ከደራሲያን ዓምባ

Monday, November 28, 2022

22ኛው የዓለም ዋንጫ በኳታር_2022

22ኛው የዓለም ዋንጫ ኳታር 


በባህረሰላጤዎች የተከከበች
ኳታር ልዩ መልክዓምድር ያላት አገር ናት።  በምዕራብ እስያ የምትገኝ ሲሆን በሰሜን ምስራቅ የኳታር ባህረሰላጤ፤ በደቡብ በኩል የሳውዲ አረቢያ ባህረሰላጤ፤ የተቀረው ግዛቷ በፋርስና በባህሬን ባህረሰላጤዎች  ተከብቧል። የዓለማችንን ረጅሙን የባህር ጠረፍ  በ534 ኪሜትር አስመዝግባለች፡፡ በ338 ጫማ ከፍታዋ ከዓለማችን ረባዳማ ስፍራዎች በሁለተኛ ደረጃ የምትጠቀስ ሲሆን አንደኛውን ደረጃ በ6 ጫማ ከፍታ የያዘችው ማልድቪስ ናት፡፡  ካ ሆር አልአዳይድ  Khor Al Adaid የተባለው ክልል ባህርና በረሐ ከሚገናኝባቸው የዓለማችን አስደናቂ ስፍራዎች አንዱ ሲሆን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡



የውጭ አገራት ዜጎች የበዙበት
የኳታር አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ከ2.6 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ የሚገመት ሲሆን የውጭ አገራት ዜጎች አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ። ከህዝቧ 12%  እስከ  315,000 ኳታራዊያን ሲሆኑ 88 በመቶው ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ከተለያዩ አገራት የገቡ ስደተኞች ናቸው። በኳታር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭ ዜጎች ህንዳውያን ሲሆኑ እስከ 700ሺ ይደርሳሉ። 40% ከአረብ፤  36% ከደቡብ ኤስያ፤ 18% ከህንድ፤ 18% ከፓኪስታን፤ 10% ከኢራን እንዲሁም 14% ከተለያዩ የዓለም አገራት የመጡ ዜጎች ይገኙበታል፡፡


የቱሪዝም መስህብነቷ

ኳታር በቱሪዝም መስክ ፈጣን እድገት ካሳዩ አገራት አንዷ ነች። በየዓመቱ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ አለም አቀፍ ቱሪስቶች ይጎበኟታል፡፡  በቅርቡ ባደረገችው የቪዛ ማሻሻያ የ88 ሀገራት ዜጎች ከቪዛ ነፃ እንዲገቡ አድርጋለች፡፡ ይህም በመካከለኛው ምስራቅ ካሉ የአረብ አገራት ተወዳጅ የቱሪስት መናሐርያ ያደረጋት ሆኗል። ከዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችና ቱሪስቶች እንደሚጎበኟትም ይጠበቃል፡፡ ከኳታር የቱሪዝም መስህቦች መካከል የአርኪዮሎጂ ስፍራዎች፤ የባህር ዳርቻዎች፤ ወደቦች፤ ሙዚዬሞች፤ ብሄራዊ ፓርኮችና የገበያ ማዕከሎች ይጠቀሳሉ።


የአልታኒ ቤተሰብ

ከ1868 እኤአ ጀምሮ ኳታርን የሚያስተዳድረው መንግስት በአልታኒ ቤተሰብ የሚመራ ነው፡፡ የቤተሰቡ ልዩ አስተዳደር ስልጣን ላይ የወጣው ከኳታር እና ባህሬን ጦርነት በኋላ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ኢምር ወይም መሪ ታሚም ቢን ሃማድ አልታኒ የሚባሉ ሲሆኑ ከ203 እኤአ ጀምሮ በስልጣን ላይ ናቸው፡፡ የቤተሰቡ የሃብት መጠን ከ335 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ይገመታል፡፡ የአልታኒ ቤተሰብ በዓለም በስነጥበብ ስራዎች ላይ ኢንቨስት በማድረግና በመግዛት ግንባር ቀደም ናት፡፡
የዓለም ስነጥበብ ዋና ሰብሳቢ
በኳታር የመንግስት አስተዳደር ላይ የሚገኙት የአልታኒ ቤተሰብ በእስልምናና ዘመናዊ ስነጥበብ ፍቅራቸውና አሰባሳቢነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ከ14 ዓመታት በፊት በአረቡ ዓለም ምርጡን የእስልምና ጥበብ ሙዚየም The Museum of Islamic Art  መስርተዋል፡፡  በኳታር ሙዚየሞች ባለስልጣን ስር የሚተዳደሩ ሌሎች በርካታ ሙዚየሞች በዶሃ ከተማ ውስጥ የተገነቡ ሲሆን Arab Museum of Modern Art ይጠቀሳል፡፡ በመላው ዓለም ከ65 በላይ አገራትን የወከሉ ከ300 በላይ አርቲስቶችን የሚያስተናግደው ኳታር ኢንተርናሽናል አርት ፌስቲቫልም QIAF  አገሪቱ ለስነጥበብ የሰጠችውን ትኩረት ያመለክታል፡፡


ሙሉ ከተማ የሆነው ሃማድ

ሃማድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በ2021 እኤአ ላይ ስካይትራክስ በሰጠው የዓለም አየር ማረፊያዎች አዋርድ ላይ የዓለም ምርጥ ተብሏል። ተመሳሳይ ሽልማትን ለ6 ጊዜያት በመውሰድም ከፍተኛውን ስኬት አስመዝግቧል፡፡ የአየር ማረፊያው የአውሮፕላን መንደርደርያ እስከ 4850 ሜትር ርዝማኔ በማስመዝገብ በምዕራብ ኤስያ ቀዳሚው ሲሆን በዓለም በ6ኛ ደረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡ በሰባቱም አህጉራት የበረራ መስመሮችን በመዘርጋትም የሚታወቀው አየር ማረፊያው፤  በዓመት እስከ 50 ሚሊዮን ተጓዦችን ያስተናግዳል፡፡ ተመሳሳይ አቅም ያላቸው የአየር ማረፊያዎች የቶኪዮው ሃኔዳ፤ የሲንጋፑር ቻንጊ፤ ተዱባዩ ዲአየኤ እና የለንደኑ ሂትሮው ናቸው፡፡ የሃማድ ዓለም አቀፍ ማረፊያ 29 ስኩዌር ኪሎሜትር በመሸፈን  በግዝፈቱ ከዓለም በ9ኛ ደረጃ ይቀመጣል፡፡ ቅጥር ጊቢው ከ100 በላይ ህንፃዎች ፤ ከ100 በላይ ሱቆችና ሬስቶራንቶችን ይዟል፡፡


ኳታር ኤር ዌይስ


ኳታር ኤርዌይስ በዓለም ዙርያ ከ45 ሺ በላይ ሰራተኞችን ቀጥሮ የሚያስተዳድር ነው። ከዓለማችን ትልልቅ አየር መንገዶች አንዱ ሲሆን ከዶሃ በመነሳት  ከ150 በላይ ዓለምአቀፍ መዳረሻዎች አሉት፡፡


የአየር ማቀዠቀዣ ያላቸው ስታድዬሞች
22ኛው የዓለም ዋንጫው የሚካሄዱትን 64 ጨዋታዎች የሚያስተናግዱ 8 ስታድዬሞች ልዩ አየር የማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂ  ተገጥሞላቸዋል። በጨዋታ ሜዳ ላይ የሚያስፈለገውን የሙቀት መጠን ለማመጣጠን ተግባራዊ በሆነው ቴክኖሎጂ በየስታድዬሙ ያለውን የሙቀት መጠን  እስከ 26 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል፡፡ የአየር ማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂው ዘላቂ እና ኃይል ቆጣቢ በሆነ መንገድ ከመስራቱም በላይ በየስታዲየሙ የሚገኘውን ተመልካች በመመርኮዝ የሙቀት መጠኑን መቆጣጠር የሚቻልበት ነው፡፡



የኤሌክትሪክ አውቶብሶች
22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ተግባራዊ ከሚሆኑ አስደናቂ ቴክኖሎጂች መካከል በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አውቶብሶች ይገኙበታል። ደጋፊዎችን ወደ ስታዲየሞችና ወደ የተለያዩ የዶሃ ከተማ ስፍራዎች የሚያመላልሱ ናቸው፡፡  በዓለም ዋንጫ ታሪክ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች ለትራንስፖርት አገልግሎት ሲውሉ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን በከፍተኛ የቴክኖሎጂ የመረጃ መሳሪያዎች የሚታገዙ የትራንስፖርት አገልግሎት ናቸው።


ከጨዋታ ውጭን የምትቆጣጠረው ኳስ
አል ሪሃላ Al Rihla ለ22ኛው የዓለም ዋንጫ በአዲዳስ የተሰራች ኳስ ናት፡፡ የዓለም ዋንጫዋ ኳስ  እውነተኛ መረጃን ለVAR ባለሙያዎች የምታስተላልፍ፤ ፊፋ ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ ከሚያደርገውና በከፊል አውቶሜትድ ከሆነ የኦፍሳይድ መቆጣጠርያ ቴክኖሎጂ ጋር በመናበብ የምትሰራም ነች፡፡ በሜዳው ዙርያ የሚገጠሙ  12 ካሜራዎችን ከኳሷ እንቅስቃሴ ጋር በማዋሃድ  የሚሰራ ቴክኖሎጂ ተለጥፎባታል፡፡ከጨዋታ ውጭ የሆኑ ኳሶችን ለመቆጣጠር ፊፋ ተግባራዊ የሚሆነው አዲስ ቴክኖሎጂ ዳኞች ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንዲሰጡ ያግዛቸዋል፡፡



ረጅሙ የብስክሌት ጎዳና

ኳታር የዓለማችንን ረጅሙን የብስክሌት ጎዳናም ገንብታለች፡፡ በዶሃ የሚገኘው የኦሎምፒክ ደረጃ ያለው የብስክሌት ጎዳና በ33 ኪሜ ርዝማኔው በጊነስ ሪከርድ ሬከርድ የተመዘገበ ነው፡፡ ከጎዳናው 25.3 ኪሜትር በአስፋልት ኮንክሪት መነጠፉም ክብረወሰን ላይ ሰፍሯል፡፡


ከዓለም ሃብታም አገሮች ተርታ
ኳታር በድፍድፍ ነዳጅ ና ተፈጥሮ ጋዝ በተገነባው ኢኮኖሚዋ ከዓለማችን ሃብታም አገራት ተርታ ትሰለፋለች፡፡    ነዳጅ የኢኮኖሚ ዋልታዋ ሲሆን በጥልቀት ከተቆፈሩ ጉድጓዶች አንዱ 12290 ሜትር ተለክቷል፡፡ ኳታር ከሉክሰምበርግ፣ ስዊዘርላንድና ሲንጋፖር በመቀጠል አራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ የዓለም ሃብታም አገር ናት፡፡  አንድ የኳታር ዜጋ የነፍስ ወከፍ ገቢ እስከ 100ሺ ዶላር ይደርሳል፡፡


አረቢያን አጋዘን
አረቢያን አጋዘን የኳታር ብሄራዊ እንስሳ ሆኖ ይታወቃል፡፡ ይሄው አጋዘን  መሰል እንስሳ የኳታር ኤርዌይስ ሎጎ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በ1972 እኤአ ላይ ከዱር የጠፋው እንስሳ ከ10 ዓመት በኋላ እንደገና ወደ ዱር እንዲመለስ በማድረግ በማድረግ የኳታር መንግስት ከምድር ገጽ እንዳይጠፋ ተረባርቧል፡፡



በዓለም ዋንጫ ታሪክ ከፍተኛው የገንዘብ ሽልማት
በዓለም ዋንጫው ታሪክ ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ የተመደበ ሲሆን አጠቃላይ መጠኑ 440 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከ4 ዓመታት በፊት ራሽያ ካስተናገደችው 19ኛው የዓለም ዋንጫ በ40 ሚሊየን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የዓለም ዋንጫው አሸናፊ 46 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኝ ያገኛል፡፡ በ21ኛው ራሽያ ላይ 38 ሚሊዮን ዶላር፤ በ20ኛው ብራዚል ላይ 35 ፤ በ19ኛው ደቡብ አፍሪካ ላይ 30፤ በ18ኛው ጀርመን ላይ 20  እንዲሁም በ17ኛው በጃፓንና ደቡብ ኮርያ ላይ 8 ሚሊዮን ዶላር ለዋንጫው አሸናፊዎች ተሸልሞ ነበር፡፡



ሌሎች ተሳታፊዎች የሚሸለሙት
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ለሁለተኛ ደረጃ 30 ሚሊዮን ዶላር፤ ለሶስተኛ ደረጃ 27 ሚሊዮን ዶላር፤ ለአራተኛ ደረጃ 25 ሚሊዮን ዶላር፤ ከአምስት እስከ 8ኛ ደረጃ ለሚያገኙት 17 ሚሊዮን ዶላር፤ ከ9 እስከ 16ኛ ደረጃ ለሚያገኙት 13 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከ17 እስከ 32ኛ ደረጃ ለሚኖራቸው 9 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ የሚከፈል ይሆናል፡፡


የጭልፊት አደንና በረራ ስፖርት
በኳታር ጭልፊት ማልመድ፤ ልዩ የአደንና የበራራ ውድድር ማካሄድ የእግር ኳስን ያህል  አድናቂዎች እያፈራ ነው፡፡  የአየር ሙቀቱ ለጭልፊቶቹ ተስማሚ በሚሆንበት ጊዜ  ለአሸናፊዎች ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማቶች እየተዘጋጀ ልዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ይካሄዳሉ። ጭልፊቶች ከኳታራዊያን የእለት ኑሮ  ፈጽሞ የራቁ አይደሉም፡፡ በዶሃ ከተማ ያሉ የጭልፊት መሸጫ ሱቆች የቅንጦት መኪና ከሚሸጥባቸው ማዕከሎች ደረጃቸው ይስተካከላል፡፡ ዋጋቸው ከ2000 ፓውንድ ጀምሮ እስከ 200ሺ ፓውንድ ይደርሳል፡፡



የግምሎች ሽቅድምድም

በኳታር ተወዳጅ ከሆኑ ስፖርቶች የግምሎች ሽቅድምድም ዋንኛው ነው፡፡ ስፖርቱ በዶሃ ከተማ ውስጥ አልሻሃንያ የሚባል ዘመናዊ የመወዳደርያ ትራክ ተሰርቶለት የኳታር ባህል መለያ ሆኗል፡፡  የስፖርት አይነቱ የቱሪስት መስህብ ሆኖ ቆይቷል። ከዶሃ መሃል ከተማ የአንድ ሰአት የመኪና መንገድ ርቆ የሚገኘው አልሻሃኒያ በግመሎች የሚካሄዱ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ውድድሮችን ያስተናግዳል፡፡ በአንድ አመት ውስጥ ከ6000 በላይ ግመሎች በዚህ ውድድር ይሳተፋሉ፡፡ ተወዳዳሪ ግመሎች በሰዓት እስከ 40 ማይል ይሮጣሉ፡፡


ቡርጃ ዶሃ
በዶሃ ከተማ ከሚገኙ አስደናቂ  ህንፃዎች ቡርጃ ዶሃ ታወር አንዱ ሲሆን በፈረንሳዊው አርክቴክት ጂን ኖቭል የተሰራው ባለ 48 ፎቅ ህንፃ ነው፡፡


 ማቻቡስ
ማቻቡስ የኳታር ተወዳጅ ብሄራዊ ምግብ ነው፡፡ ከሩዝ፤ ስጋ፤ ሽንኩርት፤ ቲማቲም እና ከጀተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ጋር ተዋህዶ ይሰራል፡፡


ስፖርት አዘጋጅነት በኳታር
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ ኳታር ከዓለማችን ታላላቅ የስፖርት መድረኮች የመጀመርያውን ማዘጋጀቷ ነው፡፡  በ2006 እኤአ ላይ ያዘጋጀችውን የኤስያ ኦሎምፒክ በ2030 እኤአ ላይም እንድታስተናግድ ተመርጣለች፡፡


አዳዲስ ታሪኮች የበዙበት የዓለም ዋንጫ
22ኛው ዓለም ዋንጫ  በታሪክ ትንሿ አገር የምታዘጋጀው፤ በፈረንጆች አዲስ አመት ዋዜማ ለመጀመርያ ጊዜ የሚካሄድ፤ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ እግር ኳስ አፍቃሪዎችና ቱሪስቶች የሚሳተፉበት፤ በድምሩ እስከ  5 ቢሊዮን ተመልካች እንደሚያገኝም የተገመተ ፤ እስከ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል የተጠበቀ ነው፡፡



የምንግዜም ውዱ የዓለም ዋንጫ

በ220 ቢሊዮን ዶላር ወጭው የምንግዜም ውዱ ዓለም ዋንጫ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከብራዚልና ከራስያ ዓለም ዋንጫዎች በ10 እጥፍ፤ ከደቡብ አፍሪካ ዋንጫ በ64 እጥፍ የሚልቅ በጀት ወጥቶበታል፡፡



*********

ግሩም ሠይፉ_ አዲስ አድማስ ጋዜጣ 

https://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=30194:%E1%8B%93%E1%88%88%E1%88%9D-%E1%89%A0%E1%8C%89%E1%8C%89%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%8C%A0%E1%89%A5%E1%89%80%E1%8B%8D-%E1%8B%A8%E1%8B%93%E1%88%88%E1%88%9D-%E1%8B%8B%E1%8A%95%E1%8C%AB-%E1%8A%90%E1%8C%88-%E1%89%A0%E1%8A%B3%E1%89%B3%E1%88%AD-%E1%8B%AD%E1%8C%80%E1%88%98%E1%88%AB%E1%88%8D&Itemid=101

https://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=30164:%E1%8B%A8%E1%88%B0%E1%8B%93%E1%88%8A-%E1%89%B0%E1%88%B0%E1%88%9B-%E1%88%A5%E1%8A%90%E1%8C%A5%E1%89%A0%E1%89%A3%E1%8B%8A-%E1%8B%B2%E1%8D%95%E1%88%8E%E1%88%9B%E1%88%B2-%E1%89%A0%E1%8A%B3%E1%89%B3%E1%88%AD&Itemid=276


ዶሃ:- የባሕረ ሰላጤዋ ዕንቁ
(ከመኩሪያ መካሻ)

***************
የባብ ኤል ባህር ዳርቻ ነው። መሻሽቷል። ሂልተን ዶሃ ስምንተኛው ፎቅ ላይ ነው ያለሁት። ቁጥር 81ዐ። ከዚያ ፎቅ ላይ የዶሃ ከተማን ዙሪያ ገባ መመልከት ይቻላል። በቀን ብርሃን ዶሃን በወፍ በረር ከመቃኘት ይልቅ አመሻሹን መመልከት የልብ ሃሴትን ይሰጣል። ዶሃ የካጣር ዋና ከተማ ናት።


በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢተ ኢሳይያስ የተጠቀሰውን ምዕራፍ 21ን መለስ ብዬ አነበብኩ። ‹‹ዐውሎ ነፋስ ከደቡብ እንደሚመጣ፣ እንዲሁ ከሚያስፈራ አገር ከምድረ በዳ ይወጣል›› ይላል። አዎን! Qatar ካጣር፣ (አንዳንዶች ኳታር ይሏታል) ምድረ በዳ ናት። ዳሩ ግን የምታስፈራ ምድረ በዳ አይደለችም። እንዲያውም ‹‹ማርና ወተት የሚፈልቅባት›› ቢባል ያንሳታል እንጂ አይበዛባትም። ይህች ትንሽዬ የባህረ-ሰላጤ ሀገር በዕንቁና በጥቁር ወርቅ ሀብቷ መትረፍረፍ ሰማይ ጥግ ደርሳለች።
የዛሬዋ ካጣር (Qatar) ከመመሥረቷ በፊት ጥንታዊቷ ካጣር የዕንቁ ንግድ የሚካሄድባት ነበረች። ከቻይና፣ ከአውሮፓ፣ ከአፍሪካውያን ጋር ስትነግድ ኖራለች። በ2ዐኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ የበላይ ጠባቂነት ሥር ስትተዳደር ቆይታለች። በ1971 (እ.ኤ.አ.) ነው ነፃነቷን የተጐናፀፈችው። ነፃነቷን ከማግኘቷ በፊት እንግሊዞች ባወጡት የነዳጅ ሀብት ትንሽየዋ ሀገር ፈረጠመች። ነፃነቷን ከመጐናፀፏ አንድ ዓመት በፊት ደግሞ የተፈጥሮ ጋዝ አገኘች። ከዚህ በኋላማ ማን ይድረስባት። ሀብት፣ በሀብት ሆነች። ተድላና ደስታ በእያንዳንዱ ካጣሪ ቤት ውስጥ ገባ። በነገራችን ላይ የዜጋው አማካይ የገቢ መጠን ከ9,5ዐዐ ዶላር በላይ ሁኗል። እስቲ ይህን ገቢ ከኢትዮጵያውያን ገቢ ጋር አስሉት፣ ከ14 እጥፍ በላይ ነው። ይህ የሀገሪቱ ሀብት ለ3ዐዐሺ ዜጐቿ ይከፋፈላል። በካጣር አስገራሚው ነገር የውጭ ሀገር ዜጋ ከሀገሬው ዜጋ በአሥር እጥፍ መብለጡ ነው። በየስፍራው የፓኪስታንን፣ የህንድን፣ የሲሪላንካን፣ የኔፖልን፣ የፊሊፒንስን፣ የዩክሬይን ወዘተ. ዜጐች የሀገሪቱን ህይወት ወደፊት ይመራሉ። ለአንድ ካጣሪ አሥር የውጭ ዜጋ ይደርሰዋል እንደማለት ነው።
ሳውዲን ከሳውዲ ቤተሰብ (House of Saud) የወጡት እንደሚመሯት ሁሉ ካጣርን የአል-ታኒ ቤተሰቦች (House of Thani) ይመሯታል። የዶሃን የዘንድሮውን ዓለማቀፍ ፎረም (Doha Forum) በንግግር የከፈቱት ዘንካታው ሼህ አልታኒ (ታማም ቢን ሃማድ አልታኒ) ነበሩ። ዛሬ በዓለማችን ታዋቂውን የአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ 15ዐ ሚሊዮን ዶላራቸውን ሆጭ አድርገው ያቋቋሙት እኚሁ ሰው ናቸው። በካጣር ከሌላው የዐረብ ዓለም የተሻለ ዘመናዊነትና የሴቶች መብት ይከበራል። በዶሃ ጐዳናዎች ረጃጅም ሌክሰስና ጂኤምሲ (GMC) መኪናዎችን ሴቶቹ በነፃነት ያሽከረክራሉ። የእኛ ሴቶች የሚያዘወትሯት ቪትዝ ትኖር ይሆን? ብዬ ነበር፤ አንድም ለዓይን የለችም። የካጣር ሴቶች ተነግሮ የማያልቅ ውበት አላቸው። ከጥቁሩ ሂጃብ ውስጥ ለተመለከታቸው የዕንቁ ፈርጦች ናቸው። ከነዚሁ ሴቶች አንደኛዋና ወደ ዶሃ የጠሩኝ ወይዘሮ ሎልዋህ ራሽድ አልካጠር ነበሩ። አዲስ አበባ ሲመጡ የካጣር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሆነው ሲሆን፣ አሁን ዶሃ ፎረም ላይ ሳገኛቸው በስልጣናቸው ጨምረው ጠበቁኝ። በሚፍለቀለቅ ፈገግታቸው ተቀበሉኝ። ‹‹ሹመት ያዳብር!›› አልኳቸው። ‹‹በናንተ መጀን የኢትዮጵያ ምልኪ (Omen) መልካም ነበር፣ ይኸው ለዚህ በቃሁ›› አሉኝ። በሉ፣ ይበርቱ!›› ብያቸው ተለያየን።
ከፊት ለፊት በሻይ ጠረጴዛ ዙሪያ ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከባለቤታቸው ጋር፣ አምባሳደሯ ወ/ሮ ሳሚያ ያወራሉ። ጠጋ ብዬ ተወወቅሁ። አለፍ ስል ወርቅነህ ገበየሁን ተመለከትኩ። ለሠላምታ እጄን ስሰነዝር በቁመታቸው ልክ የሞቀ ሠላምታ ሰጡኝ። ከዐቢይ መንግሥት ወዲህ የባለስልጣኖቻችንን የባህርይ ለውጥ ተመለከትኩ። ከመጀነን ይልቅ ሠላምተኛ ሆነዋል። ከእኔ ትይዩ የፍልስጤሟ የፖለቲካ ሰውና ቃል አቀባይ ሃናን አሽራዊ ተከበው ያወራሉ። እሳቸውንማ መተዋወቅ አለብኝ ብዬ ተጠጋሁ። ተዋወቅኳቸው። ‹‹ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ ኦሪያና ፋላቺ የፃፈችውን የአቡ አማርን (የያሲር አረፋት የሽምቅ ስም) ቃለምልልስ ወደ ሃገሬ ቋንቋ ተርጉሜ አስነብቤያለሁ›› አልኳቸው። ፊታቸው ደስታን ረጨ። ፎቶ ራስ-ገጭ (ሰልፊ) ተነስተን ተለያየን። ሃናን ደስ አላቸው፤ እኔም ውስጤ ደስታን አዝሎ ተሰናበትኳቸው።
አለፍ እንዳልኩ በግራንድ ሸራተን መስተናገጃ ስፍራ ቡና ማፍያና ማቅረቢያ ስኒዎች የደረደረ ሰው ተመለከትኩ። ዕጣንም አጠገቡ እያጨሰ ሀድራው ሞቅ ብሏል። የቡና ሱሴ ውል አለብኝ። የሊሙ ኢናሪያን ቡና ሲለቅምና ሲጠጣ ላደገ ለእኔ ዓይነቱ ሰው ቡና ሁሉም ነገር ነው። የግራንድ ሸራተኑ ቡና ከእኛ ሀገሩ ቡና ጋር አይመሳሰልም። ልዩ አቀራረብና መልክ አለው። እንደኛው ዓይነት የፈረስ ጭራ የመሰለ ቡና አለመሆኑ ደንቆኛል። ጠጋ ብዬ ቡና ቀጂውን ሰዒድ አቡበከርን ‹‹ይቻላል?›› አልኩት። ግማሽ ፍንጃል ለቅምሻ የሚሆን ቀዳልኝ። ስመለከተው ጠጅ ሊያስቀምሰኝ የቀዳልኝ እንጂ ቡና አይመስልም። ለመጀመሪያ ጊዜ ብጫ ቡና ልጠጣ ነው። ፉት ስላት አለቀች። ፍንጃሉን መለስኩለት። ደገመኝና ቴምር ሰጠኝ፤ የሚገርም ቴምር፣ የሚገመጥ ቴምር ነበር።
የካጣር ቡና አይቆላም። ጥሬው ተጨምቆ ነው የሚፈላው። ለዚህም ነው መልኩ ብጫ የሚመስለው። ፍፁም አርኪ ቡና ነበር። ወዲያው ሱሴን አበረደልኝ። ‹‹ሹክረን›› ብዬ ሰዒድን ተሰናበትኩና ወደ ማረፊያዬ ተመለስኩ። የኤሌክትሮኒክ ቁልፉን ለበሩ አሸተትኩት። ተበረገደ። ለዓይን ያዝ ማድረግ ጀምሯል። የቁጥር 81ዐን መስኮት ከፍቼ ቀዝቃዛውን አየር ማግ፣ ማግ አደረኩ። የተለየ ጠረን አወደኝ። የቱስካኖ ሲጋራም፣ የሺሻም ሺታ መሰለኝ። ለማንኛውም ወደ ባህሩ ዳርቻ ልውጣ ብዬ ወደዚያው አመራሁ። የባብ ኤል ባህር ሰርጥ ዳርቻ አሸብርቋል። ከቡና ቤቱ የሚፈሰው ሙዚቃ ይንቆረቆራል። የሪታ ኦራ ‹‹Let you Love me›› ሙዚቃ ነው። የዌስት ቤይ የባህር ወጀብ ፋልማውን ተጠግቶ ይገማሸራል። ከባህሩ ወጀብ ጋር የቀዘቀዘ አየር እየማጉ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። ነጫጭ ጀለቢያቸውን የለበሱ አሚሮች፣ ሼኮች፣ የዶሃ እመቤቶች ተቀምጠው የሺሻቸውን ኵርቢት ይምጋሉ። ስለ ቢዝነስ ያወራሉ። ስለፍቅርም ሊሆን ይችላል የሚያወሩት። አንዱ ሼህ ከኋላዬ ከሎንደን የቢዝነስ አጋሩ ጋር በሞባይሉ ያወራል። ጆሮዬን ጣልኩበት። በዶሃ 2ዐ22 በሚዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ውድድር ስለሚያስገባው ዕቃ ነበር ድርድሩ። ‹‹ሦስት ቢሊዮን ነው?›› አለው። ጆሮዬን አላመንኩም። ሦስት ቢሊዮን! ‹‹ከሎንደን ወገን ከ2.6 እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር ቢሆን ነው›› ይለዋል። ‹‹ችግር የለም ቶሎ እንዲገባ ይሁን!››። ‹‹Let you love me›› ሙዚቃን በዓይን የማዬት ያህል በኦራ ድምጽ ሲንቆረቆር ወደ ሌላ ትዝታ ይዞ ይነጉዳል። ሺሻ ይጨሳል፣ ድርድር ይካሄዳል። የዶሃ ወይዛዝርት ለሁለት፣ ለሦስት፣ ሆነው በሺሻ ማጨሺያ ክፍሎች ሺሻውን ይምጉታል። የዶሃ ምሽት እንዲህ እየተንተከተከች ከሺሻው ጭስ ጋር የዶሃ ወይዛዝርትና አሚሮች ሃሳባቸውን አራግፈው ከዶሃ ሂልተን ወደየቤታቸው ይለያያሉ።
ከባህሩ ፋልማ ላይ ተቀምጨ ስቆዝም ባህሩ ላይ ቱሪስቶች ምሽቱን ተጠግተው በፈጣን ጀልባ ይንሸራሸራሉ። እኔን ባደረገኝ ያሰኛል። መልካም ያበሻ ቅናት። በመሃሉ ጨረቃዋ ሰማዩን ቀዳ ከባህሩ ስትወለድ ታየችኝ። እኔ ከልምዴ ጨረቃን ሰማይ ሲያዋልድ ነው የማውቀው። በገልፍ ሀገሮች ግን ባህር ቀዳ የምትወጣ ነበር የምትመስለው። ከዚያም ባህሩ ላይ ባውዛዋን ረጨች። ለካስ ዐረቦች ከጨረቃ ጋር ያላቸው ቁርኝት ከምንም ተነስቶ እንዳልሆነ ገባኝ። ድምቀቷ ጤፍ የሚያስለቅም ነበር። ‹‹Let you love me›› ቀጥሏል።
ፋታ ሳገኝ ‹‹መቀመጥ-መቆመጥ›› በሚለው መርህ መሠረት ወጣ ማለት ፈለግሁ። የሆቴሉን አስተናጋጅ ግብፃዊ መሀመድን ‹‹ዬት ሄጄ ታሪካዊ ነገር ብቃኝ ትመክረኛለህ?›› ስል ጠየኩት። ‹‹ወደ ሱቅ ዋቂፍ ሂድ!›› ሲል መከረኝ። መቼም ዶሃና የዶሃ ፎቆች የሚጠገቡ አይደሉም። ሁሉም ፎቆች ትናንት አልቀው ርክክብ የተደረጉ የሚመስሉ ጥርትና ልቅም ያሉ ናቸው። የፎቆች ዝናብ በዶሃ የዘነበ ይመስላል። ዲዛይናቸው ምርጥ የተባሉና አስደማሚ ናቸው። የዶሃ ዘንባባዎች እንደ ክብር ዘብ በሰልፍ ቆመው ይዘናፈላሉ። ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ፈጥረዋል። አንዱን አይተው ሳይጨርሱ ሌላኛው ፎቅ ይማርካል። የከተሜነት አዋሲስ (illusion) ሰቅዞ ባለ በሌለ ሀይሉ ይይዛችኋል። ምናለ የእኛ አርክቴክቶች ለአንዲት ቀን ዕድል አግኝተው ቢያዩዋት ያሰኛል። የአል-ታኒ ቤተሰቦች ገንዘባቸውን በሀገራቸው ግንባታ ላይ ማዋላቸውን መመስከር ይቻላል። ከቤጂንግ፣ ወይም ከኒውዮርክ ፎቆች በላይ የጐብኚን ዓይን መማረክ የሚችሉ ናቸው። ፎቆች ላይ የሚለጣጠፉ ማስታወቂያዎች ዓይን አይረብሹም። ምናለ የእኛዎቹ የከተማ አስተዳዳሪዎች ዶሃን በጐበኙ ያሰኛል። የኢቢሲው አብዱል ጀሊል በህንፃዎቹ ከመማረኩ የተነሳ ቀንም ማታም ህንፃዎቹን ፎቶ ያነሳል። ‹‹ምን ዓይነት ተአምር ነው?›› እያለ መልስ የሌለው ጥያቄ ይጠይቃል።
እስቲ የዶሃን ታላቅ ሱቅ ልጐብኝ ብዬ ወደ ሱቅ ዋቂፍ (Waqif) አመራሁ። ሱቅ ዋቂፍ ከዶሃ ዘመናዊነት መንጥቆ ወደ ቀድሞ የዶሃ ጥንታዊነት የሚወስድ ቋሚ ገበያ ነው። ይህ የደራ ገበያ አልባሳት፣ ቅመማ-ቅመሞች፣ ዕጣኖች፣ ሽቱዎች፣ የዐረብ ጣፋጮች፣ የስጦታ ዕቃዎችና ስዕሎች ይገኙበታል። ከካጣር ዘመናዊነት ዓለም አውጥቶ የካጣር ጥንታዊነትን ለመጎብኘት ትክከለኛው ሥፍራ ሱቅ ዋቂፍ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ባለእጆችና ባህላዊ ልብስ ሰፊዎች ይታዩበታል። የሶሪያ፣ የሊባኖስ መመገቢያ ሥፍራዎችና የሺሻ ማጨሻዎች ዓይንና ልብን ሰቅዘው ይይዛሉ። ዋጋቸው ግን ለአበሻ ኪስ የሚሆኑ አይደሉም። በዓይን ጠግቦ መውጣት የሚቻልበት ሥፍራ ሱቅ ዋቂፍ ብቻ ይመስለኛል።
ከጣርን ከገልፍ ሀገሮች ሁሉ እጅግ ተፈላጊ ያደረጋት ስትራቴጂካዊ አቀማመጧ ነው። የአሜሪካና የእንግሊዝ የአየርና የህዋ ኦፕሬሽን ማዕከል የሚገኘው እዚያ ነው፤ በአል ኡዴድ የአየር ምድብ። ይህ የኃያላን ሀገራት የዕዝና ቁጥጥር ማዕከል ከኢራን እስከ አፋጋኒስታን ዘልቆ 17 ሀገራትን ይቆጣጠራል። ስለዚህ ካጣር ዋና ስትራቴጂካዊ ማዕከልና ለአሜሪካኖቹ እጅግ አስፈላጊ ሀገር ናት። በዚህ ልዩ ቦታዋ ዓለማቀፋዊ ኮንፈረንሶችን ታዘጋጃለች። የዘንድሮው የዶሃ ፎረም እንኳ 4ዐዐዐ ሰዎችን ከ1ዐዐ ሀገራት አስተናግዷል። በዚህ ሸብ-ረብ ውስጥ ዋነኛውን ሚና የሚወጣው አልጀዚራ ሲሆን፣ የአልጀዚራ ጋዜጠኞች በአስተባባሪነት፣ በመድረክ መሪነት፣ በጠያቂነት፣ ሪኮርድ በማድረግ ይሳተፋሉ። የእኛን የኢትዮጵያውያንን ጉዞ ያደራጀልን ወዳጄ፣ ዕውቁ ጋዜጠኛና የአልጀዚራ የኢትዮጵያ የቢሮ ሃላፊ መሀመድ ጠሃ ተወከል በዚህ አጋጣሚ ሊመሰገን ይገባል። ሀገር ቤት ገብቼ ኢ-ሜሌን ስከፍት ሙሉ ዶክመንቱ ደረሰኝ። ደስም አለኝ።
የዶሃ ፎረም ስብሰባ እንደተጠናቀቀ ጉብኝቴን የቀጠልኩት በአልጀዚራ ጣቢያና የሚዲያ ማሠልጠኛ ተቋም ጉብኝት ነበር። አልጀዚራ ሚዲያ ከሥራውና ካለበት ህንፃ ጋር ሲወዳደር ‹‹አልጀዚራ እዚህ ሆኖ ነው እንዴ ዓለምን የሚያነጋግር ሥራ የሚሠራው?›› ያሰኛል። የተቋሙ አባል የሆነውና አስጐብኚያችን ሙንታሲር ሙራይ እንደነገረኝ ‹‹ለሚዲያ ጥንካሬ ዋናው ህንፃና ዕቃ ሳይሆን የያዘው ሙያተኛ ነው ወሳኙ›› ሲል ነበር የሰው ኃይልን ወሳኝነት የገለፀልኝ።
*****
የመጨረሻው የዶሃ አዳሬ ዶሃን ብቻ ሳይሆን ሀገሬን እንዳስብ አደረገኝ። አንዲት የባህረ-ሰላጤ ትንሽ ሀገር 3 ሚሊዮን ለሚበልጡ የውጭ ሀገር ዜጐች የሥራ ዕድል ፈጥራ ስታሰራ ስመለከት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ዬት ነን? እላለሁ። ቅናት አይሉት የውድድር አባዜ ብቻ በእዝነ-ልቡናዬ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ተመላለሱብኝ። ዛሬ የሚታየው የኢትዮጵያውያን እርስ በርስ መናከስ፣ መበላላትና የሰው ልጅ ሊፈጽመው ይችላል ተብሎ የማይታሰብ የአውሬነት ባህርይ ከየት መጣ? ስል ጠየቅኩ። ይህች የባህረ-ሰላጤ ዕንቁ ከተማና የእኛ ከተሞች ህይወት በንጽጽር በዓይኔ እየተደቀኑ በማይጐረብጠው፣ እጅግ ምቾት - በምቾት በሆነው 81ዐ ክፍል ውስጥ ዕንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር ነቃሁ። ለካስ ምቾትም እንቅልፍ ይነሳል?
ወለል ብሎ የዶሃ ሰማይ በርቷል። በመስኮት ስመለከት የባብ ኤል ባህር ዳርቻ ህይወት እያንሰራራ ነው። የባህረ-ሰላጤው ባህር ፋልማውን እየገጨ ይፎክራል። የዶሃ-ህይወት መንተክተኳን ቀጥላለች። በስሱ የተለቀቀ የEasy Listening ሙዚቃ ጆሮ ሰርስሮ ይገባል። የልብ ሀሴትን ይሰጣል። ‹‹Lake of Peace›› ሙዚቃ ነበር የሚንቆረቆረው።
አሁን ሰዓቱ ደረሰ። በፍቅር የጣለችኝን ዶሃ ለቅቄ መብረሬ ነው። ከኢትዮጵያ ከመጣነው የቡድን አባላት ጋር የሃማድ አለማቀፍ አይሮፕላን ማረፊያን መንገድ ተያያዝነው። የዶሃን ልዩ ከተማነት፣ የህዝቡን ሥርዓትና እንግዳ አክባሪነት እያደነቅን ሃማድ አለማቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ ደረስን። በአይሮፕላን ጣቢያው ልክ እንደ ግራንድ ሸራተኑ የካጣር ቡና (ቃዋ ነው እነሱም የሚሉት) ተፈልቶ ጠበቀን። አንድ ፍንጃል ቃዋዬን አወራርጄና ቴምር ቀምሸበት ዶሃን ተለየሁ። ዶሃ የባህረ-ሰላጤዋ ዕንቁ ከተማ ሁሌም ከአእምሮዬ የምትጠፋ አትሆንም። የሪታ ኦራ ‹‹Let you love me›› አሁንም በውስጤ ይሞዝቃል።



https://www.facebook.com/photo/?fbid=5979201378771420&set=a.100394486652168

https://www.youtube.com/watch?v=TiTg-op7yc0

2፡የዓለም ዋንጫ 2022፡

የዓለም ዋንጫ 2022

የዓለም ዋንጫ 2022

የዓለም ዋንጫ 2022

የዓለም ዋንጫ 2022

No comments:

Post a Comment