ከደራሲያን ዓምባ

Thursday, August 14, 2025

የተራራው ምርኮኞች

 የተራራው ምርኮኞች_አሳፍ ሃይሉ
 Alive : The Story of the Andes

 Survivors




"ሁላችንም ጥቂት ጥቂት የተራራ ምርኮኞች ነን!"

ይሄን መፅሐፍ የኢትዮጵያ አንባብያን "የተራራው ምርኮኞች" በሚል በሀዲስ እንግዳ አይቼህ ግሩም ተደርጎ ተተርጉሞልን አንብበነዋል። ሁልጊዜ ከሃሳቤ የማይጠፋ መፅሐፍ ነው።

በዕለተ አርብ፣ በፈረንጆቹ አቆጣጠር Friday 13 October 1972 ዓመተ ምህረት፣ የፓራጓይን የራግቢ ኳስ ተጫዋቾች ቡድን የያዘ የአየር ኃይል አውሮፕላን፣ በላቲን አሜሪካ እጅግ ግዙፉ በሆነው የአንዲዝ በበረዶ የተሸፈነ ተራራ ላይ ይከሰከሳል።

ይህ መፅሐፍ፣ ከአደጋው በህይወት የተረፉት እነዚያ ተሳፋሪዎች፣ በዚያ ከዜሮ በታች በሆነ በረዷማ ተራራ ላይ ለቀናት፣ ለሣምንታት፣ ... ብሎም ከሁለት ወራት በላይ ከበረዶ፣ ከረሃብ፣ ከጥማት፣ ከአሰቃቂ ህመምና ከሞት ጋር እየታገሉ ለመቆየት የተገደዱበትን እጅግ አስከፊ የህልውና ግብግብ የተረከ መፅሐፍ ነው።

ከታሪኩ የማይረሳኝ እነዚያ የተራራ ምርኮኞች የሚፈልጋቸውና የሚያድናቸው አካል ጠፍቶ፣ እነሱን ፍለጋ ይደረግ የነበረውም የቅኝት በረራ በተስፋ መቁረጥና በአስቸጋሪ አየር ንብረት ተቋርጦ፣ በቅርቡ እንደሰማናቸው የማሌይዢያ አየር መንገድ ተሣፋሪዎች ደብዛቸው ስለመጥፋቱ የመርዶ ዜናዎችን ዓለምና ቤተሰቦቻቸው እየተቀባበሉ እያለ፣ የሚላስ የሚቀመስ በሌለበት፣ በመጨረሻ በህይወት ለመሠንበት አንድ ነገር መወሰን ነበረባቸው።

ከመካከላቸው የበረዶውን ቅዝቃዜና ስቃይ መቋቋም ያልቻሉ ጓደኞቻቸው ሞተው፣ አስከሬናቸው በበረዶው እንደቀዘቀዘ አለ። ሁላችንም በረሃብ ከምንሞት ቀድመው የሞቱትን አስከሬን እንብላና የቻልነውን ያህል እንሰንብት፣ እስከዚያ እርዳታ ይደርስልን ይሆናል የሚል ሃሳብ ያመጣሉ።

ሃሳቡ አሰቃቂ ነው። ግን ካሉበት ነቅነቅ ለማለትም የሚበላ መቅመስ አለባቸው። መኖር፣ መትረፍ አለባቸው። ብዙዎቹ በመጨረሻ እየዘገነናቸውም ቢሆን በሃሳቡ ይስማማሉ። አልበላም የሰው ሥጋ ልሙት ብሎ ከነአቋሙ በጠኔ የሞተም አለ።

ሌሎቹ ግን የቀዘቀዙ የጓደኞቻቸውን አካል ቀስ በቀስ እየቆነጠሩ በሉ። ቀድሜ ከሞትኩ ብሉኝ የሚሉም ነበሩ ከመሐላቸው። ከፊት ሆኖ እያበረታ ይመራቸው የነበረ ጓደኛቸው በመጨረሻ አቅሙም ቅስሙም ዝሎ ወደ ወዲያኛው ሲያሸልብ፣ ቀድሞ የመነሳሳት መንፈስ ያልነበረው ሰው፣ አስገራሚ ቆራጥነትን ተላብሶ የተረፉትን አደፋፍሮ ሲመራቸው ይታያል።


በዚያ የፍጡራን ዘር ዝር በማይልበት የበረዶ ተራራ፣ 72 ቀናት ዙሪያቸውን ከከበባቸው ነጭ ሞት ጋር ታላቅ የሰርቫይቫል ግብግብ ገጥመው፣ በቃላት ሊነገር የማይችል ስቃይን ተቋቁመው፣ አሳሽ ሄሊኮፕተሮች ሊያዩአቸው ወደሚችሉበት ቦታ እያነከሱም፣ እየተሳቡም በበረዶ መሐል ተጉዘው፣ በመጨረሻ 16 ሰዎች በህይወት ተገኙ።

ዜናው ሲሰማ ዓለም ተንጫጫ። ግማሹ በአድናቆት። ግማሹ በውግዘት። በሰው ልጅ የቅርብ ዘመን ታሪክ በአንዲዝ ተራራ 72 ቀን አይደለም፣ ለአስር ቀን ብቻውን ተጥሎ ሊተርፍ የሚችህ ሰው አይታሰብምና ለብዙዎች የመትረፋቸው ዜና ተዓምር ሆነ።

አስከሬናቸው በጓደኞቻቸው የተበሉትን ተጓዦች ቤተሰቦች ሆነህ አስበኸዋል? ምን ዓይነት ሰቆቃ እንደሚሆንብህ?

ተጫዋቾቹ የጓደኞቻቸውን ሥጋ በልተው እንደተረፉ መጀመሪያ ደብቀው ነበር፣ በኋላ ያገራቸውን ጋዜጠኞች ለብቻ ጠርተው፣ በቃ እውነቱን እንንገራችሁ፣ የሆነው ይህ ነበር አሉ።

ከፈለጋችሁ ፍረዱብን፣ ማንም ህሊና ያለው ሰው በኛ ቦታ ቢሆን ማድረግ የነበረበትን ውሳኔ ወስደን አድርገነዋል። ለመትረፍ ያላየነው ስቃይ የለም። በህይወት ያለን ጓደኛችንን ለመብላት ስንል አልገደልንም። ...

ያለፍንበትን ገሃነማዊ ቆይታ ተረዱን፣ ይህ የፅናት ታሪካችን ነው። ከሰቆቃ የተረፍን ንፁህ ሰዎች ነን። ይህ በማንም ላይ እንዲደርስ አንፈልግም። ተገደን ያደረግነውን አድርገናል አሉ። የሰማ ሁሉ በድንጋጤ ተያዘ። እውነቱን ተናግረው ሀዘንና ፍቅር ግን ዘነበላቸው።

ይሄ እንግሊዛዊ ጋዜጠኛና ደራሲ፣ ተራፊዎቹን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ የአሳሽ ግብረሃይል አባላትንና የህክምና ቡድኖችን ሁሉ ጠይቆ፣ ተዓምራዊው ዜና በተሰማ በሁለት ዓመቱ በመፅሐፍ መልክ አተመው። የራሳችንን ጨምሮ፣ 20 በላይ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ታሪካቸው ለዓለም ተዳረሰ። ፊልሞችም ተሠርተውበታል።

የሰው ልጅ ከማይቻል መከራ ጋር ሲጋፈጥ፣ ችሎ የሚወጣ ፅኑ ፍጥረት መሆኑን የእነዚህ ኡራጓውያን እውነተኛ ታሪክ ህያው ምስክር ሆኖ፣ ተደጋግሞ ይወሳል።

ስሱ የሚመስለው ሰው፣ የቁርጡ ቀን ሲመጣ፣ መኖሩንም የማያውቀው ተፈጥሮ በውስጡ ያኖረችው የመኖር instinct ይወጣል። ያላሰበውን ቆራጥነት ይላበሳል። ተፈጥሮ ከሰው ልጅ አቅበላይ የሆነ ችግርን አልደቀነችም። ሰው ብርቱ ነው። ፅኑ መንፈስ የሰው ልጅን በመከራዎች መሐል ያኖረው ትልቁ ፀጋው ነው።

ዛሬ በመከራ የተከበብን ሰዎች፣ በተስፋ አስቆራጭ ችግር የተያዝን ሰዎች፣ እንደ አንዴዝ ተራራ፣ ከአቅማችን በላይ የመሠለን ስቃይ ዙሪያችንን ያጠረብን ምስኪኖች፣ ችግራችን እንደ ተራራ ተከምሮ ገዝፎ የታየን፣ አትተርፉም አበቃላችሁ የተባለልን፣ ከንፈር የተመጠጠልን ሰዎች... ከእነዚህ ባለታሪኮች ምን እንማር ይሆን?

በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንገኝ ተስፋ አለመቁረጥን። ፅናትን። ዕምነትን። የማንቋቋመው የመከራ ተራራ እንደሌለ። ሰው በመሆናችን ብቻ አይበገሬነት በውስጣችን እንዳለ።...

ዕምነት ካለን ተራራውን ከፊታችን ነቅለን ማንሳትና መሻገር እንደምንችል። ከመከራ ፊት ቀድሞ ከመሸነፍ፣ እየታገሉ መሸነፍ ታላቅ ክብር እንደሆነ።...

እና ደሞ በሰው ቶሎ አለመፍረድን...! በሰው ቦታ ብሆን እኔስ ምን አደርግ ነበር? ብሎ ቆም ብሎ ማሰብን። ...

እና ምናልባት... የፈጣሪንም ተዓምር አለመርሳትንም የሚያስተምር ይመስለኛል ይሄ የተራራው ምርኮኞች ታሪክ።

ሁላችንምኮ የዚህን ያክል extreme የወጣ ባይሆንም፣ የየራሳችን ተራራ ያለን ነን። ሁላችንም የየራሳችንን የኑሮ ዐለት በተራራው ላይ የምንገፋ የየራሳችን ሲሲፈሶች ነን። ሁላችንም ትንሽ ትንሽ የተራራው ምርኮኞች ነን።...

ይህን አለመርሳት፣ ህይወትን እንዳመጣጧ ማስተናገድ፣ ትዕግሥት፣ ፅናት፣ ተስፋ፣ ፍቅር..! የሰው ልጅ የመከራ ቀን ማለፊያዎች፣ የደስታ ቀን ጌጦች ናቸው። Nothing is impossible! Even the sky is not the limit!😊

Live and Let Live!

ሸጋ ቀን ተመኘሁ።

*****************

Assaf Hailu Facebook page

https://web.facebook.com/photo/?fbid=24143585448603261&set=a.222487634473044