እንቁጣጣሽ!!!
መስከረም 1
ዘመን መለወጫ
ርእሰ ዓውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ
****************************************************************************
እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡
ዓመታት ተፈጽመው አዲስ ዓመት ስንጀምር ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዓውደ ዓመት፣ አዲስ ዓመት ፣ እንቁጣጣሽ እየተባለ
ይጠራል፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደሚያስረዱት እንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜው አመጣጥ ወይመ ጥንተ ታሪክ በመጀመሪያ
ኖኅ ለሦስቱ ልጆቹ አህጉራትን በዕጣ ሲያካፍላቸው አፍሪካ ለካም ደረሰችው፡፡ በአፍሪካ ምድርም ሲገባ በመጀመሪያ
ያረፈው በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ሀገሪቱም በአደይ አበባ አሸብርቃ ነበር፡፡ ወሩ ወርኃ መስከረም በመሆኑ ደስ ብሎት
«ዕንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ» ይህችን ወቅት እንቁጣጣሽ ብሏታል፡፡ ሁለተኛው የሀገራችን ንግሥት ንግሥተ ሳባ የንጉሥ
ሰሎሞንን ዜና ጥበብ እየሰማች ስታደንቅ ትኖር ነበር፡፡ በጆሮዋ የሰማችውን በዓይኗ ዓይታ ለመረዳት ስለፈለገች
በግመሎች ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኝ በኢየሩሳሌም የማይገኝ ልዩ ልዩ ገጸ በረከት
አስጭና ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፡፡ ከንጉሡ ሰሎሞንም ጋር ተገናኝታ የያዘችውን ገጸ በረከት
ከሰጠችው በኋላ ብዙ ነገሮችን ጠየቀችው፡፡ እርሱም አንድ ነገር ላይ ሰውሮ ሁሉንም ገለጸላት፡፡ ቤተ መንግሥቱንም
በቤተ መንግሥቱ የሚገኙ እጅግ በጣም የከበሩ ዕቃዎችን ሁሉ አስጎበኛት፡፡ ሲያበቃ «ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ»
ሲል እጅግ በጣም የከበረ ዕንቁ አበረከተላት/ሰጣት/፡፡ ወሩም ወረኃ መስከረም ነበር፡፡ ከዚህ በመነሣት እንቁጣጣሽ
የሚለው መጥቷል፡፡ አሁን ከሚፈጸመው ሥነ ሥርዓት ደርሶ በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ የሚከበረውም መስከረም አንድ ቀን
ነው፡፡ አንድም «ዕንቁ ዕፅ አወጣሸ» ብሎ የአበባውን መፈንዳትን ያስረዳናል፡፡
መስከረም አንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያጠመቀው የቅዱስ ዮሐንስ መታሰቢያ ዕለትም ነው፡፡ መስከረም ሁለት ደግሞ ይህ አባት አንገቱን የተቆረጠበት ቀን ነው፡፡
በገሊላ ሀገር የነገሠ ሄሮድስ የሚባል ሰው ነበር፡፡ እርሱም የወንድሙን የፊልጶስ ሚስት ሄሮድያዳን ስላገባ ቅዱስ
ዮሐንስ ሳይፈራ ንጉሡን «የወንድምህን ሚስት ልታገባት አልተፈቀደልህም» ብሎ ይነግረው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት
ንጉሡ ተቆጥቶ ዮሐንስን አስሮት ነበር፡፡ ሊገድለውም ፈልጐ ሕዝቡ ዮሐንስን በጣም ስለሚወዱት እነርሱን ፈርቶ
ተወው፡፡
አንድ ቀን የሄሮድስ የልደቱ ቀን በሆነ ጊዜ ታላቅ ድግስ ተደግሶ እንግዶች ተጋባዦች ተሰብስበው ሲበሉና ሲጠጡ
የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ገብታ ለንጉሡ ዘፈነችለት ደስም አሰኘችው፡፡ ስለዚህ የምትለምነውን ሁሉ ሊሰጣት
ማለላት፡፡ እርሷም እናቷን አማክራ የመጥምቁ የዮሐንስን ራስ አሁን በስሀን ስጠኝ አለችው፡፡ ንጉሡም ወታደሮቹን ልኮ
በእስር ቤት ሳለ የዮሐንስን ራስ አስቈረጠው፡፡ ራሱንም በሰሀን አምጥተው ለዚያች ልጅ ሰጡአት እርሷም ወስዳ
ለእናቷ ሰጠቻት፡፡ እግዚአብሔርም ለቅዱስ ዮሐንስ አንገት ክንፍ ሰጣት እየበረረችም ለ15 ዓመት አስተማረች፡፡
መልካም አዲስ አመት ተመኝተን መጪዉን አመት ጠንክረን የምንሰራበት፣ የጀመርነዉ ነገር ካለ የተሻለ ደረጃ የምናደርስበት፣ የጀመርነዉ ከሌለ ያሰብነዉን የምንጀመርንበት፣ ያሰብነዉ ነገር ከሌለ ደግሞ ለማሰብ የምንነቃቃበት እንዲሆን እንመኛለን፡፡ እንዲሁም ከቻልን ለሰዎች የምንተርፈበት ካልቻልን ደግሞ እራሳችንን የምንችልበት እንዲሆንልን ምኞታችን ነዉ፡፡
እንቁጣጣሽ
በያመቱ
ያምጣሽ!
መልካም
አዲስ
አመት!
Happy
Ethiopian
New year!
መጭው አመት የሰላም እና የደስታ
ዘመን ይሁንላችሁ!!!2005 ዓመተ ምህረት
No comments:
Post a Comment