ከደራሲያን ዓምባ

Friday, July 30, 2021

ድምፀ-ነጎድጓዱ ጋዜጠኛ ታደሠ ሙሉነህ

ጋዜጠኛ ታደሠ ሙሉነህ (1938 ዓ.ም. - 2004 ዓ.ም.)
  • ድምፀ-ነጎድጓዱ ጋዜጠኛ
  • ድምፀ ሸጋው ጋዜጠኛ
  • ራሱ ታደሠ ሬድዮ ነው።
  • የኢትዮጵያ ሬድዮ የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም ጀማሪ
  • ጋሽ ታዴ ...

"ዜና እንደሙዚቃ ተደመጠ ማለት፣
 ታደሰ ተረኛ ሆኖ የገባ ዕለት።"       ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ ጋሽ ታዴ  የተቀኝለት

 አንጋፋው ጋዜጠኛ ጋሽ ታደስ ሙሉነህ በሸገር ሬድዮ በትዝታ ዘአራዳ












Tuesday, May 18, 2021

ይህ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ነው

 

“የሕዝቡን ዐይን በሬዲዮ እንክፈት” 

በሚል በፈር ቀዳጅነት የተተከለው የኢትዮጵያ ሬዲዮ፤ 

የ85ኛ ዓመት ሻማውን 
(መስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም.) ለኮሰ።


 

በአሁኑ ወቅት ንፋስ ስልክ በሚል የምናውቀው አካባቢ ስሙን ያገኘው ሬዲዮ ለሚለው ቃል ሀገራዊ መጠሪያ ሲወጣለት በነፋስ የሚሄድ “ያለ ሽቦ ቃል የሚያሳልፍ መኪና” ተብሎ ከመሰየሙ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ታሪክ ከቴሌ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የቴክኒክ ሰራተኞቹ ቅጥር በቴሌ ስር ነበር፡፡ በቀደምቱ ጊዜ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ለሚሰራ ጋዜጠኛ ትልቁ እድሉ ከአንጋፋዎቹና ነባሮቹ ጋር መካከለኛዎቹና አዲሶቹ ተጣምረው ስለሚሰሩ ደቀ መዝሙሮቹ ከመምህሮቹ የካበተ እውቀትና የተፈተነ ልምድ የሚቀስሙበት ሰፊ እድል ነበር፡፡ ጀማሪዎች ወደ ህዝብ ከመቅረባቸው በፊት በሙያ ተገርተው ተቃንተው እውቀትን ከክህሎተ በማዳበር የሙያ ስነ ምግባርን ከማህበራዊ ህይወት አዋዶ ለመማር የሚያግዝ ታላቅ ኮሌጅ ነው ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡

ግርማዊ ቀዳማዊ ሀ/ስላሴ የማእዘን ድንጋይ በ1923 ሲያስቀምጡ “ያለሽቦ ቃል የሚያሳልፍ መኪና” ብለው ነበር ሬዲዮን የጠሩት፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮ የኢጣሊያ አንሶልዶ ኩባንያ በንፋስ ስልክ አካባቢ በሰራው ሬዲዮ ጣቢያ ስራውን መስከረም 2 / 1928 ጀምሮ ዛሬ ላይ 85ኛ አመቱን ሲያከብር የመጀመሪያዎቹ የሬዲዮ አንባቢዎች ከወንዶች ከበደ ሚካኤል ከሴቶቸ ደግሞ ወ/ሮ ሮማነወርቅ ካሳሁን ይጠቀሳሉ፡፡

ዲዮው ያኔ ከአ/አ ርቆ አለመሰማቱ ብቻ ሳይሆን ፉጨትና ይጮህም ስለነበር ጥራት ይጎድለዋል፡፡ ግርማዊነታቸው በነገሱና ሬዲዮውም በጀመረ አጭር ጊዜ ውስጥ ኢጣሊያዎች ጣቢያውን አስቀርተው የራሳቸውን ጣቢያ አቡነ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ መስርተው ዘመናዊ ትምህርት ያላቸውን ኢትዮጵያውያን አሳደው መግደልና የተረፉትንም ለራሳቸው ቢሮ ግልጋሎት እየነጠቁ ከተወሰዱት መካከል ብላታ ወ/ጊዮርጊስ ወ/ዮሀንስና ከበደ ሚካኤል ይጠቀሳሉ፡፡ ጣቢያውንም አፍሪካ ኦሪዬንታሌ ኢታልያና በማለት የኢጣሊያ ምስራቃዊ አፍሪካ ሬዲዮ በማለት በኢትዮጵያ _ በኤርትራና በሶማሊያ ሀገርን የሚያዳክም ፐሮፖጋንዳ ይሰራጭበት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮም በ1933 ቀድሞ ወደነበረበት ንፋስ ስልክ አልተመለሰም፡፡

በይዘት ደረጃ ደግሞ ከ1950ዎቹ ወዲህ በእንግሊዝኛ ውጭ ተምረው የመጡት እነ ጋሽ ሉልሰገድ ኩምሳ ‘ ወ/ሮ እሌኒ መኩሪያ እና ሳሙኤል ፈረንጅ አይዘነጉም፡፡ ያኔ በሞጋችና በይዘት ጥልቅ ቅንብሮቻቸው ስመጥር ከነበሩት መካከል አሳምነው ገ/ወልድ ‘ በመምህሬ አብራራው መጠሪያ የሚታወቀው መንግስቱ መኮንን ‘የስፖርቱ ሰለሞን ተሰማ ‘ በአጠቃላይ ትንተን አሀዱ ሳቡሬና አቶ ነጋሽ ገ/ማርያም በሳይንስ ሻምበል አፈወርቅ ዮሀንስ ‘ ጳውሎስ ኞኞ ‘ በአሉ ግርማ እንዲሁም በጥበባት ደግሞ ዮሀንስ አድማሱ ‘ አብዬ መንግስቱ ለማ ‘ ሰአሊና ገጣሚ ገ/ክርስቶስ ደስታ ‘ ሰለሞን ደሬሳና ተስፋዬ ገሰሰ “የኪነ ጥበባት ጉዞ” የሚል ፕሮግራምን ያዘጋጁ ነበር፡፡

ያኔ በሬዲዮ ጅማሮው ወቅት የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት ድጃዝማች ግርማቸው ተ/ሀዋርያት በ1954 የአለም አቀፍ አገልግሎቱ ጅማሮ ሁነት ላይ፡_ “ከእንግዲህ ወዲህ ኢትዮጵያ ወዳጅ በሆኑት አፍሪቃ ‘መካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ የምትሰማ ይሆናል፡፡ ከአለም ህዝቦች ጋር ለመቀራረብም እንደሚረዳ የታመነ ነው ብለው ነበር፡፡

እኔ ከ1980ቹ አጋማሽ ወዲያ ከዩኒቨርስቲ ወጥቼ ከጥቂት ወራት መምህርነት ቀጥሎ ዜና ፋይልን ስቀላቀል ከአንጋፋዎቹ ጋሽ ጥላሁን በላይና ከጋሽ ዳሪዎስ ሞዲ አለቆቻችን አንስቶ ‘ የፈረቃ መሪዎች ከነበሩት እጅግ ነባሮቹ ዳንኤል ወ/ሚካኤል ‘ በቃሉ ደገፋው ‘ ንግስት ሰልፉ ‘ ዋጋዬ በቀለና ነጋሽ መሀመድ ነበሩ፡፡ በመቀጠል አሁንም ከነባሮቹ መካከል አማረ መላኩ ‘ ተካልኝ ይርሳው ‘እ/ህይወት ደምሴ ‘ ደበበ ዱፌራ ‘ ገነት አስማረ ‘ ተስፋዬ መክብብ ‘ አለምነህ ዋሴ ‘ ደስታ ሎሬንሶ ‘ብርትኩዋን ሀ/ወይን ‘ ተፈሪ አንለይ ‘ ተፈሪ ለገሰ ‘ ሺበሺ ጠጋዬና ቴዎድሮስ ነዋይ ሲወሱ በተከታይነትም እሸቱ ገለቱ ‘እሸቱ አበራ ‘እሸቱ አለሙ ‘ ስለሺ ሽብሩ ‘ ደግነህ ገ/ስላሴ ‘ ዘመድኩን ተክሌ ‘ ብሩከ ነጋሽ ‘ ታደሰ ዝናዬ’ አማኑኤል አብዲሳ ‘አዲስ አለማየሁ ‘ የኔነህ ከበደ ‘ አብዱልሰመድ መሀመድ ‘ቢኒያም ከበደ ‘ ለምለም በቀለ ‘ እያደር አዲስ ‘ዳንኤል አማረ ‘አለማየሁ ግርማ ‘ ሰለሞን ግዛው ‘ ሳሙኤል ፍቅሬ ‘ ሲሳይ ዘሪሁን ‘ ጌታሁን ንጋቱ ‘ ምናላቸው ስማቸው ‘ሀ/እየሱስ ወርቁና ጋሻው ተፈራ ነበሩ፡፡

ከዚህ ወዲያ ነበር እነ አሸናፊ ሊጋባ ‘ ነጣነት ፈለቀ ‘ አዲሱ መሸሻ ‘ ሰሎሜ ደስታ ‘ሰኢድ ሙሄ እና ሰለሞን ዮሀንስ የተቀላቀሉን፡፡ ከዜና ክፍል ጋር በስፖርቱ ጋሽ ይንበርበሩ ምትኬ ‘ ጎርፍነህ ይመር ‘ ደምሴ ዳምጤ ‘ ዳዊት ንጉሴ ‘ ዳንኤል ጋሻውና ታደለ ሲጠቀሱ ለፕሮግራም ስራ መስክ በወጡ ቁጥር ዜና ይዘው ከሚመጡት መካከል ደግሞ ሞገስ መኮንን ‘ አስቻለው ጌታቸው እና ነቢያት ገቢሳ አይዘነጉኝም፡፡

በኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ጥበባዊ ዝግጅቶችን በማቅረብም እነ ጋሽ ታደሰ ሙልነህ ‘ንጉሴ አክሊሉ ‘ አዲሱ አበበ ‘አባይነሽ ብሩ ‘ታምራት አሰፋ ‘ጠሀይ ተፈረደኝ ‘ደረጀ ሀይሌ ‘ዳንኤል አያሌው ‘ ጌታቸው ማንጉዳይ ‘ ቤዛዬ ግርማ ‘ ነጋሽ ግዛው ‘ሰለሞን ደስታ ‘ ሂሩት መለሰ ‘ደጀኔ ጥላሁን ‘ አስፋው ገረመው ‘ በልሁ ተረፈ ‘ ልባርጋቸው ሽፈራው ‘ብርሀኑ ገ/ማርያም ‘ ቅድስት በላይ ‘ መስፍን ዘለቀ ‘ አምባዬ አማረ ‘አስካለ ተስፋዬ ‘ ዘውዱ ግርማና መሳይ አለማየሁ ሲሆኑ ከብሄራዊ ሬዲዮ አገልግሎቱ የተዛወሩትንም ለአብነት እንዳልካቸው ፈቃደ ‘ አስቻለው ሽፈራው ‘ ኤልሳቤት ሳሙኤል ‘ ማርታ ጠጋውና አበበ ፈለቀ ሊነሱ ይችላሉ፡፡

ከ1956 ወዲህ ሰፋ ያለ አካባቢን የሚሸፍን በ9 ቦታዎች ማሰራጫ በመትከል ለማሻሻል ታስቦ በገንዘብ ውሱንነትን የየአካባቢው የፖለቲካ ሽፍታ በትንሽ መሳሪያ ጣቢያውን በመቆጣጠር ንጉስ ሆኛለሁ እያለ ስጋት እንዳይጭር በሚል በ3 ቦታ ብቻ ተወስኖ በአዲስ አበባ ጌጃ ዴራ _ በአስመራ አዲ ኡግሪ እንዲሁም በሀረር ሀኪም ጋራ ላይ ተተከለ፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮ የማሰራጫ አድማሱን በማስፋት ከ1984 ወዲህ የመቱ ማሰራጫ አኙዋክና ኑዌርን ከጨመረ አንስቶ በ11 የመግባቢያ መንገዶች መረጃዎችን ለህዝብ እያቀበለ እንደቀጠለ ነው፡፡ ከ1959 ወዲያ ግርማዊነታቸው በ35ኛው የዘውድ በአላቸው ሰፊ ሽፋን ያለውን ማሰራጫ አስመርቀው የአዲስ አበባ ብቻ በሚል ይጠራ የነበረው የኢትዮጵያ ለመባል በቃ፡፡

በተማከለ መልኩ የሬዲዮ ዜና ማእከል ሁሉንም ዴስኮች ካሰባሰበ ወዲያ ከኦሮምኛ እነ ጋሽ ተስፋዬ ቱጂ ‘ ሀሊማ ኢብራሂም’ ዮሀንስ ዋቆ ‘ፉሪ ቦንሳ ‘ ጋሸ አለማየሁ ‘ ጋሽ ሁሴን ‘በዳሶ ሀጂ ‘ መክብብ ሸዋ ‘ኢሳ ኡመር ‘ ካሳሁን ፈይሳ ‘ራሄል ግርማ ከብዙ በጥቂቱ ሲታወሱ ከትግርኛ ደግሞ እነ ነጋ ‘ተወልደ ‘ ኪሮስ ‘እዮብ ‘ ብርሀነ ‘ትርሀስ ‘ አማን አሊ ‘ ገ/አምላክ ተካ ‘ አክሊሉ ደባልቀው ‘ አሰፋ በቀለ ‘አልማዝ በየነና ዮናስ አይዘነጉም፡፡

ከአንግሊዝኛ ዴስክ ጋዜጠኞች እነ ጋሽ ዮሀንስ ወ/ሩፋኤል ‘ ግሩም ታሪኩ ‘ መለሰ ኢዳ ‘ስለሺ ዳቢ ‘ ባህሩ ተመስገን ‘ፍ/ህይወት ‘ ንግስት ‘ቴዎድሮስ ዘውዴ ‘ ሲሳይ ሀ/ስላሴ ‘ ብሩኬ ከብዙ በጥቂቱ ሲነሱ ከፈረንሳይኛ እነ ጋሽ ጌታቸው ተድላ ‘ ጋሽ ፍራንሲስ ‘ጋሽ ተስፋዬ ‘ ርብቃን እናውሳና ከአረብኛ እነ ጋሽ አደም ኡስማን ‘ሼህ ኢብራሂም ‘ ጋሽ መኮንን ‘ ከድርና ካውሰር ይጠቀሳሉ፡፡ ከሶማሊኛ ጋሽ ጊሬ ‘ ሀሰን እና አብዱላሂን ሳንዘነጋ አፋር ዴስክ ጋ ስንሻገር እነ አብዲና አህመድን ሳንጠቅስ አናልፍም፡፡

ከ1990ዎቹ ወዲያ የመጡትን ደግሞ ከአሸናፊ ሊጋባ በከፊል ወስጄ የሚከተሉትን ለመጥቀስ ያህል ብሩክ ያሬድ ፣ አብዲ ከማል ፣ የትምወርቅ ዘለቀ ፣ ፍትሃወቅ የወንድወሰን ፣ ሀና ተሟሪ ፣ ፋሲል ግርማ ፣ ህይወት ደገፉ ፣ መሰረት ተመስገን ፣ እያሱ ፈጠነ ፣ ሰለሞን ገዳ ፣ ሰይፉ ገብረጻድቅ ፣ እየሩሳሌም ተክለጻዲቅና ሌሎችንም እናንተው አክሉበት፡፡

በመዝናኛው ዛሬ ላይ የሸገር ሬዲዮ ባለቤት የሆኑት እነ መአዛ ብሩና ተፈሪ አለሙ _ የኢትዮ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ታላቅ ባለድርሻዎች በአብዬ ዘርጋው የሚታወቀው ሰራዊት ፍቅሬና ሰይፉ ፋንታሁን እንዲሁም የአሻም ቲቪ ባለድርሻዎቹ እነ ሱራፌል ወንድሙ ‘ ግሩም ዘነበ ብሎም በግዞ ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ መለያው የነበረው የባላገሩ ቲቪ ባለድርሻው አብረሃም ወልዴ _ እነ አብረሀም አስመላሽና እከ ንብረት ገላውን ጨምሮ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ስራቸው ለምልሞ ያደጉ ናቸው፡፡ በሀገር ቤትና ውጭ ያሉና የነበሩ እነ አሸናፊ ዘደቡብ ‘እሸቴ ከጃን ሜዳ ‘ ዳንዴው ሰርቤሎ ‘ ቀስቶ ከኮተቤ ‘እነ ሀይሉ ጠጋዬ ‘ ተመስገን አፈወርቅ ብቻ ማንን ጠቅሼ ማንን ልተው የዘለልኩትን አክሉበት፡፡

ከቴክኒክ ክፍሉ ከእነ ጋሽ ተካ ወ/ሀዋርያት ‘ ጋሸ ገበየሁ ኑሬሳ ‘ መቅደስ አማረ ‘ ትርሲት ወንድሙ ‘ አቢ ‘ ይትባረክ ‘የአይኔአበባ ተክሌ ‘ በለጥሻቸው ‘ ሰላማዊትና ቤቲ ከብዙ በጥቂቱ እንዲሁም ከማሰራጫ ጋሸ ከበደ ጎበና ‘ጋሽ መላከ ‘ ኢ/ር ዘገየ ‘ጋሽ ካሳ ሚልኮ ‘ ሲሳይ ‘ክንዱ ‘ዘሪሁን ‘ ገረመው ‘ ተስፋዬ ‘ዳዊት ‘ ለዊ በተጨማሪነትም በሞኒተሪንግና ታይፕ እነ ሙሉ ‘ገነት ‘ ቆንጂት ‘ታየች ‘ጥሩዬና ሰናይት ‘ መስፍኔ ‘አስኒ ‘ ብዙዬ እና አሰለፍ አይረሱኝም፡፡

ያኔ ከወረራው ወዲህ በ1934 ኢትዮጵያ ሬዲዮ ተመልሶ እንደገና በቀን የ4 እና 5 ሰአት የቀጥታ ስርጭቱን ሲቀጥል 3 አላማዎች ነበሩት፡፡ ያኔ በጃንሆይ በድልድሉ መሰረት . . . 1 _ ዜናን ኢንፎርማሊያን . . . 2 _ ትምህርታዊ ኢጂኬሽን . . . 3 _ አዝናኝ ኢንተርቴይንመንት ሆነው በምጣኔ ረገድ 60 በመቶው አሳዋቂና አስተማሪ መሆን ሲጠበቅባቸው ቀሪ 40 በመቶው እጅ ደግሞ ለመዝናኛ እንዲሆን ተወስኖ ነበር፡፡ (*የጋዜጠኛ እሸቱ ገለቱ ጽሑፍ)


የኢትዮጵያ ሬዲዮ ትዝታ: በ አርትስ ቲቪ በነገራችን ላይ ክፍል _፩ 

የኢትዮጵያ ሬዲዮ ትዝታ: በ አርትስ ቲቪ በነገራችን ላይ ክፍል _፪

የኢትዮጵያ ሬዲዮ ትዝታ: በ አርትስ ቲቪ በነገራችን ላይ ክፍል _፫




 




Monday, May 3, 2021

ሚሻ ሚሾ (ሙሾ)

 


 ከበዓለ ስቅለት ባህላዊ መገለጫዎች አንዱ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚዘወተረው ‹‹ሚሻ ሙሾ›› ነው፡፡

ስለዚህ ባህላዊና ትውፊታዊ ሥርዓት ቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ መታፈሪያ ‹‹መዝገበ በረከት ዘሰሙን ቅድስት›› በተሰኘውና መሰንበቻውን ለንባብ በበቃው መጽሐፋቸው ዘርዘር አድርገው ማስረጃዎች እያጣቀሱ አቅርበውታል፡፡

በደራሲው አገላለጽ፣ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ወንዶች ሕፃናት ደግሞ ‹‹ሚሻ ሙሾ›› እያሉ እየዘመሩ በየቤቱ እየዞሩ ዱቄት ይለምናሉ፡፡ በዓሉ በቂጣ ስለሚከበር የአይሁድ የቂጣ በዓልን ይመስላል፡፡ አለቃ ታየ ገብረ ማርያም በ1902 ዓ.ም. በታተመው የትብብር ሥራቸው ‹‹ሚሻ ሚሾ›› የሚለው ስያሜ የት መጣ ‹‹ውሾ ውሾ›› ከሚል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህ ‹‹ማኅበራዊ ኑሮ በኢትዮጵያ›› ብለው በሰየሙት መጽሐፋቸው፣ ይህም አይሁድን ለመስደብ የተሰነዘረ እንደሚመስል ይገልጻሉ፡፡ በሌላ መልኩ መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ደግሞ ‹‹ሚሻ ሚሾ›› ወዲያ ወዲህ፣ ከዚያ ከዚህ ማለት ነው፡፡ ይህም ከየቤቱ ዱቄቱ የሚሰበሰብ መሆኑን ለማመልከት ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም የትውፊቱ ትክክለኛ መጠሪያ ‹‹ሙሾ ሙሾ›› የክርስቶስን ሕማም ለመግለጽ የተሰጠ መሆኑን፣ በጊዜ ሒደት ተለውጦ ‹‹ሚሻ ምሾ›› መባሉንም ይገልጻሉ፡፡

አለቃ ደስታ ተክለ ወልድም የቃሉን ፍች ‹‹ሙሾ (ምሾ) የለቅሶ ዜማ፣ የለቅሶ ቅንቀና፣ ግጥም፣ ዜማ፣ ቁዘማ፣ እንጉርጎሮ፣ ረገዳ፣ ጭብጨባ ያለበት›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ ይኼኛው ሐተታ ከክዋኔው ጋር ቀጥታ ቁርኝት አለው፡፡ ሕፃናቱ በየቤቱ መሄዳቸው አይሁድ ሐሙስ ሌሊት ከሐና ወደ ቀያፋ፣ ከቀያፋ ወደ ሊቀ ካህናቱ ቤት መዞራቸውን ለመዘከር ነው፡፡ ሕፃናት ይህን ዕለት እንዲያስታውሱት በየዓመቱ እንዲዘክሩ በማድረግ ይቻል ዘንድ ሊቃውንት ይህንን ሥርዓት እንደሠሩ ይናገራሉ፡፡

‹‹ሕፃናት ከምሴተ ሐሙስ ጀምረው እስከ በዓለ ስቅለት ምሽት የሚሻ ሙሾን ዝማሬ እያሰሙ በየቤቱ በመዞር ዱቄት የሚያሰባስቡት ትውፊታዊ ክዋኔ አለው፡፡ ሕፃናቱ በየቤቱ ዱቄት ለመሰብሰብ ሲዞሩ በቀለማት ወይም በእሳት ተለብልቦ የተዥጎረጎረ ቀጭን ዘንግ ይይዛሉ፡፡ መሬቱን በዘንግ በመምታት ዱቄት እስኪሰጣቸው ድረስ በተለያዩ ግጥሞች የታጀበ ዝማሬ ያሰማሉ፡፡ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዘንግ መመታቱን ለማዘከር ነው፡፡

 


 

በዝማሬያቸው

‹‹ሙሻ ሙሾ ስለ ስቅለቱ

አይንፈጉኝ ከዱቄቱ፡፡

ሚሻ ምሾ፣ ሆ ሚሻ ሙሾ

ሳይጋገር መሸ፣

እሜቴ ይውጡ ይውጡ

ይበላዋል አይጡ፣

እሜቴ ይነሱ

ይንበሳበሱ፣

ከቆምንበት

ቁንጫው ፈላበት፣

ስለ አቦ

ያደረ ዳቦ፣

ስለ ስቅለቱ

ዛቅ አድርገው ከዱቄቱ፤››

በማለት ይዘምራሉ፡፡

ሕፃናት ሚሻ ሙሾ ብለው አንድ ቤት ሲጨፍሩ ከቤቱ ዱቄት፣ አዋዜ፣ ቅባኑግ ወይም ጨው ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ ይኼንን ሲያገኙ 

‹‹ዕድሜ የማቱሳላን፣

 ጽድቅ የላሊበላን ይስጥልን፤›› ብለው መርቀው ይሄዳሉ፡፡ 

በተጨማሪም ሕፃናት በዚህ ክዋኔ ታላቅ ምርቃት ይሰጣቸዋል፡፡ ሕፃናቱ ለምነው ምንም ነገር ሳይሰጣቸው ከቀረ

‹‹እንደ ሰፌድ ይዘርጋሽ፣ 

እንደ ማጭድ ይቆልምሽ፣ 

ቁመት ያውራ ዶሮ፣ 

መልክ የዝንጀሮ፣ 

ግማት የፋሮ ይስጥሽ፤›› ብለው ተራግመው እንደሚሄዱ አለቃ ታየ ትውፊቱን አስቀምጠዋል፡፡

ሕፃናቱ በልመና ባገኙት ዱቄት ቂጣ ጋግረው ቅዳሜ ምሽት በጋራ ይመገቡታል፡፡ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህ ግን ዳቦውን በትንሣኤ ሳምንት አስጋግረው ጎረቤቶችንና ሽማግሎችን ጋብዘው እንደሚበላ ተናግረዋል፡፡

 ******+++******


 

አርብ ፦ሚሻሚሾ

ሆሆ ሚሻ ሚሾ ሚሻ ሚሾ
አንድ አውራ ዶሮ እግሩን ተሰብሮ
እሜቴ ይነሱ ጉሽጉሻውን ይዳስሱ
ስለ ስቅለቱ ዛቅ አድርገው ከዶቄቱ


እያሉ ህፃናት ተሰብስበው በየቤቱ እየዞሩ የቤቱን ደጃፍ በያዙት ዱላ እየደበደቡ ከላይ ያለውን ግጥም በዜማ ይላሉ። አስቀድመው ግን ዱላ ያዘጋጃሉ ዱላ ሲያዘጋጁም ይልጡትና በልጡ ግማሹን ይሸፍኑትና በእሳት ይለበልቡታል ከዛ ሲወጣ ዝንጉርጉር ይሆናል ነጭና ጥቁር ።በጲላጦስ አደባባይ ጌታችን አጥንቱ እስኪታይ መገረፉን ለማመልከት መሆኑንም ታላላቆቻችን ይናገራሉ.... ሚሻ ሚሾ አንዳንዶች ውሾ ውሾ እያሉ ጌታችንን ማህበራነ አይሁድ መስደባቸውን ለመግለፅ ነው ይላሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ዕለቱ የሐዘን ነው አልቅሱ እዘኑ ለማለት ነውም ይላሉ ምሻሚሾ (ሙሾ-ሐዘን ፣ለቅሶ እንዲል ዱቄቱን ከሰበሰቡ በኃላ ደግሞ ድንጋይ እና ድንጋይ በማጋጨት ጫጫ መሰልቀጫ ሚስቴ ወልዳብኝ ጨውና ዘይት ብላብኝ እያሉ ይዞራሉ ለምን ድንጋይ እንደሚይዙ ግን እስካሁን አልገባኝም በኃላም ከተመረጠ ቤት ይሰበሰቡ እና የሰበሰቡት ዱቄት ተቦክቶ ቂጣ ይጋገራል ከዛ ደግሞ የሰበሰቡት ጨው እና ዘይት ይለወስና ቂጣው ይቀባል ከዛ የሚበላው ተቆርሶ ይሰጠዋል ለሚፆመው ደግሞ ይቀመጥለት እና ከቤተ ክርስቲያን መልስ ትልቁም ትንሹም ከተመረጠው ቤት ቡና ተፈልቶ የሚበላው በልተው ጠጥተው የሚያከፍለውም በጨዋታው መሀል ተገኝቶ ተመራርቀው ይለያያሉ

የአርብ ስቅለት በጎንደር እና አከባቢው እንደዚህ ይከበራል እንደሰማሁት በትግራይ አከባቢ ደሞ ልጃገረዶች ሙሉ ቀኑን በባዶ ሆዳቸው ሆዳቸውን በመቀነት አጥብቀው በማሰር ዥዋዥዌ እያሉ ይውላሉ መንገላታቱን ለማሰብ፤ በዋግም እንደዚሁ፤በጎጃም አገዎችም አጎላ ጎሊ ይባላል።


 በጎጃም አገዎችም አጎላ ጎሊ ይባላል:-


 
 
#EBC ሚሻ ሚሾ/አጎላ ጎሌ በአ እንዴት እንደሚጨፈር እና ምን አይነት ሂደቶችና ስርዓቶች እንዳሉት ያስቃኘናል
 


እጅጋየሁ (ጂጂ) ሽባባው አጎላ ጎሌ


***********************************************

ምንጭ:- https://www.ethiopianreporter.com/article/21944

           :- የጥበብ ወሬዎች 

 

 

Monday, March 1, 2021

የአድዋ ድል _ በእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)

 

እጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ)_አድዋ
♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪ 

የሰው ልጅ ክቡር
ሰው መሆን ክቡር
ሰው ሞቷል

ሰው ሊያድን

ሰውን ሲያከብር
በደግነት፣  

በፍቅር፣  

በክብር ተጠርቶ፣
በክብር ይሄዳል፥ ሰው ሊኖርሰው ሞቶ፤

♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪
የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ካጥንት፣
ስንት ወገን ወደቀ በነፃነት ምድር
ትናገር አድዋ፣ ትናገር ትመስክር፣
ትናገር አድዋ፣ ትናገር አገሬ፤
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ፤

 
♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪
በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር፣
በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን
ደሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን።

♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪
አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትናንት፣
መቼ ተነሱና የወዳደቁት፣
ምስጋና ለእነሱ ለአድዋ ጀግኖች፣
ለዛሬ ነፃነት ላበቁኝ ወገኖች፣

♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪
የጥቁር ድል አምባ፣ አድዋ
አፍሪካ፣ እምዬ ኢትዮጵያ
ተናገሪ
የድል ታሪክሽን አውሪ።
♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪

 አድዋ- ጂጂ

♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪♪

 


 

የእጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) ሰርክ ገዝፎ የሚንጥ፣ እሩቅ ግን ቅርብ ውብ ስሜት…. አድዋ!!

| ተስፋዬ እሸቱ (/ ፕሮፌሠር)

*******************



ከያኒ የአንጻር ጌታ ነው፡፡ የነበረውን፣የሰማውን፣ ያነበበውን የኖረውን ሁነትና እውነት ለመገልበጥ አይታትርም፡፡ ሰው አይቶት፣ ተገንዝቦ የኖረበትን ወይንም እየኖረበት ያለን እውነት አይደግምም፤ ከያኒ፡፡

ለዚህም ነው የከያኒ እውነት ሁሌም አንጻር (point of view) አለው የሚባለው፡፡ በጋራ ያየነውን ሀቅ፣ አምነን እየኖረበት ያለን እውነት፤ እሱ በወደደው፣ በፈለገው መንገድ ሌላ የሚተኮር፣ የሚወደድ፣ ግብ ይሰጠዋል፡፡ የግቡ ትልም ደግሞ አንጻር ነው፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ የከያኒ እውነት ትናንትን አጣቅሶ፣ ዛሬ እንድንኖርበት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ነገንም እንድንናፍቅ ያስገድደናል፡፡

ከያኒ ሲልቅ፣ ታሪክ ላይ ሌላ እውነት ፈልፍሎ፤ አውዱ ላይ ሌላ ሀቅ አብጅቶ በጉዳዩ እንድናተኩር፣ አተኩረንም ህይወትን እንድናጣጥም አድርጎ እያዋዛ፤ ረግቶ ከጠነዛ መንፈስ ይፈታናል፡፡

˝አይለወጥም፣ አይነካም ቅዱስ ታሪክ ነው˝ ብለን ከታሰርንበት፣ ሀቅ ብለን ካመለክነው አምልኮ አላቆ ሌላ መንገድ፣ ሌላ ስርየት ያጎናጽፈናል፡፡ የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) አድዋም ነገረ-መሰረቱ፣ ማጠንጠኛ ሀቁ ይሄው ነው፡፡ ሌላ ደግሞ፤ሌላ እውነት! ሌላ አድማስ! ገዝፎ የሚንጥ፤ እሩቅ ግን ደግሞ ቅርብ ውብ ስሜት፤ የጂጂ አድዋ!

የእጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) አድዋ፣ ስር እና መንፈሱ ድሮ ጥንት ተጉዞ፤ የሰው ልጅ ˝˝ ብሎ ሲፈጠር ከተሰጠው ጸጋና ክብር ይጀምራል፡፡ ˝የሰው ልጅ ክቡር፤ ሰው መሆን ክቡር…˝ እያለ እየተጎነጎነ፣ እየተስረቀረቀም፡፡ ሰውን በአምላኩ አምሳያ ፈጠረው የተባለውንም አገናዝባ፤ ˝ሰብዕ የዐቢ እምኩሉ ፍጥረት˝ ያለውን አስታውሳም ነው፡፡ ጂጂ አድዋን፣ ˝የሰው ልጅ ክቡር፣ ሰው መሆን ክቡር˝ ብላ አህዱ ያለችበት መንገድ ታሪከ-አድዋን ያየችበት፣ ሀቁን የተገነዘበችበት እና እንዲተኮር የፈለገችው ትርጓሜ ነው፡፡

የሰው ልጅ ትልቁ ጻጋ፣ ሰው ሆኖ የመፈጠር፣ ተፈጥሮም በክብር የመኖር ጸጋ ሲገፈፍ ሰው መሆን ˝አዲዎስነው ትላላች ጂጂ በአድዋ ውስጥ ስታስብ፤ ደግሞም ከሩቅ ስባ በምክንያት ስታመጣም፤ ስትመዝም፡፡ ታዲያ እጅጋየሁ ሽባባው ይህንን የመሰለ የእይታ አድማስ ይዛ ስትመጣ ንቡር ነቃሽም ነበረች ማለት ይቻላል፡፡

የሰው ልጅ ከተሰጠው ክብር አንሶ ሲወርድ፣ ረክሶ ግን ለዘለአለም እንዳይኖር፣ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መድህን ይሆን ዘንድ፣ አምላክ ሰው ሆኖ ሞቶ፣ ለሌሎች ምሳሌነትን የገለጸበት፤ "አንዱ፡ስለ፡ዅሉ፡ሞተ" እሷ በአድዋ ˝ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን…˝ ብላ አዛምዳዋለች፡፡ እናም የጅግጋየሁ ሽባባው አድዋ ጥንት፣ ድሮ የትየለሌን ከትልቁ መጽሀፍ፣ መጽሀፍ ቅዱስ አጣቅሷል ስል መነሻዬ ይሄው ነው፡፡

ይህንን ለሰው ልጅ ቤዛ የመሆንን አስተምህሮት፤ ለሰው መሞት፣ ለሰው ክብር መሰዋት፤ ከምንም በላይ ሰው ክብር መሆኑን መገንዘብ ነው የአድዋ አባቶቻችን በአፍ ሳይሆን በተግባር ሳያጎድሉ ከወኑት የምትለን ጂጂ፤ በአድዋ፡፡ የጂጂ ንቡር ጠቃሽነትም ወደር የማይገኝለትና ምክንያታዊ ሆኖ የቀረበው፣ በሙዚቃው ወስጥ ጀግኖች አባቶቻቻን ሰው ልጅ ክብር፣ ሰው መሆን ክቡር መሆኑን ተገንዝበውና አስገንዝበው እንዳለፉ አጽንዖት ሰጥታው ታልፋለች፡፡

ይህንን ከላይ የተወሰደ እና ለሰው ክብር ሲባል መሞት ትልቁ የፍቅር መገለጫ በዚህችው አገር፣ በአድዋ ተራራ ሲከወን ˝ በክብር ይሄዳል፣ ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ…˝ እያለች በድጋሚ፤ ግን ደግሞ በተለየ ገለጻ በደማቁ ከትባው ታልፋለች፤ በሙዚቃ- አድዋዋ፡፡

ቀጠል አድርጋም አባቶቻችን የህይወት፣ የመዳን፣ የፈውስ፣ የቤዛ ምልክቶች ናቸው ልትለን እና አድዋን ግዘፍ ልትሰጠው ስትፈልግ ˝ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት…˝ ስትለንም ተምሳሌትነቱ ክርስቶሳዊ፤ ሰማያዊ እንጂ ምድራዊስ አይደለም ብላ አጽንዖት ልትሰጥ የፈለገች ይመስላል፡፡ ይህ የአምላክን ድንቅ ፍቅር፣ አምላክን አባት፣ ሰውን ልጅ ያደረገ ኪዳን፣ አባቶቻቸን ˝ የሰው ልጅ ክቡር፤ ሰው መሆን ክቡር…˝ ብለው ስለከወኑት፤ ደግሞም ውድ ህይወታቸውን ሳይሰስቱ፣ በደግነት፣ በፍቅር፣ ሰጥተው ስላለፉ፤ ለዛሬ ሳይጓደል ለተገኘ ነጻነት ህያው ምስክር እንደሆኑ ምስክር ስትጠቅስም ˝ትናገር አድዋ፣ ትናገር ትመስክር፤ ትናገር አድዋ፣ ትናገር አገሬ…˝ እያለች ቋሚ እማኝ፤ ቋሚ የታሪክ ምሥክር ትጠራለች - ህያው አብነትነቱ በእኛ በልጆቻቸው ልቦና ውስጥ ህይወት ዘርቶ፤ ግዘፍ ነስቶ በዘላቂነት እንዲኖር!

 

የእጅጋየሁ ሽባባው አድዋ ትዕምርታዊ ተምሳሌቱ ክርስቶሳዊ እንደሆነ፤ ተመርጠው በተደጋጋሚ፤ ግን ደግሞ በተለያያ መንገድ ተሰድረው በመካነ ድምጿ የሚንቆረቆሩት ስንኞች ጉልህ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ስትጀመር ˝ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን…˝ ትለናለች፡፡ ˝ሰው ሊኖር ሰው ሞተ…˝ እያለች ትቀጥልናም ˝ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት…˝ ብላ ትሠልሳሰች፡፡ በእጅጋየሁ ሽባባው አድዋ ሰው በክብር ለሰው መድህን እንዲሆን የሞተው፤ ወራሪን ለመመከት፣ አገር ለመስራት፣ ቅኝ ግዛትን ለማውገዝ ወዘተ ለሚባል ታካችና ሰርክ ለምንሰማው ጉዳይም አይደለም፡፡

ጂጂም ˝ የሰው ልጅ ክቡር፤ ሰው መሆን ክቡር…˝ ብላ ጀምራ፣ አባቶቻችን የወደቁት ወራሪን ገጥሞ ለመጣል ነው ብትል የተነሳችበትን የዳጎሰና ፍጹም የሆነ የሀሳብ ልቀት የታየበትን አድማስ ያኮስስባት ነበር፡፡ እሷስ ምኗ ሞኝ፤ ወራሪ ምናምን የሚል ነገር አልወጣትም፡፡ ይልቅ የተነሳችበት ሀሳብ ይበልጥ ይጎለብት ዘንድ፤ የሰው ልጅ ሰውን በመውደድ፣ ሰው መሆን ክቡር መሆኑን በተግባር ሲገልጥ ሌላ የደረጀ ሀሳብ ባለቤት ይሆናል፡፡ እሱም ደረጃ ነጻነትን ይጎናጸፋል ትለናለች፤ቃሉን ˝ነጻነት˝ እየደጋጋመች፣ እኛ ዘንድ እንዲታተም፡፡

ነጻነትም ሰው ሆኖ ከመፈጠር ጋር የሚሰጥ እንጅ የማንም ችሮታን እንደማይጠይቅ፣ ጥንት አባቶቻቻን እንደተረዱት በጂጂ ሙዚቃ ውስጥ በጉልህ ተመልክቷል፡፡ በሙዚቃው፣ የጻነት ትርጓሜ ደግሞ ምንጩ የሰው ልጅ ክቡር እንደሆነ መረዳትና ለዚህም እንደክርስቶስ እራስን አሳልፎ መስጠት እንደሚያስፈልግ አስገንዝባ አልፋለች፤ እጅጋየሁ ሽባባው፡፡

እንደካባ የተጎናጸፈችውን ነጻነት፣ ˝በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር፤ በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን…˝ እያለች ታሽሞነሙናለች ፡፡ የእውነት ግን ማን እንደእሷ፣ ማን እንደህዝቧ ˝ሰው ልጅ ክቡር፤ ሰው መሆን ክቡር˝ በአግባቡ ተረድቶ፣ ድልን፣ ነጻነትን በቀን በቀን ይተነፍሳል? ኣባቶቾ፣ አባቶቻችን የፈጸሙት ገድል ክርስቶሳዊ ካልሆነ በስተቀር!

ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ የእጅጋየሁ ሽባባው አድዋ የትላንት በፊትን፣ ከትላንት ጋር ብቻ አስተሳስሮ ለማለፍ አልተጋም፡፡ ይልቅስ አድዋ ትላንትን ከዛሬ ጋር ሲያዛምድ፣ ሲሰፋ ይታያል፡፡ ˝አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትናንት….˝ እያለ፤ ከትናንት ሽቅብ ወደ ዛሬ እንድንደረድር እየፈለገ፡፡ በሁለት መንገድ፤ አንድም በኩራት፡፡….. ሁለትም በቁጭት፡፡

ከቁጭቱ ልጀምር፡፡ ከላይ ከክርስቶስ፣ እራስን ለሰው ልጅ አሳልፎ መስጠትን በወጉ ተምረውም ተግብረውም፣ አድዋ ላይ ህይወታቸውን ለሰው ልጅ ክብር የሰጡ፣ ˝ሰው መሆን ክቡር˝ ያሉ የጀግኖች አባቶቻችን ርዕይ ሜዳ ላይ ብቻ፣ በወሬ ብቻ ወድቆ መቅረቱ ጂጂን ያንገበገባት ይመስላል፡፡

በጂጂ አድዋ ጀግኖች አባቶቻቻን በክብር አላረፉም፡፡ የሚያሳርፉ ልጆች አላገኙም እና ቁጭቷን እንዲህ ትገልጸዋለች፡፡ ˝አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትላንት፤ መቸ ተነሱና የወዳደቁት…˝!

የወዳደቁት አልተነሱም፡፡ ጂጂ እውነት ያላት ይመስላል፤ ደግሞም እውነቷን ነው - እንደእኔ፡፡ በጂጂ ˝አድዋ˝ የተሰዉት ጀግኖች አባቶቻቻን በሰላም አላረፉም፡፡ በየጥሻው እንደወዳደቁ ናቸው፡፡ ይሄ ለጂጂ ጸጸት ነው፤ ውስጥ ድረስ ሰርስሮ የሚበላ ቁጭት! ትላንት ስለሰው ልጆች ክብር ˝ሰው መሆን ክቡር˝ ብለው የወደቁ አባቶች በነበሩባት አገር፣ ዛሬ ሰው እንደ ተራ ቁስ የሚቆጠርበት አገር ሲሆን፣ የአድዋ ኣባቶቻችን መንፈስ ወድቆ እንደቀረ ነው፤ እንደተሰበረ፡፡

ትላንት ˝በነጻ ምድር˝ ስለሰው ልጅ ክብር ሲባል ደምና አጥንቱን ከፍሎ አገሩን፣ ጦቢያን የአፍሪካ እና የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ቀንዲል እንድትሆን ያደረገ ጀግና በተፈጠረበት አገር፣ ዛሬ አገረ ኢትዮጵያ አገር-ተከታይ፤ ድህ፣ ጭቁን፣ ርሀብተኛ፣ ውዳቂ የምትባል አገር ስትሆን የወደቁት ኣባቶቻችን አጥንት ገና አልተሰበሰበም፤ በክብር፡፡ ህያው አገር፣ ነጻ አገር ለመፍጠር የወደቁ አባቶች በነበሩበት አገር፣ ዛሬ ˝ብሄር˝ በሚባል ጥብቆ ታንቀው፤ጎሳን ከአገር፣ ያውም ኢትዮጵያን ከምታክል ታላቅ አገር የሚያስበልጡ ህዝቦች አገር ሆንና አረፍነው፡፡

እናስ?... ጂጂ ˝መቸ ተነሱና የወዳደቁት˝ ብትል ሀቅ አላት፡፡ ትላንት ሰው የሚባል አርማ አንስተው፣ ሰው በሚባል የወል ስም ለሰው የሞቱ አባቶች በነገሱበት አገር፣ ዛሬ ˝አድዋ ላይ የተታኮሰው ቀኝ አዝማች እከሌ፣ የወደቀው ደጃዝማች እከሌ እኮ ብሄሩ እንትን ነው…..የኛ ጀግና ሳይሆን የኔ ዘር ብቻ ጀግና ነው….˝ በሚባልበት አገር፣ የሞቱትን አላሰረፈምና፤ ተከታይም አላፈሩምና ጂጂ ˝አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትላንት፤ መቼ ተነሱና የወዳደቁት…˝ ብትል፤ አብዝታም ብትቆጭ የሚጨበጥ አመክንዮ አላት፡፡

በሚስረቀረቅ፤ ግን ደግሞ በሚንገበገብ ድምጿም ˝ተናገሪ˝ ትላላች፤ አድዋ አፍ ያለት ይመስል፡፡ ˝ተናገሪ˝ ጦቢያ ትላላች፣ አገር ያልታዘበች ይመስል፡፡ ትናገር ትላለች ትውልድ ዠሮ ያለው ይመስል፡፡ ምንታድርግ፤ ጂጂ ብትበሽቅ ነውና ደግ አደረግሽ እላላሁ፤ እኔ ደግሞ፡፡
ከያኒ ሲበቃ እንደ ጂጂ ነው፤ ከትላንት ወዲያን ከትላንት ማዛመድ ብቻ ሳይሆን ትላንት ላይ ቆሞ ተንብዮ፣ መሲህ ሆኖ የአገር ጌጥ ይሆናል፤ ሲመጥቅ፡፡

ሌላው ጂጂ፣ ˝አድዋ ዛሬ ናት፣ አድዋ ትላንት˝ ስትል ያዛመደችው እውነተኛ ከሆኑት የዛሬ የአድዋ ልጆ ጋር ነው፡፡ ሰውን በሰውነቱ ለሚወዱ፣ አገራቸው ነጻ አገር እንደሆነች ለሚያሰቡ፣ ˝እኔ ኢትዮጵያ ነኝ˝ ለሚሉ፤ የሰው ህመም ህመማቸው፣ ስቃዩ ስቃያቸው ለሆነባቸው፤ አገራቸው የምንግዜም ጌጣቸው የሆነችላቸው የዛሬ የአድዋ እውነተኛ ልጆችን እጅጋየሁ ሽባባው በተቃራኒው እንዲህ ትላቸዋለች - እሷኑ ራሷኑም ጨምራ፡በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር፤ በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን!…˝፡ ከነዚህኞቹ ወገን ያድረገኝ - እኔን፡፡

በመጨረሻም፤ ራስን ለሰው ልጆች አሰልፎ የመስጠትን ክርስቶሳዊ አስተምህሮ ከአድዋ ጀግኖች፤ የአድዋ ጀግኖችን ደግሞ ከዛሬዎቹ አውነተኞቹ የአድዋ ልጆችና ጋዜጣ-ውልድ ጎሳዊያን ጋር የሰፋችበት መንገድ እጅን በአፍ አስጭኖ ˝አጀብየሚያሰኝ ነውና ጂጂን፡እድሜና ጤና ይስጥሽ፤ ˝አድዋ˝ የተጠበበው አእምሮሽ ብርሀኑን አይጣ፡፡˝ ልላት እወዳለሁ፡፡ እኔው ራሴውም ደግሞ ስለእሷው ˝አሜን˝ብልላት ምን ይለኛል?…አሜን!!


 

************************* 

አድዋ – የሰው ልጅ ክቡር! _ዮሐንስ ሞላ

************************* 

በአድዋ- የደመቁ ጥበበኞች

************************

የጂጂ ቃለ መጠይቅ - Ejigayehu Shibabaw (GiGi) Interview 


እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ከመዓዛ ብሩ ቆየት ያለ ጨዋታ Sheger Fm Yechewata Engida - Ejigayehu Shibabaw (Gigi) Interview With Meaza Birru


ናፋቂዋ ተናፋቂ፤ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)_ፋና ቴሌቪዥን