ከደራሲያን ዓምባ

Thursday, June 12, 2014

ካሳየን አጣሁት – አቦነሽ አድነው


 

ለጎንደሩ ጀግና ለጠፋው መቅደላ፣
አብሮ አልቅሱለት ቋራና ኦሜድላ፣
ፍቅሩም ሳይወስነው በትግሬ በወሎ፣
እራሱን የጣለው ጦቢያን አድን ብሎ።
ምንጊዜም ይወራል ዝናው፣
በታሪክ አይሞትም ጀግናው፣
ይጠራል ስሙ በዚህች ምድር፣
ላገሩ ስለዋለው ብድር።

በሰንበት ባውዳመት ተጎድቼ በባል፣
እንግዲህ ምንጠቅሞኝ ተዋበችስ ብባል፣
ከፍቅሬም ካካሌም ባንዴ እየተለየሁ፣
ቀረሁኝ በተስፋ እያልኩ ዓለማየሁ።



 እናቴ ሞሽራ ልትድረኝ ለጀግና፣
ተነስቶ ባገሩ አንድነት ያፀና፣
ሚስት ናት ገረድ ናት ሲለኝ እንዳልኖረ፣
ነፍሱን ላገር ሰጥቶ የኔ ካሳ ቀረ።
ከንግስ ከግርማዊነት ያኮራል ያለው ጀግንነት፣
ወገኔ ጥለህ ተሰደድ እያየው የሱ ጀግንነት።
ዓለማየሁ ብሎ ሀዘንን መቀበል፣
ዕጣው በኔ ሲደርስ እንግዲህ ምን ልበል፣
ጎንደርን ማሳለፍ ምንስ ጎደለብኝ፣
መቅደላ ነው እንጂ ካሳው የቀረብኝ።
 
ሙሉ ቤቴን ሳጣው አላልኩም እየዬ፣
የኑሮ መከታ ባላገር ነው ብዬ፣
ተዋቡ ለሚለኝ ለፍቅሬም ሳይሳሳ፣
ከኔ ለበለጠው ለአገር ሆኗል ካሳ።

ማተብ በጥሶ ቃል ከማጠፍ፣
ይሻላል ቆርጦ ነፍስን መቅጠፍ፣
ሆነልት እንጂ ታሪክ ርስቱ፣
አላጓጓውም ቤተመንግስቱ።
ይሄ ነው ቆራጥ ይሄ ነው ጀግና፣
በታላቅ ስራው ፍቅሩን የሚያፀና።


ስሙ አባታጠቅ የሱ ፈረስ፣
ያውቃል ካሰበው ፈጥኖ መድረስ፣
ቼ እያለ ገስጋሽ ብርቱ ጋላቢ፣
ሜዳነው ሲሉት የሚገኝ ግቢ።
ዘውዱ ነበርኩኝ በሚስትነቴ፣
ንጉሴን አጥታ ጠፋች እናቴ፣
በጎዶሎ ቀን በዕድለ አንካሳ፣
አልኖርም አለች ነፍሴ ያለካሳ።



 


ማተብ በጥሶ ቃል ከማጠፍ፣
ይሻላል ቆርጦ ነፍስን መቅጠፍ፣
ሆነልት እንጂ ታሪክ ርስቱ፣
አላጓጓውም ቤተመንግስቱ።
ይሄ ነው ቆራጥ ይሄ ነው ጀግና፣
በታላቅ ስራው ፍቅሩን የሚያፀና።






https://www.youtube.com/watch?v=ZVKUwPtV5ec 

Tuesday, June 3, 2014

የሙዚቃ ሊቁ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ

የሙዚቃ ሊቁ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ
(ከ 1930 - 1990 ዓ.ም)
በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ እውቀት ላይ የተመሠረተ ትምህርት በመማር የላይኛው
ጥግ ላይ የደረሰ ነው። በሀገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሙዚቃ ት/ቤት እንዲከፈት አስተዋፅኦ
ካደረጉ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። በዚሁ የሙዚቃ ት/ቤት ማለትም በቅዱስ ያሬድ ሙዚቃ
ት/ቤት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዳይሬክተር ሆኖ አገልግሏል። ከዚህምአልፎ በዓለም
አቀፍ ደረጃ የሙዚቃን ጥበብ እና መንፈስ ሲያስተምር የኖረ ነው። ዛሬ የሕይወት ታሪኩን
በጥቂቱ የምናነሳሳለት ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ሊቅ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ነው። አሸናፊ
ከበደ የተወለደው እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በ 1930 ዓ.ም ነበር። አሸናፊ ከበደ ገና
በህፃንነቱ ድክ ድክ ሲል ነው ከሙዚቃ ጋር የተዋወቀው። የተዋወቀበትም አጋጣሚ በእናቱ
በኩል ነው። ወላጅ እናቱ ሁሌም ትዘምራለች። መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ሀረጋት
ከመዝሙረ ዳዊት ውስጥ እያወጣች ትዘምራለች።
ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ዜማዎችን ታንጐራጉራለች። ታዲያ ይህ መዝሙር እና እንጉርጉሮ በሕፃኑ
አሸናፊ ልብ ውስጥ፣ ጭንቅላት ውስጥ እና በአጠቃላይ እዝነ ልቡናው ውስጥ እየተዋሀደው
መጣ። የሙዚቃ ረቂቅ ስሜት እና ፀጋ በእናቱ በኩል ወደ እርሱ ተሸጋግራ አሸናፊ ውስጥ
ጓዟን ጠቅልላ ገባች። የሥነ-ጽሑፍ መምህሩ እና ታዋቂ ገጣሚ የሆኑት ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በ
1980 ዎቹ አጋማሽ ላይ Ethiopian Review በተባለ መፅሔት ላይ እንደፃፉት ከሆነ
የሙዚቃ ለዛ እና ጣዕም ኮተቷን ሰብስባ ወደ አሸናፊ ከበደ ሰብዕና ውስጥ የገባችው በእናቱ
በኩል ነው። እናቱ አሸናፊ ከበደ የሚባል የሙዚቃ ሊቅ ፈጥራለች እያሉ ፅፈው እንደነበር
አንብቤያለሁ። ታዲያ ምን ያደርጋል ይህች እናት ተልዕኮዋን ፈፀመች መሰል፣አሸናፊ ከበደ
ገና የዘጠኝ ዓመት ጮርቃ ሳለ ሕይወቷ አለፈች።
ግን የዘራቻት ዘር ዘላለማዊ ፀጋ ተጐናፅፋለችና ከአሸናፊ ከበደ ጋር አብራ አደገች፤ በኋላም
በአሸናፊ በኩል ተወለደች። ከዚያም እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ
እንዳስደሰተች ትኖራለች። እ.ኤ.አ በ 1999 ዓ.ም ኪምበርሊን ቺንታ የተባሉ ፀሐፊ ስለ
አሸናፊ ከበደ የሕይወት ታሪክ ፅፈው ነበር። ርዕሱም The Scholarship and Art of
Ashenafi Kebede (1938-1998) የሚል ነበር። በአማርኛ “ምሁሩ እና ጥበበኛው
አሸናፊ ከበደ ከ 1930-1990 ዓ.ም” ብለን ልንተረጉመው እንችላለን። ታዲያ በዚህ ጽሁፍ
ውስጥ ፀሐፊው ከሚገልጿቸው ሃሳቦች መካከልየአሸናፊ ከበደን የእውቀት ርቀት እና ጥልቀት
ነው።
እንደ ፀሐፊው አባባል ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ኢትዮጵያ ካሏት (ካፈራቻቸው)
የባህልናየማንነት ቅርሶች መካከል በሙዚቃው ዓለም ትልቁን ስፍራ የሚይዝ ነው። አሸናፊ
የኢትዮጵያ የባህል ቅርስ ነው። የሙዚቃ አቀናባሪ ነው። መራሔ-ሙዚቃ /Conductor/
ነው። የሙዚቃ ታሪክ ተመራማሪ ነው። የሙዚቃ መምህር ነው። የልቦለድ ድርሰት ፀሐፊ
ነው። ባለቅኔ ነው። ወደር የማይገኝለት ጥበበኛ እያለ ኪምበርሊን ቺንታ ፅፏል።
Professor Ashenafi Kebede, one of Ethiopia’s greatest
cultural treasurescomposer, conductor, ethnomusicologist,historical musicologist, music educator, novelist and poet.
እየተባለ ለፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ተፅፏል።



አሸናፊ ከበደ አብሮት ያደገውን የሙዚቃ ፍቅር ቅርፅ ሊያሲይዘው በ 1950 ዓ.ም ወደ
ዩናይት ስቴትስ አሜሪካ ተላከ። እዚያም Eastman School of Music ከተባለ
ዩኒቨርሲቲ በሙዚቃ ጥናት በ B.A ድግሪ ተመረቀ። ከዚያም ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ መጥቶ
የቅዱስ ያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት እንዲከፈት ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት መካከል አንዱ ስለሆነ
በተጨማሪም ደግሞ ሙዚቃን እንደ ጥበብ ተምሮ የመጣ ወጣት በመሆኑ የመጀመሪያው
የት/ቤቱ ዳይሬክተር ሆኖ ተሾመ። በዚህ በቅዱስ ያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት ለአምስት ዓመታት
ካገለገለ በኋላ እንደገና የሁለተኛ ድግሪውን ሊያጠና ወደ አሜሪካ ተጓዘ። Wesleyan
University ገብቶ በ 1960 ዓ.ም የማስትሬት ድግሪውን ተቀበለ። የሙዚቃ ሊቁ አሸናፊ
ከበደ በዚህ ብቻም አላቆመም። የሙዚቃን ጥግ ማወቅ ስላለበት የዶክትሬት ድግሪውንም
ሊያጠና አመለከተ። ከዚያም የመግቢያ ፈተና ተሰጠው። ፈተናውንም በከፍተኛ ውጤት
አልፎ የዶክትሬት ድግሪውን መማር ጀመረ። በአስገራሚ ብቃት እና ችሎታ የአራት ዓመቱን
ትምህርት በሦስት ዓመት ውስጥ አጠናቆ በ 1963 ዓ.ም የዶክትሬት ድግሪውን እንዳገኘ
የሕይወት ታሪኩ ያወሳል።
አሸናፊ ከበደ በሙዚቃው ዓለም የተማረውና የዶክትሬት ድግሪውን ያገኘው ሙዚቃን
ከባሕል፣ ከታሪክ፣ ከማንነት፣ ከቋንቋ፣ ከሰው አንፃር በሚያጠናው የትምህርት ክፍል ማለትም
ethno-musicology የትምህርት ዘርፍ ነው። በዚሁ የትምህርት ዘርፍ የዶክትሬት
ድግሪውን ያገኘው በከፍተኛ ማዕረግ ነው። የሚገርመው ማዕረጉ አይደለም። በዚህ
የትምህርት ዘርፍ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ የመጀመሪያው ተመራቂ እንደሆነም ተፅፎለታል።
ስለዚህ አሸናፊ የባሕል፣ የታሪክ፣ የማንነት፣ የቋንቋ እና የሰው ልጅን ስነ-ልቦና በሙዚቃ
ዓለም ውስጥ የሚያጠና እና ሙዚቃንም የሚቀምር ባለሙያ ነበር። አሸናፊ ከበደ፣ የሕይወት
አጋጣሚ ጠለፈችውና አሜሪካ የምትባል ሀገር አለቅህም ብላ ያዘችው። በተፈጥሮ እና
በትምህርት የተሰጠውን ፀጋ በአሜሪካ ልዩ ልዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ማስተማር ቀጠለ።
በመጀመሪያ ያስተምር የነበረው Queens College ውስጥ ነበር። እዚያ የተወሰኑ
ዓመታትን ካገለገለ በኋላ የማስትሬት ድግሪ ተመራቂ ተማሪዎች ወደሚማሩበት The City
University of New York ተብሎ ወደሚጠራው ተቋም ተዘዋውሮ ማስተማሩን
ቀጠለ። ከዚያም Brandeis University በሚባለው የሙዚቃ ት/ቤት ውስጥ አስተማረ።
ከነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ሌላም በተለያዩ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተጋባዥ ፕሮፌሰር
እየሆነ ሙዚቃን ለአሜሪካ ያስተምር ነበር።
አሸናፊ ከበደ ከማስተማሩ ጐን n ለጐን በስፋት የሚታወቅበት ችሎታው የጥናትና የምርምር
ሰው መሆኑ ነው። በተለይ በአፍሪካ ባሕሎችና ታሪኮች ላይ የተለያዩ የምርምር ወረቀቶችን
አቅርቧል። ከአፍሪካም ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ እያተኮረ የዚህችን ሀገር ጥንታዊ ስልጣኔና
ማንነት እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የዋለችውን የታሪክና የባህል ብሎም
የስልጣኔ ውለታ በጥናቱ ያካትት ነበር። ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፣ 
ዓለም ገናከእንቅልፉ ሳይነቃ በዝማሬና በዜማ በኩል ያበረከተውን አስተዋፅኦ አሸናፊ ለዓለም
ሲያስተዋውቅ ኖሯል።
አሸናፊ ከበደ በተለያዩ አፍሪካዊ ጥናቶቹ እና ምርምሮቹ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ በሙዚቃው
ዓለም ተቀብሏል። ወደ ፍሎሪዳ ስቴትስ ዩኒቨርሲቲም በመሄድ የጥቁሮች የባሕል ማዕከል
/Center for Black Culture/ ተብሎ በሚጠራው ተቋም ውስጥ ዋና ዳይሬክተር ሆኖ
ተሾመ። ይህ ተቋም በኋላ “የአፍሪካ አሜሪካውያን የባህል ማዕከል” በሚል መጠራት
ጀምሯል። እስከ አሁንም ድረስ መጠሪያው Center for African American Culture
እየተባለ ነው። ዳይሬክተሩ ደግሞ ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ሊቅ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ
ነበር።በዚህ ታላቅ ተቋም ውስጥ ዳይሬክተር ከሆነ በኋላም፤ ጥቁሮች እና ነጮች እንደ ሰው
የሚያገናኛቸውን ባሕላዊ፣ ሙዚቃዊ እና ታሪካዊ ጉዳዮችን እያነሳሳ ያወያያል። ያቀራርባል።
የተለያዩ ታላላቅ የዓለማችንን የሙዚቃ ሊቆች እየጋበዘ ኮንሰርቶችን እና አውደጥናቶችን
ሲያዘጋጅ ኖሯል። ፕሮፌሰር አሸናፊ ደራሲም ነው። በተለይ የጥቁር ህዝቦችንየሙዚቃ
ታሪክና ባህል ብሎም ማንነትን በሚያሳየው Roots ofBlack Music በተሰኘው
መፅሐፍውስጥ አያሌ መጣጥፎችን በዋናነት የሚፅፈው ይኸው ኢትዮጵያዊው ሊቅአሸናፊ
ነበር። በ 1959 ዓ.ም ደግሞ ሀንጋሪ ውስጥ The Black Kodaly በተሰኘ ዝግጅት ላይ
ባለ ዋሽንቱ እረኛ /The Shepherd Flutist/ በሚል ርዕስ አጅግ ድንቅዬውን ሙዚቃ
አቀረበ። ይህ ባለ ዋሽንቱ እረኛ የተሰኘው ሙዚቃ በዘመኗም ሆነ እስከ አሁን ድረስ የረቂቅ
ሙዚቃዎች ሁሉ የቁጥር አንድ ቦታዋን እንደያዘች ትገኛለች። ፕሮፌሰር አሸናፊ
ሌሎችአያሌ ሙዚቃዎችንም ተጫውቷል። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ሰፊ ምርምርና ጥናት
ያደረገው ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ፣ ዛሬም ድረስ ፅሁፎቹ በአሜሪካን ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች
መማሪያዎች ናቸው። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሙዚቃ እና ባህል ላይ ተመርኩዞ ባህሉንና
እድገቱንየፃፈበት የዶክትሬት መመረቂያ ፅሁፉ በቅርቡ በአንድ ጆርናል ላይ ዳሰሳ
ተሰርቶበታል። የዶክትሬት መመረቂያ ፅሁፍ ርዕሱም The Music of Ethiopia: Its
Development and Cultural setting የሚል ነበር። ኢትዮጵያ ሐገሩን እናህዝቦቿን
በተለይም ደግሞ መላውን አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲያስጠራ የኖረው ፕሮፌሰር አሸናፊ
ከበደ ግንቦት አንድ ቀን 1990 ዓ.ም በ 60 ዓመቱ ፍሎሪዳ ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት
ተለየ። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ሊቅ አረፈ እያሉ በርካታ ሚዲያዎች በጊዜው ዘግበውለታል።
አሸናፊ ከበደ የሦስት ሴቶችና የአንድ ወንድ ልጅ አባትም ነበር። የመጀመሪያ ልጁ ኒና አሸናፊ
ዳኛ ናት። ሰናይት አሸናፊ ደግሞ ተዋናይት ሆናለች። ሦስተኛዋ ሴት ልጁ ሳምራዊት አሸናፊ
ስትባል ወንድየው ደግሞ ያሬድ አሸናፊ ይባላል። በአጠቃላይ ሲታይ የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ
የጥናትና የምርምር ፅሁፎች በአብዛኛው አሜሪካ ውስጥ ስለሚገኙ የያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት
ሰብስቧቸው ለትውልድ መማሪያ እንዲሆኑ ማድረግ አለበት እላለሁ። በተረፈ እንዲህ አይነት
የሙዚቃ ሊቅ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲፈጠር ሁሉንም ነገር ያመቻቹለትንም ግርማዊ
ቀዳማዊ ኃይለስላሴም ምስጋና ይገባቸዋል።
***********************************************************
ምንጭ :--ሰንደቅ 9 ኛ ዓመት ቁጥር 447 ረቡዕ መጋቢት 24 2006 ዓ.ም.

Thursday, April 3, 2014

የሞኞች ቀን(የማምኛ ቀን) April the fool


በየዓመቱ በፈረንጆች ሚያዚያ 1 ቀን የሚውል የአውሮፖውያን የቀልድ ልማድ ቀን ነው በዚህ ዕለት አውሮፖውያን ወዳጅ ዘመድ ጓደኛን በማሞኘት ነው የሚያሳልፉት፡፡ ለመሆኑ የዚህን ዕለት ታሪካዊ አመጣጥ ያሉቃሉ ?
እ.ኤ.አ በ16ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ የኖርዌይ ተወላጅ የሆነው ሉፍ ሊርፖ(Loof Lirpa)የተባለ ሳይንቲስት የበራሪ ምስጢርን ለማወቅ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ አንድ ቀን ሙከራው ስለተሳከለት በወቅቱ የሀገሪቱ ንጉስ ለነበረው ለንጉስ ሄነሪ 8ኛ ደብዳቤ ያፅፍለታል፡፡ የደብዳቤው ፍሬ ሃሳብ የበራሪ ምስጢርን ተመራምሮ ማግኘቱንና አውሮኘላን ሠርቶ መጨረሡን የሚገልፅ ነበር፡፡ የሙከራው ድነቅ ውጤት ለህዝብ በትርኢት መልክ ለማሳየት ስለፈለገም በዚሁ ዕለት ንጉሱ የክብር እንግዳ በመሆን የልፋቱን ውጤት እንዲመለከትለት ይጋብዘዋል፡፡ ትርኢቱም የሚቀርብበት ዕለት እ.ኤ.አ ሚያዚያ 1 ቀን 1545 ነበር፡፡
ንጉሱ የሊርፖን ደብዳቤ ካነበበ በኃላ በሳይንቲስቱ የምርምር ችሎታ በመደሰት ታላላቅ ሹማምንቱን አስከትሎ ወደ ትርኢቱ ሥፍራ ይሄዳል፡፡ ለክብር በተዘጋጀው ሰገነት ላይ በአካባቢው ከተሠበሰበው ህዝብ ጋር ሆኖ ሳይንቲስቱን መጠባበቅ ጀመረ፡፡ ይሁን እንጅ ሊርፖ በወቅቱ ሳይመጣ ቀረ የንጉሱ ባለሟሎች ተጨነቁ ተጠበቡ፡፡ በመጨረሻም ንጉሱም ተናዶ ወደ ቤተ መንግስቱ ተመለሠ፡፡ ለጊዜው የሊርፖ ጉዳይ ምስጢር ሆኖ ቆየ፡፡

ድርጊቱ ሊርፖ ንጉሱን ለማሞኘት ሆነ ብሎ ያደረገው አልነበረም፡፡ ሙከራው ሳይሳካለት ቀርቶም አይደለም፡፡ ከጊዜ በኃላ እንደተረጋገጠው ሉፍ ሊርፖ የበራሪውን ትርኢት ሳያሳይ የቀረዉ እጅግ በማያሳዝን ሁኔታ ነበር፡፡ 

ሊርፖ የክቡር እንግዳውና ህዝቡ ወደ ተሠበሰበበት ቦታ አውሮኘላኑ እያበረረ ለመድረስ ገና ጉዞ እንደጀመረ ከአንድ ትልቅ ዛፍ ጋር ተላትሞ ህይወቱ ያልፋል፡፡ በዚህም የተነሳም ከሚያዚያ 1 ቀን 1545 እ.ኤ.አ ጀምሮ የደረሠውን አጋጣሚ መሠረት በማድረግ ልክ እንደ አንድ ልማድ በመውሠድ ዘመድ ወዳጅና ጓደኞቻቸውን በማሞኘት በተሞኙት ላይም በመሳቅ ቀኑን ማክበር ጀመሩ፡፡ ባሉርፖ ስምም ከአሳ ከሙዝ ከማርማላታና ከቼኮሌት ልዩ ልዩ ኬኮችን በመስራት በመመካብ ያከብሩታል፡፡ አብዛኛዎቹ ግን ቁራን የሚያከብሩት ሰዎችን በሚያስቅና በሚያዝናና ሁኔታ በማሞኘት ነው፡፡
ይህ ልማድ ከግለሠቦች የእርስ በርስ ማሞኘት ሌላ በዜና ማሠራጫዎችም አልፎ አልፎ ይደረጋል፡፡ ግን በማይጐዳ መልኩ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የቢቢሲ ቴሌቨዥን ጣቢያ በዚያን ዕለት ያቀረበው ዜና ከማሞኘትም አልፎ የሚያጃጅል ነው፡፡ ጣቢያው እንዳለው ከሜዲትራኒያን የባህር ዳርቻ የነፈሠው ነፋስ በዛፍ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱና የፖስታ ምርት ስለቀነሰ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እንዳስከተለ የሚገልፅ ዜና አስተላለፈ፡፡
ይህንን አስከፊ ዜና የሠማው ህዝቡም ከየመደብሮች የቀሩትን ፖስታ ለመግዛት ሰልፍ ያዘ፡፡ ህዝቡ በወቅቱ ፖስታ ከዱቄት እንጅ ከዛፍ እንደማይመረት ለማገናዘብ አልቻለም ነበር፡፡ ከጥቂት ሠዓታት በኃላ ጣቢያው ዕለቱ ኤንሪትል ዘፈል መሆኑን ሲገልፅ ህዝቡ በራሱ ላይ ስቋል፡፡


******************************************************************
ምንጭ:--በታከለ ኩዳን/ቁምነገር መፅሄት ቅፅ 2 ቁጥር 14 መጋቢት 1995 ዓ.ም/

Thursday, March 27, 2014

ዋናው ነገር ጤና


የነጭ ሽንኩርት 34 የጤና በረከቶች

1. የደም ቅዳ (Artery) ግድግዳዎችን በማደደርና በማጥበብ የሚታወቀውን አቲሮስክሊሮሲስ የተሰኘውን በሽታ ይዋጋል፡፡ 
2.የኮልስትሮል መጠንን ይቀንሳል፡፡
3. የደም ግፊትን ይቀንሳል፡፡
4. ጉንፋንንና ሌሎች መሰል የላይኛው የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን ይከላከላል፣ ይፈውሳልም፡፡ 
5.የባክቴሪያ መራባትንና መዛመትን ይከላከላል፡፡
6. ቲቢን ለማከም ይረዳል፡፡
7. መግል የቀላቀለ ቁስልን ለማከም ይረዳል፡፡
8. የብልት በሽታ (Trichomoniasis) የሚሰኘውን የአባላዘር በሽታ ለማከም ይረዳል፡፡ 
9.በህዋሳት ውስጥ የሚካሄደውን ዋንኛውን ኬሚካላዊ ውህደት (Metabolism) ያነቃቃል፡፡ 
10.ከነቀርሳ (Cancer) ዓይነቶች አንዱ የሆነውን የኮለን ካንሰር መስፋፋትን ይገታል፡፡ 
11. የሐሞት ከረጢት ካንሰር መስፋፋትን ይገታል፡፡ 12. የፊንጢጣ ካንሰር መስፋፋትን ይገታል፡፡ 
13. የጡት ካንሰር መስፋፋትን ይገታል፡፡
14. በወንዶች ላይ የሚከሰተውን የፕሮስቴት ካንሰር መስፋፋትን ይገታል፡፡ 
15. ለምግብ መፈጨት ሂደት ይረዳል፡፡
16. በልጆች ላይ የሚከሰተውን የማያቋርጥ ሳል ለመከላከል ይረዳል፡፡ 17. የእርጅናን ሂደትን በተወሰነ መልኩ ለመግታት ይረዳል፡፡
18. የአንጀት ውስጥ ትላትልና ተህዋስያንን ይገድላል፡፡
19. የምግብ ፍላጎትን ይጨምራል፡፡
20 በአብዛኛው በእድሜ ሳቢያ የሚከሰተውን ካታራክት የተሰኘውን የአይን እይታ ችግርን ለማከም ይረዳል፡፡ 
21 . የደም መርጋትን ለማሟሟት ይረዳል፡፡
22 . ለስኳር በሽታ ህክምና ይረዳል፡፡
23 . የጥርስ ህመም ስሜትን ይቀንሳል፡፡
24 . የእንቅልፍ እጦት ችግር ላለባቸው ይመከራል፡፡
25 . የሰውነትን የበሽታ መከላከል አቅም ይገነባል፡፡
26 . የእርሾ ኢንፌክሽንን ለማከም ይረዳል፡፡
27 . የመገጣጠሚያ አካላት በሽታን ለማከም ይረዳል፡፡
28 . በባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰተውን ስታፊሎኮካል ኢንፌክሽንን ለማከም ይረዳል፡፡ 
29 . ኪንታሮትን ለማከም ይረዳል፡፡
30 . የቆዳ ላይ ብጉንጅና እብጠቶችን ለማከም ይረዳል፡፡
31 . አንዳንድ የቆዳ በሽታዎችን ለማከም ይረዳል፡፡
32 . ለአንጀት ጤንነት ተመራጭ ነው፡፡
33 . ፋይቶንሳይድስ የተሰኘ ኬሚካል የሚገኝባቸው የነጭ ሽንኩርት ዓይነቶች የአስም በሽታን ለማከም ይረዳሉ፡፡ 
34 . አደገኛ የብሮንካይተስ ህመምን ለማከም ይረዳል፡፡

Monday, February 3, 2014

ያልተዘመረለት ጀግና – አብዲሳ አጋ



አብዲሳ አጋ ጣልያን በአድዋ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ባደረገው የ1928ዓ.ም ወረራ ወቅት በምርኮኝነት ጣልያን ተወስዶ ከታሰረ በኋላ የተሰጠውን ብርድልብስ ቀዳዶ በመቀጣጠል በመስኮት በኩል ማምለጡ ጎልቶ የሚወሳለት አርበኛ ነበር። ተሳክቶለት ቢያመልጥ እንግዳ የሆነ አገር እንደሚቀላቀል እና ለሃገሩም እሩቅ መሆኑን እያወቀ እንኳን ነጻነቱን አሳልፎ ላለመስጠት በሚል ብልጠት በታከለበት ሁኔታ ያመለጠው አብዲሳ አጋ አስገራሚ ጀግንነቱን ያሳየው ከእስር ቤቱ ካመለጠ በኋላ ነበር።
በኦሮሚያ ወለጋ የተወለደው አብዲሳ የኢትዮጲያን ጦር የተቀላቀለው በ14 አመቱ ሲሆን ጣልያን ኢትዮጲያን ስትወር አገሩን ለመከላከል በሚደረግ ውጊያ ላይ መሳተፍ ጀመረ። እጅግ ዘመናዊ መሳሪያዎች ከታጠቀው የጣልያን ጦር ጋር በሚደረገው ውጊያ ላይ ባጋጠመው የመቁሰል አደጋ ህክምና ላይ ከቆየ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ ቤት በቁም እስር ላይ ነበር። በኋላ ጣልያን ኢትዮጲያን እንዲያስተዳድር በሾመችው ግራዚያኒ ላይ የመግደል ሙከራ ከተደረገ በኋላ አብዲሳ አጋ እና ሌሎች 37 የሚሆኑ የቁም እስረኞች ተጠርጣሪ ተብለው በከባድ ስቃይ እስር ቤት ከቆዩ በኋላ በወቅቱ የጣልያን ግዛት በነበረችው በሱማሊያ በኩል ወደ ሲሲሊ ተወስዶ በጣልያን አገር የጦር እስረኛ ተደረገ። በእስር ቤት ጠባዎች ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት አብዲሳ እዛው ታስሮ የሚገኝ ሁሊዮ የተባለ የዩጎዝላቪያ ምርኮኛ በጋራ እቅድ በማውጣት ከእስር ቤት ማምለጥ ቻለ።  ከእስር ካመለጡ በኋላ ከፋሺስት ጣልያን ወታደሮች በመደበቅ እና በመሸሽ ፋንታ በአብዲሳ መሪነት እና እቅድ አውጪነት በሌሊት ታስረው ወደነበረበት እስር ቤት ተመልሰው ጠባቂዎቹ ላይ ጥቃት በመፈጸም የታሰሩትን እስረኞች በሙሉ ነጻ በማውጣት የኢትዮጲያውያንን ጀግንነት በአድዋ ብቻ ሳይሆን በጣልያን ምድርም ያስመሰከረ ድንቅ ተዋጊ ነበር።
የአብዲሳ ጀግንነት በዚህ አላበቃም ከእስር ቤት ያስመለጧቸውን ሰዎች በማሰባሰብ የራሱን ጦር ካደራጀ በኋላ ጣልያኖችን በገዛ አገራቸው ያንቆራጥጣቸው ገባ። ከአድዋ ጀምሮ የኢትዮጲያውያንን ወኔ የተረዱት ጣልያኖች የአብዲሳን ጦር በፍርሃት ያዩ የነበረ ሲሆን በተለያዩ ቦታዎች ከጣልያን ጦር ጋር በመዋጋት ብዙ ድሎችን እያስመዘገበ ነበር። ቆራጥነቱን የተረዱት ጣልያኖች የሚያረጉት ግራ ቢገባቸው ከበርካታ ስጦታዎች ጋር ጦሩን ይዞ የጣልያንን ሰራዊት እንዲቀላቀል መማጸን ጀምረው ነበር። ለፋሺስት ጦር መዋጋት አገር መክዳት እንደሆነ አስረግጦ የተናገረው አብዲሳ ትግሉን አፋፍሞ በቀጠለበት ወቅት የሁለተኛው የአለም ጦርነት ተቀሰቀሰ።
የተባበሩት የአሜሪካ እና እንግሊዝ መንግስታት ከጀርመን ጋር ያበረችውን ጣልያንን እየተዋጉ በነበረ ሰዓት ስለ አብዲሳ ዝና ከሰሙ በኋላ ለጦሩ የሚገባውን ድጋፍ በማድረግ የፋሺስት ስርዓቱን ለማዳከም ከሚያግዙ መንገዶች አንዱ ሆኗቸው ነበር። በድጋፉ በመጠናከር ፋሺስቱን ሰራዊት ማርበድበድ የቀጠለው አብዲሳ የጣልያን ጦር ተሸንፎ ዋና ከተማዋ ሮም በአሜሪካን እና እንግሊዝ የሚመራ ጦር እጅ ስር ከወደቀች በኋላ የሚመራቸውን ከተለያዩ አገር የወጡ ወታደሮች በሙሉ ክንዳቸው ላይ የኢትዮጲያን ባንዲራ እንዲያስሩ በማድረግ የሃገሩን ባንዲራ እያውለበለበ ሮም ከተማ ሲገባ በአለም አቀፉ ህብረት ጦር ትልቅ አቀባበል ተደርጎለት ነበር። ከዛም በኋላ ከተጨማሪ ወታደሮች ጋር በአለም አቀፉ ህብረት ስር የሚመራ ጦር መሪ በመሆን ጀርመንን ለማሸነፍ በሚደረገው የመጨረሻ ውጊያ ላይ ተሳትፎ ግዳጁን በሚገባ በመወጣት የኢትዮጲያን ባንዲራ ከእጁ ሳይለይ በርካታ የጀርመን ከተሞችን ነጻ ማውጣት ችሎ ነበር።
ከጦርነቱ መገባደድ በኋላም የእንግሊዝ፣ የካናዳ እና የአሜሪካ መንግስታት ጦራቸውን ተቀላቅሎ እንዲቀጥል በርካታ ጥቅማ ጥቅሞችን አቅርበውለት ነበር። እብዲሳ ግን ኢትዮጲያ ምንም ያህል ድሃ ብትሆንም ህዝቡን እና መንግስቱን ጥሎ እንደማይሄድ አስረግጦ በመናገር ጥያቄውን ውድቅ አደረገ። በዚህ የተናደዱ ምዕራብውያንም በፈጠራ ወንጀል ከሰው ወደ እስር ቤት አስገብተውት ነበር። በኋላም እስሩ ወደ ገንዘብ ቅጣት ተቀይሮ ከተከፈለ በኋላ በክብር ወደ ሃገሩ ሊመለስ ችሏል።
ወደ ኢትዮጲያ ከተመለሰ በኋላ ሰራዊቱን በቅንነት ያገለገለው አብዲሳ በኮረኔልነት ማዕረግ የአጼ ሃይለስላሴ ልዩ ጠባቂ ጦር እየመራ ቆይቶ ንጉሱ ከስልጣን ከወረዱ ከጥቂት አመታት በኋላ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።  የአብዲሳ አጋን ሙሉ የህይወት ታሪክ በደንብ ማወቅ ከፈለጉ 
 ይችላሉ።

የሃይማኖት አስተማሪዎች በአንድ የስነ ጥበብ ዝግጅት ያደረጉት አዝናኝ ንግግር

በቅርቡ በተዘጋጀ የስነ ጽሁፍ ዝግጅት ላይ የተገኙት የሃይማኖት አስተማሪዎች ከሃይማኖት ውጪ የሆኑ ርእሶች ላይ ሃሳባቸውን ያካፈሉ ሲሆን መጋቢ ሃዲስ እሸቱ ስለ ባህል እና ዘመናዊነት አዝናኝ ንግግር ሲያቀርብ ዲያቆን ዳንኤል ደግሞ አንድ የዩንቨርስቲ መምህር የሚል አነቃቂ ስነ ጽሁፉን አካፍሎ ነበር። ይመልከቱት …
የሃይማኖት አስተማሪዎች በአንድ የስነ ጥበብ ዝግጅት ያደረጉት አዝናኝ ንግግር