ከደራሲያን ዓምባ

Monday, March 27, 2017

ዋ …ያቺ አድዋ_ፀጋዬ ገብረመድኅን



ዋ …
አድዋ ሩቅዋ
የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ችጋግ ዳስዋ
አድዋ . . .
ባንቺ ብቻ ህልውና
በትዝታሽ ብጽዕና
በመስዋእት ክንድሽ  ዜና
አበው ታደሙ እንደገና፡፡
ዋ …
ዓድዋ የዘር ዐፅመ ርስትዋ
የደም ትቢያ መቀነትዋ
በሞት ከባርነት ስርየት
በደም ለነፃነት ስለት
አበው የተሰውብሽ ለት
ዓድዋ
የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ
የኢትዮጵያዊነት ምስክርዋ
ዓድዋ
የኩሩ ደም ባንቺ ጽዋ
ታድማ በመዘንበልዋ
ዐፅምሽ ቤንሳኤ ነፋስ
ደምሽ በነፃነት ህዋስ
ሲቀሰቀስ ትንሳኤዋ
ተግ ሲል ሲንር ትቢያዋ
ብር ትር ሲል ጥሪዋ
ድው እልም ሲል ጋሻዋ
ሲያስተጋባ ከበሮዋ
ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ
ያባ መቻል ያባ ዳኘው
ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው
ያባ በለው በለው ሲለው
በለው በለው በለው በለው!

ዋ …ዓድዋ …
ያንቺን ጽዋ ያንቺን አይጣል
ማስቻል ያለው አባ መቻል
በዳኘው ልብ በአባ መላው
በገበየሁ በአባ ጎራው
በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው
በለው ብሎ፡ በለው በለው!
ዋ . . .ዓድዋ . . .
ዓድዋ የትላንትናዋ
ይኸው ባንቺ ህልውና
በትዝታሽ ብፅዕና
በመስዋዕት ክንድሽ ዝና
በነፃነት ቅርስሽ ዜና
አበው ተነሱ እንደገና፡፡
ዋ!  . .  ያቺ ዓድዋ . . .
አድዋ ሩቅዋ
የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ
ሰማይ ጠቀስ ችጋግ ዳስዋ
አድዋ . . .


Thursday, March 9, 2017

ስለ ቋንቋ መበላሸት ትንሽ እናውራ!



አንዳንድ ሰዎች በተሳሳተ አነጋገር ላይ እርማት ሲደረግ “ቋንቋ መግባቢያ ስለሆነ ሰው እንደ ፈለገ ቢናገረው ምናለበት” ሲሉ ይሰማሉ። አዎ ቋንቋ መግባቢያ ነው። ነገር ግን መግባቢያነቱ የሚሰምረው በትክክል ሲነገር ወይም ሲጻፍ ብቻ ነው። ስህተት ሆኖ ሲነገር ግን ሌላ ቢቀር ማደናገሩ አይቀርም። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ ወሎ ውስጥ በገጠር አካባቢዎች በሁለተኛና በሦስተኛ ሰው (በርስዎና በሳቸው) መካከል የተሳሳተ አነጋገር ይሰማል። እሳቸው መጥተው ነበር ለማለት እሰዎ (እርስዎ) መጥተው ነበር እያሉ ሲያወሩ ይሰማል። ልክ በጎጃም አባባል አልበላሁም ለማለት “አልበልቸም” እንደሚለው አነጋገር መሆኑ ነው። ጎጃምኛው አለመለመዱ ነው እንጅ ስህተት አይመስለኝም። ታዲያ አንድ መንደርኛውን አነጋገር የረሳ ወሎየ ዘመዶቹ ዘንድ (ጋ) ሄዶ ሲጫወት የገጠሬው ዘመዱ “ያንዬ እስዎ ሞተው ሃዘን ላይ ሆነን” ሲለው “እረ ተው ምቸ ሞትኩ እኔ” ሲል ደነገጠ ይባላል። ያ ገጠሬው ሰው ሊል የፈለገው “ያንየ እሳቸው ሞተው ሀዘን ላይ ሆነን” ለማለት ነው። ስለዚህ ቋንቋ በትክክል ካልተነገረ ወይም ካልተጻፈ መግባባት ሳይሆን ማደናገርን ነው የሚፈጥረው-ከላይኛው ምሳሌ እንዳየነው።
ዛሬ የቋንቋ ብልሽት በብዙ መልክ ይታያል። የፈረንጅኛ ቃላት፣ ያውም የተሳሳቱ አባባሎችን ካልጨመሩ ሃሣባቸውን መግለጽ የማይችሉ የሚመስላቸው ሰዎች ብዙ ናቸው። ፋዘር፣ ማዘር፣ ፍሬንድ የሚሉት ቃላት በሰፊው ሲነገሩ ይሰማል። ሽማግሌዎችና አሮጊቶችም ፋዘር፣ ማዘር ሲሉ መሰማት ጀምሯል። ለምን ቢባል “ዘመናዊ” ለመሆን ነዋ! “አባት፣ እናት፣ ጓደኛ ካለ አንድ ሰው ስልጡን እንዳልሆነ ነው የሚታሰበው” አለኝ አንድ ወያላ ሲያብራራልኝ። ለመሆኑ ፋዘር፣ ማዘር የሚባሉት የሰንት ዓመት ሰዎች ናቸው ብዬ ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ የሚገርም ነው። “ወንዱን ፋዘር የምንለው ትንሽ ሽበት ካወጣ ወይም ጸጉሩ ከተመለጠ ነው። ሴትዋም ሻሽ ካሠረች ያው ማዘር ነች” አለ እየሳቀ። ወያላዎች ግራንድ ፋዘር (ግራንድፓ) ወይም ግራንድ ማዘር (ግራንድማ) የሚሉትን የእንግሊዝኛ ቃላት ስለማያውቋቸው ያርባ አመትም ሆነ የሰማንያ ዓመት ሰው ያው ፋዘር ነው የሚባለው። ሴትዋም ያው ማዘር ነች። እነኝህ ፋዘር፣ ማዘር፣ ፍሬንድ የሚሉት ቃላት ትርጉሞች በሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እንደሚገኙ የሚታወቅ ነው። ቁልምጫዊ ዘይቢያቸው ሳይቀር አለ። ለምሳሌ በአማርኛ አባቴ፣ አባብዬ፣ እማማ፣ እማምዬ፣ ጓደኛዬ፣ ጓዴ ወዘተ የሚሉ ቃላት አሉ። የቅርብ ዘመድንና የቤተሰብ አባላትን በቁልምጫ ለመጥራትም ብዙ ቃላት አሉ። ታላቅ ወንድምን፣ ወይንም አጐትንም ሆነ የቅርብ ወንድ ዘመድን፣ ጋሽየ፣ ወንድምዓለም፣ ወንድምጋሼ፣ ጥላዬ ማለት እንደሚቻለው ሁሉ፣ ለሴት እህትም ወይም አክስት፣ እታለም፣ እትአበባ፣ አክስቴ ማለት ይቻላል።
ሌላው በብዛት ስህተት ሲስተናገድበት የሚታየው/የሚሰማው በግዕዝና በአማርኛ እርባታ ላይ ነው። ብዙ ሰዎች በግዕዝ በተረባው ቃል ላይ ቶች፣ ዎች ወይም ኖች በመጨመር የብዙ ብዙ አነጋገር ስህተቶችን ሲፈጽሙ ይሰማሉ። የሚከተሉትን እንመልከት!
የአማርኛ ዕርባታ (ነጠላ-ብዙ) የግዕዝ ዕርባታ (ብዙ)   ጸያፍ ዕርባታ (የብዙ ብዙ)
ሊቅ         ሊቆች             ሊቃውንት             ሊቃውንቶች
አስተማሪ    አስተማሪዎች       መምሕራን             መምሕራኖች
ሕፃን        ሕፃኖች            ሕፃናት                ሕፃናቶች
ቄስ          ቄሶች             ቀሳውስት              ቀሳውስቶች
መነኩሴ      መነኩሴዎች        መነኮሳት              መነኮሳቶች
ካህን         ካህኖች            ካህናት                ካህናቶች
ዲያቆን       ዲያቆኖች          ዲያቆናት              ዲያቆናቶች
ንጉሥ        ንጉሦች           ነገሥታት              ነገሥታቶች
እንስሳ        እንስሶች           እንስሳት               እንስሳቶች
ገዳም         ገዳሞች           ገዳማት                ገዳማቶች
ጳጳስ          ጳጳሶች           ጳጳሳት                 ጳጳሳቶች
ባህታዊ        ባህታዊዎች       ባህታውያን             ባህታውያኖች

ባሁኑ ጊዜ በጣም ገንኖ የሚታየው ሌላው ስህተት በ ጋ እና ጋር መካከል ያለው ያጠቃቀም ውዥንብር ነው። በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው “አማርኛ መዝገበ ቃላት” እንደሚገልጸው ጋ የሚለው ፊደል “አንድ ነገር የት እንደሚገኝ የሚያመለክት ቃል” ነው። መጽሐፉ ጠረጴዛው፣ እዚያ ነው። ጋር የሚለው ቃል ደግሞ “አብሮ” የሚለውን ሃሣብ የሚገልፅ ነው። ስለዚህ ጋ ዘንድ ሲሆን ጋር ደግሞ አብሮ ማለት ነው። ምሳሌ፣ እኔ ዛሬ ወንድሜ ጋ እሄድና ከሱ ጋር ሄደን ምሳ እንበላለን። ስለዚህ ጋ የሚለው ዘንድ ማለት ሲሆን ጋር የሚለው ቃል ግን አብሮ ማለት ነው። ለምሳሌ ስልክ ተደውሎ የት ነው ያለኸው ሲባል ወንድሜ ጋ ነኝ (ወንድሜ ዘንድ ነኝ) መሆን ነው ያለበት መልሱ። ዛሬ ግን ጋ ለማለት ጋር በማለት ውዥንብር እየተፈጠረ ነው። መጽሐፉ የት ነው ያለው? ብለህ ስትጠይቅ ከበደ ዘንድ ነው ለማለት ከበደ ጋር ነው ይልሃል። ትክክል ያልሆነ አነጋገር ነው። የቃና ቴሌቪዥን ተዋንያን ሳይቀሩ የተሳሳተውን የቋንቋ አገባብ ይዘው ጋ የሚለውን ጋር እያሉ ነው የሚያወሩት። ከአንድ ሰዓት በኋላ ወንድሜ ጋ (ቤት) እሄዳለሁ ለማለት፣ ከአንድ ሰዓት በኋላ ወንድሜ ጋር እሄዳለሁ እየተባለ ነው። ስህተት ነው።
ሌሎች በባዕድ ቋንቋዎች የምንሠራቸው አስቂኝ ስህተቶች አሉ። አንድ ልጅ አባቱ ያልሆነውን ሰው ፋዘር ወይም ዳዲ ብሎ ሊጠራው አይችልም። አንድ ጊዜ አራት ኪሎ አንድ ፈረንጅ ታክሲ ውስጥ ሆኖ ወጣቶች ከበው ገንዘብ ስጠን ለማለት ፋዘር፣ ዳዲ እያሉ ሲያስቸግሩት ደርሼ ገላግየዋለሁ። “ፋዘር ዳዲ ሞኒ ሞኒ” እያሉ በግራና በቀኝ ሲጮሁበት ፈረንጁ ተናዶ I swear I did not father any of these kids (ከነኝህ ልጆች አንዱንም እንዳላስወለድኩ እምላለሁ ነበር ያለው።) ሌላው አስቂኝ ቃል ክላስ የሚለው ነው። ሆቴል ስትገቡ እንግዳ ተቀባዩ ክፍል ይፈልጋሉ ለማለት ድፍረት በተሞላ አነጋገር ክላስ ነው የሚፈልጉት ነው የሚላችሁ። ክላስ ወይም ክላስሩም የመማሪያ ክፍል ነው እንጅ የመኝታ ክፍል አይደለም። የኛም የውጭውም ቋንቋ እንደዚህ ተዘበራርቋል።
በየቀኑ በስህተት የሚነገሩ የውጭ አገር ቋንቋዎችና ቃላት ብዙ ናቸው። አመሰግናለሁ ለማለት ቴንክዩ ወይም ታንክዩ የሚሉ ብዙ አሉ። የቋንቋው ባለቤቶች እንግሊዞች ግን ትክክለኛውን ቃል ለማውጣት ምላስን በላይኛውና በታችኛው ጥርሶቻችን መካከል ብቅ አድርጎ መልሶ ወደ ውስጥ በመሰብሰብ የሚፈጠር ድምፅ ነው ይላሉ። ያን ድምፅ በአማርኛ መጻፍ ባይቻልም ሳንክዩ ለሚለው ቃል ነው የሚቀርበው።
ባሁኑ ጊዜ ቋንቋን ከሚያበላሹ ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የመገናኛ ብዙሐን ሰራተኞች በተለይ የቴሌቪዥንና የሬድዮ ጋዜጠኞች ናቸው። እጅግ በጣም ጥሩ፣ በጣም ቆንጆ የሚሉትን የአማርኛ ገላጭ ቃላት አሪፍ በሚል የአረብኛ ቃል ለውጠዋቸዋል። አገሩ ሁሉ አሪፍ፣ አሪፍ እያለ ነው። “አሁን ደግሞ “አሪፍ” ሙዚቃ እንጋብዛችኋለን” ማለት የተለመደ የሬድዮ ጣቢያ አነጋገር እየሆነ መጥቷል። ከፈረንጅ ጥገኝነት ወደ አረብ ጥገኝነት በቀላሉ እየተሽጋገርን ይመስላል። ምንም እንኳን ቋንቋ ይወራረሳል፣ ያድጋል ቢባልም የሚወራረሰውም የሚያድገውም የራስ ቋንቋ የማይገልጸውን የሚገልጹ የባዕድ ቃላት ሲገኙና በግልጽ በሥራ ላይ መዋል ሲያስፈልጋቸው ነው። ዛሬ ቀኑ፣ ዓየሩ፣ ጥሩ ነው፣ ቆንጆ ነው፣ ተወዳጅ ነው ወዘተ ለማለት ሁሉም የሚሸፈነው “አሪፍ” በሚለው ቃል ሆኗል። ቃሉ በጣም ከመወደዱ የተነሳ በረጅም ቅላጼ ነው የሚነገረው። ይህ ደግሞ የራሳችንን ቋንቋ ማሳደግ ሳይሆን ለባዕድ ቋንቋ ጥገኛ መሆንና የራስን ቋንቋ ማዳከም ነው። እንድንግባባ እኔም ቃሉን ልዋሰውና አሪፍ የጥገኝነት ባህሪ ነው ልበላችኋ!
ሰርተፊኬት የሚለው ቃል በሰፊው ተለምዶ በሬድዮና በቴሌቪዥን ሲነገር በጽሁፍም ሲቀርብ ይታያል። የቋንቋው ባለቤቶች ሰርቲፊኬት ነው የሚሉት። ስለዚህ እኛ ቃሉን በትክክል ለመጠቀም ወይ ባለቤቶቹ እንደሚሉት ሰርቴፊኬት ማለት አለብን አለዚያም በራሳችን ትርጉም የምስክር ወረቀት ማለቱ ይመረጣል። ሌላው ተመሣሣይ ችግር ያለው ፕረስ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ነው። ቃሉ ከሕትመት ሥራ ጋር ማለት ከመጫን፣ ከማተም ጋር የተያያዘ ስለሆነ በእንግሊዝኛ ፕረስ የሚለው አነባበብ ይስማማዋል። እኛ ግን ለራሳችን የሚስማማን ፕሬስ ነው በማለት ቃሉን ከትክክለኛው አነጋገር ከፕረስ ወደ ፕሬስ ወስደነዋል። ይህ ድርጊት ምንም ምክንያታዊ አይደለም። አሁንም ሌላው ከትክክለኛ አነጋገር ወደ ተሳሳተ አባባል በልማድ የተወሰደና በስህተት እየተነገረ የምሰማው ኦሎምፒክ የሚለው ቃል ነው። ቃሉ በእንግሊዝኛ OLYMPIC (ኦሊይምፒክ) ነው። የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለማለት OLYMPIC GAMES ነው የሚባለው። ባንድ ወቅት አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ኦሊይምፒክ የሚለውን ቃል ኦሎምፒክ ብሎ በስህተት አነበበው። ከዚያ ወዲህ እኛ አገር ትክክለኛው አነባበብ ተሽሮ ኦሎምፒክ ሆኖ ቀረ።
ወደ ጣልያንኛ ቋንቋ ደግሞ እንሂድ። በመኪና ላይ ከሁዋላ የሚመጡትን ተሽከርካሪዎች ለመቆጣጠር በግራና ቀኝ ያሉት መስትዋቶች በጣልያንኛ ስፔኪዮ ነው የሚባሉት። ከተጠራጠሩ የጣሊያንኛ ቋንቋን በደምብ የሚያውቅ ሰው ይጠይቁ ወይም የኢጣልያንኛ መዝገበቃላትን ይመልከቱ። በኛ አገር ግን ሕዝቡ በሙሉ ስፖኪዮ ሲል ነው የሚሰማው። ስፖኪዮ አይደለም ስፔክዮ ነው ብለህ ብታርመው ሰው ሁሉ ይስቅብሃል። ብዙዎቻችን ይበልጥ ከሚያውቁ ሰዎች ጠይቀን ከመማር ስህተታችንን ይዘን መኖር የምንመርጥ ይመስላል።
SERIES ተመሣሣይ፣ ተዛማጅ ወይም ተከታታይ ማለት ነው። Series of books ማለት ተከታታይ መጸሕፍት ማለት ነው። በቴሌቪዥን የምንሰማው ማስታወቂያ ግን SERIOUS (ሲሪየስ) of books እየተባለ ነው የሚነበበው። SERIOUS የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ደግሞ ኮስታራ፣ ቁም ነገረኛ፣ ምራቁን የዋጠ ማለት ነው። ሁለቱ የእንግሊዝኛ ቃላት አነባበባቸውም፣ ትርጉማቸውም የተለያየ ነው። አንድ ሰው አነባበቡን በትክክል የማያውቀው የባዕድ ቃል ሲገጥመው በግምት ከማንበብና መሣቂየ ከመሆን ይልቅ ያንን ቋንቋ የሚያውቀውን ሰው ጠይቆ መረዳት ወይም የዚያን ቋንቋ መዝገበ ቃላትን ማየት ያስፈልጋል።
የዘመኑን ቋንቋ በተመለከተ ሌላው አነጋጋሪ ቃል ማለት የሚለው ነው። ማለት ግልጽ ያልሆነን ሃሣብ ለማብራራት፣ ለመግለጽ የምንጠቀምበት ቃል እንደሆነ ለሆሉም ግልጽ ይመስለኛል። አንድን ቃል ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ለመተርጎም ይህ ቃል ምን ማለት ነው፣ ይህ ጽንሠ ሃሣብ ምን ማለት ነው ወዘተ እያልን በቃሉ ስንጠቀም ኖረናል። ያሁኑ አዲሱ አጠቃቀም ግን “ማለት ነው” የሚሉትን ሁለት ቃላት ትርጉም የሌላቸው ያደርጋቸዋል። አሁንም በዚህ በተሳሳተ መንገድ በቃሉ እየተኩራሩ የሚጠቀሙት ሕዝብን ማስተማር የማገባቸው የመገናኛ ብዙሐን ሰዎች ናቸው። ያሳዝናል! ጥቂት ምሳሌዎችን ልጥቀስ።
ከዜናው በኋላ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የተዘጋጀውን የትንተና ጽሑፍ እናቀርባለን ማለት ነው። ለዚህ አረፍተ ነገር መጨረሻ ሆነው የገቡት “ማለት ነው” የሚሉት ሁለት ቃላት ለአረፍተ ነገሩ ምንድን ነው የጨመሩለት? “ከዜናው በኋላ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የተዘጋጀውን የትንተና ጽሁፍ እናቀርባለን የሚለው በቂ አይደለም? ለምንድን ነው “ማለት ነው” የተባሉት ሁለት ቃላት የተጨመሩት? ሌላ ምሳሌ፣ ዘንድሮ ትምሕርቴን በደንብ ተከታትዬ የመጀመሪያ ዲግሪየን ከያዝኩ ሥራ ሳልፈልግ በቀጥታ ለሁለተኛ ዲግሪ ማለት ለማስተርስ እመዘገባለሁ ማለት ነው። አሁንም በዚህ አረፍተ ነገር የመጀመሪያው ማለት ትክክል ሲሆን መጨረሻ ላይ የገቡት “ማለት ነው” የሚሉት ሁለት ቃላት ግን ፈጽሞ አስፈላጊ አይደሉም።
 የጠቃሽ አመልካች ሥራዋን እንዳታከናውን ተጽዕኖ እየደረሰባት ነው። ስለሆነም አባቴን ለማየት ወደ አገር ቤት እሄዳለሁ በማለት ትክክለኛው አነጋገር ፈንታ አባቴ ለማየት ወደ አገር ቤት እሄዳለሁ ሆኗል የዘመኑ አነጋገር። አባቴን፣ እናቴን፣ አገሬን እወዳለሁ የሚለው ትክክለኛ አነጋገር ቀርቶ አባቴ፣ እናቴ፣ አገሬ እወዳለሁ ሆኗል አሪፉ የዘመኑ አነጋገር። በዉ ካዕብና በው ሳድስ መካከል ያለው ልዩነት እየጠፋ በመሄድ ላይ ነው። በላሁ በማለት ፈንታ በላው እየተባለ ይጻፋል። ለመሆኑ ወዴት እየሄድን ነው? አደግን፣ ሠለጠንን ተባለና ፊደሎቻችንን መለየት ከማንችለበት ደረጃ ደረስን ማለት ነው?
የባዕድ ቋንቋዎችን በትክክል ለማወቅ መሞከርና በትክክል በጥቅም ላይ ማዋል ተገቢ ነው። ከራስ ቋንቋ በላይ (ለዚያውም በተሳሳተ መልኩ) ለባዕድ ቋንቋና ቃላት ጥገኛና ተገዥ መሆን ግን ጤነኛ አስተሳሰብ አይመስለኝም። አመሰግናለሁ።
*****************************************
* አቶ ማዕረጉ በዛብህ አንጋፋ ጋዜጠኛ ሲሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ክፍል ማኔጂንግ ኤዲተር ናቸው።
****************************************
http://www.sendeknewspaper.com/milkta/item/5545_Wednesday, 08 March 2017



  


Sunday, July 24, 2016

አባተ መኩሪያ ‹‹ተንቀሳቃሹ ቴአትር ቤት›› (1932 - 2008)


‹‹ጥበበኛ በጥበብ እግር ይመላለሳል›› (ጠቢብ የሐውር በእግር ጥበብ) እንዲሉ፣ አባተ መኩሪያ ከግማሽ ምታመት በዘለለ በኢትዮጵያ ቴአትር ሕዋ ውስጥ በጥበብ ለጥበብ ኖሯል፡፡ ለቴአትር እስትንፋሱ ነበርም ይሉታል፡፡ በርሱ ጥበብ ያለፉት ሁሉ፡፡
በጥበብ የባተው አዘጋጅ፣ የውዝዋዜ አሠልጣኝ (ኬሪዮግራፈር)፣ ጸሐፌ ተውኔት፣ የፊልም አዘጋጅ የነበረው አባተ መኩሪያ በአገሪቱ የቴአትር ታሪክ ውስጥ ስማቸው በግዘፍ ከሚነሱትና አሻራቸውን ካሳረፉ በኩሮች አንዱ ነበር፡፡ በተለይ በተውኔት አዘጋጅነት ስመ ጥር ለመሆኑ ዘመን ተሻጋሪ ተውኔቶችን ወጥ እና ትርጉሞች በማዘጋጀቱ ይጠቀሳል፡፡
ከታዋቂ ሥራዎቹ መካከል ሀሁ በስድስት ወር (1966) አቡጊዳ ቀይሶ (1971)፣ መልእክተ ወዛደር (1971)፣ የመንታ እናት (1971)፣ መቅድም (1972)፣ ጋሞ (1973)፣ አሉላ አባነጋ (1979) ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ በ19ኛው ምታመት አሐዳዊት ኢትዮጵያን እውን ባደረጉት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ላይ የተመሠረተው የጸሐፌ ተውኔት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹ቴዎድሮስ›› ነውን ከነበር ጋር ያስተሳሰረበት አዘገጃጀቱ፣ የንጉሠ ነገሥቱን ቴዎድሮስ ልዕልና ያንፀባረቀበት ነበር፡፡
ብዙዎቹ አባተ ያዘጋጃቸው ተውኔቶች በሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን የተደረሱ ሲሆኑ ረዣዥም ቃለ ተውኔት፣ ታሪክ ጠቃሽ ዘይቤዎችን ያዘሉ ናቸው፡፡ የአባተ ክሂል የተንፀባረቀውም እነዚያን ረዣዥም ቃለ ተውኔቶች (መነባነቦች) ተደራሲን በሚይዝ መልኩ እንዲመደረኩ በማድረጉ ነበር፡፡ እንደ አዘጋጅነቱም የድራማን ሥነ ጽሑፍ በምሁራዊ ዓይን አይቶ ማዳበሩን ተክኖታል፡፡
በዎርልድ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ ኮንቴምፖራሪ ቴአትር እንደተገለጸው፣ አባተ ተውኔት ተመልካቹን በግሩም ሁኔታ መቆጣጠር የሚያስችል ክሂል ነበረው፡፡ በጸጋዬ የተተረጐሙት የዊልያም ሼክስፒር ማክቤዝ፣ ኦቴሎና ሐምሌት በታዳሚው ትውስታ ውስጥ የቃለ ተውኔቱ (ግጥም) ውበት ብቻ ሳይሆን፣ ተውኔታዊ ክዋኔዎች እንዲታወሱ የሆነው በአባተ መኩሪያ አዘገጃጅ ስምረት መሆኑን ኢንሳይክሎፒዲያው አስነብቧል፡፡
ከመንግሥቱ ለማ ታዋቂ ሥራዎች አንዱ የሆነው ‹‹ያላቻ ጋብቻ›› የአባተ አዘጋጅነት እጅ አርፎበታል፡፡ አባተ ከሚታወቅባቸው የመድረክ ተውኔቶች ባሻገር በአደባባይ ላይ ባዘጋጃቸው (ከአዳራሽ ውጭ) ተውኔቶቹም ይወሳል፡፡ ‹‹ኤዲፐስ ንጉሥ›› ተውኔትን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኰንን አዳራሽ ፊት ለፊት በሚገኘውና በዘልማድ ‹‹ኪሲንግ ፑል›› በሚባለው ወለል ላይ ያሳየው ይጠቀሳል፡፡ ሐቻምና በኢትዮጵያ የተውኔት ታሪክ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፈው የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ‹‹አፋጀሽኝ›› ዳግም የመድረክ ብርሃን ያየው በአባተ መኩሪያ ነበር፡፡
አባተ ከአዘጋጅነቱ ሌላ በጸሐፌ ተውኔትነቱም ይታወቃል፡፡ ራሱ ደርሶ ራሱ ያዘጋጀው ‹‹የሊስትሮ ኦፔራ›› (1982) በወቅታዊ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የተመሠረተ በሙዚቃ የታጀበ ሥራው ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ ሽልማትም አግኝቶበታል፡፡
በዩኔስኮ አፍሪካዊ ተውኔትን በደብሊን አቤይ ቴአትር እንዲያዘጋጅ የተመረጠው አባተ፣ የጸጋዬ ገብረ መድኅንን “Oda Oak Oracle” (የዋርካው ሥር ንግርት) አዘጋጅቷል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከእንግሊዛዊው ዕውቅ የቴአትር አዘጋጅ ሰር ፒተር ሆል ጋር በኮንቬንት ጋርደን ኦቴሎን ለማዘጋጀት ዕድል አግኝቷል፡፡
መቀመጫውን በታንዛኒያ ያደረገውን የምሥራቅ አፍሪካ ቴአትር ኢንስቲትዩት በመሥራች አባልነትና በኃላፊነት ከመምራቱም ባሻገር፣ በአዲስ አበባ የመኩሪያ ቴአትር ስቱዲዮና መዝናኛ የተሰኘ ተቋምን መሥርቶ ‹‹ቴአትር ለልማት›› የሚባለውን የተውኔት አቀራረብ ፈለግ መሠረት በማድረግ ብዙ ትምህርት ሰጪ ተውኔቶችን በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተመሥርተው በማዘጋጀት ለመድረክ አብቅቷል፡፡ በታሪካዊ መዝገበ ሰብ እንደተመለከተው፣ ለመድረክ ካበቃቸው ተውኔቶች መካከል ሕሊና፣ ጠለፋ፣ ጆሮ ዳባ፣ በሐምሌ ጨረቃ ጉዞ፣ ድንቅ ሴት ሲጠቀሱ ከዘጋቢ ፊልሞችም የፍትሕ ፍለጋ እና የመስከረም ጥቃት ይገኙበታል፡፡
መኩሪያ ስቱዲዮ በየክልሉና በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ አማተር ከያንያን የቴአትር፣ የሰርከስና የሙዚቃ ሥልጠና መስጠቱን፣ ከኢትዮጵያ ውጪም ወደ ተለያዩ አገሮች እየተጓዘ ትርኢት ማቅረቡም ይታወቃል፡፡
በየዓመቱ ከሚከበረው የዓድዋ ድል ጋር ተያይዞ አባተ መኩሪያ ከነጥበብ ጓዙ የሚነሳበት አጋጣሚ ከ30 ዓመት በፊት ተፈጥሯል፡፡ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. በዳግማዊ ምኒልክ ጠቅላይ አዝማችነት፣ በወራሪው የኢጣሊያ ሠራዊት ላይ ኢትዮጵያ የተቀዳጀችው ድል በየዓመቱ ሲዘከር በቴሌቪዥን መስኮት የሚታይ የቅድመ ጦርነት ዝግጅት የቪዲዮ ምሥል የአባተ መኩሪያ ትሩፋት ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ የተመሠረተችበት 100ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓል ሲከበር ለበዓሉ ድምቀት ከተዘጋጁት አንዱ ንጉሠ ነገሥቱ ‹‹ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት›› ብለው ለዘመቻ ሲነቃነቁ ባለፉበት በባልደራስ አካባቢ በሚገኘው የቀበና ወንዝ ነባር ድልድይ አጠገብ አዲስ የተሠራው ‹‹የዓድዋ ዘመቻ መታሰቢያ ድልድይ›› የተመረቀው የዚያን ዘመን የክተት ስሪት በሚያሳይ መልኩ አምሳያ የተፈጠረላቸው ንጉሠ ነገሥቱን፣ እቴጌይቱን፣ መኳንንቱን፣ የጦር አዝማቾችን፣ ዘማቾቹን፣ ሴቶች አገልግል ተሸክመው ሁሉም እየፎከሩ እየሸለሉ የሚያሳየውን ‹‹የራስ አባተ ጦር እለፍ ተብለሃል…›› ወዘተ እየተባለ በ400 ተሳታፊዎች የቀረበው ክዋኔ ለዘመን ተሻጋሪነት የበቃው በአባተ መኩሪያ ነበር፡፡ አባተ ዓድዋንና ድሉን የሚዘክር ላቅ ያለ ይዘት ያለውን የዓድዋ ፊልም ፕሮጀክትን ከአራት ዓመት በፊት ቢቀርጽም፣ በወቅቱም በ35 ሚሊዮን ብር በጀት ሊሠራ መታቀዱንና ፕሮጀክቱን ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በበላይ ጠባቂነት እንደያዙት ቢነገርም እስካሁን ድምፁ አልተሰማም፡፡
ትምህርትና ኃላፊነት
አባተ በትምህርት ዝግጅቱ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በእንግሊዝኛና በንኡስ ትምህርት (ማይነር) ድራማን በማጥናት አግኝቷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በጀርመን ብሮድካስቲንግ ኢንስቲትዩት በፊልምና ሚዲያ ሲሠለጥን ከለንደን ኦፔራ ሴንተር የኦፔራ ትምህርት፣ በአየርላንድ አቤይ ቴአትርና በአሜሪካ ቴአትርና ሙዚቃ በምሥራቅ አውሮፓና በአፍሪካ አዘገጃጀትን አጥንቷል፡፡ የተለያዩ አገሮች ትምህርታዊ ጉዞም አድርጓል፡፡
በሥራ አገልግሎትም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት (የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር) የቴአትር ዳይሬክተር፣ እንዲሁም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኪነ ጥበባት ወቴአትር (ባህል ማዕከል) ዳይሬክተር ሆኖ ሠርቷል፡፡
በ1950ዎቹ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹መዝናኛ በክዋኔ ጥበባት›› (Entertainment in Performing Arts) በሚል ርዕስ በየሳምንቱ ዓርብ ለአንድ ዓመት የዘለቀ ፕሮግራም ማዘጋጀቱን፣ ፕሮግራሙም የአዝማሪ ጨዋታ በኢትዮጵያ ሕዝብና በክዋኔ ጥበባት ውስጥ የነበራቸውን ሚና ይዳስስበት ነበር፡፡ የተለያዩ ብሔረሰቦች ባህልን፣ እምነትን፣ ደስታን፣ ሐዘን፣ ወዘተ በጥበብ አንፃር ይታይበት እንደነበር፣ ቤተ ክህነት ለጥበቡ ዕድገት ያደረገችውን አስተዋጽኦ ከታዋቂ የጥበብ ሰዎች ካበረከቱት ሥራ ጋር የሚቀርብበት እንደነበር ገጸ ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ለምሳሌ ጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹የከርሞ ሰው›› የሚለውን የጻፈውና ሙላቱ አስታጥቄ ለከርሞ ሰው ሙዚቃውን የሠራው በዚሁ የአባተ ፕሮግራም ነበር፡፡
አባተ ከብሔራዊ ቴአትር ሌላ በሀገር ፍቅር ቴአትር፣ በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ በአዘጋጅነት፣ በጸሐፌ ተውኔትና መራሔ ተውኔትነት እንዲሁም በኃላፊነት ጭምር አገልግሏል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ ነበር፡፡ ባለፈው ታኅሣሥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከል ‹‹ዝክረ አባተ መኩሪያ›› ብሎ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ዲን አቶ ነቢዩ ባዬ እንደተናገረው፣ ‹‹አባተ የዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት በትክክለኛው መሠረት ላይ እንዲገኝ የላቀ ሚና ተጫውቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የኪነ ጥበብ የፈጠራ ማዕከል እንዲቋቋም አሻራውን አኑሯል፡፡ የተለያዩ የቴአትር ንድፈ ሐሳቦችን በማቅረብ ግንባር ቀደም አርቲስት ነው፡፡››

ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያን የቴአትር ዕድገትና የተመልካቹን ሁኔታ በተመለከተ አባተ መኩሪያ በአንድ መድረክ የተናገረውን የፋንታሁን እንግዳ ‹‹ታሪካዊ መዝገበ ሰብ›› እንዲህ ገልጾታል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ባህል አትኩሮ የሚያጣጥምና የሚወድ ነው፡፡ ቴአትር ቤቱ ይሞላል፡፡ ግን ከቴአትር አንፃር (ከድርሰቱ) ያየነው እንደሆነ ብዙ የሚተቹ ነገሮች አሉ፡፡ እንደ ቴአትር አዋቂ ተመልካች ቴአትሮቹን ብናያቸው ብዙ ግድፈቶች እናገኛለን፡፡ ተመልካቹ ለዚያ ሁሉ ደንታ የለውም፡፡ የራሱን ሕይወት ማየት ይወዳልና ይመጣል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥበቡ ሳይሆን ተመልካቹ ነው የሚፈታተነን፡፡ ደግሞ የኛን አገር ቴአትር እንዳያድግ የገደለው ቴአትር ቤቶች በመንግሥት እጅ መሆናቸው ነው፡፡ ቴአትር ቤቶች አንድ ዓይነት ሥራ ነው የሚሠሩት፡፡››
የአባተ የጥበብ ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ውጣ ውረዶችን አይቷል፡፡ ቀዳሚው ፈተና በዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ጐን ለጐን በኪነ ጥበብ ወቴአትር (ክሬቲቭ አርት ሴንተር) በሚሠራበት አጋጣሚ በነበረው የግጥም ጉባኤ ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ ያቀረበው ‹‹ላም እሳት ወለደች በሬ ቀንድ አወጣ፣ በሥልጣን ሊቅ መሆን ይህም አለ ለካ›› ግጥም በዩኒቨርሲቲው ኃይለኛ ቁጣ በመቀስቀሱ ማዕከሉ ይዘጋል፡፡ አባተን ጨምሮ ሁሉም ባልደረቦች እንዲባረሩ መደረጉ አንዱ ነው፡፡
በየዐረፍተ ዘመኑ በሦስቱ ሥርዓተ መንግሥታት ፈተና አልተለየውም፡፡ ቴአትር ቤቶች መድረክም ነፍገውት ነበር፡፡ የሎሬት ጸጋዬ የተውኔቶች መድበል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በተመረቀበትና ቅንጫቢ ትዕይንቶች በቀረቡበት ጊዜ መድረክ እንደሚሰጠው ቢነገርም የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡
ለዚህም ይመስላል በታኅሣሡ የብሔራዊ ባህል ማዕከል የአክብሮት መድረኩ ላይ አባተ ለተሰጠው ሽልማትና ለደረቡለት ካባ ምስጋናውን ያቀረበው፣ ‹‹እባካችሁ መድረክ ስጡኝ ልሥራበት፡፡ እኔ ሠርቼ አልጠገብኩም፤ ገና ብዙ መሥራት እፈልጋለሁ፤ ስለዚህ እባካችሁ መድረኩን ስጡኝ፤›› ብሎ በመማፀን ነበር፡፡ ሳይሆንለት አዲሱ ትውልድም ነባሩን ብሉዩን (ክላሲክ) የነጸጋዬ ገብረመድኅን ሥራዎችን በአባተ መኩሪያ አጋፋሪነት ሳያይ አመለጠ፡፡
ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 1932 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አዋሬ ሠፈር ከአባቱ ከአቶ ስለሺ ማንደፍሮና ከእናቱ ከወ/ሮ ውብነሽ መኩሪያ የተወለደው አባተ መኩሪያ፣ የእናቱ አባት ስምን እንደ አባት የወሰደው አያቱ ‹‹እኔ ነኝ የማሳድገው›› ብለው በስድስት ወሩ ወስደው ስላሳደጉት ነው፡፡ በተወለደ በ76 ዓመቱ ሐምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ያረፈው አባተ በማግሥቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡ ከ42 ዓመት በፊት ከወ/ሮ ምሕረት አረጋ ጋር ጎጆ የቀለሰው አባተ ቴዎድሮስና ውቢት የተባሉ ሁለት ልጆቹን ሲያፈራ የልጅ ልጆችም አይቷል፡፡
በዐውደ ምሕረቱ ላይ የሕይወት ታሪኩን ያነበበው ከዕለታት ባንዱ ዕለት ‹‹ራሴን ፈልጌ እንዳገኝ የገራኝ፣ መንገዱን ያሳየኝ፣ የገሰፀኝ፣ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ያበቃኝና ያሳደገኝ የጥበብ አባቴ ነው፤›› ያለው ታዋቂው ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም ነበር፡፡
እንዲህም አነበበ፤ ሕፃኑ አባተም በአያቱ አባትነት ያድጋል፡፡ አያቱ አባትም ሆነውታልም፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስማቸው መጠሪያው ሆነ፡፡ እነሆም በተግባር የናኘው የዛሬው ገናን ስም ‹‹አባተ መኩሪያ!›› እንዳባተ እንዳኮራ ዘመናትን ሊሸጋገር በቃ! የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት (ኮከበ ጽባሕ) ሲከታተል፣ አቶ መኩሪያ ልጃቸው ነገረ ፈጅ እንዲሆንላቸው ቢፈልጉም አባተ ግን ‹‹በፊደል ነው የተለከፍኩት!›› እንዲል እሱ ያገዘፈው የ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››ሩ ገጸ ባሕሪ፣ እሱውም ‹‹በጥበብ ነው የተለከፍኩት!›› ብሎ ጥበብን የሙጥኝ አለ፡፡ ተለክፎም ቀረ! መለከፉም ለመልካም ሆነ፡፡ ተከታታይ የጥበብ ትውልድ ፈጠረ፤ እሱውም በትውልዶች ውስጥ ኖረ፡፡ …ከዚያስ በሰባ ስድስት ዓመቱ… ተንቀሳቃሹ ቴአትር ቤት አረፈ!
**********************************************
ምንጭ:--- http://www.ethiopianreporter.com/ _ እሁድ  ሐምሌ 17  ቀን 2008 ዓ. ም.

Tuesday, March 15, 2016

የግጥም ጣዕም


                ደበበ ሰይፉ
**************************
ውል አልነበረንም የፍቅር ቀጠሮ
ቃልም አላኖርንም በወግ ተቀምሮ፤
እኔ አንቺን እንዳላይ
አንቺ እኔን እንዳታይ አምባችን ተቃጽሮ
ዕጣችን ተካሮ፤
ቀለምሽ ከዐይኔ አሻራሽ ከጣቴ ባይጠፋ ተማትሮ
(እትብት እምብርት ሁኖ እንዲኖር ደድሮ)
ይኸው አካሄደን በድንገት ዘንድሮ።
የገጽሽ ብርሃን ቢጠይም ፀዳሉ
ድምፅሽ ቢቀጥንብኝ ቢሠልብኝ ቃሉ
ወዘናሽ ቢማስን ዛሬ ያለውሉ
በእጆችሽ ጨበጠኝ ሐዘንሽ ሥዕሉ
ሐዘንሽ አመመኝ
ብሶትሽ ጠቀሰኝ።
ጀንበር ነሽ አበባ ሕይወት ተስፋ ዘቦ
ፋሲካ ዕንቁጣጣሽ ማኅሌተ ገንቦ
በዬ ያወደስኩበት ታዘበኝ ዘመኔ የትላንታት ቀኔ
ዛሬ ሊጮህብኝ ቅኔ እንዳይደል እውኔ፤
ሐዘንሽ አመመኝ
ብሶትሽ ጠቀሰኝ።
የገደል ማሚቶን ታዘብኳት ተኝታ
በጩኽትሽ ማየል አኩርፋና ታክታ
ላንቃዋ ይታየኛል ደም ለብሶ ደም ጐርሶ
ቃልሽ ያለፈበት በጭንቅ ተለውሶ፤
ሐዘንሽ አመመኝ
ብሶትሽ ጠቀሰኝ።
ጽጌሬዳይቱ ንቦችሽ አለቁ ሰዎችሽ ደቀቁ
ጨፌ ላይ ተኝተው ባድማ ላይ ነቁ፤
ዐዋይን ሰማኋት ስታለቅስ በይፋ
ከጐጆሽ ስትወጣ ትቢያዋን አራግፋ፤
ሐዘንሽ አመመኝ
ብሶትሽ ጠቀሰኝ።
አላውቅልሽ ብዬ አታውቂልኝ ብዬ
እምነትሽን ጥዬ ፍቅርሽን ገድዬ
አኩርፌሽ ስቀመጥ ያው እንደ ባላንጣ
ይኸው ነጭ ማተብሽ ሊያስታርቀን መጣ፤
ሐዘን ነው ውበትሽ ውበት ነው ፍቅርሽ
ብርሃንጥለት አልቦ ከል ነጠላሽ
ዐይኔን የገለጠው ጥቁር ጨለማሽ፤
ሐዘንሽ አመመኝ
ብሶትሽ ጠቀሰኝ።
******************
ግንቦት 1966..
ደበበ ሰይፉ