ከደራሲያን ዓምባ

Tuesday, December 24, 2013

የእንግሊዝኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላት አዘጋጅ

                         ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ

                                  (እንግሊዝኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላት አዘጋጅ) አረፉ፡፡ 
                         / ነሐሴ 27 ቀን 1922 ዓ.ም.--- ታኅሣሥ 10 ቀን 2006 ዓ.ም./

 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ) ለ33 ዓመታት ያገለገሉትና በተለያዩ መጽሐፎቻቸው የእንግሊዝኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላትን ጨምሮ ታዋቂ የሆኑት ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ በ84 ዓመታቸው አረፉ::
ከቅርብ ዓመት ወዲህ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ሕክምናቸውን ሲከታተሉ የነበሩት ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ታኅሣሥ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ነው::


የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር የሳይንትፊክ ቡድን ዳይሬክተር ሆነው ለአንድ ዓመት (1954-55) ያገለገሉት ዶ/ር አምሳሉ፣ ከ1955 ዓ.ም. ጀምሮ በጡረታ እስከተገለሉበት እስከ 1985 ዓ.ም. ድረስ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲ ከሌክቸረርነት እስከ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማገልገላቸውን ገጸ ታሪካቸው ያመለክታል:: በተለይ በግእዝ፣ በአማርኛና በዓረብኛ ቋንቋዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክን በማስተማር ይታወቃሉ::
የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ሊቀመንበር፣ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም ዲን፣ የኢትዮጵያ
ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ የቦርድ አባልም ሆነው ሠርተዋል:: አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1997 ዓ.ም. የፊሎሎጂ (ጥንታዊ ጽሑፎች ጥናት) ትምህርት ክፍል ሲከፈት በድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር ስለኢትዮጵያ ፊሎሎጂ፣ ስለግእዝና ዓረብኛ መዋቅር በኮንትራት አስተምረዋል::
ዶ/ር አምሳሉን ስመጥር ካደረጓቸውና ካበረከቷቸው ትምህርታዊ የሕትመት ውጤቶች መካከል 


*‹‹እንግሊዝኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት›› (ከጂ.ፒ. ሞስባክ ጋር /1966 ዓ.ም.)፣ 
*‹‹የአማርኛ ፈሊጣዊ አነጋገሮች›› (ከዳኛቸው ወርቁ ጋር/1979 ዓ.ም.) 
*‹‹የእንግሊዝኛና አማርኛ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት›› (ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ ጋር) 
*‹‹ጥሩ የአማርኛ ድርሰት እንዴት ያለ ነው?››  (ከደምሴ ማናህሎት ጋር/1989 ዓ.ም.)፣ 
*‹‹አጭር የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ›› (ያልታተመ)፣
*‹‹አማርኛ-ዓረብኛ መዝገበ ቃላት›› (ከሙኒር አብራር ጋር/1999 ዓ.ም.)፣ 

*‹‹ግዕዝ መማሪያ መጽሐፍ Ge’ez Textbook›› (2003 ዓ.ም.)፣ 
‹‹የአማርኛና ሞክሼ ሆሄያት ጠንቅቆ ያለመጻፍ ችግርና መፍትሔ›› (2002 ዓ.ም.)፣ 
 በጀርመን ሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ በታተሙት ተከታታይ 
*‹‹ኢንሳይክሎፔዲያ ኢትዮፒካ››
እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበዋል::
በቀድሞው አጠራር በወሎ ጠቅላይ ግዛት ደሴ ከተማ
ነሐሴ 27 ቀን 1922 ዓ.ም. የተወለዱት ዶ/ር አምሳሉ፣ ከቄስ ትምህርት ቤት በኋላ መደበኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከካይሮ ዩኒቨርሲቲ በነገረ መለኮት (ባችለር ኦፍ ዲቪኒቲ)፣ እንዲሁም ከካይሮው አሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ባችለር ኦፍ አርት በተመሳሳይ ዓመት በ1949 ዓ.ም. አግኝተዋል::
የአማርኛ፣ ዓረብኛ፣ እንግሊዝኛና ጀርመንኛ ቋንቋዎች አዋቂ የነበሩት ዶ/ር አምሳሉ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን
ከጀርመን ቱቢንግ ዩኒቨርሲቲ በ1954 ዓ.ም. ሲያጠናቅቁ፣ የመመረቂያ ድርሳናቸውን (ዲዘርቴሽን) የሠሩት በኦገስት ዲልማን የግእዝ መዝገበ ቃላት ላይ ነው::
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል አስተባባሪው ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣
የዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ (ታኅሣሥ 13 ቀን 2006 ዓ.ም.) እኩለ ቀን (6 ሰዓት) በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል::

*************************************
ምንጭ:--http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment