ከደራሲያን ዓምባ

Thursday, October 13, 2022

እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ__የፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው መጽሐፍ

 የፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ . . . መጽሐፍ __ሔኖክ ያሬድ



‹‹ስለ ሀገሬ ኢትዮጵያ ባሰብኩ ቁጥር ስለ ጥንታዊቷ አገር ያነበብኳቸው የታሪክ መጻሕፍትና አሁን ያለንበት ሁኔታ አልገጣጠም ይለኝና ‹ለምን ይህ ሆነ?› እያልኩ ብቻዬን እነጋገራለሁ፤ እተክዛለሁ በተመስጦም ዝም ብዬ ቁጭ እላለሁ፡፡ ቀድሞ የነበርንበትን የከበረ ወንበርና አሁን ደግሞ ያለንበትን ከባድ ጉስቁልና ሳስብ ውስጤ በቁጭት ይሞላል፡፡ ብዙ ጊዜ በጥሞና ውስጥ ሆኜ አዲሲቱንና የምንመኛትን አገሬን በዓይነ ሕሊናዬ አያታለሁ፡፡ ታዲያ እንደገና መለስ ብዬ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ሳስብ ወደምንመኛት፣ ማርና ወተት ወደምታፈስ አገር ለመድረስ ምን መደረግ አለበት? ብዬ ሳውጠነጥን መያዣ መጨበጫው ይጠፋኛል፡፡ ችግሮቹ እጅግ የበዙ ናቸውና፡፡››

መሰንበቻውን የኅትመት ብርሃን ባየው የፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ‹‹እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ . . .›› መጽሐፍ መግቢያ ላይ ደራሲ የተንደረደሩበት እሳቦት ነው፡፡ ቀድሞ ገናና የነበረች አገር በዚህ ዘመን ምን ዱብዳ ወድቆባት ነው ጭራ የሆነችው? የሚለውን የኅብረተሰብ ቁጭት መርምረው መፍትሔ ነው የሚሉትን ሐሳቦች በመጽሐፉ ላይ አስፍረውታል፡፡

የአስተሳሰብ የማያቋርጥ ዕድገት ለአገሮች ብልፅግና መሠረት መሆኑን  ያመለከቱት ደራሲው፣ ሐሳባቸውን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ለአገሪቱ ዕድገት የኢትዮጵያውያን የልቦና ውቅር መለወጥ (ፓራዳይም ሺፍት/Paradigm Shift) እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡

መጽሐፉ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲመረቅ የምሕንድስና ፕሮፌሰሩ እንደተናገሩት፣

 ‹‹የምንመኛትን ኢትዮጵያ በማየት እዚያ እንዴት ነው መድረስ የምንችለው? አስተሳሰባችን አመለካከታችን ልንቀይር ይገባል፡፡ አሁን ያለን አመለካከት ድሮ በኖርንበት ከሆነ የትም መድረስ አንችልም፡፡ ዓለም እየተቀየረች ነው፡፡ በፖለቲካ፣ በጂኦግራፊ፣ በኢኮኖሚ በሁሉም አቅጣጫ እየተቀየረች ሲሆን እኛ ደግሞ ሐሳባችንና አመለካከታችን መቀየር አለበት፡፡››

ይህንኑ መሠረተ ሐሳባቸውን በመግቢያቸው እንዲህ አብራርተውታል፡፡  

‹‹ኢትዮጵያን ስናስብ በራቀው የታሪካችን ምዕራፍ ውስጥ ምን ያህል ገናና ታላቅ አገር እንደነበረች እንረዳለን፡፡ ጥቂትም ቢሆኑ ትንግርት መስለው የቆሙ ምስክሮቻችን ለቀድሞ ትውልድ ማንነት ማስታወሻ፣ ለአሁኖቹ የጥያቄዎቻችን ምንጭ፣ ለሌሎቹ ደግሞ የግርምታቸው ዘሀ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ታዲያ ከዓለም በፊት ቀድመን፣ ሰው ተኝቶ ሳያልም እኛ ርዕይ አይተን እንዳልነበር ለምን አሁን የሀገራት ጭራ ሆንን? ጥያቄው የሁላችንም፣ ምክንያቱ ፈርጀ ብዙ ይሆናል፡፡

‹‹ይሁን እንጂ አሁንም እንደትውልድ ለቀጣዩ እንድናስተላልፍ ያልተቀበልነው ዱላ፣ እንደታሪክ ያልተሻገርነው ክፍተት አለ ማለት ነው፡፡ አገራችን እጅግ ከባድና መራራ ጊዜ ብታሳልፍም፣ የቱንም ያህል ጠላቶቻችን ቢበዙና ቢያይሉ ከሥራ ለዘብተኛነትና ቸልተኝነት በላይ የሚጎዳን፣ ከፍቅርና ኅብረት ማጣታችን የባሰ የሚያሸንፈን ነገር አይኖርም፡፡ በመሆኑም በአገር ደረጃ ከፍ ብለን ለመታየትና፣ የምንመኛትንም ዓይነት የበለፀገችና ጠንካራ አገር በሁላችንም ጥረትና ሥራ ለማምጣት የጋራ ርዕይ ያስፈልገናል፡፡ ይህን ርዕይ ደግሞ ሁላችንም ልንደርስበት የምንችለው በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የታተመ ሲሆን ነው፡፡››

ሌላው ተናጋሪ፣ 

‹‹አገርን ለመውደድ መጀመርያ ራስን መውደድ ያስፈልጋል የሚል ነገር አለ፡፡ እዚህ ላይ ነው የልቦና ውቅር የሚመጣው፡፡ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው ያለፉበት መንገድ አለ፤››

 

የሚሉት በመጽሐፉ ላይ አስተያየት የሰጡት የሥነ ልቦና ምሁሩ ዶ/ር መስፍን አርአያ ናቸው፡፡  

እንዲሀም አብራሩት፣ በአንድ ወቅት ካሜራ ኢትዮጵያ ሲገባ ለአፄ ምኒልክ እንዴት እንደሚሠራ ሲያሳዩዋቸው በአካባቢያቸው የነበሩት በጣም ነበር የነቀፉት፡፡ ለምን ይህ የሰይጣን ሥራ ነው የሚል አመለካከት ነበራቸውና፡፡ እንዲህ ያለ ነገር አገራችን መግባት የለበትም፤ መኪና ፈቀዱ፣ ሰላቢ የሆነ በሽቦ ውስጥ የሚሄድ ድምፅ እንዲሠራ ፈቀዱ፤ በአገራችን መከራ አሳር ያመጣል፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረውን የልቦና ውቅር ያሳያል፡፡ አርቆ አሳቢው መሪ ግን ራሳቸው እንዳሳዩት ካሜራውን መጠቀም፣ መኪናውን መንዳት ነበረባቸው ራሳቸው በስልክ መነጋገር ነበረባቸው፡፡

‹‹እንደዚህ ዓይነቱን ውቅር ለውጥ እስካላመጣን ድረስ በአገሪቱ በአንድ ቦታ ላይ የምንሰቃይ ከሆነ መራመድ አንችልም፤ ወሳኝ የሆነ ነገር ነውና የልቦና አወቃቀር ጽንሰ ሐሳብን ሁላችንም መያዝ እንዳለብን በሚገባ መጽሐፉ ያመለክታል፤›› ያሉት ዶ/ር መስፍን፣ ሙሉ ሰዎችን ለማፍራት ትክክለኛ የልቦና ውቅር ለውጥ መምጣት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡ በየትውልድ ላይ የሚቀየሩ ነገሮች እንደሚስተዋሉ ያመለከቱት አንድ ዘለላ ምሳሌ በማምጣት ነው፡፡

‹‹በአሁን ሰዓት የአሜሪካን ሕዝብ መዝሙር ለማጥናት የሚተጉ ወጣቶችን አስተውላለሁ፡፡ አንፃሩ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ከ‹ኢትዮጵያ ሆይ› ጀምሮ እስካሁን እስካለው ‹የዜግነት ክብር› ድረስ ያለውን መዝሙር የምናውቀው ስንት ነን? ብንል በጣም ጥያቄ ውስጥ የምንገባ ነው የሚሆነው፡፡ የልቦና ውቅር ሰፊ ነው ወደ ሚለው ይወስደናል፡፡

የምንመኛት ኢትዮጵያን በተመለከተ በልማቱ ዘርፍ ምርታማነትና ጥራት ላይ ብዙ ጽፈዋል፡፡ ወደዚያ ለመድረስ ከፈለክ ግን መጀመርያ ያለውን የልቦና አወቃቀራችንን ለመቀየር መዘጋጀት አለብን የሚለው ከዚህ መጽሐፍ ላይ የምወስደው ነው፡፡››

በዶ/ር መስፍን አርአያ አገላለጽ፣ የልቦና ውቅርን ከሰብእና ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ሰብእና አንድ ሰውን ሲያመለክት ልቦና ውቅር ደግሞ በዚያ ሰውና በአካባቢው የሚቀረፁ ሒደቶችን ያመላክታል፡፡

‹‹እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ. . .›› መንግሥታዊና ግላዊ ተቋማት እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትስስር የተሻለ እንዲሆን ይመክራል፡፡ ምርታማነት እንዲጨምር ያሠራር መንገዶችን በቀጣይነት ስለማሻሻል ያትታል፡፡ በተለይም የሐሳቦች ዋነኛ አትኩሮቱ ጥራት ላይ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ዕድገት ያገልግሎትና ምርት ጥራት ጉዳይ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑንም አስረግጦ ይናገራል፡፡ ይህንኑ  ፕሮፌሰር ዳንኤል ሲያመለክቱ፣ ‹‹ጥራት ሒደት ነው፤ ጥራት የዕድገት ደረጃ ነው፡፡ አሜሪካኖቹ አውሮፓውያኑን በሰባት ዓመት ይበልጧቸዋል ይላል ሊትሬቸሩ፤ አውሮፓውያኑ ደግሞ እኛን በብዙ ዓመት ይበልጡናል፡፡ ስለዚህ ይህን የጥራት ባህል የምናመጣው እያንዳንዳችን ከልጅነት ጀምሮ ስንማር ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመድረኩ እንደታወሰው፣ አገሪቱ አማካይ ነገር ላይ ነች፡፡ በድህነትና በብልፅግና፡፡ እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማምጣት ‹‹እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ . . .›› አንድ ማሳያ ነው፡፡ ‹‹የመንግሥተ ሰማያት መንገድ ቀጭን ነች፡፡ የኢትዮጵያን ቀጭን መንገድ ሁላችን ልንጓዝበት ይገባል፡፡ በሩ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ የኢትዮጵያችን በር መስፋት አለበት፡፡ ጥቂቶች የሚበለፅጉበት ሌሎች መናጢ የሚሆንበት መንገድ መኖር የለበትም፡፡ የልቦና ውቅር ለውጥ መምጣት አለበት፤›› በመድረኩ ተስተጋባ፡፡

በአገሪቱ መተባበርና መወዳደር (Cooperative and Competition) ለዕድገት እንደሚበጅ ደራሲው ያሰመሩበት ቁም ነገር በምሳሌ የታጀበ ነው፡፡ ‹‹አቅርቦት (Delivery)›› በተሰኘው ምዕራፋቸው ያነሱት ነጥብ እዚህ ላይ ይነሳል፡፡

‹‹የጫማ ፋብሪካ የሚጠይቀው የአቅርቦት መጠን እራሱ ካለው የአቅርቦት አቅም በላይ ከሆነ፣ እሱን መሰል ከሆኑ ሌሎች ፋብሪካዎች ጋር በመተባበር የተጠየቀውን የአቅርቦት መጠን ማሟላት ይችላል፡፡ ተመሳሳይ ድርጅቶች በጋራ ሆነው መሥራት፣ ሲያስፈልግም ደግሞ እርስ በርስ መወዳደራቸው ክላስተሪንግ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህን ክላስተሪንግ የተሰኘ ጽንሰ ሐሳብ ማስተማሪያ የሚሆን ምሳሌ ሳስብ እ.ኤ.አ. 2003 የተካሄደው የፓሪሱ የዓለም ሻምፒዮና የ10,000 ሜትር ሩጫ ውድድር ወደ አዕምሮዬ ይመጣል፡፡

‹‹በዚያ ፈታኝና እጅግ እልህ አስጨራሽ ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያኑ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለና ስለሺ ስሕን ተወዳድረዋል፡፡ ሦስቱ ጀግና አትሌቶቻችን ከመነሻው ጀምሮ በመተባበር ሌሎቹን ተወዳዳሪዎች ካዳከሟቸው በኋላ ሦስቱም ብቻቸውን አፈትልከው ወጥተዋል፡፡ ዓለም በአንድ ሳንባ የሚተነፍስ እስኪመስል ድረስ ትንፋሽ አሳጥቶ የነበረው ውድድር ላይ ተነጥለው የወጡት አትሌቶች ቀሪው ሥራቸው እርስ በርስ መወዳደር ነበር፡፡ እናም ሦስቱ ብርቱዎች እርስ በርስ ተፎካክረው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ወጡ፡፡

‹‹እነዚህ ጀግኖች ተመሳሳይ ስልት ተጠቅመው እ.ኤ.አ. 2004 በአቴና ኦሊምፒክ ከዚያም እ.ኤ.አ. 2008 በቤጂንግ ኦሊምፒክ የ10,000 ሜትር ሩጫ ውድድሮች ላይ በተደጋጋሚ አስደናቂ ውጤት አግኝተዋል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ በመተባበርና በመወዳደር አንፀባራቂ ድል ማስመዝገብ፡፡ ኢንዱስትሪዎቻችንም አንዱ ብቻውን አከናውኖ ማቅረብ የማይችለውን በመተባበር ቢሠሩ በድል አድራጊነት መወጣት ይችላሉ፡፡››

-----------------------------------------------------

SOURCE :- https://www.ethiopianreporter.com/49545/

                  www.henockyared.com/2016/08/blog-post_20.html

አውደ ሰብ - ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ክፍል - 1 EBC /EthiopianBroadcastingCorporation/


አውደ ሰብ - ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ክፍል - 2


የልቦና ውቅር - በሃገራችን በአስተሳሰብ በአመለካከት እንዴት መለወጥ ይቻላል ከፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ጋር ቆይታ


የንባብ ክሊኒክ - ቆይታ ከፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ጋር ክፍል 1 ESAT


የንባብ ክሊኒክ - ቆይታ ከፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ጋር ክፍል 2 ESAT






No comments:

Post a Comment