ከደራሲያን ዓምባ

Wednesday, October 19, 2022

እረኛዬ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ

 


በቅድሚያ ሦስቱ የኪነት አበባዎች ብዬ የሰየምኳችሁ ቅድስት ይልማ፣ አዜብ ወርቁና ቤዛ ኃይሉ ደራሲነት የሁሉም ተዋንያን ድንቅ ችሎታና ብቃት ለታየበት “እረኛዬ” ተከታታይ ተውኔት ያለኝን አድናቆት ስገልጽ በምሥጋናዬ ውስጥ አገሬና ሕዝባችን እየታዩኝ ነው።

ስለአገራችን ኢትዮጵያና ስለሕዝቧ በርካታ ድምፃውያን፣ ደራሲያን፣ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች፣ ሠዓሊያን፣ ተዋንያን እንደየዘርፋቸው አዚመዋል፣ አንጎራጉረዋል።  ከያኒያን አገሬን ብለው ገጥመዋል፣ ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ አርገዋል፣ ወንዞች ተራሮቿን ዳሰዋል፣ ዓባይን ከብዕራቸው አፍስሰው ስንኝ ቋጥረው አድንቀዋል፣ ኢትዮጵያችንን አንድ መጽሐፍ ከሚገልጸው በላይ በሥዕሎቻቸው ተናግረውላታል።

ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት፣ ወይም ታዋቂ የፖለቲካ ተንታኝ ነን ብለው እንደ አሸን ከሞሉት ምሁራን በእጅጉ በሚያስንቅ ሁኔታ ድምፃውያን ኢትዮጵያን ከፍ አድርገዋታል። የአገር አንድነት እንዳይዛባ በድምፃቸው ጮኸዋል፣ መድረክ ላይ ወጥተው ጀግኖችን ቀስቅሰዋል፣ አወድሰዋል። ታሪክን አዚመዋል፣ ቅርስን አስተዋውቀዋል።

በዚህ ጽሑፌ በቅርቡ የተጠናቀቀው የ“እረኛዬ” ተከታታይ ተውኔት የዜማ ቅላፄ፣ የቅኔ ዘረፋ፣ የመቼት መረጣ፣ የአብሮነት ዜማ፣ የእናትነት አንጀት፣ የሃይማኖት ክብሩ፣ የዘራፊን ምግባሩ፣ ኢትዮጵያዊነት ክብሩ፣ ደግነቱ፣ አብሮነትን፣ ይቅር ባይነትን፣ የትውልድ፣ የታሪክ፣ የአገር፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የሰው በሰው ሥራ ሌላም ሌላ እውነትን አፍክቶ፣ ማንነትን አውጥቶ፣ ስሜትን ገዝቶ ከመደነቅ አሻግሮ ዛሬም ትውልድ አለ፣ ዛሬም ነገም አገር አለች፣ ያስባለኝን ውስጤን በመጠኑም ቢሆን ለአንባቢያን ላጋራ ፈለግሁ።


“እረኛዬ” አሸንፏል! በዘርና በቋንቋ በተከለለች አገር ዘረኝነት ላይ ዘምቷል፣ በሙስና በተጨማለቀች አገር ሌብነትን አጋልጧል፣ አኩሪ ባህሉን እንዲዘነጋ በተደረገ ትውልድ ላይ “ባህሌን አገሬን” አዚሟል፡፡ በጥላቻ፣ በቂም ላይ ፍቅርን፣ ይቅር ባይነትን ሰብኳል፡፡ በትዳር ውስጥ የእናት ሆድ ዥንጉርጉርነትን ተንተርሶ የእናትነት መንሰፍሰፍን ዳሷል። ሌላም ሌላ፡፡ ከደራሲያኑ ብጀምር የሴቶችን ጠንካራ አመራር ሰጪነትና ኅብረት “እረኛዬ” ይመሰክራል። ዛሬ አንዱ ለአንዱ ምቀኛና ቀናተኛ በሆነበት አገራችን በጋራ ሠርተው የጋር ፍሬያቸውን በጋራ እንድንመለከት፣ እንድንመሰጥ፣ እንድንገረም፣ እንድናለቅስና እድንጓጓ እያደረገ የተጓዘ ተውኔት ነበር ብል አብዛኞች ይጋሩኛልና ልክ ነኝ።

“እረኛዬ” ኪነት ለአገር፣ ኪነት ለኢትዮጵያ፣ ኪነት ለሕዝብ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው ከአንድ የፖለቲካ ፓርቲ በላይ ሥር የሰደደ መልዕክት የተላለፈበት ተውኔት ነው። “እረኛዬ” በጨለማ ውስጥ የደመቀ ኮከብ ነው። ደምቆም አላቆመም ተወርዋሪ ሆኖ ሕዝብ ጋ ደርሷል።    

“እረኛዬ” በአብነት መንደር ኢትዮጵያዊነትን ረጭቶ በእማማ ቸርነት ጎጆ መማር ለፈለገ ትህትናን፣ ቀናነትን፣ አብሮነትን አስተምሮ የተጓዘ ተውኔት ነው፡፡ ወግን፣ ጥጋብን፣ ጥበብን፣ ፍቅርን፣ እንባን፣ ዝላይን፣ ጭፈራን፣ ታዛዥነት፣ ትህትናን፣ በእናና አጋጅነት ተሰባስበው የተረጩበት ተውኔት ጎልቶ የታየበት ተመልካችን ያስደመመ ሁሉም ዘር ዓይንና ጆሮ የሰጠው ተውኔት ደራሲያኑንና ከኒያኑን በጥቅሉ በ“እረኛዬ” ላይ አሻራቸውን ላሳረፉ ሁሉ ደስ….ስ ስላለኝ አመሠግናለሁ።

በዚህ አጋጣሚ ስለአገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ድምፃውያን አድምቀው አንጎራጉረዋል። ሁሉንም ባይሆን ስሜቴን ከኮረኮሩት ውስጥ ትንሽ ልበልና ላስታውሳቸው፡፡ ዛሬ ከመድረኩ ራቅ ብትልም ሕወሓት/ኢሕአዴግ “ጉሮ ወሸባዬ” ብሎ የዛሬ 31 ዓመት ይዞት የተነሳውን ዘረኝነት ገና ከጅምሩ ‹‹የዘር በሽታ፣ መድኃኒት አለው የማታ ማታ›› ብላ አንጎራጉራ የፍቅር ረሃቧን ለአየር ያበቃችው ጂጂ እምቅ ሥራዎችን መለስ ብዬ እንድቃኝ አድርጎኛል። ‹‹ጎጃም ያረሰውን ወለጋ ካልሸጠ፣ የሸዋ ሰው ልጁን ለትግሬ ካልሰጠ›› ምኑን አገር አለች አገርስ ያሰኛል፡፡ ብላ ቀደምት ሙግቷን ለአገር ያበረከተችው ሥራዋ ዛሬም ነገም ሲታወስ ይኖራል።

ለዓባይ ያላዜመ ድምፃዊ ባይኖርም ስለዓባይ ሲጻፍ፣ ሲተረክ ለአገሩና ለሕዝቡ አገልጋይ ይሆን ዘንድ “ዓባይ ወቶ አዳሪ…” ብላ ዘለዓለማዊ ድምጿን ከሕዝብ አድርሳለች። የስደት ሕይወትን ከአገሯ ባህል ጋር ስትገልጸው በአጭር አገራዊ አገላለጽ “የሰው በግ እያየሁ…” ስትል ቅኔዋን ዘርፋለች። ዛሬ እምን ሁኔታ ላይ እንዳለች ባላውቅም ጂጂ ብልጭ ብላ ድርግም ያለችብኝ አገርን በፍቅር፣ ባህላችንን በወግ አላስነካ ያለች ጎበዝ “ስንት በሠራች” ቁጭት ይወረኛል። “አልወድም ጎበዝ ጀግና ሲረሳ” ብላ ለጀግኖቻችን እስትንፋስ የሰጠች ኪነት ለኢትዮጵያ ያበረከተች፣ ኢትዮጵያዊነት መሠረት ውሉ እንዳይበጠስ አጥብቃ የተውረገረገች ዜመኛ ሥራዋ ሁሌም ይጠራታል።

ወያኔ/ሕወሓት ሕዝብ ሆነበትና ባይገድለውም የምሬት ዳርቻቸው ለእስር የዳረገው የኢትዮጵያ ልጅ ቴዲ አፍሮ ዕውን ማን እንደ እሱ ለአገር ሞገተ? ማን እንደ እሱ ስለአንድነት ሰበከ? ማን እንደ እሱ ኢትዮጵያዊነትን አነቃነቀ? ማን እንደ እሱ ምኒልክ፣ ቴዎድሮስ ላይ ስቅታ ለቀቀ ቢባልለት ሲያንሰው ነው።

የዛሬ 17 ዓመት ከ1997 ዓ.ም. የምርጫ ዋዜማ ለአየር በቅቶ ፖለቲከኞቻችን ገደል ቢከቱትም፣ ምርጫው በድል ይጠናቀቅ ዘንድ ፊት ለፊት የተጋፈጠው “ያስተሰርያል” ዜማው አንድነትን ፈጥሯል፣ ሕዝባዊነትን አቀናጅቷል፣ ፍቅርን አንግሷል፣ ወያኔን አርበድብዷል፣ ኢሕአዴግን ዘርሯል። ፖለቲከኞቻችንና ምሁሮቻችን መጠቀም አቃታቸው እንጂ ኦሮሞን፣ ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከጉራጌ፣ ከጋምቤላ፣ ከሐረሪ፣ ከወላይታ፣ ከሲዳማ ሁሉን ኢትዮጵያዊ እጅ ለእጅ ያያያዘ ነበር። “ይቅር እንባባል” ብሎ ፍቅርን የሰበከ፣ ማማዬ፣ ኢትዮጵያዬ ብሎ መድረክ ላይ የተፋለመ፣ በሚሊዮኖች ያነቃነቀ ፖለቲካውን በዜማ ቅላጼው የተቆጣጠረ ብርቅዬ ነበር ዛሬም ነው። 

የቴዲ ሥራዎች በተለይ በወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያዊነት እንዳይሳሳ፣ ሰንደቅ ዓላማ እንዳይረሳ፣ ጀግኖች እንዳይደበዝዙ፣ አዚሟል “ኡ ኡ ታዬ” ብሎ እሪ ብሏል። ምኒልክን አንግሦ፣ ቴዎድሮስን አሞግሶ ትውልድን ቀስቅሷል፣ አነቃቅቷል። እስላም ክርስቲያኑን አንድ ነው ቤታችን ብሎ አስተቃቅፏል። ፍቅርን፣ ይቅርታን፣ አንድነትን፣ ኅብረትን በጠነከረ ዜማው ከሕዝብ አዋህዷል። ኢትዮጵያዬ ብሎ ኢትዮጵያዊነትን አሳይቷል። ዘመን ከፈጠራቸው የትውልድ ጀግና፣ አዋጊ ዜመኛ፣ ድምፃዊ ፓርቲ ቢባል ይገባዋል። 

“እረኛዬ”  ወደ ሌላ ተዛማጅ ጉዳዮች ቢወስደኝም አንኳሩ ኪነት ምን ያህል ለአገር፣ ለሕዝብ፣ ለትውልድ ያላትን እምቅ ችሎታ ለማስመር ነው። የ“እረኛዬ” አባላትንም ሆነ ሌሎች ባለሙያዎች ሌላም የፈጠራ ሥራዎቻችሁን አሳዩን እያልኩኝ፣ የምሥጋና ድምፄን በአንድ ቃልና በአራት ነጥብ ላብቃ። በርቱ።

በነሲቡ ስብሐት

https://www.ethiopianreporter.com/110256/

ባህልን በምልዓት ያንፀባረቀው ‹‹እረኛዬ››


የኢትዮጵያ ባህል፣ እሴት፣ ወግና ሌሎች ነገሮች ተካተውበት ከተሠሩ ተከታታይ ድራማዎች መካከል ‹‹እረኛዬ›› ይጠቀሳል፡፡

ይኼው በሳምንት ሦስት ቀናት በአርትስ ቲቪ ለሕዝብ ይተላለፍ የነበረው ተከታታይ ድራማ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነትና ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡ ድራማው እንዲወደድ ካደረጓቸው ነገሮች መካከል የቦታ አመራረጥ፣ አቀራረፁ፣ ተዋናዮቹ፣ ድርሰቱ፣ የቪዲዮ ጥራትና በብዙ ማኅበረሰቦች ውስጥ ያለውን አገራዊ ይዘት ያለው በመሆኑ ነው የሚሉ አልታጡም፡፡

እረኛዬ ድራማ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ብቅ ካሉ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች አንዱ ነው፡፡ ከወረርሽኙ በኋላ የፊልም ኢንዱስትሪው እየተነቃቃ እንደሚገኝ፣ እነዚህ መነቃቃቶች ከታዩባቸው መካከል እረኛዬ አንዱ መሆኑንና የድራማው ደራሲዎች ደግሞ ሦስቱም ሴቶች (ቤዛ ኃይሉ፣ ቅድስት ይልማና አዜብ ወርቁ) መሆናቸው ድራማውን ይበልጥ አጉልቶታል፡፡

በዚህ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ለረዥም ዓመታት ከቴሌቪዥን መስኮት የጠፉ ዕውቅ አርቲስቶች ብቅ ያሉበት በመሆኑም ለየት ያደርገዋል፡፡

በድራማውም መሉዓለም ታደሰ፣ ሳያት ደምሴ፣ ድርብ ወርቅ ሰይፉ፣ ቃል ኪዳን ጥበቡ፣ አበበ ተምትምና ሰለሞን ቦጋለን ጨምሮ በርካታ አዲስና ነባር ተዋናዮች ተሳትፈውበታል፡፡

በአርትስ ቴሌቪዥን ሲቀርብ የነበረው እረኛዬ ድራማ ለሦስት ተከታታይ ምዕራፍ ለዕይታ ቀርቦ መቋረጡ ይታወሳል፡፡ በግንቦት መጨረሻና ሰኔ መጀመርያ ይጀመራል የተባለውን የቴሌቪዥን ድራማ በተመለከተ፣ ቅዳሜ ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ቅጥር ግቢ ውስጥ የድራማው ተዋናዮች፣ ደራሲዎቹና ታዳሚዎች በተገኙበት የፓናል ውይይት ተካሄዷል፡፡ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነ ጥበብ ማዕከል ባዘጋጀው መድረክ በተውኔቱ ላይ ሙያዊ ዳሰሳ ያቀረቡት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ሰለሞን ተሾመ (ዶ/ር)፣ የእረኛዬ ድራማ ከባህል አንፃር እንዴት ይታያል የሚለውን ሁኔታ በአምስት ነገሮች በመከፋፈል አቅርበውታል፡፡

የእረኛዬ ድራማ የገጸ ባህርይ አሣሣል፣ የቦታ መረጣ፣ ርዕስ፣ በድራማ ውስጥ ያለው ይዘትና አጠቃላይ የቀረበበት መንፈስ ምን ይመስላል የሚለውን ማየታቸውን የተናገሩት ሰለሞን (ዶ/ር) ከዚህ አንፃርም ‹‹የተዋጣለት ድራማ›› መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በትንታኔያቸውም እንዳከሉት፣ ‹‹ይህ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ የታሪክ አወቃቀሩ፣ የገጸ ባህሪዎቹ አመራረጥ፣ የትወና ብቃት፣ የቦታ አመራረጥ፣ ዳይሬክቲንግና ቀረፃው የሙያውን ደረጃ ከፍ ያደረገና አገራዊውን የፊልም ገጽታ የቀየረ ነው፡፡››

የእረኛዬ ድራማ ዋናው ጭብጥ ‹‹የኢትዮጵያን ችግር በኢትዮጵያ ባህል እንፍታ›› የሚል እንደነበር፣ ድራማው በሚቀረፅበት ወቅት የተመረጡት ቦታዎችና ተዋናዮቹ ብቃት ብርሃን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል፡፡

በድራማው ውስጥ የተለያዩ ተፋላሚ ኃይሎች፣ በተቃራኒ ጎራ፣ በተቃራኒ ሐሳብ፣ በተቃራኒ ፍላጎት ተወዳድረው ሲፋተጉና ሲጋጩ እንደሚታዩ፣ ይህም የሚያሳየው የእኛነት ስሜትን ያንፀባርቃል ሲሉ ሰለሞን (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

በድራማው ውስጥ የነበሩ ተቃርኖዎች ቅንነትን በእማማ ቸርነት፣ በዳዊትና በእናና፣ አለመታመንን በጣሰው ላይ የታየ ሲሆን፣ ባለቤትና ባይተዋርነት ፍቅርና ጥላቻን ያሳያል የሚሉት ዶ/ር ሰለሞን፣ በተፈለገው ልክ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ በድራማው ላይ ማየት ተችሏል፡፡

በተለይም በእንጉርጉሮ መልክ የሚቀርቡ መልዕክቶች ልብ ይነኩ እንደነበር፣ የተስፋና የተስፋ ቢስነት ግጭትን የሚያሳይ መሆኑን በዳዊትና በጣሰው ገጸ ባህርያት ላይ ማየት እንደተቻለ አክለዋል፡፡

ድራማው የተጀመረ ሰሞን የነበረው የገጸ ባህርይ ሁኔታ መተሳሰብና መቻቻልን የሚያሳይ ነው የሚሉት ሰለሞን (ዶ/ር)፣ ድራማውም በአጠቃላይ ኋላቀር የሆነ የፖለቲካ ባህልን እንደሚያንፀባርቅ፣ ዓብይ ትግሉም ከኋላቀር የፖለቲካ አስተሳሰብ ተላቅቆ ወደ ሠለጠነ አስተሳሰብ የሚደረግ የሽግግር ሒደትን ይጠቁማል ብለዋል፡፡

የእረኛዬ ድራማ ርዕስ ‹‹እግዚአብሔር እረኛዬ ነው›› ከሚለው መዝሙራ ዳዊት ክፍል የተወሰደ መሆኑን የተናገሩት የድራማው ደራሲ ወ/ሮ ቅድስት ይልማ ናቸው፡፡

የእረኛዬ ድራማ ከጽሑፍ ጀምሮ ወደ ዕይታ ለማምጣት አምስት ዓመታት እንደፈጀ፣ አብዛኛውን የድራማው ጭብጥ አንድ ኢትዮጵያን ያሳየ ነውም ብለዋል፡፡

በድራማውም የነበሩ ይዘቶች መልካምነትን የሚያንፀባርቁ፣ በተቃራኒው ደግሞ ጥላቻን የሚፈጥሩ ታሪኮችን የያዘ እንደነበር ገልጸው፣ የድራማው ጥንስስ የኢትዮጵያን ትውፊቶችን የሚያሳይ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የድራማው አዘጋጅና ደራሲ ቅድስት ይልማና ደራሲዎቹ አዜብ ወርቁና ቤዛ ኃይሉ ድራማው የኢትዮጵያን ባህል፣ ሥነ ልቦና፣ ትውፊቶችንና እሴቶችን የተላበሰና ሳቢ እንዲሆን በማድረግ ትውልድን ከባህል ብረዛና ከማንነት ቀውስ ለመታደግ ታልሞ እንደተሠራ ገልጸዋል።

በአብዛኛው ደራሲዎች ፊልሞች ላይ ሴቶችን ሲመድቡ (ካስት ሲያደርጉ) የግድ ቆንጆ መሆን አለባት የሚል እምነት እንዳላቸው፣ በእረኛዬ ድራማ ላይ ግን ይህንን ችግር በማስወገድ ለድራማው የሚሆኑ ተዋናዮች ተመርጠው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጋቸውን ደራሲዎቹ አብራርተዋል፡፡


እረኛዬ ከመጽሐፍ ይልቅ በድራማ እንዲቀርብ የተደረገው፣ አብዛኛውን ጊዜም የፊልም ኢንዱስትሪው በቃና የታበጀ በመሆኑና የተከታታይ ድራማን መንፈስ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት በማለም መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የእረኛዬ ድራማ ዋናው ዓላማ ትንሿን ኢትዮጵያ መፍጠር እንደሆነ፣ በድራማው ከዚህ ቀደም የነበሩ የመተሳሰብን፣ አብሮ የመብላት መንፈስን በመገንባት ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ገጽታ ለማሻሻል የታሰበ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የእረኛዬ ድራማ ላይ የተሳተፉ ተዋናዮች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጡ እንደሆነ፣ በአሁኑ ወቅትም በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት እንደተቻለ በወቅቱ ተገልጿል፡፡

በቴሌቪዥን ድራማው አብዬ በቃሉን ሆነው የተወኑት የ‹‹የወዲያነሽ›› እና ‹‹ጉንጉን›› ተወዳጅ ልብ ወለዶቻቸውና ‹‹እንካ ሰላምቲያ›› በተሰኘው ድርሰታቸው የሚታወቁት ኃይለ መለኮት መዋዕል፣ እማማ ቸርነትን ሆና የተወነችው ድርብ ወርቅ ሰይፉ በድራማው ላይ ስለነበራቸው ተሳትፎ አብራርተዋል።

የመድረኩ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት ድራማው የበርካታ ተመልካቾችን ቀልብ የሳበ፣ በትርጉም ከሚቀርቡ የውጭ አገር ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ዓይናችንን ወደ አገርኛ የመለሰ ተከታታይ ድራማ ነው ሲሉ አሞካሽተውታል። ድራማው ከሰፊ ማኅበራዊ ጠቀሜታው ባሻገር ጉልህ ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዳለውም ተጠቁሟል።

የድራማው ተከታታይ ክፍሎች መቼ እንደሚጀምሩ ከታዳሚዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ ደራሲና ዳይሬክተሯ ቅድስት ይልማ በሰጡት ምላሽ፣ የቀጣይ ክፍሎች ቀረፃ ተጠናቆ ቅንብር ላይ እንደሚገኝና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለዕይታ እንደሚበቃ አሳውቀዋል።

ተመስገን ተጋፋው

https://www.ethiopianreporter.com/82463/

እረኛዬ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማን እንዲወደድ ያደረጉ ምክንያቶች


እረኛዬ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በአርትስ ቴሌቭዥን በአራት ምዕራፎች በ48 ክፍሎች ሲተላለፍ ቆይቶ አርብ ነሐሴ 13/2014 ዓ.ም. ተጠናቋል።

ይህ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በአዜብ ወርቁ፣ በቤዛ ኃይሉ እንዲሁም በቅድስት ይልማ የተጻፈ ሲሆን፣ ያዘጋጀችው ደግሞ ከደራሲዎቹ መካከል አንዷ የሆነችው ቅድስት ይልማ ነች።

እነዚህ ሦሰት ደራሲያን ለፊልም ጽሁፍ እንዲሁም ዝግጅት እንግዳ አይደሉም። በስማቸው በርከት ያሉ ሥራዎች ሰፍረው ይገኛሉ።

በጥምረት ግን ሲሰሩ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

እረኛዬ ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ መቼቱን ያደረገው ከከተማ ግርግር ርቆ፣ ሕይወት ስክን ብላ በምትፈስበት ገጠር ውስጥ ነው።

ይህ አብነት የተሰኘ የገጠር መንደር በምናብ የተፈጠረ ነው።

ይህች የገጠር መንደር ኢትዮጵያን እንድትመስል ተደርጋ ነው የተሳለችው።

በዚህ መንደር በፍቅር ተሳስበው የሚኖሩ ዘመዳሞች እና ጎረቤታሞች ፍቅራቸውን የሚነቀንቅ ተቀናቃኝ መጥቶባቸዋል።

ይህ ተቀናቃኝ ባለሀብት ነው።

በሀብቱ ብዛት መሬታቸውን ሊነጥቅ የቋመጠ፣ ለዚህም በቀኝ በግራው፣ በፊት በኋላው ግለሰቦችን ያሰለፈ ነው።

ይህ ባለሀብት የሚነጥቃቸው መሬት ይምሰል እንጂ ከመሬቱ ጋር የተሰፋ ማንነት፣ ባሕል እና ትውፊት አብሮ አለ።

የአብነት መንደር ነዋሪዎች ይህንን የኖረ ባሕላቸውን፣ ማንነታቸውን ለመከላከል በገበሬ አቅማቸው ይውተረትራሉ።

በድራማው የመጀመሪያ ክፍል ላይ የምናያቸው እና በኋላም በታሪኩ ውስጥ በተደጋጋሚ በአርዓያ ሰብነት የሚጠቀሱት አብዬ በቃሉ ከአካባቢው ሁሉ የተለዩ ግለሰብ ነበሩ።

መለየታቸው ለመልካም ነው። ሕብረት ይወዳሉ፤ ድንበር አይፈልጉም። አገራዊ እውቀቶች ከአንዱ ሰው ወደ ሌለው እንዲተላለፉ አጥብቀው ይሻሉ። ለእርሱም ትምህርት ቤት ከፍተው የአብነትን ነዋሪዎች ያስተምሩ ነበር።

ነገር ግን ልጃቸው ከጋብቻ ውጪ አርግዛ የሠርጓ ዕለት በመውለዷ በድንጋጤ ሕይወታቸው አለፈ።

አገሬው ጉድ አለ፤ የአቶ በቃሉ ሕልም ተዳፈነ። ቤተሰቡ አንገቱን ደፋ። ልጃቸው ወጋየሁም ጨርቄን ማቄን ሳትል ሌሊቱን ማንም ወደማያውቃት አገር ተሰደደች።

የአብነት መንደር ወግ ባሕል ልማድ የተጣሰው ዋነኛ ተቆርቋሪ በሆኑት አብዬ በቃሉ ልጅ፣ ወጋየሁ ነው።

በኋላ ግን የጠፋው ወግ ባሕል ልማድ በእርሳቸው የልጅ ልጅ እንደ አዲስ ሲያንሰራራ እንመለከታለን።

በአንድ ማህጸን ያደሩት ዳዊት እና መንግሥቱ በተለያዩ ወላጆቻቸው እጅ ማደጋቸው፣ የተለያየ ባሕርይ እና ማንነት ሰጥቷቸው የማይግባቡ ዥንጉርጉሮች አድርጓቸዋል።

ያደሩበት ማህፀን፣ ተካፍለው የጠቡት ጡት ያቆየላቸው እንጥፍጣፊ ፍቅር ያለ አይመስልም።

እረኛዬ በእነዚህ ገፀ ባሕሪያት በኩል የአገርኛ እውቀቶች እንዲያብቡ፣ ባሕል ወግ ልማድ እንዳይጣስ፣ ፍቅር ይቅርታ የኑሮ አምድ እንዲሆኑ ደጋግሞ ይወተውታል።

በበርካቶች ዘንድ ትኩረትን ያገኘው ለዚህ ይሆን? ድራማውን የተከታተሉ ሁለት ግለሰቦች አነጋግረናል።

ገሸሽ ያደረግነውን ማንነት ፍለጋ

በእረኛዬ ድራማ ላይ የምናያቸው የማምረቻ መሳሪያዎቹ፣ አልባሳቱና ጌጣጌጦቹ፣ ወዘተ የራሳቸው የሆነ ቱባ ሥነ ውበታዊ ገጽታ አላቸው።

በአሰራራቸው የአገርኛ ጥበብ አሻራ ታትሞባቸው ይገኛል።

በድራማው ላይ የሚታዩት የሰላምታ ልውውጦች፣ የግብይት ልማዶች፣ የጋብቻ ሥርዓቶች፣ የአምልኮ ትውፊቶች፣ የለቅሶ ልማድ ሁሉ የየራሳቸው ውበትና መስህብ እንዲኖራቸው ተመልካችን እንዲያማልሉ ሆነው ተቀርፀዋል።

በድራማው ላይ በእረኞች እና በኮማሪቷ ማስረሻ፣ የሚገጠሙ ግጥሞች የማኅበረሰቡን ማንነትና ስሜት ከማንጸባረቅ ትይዩ የቆሙ፣ ሥነ ጽሑፋዊ ቴክኒክ ተላብሰው የቀርቡ ናቸው።

ይህም የማዝናናት ለዛቸውን አጉልቶ፣ አይረሴና ተጨባጭ አድርጓቸዋል።

ድራማው አካብቶ ያቀርብልን የማኅበረሰቡ ጠቅላላ የተሞክሮ ዕውነታ ባሕላዊ ማንነትን የሚያጎሉ ቅርሶች የተዝናኖት ፋይዳ ጨምረውለታል።

የደራሲዎቹ የተጠባቢነት አቅም ልኩ የሚመዘነው ደግሞ እነዚህን አጣጥሞ በማቅረብ ብቃቱ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የባላገሩ ቴሌቪዥን የፕሮግራም ዳይሬክተር የሆነው ሲራክ ተመስገን ይናገራል።

የትያትር እና የፊልም መምህር የሆነው አንተነህ ሠይፉ በበኩሉ እረኛዬን የወደድንበትን ምክንያት ሲያነሳ አስቀድሞ የሚጠቅሰው መቼቱን ነው።

በኢትዮጵያ የፊልም እና የተከታታይ ድራማ ታሪክ መቼታቸውን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያደረጉ ሥራዎች በቀላሉ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እና ተወዳጅነት ማግኘታቸውን በማንሳት እረኛዬም ይህ እንደረዳው ይገልጻል።

የዚህ ተከታታይ ድራማ ደራሲና አዘጋጅ የሆነችው ቅድስት ይልማ ቀዳሚ ሥራ የሆነው ‘ረቡኒ’ን በምሳሌነት ያነሳው አንተነህ፣ በተመሳሳይ መልኩ መቼቱን ገጠር በማድረጉ ተወዳጅነትን አትርፎ እንደነበር ያስታውሳል።

አንተነህም ሆነ ሲራክ፣ እረኛዬ ተከታታይ ድራማ፣ ያነሳው ታሪክ ወደ ጥንታዊ ማንነት፣ ገሸሽ ወዳደረግናቸው ባሕላዊ እሴቶቻችን መመልከቱ በተመልካች ዘንድ ተወዳጅነት ለማግኘቱ አስተዋጽኦ ማድረጉ ላይ ይስማማሉ።

አክለውም ታሪኩ የተዋቀረበት እና ገጸ ባህሪያቱ የመጡበት ዓለም፣ ከማኅበራዊ ከሌሎች እሴቶቻችን ጋር መሳ ለመሳ መሆኑ ተቀባይነት ለማግኘት አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይናገራሉ።

ዳይሬክተሯም ገጸ ባህሪያቱ የተቀዱበት ማኅበረሰብን ማንነት ለማጉላት የተጠቀመችባቸው ነባር እሴቶችም አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አንተነህ አክሎ ይገልጻል።

ኢትዮጵያ ያለችበት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ



እረኛዬ ድራማ በአገሪቱ ካለው እውናዊ ሕይወት በትይዩ ይሳል እንጂ፣ የማኅበረሰቡን ስምና አድራሻ በቅጂነት ከነምግባሩ አያነሳም።

ገጸ ባህሪያቱ በምናብ በተፈጠረ መንደር፣ አብነት፣ ልቦለዳዊ ኑሯቸውን መስርተዋል።

የማኅበረሰቡን ኑሮ አይኑሩ እንጂ፣ ለኑሮው መስታወት ሆነው የራሱ የዕለት ተለት ገመና መልሶ እንዲመለከት አድርገውናል።

በድራማው ውስጥ የማኅበረሰቡን እንከን፣ ሠላም የማጣት፣ የመናቆር፣ ይቅር ማለት አለመቻል ፍጥጥ ብሎ እንዲታይ አድርጓል።

ለዚህም እንቆቅልሽ ብሎ በመጠየቅ ከራስ መልስ እንደመጠየቅ አይነት ነው።

ደራሲዎቹ በገጸ ባህርያቱ ሕይወት በኩል እንቆቅልሽ ብለው ይጠይቃሉ። ተመልካቹም ፍንጮቹን እየተከተለ የሕይወትን እንቆቅልሽ የመፍታት ድርሻን ይወስዳል።

አንተነህ ይህንን ሃሳብ ሲያጠናክር “ወቅቱን የሚገልፁ፣ ሰዉ ልብ ውስጥ ያለውን፣ በአደባባይ መተንፈስ መናገር የማይችለውን ነገር በድራማ መልክ ስለማንነታችን፣ ስለ እርስ በእርስ ግንኙነታችን ስለአናኗራችን አሁን ስላለው ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ በጥሩም ይሁን በመጥፎ ያነሳሳል” ይላል።

ላለው ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ጥያቄ ነው ያለውን ድራማው ያነሳል፤ እንደ ታምራት ገለፃ መልስ ነው መፍትሔ ይሆናል ያለውንም እዚያው ይጠቁማል፤ ይመልሳል።

ሲራክም ሆነ አንተነህ በድራማው በኩል የራሳችን ገበና፣ ከአደባባይ ርቀን በማጀታችን የምናወራው ነገር ሲቀርብልን፣ መተንፈሻ ፉካ ሆኖን በማገልገል ተወዳጅነትን አትርፏል ይላሉ።

ሲራክ አክሎም ዳይሬክተሯ ቅድስት አገሪቷ ያሉባትን ችግሮች፣ አገር በቀል በሆነ እውቀት ውስጥ መፍትሔ መፈለግን እንደ ስልት ይዛዋለች ይላል።


ጀግኒት ፀሐፊያን እና አዘጋጅ

የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ የወንዶች ዓለም ነው በሚለው ሀሳብ አንተነህና ሲራክ ይስማማሉ።

አብዛኞቹ ታሪክ ነጋሪዎችና ፀሐፊዎች ወንዶች በመሆናቸው በወንድ ዐይን ነው ዓለሙን የሚያሳዩን ይላል አንተነህ።

የምንኖረውን የአባታዊ ሥርዓት፣ በምንታደመው የጥበብ መድረክ ላይም የምናየው ሕይወት የወንዶች ምናብ ውጤት ነው በማለት ያክላል ሲራክ።

“ዓለሙን፣ ሕይወትን፣ አገርን የሚተረጉሙት በወንድ መነጽር ነው” ይላል አንተነህ።

የእረኛዬ ደራሲዎች ግን ከዚህ ተቃራኒ ዕድል ነበራቸው።

እንዲህ ሴቶች በድርሰትም በዝግጅትም ሰብሰብ ብለው መምጣታቸው እንደ እረኛዬ አይነት በሥርዓተ ጾታ ላይ ጥንቁቅ የሆነ ድራማ እንድናገኝ ረድቶናል ይላል ሲራክ።

ለዚህም ነው የእረኛዬ ሴት ገጸባህሪያት የድራማው ደምና አጥንት ሆነው ነው የተሳሉት።

የአብነት መንደር ሕይወት በጫንቃቸው ነው። የአብዬ በቃሉ አደራ በደም ሥራቸው ይፈሳል።

የትምህርት ቤት ደጃፍ ባይረግጡም፣ የፊደል ዘር ባይለዩም ሕይወትን፣ በዙሪያቸው የተንሰራፋውን ዓለም በገባቸው ልክ የሚተረጉሙ እና እርሱንም አጽንቶ ለማቆም የሚታገሉ ናቸው።

የእረኛዬ ሴት ገጸ ባህሪያት ለከተማ ሕይወት ባዳ ሆነው፣ የቀለም ዘር ሳይለዩ ለመብታቸው የሚቆሙ ናቸው የሚለው ደግሞ አንተነህ ነው።

በዚህ ሃሳብ ሲራክም ይስማማል። “በእረኛዬ ድራማ ላይ ልፍስፍስ ሴት አትታይም፤ ከወንዶች እኩል የምትገዳደር ሴት እናገኛለን” ሲል ያክላል።

አንተነህ ሲያክልበት ደግሞ “ለእህቷ ለጓደኛዋ መብት የምትቆም ሴት. . .ልጆቿን ሕልውናዋን ለመመለስ የምትታገል ሴት. . .ቤቷን ብቻ ሳይሆን አካባቢዋን አጽንቶ ለማቆም የምትታገል እናት” ማየታችን በሴት ደራሲያን የመጻፉ ትሩፋት መሆኑን ያስረዳል።

የድራማው ደራሲያን ሴት መሆናቸው ወንዶች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሲጽፉ የሚያጎዱሉት ነገር ቁጭት እና እልህ አለባቸው የሚለው አንተነህ፣ ጠንካራ ሴት ገጸ ባህሪያትን በመሳል ረገድ እንደተዋጣላቸው ይመሰክራል።

ደራሲያኑ እንዲሁም ዳይሬክተሯ ሴቶች መሆናቸው “ለሚገባቸው ሚና የሚታመኑ ጠንካራ ገጸ ባህሪያትን” ጠንካራ ሴቶች እንድናይ አድርጎናል ሲል ይገልጻል።

የእረኛዬ ሴት ገጸ ባህሪያት ከእነርሱ ሕይወት ይልቅ የሚኖሩበት ማኅበረሰብ ሕልውና ያሳስባቸዋል።

በዋና ገጸ ባህሪይነት የተሳሉት ሴቶች ሁሉ ከራሳቸው በላይ ሰንደቅ ሆኖ የሚውለበለብ ዓላማ አላቸው።

የእናና ገጸ ባህሪ ደግሞ ለሞቷ ሰበብ የሆነውን የጥቅም ፈላጊዎች ጠብ፣ ለመኖሪያ ቀዬዋ ነዋሪዎች ቀጣይ የጠብ ጥንስስ መነሻ እንዳይሆን በመመሸግ፣ መስዋዕት እስከመሆን ትደርሳለች።

ጎምቱ እና ተወዳጅ ተዋንያን መሳተፋቸው



በእረኛዬ ድራማ ላይ የተሳተፉት ተዋንያንም ቢሆኑ ስምና ዝና ያላቸው፣ ክህሎትም ቢሆን ጠንቅቀው የተካኑ መሆናቸው ለተወዳጅነቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን አንተነህ እና ሲራክ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።

“ከእረኛዬ ድራማ የተመቸኝ አንድ ነገር ቢኖር ገጸ ባህሪ አሳሳሉ እና ተዋናይ መረጣው ነው” ይላል ሲራክ።

እረኛዬ ድረማ “የደርቢ ስብስብ ይመስላል” የሚለው ደግሞ አንተነህ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በድራማው ላይ ወሳኝ ስፍራ የያዙት ተዋንያን ስምም ዝናም ያላቸው መሆናቸውን ነው።

በእርግጥ በድራማው ላይ አዳዲስ ፊቶች የታዩ ቢሆንም እንደ አበበ ባልቻ፣ ሙሉዓለም ታደሰ፣ ድርብ ወርቅ ሠይፉ፣ ሳያት ደምሴ፣ ኩራባቸው ደነቀ፣ አማኑኤል ሐብታሙ፣ ቃልኪዳን ጥበቡ እንዲሁም ሠለሞን ቦጋለ ያሉ ተዋንያንን ማሳተፉ አድናቂዎቻቸውን ወደ ድራማው በመጥራት ረገድ አስተዋጽኦ ማድረጉን ይጠቅሳል።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ተዋንያኑ የተወከሉበትን ገጸ ባህሪ በሚገባ መጫወታቸው፣ ተደራሲያንን ወደ ታሪኩ ጎትቶ በማስገባት ረገድ የላቀ ሚና እንደነበረው ያነሳል።

ከተለመደው አቀራረብ ወጣ ማለቱ

የእረኛዬ ገጸ ባህሪያት ከሚኖሩበት አብነት መንደር ርቀው አይሄዱም። ወደ ተለያዩ ከተሞች ልጇን ፍለጋ የምትባዝነው ወጋየሁም ብትሆን ትንንሽ የገጠር ከተሞችን ታካልላለች እንጂ ሕንጻ ወደተንጠለለበት ከተማ ጎራ አትልም።

ይህ ግን ተደራሲው ላይ ያጎደለው ነገር የለም። ድራማው የሚያነሳው አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን በየቀኑ የሚውሉበትን፣ የሚወጡ የሚወርዱበትን በመሆኑ በታሪኩ ላይ ጉድለት አልፈጠረም።

እረኛዬ ታሪኩን የመሰረተው ከከተማ ውጪ ያለ ሕይወት ላይ መሆኑ፣ ተመልካቹ ከለመደው ውጪ ነገር ይዞ መቅረቡ ለተወዳጅነቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን አንተነህ ያነሳል።

ይህ የታሪክ አቀራረቡ በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ እንዲሁም ፊልም ከተለመደው ውጪ መሆኑ የራሱ ድርሻ ነበረው።

ሲራክ በበኩሉ በበርካታ የፊልም ባለሙያዎች ዘንድ ኢትዮጵያዊ ፊልም መስራት የሚለው አጀንዳ ሲነሳ እሰማለሁ በማለት ኢትዮጵያዊ ድራማ ማለት ገጠር ውስጥ የሚከወን ብቻ መሆኑ ላይ ጥያቄ ያነሳል።

የእረኛዬ ድራማ በአብነት የገጠር መንደር መኖራቸው፣ ከተማ ጠል መሆናቸው ባይጎረብጠውም ኢትዮጵያዊ ለማድረግ ብቻ ግን ገጠሩን መምረጥ አዋጭ ሃሳብ አለመሆኑን አንስቶ ይሞግታል።

በማጠቃለያውም ላይ ከተሜ ሆኖ ኢትዮጵያዊ ወግ ባሕል የሚታይበት ኑሮ እኮ አለ ሲል ያክላል።

https://www.bbc.com/amharic/articles/cv2l9y818q2o

<ልንለው የምንፈልገው አለን> ከእረኛዬ ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ


No comments:

Post a Comment