ከደራሲያን ዓምባ

Tuesday, February 20, 2024

የካቲት12 ቀን 1929 የሰማዕታት ቀን

 

ወራሪዋ ጣልያን በአዲስ አበባ የፈጸመችው ጭፍጨፋ 

አርብ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም.

፨፨፨(የየካቲት 12) የሰማዕታት ሐውልት፨፨፨
መታሰቢያነቱ - ፋሽስት ጣሊያን በወገኖቻችን ላይ ላደረሰው መከራና በግፍ 
በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ለተጨፈጨፉ ኢትዮጵያውያን
የሐውልቱ ቀራጮች - አጉበቲን ሲች አንቶንና ከርሰኔች ፋራን 
የተባሉ የዩጎዝላቪያ ዜጎች ናቸው፡፡
ሐውልቱ የቆመበት ቦታ ዲያሜትር - 26 ሜትር
የሐውልቱ ቁመት - 28 ሜትር
መገኛ ሥፍራ - 6 ኪሎ

(ምንጭ ፡- ኅብረ ኢትዮጵያ ፣ ቴዎድሮስ በየነ)


 

“--አየህ! የዚያን ዕለት ብዙ ጣሊያኖች ብዙ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ወደ ማታ ገደማ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ስንገናኝ፣ ጓደኛዬ ቦምብ ስጥል የዋልሁበት እጄ ዝሏል ብሎ ነገረኝ። አንዱ ኢጣሊያዊ ሲያጫውተኝ፣ ባንዲት ትንሽ ጣሳ በያዝኳት ቤንዚን አስር ቤቶች አቃጠልኩበት አለኝ፤ በዋናው ጦርነት ጊዜ ጥይት ተኩሰው የማያውቁት ጣሊያኖች ሁሉ በዚያን ቀን ሲተኩሱ ዋሉ--”

           ይህ አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ኢጣሊያዊ፣ ለጓደኛው ለሲኞር ዲሰማን የነገረውና  የታሪክ ጸሐፊው አንጄሎ ዲል ቦኮ የመዘገበው ሲሆን ደራሲ ጳውሎስ ኞኞም  “ኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት; በተባለው መጽሐፉ ታሪኩን ለእኛ አድርሶታል። የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላይ፣ በጣሊያን ወታደሮች የተፈጸመው ጭፍጨፋ ታሪክ ቀርቧል፤ በመጽሐፉ፡፡ በዚህ ወቅት በመዲናዋ  ለሦስት ተከታታይ ቀናት በጣልያን ጨካኝ ወታደሮች በተካሄደው ጭፍጨፋ፣ 30 ሺህ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል፡፡ አንዳንዶች ይህ ቁጥር የሚታመን ነውን? የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ጥያቄውን ለመመለስ ከላይ የተጠቀሰውን ምስክርነት ይዘን፣ በወቅቱ በአዲስ አበባ የከተመውን የጣሊያን የጦር ሰራዊት ክምችት መመልከት ተገቢ ይሆናል።
ጳውሎስ ኞኞ፣  በወቅቱ የነበረውን የጣሊያን የወታደር ኃይል በመጽሐፉ ሲገልጽ፤ “35ሺ የጣሊያን ሜትሮ ፖሊታንት (የከተማው ወታደሮች)፣ 40ሺ ባለ ጥቁር ሸሚዝ ሚሊሺያ፣ 3ሺ የሊቢያ ተወላጅ ወታደሮች፣ 5ሺ የኤርትራ ወታደሮች ነበሩ፡፡; ብሏል፡፡ በተጨማሪም #የኤርትራ ተወላጅ ወታደሮች፤ “እኛ ወታደሮች ነን፤ መሳሪያ በሌለውና በሴት ላይ አንተኩስም” በማለታቸው ብዙዎቹ በሰፈራቸው ውስጥ ተገደሉ” ሲልም አክሎ ጽፏል፡፡ ከዚህ አንጻር 78ሺ የሚሆነውን የጣሊያን ሠራዊት፣ በጭፍጨፋው ላይ ከማሰማራት የሚያግደው ነገር አልነበረም፡፡
የኒፒልስ ልዕልት መውለዷን ምክንያት በማድረግ ጀኔራል ግራዚያኒ፣ ለድሆች ምፅዋት ለመስጠት በገነት ልዑል ቤተ መንግሥት፣ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ፣ ድሆች  እንዲሰበሰቡ ጥሪ አድርጎ ነበር።   እስከ እኩለ ቀን ባለው ጊዜም ሶስት ሺህ የሚሆኑ ድሆች ተሰበሰቡ፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ ሰላሳ የሚሆኑ የጣሊያን ከፍተኛ ሹማምንቶች ተገኝተዋል፡፡ ይህን አጋጣሚ ራሳቸውን እያዘጋጁ ይጠብቁ የነበሩት አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም፣ ከነሱ ጀርባ የተሰለፉት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴን ጨምሮ፣ ብዙዎች ጄኔራል ግራዚያኒን በመግደል፣ የጣሊያንን የወራሪነት ቅስም ለመስበር ቆርጠው ተነሱ፡፡ ጄኔራል  ግራዚያኒ፣ ለድሆችና በቦታው ለተገኙ ሰዎች ንግግር እያደረገ እያለ፣ እነ አብርሃም አከታትለው የእጅ ቦንብ ወረወሩ፡፡ ግራዚያኒ  ጀርባው ላይ ተመታ፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጣሊያናዊው ጎይዶ ክርስቴና ሌሎች ሰላሳ ሰዎችም ቆሰሉ፡፡ ከሚወረወረው ቦምብ ለማምለጥ መሬት ላይ ተኝተው የነበሩት ከርቤጌሮች ከተኙበት ተነስተው ተኩስ ከፈቱ፡፡ ያገኙትን አበሻ ሁሉ እንዲገድሉ ከንቲባ ጐይዶ ክርስቴ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ የጣሊያን ሹፌሮች ሳይቀሩ በአዲስ አበባ ከተማ እየተዟዟሩ ሕዝቡን ፈጁት፡፡ የቤተ መንግሥቱ ዙሪያ መንገዶች በሬሳ ተሞሉ። የመዲናዋ ቤቶች ከነዋሪዎቹ ጋር በእሳት ነደዱ፡፡ ነፍሳቸውን ለማትረፍ የሚሞክሩ ሰዎች እየተያዙ፣ ቤት እየተዘጋባቸው እንዲቃጠሉ ተደረገ፡፡ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው በዚህ ጭፍጨፋ፣ ሰላሳ ሺህ ሰዎች እንደተገደሉ ነው የተመዘገበው፡፡  
እኔ በዚህ ቁጥር አልስማማም፡፡ መግቢያው ላይ ያሰፈርኩትን ምስክርነት ይዞ ነገሩን የሚገመግም ሰውም ይስማማል ብዬ አልጠብቅም፡፡ ከጣሊያን ጦር ውስጥ ከ15ሺ እስከ 20ሺ  የሚሆነው ለሰፈር ጥበቃ እንዲቀር ቢደረግና  ቀሪው ሃምሳ ሺህ ወታደር እንኳን አንድ አንድ ሰው ቢገድል፣ ያለ ጥርጥር  የተጨፈጨፉት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ሃምሳ ሺህ ይደርሳል፡፡ 


አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአንድ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩ የዓይን ምስክርን አነጋግሮ፣ የሟቾቹ  ቁጥር ከሀምሳ ሺህ እስከ ሰማኒያ ሺህ ሊደርሱ እንደሚችሉ በመጠቆም መዘገቡን አስታውሳለሁ። እኒህ ሰው እንደተባለው ጭፍጨፋው በሦስት ቀናት ውስጥ አለመቆሙንና ለወር ያህል መዝለቁንም ተናግረዋል፡፡  ከዚህ አንጻር የየካቲት ሰማዕታት ቁጥር 30 ሺህ ነው ማለት ትክክል አይመስለኝም፡፡ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት እልቂትም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ የየካቲት 12 አንድ ገጽታ ነውና፡፡
ከሃምሳ ሺህ ሰዎች በላይ የተጨፈጨፉበት፣ ከአስር ሺህ በላይ ደግሞ ደናኔ ተወስደው በእስርና በበሽታ እንዲያለቁ የተደረገበት የየካቲት 12 ቀን መስዋዕትነት በከንቱ አልቀረም፡፡ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ለኢጣሊያ መንግሥት አልገዛም በማለታቸው፣ በአደባባይ በጥይት ተደብድበው በተገደሉት በአቡነ ጴጥሮስ ሞት ያኮረፈውን የአዲስ አበባን ነዋሪ፣ በየካቲት 12 ጭፍጨፋ፣ ጨርሶ ልቡ እንዲቆርጥና እንዲነሳሳ አድርጎታል። እጅግ የሚበዛውም ፊቱን ወደ አርበኝነት አዞረ፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሳይቀር ለነፃነት በሚደረገው ትግል፣ የውስጥ አርበኛው እየተናበበ ሔደ፡፡
እንደ ሚያዚያ 27 የድል ቀን ሁሉ፣ በየዓመቱ ብሔራዊ በዓል ሆኖ ሲከበር የነበረው የየካቲት 12 ሰማዕታት ቀን፣ እየታሰበ መዋል ከጀመረ አርባ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት አንድም የመንግሥት ባለሥልጣንም ሆነ መንግሥት ወደ ቀድሞ ክብሩ ሊመልሰው አልቻለም፡፡  
“ኢትዮጵያ የቆመችው በልጆቿ መስዋዕትነት ነው; እያልን እንዴት  ዓመታዊ  የሰማዕታት ቀን አይኖረንም?
ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ድረስ በዱር በገደሉ ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ነፃነታችን ተከብሮ እንዲቆይ ያደረጉ የአምስት ዓመቱ አርበኞች፣ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ሰማዕት ናቸው፡፡
ሁለት ጊዜ የተቃጣውን የሞቃዲሾ ወረራ የመከቱ፣ የተጣሰውን ድንበር ያስከበሩና የሀገር ታሪክ እንዳይደፈር የተሰዉ ወገኖቻችን ሰማዕቶቻችን ናቸው፡፡
የጦርነቱ ምክንያት በግልጽ ባይታወቅም፣ ከኤርትራ ጋር በተቀሰቀሰው ጦርነት፣ ከአካል እስከ ሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ወገኖቻችን ለሀገራችን ሰማዕት ናቸው፡፡
 ሰማዕታት ትናንትም ዛሬም አሉን፤ነገም መስዋዕትነት የሚከፍሉና ሰማዕታት የሚሆኑ ወገኖቻችንን  የምንዘክርበት የሰማዕታት ቀን የሚኖረን መቼ ነው? ሺህ ጊዜ የሚነሳ ጥያቄ! 

                              ስድስት ኪሎ የሚገኘው የካቲት 12 የሰማዕታት ሃውልት ላይ

https://www.addisadmassnews.com/ 

Written by  አያሌው አስረስ Saturday, 20 February 2021

***********

የካቲት 12 እና የግራዚያኒ አዲስ አበባ

ህላዊ ሰውነት በሻህ (አርኪቴክት)
Helawi Sewnet Beshah (Architect) 
ጣሊያን ኢትዮጵያ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ወረራ አድርጎ ለአምስት አመት በተቆጣጠረበት ወቅት 1929 ዓ.ም. በየካቲት 12 እለተ አርብ ነበር። የአጼ ሀይለስላሴን ወደ እንግሊዝ መሰደድ ተከትሎ እና የሙሶሊኒን የቅኝ ግዛት ህልም እንዲያሳካ የኢትዮጵያ አስተዳዳሪ ሆኖ የተሾመው ግራዚያኒ፣ የኔፕልሱን ልዑል መወለድ አስመልክቶ ለችግርተኛ ቤተሰቦች ገንዘብ እሰጣለሁ ብሎ በገነተ ልዑል ቤተመንግስት (የዛሬው አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስድስት ኪሎ ግቢ) በርካታ እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች እንዲሰበሰቡ አዘዘ። ከተጋባዥ እንግዶቹም መካከል የጣልያን ሹማምንት የሜትሮፖሊታን ጳጳስ አቡነ ኪርል እና ሌሎች የኢትዮጵያ መኳንንቶች ተገኝተው ነበር።

ብራማ በነበረችው በዛች የወረሃ የካቲት አርብ የተገኙትም ኢትዮጵያውያን ከጠዋት ጀምረው አንድ በአንድ ቤተመንግስቱ ግቢ መሰብሰብ ጀመሩ። እስከረፋዱም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሶስት ሺህ ያህል ነዋሪዎች በተገኙበት የግራዚያኒ መረሃ ግብር ተጀመረ። የዕለቱ አጀማመር ሲታይ ሊመጣ ያለውን የሀዘን ድባብ የገመተ ሰው ይኖራል ብሎ ለማሰብ ያዳግታል። ጥቂት ቆይቶ እኩለ ቀን ገደማ ሊሆን አካባቢ በዋናው በር በኩል ቦንብ ፈነዳ፣ ሁለተኛም ፈነዳ። ገነተ ልዑል ቤተመንግስት ከየአቅጣጫው ጩኸት አስተጋባ። ሶስተኛ ቦብም ግራዚያኒ እና መኳንንቱ ከተቀመጡበት ጠረጴዛ አጠገብ ሲወረወር ግራዚያኒ ጠረጴዛ ስር ወደቀ። የተወሰኑ የጣልያኖቹን ሹማምንት መታ።

ቦምቡን የጣለው ከጣልያኖቹ ዘንድ በአስተርጉዋሚነት ይሰራ የነበረ አብርሃ ደቦጭ እና ጓደኛው ሞገስ አስገዶም የሚባሉ የኤርትራ ክፍለሀገር ተወላጅ ወጣቶች ነበሩ። በጥቅሉ ሰባት ቦምቦች ፈነዱ። ወዲያው ካርቴሲ ወደኢትዮጵያውያኑ መኩዋንንት ሽጉጡን አነጣጥሮ የመጀመሪያዋን አንድ ጥይት ተኮሰ። ካራ ቢኔሬዎችም (የጣሊያን የሲቪል ጠባቂዎች) ምሳሌውን ተከተሉ። በጥቂት ጊዜ ውስጥም ሶስት መቶ ሬሳዎች በዛ ግቢ ውስጥ ተከመሩ። ሀይለኛና ተገቢ ያልሆነ ጭፍጨፋ ነበር። ሽማግሌዎች፣ አይነስውራን፣ እግር የሌላቸው ለማኞች፣ ድሆች እናቶች እስከልጆቻቸው ነበሩበት። ሰላሳ ያህል ሰዎች ቆሰሉ። ለሶስት ሰአታት ያህል ያለቋረጥ በግቢው ውስጥ ተኩስ ተከፈተ። ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ባለጥቁር ሸሚዞች፣ የጣልያን ሾፌሮች የቅኝ ግዛቱ ወታደሮች በአዲስ አበባ ከተማ እየዞሩ ህዝቡን ይፈጁት ጀመር።

እዚህ ቀን ላይ እንዴት ተደረሰ የሚለውን ታሪካዊ ዳራ ወደኋላ መለስ ብለን እንመልከት። አውሮፓውያን በ1877 ዓ.ም. በጀርመን በርሊኑ ኮንፈረንስ ተገናኝተው አፍሪካን አንደቅርጫ ከተከፋፈሏት ከ11 ዓመታት በኋላ ጣልያን ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ስትመጣ አድዋ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ድል ትደረጋለች። አንድ ትውልድ አልፎ ከአርባ አመታት ቆይታ በኋላ በስልጣን ላይ የነበረው የጣልያኑ ፋሽስት ሙሶሎኒ የአድዋን ቁጭት ባለመርሳቱ ከበቀል ጋር ዘመናዊ የሆነ የአየርና የምድር ጦሩን ይዞ ኢትዮጵያ በድጋሚ መጣ። በዚህ ወቅት የጣሊያን ጦር ለኢትዮጵያ ሰራዊት ብርቱ ስለሆነበት አጼ ሃይለስላሴ በሚያዝያ (May 2, 1936) ጠዋት ከአገር ይሰደዳሉ። የጣሊያኑ ሙሶሊኒም ኢትዮጵያን በስተመጨረሻ በእጁ እንዳስገባ በሮማ ለተሰበሰበው ህዝቡ በደስታ አዋጁን አሰማ።

የኢትዮጵያን ጦር ማይጨው ላይ መሸነፍ እና እንዲሁም የንጉሱን ከአገር መውጣት ተከትሎ የጣሊያኑ አስተዳደር አዲስ አበባ እስኪገባ ድረስ በመሀል በተፈጠረው ክፍተት መዲናዋ ክፉኛ በተደራጁ ሌቦች ተዘረፈች፣ ጣሊያኖቹ እንዳይጠቀሙ በሚል ብዙ ህንጻዎችም በግለሰቦች ተቃጠሉ፣ ፈረሱ። ሙሶሊኒ ከጣሊያን በሰጠው ቀጥተኛ ትእዛዝ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የቅጣት እርምጃ አስወሰደ። ጉዳት የደረሰባት አዲስ አበባም ለወራሪዎቹ መልካም አቀባበል ያደረገች ምቹ ከተማ አልሆነችላቸውም። የጣሊያኑ ኮማንደር ባዶግሊዮ ወዲያውኑ ለሮም በላከው ቴሌግራም ላይ ሙሶሊኒ ወደኢትዮጵያ በስድስት ወራት ውስጥ ሊልካቸው ያሉትን የጣሊያናዊ ቤተሰቦች ዕቅድ ትንሽ እንዲቆጥበው መልዕክቱን አደረሰ። አዲስ አበባም የአዲሱ የፋሺስት ግዛት መዲና የመሆኗ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አነጋጋሪ ሆነ።

የጣሊያንን መንግስት ከሚያማክሩት ባለሙያዎች ውስጥ አብዛኞቹ አዲስ አበባን መዲና አድርጎ ማስቀጠል ስህተት እንደሚሆን አስጠነቀቁ። በሸለቆዎች የተሰነጣጠቀው ተራራና ኮረብታማ የመልከአ ምድሯ አቀማመጥና ከፍታማነት አድካሚ እና ለጉልበት ስራ አዳጋች እንደሚሆንባቸው እንዲሁም ዘርዘር ያለው የከተማዋ አሰፋፈር ለትራንስፖርት ፈተና እንደሚሆን ቅሬታዎች ቀረቡ። የአፈሩ ባህሪ ተንሸራታችነት ለመሰረት ግንባታ የሚኖረው ተግዳሮት እንዲሁም የነበረው በርካታ የባህር ዛፍ ደን ለኢትዮጵያ ሽፍቶችና ታጋዮች ምሽግ እንደሚሆን ጣሊያኖቹ ሰጉ። ከሁሉም በላይ ግን በአዲስ አበባ የነበረው ብዝሃ ጥቁር አፍሪካዊና ኢትዮጵያዊ ህዝብን አፈናቅሎ ወደሌላ ቦታ ለማስፈርና የቅኝ ገዢዎቹን የመከፋፈል ፖሊሲ ለማራመድ ፈተና እንደሚሆንና እንደፋሺስቱ አመለካከት ከአገሬው ተወላጅ አሻራ የጸዳ አዲስ ከተማ መቆርቆር እንደሚያስፈልግ አመላከቱ። ለአዲስ መዲናነት ደሴ፣ ሞጆ፣ ነቀምት እና ሐረር እንደ አማራጭነት ቀረቡ። ነገር ግን በሙሶሊኒ እይታ ከአዲስ አበባ ውጪ የሆነ የዋና ከተማ ሀይሉን እና ክብሩን ለማሳየት በፍጹም አማራጭ እንደማይሆን ከለንደኑ ዴይሊ ቴሌግራፍ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ይፋ ቢያደርግም ብዙ የቅኝ ግዛት ሹማምንቶቹ ሀሳቡን ይቀይራል የሚል ተስፋ ነበራቸው።

በመጀመሪያዎቹ ወራት የፋሽስቱ አስተዳደር የህዝብ የመንገድ ዳር ምልክቶች በጣልያንኛ ተተርጉመው እንዲጻፉ ተደረገ። የዋና ጎዳናዎች ስሞችም በሙሶሊኒ መንግስት ውስጥ በነበሩ አንዳንድ አመራሮች ስም ተሰየሙ። በየቦታውም ሆነ በየቤቱ የሙሶሊኒ ምስል እና በአንዳንድ ቦታዎች ለህዝቡ ፕሮፖጋንዳ የሚያስተላልፉ የድምጽ ማጉያዎች ተሰቀሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ፋሺስቶቹ ከኢትዮጵያ ነጻነት ጋር የተያያዙ ምስሎች እና ሀውልቶችን ማስወገድ ላይ ተጠመዱ። ከነዚህም ውስጥ አራዳ ጊዮርጊስ አደባባይ ላይ የሚገኘው የምንሊክ ፈረስ ጋላቢ ሀውልት፣ ታላቁ ቤተመንግስት አጠገብ ያለው የባእታ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው የምኒሊክ መቃብር፣ ለገሀር ባቡር ጣቢያ ፊት ለፊት የቆመው የይሁዳ አንበሳ ሀውልት፣ በወቅቱ አዲስ አበባ ላይ የነበረ የአክሱም ሀውልት አምሳያ፣ የስላሴ ኮኮብ ሀውልት፣ እና በርካታ በወቅቱና ቀደምት የነበሩ መሪዎች ምስሎችን ያካትታል። ሙሶሊኒም በቴሌግራፍ በላከው መልዕክት “የምኒሊክ ሀውልትን መፈንዳት ይኖርበታል” ሲል አቅጣጫውን አስቀመጠ።

በወቅቱ የአገሪቱ ተጠባባቂ ገዢ ሆኖ ወደአዲስ አበባ የመጣውና በቅጽል ስሙ “የሊቢያ ጅብ” በመባል ይታወቅ የነበረው የቀድሞ ወታደሩ ግራዚያኒ ከሀውልቶቹ ጋር ተያይዞ የተሰጠውን ትዕዛዝ ለመፈጸም በማቅማማት ለጣልያኑ የቅኝ ግዛቶች ሚንስትር እንዲህ የሚል ቴሌግራፍ መልዕክት ላከ። “አዲስ አበባ እንደመጣሁ የምኒሊክ እና የይሁዳ አንበሳ ሐውልት አልተነሱም ነበር፤ ማንም የክቡርነትዎን ትዕዛዝም አላስተላለፈልኝም ነበር። ነገር ግን አሁን እንዲህ አይነቱ እርምጃ ማስተዋል ያለበት አይመስለኝም፣ በተለይ ተከትሎኝ ከመጣው መጥፎ ስሜ አንጻር። እናም ስኬታማ የሆነ ፖለቲካዊ ውጤት የማመጣ ከሆነ የበረደ አካሄድ መከተል ይኖርብኛል፤ በተለይ የዚህ አይነቱ እርምጃ ከሚነጥለን ከቤተክህነት ጋር፣” በማለት ስጋቱን ገለጸ።

በእንደዚህ አይነት ምክንያት ያልተደነቀው ሙሶሊኒ፣ ውሳኔው በአፋጣኝ እንዲፈጸምለት በድጋሚ ስላዘዘ በሀያ አራት ሰዐት ውስጥ የምኒሊክን እና የይሁዳ አንበሳን ሐውልት እንድታነሳ የሚል ትዕዛዝ ለግራዚያኒ በቴሌግራፍ ደረሰው። ከእንደዚህ አይነት ዱብ እዳ ጋር የተጋፈጠው ግራዚያኒ ትዕዛዙን እንደሚፈጽም ነገር ግን ጊዜ እንደሚያስፈልገው ጠቅሶ ለቅኝ ግዛት ሚንስትር ድኤታው ጻፈ። “እለምንዎታለሁ ክቡርነትዎ፤ የሚንስትሩን ትዕዛዝ እንደምፈጽም ያረጋግጡልኝ። ነገር ግን ሁለቱም ሀውልቶች በርካታ ቶን የሚመዝኑ እንደመሆናቸው፣ ከቆሙበት የማንሳቱ ስራ ባለሙያዎችን እና በርካታ ቀናት ይፈልጋል፣” ሲል በድጋሚ ተማጸነ። ከበርካታ ወራት በኋላ ስራው በጥቅምት 6 ሌሊት ላይ ተጠናቀቀ።

ኢትዮጵያውያኑ ከእንቅልፋቸው ተነስተው የምኒሊክን ሀውልት መነሳት ሲያዩ እጅግ ተቆጡ። በአደባባይ ላይ በርካቶች በእንባ ተራጩ። “ምኒሊክን አበቃ። በሌሊት ሰረቁት” ሲሉ አለቀሱ። ህዝቡ ሲሰበሰብ የጣሊያን ወታደሮች በሳንጃ ያባርሯቸው ጀመር። ይህም የሀውልቶቹን መነሳት ተከትሎ የተፈጠረው የኢትዮጵያውያኑ ፀረ ፋሽስት ተአማኒ ስሜት ዜና የጣሊያን መንግስት ጋር ደርሶ ብስጭት ፈጠረ። ግራዚያኒም ከሳምንታት በኋላ በእርምጃ እንደተቆጣጠረው አሳወቀ። በወቅቱ የነበረ አንድ ስዊድናዊ ከአመት በኋላ እንደተናገረው፣ ኢትዮጵያውያኑ እርስ በእርሳቸው ስለጣሊያኖቹ “መንፈሱን እራሱ ይፈሩታል። አድዋን እኛ እንደምናስታውሰው ነው የሚያስታውሱት፤” እያሉ እንደሚንሾካሾኩ ምልከታውን ገልጿል። የኢትዮጵያውያኑም ተቃውሞ እና ትግል በየቦታው ቀጠለ።

እናም በዚህ ሁኔታ ከወራት በኋላ አብርሃና ሞገስ በዳግማዊ ምንሊክ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ለመከታተል የመጡት። አብርሃ በጽኑ የጣሊያኖቹን ዘረኛ ተግባራት ይቃወም ስለነበር ትግሉን ተቀላቅሎ ግራዚያኒን ከግብረአበሮቹ ጋር ለመግደል ሙከራ ያደረገው። በግራዚያኒም አጸፋ ሰላሳ ሺህ ያህል ንጹሀን ተገደሉ፤ ክስተቱም በኢትዮጵያ ታሪክ እጅግ አስከፊ የነበረ ጭፍጨፋ ሆነ።

ለማጠቃለል፣ አዲስ አበባ ከአድዋ ድል ማግስት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎችና ከውጭ ሀገራት በመምጣት ሀብትና ንብረት አፍርቶ እየኖረ የነበረው እንዲሁም በከተማዋ እየተበራከተ በመጣውና በተለያዩ የንግድ እና የማህበራዊ አገልግሎት ስራ መስኮች ላይ በተሰማራው የከተማዋ ነዋሪ ቅሬታ አማካኝነት አጼ ምኒሊክ ወደ አዲስ አለም ከተማ ሄዶ አዲስ መዲና የመቆርቆር እቅዳቸውን ሊቀለበስ ችሎ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታም፣ ከአርባ አመት በኋላ የጣሊያን መንግስት ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ፣ በርካታ የሙሶሊኒ መንግስት አማካሪዎች አዲስ አበባን ትተው አዲስ ከተማ እንዲቆረቆር ቢጎተጉቱትም ሙሶሊኒ አሻፈረኝ በማለቱ አዲስ አበባም አሁን ላለችበት ትሩፋትና ማንነት የካቲት 12 እና በወቅቱ የነበረው የግራዚያኒ አስተዳደር የራሱን አሻራ ጥሎ ሊሄድ ችሏል። ለዚህም ነው የከተማ ቅርስ ስላለፈው ታሪካችን፣ ባህላችን እና ስለማህበረሰባችን ዝግመተ ለውጥ ፍንጮች የሚሰጠን መስኮት ነው የምንለው። ቸር እንሰንብት!

https://ketemajournal.com/issue/

*******************************

ምላሹ የዘገየው የኢትዮጵያዊያን የካሳ እና ይቅርታ ጥያቄ ፣ወደ ቫቲካን ሰዎች

ከያኔው ገነተ-ልዑል ቤተመንግስት፣ከዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዝቅ ብሎ ኢትዮጵያ መቼም የማትዘነጋውን የእልቂት ቀን የሚዘክር ባለ 28 ሜትር ሃውልት አለ፡፡

በያመቱ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ስፍራ የካቲት 12 ቀን ይሰበሰባሉ፡፡አባት እና እናት አርበኞች "እመ-ሰቆቃ" ግራዚያኒን በቀረርቶ ያወግዛሉ፣አምስት አመት ጣልያን ታግለው ለሀገሪቱ ዳግም ነጻነትን ያመጡትን ጀግኖች እያነሳሱ በፉከራ ያሞግሳሉ፡፡አንዳንዶቹ ደግሞ የዚህ ሁሉ በደል ፈጻሚ ሀገር መቼ ይሆን ይፋዊ ይቅርታ የምትጠይቀው? እጃቸው ያለበት አካላትስ የካሳ ከረጢታቸው መቼ ይሆን የሚፈታው ? ሲሉ ከንፈራቸውን ይነክሳሉ ::

የካሳ እና ይቅርታ ዘመቻ ወደ ቫቲካን ሰዎች

የሙዚቃ መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀ የማርሽ ባንድ ሰራዊት፣ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የመጡ ብላቴናዎች ክያኔ፣ለዝክር የመጣው ሰው ስነ-ስርዓቱ ካለቀ በኋላ ቤቱ ገብቶ የሚያወራው አዲስ ነገር አሳጥተውት አያውቁም፡፡

የ2002 ዓመተ ምህረቱ የሰማዕታት ቀን ማግስት አዲስ ነገርን በተመለከተ በአያሌው ዕድለኛ ሳይሆን አልቀረም፡፡

አዲስ አበባ ጀግኖችን አሞግሳ ፤ለሰማዕታት የነፍስ ይማር ጸሎት አድርሳ በተመለሰች ማግስት፣ የካቲት 29-2002 ዓ.ም ፣ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ‹ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ› የተሰኘ ተቋም በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ትብብር የሚጠይቅ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ይፋ አደረገ።

የዘመቻውን ይዘት ከሚያብራራው ጥራዝ ላይ ትንሽ እንቆንጥር፣

"በ1935-41(እኤአ) ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወርራ ባደረሰችው አሰቃቂ የጦር ወንጀል፣ የቫቲካን መንግስት እጅ ከጓንት ሆና ተባባሪ ስለነበረች፤የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ ተጽዕኖ እንዲደረግባት ፣ለዓለማቀፋዊው ህብረተሰብ ፣በዓለም ላሉ መንግስታት ሁሉ ፣ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፤ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣….ለሌሎች ለሚመለከታቸው ድርጅቶችና ለእውነት ለቆሙ ህዝቦች ድጋፋቸውን እንዲያበረክቱ አቤቱታችንን በታላቅ ትህትና እናቀርባለን፡፡"

የዘመቻው ተጽዕኖ ውጤታማ ይሆን ዘንድ፣ 100ሺ ሰዎች ፊርማቸውን እንዲያኖሩ ተቋሙ በወቅቱ ጠይቋል።

ስምንት ዓመታት አለፉ፣ዘመቻውን የተቀላቀሉ ሰዎች ቁጥር 7ሺ አልሞላም፣ቫቲካንም ይቅርታ አልጠየቀችም።

የቫቲካን ዝምታ …የአረጋዊው ቁጭት

ዘመቻው ይፋ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በየአደባባዩ ብቅ እያሉ የዘመቻውን አስፈላጊነት ለማስረዳት ሲለፉ የሚታዩ አረጋዊ አሉ። እኝህ ሰው "ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ" የተሰኘው ተቋም ሀላፊ ኪዳኔ ዓለማየሁ ናቸው ፡፡

የታለመው የፈራሚ ብዛት ካለመስመሩ ጎን ለጎን፣ ቫቲካን ካለወትዋች እስከአሁን ኢትጵያዊያንን ይቅርታ አለመጠየቋ አይወጥላቸውም ፣"ናዚዎች በአይሁዶች ላይ እልቂት ሲፈጽሙ ቫቲካን ዝም በማለቷ ብቻ በክርስቲያናዊ ትህትና አይሁዶችን ይቅርታ ጠይቃለች ፣" ሲሉ የሚያነሱት አቶ ኪዳኔ ፣« እንደ ክርስቲያን ድርጅት ለፈፀሙት የወንጀል ተባባሪነት ይቅርታ መጠየቅ አይበዛባቸውም። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገር ስለሆነች ይሆን ወደኃላ የሚሉት?ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው፣›› ሲሉ ጥያቄ ይመዛሉ፡፡

የተቋማቸውን ስልክ የመታ ሰው ከሚነሳቸው ጥያቄዎች አንዱ ቫቲካን በኢትዮጵያዊያን እልቂት ውስጥ ያላት ተሳትፎ ምን ያህል ነው? የሚል ነው፡፡ ከሌላኛው ጫፍ ብዙ ጊዜ የማይጠፉት አቶ ኪዳኔ የቫቲካንን ተሳትፎ ፤ የይቅርታውን አስፈላጊነት ለማስረዳት አይታክቱም።

"ፋሽስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ብዙ ወንጀሎች ተፈፅመዋል። አንድ ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ተጨፍጭፈዋል፣ከዚያ ውስጥ በአዲስ አበባ በሶስት ቀናት ብቻ 30ሺ ሰዎች ተጨፍጭፈዋል፣ ከ2ሺ በላይ ቤተ-ክርስቲያኖችና 525ሺ ቤቶች ወድመዋል። ፋሽስት ጣልያኖች ብዙ ዝርፊያ፣ስደት እና እንግልት በኢትዮጵያዊያን ላይ አድርሰዋል።እንዲያ በሚሆንበት ጊዜ ቫቲካኖች ፋሽስት ጣልያኖችን ደግፈዋል፣ባርከዋል ቀድሰዋል፣" ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።

አቶ ኪዳኔ ዓለማየሁ ከታሪክ አዋቂዎች፣ ከንጉሳዊያን ቤተሰቦች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በመሆን ያቋቋሙት ተቋም፣ ቫቲካን ይቅርታ ትጠይቅ ዘንድ የሚለፋው -ይቅርታው ለኢትዮጵያዊያን ስነልቦናዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ካሳን ብሎም ዓለማቀፋዊ ዕውቅና እንደሚያመጣ በማመን እንደሆነ ያብራራሉ።

በተቀናጀ ዘመቻ አቤቱታቸውን ያሰሙ ህዝቦች ለተገቢ ካሳ መብቃታቸውንም ለአብነት ይዘረዝራሉ፣"ጣልያኖች 30ሺ ሊቢያዊያንን በመጨፍጨፋቸው ፣ለዚህ አድራጎታቸው 5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ካሳ (በልማት ስራ መልኩ) ለመክፈል ተስማምተዋል፣" በማለት ካለመናገር ደጅ አዝማችነታችን እንዴት እንደተነፈገ ያሰምራሉ፡፡

ይሄ ዘመቻ እንደ ኢትዮጵያ መንግስት እና የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ያሉትን ተቋማት ድጋፍ ቢያገኝ ኖሮ ውጤቱ ይፈጥን እንደነበረ የሚያነሳሱት አቶ ኪዳኔ ፣ዘመቻው ከታለመው የፈራሚዎች ቁጥር እስከ አሁን ድረስ አንድ አስረኛውን አለማግኘቱ የፈጠረባቸውን ቅሬታ አይሸሸጉም፡፡

"ዲፕሎማሲን " የሚመክረው የአርበኞች ማህበር

"በደም እና አጥንት ግብር " ሀገራቸውን ያቆዩ እናትና አባት አርበኞች ያቋቋሙት "የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር" በስምንት ዓመታት ውስጥ የተለያዩ ለውጦችን አስተናግዷል፡፡

ጥቂት የማይባሉት አባላቱን በሞት ተለይተዋል፣ የአስተዳደር ሽግሽግም ተፈጽሟል፡፡ የዛሬ ስምንት ዓመት ማህበሩን ይመሩ የነበሩት ሊቀ-ትጉሃን አስታጥቄ አባተ -በልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ተተክተዋል፡፡እንደነበር ከቀጠሉት አንዱ ወኔ ይመስላል፣በማህበሩ መሪ ድምጸት ውስጥ እንደሚሰማው ያለ፣

"የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የኢትዮጵያ ንብረት የሆነ ሚስማር ጭምር ያለአግባብ ሄዶ እንደሆነ 'ወደ ሀገሩ መመለስ አለበት' የሚል ፅኑ የሆነ፣ የማያወላውል አቋም አለው ፣" ይላሉ ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የቫቲካን እና የይቅርታው ጉዳይ ሲነሳ፣ የጋለ ድምጸታቸው መልሶ ይሰክንና በተጀመረው አይነት መንገድ ካሳ እና ይቅርታን የመጠየቅ ሂደት ውስጥ ማህበራቸው ሊሳተፍ እንደማይችል ይናገራሉ። ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ማህበሩ የተመሰረተበት ህግና ደንብ ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት ዘመቻ ለመከወን የማያስችል መሆኑ ነው።

ከሁሉም ከሁሉም ግን የማህበሩ ፕሬዚደንት በግለሰቦች አስተባባሪነት እዚህ የደረሰው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ውጤታማ ስለመሆኑ ጥርጣሬ አላቸው።በጋርዮሽ ተፅዕኖ የመፍጠር ሙከራ ይልቅ በመንግስታት መካከል የሚደረግ ንግግር ፍቱን መፍትሄ እንደሚያመጣ ለማሳየት ባቀደ መልኩ፣ "የአክሱምን ሀውልት የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ሄዶ አላመጣውም … ዲፕሎማሲ እንጂ" ይላሉ፡፡

ቫቲካን 'አላት'የሚባለውን የግፍ ተሳትፎንም ልጅ ዳንኤል ጆቴ ይጠራጠሩታል፣ "እኛ እንደምንረዳው( የጣልያንን ጦር) ባርኮ የላከው ሚላኖ ላይ የነበረ ቄስ ነው። የአቶ ዘውዴ ረታን መፅሃፍ ላይ ራሱን የቻለ ታሪካዊ መግለጫ አለው(አቶ ዘውዴ ረታ አምባሳደር በነበሩበት ወቅት ተመራምረው እና ጥናት አድርገው የፃፉት መፅሃፍ ነው)። አንዳንድ ታሪኮችን በስሜታዊነት ተነስቶ ከማየት ርቀን፣ አንስተን እና አውርደን በደንብ ተዘጋጅተን የቀረብን ጊዜ ጣልያኖችም ሆነ እንግሊዞች ነገሮችን የማይመልሱበት ፣የተጠየቁትን የማያደርጉበት ምንም ምክንያት የለም፣"ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር በዘመቻው ላይ ያለውን የፍሬ ነገር ጥርጣሬ ያጋራሉ፡፡ 

"የኢትዮጵያ አምላክ፣ይረዳናል!"

በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው ‹ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ› ሃላፊ ኪዳኔ ዓለማየሁ ድምጽ ውስጥ ሀዘን ተጠልሏል፡፡በልጅ ዳንኤል ጆቴ በኩል የተሰጠው ምላሽ እንዳልተዋጠላቸው ያሳብቃል፡፡

"ለፍትህ ጉዳይ ሁላችንም ሃላፊነት አለብን።እንኳን እኛ ኢትዮጵያዊያኑ ይቅርና ጣልያኖች ሳይቀሩ እየደገፉት ያለ ጉዳይ ነው።በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ኋላ ማለት ለአገር የሚያኮራ ጉዳይ አይደለም፣" ሲሉ ይመክታሉ፡፡ የቫቲካን ተሳትፎ ላይ ጥያቄ መነሳቱም ቢሆን ለእሳቸው እንቆቅልሽ ነው፣ "ብዙሃኑ ጳጳሳት ወርቃቸውን ሳይቀር እያወጡ ለጦርነቱ አስተዋፅኦ ያደረጉ መሆኑን፣ አንደኛው ‹ካርዲናል› ይሄ ጦርነት ቅዱስ ጦርነት ነው ሲሉ የተናገሩት መረጃ አለን፣ የጣልያን ጦር አዲስ አበባ ሲገባ የደስታ መግለጫ ካወጡት መካከል የመጀመሪያው (የቫቲካኑ) ፖፕ ሃያስ ነበሩ፡፡ ይሄንና ሌላ ማስረጃዎችን ያየ ..እንዲህ ያለ የማይሆን ነገር ለመናገር አይችልም፣" ሲሉ ይሟገታሉ፡፡

አቶ ኪዳኔና አጋሮቻቸው ከእኒህ ሁሉ ዓመታት በኃላ "ይሄ ነገር አይሰምርም" ብለው መዝገባቸውን ለማጠፍ ዝግጁ አይደሉም፡፡ ከዚህ ቀደም በቫቲካን ተባባሪነት ለደረሰ በደል፣ የነዋይ ካሳን እና ይፋዊ ይቅርታን ማግኘት እንዲሁም በወቅቱ የተዘረፉ ቁሳቁሶች እና ቅርሶች ወደሀገራቸው ተመላሽ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረታቸው እንደሚቀጥል ይናገራሉ።

በእነ አቶ ኪዳኔ አለማየሁ መንደር የተስፋ ጀምበር አልጠለቀችም ፡፡በዚህ ዓመት ህዳር ወር ላይ ከ81 ዓመት በፊት የካቲት 12 ለተፈጠረው እልቂት ሰበብ የሆነው ሩዶልፎ ግራዚያኒ መታሰቢያ ሃውልት 'አፊል' ከተሰኘችው የሮማ ጎረቤት ከተማ እንዲነሳ ተወስኗል፡፡

ሃውልቱ እንዲሰራ የገንዘብ ፈሰሱን ያጸደቁት የከተማዋ ከንቲባ እና ሁለት የአስተዳደር አባላት ‹‹ፋሽስት ይቅርተኝነት›› Apologia del Fascismo የሚሰኘው ህግ ተጠቅሶ በስምንት እና ስድስት ወራት እስር እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡

ሃውልቱ መወገድ እንዳለበት ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ሲጎተጉቱ ከነበሩ ተቋማት አንዱ ለሆነው 'ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ'፣ውሳኔው የሌሎች ዘመቻዎች ተስፋም ፈጽሞ እንዳልከሰመ የሚያሳይ ምልክት ይመስላል፡፡

ሃላፊው የ ቫቲካን ይቅርታ መዘግየት የሚያብከነክናቸውን ያክል አንድ ቀን ይቅርታው እንደሚሰማ ያላቸውን ዕምነትም ከፍተኛ ነው፡፡ ይሄን የሚደግፈው የሚደጋግሙት ሀረግ ነው ''የፍትህ አምላክ፣የኢትዮጵያ አምላክ፣ይረዳናል!'' የሚለው፡፡

https://www.bbc.com/amharic/news-44198353

**********************************************

https://www.gudayachn.com/2014/02/12.html

 

 https://www.facebook.com/1845896815651636/photos/%E1%8B%A8%E1%8A%AB%E1%89%B2%E1%89%B5-121929-%E1%8B%93%E1%88%9D-%E1%8A%A0%E1%8B%B2%E1%88%B5-%E1%8A%A0%E1%89%A0%E1%89%A3-%E1%8A%A8-%E1%88%B0%E1%88%8B%E1%88%B3-%E1%88%BA%E1%88%85-%E1%89%A0%E1%88%8B%E1%8B%AD-%E1%8A%90%E1%8B%8B%E1%88%AA%E1%8B%8E%E1%89%BD%E1%8B%8B-%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%8B%B2%E1%89%B5-%E1%8C%80%E1%8A%95%E1%89%A0%E1%88%AD-%E1%88%B0%E1%88%9B%E1%8A%A0%E1%89%B5%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%89%80%E1%89%A0%E1%88%89%E1%89%A3%E1%89%B5-%E1%89%80%E1%8A%95-%E1%8A%90%E1%89%A0%E1%88%A8%E1%89%BD-%E1%8B%A8%E1%8B%9B%E1%88%AC/1846383585602959/?paipv=0&eav=AfZREjMYFPEAQaC2VRnSiLcsQAmnYg9Hb5p8A9BfqGm_g6GUJluev1DD_RYna2cmipU&_rdr

 

 

 

 

 

 

No comments:

Post a Comment