ከደራሲያን ዓምባ

Monday, October 22, 2012

ከደራሲያን ዓምባ

ከበደ ሚካኤል


ከበደ ሚካኤል (1909-1991)
በደብረ ብርሃን ከተማ፣ ገርም ገብርኤል አጥቢያ ጥቅምት 23 ቀን 1909 ዓ.ም.ተወለዱ። ወደ አዲስ አበባ እንደ መጡ መጀመሪያ በአሊአንስ ኢቲዮ-ፍራንሴዝ በኋላም በላዛሪስት ሚሲዮን ትምህርታቸውን ተከታተሉ። የሼክስፒርን ሮሜዎና ዡልየትን ማክቤዝን በመተርጎም እውቅናን ለማትረፍ ችለዋል።
ከበደ ሚካኤል 30 ገደማ መፃሕፍትን ፅፈዋል።
ከበደ ሚካኤል በርካታ የስነ ጽሁፍ ስራዎች ባለቤት በመሆናቸው በተለይም ለልጆች ትምህርት አዘል ጽሁፎችን የግጥም የፈጠራ ስራዎችን ቅኔዎችን በስፋት በማበርክታቸው በኢትዮጵያ የስነጽሁፍ መድረክ ገናና ከሆኑት ደራሲዎች አንዱ ናቸው። 
የሰዎች ስነ ምግባር ላይ የማተኮርና ምክር አዘል መልእክቶችን የማስተላለፍ ዝንባሌአቸው በአብዛኛው ስራቸው ላይ ይንጸባረቃል።
ዘመናዊት ኢትዮጵያን ለማደርጀት በተደረገው ትግል በግንባር ቀደምትነት የተሳተፉ እኒህ ፈላስማ፥ ባለቅኔ፥ ጸሐፌ-ተውኔት፥ ደራሲና አንጋፋ ጋዜጠኛ ፥ የቀለም ሰው በሀገራችን የመጀመሪያ የነበረውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት በቀዳሚነት የተቀበሉ ሲሆን፣ አዲስ ትውልድ ላፈራ ስብእናቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቅምት 26 ቀን 1990 ዓ.ም. በሥነ ጽሑፍ የክብር ዶክቶሬት ዲግሪ ሸልሟቸዋል። በተረፈም ከፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሶቭየት ህብረትና ሜክሲኮ ሽልማትን ተቀብለዋል።
በተረፈ የትምህርት ሚኒስትር ዳይረክተር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተከታይ ዳይሬክተር (1942)፣ የብሄራዊ መጻህፍት ቤት ዳይረክተር (1944)ና የካቢኔ ሚንስትር ሆነው አገልግለዋል።
ክቡር ዶክቶር ከበደ ሚካኤል፥ ኢትዮጵያዊ የቀለም ሰው ኅዳር 3 ቀን 1991 ዓ.ም. በሰማንያ ሁለት ዓመታቸው አረፉ።


የ ክቡር ዶክቶር ከበደ ሚካኤል ሥራዎች:--

  1. የትንቢት ቀጠሮ (ሥነ-ግጥም መማሪያ መጽሀፍ) 1938
  2. ሮሚዎና ዡሊየት (ተውኔት ትርጉም) 1946
  3. ታላላቅ ሰዎች (ኢ-ልብወለድ) 1943
  4. የዓለም ታሪክ (ኢ-ልብወለድ) 1956
  5. አኒባል (ተውኔት-ግጥም) 1956
  6. የቅጣት ማዕበል (ተውኔት-ግጥም) 1951
  7. ሄሮዶተስ (ኢ-ልብወለድ-ትርጉም)
  8. ታሪክናምሳሌ (መማሪያ መጽሀፍ) 1934
  9. ጃፓን እንዴት ሰለጠነች (ኢ-ልብወለድ) 1946
  10. የዕውቀት ብልጭታ (ኢ-ልብወለድ) 1939
  11. ካሌብ (ተውኔት) 1958
  12. ኢትዮጵያና ምዕራባዊ ስልጣኔ (ኢ-ልብወለድ) 1941
  13. የኀሊና ደወል
  14. ብርሃንና ኅሊና (ሥነ-ግጥም) 1933
  15. የኢትዮጵያ የጥንት ዕሎች 1961
  16. አክአብ (ተውኔት)
  17. ሥልጣኔ ምንድነች? (ኢ-ልብወለድ)
  18. የቅኔ ውበት (ሥነ-ግጥም) 1957

ከግጥሞቻቸው በጥቂቱ :--

የተማረ ሆኖ እውነቱን የማይገልጽ ፣ 
ባለ ጸጋ ሆኖ ገንዘቡን የማይሰጥ፣
ደሃ ሆኖ መስራት የማይሻ ልቡ፣
ሶስቱም ፍሬ ቢሶች፣
ለምንም አይረቡ።
*************
ፍሬ መሬት ወድቆ ከዋለ ካደረ፣
ሠው ገንዘብ አግኝቶ መክበር ከጀመረ፣
የመጣ ነውና ቀድሞውንም ከጥንት፣
ሁለቱም አይድኑም ከመበላሽት
        **********************
ጊዜ እየበረረ ሳይታጠፍ ክንፉ፣
እኛ በቁማችን ምንድነው እንቅልፉ።

**************************

መርዝም መድሃኒት ነው ሲሆን በጠብታ፣
እንዲሁም ለተንኮል አለው ቦታ ቦታ፣
ምን ቢሰለጥኑ ቢራቀቁ በጣም፣
ሁልጊዜ ደጋግሞ ብልጠት አያዋጣም።
በጅ የተበተቡት ተንኮል ዞሮ ዞሮ፣
ማጋለጡ አይቀር እጅና እግር አስሮ ።
መጽሓፉም ይለናል ሲያስተምረን ጥበብ፣
ብልጥ ሁን እንደባብ የዋህ ሁን እንደርግብ፣
ስለዚህ በብልጠት ተንኮል ስትሰሩ፣
በዝቶ እንዳይገላችሁ ገርነት ጨምሩ

Friday, October 5, 2012

ምርጥ አባባሎች

''' ምርጥ አባባሎች'''


• በአንድ ሰው የማስታወሻ መያዣ ደብተር ውስጥ ቦታ ማግኘት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በልቡ ውስጥ ቦታ ማግኘት ችግር ነው፡፡
• ሕጎችን ማውጣት ቀላል ነው መተግበር ግን ችግር ነው፡፡
• በየዕለቱ ማለም ቀላል ነው፡፡ ህልምን እውን ለማድረግ መታገል ግን ከባድ ነው፡፡
• ሙሉ ጨረቃን አይቶ ማድነቅ ቀላል ነው፡፡ የጨረቃን ሌላ ገጽታ ማየት ግን ችግር ነው፡፡
• ለአንድ ሰው አንድ ቃል መግባት ይቻላል፡፡ ቃልን መፈጸም ግን ችግር ነው፡፡
• ሌሎችን መውቀስ ይቀላል፡፡ ራስን ግን ይከብዳል፡፡
• አንድን ነገር ለማሻሻል ማሰብ ቀላል ነው፡፡ ማሰብን አቁሞ ወደ ተግባር መግባት ግን ጭንቅ ነው፡፡
• ሌሎችን በመጥፎነት መፈረጅ ቀላል ነው፡፡ ጥሩ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ማሰብ ግን ከባድ ነው፡፡
• ፍቅር የሚጠይቀው ብቸኛ ስጦታ "ፍቅር" ነው፡፡ (ጆን ግሬይ)
• መሳሳት ሰብዓዊነት ሲሆን ስህተትን ማመን ግን ቅዱስነት ነው፡፡ (ዳፍ ባውርሰን)
• በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ያለው ሰው ራሱን እንደ ሕዝብ ንብረት አድርጎ ይቆጥራል፡፡ (ቶማስ ጀፈርሰን)
• ወንዶች ሴቶችን የሚያፈቅሩትን ያህል ሰማያዊውን ዓለም ቢያፈቅሩ ኖሮ መላዕክት (አማልክት) መሆን በቻሉ ነበር፡፡ (ማልኮላም ኤክስ)

******************
ምንጭ:---(ምርጥነህ ታምራት፣ ጣዝማ፣ 1999)

-   የራስህ ቤተ መንግሥት ሁን፡፡ አለበለዚያ ዓለም እስር ቤትህ ትሆናለች፡፡ (ጀንደን)
-  ቅናት ሲመገብ ያደገ ፍቅር አሟሟቱ ከባድ ነው፡፡ (ዴቪድ)
-  ቅናትን እንደሳቅ የሚያስፈራው ነገር የለም፡፡ (ፍራንሷ ሳንጋ)
-  ቅናትን የሚፈጥረው ፍቅር ሳይሆን ራስ ወዳድነት ነው (ዋሊንግተን)
-  ከሞትክ አይቀር ደስ ብሎህ ሙት፡፡ (ቻርልስ ጀምስ ፊክስ)
-  ትዳር ያዙ ወይ የሞቀ ትዳር ይሆንላችሁና በደስታ ትኖራላችሁ፣ ወይም ጨቅጫቃ ትዳር ይሆንባችሁና ፈላስፋ ትሆናላችሁ፡፡ (ሶቅራጥስ)
-  ገበታህን በፍቅር ቅመም አሳምረው፡፡ ሁሉንም ሰሃን በደስታ ይሞላዋልና፡፡ (ዥን ኮክቶ)

***************************************************************

ምንጭ:---(ምርጥነህ ታምራት፤ጣዝማ የሚሊኒየሙ ምርጥ አባባሎች፣2000)

- የማያውቅ ማወቅንም የሚያውቅ ምሁር ነውና ተከተለው
- ለገዛ ራስህ ክቡር ዓላማዎች ታምኝ ሁን።
- የትምህርት ሁሉ ዓላማና ግብ ስብዕናን ማዳበር ነው።
- ማለዳ ስንነሳ ልብ እንበል? ከሐብት ሁሉ የሚልቁት 24 ሳዓታት የኛ ናቸው።
- ምንም ሳንሰራ ከምናሳልፈው ህይወት ስህተት እየሰራን የምንገፋው ህይወት የተሻለ ነው።
- የያውን ሁሉ ለመያዝ የሚሞክር አንድ ቀን እባብ ጨብጦ ይነደፋል።
- የቁም ነገር ጫፍ የሚባለው ሩቅ ያለውን መመልከት ሳይሆን በእጁ ያለውን መስራት ነው።-
- ስህተቱን ሲያውቅ ጩቤ የማይረግጥ ምሁር ምሁር ሊባል አይችልም።
- ነፃነት ስህተት የመሥራት መብትን ካላካተተ መኖር ፋይዳ የለውም።
- ሲጋራ በአካል ውስጥ የሚጓዝ የጫካ ውስት እሳት ነው።
- በዓለም ከፍተኛ መራራ ነገር ቢኖር ራዕይ አባል ሆኖ መፈጠር ነው።
- ባልና ሚስት በጋራ የሚተነፍስ ሳንባ ባይነራቸውም በጋራ የሚጓዝ የትዳር ሰንሰለት አላቸው።
- በዓለም ትልቁ ውርደት ከመስራት የሰው እጅ ማየት ነው።
- በአንድ ዛፍ የሚዘሉ ጉሬዛና ጦጣ አብረው ቢውሉም ተቃቅፈው አይተኙም።
- በኢላማህ የማትተማመን ከሆንክ ወደ ነብር አትተኩስ።
- በዛሬ ደስታ ብቻ የሚፈነድቁ ሰዎች ውብ አበባ ከተቀጠፈ መጠውለጉን የሚዘነጉ ናቸው።
- በፍቅር የተነሳ ልብ በፍቅር ይሰክናል።
- ብርቱካን መጨመቁን ቢያውቅ ውሃ አይዝልም ነበር።
- ብቃት የሚመጣው በውጥረት ሳይሆን በተግባር ምጥቀት ነው።
- ለማመን እንጂ ላለማመን ምክንያት አያስፈልግም::
- መልከመልካም ሴት ባየህ ጊዜ ተፈጥሮን አድንቅ እንጂ የዝሙትን መንፈስ አይሰማህ' ዝሙት ከደካማ መንፈስ የሚመንጭ ነው።
- እያንዳንዱ ይሕይወት ቀን ወደ ሞት የሚያደርስ ደረጃ ነው።
- ወደ ፊት የምንራመድ ከሆነ ታሪክን መድገም ብቻ ሳይሆን አዲስ ታሪክ መፍጠር አለብን።/መሀተመ ጋንዲ/ 

******************************************************************************
ምንጭ:---http://girmayreda.blogspot.com

Monday, October 1, 2012

ከደራሲያን ዓምባ

  ሀዲስ ዓለማየሁ እና ስራዎቻቸው 

                ( ጥቅምት 7 ቀን 1902 ዓ.ም- ህዳር 26 ቀን1996 ዓ.ም)

ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ ከአባታቸው ከቄስ ዓለማየሁ ሰለሞን እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ደስታ ዓለሙ በደብረ ማርቆስ አውራጃ በጎዛመን ወረዳ በእንዶዳም ኪዳነ ምኅረት ቀበሌ በ ጥቅምት ፯ ቀን ፲፱፻፪ ዓ.ም. ተወለዱ። 
ሀዲስ ዓለማየሁ በርካታ የስነጽሑፍ ሥራዋችን አበርክተዋል። 
  1. ተረት ተረት የመሰረት -1948 ዓ.ም. (ልብ ወለድ)
  2. ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል? - 1953 ዓ.ም. ((ኢ-ልብ ወለድ))
  3. ፍቅር አስክ መቃብር - 1958 ዓ.ም. (ልብ ወለድ)
  4. ወንጀለኛው ዳኛ - 1974 ዓ.ም. (ልብ ወለድ)
  5. የልም  ዣት - 1984 ዓ.ም.(ልብ ወለድ)
  6. የትምህርትና የተማሪ ቤት ትርጉም - 1948 ዓ.ም. (ኢ-ልብ ወለድ)
  7. ትዝታ - 1985 ዓ.ም. (ግለታሪክ )
  8. የአበሻና የወደኋላ ጋብቻ -  (ተውኔት)

 ሀዲስ ዓለማየሁ በኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማበርከታቸው 
በሥነ ጽሑፍ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ ፣
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክቶርነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል ። 
ደራሲው በኅዳር 26 ቀን 1996 ዓ.ም. በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ።


 ምርጥ አባባሎች:-
  • " የትልቅ ሰውን ትልቅ ስራ ሌሎች ይናገሩለታል እንጂ እርሱ አይናገርም።" (የልም  ዣት)
  • " የምትወደው ሁልጊዜ ሲለይህ የሚያስረሳህ እንጂ የሚያስታውስህ  ነገር አትፈልግ ያለዚያ ህይወትህ የስቃይ ህይወት ይሆናል።" (ፍቅር አስክ መቃብር)
  • " ሰው ባለመብት የሚያደርገው የሚፈፅመው ተግባር ነው ተግባሩን ሳይፈጸም በመብቱ የተጠቀመ ሁሉ ባለዕዳ ነው።" (ወንጀለኛው ዳኛ)

Thursday, September 27, 2012

ከኢትዮጵያ ተረቶች

ንግስት ፉራ 

 

ንግስት ፉራ ስመጥር የሲዳማ ንግስት የነበረች ሲሆን ሴቶችን ሁሉ መልካም ባህሪን ያስተማረችና እስካሁንም ድረስ ተቀባይነት ያላት ሴት ነች፡፡ ንግስቲቱ በጣም ብልህ ነበረች፡፡ በቅድሚያ ሴቶች ለወንዶች ሙሉ ለሙሉ ተገዢ እንዳይሆኑ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሴቶች ለወንዶች ሙሉ ለሙሉ ታዛዥ እንዳይሆኑ ትመክራቸው ነበር፡፡ ከዚያም በላይ ሴቶች አይን አፋር እንዲሆኑና ወንዶች እነርሱ ስለሚያስቡት ነገር ሁልጊዜም ግምታዊ እንጂ ግልፅ እንዳይሆን ታስተምራቸው ነበር፡፡ ሃፍረተ ገላቸውንም በአደባባይ እንዳያሳዩና ሰውነታቸውንም ከጉልበታቸው እስከ ወገባቸው ድረስ እንዲሸፍኑ ትነግራቸው ነበር፡፡ ወንዶች በውበት ስለሚማረኩ ሴቶች ራሳቸውን በደንብ እንዲጠብቁ ታስተምራቸው ነበር፡፡
ነገር ግን ንግስት ፉራ ለወንዶች በጣም መጥፎ ሴት ነበረች፡፡ የማይቻሉ ነገሮችን ሁሉ እንዲሰሩ ታዛቸው ነበር፡፡
“ወደ ወንዙ ሄደህ ውሃ በወንፊት አምጣ፡፡” እያለች ታዝ ነበር፡፡ ወይም በጣም ስስ ከሆነ ሳር ትልልቅ ገንዳዎችን እንዲሰሩ አለያም ከረጃጅም ፀጉሮቿ አንዱን ነቅላ ስድስት ቦታ እንዲሰነጥቁት በማዘዝ ወንዶችን ታሰቃያቸው ነበር፡፡
ከሁሉ በላይ ግን ራሰ በራና አጭር ወንዶችን አጥብቃ ትጠላ ነበር፡፡ ስለዚህ አጫጭር እንዲሁም ራሰ በራ ሰዎችን ሁሉ እንዲገደሉ ታዝ ነበር፡፡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አጫጭርና ራሰ በራ ሰዎች ሲገደሉ አንድ መላጣና አንድ ራሰ በራ ወንዶች ግን ከዚህ ችግር ተርፈው ነበር፡፡ አጭሩ ሰው ረጃጅም ተረከዝ ያሏቸው ጫማዎች በማድረግ ሲተርፍ (ረጅም ተረከዝን የፈጠረው እርሱ ነው) ራሰ በራው ሰው ደግሞ ሰው ሰራሽ ጸጉር (ዊግ) በማድረግ ከሞት ዳነ፡፡ (ዊግን የፈጠረው ሰው እርሱ ነው፡፡)
ታዲያ አጭሩና ራሰ በራው ሰዎች ንግስቲቱን ምን እንደሚያደርጓት ግራ ገብቷቸው ነበር፡፡ ሊገድሏትም አሰቡ፡፡ ነገር ግን ይህን ማድረግ ሁለት ግዙፍ ችግሮች ነበሩት፡፡ የመጀመሪያው በባህሉ መሰረት ሴትን መግደል በፍፁም ነውር ነው፡፡ ሁለኛው ደግሞ እርሷ ንግስት ስለነበረች ይህ የማይሆን በመሆኑ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተቸገሩ፡፡
ከዚያም ጥቂት ካሰቡ በኋላ አንድ ዘዴ ዘየዱ፡፡ አንድ ቀጭኔ ለመያዝ አስበው ቀጭኔዎቹን ሁሉ እያሳደዱ ወደ ረግረጋማው ስፍራ ከነዷቸው በኋላ አንዱ በጭቃው ተይዞ ሲቀር እርሱን ያዙት፡፡
ንግስቲቱንም ጠርተው “አንቺ ታላቅ ንግስት ነሽ፡፡ አንቺ መሳፈር ያለብሽ ተራውን እንስሳ ሳይሆን ረጅምና ሞገስ ያለውን እንስሳ ነው፡፡” አሏት፡፡
ከዚያም በሰአቱ ቀጭኔው እግሩ ጭቃው ውስጥ ዘልቆ ስለነበረ ንግስቲቱ ያለችግር ተሳፈረችው፡፡ ከዚያም ንግስቲቱን ቀጭኔው ላይ አስረዋት ቀጭኔውን ከጭቃው ካወጡ በኋላ ሲያባርሩት ቀጭኔው ሲሮጥ፣ ሲሮጥ፣ ሲሮጥ፣ ንግስቲቱ እየተቆራረጠች መውደቅ ጀመረች፡፡ ጭንቅላቷ ወደ አንድ ቦታ፣ እጆቿ ወደ ሌላ ቦታ፣ አንጀቷ ወደ አንድ አቅጣጫ፣ እግሮቿ ወደ ሌላ ስፍራ ተበጣጥሰው ወደቁ፡፡
በዚህ ምክንያት ነው እስከ ዛሬ ድረስ ሲዳማ ውስጥ ጭንቅላት፣ እግር፣ ሰውነት፣ አንጀት፣ እጅ የሚባሉ የከተማ ስሞች ያሉት፡፡
አኦውን፣ ጭንቅላት፤ ጎዱቦሬ፣ አንጀት፤ ሌላ፣ እግር፤ አንጋ፣ እጅ ማለት ነው፡፡
********************************************************
በአበበ ከበደ የተተረከ
ምንጭ:-- www.ethiopianfolktales.com

 

Monday, September 24, 2012

የመስቀል በዓል / በዓለ መስቀል

 እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሠላም አደረስዎ!
 
 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው ዐበይት እና ንዑሳን በዓላት መካከል አንዱ በዓለ መስቀል ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በወርኃ መስከረም ብቻ በዓለ መስቀልን አራት ጊዜ ታከብራለች፡፡
የመጀመሪያው ምክንያተ ክብረ በዓል፣ በኢትዮጵያ ነግሦ የነበረው ዓፄ ዳዊት ከግብፅ ንጉሥና ሊቃነጳጳሳት የተላከለትን በቅዱስ ሉቃስ እጅ የተሳለችውን ስዕለ ማርያምን፣ በወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ የተሳለውን ኩርዓተ ርእሱን ፣ ሌሎች ንዋያተ ቅድሳትን እና የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ግማደ መስቀል የግብፅ እና ኢትዮጵያ ድንበር ከነበረችው አስዋን ከተባለችው ቦታ ተረክቧል፡፡
ንጉሡ የያዘውን በረከት ወደኢትዮጵያ ሳያደርስ ስናር በተባለው ቦታ ዐረፈ፡፡ ከጊዜ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ የተባለው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ  ተቀብሎ በደብረ ብርሃን፣ በየረር፣ በመናገሻ እና በልዩ ልዩ ተራራማ ቦታዎች ሲዘዋወር ቆይቶ “ መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አኑር ”  የሚል ራእይ ተገልጦለት ቅዱስ መስቀሉን በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ በግሸን ደብረ ከርቤ አስቀምጦታል ፡፡ መጋቢት ዐሥር ቀን ደብረ ብርሃን ሲገባ ብርሃን ስለወረደና ዐፄ ዳዊት ከግብፃውያን ጳጳሳት እና ንጉሥ እጅ መስቀሉን የተረከቡበትን ቀን በማዘከር የአድባራት እና የገዳማት ሊቃውንት ልብሰ ተክህኖአቸውን ለብሰው የብር መቋሚያ እና ጸናጽል  ይዘው ወደ ነገሥታቱ ሔደው ተቀጸል ጽጌ እያሉ  እያሸበሸቡ ጸሎተ ወንጌል  ያደርሱ ስለነበር መስከረም ዐሥር ቀን የዓፄ መስቀል በዓል ተብሎ ይከበራል፡፡
ሁለተኛው  መስቀሉን በቁፋሮ ያገኘችው ንግሥት እሌኒ ደመራ ያስደመረችበት እና የእጣኑ ጢስ መስቀሉ ወደተቀበረበት ድልብ አከል ተራራ ያመለከተበት ዕለት መስከረም ዐሥራ ስድስት ቀን በመሆኑ የመስቀል ደመራ በዓል በዚሁ ዕለት ይከበራል፡፡
መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ደግሞ ቁፋሮ ያስጀመረችበት ዕለት ሲሆን መጋቢት ዐሥር ቀን መስቀሉን አግኝታለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን አሠርታ፣ መስቀሉን አስገብታ ቅዳሴ ቤቱን ያከበረችበት ዕለት ግን መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ነው፡፡ የመስቀሉ መገኘት ጥንተ በዓሉ መጋቢት ዐሥር ቀን ቢሆንም አባቶቻችን በታወቀና በተረዳ ነገር ዋናው የመስቀል በዓል የሚከበርበት ዕለት መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም መስከረም ሃያ አንድ ቀን በዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በግሸን ደብረ ከርቤ መስቀሉ ያረፈበት ዕለት ስለሆነ
“ በልደቱ ፍስሐ ፤
በጥምቀቱ ንስሐ ፤
በመስቀሉ አብርሃ፤ ” እያልን  በማኅሌት፣ በዝማሬና  በቅዳሴ ለዘለዓለም ስናከብረው እንኖራለን ፡፡
 
 
 
በሰማኸኝ በለው - ደቦት እንስራ  
***********************



እንደምነሽ ዘፈን እንዴት ነሽ ድለቃ
ስክስክ እንክትክቱ የዋንጫ ልቅለቃ
ታሪክ ሆኖ እንዳይቀር እንደነበር እቃ
ያበሻነት ዘሩ እንዲህ ሳያበቃ
ደቦት እንስራ……..…………………...ሆ እያበላ ሆ
ውጣ ኮበሌ…………….………….…..ሆ እያበላ ሆ
ሽንሺንህ ይሸንሸን እያለች አሌ.………..ሆ እያበላ ሆ
ጉብሌ አትፍሪ………………………….ሆ እያበላ ሆ
መጣን ከደጂሽ…………………………ሆ እያበላ ሆ
ቤትና አዝመራውን ጎሮ ገባሽ……………ሆ እያበላ ሆ
ሆ እያበላ ሆሆ ሆ እያበላ ሆሆ
ሆ እያበላ ሆሆ ሆ እያበላ ሆሆ…………..ሆ በል ጃሌ
ቆንጆና ኮበሌ…………………………..ሆ በል ጃሌ
እየተጠራራ………………………….…ሆ በል ጃሌ
የሰበሰብንበት……………………….….ሆ በል ጃሌ
የፍቅር አዝመራ………………….……ሆ በል ጃሌ
ደሞ ሲቀራርብ…………….………….ሆ በል ጃሌ
እንዲጠጣ ጠላ………………………..ሆ በል ጃሌ
ደመራዉም ሲነድ………………….….ሆ በል ጃሌ
ሲበላ ………………………………..ሆ በል ጃሌ
ሆ በል ጃሌ ሆሆ ሆ በል ጃሌ ሆ
ሆ በል ጃሌ ሆሆ ሆ በል ጃሌ ሆ
እያ በል እያ………………………………….እያ
እያ በልያ……………………………………እያ
ጋሬጣና እሾክ…………………….…………እያ
ካልተክነህ………………………………….እያ
ያሳፍርሃል………………………………….እያ
ወንድነትህ.………………………………..እያ
አጎጠጎጤው………………………………..እያ
ጎፈሬው በዛ………………………………..እያ
ማነው ደፋሩ……………………………….እያ
አሁን የዋዛ…………………………….…..እያ
ማነው ሚነካሽ…………………………….እያ
ምን ያጎበረው……………………………..እያ
አሳይኝና………………………………….እያ
ልቡን ልበለው…………………………….እያ
እያ በል እያ……………………………….እያ
እያ በል እያ……………………………….እያ
እያ በል እያ………………………………እያ
እያ በል እያ……………………………….እያ
ደቦት እንስራ……………………………….ሆ እያበላ ሆ
ውጣ ኮበሌ………………………….…….ሆ እያበላ ሆ
ሽንሺንህ ይሸንሸን እያለች አሌ…………….ሆ እያበላ ሆ
ጉብሌ አትፍሪ………………………….…ሆ እያበላ ሆ
መጣን ከደጂሽ…………………………...ሆ እያበላ ሆ
ቤትና አዝመራውን ጎሮ ገባሽ………………ሆ እያበላ ሆ
ሆ እያበላ ሆሆ ሆ እያበላ ሆሆ
ሆ እያበላ ሆሆ ሆ እያበላ ሆሆ…………….....…ሆ በል ጃሌ
ገና ጉብሉን ልጅ……………………………….ሆ በል ጃሌ
ያደገ በቁምጣ……………………………..…..ሆ በል ጃሌ
ልቡን አስወጋችው……………………………..ሆ በል ጃሌ
ሳያስበው መጣ…………………………..…….ሆ በል ጃሌ
የመስቀል ወፍና…………………………………ሆ በል ጃሌ
አንቺ ልጅ ያው ናችሁ……………………...…..ሆ በል ጃሌ
ባመት አንዴ ብቻ…………………………….....ሆ በል ጃሌ
ብቅ ትላላችሁ…………………………………..ሆ በል ጃሌ
ሆ በል ጃሌ ሆሆ ሆ በል ጃሌ ሆ
ሆ በል ጃሌ ሆሆ ሆ በል ጃሌ ሆ
እያ በል እያ……………………………………..እያ
እያ በል እያ……………………………………..እያ
ጭሱን አባሪው……………………………….…እያ
ዓይኔን አሞኛል…………………………………..እያ
በየሰበቡ………………………………………….እያ
ማልቀስ መሮኛል………………………………...እያ
በጋው ዘለቀ………………………………………እያ
እሰየው ጓዴ………………………………………እያ
እጨድ እንግዲህ………………………………….እያ
ጤፍና ስንዴ……………………………………..እያ
ጎተራው ይሙላ…………………………………..እያ
አይጉደል ቤቱ……………………………………እያ
እንደውሃ ሙላት…………………………………እያ
ይፍሰስ ሙሂቱ……………………………………እያ
አብሮ ያዝልቀን………………………………….እያ
ይፍጠን አመቱ…………………………………..እያ
እያ በል እያ……………………………………..እያ
እያ በል እያ………………………………………እያ
እያ በል እያ……………………………………..እያ
እያ በል እያ………………………………………እያ
 
 
 

የግጥም ጥግ

እሳት ወይ አበባ 

ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን
እሳት ወይ አበባ

 ሌት ከዋክብቱ  እንደ ፀደይ
አጥለቅልቆን  በቀይ አደይ
ሰማዩ  ሥጋጃ  አጥልቆ
ተሽለምልሞ  አንጸባርቆ
ፈክቶ አሸብርቆ  ደምቆ
በአዝመራ  በአጥቢያ  ዐፀድ  ሰፍኖ
የዓደይ  አዝርዕት  ተከሽኖ
በዕንቁጣጣሽ  ሰብል  ታጥኖ
ኢዮሃ  አበባዬ  ሆኖ፥
ጨረቃዋ  ከቆባዋ፥  ከሽልምልሚት  እምቡጧ
ብላ ከሰንኮፈንዋ፥ ተንዠርግጎ የእንኮይ ቡጧ፥
ድንግል  ጽጌ-ረዳ  ፈልቃ
ፍልቅልቂት  ድምቡል ቦቃ
ተንሠራፍታ  የአበባ  ጮርቃ፥
ታድያን  ብሌኑ  የጠጠረ
ባሕረ-ሃሳቡ የከረረ
የውበት ዓይኑ የታወረ
ልበ-ሕሊናው  የሰለለ
አይ፥ አበባ አይደለም አለ፤
አይ፥ እሳት አይደለም አለ፤
ያልታደለ።
ሰማይ  ጨለማ  ነው እንጂ፥  እሳት አደል ብሎ ካደ
እቶን  ባይኑ  እየነደደ።
ከዋክብቱ  እንደ  ችቦ
በነበልባል  ወርቀ  ዘቦ
ከፅንፍ  ፅንፍ  አውለብልቦ
ደመራው  እየተመመ
እየፋመ  እየጋመ
ደመና  እንደንዳድ  ሲነድ
መንጸባርቅ  ሰደድ  ሲወርድ፥
በራሪ  ኮከብ  ተኩሶ
በአድማሳት  እሳት  ለኩሶ
ይኸ እንደኔና  እንዳንቺው፥  የውበት ዓይኑ  የሰለለ
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ፥  እሳት እኮ አይደለም አለ፥
ያልታደለ።

ይቅር ብቻ  አንናገርም፥
እኔና  አንቺ  አንወያይም፤
ለውይይት  አልታደልንም
እንዲያው ዝም፥ እንዲያው ዝምዝም።
አበባ አንሆን ወይ እሳት
ተጠምደን  በምኞት  ቅጣት
ሰመመን  ባጫረው  መዓት
ዕድሜ አችንን እንዳማጥናት፤

እሳት አንሆን ወይ አበባ
በሕቅ  እንቅ  ስንባባ
ባከነች  ልጅነታችን፥ እየቃተትን ስናነባ
ሳንፈጠር  በሞትንባት
ሳናብብ  በረገፍንባት
ሳንጠና ባረጀንባት
አበባ ወይንም እሳት፥  መሆኑን ብቻ አጣንባት።
*************************************************
1966 ዓ.ም.
ብርሀንና ሠላም ማተሚያ ቤት