ከደራሲያን ዓምባ

Friday, November 21, 2014

የባንዲራ ታሪክ_በኑረዲን ዒሣ

የግጥም ጣዕም 

የባንዲራ ታሪክ_ኑረዲን ዒሣ

 

በሃበሻ ምድር
እንዲህ እንደዛሬው ዋጋው መሣ ሳይሆን
እኩል ከእራፊ ጨርቅ
ለሃገር ክብር ሲባል
ከባንዲራ በፊት – ሰው ነበር የሚወድቅ።
መሣፍንቱ በጎጥ ሸንሽኖ ከፋፍሎ
የማሽላ ዳቦ ያረጋትን ሃገር
ገብርዬ ሲለካት – እንቅጯን ሁለት ክንድ
በሆነች ባንዲራ ገጣጥሞ በማሰር
አንድን ሕዝብ አንድ አርጎ
ማኖር እንደሚችል ከተዋበች በቀር
ሕዝቡም፣ ሹማምንቱም፣ እራሱ ቴዎድሮስም – ከቶ አያውቅም ነበር።
የዛን ቀን ለሊት ግን
እንደ ነገ ጠዋት፣ ደረስጌ ማርያም ላይ
ንግሥና ሊቀባ፣ ክፉኛ ሃሳብ ይዞት
እንቅልፍም እንደሰው ሙልጭ አርጎ ክዶት
እልፍኙ ውስጥ ሆኖ….
ስለአንዲት ሃገሩ፣ ስለአንዲት ወዳጁ
እቋፍ ላይ ስላለች
ላሳቡ ማሰሪያ አጥቶ – እግር ተወርች
እንዲህ ሲንጎራደድ
ሌላኛ ወዳጁ
የሴት ባለመላ – ተዋበች አሊ ግን ልታነቃው አለች።
«ካሣ መከታዬ»
ሃሳብ ለምን ገባህ አልልም የኔ አባት
ቅድምም አየውህ – ማዱን ስትገፋው
አልዋጥ ብሎ፣ ባፍህ ሲንከራተት የጎረስከው እራት።
አውቃለሁ ጌታዬ
የእንቅልፍህ፣ የእረፍትህ፣ ያንዠትህም ጠላት
ይቺው ሃገርህ ናት።
ደሞ ምናባቱ…እንቅልፍስ ይቅርብህ – ወዴት ታውቀውና
እጣህን የመንቃት አድርጎት ሲያበቃ…
ምኑን ታርፈዋለህ
ይኼው ጎበጥክ አይደል – ሃገር ስታቀና።
እንቅልፍስ ይቅርብህ ወዴት ታውቀውና።
ቁስሉን ነካችበት
ብሶቱ ልፋቱን – መከራውን አልፋ ሕልሙን አየችበት።
ካሣ አንገቱን ደፋ
እሷ ፊቷን ዞረች።
እንዲህ የሆነ ዕለት – ከሱና እሷ በቀር – ባዕድ የማያውቃት
ያይኑን ገደብ አልፋ – የምትፈስ እንባ አለች
ያቺ ዕንባ ጠብ አለች።
እንግዲህ አለ መይሳው
እንግዲህ…
በእኔ ልፋትና በኔ ድካም ሳይሆን
በእግዜር ይሁን ማለት
ለዚህ ማዕረግ መርጦ – ሰጥቶኛል ይኽን ሹመት
እኔ ስሰነዝር እሱ ከኔ ቀድሞ ባላንጦቼን እየጣለ
ወሰኔን እያሰፋ – የታጠቅ ጉልበት እንደቻለ
ሞገሴን እያገዘፈ….
እንደልቤ መሻት—እርከኔን እያከለ።
እግዛቤር ይመስገን
ይኼው … ለዚህ በቅቻለሁ
ተመስገን ከማለት ውጪ
ለስለት እከፍለውስ—ምን የከበረ አስገባለሁ።
ግን አለ መይሳው!
ግን ነገ ማለዳ…ቅባቱን ተቀብዬ – ዘውዱን ስደፋ
ሕዝቡ!
ይጠብቃልና…እገባለት ኪዳን – ፈቅደህ ስጠኝ ስለው ይቺን ትልቅ ሃገር
ምን ይዤ ልማልለት – ምን ጨብጬ ልቁረብለት
ምንስ ብዬ ልናገር
እስኪ መላ ካለሽ – ተዋቡ – ካንቺ እንኳን ልበደር።
በማተቤ እንዳልምል
የባለሌጣ አንገቱም የእስላሙም ናት ይቺ ሃገር
በጊዮን እንዳልምል
ኦሞ፣ ጉደር፣ አዋሽ፣ ቦርከና፣ ባሮ፣ ተከዜ፣ ጉማራ በይው ሎኒያ
ሁሉም ገንዘቧ ነው
የቱ ከየትኛው በልጦብኝ – በየትኛው ልማልላት ለኢትዮጵያ!
ሽናሻ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ አገው፣ ወላይታ
ትግሬ በይው አማራ፣
በምድሯ የተቀነበበ ሁሉ በስሟ ነው የሚጠራ።
እህም…አለች ተዋቡ
እህም…አሁን እስላም ስትል – ሸማኔው ትዝ አለኝ
እጀ ወርቅ የሚሉት – አህመዴ ቦጋለ
በል ቶሎ በል ካሣ – አሽከር አስጠራልኝ – ገብርዬ የታለ
ገብርዬን አስጠራው
እሱ ነው የልቤ – ሲጋልብ የሚነፍስ
ከጎህ ቅዳጅ በፊት – መልዕክቴን ይዞልኝ – ከደጁ የሚደርስ።
ካሣን ግራ ገባው፣ ግን አይጠይቃትም፣
አምስት ስድስት ጊዜም እንደዚህ አዋክባው
እሷው ነድፋ፣ እሷው አባዝታ
እሷው አድርታ፣ እሷው ፈትላ
ባመጣችው ሃሳብ፣ ባሳየችው መላ
ብትንትን ሃሳቡን ገጣጥማ ስትሰፋው – አይቷልና ባይኑ
ለምን ማለት ትቶ፣ እንዴት ማለት ትቶ
«ገብርዬ ይጠራ» አለ ወዲያውኑ።
ገብርዬ
ከታንጉት ሙቅ እቅፍ
በውድቅት ተላቆ – ከነ ጋሻ ጃግሬው ገና እንደደረሰ
«እሰይ የኔ አንበሳ» ስትለው ተዋበች
ገና እንኳን በወጉ የወጉን እጅ መንሳት ሰጥቶም አልጨረሰ።
«እሰይ የኔ አንበሳ…
እንትፍ ይቺ ምራቅ ምድር መጥጧት ሳትከር
ስትገሰግስ ሄደህ…ደገኞቹ መንደር
አህመዴ ለሚባል
እጀ ወርቅ ሸማኔ … ቃሌን ቃል ሳትጨምር፣ እንዲህ ብለህ ንገር።
ባገር ሠማይ ስትፈልቅ
የቅርቡም የሩቁም እኩል እንደሚያያት የማሪያም መቀነት፣
በዚህ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ጥለት
አንተ ስትለካት – ሁለት ክንድ የሆነች – ጥብቅ ምት ባንዲራ፣
ሁነኛ አርጎ ሰርቶ
ነገ ማሪያም ድረስ – ይዟት እንዲመጣ – አጥብቀህ … አርቀህ ንገረው አደራ።
በማለት ተዋበች…
ግብጦች ለእጅ መንሻ – ከላኩላት መሐል -
የሃር የሆነውን ጥለት ጥድፍ ብላ
ለገብርዬ ሰጥታው – እሱም ጥድፍ ብሎ
ከነጀሌዎቹ ከወጣ በኋላ
ካሣ ፈገግ አለ፣
የጥድፈቷ ሚስጥር ቋጠሮው ተፈትቶ፣ ብትንትን ሃሳቡን
ባንድ ስላዋለ
ካሣ ፈገግ አለ።
ሺህ ስምንት መቶ አርባ አምስት – ዓመተ ምህረት
የተራራው አናት – ገና ሳይላቀቅ
ካድማስ ጥቁር እግር
ባህመዴ አማርኛ – ሠማዩ ሳይቀላ ባግባቡ ሳይፈጅር
አህመዴ ቦጋለ
የንጋት ስግደቱን – አስላምቶ አብቅቶ
ልክ! ፊቱን እያበሰ
ፊታውራሪ ገብርዬ
ከነጀሌዎቹ ደጁ ላይ ደረሰ።
የፈረሶች ኮቴ – ደጁን ሲረመርም የሰማው አህመዴ
ልቡ ድንግጥ አለ፣
«እንዲህ በማለዳ – የሚደርስ ከደጄ
መርዶ ነጋሪ ነው
ደሞ ማን ተለየኝ – የትኛው ዘመዴ?
ከቶ የኔ ሐዘን ዳርም የለው እንዴ
«እንዴት አደራችሁ…ቤቶች»
ይበልጥ ተረበሸ ይኼን ድምፅ ያውቀዋል፣
ምላሽም አልሰጠ፣ በርም አልከፈተ
ድርቅ ብሎ ቁሞ – ወይ ወንድሜን አለ
ክተት ሲባል ከቶ ከመይሣው ጋራ አብሮ የዘመተ
አንድ ወንድም ነበረው… ያ ወንድሙ ሞተ?
«ቤቶች…ቤቶች
ገብርዬ ጥሪውን እንዲህ ሲደጋግም
ገፋ አድርጎ ወጥቶ የጎጆውን ግርግም
ድሮ አውቄዋአለሁ
ለደግም አልነበር አደባባይ ቆሜ
ሸማ ሳውለበልብ ያየሁት በህልሜ
ወይ ወንድሜን ወንድሜ!
«የለ እንደሱም አይደል» ገብርዬ አቋረጠው
«ተዋበች ልካን ነው»
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ጥለቱን ሰጠው።
አስከትሎ ደግሞ
ቃሌን ቃል ሳትጨምር – ያለችውን መልዕክት
ቃሏን ቃል ሳይጨምር – ረግጦ ሲነግረው
የመናቡ ተፍሲር – ብስራት ሆኖለት
እጀ ወርቅ ደስ አለው።
አለም፦
እንዴት ያንድ እናት ሆድ፣ አንድ ላይ ያበቅላል፣ አንድ ደህና አንድ ጠፍ
ብረገም ነው እንጂ
ክተት ሲል ከትቼ – እንደዚያ ወንድሜ – ከመይሣው ጋራ ጎኑ ማልሰለፍ፣
ብዬ እቆጭ ነበር፣… ይኼው ዛሬ ግና
አላህ ያለ ለታ፣ ላገር ሥራ ሲለኝ ረብ ያለው ሥራ
ያውም የመይሳውን ያውም የኢትዮጵያን … ያውም ያገሬን ባንዲራ
ያውም በኔ ጥበብ…
ያውም በሰው እጆች … ከሰውም በኔ እጆች … በሸማ እንድሰራ
ታሪክ እድል ሰጠኝ፣ ብሞትም አይቆጨኝ ከዚህስ በኋላ!
አህመዴ ሸለለ፣
አህመዴ ፎከረ … በደስታ ሰከረ፣ በደስታ አለቀሰ
ሩጦ ቤቱ ገባ፣ ሦስቱንም ልጆቹን – ሚስቱን ቀሰቀሰ።
ነገራት ለሚስቱ፣
ከምርጥ ዘሃ መሀል – ምርጡን ዘሃ መርጣ
እንድታቀርብለት – ቶሎ ብላ አዝግታ።
አዘዘ ልጆቹን
ቱባ ተከፋፍለው – ከየአንዳንዱ ጥለት
አሥር አሥር ቀለም – እንዲያዳውሩለት።
ሦስት ሰዓትም አልፈጀ
መቀነት ሸማቃው ከኖረበት ወርዶ
ዝግ ዘሃው ተቋጥሮ
ጥለቱ ተጥሎ.. ድምድሙ ተመትቶ – ባንዲራው ሲቆረጥ
በቅሎው ከጋጥ ወጥቶ
በጌጥ ተሸልሞ አህመድ ተነሚስቱ እጋማው ላይ ወጥቶ
እሱ – ሲኮለኩል – በቅሎው ንሮ ሲሮጥ … ሲሮጥ … ሲሮጥ
ደረስጌ ማሪያም ላይ ደርሰው ሆታው ሲቀልጥ
በዚያ መሀል አልፈው አህመድ ለመይሣው ባንዲራውን ሲሰጥ
ሰዓትም አልፈጀ
መይሣው ደስ አለው
የወርዱ ምጣኔ፣ የጠርዙ ጥብቅነት፣
የጥለቱ አጣጣል፣ ጥበቡ ደነቀው፣
ቁርጥማት አይንካህ
በሆዱ መረቀው
ካሣ ዞሮ ሄደ።
አህመዴ ተጣራ
መይሳው ዞር አለ
ባንዲራው ሲሰራ
ተርፎ ስለነበር ብዙ የሃር ጥለት ካቁማዳው አውጥቶ … እጁን ዘረጋለት።
ካሣ….!!
የዚህን ደሃ ሰው – ፍፁም ታማኝነት፣ ገራገር ልቦና ባስተዋለ ጊዜ፣
የጎንደር አዝማሪ ያቀነቀናትን በልቡ እያዜማት
በልቡ ያላትን … ያቺኑ ምርቃት…
ተባረክ እጅህን አይንካው ቁርጥማት
በአፉም ደገማት።
የጎንደር አዝማሪ በእነ አህመዴ ዘመን፣
«እስላም አልኩሽ እንጂ – እጁ የሚታመን
ሸማኔማ ሞልቷል ደሞ ለመሸመን»
ይል ነበር።                        

https://www.youtube.com/watch?v=rekboLUx2wI

1 comment:

  1. Coin Casino
    Coin Casino offers the most attractive welcome bonus for 코인카지노 new players! Check out the welcome 메리트카지노 bonus at Coin Casino, the best online casino 1XBET for Bitcoin! Rating: 5 · ‎3 votes

    ReplyDelete