ከደራሲያን ዓምባ

Monday, May 20, 2013

የግጥም ጥግ

"አበበ እንጂ መቼ ሞተ!!"
በሎሬት ፀጋየ  ገብረ መድኅን
******************

























በቅፅበት ፀንሶ ሞቱን
ድፍን አለም ደፍቶ አንገቱን
በልቡ ቀርፆት ፀሎቱን
በህሊናው ነድፎት ስሙን
በገፁ ፅላት ታሪኩን፡፡
አእዋፍን በደመና፣ ጀግናን በምድር ያስደነቀ
ማራቶን ጮራው ጠለቀ
በራሪው ኮከብ ወደቀ፡፡























 በቃ ጀግናው ተከተተ
ይኸው የማይሞት ሰው ሞተ፡፡
ብለን እንበል እባካችሁ፡- አበበ ጀግና ነውና
ተስፋ አይቀበርምና፡፡
የጎበዝ ነባቢት ነፍሱ
የሰው መዝርዕቱእ አርያ፤ የማይታጠፍ መንፈሱ
በጥራት የታጠፈለትየምድር አጥናፍና አድማሱ፡፡
የየብስ የአየሩ ነበልባል
የማራቶን እፁብ አይጣል፡፡
























የምድር አለሙ ገሞራ
አገሩንበክብር ያስጠራ
ሳተናው እግረ ጆቢራ
ሎጋ ቢቂላ ዋቅጂራ፤
የጎበዛዝ ንጥረ ወዙ
የተስፋ ብርሃን መቅረዙ፤
ስሙን ላገር ስም ሰይሞ፡ የምስራች ያስደወለ
ስንቱን ስንቱን ልበ ሙሉ፡ ከአድማስ አድማስ ያስከተለ፡፡
የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ
ያረጋት የኦሎምፒክ አርማ፡፡
























በወገኖቹ ልቦና ቀና ኩራት ያሳደረ
እንደፍላፃ በአክናፉ የአየርን ሰርጥ የሰበረ
የፍስሃዋን አዋጅ ለአለም በአቅመ ወዙ ያስነገረ፡፡
በአገር ፍቅር ልቡን ሞልቶ ላቡን ነጥቦ የዋተተ
የአለምን ጀግና በአድናቆት በቅን ቅናት ያስሸፈተ
አልሞተም እንበል እባካችሁ "አበበ እንጂ መቼ ሞተ?"

























**********************************
     ምንጭ:---http://www.eaf.org.et

የግጥም ጥግ

የሰንበት ጽንስ
            ፊርማዬ ዓለሙ 
********************
በስራው ቀን ቀርቶ በተፈቀደበት፣
በእሁድ በቅዳሜ በሰንበት ሰርቼ ባል በተባለበት፣
ፈጣሪ ሥራውን ሁሉ ባበቃበት፣
በሰንበት ጸንሼ ባል በተባለበት።
ተዘፍዝፎ ቀረ ልጄ ከጅምሩ፣
ሲፈራረቅበት ውኃ፣ ጣይ፣ አየሩ።
እሱን እየማገ  እየተነፈሰ፣
ላቅመ ሔዋን በቃ ልቡ እንደፈሰሰ፣
ለሰንበት ጽንሶቹ አጅሬም ደረሰ።
የእሁድ ቅዳሜ ጽንስ በረከት የራቀው፣
ሰበዝ አልባ ውጥን ሲጀመር የሚያልቀው።
ቢመክሩት በጅ አይል የሚረዳው የለ፣
ተቀምጦ ለመኖር ብቻ ይታደለ።
የዕድሜውን አገዳ በተራ እየላጠ፣
ተዘፍዝፎ ቀረ ነገር እየበላ ወሬ እያላመጠ።
***************************
ምንጭ፡--አዲስ ዘመን ግንቦት 2005

Friday, January 11, 2013

የግጥም ጥግ


እማሆይ ገላነሽ አዲስ ማን ናቸው?

እማሆይ ገላነሽ አዲስ_፲፰፻፹፱᎗፲፱፻፸፰ ዓ.ም.

እማሆይ ገላነሽ አዲስ

ስለ አንዲት ስመ-ጥሩ ኢትዮጵያዊት መምህርትና ባለ ቅኔ ታሪክና ማንነት ስናስታውስ ‘ጽላሎ ይበልጣል አንቺ ያለሽበቱ‘ የተባለላቸውንና ሣር ቅጠሉ አድናቆቱ የቸራቸውን እማሆይ ገላነሽ አዲስን ከጽላሎ አማኑኤል ሳናነሳ አናልፍም።

ከቄስ ገበዝ ሐዲስ ኪዳናትና ከወ/ሮ ወርቅነሽ እንግዳ በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት በይልማና ዴንሳ ወረዳ በሚገኘው ደብረ ጽላሎ አማኑኤል በ፲፰፻፹፱ ዓ.ም ተወለዱ። በእናት አባታቸው ቤትም በንክብካቤ አደጉ። አባታቸው የሚያስተምሩትንም ቅኔ ሥራዬ ብለው ይከታተሉ ነበር።

የስምንት ዓመት ልጅ እያሉ አንድ ቀን ከእናታቸው ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ። በሴቶች መቆሚያ ከእናታቸው ፊት ተቀምጠው እንዳሉ በዚያው ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉት ከሥርዓተ ቅዳሴው በኋላ ቅኔ ይዘርፋሉ።

“በታቦርሂ አመ ቀነጸ መለኮትከ ፈረስ” ማለትም መለኮትህ ፈረሰ በደብረ ታቦር ተራራ በዘለለ ጊዜ ብለው ቄስ ገበዝ ለዓለሙን ሲጀምሩ፡ ገላነሽ ሐዲስ ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ ከተቀመጡበት ተነሥተው “ኢክሀሉ ስሂቦቶ ሙሴ ወኤልያስ” አሉና ነጥቀው እርፍ። ትርጉሙም ሙሴና ኤልያስ ሊስቡት አልቻሉም ብለው አባታቸውን በጉባኤ መካከል ነጥቀዋቸው መወድሱን ጨርሰውታል። አባታቸውም እዚያው ጉባኤ መካከል አዚምላት በማለት ተናግረዋል ይባላል። በኋላም መልሰው እንዲህ አሏቸው፡ “ወእንዘ ትትናገሪ ዘንተ በአድንኖ ክሳድ ወርእስ በከመ አነ ስማዕኩክ ኢይሰማዕኪ ጳውሎስ።“

ይህ ጳውሎስ በመልእክቱ ሴቶች በጉባኤ መካከል ገብተው እንዳያስተምሩ የተናገረውን ቃል በማስታወስ እኔ እንደ ሰማሁሽ ይህንን ስትናገሪ ጳውሎስ እንዳይሰማሽ ለማለት ነው።

ከዚህ በኋላ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የተሰባሰቡት ሊቃውንትና ሕዝብ ይህ ምስጢር እንደተገለጸላቸው ባዩ ጊዜ፤ በሁኔታው በመገረምና በመደነቅ ካህናቱ በወረብ፥ ጎበዛዝቱ በሆታ ሴቱ በእልልታ ገላነሽን እያመሰገኑ መንገድ ጀመሩ። እንደ ንግሥት ጉዞ በአልጋ ሆነው መጋረጃ ተጋርዶላቸው እቤታቸው ደረሱ። ሕዝቡም ከፍ ያለ የደስታ ግብዣ አድርጎ ሰነበተ።

          ይህ ደስታ ብዙም ሳይቆይና ስሜቱ ሳይደበዝዝ ገላነሽ ሕይወት ላይ አስደንጋጭ ክስተት ተፈጠረ። በለጋ ዕድሜያቸው ኩፍኝ በተባለ በሽታ ይያዙና ዓይኖቻቸው የማየት ብርሃናቸውን ያጣሉ። ይሄን ጊዜ አባታቸው የቤተ ክህነት ትምህርት እንዲጀምሩ በማድረግ ዳዊትን፣ ውዳሴ ማርያምን፣ ቅዳሴ ማርያምን፣ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜን እንዲሁም ለዘመናት ሲያስተምሩት / ከሃምሳ ዓመታት በላይ የኖሩትን ቅኔን ከነ-አገባቡ በሚገባ እንዲያጠናቅቁ ያደርጋሉ። ለካ የዚያን ጊዜዋ ገላነሽ ሐዲስ ዐይናቸው እንጂ ልባቸው ብርሃን ነበረ።

ገላነሽ አባታቸው ካስተማሯቸው በኋላ በመምህርነት ይመርቋቸውና በአባታቸው ጉባኤ ውስጥ ተቀምጠው በየተራ ሲያስተምሩ ቆይተዋል። ለአካለ-መጠን ሲደርሱ ወላጆቻቸው “እኛ ከሞትን ማን አላት? ባል ታግባና ልጅ ትውለድልን” ብለው በማሰብ በዚሁ ገዳም ጽላሎ አማኑኤል አካባቢ ተወልደው ያደጉ ነገር ግን የቤተ ክህነት ትምህርት ያልተማሩ አቶ ጥሩነህ በላይ የተባሉትን ሰው አጋቧቸው። ባል ያግቡ እንጂ ከወላጆቻቸው ቤት ሳይወጡ አብረው እየኖሩ ሲያስተምሩና አባታቸውን ሲረዱ በማኅበራዊ ክንዋኔዎችም ሲሳተፉ ኖረዋል። በዚህ ትዳራቸው አዳም ጥሩነህና መሠረት ጥሩነህ የተባሉ ወንድና ሴት ልጆች አፍርተዋል። ሦስተኛ ልጃቸው ግን በሕፃንነቱ ሞቶባቸዋል።

ገላነሽ በዚህ ሁኔታ ኑሯቸውን እየገፉ ባሉበት ጊዜ ፲፱፻፳፰ ዓ.ም የጣልያን ፋሽስት መንግሥት ሀገራችንን ኢትዮጵያን ወረረ። የጽላሎ ሕዝብ ገዳሙን ትቶ በመሸሽ ጫካ ገባ። ቄስ ገበዝ ሐዲስ፣ ባለቤታቸው፣ ልጃቸው ገላነሽ ከሊቃውንቱም ከመነኰሳቱም የተወሰኑት “ቤተ ክርስቲያናችንን እንዴት ትተን እንሄዳለን” በማለት በዚያው በገዳም ቀሩ። የጣልያን ጦርም በሚያሳዝን ሁኔታ እዚያ ያገኛቸውን ሊቃውንትና መነኰሳት የገላነሽን ወላጆች ጨምሮ በግፍ ገደላቸው። ገላነሽ ዐይነ ሥውር ሰለ ነበሩ ሳይገድሏቸው ከሞት አመለጡ። ወላጆቻቸውን በሞት በመነጠቃቸው ግን ሕይወታቸው ጎደሎ ሆኖ ነበር።

ገላነሽ የገጠማቸውን መከራ ተቀብለው በመመንኮስ ሀገር ሰላም ሲሆን ከዚያው ከአባታቸው ቦታ ላይ ጉባኤያቸውን አጠናክረውና አስፍተው የተጠሩበትን የቅኔ መምህርነት በመቀጠል ማስተማሩን ተያያዙት። ተማሪው ዝናቸውን ከየሀገሩ እየሰማ በእርሳቸው እየተደነቀ ለመማር ይጎርፍ ነበር። በቅኔ መምህርነት በቆዩባቸው ኅምሳ ዓመታት ውስጥ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከትግራይ፣ ከኤርትራና ከሸዋ ክፍላተ ሀገራት እንዲሁም ከላስታና ከላሊበላ የተሰበሰቡበትን አንድ ሺ ሰባት መቶ ሃምሳ ተማሪዎች አስተምረዋል። ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍላተ-ሀገር የመጡ ሠላሳ ስድስት መሪጌቶችን በቅኔ መምህርነት አስተምረው ብቁ መሆናቸውን በመመስከር አረጋግጠዋል።

እማሆይ በመማር ማስተማር ሥራ ላይ ሴቶች ከወንዶች እኩል መሆናቸውን ሁልጊዜ ይናገሩ ነበር። ይህንንም ቀሲስ ከፍያለው መራሒ “ሴቶች በኢትዮጵያ” በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸውት ይገኛል። እማሆይ “መማርም ሆነ ማስተማር ብርታትን እንጂ ጾታን አይመለከትም። ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል ተሰልፈው መሥራት የኖረ እንጂ እንደ እንግዳ ደራሽ አይደለም” ይሉ ነበር። ለዚህም ማስረጃ ሲጠቅሱ መምህራችን ክርስቶስ ሴቶች ደቀ-መዛሙርቱን ሂዱና ትንሣኤዬን ንገሩ ብሏቸውላና ልዩነት የለም ይላሉ።

እማሆይ ገላነሽ አዲስ በጠባያቸው አስተዋይ ብልህና ንቁ እንዲሁም ቅን አሳቢ ሰው እንደነበሩ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ። ችኩልነትንና ሽንፈትን የማይወዱ የማስተማር ፍቅር የተሰጣቸው የዘመናችን ታላቅ ሴት ናቸው። እማሆይ ዐይነ-ሥውር ይሁን እንጂ ዐይነ-ሥውርነታቸው ሴቶች ከሚያከናውኗቸው ድርጊቶች አልገታቸውም። ልጅ ወልደው ያሳደጉ፣ በቀለም ያጌጡና የተሸለሙ ስፌቶችን ይሰፉ፡ ከዐይናማዎች እኩልም ፈትል ይፈትሉ ነበር። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ለሌሎች ከብደው እንዳይገኙ በዚህ ሞያቸው በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውን ያስተዳድሩ ነበር።

ለብዙ ሰዎች ዐይነ-ሥውር መሆን ድቅድቅ ጨለማን ያህል ከባድ ነው። እንደ እማሆይ ያሉ መንፈሰ-ጽኑ ሰዎች የዐይን ብርሃን የላቸውም ግን ያያሉ፣ ጆሮአቸውም ላይሰማ ይችላል ግን ያዳምጣሉ፣ አንደበታቸውም ተዘግቶ ሊሆን ይችላላ ግን ዲዳ አይደሉም። እማሆይ ገላነሽ ዐይነ-ሥውርነታቸው ከማየት ከመመራመር ከማስተማር አልከለከላቸውም።

እማሆይ ገላነሽ ለብዙ ዘመናት ሊቃውንት በማፍራትና በጥሩ ሥነ-ምግባር ያሳለፉ፣ በአካባቢያቸው ሕዝብ ዘንድም ዝናን ያተረፉ ሊቅ እናት እንደሆኑ ታሪካቸው ምስክር ነው።

እማሆይ ገላነሽ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በባሕር ማዶ ሣይቀር ዝናቸው የታወቀ በመሆኑ ከውጭ ድረስ እየመጡ የተለያዩ ግለሰቦች ይጠይቋቸው እንደነበር ይነገራል።

የእማሆይ ገላነሽ ሐዲስ ሥራዎች ለግእዝና ለአማርኛ ቅኔዎች ዕድገት አስተዋጽዖ በርክተዋል። ለምሳሌ ያህል የአማርኛና የግእዝ ሁለት ቅኔዎቻቸውን ወስደን ብንመለከት የእማሆይ ገላነሽ ቅኔዎችን የምሥጢር ጥልቀትና ርቀት የቋንቋ ምጥቀት መገንዘብ ያስችለናል።

፩. ተርቢኖስ በኩር

እመ ኢበልዐ በልዐ

ምግበ ገድል ጸገብኩ

ኢይቤ ቤተ ሃይማኖት ጽኑህ

ትርጉም፡

ተርቢኖስ በኩር የተባለ አለቃ ጽኑ ከሆነ የሃይማኖት ቤት የተጋድሎን ምግብ ቢበላም ባይበላም በቃኝ ጠገብኩ አይልም።

ሰም፡

ሥት ያለበት አለቃ ሰው እንጀራን ቢበላም ባይበላም ጠገብኩ አይልም።

ምስጢር፡

ተርቢኖስ ማለት ጊዮርጊስ ነው። እሲም ሰማዕት ነው፡ የሰማዕታት አለቃ ነው። ስለዚህ ከሰባ ነገሥታት ጋር ሰባት ዓመት ተጋድሎ ሲያደርግ ከሃይማኖቱ ጽናት የተነሣ ደከመኝ ሰለቸኝ፣ ጠገብኩ ሳይል መከራን ስቃይን ተቀብሏል ሲሉ ነው።

፪. የአማርኛ መወድስ ቅኔ

የአንተ ስጦታ ዓባይ

ዲካ የሌለው

ስለማይደርስበት ይብስት

ሞልቶ ፈሰሰ በዓለም

የልብህ ጥበብ ፈለግ

እየፈለቀ ከጎጃም

ማዕከለ ባሕር አልቆመ

ድልድይ ስመ እንቲአከ

ዘበየማን ወጸጋም

ይሻገሩ ዘንድ ወዳጆችህ

ሊቃውንተ ሥርዓት ወሕግ

የመረጥካቸው ቀደም

ለዓለም ወለዓለም

ጥበብስ እመ ተከልኮ

በማይናወጽ ገዳም

የፍሬ ምስጋናን አፈራልን ሁሉን የሚጠቅም

ቀርበን ብናየው በዓይን

እስከ ሥሩ ነው ለምለም

በቅዱስ እጅህ ተባርኳልና የእርሱ ልምላሜ አይጠወልግም።

ለአብነት ያህል ይህንን ጠቀስን እንጂ መምህርቷ በቅኔዎቻቸው ውስጥ ብዙ ጉዳዮችን አመስጥረው ይገኛሉ። በተቀኟቸው ቅኔዎች ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን ቅኔዎች አመስጥረዋል። ከዚህ በመነሳት እማሆይ ሃይማኖተኛና መንፈሳዊነትን የተላበሱ እንደነበሩ እንዲሁም ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው በጥልቀት የተረዱ እናት እነደነበሩ ለማየት ይቻላል።

እማሆይ ገላነሽ እርጅና እየተጫናቸው ሲመጣ ቀድሞ የሚሠሩትን የእጅ ሥራ ለመሥራት ባለመቻላቸውን የምትረዳቸው ሴት ልጃቸው ትዳር በመያዟ የደረሰባቸውን ችግር በመስማት የካቲት ፴ ቀን ፲፱፻፷፫ ዓ.ም በባላምበርስ ዘገየ ገብረ ወልድ አሳሳቢነት በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሕንፃ በአንድ ጽ/ቤት ውስጥ ጊዜያዊ የርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተቋቁሞ የበኩሉን ወገናዊ አስተዋጽዖ ተወጥቷል። እርሳቸውም በአንድ ወቅት “ከቤተ ክህነት ወይም ከሌላ የሚሰፈርልኝ ቀለብ የለም። በሥጋ የሚዛመዱኝ ጉልማ ያርሱልኛል። ተማሪዎቼም ተቀኝተው ለመምህርነት በቅተው ሲሄዱ የሰሌን ጥላና ምንጣፍ ሠርተው ያን ሸጠው ለበረከት ይሰጡኛል። የኔ ሕይወት ቅኔ ነው የቅኔ ዓይነት መዝረፍ፣ ሌላ ሕይወት የለኝም። ከተማሪዎቼ የተለየ ምቾት አላገኘሁም። በዚህም አላዝንም” በማለት በህልውናቸው በኑሯቸው በኩል ያለውን ጉዳይ በማቃለል ዘወትር ይናገሩ ነበር።

በዚህ ሁኔታ ከኖሩ በኋላ በተወለዱ በሰማንያ ዓመታቸው ባደረባቸው ሕመም ምክንያት የቅኔዋ ምንጭ እማሆይ ገላነሽ አዲስ ከነማይጠገብ ለዛቸው ሐምሌ ፲፪ ቀን ፲፱፫፸፰ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ባደጉበትና ባስተማሩበት በደብረ ጽላሎ አማኑኤል ገዳም ተፈጽሟል።

እማሆይ ገላነሽ ሐዲስ ቤተ ክርስቲያንና ታሪክ ሊዘክራቸው የሚገቡ የዘመናችን የአጥቢያ ኮከብ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሴቶች ቦታ ባላገኙበት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በቅለው ለዚያውም ዐይነ-ሥውርነት ተጨምሮበት ነጥረው የወጡ ስመ-ጥሩ ሴት ናቸው። ለዚህም ነው ዓለም የሃያኛው ክፍለ ዘመን አስገራሚ ከሆኑት ሴቶች መካከል አንዷ መሆን የሚገባቸው።

በአሁኑ ሰዓት በባሕር ዳር ከተማ በእኅት ልጃቸው በአቶ ተሾመ አዲስ አማካይነት መታሰቢያ ሙዝየም ተዘጋጅቶላቸው ሥዕላቸው በትልቁ ተስሎና አንዳንድ ቅኔዎቻቸው ተሰብስበው ተቀምጠዋል። ሙዝየሙን የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ በርናባስ ጥር ፳፫ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም መርቀው ከፍተውታል።

እማሆይ ገላነሽ አዲስ ሕይወታቸውና ቅኔዎቻቸው / ሥራዎቻቸው ሊጠኑ ከሚገባቸው የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አንዷ መሆናቸውን ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል።
********************************************************************************
ምንጭ፡--ሰሎሞን ሐዲስ ፤ የእማሆይ ገላነሽ ሐዲስ ዘጽላሎ አማኑኤል የሕይወት ታሪክና ሥራዎቻቸው፥ ለመጀመሪያ ዲግሪ ከፊል ማሟያ የቀረበ፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል፤ እ.ኢዮ ፲፱፻፺ ዓ.ም
ምስጋና ለሰሎሞን ሐዲስ
የፎቶ ግራፍ ምንጭ:- ዶክተር ዘላለም ጌታቸው 
https://www.facebook.com/profile.php?id=100071001585291

Friday, December 28, 2012

የግጥም ጥግ

አህያ ባረገው


አምነው የጫኑበት
ፈቅደው ያሸከሙት
“አደራ” ነው ያሉት
የስልጣን ሽልጦ፣ የሹመት ዘመራ
ለተጫነው እንጂ፣ ለጫኞች ካልሰራ
ካረገው ተጫኙ - ውኃ፣ ልብስ፣ እንጀራ
ርቦት ከጎረሰው
ጎርሶት ከጠገበው፣
በርዶት ከደረበው
ደርቦት ከሞቀው፣
ጠምቶት ከመጠጠው
መጦት ካሰከረው፣…
ምናለበት እግዜር
አዙሮ ቢጥለው!!
ወይም በጥበቡ፣ ምናል ቢለውጠው!
“እፍ” ያለውን ትንፋሽ፣ መልሶ ቢመርቀው!
ምናል ቢአሳድገው! ምናል ቢመርቀው!
ሰውነቱን ገሮ አህያ ቢአረገው!!
***********************
ምንጭ:-- ( ጌትነት እንየው ‹‹እውቀትን ፍለጋ›› )

Monday, December 3, 2012

የግጥም ጥግ

***********************************************************************************
ምንጭ:--http://ethioliteraturepaltalk.blogspot.com

ማኅበራዊ መረቦች/ገጾች

ፌስቡክ (Facebook)

ፌስቡክ በዓለማችን ትልቁ የማኅበራዊ ግንኙነት ድረ ገጽ ነው። በማኅበራዊ መረቦች ሰዎችን ለማግኘት የሚፈለጉ በቅድሚያ ከሚሔዱባቸው ቦታዎች ቀዳሚው ፌስቡክ ነው። ይህ ማለት ፌስቡክን መጠቀም ሌሎች ገጾችን ከመጠቀም የበለጠ ለአደጋ የተጋለጠ ነው እንደማለት ነው። በመላው ዓለም ተጠቃሚዎች ያሉት በመሆኑ የምንለጥፈውን ነገር ማንም ሊያየው ይችላል ማለት ነው።
የፌስቡክ መሥራች ማርክ ዙከርበርግ ራሱ “የኦንላይን ምሥጢራዊ ደኅንነት አብቅቶለታል” ሲል በአደባባይ ተናግሯል፤ ስለዚህም በፌስቡክ ምሥጢራዊነትንና ደኅንነትን ማረጋገጥ እጅግ አጠራጣሪ ነው። አደናጋሪውን የፌስቡክ የምሥጢራዊነት አማራጭ በመጠቀም መረጃዎቻችንን የመረጥናቸው “ጓደኞቻችን” ብቻ እንዲያዩት አዘን/አድርገን ይሆናል፤ ሆኖም “ጓደኞቻችን” ያልሆኑ ሰዎች በቀላሉ በኢንተርኔት ሐሰሳ በመጠቀም የተወሰነ መረጃ ማየት ይችላሉ። የጨዋታዎች እና የተለያዩ አፕሊኬሽኖች ፈጣሪዎች (developers) መረጃዎቻችንን በቀላሉ ሊያገኙት ይችላሉ።
አንድ አስገራሚ ነገር መርሳት የለብንም፤ አንድ ጊዜ የፌስቡክ አካውንት/አድራሻ ከፈጠርን በኋላ ልናጠፋው አንችልም። ጥያቄውን ካቀረብን ፌስቡክ አካውንታችንን “ከአገልግሎት ውጪ” ('deactivate') ሊያደርገው ይችላል፤ ሆኖም አንድም መረጃው ሳይጠፋና ሳይነካ መልሰን ወደ አገልግሎት ልናመጣው ('reactivate') እንችላለን። መረጃችን ከፌስቡክ ፈጽሞ አይጠፋም።
በhttp://www.facebook.com/terms.php የምናነበው “ስምምነት” ነገሩን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል- “በአእምሯዊ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ሽፋን የተሰጣቸውን ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ('IP content') በተመለከተ እርስዎ (ተጠቃሚው) የሚከተሉትን ፈቃዶች ሰጥትውናል፤ ይህም በእርስዎ የምሥጢራዊነት (privacy) እና የአፕሊኬሽን ምርጫዎች (application settings) ላይ የተመሠረት ይሆናል። በዚህም በፌስቡክ የሚለጥፏቸውን ማናቸውንም ይዘቶች ያለገደብ የመጠቀም መብት (a non-exclusive, transferable, sub-licensable, royalty-free, worldwide license to use any IP content) ሰጥተውናል። ይህ የአይፒ ፈቃድ (‘IP License’) የሚቋረጠው የለጠፉትን የአይፒ ይዘት ወይም አካውንትዎን/አድራሻዎን ፈጽመው ካጠፉት (delete) ነው፤ ይህ የሚሆነው ግን የለጠፉዋቸው ይዘቶች ለሌሎች ከተካፈሉ እና እነርሱ ካላጠፉት ብቻ ነው።” በሌላ አነጋገር ፌስቡክ እኛ የምንለጥፈውን ማንኛውንም ነገር ባለቤትነት ይወስዳል፣ በማንኛውም በፈለገው መንገድ ሊጠቀምበትም ይችላል ማለት ነው።
የአሜሪካ መንግሥት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ፌስቡክን እና ሌሎች የማኅበራዊ የመገናኛ መረብ ገጾችን ይከታተላል (monitor)፤ ሌሎች መንግሥታትም እንዲሁ እንደሚያደርጉ ይታመናል።

ለፌስቡክ የጥንቃቄ ጥቆማዎች!

  • በፌስ ቡክ የደኅንነት ጥበቃ አማራጮች (privacy settings) ተገቢውን ምርጫ ማድረጋችንን መላልሶ ማረጋገጥ! የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች ብዛት በጣም እየጨመረ የሚመጣ በመሆኑ እና ከተያያዥ ጫናዎች የተነሣ የምሥጢራዊነት ፖሊሲዎች በየጊዜው ይቀያየራሉ።
  • በፌስቡክ ላይ ሌሎች ሰዎችን “በጓደኝነት” ተቀበልን ማለት ከእነዚህ “ጓደኞቻችን” ጋራ ቀጥታ ግንኙነት ፈጠርን፣ መረጃዎቻችንን እና በፌስቡክ ላይ የምናደርገውን ነገር ሁሉ እንዲመለከቱ ፈቀድንላቸው ማለት ነው። ስለዚህ በፌስቡክ ልናምናቸው የምንችላቸውን ሰዎች ብቻ ጓደኛ ማድረግ የተመረጠ ነው።
  • ከአካውንታችን በወጣን (sign out) ቁጥር አካውንቱን ዲአክቲቬት (de-activate) ማለትም ከአገልግሎት ውጭ ማድረግ ያስፈልግ እንደሆነ ማሰቡም አይከፋም። ይህ ማለት አካውንቱን እኛ ወደአገልግሎት እስክንመልሰው ድረስ ማንም ሊያየው አይችልም ማለት ነው። ወደ ፌስቡክ ስንገባ (log in) አካውንቱን ወደ አገልግሎት እንመልሰዋለን (reactivate) ማለት ነው፤ ሁሉንም ነገር እንደነበረ እናገኘዋለን።
ስለፌስቡክ የምሥጢራዊነት/የደኅንነት መጠበቂያ አማራጮች በሚገባ ለመረዳት “'Controlling How You Share” የሚለው የድረ ገጹ ክፍል በጣም ጥሩ ምንጭ ነው http://www.facebook.com/privacy/explanation.php

ትዊተር (Twitter)

አገልግሎት (Function)፦ የሁኔታ ማሳወቂያ (ስታተስ አፕዴት)
ትዊተር ሲጀመር ዓላማው ከሞባይል ስልክ ወደ ኢንተርኔት ወቅታዊ መረጃዎችን መለጠፍ ነበር። 140 ቦታዎችን (የፊደል ቦታዎች) ብቻ የሚፈቅደውም ከዚህ በመነሣት ነበር። “የኢንተርኔት ኤስኤምኤስ” በመባል የሚጠራውም ለዚህ ነው። በትዊተር ሌሎች የሚሉትን/የሚጽፉትን ለመከታተል የምንፈልጋቸውን ተጠቃሚዎች “መከታተል” ('follow') እንችላለን። ሰዎቹን ልናውቃቸውም ላናውቃቸውም እንችላለን፤ ዋናው ነገር ሰዎቹ የሚለጥፉትን ጉዳይ መከታተል መፈለጋችን ነው። በተመሳሳይም “የሚከታተሉን” ሰዎች ጓደኞቻችን ላይሆኑ ይችላሉ፤ ይህም በአብሮነት ከሚመጣ አበሳ/ክስ (guilt by association) በተሻለ መልኩ ይከላከላል። ማንነትን ለመሰወርና ተለዋጭ ስሞችን ለመጠቀምም ምቹ ነው።
ትዊተር በአገልግሎት መስጠት ስምምነቱ እንዲህ ይላል፤ “ይህ ፈቃድ/ስምምነት ትዊት የሚያደርጓቸውን ነገሮች መላው ዓለም እንዲያገኘው እንድናደርግ ሥልጣን ይሰጠናል፤ ሌሎች ተጠቃሚዎችም ይህንኑ ማድረግ ይችላሉ። ሆኖም የእርስዎ የሆነው ሁሉ የእርስዎ ነው፤ የለጠፏቸው ይዘቶች ባለቤትነት የእርስዎ ነው።” ምንጭ http://twitter.com/terms)
ትዊተር ድረ ገጽ ነው። ይሁንና ብዙ ሰዎች “Twitter clients” በሚባሉ አፕሊኬሽኖች አማካኝነት ከዴስክቶፕ ኮምፒውተሮቻቸው ትዊተርን መጠቀም ይችላሉ። የትዊተር ተጠቃሚ (Twitter client) ከሆንን ከእውነተኛውና ደኅንነቱ ከተጠበቀው ድረ ገጽ ጋራ መገናኘቱን ማረጋገጥ አለብን።
የአሜሪካ መንግሥት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ትዊተርን እና ሌሎች የማኅበራዊ የመገናኛ መረብ ገጾችን ይከታተላል (monitor)፤ ሌሎች መንግሥታትም እንዲሁ እንደሚያደርጉ ይታመናል።

ለትዊተር የአጠቃቀም ጥቆማዎች!

  • በትዊተር የሚለጠፍ ማንኛውም ነገር በቅጽበት ውስጥ በመላው ዓለም ሊታይ ይችላል። “እርስዎ ትዊት የሚያደርጉትን ነዎት፤ You are what you Tweet!”
  • በትዊተር የሚለጠፍ ማንኛውም ነገር በጊዜ ቅደም ተከተል ወደ ትልቁ የትዊቶች ባሕር ይገባል፤ ስለዚህ “በሚከታተሉን” ሰዎች ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሊታይ ትችላል። ስሱ መረጃዎችን የምንለጥፍ ከሆነ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብናል። ትዊቶችን መጠበቅ ማለት “የሚከታተሉን” ሰዎች ብቻ እንዲያዩዋቸው ማድረግ ማለት ነው። ሆኖም “የሚከታተሉን” ሰዎች መልሰው ሊለጥፏቸው ወይም ሪትዊት (retweet) ሊያደርጓቸውና ለሕዝብ ሁሉ ሊደርሱ እንደሚችሉ መዘንጋት የለብንም።
  • መንግሥትን ወይም ባለሥልጣናትን የሚተቹ ነገሮችን ትዊት የምናደርግ/የምንለጥፍ ከሆነ ማንነታችንን ደብቀን በተለዋጭ ስሞችና ማንነቶች መጠቀም ይመረጣል።

ዩትዩብ (YouTube)

አገልግሎቶች (Functions):- ቪዲዮዎችን እና ሌሎች የኢንተርኔት ይዘቶችን ማካፈል
የዩትዩብ ባለቤት ጉግል (Google) ነው። ዩትዩብ ቪዲዮዎችን በሚልዮን ለሚቆጠሩ ተጠቃሚዎቹ ለማካፈል በጣም ምቹ መንገድ ነው። ነገር ግን የጉግል አስተዳዳሪዎች የለጠፍነውን ቪዲዮ በተለያየ ምክንያት “አግባብነት/ተቀባይነት የሌለው”( objectionable) መሆኑን ካመኑበት ሊያጠፉት ይችላሉ። ይህም ዩትዩብ ቪዲዮዎቻችንን ለማስቀመጥ አስተማምኝ አማራጭ እንዳይሆን ያደርገዋል። በተጨማሪም ጉግል ከተለያዩ ወገኖች በሚመጣበት ጫና እና ድረ ገጹ ሳንሱር እንዳይደረግ ለመጠበቅ ሲል ቪዲዮዎችን ከገጹ እንደሚያጠፋ ይታወቃል። ስለዚህ ሰዎች ቪዲዮዎቻችንን እንዲያዩልን ከፈለግን ቅጂውን ዩትዩብ ላይ መጫን (upload) እንችላለን፤ ነገር ግን ብቸኛ ቅጂያችንን ለጥንቃቄ በሚል ዩትዩብ ላይ ማስቀመጥ የለብንም።
ጉግል በገጹ ላይ የሚጫኑ (uploaded) ቪዲዮዎችን የጫነውን ተጠቃሚ ስም እና ያለበትን ቦታ ይጽፋል። ይህም የጫኑትን ሰዎች ለመከታተል ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። በዩትዩብ ላይ የምንጭነው ቪዲዮ የባለቤትነት መብት የራሳችን ነው፤ ነገር ግን ዩትዩብ ላይ በመጫን ለጉግል የማሰራጨት ፈቃድ እንደሰጠነው ይቆጠራል።
እ.አ.አ. ከመስከረም 2010 ጀምሮ ዩትዩብ በቻይና፣ በኢራን፣ በሊቢያ፣ በቱኒዚያ እና በቱርክሜኒሰታን ታግዷል። ይህ መጻሕፍ በሚታተምበት ወቅት በእነዚህም ሆነ በሌሎች አገሮች ያለው ሁኔታ ተቀይሮ ሊሆን ይችላል።

የዩትዩብ የጥንቃቄ ጥቆማዎች

  • የሌሎች ሰዎችን ቪዲዮ ያለፈቃዳቸው አንጫን። ፈቃደኛ ቢሆኑ እንኳን ቪዲዮውን ከመጫናችን በፊት ድርጊቱ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ይኖር እንደሆነ መላልሰን ማሰብ አለብን።
  • ምንግዜም በጉግል/ዩትዩብ በመጫን ለሌሎች የምናካፍለውን ቪዲዮ መጠባበቂያ ቅጂ ማስቀመጥ ይኖርብናል።
  • የተወሰኑ ሰዎች ብቻ እንዲያዩት የምንፈልገው ቪዲዮ ሲኖር ይህን ለማድረግ የሚያስችለውን ምርጫ (private setting) መምረጥ አለብን።

ፍሊከር (Flickr)

አገልግሎት (Functions)፡ ፎቶ/ቪዲዮ እና የኢንተርኔት ይዘቶችን ማጋራት
የፍሊከር ባለቤት ያሁ! (Yahoo!) ነው።
በፍሊከር ላይ የለጠፍነው ነገር ባለቤቶች እኛው ነን፤ አልፎም የፈጠራ ባለቤትነት እና የመጠቀም ፈቃድ (creative commons licenses or copyright) ልንፈጥርላቸው እንችላለን። ሆኖም ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን ስንለጥፍ ለያሁ! የማሰራጨት ፈቃድ እንደሰጠነው ይቆጠራል።
ፍሊከር የተለያዩ የመለያ ፈቃድ (licensing attribution) አይነቶችን የሚያቀርብ በመሆኑ ለተለያየ ዓለማ የሚውሉ ምስሎችን በቀላሉ ፈልጎ ለማግኘት እና ከምንፈልጋቸው ወገኖች ጋራ ምስሎችን ለመጋራት በጣም የተመቸ ነው።

የፍሊከር የጥንቃቄ ጥቆማዎች

  • ፍሊከር በካሜራችን የሚመዘገቡ ስውር መረጃዎችን (metadata) (ለምሳሌ ቀን፣ ሰዓት፣ ጂፒኤስ ስፍራ፣ የካሜራ ሞዴል ወዘተ) ገልጦ እንደማያሳይ ማረጋገጥ
  • ፈቃዳቸውን ሳናገኝ የሰዎችን ፎቶ በፍሊከር ለሌሎች አለማካፈል፤ በተጨማሪም ከምስሉ ጋራ የምናያይዘው የፈቃድ አይነት ባለምስሎቹ የሚስማሙበት መሆኑን ማረጋገጥ
የአሜሪካ መንግሥት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ፍሊከርን እና ሌሎች የማኅበራዊ የመገናኛ መረብ ገጾችን ይከታተላል (monitor)፤ ሌሎች መንግሥታትም እንዲሁ እንደሚያደርጉ ይታመናል።

ማስታወሻ፤ አማራጭ መሣሪያዎች (Alternative Tools)

በዚህ ምእራፍ የቀረቡት በስፋት ታዋቂ የሆኑት እና በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉት ማኅበራዊ መረቦች/ገጾች መሣሪያዎች (tools) ናቸው። መንግሥታት አፈና መፈጸም ሲጀምሩ በቅድሚያ የሚወስዱት እርምጃ እነዚህን ድረ ገጾች ማገድ ነው። በተጨማሪም እነዚህ መሣሪያዎች በግል ኩባንያዎች ባለቤትነት ስር የሚገኙ እንደመሆናቸው አስፈላጊ ሲሆን ለመንግሥት ጫና መገበራቸው እና ሳንሱር ማድረጋቸው አይቀርም። ስለዚህም የዲጂታል ደኅንነትን እና የመብት አቀንቃኞችን ከግምት በማስገባት የተፈጠሩትን ዲያስፖራ (Diaspora) (http://joindiaspora.com) እና ክራብግራስ (Crabgrass) (http://we.riseup.net) የመሳሰሉትን አማራጮች መመልከት ይመከራል።
*********************************************************
 ምንጭ:--https://securityinabox.org/am/chapter-10-3