ከደራሲያን ዓምባ

Thursday, August 24, 2023

የኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን ተሳትፎ

 


የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እ.ኤ.አ. በ1983 በፊንላንድ ሔልሲንኪ ከተማ የተጀመረው በቀድሞ አጠራሩ የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር አማካይነት ነው።

ከመጀመሪያው ውድድር በኋላ ሻምፒዮናው እስከ 1991 ድረስ፣ በየአራት ዓመቱ ይደረግ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ውድድሩ በሁለት ዓመት እንዲከናወን ተወሰነ።

በመጀመርያ ሻምፒዮና ከ153 አገሮች የተውጣጡ 1,333 አትሌቶች ተሳትፎ ማድረግ ችለዋል።

እ.ኤ.አ. በ1987 የሴቶች 10,000 ሜትር እና 10 ኪሎ ሜትር ዕርምጃ ተጨምሯል። በ1995 የሴቶች 3000 ሜትር በ5000 ሜትር ሲተካ። በ2005 የሴቶች 3000 ሜትር መሰናከል ተጨምሯል። ዓምና በአሜሪካ ኦሪገን በተከናወነው (2022) የዓለም ሻምፒዮና የ50 ኪሎ ሜትር የወንዶችና የሴቶች፣ የ35 ኪሎ ሜትር ዕርምጃ ተካቷል።

 


ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና ተሳትፎ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን በመጀመርያው ሻምፒዮና 10 አትሌቶች በአምስት የውድድር ዓይነቶች ተሳትፏል። ኢትዮጵያ በወዳጆ ቡልቲ፣ ሥዩም ንጋቱ፣ መሐመድ ከድር፣ በቀለ ደበሌ፣ ግርማ ብርሃኑ፣ እሼቱ ቱራ፣ ግርማ ወልደሃና፣ ከበደ ባልቻና ደረጀ ነዲ ነበር የተወከለችው። አትሌቶቹ በ3000 ሜትር መሰናከል፣ 5000 ሜትር፣ 10 ሺሕ ሜትር፣ ማራቶንና 20 ኪሎ ሜትር የዕርምጃ ውድድሮች ተሳትፈዋል። ከእነዚህ አትሌቶች መካከል ከበደ ባልቻ በወንዶች ማራቶን ለኢትዮጵያ የመጀመርያውን የብር ሜዳልያ አስገኝቷል፡፡

በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ 15ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ኢትዮጵያ የዓለም ሻምፒዮና ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በ18ቱም ሻምፒዮናዎች መካፈል ችላለች። እ.ኤ.አ. በ1993 በስቱትጋርት በተደረገው ውድድር ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በ10 ሺሕና በ5 ሺሕ ሜትር ወርቅና ብር አግኝቷል፡፡

የኢትዮጵያ ስኬታማ ውጤት

እ.ኤ.አ. በ2009 በጀርመን በርሊን በተከናወነው የዓለም ሻምፒዮና በተለያዩ ርቀቶች የሚሳተፉ 38 አትሌቶችን ይዛ ቀርባለች። ቡድኑ በመካከለኛ ርቀት ጭምር የሚሳተፉ አትሌቶችን ያቀፈ ነበር። በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በተለያዩ ርቀቶች የሚወዳደሩ ተጨማሪ አትሌቶች ይዛ እንድትገባ የተፈቀደላት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በእነዚህ ውድድሮች ተጠባባቂ አትሌቶችን መርጦ ይዞ ቀርቦ ነበር።

በሻምፒዮናው በወንዶች 5000 ሜትርና 10 ሺሕ ሜትር ቀነኒሳ በቀለ ሁለት ወርቅ በማምጣት አዲስ ታሪክ ያጻፈበት ክስተት ነበር። ቀነኒሳ በ10 ሺሕ ሜትር 26:46.31 በማጠናቀቅ የቦታውን ክብረ ወሰን ጭምር ማሻሻል ችሏል። በ1500 ሜትር ወንዶች ደረሰ መኮንን የብር ሜዳልያን ሲያሳካ፣ ፀጋዬ ከበደ በማራቶን ሁለተኛውን የብር ሜዳልያ ያስገኝ አትሌት ሆኗል።

በሴቶች መሠረት ደፋር በ5000 ሜትር የነሐስ ሜዳልያ፣ መሰለች መልካሙ በ10 ሺሕ ሜትር ብር፣ ውዴ አያሌው ነሐስ፣ እንዲሁም አሠለፈች መርጋ በማራቶን የነሐስ ሜዳልያ አስገኝተዋል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ስምንት ሜዳልያ በመሰብሰብ ከዓለም ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ የቻለችበት ሻምፒዮና ነበር።

ከሁለት ዓመት በኋላ በ2011 በደቡብ ኮሪያ ዴጉ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተካፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 34 አትሌቶችን ይዞ መሳተፍ ችሎ ነበር። ሆኖም በ10 ሺሕ ሜትር ወንዶች በኢብራሂም ጄላን ወርቅ ሲገኝ፣ ደጀን ገብረ መስቀል በ5000 ሜትር፣ ኢማና መርጋ 10 ሺሕ፣ ፈይሳ ሌሊሳ በማራቶን እንዲሁም በ5000 ሜትር ሴቶች በመሠረት ደፋር አራት የነሐስ ሜዳልያ በአጠቃላይ አምስት ሜዳልያዎች ማጠናቀቅ ትችሏል። ይህም ውጤት ኢትዮጵያ በበርሊን ዓለም ሻምፒዮን ከነበረው ውጤት ዝቅተኛው ነበር።

በ2013 በሩሲያ በተሰናዳው የሞስኮ የዓለም ሻምፒዮን ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት ያመጣችበት ነበር። በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በመሠረት ደፋር በ5000 ሜትር ወርቅ፣ በጥሩነሽ ዲባባ 10 ሺሕ ሜትር ወርቅ፣ እንዲሁም በ800 ወንዶች በመሐመድ አማን ወርቅ ማምጣት ተችሎ ነበር። በተለይ ባልተለመደ መልኩ በ800 ሜትር ርቀት በመሐመድ ወርቅ መምጣቱ ሻምፒዮናው ለኢትዮጵያውያን ልዩ አድርጎታል። በሌሎች ርቀቶች ሦስት የብርና ሦስት የነሐስ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም ስድስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ትችሏል።

ሌላው ኢትዮጵያ የደመቀችበት የ2015 ዓለም ሻምፒዮና ይጠቀሳል። የአትሌቲክስ ቡድኑ በሻምፒዮናዎች በረዥም ርቀቶች ብቻ ውጤት ከማምጣት በዘለለ፣ በመካከለኛ ርቀትም የተሻለ ውጤት ማምጣት የቻለበት አጋጣሚም እየተፈጠረ የሄደበት ሁኔታ ነበር። በዚህም መሠረት በቤጂንግ ዓለም ሻምፒዮን ገንዘቤ ዲባባ በ1500 ሜትር ወርቅ ማምጣት ችላ ነበር። ይህም ኢትዮጵያ በመካከለኛ ርቀት በዓለም ሻምፒዮና ተስፋ የሰነቀችበት ነበር።

ኢትዮጵያ በቤጂንጉ የዓለም ሻምፒዮን አልማዝ አያና በ5000 ሜትር ወርቅ፣ ማሬ ዲባባ በማራቶን ወርቅ ሲያሳኩ፣ በሦስት የብርና በሁለት የነሐስ ሜዳልያዎችን  በመሰብሰብ ከዓለም አምስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በ2017 የለንደን ዓለም ሻምፒዮን ሁለት ወርቅና ሦስት የብር ሜዳልያ፣ በ2019 በኳታር ሁለት ወርቅ፣ አምስት ብርና አንድ የነሐስ ሜዳልያ ማምጣት ተችሏል። በኳታር ዓለም ሻምፒዮን ለሜቻ ግርማ በ3000 መሰናክል የብር ሜዳልያ ማሳካት፣ ሌላው ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ተስፋ የተሰነቀበት ድል ያደርገዋል።

ዓለም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ዝግ ሆና መቆየቷን ተከትሎ በተለይ አትሌቶች አስቸጋሪ ጊዜ ያሳለፉበት ወቅት ነበር። ይህም ለሁለት ዓመታት ማንኛውም ውድድሮች ሳይከናወኑ መቆየታቸው ይታወሳል። በአንፃሩ ወረርሽኙ አገግሞ የ2022 የኦሪገን ዓለም ሻምፒዮን ለአትሌቶች ተስፋ ያጫረ ሆነ። በልምምድ የዛለው የአብዛኛው አትሌት ጉልበት መፈተሻ መድረክ አገኘ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንም ስኬታማውን የዓለም ሻምፒዮን ያስባለውን ውጤት አስመዘገበ። ኢትዮጵያ 21 ወንድና 19 ሴት አትሌቶችን በተለያዩ ርቀቶች ማሳተፍ ቻለች። ይህም ቁጥር ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና ካሳተፈቻቸው አትሌቶች ቁጥር ላቅ ያለ ነበር። የቁጥር መጨመር ምክንያትም በየሻምፒዮናው የሚመዘገቡ ውጤቶች አማካይነት ነው። በኦሪገን ዓለም ሻምፒዮን በማራቶን በሁለቱም ፆታ (በታምራት ቶላና ጎተይቶም ገብረ ሥላሴ)  እንዲሁም በ10 ሺሕ ሜትር ሴት ለተሰንበት ግደይና በ5000 ሜትር ሴቶች ጉዳፍ ፀጋይ አራት ወርቅ ማሳካት ተችሏል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማራቶን በሁለቱም ፆታ የቦታውን ክብረ ወሰን ማሻሻል የቻሉበት ሲሆን፣ በ10 ሺሕ ሜትር ለተሰንበት የዓመቱን ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ መቻላቸው ልዩ ያደርገዋል። ኢትዮጵያ በኦሪገኑ ዓለም ሻምፒዮን ከአራቱ ወርቅ በተጨማሪ አራት የብር፣ ሁለት የነሐስ ሜዳልያ በድምሩ 10 ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ የቻለችበት ስኬታማው የዓለም ሻምፒዮን ያደርገዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት በዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት ውስጥ ሆና የተመዘገበ ውጤት መሆኑ የተለየ ቦታ እንዲሰጠው አስችሎታል።

ከኦሊምፒክ ጨዋታና ከእግር ኳሱ የዓለም ዋንጭ ቀጥሎ፣ ምርጡ ውድድር እንደሆነ የሚገለጽለት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን፣ ዘንድሮ በቡዳፔስት ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዓምና በአራት ወርቅ የተመለሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድኑ ዘንድሮስ ምን ሊያሳካ ይችላል? የሚለው በአብዛኛው ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።

https://www.proworksmedia.com/121159/ ዳዊት ቶሎሳ


No comments:

Post a Comment