ከደራሲያን ዓምባ

Thursday, September 1, 2022

መምህር፣ጋዜጠኛ እና ወግ አዋቂው ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል

 


የወዲያነሽ - ረዥም ልቦለድ 1978ዓ.ም.
ጉንጉን - ረዥም ልቦለድ 1982ዓ.ም.
እንካሰላምታ - 2005ዓ.ም.
ኦቴሎ - (ትግርኛ) 2007ዓ.ም.

መምህር እና ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል በሰሜን ሸዋ ማጀቴ ከተማ ተወልዶ፣ ኮምቦልቻና አስመራ አድጓል። አስመራ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ከጨረሰ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የቀን ሥራ ሠርቷል፤ በመምህርነትም አገልግሏል። የግል ትምህርት ቤቶች መምህራንና ሠራተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን ለመብታቸው ተሟግቷል። በደርግ ሥርዓት በኢህአፓ ውስጥ በኅቡእ ተደራጅቶ ሲታገል በደርግ መንግሥት ተይዞ ሁለት ዓመት ከአስር ወር ከታሰረ በኋላ ተፈቷል። ከተፈታ በኋላ ደርግ በድጋሚ ሊያስረኝ ይችላል ብሎ ስለሰጋ ወደ ትውልድ አካባቢው ሰሜን ሸዋ ማጀቴ ገጠር ሄዶ ከፊል ገበሬ ሆኖ እየሠራ በኋላ “የወዲያነሽ” በሚል ርዕስ ያሳተመው ተወዳጅ መጽሐፉን ይጽፍ ነበር።

በ1976 ዓ.ም. በሚኖርበት አካባቢው ድርቅ በመከሰቱ ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት መጀመሪያ ጋራዥ ውስጥ ሰርቷል ፤ ቀጥሎም በመምህርነት አገልግሏል። በመምህርነት ለ33 ዓመታት ያገለገለ ሲሆን “የወዲያነሽ” እና “ጉንጉን” የሚባሉ የልቦለድ መጽሐፍ እንዲሁም “እንካስላንቲያ” በሚል ርዕስ ሥነቃላዊ መጽሐፍ በአማርኛ ቋንቋ ጽፎ ለንባብ አብቅቷል። የአቶ ገብረክርስቶስ ገብረእግዚአብሔር የሕይወት ታሪክንም ጽፎ አሳትሟል።

በትግሪኛ ቋንቋ ደግሞ “ኦቴሎ” ቲያትርን ተርጉሞ በ2005 ዓ.ም. ከማሳተሙ በተጨማሪ ሌሎች ቲያትሮችም ጽፎ ለሕትመት ዝግጁ አድርጎል። የማክሲም ጎርኪን “እናት” የተባለውን ድርሰት ወደ ቲያትር በመቀየር በአማርኛ ቋንቋ ተርጉሟል። በጋዜጠኝነት ከመሥራቱ በተጨማሪ “እረኛዬ” በተሰኘ ተከታታይ ድራማ ላይ ተውኗል። የብዙ ወጣቶችን ድርሰት የአርትኦት ሥራ በመሥራት አስተምሯል፤ አግዟል። በተለያዩ ፕሮግራዎች ላይ አስተማሪና አዝናኝ ንግግሮች በማድረግ ወግ አዋቂነቱንም አስመስክሯል። የዚህ መምህር፣ ደራሲ፣ ጋዜጠኛ እና ወግ አዋቂ ሕይወት ብዙዎችን ያስተምራል ብለን በማመን እንግዳችን አድርገነዋል። መልካም ንባብ!

ውልደትና ዕድገት

መምህርና ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል፣የጣልያኖችን የግፍ አገዛዝ በመሸሽ በ1926 ዓ.ም. ከአስመራ ወደ መሃል አገር ከመጡት አቶ መዋዕል መሐሪ እና ማጀቴ ተወልደው ካደጉት ከወይዘሮ ሙላቷ ሀብተሚካኤል በሰሜን ሸዋ ይፋትና ጥሙጋ አውራጃ ገምዛ ወረዳ ሰኔ 16 ቀን 1943 ዓ.ም. ማጀቴ ከተማ ደይ-ምድር መንደር ተወለደ። ኃይለመለኮት ለእናቱ የመጀመሪያ ልጅ፣ ለአባቱ ደግሞ ሰባተኛ እና የመጨረሻ ልጅ ነው። የአራት ዓመት ሕጻን ሳለ ወላጆቹ በመለያየታቸውና አባቱ ለሥራ ኮምቦልቻ ተቀይረው ስለሄዱ አጎቱ ቤት ጌሾ፣ጥጃ እና ማሽላ እየጠበቀ አደገ። ከአጎቱ ቤት በመቀጠል አያቶቹ ዘንድ አድጓል። አያቶቹ ከፍተኛ ፍቅር ቢያሳዩትም ከአባትና እናት ጋር በመሆን የሚገኝን ልዩ የወላጅ ፍቅርን ሳያገኝ እንዳደገ ይናገራል።

አያቶቹ ዘንድ እያደገ ሳለ አባቱ የቴሌኮሚኒክሽን ሥራ ከሚሠሩበት ከኮምቦልቻ በመምጣት ወደ ሥራ ቦታቸው ይዘውት ሄዱ። ያን ጊዜ የኮምቦልቻ ከተማ ሃያ እና ሰላሳ ቤቶች ብቻ የነበሩባት በመሆኗ በሆያ ሆዬ የሚዳረሱ ነበሩ በማለት ይገልጸዋል። ኮምቦልቻ ከሄደ በኋላ የመጀመሪያዋ እንጀራ እናቱ ክፉ ስለነበሩ ከእሳቸው ጋር አብሮ መኖሩ አሰልቺ ሆነበት። ከእንጀራ እናቱ ጋር ሲኖር በድሮው ፋሽኮ ጠርሙስ ውሃ ለመቅዳት ይዞ ወጥቶ ሳለ አዳልጦት ወድቆ ጠርሙሱ ስለተሰበረ ወደ ቤት መሄድ ፈርቶ ዛፍ ላይ ያደረበትን ቀን አሁን ድረስ በኀዘን ያስታውሳል። እኚህ እንጀራ እናቱ ከአባቱ ጋር ተጣልተው ከሄዱ በኋላ ወደ አራት እንጀራ እናት አይቷል። ኮምቦልቻ የቄስ ትምህርት መማር እንደጀመረ ዘመናዊ ትምህርት በስፍራው ስለተከፈተ አንደኛ ክፍል ገብቶ በእጥፍ (ደብል እየመታ) እያለፈ እስከ አራተኛ ክፍል ተምሯል።

አባቱ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ኤርትራ ሲሄዱ ከኮምቦልቻ ወደ አስመራ በትሬንታ ኳትሮ የጭነት መኪና ከአባቱ ጋር ተሳፍሮ ሄደ። በመቀጠልም ከአስመራ ስምንት ኪሎ ሜትር ያህል ወደምተርቀው ወክድባ መንደር በመሄድ መኖር ጀመረ። በዚያን ወቅት እዚያ መንደር አማርኛ መናገር የሚችሉት እሱና አባቱ ብቻ ስለነበሩ ትምህርት ለመቀጠል ተቸገረ። ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ውጭ ትምህርት የሚሰጠው በትግርኛ ስለሆነ አንድ ዓመት ቆይቶ እንዲመጣ በአስተማሪዎች ስለተነገረው በመንደሩ ውስጥ ያለትምህርት ትግርኛ ቋንቋ እየለመደ ቤተሰቡን ሲያገለግል ቆየ።

በመቀጠል አስመራ ከተማ ሐዲሽ ዓዲ ሰፈር አክስቱ ጋር ሆኖ በመማር አክሪያ ትምህርት ቤት ከ5- 8 ክፍል፣ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ከ9- 12 ክፍል ተምሮ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ። አስመራ እየተማረ ሳለ ዕዳጋ ዓርቢ በሚባል የገበያ ቦታ ሽሮ፣ በርበሬ፣ ተልባ እና ቆሎ ከአክስቱ ጋር ይዞ በመሄድ ሸጧል። አክስቱ ዶሮ ያረቡ ስለነበረ የዶሮዎቹ ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አገልግሏል፤ በከተማው ውስጥ በመዘዋወርም እንቁላልና ዶሮ ይሸጥ ነበር። ክረምት- ክረምት ደግሞ ክብሪትና ጆንያ ፋብሪካ በቀን አርባ ሳንቲምና ከዚያ በታች እየተከፈለው የጉልበት ሠራተኛ በመሆን ሠርቷል።

አሥራ ሁለተኛ ከፍል ከጨረሰ በኋላ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ውጤት ባለማምጣቱ ወክድባ በመሄድ ቤተሰቡን አገልግሏል። ከዚያም አዲስ አባባ በ1962 ዓ.ም. በመምጣት መጀመሪያ በግንባታ ሥራ ውስጥ በጉልበት ሠራተኝነት በቀን ሰባ አምስት ሳንቲም እየተከፈለው ሠርቷል። በመቀጠልም በ19 ዓመቱ ዓለም ማያ በሚባል በግል ትምህርት ቤት በወር ሠላሳ ስምንት ብር እየተከፈለው በመምህርነት ተቀጠረ። በጊዜ ሂደት ደግሞ ክረምት- ክረምት (1967- 68ዓ.ም) በመማር በመምህርነት መጠነኛ ስልጠና አገኘ። ኮልፌ መሠረተ ዕድገት ትምህርት ቤት በኋላም እድገት ጎልማሶች አዳሪ ትምህርት ቤት አስተምሯል። በመሃል በተለያዩ ምክንያቶች እያቋረጠ እንደገና እየጀመረ በአጠቃላይ በመምህርነት 33 ዓመታት አገልግሏል።

የንባብና ድርሰት ጅማሮ

የድርሰት ሥራ ጅማሮው አስመራ ከተማ ሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ የቤት ሥራውን ስለግመል ጽፎ የመጣው ነበር። በወቅቱ እስኪርቢቶ አምስት ሳንቲም በሚሸጥበት ጊዜ የአምስት ብር ፓርከር በጻፈው ድርሰት ምክንያት ከአማርኛ አስተማሪው ከመምህር ጌታቸው ተሸልሟል። መምህር ጌታቸው የንባብ ዓለምን ያስተዋወቁት የንባብ አባቱ ናቸው(መምህር ጌታቸው በኋላ አዲስ አበባ የኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል)። ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበበው መጽሐፍ “ገልጠን ብናየው” የሚል በቤካ ነሞ የተጻፈውን ነበር። ከዚያ በኋላ በአማርኛም በእንግሊዝኛም የተጻፉ መጻሕፍትን አስመራ በሚገኙ ቤተመጻሕፍት በመግባት አንብቧል።

ዘጠነኛ ክፍል እያለ አንድ ጊዜ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ሲሄድ ለሚያያት ልጅ አንዴ ስለእግሯ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስለፀጉሯ፣ ወዘተ. በትግሪኛ ግጥም በመጻፍ ለመስጠት ፈልጎ ሲተወው፤ በነጋታው ሌላ ሲጽፍ ለመስጠት ሲፈራ፤ ሌላ ጊዜ ተጨማሪ በመጻፍ ለመስጠት ሲፈራ፤ በመጨረሻ አንዱንም ሳይሰጣት ተወው። ለጓደኛው የተሻለ የሚለውን ግጥም ሲያሳየው አምጣ ብሎ ለራሱ የሴት ጓደኛ ሰጣት። የሴት ጓደኛው ደግሞ ለጋሽ ኃይለመለኮት ጎረቤቱ ስለነበረች ምላሽ ጻፍልኝ በማለቷ የሁለቱን የጽሑፍ ምልልስ በመፃፍ የመጻፍ ችሎታውን አሻሽሏል። ችሎታውንም ለማሳየት አንዳንድ ጽሑፎቹን የቤተክህነት ትምህርት ዕውቀት ላላቸውና አንባቢ ለሆኑት አባቱ በማንበብ ያቀርብ ነበር። ከእሳቸውም አድናቆት ተችሮታል።

የእኔ ዩኒቨርሲቲ ቤተመጽሐፍ ወመዘክር ነው የሚለው እንግዳችን ወመዘክር ቤቱ የሆነ ያክል የተጠቀመበት ሥፍራ ነው። ጠዋት ለንባብ ገብቶ ምሳውን እዚያው አካባቢ ከበላ በኋላ ተመልሶ ለንባብ ገብቶ ማታ የሚወጣባቸው ጊዜያት ብዙ ናቸው። አክስቱ ጋር በነበረባቸው ጊዜያት ለአራት ዓመት ከስድስት ወር በተከታታይ የተወሰኑ ቀናትን ሥራ ለመሥራት ከቀረባቸው ጊዜያት ውጭ ወመዘክር ገብቶ አንብቧል። አንድ ጊዜ ወመዘክር ያነበበው ሄንሪ ዴቪድ ቶሮ የተባለ ደራሲ የጻፈውን መጽሐፍ አሮጌ መጽሐፍ መሸጫ ሥፍራ ያይና ገዝቶ የራሱ ለማድረግ ስንት እንደሆነ ይጠይቃል። ሻጩ ሦስት ብር እንደሆነ ሲነግረው ሦስት ብር ስላልነበረው በጣም ያዝናል። ትንሽ ቆይቶ ግን አንድ ሐሳብ መጣለት፤ ሦስት ብር ባይኖረውም ሦስት ሱሪ ስላለው አንዱን ሸጦ መጽሐፉን መግዛት። አላወላወለም፤ ሌላ ሰው ቀድሞት መጥቶ መጽሐፉን እንዳይወስድበት በፍጥነት ወደ ቤቱ ሄዶ ሱሪውን ገበያ ውስጥ ሸጦ መጽሐፉን እጁ አስገባ። አሁን ድረስ መጽሐፉ እሱ ዘንድ ይገኛል። መጽሐፉን የሸጠለት ደግሞ ያን ጊዜ መጽሐፍ ሻጭ የነበረው ደራሲ አውግቸው ተረፈ (ህሩይ ሚናስ) ነበር።

ወመዘክር የሕይወቴ አቅጣጫ መለወጫ እና ዕውቀት የገነባሁበት ቦታ ነው የሚለው እንግዳችን ወመዘክር ካነበባቸው መጻሕፍት ውስጥ “ጫት እንደበላ ሰው ያመረቀነኝ” የሚለው የፀጋዬ ገብረመድሕን “ኦቴሎ” የሚለው መጽሐፍ ነበር። የሼክስፒርን እንግሊዘኛ መጽሐፍና የፀጋዬን አማርኛ መጽሐፍ በመያዝ በ1963 ዓ.ም. “ኦቴሎ”ን ወደ ትግርኛ ቋንቋ ተርጉሟል። “ፀላም መቀነት” (ጥቁር መቀነት)፣ “ጋሕሲ ስቃይ” (የስቃይ መቃብር) የሚል ርዕስ ያላቸው ቲያትሮች በትግርኛ ቋንቋ ጽፏል። የቲያትር ጽሑፎቹን ለደራሲ ፀጋዬ ገብረመድህን ተርኮለት ታሪኩ ጥሩ ነው፤ ቲያትር በመድረክ ላይ በተግባር የሚታይ፣ የሰውን ኅሊና መመሰጥ የሚችል ስለሆነ በዚህ ጽሑፍ ያሰፈርከውን ታሪክ በሙሉ የሚያጤንልህ ስለሌለ በዚህ መልኩ ጻፈው ብሎ ምሳሌ በመስጠት አስተያየት ሰጥቶታል። በተጨማሪም በቲያትር መድረክ ላይ ብቻ አይደለም መቅረት ያለብህ በሰፊው መሄድ የምትችለው ልቦለድ (ኖቭል) በመጻፍ ነው በማለት መክሮታል። አስተያየቱን ተቀብሎ አስተካክሏል፤ ልቦለድ በመጻፍም የተሰጠውን ምክር ተግባራዊ አድርጓል።

ኃይለመለኮት የጽሕፈት ሥራውን በመቀጠል የውጭ ጸሐፍት ሥራዎችን መገሻ ዓሻ (የቂል ጉዞ)፣ ሩፋኤል ጸበል፣ የደንከል ዱቄት፣ በሚል በትግርኛ እና በአማርኛ ቋንቋ ተርጉሞ በመጨረስ የድርሰት ችሎታውን ይበልጥ በማሻሻል “የወዲያነሽ” የሚለውን ልቦለድ በአማርኛ መጻፍ ጀምሯል።



የትግል ሕይወት

በ1965 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ወመዘክር ቤተመጽሐፍ ያገኘው አንድ መምህር፣ ቡና እና ሻይ ሕንጻ አጠገብ ኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር ውይይት ስላለ እንድትገኝ ብሎ ሁለት- ሦስት ጊዜ ዓለም ማያ ትምህርት ቤት ድረስ መጥቶ ጋበዘው፤ ኃይለመለኮት ጊዜውን በማንበብ ለማሳለፍ ስለፈለገ አልሄደም። መምህሩ ባለመሰልቸት መጋበዙን በመቀጠሉ በመጨረሻ በውይይቱ ላይ ተገኘ። የሄደበት ስፍራ ስለመበዝበዝ፣ ስለመጨቆን እና ስለመደራጀት አለመቻል በሁለት የማኅበሩ መሪዎች ትምህርት ከመሰጠቱ በላይ፣ ውይይት ተደርጎ ስለነበረ ለሕልሙ ፈውስ ያገኘ መሰለው። ከዚያ በኋላ የትምህርቱና ውይይቱ ዋና ተከታታይሆነ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሁለቱ የማኅበሩ መሪዎች ሌላ ሥራ አግኝተው መሪነቱን ስለለቀቁ ማኅበሩን በፈቃደኝነት የሚመራ ሰው አልተገኘም። ኃይለመለኮት ማኅበሩ መፍረስ የለበትም በሚል ቁጭት ተመራጭ አመራር እስኪሰየም ድረስ በፈቃደኝነት እንደሚመራ መድረክ ላይ ወጥቶ ተናገረ። ሌላም ሰው ሊያግዘው ፈቃደኛ ሆኖ በመገኘቱ ማኅበሩም ከመፍረስ ዳነ።

ሁለት ወር ያህል በመሪነት እንደሠራ ምርጫ ሲካሄድ የግል ትምህርት ቤት መምህራንና ሠራተኞች አንድነት ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ። ከ1965 ዓ.ም. እስከ 1969 ዓ.ም. የማኅበሩ መሪ በመሆን ከመቶ በላይ ለሆኑ በደል ለደረሰባቸው መምህራንና ሠራተኞች ከሌሎች የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ጋር በመተባበር ፍርድ ቤት በመቅረብ ስለደረሰባቸው በደል ተከራክሯል። በዚህ ጊዜ ባደረገው እንቅስቃሴ በየካቲት 1966 ዓ.ም. በንጉሡ ጊዜ ለአምስት ቀን ታስሮ ክስ ተመስርቶበት፣ በደርግ ጊዜ በ1967 ዓ.ም. ሃምሳ ብር ቅጣት እንዲከፍል ተበይኖበት ከፍሏል።

የማኅበሩ መሪ ሆኖ ሳለ የወዲያነሽን ከአጠገቡ ገሸሽ አደረገ፤ ልቦለድ ድርሰት መጻፉንም አቋረጠ። በቤተመጽሐፍ ስለሙያ ማኅበራት የሚተርኩ መጻሕፍትን አብዝቶ አነበበ፤ የሶሻሊዝም ርዕዮት ተከታይም ሆነ። ጋዜጣ ላይ በብዕር ስም ሲጽፍ የነበረውን ሥነጽሑፋዊ ሥራዎች በመተው ስለሠራተኛው መደብ መጨቆን እና ስለመደራጀት መጻፍ ጀመረ። በዚህ ሂደት በኢሕአፓ ውስጥ በኅቡእ ተደራጅቶ እየታገለ ሳለ በደርግ መንግሥት ተይዞ በቅድሚያ ሶስት ወር በታላቁ ቤተመንግሥት (በወቅቱ ደርግ ጽ/ቤት በነበረው) ታስሯል። ከሦስት ወር በኋላ ደግሞ በዝውውር ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሯል። በአጠቃላይ ሁለት ዓመት ከአስር ወር ከታሰረ በኋላ በ1972 ዓ.ም. ተፈታ።

ስለእስር ቤት ሕይወቱ ሲናገር ‹‹እስር ቤቱ እጅግ በጣም የስቃይ ቦታ ነው። አንድ ሰው ጠቦ፣ ጠቦ፣ ጠቦ ሲጨንቀው ራሱ ውስጥ የሚቀርበት ሥፍራ ነው። በሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የመጀመሪያው 10 ካሬ ሜትር ሁለተኛው 12 ካሬ ሜትር በሆነ መስኮት በሌላቸው ቤት ውስጥ 46 እስረኞች ታስረን ነበር። በመኝታ ጊዜ አስቸጋሪ ስለሆነ እግራችን በግራና በቀኝ ተላልፎ ቁልፍልፎሽ ነው የምንተኛው። በጣም የሚገርመኝ ጉዳይ በዚያን ጊዜ የነበረው የስቃይ ሁኔታ እስከ አሁን ድረስ ሳይቀረፍ ዘልቆ መቀጠሉ ነው። ሲገረፍ የነበረው ሰው ገራፊ ይሆናል ብዬ አላስብም ነበር፤ በተግባር ያየሁት ግን ብሶበት መገኘቱን ነው›› ይላል።

ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እስር ቤት ውስጥ የማክሲም ጎርኪን “እናት” የተባለውን ድርሰት አብሮት የታሰረው ዮሐንስ ክፍሌ ከእንግሊዝኛው መጽሐፍ ወደ አማርኛ ሲተረጉም፣ ኃይለመለኮት የአርትኦት ሥራውን እየተከታተለ ከአሳሪዎቹ ተደብቆ አከናውኖ ጨርሷል። አርትኦቱን ከጨረሰ በኋላ ደግሞ አሳሪዎቹ እንዳያውቁበት ሌሊት ከስድስት ሰዓት በኋላ እየጻፈ ደግሞ “እናት” መጽሐፍን ብቻውን ወደ ቲያትር በመለወጥ በአማርኛ ጽፏል። ጽሑፉን ሲጽፍ የደብተር ሉክን አንዷን መስመር ለሁለት በመክፈል ነበር። የጻፈበትን አንድ መቶ ሰባት ገጽ ደብተር ከእስር ቤት እንዲወጣ ያደረገው ደግሞ በፔርሙስ ቂጥ ሥር አስገብቶ በመደበቅ አምስት ስድስት ሉክ በማስቀመጥ ለወንድሙ በመላክ ነበር። በዚያ ደብተር የተጻፈው ጽሑፍ አሁን የአርትኦት ሥራው ተጠናቆ ለሕትመት ዝግጁ ሆኖ አልቋል። አሳታሚ ቢያገኝ ለማሳተም ፈቃደኛ ነው።

ወደ ስነጽሑፍ ሥራ መመለስ

እንግዳችን ሁለት ዓመት ከአስር ወር ታስሮ ከተፈታ በኋላ ሳጥን ውስጥ አስቀምጦት የነበረውን የወዲያነሽን ድርሰት አውጥቶ መጻፍ ቀጠለ። ትንሽ ቆይቶ ደርግ በድጋሚ ሊያስረኝ ይችላል ብሎ ስለሰጋ ወደ ትውልድ አካባቢው ሰሜን ሸዋ ማጀቴ ገጠር በ1973 ዓ.ም. ሄዶ ከፊል ገበሬ ሆኖ እየሠራ የወዲያነሽ ድርሰትን ካቆመበት መጻፉን ተያያዘው። በ1976 ዓ.ም. ደግሞ በአካባቢው ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት ከማጀቴ ወደ አዲስ አበባ መጣ። አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ አንድ ዓመት ያህል ጋራዥ ሠራ። ጋራዡ አካባቢ ለሚሠራ ጓደኛው ለሆነ አቶ ዘለቀ ብሩ ለሚባል ሰው የወዲያነሽን ረቂቅ እንዲያነበው ሲሰጠው፣ ለሦስት ቀን ያህል ካነበበ በኋላ ድርሰቱን አድንቆ ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት እንዲያትምለት መስጠት እንደሚችል ይነግረዋል።

ከአቶ ዘለቀ ጋር አብረው በመሄድ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ረቂቁን ይሰጣሉ። ከአስር ወር በኋላ የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ቦርድ እንዲታተም መፍቀዱ ተነገረው። መስፍን ሀብተማርያም ደግሞ የአርትኦት ሥራ እንዲሠራለት ተመደበ። መስፍን መጽሐፉን በአድናቆት እየካበ ከነገረው በኋላ ማስተካከል የሚገባውን አንድ ነገር ነገረው። ባሻ ያየህይራድ ጨቋኝ ስለሆኑ፣ በደል ስለፈጸሙ፣ ጊዜው ሶሻሊዝም ስለሆነ መሞት ስላለባቸው ግደላቸው ተብሏል አለው። እሱም ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ገደላቸው። “የወዲያነሽ” በ1978 ዓ.ም. ታተመ። የመጀመሪያ መጽሐፉ ሲታተም ኮልፌ መሠረተ ዕድገት የሚባል ትምህርት ቤት ያስተምር ነበር። እጅግ በጣም ደስተኛ ከሆነባቸው ቀኖች አንዱ እንዲታተምልህ ተፈቅዷል ተብሎ የተነገረው ቀን እንደሆነ ይናገራል።

“የወዲያነሽ” ታትሞ በወጣ በሃያ ቀኑ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ መጽሐፉን በመተቸት ወቀሳ አዘል አስተያየት ሰጡ። ኃይለመለኮት ምላሽ እንዲሰጥ ሲጠየቅ ‹‹እኔ እሳቸው በጻፉት መጽሐፍ ተምሬ ያደኩኝ ስለሆነ ምላሽ መስጠት አልችልም›› አለ። መምህር፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ደምሴ ጽጌ ግን ‹‹“የወዲያነሽ” እንደዚህ አይደለችም›› ብሎ ለጽሑፉ ምላሽ ሰጠ። ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ‹‹ባለአደራ ይጣራል ከጋራ›› በሚል በድጋሚ ጻፉ። እንኳን ባለአደራነት ደረጃ ሊዳረሱ ኃይለመለኮትና ደምሴ በወቅቱ በአካል የሚተዋወቁ ሰዎች አልነበሩም። በመጨረሻ አሸናፊ ዘደቡብ አዲስ አበባ የሚባሉ እውቅ ጸሐፊ ማሞ ውድነህን ነቅፈው ኃይለመለኮትን ደግፈው ጻፉ። በዚህ ሂደት “የወዲያነሽ” ታዋቂና ተነባቢ መጽሐፍ ሆነ። በኢትዮጵያ ሬድዮ “የመጽሐፍ ዓለም” በሚል ፕሮግራም ላይ በ1979 ዓ.ም. በተፈሪ ዓለሙ ለመተረክም በቃ። ከኢትዮጵያ ሬድዮ በተጨማሪ በአሜሪካና በጀርመን አገር በማኅበረሰብ ሬዲዮ ተተርኳል።

በሠዓሊ ጥበበ ተርፋ እና በአውግቸው ተረፈ መኖሪያ ቤት ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ አልአዛር ሳሙኤል፣ ሥዩም ተፈራ፣ መስፍን ዓለማየሁ፣ ባሴ ሀብቴ፣ ደምሴ ጽጌ ፣ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ ቅድስት ክፍለዮሐንስ እና የቤቱ ባለቤቶች ቅዳሜ – ቅዳሜ እየተገናኙ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ሥነጽሑፋዊ ሥራዎችን እያቀረቡ እርስ በእርስ በነፃነት አስተያየት ይሰጣጡ ነበር። ተሳታፊዎቹ የሚሰጡት አስተያየት ጸሐፊውን የሚገነባ፣ የተሻለ እንዲሆን ጥረት ያደርጉ ነበር። ከተጠቀሱት ዋነኛ ተሳታፊዎች በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት በጊዜያዊነት ሌሎች ባለሙያዎችም እየመጡ ተሳትፈዋል። ደራሲና ጋዜጠኛ ኃይለመለኮት በዋነኛነት የሚሳተፉትን አባላት ሲገልጻቸው‹‹በየግሉ አንብቦ የመጣ፤ ሰው ማክበር ራስን ማክበር እንደሆነ የተረዳ፣ ለሥነጽሑፍ (ጥበብ) ከፍተኛ ፍቅር ያለው፣ አንብቦና አድምጦ የማይጠግብ፤ አንዱ የሌላውን ነፃነት የሚጠብቅ ስብስብ ነበር›› ይላል።

በዚህ የስነጽሑፍ ስብስብ ውስጥ የ“ጉንጉን” መጽሐፍ በማጀቴ አነጋገር ዘይቤ መጻፍ ተጀምሮ ተጠናቋል። መጀመሪያ ኃይለመለኮት ህዳር ወር 1980 ዓ.ም. አስራ ስምንት ገጽ ጽፎ አነበበ፤ ጋሽ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ካዳመጠ በኋላ ‹‹ለእኔ ክላሲክ ሥራ ነው›› አለ። በቡድኑ አስተያየት እየተሰጠበት በየጊዜው ጋሽ ኃይለመለኮት ሲጽፍ፣ ሲያነበብ እንዲሁም አስተያየት ሲሰጥበት ቆይቶ ነሐሴ ወር 1980 ዓ.ም. ተጽፎ ተጠናቀቀ። በ1981 ዓ.ም. ደግሞ የአካባቢውን ስያሜዎች ትክክለኛነት ለማጣራት ማጀቴ ድረስ በመሄድ በየመንደሩ በመዘዋወር አረጋግጧል። በመጨረሻ በ1982 ዓ.ም. ኩራዝ አሳታሚ ድርጅትን ሳይጠይቅ ድርጅቱ ራሱ ኃይለመለኮት በግሉ በማሳተም ላይ እንዳለ አውቆ ጥያቄ አቅርቦ “ጉንጉን” ታተመ። ከታተመ በኋላ በሸገር ሬዲዮ ለሁለት ጊዜ ተተርኳል። ከሸገር ሬድዮ በተጨማሪ በጀርመን አገር በማህበረሰብ ሬዲዮ ለመተረክ በቅቷል።

ከ“የወዲያነሽ”ና ከ“ጉንጉን” በተጨማሪ በ2005 ዓ.ም. “እንካስላንቲያ” በሚል ርዕስ ሥነቃላዊ መጽሐፍ አሳትሟል፤ እንዲሁም በ2013 ዓ.ም. የዶክተር ተወልደ እና ጋሽ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ታላቅ ወንድምን የአቶ ገብረክርስቶስ ገብረእግዚአብሔር የሕይወት ታሪክ ጽፎ ለንባብ አብቅቷል። በትግርኛ ቋንቋ ደግሞ “ኦቴሎ”ን በ2005 ዓ.ም. አሳትሟል። “ኦቴሎ” በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቲያትር ተማሪዎች ለከተማዋ ነዋሪዎች በመድረክ ቀርቦ ታይቷል። ከጎቴ የባህል ማዕከል ጋር በመተባበርም ወደ ስምንት የሚሆኑ የሕጻናት መጽሐፍ ተርጉሞ ታትመዋል።

ዶክተር እንዳለጌታ ስለ አንጋፋው የስነ ጽሁፍ ሰው ሲናገር ‹‹ድንቅ መምህርና ደራሲ ብቻ ሳይሆን ድንቅ ወግ አዋቂ ነው›› በማለት ይገልጸዋል። በተለያዩ ጋዜጦች ላይ ጽሑፎች በማቅረብ እየተሳተፈ ታትሞለታል። በጋዜጠኝነት “እፎይታ” መጽሔት ላይ ምክትል አዘጋጅ በመሆን ከመሥራቱ በተጨማሪ “ፈርጥ” መጽሔት ላይ የአርትኦት ሥራ ሠርቷል። በ“እረኛዬ” ተከታታይ ድራማ ላይ ተዋናይ በመሆንም ሠርቷል። ጋሽ ኃይለመለኮት በድራማው ላይ የተሳተፈው በአጋጣሚ መሆኑን ይናገራል። የፊልሙ ደራሲ ከሆኑት ውስጥ አንዷ የሆነችው አዜብ ወርቁ በአጋጣሚ ታገኘውና ከአንተ ሕይወት ጋር የሚሄድ አንድ ድራማ ስላለ ትተውናለህ በማለት ትጠይቀዋለች። እሱ መጀመሪያ አይሆንልኝም ብሎ ቢያንገራግርም በመጨረሻ እንደሚችል ታግባባውና ለፊልሙ ታሪክ መነሻ የሚሆን ሥራ በማቅረብ አብዬ በቃሉን ወክሎ ሲተውን ታይቷል።

ሌሎች የሕይወት ገጾች

መምህርና ደራሲ ኃይለመለኮት ላበረከተው አስተዋጽኦ የተለያዩ እውቅናዎችን አግኝቷል። በኮልፌ መሠረተ እድገት ትምህርት ቤት በ1976 ዓ.ም. እና በ1977 ዓ.ም. በትምህርት ቤት ደረጃ ምስጉን መምህር በሚል ተሸላሚ ሆኗል። በ1979 ዓ.ም. ደግሞ ከአዲስ አበባ ብቸኛ ተመራጭ በመሆን በኢትዮጵያ ደረጃ ምስጉን የትምህርት ባለሙያ ተብሎ የነሐስ ሜዳልያ ተሸልሟል። በወቅቱ በአገር ደረጃ የተሸለሙት መምህራን ሃያ አንድ ነበሩ። ኮልፌ መሠረተ እድገት ትምህርት ቤት ያስተማራቸው ተማሪዎቹ ደግሞ በመምህርነት ላደረክልን ሁሉ እናመሰግንሀለን በማለት በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ውስጥ በአካባቢው ሕዝብ ፊት ዕውቅና በመስጠት ልዩ ተሸላሚ በማድረግ ካባ አልብሰውታል፤ ገንዘብም ሰጥተውታል።በሽልማቱ ሥነሥርዓት ላይ ግን ሌላ ጊዜ ለመናገር የማይቸገረው አንደበቱ በደስታ ብዛት ተሳስሮበት እንደነበረ ያስታውሳል። በደራሲነቱ ባበረከተው አስተዋጽኦ ደግሞ “ኢትዮጵያ ታመሰግናለች” ተብሎ ከሌሎች የሥነጥበባት ሰዎች ጋር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ ሜዳልያ ተበርክቶለታል።

በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ከወረዳ 24 የምርጫ ጣቢያ በ1987 ዓ.ም. አንደኛ በመሆን ተመርጦ በሥራ አስፈጻሚነት በማኅበራዊ ዘርፍ ቢሮ ተሰጥቶት ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሠርቷል። በዚህ ወቅት የቢሮክራሲው አስተዳደር ልምድ ስላልነበረው መንፈሱ የተጨነቀበትና በመምህርነት ሲያገኝ የነበረው ነጻነቱን ያጣበት ጊዜ መሆኑን ይናገራል። ስለሆነም ነፃነቱን ወደሚያገኝበት መምህርነት ሥራ ተመልሷል።

በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ስድስት ዓመት ሙሉ አባትህ ኤርትራዊ ነው በሚል ሰበብ ያለቀበሌ መታወቂያ ቆይቷል። በወቅቱ እናታቸው ወይም አባታቸው ኤርትራዊ ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለሥልጣን ሆነው እያስተዳደሩ ባሉበት አገር፣ እሱ ኢትዮጵያዊነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ መታወቂያ መከልከሉ እጅጉን አበሳጭቶታል፤ አሳዝኖታል። ባንክ ቤት የራሱን ገንዘብ ለማውጣት ሄዶ “የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ ከሌለህ አትስተናገድም” የተባለበትን ቀን አሁን ድረስ በሀዘን ያስታውሰዋል። በዚሁ ሰበብ ከሚያስተምርበት ት/ቤት እንዲባረር ሲመከርበት እንደነበረና በመጨረሻ እንዳልተባረረ ይናገራል።

የይፍራታ ተወላጅ የሆኑት ባለቤቱ ወይዘሮ ጽዱ ጌታቸው የቤት እመቤት ሲሆኑ የድርሰት ሥራውን ሲሠራ ቋንቋውን ከማስተካከል በተጨማሪ የማጀቴ አካባቢ ቃላት ሲጠፋው በማስታወስ አስተዋጽኦ አድርገዋል። የአንድ ሴት እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት እንዲሆንም አድርገውታል። ባለቤቱ የቤተሰብ ጉዳይን ጠቅልለው ስለሚሠሩ እሱ ጊዜ ኖሮት መሥራት የሚፈልገውን እንዲሠራ ጊዜ አግኝቷል።

መምህርና ደራሲ ኃይለመለኮት ለፍትሕ የሚቆምን ሰው ያደንቃል። ሰው አደርገዋለሁ ባለው ጉዳይ አሸናፊ መሆኑ አይቀርም፤ዋናው ተስፋ አለመቁረጥና አለመንበርከክ ነው። ተስፋ ላለመቁረጥና ላለመንበርከክ የሚያግዘው ደግሞ ማንበብና የተግባር ሰው መሆን ነው የሚል ፍልስፍና የሚከተል መሆኑን የሚናገረው እንግዳችን የአርትኦት ሥራ አስተማሪዎቼ አረፍአይኔ ሃጎስ እና ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ናቸው ይላል። የሰማንያ ሰዎችን መጽሐፍ በነጻም በክፍያም የአርትኦት ሥራ ሠርቷል። በአርትኦት ሥራ የሰጠውን አገልግሎት በጣም እንደሚደሰትበትና ብዙ ወጣቶችን እንዳስተማረበትና እንደረዳበት በኩራት ይናገራል። በዚህም ምክንያት የራሱን የድርሰት ሥራ አጠናቆ ለማውጣት እንዳዘገየበት ይጠቅሳል። ለጸሐፊዎች ምክር ሲሰጥ፤ ሀሳባችሁን ለማውረድ ፍጠኑ፣ ያለማቋረጥ ጻፉ፣ ደጋግማችሁ አንብቡና አስተካክሉ፣ የጽሞና ጊዜ እየሰጣችሁ አርሙ፣ ሥራችሁ እንዲያድግና እንዲስፋፋ ችሎታችሁን በንባብ አበልጽጉ፣ ያነበበ ሰው ብዙ የእውቀት ምንጮች ይኖሩታልና አንብቡ- አንብቡ፣ ከሰዎች ጋር በቅንነት ስለሥራችሁ ተወያዩ፣ በአጭር ጊዜ ጥሩ ደራሲ መሆን አይቻልምና አትቸኩሉ ይላል።

ስሜነህ ደስታ

ዘመን መጽሔት ሐምሌ 2014 ዓ. ም

ስለ ኃይለመለኮት መዋዕል ተስፋዬ ገብረአብ በአንድ መጻሕፉ እንዳሰፈረው፣ "... [ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል] ግማሽ መንዜ - ግማሽ ኤርትራዊ ነው። ከሁለቱም ወገን አክስቶቹ እሱ ቤት ሲገናኙ እሱ አስተርጓሚ ሆኖ ያዋያቸዋል። ማርያም ሰላም ታመጣ ዘንድ የሚለምኑ ደጋግ አክስቶች ነበሩት። የኢትዮ - ኤርትራ ጦርነት እየተካሄደ እነሱ ቡና እየጠጡ አምላክን ይለማመኑ ነበር።"__ዳኛቸው ወርቁ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሌሎች ጋር ያልተቀላቀለ ንፁህ ብሔር የለም ይላል፡፡ የአባቱ የአቶ ወርቁ በዛብህ እናት የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ እንደሆኑም ራሱ ዳኛቸው ለዶክተር ሬይዱልፍ ሞልቬር ተናግሯል፡፡ ስለ ራሱ ብሔር በዶክተር ሞልቬር ተጠይቆ የሰጠው መልስም፤ “no tribal feelings”፡፡

ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ፣ ባለበቱ ወ ሮ ፅዱ ጌታቸው ፣ ልጆቹ ዶ/ር ማህደረ ኃይለመለኮት እና  ዮናታን ኃይለመለኮት

‹‹አእምሮን በተገደበ ነፃነት ውስጥ ማንቀሳቀስ ትርፉ ባርነት ነው››

‹‹ንጉን›› እንዲሁም ‹‹የወዲያነሽ›› በተሰኙ መጻሕፍቱ ይታወቃል፤ ኃይለመለኮት መዋዕል። እርሱ ዋናው ሥራዬ መምህርነት ነው፤ ደስታና ክብር የሚሰማኝ በመምህርነቴ ስጠራ ነው ቢልም፤ እነዚህ መጻሕፈቱ ዘመን ተሸጋሪ ደራሲ አሰኝተውታል። ሰሜን ሸዋ ማጀቴ ከተማ 1943 ነው ትውልዱ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ወሎ ኮምቦልቻ የተማረ ሲሆን፣ ከ5ኛ ክፍል እስከ 8ኛ አስመራ አክሪያ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ኹለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ተምሯል።

1962 ጀምሮ በመምህርነት ማገልገል የጀመረው ኃይለመለኮት፣ ከ1969 ጀምሮ እስከ 1972 በእስር ቆይቷል። ‹‹በእኔ እምነት ዋናው ሥራዬ መምህርነት ነው።›› የሚለው ኃይለመለኮት፣ ከ43 ዓመታት በላይ በመምህርነት ሠርቷል። አሁንም ላይ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሆን በተለያዩ ክልል ከተሞችና ትምህርት ቤቶች እየተንቀሳቀሰ የንባብን ባህል በተመለከተ እይታውን፣ ልምዱንና እውቀቱ ያካፍላል።

የንባብን ነገር በሚመለከት እንዲሁም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ስምምነትን ተከትሎ ከ50 ዓመት በኋላ ኤርትራ የሔደበትን ምክንያትና ሌሎችም ጉዳዮችን በማንሳት ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል? ከሆነስ ምን ዓይነት ሙላት ነው?

ይህ አባባል መቼ እንደመጣ ዓመቱን በትክክል ባላስታውስም 10 ዓመት ገደማ ይሆነዋል። በትክክል እነማን ጀመሩት የሚለውንም ለይቼ ባላውቅም፣ ወደ ሕዝብ ያመጡት እነ በፍቃዱ አባይ (ጋዜጠኛ- ብራና የራድዮን ፕሮግራም አዘጋጅ) እና ባልደረቦቹ ይመስሉኛል። እነሱ የንባብ ፕሮግራም፣ የመጻሕፍት ግምገማ ያዘጋጃሉ፣ መጽሐፍት እንዲነበቡና ደራስያን እንዲበረታቱም ጥረት ያደርጋሉ። ጥረታቸውን የሚያግዙ ልዩ ልዩ ድርጅቶች በዚህ ተሳታፊ ናቸው።

አባባሉ ግን ከእኛው አገር የበቀለ አይደለም። ሆኖም ይህ አባባል በቀጥታ መተርጎም የለበትም። ይዘቱ ነው መተንተን ያለበት። ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል ስንል የአሠራር ባህርያትን፣ የአገላለጽ መንገድን ነው የሚመለከተው። ሙሉ ሰው ሲባል ምንም ያልጎደለው፣ እንከን የሌለው ወይም ስህተት የማይገኝበት ማለት አይደለም። ሰው እያነበበና እየተመራመረ በሔደ ቁጥር እየተሻሻለ ይሔዳል። ከትላንት ዛሬ ይሻላል የሚለውን ማመላከቻ ነው።

በዚህ ዓለም ላይ ሙሉና ፍጹም ሰው የለም/ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም የምንኖረው አንዳችን በሌላችን እውቀት እየተጋገዝን እየተሞላላን ነው። ግንበኛው፣ አናጢው፣ ጸሐፊው፣ የፖለቲካ መሪ፣ ገበሬው፣ በሙሉ የተለያየ እውቀትና ችሎታ ይዘው ይመጣሉ። ሌሎችም ሙያዎች አንድ ላይ ተጠራቅመው አንድ ኅብረተሰብ የሚፈልገውን ሊያሟሉ ይችላሉ ነው።

አንድ ሰው በእድሜ ዘመኑ ኹለት ወይም ሦስት ሺሕ መጽሐፍ ቢያነብ በሁሉ ነገር የተሟላ ይሆናል ማለት አይደለም። እውቀቶች ግን ይኖሩታል። በእያንዳንዱ ጉዳይ የተወሰነ እውቀት ይይዛል። እናም አባባሉን አስፋፍተንና አብራርተን ስንመለከተው የተሻለ ሰው ለመሆን የምንታገዝበት መንገድ ለማለት ነው።

እውቀት የሚገነባ ሕንጻ ነው። ሕንጻው እያደገ ይሔዳል። የእውቀት መጨረሻ ገደብ የለም፤ ቢኖር ኖሮ የሰው ልጅ ሥልጣኔ አንድ ቦታ ላይ ይቆም ነበር። እየጨመረበት ስለሚሔድ ነው ያልቆመው፤ ሙሉ ስላልሆነ።

ማንበብ የተለያዩ ሰዎችን ሐሳብ በራስ ላይ መጫን ነው፤ በራስ ማሰብን ይገታል የሚሉ ሰዎች አሉ። ትስማማለህ?

እኔ በዚህ አላምንም። እንደውም የራስን አስተሳሰብና አስተያየት፣ ግንዛቤ እያሰፋ የሚሔድው ከሌሎች ሲጨመር ነው። እኔ የራሴን ሻማ ልለኩስ እችላለሁ። ያቺን ሻማ ይዤ ብቀመጥ በቂ ብርሃን አትሰጠኝም። በአንድ አካባቢ የተሰበሰብን ሰዎች አንድ ላይ ሆነን ብዙ ሻማ ስናበራ የበለጠ ብርሃን እናገኛለን። የራስ ሐሳብ የሚያጠብ ሳይሆን እንደውም ሐሳብን እንዲያሰፋ ያደርጋል፤ ማንበብ።

ሐሳብ ከፍ እያለ የሚሔደው በተጨማሪ ጉልበት ነው። እንዲህ የሚል ሰው ሐሳቡ ሊያድግና ሊሰፋ የሚችለው የሌሎችን ሐሳብ ወደ ውስጡ ባስገባ ቁጥር ነው። ይሔኔ ይተቻቸዋል፣ ይነቅፋቸዋል፣ የተሳሳቱት ካለ ሐሳባቸውን ያርማቸዋል። ይህን የሚያደርገው ስላነበበ ነው። አልፎም እነሱ ካዩበት ርቀት አልፎ ሊመጥቅ ይችላል።

ማንበብ ውስጥሽ የነበረውን ስህተት ለማረም ይጠቅማል። የመጥፎ ሐሳብ አረም የሚነቀለው ከሌሎች በሚወሰድ ልምድ፣ በሚመጣ እውቀትና ተሞክሮ ነው። ትምህርት ቤት የምንገባውምኮ ያለን እውቀት አነስተኛ ስለሆነ የሌሎችን ለመጨመር ነው። እንቢ ካለማ አንደኛ ክፍል ይቀራል አይጨምርም ማለት ነው።

ማንበብ በራስ ሐሳብ መወሰን ሳይሆን ተጨማሪ ሐሳብ እንዲፈልቅ መንገድ መጥረግ ነው። እውቀት በአንድ ሰው አይገነባም። እውቀት የኅብረተሰብና የአገር ሐብት ነው። ያንን በማስፋፋት ነው ወደ ትልቅነት የሚመጣው። አለበለዚያ ትምህርት ቤትና ተጨማሪ እውቀት አያስፈልገንም፤ ሁሉም እንደጋሪ የየራሱን ብቻ እያየ የሚሔድ ነው የሚሆነው።

አእምሮአችንን በተገደበ ነጻነት ውስጥ ማንቀሳቀስ የለብንም። ያ ከሆነ ትርፉ ባርነትና ተገዢነት ነው። ከሌሎች እውቀት መሸመትና እየመረጡ ሥራ ላይ መዋልና ማሳደግ ያስፈልጋል። እንጂ የራስን ሐሳብ አይገድብም። ዓለም እዚህ የደረሰችው እንደዛ ባለ አስተሳሰብ ሳይሆን ሌሎች የጻፉትን በማንበብ የእኔ ያድጋል በማለት ነው። እናም ይህ የሚያሳድግ ሐሳብ አይደለም።

የንባብ ባህል ምን ማለት ነው? በአገራችንስ ይህ ባህል አለ?

ባህል ሰዎች በተደጋጋሚ የሚያደርጉት ጠቃሚ ድርጊት ነው። ከባህል የሚታረም አለ። ጥርት ብሎ የሚወጣ ነገር አይደለም። ያም ደረጃ በደረጃ ይስተካከላል፣ ይታረማል። ዘመኑን እያየ ደግሞ ኅብረተሰቡ የሚቀበለውና የሚቀጥል ባህል አለ፤ ከኅብረሰተቡ እድገትና የአእምሮ ስፋት ጋር የማይሔድ ባህል ሲኖር ደግሞ ኅብረተሰቡ ራሱ ቀስ እያለ ያገለዋል። አንዳንዴ ሕግ ያስፈልገዋል።

ባህል የመጨዋወት፣ የአበላል፣ የአጠጣጥ፣ የሽምግልና፤ ጸብን የማስወገድ፣ የመቻቻል ባህል ወዘተ ሊሆን ይችላል። በጥቅሉ ባህል ሰፊ ትርጉም አለው።

የንባብ ባህል ነበረን ወይ ለሚለው አልነበረንም፤ ወይም በጣም ውስን ነው። የንባብ ባህል የነበራቸው በሐይማኖት አካባቢ የነበሩት ናቸው። በእስልምናም ይሁን በክርስትና ወይም በሌላ የሚገኙ የሐይማኖት ሰዎች፣ ከሐይማኖት መጻሕፍት ጋር በተያያዘ በየእለቱ ስለሚጽፉ፣ ስለሚያነቡና ስለሚመዘግቡ፣ እነዛ የማንበብ ባህል አላቸው። ሰፊው ሕዝብ ወይም ገበሬው፣ አርሶ አደሩ፣ ላብ አደሩ፣ የቤት እመቤቱ ግን በእለታዊ ሥራ ተጠምዶ ስለሚውል፣ እለታዊ ሥራው ከኑሮው ጋር የተያያዘ ስለሆነ ያንን ለማሟላት ሲል ሲራወጥ ይውላል።

ተማር ብሎ ትምህርት ቤቶች የሚከፍትለት አልነበረም። ይህን ኅብረተሰብ ለመለወጥ ትምህርት ያስፈልጋል። ትምህርት የአንድ ሕዝብ ትልቁ የባህል መገለጫ፣ የእድገቱ ደረጃ ነው። የሚማር ኅብረተሰብ ለማንኛውም የእውቀት ዘርፍ መንገዱ የተከፈተ ነው። ለራስና ለሌሎች ነጻነት ለመቆም የንባብ ባህል አስፈላጊ ነው።

ባለፉት ዘመናት የማንበብ እድላችን እጅግ አነስተኛ እና ጠባብ ነበር። አነበቡ የሚባሉ ደግሞ የማንበብ እድሉ የተሰጣቸው ናቸው። ሠራተኛውና ‹ተራው› ሕዝብ ሳይሆን በድሮ አገላለጽ ሐብት ያላቸውና ንብረት የተረፋቸው ወይም ሐይማኖቱ አካባቢ ያሉ ሰዎች ነበሩ እድሉ የነበራቸው። 

ስለዚህ ባህሉ አለን ወይ ለማለት ትምህርት ነበር ወይ የሚለውን ማንሳት ያስፈልጋል። ትምህርት ተስፋፍቶ አልነበረም። ስለዚህ የንባብ ባህላችን እጅግ በጣም ደካማ ነው። በእርግጠኝነት ማለት የምችለውም የማንበብ ባህል አልነበረንም። በቅርብ ቀን አንድ ደራሲ እንደገለጸው፤ ከአፍሪካ በአንደኛ ደረጃ የሚያነቡት ግብጻውያን ናቸው። መጨረሻ ተርታ ካሉት አገራት ነው እኛ ያለነው።

በዓመት 20/30 ልብወለድ የሚነበብበት አገር አለ፤ በግለሰብ። ከዛ እየቀነሰ ወደ አፍሪካ አንድና ኹለት፣ ሦስትና አራት መጽሐፍ ይሆናል። እኛ አገር ግን በዓመት አንድ አንቀጽ ወይም አንድ አረፍተ ነገር ነው የሚደርሰን። ይህ የመጨረሻ አሳፋሪ ነው። በንባብ ደረጃ የዘቀጥን መሆኑን ያሳያል። ለዚህ ማስረጃው አሁን በአገራችን መጻሕፍት ይታተማሉ። ብዙ ታተመ ሲባል ሦስት ወይም አምስት ሺሕ ነው። የአዲስ አበባ ነዋሪ 6 ሚሊዮን ደርሷል ይባላል፤ በግምት። ሦስት ሺሕ መጻሕፍት እኮ በአንድ ቀን ማለቅ ያለበት ነው።

ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ ከግማሽ በላዩ አያነብም ብንል፤ ከቀረው ግማሽ ገሚሱ ማንበብ ባይፈልግ እንኳ ቢያንስ ኹለት ሚሊዮን ተኩሉ ወይም 1 ሚሊዮን አንባቢ እንዴት እናጣለን? ስለዚህ የማንበብ ባህላችን የመጨረሻው የወረደ ቦታ ላይ የደረሰ እንደሆነ በዚህ መረዳት ይቻላል። ሦስት ሺሕ መጻሕፍት አሳትሞ አንድ ዓመትና ስድስት ወር የሚቆይበት ጊዜም አለ። 

አምስት ሺሕ በአሁኑ ጊዜ በጣም ትልቅ ቁጥር ነው። በደርግ ዘመን እነ ሰመመን፣ ዶሰኛው፣ የወዲያነሽ ሲታተሙ ህትመት ብዛቱ 15 እና 20 ሺሕ ነበር። ስድስት ወር ቆይቶም ኩራዝ በድጋሚ ያሳትማል። በጣም የታወቀ ደራሲና ጥሩ መጽሐፍ ከተባለና መጽሐፉ ተፈላጊ ከሆነ እስከ 80/90 ሺሕ ተሸጧል። አንባቢ ኅብረተሰብ እየፈጠርን ነበር።

አሁን በዛ ደረጃ አይደለም፤ ተሻሚ መጥቷል። ሕዝቡ ባለው የኑሮ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታዎች መለዋወጥ የተነሳ ከመጻሕፍት ንባብ ይልቅ ወደ ጋዜጣ ንባብ ሔዷል። ከዛ ቀጥሎ ደግሞ በእጁ ላይ ያሉ ሞባይሎች ከዓለም ጋር የሚያገናኙ መገናኛ ብዙኀን ሆነዋል። ስለዚህ በኢንተርኔት ጠቃሚም ይሁን አይሁን ወይም ሐሰተኛ ዜና ያያል። ቀጥታ ከመረጃው ጋር ይገናኛል። ቀጥታ የሚያነበውም ክፉውን ነው፤ ከሕይወቱ ጋር ያያይዝና ከመከራ ሚዛን ውስጥ ይገባል።

ይህን ትውልድ ግን ለምን አላነበበም ብለን ለመውቀስ የሚያስችለን የተረጋጋ ሁኔታ የለም። ለማንበብ ሰላምና እርጋታ ያስፈልጋል፤ ለማንበብ የኢኮኖሚ ወጪ መሸፈኛም ያስፈልጋል። አንድ ምግብ በሰባ ሰማንያ ብር የሚበላ ወጣት፣ በዛ ብር መጽሐፍ ግዛ ቢባል የነገ ምሳውስ? ንባብ በአንድ በኩል ከኢኮኖሚና ከሕይወት ጋር ይያያዛል። በብዙ ነገር ተጨንቆና ነገን በደቀቀና ቆሞ በማይሔድ ተስፋ እየተመለከቱ ለንባብ የሚጋብዝ ነገር የለም።

አንድ ጋዜጠኛ ከደሞዙ ግማሹን ለኪራይ ሰጥቶ የቀረውን ለምግብና ትራንስፖርት እንዲሁም ማኅበራዊ ግንኙነት ዙሪያ ካወጣ በኋላ እጁን አጣምሮ ይቀመጣል። ስለኑሮው እንጂ ምርጥ መጽሐፍ ወጣ ቢባል የንባብ ሱስ ከሌለበት በቀር ገዝቶ ለማንበብ እድሉ ጠባብ ነው።

ግን ብዙዎቹ ወጣቶች ያነባሉ። ለዛ ነው ምርጥ መጽሐፍ እየወጣ እያየን ያለነው። በተለያየ ሙያ ውስጥ ያሉ ሰዎችም ጽፈው አስነብበውናል። ለአእምሮ የሚያስደንቁ ልጆችን በየመድረኩ እያየን ነው። ግን የማንበብ ባህላችን ሊሠራበት ይገባል። መንግሥት ለተለያዩ ጉዳዮች ዓመታዊ በጀቶች እንደሚመድበው ሁሉ፣ ለአብያተ መጻሕፍት የሚያገለግል ዓመታዊ በጀት ያስፈልጋል።

አሁን ላይ ለማረሚያ ቤቶች መጽሐፍት እየተሰጠ ነው፤ ይሄ ድንቅ ነገር ነው። ትልቁ ስጦታም ነው። መንግሥትም በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ወመዘክር በኩል ለተለያዩ ማረሚያ ቤቶች መጻሕፍት እየሰጠ ነው። መንገድና ሌላው መሠረተ ልማት ላይ እንደሚሠራው፣ አብያተ መጻሕፍት ተከፈቱ ማለት የኅብረተሰቡ እድገተ ማስፋፋት ስለሆነ ሊበረታታ የሚገባው ነገር ነው።

በመጽሐፍት ሥራዎቻችን የቋንቋ ብዝኀነት በበቂ ሁኔታ ታይቷል?

በቂ አይደለም። አማርኛ ባለፉት በርካታ ዓመታት የመንግሥት መጠቀሚያ ቋንቋ ከመሆኑ የተነሳ በማኅበራዊ ኑሮም እየሰፋ መጥቷል። ይህ በመሆኑ አማርኛ በኢትዮጵያ የትኛውም ቦታ መነጋገሪያ መሆን ችሏል። ኹለትና ሦስት ብናደርገውም የበለጠ ጥሩ ነው። ቋንቋን ማስፋፋት ግንኙነትን ማዳበር ነው። የአገራችን ሁሉም ቋንቋዎች እንዲያድጉ፣ እንዲበለጽጉና እንዲስፋፋ ማድረግ በእኔና በሌሎች ሰዎች መካከል የሚገኝን ግንኙነት የበለጠ ማሻሻል፣ እድገትን፣ ልማትን ፍቅርን መጨመር ነው።

ከመንግሥት ብቻ ሳይጠበቅ ኅብረተሰቡም ቋንቋውን ለማሳደግ መጣር አለበት። ግንኙነታችን የሚጠነክው አንዳችን የሌላችንን ቋንቋ ስናውቅ ነው፤ ለማወቅ ደግሞ ሁላችንም ልባችን ክፍት መሆን አለበት። የማወቂያ መንገዱም ሊከፈት ይገባል። እኔ አማርኛ እንዲሁም ትግረኛ አሳምሬ እናገራለሁ። ነገ የኦሮምኛ ቋንቋ ማስተማርያ ቢከፈት ብማር ደስ ይለኛል። ብዙ ጓደኞች አሉኝ፣ እነርሱ ቤት ገጠር ስሔድ በኦሮምኛ ቋንቋ ብግባባ ደስ ይለኛል።

በተቻለ መጠን ሁላችንም በምንግባባበት ቋንቋ መነጋገር አለብን። ይሄ ነው ሊያዋህደን የሚችለው፤ ቂቤና ሽሮ ሲገናኙ ይጥማሉ። እንዲሁ ሆነን ነው አንድነታችን እና ኅብረታችን ሊያድግ የሚችለው። እንጂ የአንተን ቋንቋ አልሰማም፣ አልማርም ብሎ አይደለም። በቋንቋ ምክንያት መጋጨት የለብንም። ሁሉም የእኛ ናቸው።

መጻሕፍት ግን የሉም ማለት ይቻላል፤ በጣም አነስተኛ ነው። ይህ ትልቅ ሥራ ይጠይቃል። በየብሔረሰቡ የሚገኙ የተማሩ ሰዎች የተለያዩ መጻሕፍትን በየሙያ ዘርፋቸው ሊጽፉ ይገባል። ሲጻፍበት ነው ቋንቋ የሚያድገው እንጂ በግድ አይደለም። ቋንቋዎቻችን ሊያድጉ የሚችሉት በተለያ የትምህርት ዘርፍ የተማሩ የብሔሩ ሰዎች ሲጽፉባቸው ነው። ቴአትርን፣ ሙዚቃውን የግብርና እና የጤናውን የመሳሰለውን ከተራ ጉዳይ አንስቶ መጻፍ ያስፈልጋል።

መጀመሪያ እንዳልኩት ትምህርት መሠረት ነው። ሰው ከተማረ ነው ወደ ማንበብ የሚመጣው። በትምህርቱ ደረጃ በደረጃ መጽሐፍ ማቅረብ ያስፈልጋል። እኛም ጋር ከአነስተኛው ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ድረስ እየጨመረ በሚሔድ ደረጃ ሊዘጋጅ ይገባል። ይህን መሥራት የሚችሉት የተማሩ ቋንቋውን የሚያውቁት ናቸው። የመንግሥትንም ከፍተኛ ድርሻ ይጠይቃል። የወረቀት ዋጋን ዝቅ በማድረግ፣ ቀረጥን በማሳነስ። እንጂ አንድ ጸሐፊ ወይም ደራሲ ሠርቶ ማሳተሚያ ካጣ የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ ይቀራል።

ሁሉም ቋንቋዎች እንዲያድጉ የተማሩ ሰዎች ሊጽፉ ይገባል፤ የተጻፉት እንዲደርሱ ደግሞ የህትመት ዋጋው ሊታሰብበት ያስፈልጋል።

በሥም የሚታወቁ ደራሲያን ሥራዎች ምንም ሆነ ምን በብዛት ይነበባሉ። አዳዲስ ጸሐፍያንየሚታዩበት አጋጣሚ ግን ጠባብ ነው። ይህን እንዴት ታየዋለህ?

ነባርና የታወቁ ደራስያን መጻሕፍት ይሸጣል። ይህ በመላው ዓለም ያለ ነው። በየትኛውም ዓለም 5 እና 6 መጻሕፍት ወይም 1 እና 2 ጽፎ ዝነኛ ከሆነ፣ የዛን ሰው ለመግዛት እሽቅድድም አለ። ግሩም ሆቴል አዲስ አበባ የከፈተ ሰው ከአዲስ አበባ ውጪ የሆነ ከተማ ሌላ ሆቴል ቢከፍት፣ በቀጥታ ‹የአዲስ አበባው ሰውዬ› ብሎ ሰው ይሔድለታል። መጀመሪያ ጥሩ አሠራር ስላሳየ ነው።

አንድ መልካም ደራሲም ጥሩ ሥራ ካበረከተ፣ በቋንቋ፣ በታሪክ አወቃቀርና አቀራረብ፣ በድርሰቱ ተዓማኒነት ይወዱታል፤ ቅድሚያም ይሰጡታል። ይሄ ግን አያዋጣም። ምክንያቱም ከሱ በኋላ ያንን ሰው የሚበልጡ ሥራዎች ይወጣሉ። ስለዚህ ኅብረተሰቡ በነባር ሥራዎች ብቻ የተመሠረተ እውቀትና ፍቅር ሊኖረው አይገባም። ከአዳዲሶችም መምጣት አለበት።

የተሻሉና የበለጸጉ የብዕር ሰዎች እንዳሉ ማወቅ አለብን። ይሄ ማበረታታት ብቻ ሳይሆን ተመራምሮና መርጦ ማንበብ ያስፈልጋል ነው። አዲሱ ትውልድ ካለፈው ተምሮ የተሻለ እንደሚፈጥር መገንዘብ ያስፈልጋል። አንዴ ታውቀዋል ብለን በነዛ ሰዎች ላይ አምልኮተ ብዕር ሊኖር አይገባም። የ‹ፍቅር እስከ መቃብሩ› ሐዲስ ዓለማየሁ ሳያሳትሙት የቀረ አንድ መጽሐፍ ተገኘ ቢባል፣ በሥማቸው በወረፋ ነው የሚሸጠው። ወይ የበዓሉ ግርማ ያልታተመ ያስቀመጠው አንድ መጽሐፍ ተገኘ ቢባል ሰዉ በሰልፍ ነው የሚገዛው።

በዘመናችን ያለ ደራሲ ድርሰት ሲያወጣ ራድዮ እና ጋዜጣ፤ ያነበቡ ሰዎችም ሊያስተዋውቁለት ይገባል። በዚህ መልክ ነው መሆን ያለበት። በሥም ብቻ ለዘለዓለም መኖር አይቻልም። ሥም እየታደሰ መሔድ አለበት። አዳዲስ ምርጥ ተነበው የተመሰከረላቸው የመጻሕፍት ሥራዎችንም ማየት ያስፈልጋል።

ስለዚህ የድሮዎቹን ብቻ እያደነቁ አዲሶቹን ገለል ማድረግ አዳዲስ ብርሃን እንዳይፈነጥቅ ማድረግ ነው። አዲስ ብርሃን ሲመጣ እድል መስጠት ያስፈልጋል። ይህም የሚሰጠው በሥራው ነወ። እስከዛሬ ድረስ በተለያዩ የዓለም አገራት በሥራቸው የተደነቁና ምንጊዜም ቢሆን ሥራዎቻቸው ቸል የማይባል ሥራ የሠሩ ደራስያን አሉ። መምረጥ መብት ነው። ስንመርጥ ግን አዳዲሶቹንም ማየት አለብን።

በአሁን ሰዓት ብዙ ደራስያን አሉ፤ በተቻለን መጠን ያተሙትን መጽሐፍ መግዛት፣ አይተንም ማበረታታት አለብን። ሒስ ደግሞ እንዲበረቱ አስፈላጊ ነው። አጥፊ ሳይሆን ገንቢ ሒስ መስጠት፣ ትክክለኛውን እርማት መስጠት። አንድ አትክልት አየተኮተኮተ ሲሔድ እያደገ ይሔዳል። ደራሲም በትክክል በእውቀት ከታረመ እያደገ እየበለጸገ ይሔዳል።

ኃይለመለኮት ከ‹ወዲያነሽ› እና ከ‹ጉንጉን› በኋላ በስፋት ለሕዝብ የደረሰ ሥራ አላቀረበምና የት ጠፋእየተባለ ነው። ጋሽ ኃይለመለኮት የት ጠፋ?

ባለፉት ዓመታት በብዛት ስሠራ የነበረው በንባብ ባገኘሁት፣ ባለኝ አቅምና እውቀት ወጣቶችን ማገዝ ነው። በተለያዩ በተለይም በአጫጭር ታሪኮችና ልብወለዶች አንዳንድ ጥያቄ ሲያቀርቡ ማማከርና ማገዝ ላይ ነበርኩ። የአርትዖተ ሥራ ስሠራም ነበር። ባልመዘግባቸውም በጥቂቱ ከማስታውሰው ወደ 64 መጻሕፍት አርትዖት ሠርቻለሁ። የራሴንም በፊት ተሠርተው የነበሩ ሥራዎች አርትዖት እየሠራሁ ነው፤ በወጣትነት እድሜ የጻፍኳቸውንም። አሁንም እየጻፍኩ እየሠራሁ ነው። በሕይወት ትግል ያለውን ውጣ ውረድ አልፎ አሁን እየደረሰ ነው። እና አለሁ፣ እየሠራሁ ነው።

ከበርካታ ዓመታት በኋላ ኤርትራ ሔደሃል። ቆይታህ እንዴትና ስለምን ነበር?

በሕይወቴ ብዙ የደስታ ጊዜ አሳልፌአለሁ። የመከራ ጊዜም እንደዛው። መከራው ብዙም የሚያስመርር አይደለም። አብዛኛው የሕይወቴ ክፍል በደስታ የተሞላ ነው። በሥራዬ፣ በትዳሬ፣ በልጆቼ፣ ከሰዎች ባለኝ ግንኙነት በጣም ደስተኛ ነኝ። አንዴ የታሰርኩበት ጊዜ ነው የከፋው። እሱም በዘመኑ በማንኛውም ኢትዮጵያዊ ላይ የደረሰ እንጂ ለብቻዬ የመጣ መከራ አይደለም።

በወቅቱ በመንግሥት በኩል የነበሩትም መከራ ነበረባቸው፣ በእኛም ተቃዋሚ በነበርነው መከራ ነበረብን። እና የሁላችን እንጂ በእኔ ለይቶ የመጣ አልነበረም። ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ የኑሮ ውጣ ውረድና መሰናክል እንጂ የሚያስመርር ችግር ገጥሞኝ አያውቅም። በኑሮ ትግል ተሸንፌ አላውቅም፤ እፍጨረጨራለሁ ድል አደርጋለሁ።

በሕይወቴ ደስ ከተሰኘሁበት ቀናት መካከል ግን አንዱ ልክ የዛሬ ዓመት ነው፤ ኤርትራ አስመራ ነበርኩ። በ1962 ከኤርትራ አንዴ ከወጣሁና እዚህ [ኢትዮጵያ] ከገባሁ ወዲህ አልተመለስኩም። በመጀመሪያዎቹ ዓመታት አባቴ ጋር ምን ይዤ እሔዳለሁ ስል ቆየሁ፤ ከዛ አብዩቱ መጣ። ያኔ ደግሞ ለመሔድ ለመምጣት የሚቻልበት ጊዜ አልነበረም። በደርግ 17 ዓመታት መሔድ ይቻል ነበር፤ ነገር ግን ዛሬ ነገ ስል በዛ አለፈ። ከ1983 በኋላም በተመሳሳይ ነገ ከነገ ወዲያ ስል ቆየሁና ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲነሳ ጨርሶ ተቋረጠ። ከሃምሳ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ አንዴ ከመጣሁ ወደ ኤርትራ አልተመለክስኩም።

አባቴን ሳላገኘው እዚህ እያለሁ ነው የሞተው፤ በመሃል አንድ ጊዜ መጥቶ ተያይተናል እንጂ። የምወዳቸው ሦስት እህቶቼ ሞተው ነው የቆዩኝ፣ በጣም የምወደው ወንድሜ ‹ጉንጉን› መጽሐፍ ላይ መታሰቢያ ያደረኩለት አፈወርቅ የሚባለውና ብዙዎቹን በአባቴ ወገን ያሉትን በሕይወት አላገኘኋቸውም። ያው ትውልድ ይቀጥላል፤ ‹‹ሲፈጭ ሲቢካ ሲሞት ሲተካ›› እንዲሉ የአጎቶቼን ልጆች እና የእህት ወንድሞቼን ልጆች አግኝቻለሀ። ከእህት ወንድሞቼ ታላቆቼን ኹለት አግኝቻለሁ።

ኅዳር 20 አስመራ ኤርፖርት ስደርስ የተቀበሉኝ የእህት የወንድም፣ የአጎት የአክስት ልጆች አበባ ይዘው ነው፤ ሠላሳ ይጠጋሉ። እኔ ወደዛ ከመሔዴ በፊት ድንበሩ እንደተከፈተ ታላቅ ወንድሜ ከባለቤቱ ጋር መጥቶ ነበር። እሱ በመጣ በኹለተኛ ሳምንት ነው የሔድኩት። እና በቴሌቭዥን ያዩኝ ስለነበር ገና ስመጣ ‹‹አያይ መጣ!›› አሉ፤ ጋሼ ማለት ነው። በደስታ አለቀስኩ። ልቆጣጠረው አልቻልኩም። ተቃቅፈን ተላቅስን፤ የደስታ እንባ ነው። 

ያን ጊዜ ለመግለጽ ያስቸግራል። ለቅሶ የጀመርኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስመራ ሔዱ መባሉን ልጄ ነግሮኝ በቴሌቭዥን ተከፍቶ ስመለከት ነው። ልጄ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አንድ ላይ ተሰቅሎ አሳየኝ። ‹‹ዐቢይ አስመራ ሔዷል›› አለኝ። በእለቱ የነበረውን ስርዓት ስመለከት አንድ ጊዜ ብቻ ነው ከወንበሬ የተነሳሁት፤ እዛው ቲቪ ላይ ተተክዬ እየተደጋገመ ሲታይ እኔም ሳይ ነበር። ይህ ሲሆን ግን አለቅስ ነበር። ይህ ቀን በሕይወቴ ይመጣል ብዬ አልጠበኩም።

በሔድኩኝ በማግስቱ አስመራ ማርያም ጽዮን ነበር። አስመራን እንደ እጄ መዳፍ ነው የማውቀው። ተሠርቶ ያለቀ ከተማ ስለነበር፤ ታክሲ ተሳፍሬ መሃል ከተማ ኩምቡሽታቶ ውሰደኝ አልኩት። ሔድኩኝ፤ ቅድስት ማርያምን ተሳለምኩም፤ ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ የተማርኩበት ‹አክሪያ› የተባለ ትምህርት ቤት ሔድኩ። ክፍሎቹ እንዳሉ አሉ።

ግን አይቼ አልጠገብኩም። ጎዳናውን፣ ሰዉንም፣ በአካባቢው የነበረውን ትዕይንት በሙሉ አልጠገብኩም። ቀጥሎ የአባቴ አገር ከአስመራ 8 እና 9 ኪሎሜትር በምዕራብ ነው። እዛ ሔጄ ታላቅ እህቴንና ዘመዶቼን አገኘሁ። እስከ እኩለ ሌሊት የልጅነት ዘመናችንን ከቤተሰብ ጋር ስንጫወት፣ ሳናወራ ሰነበትኩ። 26 ቀን ገደማ ቆይቼ ነው የተመለስኩት።

በልጅነት ከነበሩ ጓደኞቼ መካከል ግን ኹለቱን ብቻ ነው ያገኘሁት። የተቀሩት በሙሉ በጦርነት፣ ግማሾቹ ታጋይ ሆነው በዛው ሞተዋል፤ አንዳንዶቹ የት እንዳሉ አድርሻቸውን ማወቅ አልቻልኩም። አስመራን ከዳር እስከ ዳር አዳረስኩት። በጉብኝቴ ረክቻለሁ፤ ሆኖም ገና ማየት እፈልግ ነበር። በጣም ደስ ካለኝና ካየሁት ነገር አንዱ፣ እንጨትና በለስ የምንለቅምበት ነበር። ከአስመራ ወደ ምጽዋ መንገድ አካባቢ ከጓደኞቼ ጋር ነበር የምንሔደው። አሁን በምሔድበት ጊዜ ግን አንድም ጓደኛ በዛ ደረጃ ባለማግኘቴ ዐስሩን ኪሎሜትር በትዝታ እያለቀስኩ ነው የሔድኩት።

በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው ሰላም ለእኔ ከምንም ነገር በላይ ትልቁ ደስታዬ ነው። የእነዚህ ሕዝቦች አንድነትና ፍቅር ለዘለዓለም ጸንቶ እንዲኖር ምኞቴ ነው። ከዛም ባለፈ ሁኔታ ቢፈጸም። እናም የኹለቱ ሕዝቦች አንድነት በመመለሱ፣ የጦርነት ስጋት በመቀነሱ፣ አሁን ደግሞ እያደር በፖለቲካና በዲፕሎማሲ መንገድ ለጊዜው የተዘጋው ድንበር ሕግን ስርዓት ተበጅቶለት፤ የኤርትራ ሕዝብ እንደልቡ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ኤርትራ እንደ ልቡ እንዲሔድ፤ አልፎ ተርፎ እዛም እዚም እንዲሠራ የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሮ አይቼ ብሞት እላለሁ፤ እንደሚፈጠር ደግሞ ተስፋ ነኝ።

ያ ሕዝብ እና ይሄ ሕዝብ ከኩሬ አይደለም ከአንድ ትልቅ የታሪክ ባህር የተቀዳ አንድ ሕዝብ ነው። ወንድማማች ሕዝብ ነው። አንዱ በሌለው የሚቆም ነው። አንዱ በሌላው ላይ ፍጹም ጠመንጃ መምዛዝ የለበትም። ከዚህ በፊት የተደረገውም የስህተት፣ የአስተሳሰብ ድህነት ጦርነት ነው። ከእንግዲህ ስለ ሰላም እና በጋራ ስለመበልጸግ ነው ማሰብ ያለብን።

የጦር ሜዳ ዛሬ የእህልና የልማት አውድማ ማድረግ አለብን። በአንድ ላይ ስንሆን አብረን እንበለጽጋለን፤ ለሕዝቦች ጥቅምና መብት በጋራ እንታገላለን። ስለዚህ የኹለቱ ሕዝቦች ፍቅርና አንድነት ዘለዓለም ይኑር እላለሁ።

የማንን መጽሐፍ ደጋግመህ አንብበሃል?

አነባለሁ፤ ጊዜ ባለኝ ቁጥር ሁሉ ማንበብ ሥራዬ ነው። የወጣቶቹን በብዛት አነባለሁ፤ መምረጥ ያስቸግራል። መጀመሪያ ያነበብኩትን መጽሐፍ መጥቀስ ደስ ይለኛል። ‹‹ገልጠን ብናየው›› የምትባል፣ ቤካን የተባሉ ደራሲ ናቸው የደረሷት። እርሳቸውን ምንጊዜም አልረሳቸውም፤ ወደ ንባብ ያመጣኝ የእርሳቸው መጽሐፍ ነው።

ከዛ በኋላ የድሮዎቹን ደራስያን በሙሉ ከነቋንቋቸው፣ በዘመኑ ከነበረው ታሪክ፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ ትስስር ላይ ተመሥርተው የጻፉትን እወደዋለሁ። ብርሃኑ ዘሪሁንን በጣም እወደዋለሁ፤ በጣም። የ‹አደፍርስ›ን ደራሲ ዳኛቸው ወርቁን በጣም እወደዋለሁ። እና ወዘተ…ብዙ ናቸው። ብዙ ስለሆኑ እገሌ እገሌ የለውም። ለእኔ ሁሉም ደራሲ በየአቅሙ በሚጽፈው መጠን አደንቃለሁ። ምክንያቱም ሁላችን በአቅማችን ነው የምንዘለው። በየአቅሙ የሚጽፍን ወጣትም ሆነ የድሮ ደራሲም ቢሆን፣ አደንቃለሁ።

በ2012 የጻፈ ደራሲ ከዓመታት በኋላ ቢጽፍ ሌላ ሰው ሆኖ ነው የሚገኘው። እነ እንዳለጌታ ከበደ እና እነ ዓለማየሁ ገላጋይ የጀመሩበትን መጽሐፍ እና አሁን ያሉበትን መጽፍ ስታነጻጽሪ፤ ሲጀምሩ እና አሁን አንድ አይደሉም። በእውቀቱ ስዩም ድሮ ሲጽፍበት የነበረውን የግጥም ደረጃ ዛሬ ላይ ሲታይ አንድ አይደለም። ይህን እድገታቸውንና ጥረታቸውን አደንቃለሁ። እነዚህን ለምሳሌ ነው ቅርብ ስለሆኑ የማነሳው። ስለዚህ ሁሉም ደራሲ አቅሙ እየጨመረ እንደሚሔድ ስለማምን፣ ባነበበ ቁጥር የተሻለ እንደሚሆን ስለማውቅ፣ አንባቢዎችም ስለሆኑ አድናቆቴ ለሁሉም ደራስያን፣ ገጣምያን፣ ሰዓልያን እና ሙዚቀኞች ነው። ሙዚቃ ደግሞ እጅግ ነው የምወደው።

ከአዲስ ማለዳ የተወሰደ | እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 01 ቀን 2020 

https://bfaethiopia.wordpress.com/2020/02/24/%E1%8A%A0%E1%8A%A5%E1%88%9D%E1%88%AE%E1%8A%95-%E1%89%A0%E1%89%B0%E1%8C%88%E1%8B%B0%E1%89%A0-%E1%8A%90%E1%8D%83%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8B%8D%E1%88%B5%E1%8C%A5-%E1%88%9B%E1%8A%95/

በአዝናኝና አሳዛኝ ገጠመኞች የተሞላው የደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ጨዋታዎች ከደራሲ ዶ/ር እንዳለገታ ከበደ ጋር ክፍል 1 


 የደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ጨዋታዎች ከደራሲ ዶ/ር እንዳለገታ ከበደ ጋር ክፍል 2








Monday, June 27, 2022

ጎዳናው ይገርማል?! ___በረከት በላይነህ



ጎዳናው ይገርማል?!

በረከት በላይነህ _ጋዜጠኛ፣ ገጣሚና ደራሲ
************************
ይገርማል መንገዱ
እግረኛው ይገርማል

ሸራ ጫማ ባ'ይነት
በነጫጭ ካልሲ
በሲኪኒ ሱሪ
ከመምህሩ ጋራ
አይስክሬም ሚልስ
የሀይስኩል ተማሪ
.
ፀባይኛ ወጣት
ጃንቦ ተከልሎ
በምርቃና ሆኖ
ሀሳብ የሚፈትል
አንዲት ሙ......ደኛ እናት
በ'ድሜ ከልጆቼ አንሳለው የምትል
ፒዛውን የሚገምጥ
ጭማቂ የሚመጥ
አራዳ አባወራ
በሚስቱ ትከሻ
በልጆቹ ምላስ
ቅምጥ የሚጣራ
.
አንድ ፍሬ ሴቶች
በተገዛ ቅንድብ
በተገዛ ፀጉር በተገዛ ጥፍር
በውሰት ወዘና የተብለጨለጩ
ማኪያቶ ከበው
ለውስኪ ሚንጫጩ
ጅናም ጅንሳም ወንዶች በሴቶች ጫጫታ የሚቁለጨለጩ
.
ይገርማል ጎዳናው ይገርማል መንገዱ....
.
ድንቡሽቡሽ ህፃናት
በቶም ኤንድ ጄሪ ሱስ
ቀልባቸው የከሳ
በአይፎኑ አጮልቆ
ያንጀሊናን ከንፈር የሚስም ጎረምሳ
.
ቀውጢ ዳያስፖራ
.
የሎቲው የቁምጣው የቲሸርቱ ጥለት የተንዘረፈፈው
አማርኛ ሲሸሽ "what's happen" የጠለፈው
.
ነቄ ብላቴና
.
ከዮፍታዬ ቀዬ
ካ'ዲስ አለማየሁ
ከመዝገቡ መንደር
የአዲስ አ'ባ ጥሪ
በቁምጣ ያበረረው
ከቅኔ ተጣልቶ
ከግዕዝ ተኳርፎ ሎተሪ ሚያዞረው
.
ፀዴ ብላቴና
.
ከባላገር ዘመን
ከጨለማ ዘመን
ወደ ብርሃን ጥግ ተሸጋገርኩ ብሎ
በሸንኮራ ምርኩዝ ከተማ ሚያካልል መቋሚያውን ጥሎ
ነብሱ እየሰለለች
በከተሜነት ወግ ባ'ራዳነት ልምሻ
ሲያዘግም የሚውል
ሊስትሮውን ጭኖ በታቦት ትከሻ
.
ፎቆቹ
.
በመስታወት ቁመት በቆርቆሮ ገፆች
ባ'ልሙኒየም ጥራዝ የተብረቀረቁ
የጌቶቻቸውን እድሜ ሚያሳብቁ
ሁሉም........ ሁሉም......ሁሉም ጥግ ናቸው
ለወደቀ ወገን ይራራል ልባቸው
.
ሁሉም
...... ሁሉም
.
ከዘለለት ጥድፊያ
ከሰርክ ውጣ ውረድ በተረፈች አንጀት
ለወደቀ ወገን ምርኩዝ ማበጃጀት
ሁሉም...... ሁሉም ይችላሉ
ስለ'ግዚአር ላለ ይመፀውታሉ
.
እኔ ግን........ እኔ ግን .........ቆጥራለው
የ'ድሜ ክቡር ጀንበር
በጎዳና ፅልመት ሲዋጥ አስተውላለው
ጡረታ መንገድ ዳር ሲከፈን አያለው
.
ቆጥራለው.....ቆጥራለው
.
ቆጥራለው አዛውንት
በየአቀበቱ በየቁልቁለቱ
ማረፊያ ፍለጋ የሚንከራተቱ
ቆጥራለው አዛውንት ከልጆቻቸው ፊት
የልመና መዝገብ የገለጡ አሮጊት
ቆጥራለው በየመንገዱ ዳር
እርጅና ሙሽራው ለምፅዋት ሲዳር
ቆጥራለው በየሸንተረሩ በየተፋሰሱ
አቀርቅሮ ሲያዘግም እርጅና ሞገሱ
ቆጥራለው በ'ያደባባዩ
የሽማግሌ አይኖች የልጅ ፊት እያዩ
ቆጥራለው በየሰርጣሰርጡ
በልመና ጉልበት ከሞት ሲፋጠጡ
የ'ርጅና መዳፎች እሾህ ሲጨብጡ
.
ቆጥሬ..... ቆጥሬ.......ቆጥሬ
በለማኝ አዛውንት ብዛት ተሳክሬ
የማሰንበቻ ስንቅ ከኪሴ ቆንጥሬ
ያፅድቆቴን ዋጋ በሳንቲም መንዝሬ
ባ'ዛውንት ምርቃት ከሀገር ከቀዬው ትርፌን ሳመሳስል
በጎዳናው ቀለም ፃድቅ መልኬን ስስል
ጎልቶ ሚታየኝ ግን የሚያሳፍር ምስል
በቀላል ጥያቄ የነተበ ምስል
.
ጥያቄ
.
የዲጄ ኳኳታ የደናሽ ጋጋታ
የድራፍት እርካታ ያ'ረቄ ድንፋታ
ባጣበበው መንገድ
እንደምን ይቻላል
ላ'ያት ሳንቲም ሰጥቶ በ'ርካታ መራመድ?
.
ለወጣት ሹክሹክታ ለገደል ዝምታ
ላስመሳይ ጫጫታ ላድርባይ እሪታ
በተሰራ መንገድ
እውነት ቀላል ነው ወይ
ላ'ያት ሳንቲም ሰቶ በ'ርካታ መራመድ?
.
ለቡቲክ ሰልፈኛ ለካፌ 'ድምተኛ
ለውስኪ ጭሰኛ ለበርገር ምርኮኛ
በተሰራ መንገድ
እንደምን ይቻላል
ላ'ያት ሳንቲም ሰቶ በ'ርካታ መራመድ?
.
አያት....አያት...አያትነት ማለት
በደማቅ አሻራ የሸመኑት ጥለት
ለተራኪ እድሜ የተሰጠ አንደበት
ባ'ባት በ'ናት ፅናት የማይደክም ጉልበት
በልጅ ልጅ መነፅር የማያረጅ ውበት
በልጅ ልጆች ጥበብ የሚታደስ እውቀት
.....................................የሚታደስ እውነት
አያት ሆኑ ማለት
ድርብ አባትነት
ድርብ እናትነት
.
በተለይ እዚህማ.......
በዚህች አይነት ሀገር
ጎጆዋን ላቆመች
በተጋድሎ ካስማ
ባርበኝነት ማገር
በዚህች አይነት ሀገር
ጥያቄና መልሷን
ባ'ዛን በቅዳሴ በምትሰራ መንደር
በዱአ በፀሎት
በምናኔ ምርኩዝ በከረመች ሰፈር
የአያትነት ዋጋው በልኩ ቢሰፈር
ለሳንቲም ምርቃት ባልተሻማን ነበር!
.
ታሪክ በመዳፉ ስላደላደለው
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንጉስ አያት አለው
የልጅ ልጆች ስባት ባያመነምነው
ያያቶቻችን መልክ ሁሌም አንድ አይነት ነው
.
እላለው... እላለው....
.
የልጆች ምፅዋት ያ'ያቶች ልመና
ያ'ባቶች ግርግር በሞላው ጎዳና
መንገዱ አይልቅም
ጎዳናው አያልቅም
ይሰፋል ይረዝማል ይሄዳል ይጓዛል
እግረኛው ሞኝ ነው
ሳንቲሙን ዘርዝሮ
ከወደቁ አዛውንት ምርቃት ይገዛል
.
መንገዱ ያስፈራል
መንገዱ ይጨንቃል
ልጆች ሳቅ ሲያንቃቸው
አያት እምባ ይጨምቃል
መንገዱ ያሰጋል መንገዱ ያረጃል
ከዘናጭ ልጆች ጎን እርዛት ያዘለ አያት ይወለዳል
.
ሰጪ ካለቀሰ ተበዳሪ ስቆ
ጌታ ከለመነ አማኙ 'ግር ወድቆ
ልዑል ከዘመረ ንጉሱ ተዋርዶ
ገፁ ተመሳቅሎ ሽፋኑ ካማረ
ወለሉ ተንቆ ምንጣፍ ከከበረ
ባ'ገርኛ ስሌት ማነው ያልከሰረ?
.
እላለው........እላለው
.
ከየጎዳናው ገፅ ጥያቄ አነሳለው
ጥያቄ እጥላለው
እርጅና ለማምሻው ጎዳናን ካመነ
አያት ከልጅ ልጁ ሳንቲም ከለመነ
ባገርኛ ስሌት ማነው ያልመከነ?
.
በ'ግዚኦታ ዘመን በምዕላ ዘመን
እመንገድ ዳር ወድቆ ትራፊ መለመን
በጥሞና ዘመን የሚያስቡት ማጣት
በማውረሻ እድሜ የሚሰጡት ማጣት
በማልበሻ ዘመን በ'ርዛት መቀጣት
በለጋሽነት ወቅት በማጉረሻ ዘመን
በጥማት መገረፍ በርሀብ መመንመን
ከሆነ እጣችን
ይጠየቅ ትርጉሙ የልጅነታችን
ይፈተሽ መንገዱ የልጅ ልጆቻችን

ግድ የለም እንመን

እንመን

በሰውኛ ስሌት ውጤቱ ሲሰራ
ትውልድ ያደኸያል ያያቶች ኪሳራ
በልጅ ልጆች ዓለም
እንደጉድ ቢደለቅ ቢዘመር ቢዘፈን
አባት ይወራጫል ባ'ያቶች መታፈን
.
አባት ሆይ
.
ለልጆችህ ርዕዮት
ትላንቱን የረሳ ተስፋ ሲደራረት
ህልሜ ነው ይልሀል ያ'ያቶቹ ቅዠት
ከልጅህ አንደበት
ቋንቋ እንደዶፍ ቢዘንብ
ትርጉም ቢንፎለፎል ሺ ቃላት ቢጎርፍም
የልጅ ልጅ አግባቢ ግማሽ ገፅ አይፅፍም
ከልጆችህ ባህር
አሳ የሚያጠግቡ ለአሳ ሚስማሙ
እፅዋት ተክሎች
እንደጉድ ቢራቡ እንደጉድ ቢያብቡ
ገበታው አይሞላም ተቀዷል መረቡ
.
ግድ የለም እንመን........እንመን
.
የስኬት ክብደቱ
የምቾት አይነቱ
የነገ ውበቱ ባሻው ቋት ቢለካ
በምንም ቢሰፈር ባሻው ቃል ቢነገር
ጀግና ልጅ አትወልድም
አያቶቿን ገድላ የምትሸልል ሀገር
.
ከፎቆቹ ጥላ....
ከያስፓልቱ ገላ ሲታተም ድምቀቴ
በመስታወት አጀብ ሲጠገን ጉልበቴ
ይኸው አነበብኩት
አያቶቼ ፊት ላይ ተፅፏል ሽንፈቴ
በመኪና ብዛት
በመስታወት አይነት ሲለካ ፍጥነቴ
በግንብ አጥር መአት
በፎቆች ጋጋታ ሲሰላ ስኬቴ
ይኸው ይታየኛል
አያቴ ገፅ ላይ ተስሏል ውድቀቴ

ተስሏል ሽንፈቴ!

።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።


Thursday, March 3, 2022

ፕሮፌሰር ሐይሌ ገሪማን በጨረፍታ

 A Glimpse of Prof Haile Gerima
 *************************** 
(የዘመን አቆጣጠሩ ሁሉ እንደ አውሮፓውያን ነው ) ከአሥር ልጆች አራተኛ በመሆን የተወለደው ኃይሌ ገሪማ መጋቢት 1946 ላይ ነው ይችን አለም የተቀላቀለው ፡፡ እናቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ ሲሆኑ አባቱ አቶ ገሪማ ታፈረ ደግሞ የተውኔት እና የቴአትር አዘጋጅ ነበሩ፡ እንደ ሳንኮፋ ድረገጽ ከሆነ ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ ገና በወጣትነት ዘመኑ የአባቱን ፈለግ በመከተል በአባቱ ቲያትሮች ይለማመድ ነበር ፡፡ ሃይሌ እና እህቱ ዘመናዊ ትምህርት ቤት በመሄድ በቤተሰባቸው ውስጥ የመጀመሪያዎቹ እንደሆኑ ድረገጹ ጠቅሶ የሃገሩን ባህል እና ሥርዓተ ትምህርት በማስተማር እና ለአሜሪካ የሰላም ጓድ አባላት እንዴት ፊደል መጻፍ እንደሚቻል በማስተማር እንዲሁም ባህሉን በማስተዋወቅ የድርሻውን ተወጥቷል ፡፡ 
ፕሮፌሰር ሃይሌ. "ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በፈጠራ ጥበብ ማዕከል ውስጥ አጭር ቆይታ ካደረገ በኋላ, ድራማ ለማጥናት ወደ አሜሪካ አቅንቷል፡፡ እዚያም ሸሪኪያና ከተባለች ሴት ጋር በትዳር ተጣምሮ አምስት ልጆችን አፍርቷል፡፡ በሎስ አንጀለሰ ከተማ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ከ1976 ጀምሮ የፊልም ጥበብን በማስተማር ስራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል ፡፡ 
የፊልም ጥበብ ቀማሪው ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ ከሰራቸው ፊልሞች መካከል 
አወር ግላሰ ፣ 
ቻይልድ ኦፍ ሬንሰንስ ፣ 
ቡሽ ማማ የተባሉ ስራዎችን በ1975 የሰራ ሲሆን 
ስሪ ታውዘንድ የተሰኘ ፊልም በ1976 ፣ 
ዊልምግተን ፣ ቴን ዩ ኤስ ኤ ቴን ታውዘንድ የተሰኘን ፊልም በ1977 
አሽስ ኤንድ ኢምበርስ በ1982፣ 
አፍተር ዊንተር ስተርሊን ብሮውን በ1985 ፣ 
ሳንኮፋ በ1993 
አድዋ አን አፍሪካን ቪክትሪ በ2000 የሰራ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ተሸላሚም ነው፡፡ የፓን አፍሪካን የፊልም አዘጋጆች ፌዴሬሽን እና የአፍሪካን የፊልም አዘጋጆች ኮሚቴ አባልም ነው ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ፡፡ 

ከሰራቸው ፊልሞች መካከል:- 
 • 1972 - Hour Glass Hour Glass 
• 1972 - Child of Resistance 
• 1976 - Bush Mama 
• 1976 - Mirt Sost Shi Amit (also known as Harvest: 3,000 Years) 
• 1978 - Wilmington 10 -- U.S.A. 10,000 
• 1982 - Ashes and Embers 
• 1985 - After Winter: Sterling Brown 
• 1993 - Sankofa 
• 1994 - Imperfect Journey 
• 1999 - Adwa - An African Victory 
• 2009 - Teza Over the course of his career, Gerima has received numerous awards and distinctions in film festivals:- 
• 1976 - Grand prize / Silver Leopard for Harvest: 3,000 Years- Locarno 
• 1982 - Grand Prix Award for Ashes and Embers-Lisbon International Film Festival 
• 1983 - FIPRESCI Film Critics Award for Ashes and Embers-Berlin International Film Festival 
• Outstanding Production Ashes and Embers - London Film Festival 
• 1984 - Tribute Festival De la Rochelle, France 
• 1987 - Long Metrage De Fiction-Prix de la Ville de Alger for Ashes and Embers 
• 1993 - Best Cinematography Award for Sankofa, FESPACO, Burkina Faso 
• 2003 - Lifetime Achievement Award, 4th Annual Independence Film Festival, Washington D.C. 
• 2006 - Festival De Cannes Selection Official Cannes Classic -Harvest: 3,000 Years 
• 2008 - Venice Film Festival Special Jury Prize and Best Screen Play Award - Teza 
• 2009 - Jury Award at the 18th International Film Festival Innsbruck/Austria - Teza 
• 2009 - Golden Stallion of Yennenga at the FESPACO African Film Festival - Teza http://www.rfi.fr/ actuen/articles/111/article_3102.asp 
• 2009 - Dioraphte Award Hubert Bals film in highest audience regard at the Rotterdam Film Festival 
• 2009 - Golden Tanit/Best Film Award for its "modesty and genius," Best Music (Jorga Mesfin Vijay Ayers), Best Cinematography (Mario Massini), Best Screenplay (Haile Gerima), Best Supporting Actor Abeye Tedla at the Carthage/Tunisia Film Festival for Teza 
• 2009 - Golden Unicorn and Best Feature Film at the Amiens/France International Film Festival France for Teza 
• 2009 -The Human Value's Award at the Thessaloniki Film Festival in Greece for Teza 
• 2009 - Official Selection at the Toronto Film Festival for Teza 
 ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ በሚሰራቸው የፊልም ጥበቦች ሃገሩን በማሰተዋወቅ ባለውለታ እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክሩለታል፡፡ ወደፊት በሚያበረክታቸው የፊልም ስራዎቹ ውስጥ ለሃገሩ ልዩ ቦታ እንደሚሰጥ ተናግሯል፡፡
ከጎንደር ተራሮች እስከ ሺካጎ አሜሪካ ------- 
እ.አ.አ በ1976 በምርጥ Feature Film ዘርፍ የሚቼክስ አዋርድን ወስደዋል፣ በፓን አፍሪካን የፊልም እና የቴሌቪዥን ፌስቲቫል ላይ ደግሞ ምርጥ ሲኒማቶገራፈርም እርሳቸው ነበሩ፣ እ.አ.አ በ1993 በከንቲባው አርቲስት አዋርድ የላቀ አርቲስቲክ ዲሲፒለን ተሸላሚው በዋሽንግተን ዲሲ አሁንም የእኛው ሰው ነበሩ፡፡ የፓን አፍሪካን የፊልም ባለሙያዎች አባልና ኮሚቴም ናቸው፡፡ 
 እ.አ.አ በ1975 Hour Glass, Child of Resistance, Bushmama፣ እ.አ.አ በ1976 Harvest: 3000 Years፣ እ.አ.አ በ1977 Wilmington 10-USA 10,000፣ እ.አ.አ በ1982 Ashes and Embers፣ እ.አ.አ በ1985 After Winter, Sterling Brown፣ እ.አ.አ በ1993 Sankofa፣ እ.አ.አ በ2000 Adwa: An African Victory፣ ጤዛ.. የመሳሰሉትን ፊልሞች ለእይታ አብቅተዋል፡፡ 
 እ.አ.አ ከ1976 ጀምሮ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ፐሮፌሰር ሲሆኑ ማይፊደህ ፊልም የተሰኘው የፊልም አከፋፋይ ድርጅት እና ሳንኮፋ ቪዲዮና መጽሐፍ መደብር እንዲሁም ኔጎድጋድ ፊልም ፕሮዳክሽንም ባለቤት ናቸው፡፡ ታሪክ ዘመኑን እ.አ.አ መጋቢት 4 1946 ነበር ብሎ መዝግቦታል፡፡ ቦታውም ጎንደር፡፡ 
ለፀሀፊውና ድራም ተጫዋቹ አባቱ እና ለመምህሯ እናቱ 4ኛ ልጅ ሆኖ ሲወለድ ወደፊት አፍቃሬ አፍሪካ እና ስመ ጥር የፊል ባለሙያ ብሎም ፐሮፌሰር ይሆናል ብሎ የጠረጠረ ስለመኖሩ እንጃ፡፡ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ! በገጠራማ አካባቢዎች በመዞር የድራም ብቃታቸውን ያሳዩ የነበሩት አባቱ በህይወቱ የመጀመሪያው ተፅዕኖ አሳራፊ እንደነበሩ ይናገራል፡፡ ታዲያ ልጅ ሳለ የቅኝ ግዛት ስርዓት በፊልም ላይ ያለው እምብዛም በንቃት ስለማይታወቀው ተፅእኖው ይወያይ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ በፊልም ላይ የተመለከቷቸውን ነገሮች በማስመሰል ለመጫወት ይሞክሩ ነበር፡፡ በገጠራማ አካባቢዎች በመዞር የድራም ብቃታቸውን ያሳዩ የነበሩት አባቱ በህይወቱ የመጀመሪያው ተፅዕኖ አሳራፊ እንደነበሩ ይናገራል፡፡ ታዲያ ልጅ ሳለ የቅኝ ግዛት ስርዓት በፊልም ላይ ያለው እምብዛም በንቃት ስለማይታወቀው ተፅእኖው ይወያይ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ በፊልም ላይ የተመለከቷቸውን ነገሮች በማስመሰል ለመጫወት ይሞክሩ ነበር፡፡ 
ወደ ጎንደር ተራሮች በመሄድ የካውቦይ እና የህንዶችን ገፀ ባህርይ ይጫወታሉ፡፡ ካውቦዮች እንዴት አድርገው ህንዶችን ድል እንዳደረጓቸው የሚያሳዩ ገፀባህርይዎችን መልሰው መላልሰው ሲጫወቱ ይውላሉ፡፡ በሚገርም ሁኔታ ግን እነዚህን ገፀ ባህርይዎች ሲጫወቱ የህንዶች ደጋፊ ናቸው መባል አይፈልጉም አልያም ካውቦዮች እንዲያሸንፉ አንዳች ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ ይህን ጉዳይ ፕፌሰሩ ሲያስረዱ “ሌላው ቀርቶ በታርዛን ፊልም ላይ እንኳን እንቅስቃሴዎችን እምንመለከታቸው ከአክተሩ የእይታ ቦታ ሆነን ታሪኩ ከየትኛው የእይታ ነጥብ ተነስቶ የት ይደርሳል የሚለውን ነበር እምንከታተለው፣ በቃ ሙሉለሙሉ ትኩረታችንን የሚይዘው የታሪኩ አወቃቀር ነበር፡፡ ልክ አፍሪካዊዎች አድብተው ሊይዙት ሲሞክሩ ታርዛን ማን እንደመጣበት አይቶ እንዲጠነቀቅ እንጮህለት ነበር፡፡” ይላሉ፡፡ ምናልባት የፊልም ሙያ የፕሮፌሰሩን ቀልብ የገዛቸው በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፡፡ 
 ወደ አሜሪካ መሄድ -------- እ.አ.አ በ1966 ወደ አሜሪካ በመሄድ ሺካጎ Goodman School of Drama ውስጥ በመግባት የትወና ትምህርት ይከታተል ገባ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በሎስ አንጀለስ ታይምስ ጋዜጣ ላይ የሚከተለውን አስፍሯል “እያደግሁኝ ስመጣ በቴኣትር መሰራት ፈልጌ ነበር ነገር ግን የሆሊውድን ፊልሞች እየተመለከትሉ ማደጌ ወደፊልሙ እንዳዘነብል አድርጎኛል፡፡ በርግጥ በጊዜው ፊልም መስራት በአገሪቱ መንግስት የሚበረታታና የሚደገፍ ነገር አልነበረም፡፡” ኋላ እ.አ.አ በ1970 ወደ ካሊፎርንያ ተጓዘ፡፡ በዚያም ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በFine Arts ዘርፍ የባችለርና ኋላም የማስተርስ ዲግሪውን በእጁ ማስገባት ቻለ፡፡ 
/አንድ ለመንገድ/ -------- በነገራችን ላይ ህይወት በአሜሪካ ለፕሮፌሰሩ ያን ያክልም አልጋ በአልጋ አልነበረችም፡፡ በተለይ የልጅነት ህልማቸውን ለማሳካት የተጓዙበት ርቀት የዓላማ ፅናታቸውን በሚገባ የሚያመላክት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ሆሊውድ ፊት ነሳው፣ ፊልሙን ለመቅረፅ ፈንድ የሚያደርገውም እስከማጣት ደረሰ፡፡ በዚያም በዚህም ብሎ ፊልሙን ቀረፆ ሲጨርስ ደግሞ የሚያከፋፍልለት ጠፋ፤ ይሄኔ እጅ መስጠት በዚያ የለችምና የሚልም አከፋፋይ ድርጅት አቋቋመ፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቪዲዮ አከራዮች ያንተን ፊልም በመደብራችን ማስቀመጥ አንፈልግም ሲሉት የቪዲዮ መደብር ከፈተ፡፡ ሁሉን በታላቅ ፅናትና ትግል አልፎ ፊልሞቹን ቴኣትር ቤት ለማገባት ሄደ፣ በራቸውን ዘጉበት፡፡ እና ምን ተሻለ? ለምን በየአገራቱ የሚገኙ ቴኣትር ቤቶችን ተከራይቼ ፊልሜን አላሳይም አለ፡፡ አደረገው፡፡ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ! የእኛ ሰው! *********************************************************************
Source:-- Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን) facebook page 
https://sewasew.com


ፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ ከሸገር ሬድዮ ለዛ ፕሮግራም አዘጋጅ ብርሃኑ ድጋፌ ጋር ታህሳስ 18 ቀን 2001 ዓ. ም.
Professor Haile Gerima With Berhanu Digaffe on ShegerFm Leza Program


"አያቱ ኢንተርስት ያላደረገችው ፊልም ሰሪ ለኔ ፊልም ሰሪ አይደለም" ፕሮፌሰር ሐይሌ ገሪማ ..ጥበብና_ ትውልድ_ ክፍል ፩



'የኢትዮጵያ ትያትር የመቶ ዓመት እድሜ ነው ' የሚባለው ስኽተት ነው "ትያትር ራሱ የተጀመረው አፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው"_ፕሮፌስር ሐይሌ ገሪማ_ክፍል ፪



"አንድ ከነገሠ ሰው ጋር ጊዜውን የሚያጠፋ አርቲስት አርቲስት ሳይሆን ፖለቲሻን ነው" ጥበብ-እና- ትውልድ _ክፍል ፫


ሰይፍ ፋንታሁን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ከፕሮፌስር ሐይሌ ገሪማ_

Seifu Fantahun show interview with Haile Gerima_2014

ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ይባላሉ በዋሽንግተን ዲሲ ሀዋርድ ዩኒቨርስቲ የፊልም ጥበብ ፕሮፌሰር ናቸው።
***********************************************************

☀️በውጪው አለም በተለይም በጥቁር አሜሪካውያን ዘንድ የሚታወቁት ብዙ ሽልማትንም የተቀበሉት ሳንኮፋ (Sancofa) በሚባል ፊልማቸው ነው።

☀️ Sankofa በጋናውያን 'Akan Twi' እና 'Fante' ቋንቋ የራስ የሆነን ነገር ግን ጠፍቶ የነበረን ነገር መልሶ ማግኘት የሚል አንድምታ አለው።
ይህንን ሀሳብም ለመግለፅ ወደፊት የምትሄድ ነገር ግን ፊቷን ወደኋላ ያዞረች በአፏ እንቁላል የያዘች ወፍ ምስል ይጠቀማሉ።

☀️በተጨማሪም ፕሮፌሰር ሐይሌ ገሪማ ይህንን ፊልም በሚሰሩበት ጊዜ የጋናዊዋ ባለቤታቸው አስተዋፆ እንዳለበት ተናግረዋል።

☀️እሳቸውም ጥቁር አሜሪካውያን ሆይ የመጣችሁበትን ዘወር ብላችሁ ተመልከቱ የጠፋባችሁን ፈልጉ ሲሉ በፊልሙ አመልክተዋል።
☀️አገር ወዳድነታቸው ዳር የለውም ከአማርኛ ፊልሞቻቸው ጤዛ የሚለው ያንን ትውልድ ከዚህኛው ያስተያየንበት የትላንቱን ኩነት የገመገምንበት የፊልም ጥበብን የተረዳንበት ነው።

☀️ፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ ከ'ጤዛ' በተጨማሪ
* የ 3000 ዘመን ምርት
* Sankofa
* Adwa
* Bush Mama
* Imperfect Journey (Documentary
* Ashes and Embers
* Child of Resistance
እና ሌሎችም የፊልምና የዶክመንተሪ ስራዎች አሏቸው።

😉እነዚህን ስራዎች ሲሰሩ የትኛውንም የነጭ የገንዘብ እርዳታ ላለመጠየቅ በሚል የተቋቋመ Sankofa የሚባል የመፅሐፍ መሸጫ መደብር አቋቁመዋል። እዛችው ክፍል ውስጥ ከመፅሐፍ መሸጥ በተጨማሪ በጥቁሮች እና በአፍሪካውያን ታሪክ፣ ባህል፣ ስልጣኔ፣ ነፃነት እና የአኗኗር ዘይቤ ላይ የሚያተኩሩ ጥናታዊ ፅሑፎች አና ውይይቶች በተለያዩ ጊዜዎች ያካሔዳሉ።

EBS tv Riyot Tewodros Tsegaye interview with professor Haile Gerima part_1



EBS tv Riyot Tewodros Tsegaye interview with professor Haile Gerima part_2


EBS tv Riyot Tewodros Tsegaye interview with professor Haile Gerima part_3


EBS tv Riyot Tewodros Tsegaye interview with professor Haile Gerima part_4




EthioTube Presents Legendary Ethiopian Filmmaker Haile Gerima __June 2015

https://www.youtube.com/watch?v=Mh591qME_bM

 

https://www.youtube.com/watch?v=UoqoecV4jLo