ከደራሲያን ዓምባ

Monday, September 28, 2020

አደይ አበባ በመስከረም

 

አደይ አበባ

                                                                       *🌻🌻🌻*

የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ በአል ሁሌም በየአመቱ መስከረም አንድ ቀን ይከበራል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያንም ዘመን በሚለውጡበት መስከረም ወር ተፈጥሮ የምትለግሳቸውን አደይ አበባ በናፍቆት ይጠብቃሉ፡፡ ዙሪያው ገባውን በቢጫው አበባ ተውቦ ሲመለከቱ ያኔ አዲስ አመት ባተ ይላሉ፡፡ ወለል ግድግዳቸውን በአበባው ያስጌጣሉ፡፡ ልጃገረዶች “አባባዮሆሽ” ሲጨፍሩ አደይ አበባን ይዘው መዞራቸውም የተለመደ ውብ የበዓል ትእይንት ነው፡፡
 
የአደይ አበባ ከዘመን መለወጫ ጋር የመተሳሰሩ ሚስጥርም ከኖህ ታሪክ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ነገሩ እነዲህ ነው ምድር በጥፋት ውሃ በተጥለቀለቀች ጊዜ ኖህ እና ቤተሰቦቹ በመርከብ ውስጥ ገብተው ተርፈዋል፡፡ ታዲያ ከጊዜ በሁዋላ ኖህ የውሃውን መጉደል ለማረጋገጥ እርግብን ይልካታል፤እርግብም ለምለም ቅጠል፣አደይ አበባ እና ሳር ይዛ በመመለስ የውሃውን መጉደል አበሰረች፡፡ በዚህም በተለይ አደይ አበባ የአዲስ አመት ማብሰሪያ እና የተስፋ ምልክት ሆኖ በኢትዮጵያ ይታወቃል፤ይዘከራል፡፡
 
የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ የሆነው አደይ አበባ ከምን ዓይነት የዕጽዋት ዝርያ ይመደባል? ምን አይነት ጥቅም እንዳለው? ምን ያህል ዝርያዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ? ከኢትዮቤስት ዶት ኮም እና ከዲደብሊው ያገኘነውን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበንላችሀል!መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆንላችሁም ተመኝተናል!
 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-እፅዋት መምህር ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው ከኢትዮቤስት ዶት ኮም ባደረጉት ቃለምልልስ እንደተናገሩት አደይ አበባ የሚባሉት አንድ አይነት ብቻ ዝርያ ያላቸው ሳይሆኑ ሁለትና ሶስት የሚሆኑ በቤተሰብ ተመሳሳይነት ያላቸው ዝርያዎች ናቸው::በቤተሰብ የሳይንሳዊ መጠሪያቸው ባይደንስ በሚል ይታወቃሉ::
የዘርፉ አጥኝዎች በአለም እስከ 300 የሚደርሱ የባይደንስ ዝርያዎች እንዳሉ ጠቁመዋል:: በአሃያ ዩኒቨርሲቲ የእጽዋት እና ብዝሃ ህይወት መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን ታደሰ ከመረጃ ምንጫችን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደጠቆሙትም አፍሪካው ውስጥ ወደ 64 የባራደንስ ዝርያዎች ሲኖሩ ከነዚህ ውስጥ 21 ያህሉ ዝርያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ:: ከ21 ውስጥ ወደ 12 ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ናቸው::እነዚህ ደግሞ ባይደንስ ማይክሮ ካርፖ የሚባለው በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያዎች አካል ናቸው::
ባይደንስ ማክሮ ካርፖ የተባሉት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙት የአደይ አበባ ዝርያዎች ከሌሎች መሰሎቻቸው(የባይደንስ ቤተሰቦች) የሚለዩባቸው ባህርያት አሏቸው:: ፅዋቶቹ አንዳቸውን ከሌላቸው ከሚለያቸው መገለጫዎቻቸው መካከል የቅጠሎቻቸው ቁጥር መብዛት እና ማነስ አንዱ ነው:: ሌላው ደግሞ የቅጠሎቻቸው አዘረጋግ ነው:: የአበባዎቻቸው እና የፍሬያቸው ሁኔታም ልዩነቶች ከሚገለፁባቹው መስፈርቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው::
 

 
አንዳነዶቹ የባይደንስ ቤተሰብ የአደይ አበባ ዝርያወች ቅጠሎቻቸው ከሁለት እስከ ሶስት ስንጥቅ ሲኖራቸው አንዳንዶቹ ደግሞ አምስትና ስድስት ስንጥቆች አሏቸው::
ሌላው ከአባባው ጋር የተያያዘው ልዩነት የቀለም ነው:: የአንዳንድ የአደይ አበባዎች ቀለም ፈዘዝ ያለ ቢጫ ሲሆን የሌሎቹ ቀለም ደመቅ ያለ እና የተለየ ነው:: ከፍሬውም አንፃርም በእኛ አገር የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያ ከሌሎች ዝርያዎች አንፃር ፍሬው ትልቅ መሆኑም ሌላዉ የሚለየው ባህሪ ነው::
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያ የዕድገት ጊዜውን ሲጨርስ የሚሞት ሲሆን ፍሬው ብቻ መሬት ውስጥ ተቀብሮ የሚቀር ነው:: የሌሎች ግን ግንዳቸው ወይም ስራቸው ተርፎ የሚቀር ነው::
የዚህ የአደይ አበባ ዝርያ ፍሬ አፍርቶ አትክልቱ ከሞተ በኋላ ፍሬው መሬት ተቀብሮ ከስድስት ወር እስከ ሁለት አመት ሊቆይ ይችላል:: ይህ ወቅትም የሽልብታ /የዶርማንሲ ፔሬድ/ ጊዜ ይባላል:: በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ፍሬው እንደገና ዕፅዋቱ እንዲበቅል ያደርጋል ማለት ነው::
አበባው አንዴ ካበበ በኋላ እንደፈካ ምድርን አስውቦ የሚቆየው ለረጅም ጊዜ አይደለም:: ቢበዛ ለሶስት ወራት ብቻ ጋራና ሸንተረሩን፤ ሜዳና ተራራውን በተስፋ ሰጪው ቢጫማ ቀለም አስውቦ ይቆይና ይጠፋል:: ይህም ሌላው የአደይ አበቦች መለያ ባህሪ ነው::
የኦሀዮ ዩኒቨርሲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን አደይ አበባ ጋራና ሸንተረሩን፤ ሜዳና ተራራውን ከማስጌጥ ያለፈ ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል:: አበባው በተለይ በአሩሲና በከፋ አካባቢ ጥቅም ላይ ይውላል፤በነዚህ አካባቢዎች የአደይ አበባ በስፋት ለደም ማቆሚያት እንደሚውል ተናግረዋል::
ፕሮፌሰሩ ከ30 አመት በፊት በኢትዮተያ ባደረጉት ጥናት የአደይ አበባ በተለይ ሴቶች ወልደው ደም እየፈሰሰ አልቆም ካላቸው ጨቅጭቀው ጭማቂውን እንዲጠጡ በሚደረግበት ጊዜ የሚፈሰውን ደም እንደ ሚያስቆምላቸው መስማታቸውን ተናግረዋል::ከዚህ በተጨማሪ ፀረ ተዋህስ /Anti- infction/ በመሆን እንደሚያገለግለም ጠቁመዋል::
ሌሎች አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም የአደይ አበባ ለስኳር በሽታና ለጭንቅላት ካንሰር ህክምና እንደሚውል ፍንጭ ሰጥተዋል:: ዩኮፒያ የተባለ አንድ በኢትዮጵያ የሚገኝ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከአደይ አበባ ክሬም አምርቶ ለገበያ ማቅረቡም ታውቋል::
ክሬሙ ወንዶች ፂማቸው ከተላጩ በኋላ ለማለስለሻነት የሚቀቡት ነው:: ሌላው ከዚህ በአበባ ለሴቶች የተሰራው ክሬም ደግሞ ለማዲያት መከካለያ(ማጥፊያነት) የሚውል መሆኑም ታውቋል::
ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙ የተለያዩ የአደይ አበባ ዝርያዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚውሉም መረጃዎች ይጠቁማሉ::የአበባው ዝርያ ዋና መገና እንደሆነች በሚነገርባት ሜክሲኮ ሴቶች ጨቅጭቀው ፊታቸውን በመቀባት ለውበት መጠበቂያነት ይገለገሉበታል:: ከዚህ በተጨማሪም ከአበባው ተጨምቆ የሚገኘውን ፈሳሽ ለልብስ ማቅለሚያነት ይጠቀሙበታል::
አደይ አበባዎች ከፍተኛ የሆነ ማር ለማምረት የሚውል ንጥረ ነገር በውስጣቸው አላቸው::በዚህም ምክንያት በማር ምንጭነቱ ይታወቃል::ታዲያ ንቦች ይህን ንጥረ ነገር በመቅሰም የሚሰሩት ማር ለምግብነት ለመድሃኒትነት እና ለሌሎችም በርካታ አገልግሎቶች ይውላል፡
 

 ********************************************************************************
መልካም አዲስ ዓመት
(አዲሱ አያሌው)
በኩር ጳጉሜ 4 ቀን 2011 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዘወትር ሰኞ የምትታተም  ጋዜጣ
https://www.dw.com/am/%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%8B%B0%E1%8B%AD-%E1%8A%A0%E1%89%A0%E1%89%A3-%E1%89%A3%E1%88%85%E1%88%AD%E1%8B%AB%E1%89%B5-%E1%8A%A5%E1%8A%93-%E1%8C%A5%E1%89%85%E1%88%9E%E1%89%B9/a-40495412