም አንድ አይነት ነው
.
እላለው... እላለው....
.
የልጆች ምፅዋት ያ'ያቶች ልመና
ያ'ባቶች ግርግር በሞላው ጎዳና
መንገዱ አይልቅም
ጎዳናው አያልቅም
ይሰፋል ይረዝማል ይሄዳል ይጓዛል
እግረኛው ሞኝ ነው
ሳንቲሙን ዘርዝሮ
ከወደቁ አዛውንት ምርቃት ይገዛል
.
መንገዱ ያስፈራል
መንገዱ ይጨንቃል
ልጆች ሳቅ ሲያንቃቸው
አያት እምባ ይጨምቃል
መንገዱ ያሰጋል መንገዱ ያረጃል
ከዘናጭ ልጆች ጎን እርዛት ያዘለ አያት ይወለዳል
.
ሰጪ ካለቀሰ ተበዳሪ ስቆ
ጌታ ከለመነ አማኙ 'ግር ወድቆ
ልዑል ከዘመረ ንጉሱ ተዋርዶ
ገፁ ተመሳቅሎ ሽፋኑ ካማረ
ወለሉ ተንቆ ምንጣፍ ከከበረ
ባ'ገርኛ ስሌት ማነው ያልከሰረ?
.
እላለው........እላለው
.
ከየጎዳናው ገፅ ጥያቄ አነሳለው
ጥያቄ እጥላለው
እርጅና ለማምሻው ጎዳናን ካመነ
አያት ከልጅ ልጁ ሳንቲም ከለመነ
ባገርኛ ስሌት ማነው ያልመከነ?
.
በ'ግዚኦታ ዘመን በምዕላ ዘመን
እመንገድ ዳር ወድቆ ትራፊ መለመን
በጥሞና ዘመን የሚያስቡት ማጣት
በማውረሻ እድሜ የሚሰጡት ማጣት
በማልበሻ ዘመን በ'ርዛት መቀጣት
በለጋሽነት ወቅት በማጉረሻ ዘመን
በጥማት መገረፍ በርሀብ መመንመን
ከሆነ እጣችን
ይጠየቅ ትርጉሙ የልጅነታችን
ይፈተሽ መንገዱ የልጅ ልጆቻችን

ግድ የለም እንመን

እንመን

በሰውኛ ስሌት ውጤቱ ሲሰራ
ትውልድ ያደኸያል ያያቶች ኪሳራ
በልጅ ልጆች ዓለም
እንደጉድ ቢደለቅ ቢዘመር ቢዘፈን
አባት ይወራጫል ባ'ያቶች መታፈን
.
አባት ሆይ
.
ለልጆችህ ርዕዮት
ትላንቱን የረሳ ተስፋ ሲደራረት
ህልሜ ነው ይልሀል ያ'ያቶቹ ቅዠት
ከልጅህ አንደበት
ቋንቋ እንደዶፍ ቢዘንብ
ትርጉም ቢንፎለፎል ሺ ቃላት ቢጎርፍም
የልጅ ልጅ አግባቢ ግማሽ ገፅ አይፅፍም
ከልጆችህ ባህር
አሳ የሚያጠግቡ ለአሳ ሚስማሙ
እፅዋት ተክሎች
እንደጉድ ቢራቡ እንደጉድ ቢያብቡ
ገበታው አይሞላም ተቀዷል መረቡ
.
ግድ የለም እንመን........እንመን
.
የስኬት ክብደቱ
የምቾት አይነቱ
የነገ ውበቱ ባሻው ቋት ቢለካ
በምንም ቢሰፈር ባሻው ቃል ቢነገር
ጀግና ልጅ አትወልድም
አያቶቿን ገድላ የምትሸልል ሀገር
.
ከፎቆቹ ጥላ....
ከያስፓልቱ ገላ ሲታተም ድምቀቴ
በመስታወት አጀብ ሲጠገን ጉልበቴ
ይኸው አነበብኩት
አያቶቼ ፊት ላይ ተፅፏል ሽንፈቴ
በመኪና ብዛት
በመስታወት አይነት ሲለካ ፍጥነቴ
በግንብ አጥር መአት
በፎቆች ጋጋታ ሲሰላ ስኬቴ
ይኸው ይታየኛል
አያቴ ገፅ ላይ ተስሏል ውድቀቴ

ተስሏል ሽንፈቴ!

።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።