ከደራሲያን ዓምባ

Tuesday, May 21, 2013

ከባሕል አምባ

                                 ጥር፣ጥምቀት፣ ፍቅርና ትዳር

                                                    ****************************በአለማየሁ ታደለ 


የፍቅረኛዋ ድንገት ከሰፈሩ መጥፋት ሲከነክናት የሰነበተችው ኮረዳ ከእለታት አንድ ቀን ማለዳ ተነስታ ውሃ ለመቅዳት ከመሰሎቿ ጋር ወደጅረት ስትሄድ ያን ፍቅረኛዋን ለምሳ የሚሆነውን ስንቅና ወንጭፉን ይዞ ወደ ማሽላ ጥበቃው ሲገሰግስ ታገኘዋለች፡፡ በዚያን ጊዜ ሲያብከነክናት የነበረው ትዝታው ይቀሰቀስባትና ናፍቆቷም ጤና ይነሳታል፡፡ መናፈቋን እንዲያውቅላትም በዘፈን አስመስላ ጓደኞቿ እንዳያውቁባት እንዲህ ትለዋለች፡፡
እያለ የሌለው ሲሹት የማይገኝ
እኔስ የሱ ነገር እረ ምን ይበጀኝ
ምንድነው ነገሩ ምንድነው ምስጢሩ
ለእይታ የጠፋው እንዲህ ከመንደሩ
እናወዛለሁኝ በውሃ ወረፋ
የሚረዳኝ የለም ብቻዬን ስለፋ፡፡
ብላ ለፍቅረኛዋ ናፍቆቷን ብታስተላልፍለት እሱም ሚስጢሩ ስለገባውና ምንም ያህል ብትናፍቀው የመኸር ወቅት ስለሆነ ጥበቃውን ትቶ ወደየትም መሄድ እንደማይችል ለመግለጽ እንዲህ ይላታል፡፡
የሆድ ነገር ሆድ ነው ትቼ አልመጣ ወፉን
አፋፍ ቁጭ ብለሽ አድምጪው ወንጭፉን
በማለት ጭውውትም ሆነ ፍቅር ከስራ በኋላ መሆኑንና ያለስራ መደሰት የሌለ መሆኑን እሱም መልሶ በግጥም ነገራት፡፡
ውድ አንባቢያን እንደምን ከርማችኋል? እነሆ አዲስ ብለን ከተቀበልነው 2004 ዓ.ም አራቱን ወራት ሸኝተን አዝመራው ፍሬ በሚያፈራበት፣ ጎተራው በሚሞላበት፣ የመኸር ወቅት ላይ ደረስን፤ እንኳን አደረሰን፡፡ ለዛሬው የርዕሳችን መነሻ የወጋችን መጠንሰሻ የመኸር ወቅትን ተከትሎ የሚመጣው የጥር ወር ነው፡፡ ለወራት ሲባክን ለከረመው አርሶ አደር የእፎይታ ወቅት የሆነው የጥር ወር በባላገሩ ህብረተሰብ ዘንድ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ማህበራዊ ትስስሩ የሚጠነክርበትና ጥንዶችም በጋብቻ ተጫብጠው ጎጆ ለመውጣት በጉጉት የሚጠብቁት ተመራጭ ወር ነው፡፡ ጥርን የፍቅርና የትዳር ወር ከሚያስብሉት ነገሮች አንዱ የጥምቀት በዓል በዚህ ወር ላይ መከሰቱ ነው፡፡
ጥምቀት በሀገር ቤት የኮረዳና ኮበሌዎቹ መተያያና መተጫጫ ሁነኛ ጊዜ ሲሆን የጥር ወር ደግሞ ጥንዶቹ በጋብቻ ተጫብጠው ለሶስት ጉልቻ የሚበቁበት ተመራጭ ወር ነው፡፡
ጥር፣ ጥምቀት፣ ፍቅርና ትዳር ሰምና ፈትል ናቸው በሚለው ከተስማማን ዘንዳ ከላይ በመግቢያችን ያየናቸው አይነት ባተሌ ፍቅረኞች ከሰብል ጥበቃ፣ ከእንስራ ሸከማ፣ ከኩበት ለቀማ፣ ከአክርማ ቀጨታና ከልብስ አጠባ ከመሳሰሉ የእለት ተዕለት ክንውንና የኑሮ ዘይቤው ግድ ከሚለው ዘለለታዊ ህይወት ለጊዜውም ቢሆን ተላቀው ከከንፈር ወዳጆቻቸው ጋር በነፃነት ከሚገናኙበት አብይ በዓል ከሆነው ጥምቀት ወጋችንን እንጀምራለን፡፡
ጥምቀት ከሀይማኖታዊ አከባበሩ ባሻገር ባህላዊ ጎኑ ያመዝናል፡፡ ከክርስትና እምነት ተከታዮች አበይት በዓላት አንዱ የሆነው ይኸው በዓል በአብዛኛው የሀገሪቱ ክልሎችና በመዲናችን አዲስ አበባም እንደጃንሜዳ ባሉ ሰፋፊ የህዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎችና አደባባዮች በዝማሬ፣ በእልልታ፣ በጭፈራና በሆታ ይከበራል፡፡ በዚህ በዓል ኮረዶችና ኮበሌዎች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ አምረውና ደምቀው ይወጣሉ፡፡ ወጣቶቹ ለፈቀዱት ከንፈር ወዳጅ ሎሚ ብቻ ሳይሆን ለዛ ያላቸውን የፍቅር ስንኞችንም ይወረውራሉ፡፡
በቀደመው ጊዜ ነው አሉ አንዲት አፍቃሪ የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ጃንሜዳ አካባቢ በአይን ፍቅር ትብሰከሰክለት የነበረውን አንድ የአራዳ ጎልማሳ ድንገት ታገኘውና አጋጣሚውን በመጠቀም ፍቅሯ እንደፀናባትና ጓዟን ጠቅላ መግባት እንደከጀለች እንዲህ በማለት ገለፀች ይባላል፡፡
በፍቅርህ ስቃጠል ሆነህ ለልቤ እሳት
ታቦታቱን ሳስስ ሳስጨንቅ በስለት
ልመናዬን ሰማ ይመስገን አቤቱ
አምላኬ ላከልኝ በእለተ ጥምቀቱ
አራዳ ገበያ ይሸጣል ባርኔጣ
ትችለኝ
እንደሆን ከነጓዜ ልምጣ፡፡ ብትለው ወዲህ የሷ ልጅነት እና የሱ ጎልማሳነት እያሳሰበው፣ ወዲያ ደግሞ የልጅቷ ውበት እያነሆለለው
"አይ፣ አይ፣ ልጅም አይደለሽ
ለምንስ ቸኮልሽ?" ቢላት እሷ ደግሞ መለስ አድርጋ
ምነው ትለኛለህ ልጅ ገና ልጅ ገና፣
ዶሮም ትበላለች አጥንቷ ሳይጠና፡፡ 
ብላ ገላገለችው፡፡
እርሱም ምንተፍረቱን ወደማርጀት የተጠጋና ጠና ያለ ሰው መሆኑን ቢገልፅላት መች ልትሰማው፡፡ ጭራሽ የመጣው ይምጣ ብላ
አረጀህ አረጀህ የሚልብኝ ማነው
ዶሮም የሚወደድ ገብስማ ሲሆን ነው፡፡ 
ብላ ያሰበችውን አሳካች፡፡ እሱም በውበቷ እንደተማረከና በሷም ደስ እንደሚለው ለመግለፅ
እስቲ ወዲያ ሄደሽ ወዲህ ተመለሽ
እኔም ደስ ይበለኝ አራዳም ይይሽ፡፡ 
የሚለውን ዜማ እያንጎራጎረ ይዟት በረረ ይባላል፡፡
ዛሬ ዛሬ በጥምቀት ጃንሜዳ ላይ ይሰሙ የነበሩ እነዛ ለዛ ያላቸው ባህላዊ ግጥሞች ድሮ ቀሩ በሚባሉበት ደረጃ ላይ የደረሱ ይመስላል፡፡ በቀደመው ዘመን ጃንሜዳ የታደመ ማንኛውም ሰው ይሰማቸው የነበሩ አንዳንድ ባህላዊ ዘፈኖች መልካቸውን እየቀየሩ እንደመጡም ይገነዘባል፡፡ ድሮ ይዜሙ የነበሩ
ሎሚ ብወረውር ደረቱን መታሁት
አወይ ኩላሊቱን ልቡን ባገኘሁት፡፡ 
መሰል ልብ ስር ተጎዝጉዞ ፍቅርን ለመቋደስ ይቀርቡ የነበሩ የተለመዱ የፍቅር ተማፅኖ ዜማዎች ባለፈው አመት በታደምኩበት የጃንሜዳው ጥምቀት በዚህ መልኩ ተለውጠው ሲቀነቀኑ አድምጫለሁ፡፡
እባክህ አምላኬ አዲስ ዘመን አምጣ ፍቅር በቆርቆሮ ታሽጐ እንዲመጣ፡፡
ወርቃማ ባህላዊ ዘፈኖቻችን በመሰል ስንኞች ተተክተው ሲዜሙ ያደመጠ ሰው በርግጥም ወጣቱ ፍቅርን ባቋራጭ እየሻተ ከመምጣቱ ባሻገር ባህሉንም እየዘነጋ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
"የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው" እንዲሉ ፍቅር እንዴትም ሆኖ ቢመጣ ወደ ትዳር ከማምራት አስቀድሞ እርስ በእርስ መገማገም መጠናናትና ለቁም ነገር መብቃት ከፍቅር ሀሁ ጀምሮ ሊዘነጉ የማይገባቸው አበይት ተግባራት ናቸው፡፡ እንደቀደመው ዘመን
የአይኔ ማረፊያ የነፍሴ ትፍስህት
ካንቺ ጋራ አድሬ ሲነጋ ልሙት፡፡ አይነት እንጉርጉሮ በዚህ ዘመን እንደተመኙት የምር ይገድላልና ጠንቀቅ ማለቱ ይበጃል፡፡ እንዲህ በየቦታው ስለጥምቀትና መጠናናት ሲወጋ ትዝ የምትለኝ አንዲት አብሮ አደግ ጓደኛዬ አለች፡፡ ልጅቱ ውብናት፡፡ ውብ ብቻ አይደለችም ባለቅኔው እንዳለው
"የናት ያባቷን ቅርስ አጥብቃ የያዘች
ወንድ ሲስቅላት ግንባር የቋጠረች
በቁጣ ግልምጫ አፈር ያለበሰች፡፡ ሁለመናዋ የሚያባብል ኮረዳም ጭምር ናት፡፡ እናም ይቺ ልጅ የፍቅርን ሀሁ ያስጀመራትን የመጀመሪያ ፍቅሯን አትረሳውም፡፡ የከተራ እለት ታቦታቱን ወደ የማደርያዎቻቸው ለማስገባት ሲባል በተከሰተ ግርግር የወደቀችዋን ቆንጆ ከመረጋገጥ የታደጋት አንድ ወንዳወንድና መልከ መልካም ወጣት ቀልቧን ገዛው፡፡ ልጁ በልጅነቷ የም ትመኘውን አይነት ወንድ ነበረና የፍቅር ጥያቄ ሲያቀርብላት እንደሌሎቹ ወንዶች ምላሿን አልነፈገችውም፡፡ "ጉድና ጅራት ወደኋላ" እንዲሉ ያቺ ጠንቃቃ ልጅ በጨቅጫቃ መዳፍ ውስጥ እንደወደቀች ዘግይታ ተረዳች፡፡ አፍቃሪዋ በተደጋጋሚ እኩለ ሌሊት ላይ በተንቀሳቃሽ ስልኳ ይደውልላታል፡፡ ልጅቱ በድንጋጤ ከእንቅልፏ ባንና ስልኩን ታነሳና "ሄሎ" ትላለች፡፡ አፍቃሪው የረባ ሰላምታም ሳያቀርብ "የት ነሽ?" ይላታል፡፡ "ቤት ነኝ ተኝቻለሁ፡፡; እንግዲያውስ በቤት ስልክ እደውላለሁ፡፡" ይላታል፡፡ ድንገት የቤት ስልኳ ከተበላሸ ደግሞ "እስቲ የቴዲ አፍሮን ዘፈን ክፈቺልኝ::" ብሏት ላምባዲና አላምን አለና … ወዘተ ዘፈኖችን በስልኩ እየኮመኮመ ይነዘንዛታል፡፡ በቤት ውስጥ መብራት ከሌለና ቴፕ መክፈት ካልቻለች "ማንኪያና ስኒ አጋጭልኝ፡፡" ይላትና በሌሊት ሻማ ለኩሳ ማንኪያና ስኒ ለማጋጨት ረከቦት ፍለጋ ትማስናለች:: ይቺ ልጅ ታዲያ ፍቅራቸው ሶስተኛ ወሩን እንዳገባደደ ልጁን ትጠራውና አንተ "ቦዲጋርድ; እንጂ "ቦይፍሬንድ; መሆን ስለማትችል በቃኸኝ ብላ ስቃይዋን አበቃች፡፡
እንግዲህ ከጋብቻ በፊት መጠናናት ቢያንስ ብዙ ከመራመዳችን አስቀድሞ እንዲህ እንደልጅቱ የማያዳግም ውሳኔ ለማሳለፍ የሚረዳ ቢሆንም በእንጠናና እና በሁነኛ ሰው ፍለጋ ሰበብ በስተርጅናም ከቤተሰብ ጋር የምንኖር ላጤዎችም አንታጣምና ከወዲሁ ልናስብበት ይገባል፡፡ የእድሜ ጣርያ አርባ ቤት ውስጥ በሚጫወትባት ኢትዮጵያ ይህ እድሜ ጉድጓድ የመማሻ እንጂ ፍቅር መጠንሰሻ ስላይደለ ቢያንስ ለምንወልዳቸው ልጆች በማሰብ ፈጠን ማለቱ አይከፋም፡፡ በተገረዙበት ቤት መገነዙስ አይከብድም ትላላችሁ?
ይህን ጉዳይ ካነሳሁ አይቀር ከአባባሌ ጋር የሚዛመድ የአንድን ሰው ታሪክ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ ሰውየው ለወላጆቹ አንድያ ልጃቸው ነው፡፡ አሳድገውና ለቁም ነገር አብቅተውት በአንድ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ተቀጥሮ ወፍራም ደሞዝ ያገኛል፡፡ ወላጆቹ ከሀያዎቹ እድሜው አንስቶ እንዲያገባና ዘራቸውን እንዲቀጥል ቢወተውቱትም ሁነኛ ሚስት ፍለጋ በሚል ሰበብ ሰላሳዎቹን ያልፋል፡፡ ቤተሰቡ በወዳጅ ዘመድ ቢያስመክሩትም በድጋሚ "ትዳር ዝም ብሎ ማንም የሚደልቀው ከበሮ አይደለም ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡" እያለ የመጣውን ሁሉ በመመለስ አርባዎቹን ይሻገራል፡፡ ከእለታት አንድ ቀን አባት ወደ ልጃቸው ቤት በማምራት ለመጨረሻ ጊዜ የማያገባበትን ምክንያት እንዲያስረዳቸው ይጠይቁታል፡፡ ልጅ አሁንም ሁነኛ ሚስት ማግኘት እንዳልቻለ ያስረዳል፡፡ አባትየውም በእጅጉ ተገርመው "አንተ ልጅ በዚህ ሀገር ላይ እየፈለግክ ያለኸው ሚስት ነው ወይስ ነዳጅ; አሉት ይባላል፡፡
ምንም እንኳ እንደ ሰውየው ባናበዛውም የትዳር አጋር ፍለጋና መጠናናቱ በብልሀት መሆኑ ይደገፋል፡፡ መገማገሙ አብቅቶ ትዳር ሲታሰብም በተለይ በከተሞች ከጋብቻ ይልቅ በየዓመቱ የፍቺ ቁጥር እያደገ የመምጣቱን ጉዳይ ከቁም ነገር ልንጥፈው ይገባል፡፡ ግንኙነታችን የተመሰረተው በጥቅም ወይስ በፍቅር የሚለው ጉዳይም መጤን አለበት፡፡እንዲህ በጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ሲወሳ የሚነገር አንድ አፈታሪክ አለ፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡
ሰውየው በአንድ ምሽት ከተዋወቃት ከአንዲት ባለመሸታ ቤት ጋር በጊዜው እንደ መገበያያ የሚያገለግለውን ሁለት አሞሌ ጨው ከፍሎ አብሮ ለማደር ይስማማል፡፡ አዳር ላይ ሁለቱም ይስማሙና ለዘለቄታው አብሮ ለመኖር ይወስናሉ፡፡ እሷም ያላትን ገንዘብ ለሱ ሰጥታ ንግድ ይጀምራሉ፡፡ ኑሮ "ፏ"ይላል፡፡ ንብረት በንብረት ሀብት በሀብት ይሆናሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ 10 ዓመታት ከቆዩ በኋላ ሰውየው በዘመዶቹ ሴትኛ አዳሪ አግብቶ መኖሩ ተገቢ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ስለተነገረው እሱም አምኖበት ያባርራታል፡፡ ሴትየዋ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ብትከሰውም ሰማንያ የሌላት በመሆኑ ንብረቱን መካፈል እንደማትችል እየተነገራት ትመለሳለች፡፡ ተስፋ ያልቆረጠችው ሴት በጊዜው አባመላ ወደ ሚባሉ ሹም በማምራት ጉዳይዋን በድጋሚ እንዲያዩላት ደጅ ትጠናለች፡፡ ሹሙም ይስማሙና ባልና ሚስት ባሉበት ጉዳያቸው ይታያል:: ሁለቱም የመከራከርያ ሃሳባቸውን አሰምተው እንዳበቁ ሹሙ ፍርድ ሰጡ፡፡ በፍርዳቸውም ሚስት ሰማንያ ወረቀት የሌላት በመሆኑ ንብረት የመካፈል መብት እንደሌላት ይወስናሉ፡፡ ሆኖም በመጀመሪያ ቀን አብረው ሲያድሩ በተስማሙት መሰረት ከ10 ዓመታት በላይ አብራው ላደረችበት ለያንዳንዱ ቀን ሁለት አሞሌ ጨው አስቦ እንዲከፍላት ወስነው ችሎቱን ዘጉ ይባላል:: በቡዳ ቤት ሰላቢ ገባ ይላችኋል ይሄ ነው፡፡ በአጠቃላይ ብቸኝነት አንገፍግፎት ከወዳጁ ጋር ተጠቃሎ ሶስት ጉልቻ ለማበጀት የሚፈልግ እንዳለ ሁሉ ለጥቅም ሲል መዳበል የሚፈልግም ይኖራልና መጠርጠሩ አይከፋም፡፡
በተረፈ ሁሉንም ደረጃዎች አልፋችሁ በጥር ወር ለትዳር የምትበቁ ጥንዶች እንኳን ለዚህ ክብር አበቃችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡ በግምገማ ላይ ላላችሁ የከርሞ ሙሽራ ያድርጋችሁ በማለት ከወዲሁ እሰናበታለሁ፡፡

*****************************************************
ምንጭ--:WWW.addisababacity.gove,et

No comments:

Post a Comment