ከደራሲያን ዓምባ

Tuesday, August 8, 2023

የኢትዮጵያና የሩሲያ ወዳጅነት


የኢትዮጵያና የሩሲያ ወዳጅነት 

ከአፄ ምንሊክ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)


ንደ መንደርደሪያ

የሩሲያንና የኢትዮጵያ ወዳጅነትና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታሪካዊ ጅማሬው ምን ይመስል ነበር የሚለውን ከታሪክ መዛግብት በጥቂቱ ለመፈተሽ ልሞክር እስቲ፡፡ 

ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር የጋራ ግንኙነት ለመመሥረት ፍላጎት ማሳየት የጀመረችው በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ አካባቢ ነው፡፡ የታሪክ መዛግብትና ሰነዶች እንደሚያሳዩት ከዚያ ቀደም ብሎ የሁለቱ አገሮች (የኢትዮጵያና የሩሲያ) ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ምዕመናን ኢየሩሳሌም ለመንፈሳዊ ጉዞ በሚሄዱበት ጊዜ ይገናኙ ስለነበር፣ አንዳቸው ስለአንዳቸው መረጃውና ዕውቀቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ነበራቸው፡፡

የታሪክ መዛግብት እንደሚጠቁሙት እ... 1673 ሎሬንቲየስ ሪንሁበር (Laurentius Rinhuber) የተባለ የዛር አሌክሲ አገልጋይ፣ ሩሲያ የኦቶማን ቱርክ ኃይልን ለመቋቋም ከኢትዮጵያ ጋር ትብብር እንደትፈጽምና የሩሲያ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ እንዲላክ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ በወቅቱ ይህ ሐሳብ በሩሲያ መንግሥት ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ የነበረ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሐሳቡን ዕውን ለማድረግ ሳይቻል ቀርቷል፡፡

ይሁን እንጂ ሩሲያውያን ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በይበልጥ ለማወቅ አልቦዘኑም ነበር፡፡ ሩሲያውያን በወቅቱ ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ለማጥናት እንደ መረጃ ይጠቀሙባቸው ከነበሩት ጥንታዊ የታሪክ ሰነዶች መካከልም፣ በጀርመናዊው የቋንቋና የታሪክ ሊቅ በሂዮብ ሉዶልፍ (Hiob Ludolf) የተጻፈውን ‹‹Historia Aethiopica›› የተሰኘው መጽሐፍ ይጠቀሳል፡፡

19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት በዋነኝነት በኢትዮጵያ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የተለያዩ የሩሲያ ሰዎች ከኢትዮጵያ የተለያ የግዕዝ መዛግብትን ይዘው ወደ ሩሲያ ከመሄዳቸውም ባሻገር፣ ሩሲያውያኑ በአገራቸው የግዕዝን ቋንቋ እስከ ማስተማርም ደርሰዋል፡፡ እ... 1829 እስከ 1836 .. በሩሲያ (University of Kharaov) የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡

የአፄ ምንሊክና የሩሲያ ወዳጅነት

1895 .. አፄ ምንሊክ በፊታውራሪ ዳምጠው የተመራውን የመጀመርያውን የዲፕሎማቲክ ልዑክ ወደ ሩሲያ ላኩ፡፡ ይህ ሲሆን ጣሊያን ኢትዮጵያን በሞግዚነት እንደምታስተዳድር የሚገልጸው የውጫሌ ውል በጣሊያን በኩል ይፋ ሆኖ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ በኩል የውጫሌ ውል ተቀባይነት እንደሌለው የተገለጸ ቢሆንም፡፡ ቢሆንም ጣሊያን ይህን በኢትዮጵያ በኩል ውድቅ የተደረገውን የውጫሌ ውል በመጥቀስ የኢትዮጵያውያን ልዑካን ኦፊሴላዊ ጉብኝት ላይ ጥያቄ አንስታ ነበር፡፡

ሩሲያ ግን አፄ ምንሊክ የላኩትን የኢትዮጵያ ልዑክ በሉዓላዊ አገር ልዑክነት ዕውቅና በመስጠት በተገቢው ወግና ማዕረግ በክብር ነበር የተቀበለችው፡፡ በውጭ ጉዳይም ሚኒስትሯ በኩልም ኢትዮጵያን እንደ ሉዓላዊ አገር ብቻ እንደምታውቃትና ግንኙነቷም በዚያ መንገድ መሆኑን ጠቅሳ ለጣሊያን ጥያቄ መልስ ሰጥታ ነበር፡፡

የልደታው ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል - 1968 ዓ.ም

በፊታውራሪ ዳምጠው ከተመራው ልዑክ በኋላ የሩሲያ መንግሥት በጊዜው የጣሊያን ወረራ ሥጋት ለነበረባት ኢትዮጵያ የመሣሪያ ሽያጭ አድርጋ ነበር፡፡ ምንም እንኳን መሣሪያው በታቀደለት ጊዜ ለዓድዋ ጦርነት ባይደርስም፣ ከመሣሪያ ሽያጩ በተጨማሪ የሩሲያውያን የቀይ መስቀል ማኅበር አባላት የጦርነቱን ቁስለኞች ለመርዳት በጦርነቱ ማግሥት በኢትዮጵያ ተገኝተዋል፡፡

ይህ የሩሲያ የሕክምና ቡድን በዓድዋ ጦርነት ከቆሰሉት ወታደሮች በተጨማሪ፣ በጠቅላላው ከ30,000 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች በአዲስ አበባና በሐረር የሕክምና ዕርዳታ ማድረጉን የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ሩሲያውያን ሐኪሞች ታማኝ የአፄ ምንሊክ የግል ሐኪሞች ሆነው እስከ መመረጥም ደርሰው ነበር፡፡     

ከሩሲያ/ከመስኮብ ወደ ኢትዮጵያ ስለመጡት ልዑካንና አፄ ምኒልክ ወደ ሩሲያ የላኩትን መልዕክተኞቻቸው በተመለከተ፣ የዳግማዊ አፄ ምንሊክ ጸሐፊ ትዕዛዝ የነበሩት አለቃ ገብረ ሥላሴ፣ ‹‹ታሪክ ዘዳግማዊ ምንሊክ›› በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ተርከውታል፡፡

በዚያን ዘመን የመስኮብ መልዕክተኞች መጥተው ከባህር ጠረፍ ደረሱ የሚል ወሬ ተሰማ፡፡ አፄ ምንሊክም ለራስ መኮንን እነዚያን የመስኮብ መልዕክተኞች አክብረህ ተቀብለህ ስደዳቸው ብለው ላኩ፡፡ እነዚያም መልዕክተኞች አዋሽን ተሻግረው ምንጃር በደረሱ ጊዜ በያደሩበት መስተንግዶ እየተሰናዳላቸው፣ በመስተንግዶ ደስ እያላቸው በጉዟቸው የሚቀመጡበት ሁለት  የተሸለሙና ያጌጡ በቅሎዎች ሰደዱላቸው፡፡

መልዕክተኞቹም መጥተው በአዲስ አበባ ከተማዋ አጠገብ በደረሱ ጊዜ የሚቀበላቸው ሰው ታዞ ተሠልፎ ሂዶ በእንቢልታና በመለከት ተቀበሏቸው፡፡ በታላቅ ክብር በተድላና ደስታ ከጃንሆይ ተገናኙ፡፡ የሚያርፉበትን ቤት አምሮ ተዘጋጅቶ ቆይቶ ነበርና ከዚያ ሄደው ገቡ፡፡ ድርጓቸውም ታዞ ሄደላቸው፡፡ ይኼውም ድርጎ እስኪሄዱ ድረስ አልጎደለባቸውም፡፡


በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያና የመስኮብ ፍቅር ተጀመረ፡፡ ነገር ግን የአፄ ምንሊክ ደግነት ሁሉን ያሸንፋል፡፡ በፍቅር ከሆነ የማንም አገር ሰው ቢመጣ ማክበር፣ መውደድና መስጠት ነው እንጂ መሰልቸት የለም፡፡

የመስኮብ መልዕክተኞችም የኢትዮጵያ ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው የሚሄዱበት ቀን በደረሰ ጊዜ፣ አፄ ምንሊክ ወደ መስኮብ ንጉሠ ነገሥት የሚሄዱ መልዕክተኞችን አዘዙ፡፡ የታዘዙትም ሰዎች ስማቸው ይህ ነው፡፡ ፊታውራሪ ዳምጠው፣ ቀኝ አዝማች ገነሜ፣ መምህር ገብረ እግዚአብሔር ሌሎችም መኳንንት ተጨምረው እንዲሄዱ ተዘጋጁ፡፡

ለመስኮብ ንጉሠ ነገሥት ለኒቆላዎስ ቄሣር በረከት የሚሄድ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ዘውድ፣ ማለፊያ የወርቅ መስቀል፣ አራቱ ወንገጌል መጻሕፍት፣ ሌላም የኢትዮጵያ ብዙ ገፀ በረከት ሰደዱ፡፡ በበኩላቸው ንግሥቲቱ እቴጌ ጣይቱም ለመስኮብ ንግሥት ለአሌክሳንድራ በረከት የሚሄድ ዕፁብ ድንቅ የተባለ በወርቅ አጫዋች ያጌጠ የሐር መሶብ፣ የሴት ወ/ሮ መሣሪያ ወርቅ፣ የእግር ክታብ ወርቅ፣ አልቦ ወርቅ፣ ጠልሰም ወርቅ፣ ድሪ ወርቅ፣ ወለባ ይህን ሁሉ አዘጋጅተው ሰደዱ፡፡

እነዚህም የአፄ ምንሊክ መልዕክተኞች ከመስኮብ መንግሥት በደረሱ ጊዜ በታላቅ ክብር ተቀበሏቸው፡፡ ዓይነተኛውን/የመልዕክተኞቹን መሪ ፊታውራሪ ዳምጠውን በወርቅ ባጌጠ ሠረገላ አስቀምጠው ወደ ተዘጋጀላቸው ማረፊያ ቤት ወሰዷቸው፡፡ ከከተማው በገቡ በአምስተኛው ቀን ለንጉሠ ነገሥቱ ኒቆላዎስ ቄሳር፣ ለንግሥቲቱም ለአሌክሳንድራ የያዙትን ስጦታ/በረከት አቀረቡ የሚል ቃል ወደ አፄ ምንሊክ መጣ፡፡

እንደ መውጫና መደምደሚያ

ከሰሞኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) የሩሲያ ጉብኝትና ከአገሪቱ ወሳኝ ሰው ከሆኑት ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ያደረጓቸው ስምምነቶችና ውይይቶች ትልቅ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ይህም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ አንድም ሁለቱ አገሮች ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ አገራችን የሺሕ ዘመናት ታሪክና ሥልጣኔ ባለቤት፣ የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ዓርማ የአፍሪካ መዲና የመሆኗ እውነታ በዓለም አቀፍ መድረክ ልዩ ሥፍራ ስለሚያሰጣት ነው፡፡


ከዚህ የታሪክ ሀቅ ጋር በተያያዘም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (/) የሩሲያ ጉብኝት፣ በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው ዓለም ትልቅ አንድምታ እንዲኖረው አድርጓል፡፡

በሌላም በኩል ደግሞ ምዕራባውያንና አሜሪካ፣ በተቃራኒው ደግሞ ሩሲያ በዲፕሎማሲው መስክና በኃይል አሠላላፍ ረገድ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የተያያዙትን የገመድ ጉተታ አገሮችን ከጎናቸው ማሳለፍ ዋነኛ ጉዳያቸው በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ረገድም የአፍሪካ መዲና፣ የአፍሪካውያንና የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ዓርማ፣ የዓላማችን ታላላቅ ሃይማኖቶች ቤት፣ በአፍሪካና በአፍሪካ ቀንድ ወሳኝ የሆነ ጂኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥን የያዘች እንደ ኢትዮጵያ ያለ አገርን ኃያላኑ አገሮች ከጎናቸው እንድትሆን/እንድትቆም ማድረግ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ከመሆኑ እውነታ ጋርም የሚያያዝ መሆኑ ነው፡፡

ይህን የኢትዮጵያንና የሩሲያን ታሪካዊ ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል፣ ባለፈው ዓመት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በአፍሪካ የአፍሪካ ኅብረት መገኛና መዲና በሆነችው በሆነችው አዲስ አበባ ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡ ይህን የላቭሮቭን ጉብኝት ተከትሎ መቀመጫውን በሩሲያ ያደረገው አሜሪካዊ የፖለቲካ ተንታኝ አንድሩ ኮሪብኮ ባወጣው ጽሑፍ፣ ‹‹የሩሲያ-ኢትዮጵያ ወዳጅነት የባለብዙ አቅጣጫ አጋርነት ማሳያ ሞዴል መሆኑንና የላቭሮቭ ጉብኝት ሩሲያ ከመላው የአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን የጋራና ሁለገብ ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል ያላትን ፍላጎት ያሳየ መሆኑንም፤›› አትቶ ጽፎ ነበር፡፡


አንድሩ፣ ‹‹አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ብቻ ሳትሆን የመላው አፍሪካውያን የፀረ ቅኝ ግዛት ተጋድሎ ትእምርት/ሲምቦልና የፓን አፍሪካኒዝም ታሪካዊ መገኛ በመሆኗ የአኅጉሩ መንፈሳዊ መዲና ናት፤›› ብለው በርካቶች እንደሚያምኑም በጽሑፉ አውስቷል፡፡

ሩሲያና ኢትዮጵያ ለቀሪው ዓለም በተለይም ለአፍሪካ አገሮች እንዴት ከቅኝ ግዛት ነፃ መውጣት እንደሚቻል በማሳየት ረገድ ግንባር ቀደም ሆነዋልም ነው ያለው የፖለቲካ ተንታኙና ጸሐፊው አንድሪው፡፡ በጽሑፉ ማጠቃለያም፣ ‹‹ላቭሮቭ ወደ አዲስ አበባ ያደረጉት ጉዞ የሩሲያና የኢትዮጵያ መፃዒ ግንኙነት ጠንካራ እንደሚሆን ከወዲሁ የጠቆመ ነው፤›› ሲል ነበር የደመደመው፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ!

 


SOURCE:- https://www.ethiopianreporter.com/121093/

https://www.dw.com/am/%E1%8D%91%E1%89%B2%E1%8A%95%E1%8A%93-%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB%E1%8B%89%E1%8B%AB%E1%8A%91-%E1%89%A0%E1%88%A9%E1%88%B5%E1%8B%AB/a-50043226



No comments:

Post a Comment