ከደራሲያን ዓምባ

Tuesday, December 24, 2013

የእንግሊዝኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላት አዘጋጅ

                         ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ

                                  (እንግሊዝኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላት አዘጋጅ) አረፉ፡፡ 
                         / ነሐሴ 27 ቀን 1922 ዓ.ም.--- ታኅሣሥ 10 ቀን 2006 ዓ.ም./

 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ) ለ33 ዓመታት ያገለገሉትና በተለያዩ መጽሐፎቻቸው የእንግሊዝኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላትን ጨምሮ ታዋቂ የሆኑት ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ በ84 ዓመታቸው አረፉ::
ከቅርብ ዓመት ወዲህ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ሕክምናቸውን ሲከታተሉ የነበሩት ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ታኅሣሥ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ነው::


የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር የሳይንትፊክ ቡድን ዳይሬክተር ሆነው ለአንድ ዓመት (1954-55) ያገለገሉት ዶ/ር አምሳሉ፣ ከ1955 ዓ.ም. ጀምሮ በጡረታ እስከተገለሉበት እስከ 1985 ዓ.ም. ድረስ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲ ከሌክቸረርነት እስከ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማገልገላቸውን ገጸ ታሪካቸው ያመለክታል:: በተለይ በግእዝ፣ በአማርኛና በዓረብኛ ቋንቋዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክን በማስተማር ይታወቃሉ::
የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ሊቀመንበር፣ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም ዲን፣ የኢትዮጵያ
ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ የቦርድ አባልም ሆነው ሠርተዋል:: አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1997 ዓ.ም. የፊሎሎጂ (ጥንታዊ ጽሑፎች ጥናት) ትምህርት ክፍል ሲከፈት በድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር ስለኢትዮጵያ ፊሎሎጂ፣ ስለግእዝና ዓረብኛ መዋቅር በኮንትራት አስተምረዋል::
ዶ/ር አምሳሉን ስመጥር ካደረጓቸውና ካበረከቷቸው ትምህርታዊ የሕትመት ውጤቶች መካከል 


*‹‹እንግሊዝኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት›› (ከጂ.ፒ. ሞስባክ ጋር /1966 ዓ.ም.)፣ 
*‹‹የአማርኛ ፈሊጣዊ አነጋገሮች›› (ከዳኛቸው ወርቁ ጋር/1979 ዓ.ም.) 
*‹‹የእንግሊዝኛና አማርኛ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት›› (ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ ጋር) 
*‹‹ጥሩ የአማርኛ ድርሰት እንዴት ያለ ነው?››  (ከደምሴ ማናህሎት ጋር/1989 ዓ.ም.)፣ 
*‹‹አጭር የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ›› (ያልታተመ)፣
*‹‹አማርኛ-ዓረብኛ መዝገበ ቃላት›› (ከሙኒር አብራር ጋር/1999 ዓ.ም.)፣ 

*‹‹ግዕዝ መማሪያ መጽሐፍ Ge’ez Textbook›› (2003 ዓ.ም.)፣ 
‹‹የአማርኛና ሞክሼ ሆሄያት ጠንቅቆ ያለመጻፍ ችግርና መፍትሔ›› (2002 ዓ.ም.)፣ 
 በጀርመን ሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ በታተሙት ተከታታይ 
*‹‹ኢንሳይክሎፔዲያ ኢትዮፒካ››
እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበዋል::
በቀድሞው አጠራር በወሎ ጠቅላይ ግዛት ደሴ ከተማ
ነሐሴ 27 ቀን 1922 ዓ.ም. የተወለዱት ዶ/ር አምሳሉ፣ ከቄስ ትምህርት ቤት በኋላ መደበኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከካይሮ ዩኒቨርሲቲ በነገረ መለኮት (ባችለር ኦፍ ዲቪኒቲ)፣ እንዲሁም ከካይሮው አሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ባችለር ኦፍ አርት በተመሳሳይ ዓመት በ1949 ዓ.ም. አግኝተዋል::
የአማርኛ፣ ዓረብኛ፣ እንግሊዝኛና ጀርመንኛ ቋንቋዎች አዋቂ የነበሩት ዶ/ር አምሳሉ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን
ከጀርመን ቱቢንግ ዩኒቨርሲቲ በ1954 ዓ.ም. ሲያጠናቅቁ፣ የመመረቂያ ድርሳናቸውን (ዲዘርቴሽን) የሠሩት በኦገስት ዲልማን የግእዝ መዝገበ ቃላት ላይ ነው::
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል አስተባባሪው ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣
የዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ (ታኅሣሥ 13 ቀን 2006 ዓ.ም.) እኩለ ቀን (6 ሰዓት) በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል::

*************************************
ምንጭ:--http://www.ethiopianreporter.com/

Thursday, December 19, 2013

ዋናው ጤና

የእንቅልፍ ጥቅሞች

 በቂ እንቅልፍ አግኝተው ሲነሱ የሚሰማ የመንፈስ እርጋታ እና ሰላም በሌላ በምንም ሊተካ የማይችል ነው። የሰው ልጅ በቀን ውስጥ ከ6-8 ሰአት የሚሆነውን ግዜ በእንቅልፍ ማሳለፍ እንዳለበት ተደጋግሞ ይነገራል። እንቅልፍ ሰውነታችን እና አእምሮአችን የሚያርፍበት የጤናማ ህይወት አካል እንደሆነ የሚያስረግጡት ባለሙያዎች በቂ እንቅልፍ በመተኛት የሚገኙ ጥቅሞችን ዘርዝረዋል።

  • የማስታወስ ችሎታን ማዳበር :- ተኝተን ለምን ህልም እንደምናይ ባለሙያዎች እስካሁን ያልደረሱበት ቢሆንም በእንቅልፍ ግዜ አእምሮአችን በውስጡ የያዘውን መረጃ የማሰባሰብ እና የማስተካከል ስራ ይሰራል። ፋይሎችን ቦታ ቦታ እንደማስያዝ ማለት ነው። በዚህ ግዜ ነው እንግዴ ነገሮችን ማስታወስ አለማስታወሳችን የሚወሰነው።
  • ረጅም እድሜ ለመኖር :- የልባችንን አሰራር በማጎልበት ፣ ሰውነት ውስጥ ያለ የኬሚካል ብዛት በማመጣጠን እና አጠቃላይ ህይወታችንን በጥሩ መልኩ በመጨመር እድሜን ከእንቅልፍ ጋር ያጣጥሙት።
  • የፈጠራ ችሎታን ማሻሻል :- ድርሰት ለመጻፍ ብዕሮን ከማንሳትዎ በፊት ወይም ስዕል ለመሳል ብሩሽ ከመጨበጥዎ በፊት ጥሩ እንቅልፍ ቢያገኙ ይመረጣል።
  • ንቃትን መጨመር :- በቂ እንቅልፍ አለመተኛት እንዴት እንደሚያንገላጅጅ ያቁታል መቼም።
  • ጥሩ የሰውነት ክብደት :- ክብደት ለመቀነስ የምግብ ቁጥጥር ወይም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ መጀመር ካሰቡ በቂ እንቅልፍ ማግኝተትንም ከሚደረጉ ነገሮች ዝርዝር ውስጥ ያስገቡ።
  • ጭንቀትን መቀነስ :- በዚህ ወከባ በበዛበት ውስብስብ አለም ውስጥ በእንቅልፍ በሚገኝ እርጋታ ጭንቀትዎን ይቀንሱ።
  • ሰውነትን መጠገን :- ሰውነታችን በእንቅልፍ ግዜ ብዙ ፕሮቲኖችን በማምረት የተጎዱ ሴሎችን ይጠግናል።
****************************************************
ምንጭ:--http://thearadaonline.com

 

ፈገግታን እንደ ፈውስ

ከልብ ከሆነ የጥርጣሬን በረዶ ያቀልጣል። ለዓመታት ሲከማች የኖረ ጭፍን ጥላቻን ያስወግዳል። በእምነት ማጣት ስነልቦናዊ ፍራቻን አሳድሮ በጥርጣሬ ዓይን ያስተያይ የነበረን ልብ ያለሰልሳል። ብዙዎቹ እፎይታና ደስታ እንዲያገኙ ያደርጋል።
“ገብቶኛል፤ ችግር የለም” የሚል መልዕክት ያስተላልፋል። “ጓደኛ ልንሆን እንደምንችል ይሰማኛል” የሚል ግብዣ ያቀርባል። “ፈገግታ!’’
“ፈገግታ” ምንድነው? መዝገበ ቃላት ‘መደሰትን ወይም መስማማትን ለመግለጽ ከንፈር ሲሸሽና በመጠኑ ጥርስ ሲገለጥ በፊት ላይ የሚታይ ሁኔታ’ እንደሆነ አድርገው ይፈቱታል። ሞቅ ያለ ፈገግታ ለማሳየት ምሥጢሩ ይኸው ነው። ፈገግታ አንድ ሰው ያለ አንደበት ስሜቱን የሚገልጽበት ወይም ከሌላው ሰው ጋር ልብ ለልብ የሚግባባበት መንገድ ነው። እርግጥ ነው ፈገግታ ንቀትን ወይም ጥላቻን ወይም ንዴትን ሊገልጽ ይችላል።
በርግጥ ፈገግታ ማሳየት ወይም አለማየት ይህንን ያህል ለውጥ ያመጣልን? አንድ ሰው ፈገግታ ሲያሳይ ደስ የተሰኛችሁለትን ወይም ዘና ያላችሁበትን ጊዜ አስታወሱ፤ ወይም ደግሞ ሰዎች ፈገግታ ሲነፍጓችሁ የሚጨንቃችሁን ጊዜ ልብ በሉ። አዎ! ፈገግታ ማሳየት ወይም አለማሳየት ልዩነት ያመጣል። በፈገግታ ሰጪውም በተቀባዩም ላይ ተፅዓኖ ያሳድራል።
ሞቅ ያለ ፈገግታ ከውጥረት ተንፈስ ለማለት ሊረዳ ይችላል። ፈገግታ “በፕሬዠር ኩከር” ላይ ከምትገኝ ማስተንፈሻ ባልቦላ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ውጥረት ወይም ብስጭትን አንዲሁም አእምሮአችን የተጨነቀበትን ሁኔታ ለማቅለልና ችግሮቻችንን ለመቋቋም ሊረዳን ይችላል።
ሳንድራ የተባለችው ወጣት ብዙውን ጊዜ ሰዎች ዝም ብለው እንደሚመለከቷት አስተዋለች። እርሷ አትኩራ ስታያቸው ደግሞ ቶሎ ብለው ዓይናቸውን ከእርሷ ላይ ስለሚነቅሉ የሚያሽሟጥጧት እየመሰላት ጠንካራው ስነልቦናዋ እየተሸረሸረ ሲሄድ ይታወቃት ነበር። አንድ ቀን አንዲት ጓደኛዋ ሰዎች ሲያይዋት ፈገግ እንድትል ሐሳብ አቀረበችላት።
ሳንድራ ይህንን ሀሳብ ለሁለት ሳምንታት በተግባር አዋለችው። በአፀፋው ሌሎችም ፈገግ ሲሉላትና ምላሽ ሲሰጡዋት ተገረመች፤ ውጥረቱም ለቀቃት። “ሕይወት የበለጠ አስደሳች ሆነልኝ” በማለት ተናግራለች።
ፈገግታ በሌሎች ፊት ዘና እንድንልና ይበልጥ ተግባቢ እንድንሆን እንደሚረዳ የስነልቦና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ፈገግታ በአንድ ሰው ስሜት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። አንድ ሰው ጥሩ ስሜት እንዲሰማውም ያደርጋል። ለአካላዊ ጤናም ጥሩ መሆኑን ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ። ረጅም ጊዜ የቆየ ውጥረትና ጭንቀት የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም እንደሚያዳክሙ ብዙ ጥናቶች ያመለክታሉ። ይሁን አንጂ ሳቅ በአንፃሩ የሰውነታትንን በሽታ የመከላከል አቅም ሊያጠናክር እንደሚችል ተመራማሪዎቹ ያስረዳሉ።
አንድ ምክር የሚሰጥ ሰው ምን ዓይነት ፊት ቢያሳየን እንመርጣለን። የንዴት፤ የቁጣ፤ ፊት የመንሳት ወይም ጥላቻን የሚያስተላልፍ ፊት እያሳየን ቢሆን ምክሩን እንዴት ልንቀበለው እንደምንችል መገመት አያዳግትም።
በሌላ በኩል ምክር የሚሰጠን ሰው ወዳጅነት የተላበሰ ፈገግታ ቢኖረው ይበልጥ ዘና እንድንልና ምክሩን በደስታ እንድንቀበል ያደርግናል። ታዲያ ፈገግታ ውጥረትና ጭንቀት በነገሰበት ወቅት አለመግባባቶችን ሊቀንስ የሚያስችል ተጽዕኖ አለው።
ብዙዎቻችን እንደ ተዋንያን እነርሱ በፈለጉት ጊዜ ፈገግታ ማሳየት እንደሚችሉት ለመሆን ወይም ለመምሰል አንፈልግም። ፈገግታችን ተፈጥሮአዊና ልባዊ እንዲሆን እንፈልጋለን።
አንድ የስነ ልቦና ባለሙያ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥተዋል። “ዘና ብላችሁ ከልብ ፈገግ ማለታችሁ አስፈላጊ ነው። ይህ ካልሆነ የምታሳዩት ፈገግታ የጥርስ ፈገግታ ብቻ እንጂ ልባዊ አይደለም”።
ፈገግታ የውስጥ ስሜችንን ያለ ንግግር የምናሳይበት መንገድ እንደሆነ ከአስተዋልን የምንናገረው “በልብ ሞልቶ የተረፈውን” እንደሆነና መልካም ነገር የሚወጣው “ከመልካም መዝገብ” ውስጥ እንደሆነ ካወቅን ፈገግታችን ከውስጥ ስሜታችን ጋር በቀጥታ የተያያዘ እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል።
በልባችን ውስጥ ያለው ነገር ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ በንግግራችንና በድርጊታችን ብቻ ሳይሆን በፊታችንም ላይ መገለጡ የማይቀር ነው። ስለሌሎች ሰዎች ያለን አስተሳሰብ በፊታችን ላይ በግልጽ ይነባበል። የቤተሰቦቻችንን አባላት፤ በአካባቢያችን የሚኖሩ ሰዎችና የቅርብ ወዳጆቻችን ከልባችን በምናሳያቸው ፈገግታ ቀረቤታቸው የጠነከረ ይሆናል።
ለሰዎች የምናሳየው ፈገግታ ጥሩነት፤ ምህረትና ደግነት ከሞላው ልብ የሚወጣ ልባዊ ፈገግታ ይሆናል። ዓይናችን ብሩህ ይሆናል፤ ሌሎችም ፈገግታችን ከልብ እንደሆነ ይገነዘባሉ።
አንዳንድ ሰዎች በአስተዳዳጋቸው ወይም ያደጉበት አካባቢ ባሳደረባቸው ተፅዕኖ ምክንያት እንደ ሌሎች ፈገግታ ማሳየት ቀላል ላይሆንላቸው እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። ለሰዎች ጥሩ ስሜት ያላቸው ቢሆንም እንኳ ፈገግታ ማሳየት ይቸግራቸዋል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ጃፖናውያን ወንዶች በሌሎች ፊት ረጋ ያሉና ዝምተኛ እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ የተነሳ ለማያውቋቸው ሰዎች ፈገግታ የማሳየት ልማድ የላቸውም።
አንዳንድ ግለሰቦች በተፈጥሮአቸው ዓይን አፋር ሊሆኑና ለሌሎች ፈገግታ ማሳየት ሊከብዳቸው ይችላል። ስለዚህ ሰዎችን በፈገግታቸው መጠን ወይም ብዛት መገመት አይኖርብንም። አንዱ ከሌላው እንደሚለይ ሁሉ ጠባያቸውም ሆነ ከሰዎች ጋር የሚግባቡበት መንገድ ይለያያል።
የሆነ ሆኖ ለሰዎች ፈገግታ የማሳየት ችግር ካለብን ለምን ለማሻሻል ጥረት አናደርግም? መልካምን ነገር ማድረግ ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ ፈገግታ ማሳየት ሲሆን፤ ይህ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር አይደለም።
     ፈገግታን በተመለከተ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚናገሩት “ከሰዎች ጋር ጤናማ የህይወት መስተጋብርን ይፈጥርልናል። በጭንቀትና በውጥረት በተያዝንበት ወቅት እፎይታን ይሰጠናል። ምንም ይሁን ምን ግን በጐ አመለካከታችን የሚያስከፍለን ዋጋ የለም፤ በጐ ከማሰብ በስተቀር” በማለት የሥነልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

*************************************


Monday, December 16, 2013

ከመጽሃፍት ዓለም

 ሽልንጌን!  ሽልንጌን!  ሽልንጌን!
ፋጤ ወጂን ዴማ
የቀድሞው ስምንተኛ ክፍል የአማርኛ መማሪያ መጽሐፍ
**********************************************

ብርቱኳኗንና መንደሪኗን ይዛ ወደ መንገደኞቹ ባቡር ተጠግታለች:: በጀርባዋ ያዘለችው ሕፃንም “እምቢየው ወደ ቤት እንሂድ፤ እሪ…” እያለ ይነጫነጭባታል::
የእንጀራ ነገር ነውና ይህን የያዘችውን ፍራፍሬ ሳትሸጥ የሕፃን ልጇን ጉሮሮ መዝጋት አትችልም፤ በአንድ እጇ በጀርባዋ ያዘለችውን ሕፃን እያባበለች በሌላ እጇ 
ደግሞ የተሸከመችውን የፍራፍሬ ሰሀን ወደ መንገደኞቹ እያስጠጋች ባቡሩ ከመንቀሳቀሱ በፊት ለመሸጥ በየመስኮቱ ትንጠራራለች:: ይህን ጊዜ ነበር አንዱ 
መንገደኛ እንደ ዘበት በመስኮቱ በኩል እጁን ወደያዘችው ፍራፍሬ ሰዶ አንዱን ያነሳው:: “ሽልንግ” ነው ብላው ሂሳቧን እስኪሰጣት ድረስ በጉጉት
ትጠባበቃለች:: እሱም ሽልንጉን ያስቀመጠበትን ኪሱን መፈተሽ ጀምሯል:: በቀኙ.. በግራው… በፊቱና በኋላዉ ኪሶቹን ይዳብሳል:: የባቡሩ ሞተር መሞቅ ጀምሯል::
መንገደኞች ቦታ ቦታቸውን ይዘው የጉዞውን መጀመር ይጠባበቃሉ:: የባቡሩ ጭስ እየተግተለተለ መውጣት ጀምሯል:: ፋርጎዎቹ መነቃነቅ ጀምረዋል:: ያች
ምስኪን ግን ልቧ ተሸብሯል:: “ኧረ ሽልንጌን” ማለቱን ተያያዘችው:: ደጋግማ ተጣራች:: ፋርጎው ተንቀሳቀሰ ሰውዬው መንደሪኑን በእጁ እንደያዘ 
በሌላኛው እጁ ደግሞ ሽልንጉን ከተቀበረበት ፈልጎ ማውጣቱ ላይ እንዳተኮረ ነው:: አሁን ባቡሩ እየሄደ ነው:: እሷም
ሽልንጌን!...ሽልንጌን!...ሽልንጌን!” እያለች ባቡሩ እየተከተለችው ነው:: ባቡሩ ሄዷል:: የሷም ድምፅ በሩቁ ያስተጋባል::
**************************************************************************************** 
በአንድ ወቅት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአማርኛ የተማሪ መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ባለ አወቃቀርም ባይሆን በተመሳሳይ መልኩ በወጉ ተጽፎ
የቀረበ ታሪክ ነበር:: ይህ አጭር ልብ ወለድ ታሪክ በአብዛኛው የዘመኑ ተማሪ ሕሊና ውስጥ ታትሞ ለረጅም ዘመን መቆየት የሚያስችለው ኪነ ጥበባዊ
አቅም ነበረው:: ይህ ታሪክ ከኪነ ጥበባዊ ተፈጥሮው ባሻገር የዛን ዘመኑን የባቡር እንቅስቃሴንና የድሬዳዋ ከተማን ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን ምስል ከሳች በሆነ
መልኩ አሳይቶ ያለፈ ነበር::
ደራሲው ማን ይሆን?
ማግኝት ይቻል ይሆን ?
ያላችሁ ተባበሩን ?
በትውስታ እንቆዝምበት!!!

ከመጽሃፍት ዓለም



“ ፈረንጆች፣ በውቀት ይሁን በስ ህተት በየትኛው መሆኑን እግዜር ይወቀው የሚጽፉት ሆነ የሚያስተምሩት፣ ፈረንጅን እና የፈረንጅ የሆነውን ሁሉ የሚያስወድ ድ፣ የሚያስደንቅ፣ የሚያስመኝ፣ ሌሎችንና ሌሎች የሆነውን፣ እኛንና የኛ የሆነውን ጭምር አዋርዶ፣ አጎሳቅሎ የሚያሳይና የሚያስንቅ፣ የሚያስጠላ፣ የሚያስጸይፍ ነው።
ታዲያ እንግዲህ፣ ከህጻንነታቸው ጀምረው እንዲያ ያለውን ትምርት ብቻ በትምርት ቤት እየተማሩ የሚያድጉ ልጆች፣ እንዲያ ያለው ትምርት እውነት አለመሆኑን የሚያስረዳ ማረሚያ ማስተባበያ፣ ማስተሀቀሪያ በመስጠት ፈንታ፣ በሱ ለላቁ ሽልማት እየሰጠን  በሱ እንዲመሩ እያደፋፈርን የምናስድጋቸው ልጆች  በጠቅላላው የራሳቸው የሆነውን የሚንቁ የሚጠሉ፣  በጠቅላላው የፈረንጅ የሆነውን ሁሉ የሚወዱ፣ የሚያደንቁና የሚመኙ መሆናቸው የማይቀር ነው።”  ( ሀዲስ አለማየሁየልም ዣት)
“ የቆየ ልማድ የቆየ በመሆኑ ሁሉ አይወድቅም፤ ወይም ሁሉ አይያዝም። መልካሙና ጠቃሚው ይያዛል የሚሻሻለው ይሻሻላል ሊሻሻል የማይችለው ይወድቃል። ነገር ግን የሚወድቀው ክፉ ልማድ ከስራ ይወገዳል እንጂ ከታሪክ ጸሃፊዎች መጽሀፍና ከደራሲዎች ድርሰት ሊወገድ አይገባውም። ያለዚያ በየጊዜው የሚደረገው የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚክ ወይም የአስተዳደርና የማህበራዊ ኑሮ መሻሻል ከምን ተነስቶ እምን እንደደረሰ ሊታወቅ አይችልም።” (  ሀዲስ አለማየሁ፣ፍቅር እስከ መቃብር)
“ በኔ አስተያይት ዛሬ ኢትዮጵያ በጣም የሚያስፈልጋት ኢኮኖሚዋን አፋጥኖ አልምቶ በጠቅላላ የህዝብዋን የኑሮ ደረጃ ማሻሻልና ያስተዳድርዋንም ሆነ የፍርድ ስራትዋን ለዘመናዊ ኑሮ እንዲስማማና ልማቱን እንዲረዳ ማድረግ ነው እንጂ የምዕራብን ወይም የምስራቅን ያስተዳድር ስራት እንዲሁ እንዳለ ተውሶ መልበስ ምስራቅን፣ ወይም ምዕራብን ሊያደርጋት ይችልም። ስለዚህ ያቀረብነው አሳብ ከምዕራብና ከምስራቅ የመንግስት ስሪቶች ኢትዮጵያ ዘመናዊ አስተዳድርና ልማትዋን ለማፋጠን ይረዳሉ ተብሎ የሚታመንባቸው አሳቦች ተዋጥተው ያሉበት፣ በዚያ ላይ ኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ጋር የሚስማሙ አዳዲስ አሳቦች የተጨመሩበት፣ አይነተኛ አላማው ባሥር ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያን በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚክና በማኀበራዊ ኑሮ አሁን ካለችበት ዝቅተኛ ቦታ በኃይል ገፍቶ ወደፊት ሊያራምዳት ይችላል ብለን የምናምንበት ነው።” ( ሀዲስ አለማየሁ፣ኢትዮጵያ ምን አይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል)
***********************************************************
ምንጭ:-- ሀዲስ አዲስ