ከደራሲያን ዓምባ

Thursday, November 24, 2022

የጃፓን መንገድ

 የጃፓን መንገድ _ እንደ ማንቂያ ደወል


በፍቅር እወዳቸዋለሁ! እጅግ አከብራቸዋለሁ! ፍፁም የተለዩ ህዝቦች ናቸው! ሰለጠኑ ከሚባሉት ምዕራባውያኖቹ ጋር ሲነፃፀሩ በትንሹ 20 ዓመታትን ጥለዋቸው ሄደዋል!
"...ህዝቦቿ ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው የዛሬዋን ሃገራቸውን ገነቡ!" ቢባልላቸው አያንስባቸውም!
ፀዴ ናቸው፣ ስልጡን ናቸው፣ ሰው አክባሪ ናቸው፣ ሃገራቸውን አብዝተው ይወዳሉ ሳይሆን ያፈቅራሉ። ስልጣኔ ማማው ቢታይ ጃፓን ላይ ነው። የህዝብ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም! 126 ሚልዮን ገደማ ናቸው።
ቤትህ አልበላሽ ያለህ "Sony" ቴሌቪዥን የነሱ ነው፣ ያሳደገህ ብረቱ "Hitachi" ፍሪጅ የነሱ እጅ ያረፈበት ነው፣ ሃገራችንን ብቻ ሳይሆን ዓለማችንን ያጥለቀለቀው "Toyota" መኪና የነሱ ጥበብ ውጤት ነው፣ "Nikon" እና "Canon" ካሜራዎች የነሱ አሻራዎች ናቸው፣ እንደዛ በፍቅር የምትወደው "Toshiba" ላፕቶፕህ የነሱ ነው፣ "Mazda", "Lexus", "Mitsubishi", "Honda", "Nissan", "Isuzu", "Suzuki" ምናምን የምትላቸው መኪናዎች የተፈበረኩት በነሱ ነው። እጃቸው የነካው ምርት ሁሉ ብሩክ እና ብረት ነው።
ከሁሉም በላይ የሚደንቀኝ የጃፓናዊያን የስራ ባህል ነው። የእረፍት ትርጉሙ አይገባቸውም! የዓለማችን ረጅም ሰዓታቸውን በስራ ላይ የሚያሳልፉ ዜጎች ጃፓናዊያን ናቸው። በስራ ብዛት የሰው ልጅ የሚሞተው ጃፓን ውስጥ ብቻ ነው! ሞቱን "Karoshi" ብለው ይጠሩታል። በዓመት ካላቸው የ 20 ቀን እረፍት ውስጥ 10 የሚሆነውን እንኳን በአግባቡ አይወስዱም። 63% የሚሆኑ ጃፓናዊያን በእረፍት ሰዓታቸው በሚከፈላቸው ገንዘብ ደስተኛ አይደሉም። ጌታዬ! መንግስት "....የአመት እረፍታችሁን እባካችሁ ውሰዱ! በስራ ብዛት እና ጭንቀት እየሞታችሁ ነው! እስቲ ትንሽ ዘና በሉ!..."ብሎ ሲለምን የምትሰማው የጃፓን መንግስትን ብቻ ነው።
ከለሊቱ 9 ሰዓት ላይ የጃፓን መንገዶችን ብትመለከት ሽክ ብሎ ሱፉን ለብሶ እና "briefcase" ይዞ ወደ ስራ የሚሄድ ብዙ ሰው ታያለህ። አብዛኛው ጃፓናዊ "ለምን ትሰራለህ?" ተብሎ ሲጠየቅ "ሃገሬን ስለምወድ እና ብቁ ዜጋ ሆኜ መገኘት ስላለብኝ!" ብሎ ይመልስልሃል። ያለ እረፍት ከመስራታቸው ብዛት የጃፓን መስሪያ ቤቶች ውስጥ ጠረጴዛቸውን ተደግፈው የሚያንቀላፉ ሰዎችን ማየት የተለመደ ነው። የታታሪነት፣ የብርቱነት እና ሃገር ወዳድነት መገለጫ ነው። ከአጠቃላይ ህዝብ ቁጥሩ ውስጥ 3% የሚሆነው ብቻ ስራ አጥ ሲሆን ሰዎች ስራ ፈትተው በመቀመጣቸው ምክንያት በጭንቀት እራሳቸውን የሚያጠፉባት ሃገር ናት።
ተማሪዎቿ!
ከዓለማችን ብቁ ተማሪዎች ተርታ ይሰለፋሉ። 100% የሚሆነው የሃገሪቷ ወጣቷ በሚገባ ፊደል የቆጠረ እና ቀጥቅጦ የተማረ ነው። ህፃናት ሃገራቸውን እንዲወዱ፣ ቤተሰባቸውን እና ማህበረሰባቸውን እንዲያከብሩ ተድርገው ያድጋሉ! የጃፓን ትምህርት ቤቶች ውስጥ የፅዳት ሰራተኛ አይቀጠርም! "ለምን?" ካልከኝ ከትምህርት በኃላ ሁሉም መምህራን እና ተማሪዎች ለ 15 ደቂቃ ልብሳቸውን ቀይረው ትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም ክፍሎች(መፀዳጃ ቤትን ጨምሮ) እኩል ያፀዳሉ! የጃፓን ተማሪዎች በሂሳብ፣ ፊዚክስ እና ቋንቋ መጎበዝ ግዴታቸው ነው። ተማሪዎች የፍቅር ግንኙነት መመስረት አይችሉም! እሱ ብቻ ሳይሆን ትምህርት ቤት ውስጥ መሳሳምም ሆነ መተቃቀፍ አይቻልም፣ ያስቀጣል፣ አለፍ ካለም ያስባርራል!
# 1 ገራሚ ነገር አንድ!
የዓለማችን ትልቁ አማካይ የመኖርያ እድሜ ያለው ጃፓን ነው። አንድ ጃፓናዊ በአማካይ 83 ዓመት ይኖራል። ውፍረት እንደ ሃጥያት የሚቆጠርባት ጃፓን ውስጥ የተዝረጠረጠው ህዝብ ከ 4% አይበልጥም። ጌታዬ! ይህ አሃዝ አሜሪካ ውስጥ 40% ነው! የመኖራችን ሚስጥር ስፖርት፣ አሳ እና ቅጠላ ቅጠል ነው ይላሉ! ብታምነኝም ባታምነኝም ጃፓን ውስጥ 50 ሺህ እድሜያቸው ከ 100 በላይ የሆኑ ሰዎች ይኖራሉ!
# 2 ገራሚ ነገር ሁለት!
የጃፓን ዋና ከተማ የሆነችው "ቶክዮ" ውስጥ ብቻ 38 ሚልዮን ህዝብ ይኖራል! አባዬ! አዲስ አበባ ከ 10 ሚልዮን በታች ሆና ነው እንግዲህ ልንፈነዳ የደረስነው!😀
ይህንን 38 ሚልዮን ህዝብ በብዛት ከቤት ወስዶ ወደ ቤት የሚመልሰው ባቡር ነው። ባቡር ስልህ ታድያ መሃል ላይ መብራት ጠፍቶበት የሚቆመውን አይደለም! የዓለማችን ቁጥር አንድ ቀጠሮ አክባሪ ባቡሮች ያሉት እዛ ነው። አረፈዱ ከተባለ 6 ሰከንድ ነው! አንዴ አንድ ባቡር 18 ሰከንድ አርፍዶ ጉድ ተብሏል! ስራ በሃገሪቷ ባቡሮች መዘግየት ምክንያት ብታረፍድ እራሱ ባቡር ጣብያው "...እገሌ የሚባለው ስራተኛችሁ ያረፈደው በእርሱ ድክመት ሳይሆን በእኛ እንዝላልነት ነውና ይቅርታ!..." የሚል ደብዳቤ ሰጥቶህ ትሄዳለህ! በሰዓት ከ 320 ኪሎ ሜትር በላይ የሚበሩ "bullet train" የሚባሉ ባቡሮች ያሉት እዛ ነው! ጃፓኖች ጋር ባቡር ውስጥ ድምፅን ከፍ አድርጎ ማውራት ሳይቀር እንደ ነውር ይቆጠራል!
# 3 ገራሚ ነገር ሶስት!
የምትስተናገድበት ሆቴል ወይም ሬስቶራንት ውስጥ "Tip" ለአስተናጋጅ መስጠት ነውር ነው። ለአንድ አስተናጋጅ "Tip" አስቀምጠህለት ብትሄድ እየሮጠ ተከትሎህ ይመልስልሃል! ለምን?
"...አንተን ማስተናገድ እና መንከባከብ ግዴታችን ነው፣ ስራችን ነው! ለዚህ ስራችን ደግሞ ደሞዝ ይከፈለናል! ስለዚህ ተጨማሪ ብር በ "Tip" መልክ መስጠት አይጠበቅብህም!..." ይሉሃል! እጅግ ሰው አክባሪ እና ትሁት ከመሆናቸው የተነሳ ማንኛውንም እቃ፣ ምግብ ወይም መጠጥ በሁለት እጃቸው እንጂ በአንድ እጃቸው በፍፁም አይቀበሉህም! እሱንም ከወገባቸው ጎንበስ ብለው ነው። የሚገርመው ቤት ውስጥ ውጪ የዋልክበትን ጫማ አድርጎ መግባት ነውር ነው። አይደለም ቤትህ አንዳንድ ምግብ ቤቶች ሳይቀር ተስተናጋጆች ጫማቸውን አድርገው እንዲገቡ አይፈቀድም! በር ላይ ሸበጥ/ሲሊፐር ስለሚቀመጥልህ ቀይረህ መግባት ግድ ነው።
# 4 ገራሚ ነገር አራት!
የዓለማችን ሶስተኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ የጃፓን ሲሆን ከአጠቃላይ ኤክስፖርት ከሚያደርጉት ምርት 23% የሚሆነው መኪና ነው። 38% የሚሆነው ደግሞ ኤሌክትሮኒክስ ምርት ነው። 98% የሚሆነው ህዝብ በብሄር፣ በቋንቋ እና በባህል ተመሳሳይ(Homogeneous) ነው። ጃፓናዊያን እጅግ ስርዓት ያላቸው፣ ሰው አክባሪዎች እና በህግጋት የተመሉ ስለሆኑ ከሌላ ሃገራት ለስራም ሆነ ለጉብኝት የሚመጡ ሰዎች ጃፓን ውስጥ መኖር ይቸገራሉ!


# 5 ገራሚ ነገር አምስት!
ለሃገር ቅድሚያ መስጠት፣ ለሃገር ክብር መሞት(መሰዋት) እና ለሰዎች ቅድሚያ መስጠት ጃፓን ውስጥ እንደ ባህል ይቆጠራል። የ "Titanic" መርከብ በሰመጠችበት ወቅት እንደምንም ብሎ የተረፈ አንድ ጃፓናዊ ወደ ሃገሩ ሲመለስ "እራስ ወዳድ ነህ! እንዴት መርከቧ ስትሰጥም ከሞቱት ሰዎች ጋር አብረህ አትሞትም!?" ተብሎ እንደተንቋሸሸ ይነገራል!
አስደማሚ ታሪክ!
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት (እ.ኤ.አ 1939-1945) ጃፓን በአሜሪካ ከፍተኛ ሽንፈት እየገጠማት ትመጣለች! የጃፓን የጦር ጀቶች በቀላሉ በአሜሪካ እየተመቱ መውደቅ ይጀምራሉ! ወታደሮቿም ማለቅ ጀመሩ! ጦርነቱን መሸነፋቸውም እውን እየሆነ ይመጣ ጀመር!
በወቅቱ የጃፓኑ ንጉስ ጋር ወታደሮች እና የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች እየተሸነፉ መምጣታቸው አሸማቋቸዋል! እንደ አምላክ የሚታየው የሃገሪቱ ንጉስም "...ተሸንፋችሁ ከምትመጡ ለሃገራችሁ እና ለዙፋኔ ክብር ስትሉ አጥፍታችኃቸው ጥፉ!..." ብሎ አዘዛቸው!
ጌታዬ!
የጦር አውሮፕላን አብራሪዎቹ ሳያቅማሙ ተስማሙ! እራሳቸውንም "kamikaze pilots" ብለው ሰየሙ። ለሃገራቸው እና ለንጉሱ ክብር ሲሉ የሚያበሩት የጦር አውሮፕላን ውስጥ ቦንብ እና ጋዝ(ነዳጅ) ጭነው ቀጥታ የአሜሪካ የጦር መርከቦች ያሉባቸው ቦታዎች ጋር በከፍተኛ ፍጥነት በመብረር እራሳቸው መከስከስ ጀመሩ! አባዬ! ይሄንን ያደረገው አንድ ጃፓናዊ ፓይለት አይደለም! በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጃፓናዊ ፓይለቶች ናቸው። በዚህ ሂደት 34 ግዙፍ የአሜሪካ የጦር መርከቦች እንዲሰምጡ እና ከፍተኛ ውድመት እንዲደርስባቸው አደረጉ! በአንድ ተልኮ ብቻ ከ 5000 በላይ የአሜሪካ ባህር ሃይሎች እንዲሞቱ ማድረግ ችለዋል።
እንደምትሞት እያወክ የጦር አውሮፕላንህ ውስጥ ቦንብ እና ጋዝ ጭነህ የጠላት መርከብ ላይ ወስደኸው መከስከስ ምን ያህል ድፍረት እንደሚጠይቅ አስበው እንግዲህ!
አሰቃቂ መገባደጃ!
በጃፓን ጥቃት ደርሶብኛል በማለት አሜሪካ ለመጀመርያ ግዜ በሰው ልጅ ላይ "ሄሮሺማ" እና "ናጋሳኪ" የሚባሉ ሁለት ከተሞች ላይ "አቶሚክ ቦንቦችን" ጣለች! በአንዴ ከ 150 ሺህ እስከ 200 ሺህ የሚጠጉ ንፁሃን ጃፓናዊያኖችን በሁለት ቦንብ ስልቅጥ አድርጋ በላች። ጃፓንም በመጨረሻ "ተሸንፌያለው፣ ጦርነቱ ይብቃ!" ብላ እጅ ሰጠች! ሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ያኔ አበቃ። የሩቅ ምስራቋ ጃፓን "አቶሚክ ቦንብ" የተጣለባት የመጀመርያዋም የመጨረሻማው ሃገር ሆና አለፈች።
ግን... ግን
.
.
.
.
ፍፁም ይቅር ይባባላሉ ተብለው የማይታሰቡት ሁለቱ ሃገራት ከአመታት በኃላ ወዳጅ ሆኑ፣ ታሪክ አለፈ፣ አሜሪካ ይህንን ታሪክ ይቅር የማይለውን ወንጀል ለማንጣጣት በሚመስል መልኩ ፅኑ የጃፓን ወዳጅ ሆነች፣ መሰረተ ልማቶቿን እና ከተሞቿን ገነባች! ሁለቱ ሃገራት በውትድርና፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና ቴክኖሎጂ እጅግ የተሳሳሩ ሃገራት ሆኑ!

Wendye Engida የፌስቡክ ገፅ የተወሰደ

ርዕስ ፦ የጃፓን መንገድ
ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ጠላት የለም
ጸሓፊ ፦ በአሰፋ ማመጫ አርጋው
የታተመበት ዘመን:- የመጀመሪያ እትም 2014 ዓ.ም
የገጽ ብዛት ፦366
ዋጋ፦389 ብር
የታተመበት ቦታ፦Falcon Printing Enterprise
ከ25ዐ ዓመታት በላይ እንደ አለት በደደረ መዳፍ ያስተዳደረው የቶኩጋዋ ሥርወ መንግሥት ሲገረሰስ በመቃብሩም ላይ ሜጂ (የብርሃን ዘመን) ሲሉ የሰየሙት መንግስት በጃፓን ተመሠረተ፡፡ አዲሶቹ “የለውጥ ሃይሎች” ጃፓንን ለመለወጥ የወሰዱት የመጀመሪያ እርምጃ፣ በርዕዮተ ዓለም መነታረክ ሳይኾን በዕድገት ከቀደሙት ምዕራባውያን አገሮች መማርን ነበር፡፡
ዲፕሎማቱ አሰፋ ማመጫ አርጋው፤ በጃፓን የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ጉዞ የቀሰመውን ዕውቀት በ366 ገፆች አሰናድቶ አቅርቦልናል፡፡
ጃፓን ላለፈችበት መከራ ሁሉ መንስኤው መረን ለቆ የነበረው ብሔርተኝነት ይመስለኛል። መዳኛው ደግሞ ሽንፈትን ተቀብሎ አንገትን ከመድፋት ይልቅ በአዲስ አቅጣጫ በአዲስ መንገድ እና መንፈስ፣ እንደ አገር አንድ ልብ፣ አንድ ሃሣብ ይዞ መነሣት መቻላቸው ነው፡፡
ከሁለት ምዕት ዓመት በላይ አገሪቱን ዘግቶ ያቆያት ሥርወ መንግሥት እንደወደቀ፤ አብዮተኞቹ ቀጣይ ሥራቸው አገራቸውን እንደምን አበልጽገው ከሃያላን ተርታ ማሰለፍ እንጂ በርዕዮተ ዓለም ጎራ ለይቶ መፋጀት አልነበረም፡፡ እኒያ የጃፓንን የብርሃን ዘመን ሻማ የለኮሱ ቀደምት እንደምን በአንድ ልብ ተነስተው አገሪቱን ሃያል እንዳደረጓት አሰፋ መረዳቱን እንካችሁ ብሎናል፡፡
አገር ከርዕዮት ዓለም በላይ ናት፡፡
አገር ከብሔር በላይ ናት።
አገር በዘፈን እና ዳንኪራ፣ ዘመን ባነገሰው የብሔር ብሔረሰብ ድለቃና ገድሎ በመሞት ብቻ አትበየንም፡፡ አገር በሁሉ ስምም ርዕይ የጋራ ምሰሶና ካስማ፣ ሁሉን አቅፋ የምታኖር የትናንት አደራ፣ የነገ ስም የዛሬ ማረፊያ ናት፡፡ እንጂ ለ”ከእኔ በላይ ለአሣር” በሚል የምትሰዋ በግ፣ አይደለችም፡፡
ጃፓን እንዲህ ነው ያደገችው፡፡ ለዘመናት ዘግቶና ጠርንፎ የያዘ የሾገኑ አገዛዝ ተገረሰሰ ብለው የተነሱ ወጣት አብዮተኞች፤ ለሌላ ትግል መነሻ እርሾ አልኾኑም፤ የተነሱበትን ዓላማ ከተነሱለት ሕዝብ ጋር ተገበሩት እንጂ፡፡
የሰውን ልጅ የሕይወት ፍኖት አቅጣጫ የሚቀይረው አንድ አሳቢ ነው፡፡ ሃሣቡ ግን መሬት የረገጠ፣ የሰው ልብ የሚገዛ፣ ገቢራዊ የሚሆን፣ ውጤቱ የሚገለጥ ነው፡፡ የማኀበረሰቡ ሕይወት እና አስተሳሰብ ላይ በልካም ተጽዕኖ የሚያሣድር አንድ ሰው አገር ያነቃል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የምናየው ፋኩዛዋ ዩኪቺ እንደዚያው ነው፡፡
ፀሐፊው የጃፓንን ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዞ ቀለል አድርጎ በሚነበብ መልኩ አቅርቦልናል ፡፡ ስለ ጃፓን የእርስ በርስ ጦርነት፣ በቅኝ ገዢነት ያደረገችው ጦርነት ብሎም ስላስከፈላት ዋጋ፣ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ስለደረሰባት ውድቀት ፣ በሽንፈት ከመሰበር እንደምን መንቃት እንደሚቻል፤ ስለ ይቅርታ፣ እንደ አገር በአንድ ርዕይ እንደምን መነሣት እንደሚቻል፣ የሥራ ባሕልን በማኀበረሰብ ውስጥ ስለ ማስረፅ እጅግ በአስደማሚ ሁኔታ አስነብቦናል፡፡
በአለማችን ብቸኛዋ በአቶሚክ ቦምብ የጋየች አገር ከዚያ ውድመት እንዴት እንዳንሰራራችና ከተረጂነት ወጥታ ወደ ቁጥር አንድ እርዳታ ሰጪነት እንደተቀየረች ያስነብበናል ፡፡

Meseret Alemayehu Dagnew የፌስቡክ ገፅ የተወሰደ


የጃፓን መንገድ - እንደ ማንቂያ ደወል
#Ethiopia | ፈር መያዣ
ለመቶ ዓመታት ያኽል በመሣፍንት እና በጦር አበጋዞች ስትታመስ ለነበረችው ጃፓን ቶኩጋዋ ኤያሱ የተባለ የጦር መሪ ተነሣላት፡፡ በየመንደሩ እና በየጎጡ ነፍጥ አንስተው ሲታጋተጉ የነበሩ ጦረኞችን ድል ነስቶ የራሱን ወታደራዊ መንግሥት መሠረተ፡፡
የቀደመውን የንጉሥ ሥርዓት ለይስሙላም ቢኾን ወደ መንበሩ መለሰው፡፡ ይኽ ከ25ዐ ዓመታት በለይ የዘለቀው ወታደራዊ የመንግሥት ሥርዓት ሾገን በመባል ይታወቃል፡፡
ይኽ ወታደራዊ ሥርዓት የጃፓንን በር ጠርቅሞ ከሌላው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት በማቋረጥ ነጠላት፡፡
የአገሩን ሕዝብ በመደብ ለይቶ፣ በሥራም ኾነ በማኀበራዊ ግንኙነት እንዳይተሳሰር ከፋፈለው፡፡ የእያንዳንዱ ጃፓናዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንኳ በሕግ ተደነገገ፡፡ ጃፓን ውስጥ የነበሩ አውርጳውያንን ከአገሩ አስወጣ፡፡
የአገሩም ሰው ከጃፓን ውጭ ወደየትም ውልፍት እንዳይል አዘዘ፡፡ ቀደምት መጻተኞች የሰበኩትን ክርሰትና አገደ፣ አብያተ ክርቲያን እሣት በላቸው፡፡
የወቅቱን ሁኔታ በአጭር ለመግለጽ ፀሃፊው ከባለቅኔ ከበደ ሚካአልን “ጃፓን እንደምን ሰለጠነች?” ይጠቅሳል፡፡
“. . . ከእንግዲህ በኋላ ፀሐይ በመሬት ላይ አብርታ እስከምትኖርበት ጊዜ ማንም ሰው ቢኾን ጃፓን አገር ለመግባት አይድፈር . . . ይኽን ዐዋጅ ጥሶ ሲገባ የተገኘ የውጭ አገር ሰው ሁሉ በሞት ይቀጣል፡፡” (ገጽ፤26)
የሰው ልብ በቅጥር አይያዝም
የሰው ልብ፣ የሰው ምኞት ግን አይቀጠርም፡፡ በሥፍራ ተለይቶ አገር ድንበር ተበጅቶለት ይቀመጥ እንጂ ሰው ልቡ እግረኛ ነው፡፡ የትም መቸም፡፡ ዘራሰብ ሉላዊ ነው፡፡ ዘመነኞች ስደት በሚል ይበይኑት እንጂ ዕጣ ፈንታ እንዲህም እንዲያም ብሎ ያገናኘዋል፡፡
ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው “ጉልበተኛ የፈጠራት ዓለም” የሚለው ግጥማቸው እንደህ የሚል ሃሣብ አለው፡-
እስኪ ከዚህች ወዲህ፤ ከዚያ ወዲያ ብሎ፤
ዛቻ ከፖለቲካ ቀላቅሎ፤
ከለላት እንጂ
አሰመራት
ዓለማችን
መች ድንበር ነበራት
ከመሣፍንትና የጦር አበጋዞች ነፍጥ አስጥሎ፣ የአገሪቱን መግቢያ መውጪያ የከረቸመው የሾገኑ አስተዳደር ከምዕራቡ ዓለም የዕድገት ወሬ የጃፓናውያንን ልብ በቅጥርም ኾነ በነፍጥ መከለል አልቻለም፡፡
በተለይ የባህር ዳርቻ ግዛት አስተዳዳሪዎች የወሬው ነፋስ እና እነርሱ ያሉበት ኹኔታ ከተራ መንፈሳዊ ቅናት አልፈ፡፡ የአገራቸው መፃዒ ዕድል ያሣስባቸው ጀመር፡፡
በአናቱ ጥቁር ጢሱን እያትጎለጎለ “ጥቁሩ መርከብ” (The Black Ship) ደረሰ፡፡
ይኽን ተከትሎ ከሁለት መቶ ሃምሣ ዓመታት በላይ ተዘግቶ የነበረው በር ተከፈተ፡፡ የመርከቡ ጢስ ለቶኩጋዋ ሥርወ መንግሥት መፍረክረክ ለለውጥ ፈላጊ ወጣተቶች ግን የማንቂያ ማጠንት ኾነላቸው፡፡ ዓመጽ ማቀጣጠሉን ገፉበት፡፡
የተፍረከረከውን ነባር ሥርዓት ለማስቀጠል የቆረጡ “ታማኞች” በለውጡ እሣት አቀጣጣዮች ላይ ብረት አነሱ፡፡ ብረት ያነሱ በብረት ይጠፉ ዘንድ ተጽፏልና የሾገኑ ሥርዓትና ጭፍሮቹ ማብቂያ ኾነ፡፡
ጃፓንን ከ25ዐ ዓመታት በላይ እንደ ብረት በጠነከረ መዳፍ ያስተዳደረው የቶኩጋዋ ሥርወ መንግሥት ተገረሰሰ፡፡
በመቃብሩም ላይ ሜጂ (የብርሃን ዘመን) ሲሉ የሰየሙት መንግስት ተመሠረተ፡፡ የጃፓን አዲስ ጉዞ ተጀመረ፡፡
አዲሶቹ “የለውጥ ሃይሎች” ጃፓንን ለመለወጥ የወሰዱት የመጀመሪያ ርምጃ በርዕዮተ ዓለም መነታረክ ሰይኾን በዕድገት ከቀደሙት ምዕራባውያን አገሮች መማርን ነበር፡፡



መብሰልሰል
ከጃፓን መንግሥት በተገኘ የባሕል፤ የቋንቋና የዲፕሎማሲ ስልጠና ለስምንት ወራት ያህል ጃፓን የቆየው ዲፕሎማቱ አሰፋ ማመጫ አርጋው በጃፓን የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ጉዞ ያደረበትን ምሳጤ በ366 ገፆች ቀንብቦ አቅርቦልናል፤- በ “የጃፓን መንገድ”፡፡
የዓለምን ኢኮኖሚ ከሚመሩት አገሮች አንዷ የኾነችውን የዚህችን ትንሽ አገር ውድቀትና አነሣስ ድርሳናት አገላብጦ፣ የዜና አውታሮችን ዘገባ ፈተሾ ቅልል ባለ ቋንቋ አጠገባችን ኾኖ እንደሚተርክ ሰው እስኪሰማን ድረስ ወጉን ይቀዳልናል፡፡
እውነት እውነት እላችኋላሁ በየምዕራፎቹ እንደ መስታዎት የእኛን የእስካሁን የአብዮትም የነውጥም ጉዞ የሚያስታውሰ ተረኮች በርካታ ናቸው፡፡ የፀሐፊው ዋና ቁብ ይኽው ይመስለኛል፡- ቁጭትን መፍጠር፡፡
ጃፓን ላለፈችበት መከራ ሁሉ መንስኤው ልጓም ያልተበጀለት ብሔርተኝነት ይመስለኛል፡፡ መዳኛዋ ደግሞ ሽንፈትን ተቀብሎ ከመሰበር ይልቅ በአዲስ አቅጣጫ በአዲስ መንገድ እንደ አገር አንድ ልብ አንድ ሃሣብ ይዞ መነሣቷ ነው፡፡
ከሁለት ምዕት ዓመት በላይ አገሪቱን ዘግቶ ያቆያት ሥርወ መንግሥት እንደተቀየረ፤ አብየተኞቹ ቀጣይ ሥራቸው አገራቸውን እንደምን አበልጽገው ከሃያላን ተርታ ማሰለፍ እንጂ በርዕየተ ዓለም ጎራ ለይቶ መታጋተግ አይደለም፡፡
እኒያ የጃፓንን የብርሃን ዘመን ማሾ የለኮሱ ቀደምት እንደምን በአንድ ልብ ተነስተው አገሪቱን ሃያል እንዳደረጓት አሰፋ ከሰው አውግቶ፣ ከማዕምራን ጠይቆ እና ዳርሣናት ፈትሾ ነው መብሰልሰሉን የሚያካፍለን፡፡
. . . ለኔ ብለህ ስማ
የአሰፋ ትረካ ስማትን የሚበረብር ነው፡፡
መጽሐፉ ከገጽ ገጽ በተገለፀ እና በተነበበ ቁጥር ወረቀትነቱ ተዘንግተ የእኛን የእስከዛረ ጉዞ እና አሁናችንን እንድንጠይቅ፣ የት ጋር እንደጎደልን ውስጣችንን እንድንበረብር የጎተጉታል፡፡ ለምን በመፈክርና ቃላት በማሽሞንሞን ላይ ተቸነክረን ቀረን? የጃፓን መንገድ እንዲህ ውስጥን ይሞግታል፡፡



“. . . የቀድሞው መንግሥት በአመጽ ተወግዶ የሚጂ ንጉሣዊ መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ ጃፓን ድሃ እና ኋላቀር አገር ነበረች፡፡
[. . .]
እናም አገሪቱን ከኋላቀርነት ፈጥና ለማውጣት ለለወጡ መበዎቹ ከለሎች የሠለጠኑ አገራት ልምደ መቅሰም ወሳኝ ጉዳይ ኾነ፡፡
[. . .]
ለዚሁ ዓላማ ሥልጣን የጨበጡት ወጣተቹ የለውጥ መሪዎች በታሪክ “ኢዋኩራ ሚሽን” በመባል የሚታወቀውን የልዑካን ቡድን አዘጋጁ” (ገጽ 46-47)
በወቅቱ እንደተነገረን የኢትየጽያ አብዩት በግብታዊነት ከፈነዳ በኋላ እና ከግማሽ ምዕት ዓመት መንበራቸው ንጉሡን ከገረሰሰ በኋላ ምን ተፈጠረ? ከአንድ ጥራዝ የሶሺያሊዝምን ፍልስፍና ያነበቡ ወጣት ተማሪዎች ጎራ ለይተው መተጋተግ ጀመሩ፡፡ ስልጣኑን የጨበጠው ወታደር በበኩሉ ተማሪ አርፈ ትምህርቱን ይማር፡፡
በዚህ ግርግር ይህች አገር እንደ እንቁላለ ከእጃችን ወድቃ እምቦጭ ማለት የለባትም አለና ጠብመንጃውን አቀባበለ፡፡ ያነ የተጀመረ መናቀር አንድ ደርዝ ሳይበጅለት የትውልድ ዕድማ እየበላ ይገኛል፡፡
አገር ከርዕየተዓለም በላይ ናት፡፡ አገር ልብ በሚያሞቅ ዘፈን፣ ነፋስ በሚነሰንሰው የሰንደቅ ዓላማ ዳንስ፣ ገድሎ በመሞት ብቻ አትበየንም፡፡
አገር በሁሉ ስምም ራዕይ የጋራ ምሰሶና ካስማ፣ ሁሉን አቅፋ የምታኖር የትናንት አደራ፣ የነገ ስም የዛሬ ማረፊያ ናት፡፡ እንጂ ለ”ከእኔ በላይ ለአሣር” የምትሰዋ በግ፣ ጭዳ የምትኾን ዶሮ አይደለችም፡፡
ጃፓን እንዲህ ነው ያደገችው፡፡ ለዘመናት ዘግቶ እና ጠርንፎ የያዘ የሾገኑ አገዛዝ ተገረሰሰ ብለው የተነሱ ወጣት አብየተኞች ለሌላ ትግል መነሻ እርሾ አልኾኑም፤ የተነሱበትን ዓላማ ከተነሱለት ሕዝብ ጋር ተገበሩት እንጂ፡፡
ሰው ጥሩ አንድ ሰው
የሰውን ልጅ የሕይወት ትልም በአንድም በሌላ መልኩ የሚቀይረው የአንድ አሳቢ (አፈንጋጭ) ሃሣብ ነው፡፡ ሃሣቡ ግን መረት የረገጠ፣ የሰው ልብ የሚገዛ፣ መረት የሚወርደ፣ ውጤቱ የሚገለጥ ነው፡፡
የማኀበረሰቡን ሕይወት እና አስተሳሰብ በበጎ ተጽዕኖ የሚያሣድር አንድ ሰው አገር ያነቃል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የምናየው ፋኩዛዋ ዩኪቺ እንደዚያው ነው፡፡
መደምደሚያ
ፀሐፊው የጃፓንን ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዞ ቀለል አድርጎ በሚነበብ መልኩ አብርቧል፡፡
ጃፓን ከእርስ በርስ ጦርነት፣ በቅኝ ገዢነት ያደረገችው ጦርነት ስላስከፈላት ዋጋ፣ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ስለደረሰባት የሰው እና የቁስ ውድመት፣ በሽንፈት ከመሰበር እንደምን መንቃት እንደሚቻል፣ ስለ ይቅርታ፣ እንደ አገር በአንድ ርዕይ እንደምን መነሣት እንደሚቻል፣ የሥራ ባሕልን በማኀበረሰብ ውስጥ ስለማስረፅ እጅግ በአስደማሚ ሁኔታ አስነብቦናል፡፡
ብቸኛዋ በአቶሚክ ቦምብ የተመታች አገር ከዚያ ውድመት እንዴት እንዳንሰራራችና ከተረጂነት ወደ ቁጥር አንድ የልማት ትብበርና ርዳታ ሰጪነት እንደተቀየረች ያሣያል፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ ከንባብ አንፃር አንጽንኦት ለመስጠት በማሰብ አንዳንድ ምዕራፎች መግቢያ ላይ ቀድሞ የተነገረ ታሪክ ይደገማል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ “ወረድ ብለን እንደምናየው”፣ “በሌላ ቦታ በሰፊው እንደምናየው” የሚሉ አገላለፆች አንባቢውን ከንባቡ ፍሰት የሚያናጥቡ በመኾኑ በቀጣይ ሕትመት ቢስተካከሉ ተመራጭ ይመስለኛል፡፡
በቀረው ፀሐፊው የካበተ ልምድ እንዳለው ዲፕሎማት የጃፓንን ጉዞ በንስር ዓይን መርምረው ይኽን ሥራ ማበርከታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡



ክቡር ዶ/ር ደራሲ ከበደ ሚካኤል ‹‹ጃፓን እንደምን ሠለጠነች?›› ብለው ጀምረው ከዚያም የተለያዩ ሀገሮችን እንዴት እንደሠለጠኑ መጻፍ ጀመሩ፡፡ ሦስተኛው መጽሐፍ ላይ ሲደርሱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስጠሯቸው፡፡

‹‹ከበደ ምን እየሠራህ ነው?›› ብለው ጠየቋቸው፡፡ ከበደ ሚካኤልም:-
‹‹እንትን እንዴት ሠለጠነች? የሚል አራተኛ መጽሐፍ ልጽፍ ነው፡፡›› በማለት መለሱ፡፡

‹‹እንዳትጽፍ፤ አቁም እንዳትጽፍ›› አሉ ንጉሡ፡፡

‹‹ለምን?›› ጠየቁ ከበደ ሚካኤል፡፡

ንጉሡም:-
‹‹ሥነ ምግባር የሌለው ሕዝብ ቢሠለጥን ጥቅም የለውም፡፡ የገነባውን ያፈርሰዋል፤ የሰራውን ይንደዋል፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ስለ ሥነ ምግባር ጻፍ፡፡ የጀመርከውን ከዚያ በኋላ ትጽፈዋለህ›› አሏቸው፡፡

ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ደስ ሳይላቸውም ቢሆን ወደ ቢሮአቸው ሄዱ፡፡ ከዚያ በኋላ ‹‹ታሪክና ምሳሌ›› የሚባሉትን እጅግ በጣም የምንወዳቸውን እንዲሁም የተማርንባቸውን የሞራል ማስተማሪያ መጻሕፍትን ጻፉ።

ከ  Tadele tibebu - ታደለ ጥበቡ  የፌስቡክ ገፅ የተወሰደ











No comments:

Post a Comment